
Administrator
መንግሥት የአሸባሪዎች የጥቃት ስጋት እንደሌለ አስታወቀ
“ኢቦላ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቷል የሚባለው ሃሰት ነው”
የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ክፍሉ ጠንካራና ህብረተሰቡን ያማከለ በመሆኑ ከአልሸባብም ሆነ በሌሎች ሀገሮች ከሚደገፉ አሸባሪዎች ሊደርስ የሚችል ጥቃት እንደማይኖር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አረጋገጠ፡፡
ሰሞኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲው አማካኝነት በቦሌ አካባቢ አልሸባብ ጥቃት ሊፈፅም እንደሚችል መረጃው ደርሶኛል በማለት ዜጐቹ በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በድረገፁ መልእክት ማስተላለፉ የሚታወስ ሲሆን በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ጉዳይ ዳይሬክተር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ በበኩላቸው፤ “የሀገሪቱ ፀጥታ የተጠናከረ ነው፤ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ስጋት አይግባው” ብለዋል፡፡
የሀገሪቱን ደህንነት የምንጠብቀው በተለያዩ ጊዜያት በሚሰጡ የጥቃት ማስጠንቀቂያዎች አይደለም ያሉት አምባሳደሩ፤ የፀጥታ ሃይሉ የህብረተሰቡን ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነቱን ለመወጣት እለት ከእለት በጥንካሬ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በትናንትናው እለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ለዲፕሎማቶችና ለአለማቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች በሰጠው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የኢቦላ ታማሚ እንደሌለ አረጋግጧል፡፡
ሰሞኑን በማህበራዊ ድረ-ገፆች ኢትዮጵያ ውስጥ በጥቁር አንበሳና በቅዱስ ያሬድ ሆስፒታል የኢቦላ ታካሚዎች አሉ በሚል የተሰራጩ መልእክቶች ከእውነት የራቁ መሆናቸውን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡
ከተለያዩ ወገኖች የሚቀርቡ ጥቆማዎች በስልክ መስመር 8335 ላይ እያስተናገደ መሆኑን የጠቆመው መስሪያ ቤቱ፤ የኢቦላ ታማሚ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢገኝ እንደማይደበቅና ሀገሪቱ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደሆነ ገልጿል፡፡
በሽታው ሀገር ውስጥ ቢገባ እንኳን በብቃት ምላሽ ለመስጠት ጠንካራ ዝግጅት መደረጉንም ጠቁሟል፡፡
ፕ/ር መስፍን በአውስትራሊያ የእድሜ ዘመን ስኬት ሽልማት ይቀበላሉ
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ተቀማጭነቱ በአውስትራሊያ የሆነው ‘ዲሞክራሲ ፎር ኢትዮጵያ ሰፖርት ግሩፕ’ የተሰኘ ቡድን ያዘጋጀውን የእድሜ ዘመን ስኬት ሽልማት ለመቀበል ሰሞኑን ወደ አውስትራሊያ መሄዳቸውን ምንጮቻችን ገለጹ፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በአገሪቱ ሁሉን አቀፍ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ለማስቻል ለረጅም አመታት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ያለው ቡድኑ፣ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት በማሰብ ሽልማቱን እንዳበረከተላቸው አስታውቋል፡፡
