Administrator

Administrator

 የለውጥ ሐሳብን የምንቀበልበት መንገድ ከሦስት አንዱን ሳንካዎች የያዘ ነው፡፡ የመጀመሪያው “ሞገደኝነት” ሲሆን ይህም ሁሉንም የለውጥ ሐሳብ ላለመቀበል ሰበብ መደርደርና ለመዋጥ መቸገር ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ “ፌዘኝነት” ሲሆን፤ ይኸም ትላልቅ የለውጥ ሐሳቦችን ሁሉ ለቀልድና ለቧልት እያዋሉ ከቁም ነገራቸው ይልቅ ቀልዳቸው እንዲበዛ ማድረግ ነው፡፡ ነገሮችን በነጠረ ዐይን አይቶ ከማሰላሰል ይልቅ ነገሩን ዋዛና ፈዛዛ አድርጐ ማለፍ ነው፡፡ ፌዘኝነት በብዙ መልኩ ከሞገደኝነት ጋር የተያያዘ ወይም የሞገደኝነት ውጤት ነው:: ሦስተኛው ደግሞ “አድር ባይነት” ሲሆን ከለውጥ ሐሳቡ ይልቅ ለግለሰቡ በማበር ሳይገባን ለመቀበልና ለማስረዳት መሯሯጥና በዚህም የባሰ ጥፋት ማድረስ ነው፡፡ በለውጥና ስኬት ውስጥ ሀገርና ሕዝብ እንዲጠቀሙ ሳይሆን ከለውጡ ይገኛል ተብሎ የሚታሰበውን ፍርፋሪ ለመልቀም ማቶስቶስን፣ እያወደሱ፣ እያንቆለጳጳሱና የተለወጡ እየመለሱ የግል ጥቅምን ማሳደድን ይመለከታል፡፡
“ሞገደኝነት”የምንለው አዲስ ነገርን ለመቀበል የምናሳየውን ልግመትና እምቢታ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት መሪዎች ከሌሎች ሀገራት የተማሩትን ጠቃሚ ነገር ወደ ሀገራችን ለማስገባት እጅግ ይቸገራሉ፡፡ ይኸም ብቻ ሳይሆን መሪዎቹ ራሳቸው አዲስ ነገር ለመቀበል ልግመኝነት ሲያሳዩም ይስተዋላል፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን አዘምናለሁ ብለው ሲነሱ የገጠማቸው አንዱ ፈተናም ይኼ ነው፡፡ ከአዲሱ ሐሳብ ጋር ተገናዝቦ ለውጣቸውን ከማፋጠንና ጉድለቱን ሞልቶ የተሻለ እንዲሆን ከማገዝ ይልቅ ብዙዎች ዳር ቆመው እንደ እብድ ያዩዋቸው ነበር፡፡
አዲስ ነገርን ለመቀበል በምናሳየው “ሞገደኝነት” ምክንያት የመሪዎች ሕልም ወደ ሕዝቡ ዘልቆ ለመግባት ዕንቅፋት ይበዛበታል:: በዚህም ምክንያት አዲስ ሐሳብ ይዘው የሚመጡ መሪዎች ከሕዝባቸው ሞገደኝነት ጋር መጋጨታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ይኼኔ ሕልማቸውን ለማስፈፀም ሲሉ ከሞገደኞች ጋር ግብግብ ይገጥማሉ፡፡
ብዙ ጊዜ መሪዎችን ገዢ የሚያደርጋቸው ዋና ምክንያት የሕልማቸው ከፋት ሳይሆን ሕልማቸውን ለማስፈፀም ከጥበብና ከብልሃት ይልቅ ጉልበት መጠቀማቸው ነው፡፡
ጉልበትን መጠቀም ቀላሉና አእምሮን የማይጠይቀው ዘዴ ነው፡፡ ሕዝብን አሳምኖና በጐ ተጽእኖ ፈጥሮ መምራት ግን እጅግ ፈታኝና ጥበብን የሚጠይቅ መንገድ ነው፡፡
መሪዎች ቀላሉን መንገድ በመምረጥ ሕልማቸውን ለማስፈፀም በሚያደርጉት መውተርተር ውስጥ ሕልማቸውን ማስፈፀም ቀርቶ የነበረንን እንኳን እንድናጣ እየሆንን ጉዟችን ወደኋላ ሆኗል፡፡
“ፌዘኝነት” በሌላ በኩል ቁም ነገሮችን ሁሉ ወደ ቧልት በመቀየር ሐሳቦቹ ተገቢውን ዋጋ እንዳያገኙ ማድረግ ነው፡፡ እንደ ማኅበረሰብ ካሉብን ችግሮች አንዱ ሊያንገበግበን፣ ሊያስቆጨንና ሊያብሰለስለን በሚገባው ሁሉ ላይ ፌዝና ቧልት እየተረክን እንደማሽላው እያረርን መሳቃችን ነው፡፡ በሂደት የጉዳዩ አሳሳቢነት ቀርቶ ስለጉዳዩ እንቶኔ የቀለደው ቀልድ እየገነነ፤ ከችግራችን መፍትሔ ሳይሆን ቀልድ እንፈጥራለን፡፡
አንድ አዲስ ሐሳብ ያነሣ ሰው ሐሳቡን ከፌዝና ከቧልት መጠበቅ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ለቁም ነገር የተባለው ሐሳብ ለቀልድ ውሎ ባክኖ ይቀራል፡፡ ቀልድ ጭቆናን ለመቋቋም የሚያገለግል ነገር ነው፡፡ ብዙ በጭቆና ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች የጭቆናቸውን ሕመም የሚቋቋሙትና ኑሯቸውን የሚያስቀጥሉት ራሳቸውን በቀልድ እየደለሉ ነው፡፡ ነገር ግን ቀልድ ሰዎች ጭቆናን በሥርዓት ታግለው እንዳያሸንፉ ጊዜያዊ መደለያ ስለሚሆናቸው በሽታውን ከማዳን ይልቅ ሕመሙን የማስታገሻ መንገድ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ጭቆናን የማስቀጠል ሚና ይኖረዋል፡፡
ኢትዮጵያውያንም ለረጅም ዘመን በጭቆና ውስጥ በመኖራችን ምክንያት የጭቆናን ሕመም የምንደልልበት የቀልድ ልማድ አዳብረናል:: በርግጥ ቀልድ ጭቆናን ከመደለል ባሻገር ለገዢዎች መራራውን እውነት አዋዝቶ ለማቅረብ ይጠቅማል፡፡ ነገር ግን በቀልድ የቀረበን ነገር ከቁም ነገር ቆጥረው መፍትሔ የሚሰጡ ገዢዎች ከስንት አንድ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ቀልድ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ መግባት ሲጀምርና ከቁም ነገር ጋር የሚለያቸውን ድንበር አልፎ ሲሄድ ጭቆናንም ሆነ ማንኛውንም ስህተት ለማረም ዕድል ይነፍጋል:: ትልልቅ ሐሳቦችን ያጫጫል፡፡
የፌዘኝነት ልማድ የሰዎችን ሐሳብ ዕድገት ሲገድል ነው የኖረው፡፡ በተለየ መንገድ ለማሰብ የሞከሩ የሀገራችን ሰዎች ቀልደኞች ተደርገው ሲቆጠሩ ኖረዋል፡፡
