Administrator

Administrator

የትጥቅ ትግል ተፋላሚዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በምክክሩ ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችል አቅም እንዳለው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) ባለፈው ረቡዕ ሐምሌ 10 ቀን 2016 ዓ.ም በጽሕፈት ቤታቸው ከሌሎች ኮሚሽነሮች ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ለተፋላሚዎቹ አስቻይ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ መንግስትንና ሌሎች አካላትን ኮሚሽኑ እየጠየቀ መሆኑን ተናግረዋል።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በመጪው ሳምንት በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪና በድሬዳዋ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት እንደሚጀምር የገለፁት ዋና ኮሚሽነሩ፤  ስራውን ለማስተባበር የኮሚሽኑ ሞያተኞችና ኮሚሽነሮች ወደ አካባቢዎቹ ስምሪት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ስራውን ለመጀመር ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጋር በተገናኘ፣ ቀሪ ስራዎች እስከሚጠናቀቁ እየተጠባበቀ መሆኑም ተጠቁሟል።
አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱ በአብዛኛዎቹ ክልሎች እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ በአፋር ክልል ወቅታዊ የአየር ሁኔታ ከባድ ሙቀት ያለበት በመሆኑ፣ በክልሉ የሚከናወነው አጀንዳ ማሰባሰብ ጥቅምት ወር ግድም እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ ተፋላሚዎች በአገራዊ ምክክር ሂደቱ የመሳተፍ ፍላጎት ካላቸው፣ ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲሳተፉ የማድረግ አቅም እንዳለው ኮሚሽኑ በመግለጫው አመልክቷል፡፡
“ይህ የምክክር ሂደት ክርክር አይደለም፤ ሁላችንም አሸናፊ የምንሆንበት ሂደት ነው” ያሉት መስፍን (ፕ/ር)፤ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ካሉበት ሆነው ለኮሚሽኑ አጀንዳ መላክ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
መግለጫውን የሰጡት ሌላው የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር መሐመድ ድሪር፣ ለስራ በተንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች በሂደቱ ላይ ያለመሳካት ጥርጣሬ አለመነሳቱን አውስተው፣ “በሕዝቡ ዘንድ የመሸማቀቅና ጥያቄ ያለማቅረብ ሁኔታ እስካሁን አልታየም” ብለዋል። ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም፣ “ምክክር አሁን በስልጣን ላይ ካለው መንግስት ጋር የሚያያዝ አይደለም፤ ሂደቱ ለአገሪቱ ያስፈልጋታል፤ ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ መንግስት ኮሚሽን አይደለም።” ሲሉ ተናግረዋል። አያይዘውም፣ “የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ የመንግስት ሃሳብ ነው። ነገር ግን የእኛን አካሄድ ይዘውረዋል ማለት አይደለም” በማለት አስረድተዋል።
“የአማራና የትግራይ ክልሎች ቀርተው ምክክር ተካሄደ ቢባል ቀልድ ነው” ያሉት ኮሚሽነር መላኩ፣ “መንግስትን እንደባለድርሻ አካል ነው የምንቆጥረው” ብለዋል።
“በትግራይ የተለየ ዕንቅፋት አልገጠመንም። ከፕሪቶሪያ ስምምነት ጋር የተያያዙ የሚቀሩ የቴክኒክ ስራዎች ስላሉ ነው። ስራዎቹ ሲጠናቀቁ፣ ሂደቱ ይጀምራል” ሲሉ ያብራሩት ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ “የግድ ሁሉም አንድ ላይ እስኪሆኑ መጠበቅ ላያስፈልግ ይችላል” ብለዋል።
በአገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ቅሬታቸውን በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ ከቆዩ የሃይማኖት ተቋማት ጋር ኮሚሽኑ ምን እየሰራ እንደሆነ ከአዲስ አድማስ  የተጠየቁት ለኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ  ተናግረዋል። “ከሃይማኖት ተቋማቱ ጋር ውይይት ተደርጎ ችግሩ ተፈትቷል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ወደ ስራ ከገባ፣ ሁለት ዓመታትን ማስቆጠሩ የሚታወቅ ነው።

አብሮ አደግ በፍቅር የመረዳጃ ማሕበር ያዘጋጀው የዕውቁ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ የተዘከረበት መርሃ ግብር ዛሬ በተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል። በዚህ መርሃ ግብር የገነነ ስራዎች እና ሕይወት በዝርዝር መዘከሩ ተነግሯል።

መርሃ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የማሕበሩ ሰብሳቢ አቶ ቤዛው ሹምዬ ማሕበሩ ባለፉት አስር ዓመታት ስላደረጋቸው ዕንቅስቃሴ አትተዋል። አክለውም "ያለፉትን በመዘከር፣ የሰሩትን በማክበር ተተኪዎችን እንፍጠር!" በሚል መሪ ቃል ስለተዘጋጀው ይህ መርሃ ግብር በዝርዝር አብራርተዋል።

የገነነ መኩሪያ የሕይወት ታሪክ በንባብ የቀረበ ሲሆን፣ በሕይወት ዘመኑ ያበረከታቸው የተለያዩ ስራዎች በመታሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ ተዘክረዋል። ከገነነ መኩሪያ "ኢሕአፓ እና ስፖርት" መጽሐፍ የተቀነጨበ ስራ ለዕድምተኞች በትረካ ቀርቧል።

በተጨማሪም፣ ለቀድሞ የእግርኳስ ተጨዋቾች ተካ ገለታ፣ ግርማ አበበ፣ እና ጌቱ መልካ፤ ለቀድሞ ቦክሰኛ ደረጀ ደሱ እና ለድምጻውያኑ ጎሳዬ ተስፋዬ እና አብዱ ኪያር፣ ለሁለገቡ የኪነ ጥበብ ሰው ዳዊት አፈወርቅ፣ ለተዋናይ ተሰማ ገለቱ፣ ለኬሮግራፈር ዳንኤል ደሳለኝ፣ ለጋዜጠኛ እንግዱ ወልዴ እና ለሕግ ባለሞያዋ ሰናይት ፍስሐ (ፕ/ር) ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ እና የገነነ መኩሪያ ባለቤት ወይዘሮ አስቴር አየለ ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመርሃ ግብሩ ላይ ታድመዋል።

አብሮ አደግ በፍቅር የመረዳጃ ማሕበር የተመሰረተበትን አስረኛ ዓመት በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ተከብሯል።

ከ15 ሚሊዮን በላይ ታዳሚዎች ያገኛል
ኢትዮጵያ 3 ወርቅ፣ 5 ብርና ነሀስ- Nielsen
ኢትዮጵያ የወርቅ፣ 5 ብርና 5 ነሐስ- Athletics weakly
ባለፉት 32 ኦሎምፒያኖች ከኢትዮጵያ 282 ኦሎምፒያኖች (208 ወንድና 74 ሴት) ተሳትፈዋል 58 ሜዳልያዎች (23 የወርቅ፣ 12 የብርና 23 የነሐስ) ተገኝተዋል

 