ፕሮፌሰሩ ሽልማቱን ከመቀበላቸው በተጨማሪ፣ ከነገ ጀምሮ በሚልቦርን፣ በሲድኒ፣ በብሪስባኔና በሌሎች የአውስትራሊያ ከተሞች ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በአገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
በሰብዓዊ መብቶች፣ በታሪክ፣ በጂኦግራፊና በልማት ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ የተለያዩ መጽሃፍትንና የጥናት ወረቀቶችን የጻፉትና ለረጅም አመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በተለያዩ የመንግስት ድርጅቶች ያገለገሉ ፕ/ር መስፍን፣ ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ መስራቾች አንዱ ሲሆኑ፣ ለተለያዩ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማካሪ ሆነው ሲሰሩ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
የጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ የቀብር ሥነ-ስርዓት ዛሬ ይፈፀማል ተብሎ ይጠበቃል
በኬንያ በስደት ላይ ሳለ በጥቂት ቀናት ህመም ህይወቱ ያለፈው የጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ የቀብር ስነ ስርዓት በዛሬው እለት በትውልድ ሀገሩ ይርጋጨፌ ይፈፀማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተለያዩ የግል የህትመት ውጤቶች ላይ ለረጅም አመታት በጋዜጠኝነት ሙያ ሲሰራ የቆየውና “ማራኪ” የተሰኘ መፅሄት አሳታሚ የነበረው ጋዜጠኛ ሚሊዮን፤ ባደረበት ድንገተኛ ህመም ባለፈው ሰኞ ህይወቱ ያለፈ ሲሆን ትላንትና ምሽት አስከሬኑ አዲስ አበባ እንደሚገባና ይርጋጨፌ ወደሚገኙት ቤተሰቦቹ ተልኮ በዛሬው እለት የቀብር ሥነ ስርአቱ ይፈፀማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ታውቋል፡፡
ጋዜጠኛው ናይሮቢ ኬንያታ ሆስፒታል ለ15 ቀናት በህክምና ሲረዳ መቆየቱን የጠቆሙት ምንጮች፤ ሃኪሞች ታይፎይድና ከሆድ ውስጥ ደም መፍሰስ ጋር የተያያዘ ህመም አጋጥሞት እንደነበር መግለፃቸውን አመልክተዋል፡፡
የጋዜጠኛው ህይወት ካለፈ በኋላ በገንዘብ እጥረት ለ4 ቀናት በኬንያታ ሆስፒታል የአስክሬን ማቆያ ውስጥ መቀመጡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጋዜጠኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ አንተነህ አብርሃም፤ ሟች ሚሊዮን የማህበራቸው ግንባር ቀደም አባል ስለነበር በኃላፊነት ስሜት አስከሬኑን ወደ ሀገር ቤት ለማምጣት በተደረገው ጥረት ውስጥ መሳተፋቸውን፤ አስከሬኑን እንድታመጣም የሟችን እህት ከሌሎች ተባባሪዎች ጋር ሆነው ገንዘብ በማዋጣት ወደ ኬንያ መላካቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
አስከሬኑን ለማስመጣት በተደረገው ጥረት የገንዘብ እጥረት አጋጥሞ እንደነበር የጠቆሙት አቶ አንተነህ፤ ለሆስፒታል መከፈል የነበረበትን 1600 ዶላር የምስራቅ አፍሪካ የጋዜጠኞች ህብረት እና አርቲክል 19 ተባብረው መክፈላቸውንና አስፈላጊውን የመጓጓዣ ሰነድ በማስፈፀምም ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል፡፡
ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ ለረጅም አመታት ከቀድሞ “ኢትዮጵ” ጋዜጣ ጀምሮ በተለያዩ የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች ላይ ሲሰራ የቆየ ሲሆን ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ አገር ጥሎ እስከወጣበት ነሐሴ መጨረሻ ድረስ ”ማራኪ” የተሰኘች በማህበራዊና በኪነጥበባዊ ጉዳዮች ላይ የምታተኩር መፅሄት ያሳትም እንደነበር ይታወቃል፡፡
