Administrator

Administrator

በአባይ ጉዳይ ላይ ከተፃፉት አዳዲስ መፃህፍት መካከል አንዱ፤ የኒውዮርክ ከተማ ነዋሪ በሆኑት አቶ ገብረፃድቅ ደገፋ የተዘጋጀ ሲሆን፣ “ናይል ታሪካዊ፣ ሕጋዊና ልማታዊ ገጽታዎች - ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ማስጠንቀቂያ” በሚል ርእስ ተተርጉሟል፡፡ በአቶ ወርቁ ሻረው ተተርጉሞ በ406 ገፆች የቀረበው መፅሐፍ፤ በ60 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

የአምስት ወር ነፍሰጡር የነበረችውን ባለቤቱን ሆዷ ላይ ስድስት ቦታ በጩቤ ወጋግቶ የገደለው ተጠርጣሪ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ፡፡ ባልና ሚስቱ ለአራት ዓመታት በጋብቻ ተሳስረው ሲኖሩ የሁለት ዓመት ልጅ አፍርተዋል፡፡ በምዕራብ ጐጃም ቡሬ ከተማ ውስጥ በተፈፀመው በዚህ ወንጀል ከሟች ሌላ የሟች ወ/ሮ ተናኜ ገረም ወላጅ እናትና አባት በጩቤ የመወጋት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ የቡሬ ወረዳ ፖሊስ ፅ/ቤት መርማሪ የሆኑት ዋና ሳጅና አልማው ደሴ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት ባለፈው ወር መጨረሻ በባልና ሚስት መካከል በተፈፀመ ያለ መግባባት ሚስት ወደ ወላጆቿ ቤት ሄዳ ነበር፡፡

ባል እዚያ ሄዶ ግድያውን መፈፀሙን ተናግረዋል፡፡ ተጠርጣሪው በትዳር አጋሩ ላይ ይህን ወንጀል በፈፀሙ የአካባቢው ህብረተሰብ ቁጣ ተቀስቅሷል፡፡ ተጠርጣሪው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ መካሄዱን የጠቆሙት ዋና ሳጅን አልማው የምርመራ መዝገቡ ለዐቃቤ ሕግ ተላልፎ ክስ መመስረቱንም ጠቁመዋል፡፡ በተጠርጣሪው በጩቤ የተወጉት የሟች ወላጅ እናትና አባት በአሁኑ ወቅት በህክምና ላይ እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በመንፈሳዊ ኮሌጁ ትምህርት ተቋርጧል፤ ተማሪዎቹም ምግብ መመገብ አቁመዋል

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት÷ ለትምህርት ጥራት መሻሻልና ለደቀ መዛሙርቱ መብት መከበር ከመቆም ይልቅ ገንዘብ ለመሰብሰብና የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ቅድሚያ ይሰጣሉ ያሏቸው ሁለት የአስተዳደር ሓላፊዎች ከሥልጣን እንዲወገዱ ያቀረቡት ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ባለማግኘቱ ትምህርት ማቆማቸውንና ምግብ ከመብላት መከልከላቸውን አስታወቁ፡፡ በጥያቄያቸው ያመለከቷቸው በርካታ የኮሌጁ ችግሮች ላለፉት ዐሥራ አራት ዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ መኾናቸውን የገለጹት ደቀ መዛሙርቱ÷ የመምህራኑ አቅም ማነስና የትምህርት ጥራት መውደቅ፣ የምግብ መበከልና የአስተዳደሩ በጥቅም ትስስርና በሙስና መዘፈቅ ሊታገሡት ከሚችሉት በላይ በመኾኑ ፓትርያሪኩና የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤቱ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጧቸው መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡

ይኹንና ፓትርያሪኩን በአካል አግኝቶ ለማነጋገር አልያም የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ሓላፊዎችን ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረጉት ጥረት ከኮሌጁ ሓላፊዎች ጋራ በጥቅም ተሳስረዋል ያሏቸው አካላት እንደፈጠሩት በሚያምኑት መሰናክል አለመሳካቱን አስታውቀዋል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ከኮሌጁ አስተዳደር ጋራ የገቡበት ውዝግብ ከተቀሰቀሰ ሁለተኛ ሳምንቱን የያዘ ሲኾን ትምህርት መቋረጡም ተዘግቧል፡፡ ለደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ምላሽ እንደሚሰጥ የገለጸው አስተዳደሩ÷ ደቀ መዛሙርቱ ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ ያቋረጡትን ትምህርት እስከ ረቡዕ ቀትር ድረስ በአስቸኳይ እንዲቀጥሉ አሳስቧል፡፡ ደቀ መዛሙርት ወደ ትምህርታቸው የማይመለሱ ከኾነ ደግሞ በዚያው ዕለት ንብረትና መታወቂያ እያስረከቡ ኮሌጁን ለቀው እንዲወጡ አስተዳደሩ አስጠንቅቋል፡፡

‹‹ለሁለት ሰዎች ሲባል ሁለት መቶ ተማሪ አይባረርም፤ ብቃት የሌላቸውና ኮሌጁን እንደ ርስት በዘመድ ይዘው የጥቅም ማግበስበሻ ያደረጉት አካዳሚክ ዲኑና የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው ከሓላፊነታቸው ይነሡልን፤›› የሚሉት ደቀ መዛሙርቱ በበኩላቸው÷ ችግሮቻቸው በመሠረቱ ደረጃ በደረጃ መፈታት እንደሚገባቸው ቢቀበሉም ወደ ትምህርት ገበታቸው የሚመለሱት ግን የኮሌጁ ምክትል አካዳሚክ ዲንና የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው ከሓላፊነታቸው ሲነሡ ብቻ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ እንደሚያስረዱት÷ በተጠቀሱት የኮሌጁ አስተዳደር ሓላፊዎች ደረጃ ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ ምእመኑ ‹‹የገንዘብ ምንጭ ብቻ ኾኗል፤ አገልጋይ ጠፍቷል፡፡›› ደቀ መዛሙርቱ÷ ኮሌጁን እንደ ግለሰብ ቤትና እንደ ዘመድ ርስት ይቆጥራሉ በሚሏቸው ጥቂት ሓላፊዎች መካከል አለ የሚሉት የጥቅም ትስስር በትምህርት ጥራትና በመብታቸው ላይ የፈጠረውን ተጽዕኖ የሚገልጹት ‹‹ኮሌጁ የትምህርት ሳይሆን የንግድ ማእከል ኾኗል፤›› በሚል ነው፡፡

ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡ የደቀ መዛሙርቱ መማክርት አባላት እንዳስረዱት÷ የተለያዩ ገባሬ ሠናይ ድርጅቶች ለኮሌጁ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ፤ ከእነርሱም በላይ በዋናነት ሁሉም አህጉረ ስብከት ከጠቅላላ ገቢያቸው አምስት ከመቶ ፈሰስ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኮሌጁ ሕንጻውን በማከራየትና የመማሪያ ክፍሎቹን ለተለያዩ ኮሌጆች በመፍቀድ ከፍተኛ ገቢ ይሰበስባል፡፡ ይኹንና ደቀ መዛሙርቱ በሜዳ ላይ የሚማሩበት አጋጣሚ አለ፡፡ በየመርሐ ግብሩ ከተዘረጉት ኮርሶች ብዛት ጋራ የሚመጣጠኑ መምህራንን መቅጠር እየተቻለ የመምህራን ምደባው አራትና አምስት ኮርሶችን በሚይዙ ጥቂት መምህራን መካከል የተወሰነ ነው፡፡ የመምህራኑ ዕውቀት ‹‹ሙሉዕ በኩለሄ›› እስካልኾነና መምህራኑ ከተጨማሪ ሓላፊነቶች ጋራ ከሚያጋጥማቸው የዝግጅት ማነስ የተነሣ ምደባው የትምህርት ጥራቱን የሚጎዳው ይኾናል፡፡ ይህም በትምህርት አሰጣጡና በምዘናው ላይ በሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ የተነሣ አቤቱታ የሚያቀርቡ ደቀ መዛሙርትን የሚያሸማቅቁ፣ ከዚህም አልፎ በመማሪያ ክፍሎችና በቤተ መጻሕፍት ውስጥ ሳይቀር የሚደበድቡ መምህራን መኖራቸውን ነው ደቀ መዛሙርቱ ለአዲስ አድማስ የተናገሩት፡፡