ሰዎች ሞክሮ መሳሳትንና አዲስ ነገር መጀመርን ይፈሩታል፡፡ ይሳቅብናል፤ መሳቂያ መሳለቂያ እንሆናለን፤ እናፍራለን፤ የሀገር መተረቻ እንሆናለን ብለው ይፈራሉ፡፡ በቁም ነገር ወስዶ ከማበረታታትና ከማረም ይልቅ በነገሩ ላይ ማፌዝ ስለሚመረጥ ከመናገር ዝምታ፣ ከመሥራት እጅ ማጣጠፍ፣ ከመሞከር መቆጠብ፣ ከመጀመር መከተል እንዲመረጥ አድርጐታል፡፡
ሦስተኛው ሳንካ “አድር ባይነት” ለውጥን የሚፈትነው ሌላኛው የአስተሳሰብ ጽንፍ ነው:: አድር ባይነት የመሪዎችን ሕልም ለጊዜያዊ ጥቅም ሲሉ ሳያላምጡ የመዋጥ ችግር ነው፡፡ አድር ባዮች ሕልሙን ሳያላምጡ ስለሚውጡት የሕልሙን ጣዕም አያውቁትም፡፡ የተነገራቸውን ሁሉ “እሽ” ብለው የሚቀበሉና “አቤት ወዴት” የሚሉ በመሆናቸው በገዢዎች ዘንድ ተወዳጅና ተመራጭ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን አድርባ ባይነት ሕልምን ለማሳካት የሚጫወተው ሚና በአመዛኙ አሉታዊ ነው፡፡ መሪዎች ሕልማቸውን ከልቡ ተጋርቶ ያንን እውን ለማድረግ የሚደመርና ሕልሙ ላይ ችግር ሲኖርም ያንን ችግር ለመናገር፣ ከመሪዎችም ጋር ለመወያየትና ለመከራከር ወደኋላ የማይል ተከታይ ነው የሚያስፈልጋቸው፡፡ በሀገራችን ይህ የአድር ባይነት አስተሳሰብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጣም እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት የሕዝብን ድጋፍና ተቃውሞ መለየት እስኪሳነን ድረስ ደርሶ ነበር፡፡ አድር ባይነት የጋራ ግብን አስቀምጦ ለመንቀሳቀስ ትልቅ ዕንቅፋት የሆነብን ችግር ነው፡፡
በፖለቲካውም ሆነ በሕዝብ አገልግሎት አመራር ሂደት ውስጥ አድር ባይነት ትልቅ በሽታችን ነው፡፡ በፖለቲካው መስክ አድር ባይነት በሕዝብ ዘንድ ሲሠርጽ በሕዝብና በመሪ መካከል የሐሳብ ግብይት አይኖርም፤ ቢኖርም ጤናማ አይሆንም፡፡ ይኸም ማለት በአንድ ሀገር ፖለቲካ ውስጥ መንግሥት የሕዝብን ድምጽና ትክክለኛ ፍላጐት ማወቅ የሚችልበት መንገድ አይኖርም ማለት ነው፡፡ በዚህም መንግሥት የሕዝብን ሐሳብ ሳይገዛ የራሱን ሕልም ለመሸጥ የሚሞክርበት ሁኔታ ይፈጠራል፤ ያ ደግሞ ለፖለቲካ ቀውስ ይዳርጋል፡፡ መንግሥት የሕዝብን ፍላጐት ማወቅ የሚችለው ምክንያታዊ የሆነ የሐሳብ ልውውጥ በመሪና ተመሪ መካከል ሲካሄድ ነው፡፡ ድጋፉንም ሆነ ተቃውሞውን በግልጽ መመርመርና ለውጥ ማምጣት የሚቻለው አድር ባይነቱ ሲቀር ነው:: በሕዝብ አገልግሎት ሥራዎች ላይም መሪዎች በአድርባይ ሠራተኞች ስለሚከበቡና ከሞገደኞች ለመራቅ ሲሉ ከአድር ባዮች ጋር የጫጉላ ሽርሽር ውስጥ ይገባሉ፡፡
አድርባ ባዮቹ ለተቋማት ስኬትና ለሕዝብ ጥቅም ከመጣር ይልቅ መሪዎቻቸውን በማስደሰት ጥቅም ለማግኘት ይጥራሉ:: በተቋማት ውስጥም ለሕዝብ ከመቆምና ለተቋሙ ራዕይ ስኬት ከመረባረብ ይልቅ አለቃን ለማስደሰት ሲባል የመኩነስነስ ባሕርይ ይሰፍናል፡፡
ሞገደኞች፤ ፌዘኞች እና አድርባዮች ወደ ምክንያታዊ ተከታይነት እስካልተለወጡ ድረስ ማንኛውም በጐ ሕልም በእነዚህ አስተሳሰቦች ምክንያት በቶሎ ይመክናል፡፡ ይህ ሲባል ግን ሞገደኝነትም ሆነ አድር ባይነት የሕዝብ ወይም የተመሪ ችግሮች ብቻ ሳይሆኑ በመሪዎችም ላይ የሚስተዋሉ ጉዳዮች መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
መሪዎች ከሕዝብ የሚነሳን ወይም ከተመሪዎቻቸው የሚሰነዘርን ተቃውሞና ሐሳብ እንደ አስፈላጊነቱ የሚቀበሉ ካልሆኑ ራሳቸው ሞገደኛ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ይኸም መሪነት የሚያስፈልገውን የጋራ ሕልምን ትቶ የራሱን የመሪውን ሕልም ብቻ ይዞ ስለሚጓዝ መሪውን ከመሪነት ወደ ገዥነት ይቀይረዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የሕዝብን ሐሳብና ፍላጐት እያነጠሩ ከመውሰድ ይልቅ ሳያላምጡ የሚውጡ ከሆነ “ሕዝበኝነት” ያጠቃቸዋል:: ሕዝበኝነት የመሪዎች አድር ባይነት ነው፡፡ መሪዎች የሕዝብን ስሜታዊ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ የሕልም እንጀራ የሚጋግሩበት መንገድ ነው፡፡ አመክንዮአዊ በሆነ መንገድ እንደማይሳካ፣ ትክክልም እንዳልሆነ እያወቁ የሕዝብን ስሜታዊ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ግን የማይሆነውን ይሆናል ይላሉ፡፡ ከዘላቂ ዓላማ ይልቅ ጊዜያዊ ነጠብጣቦችን ይመርጣሉ፡፡
የምክንያታዊነት ጉድለታችን ሕይወት የሰጣቸው የሞገደኝነት፤ የፌዘኝነትና የአድር ባይነት ችግሮች ምክንያታዊነት እየጐለበተ ሲሄድ እንደሚቀረፉ ግልጽ ነው፡፡ ምክንያታዊነት ሲጐለብት ተነጋግሮ ለመግባባት የሚያስችል ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ንቃተ ህሊና ይኖራል:: ይህ ሲሆንም በብቸኝነትን ጉድለት ውስጥ እየበሰበሱ ከመምጣት ወጥቶ ወደ ከሱትነት ለማምራት ይቻላል፡፡
(“መደመር” ከዶ/ር ዐቢይ አህመድ
መፅሐፍ የተወሰደ)