ጋዜጠኛው በ2005 ዓ.ም “ወሲባዊ ውስልትና (ዘ አዲስ አበባ)” የተሰኘ መፅሃፍ ፅፎ ለአንባቢያን አድርሷል፡፡
የ30 አመቱ ጋዜጠኛ ሚሊዮን፤ ከሀገር ከመሰደዱ በፊት ማተሚያ ቤቶች “ማራኪ” መፅሄትን አናትምም እንዳሉትና ገቢ ያገኝበት የነበረ ስራው በመቋረጡ በችግር ላይ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ገልፆ ነበር፡፡ ጋዜጠኛ ሚሊዮን የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበር፡፡
“በግፊት ወደ ስልጣን እንደመጣሁት በግፊት መውረድ አልፈልግም” - ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈውራ
የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር በመሆን ላለፉት 10 ወራት ያገለገሉት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው፤ ከተወሰኑ የዳያስፖራ የፓርቲው ድጋፊ ሰጪ አመራሮችና የካቢኔ አባላት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ከኃላፊነታቸው እንደለቀቁ ተናገሩ፡፡
ለዳያስፖራዎች ክብር እንዳላቸው የገለፁት ኢ/ር ግዛቸው፤ የተወሰኑ የዳያስፖራ የፓርቲው ድጋፍ ሰጪ አባላት አገር ውስጥ ባለው አመራር ጣልቃ በመግባት ማዘዝ እንደሚፈልጉ ጠቁመው ለፓርቲው የገንዘብ ድጋፍ ስለሚያደርጉ ብቻ ፓርቲውን የእነሱ ወኪል ለማድረግ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡
“መውረድ አለብህ ብለው ጥያቄ ማቅረባቸውን አልቃወምም፤ ነገር ግን ተቃውሞዋቸውን በተቋማዊ መንገድ ማቅረብ አለባቸው” የሚሉት ኢንጂነር ግዛቸው፤ “እዚህ ቦታ ሰላማዊ ሰልፍ አድርግ፣ እዚያ ቦታ ህዝባዊ ስብሰባ ጥራ እያሉ የሚያዙትን አልቀበልም” ብለዋል፡፡ “የሚሰጡትን ገንዘብ እንደ በጎ አድራጎት ማየት የለባቸውም፤ እንደ ግዴታ መውሰድ አለባቸው፤ እኔ ለእስርም ሆነ ለሞት ቅርብ እንደሆንኩት ሁሉ እነሱም ገንዘብ የማዋጣት ግዴታ አለባቸው እንጂ በገንዘብ እጅ ለመጠምዘዝ መሞከር የለባቸውም” ሲሉ ተናግረዋል - ኢንጂነሩ፡፡
“ግንኙነታቸውም ግለሰባዊ በመሆኑ ይህንን እቃወማለሁ” የሚሉት ኢንጂነሩ፤ እኔን ከስልጣን የማውረድ መብት ያለው ጠቅላላ ጉባኤው ቢሆንም አተካሮ ውስጥ ገብቼ ፓርቲውን ላለመጉዳት ስል በገዛ ፈቃዴ መልቀቁን መርጫለሁ ብለዋል፡፡ አክለውም “አንዷለም አራጌ ታስሮ አንተ እቤት ቁጭ የማለት ሞራል አለህ ወይ? በሚል ግፊት ወደ ስልጣን እንደመጣሁ በግፊት መውረድ አልፈልግም” ብለዋል፡፡
ከተወሰኑ የካቢኔ አባላት ጋር ያለመግባባት የተፈጠረው ከመኢአድ ጋር ለመዋሃድ በተደረገው ሙከራ መሆኑንም ኢ/ር ግዛቸው ገልፀዋል፡፡ ውህደቱ መኢአድ ውስጥ ባለ ችግር ምክንያት ሊሳካ አልቻለም ብለዋል፡፡
ለውጥ በህዝባዊ አመፅም ሆነ በትጥቅ ትግል ይመጣል ብለው እንደማያምኑ የገለፁት ኢንጅነሩ፤ በቀጣዩ ምርጫ ለመወዳደርም ሆነ ላለመወዳደር ገና እንዳልወሰኑ ተናግረዋል፡፡
‹‹...ጥሩ ቤተሰብ መፍጠር ...ጥሩ አለምን መፍጠር...››
ህጻናትን በፍቅርና በሰላም ማሳደግ የሚቻለው ይበልጡኑ ወላጆች ኃላፊነት የሚሰማቸው እና ጥሩ ምሳሌ ሲሆኑ ነው፡፡ ቤተሰብህን በተሸለ ደረጃ መምራት ማለት አለምን በተሸለ ደረጃ ለመምራት ዝግጁ መሆን ማለት ነው የሚለው የጠበብት ንግግር ተግባራዊ እንዲሆን ሁሉም ልብ ሊለው የሚገባ ነገር ነው፡፡ ወላጅ ልጅን በማስተናገዱ ረገድ እራሱን ሊጠይቅ ከሚገባቸወ ነገሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
* እኔ ወላጅ ከሆንኩኝ ልጄን በትክክል ለመርዳት የሚያስችል በቂ ጊዜ ሊኖረኝ ይገባል? ወይንስ በተጣበበ ጊዜ የማደርገው ነገር ትክክል ነው?