ወጭ 9.5 ቢሊዮን ዩሮ ገቢ 5.3 ቢሊዮን ዩሮ
በፓሪስ ለሚካሄደው 33ኛው ኦሎምፒያድ ሁለት ሳምንታት ቀርተዋል፡፡ በ32 አይነት ስፖርቶች 329 የኦሎምፒክ ውድድሮች ይደረጋሉ። ከ10,672 ኦሎምፒያኖች 206 አገራትን በመወከል ይሳተፋሉ።
ፈረንሳይ ለኦሎምፒክ መስተንግዶ በአጠቃላይ ያወጣችው በጀት ከ9.5 ቢሊዮን ዩሮ አልፏል። ከበጀቱ 96 በመቶው በግሉ ሱክተር ተሸንፏል።
ዓለምዓቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ አጋር ኩባንያዎች የኦሎምፒክ የት/ቤትና የፈቃድ ቢሮ ናቸው። ግሪክ በ2004 አቴንስ ላይ 9.1 ቢሊዮን ዩሮ ፤ ጃፓን በ2022 ቶኪዮ ላይ 12.9 ቢሊዮን ዩሮ እንዲሁም እንግሊዝ በ2012 እ.ኤ አ ለንደን ላይ 15 ቢሊዮን ዩሮ ለኦሎምፒክ መስተንግዷቸው አውጥተዋል፡፡
የኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴው 4.3 ቢሊዮን ዩሮ ወጪ ሲያደርግ ዓለምአቀፍ ኦሎምፒክ ኦሎምፒክ ኮሚቴ 1.2 ቢሊዮን ዩሮ (750 ሚሊዮን ዩሮ ከቲቪ መብት፤ 470 ሚሊዮን ዩሮ ከዋና አጋሮች) መድቧል። CDES የተባለ ተቋም ባዘጋጀው የኢኮኖሚ ትንታኔ ፈረንሳይ ከኦሎምፒኩ ቢያንስ እስከ 5.3 ቢሊዮን ዩሮ ገቢ እንደምታገኝ ይጠበቃል፡፡ ከመስተንግዶው ጋር በተለያየ መንገድ የሰሩ ከ80 በላይ ኩባንያዎችም እስከ 3 ቢሊየን ዩሮ ገቢ እንደሚኖራቸው ገምቷል።
ከ15 ሚሊዮን በላይ የኦሎምፒክ ታዳሚዎች በፓሪስ እንደሚገኙ የተጠበቀ ሲሆን ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ከተለያዩ የዓለም አገራት የሚመጡ ናቸው ተብሏል።
አዘጋጅ ኮሚቴው ከ10 ሚሊዮን ትኬቶች መሸጣቸውንም አረጋግጧል።
የNielsen Gracenote ትንበያ
ኦሎምፒኩ 1 ወር ሲቀረው በዓም 55 አገራት የሚንቀሳቀሰው Neilsen የተባለ የሚዲያ ተቋም የሜዳሊያ ትንቢያውን Gracenole virtual medal table በሚል ይፋ አድርጓል። የሜዳልያ ሰንጠረዡን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ግምት ያገኙት አገራት አሜሪካ፣ ቻይና፣ ግሬት ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ናቸው፡፡
ባለፉት 8 ኦሎምፒያዶች በመሪነት የጨረሰችው አሜሪካ በድምሩ 123 ሜዳሊያዎች በመሰብሰብ አንደኛ እንደምትሆን ሲተነበይ፤ ቻይና በ87 ፣ ግሬት ብሪቴን በ62 ፣ ፈረንሳይ በ56 እንዲሁም አውስትሪሊያ በ48 ሜዳልያዎች እስከ 5ኛ ያለውን ደረጃ እንደሚያገኙ ተገምቷል፡፡
በኦሎምፒክ ሻምፒዮኖች ብዛት ደግሞ አሜሪካ በ37 መሪነቱን እንደምትይዝ ሲጠቆም፣ ቻይና በ36 ፤ ፈረንሳይ በ29፣ ሆላንድ በ17 ግሌት ብሪቴን በ14 የወርቅ ሜዳልያዎች ተከታታይ ደረጃዎችን እንደሚያገኙ ተገምቷል፡፡

ኢትዮጵያ 3 ወርቅ፣ 5 ብርና 5 የነሐስ
Nielsen Gracenote
በNeillsen ትንበያ መሰረት ኢትዮጵያ ፓሪስ ላይ 3 የወርቅ ሜዳሊያዎችን እንደምታገኝ፤ ከአፍሪካ ትልቁን ውጤት እንደምታስመዘግብና ከዓለም 16ኛ ደረጃ እንደሚኖራት ነው የተገመተው፡፡
በግሬስኖት ትንቢያ መሰረት ኢትዮጵያ 3 የወርቅ፣ 5 የብርና 5 የነሐስ በድምሩ 13 ሜዳልያዎች እንደምታገኝ ሲተነበይ የቅርብ ተቀናቃኟ ኬንያ ደግሞ 3 የወርቅ፣ 3 የብርና 3 የነሐስ በድምሩ 9ሜዳሊያዎችን እንደምትሰበስብ ተጠብቋል ፡፡
በተያያዘ Total Olympics ድረገፅ በስለው ትንታኔ መሰረት ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሎምፒክ ተሳትፎ ጠንካራ ተፎካካሪ ትሆናለች። ከ2020-2024 ከማድረጓ በፊት በዓለም ሻምፒዮና እና ሌሎች ዓለም ዓቀፍ ውድድሮች 6 የወርቅ፣ 8 የብርና 5 የነሐስ ሜዳልያዎችን መሠብሰቧን አመልክቷል።
ኢትዮጵያ 1 ወርቅ፣ 5 ብር፣ 5 ነሀስ
Athletics weekly
ታዋቂው የአትሌትክስ መፅሔት AW (Athletics weekly) ለኢትዮጵያ ዝቅተኛ ግምት የሰጠ መስላል። ከ5 ወራት በፊት በአትሌቲክስ ስፖርቶች ላይ አተኩሮ ባሰራጨው የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች ትንበያና ትንታኔ ኢትዮጵያ -- 1 የወርቅ፣ 5 የብርና 5 የነሐስ ሜዳያዎችን እንደምትሰበስብ ገምቷል። በተጨማሪ በ4ኛ ደረጃ 5 የኦሎምፒክ ዲፕሎማዎችም ለማስመዝገብ እንደምትችል አመልክቷል።
በኦሎምፒኩ ላይ ኢትዮጵያ በመካከለኛ እና በረጅም ርቀት ወድድሮች ዋና ተፎካካሪ እንደምትሆን የመፅሄቱ ትንታኔ ቢገልፅም የወርቅ ሜዳልያ የምትወስደው በሴቶች ማራቶን ብቻ መሆኑን ነው የጠቀሰው። በፓሪስ 2024 ብቸኛው የወርቅ ሜዳሊያ ግምት የተሰጣት በሴቶች ማራቶን የዓለም ሪከርድ ባለቤቷ ትግስት አሰፋ ናት። 5 የብር ሜዳልያዎችን በሴቶች1500 ሜትር ፍሬወይኒ ሐይሉ ፣ በ5ሺ ሜትር ዮሚፍ ቀጀልቻ እና ጉዳፍ ጸጋይ፤ በ10ሺ ሜትር ሴቶች ጉዳፍ ፀጋይ እና በሴቶች ማራቶን አማኔ በሬሶ ያገኛሉ ብሏል በሀተታው፡፡ አምስቱን የነሐስ ሜዳሊያዎች ደግሞ በ1500 ሺ ሴቶች ብርቄ ሃይሎም፤ በ10ሺሜትር ለተሰንበት ግደይና ሰለሞን ባረጋ፣ በ5ሺ ሜትር ወንዶች በሪሁ አረጋዊና በወንዶች ማራቶን ሲሳይ ለማ እንደሚያገኟቸው ገምቷል።
በአትሌቲክስ ዊክሊ ትንታኔ መሠረት በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሜዳሊያ አደን ከባድ ተፎካካሪ ሆነው የሚጠቀሱት በሴቶች የኬንያዋ ፌዝ ኪፕዮገን ፤የሆላንዷ ሲፋን ሀሰን በወንዶች ደግሞ የኡጋንዳና የኬንያ አትሌቶች እንዲሁም የኖርዌዮ አትሌት ኢንግሪብስተን ናቸው፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ለወርቅ ሜዳሊያ 50 ሺ ዶላር
ሲንጋፖር 737 ሺ ዶላር ጣሊያን
201 ሺ ዶላር አሜሪካ 37 ሺ ዶላር
በፓሪስ 2024 ላይ በኦሎምፒክ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለወርቅ ሜዳልያ አሸናፊዎች የሚሰጥ በዓለም አትሌቲክስ ማህበር 2.4 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ሽልማት ተዘጋጅቷል ፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በአትሌቲክስ ውድድሮች የወርቅ ሜዳልያ የሚያገኙት አትሌቶች 50 ሺ ዶላር እንደሚሸለሙ አስታውቋል
በነገራችን ላይ በኦሎምፒክ መድረክ የሜዳልያ ውጤት ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች የተለያዩ አገራት የገንዘብ ሽልማቶችን በቦነስ መልክ በማቅረብ ይሰራሉ።
ታዋቂው ፎርብስ መፅሄት በሰራው ዘገባ ከ4 ዓመት በፊት በቶኪዮ ኦሎምፒክ ለወርቅ ሜዳሊያ ሲንጋፑር 737ሺ ዶላር በመሥጠት ግንባር ቀደም ስትሆን ጣሊያን 201ሺ ዶላር በመስጠት ተጠቅሰዋል።
አሜሪካ ለወርቅ 37,500 ዶላር፣ ለብር 22,500 ዶላር እዲሁም ለነሐስ 15ሺ ዶላር የገንዘብ ሽልማት እንደምታዘጋጅ የፎርብስ ትንታኔ አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እንዲሁም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚህ ረገድ ያስታወቁት ነገር የለም፡፡ የኦሎምፒክ ኮሚቴው በሚገኘው አትሌቶችና አሰልጣኞች በኦሎምፒክ የሚመዘገብ ውጤት ላይ በሚሰጥ የገንዘብ ሽልማት እኩል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስታውቋል፡፡ እንሰጣለን ኢትዮጵያ ባለፉት 32 ኦሎምፒያዶች
ባለፉት 129 ዓመታት ውስጥ በተካሄዱት 32 ኦሎምፒያዶች ኢትዮጵያ በ14 የተሳተፈች ሲሆን 33ኛው ኦሎምፒያድ ለ15ኛ ጌዜ የምትካፈልበት ይሆናል። በኦሎምፒክ መድረክ ሁሉንም ሜዳልያዎችን የሰበሰበችው በአትሌቲክስ ስፖርት ብቻ ሲሆን በከፍተኛ የውጤት ታሪካቸው ከሚጠቀሱ 8 አገራት አንዷ ናት። አፍሪካን በመወከል ደግሞ ከኬንያ ቀጥሎ ከፍተኛውን ስኬት አስመዝግባለች፡፡
በፓሪስ ፈረንሳይ ከሚስተናግደው 33ኛው ኦሎምፒያድ በፊት ኢትዮጵያ በተካፈለችባቸው 14 ኦሎምፒያዶች 282 ኦሎምፒያኖች (208 ወንድ እና 74 ሴት) ተሳትፈዋል፡፡ ከእነሱም መካከል 36 ኦሎምፒያኖች ከ1 እስከ 3 ባሉ ደረጃዎች ስኬታማ በመሆን 58 ሜዳልያዎችን (23 የወርቅ፤ 12 የብርና 23 የነሐስ) ለኢትዮጵያ አስገኝተዋል፡፡ ከሜዳልያዎቹ ስብስብ 23 የወርቅ ሜዳልያዎችን ለኢትዮጵያ ያጎናፀፉት 14 ናቸው፡፡ በተረፈ 11 የብር ሜዳልያዎች በ12 እንዲሁም 23 የነሐስ ሜዳልያዎች በ20 የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች ተገኝተዋል፡፡
በቦክስ ስፖርት በ8 ኦሎምፒያዶች 28 ኦሎምፒያኖች (28 ወንድ )፤ በብስክሌት በ9 ኦሎምፒያዶች 31 ኦሎምፒያኖች (30 ወንድ 1 ሴት)፤ በውሃ ዋና በ3 ኦሎምፒያዶች 5 ኦሎምፒያኖች (3 ወንድ 2 ሴት) እንዲሁም በቴኳንዶ በ1 ኦሎምፒያድ (1 ወንድ) ተሳትፈዋል።
*****************

የኢትዮጵያ ቡድን
ፓሪስ 2024 ላይ በአትሌቲክስ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮኖች፤ የዓለም ሪከርድ ባለቤቶች፤ አንጋፋና ወጣት ኦሎምፒያኖች የተሰባሰቡበት ነው። የቡድኑ ሙሉ ዝርዝር ከዚህ በታች የቀረበው ነው።
800 ሜትር ሴቶች
ፅጌ ድጉማ፣ ሐብታም ዓለሙ፣ ወርቅነሽ መለሰ፤ ንግስት ጌታቸው (ተጠባባቂ)
1500 ሜትር በወንዶች -
አብዲሳ ፈይሳ፣ ሳሙኤል ተፈራ፣ ኤርሚያስ ግርማ፣ ታደሰ ለሚ (ተጠባባቂ)
1500 ሜትር ሴቶች
ጉዳፍ ፀጋዬ፣ ብርቄ ሃየሎም፣ ድርቤ ወልተጂ፤ ሂሩት መሸሻ (ተጠባባቂ)
5ሺህ ሜትር ወንዶች
ሀጎስ ገ/ህይወት፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ አዲሱ ይሁኔ፤ ሰለሞን ባረጋ (ተጠባባቂ)
5ሺህ ሜትር ሴቶች
ጉዳፍ ፀጋዬ፣ መዲና ኢሳ፣ እጅጋየሁ ታዬ፤ ፍሬወይኒ ኃይሉ (ተጠባባቂ)
10 ሺህ ሜትር ወንዶች
ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ በሪሁ አረጋዊ፣ ሰለሞን በረጋ፤ ቢኒያም መሀሪ (ተጠባባቂ)
10 ሺህ ሜትር ሴቶች
ጉዳፍ ፀጋዬ፣ ፎቴን ተስፋዬ፣ ፅጌ ገ/ሰላማ፣ አይናዲስ መብራቱ (ተጠባባቂ)
3ሺህ ሜትር መሠናክል ወንዶች
ለሜቻ ግርማ፣ ሳሙኤል ተፈራ፣ ጌትነት ዋለ፤ አብርሃም ስሜ (ተጠባባቂ)
3ሺህ ሜትር መሠናክል ሴቶች
ሲምቦ ዓለማየሁ፣ ሎሚ ሙለታ፤
በማራቶን ሴቶች
ትዕግስት አሰፋ፣ አማኔ በሪሶ፣ መገርቱ ዓለሙ፤ ጎይቶቶም ገ/ስላሴ (ተጠባባቂ)
በማራቶን ወንዶች
ቀነኒሳ በቀለ ፣ ሲሳይ ለማ፣ ዴሬሳ ገለታ፤ ታምራት ቶላ (ተጠባባቂ)
በ20 ኪሎ ሜትር ርምጃ ወንዶች
ምስጋና ዋቁማ

 

ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ሲተክሉ ነው ያገኘናቸው - የስሪላንካ አምባሳደር ቴሻንታ ኩማራሲሪ። ፍላጎታቸው ግን ችግኝ ለመትከል ብቻ አይደለም። “አረንጓዴ አሻራ እንዴት እየሄደ ነው? ምን ዐይነት ትምህርትና ልምድ እናገኝበታለን?” በማለት በቅርበት እንደሚከታተሉት ነግረውናል። አረንጓዴ አሻራ የኢኮኖሚ ጥቅም እንዲኖረው አድርጋችኋል፤ በርካታ አገራት ከኢትዮጵያ ልምድ እንደሚቀስሙ አምናለሁ ብለዋል - አምባሳደሩ።
አረንጓዴ አሻራ የሁላችንም ሥራ የሁላችንም አሻራ ነው በሚል የባለቤትነት መንፈስ ያነጋገረን ደግሞ አሸናፊ ወርቁ (አሸበል) ነው። ከቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለብ ነው የመጣነው፤ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ እየተከልን ነው ብሎናል። ሐሳባቸው ግን ከዚህም በላይ ነው። ዓመቱን ሙሉ የሚንከባከቡትና የሚያለሙት ቦታ እንዲኖር ይፈልጋሉ። እናም፣ ከመንግሥት የምንፈልገው “እዚህ ጋር ትከሉ ብሎ ቦታ እንዲሰጠን ብቻ ነው” ይላል - አሸበል።
አረንጓዴ አሻራ የፖለቲካ ሽታ እንደሌለውና ሊኖረው እንደማይገባ የገለጹልን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለስ ምን ይላሉ? አረንጓዴ አሻራ ከፖለቲካ በላይ እንደሆነ ሲገልጹ፣ ትውልድን የማኖር አገርን የማጽናት ጉዳይ ነው ብለዋል ጠቅላይ ጸሐፊው። አረንጓዴ ዕፅዋት የፈጣሪ ጸጋ ነው፤ ሀብትም ውበትም ነው። ሰዎች ጥበብ ጎድሏቸው አረንጓዴ ጸጋ አጥተዋል። እናም… ይህን ለመመለስና ትውልድን ለማዳን የሃይማኖት ተቋማት በአረንጓዴ አሻራ ላይ አርአያነታቸውን እንደሚያሳዩ ተናግረዋል - ጠቅላይ ጸሐፊው።
አረንጓዴ አሻራ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያቅፋል። አረንጓዴ አሻራ ምግብም ውበትም ነው። ይሄ፣ የከንቲባ አዳነች አቤቤ አገላለጽ ነው። የከተማችን ነዋሪዎች የፆታ፣ የእድሜ፣ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድባቸው ሀገር በቀል ዛፎችን፣ የውበት ዕፅዋትን፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ችግኞች በጋራ እየተከሉ እንደሆነ ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ታሪክ… ለዓለምም ለአገርም ነው። “አካባቢ ተራቆተ” እየተባለ በዓለም ዙሪያ ለበርካታ ዓመታት ተወርቷል። ዓለማቀፍ ስብሰባዎች በብዛት ተካሂደዋል። እልፍ የስምምነት ሰነዶች ተፈርመዋል። ነገር ግን፣ በጎ ለውጥ ሲያመጡ እንዳልታየ ጠ.ሚ. ዐብይ አህመድ ሲገልጹ፣ “በስብሰባ አይቀየርም፤ በሱፍ ለባሾች አይቀየርም” ብለዋል። ችግኝ የሚተክሉ እጆች ናቸው የችግር መፍትሔ የሚሆኑት። “ይህን ተግባር በመፈጸም ለዓለም ማስተማር ከኢትዮጵያ ይጠበቃል” ብለዋል - ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
አረንጓዴ አሻራ፣ እንደ ስሙ ልምላሜ ነው - አብቦ የሚያፈራ። ባለፉት አምስት ዓመታት በቢሊዮን የሚቆጠሩ የፍራፍሬ ችግኞች ተተክለዋል። አረንጓዴ አሻራ ፍሬያማ ነው። ግን ለዛሬ ብቻ አይደለም። ለትውልድ ይተርፋል። ለኑሮ ብቻ ሳይሆን ለታሪክም ነው። ከነስሙ “አሻራ” ተብሎ የለ!

 

