Administrator

Administrator

Saturday, 15 March 2014 13:01

አብረን ያደርን ቀን

ሰው እንዴት ተታሏል…
   ምስራቅ ምትገኝ
   ከምዕራብ በስተቀኝ
   ሰማይ ላይ ነዉ ብሎ
   ጀንበርን ሰቅሏታል አድማስ ላይ ጠቅሎ፤
ግን እንዲህ አይርቁም አይደሉም ሰማይ ላይ
     ምስራቅም በከንፈር በጥርስ አምሳል ፀሀይ
     እኔ ቤት አድረዋል ጠባብ መደቤ ላይ፡፡
* * *
    አዝናለሁ ያዳም ዘር
        ብርሃን ካልቀላወጥክ በጉበኔ ተገን
                   አ-ታ-ያ-ት-ም   ነገን !!

ፍርቱና
ስንገናኝ…
ያርባ ቀን እድሌ ያርባ ቀን እድሉ
በቀለበት ታስረው ሰማንያ ተባሉ፤
ስንለያይ…
ሰማንያዉ ተቀዶ
ለሁለት ተጎርዶ
እኔ አርባዬን ይዤ ዳግም እናቴ ጋ
እሱ አርባዉን ይዞ ሌላ አርባ ፍለጋ፡፡
አበባ የሽጥላ
   

በኤርትራውያን ታጣቂዎች የተጠለፉትን ጀርመናውያን ያስመለሱ የአፋር  ሽማግሌዎች ምን ይላሉ?