  ከዕለታት አንድ ቀን፣ በአንድ ጫካ ውስጥ፣ አንድ ነብርና አንድ አውራሪስ ይኖሩ ነበር፡፡
በጫካው ውስጥ አንዳች የሚንቀሳቀስ ፍጡር እስኪጠፋ ድረስ፣ ሁሉን በልተው፣ ሁሉን ተቀራምተው ጨረሱት፡፡ ዛፍ ቅጠሎም አልቀረም፡፡  ድሮ፣ ሁለት ሰፋፊ ጫካዎች ነበሩ፡፡ ዛሬ፣ ግን ከአንዲት ቅርንጫፍ በስተቀር፣ የእፅዋት ዘር ሁሉ ተበልቶ አልቋል፡፡
የሚበላ የሚቀመስ አጡ፡፡ የሚጠጣ ጠብታ ውሃ ጠፋ፡፡ ስለዚህ አንድ መላ መመታት ነበረበት፡፡
አንድ ጠዋት አያ ነብሮ፡-
“አያ አውራሪስ?” አለው፡፡
“እህ አያ ነብሮ - ምን ልርዳህ?”
“ችግሩ የጋራ ነው›› አለ አያ ነብሮ፡፡
“ምን ዓይነት የጋራ ችግር?”
“የኸውልህ አያ አውራሪስ፤ ነጋ ጠባ ለምግብነት የምንገለገልበትና ምግብ የምናገኝበት ጫካ፣ እያደር እየመነመነ መጣ፡፡”
“ታዲያ ምን ዘዴ እንፍጠር? እንዴትስ እናድነው?”
“አንድ መላ አለኝ በበኩሌ”
“እኮ ምን ዓይነት መላ?”
“እነግርሃለሁ፡፡ ከዚያ በፊት ግን፣ እንማማል!”
“እንማማል?”
“አዎን እንማማል”
“እሺ ምን ብለን እንማማል?”
‹‹ከዚህ ጫካ አንዳችን ካለአንዳችን ፍቃድ አንዲት ቅጠል እንኳ ላንበጥስ እንማማል”
“ከሕጉ ወይም ከመሀላው ውጪ ቅጠል በጥሰን ብንገኝስ?”
“ወንጀሉ በልጅ ልጆቻችን ይድረስ!”
‹‹ይድረስ፣ ይድረስ›› ተባብለው በመሀላው ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ በቃ፣ የጠፋው ጫካ ተመልሶ ይለመልማል፡፡ ጥንቸልና ሚዳቋ ይበረክታል አሉ፡፡
ከጥቂት ወራት በኋላ ሲታይ ግን፣ ባሰበት እንጂ አልተሻለውም፡፡ ለካ፣ አንዱ ከሌላው እየተደበቀ ቀን ከሌት መብላት ጀምሯል፡፡
አንድ ቀን አውራሪስ፣ አንዲት ቅጠል አግኝቶ እየተንጠራራ ለመቀንጠስ ሲሞክር፣ ድንገት ከኋላው ነብር ከተፍ አለ፡፡ አያ ነብር፣ የአውራሪሱን ገላ ሲያይ፣ ጎመዠ፡፡ ሳያመነታ ቸር ብሎ አውራሪሱ ላይ ጉብ ለማለት፣ አንገቱ ላይ ጥርሶቹን ለመትከል ተወነጨፈ፡፡
ሆኖም አውራሪሱን ለማነቅ በጣም ከመጣደፉ የተነሳ፣ አልፎት እቀንዱ ላይ በሆዱ አረፈና አንጀቱ ዝርግፍ አለ፡፡ ይሄኔ፣ አያ ነብሮ፤ መሬት ላይ ወድቆ እያቃሰተ ተናገረ፡፡
“ምነው አያ አውራሪስ፤ ቅጠል ላንነካካ ተማምለን?” ቅጠል የነካ፣ ተባብለን? የሚወጋ ይውጋው ተባብለን? በእርሱና በልጁ ልጆቹ ይድረስ ተባብለን?››
“ያንተ አያትና ቅድመ አያት፣ ከኔ አያት፣ ቅድመ አያት ጋር ምን እንደተማማሉ ይታወቃል?›› አለ አውራሪስ፡፡
*   *   *
በእርግጥም የማይተማመን ባልንጀራ፣ ወንዝ ለወንዝ ይማማላል ተብሏል፡፡ ምንጩ ጥርጣሬ ነው፡፡ መሠረቱ ሥጋት ነው፡፡
ዛሬ እገሌና እገሌ፣ እጅና ጓንት፣ ፈትልና ቀሰም ናቸው፡፡ አገሪቱን ቀጥ አድርገው ይመሯታል እየተባለ እየተደመደመ ሳለ፤ የቱም ሳይሰምር ‹‹ውይ ተለያዩ’ኮ›› የሚል መረጃ ይወጣል፡፡ ‹‹ዛሬ፣ እጅና ጓንት ናቸው ማለት ይቻላል›› ማለት ሊኖርብን ነው - የነገውን ከጠረጠርን፡፡
ዱሮ፣ የሶማሌ ሬዲዮ እንዲህ ዓይነት ጠርጣራ አባባሎች ነበሩት ይባላል፡፡ በአስረጅነት እንጥቀስ፡-  
“የሶማሊያ ምክር ቤት፣ ዛሬ በሞቃዲሾ ከፍተኛ ውይይት ሲያካሂድ ዋለ፡፡
ነገም ስብሰባውን የሚመሩት፣ የአብዮቱ ከፍተኛ መሪ ጄኔራል ዚያድ ባሬ ናቸው ለማለት ያስደፍራል” የሚል የሬዲዮ ዜና አይጣል ነው፡፡
የፓርቲዎች መብዛት ጥቅምም ጉዳትም አለው፡፡ ጥቅሙ ህዝቡ አማራጭ እንዲያገኝ፣ ቢሻው እንዲገባ፣ ባይሻው እንዲተው ነው፡፡ አንድም ደግሞ ሕዝቡ ሃሳቡን ለማብላላት በቂ ትንፋሽ፣ ይዞ ረዥም መንገድ ለመጓዝ የሚያስችል አቅም (ፊያቶ) እንዲኖረው ይበጀዋል:: ከቶውንም አንዳች ለውጥ ተከሰተ ሲባል፣ አዲስ ልብስ እንደተሰፋለት ልጅ ፍንድቅድቅ ያደርጋል ብሎ ማሰብ ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ ለውጥ ሁሌም ይኖራል፡፡ (Everything Changes except the law of change እንዲሉ) እያንዳንዱ ነገር ተለዋጭ ነው፣ ከለውጥ ህግ በስተቀር፡፡
አዳዲስ ለውጥ ሲከወን ባየን ቁጥር እንደምንታዘበው፣ ከዚህ ጋር ለረዥም ጊዜ ባየነው አካሄድ ውስጥ፣ የሃይማኖቶች ብዛት፣ የአደንዛዥ ዕፅ ብዛት እና የከበር - ቻቻ ቤት ብዛት ሞቅ ደመቅ እያለ ነው፡፡
በአንፃሩ ትምህርት በነበረበት - ባለበት ላይ ነው፡፡ ግብረገብነት ባለበት ላይ ነው፡፡ ጤና ግን የተባባሰ ይመስላል፡፡ የወላጆችና የመምህራን ግንኙነት አወዛጋቢ ነው፡፡ የተቃዋሚዎች ነገረ ሥራ ቅጥ አምባሩ ጠፍቷል፡፡
ምርጫው ደግሞ እየደረሰ ነው፡፡
የአሜሪካ መራጮች፣ ምርጫን በዓለም ላይ ለማስፋፋትና ዲሞክራሲን ለማስፈን ከአለም ዳርቻ እስከ ዓለም ዳርቻ ውቅያኖስ አቋርጠው ይሄዳሉ፡፡ የምርጫ ሳጥን ውስጥ ምርጫቸውን ለመክተት ግን እስከምርጫው ሳጥን ድረስ እንኳ መንገድ ማቋረጥ አይችሉም፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሳይሻል አይቀርም፡፡
“ዝም ብንል ብናደባ፣ ዘመን ስንቱን አሸክሞን
የጅልነት እኮ አይደለም እንድንቻቻል ነው ገብቶን”
ከፀጋዬ ገ/መድህን (ማነው ምንትስ?)
ዛሬም ብዙ የለውጥ ዕድል እንዳመለጠን አንዘንጋ፡፡ ገና ብዙም ያመልጠናል፡፡ ምክንያቱም ከትላንት ያለመማር አባዜ፣ ከትላንት እስከ ዛሬ፣ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ተጫጭኖናል፡፡ አዛውንት ምሁሮቻችንንና አበው የዕውቀት ካህኖቻችንን ተንከባክበን የጠዋት ልህቅናቸውን ለመጋራት እንጣር፣ እንትጋ፣ ለትውልድም እንብቃ!!


