Administrator
የፖለቲካ ጥግ
(ስለዲፕሎማት)
ዲፕሎማት ማለት ሁልጊዜ የሴትን የልደት ቀን የሚያስታውስ ነገር ግን ዕድሜዋ ትዝ የማይለው ሰው ማለት ነው፡፡
ሮበርት ፍሮስት
(አሜሪካዊ ገጣሚ)
በዚህ ዘመን ዲፕሎማት ሌላ ሳይሆን አልፎ አልፎ መቀመጥ የተፈቀደለት የአስተናጋጆች አለቃ ማለት ነው፡፡
ፒተር ዪስቲኖቭ
(እንግሊዛዊ ተዋናይ፣ ዳይሬክተርና ፀሃፊ)
እውነተኛ ዲፕሎማት የሚባለው የጎረቤቱን ጉሮሮ ጎረቤቱ ሳያውቅ መቁረጥ የሚችል ነው፡፡
ትሪግቭ ላይ
(ኖርዌጃዊ ፖለቲከኛ)
አምባሳደር ለአገሩ ጥቅም እንዲዋሽ ወደ ውጭ አገር የሚላክ ሃቀኛ ሰው ነው፡፡
ሄነሪ ዎቶን
(እንግሊዛዊ ገጣሚና ዲፕሎማት)
እኔ እንደሃኪም ነኝ፡፡ በሽተኛው ክኒኖቹን በሙሉ መውሰድ ካልፈለገ የራሱ ውሳኔ እንደሆነ እነግረዋለሁ፡፡ ነገር ግን በቀጣዩ ጊዜ በቀዶ ህክምና ባለሙያነቴ ቢላዬን ይዤ እንደምመጣ ማስጠንቀቅ አለብኝ፡፡
ዣቬር ፔሬዝዲ ሱላር
(የፔሩ ዲፕሎማት)
ውጭ አገር ስትሆን ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊ ነህ፤ አገር ቤት ግን ፖለቲከኛ ብቻ ነህ።
ሃሮልድ ማክሚላን
(እንግሊዛዊ ጠ/ሚኒስትር)
ከፍርሃት የተነሳ ድርድር ውስጥ መግባት የለብንም፤ ነገር ግን ድርድርን ፈፅሞ ልንፈራ አይገባም፡፡
ጆን ፊትዝጌራልድ ኬኔዲ
(የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት)
አንዳንድ ጥያቄዎቻችሁን እመልስላችኋለሁ። በጣም አስቸጋሪዎቹን ደግሞ የሥራ ባልደረቦቼ ይመስላችኋል፡፡
ሮላንድ ስሚዝ
(እንግሊዛዊ የቢዝነስ ኃላፊ፤ በብሪቲሽ ኤሮስፔስ
ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተናገሩት)
ወጣቶች ከሚሞቱ በዕድሜ የገፉ ዲፕሎማቶች ቢሰላቹ ይሻላል፡፡
ዋረን ሮቢንሰን አውስቲን
(አሜሪካዊ ዲፕሎማት፤ በተባበሩት መንግስታት
ድርጅት በተካሄደው ሰረዥም ውይይት ተሰላችተው እንደሆነ ሲጠየቁ የመለሱት)
“ስንት ሰዓት ነው?” ቢሉ ከተሜው፤ “የዘመኑ ሰዓትና የዘመኑ ሰው ውሸታም ነው፡፡ ዝም ብለው ጥላዎትን አይተው ይሂዱ!” አለ ባላገር፡፡
ደራሲ ከበደ ሚካኤል ከፃፏቸው አጫጭር ትርክቶች መካከል የሚከተለው ይገኝበታል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድፈረሰኛ ተራራ እየወጣ ሳለ፤ አንድ፣ አንድ እግሩ ቆራጣ የሆነ ሰው ያንን መንዲስ የሚያክልና ጫፉ ሩቅ የሆነ ተራራ፤ እየተንፏቀቀ ለመውጣት ሲፍጨረጨር ያገኘዋል፡፡ ያም እግሩ የተቆረጠ ሰው፡-
“ጌታዬ እባክህ የተወሰነ መንገድ ድረስ አፈናጠኝና ውሰደኝ?” ሲል ይለምነዋል፡፡ ፈረሰኛውም ልቡ በጣም ይራራና፤
“እሺ ወዳጄ ፈረሱ የቻለው ርቀት ያህል አብረን እንሄዳለን፡፡ ና ውጣ” ብሎ፤ ወርዶ፣ አቅፎ ያፈናጥጠዋል፡፡
ትንሽ መንገድ አብረው ከተጓዙ በኋላ፤ እግረ ቆራጣው ሰውዬ፤
“ጌታዬ፤ ብዙ ምቾት አልተሰማኝም፡፡ አካል-ጉዳተኛ በመሆኔ አንደኛው እግሬን እጅግ ህመም ተሰማኝ!” አለው፡፡
ፈረሰኛው፤
“ታዲያ እንዴት ብናደርግ ይመችሃል?” ሲል ጠየቀው፡፡
አካል-ጉዳተኛውም፤
“ትንሽ መንገዱ እኔ ልሂድ፣ አንተ እግርህ ጤነኛ ስለሆነ ተከተለኝ” አለው፡፡
ፈረሰኛው በሁኔታው አዝኖ ልቡ ራራና፤
“መልካም፤ እኔ ልውረድ አንተ ሂድ፡፡ ሲደክመኝ ትጠብቀኝና ደሞ አብረን እንጓዛለን” አለውና ወረደ፡፡
የተወሰነ ርቀት፤ አካል-ጉዳተኛው በፈረስ፣ ባለፈረሱ በእግሩ ተጓዙ፡፡
ፈረሰኛው “ደክሞኛል ጠብቀኝ” አለው፡፡
እንደገና ተፈናጠጡና መንገድ ቀጠሉ፡፡ ጥቂት እንደተጓዙ፣ ፈረሰኛው ወረደለትና አካል ጉዳተኛው በፈረስ ቀጠለ፡፡ አሁን ግን ያ አካል-ጉዳተኛ ፈረሱን ኮልኩሎ ለዐይን ተሰወረ፡፡ ፈረሰኛው ቢሮጥ፣ ቢሮጥ ሊደርስበት አልቻለም፡፡