* ለመሆኑ ማድረግ የሚገባኝን እያደረግሁኝ ነውን?
* የትኛው ትምህርት ቤት ባስተምረው ጥሩ ይሆናል?
* ልጄን በሚያዝናና መንገድ እየረዳሁ ነውን? ወይንስ?
* በማደርገው ነገር ውስጤን በትክክል አምነዋለሁኝ? ወይንስ እየተጠራጠርኩ ነው?
የሚሉትንና ሌሎችንም ጥያቄዎች ለራስ በማቅረብ ልጆችን በተገቢው መንገድ ማሳደግ በሁሉም ወላጅ እና ቤተሰብ እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ላይ የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡
የኢፌዲሪ ህገመንግስት አንቀፅ 35 ማንኛውም አንድ ህፃን ሊኖረው የሚገቡ መብቶች ብሎ የሚከተሉትን በዝርዝር አስቀምጧል፡-
ሀ) በህይወት የመኖር፣
ለ) ስምና ዜግነት የማግኘት ፣
ሐ) ወላጆቹን ወይም በህግ የማሳደግ መብት ያላቸውን ሰዎች የማወቅና የእነሱንም እንክብካቤ የማግኘት፣
መ) ጉልበቱን ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ፣በትምህርቱ፣በጤናውና በደህንነቱ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ስራዎችን እንዲሰራ ያለመገደድ ወይም ከመስራት መጠበቅ፣
ሠ.. በትምህርት ቤቶች ወይም በህፃናት ማሳደጊያ ተቋሞች ውስጥ በአካሉ ከሚፈፀም ወይም ከጭካኔና ኢሰብአዊ ከሆነ ቅጣት ነፃ የመሆን፣ከላይ ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች መካከል ተራቁጥር (መ) እንዲሁም (ሠ) ህፃናትን ከተለያዩ አካላዊ ብሎም ስነልቦናዊ ጥቃቶች ለመከላከል ታስቦ የወጣ ነው፤እንደ ኢፌዲሪ ሴቶች ህፃናት እና ወጣቶች ሚንስ..ር አገልለፅ ለጥቃት ተጋላጭ ሆኑ የሚባሉት ህፃናት...
‹‹አስፈላጊው እንክብካቤ የማይደረግላቸው እንዲሁም ደህንነታቸው በተለያየ ምክንያት አደጋ ላይ የወደቀና ህገመንግስቱ የደነገገላቸውን መብት መጠቀም ያልቻሉ ህፃናት ናቸው›› children advocacy center የሚለው ሕጻናትን ተንከባክቦ በማሳደግ ረገድ ለዚህ እትም መረጃ ያደረግነው ጽሁፍ ሲጀምር ተከታዮቹን ነጥቦች ይዘረዝራል፡፡
* ከትዳር አጋራችን ጋር የሚኖረን ጥሩ ያልሆነ ግንኙነት፣
* የኢኮኖሚ ችግር ፣
* ከእፅ እና ከአልኮል ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲሁም፣
* በልጅነት ተከስቶ ያለፈ ጥቃት፣
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ለሚያደርሱት ጥቃት እንደ መንስኤ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የቱንም ያህል ልጃቸውን የሚወዱ ወላጆች እን..ን ቢሆኑ እንደችግር ለተጠቀሱት ነጥቦች ትእግስትን ወይንም መቻልን ያጣሉ፡፡ children advocacy center የህፃናት ጥቃትን ለመከለላከል የሚያስችሉ መንገዶች ብሎ ካስቀመጣቸው ሀያ ነጥቦች ውስጥ የተወሰኑትን ሀሳቦች እናስነብባችሁ፡
1/ጥሩ ምሳሌ ወይም አርአያ መሆን፣ ወላጆች ለሁሉም የቤተሰብ አባላት ተገቢውን ቦታ እና ክብር ሊሰጡ ይገባል፤ ልጆችን ትህትና በተሞላበት መንገድ ማነጋገር ተገቢ ነው፡ አግባብ ያልሆነ ምግባር ሲያሳዩም እነሱን ሳይሆን ድርጊታቸውን እንዳልወደዱት ከመንገር ባለፈ ፈፅሞ ልጆችን ለመምታት እንዳይሞክሩ ይመከራል፡፡፡