  ብራድ ፒት ላለፉት 20 አመታት አልቅሶ እንደማያውቅ ተናገረ

           ታዋቂው ድምጻዊ ኤኮን በትውልድ አገሩ ሴኔጋል በስሙ የምትሰየም የራሱን አዲስ ከተማ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ፣ ዝነኛው የሆሊውድ ተዋናይ ብራድ ፒት ደግሞ ላለፉት 20 አመታት ገደማ አንድም ጊዜ አልቅሶ እንደማያውቅ መናገሩን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ከአስር ያህል አመታት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ትጠናቀቃለች ተብላ የምትጠበቀዋ የአዲሷ የኤኮን ከተማ ግንባታ ባለፈው መጋቢት ወር መጀመሩን ድምጻዊው ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፤ ግንባታው የሚከናወነው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ለድምጻዊው በስጦታ ባበረከቱለትና ከመዲናዋ ዳካር አቅራቢያ በሚገኘው 2 ሺህ ካሬ መሬት ላይ መሆኑንም አመልክቷል፡፡ አዲሷ ከተማ ሙሉ ለሙሉ ከጸሃይ ብርሃን የሚመነጭ ሃይል የምትጠቀመውና በቴክኖሎጂ የተራቀቀች እንደምትሆን የተነገረላት አዲሷ የኤኮን ከተማ፤ ዘመናዊ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያን ጨምሮ አንድ ከተማ ሊኖራት የሚገባው መሰረተ ልማት እንደሚሟላላትም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ኤኮን ላይቲንግ አፍሪካ በሚል ፕሮጀክት 600 ሚሊዮን ያህል አፍሪካውያንን የታዳሽ ሃይል አቅርቦት ለማሟላት አቅዶ እየሰራ የሚገኘው ድምጻዊው፤ ከዚህ ቀደም ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደር በይፋ መናገሩን ተከትሎ መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ ታዋቂው የፊልም ተዋናይ ብራድ ፒት፣ ባለፉት 20 ያህል አመታት ጊዜ ውስጥ አንድም ቀን አልቅሶ እንደማያውቅ ከሰሞኑ ከአንድ መጽሄት ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ መናገሩን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ከቀድሞ ባለቤቱ አንጀሊና ጆሊ ጋር በማደጎ 6 ልጆች ያሉት የ55 አመቱ የሆሊውድ የፊልም ተዋናይ ብራድ ፒት፤ ባለፉት 20 ያህል አመታት ብዙ አሳዛኝና ልብ የሚሰብሩ ነገሮች ቢገጥሙትም፣ ስሜቱን ከመቆጣጠር ባለፈ አልቅሶ እንደማያውቅ ተናግሯል፡፡
ብራድ ፒት በተለይም ከአንጀሊና ጆሊ ጋር ለሁለት አመታት የዘለቀውን ትዳር አፍርሶ፣ ከሶስት አመታት በፊት በፍቺ መለያየታቸውን ተከትሎ፣ በብቸኝነትና በሃዘን እየተቆራመደና መጠጥ በማብዛት ህይወቱን እየገፋ እንደሚገኝ ሚዲያዎች ቢዘግቡበትም፣ እሱ ግን የመጣውን በጸጋ በመቀበል ራሱን አረጋግቶ እንደሚኖር ገልጧል፡፡

Saturday, 30 November 2019 14:01

የዘላለም ጥግ

• የተለያዩ ሰዎች የተለያየ አመለካከት አላቸው፡፡ ሁሉንም ማክበር ጥሩ ነው፡፡
  ጁአን ፓብሎ ጋላቪስ
• ያለ አንተ ስምምነት ማንም የበታችነት እንዲሰማህ ማድረግ አይችልም፡፡
  ኤሊኖር ሩስቬልት
• ሌሎች እንዲያከብሩህ የምትሻ ከሆነ ራስህን አክብር፡፡
  ባልታሳር ግራሽያን
• ዕውቀት ሃይል ይሰጥሃል፤ ሰብዕና ግን ክብር ያጎናጽፍሃል፡፡
  ብሩስ ሊ
• ለሕይወት ክብር በመስጠት ላይ ያልተመሰረተ ማንኛውም ሃይማኖት ወይም ፍልስፍና፤ እውነተኛ ሃይማኖት ወይም ፍልስፍና አይደለም፡፡
  አልበርት ኸዌይትዘር
• ፍቅር ያለ ክብር ባዶ ቃል ነው፡፡
  ኒክሂል ሳሉጃ
• በጣም ብዙ ሰዎች ትክክለኛው ሰው ለመሆን ከመጣር ይልቅ፡፡ ትክክለኛውን ሰው በመፈለግ ይባዝናሉ፤
  ግሎርያ ስቴይኔም
• ለሌላው ክብር ስትሰጥ አንተም ክብር ታገኛለህ፡፡
  ማይክል ኑተር
• የሌሎችን አመለካከት የግድ መጋራት የለብንም፡፡ ነገር ግን ክብር መስጠት ይገባናል፡፡
  ቴይለር ስዊፍት
• ወላጆቹን ሳያከብር ያደገ ልጅ፤ ለማንም ሰው እውነተኛ ክብር አይኖረውም፡፡
  ቢሊ ግራሃም
• ሴትን ሁልጊዜ አከብራለሁ፡፡
  ኢንሪኪው አይግሬስያስ
• የሌሎችን መብት ማክበር ማለት ሰላም ነው፡፡
  ቤኒቶ ጁአሬዝ
• ለአስተማሪዎችህ የሚገባቸውን ክብር ስጣቸው፤ ምክንያቱም መድረስ የምትፈልግበት ቦታ እንድትደርስ የሚያግዙህ እነሱ ናቸውና፡፡
  ሪቻርድ ሁዋርድ