         ከሁለት አመት በፊት ነው ድርጊቱ የተፈፀመው። በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች አንዱ ወደ ሆነው ኢርታአሌ ይጓዙ የነበሩ ጀርመናውያን ቱሪስቶች ከኤርትራ ድንበር አቋርጠው በመጡ ታጣቂዎች ሲጠለፉ ሁለት ኢትዮጵያውያን ተገደሉ፡፡ ከመካከላቸው ማምለጥ የቻለው አንድ ኢትዮጵያዊ፣ በአቅራቢያ ወደ ምትገኘው የአፍዴራ ቀበሌ ኩሩርዋድ መንደር በመምጣት የተፈጠረውን ሁኔታ ለአካባቢው ነዋሪዎች ተናገረ፡፡ የመንደሯ ሽማግሌዎችም በኤርትራ ከሚገኙ የአፋር ባላባቶች ጋር በመደራደር፣ ጀርመናውያኑ በህይወት እንዲመለሱ አደረጉ፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኘው የጀርመን ኤምባሲም ባለፈው ሳምንት የመንደሯ ሽማግሌዎች ጀርመናውያኑን በማስመለስ ላደረጉት ውለታ ምስጋና ያቀረበ ሲሆን ከትግራይ ደጋማ አካባቢዎች በመነሳት በአለት ውስጥ ለውስጥ ይሄድ የነበረን የዝናብ ውሀ አቅጣጫ በማስቀየር፣ ለህብረተሰቡ ጥቅም እንዲሰጥ ያሰራውን ፕሮጀክት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ኢዝሎር ሲሩስ በተገኙበት አስረክቧል፡፡
በኤርትራ ታጣቂዎች ተወስደው የነበሩትን ጀርመናውያን በማስመለስ ትልቅ ሚና የተጫወቱት ጊልሳ ያኢድ እና ሳልህ ኡስማን ሁኔታውን አስመልክቶ የተናገሩትን እንደሚከተለው በአጭሩ አቅርበነዋል፡፡
ቱሪስቶች ኢርታአሌን ለማየት ሲሄዱ ከአፍዴራ የሚያጅቧቸው ሁለት ሚሊሺያዎች እና አንደ መንገድ መሪ ይመደባል፡፡ ከኤርትራ የመጡት ሽፍቶች ሁለቱን ጀርመናውያን ጠልፈው ሲወስዱ ሁለት ኢትዮጵያውያንን ገድለው ነው፡፡ አንዱ ኢትዮጵያዊ ስላመለጠ ሁኔታውን መጥቶ ነገረን። በአፋር ባህል እኛን ብሎ የመጣ ሰው፣ እኛ መሬት ላይ መግደል ወይም ሲገደል ማየት ትልቅ ነውር ነው፡፡ ቱሪስቶቹ ምንም አይነት መሳሪያ አልያዙም። የውሀ ጥማቸውን ለመቁረጥ የላስቲክ ውሀ ብቻ ነበር የያዙት፡፡ ድርጊቱን እንደ ሰማን የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ሀይል፣ ፖሊስ እንዲሁም  ሴቶች እና ህፃናት ሳይቀሩ ወደ ስፍራው ሶስት ቀን ተጉዘን ደረስን፡፡ ቦታው ከፍተኛ የውሀ እጥረት ያለበት ስለሆነ ግመሎቻችንን ውሀ ጭነን ነበር የሄድነው። ሴቶቹ እና ህፃናቱ ምግብና  ውሀ ለማቅረብ ነው ተከትለውን የመጡት፡፡ የሄድነው እጅግ ተቆጥተን ነበር፡፡ ብንሞትም እንሙት እንጂ እኛን ብለው የመጡ የውጪ ሰዎችን አፍነው መውሰዳቸውና ሚሊሺያዎቹንም መግደላቸው እጅግ አስቆጭቶናል። አርታአሌን  በቁጥጥር ስር ካዋልን በኋላ የተወሰኑት የተገደሉትን ሰዎች አስከሬን ጭነው ወደ አፍዴራ ሲመለሱ፣ እኛ በባህላዊው የአፋር የመረጃ መቀባበያ ዘዴ “ዳጉ” መሰረት መረጃ ማሰባሰብ ጀመርን፡፡ በኤርትራም ሆነ በኢትዮጵያ የሚኖረው አፋር  በጎሳ የተሳሰረ ነው፡፡ ማንም የታጠቀ ሀይል ይሁን ሽፍታ ከጎሳው ባላባቶች ትእዛዝ አይወጣም፡፡  አስራ ሁለቱ  የባላባት ልጆች ተሰባስበው መከሩ፡፡ ከአገር ውጪ ያሉ የባላባት ልጆችም የታገቱትን ሰዎች እንዲያስለቅቁ ጥሪ ቀርቦ መላላኩ ተጀመረ፡፡ ኤርትራ ለሚገኙት ባላባቶች ሰዎቻችን ለምን ተገደሉ? ተጠልፈው የተወሰዱት በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንዲነግሩንና አሳልፈው እንዲሰጡን ጠየቅናቸው፡፡ ባላባቶቹም በጥያቄያችን መሰረት የተጠለፉት ሰዎች እንዲመለሱ ተነጋገሩ። የባላባት ትእዛዝ የማያከብር ማንኛውም አፋር፣ የአፋር ዘር ያለበት ቦታ ላይ መኖር አይችልም። ታጣቂዎቹም ቢሆኑ የባላባቶችን ትእዛዝ ከጣሱ ማረፊያ ስለማይኖራቸው፣ የጠለፏቸውን ሰዎች ለመመለስ በተደረገው ድርድር ተስማሙ፡፡ የመንግስት አካላት በህገ መንግስት ላይ የሰፈሩ ድንጋጌዎችን እንደሚያከብሩ ሁሉ ሽፍቶችም ቢሆኑ የጎሳ ስርአቱንና ውሳኔውን ያከብራሉ፡፡  እኛም ድንበሩን ተሻግረን የተጠለፉትን ሰዎች ለመረከብ ኤርትራ ገባን፡፡ በኤርትራ ከሚኖሩ የአፋር ጎሳዎች አንዱ የሆነው የዳሂሜና ጎሳ ልጅ ሰዎቹን ይዞልን መጣ፡፡  እኛም ለሁለቱ አንዳንድ ግመል ሰጥተን፣ ውሀ የጫነችላቸውን አንድ ግመል አስከትለን ወደ መንደራችን ስንወስዳቸው፣ አጠገባቸው የነበሩት ሰዎች በጭካኔ ተገድለው፣ እነሱ በህይወት መመለሳቸው ደስታና ግራ መጋባት ውስጥ ከተታቸው፡፡ ደስታቸው ግን ወሰን አልነበረው፡፡
በኤርትራ ያሉ ታጣቂዎች እኛ ከቱሪስቶቹ በምናገኘው ጥቅም ደስተኞች ባለመሆናቸው በጣም እናዝናለን፡፡ እኛ ግን ማንም ቢሆን በኛ መሬት እንግዳ ሆኖ እስከመጣ ድረስ የደህንነቱን ጉዳይ በሀላፊነት መውሰድ ባህላዊ ግዴታችን ነው። ፈረንጆቹ እሳቱን ለመጎብኘት  ሲመጡ የግመል ኪራይ፣የአጃቢ፣ የመንገድ መሪ --- እየተባለ ስለሚከፈለን ብዙ ጥቅሞችን እናገኛለን፡፡ ከዛን ቀን በኋላም  ለቱሪስቶቹ የበለጠ ጥበቃ ማድረግ ጀመርን። አሁን በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ ከአስር በላይ የጎብኚ  ቡድን  ይሄዳል፡፡  ሁሉም በሰላም ደርሶ እየተመለሰ ነው። ከሁለት አመት በፊት ጠለፋውን የፈፀሙት ሰዎች ስላልተያዙም ልዩ የፀጥታ  ሀይል እስከአሁን ጠለፋው የተደረገበት ቦታ ላይ ይገኛል፡፡


የታክሲ---የዳቦ---የውሃ---የግብር---የቦሎ---ረዣዥም ሠልፎች----

  • የማሌዢያው አውሮፕላን ኢትዮጵያ ውስጥ አልወደቀም ተባለ!
  • “መሬት የግል ይሁን” የዘመኑ “መሬት ላራሹ” ነው እንዴ?