ባለፈረሱ ጮክ ብሎ፣ “እባክህ ሌላ ምንም አልፈልግም፣ የምነግርህን ብቻ አንዴ አዳምጠኝ?” አለው፡፡
ፈረስ ነጣቂው ባለቤቱ የማይደረስበት አስተማማኝ ቦታ ሲደርስ፤
“እሺ ምን ልትል ነው የፈለከው? እሰማሃለሁ ተናገር!” አለው በዕብሪት፡፡
ባለፈረሱም፤
“ወንድሜ ሆይ! አደራህን ይሄን እኔን ያደረከኝን ነገር ለማንም ሰው እንዳትነግር፡፡ ወደፊት በዓለም ደግ የሚያደርግ ሰው ይጠፋል!” አለው፡፡
* * *
ደግነት የብዙ ህይወታችን መሰረት መሆኑን አንዘንጋ፡፡ ቀናነት ካልተጨመረበት ዲሞክራሲም፣ ፍትሃዊነትም፣ ልማትም፣ አስተማማኝነቱ አጠያያቂ ነው፡፡ ደግ ያደረጉን ለመካስ ዝግጁ መሆን እንጂ ለክፉ ማጋለጥ አይገባም፡፡ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሀገሩ ጉዳይ ያገባዋል፡፡ መምህራን የልጆችን ተስፋ አለምላሚ ናቸው፡፡ ወታደሮች የሀገር ህልውና ጠባቂዎች ናቸው፡፡ ገበሬዎች የኢኮኖሚ ገንቢዎች ናቸው፡፡ የጥበብ ሰዎች የዘመን ዜማዎች ናቸው፡፡ ሁሉም የዴሞክራሲ ተቋዳሾች ናቸው፡፡
“ሀብት ሲበዛ ዲሞክራሲ ይረጋገጣል ያለው ማነው?” ብሏል አንድ አዋቂ፤ ምን ያህል ፖለቲካና ኢኮኖሚ እንደሚተሳሰሩ ሲያጠይቅ! ያለው ይናገራል፣ የሌለው ያፈጣል ወይም ሁሉን “እሺ” ይላል፤ የሚባል ነገር አለና አስተውለን ብናስብ ታላቅ ነገር ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ፤ እየተሳሰቡ መጓዝን የመሰለ ነገር የለም፡፡ መከራችን፤ የሀገራችን የችግር ቁልል ተራራ አካል ነውና ለብቻ አይገፋም፡፡
ከረዥም ጊዜው የኢትዮጵያ ወጣቶች ትግል አንፃር ስንመለከት ወጣቶች ልዩ ባህሪ እንዳላቸው እናስተውላለን - ታሪክን ዋቤ ቆጥረን፡፡ ባህሪያቸው፤ ቁርጠኝነትና ራስ - ወዳድ አለመሆን፣ ፍትሐዊነት፣ ጭቦኛ አለመሆን፣ የሴቶችን እኩልነት ማመን እና ትሁትነት የሚያካትቱ ልዩ ምልክቶቹ ነበሩ፤ ለማለት ያስደፍራል፡፡ እኒህ ምልክቶቹ ዛሬ ወዴት አሉ? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው! እንጠያየቅ፡፡ ወጣቱን ያላቀፈ ጉዞ፣ ጉዞ አይደለምና!
አንጋረ ፈላስፋ፤
“ፀብ ክርክር ካለበት ጮማ-ፍሪዳ፤ ፍቅር ያለበት ጎመን ይሻላል” ይለናል፡፡ ፍቅርና መተሳሰብ የልማት፣ የኢኮኖሚ ድርና ማግ ናቸው እንደማለትም ነው፡፡ ባህልን ማክበር፣ አዋቂን ማድመጥ፣ ለዕውቀት መሪ ቦታ መስጠት፣ ጎረኝነትን ማስወገድና የጋራ መድረክ፣ የጋራ ሸንጎ መሻት፣ ዋና ጉዳይ መሆናቸውን መቼም አንዘንጋ፡፡
“የአያቴ ብስክሌት መንዳት አሪፍ መሆን እኔን ከመውደቅ አያድነኝም” ይላል ገጣሚ ሰለሞን ደሬሣ (ልጅነት)፡፡ በትላንት አበው ታሪክ መመካት ብቻውን ወደፊት አያራምደንም ሲል ነው፡፡ አንድም ነገን ዛሬ እንፍጠረው እንደማለት ነው፡፡ የሁሉም እኩል የሆነች አገር አጠንክሮ ለመጨበጥ እንዘጋጅ ሲልም ነው፡፡ እርስ በርስ የማንፈራራባት፣ የማንጠራጠርባት፣ ነጋችንን ጨለማ አድርገን የማናይባት አገር ነው መገንባት ያለብን፡፡ ከሁሉም በላይ ግን፤ አለመተማመን ከመርገምት ሁሉ የከፋ መርገምት ነው፡፡ “ስንት ሰዓት ነው?” ቢሉ ከተሜው፤ “የዘመኑ ሰዓትና የዘመኑ ሰው ውሸታም ነው፡፡ ዝም ብለው ጥላዎትን አይተው ይሂዱ!” አለ ባላገር፤ የሚለው ቁም ነገር ነገን እንድናስተውል ልብ በሉ የሚለን ነው!
የአዲስ አበባ ጐዳና ተዳዳሪዎች ኑሮ ከፍቶብናል ይላሉ
ከ60ሺ በላይ የሚሆኑት ራሳቸውን እንዲችሉ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል
5ሺ የጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶች ከነገ ወዲያ ለሥልጠና ወደ አፋር ይጓዛሉ
በኮብልስቶን ከሰለጠኑት ውስጥ ብዙዎቹ ወደ ጐዳና ተመልሰዋል
“ፖሊሶች ጥፉ ይሉናል፤ ወዴት እንጥፋ? የትስ እንኑር?”