Saturday, 30 November 2019 13:59

የፖለቲካ ጥግ

• ዲሞክራሲ የተሳሳተ ምርጫ የማድረግ መብት ነው፡፡
   ሰር ጆርጅ በርናርድ ሾው
• እያንዳንዱ ምርጫ የሚወሰነው ድምፅ ለመስጠት ምርጫ ጣቢያ በሚገኘው ሕዝብ ነው፡፡
  ሴር ሳባቶ
• ዲሞክራሲ፤ እያንዳንዱን ሰው የራሱ ጨቋኝ የመሆን መብት ያጎናጽፈዋል፡፡
  ጄምስ ራስል ሎዌል
• ዲሞክራሲ በየትውልዱ እንደ አዲስ መወለድ አለበት፤ ትምህርት ደግሞ አዋላጁ ነው፡፡
  ጆን ዲዌይ
• ዲሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች አይንጣጠሉም፡፡
  ኔልሰን ማንዴላ
• ዲሞክራሲያችን የተዋጣለት እንዲሆን መራጩ ሕዝብ በምርጫ ሂደቱ እምነት ሊያድርበት ይገባል፡፡
  ብላንቼ ሊንከን
• ዲሞክራሲ ጥሩ ነው፡፡ ይሄን የምለው ሌሎች ሥርዓቶች የከፉ ስለሆኑ ነው፡፡
  ጃዋሃርላል ኔህሩ
• ዲሞክራሲ፤ ድምፅ መስጠቱ አይደለም፤ ቆጠራው ነው፡፡
  አል ስሚዝ
• ዲሞክራሲና ነፃነትን ወደ ሳጥን ውስጥ መመለስ አትችልም፡፡
  ግሎሪያ ስቴይኔም
• በዲሞክራሲ ሥርዓት ዜጎች የተለያዩ የዜናና የመረጃ ምንጮች ይፈልጋሉ፡፡
  በርኒ ሳንደርስ
• ዲሞክራሲ፤ በአንድ ላይ ለየራስ የማሰብ ጥበብ ነው፡፡
  አሌክሳንደር ማይክል ጆን
• የዕለት ተዕለት ዜግነት በሌለበት፣ የዕለት ተዕለት ዲሞክራሲ ሊኖር አይችልም፡፡
  ራልፍ ናዴር
• ነፃነት ያለ ሃላፊነት ሥርዓት አልበኝነት ሲሆን፤ ነፃነት ከሃላፊነት ጋር ዲሞክራሲ ነው፡፡
  ኸርል ሪኔይ