በተማሪዎች አቀባበል ወቅት ኮሌጁ የሙሉ ጤንነት ምርመራ እንደሚያደርግላቸው የገለጹት ደቀ መዛሙርቱ በሂደት ግን በካፊቴሪያው ጥንቃቄ የጎደለው የምግብ ዝግጅት የተነሣ ጤንነታቸው የተጎዳና በቂ ሕክምና የማያገኙ ደቀ መዛሙርት ቁጥር ጥቂት እንዳልኾነ ደቀ መዛሙርቱ ለዝግጅት ክፍሉ ገልጸዋል፡፡ በቤተ መጻሕፍት አገልግሎትና በመረጃ ቴክኖሎጂ ረገድ የሚሰጠው አገልግሎትም አንፋውን ኮሌጅ የሚመጠን እንዳልኾነ ነው ደቀ መዛሙርቱ የሚናገሩት፡፡ ‹‹የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከተቀሩት ሁለት የቤተ ክርስቲያኒቱ ኮሌጆች ጋራ ሲነጻጸር አንጋፋ ቢኾንም ዛሬ ከአስተዳደሩ ድክመት የተነሣ የሚገኝበት ደረጃ ከዘመናዊነት የራቀ ነው፤›› ይላሉ ደቀ መዛሙርቱ፡፡ ይህ የኮሌጁ ኹኔታ የሚያሳስባቸውና በጉዳዩ ላይ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ የሚመክሩ መምህራን ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጣቸውና ስለላ እንደሚካሄድባው ተመልክቷል፡፡

በኮሌጁ ሰፍኗል የሚሉትን ሙስናና የአሠራር ብልሽት የሚቃወሙት የአገርንና የሕዝብን ሀብት ከማዳን አንጻርም በመኾኑ መንግሥትም ሊያግዘን ይገባል፤ ‹‹ችግራችንን የማይፈቱልን ከኾነ ችግር ባይፈጥሩብን›› በማለትም በግል እየጠሩ ያስፈራሩናል፤ ይዝቱብናል ያሏቸውን የፖሊስ አባላት ይጠይቃሉ ደቀ መዛሙርቱ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በአድራሻ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የጻፉትን ጥያቄዎቻቸውን ለጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ለሰብአዊ መብት ኮሚሽንና ለፌዴራል ፖሊስ በግልባጭ ማሳወቃቸውን የገለጹ ሲኾን ለጥያቄዎቻቸው በቂ ምላሽ እስኪያስገኙ ድረስ ውርጩን፣ ረኀቡንና እንግልቱን ተቋቁመው ለመቆየት መወሰናቸውን ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ በደቀ መዛሙርቱ ጥያቄዎችና ተቃውሞዎች ላይ የኮሌጁን ሓላፊዎች አስተያየትና ምላሽ ለማግኘት የኮሌጁ ምክትል አካዳሚክ ዲንን በስልክ ለማነጋገር የሞከረን ቢኾንም ዲኑ በአካል ካልቀረባችኹ በስልክ ምላሽ አልሰጥም ብለውናል፡፡ የዝግጅት ክፍሉ በነበረበት የጊዜ እጥረት ዲኑን በአካል አግኝቶ ሊያነጋግራቸው አልቻለም፡፡

ኤርትራ ውስጥ ሰልጥነው በጋምቤላ ክልል ድንበር አቋርጠው ጥቃት ሊፈፅሙ የነበሩ ታጣቂዎች በሰሜንና ደቡብ ሱዳን መንግስታት ትብብር ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፈው መሠጠታቸውን ምንጮቻችን አመለከቱ፡፡ ስልጠና ካገኙበት ከኤርትራ ተነስተው ሰሜን ሱዳንና ደቡብ ሱዳንን አልፈው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ሊያቋርጡ ሲሉ በሶስቱ አገሮች መሀል ባለው የፀጥታ የትብብር ስምምነት መሠረት ለክልሉና ለፌዴራል መንግስት የፀጥታ ሀይሎች ተላልፈው ተሠጥዋል፡፡