የ27 ዓመት ወጣት ነው፡፡ ለጎዳና ህይወት የተዳረገው ወላጆቹን በኤችአይቪ በማጣቱ ነበር። በጎዳና ላይ ከጓደኞቹ ጋር ለ7 ዓመታት የኖረው ታዴ፤ አንድ ቀን ከጐዳና ወጥቼ እንደማንኛውም ሰው የተሻለ ህይወት ይኖረኛል ብሎ ያስብ እንደነበር ይናገራል፡፡
እንዳለውም ሰው ሆኖ መኖር የሚችልበት አጋጣሚ ባልጠበቀው ጊዜ ተፈጠረ፡፡ መንግስት የጎዳና ተዳዳሪዎችን አሰባስቦ በማሰልጠን ራሳቸውን እንዲችሉ ድጋፍ መጀመሩን የሰማው በ2003 ዓ.ም ነው፡፡ ወዲያው መስቀል አደባባይ አካባቢ ከሚኖርባት የፕላስቲክ ጎጆው በመውጣት፣ ከሁለት የጎዳና ጓደኞቹ ጋር ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሄዶ፣ የጎዳና ተዳዳሪ መሆኑን በማስመስከር ተመዘገበ፡፡ ከዚያም ከ2500 በላይ ከሚሆኑ ሌሎች የጎዳና ተዳዳሪዎች ጋር ጨፌ ወደሚገኘው የማሰልጠኛ ካምፕ ገባ - በሁለተኛ ዙር ምልምልነት፡፡
ስልጠናው ለአንድ ወር ብቻ የዘለቀ እንደነበር የሚናገረው ታዴ፤ በዚህ ወቅትም የኮብልስቶን አመራረትን ጨምሮ በመጠኑም ቢሆን ከስነልቦና ጋር የተገናኘ ትምህርት እንደተሰጣቸው ያስታውሳል፡፡ በስልጠናው ወቅት በየቀኑ በሬ እየታረደ በቀን ሶስት ጊዜ የስጋ ተዋፅኦ የሆኑ ምግቦችን ይመገቡ እንደነበር ይናገራል፡፡ የአንድ ወሩ ስልጠና እንደተጠናቀቀም እዚያው ጨፌ በሚገኘው የኮብልስቶን ማምረቻ ቆርቆሮ በቆርቆሮ የሆኑ ትናንሽ ክፍል ቤቶች ተሰጥቷቸው መኖር እንደጀመሩ ታዴ ይናገራል፡፡ ገቢ ማግኘት ከጀመሩ በኋላ ቁርስ፣ ምሳ እና እራት በ15 ብር ኩፖን ይቀርብላቸው ነበር፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የምግቡ ዋጋ 20 ብር ገባ፡፡
“መንግስት በሚገባ ተንከባክቦናል፤ ምቾታችን እንዳይጓደልም ብዙ ጥሯል” የሚለው ታዱ፤ አንድ ነጠላ የኮብል ድንጋይ በ2.10 ብር እንድንሸጥ ገበያ አመቻችቶልናል፤ የበረታ በቀን እስከ 200 እና 300 ብር የሚያወጣ ጥርብ ድንጋይ ማምረት ይችላል” ብሏል፡፡ በወቅቱ አንድ አምራች በወር 4ሺህ እና 5ሺህ ብር ያገኝ ነበር የሚለው ታዴ፤ እያንዳንዳቸው የባንክ ቁጠባ ደብተር ተከፍቶላቸው ሙሉ ገንዘባቸውን እንዲቆጥቡ ይደረግ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በባንክ የገባውን ቁጠባም እንደፈለጉ ማውጣት አይቻልም ነበር ብሏል፡፡
የሁለተኛ ዙር ሰልጣኞች በዚህ መልኩ እየሰሩ እየቆጠቡ፣ ከመንግስት በቅናሽ ዋጋ ምግብ እየቀረበላቸው እየተመገቡ፣ በነፃ መኖርያ ቤት ተሰጥቷቸው እየኖሩ ሳለ፣ ኤልሻዳይ የሚባል ድርጅት “ራሳችሁን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ አለባችሁ፤ እኔ በብረታ ብረትና በማሽን ኦፕሬተርነት፣ በእንጀራ መጋገርና በተለያዩ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች የምትሰለጥኑበትን መንገድ አመቻችላችኋለሁ” እንዳላቸው ታዴ ያስታውሳል፡፡
ይሄኔ ነው ቀድሞ የማይፈቀድላቸውን የቁጠባ ገንዘብ እንዳሻቸው እንዲያወጡ የተፈቀደላቸው። አብዛኞቹም ገንዘቡ የሚያልቅ አልመሰላቸውም ነበር፡፡ በባንክ ለሁለት አመት ገደማ ያጠራቀሙትን ገንዘብ በማውጣት፣ መንግስት በነፃ ከሰጣቸው ቤት ወጥተው እዚያው መድኃኒዓለም ጨፌ አካባቢ የግለሰብ ቤት እየተከራዩ መኖር ይጀምራሉ - የኤልሻዳይን ስልጠና ተስፋ በማድረግ፡፡ ብዙዎቹ የቀድሞ የገቢ ምንጫቸው የነበረውን ኮብልስቶን የማምረት ስራ እርግፍ አድርገው በመተው፣ የቆጠቡትን ያለስስት እያወጡ መብላት ጀመሩ፡፡
“ከኛ መሃል እዚያው ተጋብተው ልጆች የወለዱም ነበሩ” ይላል ታዴ፡፡ ተስፋ የጣሉበት ኤልሻዳይ ግን የውሃ ሽታ ሆነ፡፡ በዚህም የተነሳ በርካቶች ያለ ስራ ተቀምጠው ገንዘባቸውን ሙልጭ አድርገው ጨረሱት ይላል፡፡ “የሚያሳዝነው ታዲያ ዛሬ እነዚያ ወጣቶች ተመልሰው ጎዳና ላይ ወድቀዋል” ሲል ታዴ በሃዘን ተሞልቶ ይናገራል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በካምፑ ከነበሩት አንደኛና ሁለተኛ ዙር ምልምሎች መካከል እሱን ጨምሮ ከ10 የማይበልጡ ብቻ መቅረታቸውን የሚገልፀው ወጣቱ፤ በሺዎች የሚቆጠሩት ተመልሰው ጐዳናን ሲቀላቀሉ፤ ነቃ ያሉት ጥቂቶች ደግሞ ጥሩ ደረጃ በሚያደርሳቸው የስራ መስክ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ ብሏል፡፡
ሪፖርተሮቻችን ቦታው ድረስ በመገኘት እንደታዘቡትም፤ በማምረቻ ማዕከሉ ከ1ኛና ሁለተኛ ዙር ሠልጣኞች ውስጥ ከ10 የማይበልጡ ወጣቶችን የተመለከቱ ሲሆን በካምፑ ያሉ የቆርቆሮ ቤቶችም ኦናቸውን መቅረታቸውን አስተውለዋል፡፡ በካምፑ በአጠቃላይ በ3 ዙሮች ከገቡት መካከል ደግሞ 170 ያህል ሰልጣኞች ብቻ እንደሚገኙ በካምፑ ውስጥ ለሁለት አመታት የቆየው ታዴ ገልፆልናል፡፡