Saturday, 30 November 2019 13:14

ማራኪ አንቀፅ

   --እስክንድርና ታምራት ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሠራተኞች የሥራ መጀመሪያ ሰዓት አንስተው ነበር ቪዲዮ መመልከት የጀመሩት:: በስቱዲዮ ፊልም ማቀናበሪያ ማሽን እየታገዙ በሐምሌና ነሐሴ 1983 የተላለፉ ፕሮግራሞች ለሦስት ሰዓታት አዩ፡፡ አራት ዐይኖች ለረዥም ሰዓት በስክሪን ላይ ፈጠው ሊያብጡ ደረሱ፡፡
ይህ የገረመው የቲቪ ማሽን ሠራተኛ፤ “የሻይ ሰዓት ስለሆነ ዕረፍት መውሰድ ትችላላችሁ” በማለት ከተመሰጡበት ስሜት ቀሰቀሳቸው:: አክሎም፤ “ወጥታችሁ ትጠጣላችሁ? ወይስ እዚህ ላምጣላችሁ?” አለ፡፡ ሁለቱም መልሳቸው አንድ ነበር፤ ያውም በፍጥነት፡፡
“ከተቻለ እዚህ ብታመጣልን እንወዳለን” የሚል ነበር፡፡
“ደህና ...ሻይ ….ቡና …..ለስላሳ……ምርጫችሁን ብትነግሩኝ?”
“ቡና በወተት….ካላስቸገርንህ ላይተር ሲጋራም ብታስልክልን…ከይቅርታ ጋር” ታምራት በትህትና የተናገረው ነው፡፡
“ዶንት ወሪይ (Don’t worry) ….ምንም ችግር የለውም ….ምን ዓይነት ሲጋራ?”
“ዊኒስተን አንድ ፓኬት…” አለ እስክንድር፤ የሃምሳ ብር ኖት እየሰጠው፡፡
እነ ፕሮፌሰር በዚህ የቪዲዮ ሶስት ሰዓት ምልከታቸው፤ በመላው አዲስ አበባ የቀይ ሽብር ተዋንያኖች ሲጋለጡ የተላለፈውን ፕሮግራም አገባደው ነበር፡፡ በመሐል ፒያሳ እነ እርገጤ መድባቸውና ኤልያስ ኑር የጨፈጨፉት…በጉለሌ ዙሪያ ከፍተኛ ሰባትና ስምንት ፍቃዱ የገደላቸው የኢህአፓ ወጣቶች …በጉራጌ ዞን ደግሞ ገስግስ የተባለው ያደረሰውን እልቂት ወዳጅ ዘመድ እየተነሳ ሲያጋልጥ ተመለከቱ:: በተለይ አንድ አዛውንት እናት፤ ቅዱስ የሆኑ ባላቸውና ልጆቻቸው እንደተገደሉባቸው እያነቡ አጋለጡ፡፡ ገስግስ ከክልል ውጪ አዲስ አበባ መጥቶ የአብሬት ሼክ የሆኑት አዛውንት፤ ያለ አንዳች ወንጀል ከእነ መኖሪያ ቤታቸው እንደወሰዳቸው …እስከ አሁን የት እንደደረሱ እንደማያውቁ ጐልማሳ ልጆቻቸው እያነቡ አጋለጡ፡፡
እነዚህ ልጆቻቸው በማከልም “…እስከ አሁን በአባታቸው የአብሬት ሼህ በሕይወት አለመገኘትና ተሰውሮ መጥፋት ሳቢያ…እናታቸው በሐዘን ተቆራምተው…ቤተሰቦቻቸው በሰቀቀን ሲጠበሱ እንዲኖሩ …የበለጠ ደግሞ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ጨምሮ …በእስልምና ሃይማኖት ቅድስናቸው …እኝኸ የአብሬት ሼህ ያፈሯቸው የሰባት ቤት ጉራጌ ህብረተሰብ ውስጥ የሚገኙ ተከታዮቻቸው…ምንጊዜም ሀዘናቸው አብሮዋቸው ይኖራል…” አሉ፡፡
ይህ የቪዲዮ ትዕይንት እንዳበቃ የከፍተኛ ሰባቱ ፍቃዱ ሲጋለጥ የሚያሳየው ምስል ቀጠለ:: ጋዜጠኛው ሰለሞን አስመላሽ፣ ሁለት ሴቶችን ከዳርና ከዳር አስቀምጦ ከመሃል ፍቃዱን መጠየቅ ጀምሯል፡፡
“እነዚህን ሴቶች ታውቃቸዋለህ?”
“አላስታውሳቸውም…”
“እናንተስ እሱን ታስታውሱታለችሁ?”....ጋዜጠኛው ነበር፡፡
“በደንብ ነዋ! ...አንድ ሰፈር አብረን ኖረናል…በደንብ እንተዋወቃለን…”
በስተግራ የተቀመጠችው በሲቃ ተናገረች፡፡
“እሺ የተፈፀመባችሁን በደል ግለጹ!...”
“በ1969 ዓ.ም ወር አንድ እለት፣ እኩለ ሌሊት ካለፈ በኋላ በራችን ተንኳኳ፤እናቴ ስትከፍት ፍቃዱ አጥራችንን ዘለው ከገቡ ግብረ አበሮቹ ጋር መሣሪያ እንደታጠቁ ዘው አሉ፡፡ …ወንድ ልጇን ውለጂ አሏት…ካየችው እንደሰነበተ ብትገልጽም፤ ከጥፊና ርግጫ አልዳነችም፡፡…በመጨረሻ ሁላችንንም አፍሰው ቀበሌ አሰሩን፡፡
“የበደላቸው በደል ከእስር ቤት እየጠሩ ማታ ጠጥተው እየመጡ ይዳሩን ጀመር በተለይ ፍቃዱ መጀመሪያ እናታችንን …አስገድዶ ከተገናኘ በኋላ …ቀጥሎ እኔና ታናሽ እህቴን ተራ አስገባን…” በማለት እንባ እየተናነቃት ተናገረች፡፡
ጋዜጠኛው የከፍተኛ ሰባቱን ጨፍጫፊ ፍቃዱን እየተመለከተው “…እህሳ! ...ለዚህ ምን መልስ አለህ? አለ፡፡ አረመኔው ፍቃዱ የሐሰትን ሸማ እንደተከናነበ የውርደት ማቁን ተከሽኖ መዘባረቅ ጀመረ፡፡ ጊዜ የገለጠው ጉድ፣ ወቅት ያሳጣው ግፍ በዚህ መልክ ለአደባባይ በቃ፡፡
እነ ፕሮፌሰር ቡና እንደመጣላቸው፣ ቪዲዮውን አጥፍተው ዕረፍት ወሰዱ፡፡ ለትንሽ አፍታ ዝም ብለው በራሳቸው ሐሳብ ተዋጡ፡፡ ሲጋራ እየለኮሰ ዝምታውን የገረሰሰው ታምራት ነበር…ቀድሞ፡፡    
ምንጭ፡- (ከዘውዴ አርጋው “የአሲንባ ናሙና መርካቶ” የተሰኘ  አዲስ መጽሐፍ የተቀነጨበ፤2012 ዓ.ም)

Saturday, 30 November 2019 12:39

ዜና ዕረፍት - መንግሥቱ አበበ

    የወዳጆቹ ማስታወሻ - ጋዜጠኛ መንግስቱ አበበ


         ላለፉት 18 ዓመታት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ በከፍተኛ ሪፖርተርነት ሲያገለግል የቆየው ጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበ፣ ባደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ባለፈው ቅዳሜ ህዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ ሲሆን የቀብር ሥነሥርዓቱ እሁድ ህዳር 14 በቀጨኔ መድሃኒያለም ቤ/ክርስቲያን ቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹና የስራ ባልደረቦቹ በተገኙበት ተከናውኗል፡፡
ጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበ፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጣን ከመቀላቀሉ በፊት በመንግሥት እየታተመ ይወጣ በነበረው ሳምንታዊ የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ በዜናና አምድ አራሚነት፣. የጋዜጠኝነት ሥራን በ1977 ዓ.ም. የጀመረ ሲሆን ቀጠሎም ወደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በመዛወር፣ በሪፖርተርነት በኋላም የካቲት ይባል በነበረው ወርሓዊ የመንግሥት መጽሔት በተባባሪ አዘጋጅነት አገልግሏል፡፡ በመቀጠልም በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ይታተም በነበረው ዕለታዊ አዲስ  ጋዜጣም በከፍተኛ ሪፖርተርነት አገልግሏል፡፡
በመጨረሻም ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ሕይወቱ እሰካለፈበት  ጊዜ ድረስ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል፣ በተመደበበት የጋዜጠኝነት መስክ ሁሉ ሁለገብ ሆኖ የሰከኑና ሚዛናዊነትን የተላበሱ በሳል ጽሁፎችን ለአንባቢያን ሲያቀርብ የቆየ ከፍተኛ ሪፖርተር ነበር፡፡  
ጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበ፤ በተለይም በማህበራዊ፤ በሳይንስና በጤና-ነክ ጽሁፎቹ በበርካታ አንባቢያን ዘንድ የተወደደና በሥራ ባልደረቦቹ የተመሰገነ ታታሪ ጋዜጠኛ ነበር፡፡  
አመለ ሸጋው ጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበ፣ ለኢንፎርሜሽን ሳይንስ ከነበረው የጠለቀ ፍቅር የተነሳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲከታተል የነበረውን የማኔጅመንት ትምህርት አቋርጦ፣ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በኢንፎርሜሽን ማኔጅመንት ሳይንስ በባችለር ዲግሪ ተመርቋል::  
የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል፣ በጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበ ሕልፈት የተሰማውን ጥልቅ ኃዘን እየገለፀ ለቤተሰቡ፤ ለዘመዶቹ፤ ለሥራ ባልደረቦቹና ለጓደኞቹ ሁሉ መጽናናትን ይመኛል፡፡ ፈጣሪ ነፍሱን በመንግስተ ሰማያት ያኑርለት፡፡