ታጣቂዎቹ በሰላም እጃቸውን እንዲሠጡ የቀረበላቸውን ጥያቄ ባለመቀበላቸው በተከፈተ የተኩስ ልውውጥ ህይወታቸውን ያጡ እንዳሉም የጠቆሙት ምንጮቹ በክልሉ በተፈፀሙ የተለያዩ የሽብር ተግባሮች እጁ እንዳለበት የሚጠረጠረውና በአስመራ ለረጅም ጊዜ የኖረው ኦማን ካውንዳን ጨምሮ አስራ አንድ ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ባለፈው አመት በጋምቤላ ክልል የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ላይ ይጓዙ የነበሩ ተማሪዎች ላይ እና በክልሉ በኢንቨስትመንት በተሰማሩ ፓኪስታንያውያን እንዲሁም በክልሉ ፖሊሶች ላይ ጉዳት አድርሷል በሚል በመንግስት ይፈለግ የነበረው አሜሪካዊ ዜግነት ያለው ኡሞድ ኡዶል ወደ ደቡብ ሱዳን ሄዶ እንደነበር ይታወቃል፡፡

አብረውት ከነበሩ ታጣቂዎች የተወሰኑት ተገድለው አብዛኛዎቹ ተይዘው ጉዳያቸው በፍርድ ሲታይ እሱ ተሠውሮ ሲፈለግ ከቆየ በኋላ በቅርቡ በፌደራል መንግስት ፀረ ሽብር ግብረ ሀይልና የፀጥታ አካላት ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ መገደሉንና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ማረጋገጡ ይታወቃል፡፡

ባለፈው ሳምንት የአዲስ አድማስ ጋዜጣ እትም ላይ በአርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ ዙሪያ የቀረበውን አጭር ዜና ስመለከት ብዙ ሃሳቦች መጡብኝ፡፡ በእርግጥ ሠራዊት ፍቅሬ የተወራበት ነገር አሉባልታ እንደሆነ መግለፁ በዜናው ተዘግቧል፡፡ ነገር ግን ሁለት ቅሬታዎች አሉኝ፡፡ አንደኛው ቅሬታዬ በዜና አዘጋገቡ ላይ ነው፡፡ ሁለተኛው ቅሬታዬ ግን በዜና ዘገባው ላይ ሳይሆን፣ በጊዜው በአርቲስቶች ላይ በሚናፈሱ ወሬዎች ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያ ቅሬታዬን ላስቀድም፡፡ በአዲስ አድማስ የቀረበውን አጭር ዜና፣ በሙያ መመዘኛ እንየው ከተባለ ተቃራኒ ገፅታዎች ይስተዋሉበታል፡፡ ብልሃትና ጥንቃቄ የተሞላበት ዘገባ ነው፡፡

“ብልጠትም ያለበት ይመስላል” ብዬ ስሜታዊ ድምዳሜ ላይ መድረስ አልፈልግም፡፡ ጠንቃቃ ዜና መሆኑን ግን ያለ ጥርጥር መናገር ይቻላል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በዜናው አንዳንድ ገፅታዎች ላይ ግልፅ ጉድለቶች አሉበት፡፡ ለምሳሌ ዜናው ብዙ መረጃዎችን የሚሰጥ ይመስላል፡፡ ይህም የጥንቃቄ ውጤት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ነገር ግን ዜናው ከሚሰጠን መረጃ ይልቅ በርካታ መልስ የሌላቸው ጥያቄዎችን የሚፈጥርብን መሆኑ ትልቅ ጉድለት ነው፡፡ ሌላኛው ጉድለት፣ በዜናው ርእስ ላይ ጭምር የሚታይ ነው፡፡

ለዜናው መነሻ የሆነው ወሬ በዜናው ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ አንዲት ሴት፣ አርቲስቱ ሊስመኝና ሊደባብሰኝ ሞክሯል ብላለች የሚል ወሬ ነው መነሻው፡፡ እንግዲህ ከዚህ ልንገነዘብ የምንችለው ወሬው ስለ ወሲብ ትንኮሳ እንጂ ስለ መድፈር ሙከራ አለመሆኑን ነው፡፡ ደግሞም ወሬው አሉባልታ መሆኑንም አርቲስቱ ገልጿል፡፡ በሌላ አነጋገር፤ ወሲባዊ ትንኮሳ እንደፈፀመ ተደርጐ ሲናፈስ የቆው ወሬ አሉባልታ እንደሆነ አርቲስቱ ተናግሯል፡፡ የዜናው ርእስ ግን “የወሲብ ትንኮሳ” የሚል አገላለፅን ሳይሆን፣ “የመድፈር ሙከራ” የሚል ሀረግ ተጠቅሟል፡፡ ይሄ ጉድለት ነው፡፡