“ህዳሴ” የሚል ስያሜ በተሰጠው የጨፌ የኮብልስቶን ማምረቻ ማዕከል ውስጥ ከቀሩት ጥቂት ወጣቶች አንዱ የሆነው ዘሪሁን (ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ስሙ የተቀየረ)፣ ከሱ ጋር በየክፍለ ከተማው ከሚገኙ ጎዳናዎች ተለቃቅመው በ3ኛ ዙር ወደ ማዕከሉ ከገቡት ከ2ሺ በላይ ምልምሎች መካከል እሱን ጨምሮ 160 ብቻ መቅረታቸውን ይናገራል፡፡ አብዛኞቹም ወደ መጡበት ጎዳና ተመልሰዋል የሚለው ወጣቱ፤ “መገናኛና ካዛንቺስ፣ አራት ኪሎ፣ ሜክሲኮ፣ መስቀል አደባባይና ሌሎች የከተማዋ አካባቢዎች ስዘዋወር ብዙ የህዳሴ ፍሬዎችን ጐዳና ላይ እያገኘኋቸው በኪሴ የያዝኳትን ሳንቲም አካፍላቸዋለሁ” ብሏል፡፡
መንግስት ስልጠናውን ሲያዘጋጅ መጀመሪያ የልጆቹን አመለካከትና አስተሳሰብ የሚለውጥ የስነ ልቦና ምክር መሰጠት ነበረበት የሚለው ዘሪሁን፤ ይህ ባለመደረጉ ብዙዎቹ ትንሽ ጊዜ ሰርተው በዝግ ሂሳብ የተቆጠበላቸውን ገንዘብ እንኳ ሳይቀበሉ “ጎዳና ናፈቀን” እያሉ ወደ ቀድሞው ህይወት ተመልሰዋል ብሏል፡፡ እስከ 10ኛ ክፍል መማሩን የነገረን ዘሪሁን፤ በአሁን ሰዓት ከኮብልስቶን ሥራ በሚያገኘው ገቢ ከፍተኛ ክፍያ እንደሚያስገኙ ከሚነገርላቸው የሙያ መስኮች አንዱ በሆነው የዶዘር ኦፕሬተርነት እየሰለጠነ መሆኑን ገልፆልናል፡፡ “በእርግጠኝነት ነገ ራሴን የተሻለ ቦታ አገኘዋለሁ” የሚለው ወጣቱ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ጓደኞቼ ተመልሰው ጐዳና መውጣታቸውን ባሰብኩ ቁጥር ግን ሃዘን ይሰማኛል ብሏል፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን በሄደበት አጋጣሚ የቅርብ ጓደኛው የነበረ የማዕከሉን ሰልጣኝ፣ በልመና እየተዳደረ እንዳገኘውም ወጣቱ ተናግሯል፡፡ መገናኛ አካባቢም አብረውት ሲሰልጥኑና ሲሰሩ የነበሩ ወጣቶች ጎዳና ላይ ወድቀው፤ ለእለታዊ ሱሳቸው ማስታገሻ፣ የሲጋራ ቁሩና የጫት ገረባ ሲያስሱ በተደጋጋሚ እንደገጠመው ጠቁሟል፡፡
ከዛንቺስ አካባቢ ጎዳና ላይ የላስቲክ ጎጆ ቀልሶ የሚኖረው ሌላው ወጣት በበኩሉ፤ ከሁለተኛው ዙር ሰልጣኞች አንዱ እንደነበር ጠቁሞ፤ “ኤልሻዳይ” የሚባለው ድርጅት በተለያዩ ሙያዎች እንድትሰለጥኑ አድርጌ፣ተደራጅታችሁ የራሳችሁን ቢዝነስ ትሰራላችሁ” በማለቱ ከጓደኞቹ ጋር በመመካከር፣ ያጠራቀሙትን 20 ሺ ብር የሚደርስ ገንዘብ ከባንክ አውጥተው መገናኛ አካባቢ በ600 ብር የግለሰብ ቤት ለሶስት ሆነው በመከራየት መኖር እንደጀመሩ ይናገራል፡፡
“ያጠራቀምነው ብር ብዙ ስለመሰለን ከመንግስት ጥገኝነት በፍጥነት ለመውጣት ጉጉት ነበረን” የሚለው ወጣቱ፤ “በእንጨት ስራ፣ በዳቦ ቤት፣ በእንጀራ መጋገር፣ በብሎኬት፣ በፕሪካስት ስራና በመሳሰሉት ተደራጅታችሁ እንድትሰሩ ይደረጋል የሚለው ተስፋ፣ በቃ ከእንግዲህ ራሳችንን ችለናል፤ ወደ ኋላ አንመለስም ብለን እንድናስብ አድርጎናል” ይላል፡፡ ኤልሻዳይ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት በዚህን ቀን ወደ ስልጠና ትሄዳላችሁ እያለ በተስፋ ስንጠብቅ፣ ጊዜው እየነጎደ ገንዘባችንም እያለቀ መጥቶ፣ የማታ ማታ ለጎዳና ህይወት ተመልሰን ተዳረግን ይላል ወጣቱ፡፡
የጎዳና ልጆች የራሳቸው ፓርላም አላቸው። ስብሰባም ይቀመጣሉ፡፡ ውሳኔዎችም ይወስናሉ፣ ለማንኛውም ውሳኔ የጎዳና ልጆች መገዛት ግድ ይላቸዋል፡፡ በዚህ መልኩ ህይወታቸውን የሚመሩት የጎዳና ልጆች፤ ዛሬ እጣ ፈንታቸው ካጋፈጣቸው ፈተና በተጨማሪ “መንግስት እየጨከነብን ነው” ሲል ይናገራል - ሌላው ተስፉ የተባለ የጎዳና ተዳዳሪ፡፡ በኮብልስቶን ሥልጠና አለመሳተፉን የጠቆመው ወጣቱ፤በርካታ ለኮብልስቶን ስልጠና ተለይተውት የነበሩ ወዳጆቹን ተመልሰው ጎዳና ላይ ወድቀው እያገኛቸው እንደሆነ ተናግሯል፡፡ “እናንተ በኮብልስቶን ሰልጥነው የተመለሱትን ትላላችሁ፤ዛሬ ከዩኒቨርሲቲ በዲግሪ ተመርቀው የጎዳና ወዳጆቻችን ሆነው የቀሩ ብዙ ወጣቶች አሉ” ብሏል - ተስፉ፡፡
በተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አጋዥነት በስካቫተር፣ በዶዘርና ሎደር ኦፕሬተርነት፣ በኤሌክትሪሻንነት፣ በብረታ ብረት ሥራና በመሳሰሉት ሙያዎች ከ8 ወራት በላይ ሰልጥነው የነበሩ ወዳጆቹም ስራ በማጣት ተመልሰው ለጎዳና ህይወት መዳረጋቸውን ይኸው ወጣት ይገልፃል፡፡
በጎዳና ተዳዳሪዎች ዘንድ በተግባቢነቱ ከፍተኛ ዝና እንዳለው የሚነገርለትና በ97 ዓ.ም የጐዳና ልጆችን ፊርማ አሰባስቦ ለፓርላማ ሊወዳደር አቅዶ ያልተሳካላት ተስፉ፤ በዘንድሮው አመት ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር ጨምሯል፤ በየእለቱም ቁጥራቸው እየጨመረ ነው ባይ ነው፡፡ ቀደም ሲል መንግስት ለስልጠና የሰበሰባቸው ወጣቶች ተመልሰው ወደ ጎዳና መውጣታቸው ብቻ ሳይሆን የጨረቃ ቤቶች በዘመቻ እንዲፈርሱ መደረጋቸውም በርካቶችን ለጎዳና ዳርጓቸዋል፤ ከጎዳና ህይወት ከወጡ በኋላ ተመልሰው ለጎዳና የተዳረጉ በርካታ ወዳጆችም አሉኝ ይላል፡፡