       እኔ የምላችሁ … “አንድነት” ፓርቲ ባለፈው ሳምንት “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” የተሰኘውን ቁጥር 2 ንቅናቄ መጀመሩን ሰምታችሁልኛል?! አይዟችሁ … ብትሰሙም ችግር የለውም፡፡ ይሄኛው “ሽብር” ምናምን የሚል ነገር የለውም (“መሬት የግል ይሁን” ማለት ሽብር ነው እንዴ?) እናላችሁ … የአሁኑ አጀንዳዬ መሬት ነው ብሏል፤ ፓርቲው፡፡ አዎ! መሬት የግል ይሁን እያለ ነው- አንድነት፡፡ (ማን ነበር “ድርሻዬን” እያለ ያቀነቀነው?) እንደምታውቁት … ባለፈው ዓመት ፓርቲው ያደረገው ንቅናቄ፣ ለእኔ ቢጤ “አንድ ለእናቱ” ትንሽ ያስቦካ ነበር፡፡ በሚሊዮኖች ድምፅ “የፀረ-ሽብር አዋጁን አሰርዛለሁ” አይደል ያለው፤ አንድነት፡፡ ኢህአዴግ ያኔ በልቡ “On my dead body!” (ሞቻታለኋ!) ያለ አይመስላችሁም?
 እውነት ግን ፓርቲው 1ሚ. ፊርማ አሰባስቧል ማለት ነው? ለነገሩ አንድነት ፓርቲ 1ሚ. ደጋፊ ያጣል ማለት ዘበት ነው፡፡ ፓርቲው ምንም አልተንቀሳቀሰም ቢባል እንኳ ኢህአዴግ አለለት! ከምሬ እኮ ነው … አውራው ፓርቲ በየሰበቡ የሚያስቀይማቸው ሰዎች፤ አንድም ባህርማዶ አሊያም እንደ አንድነት ያሉ ተቃዋሚዎችን መቀላቀላቸው አይቀርም (ጠላት በማብዛት ኢህአዴግ አቻ የለውም!) እኔ የምላችሁ … የኢህአዴግ አባላት ቁጥር ስንት ሆነ?  ወይስ እንደ ኢኮኖሚ ዕድገቱ አሁንም እየገሰገሰ ነው፡፡ በነገራችሁ ላይ … ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ የምትሰለፍበት ጊዜ ትንሽ ቀረብ ሳይል አይቀርም (30 እና 40 ዓመት አይፈጅም ማለቴ ነው!) አንድ ወዳጄ ደስ ይለዋል ብዬ ይሄን የምስራች ብነግረው ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ? “እሰይ፤ ኢህአዴግ ተጨማሪ 30 እና 40 ዓመት ስልጣን አያስፈልገውም!” ብሎኝ ቁጭ አለ! እውነቱን ልንገራችሁ አይደል … ስለ ስልጣን ቀን ተሌት የሚያስበው ሥልጣን ላይ የተቀመጠ  ብቻ ነበር የሚመስለኝ፡፡ ለካስ እንደ እኔ ወዳጅ ያለውም ስለ ስልጣን ያስባል፡፡ (“ወንበሩ እንደሆነ አንድ ነው” ያሉት የቀድሞው መሪ ትዝ አሉኝ!)
ወደ አንድነት “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” ንቅናቄ ቁጥር 2 ልመልሳችሁ፡፡ እንዳልኳችሁ … የአሁኗ ጥያቄ ወይም ንቅናቄ በመሬት ዙሪያ የምታጠነጥን ናት፡፡ በሌላ አነጋገር “የየግላችን መሬት ይሰጠን!” የምትል ቀጭን ጥያቄ፣ ወይም ትግል ናት፡፡ (የዘመኑ “መሬት ላራሹ”!) በእርግጥ “መሬት የግል ይሁን” የሚለው ጥያቄ፣ የኒዮሊበራሊዝም ጠረን እንዳለው ከሩቅ ያስታውቃል፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት መፈልፈያም ሳይሆን አይቀርም (በግምት ነው!) እናም ለኢህአዴግ አይመቸው ይሆናል (ሁሌ አይደላም አሉ!) ሌላው መካድ የሌለብን ግን ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ የገበሬ .. የጭቁን ህዝብ .. የአርሶአደር-- ፓርቲ ነው፤ ከስር መሰረቱ ማለቴ ነው፡፡ (አሁንማ ኪራይ ሰብሳቢዎች ተደባለቁበት!) እናላችሁ … ኢህአዴግ መሬት የግል እንዳይሆን የሚፈልገው አንዳንዶች እንደሚሉት፤ የጥንት የጠዋቱ የአልባንያ ፅንፈኛ ኮሙኒዝም ትዝ ብሎት ሳይሆን ቆሜለታለሁ ለሚለው አርሶ አደር አስቦ ነው። “መሬት የመንግሥት ይሁን ያልኩት ገበሬው እንዳይሸጠው ብዬ ነው” ይላል-ኢህአዴግ (ገበሬ “ዱርዬ” መሰለው እንዴ?) አንድነት ፓርቲ ይሄኔ ምን ይላል መሰላችሁ? (“ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል!”) “መሬት በመንግሥት እጅ ይሁን ያልኩት ገበሬው ስለሚሸጠው ነው ይበል እንጂ አሁን እሱ እራሱ ለውጭ ባለሃብቶች እየቸበቸበው ነው” ሲል ይተቻል አንድነት - አውራ ፓርቲውን፡፡