Monday, 25 March 2013 11:13

ቺንዋ አቼቤ አረፈ

ከአፍሪካ ታላቅ ደራሲዎች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነው ናይጄርያዊው ቺንዋ አቼቤ በ82 ዓመቱ ትናንት በአሜሪካዋ ማሳቹሴትስ ከተማ በድንገተኛ ህመም ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡ አልበርት ቺኒዋ ሉሞጉ አቼቤ ከልቦለድ ስራዎቹ ባሻገር በገጣሚነትና በሃያሲነቱ የሚታወቅ ፕሮፌሰር ነበር፡፡

በ1960ዎቹ ስላለፈበት የቢያፍራ ጦርነት ትውስታዎችና የህይወት መታሰቢያ ታሪኩን “There Was a Country: A Personal History of Biafra” በሚል ርእስ ለመጨረሻ ጊዜ አምና ለንባብ አብቅቷል፡፡ ታዋቂው የእንግሊዝ አሳታሚ ኩባንያ ፔንጊውንስ ሞቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፣ ደራሲውን “እጅግ ምርጥ ችሎታ ያለው ፀሃፊ እና የአፍሪካ ታላቅ የስነፅሁፍ ሰብእና” ሲል አሞካሽቶታል፡፡ በአገሩ በናይጄርያና በአለማቀፍ ደረጃ በርካታ ሽልማቶችን ያገኘው አቼቤ በልቦለድ ስራዎቹ በአፍሪካዊነት፤ በብሄርተኝነት፤ በፀረ ቅኝ ግዛት ጭብጦች ዙሪያ በመፃፍ ይታወቅ በነበር፡፡

ቺንዋ አቼቤ ስነፅሁፍ በመላው አህጉሪቱ እንዲስፋፋ፣ በተማሪዎች ዘንድ የልቦለድ ባህል እንዲፈጠርና ከፍተኛ የስነፅሁፍ እድገት እንዲቀጣጠል በተጫወተው ፈርቀዳጅ ሚና ጎልቶ ይጠቀሳል፡፡ በአሜሪካ ኮሌጆች ሲያስተምር ቆይቶ እኤአ በ1958 በፃፈው ‹ቲንግስ ፎል አፓርት› በተባለ የልቦለድ መፅሃፉ ከፍተኛ ዓለማቀፍ ዝና አትርፍዋል፡፡ መጽሐፉ በመላው ዓለም በ50 የተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ 12 ሚሊዮን ቅጂዎች ተሽጥዋል፡፡

የልቦለድ መፅሃፉ በበርካታ የአፍሪካ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ ኮሌጆች እና ዩኒቨርስቲዎች እንደ መማርያ መፅሃፍ ሊያገለግልም በቅቷል፡፡ አቼቤ የናይጄርያ የመንግስታትንና የባለስልጣናትን ድክመት በመተቸት እንዲሁም ሙስናን በይፋ በማጋለጥ፤ እንዲሁም በተለያዩ የህትመት ውጤቶች መጣጥፎችን በማቅረብ ይታወቅ ነበር፡፡ አቼቤ ከ20 በላይ መፅሃፍትን ለንባብ ያበቃ ሲሆን ከፃፋቸው ልቦለዶች መካከል ‹ኖ ሎንገር አት ኢዝ›፤ ‹አሮው ኦፍ ጎድ›፤ ‹ኤማን ኦፍ ዘ ፒፕል›፤ እና ‹አንትሂልስ ኦፍ ሳቫና› የተባሉት ይጠቀሳሉ፡፡

‹‹አርሾ›› የተሰኘው የግል የሕክምና ላቦራቶሪ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ድርጅቶችንና አገልግሎቶችን ጥራትን ማዕከል በማድረግ እያወዳደረ ዕውቅና በመስጠት ከሚታወቀው “Business Initiative Directives” ከሚባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት “Century International Quality ERA Award in Gold Category” በሚለው የሽልማት ዘርፍ እ.ኤ.አ. በመጋቢት 10 ቀን 2013 ዓ.ም በአዉሮፓ የተባበሩት መንግስታት ጉባኤ ማዕከል በኾነው በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት የወርቅ ዋንጫና የዕውቅና ሰርቲፍኬት ተሰጠው፡፡

የላብራቶሪው ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ቀዲዳ ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፤ከ173 አገራት በተለያየ የግል የሥራ ዘርፍ ጥራትና ብቃት ያለው አገልግሎት በመስጠት በአየር መንገድ፣ በኢንጂነሪንግ፣ በሕትመት ሥራ፣ በፖሊስ አገልግሎት፣ በሕክምና እና በተለያዩ ሥራዎች ዘርፍ ተሰማርተው ሲሠሩ የነበሩ የተመረጡ ድርጅቶች በፕላቲኒየም፣ በወቅርና በብር ምድብ የተለያየ ሽልማት በተቀበሉበት መድረክ ላይ ‹‹አርሾ›› ተካፋይ ሆኖ በመሸለሙ እጅግ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

አክለውም “ሽልማቱ አሁን ከምንሰጠው ብቃት ያለው ሥራ የበለጠ እንድንተጋ ያደርገናል” ብለዋል፡፡ ኤርቫቢር ቲርዚያ በተባሉ አርመናዊ ፋርማሲስት በአነስተኛ ደረጃ ተመስርቶ ሥራ ከጀመረበት ከ1963 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይ ቀደም ሲል ምንም የግል የሕክምና አገልግሎት ባልተስፋፋበትና አንድም የግል ላቦራቶሪ አገልግሎት ባልነበረበት ጊዜያት ከኢትዮጵያ ጤናና ስነምግብ ኢንስቲትዩት ቀጥሎ ለሁሉም የመንግሥት፤ የድርጅቶችና የግል የጤና ተቋሞች አስተማማኝ የላቦራቶሪ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቶአል፡፡ራሱን በማሳደርግም የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመከተል እየሰጠ ባለው አገልግሎት ለዚህ ሽልማት የበቃው ‹‹አርሾ የሕክምና ላቦራቶሪ በአሁኑ ሰአት በአዲስ አበባ ስድስት ቅርንጫፎችን በመክፈት አየሠራ ይገኛል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ከሲ.ዲኤም.ኤ እና ከኢ.ቪ.ዲኦ ቀጣይ የሆነውን ሦስተኛ ትውልድ ፈጣን የ3ጂ ኢንተርኔት ጥቅል አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ፡፡የ3ጂ ፈጣን ኢንተርኔት ጥቅል አገልግሎት የቀረበው ለሦስት የአገልግሎት ዐይነት ተጠቃሚዎች ሲሆን ለ1GB ከተጨማሪ 150 ሜጋ ቢት ልዩ ጥቅም ጋር በ400 ብር፣ ለ2GB ከተጨማሪ 200 ሜጋ ቢት ልዩ ጥቅም ጋር በ600 ብር እንዲሁም 4GB ከተጨማሪ 350 ሜጋ ቢት ልዩ ጥቅም ጋር በ800 ብር ወርሃዊ ክፍያ ጥቅም ላይ እንደሚውል ኢትዮ ቴሌኮም በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

አገልግሎቱ ከመጋቢት 12 ቀን 2005 ጀምሮ መሰጠት መጀመሩን የገለፀው ድርጅቱ በቅድመና በድህረ ክፍያ መጠቀም ለሚፈልጉም አገልግሎቱ በምርጫ ቀርቧል፡፡ደንበኞች ከመጋቢት 12 እስከ ሚያዚያ 12 ቀን 2005 ዓ.ም ባለው የአንድ ወር የማስተዋወቂያ ጊዜ አገልግሎቱን መጠቀም ከጀመሩ ለማስጀመሪያ ከተቀመጠው የመቶ ብር ክፍያ ነፃ ሆነው መጠቀም እንደሚችሉም አስታውቋል፡፡ ባለ ከፍተኛ ፍጥነት እንደሆነ የተነገረለት አዲስ የ3ጂ ኢንተርኔት ጥቅል አገልግሎቱን በድህረ ክፍያ ለማግኘት ለሚፈልጉ ደንበኞች የአገልግሎቱ ክፍያ የሚፈፀመው በወር መጨረሻ ላይ ሲሆን ከተመደበው የጥቅል አገልግሎት በተጨማሪ አገልግሎቱን የሚጠቀሙ ደንበኞች በተጠቀሙት የፍጆታ መጠን በመደበኛው የአገልግሎት ክፍያ መሰረት በሜጋ ቢት 46 ሳንቲም የሚከፍሉ መሆኑን መግለጫው አብራርቷል፡፡