መምታት ወይም ሌሎች አካላዊ እርምጃዎችን መውሰድ ልጆች ሀይለኝነትን እንዲማሩ ያደርጋል፡፡ የተሳሳቱ መስሎ ተሰማዎት ይቅርታ ይጠይቁ ይህን በማድግዎ ለልጆ መልካም ባህሪን ያወርሳሉ፡፡
2/ልጅዎን ጓደኛ ማድረግ፣ልብ ይበሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ነገሮችን በቁጣ እና በንግግር ብቻ ማለፍ አለመግባባትን ለማቅለል ይረዳል፡፡ ልጆች የወላጆቻቸውን ደስታ እና ጥሩ ፊት ሲያዩ መልካም ምግባር ይኖራቸዋል ስለዚህ ከልጆችዎ ጋር መዝናናትን አሊያም የእግር ጉዞ ማድረግን ያዘውትሩ፡፡
ይህን መሰል ድርጊቶች ድካምን ለመቀነስ ብሎም ከልጆችዎ ጋር የሚኖርዎትን ግንኙነት ለማጠንከር አይነተኛ መንገድ ነው፡፡
3/ልጆችን ማመስገን ወይም ማበረታታት፣ መጥፎ ቃላት ልጆች ዋጋቢስ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ ጉዳቱም የእድሜ ልክ ነው፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ቀና ይሁኑ፡፡ ምን ያህል በእሱ/በእሷ ደሰተኛ እንደሆኑ እና በእርስዎ ዘንድ ያላቸውን ቦታ ለልጆቾ አዘውትረው ይንገሯቸው፡፡
4/እርምጃ መውሰድ ወይም ሌሎች እስኪጀምሩ አለመጠበቅ፣በስራ ቦታ እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች የህፃናት ጥቃትን በሚመለከት እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርብዎታል፡፡ ስለ ጉዳዩ ይበልጥ ባወቅን ቁጥር ድርጊቱን ለማቆም በይበልጥ እንተጋለን፡፡
5/በጎ ፈቃደኛ መሆን ፣ ጊዜዎን በህፃናት ጥበቃ እንዲሁም ለልጆች ድጋፍ የሚሰጡ ፕሮግራሞችን ለመደገፍ ያውሉት፡፡
6/ በህፃናት ማቆያ ማእከል ውስጥ ማገልገል፣ ጊዜዎን የተጎዱ እና ጥቃት የደረሰባቸው ህፃናትን ለሚንከባከብ ማእከል የበጎፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ያውሉት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ህፃናትን ከሚረዱ ማእከላት ጋር ህብረት በመፍጠር አብረው ይስሩ ፡፡
7/ ስለህፃናት ጥቃት እንዲሁም መከላከያ መንገዶቹ በቂ ግንዛቤ መያዝ፣
8/ ወላጆቻቸውን ላጡ ህፃናት ወላጅ መሆን ፣ ይህን ማድረግ ቀላል አይደለም ነገርግን አንድ ህፃን ደህንነቱ ሲጠበቅ የሚሰማውን ሲያዩ እርካታዎ ከፍያለ ነው፡፡
9/ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ እና በህፃናት ደህንነት ላይ ከሚሰሩ አካላት ጋር መስራት፣
10/ የትኞቹ ህፃናት በይበልጥ ለጥቃት ተጋላጭ እንደሆኑ መረዳት፣ ምንም እን..ን የህፃናት ጥቃት ዘር እና ባህል ሳይለይ በሁሉም ህብረተሰብ ክፍል የሚከሰት ቢሆንም አብዛኛዎቹ አካላዊ ጥቃቶች የሚከሰቱት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ባለቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ነው፡፡