እዚህ ጋ ግን አንድነት ያላስተዋለው ጉዳይ ያለ ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ መጀመርያውኑም ገበሬውን መሬት ከመሸጥ ለመከላከል ሞከረ እንጂ እኔ ራሴ “መሬት አልሸጥም! ሃራም ነው!” አላለም እኮ! በነገራችሁ ላይ በአሁኑ የአንድነት የመሬት ጥያቄ ወይም ንቅናቄ ላይ አንዳንድ ኢህአዴጎች ቢሳተፉ እንዳይገርማችሁ፡፡ (የመሬት ሱስ እንደሃሺሽ ነው!) ለምን መሰላችሁ? ነገርዬዋ እኮ የድርሻ ጥያቄ ናት! ስንቱ የኢህአዴግ ሹማምንት በ“መሬት ወረራ” ዘብጥያ መውረዱንም እንዳትዘነጉብኝ፡፡ (የባለሥልጣናት ሃብት በኢንተርኔት ሊለቀቅ ነው የተባለው እውነት ይሆን?) እናላችሁ ---- “ሲሶም ብትሆንም የግሉን  መሬት ቢያገኝ የሚጠላ የለም፡፡” ይላሉ የኒዮሊበራል ተንታኞች አሉ፡፡ (የመንግሥትም ሆኖ እኮ አልማሩትም!) እኔ የምለው--- መሬት “የመንግሥትና የህዝብ ነው” የተባለው ተቀየረ እንዴ? (መንግሥት ሳይጠቀልለው አልቀረም!) እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ ---- የ60ዎቹ ተማሪዎች የ“መሬት ላራሹ” ጥያቄ ሲያነሱ “መሬት የህዝብና የመንግሥት ይሁን” ማለታቸው ነበር እንዴ? (ታዲያ ኢህአዴግ ከየት አመጣው?)
ይሄን ሁሉ ስለፈልፍ መሬት አቅሌን አስቶኝ እንዳይመስላችሁ፡፡ የነገው የአንድነት ንቅናቄ ላይ ይገኛል ብላችሁም እንዳትጠብቁ፡፡ ወዳጆቼ፤ እኔ ሰፊ የጋዜጣ አምድ እንጂ ሰፊ መሬት ፈላጊ አይደለሁም (መሬት ላይ ይፃፋል እንዴ?) እናላችሁ … የመሬት ጉዳይ ሆኖብኝ ዝም ብዬ ብለፈልፍም ላነሳ የፈለግሁት ጉዳይ ግን ሌላ ነበር (“ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” አሉ!)
ምን መሰላችሁ የፈለግሁት? ተማፅዕኖ ነዉ - ለተቃዋሚ ፓርቲዎች በሙሉ!! (ተማፅኖቱን ያለማንገራገር ይቀበሉ ዘንድ እማፀናቸዋለሁ!) እናላችሁ----የፈለገ አፈናና ወከባ ቢደርስባቸው፣ የፈለገ ቢታሰሩና መብታቸው ቢጣስ … ሌላ መንገድ ይፈልጉ እንጂ የተቃውሞ ሰልፍ እንዳይጠሩን (የድጋፍም ቢሆን ማለቴ ነው!) በክፋት እኮ አይደለም!! ችግር ስላለ ነው፡፡ በነገራችሁ ላይ አንድነት ፓርቲ በዚህ በሁለተኛ ንቅናቄው፣ ህዝባዊ ስብሰባ እንጂ ሰልፍ ባለመጥራቱ በግሌም እንደ ህዝብም አድንቄዋለሁ (“የልብ አውቃ” አሉ!) “መንግሥት ስብሰባውን ለማደናቀፍ ከሞከረ ግን ወደ ሰላማዊ ሰልፍ እቀይረዋለሁ” ማለቱን ግን አልወደድኩለትም፡፡ እናም ሌላ አማራጭ ቢያስብ ደስ ይለኛል፡፡
ከምሬ ነው----“የእድገት ምስቅልቅሉ” እስኪያልፍልን ድረስ… የተቃውሞ ሰልፍ (የድጋፍም ቢሆን!) እንዳትጠሩን--- አደራ እላችኋለሁ! መቼም እስካሁንም ምክንያቴ ይገባችኋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይኸውላችሁ … ሰልፍ አትጥሩን የምለው በሌላ ሳይሆን ኑሮአችን ራሱ ሰልፍ ስለሆነብን ነው፡፡ ለታክሲ መሰለፍ ከጀመርን ስንት ዓመት ሆነን? (ያውም ጠዋት ማታ!) የዳቦ ሰልፍስ? ብጫ ጀሪካል እየያዙ በየሰፈሩ  ለውሃ መሰለፉስ? (“የቦቴ ውሃ” የተባለው እንደ ኔትዎርኩ ጠፋ እንዴ?) የመብራት ቅድመ ክፍያ ካርድም የሚገዛው በብር ብቻ አይደለም - በሰልፍም ነው!! በነገራችሁ ላይ ---- ኢህአዴግ ስራውን ስለሚያውቅ ሰልፍ መጥራት ትቷል! እንዴ ----- ኑሮአችንን ሰልፍ አድርጎታል እኮ!! ባይገርማችሁ----የመጪው ዓመት ምርጫ ካሁኑ ስጋት ሆኖብኛል (ምርጫም እኮ በሰልፍ ነው!)
እኔ የምለው … እንዲህ መሰለፋችን ካልቀረ ግን ለምን ይሄን የሰልፍ ገድላችንን ጊነስ ቡክ ላይ አናስመዘግበውም?! (ፈረንጅ እኮ እንግዳ ነገር ይወዳል!) እርግጠኛ ነኝ ---- ለተከታታይ ዓመታት እንደኛ የተሰለፈ የዓለም ህዝብ የለም፡፡ እናም ከዓለም አንደኝነቱን የሚቀናቀነን አይኖርም፡፡ (ይሄን ለማስመዝገብም ወረፋ አለው እንዴ!!)
 የሰሞኗን ምርጥ ኩምክና ነግሬአችሁ ልሰናበት፡፡ ይሄ የገባበት ያልታወቀው 200 ተሳፋሪዎችን የያዘ  የማሌዢያ አውሮፕላን ነው የቀልዱ ምንጭ፡፡ እናላችሁ … “አውሮፕላኑ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ አልወደቀም!” እየተባለ በእርግጠኝነት ሲወራ ነው የሰነበተው፡፡ “እንዴት ተረጋገጠ?” አትሉም
 “ወደ አውሮፕላን ተሳፋሪዎቹ ሞባይል ሲደወል ይጠራል!”
 አያችሁልኝ ---- ኢትዮጵያ ውስጥ ቢወድቅ ኖሮ አይጠራም ነበር ለማለት እኮ ነው!! (አይ ቴሌና ኔትወርክ!)
አንድ የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን “ቴሌ በዝባዥ ነው!” መባሉ ቆጭቷቸው ነው መሰለኝ “ቴሌ አትራፊ እንጂ በዝባዥ አይደለም!” የሚል ማስተባበያ እንደሰጡ ሰማሁ፡፡ ግን  “አገልግሎት ሳይሰጥ ገንዘብ የሚወስድ ምን ይባላል?” (አትራፊ ሊሆን አይችልም!)