ለዘመናት የተራቆተውን የአገር ገጽታ የሚቀይር፣ ኢትዮጵያን የሚያለመልም፣ ዘመን ተሻጋሪ ትልቅ የጥበብ ሥራ ስለሆነም፣ “ታሪካዊ” የሚል ማዕረግ አይበዛበትም።
እንደማንኛውም ትልቅ ቁምነገር፣ እንደማንኛውም ታሪካዊ ሥራ፣ አረንጓዴ አሻራ “አቃፊ” ባህርይ አለው።
የአረንጓዴ አሻራ ትርጉም፣ የተራቆተውን አገር የልምላሜ ግርማ ማጎናጸፍ ብቻ አይደለም። አዎ፣ አረንጓዴ አልብሶ ያስውባል። ሲታይ ያምራል። ነገር ግን፣ ጣዕምም ምቾትም ጭምር አለው። እንዴት ቢሉ…
ከውጭ አገር፣ ፍራፍሬ፣ የእንጨት ቁሳቁስና የሥጋ ምግቦችን እንደ ብርቅ ነገር ማስመጣት ለኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ አስቡት። የመራቆት ዕዳ እዚህ ድረስ ነው። የእንጨት ቁሳቁስ ለኢትዮጵያ ብርቅ መሆን ነበረበት? ፍራፍሬስ? ማርና ወተትስ? ብርቅ መሆን አልነበረበትም።
ኢትዮጵያ የፍራፍሬ አገር መሆን ነበረባት። መሆንም አለባት። ንቦች የሚቀስሙት አበባ፣ ላሞች የሚጥግቡበት ሳርና ሰብል፣ ለእንስሳት ሁሉ ተስማሚ መኖ እንደ ልብ የምታበቅል ለምለም አገር መሆን አለባት። በሙያተኞች ታሪክ የምትጠቀስ ኢትዮጵያን የመሰለች የጥበብ አገር፣ የእንጨት ቁሳቁስን ብርቅ ሊሆንባት፣ ተቸግራ ከውጭ አገራት ልታስመጣ አይገባም ነበር። ይሄ የዝቅታ ታሪክ መቀየር አለበት - በአረንጓዴ አሻራ።
ይህም ብቻ አይደለም። ተራራውና ሸለቆው ዛፎች ሲበቅሉበትና አረንጓዴ ሲለብስ፣ ለም አፈር እየተሸረሸረ ተቦረቦረ የኢትዮጵያ መሬት አይራቆትም። በደለል ብዛት ሐይቆችና ግድቦች ውኃ አይሸሻቸውም።
አረንጓዴ አሻራ፣ አገርን ልምላሜ ከማልበስ ባሻገር፣ የማርና የወተት ጉዳይም ነው። የፍራፍሬና የሥጋ፣ የእንጨት ሙያንና የኤሌክትሪክ ብርሃንን ሁሉ ያቅፋል - አረንጓዴ አሻራ።
“ሀብትም ውበትም ነው” የተባለው አለምክንያት አይደለም። ሲያዩት ያምራል። መዓዛው ይማርካል። ግን ደግሞ የኑሮ ጣዕምም ነው። ሲቀምሱት ሲገምጡት ይጣፍጣል። ሲመገቡት ያጠግባል። “ለምግብነትም ለውበትም” በማለት ይገልጹታል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
በአገር ደረጃ እንደታየው በአዲስ አበባም የተተከሉ ችግኞችም ከዓመት ዓመት ቁጥራቸው እየጨመረ ነው። በመጀመሪያዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ 41 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል።
ዓምና 17.5 ሚሊዮን ችግኞች።
ዘንድሮ ደግሞ 20 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከት የዓመቱ አረንጓዴ አሻራ ባለፈው ቅዳሜ “ሀ” ተብሎ ተጀምሯል።
ገሚሶቹ የአትክልትና የፍራፍሬ ችግኞች ናቸው። ገሚሶቹ አገር በቀል የደን ዛፎች ናቸው። ገሚሶቹ ደግሞ የውበት ዕፅዋት። አረንጓዴ አሻራ ሁሉንም ያቀፈ አገራዊ ፕሮጀክት ነው - የሀብትና የውበት ፕሮጀክት። ለኑሮም ለመንፈስም ነው።
ይህም ብቻ አይደለም። በልዩነቶች የታጠረ አይደለም። ሁሉንም የሚያቅፍ እንጂ።
የእገሌ ፓርቲ ችግኝ… የእከሌ ፓርቲ ችግኝ የሚል ልዩነት የለም። ችግኞች የፖርቲ አርማ ለብሰው አይጸድቁም። የዚህኛውም የዚያኛውም ችግኞች በአረንጓዴ ልምላሜያቸው አገርን ያሳምራሉ። አብበው ያፈራሉ።
በጾታ፣ በብሔር፣ በሃይማኖት ልዩነቶች የተገደበ አይደለም። አንተ፣ እሷ፣ እኔ … ሁላችንም የምንተክላቸው ችግኞች በሙሉ፣ “አረንጓዴ አሻራ” ናቸው።
ያለ ልዩነት ሁሉን የሚያሰባስቡና የሚያቀራርቡ፣ እንደ አረንጓዴ አሻራ የመሳሰሉ “አቃፊ” ቁምነገሮችና ሥራዎች እንዲበዙልን አትመኙም? ካሰብንበትና ከተጋንበት ደግሞ፣ ምኞት ብቻ ሆኖ አይቀርም። አይከብደንም። ከአረንጓዴ አሻራ ጥሩ ልምድ አግኝተንበታልና።
የአረንጓዴ አሻራ የበረከት ምሥጢር ብዙ ነው።
ከላይ እንደተጠቀሰው፣ በዓለም ዙሪያ “የአካባቢ መራቆጥ፣ የአየር ንብረት ለውጥና የዓለም ሙቀት”… እየተባለ በብዙ ስብሰባዎች ብዙ ተወርቷል። እልፍ መግለጫዎች ከግራ ቀኝ እየተቀባበሉ ይስተጋባሉ። የተፈረሙ የስምምነት ውሎችና ሰነዶችም ለቁጥር ያስቸግራሉ።
ኢትዮጵያ የዓለማችን አካል፣ ለዚያውም ከትልልቅ አገሮች መካከል አንዷ ናትና፣ ይሄ ሁሉ ኢትዮጵያን ይመለከታል። ጉዳይዋ ነው። ነገር ግን፣ ኢትዮጵያ ራሷን የቻለች ኩሩ ታሪካዊ አገርም ናት። ከአገራት ጋር የምትተባበር፣ ትምህርት የምትለዋወጥ ብትሆንም፣ በየአህጉሩና በየአገሩ የሚስተጋቡ አጀንዳዎችን በደረቁ ሊያጎርሷት ሊግቷት ቢሞክሩ፣ እሺ አትልም። በደመነፍስ “ኮፒ” እያደረገች፣ በጭፍን አትከተልም። ተነጂ አትሆንም።
ፍሬና ገለባውን ለይታ፣ የሚሆነውንና የሚበጃትን ለክታ፣ የራሷን መንገድ እየቀየሰች ትጓዛለች። ለአገርና ለሕዝብ፣ ለኑሮና ለታሪክ ትርጉም ባለው መንገድ እያገናዘበች የራሷን ቁምነገር ልብ ትላለች። የራሷን አጀንዳ ትቀርጻለች።
በርካታ አገራት “የአካባቢ መራቆትን እንከላከላለን” በማለት ኢኮኖሚያቸውን ሲያቃውሱ አይተናል። ኢትዮጵያ ግን፣ ኢኮኖሚን የማሳደግና ኑሮን የማሻሻል ራዕይን ጭምር የሚያቅፍ አረንጓዴ አሻራዋን ለዓለም እያሳየች ነው። እንዲህ ዐይነት “ዐቃፊ” የጥበብ ትጋትም ነው፤ ለሌሎች ጥሩ ትምህርትና ልምድ የሚወጣው።
የባለቤትነት መንፈስ መፍጠርስ?
ቀሲስ ታጋይ እንደሚሉት፣ የሃይማኖት ተቋማት በአረንጓዴ አሻራ መልካም አርአያነትን የማሳየት ኀላፊነት አለብን ብለው በጋራ ወስነዋል። በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ችግኞችን በብዛት ለመትከልና ለማልማት ቃል ገብተው፣ በተግባር እያሳዩ እንደሆነም ተነግሯል።
የስሪላንካው አምባሳደር በበኩላቸው፣ አረንጓዴ አሻራ በትልልቅ ቁጥሮች ተዘርዝረው የሚቀርቡ ብዙ ስኬቶችን የማስመዝገቡ ያህል፣ በቁጥር የማይገለጹ ስኬቶችንም አስገኝቷል ብለዋል። በአረንጓዴ አሻራ ውስጥ ብዙ ወጣቶችና ታዳጊ ልጆች ሲሳተፉ አይቻለሁ። ይህም የአዲሱን ትውልድ መንፈስ የሚያነሳሳና የሚያነቃቃ ነው ብለዋል - አምባሳደሩ። አረንጓዴ አሻራን በባለቤትነት ይዞ የሚያሳድግ ትውልድ ተፈጥሯል ማለት ነው።
ከቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለብ ባልደረቦቹ ጋር በየዓመቱ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ከመትከል ባሻገር፣ በባለቤትነት መንፈስ የሚያለሙት ፓርክ ላይም ችግኞችን እየተከልን እንንከባከባለን ሲል ነግሮናል። በባለቤትነት መንፈስ እየሠሩ ያስመዘገቡት ውጤት ታይቶም እንደሽልማት ሌላ የሚለማ ቦታ በአዲስ አበባ መስተዳደር እንደተፈቀደላቸው አሼበል ይገልጻል። በእርግጥ ቦታውን ገና አልተረከቡም። እናም ከመንግሥት የምትፈልጉት ድጋፍ ምን እንደሆነ ስንጠይቀው፣ “እዚህ ችግኝ ትከሉ ብሎ ቦታ እንዲሰጠን ብቻ ነው የምንፈልገው” በማለት መልሶልናል።
አረንጓዴ አሻራ የዚህን ያህል ነው ኢትዮጵያውያንን በሰፊው ማቀፍ የቻለው። ኢትዮጵያውያንም አረንጓዴ አሻራን የራሳቸው አድርገው አቅፈውታል።

በዋቢሸበሌ ሆቴል ሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም፤ ከቀኑ 11ሰዓት እስከ 2፡00 ሰዓት

 