         «የአዲስ አድማሱ ጋዜጠኛ መንግስቱ አበበ፣ ከዚህ አለም በሞት በመለየቱ በእጅጉ ሀዘን ተሰምቶኛል።
መንጌን ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል የተዋወቅሁት፣ የጉዞ አድዋ የመጀመሪያ ጉዞ ፍፃሜ ላይ፣ የካቲት 23 ቀን 2006 ዓ.ም. አድዋ ድረስ ከመጡ የጋዜጠኞች ቡድን አንዱ ሆኖ ነው።
ከተዋወቅን በኋላ በተደጋጋሚ ተገናኝተናል። ፍፁም ቅን ሰው ነበር። ለስራው በግሉ የሚወስደው ከፍተኛ ኃላፊነትና ለመልካም ነገር በፍጥነት ሁሌም የሚገኝ ሰው በመሆኑ እደሰትበት ነበር። ከዚህ አለም በሞት መለየቱን በመስማቴ በእጅጉ አዝኛለሁ።
ለቤተሰቦቹና ለስራ ባልደረቦቹ በሙሉ መጽናናትን እመኛለሁ።”
(ያሬድ ሹመቴ - ፌስቡክ)
***
«የቀድሞ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ባልደረባዬ፣ ጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበ፣ ከዚህ ዓለም መለየቱን ፌስቡክ ላይ አነበብኩ።
አንዳንድ ጊዜ ከሩቅ ሆኖ ነፍስ ይማር ማለትም ይተናነቃል። ምናልባት ሕይወቱ ማለፉን መቀበል አቅቶኝ ይሆናል።
መንጌ ጥሩ ባልደረባዬ ነበር። ብዙ ሳቆችን አብረን ስቀናል። አገሬ ተመልሼ የማገኛቸው ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየቀነሰ ሲመጣ በጣም ያስከፋል። ግን ምን ይባላል? የፈጣሪ ሥራ አይቀየር።
ለቤተሰቦቹና ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ቤተሰቦች መፅናናቱን ይስጣችሁ። እግዚያብሔር ነፍስህን በአፀደ ገነት ያሳርፈው። ደህና ሁን፤ ወንድሜ መንጌ!”
(ጽዮን ግርማ ታደሰ - ፌስቡክ)
***
“ከዚህ ዓለም በሞት የተለየንን ጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበን፣ በሥራዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቅሁት በ”አዲስ ዘመን” ጋዜጣ የ”ሕብረተሰብ” አምድ አዘጋጅ ሆኖ በሚያቀርባቸው ፅሑፎቹ ነበር።
ከዚያ በኋላ በ‘90ዎቹ መጀመሪያ  በ”ዕለታዊ አዲስ” ጋዜጣ ኤዲተርነት፣ ላለፉት 15 ዓመታት ደግሞ በተወዳጅዋ “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ላይ ከከፍተኛ ሪፖርተርነት እስከ አዘጋጅነት ሠርቷል።
በጋዜጠኝነት ሙያ የአንድ ጎልማሳ ዕድሜን ያሳለፈው መንግሥቱ አበበ ፤ ጋዜጠኛነትን  ታስሮ መግነኛ፣ የፖለቲካ መሸቀጫ፣ ጥገኝነት ማግኛና ወደ ሌላ ሙያ መሸጋገሪያ ድልድይ አድርገው የሚያዩ “የሥም ጋዜጠኞች” በሞሉባት ሀገር ላይ በሙያው በቅቶ፣ በሙያው ታምኖ፣ ሥነ ምግባር ጠብቆና “ግነን በሉኝ” ሳይል፣ ድምፁን አጥፍቶ፣ ያለፈ ጎምቱ ጋዜጠኛ ነው። ስለ ጠባዩም ባልደረቦቹ ሲያወጉኝ፤ ”ትሁትና ከአፉ መጥፎ የማይወጣው ሰው ነበር” ብለውኛል፡፡
በሠላም እረፍ መንጌ !!!”
(ጀሚል ይርጋ - ፌስቡክ)
***
“መንጌ፤ ከረጅም ጊዜ ጓደኞቼ አንዱ ብቻ ሳይሆን የሙያ ባልደረባዬም ጭምር ነበር:: እኔ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ውስጥ እሰራ በነበረበት ጊዜ፣ መንግስቱ ደግሞ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ላይ በጋዜጠኝነት ይሰራ ነበር፤ ሙያችን ያገናኘን ነበር፡፡
ከጭምትነቱ፤ ከትሁትነቱና ሰው አክባሪነቱ በላይ ስለ መንግስቱ ሳስብ በጣም የሚገርመኝ፣ ምን ቢቸገር ክብሩን የማያዋርድና ብዙዎች ዘንድ የማይታይ ጨዋ ሰው መሆኑ ነበር፡፡
ሙያውን በማክበሩና መወስለትን ስለሚጠየፍ ሳይጠቀም የኖረ ሰው ነበር፡፡
ሕመሙ በጠና ሰዓት እንኳን ሰውን ያስቸገረ እየመሰለው ዕርዳታ ማግኘት ሳይችል ተጎድቶ ያለፈ ሰው ነው፡፡  ለመንግስቱ አበበ የነበረኝን ክብር በተለየ ሁኔታ ከፍ ያደረገልኝ ሌላው ነገር ደግሞ፣ በህይወቱ የመጨረሻ ሰዓት ላይ ያደረገው እጅግ ታላቅ ነገር ነው፡፡
በእጁ ላይ የነበረችው እጅግ ትንሽ ጥሪት፣ ለኢትዮጵያ ልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ እንድትውልለት መናዘዙ፣ መንጌ ለሁላችንም ትምህርት ሰጥቶን ያለፈበት ታላቅ ተግባር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ነፍሱን ይማርልን!...”
መለሰ አወቀ
(የቀድሞ የሙያ አጋርና ጓደኛ)
***
“ከአንደበቱ ክፉ ቃል የማይወጣው፤ በቻለው አቅም ሁሉ ለሰዎች በጎ ነገር ለማድረግና ለማስደሰት የማይታክት መልካም ወዳጄ ነበር - መንግስቱ አበበ፡፡
የመንጌ ትጋትና ጥረት እጅግ የሚያስገርም ነበር፤ በህመም እየተሰቃየ ባሳለፋቸው ጊዜያት ሁሉ፣ ከስቃይ ጋር እየታገለ ስራውን ለማከናወን ደፋ ቀና ማለቱን አላቋረጠም ነበር:: መንጌ ከመልካምነቱ፣ ከቅንነቱና ከትጋቱ ጋር ወደማይቀረው ሄደ! ፈጣሪ ነፍስህን በገነት ያኑራት ጓዴ!...”
አንተነህ ይግዛው
(የስራ ባልደረባና ጓደኛ)
***
‹‹መንጌ ክብርና ኩራቱን እንደጠበቀ ነው ያለፈው››
መንጌን ያወቅኩት የአዲስ አድማስ ባልደረባ ከመሆኔ አስቀድሜ በተለያዩ የስራ ስምሪቶች ላይ ነው፡፡ በተለይም በ2003 ዓ.ም ወደ ነቀምት አብረን ከተጓዝንና አራት ቀናትን በስራ ላይ ካሳለፍን በኋላ ገራገርነቱን፣ ትህትናውን፣ ተጫዋችነቱንና ቅንነቱን ይበልጥ ለማወቅ ችያለሁ፡፡
ባለፉት 6 ዓመታት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ አብሬው ስሰራ ስራውን እንዴት እንደሚወድ ከባልደረቦቹ ጋር እንዴት እንደሚግባባ ተረድቻለሁ፡፡
መንጌ በተለይ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በበርካታ ተደራራቢ ህመሞች ጫና ውስጥ ሆኖ እንኳን ከስራውና ከስራ ቦታው ላለመለየት ከህመሙ እየታገለ ወደ ቢሮ ስራውን ይዞ ብቅ ሲል በአንድ በኩል ስናዬው ደስ ሲለን በሌላ በኩል ከህመሙ ጋር የሚገጥመውን ትግል ከፊቱ ላይ ማንበብ በእጅጉ ያሳቅቀን ነበር፡፡
አንድ ቀን መንጌ ለምን እረፍት አታደርግም ለምንስ እያመመህ ትመጣለህ? ስል ጠየቅኩት ‹‹ለበሽታማ እጅ አልሰጥም ደሞም ተኝቶ ህመም ከማዳመጥ መንቀሳቀስ ይሻላል አሁን እኮ ደህና ነኝ›› አለኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ለምን ትመጣለህ ብዬው አላውቅም ጠፋ ካለ ግን አያስችለኝም ስልክ እደውላለሁ፡፡ ደህንነቱን ይነግረኛል:: መንጌ አንጋፋ ቢሆንም አብዛኞቹ ወዳጆቹና ጓደኞቹ ወጣቶች ናቸው፡፡ ምክንያቱም መንጌ የወጣት ነፍስ ነው ያለው፡፡ መታመሙን ሲሰሙ ገንዘብ ካልሰበሰብን ካልረዳነው ያሉት ብዙዎች ናቸው ግን እሱ በዚህ ጉዳይ አይደራደርም አይደረግም አለ፡፡ ሁለት የጋራ ጓደኞቻችን በእኔ በኩል ገንዘብ ልከው ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም፡፡
ከአንድ ባልደረባዬ ጋር እግሩ ላይ ወድቀን ስንሰጠው እንኳን ደስተኛ አልነበረም ሁሌም በራስ መተማመኑ ለስራው ያለው ፍቅር እኔን ያበረታኝ ነበር፡፡ አንድ ቀን ክፉ ሲወጣው፣ ሲጨቃጨቅ ሰምቼው የማላውቀው መንጌ ከነደግነቱ ከነክብሩ እና ከነኩራቱ ነው የተለዬን:: የሰማይ አምላክ ነፍሱን በደጋጎች ጎን ያሳርፈው መቼም አንረሳውም፡፡ በዚህ አጋጣሚ በርካታ ጓደኞቹ ጋዜጠኞች መንጌን ለመሰናበትና ፍቅርና አክብሮታችሁን ለመግለጽ ከስራ ሰዓታችሁ ቀንሳችሁ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ስለተገኛችሁ አክብሮቴን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ፡፡  
ናፍቆት ዮሴፍ (ጋዜጠኛ)