ማርች 8 አለማቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ በተካሄደው የሴቶች የጎዳና ላይ ሩጫ ‹‹አንዳንድ ያልተገቡ ድርጊቶች ፈፅማችኋል›› በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉ አስር ከፍተኛ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት ትላንት ፍ/ቤት ቀርበው ፖሊስ አራት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ጠየቀባቸው፡፡
በቁጥጥር ስር የዋሉት 7 ሴቶችና 3 ወንዶች የፓርቲው አባላት በጎዳና ላይ ሩጫ ‹‹አንዷለም ይፈታ፣ ርዕዮት ትፈታ፣ ውሃ ናፈቀን፣ መብራት ናፈቀን›› የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ ነበር ተብሏል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በከፍተኛ የአመራር ቦታ ላይ ያሉና ቋሚ አድራሻ ያላቸው እንደሆኑ በመግለፅ በዋስ እንዲፈቱ ቢጠይቁም ፖሊስ በበኩሉ፤ ወንጀሉ ውስብስብ በመሆኑ አራት ተጨማሪ ቀናት የምርመራ ጊዜ ያስፈልገኛል ሲል አመልክቷል፡፡
ፍ/ቤቱም የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና መብት በመከልከል ለትናንትና ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡ ትላንት ፍርድ ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ላይ ፖሊስ ተጨማሪ አራት ቀን ምርመራ ጊዜ ጠይቆ ፍ/ቤቱም ለመጭው ማክሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