የ3ጂ ዳታ ወይም ኢንተርኔት አገልግሎት ክፍያ በ3ጂ ዶንግል ከሆነ 799 ብር እንዲሁም በዋይፋይ ራውተር ከሆነ 1529 ብር የሚጠይቅ መሆኑም ተገልጿል፡፡ በቅድመ ክፍያ ጥቅል አገልግሎቱን መጠቀም ለሚፈልጉ ደንበኞች የማስደወያ ካርድን በመጠቀም ሂሳቡን መሙላት የሚኖርባቸው ሲሆን በጥቅም ላይ ያልዋለ የቅድመ ክፍያም ሆነ የድህረ ክፍያ የጥቅል ኢንተርኔት ወይም ዳታ አገልግሎት ወደሚቀጥለው ወር የማይተላለፍ መሆኑን ኢትዮ ቴሌኮም በመግለጫው አስገንዝቧል፡፡ በኢትዮ ቴሌኮም የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ አብዱራሂም፤ አዲሱ 3ጂ አገልግሎት ከነባሩ የሚለየው ቀድሞ ሥራ ላይ የነበረው 3ጂ ሲም ካርድ የዳታና የድምፅ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን አዲሱ 3ጂ ግን የሚሰጠው የዳታ አገልግሎት ብቻ ነው፡፡ አዲሱ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅሙ ከፍተኛ ከመሆኑም በመሆኑ ከኢ.ቪ.ዲኦ ጋር የፍጥነት ልዩነት እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የሞባይል ኢንተርኔትና ሲ.ዲኤም.ኤ ኔትወርክ በማይሠሩበት፣ የ3ጂ ሲምካርድ እና ኢ.ቪዲኦ በኔትወርክ መንቀራፈፍ ደንበኞች በኢትዮ ቴሌኮም ላይ በሚማረሩበት ወቅት አዲስ አገልግሎት የመጀመሩ ፋይዳ ምንድነው? የችግሩስ መንስኤ ምንድን ነው? በሚል የተጠየቁት አቶ አብዱራሂም፤ ለኔትወርክ መቋረጥና ዘገምተኝነት የኀይል መቆራረጥና የፋይበር ኦፕቲክ ኬብል መቆራረጥን በዋነኛ መንስኤነት አስቀምጠዋል፡፡ የኀይል መቆራረጥ ከመሥሪያ ቤቱ አቅም በላይ ቢሆንም በኮንስትራክሽን ሥራና በሕገወጦች የሚቆራረጠው የፋይበር ኬብል ሌላው ለኔትወርክ መቆራረጥ ዋነኛ ምከንያት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ “ከኬብልና ከኀይል መቆራረጥ የሚመጣ የኢንተርኔት ኔትወርክ መጓተት እንጂ በአገልግሎቱ ላይ ችግር የለም” ብለዋል፡፡

በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለውን የሕዳሴ ግድብ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ረቡዕ በ11 ሰዓት በብሄራዊ ትያትር የሥነፅሁፍ ምሽት ሊያቀርብ ነው፡፡ የማህበሩ ፕሬዚደንት ደራሲና ሃያሲ ጌታቸው በለጠ እንደገለፁት፤ አንጋፋ ደራስያን በአባይ ዙሪያ የገጠሟቸው ግጥሞች በምሽቱ ይዳሰሳሉ፡፡ ከዚህም በተማሪ ጥንታዊ የቆሎ ተማሪዎችና አባይ ያላቸውን መስተጋብር የሚቃኝ ዝግጅትም ተካትቷል፡፡ በተመሳሳይ ዜና የኢትዮጵያ ሰዓሊያን ማህበር በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሥዕል አውደርእይ በቅርቡ ያዘጋጃል ተብሏል፡፡