አንዲት ምስኪን አሮጊት በአንድ መንደር ትኖር ነበር፡፡ አንድ ቀን ብዙ ባቄላ አግኝታ ልትቀቅል አሰበች፡፡ ምድጃዋ ላይ እሳት አያይዛ ቶሎ እንዲቀጣጠል የሰምበሌጥ ማገዶ ትጨምር ጀመር፡፡ ባቄላውን ማሰሮ ውስጥ እየከተተች ሳለች፣ አንድ ባቄላ ተፈናጥሮ መሬት ላይ ወደቀ፡፡ አጠገቡ አንድ ሰንበሌጥ አለ፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ አንድ ከሰል እንደዚሁ ከምድጃው ተፈናጥሮ ተንከባሎ ባቄላውንና ሰንበሌጡ አጠገብ አረፈ፡፡
ሰንበሌጡ፤ “ውድ ጓደኞቼ ከወዴት መጣችሁ?” አለና ጠየቀ- ከሰሉንና ባቄላውን፡፡
ከሰሉ፤ “እኔ ዕድለኛ በመሆኔ ከእሳቱ ተፈናጥሬ ወጣሁ፡፡ በጣም ብዙ ጥረት አድርጌ ነው የወጣሁት፡፡ ዕጣ ፈንታዬ ሞት ነበር፡፡ ይሄኔ አመድ ሆኜ ነበር” አለ፡፡
ባቄላው በተራው፤
“እኔም ቆዳዬ ሳይገሸለጥ ወጥቼ አመለጥኩ፡፡ ሆኖም አሮጊቷ እንሥራዋ ውስጥ ከትታኝ ቢሆን ኖሮ ይሄን እኔም እንደጓደኞቼ ተቀቅዬ ነበር” አለ።
ሰንበሌጡም፤
“እኔስ ከእናንተ የተለየ ሌላ ዕጣ- ፈንታ ይጠብቀኝ ነበር መስሏችኋል?” አለ፡፡ “አሮጊቷ የእኔን ወንድሞችና ጓደኞቼን በሙሉ እሳት ውስጥ ማግዳቸዋለች፡፡ ስልሳውን በአንድ ጊዜ እንደ ጨፈቃ አስራ ለሞት ዳረገቻቸው፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ ከእጇ አፈትልኬ እኔ ወደቅሁኝ፡፡”
ከሰል - “እሺ ታዲያ አሁን ምን እናድርግ ትላላችሁ?”
ይሄኔ ባቃላው - “ጎበዝ ሞትን የማምለጥ እድል ካገኘን ዘንድ እንደ ልብ ጓደኛሞች ሁሉ ወደ ሌላ አገር ሄደን ወደፊት ሊመጣብን የሚችለውን መዓት ማምለጥ አለብን”
ሁሉም በዚህ ሀሳብ ተስማሙ፡፡ ወደ ሌላ አገር ለመሄድም መንገድ ጀመሩ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን አንድ ትንሽ ወንዝ አጠገብ ደረሱ፡፡ ከወንዙ ወዲህ ማዶ ወደ ሌላኛው ዳርቻ ለማቋረጥ ምንም ድልድይ የለም፡፡ ይህን ችግር ለማቃለል ዘዴ ሲያወርዱ ሲያወጡ ሳለ፣ ሰንበሌጡ አንድ ደግ ሀሳብ አቀረበ፡፡ እንዲህ አለ፡-
እንዳውም ሰንበሌጡ ከዳርቻ ዳርቻ ተዘረጋ፡፡ ትዕግስት አልባውንና አሁንም በመቀጣጠል ላይ ያለው ከሰል በድፍረት ሰምበሌጡ ላይ ወጥቶ እየጨፈረና ዳንኪራ እየመታ፣ በአዲስ ድልድይ ላይ መጓዝ ጀመረ፡፡ ሆኖም እሰንበሌጡ ድልድይ መካከል ላይ ሲደርስ፤ ውሃው ገርገጭ ገርገጭ እያለ ሲጮህ ሲሰማ ወደፊት ለመጓዝ ድፍረት አጣ፡፡ ፈራ፡፡ በዚህ መካከል የከሰሉ እሳት የሰንበሌጡን አካል ለብልቦ ሁለት ላይ ከፈለው፡፡ ሰንበሌጢ በሁለት ተከፍሎ ወንዙ ውስጥ ገባ፡፡
እሱን ተከትሎ ከሰሉም ሰጠመ፡፡ የውሃውን ገላ ሲነካም ቸሰስ እያለ ጨሰ፡፡ የመጨረሻ እስትንፋሱም በዚያው ቆመች፡፡
ባቄላው ግን በተፈጥሮው ጠንቃቃ ነበረና ዳርቻው ላይ እንደቆመ ነበር፡፡ |የሆነውን ሲያይ ሳቁን ሊገታው አልቻም፡፡ ሳቁን ለቀቀው፡፡ መሬት ላይ እየተንከባለለ ሳቀ፡፡ ሳቀ…. በመጨረሻ ግን በሳቅ ብዛት ፈነዳና መሬት ላይ ተዘረረ፡፡ ትረፍ ሲለው አንድ መንገደኛ ልብስ ሰፊ ወንዙ ዳር አረፍ ብሎ ነበረና በባቄላው የደረሰውን አይቶ አዘነ፡፡ ጥቂት ቆይቶ ባቄላውን አንስቶ በጥቁር ክር ቆዳውን ሰፋና አዳነው፡፡ ባቄላው አመሰገነው፡፡ ሆኖም ልብስ -ሰፊው በጥቁር ክር ነበረና የሰፋው እስከዛሬ ድረስ ባቄላዎች አናት ላይ ያኔ ሰውዬው ሲሰፋ የተቋጠረው ክር ጠቁሮ ይታይባቸዋል፡፡ እንደ ጥቁር ጠባሳ መሆኑ ነው፡፡
****
እንደሰንበሌጡ ከብዙ ችግር የዳኑ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ ለሌሎች ሲሉ እንደጧፍ የነደዱና የሚነዱ ብዙ ናቸው፡፡ እንደከሰሉ ከነእሳታቸው በሌሎች መስዋዕትነት የሚደፍሩና የቁርጡ ቀን ሲደርስ ግን በስጋት የሚሞቱ አያሌ ናቸው፡፡ የሎሎችን ሥቃይ እያየ የሚስቅ ወዮለት ቢባል እውነት ነው። እንደ ባቄላው መፈንዳት አለ። ደግነቱ ከመከራ ትረፍ ያለው አትራፊ ያዝለታል፡፡ ሆኖም ጠባሳው ዕድሜ ልኩን ይከተለዋል፡፡ የሁሉም ምሳሌ ባገራችን ነበሩ፣ አሉ፣ ካልተማማርን ወደፊትም ይኖራሉ፡፡
ከስንት መዓትና የደም አበላ የወጡ ጓደኛሞች ካልተሳሰቡ ማን ሊተሳሰብ ይችላል? ስንት የጋራ ባላንጣ ያላቸው ያንድ እናት ልጆች ካልተግባቡና ህብረት ካልፈጠሩ፣ ማን ህበረት ሊኖረው ይችላል? ስንት ረዥም መንገድ የሚጠብቃቸው መንገደኞች ካልተጋገዙና አብረው ካልገፉ መንገዱ መቼ ያልቅላቸዋል?
የትላንትና ቂምን ለዛሬ አሳድሮ ለትኩስ በቀል መዘጋጀት የኖረ በሽታችን ነው። የተሳሰሩት ችግሮች አገራችንን አስረው ወደባሰው መቀመቅ እንድትጓዝ ያደርጓታል፡፡
የሀገራችን ታጋዮች የድርጅት አባላት፣ የፓርቲ አመራሮች፣ በየደረጃው በሃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ዜጎች የሃገራችንን የጋራ ስዕል ከማየት ይልቅ በዛሬ ሽርፍራፊ ጉዳዮች ላይ በትናንት የባቄላው ጠባሳ ላይ፣ በነገ ሸውራራና እኔ ብቻ ልኑር ባይ ርእይ ላይ እያተኮሩ አቅማቸውን መበታተናቸው ለአገርና ለሀዝብ የሚገድ ተግባር ላይ አለመረባረባቸው ለውድቀት እየዳረገን መሆኑ ብዙ ጊዜ የታየ ሀቅ ነው፡፡ ዛሬም ገና ያልለየለትና መፍትሄ ያላገኘ ችግር ነው፡፡ በስንቶች መስዋዕትነት የተገኘን ፍሬ ማባከን የተለመደ ሆኗል፡፡ የተፈጠረውን እድል በሰዓቱ ከመጠቀም ይልቅ እገሌ ካለበት ሞቼ እገኛለሁ በሚል ነገ ዛሬ ሲሉ፣ እድን ማጣት ዕጣ - ፈንታችን ሆኗል፡፡ በዚህም አገርን ለተደጋጋሚ ችጋር ህዝብን ለጉስቁልና መዳረጉ ይዘወተራል፡፡ “ውቃቢ አምላክ ሲቀርብ እታጠባለሁ ሲሊ እድፍ አንገት ይደርሳል” የሚባለው መሆኑ ነው፡፡
ነፃነትን፣ ዲሞክራሲን፣ ፍትህን አድሎ የሌለው ምርጫን፣ ዛሬም ይሁን ነገ በምኞትና በፀሎት ለማግኘት አይቻልም፡፡ ሁሉም በየደረጃው የሚጠይቀው መስዋዕትነት አለው፡፡ በየደረጃው የሚፈታተነው ወኔ አለው፡፡ ውጣ ውረዱ ብዙ ነው፡፡ በየጉዳዩ ላይ እስከ መጨረሻ መታገል እንደሚያስፈልግ ሁሉ፣ እያንዳንዱን ጉይ እስከ ፍፃሜው ድረስ አውጠንጥኖ ማወቅ ያሻል፡፡ ስለ ነገ የተሻለ ህይወትና የዓላማ ቁርጠኝነት ከማሰብ ይልቅ ስለ ትላንት ቂምና ቁርሾ የኋሊት ማየት ሰንበሌጡ እያለቀ ከሰሉንና ባቄላው እየበዛ መሄዱን አይቀሬ ያደርገዋል፡፡ ወደፊት ከመጓዝ ወደ ኋላ መጎተትን ያስወድደና “ዓለምን ያልጠገበ መናኝ ልጃገረዶችን ይሰናበታል” እንደማለት ነው፡፡