መጽሐፉ ለአቡነ ማትያስና ለጠ/ሚ ኃይለማርያም እንዲደርሳቸው ተደርጓል
ደብዳቤው ለእስራኤሉ ጠ/ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታናሁ እና ለተመድ ተልኳል

       ከተፃፈ ከ2 ሺህ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል የተባለውንና ስለ ቅዱስ ኤልያስ መምጣት ምስጢር የሚተነትነውን መጽሐፍ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተቀብላ ወደተለያዩ ቋንቋዎች በማስተርጎም ምዕመናኖችን እንድታስተምር፣ “ማህበረ ሥላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ” ለቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በጻፈው ደብዳቤ ጠየቀ፡፡
ማህበሩ፤የመጽሐፉን ኮፒዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ እና ለብፁዕ አቡነ ማትያስ  ህዝቡን እንዲያስተምሩበት ከሚያሳስብ ደብዳቤ ጋር መላኩን አስታውቋል፡፡
አርቲስት ጀማነሽ ሰለሞን አባል የሆነችበት ማህበረ ሥላሴ፤“ቅድስት ቤተ-ክርስቲያን ለሁለት ሺህ ዘመን ስትጠብቀው የቆየችውን ምስጢራዊ መጽሐፍ በአደራ የመረከብና ለዓለም ሁሉ የማሳወቅ ፅኑ ኃላፊነትን ይመለከታል” በሚል ርዕስ ለፓትርያርኩ፣ በግልባጭ ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዲሁም ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔትናሁ እና ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት በፃፈው  ደብዳቤ “ማህፈድ ብርህት ዘዲዮስቆሮስ አንበሳ” በሚል ርዕስ በግዕዝ ቋንቋ የተፃፈውን መጽሀፍ፣ የቤተ-ክርስቲያኗ ሊቃውንት ተቀብለው ምእመናኑን ስለ ቅዱስ ኤልያስ እና ትክክለኛይቱ ሰንበት እንዲያስተምሩበት አሳስቧል፡፡
ደብዳቤው ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የተላከው ኢትዮጵያና እስራኤል በመንፈሣዊ አሰራር አንድ ስለሚሆኑበት ሁኔታ ለማመልከት ነው ያሉት የማህበሩ አመራሮች፤ለተባበሩት መንግሥታት የተላከውም መልእክቱ ለዓለም ሁሉ እንዲዳረስ ስለሚፈለግ ነው ብለዋል፡፡
ከ2 ሺህ ዓመታት በፊት እንደተፃፈ የሚነገርለት መጽሐፉ፤ ስለ ቀዳሚት ሰንበት ምንነትና ዘለዓለማዊነት በግልፅ እንደሚያብራራ እንዲሁም የኢትዮጵያና የእስራኤልን አንድነትና ትንሳኤ ምስጢር ተንትኖ እንደሚያስረዳ ተጠቁሟል፡፡
ማህበሩ በላከው መልዕክት፣ ቅዱስ ኤልያስ ከብሄረ ህያዋን ይዞት የመጣውን መጽሀፍ፣ የቤተ-ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት እንዲመረምሩት፣ በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲተረጎምና እንዲታተም፣ ምዕመናንም እንዲያነቡት የማድረግ ግዴታ ፓትርያርኩ እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡ “ይህ ሳይሆን በእንቢተኝነትና በቸልታ ለዘመናት በተስፋ የተጠበቀውን ይህን መጽሀፍ እንዳይቀርብ ቢያደርጉ፣ ከብሄረ ህያዋን የመጣው ቀናኢ ነቢይ ዓለምን ሁሉ እየገሰፀ ባለበት ኃያል፣ ስልጣኑ ፅኑ ፈራጅነቱና ቁጣው የሚፈርድ መሆኑን አረጋግጠን እንነግርዎታለን” ብሏል፡፡ “ለቤተ-ክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ እና ካህናት ጥፋትና የመጨረሻው ውድቀት ነው” ሲልም ለመፅሃፉ ትኩረት እንዲሰጥ ማህበሩ  አበክሮ አሳስቧል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ የፓትርያርኩን ጽ/ቤት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጽ/ቤት በስልክ አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡


ነገ የሦስት ወር ንቅናቄውን በአዲስ አበባ ይጀምራል

      ከመድረክ ጋር ያለውን ጥምረት አቋርጦ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የውህደት ድርድር የጀመረው አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ፤በመጪው ዓመት ምርጫ የሚሳተፈው የምርጫው አስፈፃሚ አካላት ነፃና ገለልተኛ መሆናቸው ከተረጋገጠ ብቻ እንደሆነ  ሊቀመንበሩ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ገለፁ፡፡
በ97 ምርጫ ቅንጅት የነበረውን ጥንካሬ ፓርቲያቸው መድገም እንደሚፈልግ የገለፁት ኢ/ር ግዛቸው፤ ህዝቡ ብሶት ላይ ስለሆነ በምርጫው ተቃዋሚዎች በቀላሉ ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ፓርቲያቸው ወደ ምርጫው የሚገባው ግን ለምርጫው ነፃና ፍትሃዊ መሆን አስፈላጊ የሚባሉት ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ፣ ሚዲያ እና የፍትህ ተቋማት መኖራቸውን ካረጋገጠ በኋላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “ይህ ጥያቄያችን ከተመለሰ በምርጫው በእርግጠኝነት እናሸንፋለን” ብለዋል የፓርቲው መሪ፡፡
ፓርቲያቸው ከመድረክ ጋር ስላለው ግንኙነት የተጠየቁት ኢ/ር ግዛቸው፤ አንድነት ከቢሮ እና ከመግለጫ ፖለቲካ ተላቆ ትግሉን ወደ ህዝብ ለማውረድ  ያደረገው እንቅስቃሴ የመድረክ አመራሮችን እንዳስኮረፈና እገዳው እንደተላለፈ ጠቅሰው “እገዳው ትክክል አይደለም፤ አንሱትና ባቀረብነው የውህደት ጥያቄ መሰረት አብረን እንስራ ብለናቸዋል” ብለዋል፡፡
“መድረክ ከአንድነት የተሻለ ጥንካሬ እንደሌለው ገምግመናል” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ውህደቱን አንፈልግም ቢሉም እንኳን በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ በቅንነት አብረን ልንሰራ እንደምንችል ነግረናቸዋል ብለዋል፡፡
ከእዚህ በኋላ አንድነት በቀጥታ ውህደት ከመፈፀም ውጪ ከየትኛውም ፓርቲ ጋር ግንባርና ቅንጅት የመፍጠር ፍላጎት እንደሌለውም ኢ/ር ግዛቸው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ፓርቲው በነገው እለት “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” ሁለተኛ ዙር ንቅናቄ በአዲስ አበባ የሚጀምር ሲሆን  አጀንዳውም መሬት የግል እንዲሆን የሚጠይቅ ነው ተብሏል፡፡ ለ3 ወር ይዘልቃል የተባለውን ይሄን ንቅናቄ በተመለከተ የተጠየቁት ኢ/ር ግዛቸው፤“በአንድነት ፕሮግራም ውስጥ ከመንግሥት ይዞታና ከአንዳንድ ተቋማት ይዞታ በስተቀር መሬት የግል መሆን አለበት በሚል በግልፅ አስቀምጠናል፡፡ ይህን መነሻ አድርገን በመሬት ጉዳይ ላይ ህዝብ ተወያይቶ የራሱን አቋም የሚይዝበት ትልቅ ንቅናቄ አዘጋጅተናል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
 አሁን ያለው የመሬት ፖሊሲ ለኑሮ ውድነቱ መባባስ አስተዋፅኦ አበርክቷል ያሉት ኢ/ር ግዛቸው፤ “የኑሮ ውድነቱ ካለን የመሬት ሃብት ተጠቃሚ ያለመሆናችን ውጤት ስለሆነ፣ ጥያቄያችን የኑሮ ውድነት አጀንዳንም በበቂ ሁኔታ የያዘ ነው” ብለዋል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤ መሬት የህዝብና የመንግስት ነው የሚል ፖሊሲ እንደሚያራምድ ይታወቃል፡፡
(ከአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበሩ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ጋር የተደረገው ቃለምልልስ ሙሉ ቃል በገፅ 5 ላይ ያገኙታል፡፡)