ለአንድ ቀን ማደርያ 4 ብር እና 3 ብር ይከፈልባቸው የነበሩ አልጋ ቤቶች ወደ 20 እና 30 ብር ማሻቀባቸው የጎዳና ተዳዳሪውን ቁጥር እንዳበራከተው ተስፉ ይናገራል፡፡ ከደቡብ፣ ከአማራና ከትግራይ ክልሎች የሚመጡ ስራ ፈላጊዎችም ያሰቡት ሳይሳካላቸው ለጎዳና ህይወት መዳረጋቸው ለቁጥሩ መጨመር አስተዋፅኦ አበርክቷል የሚለው ወጣቱ፤ ህፃናት በብዛት ከሸዋሮቢትና ከሻሸመኔ አካባቢ እንደሚመጡ ይገልፃል፡፡
“ኑሮ በጎዳና ከፍቷል”
የጎዳና ልጆች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከመንግስት አካላት ጥቃት እየደረሰባቸው ነው የሚለው ተስፋ “ፖሊሶች ምሽት ላይ ባገኙን ቁጥር ‘ከዚህ አካባቢ ጥፉ’ ይሉናል፣ የላስቲክ ቤታችንን ያፈርሱብናል፤ ወዴት እንጥፋ? የትስ እንኑር?” ሲል ተስፉ ይጠይቃል፡፡
“ሴቶች የጎዳና ተዳዳሪዎች ከሰው ተራ ወጥተው ገላቸውን በአነስተኛ ዋጋ በየአጥሩ ስር ይቸረችራሉ፣ ስጋዋን ሸጣ የምታድረውም ለፖሊሶች ራት መግዛትና ካርድ መሙላት ይጠበቅባታል” የሚለው ወጣቱ፤ ከሆቴሎች ለምነን የምናገኛትን ፍርፋሪ እንኳ ሆቴሎቹን እንዳትሰጧቸው እያሉ ስለሚያስፈራሯቸው የምንቀምሰው እያጣን ነው ሲል ያማርራል፡፡
ምን እንሁን ብለን ስንጠይቅ ሃገሪቱ እየተለወጠች ነው፤ እናንተም ተለወጡ ይሉናል፤ ያለው ወጣቱ፤ ‘እንዴት እንለወጥ?’ ስንል ግን እነሱም መልስ የላቸውም ብሏል፡፡ “ስራ ለማግኘት፣ እንደሰው ለመቆጠርና ለመታመን ተያዥ ያስፈልጋል” የሚለው ወጣቱ፤ በርካታ ወጣት እውቀት እያለውና መስራት እየቻለ በእነዚህ ምክንያቶች በየጎዳናው መናኛ ሆኖ ቀርቷል” ሲል ምሬቱን ይገልፃል፡፡
“አብዛኞቹ የጎዳና ልጆች እለታዊ ችግራቸውንና ረሃባቸውን ለማስታገስ አደገኛ ሱሶች ውስጥ ከመደበቃቸው ባሻገር፤ ኑሮ ይበልጥ ሲመራቸው ለአጭር ጊዜ የምታሳስር ቀላል ወንጀል ሰርተው ማረሚያ ቤት ለመግባት ይተጋሉ፤ ይህ መሰሉ ድርጊት በተለይ በክረምት ወራት የተለመደ ነው” ብሏል - ወጣቱ የጐዳና ተዳዳሪ፡፡
ከአረብ ሃገር የስደት ተመላሾች መካከል ለጐዳና የተዳረጉት “መቀሌ ኤምባሲ” በሚል በሰየሙት የጎዳና ነዋሪዎች አካባቢ እንደሚገኙ የጠቆመው ተስፉ፤ አብዛኞቹ ቀኛማችነትን የእለት ጉርስ ማግኛ እንዳደረጉት ገልጿል፡፡
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሸለመ እንደሚሉት፤ መንግስት “ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኮሌክሽን” ከሚባል ሃገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመሆን ባለፉት 8 ዓመታት ወደ 60ሺ 759 ወገኖች ከጎዳና ላይ ተነስተው ራሳቸውን ችለው እንዲቋቋሙ የተለያዩ ስልጠናዎች ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ወደ 19 ሺ 50 ያህሉ ህፃናት ናቸው፡፡ ህፃናቱ መስራት ስለማይችሉ ትምህርት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
እነዚህን የጎዳና ተዳዳሪዎች “ለመጪው ትውልድ ልማትን እንጂ ልመናን አናወርስም፤ ልመና የሌለባት ኢትዮጵያን ማየት እንችላለን” በሚል መርህ መንግስት በነፃ ማሰልጠኑንና እያሰለጠነ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ግርማ ፤ ከስልጠናው በኋላ ያለውን ሂደት የሚከታተለው ኤልሻዳይ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባለፈው አመት 2400 የሚሆኑ የጎዳና ልጆች በአፋር ክልል ኢሚባራ ወረዳ በሚገኘው የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አዲስ ራዕይ ማሰልጠኛ ማዕከል ገብተው በተለያዩ የሙያ መስኮች ሰልጥነው እንደተመረቁ የጠቆሙት አቶ ግርማ፤ ከነገ በስቲያ ሰኞ 5 ሺህ ዪደርሱ የጎዳና ተዳዳሪዎች በሁለተኛ ዙር እንዲሰለጥኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት አሸኛኘት ይደረግላቸዋል ብለዋል፡፡ “ሰልጣኞቹ ወደ ጎዳና እንዳይመለሱ ኤልሻዳይ ይከታተላል፤መንግስትም ድጋፍ ያደርጋል፤ ወደ ጎዳና ተመልሰዋል ስለሚባለው ግን መረጃው የለንም” ያሉት ኃላፊው፤ የሰልጣኞቹን ቁጥርና የት ደረሱ የሚለውን ኃላፊነት ወስዶ እየሰራ ያለው ኤልሻዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከአዲስ አበባ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር በኮብልስቶን ሲሰለጥኑ የነበሩት የጎዳና ተዳዳሪዎች የኤልሻዳይን ስልጠና በመጠባበቅ ገንዘባቸውን ጨርሰው ወደ ጎዳና ተዳርገዋል የሚለውን በተመለከተ የጠየቅናቸው የኤልሻዳይ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ የማነህ፤ ሥልጠናው መዘግየቱን አልካዱም፡፡ “ሁኔታዎች ናቸው ያዘገዩት፤ ላቅ ያለ ነገር ለመስራት ስለታቀደ ለመቆየት ተገደናል፡፡ ወጣቶቹ በሚያገኙት ስልጠና እስካሁን የተጉላሉትንና ያጋጠማቸውን ችግር እንደሚረሱት ተስፋ እናደርጋለን›› ያሉት የኤልሻዳይ መሥራች፤ ቀደም ሲል ወደ አፋር ሄደው ከሰለጠኑት ውስጥ 95 በመቶ ያህሉ ስኬታማ መሆናቸውን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ባሎች ሚስቶቻቸውን በመደብደብ ከአፍሪካ 3ኛ ናቸው
87 በመቶ የማሊ ሴቶች ድብደባ ተገቢ ነው ይላሉ
የጊኒና የኢትዮጵያ ሴቶችም ድብደባ ተገቢ ነው ብለው ያስባሉ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተለያዩ ተቋማት በቤት ውስጥ ጥቃት ዙሪያ ያወጧቸውን ሪፖርቶች መነሻ በማድረግ በቅርቡ በ37 የአፍሪካ አገራት ላይ የተሰራ አንድ ጥናት፣ ኢትዮጵያውያን ባሎች ሚስቶቻቸውን አዘውትረው በመደብድብ 3ኛ መሆናቸውን አረጋገጠ።
‘አፍሪካ ሄልዝ፣ ሂዩማን ኤንድ ሶሻል ዲቨሎፕመንት ሰርቪስ’ የተባለው አህጉራዊ ድርጅትና በሴቶች ጥቃት ዙሪያ የሚሰሩ ሌሎች ተቋማት በጋራ የሰሩት ጥናት እንደሚለው፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ባሎች የትዳር አጋሮቻቸውን መደብደብ አግባብ ነው ብለው የሚያስቡና በተለያዩ ምክንያቶች ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ ናቸው፡፡
ጥናቱ ከተሰራባቸው የአፍሪካ አገራት የበለጠ ተደባዳቢ ባሎች ያሉባት አገር ናት ተብላ በቀዳሚነት የተቀመጠችው ኡጋንዳን ስትሆን፣ ሴራሊዮን ሁለተኛ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ሶስተኛ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
60 በመቶ ያህሉ ኡጋንዳውያን ባሎች በትዳር ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት ሚስቶቻቸውን መደብደብ ሁነኛ መላ ነው ብለው እንደሚያስቡ የጠቆመው የጥናቱ ውጤት፣ ለድብደባ ምክንያት ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከልም፤ ‘እዚህ ሄድኩ ሳትይኝ ከቤት ወጥተሸ ሄድሽ’፣ ‘የምልሽን አትሰሚኝም’፣ ‘ከእከሌ ጋር ያለሽ ነገር ምንድን ነው?’፣ ‘ልጆቼን በወጉ አልተንከባከብሽም’ እና ሌሎች ከወሲብና ከቅናት ጋር ተያያዙ ጉዳዮች እንደሚገኙበት አመልክቷል፡፡
ጥናቱ በተሰራባቸው አገራት የሚገኙ አብዛኞቹ ባሎች የድብደባን አስፈላጊነት የሚያምኑበት ሲሆን፤ በአንዳንዶቹ አገራት የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ሚስቶችም ተመሳሳይ አመለካከት እንዳላቸው ተጠቁሟል፡፡ መሰል አመለካከት ከሚንጸባረቁባቸው አገራት መካከል ጥናቱ በቀዳሚነት ያስቀመጠው ማሊን ሲሆን፣ ከ15 እስከ 49 የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ የአገሪቱ ሴቶች 87 በመቶ ያህሉ፣ ባሎች ሰበብ አስባብ እየፈጠሩ ሚስቶቻቸውን መደብደባቸው ተገቢ ነው ብለው እንደሚያስቡ አረጋግጧል፡፡ የማሊን ሴቶች ተከትለው የጊኒና የኢትዮጵያ ሴቶችም ድብደባ ይገባል ብለው ያስባሉ ብሏል ጥናቱ፡፡
የኡጋንዳ መንግስት ቃል አቀባይ ኦፎኖ ኦፖንዶ ለ “ኒውስ ቪዥን” ጋዜጣ በሰነዘሩት አስተያየት፤ የጥናቱ ውጤት ትክክለኛ መሆኑን ገልጸው፣ በአብዛኞቹ የአገሪቱ የገጠር አካባቢዎች የቤት ውስጥ ጥቃት እንደሚፈጸምና ተገቢ ነው ተብሎ እንደሚታመን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
“አብዛኞቹ ባሎች የቤተሰቡ የገቢ ምንጭ በመሆናቸው በሚስቶቻቸው ላይ የፈለጋቸውን ጥቃት ቢሰነዝሩ ሃይ ባይ የለባቸውም፡፡ አንዳንዴ ደግሞ፣ ባሎች ሌላ ሚስት ወደቤታቸው ለማስገባት ሲሞክሩ ሚስቶች ነገሩን በመቃወም ከቤታቸው ለመውጣት ይሞክሩና በባሎቻቸው ድብደባና ግርፋት ይደርስባቸዋል፡፡” ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 8ኛውን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን ተረከበ