የአእምሮ ህመም እንዲሁም የአካል ጉዳት ያለባቸው ታዳጊ ህፃናት ደግሞ ለድርጊቱ በይበልጥ ተጋላጭ ናቸው፡፡
11/ የጥቃቱን መገለጫዎች ለይቶ ማወቅ፣
በህፃናት ላይ የሚደርሱ አካላዊ እንዲሁም ፆታዊ ጥቃት መገለጫዎችን ለይቶ ማወቅ ድርጊቱን ለማወቅ በይበልጥ ይረዳል፡፡
12/ ለልጆች አስፈላጊ የሆኑ ስጦታዎችን አስቀድሞ ማዘጋጀት፣ ይህን ማድረግ ለልጆች ያለንን ፍቅርና እንክብካቤ ከመግለፅ አልፎ እነርሱን ለማሳደግ ምን ያህ እግጁ እንደሆንን ያሳያል፡፡
“አፈር ብላ” የግጥም መድበል ይመረቃል
በዳንኤል ቢሰጥ እቴቴ የተፃፉ ግጥሞች የተካተቱበት “አፈር ብላ” የተሰኘ የግጥም መድበል፤ ሰሞኑን ገበያ ላይ ውሏል፡፡ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሽሙጦችና ፍልስፍና ነክ ግጥሞች እንዲሁም አገራዊ ፉከራና ሽለላ ቀመስ ግጥሞች የተካተቱበት መፅሃፉ፤ ፈገግና ዘና የሚያደርጉ ርእሰ ጉዳዮችንም ይዳስሳል፡፡
በ100 ገፆች ተቀንብቦ የተዘጋጀው “አፈር ብላ” የግጥም መድበል፤ በ25 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ መፅሃፉ የፊታችን ሰኞ ከቀኑ 10፡30 ጀምሮ በሩሲያ የሳይንስና የባህል ማዕከል (ፑሽኪን አዳራሽ) ይመረቃል ተብሏል፡፡
“ዳነ” የጉራጊኛ ቪሲዲ ለገበያ ቀረበ
በጉራጊኛ ዘፈኑና በማራኪ ውዝዋዜው የሚታወቀው የድምፃዊ መላኩ ቢረዳ “ዳነ” የተሰኘ አዲስ የጉራጊኛ ቪሲዲ ሰሞኑን ለገበያ ቀርቧል፡፡ የ14 ዘፈኖችን ቪዲዮ ያካተተው ይኸው ስራ፤ አብዛኞቹ ግጥሞችና ዜማዎች በራሱ በድምፃዊው የተሰሩ ሲሆን ቅንብሩ በዘሪሁን ሳህለማሪያም፣ ያሬድ አስናቀ፣ አሸናፊ ከበደና በሰለሞን ኢብራሂም ነው የተሰራው፡፡
ድምፃዊው በቪሲዲው ውስጥ “ትግርኛ ምት በጉራጊኛ”፣ “አውዳመት አማርኛ በጉራጊኛ ስልት”፣ “ጐንደር በጉራጊኛ”፣ “ሱዳንኛ በጉራጊኛ” እና “ትዝታ በጉራጊኛ” የሚሉትን በማካተት ለየት ባለ ሁኔታ የቀረበ ሲሆን ከዚህ ቀደም “ትዊስት በጉራጊኛ” የተሰኘ ቪሲዲ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡ አዲሱ ቪሲዲ በዚያዳ ሪከርድስ ታትሞ እየተከፋፈለ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ድምፃዊ መላኩ ቢረዳ በአሁኑ ሰዓት በዮድ አቢሲኒያ የባህል ምግብ ቤት አዳራሽ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ሚስቴን ቀሙኝ” ፊልም ነገ ይመረቃል
በደራሲና አዘጋጅ ሙሉዓለም ጌታቸው ተሰናድቶ፣ በበርሄ ገ/መድህን ፕሮዱዩስ የተደረገው “ሚስቴን ቀሙኝ” የተሰኘ ኮሜዲ የፍቅር ፊልም፤ ነገ በመላ አገሪቱ በሚገኙ የግል ሲኒማ ቤቶች እንደሚመረቅ ፕሮዱዩሰሩ አቶ በርሄ ገ/መድህን ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
በሜርሲ መልቲ ሚዲያ ፕሮዳክሽን ለእይታ የሚቀርበውን ይሄን ፊልም ሰርቶ ለማጠናቀቅ አንድ አመት እንደፈጀ የገለፁት ፕሮዱዩሰሩ፤ ከ600 ሺህ ብር በላይ እንደወጣበትና የ1ሰዓት ከ42 ደቂቃ ርዝማኔ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