          የ38 አመቱ ኢትዮጵያዊ ዶክተር ፍሰሃ ኡንዱቼ በካናዳ የመሰረተ ልማትና የትራንስፖርት ሚኒስቴር የማኒቶባ ግዛት የአየር ንብረትና የጎርፍ አደጋ ትንበያ ዳይሬክተር ሆነው መመረጣቸውን ዊኒፒንግ ፍሪ ፕሬስ ዘገበ፡፡
የካናዳ የመሰረተ ልማትና የትራንስፖርት ሚኒስትር ስቲቭ አሽተን ዶክተሩን ለመገናኛ ብዙሃን ለማስተዋወቅ በተዘጋጀ ስነስርዓት ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፣ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ በርካታ ባለሙያዎች የተሳተፉበትን ከፍተኛ ውድድር በማሸነፍ ለማኒቶባ ግዛትየአየር ንብረትና የጎርፍ አደጋ ዳይሬክተር ለመሆን የተመረጡት ዶክተር ፍሰሃ፣ ላለፉት 15 አመታት በሃይድሮሎጂና ከጎርፍ አደጋ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች በአሜሪካና በተለያዩ የአውሮፓ አገራት የካበተ የስራ ልምድ አላቸው፡፡
ላለፉት አምስት አመታት የግዛቷ የውሃ ቁጥጥር ስርዓቶች ዕቅድ ከፍተኛ መሃንዲስ ሆነው ያገለገሉት ዶክተር ፍሰሃ፣ ከዚያ ቀደምም ኤኢኮም በተባለ አለማቀፍ የምህንድስና አገልግሎቶች ኩባንያ ውስጥ የውሃ ሃብቶች መሃንዲስ ሆነው ማገልገላቸው ተነግሯል፡፡ ኒዘርላንድ ውስጥ ከሚገኘው ኢንተርናሽናል ሃይድሮሊክ ኢንጂነሪንግ ኢንስቲቲዩት በሲቪል ምህንድስና የሁለተኛ ዲግሪያቸውን የተቀበሉት ዶክትር ፍሰሃ፣ በኖርዌጂያን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳይንስ ኤንድ ቴክኖሎጂ ሌሎች የምርምር ጥናቶችን እንደሰሩ ተጠቁሟል፡፡
ከማኒቶባ ዩኒቨርሲቲ በውሃ ሃብቶች የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከተቀበሉ በኋላም፣ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ከጎርፍ አደጋ ትንበያና ከአደጋ ቁጥጥር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች በውሃ ሃብቶች መሃንዲስነትና በመምህርነት አገልግለዋል፡፡በወቅቱ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ዶክትር ፍሰሃ፣ በውሃው ዘርፍ የጀመሩትን ጥናት አጠናክረው ለመቀጠል የሚያስችሏቸውን የጎርፍ አደጋዎች የሚበዙባቸው አካባቢዎችና በጎርፍ አደጋ ትንበያ ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ዩኒቨርሲቲዎች ሲያጠኑ እንደቆዩና ማኒቶባ ግዛት ለዚህ ተመራጭ መሆኗን በማረጋገጥ ወደዚያው ለመሄድ መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ፍሰሃ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ናቸው፡፡
           አምስቱ የአድዋ ተጓዦች ከአዲስ አበባ 260 ኪ.ሜ አካባቢ ወለቲ በተባለች ትንሽ ከተማ የበእምነት ደገፉ እናት የነገሯቸውን አሳዛኝ ነገር አይረሱትም፡፡ በእምነት ደገፉ የ5 ዓመት ህፃን ነው። ይህ ህፃን ሁለቱም ኩላሊቶቹ ደም ስለማያጣሩ ሀኪም ቤት እየተወሰደ ደሙ እየተለወጠ ነው እስካሁን በሕይወት የቆየው፡፡ ሁሉም የትንሷ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ከሚሴ ከተማ እየሄዱ ለህፃኑ ደም ለግሰዋል፡፡ አሁን በመንደሯ ለበእምነት ደም ያልሰጠ ሰው የለም፤ ሁሉም ተዳርሷል፡፡ እባካችሁ ወደ አዲስ አበባ ስትመለሱ ልጄ ዘላቂ ህክምና አግኝቶ፣ ህይወቱ ሰንብታ አድጎና ተምሮ ለአገሩ ቁም ነገር የሚሰራ ልጅ አድርጉልኝ ሲሉ ተጓዦቹን ተማፀኑ፡፡ ተጓዦቹም በሰሙት ነገር ልባቸው ክፉኛ ተነካ፡፡ በተለያዩ ሚዲያዎች በእምነት ያለበትን ሁኔታ ለኢትዮጵያ ህዝብ ገልፀው ሁሉም የአቅሙን እንዲረዳ በማስተባበር የህፃኑን ህይወት ለመታደግ ቃል ገቡ፡፡
ህፃኑን መርዳት የምትፈልጉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የከሚሴ ቅርንጫፍ ሂሳብ ደብተር ቁጥር 10000714572347 ያስገቡለት፡፡ የእናቱ ስም አትክልት እሼቱ ይባላል፡፡

ከፍተኛ ተሰጥኦ እንዳላት የሚነገርላት የኢትዮጵያ ጃዝ አቀንቃኝ የሺ ደምመላሽ በሚያዝያ ወር አጋማሽ ላይ በኒውዮርክ የሙዚቃ ኮንሰርት እንደምታቀርብ ታዲያስ መፅሄት ዘግቧል፡፡
የጃኖ ባንድና የጂጂን ሥራዎች ያሳተመው የኒውዮርኩ ፕሮዱዩሰር ቢል ላስዌል “ፋኖ” የተሰኘ ዘፈኗን ዳግም አዋህዶ እያቀናበረላት ሲሆን የሺ አዲስ አልበም ከላስዌል ጋር የመስራት ዕቅድ እንዳላት ታውቋል፡፡
ድምፃዊቷ የኒውዮርክ ኮንሰርቷን የምታቀርበው ከ “ቅኔ” ባንድ ጋር ነው ተብሏል። በኢትዮጵያ አይዶል ዳኝነቷ የምትታወቀው የሺ፤ ከያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት በፍሉትና በተጓዳኝ በፒያኖ አጨዋወት ተመርቃለች፡፡ አርቲስቷ “ቅኔ” የተሰኘ የመጀመርያ አልበሟን የዛሬ ሁለት ዓመት ለጆሮ ማብቃቷ ይታወሳል፡፡