በአምስት ወራት ውስጥ ተጨማሪ 2 አውሮፕላኖች ያስገባል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደተለያዩ አለማቀፍ መዳረሻዎች የሚያደርገውን በረራ የበለጠ አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችለውን 8ኛውን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን መረከቡን ገለጸ፡፡
የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤት የሆነውን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን በመጠቀም ከጃፓን ቀጥሎ በአለማችን ሁለተኛው መሆኑን የገለጸው አየር መንገዱ፣ 8ኛውን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን ባለፈው ሳምንት መረከቡንና እስከ መጪው ታህሳስ ወር መጨረሻም ሌሎች ሁለት ተጨማሪ አውሮፕላኖችን እንደሚያስገባ ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡የመጀመሪያውን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን በነሃሴ ወር 2012 ማስገባቱን ያስታወሱት የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ መድህን፣ አውሮፕላኑ ለተሳፋሪዎች ምቾት በመስጠትና በአጠቃላይ ይዞታው በዘርፉ አቻ የማይገኝለት መሆኑን ጠቁመው፣ አየር መንገዱ ለወደፊትም የደንበኞቹን ፍላጎት ለማሟላት የአዳዲስ ቴክኖሎጂ ውጤቶች የሆኑ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በማስመጣት አገልግሎቱን የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ይህን ዘመናዊ አውሮፕላን በመጠቀምና አገልግሎት በመስጠት ከአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ መሆኑን የገለጸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በዚህ አውሮፕላን ወደተለያዩ የአፍሪካና የአውሮፓ ሃገራት፣ ብራዚል፣ አሜሪካ፣ ካናዳና ቻይና በረራ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡
አየር መንገዱ ቦይንግ 777፣ ቦይንግ 787ና ቦይንግ 737ን ጨምሮ 68 ያህል እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመጠቀም፣ በአምስት አህጉሮች ወደሚገኙ 82 አለማቀፍ መዳረሻዎች በረራ እያደረገ የሚገኝ አለማቀፍ ዝናን ያተረፈ ተቋም መሆኑንም አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ሰዓት ቪዥን 2025 የተባለውንና ስምንት የንግድ ማዕከላት ያሉት የአፍሪካ መሪ የአቪየሽን ግሩፕ ለመሆን የሚያስችለውን የ15 አመታት ስትራቴጂክ ዕቅድ ቀርጾ በመተግበር ላይ እንደሚገኝና ባለፉት ሰባት አመታት በአማካይ 25 በመቶ አመታዊ ዕድገት ማስመዝገቡንም አክሎ ገልጿል፡፡
የሻዳይ በዓል ዘንድሮ በሰቆጣ ከተማ በድምቀት ይከበራል
*የአካባቢውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ እስከ ግማሽ ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል
በዋግ ኸመራ ዞንና አካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነውን የሻዳይ በዓል፣ ከወትሮው በተለየ መልኩ በድምቀት ለማክበር እየተዘጋጀ መሆኑን የገለፀው የዋግ ልማት ማኅበር ዋልማ)፤የአካባቢውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ እስከ ግማሽ ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ አስታወቀ፡፡
የዋልማ ሊቀመንበር አቶ ምትኩ በየነ ከማኅበሩ ሥራ አስፈፃሚ አባላት ጋር በሰጡት መግለጫ፣ ሻዳይ፣ ከጥንት ጀምሮ በአካበቢው ሕዝብ ዘንድ በድምቀት የሚከበር ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓል ቢሆንም ተቀዛቅዞ እንደነበር ጠቅሰው፤ ከ7 ዓመት ወዲህ ግን ክልሉና የዞኑ አስተዳደር በዓሉ ሃይማኖታዊና ጥንታዊ ይዘቱን እንደጠበቀ ለትውልድ እንዲተላለፍና የቱሪስት መስህብ እንዲሆን ትኩረት ይሰጠው ዘንድ ባሳሰቡት መሰረት፣ ህልውናው ታድሶ እየተከበረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በየዓመቱ ከነሐሴ 16 እስከ 18 የሚከበረው የሻዳይ በዓል፣ ማኅበሩ ከተቋቋመ ከ2002 ወዲህ ለሦስት ዓመት ከልማት ጋር ተቀናጅቶ እየተከበረ መሆኑን ጠቅሰው፣ ማኅበሩ ዘንድሮም ለየት ባለ መልኩ፣ “ኅብረት ለዋግ ልማት” በሚል መሪ ቃል፣ ከፍተኛ አገር አቀፍ ልማታዊ ኅብረት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዘንድሮ በርካታ እንግዶች ተሳታፊ ይሆናሉ ያሉት አቶ ምትኩ፤ በዓሉን የሚያከብሩት የዋግ ዞን ልጃገረዶች ብቻ ሳይሆኑ በዓሉን ‹አሸንዳ› በማለት ከሚያከብሩት አጎራባች አካባቢዎች- ትግራይ፣ ላሊበላና ቆቢ የተውጣጡ ልጃገረዶችም እንዲሳተፉ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በአሉን ከልማት ጋር ለማስተሳሰር የተፈለገው አካባቢው በርካታ ዘርፈ ብዙ የልማት፣ የትምህርትና የጤና ችግሮች ስላሉበት ነው ያሉት ሊቀመንበሩ፤ አገሪቷ እነዚህ ችግሮች እያሉባት የምዕተ አመቱን ግቦች ማሳካት ያዳግታታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“አካባቢው በተራራ ስለተሸፈነ ለማልማት አስቸጋሪ ነው፣ እስካሁን በአገሪቷ የተከሰቱ የድርቅ አደጋዎችም አካባቢውን አልፈው ሲያጠቁ ቆይተዋል፣ በአካባቢው ተራራ የሚፈሰው ውሃ ህዳሴው ግድብ ውስጥ የሚገባ ስለሆነ ተራራው ደን ከለበሰ ከተራራው እየታጠበ የሚሄደው ደለል ግድቡን በመሙላት ዕድሜውን ያሳጥረዋል፣ በአስተዳደሩ ውስጥ ካሉ 232 ት/ቤቶች ውስጥ 217ቱ ደረጃ አንድና ሁለት ቢሆኑም ከ106 ት/ቤቶች 514 የመማሪያ ክፍሎች የዳስ ወይም የዛፍ ጥላ መማሪያ ናቸው፡፡ ከ125 ቀበሌዎች ውስጥ 23ቱ ምንም ዓይነት ቁሳቁስ የላቸውም፡፡ በዞኑ የዓይን ህክምና የሚስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም ህክምናውን የሚሰጥ ተቋም ባለመኖሩ 6,342 ወገኖች አደጋ ላይ ናቸው” ሲሉ ችግሮቹን በዝርዝር ተናግረዋል፡፡
“ለልማታዊ ኅብረቱ በሚገኝ ገቢ በተመረጡ ቀበሌዎች መዋዕለ ሕፃናት በመክፈት፣የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችንና የውስጥ ቁሳቁስ በማሟላት፣ የጤና ተቋማት በመገንባት እንዲሁም የዓይን ህክምና ተቋም በመክፈት ዋና ዋና ችግሮች የተባሉትን ለመቅረፍ አስበናል” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ሁሉም የበዓሉ ታዳሚ እንዲሆንና የልማት ዕቅዳቸውን እንዲደግፍ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
“ጅማሬ” የስዕል አውደርዕይ ዛሬ ይከፈታል
አስራ አራት አንጋፋና አማተር ሰዓሊያን የሚሳተፉበት “ጅማሬ” የተሰኘ የስዕል አውደርዕይ ዛሬ በ11 ሰዓት 30 ሽሮሜዳ ኪዳነምህረት ቤ/ክርስቲያን መንገድ ላይ ታቦት ማደሪያው ፊትለፊት በሚገኘው ሚራጅ ኮፊ ሮስተር ይከፈታል፡፡
የአውደርዕዩ አዘጋጅ አቶ ዮሐንስ አክሊሉ እንደገለፁት፤ አውደርዕዩ እስከ ሐምሌ 5 ቀን 2006 ዓ.ም ለ15 ቀናት ለተመልካች ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን በየሦስት ወሩ የሚዘጋጅ ፕሮግራም እንደሆነም ታውቋል፡፡
“እኛ እና አብዮቱ” ነገ ለውይይት ይቀርባል
በደርግ ዘመን ጠ/ሚኒስትር የነበሩት ፍቅረሥላሴ ወግደረስ “እኛ እና አብዮቱ” በሚል ርዕስ በፃፉት መፅሃፍ ላይ ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቤተ-መፃህፍትና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ ውይይት እንደሚካሄድ ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ፅሑፍ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሰለሞን ተሰማ ለውይይቱ መነሻ ሃሳብ እንደሚያቀርቡ ሚዩዚክ ሜይዴይ ጠቁሞ፤ የሥነ-ፅሁፍ ቤተሰቦች በውይይቱ ላይ እንዲገኙ ጋብዟል፡፡
“Visual Art Meets Fashion” ለ3 ቀናት ይጎበኛል ከ60 በላይ ሰዓሊያንና ቀራፂያን ይሳተፋሉ
በመርሲ ዲኮር ዲዛይንና ሞዴሊንግ ማሰልጠኛ ተቋም ለሁለተኛ ጊዜ የተዘጋጀ “Visual Art Meets Fashion” የተሰኘ የስዕልና ቅርፃ ቅርፅ አውደ ርዕይ ትላንት ከምሽቱ 11 ሰዓት ላይ ቦሌ መድኃኒዓለም አካባቢ በሚገኘው ካሌብ ሆቴል የተከፈተ ሲሆን መታሰቢያነቱ ለአርቲስት አለ ፈለገሰላም እና እጅግ ለተከበሩ ለዓለም ሎሬት ዶ/ር ሜድ ጥበቡ የማነብርሃን እንደሆነ ታውቋል፡፡ ትላንት በመክፈቻው ዕለት በዲዛይነር ምህረት ምትኩ የተሰናዳ የፋሽን ትርኢት የቀረበ ሲሆን የ57 ሰዓሊያንና የ6 ቀራፂያን ሥራዎች አውደርዕይ ተከፍቷል፡፡ አውደርዕዩ እስከፊታችን ሰኞ ምሽት ድረስ ለተመልካች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡ ማሰልጠኛ ተቋሙ ባለፈው ዓመት ለተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ መታሰቢያነት ተመሳሳይ አውደርዕይ አዘጋጅቶ እንደነበር በላከው መግለጫ አስታውሷል፡፡