በፊልሙ ላይ ዮሐንስ ተፈራ (ዳረማኛ)፣ ቃልኪዳን ጥበቡ፣ ሰገን ይፍጠር፣ ካሳሁን ፍሰሃ (ማንዴላ)፣ አስራት ታደሰ፣ ፋንቱ ማንዶዬ፣ እንዳልካቸው ሰበታና ሌሎችም ወጣትና አንጋፋ ተዋንያን ተሳትፈውበታል ተብሏል፡፡
የፍቅር ጥግ
ሚስት ያላገባ ወንድ፣ አበባ አልባ የአበባ ማስቀመጫ እንደማለት ነው፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
የሚስትህን የልደት ቀን ለማስታወስ ትክክለኛው መንገድ አንድ ጊዜ መርሳት ነው፡፡
- ኤች.ቪ. ፕሮንችኖው
ፍቅር እውር ነው፤ ትዳር ግን የብርሃን ፀጋውን መልሶ ያጐናፅፈዋል፡፡
ሳሙኤል ሊችቴንበርግ
ትዳር፤ ከጠላትህ ጋር አንድ አልጋ የምትጋራበት ብቸኛው ጦርነት ነው፡፡
ፍራንሶይስ
ብዙ ቤተሰብ ባለበት ቤት ውስጥ ነው ያደግሁት፡፡ እውነት ለመናገር ሚስት እስካገባ ድረስ ብቻዬን ተኝቼ አላውቅም፡፡
ልዊስ ግሪዛርድ
ባል ማግባቴን እወደዋለሁ፡፡ በቀሪው ህይወታችሁ ልታበሽቁት የምትፈልጉት አንድ የራሳችሁ ሰው ማግኘት ድንቅ ነው፡፡
ሪታ ሩድነር
ትዳር እስከምይዝ በፍፁም በፍቺ አምኜ አላውቅም፡፡
ዲያኔ ፎርድ
ብቸኛ ለመሆን እርግጠኛው መንገድ ትዳር መያዝ ነው፡፡
ኖራ ኢፍሮን
ማንኛውም ያገባ ወንድ ስህተቶቹን መርሳት አለበት - ሁለት ሰዎች ተመሳሳይ ነገር ማስታወሳቸው ምንም ፋይዳ የለውም፡፡
ዱዌኔ ዴዌል
ትዳር ሌሊት ብቻቸውን መተኛት ለሚፈሩ ሰዎች ጥሩ ነው፡፡
ሴይንት ጄሮሜ
ከፍቅር የምንወደው ትኩሳቱን ነው፤ ትዳር ደግሞ አልጋ ላይ ያስተኛውና ይፈውሰዋል፡፡
ሚኞን ማክላውግሊን
ማራኪ አንቀፅ
በበረራ መማረክ የጀመርኩት ልጆች ሳለን አባቴ፣ እኔና እህቶቼን ወደ አየር ማረፊያ እየወሰደ አውሮፕላን ሲያርፍና ሲነሳ ያሳየን በነበረበት ወቅት ነው፡፡ አባቴ አውሮፕላኑን የሚያሳየን የአብራሪነት ፍላጎት እንዲቀሰቀስብን አስቦ አይመስለኝም፡፡ በእኔ ልብ ውስጥ የአብራሪነት ፍላጎት ያደረገው ግን በዚያ ጊዜ ነበር፡፡ ግዙፎቹ አውሮፕላኖች ሰማዩን እየሰነጠቁ ሲከንፉ በደስታ ተጥለቅልቀን መመልከታችን፣ አባታችንን ሳይከነክነው እንደማይቀር አስባለሁ፡፡ አባታችን ሁላችንም እንደየፍላጎታችን እንድንጓዝ ከማበረታታት ችላ ያለበት ጊዜ ባይኖርም፤ ያ የየሳምንቱ የአየር ማረፊያው ጉብኝታችን፣ እንዴት የበኩር ልጁ የእድሜ ልክ ሕይወትና ሙያ ሊሆን እንደቻለ አሁንም ድረስ ይገርመዋል፡፡ የተወለድኩት በ1969 ዓ.ም ባህርዳር ከተማ ነበር፡፡ አራት ልጆች ላፈሩት ወላጆቼ፤ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፡፡ ደህና ገቢ የነበራቸውን ወላጆቼን በአርአያነት እየተመለከትኩ ነው ያደግሁት፡፡ አባትና እናቴ በራሴ እንድተማመንና ህልሜን ለማሳካት እንድጣጣር ያበረታቱኝ ነበር፡፡ “ሴት በመሆንሽ ገደብሽ እዚህ ድረስ ነው” ብለውኝ አያውቁም፡፡ ያደግሁበት ማህበረሰብም፣ ለዛሬው ማንነቴ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ የአካባቢያችን ሰው ሁሉ እንደራሱ ልጅ ነበር የሚያየኝ፡፡ የእለት ተዕለት እድገቴን ከመከታተልም ባሻገር በትምህርቴ በርትቼ እንድገፋ ያበረታቱኝ ነበር፡፡