      የአለማችን ስደተኞች ቁጥር 272 ሚሊዮን ደርሷል

               በመላው አለም የስደት ህይወትን በመግፋት ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር 272 ሚሊዮን መድረሱንና ይህም ከአጠቃላዩ የአለም ህዝብ 3.5 በመቶ ያህሉ ስደተኛ መሆኑን እንደሚያመለክት አለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ከትናንት በስቲያ ባወጣው አመታዊ ሪፖርቱ እንዳለው፤ በርካታ ዜጎቿ የተሰደዱባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ህንድ ስትሆን፣ 17.5 ሚሊዮን ህንዳውያን የስደት ኑሮን በመግፋት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሜክሲኮ በ11.8 ሚሊዮን ስደተኛ ዜጎች በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ 10.7 ሚሊዮን ዜጎች የተሰደዱባት ቻይና በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትቀመጥ አመልክቷል፡፡
በመላው አለም ከሚገኙ 272 ሚሊዮን ስደተኞች መካከል 52 በመቶው ወንዶች መሆናቸውን የጠቆመው አለማቀፉ ሪፖርት፤ የአለማችን ስደተኛ ህጻናት ቁጥርም ከ31 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ይፋ አድርጓል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሌሎች አገራት ስደተኞች የሚገኙባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር አሜሪካ መሆኗንና በአገሪቱ 50.7 ሚሊዮን ያህል አለማቀፍ ስደተኞች እንደሚገኙም ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡ በ2018 ስደተኞች ወደ አገራቸው የላኩት ገንዘብ 689 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ህንድ 78.6 ቢሊዮን ዶላር፣ ቻይና 66.4 ቢሊዮን ዶላር፣ ሜክሲኮ 35.7 ቢሊዮን ዶላር ከስደተኞች የተላከላቸው የአለማችን ቀዳሚዎቹ ሶስት አገራት እንደሆኑ አመልክቷል፡፡

    በታንዛኒያ ባለፈው እሁድ በተከናወነው አገራዊ ምርጫ፣ ገዢው ፓርቲ 99.9 በመቶ ድምጽ አግኝቶ ማሸነፉን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፣ እንግሊዝና አሜሪካ ምርጫውን መቃወማቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የሁለቱ አገራት አምባሳደሮች ባለፈው ማክሰኞ ባወጡት መግለጫ፤ በታንዛኒያ ስምንት ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባልተሳተፉበት ሁኔታ የተካሄደውና መንበረ ስልጣኑን የተቆጣጠረው ቻማ ቻ ማፒንዱዚ ፓርቲ፣ 99.9 በመቶ ማሸነፉን ያወጀበት ምርጫ ተቃዋሚዎችን ያገለለ፣ ታዛቢዎች እንዳይሰማሩ የተደረጉበትና ብዙ ጉድለቶች የነበሩበት መሆኑ የምርጫውን ውጤት ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል ሲሉ መተቸታቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በምርጫው ለመወዳደር በዕጩነት ከቀረቡት የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወዳዳሪዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት፣ በቅድመ ምርጫ ሰነዶች ላይ የቃላት ግድፈት ፈጽመዋል በሚሉና ሌሎች ተልካሻ ምክንያቶች በምርጫ ቦርድ ከእጩነት መባረራቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ይህም የምርጫውን ውጤት ጥያቄ ውስጥ እንደከተተው ጠቁሟል፡፡

  የአለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ጄፍ ቤዞስ በአሜሪካ ውስጥ ለሚገኙ መኖሪያ ቤት የሌላቸው ዜጎች መርጃ የሚውል 98.5 ሚሊዮን ዶላር መለገሳቸውን ፎርብስ መጽሄት ዘግቧል፡፡የአማዞኑ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ጄፍ ቤዞስ፣ በ23 የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ ለሚኖሩ ቤት አልባ ዜጎች መኖሪያ ቤት ለሚሰሩ ድርጅቶች ገንዘቡን መለገሳቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ግለሰቡ ባለፈው አመትም ለተመሳሳይ አላማ 97.5 ሚሊዮን ዶላር በስጦታ ማበርከታቸውን አስታውሷል፡፡


Page 11 of 465