በደራሲና ገጣሚ ሚካኤል አስጨናቂ (ኢ/ር) የተሰናዳው የጸሐይ እግሮች የግጥም መፅሐፍ ለንባብ በቃ። መፅሐፉ በፍቅር በማህበራዊ ጉዳይ፣ በፖለቲካና በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ጠንካራ ሀሳቦች የተዳሰሱባቸው 75 ግጥሞችን ያካተተ ነው።
በመፅሐፉ ጀርባ ላይ አስተያየታቸውን ያሰፈሩት ደራሲና ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም፣ ገጣሚና ደራሲ ሰለሞን ሳህለ ትዕዛዙ ና ገጣሚና ደራሲ አሌክስ አብርሃም እንደገለፁት፤ ገጣሚና ደራሲ ወጣት ሚካኤል አስጨናቂ (ኢ/ር) ይህ የግጥም መድብል እንኳን ለግጥም አፍቃሪያን ከግጥም ራቅ ላሉ ሁሉ ግጥም ምን ማለት እንደሆነ ማሳያ ስለመሆኑ ብሎም ገጣሚና ደራሲው ሚካኤል የጎልማሳን ሃሳብ የትልቅ ሰው አስተውሎትን በውጥጡ አጣምሮ የያዘ ወጣት ስለመሆኑና በግጥሞቹ የማይደርስበትና የማይዳስሰው ሀሳብ እንደሌለ እንዲሁም ያልተዳሰሰ የስሜታችን ክፍል እንደሌለ መስክረዋል።
የጸሐይ እግሮች የግጥም ስብስብ መፅሐፍ በ108 ገፅ ተቀንብቦ በ250 ብር ለገበያ ቀርቧል። ደራሲና ገጣሚ ሚካኤል አስጨናቂ (ኢ/ር) ከዚህ ቀደም  “ተቤራ” እና “ሸግዬ ሸጊቱ” የተሰኙ ሁለት የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መፅሀፎችን ለንባብ ማብቃቱ አይዘነጋም።

በሱዳን አሁንም በቀጠለው የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ደህንነት አደጋ ላይ እንደወደቀ ሂዩማን ራይትስዎች አስታውቋል። ስደተኞቹ በሱዳን ጦር ሃይሎችና በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች እንግልት እየተፈጸመባቸው መሆኑን ተቋሙ አመልክቷል።
የተቋሙ የምስራቅ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር ላቲሺያ ባድር እንደጠቆሙት፤ በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጊዜ አንስቶ፣ በዋናነት ገዳሪፍ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የደህንነታቸውና የሚሰጣቸው ሰብዓዊ ዕርዳታ ሁኔታ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል። አንዳንድ ስደተኞች ካሉበት ካምፖች ለመውጣት አማራጮችን እያፈላለጉ እንደሆነም ታውቋል።
ባለፈው ወር አንድ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ “ግጭቱ ወደ ገዳሪፍና ከሰላ ከተቃረበ ደህንነታችን አደጋ ላይ ይወድቃል” የሚል መልዕክት እንደላከላቸው ያወሱት ላቲሺያ፣ የስደተኛው ስጋት ዕውን ሆኖ  አስረድተዋል።
ዳይሬክተሯ ለስደተኞቹ ከለላ ካልተሰጠ ወይም ከአካባቢው የማስወጣት ስራ ካልተሰራ፣ ሁለቱ ተፋላሚ ሃይሎች በስደተኞቹ ላይ ጥቃት ሊያደርሱ እንደሚችሉ ስጋታቸውን አጋርተዋል። በተጨማሪም፣ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ባለባቸው የደህንነት ስጋት ምክንያት ወደ አገር ቤት ለመመለስ ፍራቻ እንዳለባቸው አትተዋል።
በገዳሪፍ ባሉ ሁለት የስደተኛ ካምፖችና ከሰላ በሚገኘው ካምፕ ስደተኞቹ የተጠለሉ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ የተሰደዱት የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት መነሳቱን ተከትሎ  ተናግረዋል፣ ዋና ዳይሬክተሯ።
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት፣ በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ አገር ቤት ለመመለስ ኮሚቴ መቋቋሙን እንዳስታወቁ ላቲሺያ በማብራራት፣ የሱዳን ባለስልጣናት ለእነዚሁ ስደተኞች የጉዞ ፈቃድ መስጠት እንዳለባቸው አበክረው አሳስበዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማትም፣ ከሁለቱም አገራት መንግስታት በመተባበር፣ ስደተኞቹን ያለምንም ጉዳት ከአገሪቱ በማስወጣት ወደ አገራቸው የመመለሱን ስራ በጥብቅ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
የተለያዩ ድርጅቶችና ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ የገንዘብና የመጓጓዣ አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን ለስደተኞች በማድረግ፣  ከሚገኙበት አስከፊ ሁኔታ እንዲወጡ ያግዟቸው ዘንድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
እ.ኤ.አ. በመጋቢት ወር 2023 የተቀሰቀሰው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት እስካሁን ያላባራ ሲሆን፣ አገሪቱ ለአስከፊ የሰብዓዊ ቀውስ መዳረጓን  መረጃዎች ይገልጻሉ።
በዚህ ሳምንት ወደ ሱዳን የተጓዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር፤ ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ጋር በፖርት ሱዳን ከተማ ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ውይይታቸውም ያጠነጠነው ለእርስ በርስ ጦርነቱ እልባት በመስጠት ላይ  እንደሆነ ዘገባዎች ጠቁመዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም፣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ዕጥረትን ጨምሮ ሌሎች ተግዳሮቶች ፈተና እንደሆኑበት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ አስታውቀዋል። ባለፈው ረቡዕ፣ ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል የኩባንያው የ2016 ዓ.ም. በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም በቀረበበት ወቅት፣ የተመዘገቡ ስኬቶች በጉልህ ተጠቅሰዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ባቀረቡት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው፣ የኔትዎርክ አቅምን የማሳደግ፣ የአገልግሎት ጥራትን ማሻሻልና የአገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት ላይ በዋናነት ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን ተናግረዋል። አክለውም፣ 462 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎችን በማቋቋም፣ የሞባይል ኔትዎርክ አቅምን ማሳደግ መቻሉን ያስረዱት ፍሬሕይወት፣ በበጀት ዓመቱ 86 ሚሊዮን አዳዲስ የሞባይል ኔትዎርክ ደንበኞችን ማፍራት ማስቻሉን ነው የገለጹት።
እ.ኤ.አ. ከ2020 ወዲህ የደንበኞችን የኢንተርኔት ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ ስራዎች እንደተሰሩ ያወሱት፣ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ “የ4G ኔትዎርክ ሽፋንን የማሳደግ ስራ ተሰርቷል፤ በዚህም 424 ከተሞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል። የ5G ኔትዎርክ ስራ ወደ መደበኛ አገልግሎት የገባ ሲሆን፣ በቅርቡ በሌሎች ከተሞች አገልግሎቱ እንደሚጀምርም ተነሯል።
በግጭት ወቅት ውድመት የደረሰባቸው 179 ማዕከላት ጥገና እንደተደረገላቸው   ወ/ት ፍሬሕይወት ባቀረቡት ሪፖርት  አመልክተዋል።
በተጨማሪም፣ በበጀት ዓመቱ 78 ነጥብ 3 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞች እንዳፈራ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ጠቁመው፣ ይህም ከታቀደው ዕቅድ አንጻር የ100 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት እንደተመዘገበበት አስረድተዋል።
በትንሹ አንድ ሚሊዮን ዲጂታል መታወቂያ ለዜጎች ለማቅረብ መታቀዱ፣ በቀጣይ “ለውጥ ይፈጥራል” ተብሎ በስራ አስፈጻሚዋ ለተገለጸው ፕሮጀክት እንደሚያገለግል ነው የተጠቆመው።
ለ307 ሺህ 300 ዜጎች የስራ ዕድል እንደተፈጠረ በሪፖርቱ ተወስቷል።
በበጀት ዓመቱ 93 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ትርፍ የተገኘ ሲሆን፣ ከዕቅዱ 103 ነጥብ 6 በመቶ እንደተሳካ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አብራርተዋል። አያይዘውም፣ ካለፈው ዓመት አንጻር ሲመዛዘን፣ የ21 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል። በውጭ ምንዛሬ በኩል 198 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ እንደተገኘ አስረድተዋል።
በበጀት ዓመቱ በርካታ ስኬቶች ቢመዘገቡም የተለያዩ ተግዳሮቶችም ገጥመውታል። በመግለጽ፣ በዋናነት የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ዕጥረት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ባጋጠሙ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት የአገልግሎት መቋረጥና መሰል ችግሮች ለኩባንያው እንቅስቃሴ ፈተና እንደሆኑበት ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ከቀጠለው ግጭት አንጻርና በአገልግሎት ተደራሽነት ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ፍሬሕይወት ታምሩ ገጥመውታል። “ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተነጋገርን ነው። ለሁሉም የኢንተርኔት አገልግሎት እንደሚከፈት ተስፋ አለን። ነገር ግን እንደኢኮኖሚ ተቋማት ላሉ ሌሎች ድርጅቶች አገልግሎቱን እየከፈትን ነው።” ብለዋል።
የውጭ ምንዛሬ ዕጥረትን ለመቅረፍ ስለታቀዱ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተጠይቀውም ሲመልሱ “ከአበዳሪዎች ጋር ተደራድረን ጨርሰናል። አበዳሪውም አንድ የአሜሪካ የፋይናንስ ኩባንያ ነው። የብድር ድርድሩ በቶሎ ሊሳካ የቻለው የኦዲት አፈጻጸማችን ታይቶ ነው።” ብለዋል።
GSMA የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም ባወጣው ዘገባ መሰረት፣ ኢትዮ ቴሌኮም በአፍሪካ ሁለተኛ፣ በዓለም አስራ ሰባተኛ ደረጃን የያዘ ትልቅ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ተቋም ነው።