አብራሪ የመሆን ፍላጎቴን ሁሉም ያውቁ ስለነበር የማያደንቀኝ አልነበረም፡፡ ዘጠነኛ ክፍል ሳለሁ፣ ሁለት ታንዛኒያውያን (አንድ ወንድና አንድ ሴት) የበረራ ሰልጣኞች እኛ ሰፈር ይኖሩ ነበር፡፡ እናም በዩኒፎርማቸው ተማርኬ ፈዝዤ እመለከታቸው እንደነበር አስታውሳለሁ፡
የሶስት ዓመት ልጅ ሳለሁ፣ ቤተሰቦቼ ወደ አዲስ አበባ ስለመጡ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን በአሳይ የህዝብ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ በቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታተልኩ፡፡ በ1987 ዓ.ም ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ገብቼ፣ ሥነ-ህንፃ (አርኪቴክቸር) መማር ጀመርኩ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የልጅነት ህልሜን አልዘነጋሁትም ነበር፡፡ የአንደኛ ዓመት ተማሪ ሳለሁ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአብራሪዎች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የመግቢያ ፈተናን ወስጄ ነበር፡፡ አብዛኞቹ ተፈታኞች በመጀመርያ ሙከራቸው ይወድቁ ነበር፡፡ እኔም ሳላልፍ ቀረሁ፡፡ በእርግጥ በመግቢያ ፈተናው መውደቄ ተስፋ አለመቁረጥንና የበለጠ መጣርን አስተምሮኛል፡፡ የሥነ - ህንፃ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለሁ የመግቢያ ፈተናውን በድጋሚ ወሰድኩና አለፍኩ፡፡ ክፋቱ ግን አስቸጋሪ ሰዓት ላይ ሆነብኝ፡፡ የበረራ ሥልጠናው በሚጀመርበት በመጋቢት ወር 1992 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ነበር፡፡ እናም ለዓመታት የለፋሁበትን ትምህርት ገደል እንደመክተት ሆነብኝ፡፡ የማታ ማታ ግን በሐምሌ 1992 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደተመረቅሁ ሥልጠናውን እንድጀምር ተፈቀደልኝ፡፡
ከሁለት ዓመት በላይ የወሰደውን ሥልጠና አጠናቅቄ በአብራሪነት የተመረቅሁት በህዳር 1994 ዓ.ም ሲሆን ለቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት ተኩል በዘለቀው የሥራ ዘመኔም በረዳት አብራሪነት ለ4ሺ475 ሰዓታት አብርሬያለሁ፡፡ ከዚም ከተለያዩ ፈተናዎች፣ ምዘናዎችና ግምገማዎች በኋላ፣ እድገት ተሰጥቶኝ በዋና አብራሪነት (የካፒቴን) ሥልጠና ጀመርኩኝ፡፡ አስፈላጊውን የክህሎት ማጎልበቻ ሥልጠና እንዳጠናቀቅሁም ከመጀመሪያ በረራዬ ከሰባት ዓመት ተኩል በኋላ በ2002 ዓ.ም ካፒቴን ሆንኩኝ፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ከአንድ ሺ በላይ ሰዓታት አብርሬአለሁ፡፡ ..................
(“ተምሳሌት፡ ዕፁብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች” ከተሰኘው አዲስ መፅሃፍ ላይ የተቀነጨበ፤ 2007 ዓ.ም)