ኢ/ር ቢጃይ ናይከር የ40 በመቶ ሽርክና ከድርጅታቸው መውሰዳቸው ደስ እንዳሰኛቸው የአደይ ውበትና ስፓ ምርቶች አምራችና አቅራቢ ድርጅት ባለቤት አክሱማዊት ገ/ሚካኤል ገለፁ።
ኢ/ር ቢዳይ ነሬሽ ናይከር የግሎባል ኢንተርፕርነር ቤጃይ ኢትዮ ኢንዱስትሪያል ኤንድ ኢንጂነሪንግ ሶሉሽን የተሰኘ የሀገር በቀል የማምረቻ ማሽኖች አምራች ድርጅት ባለቤት ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚተላለፈው “ነጋድራስ” የተሰኘ የሥራ ፈጠራ ውድድር ዳኛም ናቸው።
ኢ/ር ቢጃይ በፌስቡክ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው በጥሩ ቁመናና ፈጠራ ላይ የሚገኝ አዋጭነቱ የተረጋገጠ አምራች ድርጅት ካገኙ የ40 በመቶ ወይም (የ20 ሚሊዮን ብር) ሽርክና ለመግባት ማቀዳቸውን በመግለጽ መስፈርት አስቀምጠው የዚህ እድል ተጠቃሚ የሚሆኑ ድርጅቶች እንዲወዳደሩ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት አደይ የውበትና ስፓ ምርቶች ማምረቻና አቅርቦት  ድርጅትም መወዳደሩን አክሱማይት ጨምረው ገልጸዋል።
እንደ አክሱማዊት ገለጻ ኢ/ር ቢጃይ ነሬሽ ናይከር ለተወዳዳሪዎች ቁልፍ ያሏቸውን መስፈርቶች ያቀረቡ ሲሆን፣ ከነዚህ መስፈርቶች መካከል የሃሳብና ብራንድ ጥራት፣ በኢትዮጵያ መመረት የሚችል የንግድ ሀሳብ፣ በከፊል ኤክስፖርት ተደርጎ ለሀገር የውጭ ምንዛሬ ማምጣት የሚችል 40 በመቶ ሼር ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነና የሼሩ ብርም ከ20 ሚሊዮን ያልበለጠ፣ በብራንድ፣ በቢዝነስ ሞዴል፣ በአዋጭነት በቢዝነስ ፓርትነርሽፕ ኤግዚት ስትራቴጅና የስራ ፈጠራ የባለቤትነት መብት ያለው መሆን አለበት የሚሉት ተካትተውበታል።
በዚህም መሰረት ነዋሪነቷን በአሜሪካ ያደረገችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አክሱማዊት ገ/ሚካኤል በአደይ የውበትና ስፓ ማምረቻና አቅርቦት ድርጅቷ ዙሪያ ያቀረበችው ሰፋና ዘርዝር ያለ ሀሳብ የኢ/ር ቤጃይ ነሬሽ ናይከርን ቀልብ መግዛት መቻሉን አክሱማዊት ተናግረዋል።
አደይ የውበትና የስፓ ምርቶች ማምረቻና አቅርቦት ድርጅት ዋና ዋና የውበት መጠበቂያ ምርቶቹን በኢትዮጵያ  ብቻ ወራቶችን ጠብቆ ከሚበቅለው አደይ አበባ (Bidens Macroptera) ለማምረት ማቀዳቸው ልዩ እንደሚያደርገው የገለጹት የድርጅቱ መስራችና ባለቤት አክሱማዊት በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ አካባቢ የማምረቻ ቦታ ያላትና ምርቶቹን በዋናነት ለኢትዮጵያ፣ ለአሜሪካ፣ ለመካከለኛው ምስራቅ፣ ለአውሮፓና ለምስራቅ አፍሪካ ለማቅረብ የወጠነችውን እቅድ ለውድድር ማቅረቧን ተናግራለች።
በዚሁ መሰረት በርካታ ድርጅቶች ይህንኑ ሽርክና ከኢ/ር ቢጃይ ነሬሽ ናይከር ለማግኘት በውድድሩ የተሳተፉ ሲሆን ኢ/ሩ ካቀረቡት መስፈርቶች አብዛኛውን ያሟላው “አደይ የውበትና የስፓ ምርቶች ማምረቻና አቅርቦት ድርጅት ሆኖ መመረጡን ኢ/ሩ በፌስቡክ ገፃቸው ይፋ አድርገው ተቀብለውናል ሲሉ የድርጅቱ መስራች እና ባለቤት አክሱማዊት ተናግረዋል። በዚህ የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ የገለጹት አክሱማዊት ኢ/ር ቢጃይን በእጅጉ አመስግነው በገቡት ቃልና ባቀረቡት የቢዝነስ ሞዴል መሰረት በከፍተኛ ተነሳሽነት ለመስራት ሞራል ማግታቸውን ተናግረዋል።
ከህንዳዊው አለማቀፍ ነጋዴ አባታቸው ያካበቱት ልምድ ቀላል እንዳልሆነ የሚገልጹት ኢ/ር ቢጃይ ነሬሽ ናይከር በአሁኑ ወቅት በኢቢሲ በሚተላለፈው የስራ ፈጠራ ውድድር ዳኛ፣ የአመቱ የበጎ ሰው ሽልማትን ጨምሮ በርካታ እውቅናዎች ያገኙ ሲሆን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፌስቡክ የትስስር ገፅ አዲስ የሚባል ባህል በመጀመር የንግድ ሀሳብ ኖሯቸው የመነሻ ገንዘብ ላጠራቸው ወጣቶች ሃሳቸውን በማወዳደር “ነፃ ፍሬ ፈንድ” የተሰኘ የ100 ሺህ ብር ሽልማት ለአሸናፊዎች በመሸለም ሀሳባቸውን እውን እንዲያደርጉ ብዙዎችን እያገዙ ሲሆን በርካታ ማህበራዊ ሃላፊነትን እየተወጡ በመሆኑ ለሌሎች ባለሀብቶችም ምሳሌ መሆን የሚችሉና ሊመሰገኑ የሚገባቸው ባለሃብት ናቸው ሲሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

Page 2 of 714