Administrator

Administrator

 ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ መፍጀቱ ታውቋል
     ታዋቂው የሞባይልና የኮምፒውተር አምራች ኩባንያ አፕል፣ በ5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የዓለማችንን ምርጥ የቢሮ ህንጻ በካሊፎርኒያ እየገነባ መሆኑን ዘ ዴይሊ ሜይል ዘገበ፡፡ ግንባታው በመገባደድ ላይ የሚገኘው የአፕል ዋና መስሪያ ቤት የግንባታ ስምምነት የተፈጸመው ከ6 አመታት በፊት እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ህንጻው በ260 ሺህ ስኩዌር ሜትር ቦታ ላይ ማረፉንና 13 ሺህ ያህል ሰራተኞችን መያዝ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡
በክብ ቅርጽ ለተሰራውና የዙሪያ መጠኑ 1.6 ኪሎሜትር እርዝማኔ ላለው ለዚህ ግዙፍ ህንጻ የሚገጠሙት መስኮቶች በአለማችን በግዙፍነታቸው ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዙ የተነገረ ሲሆን የግንባታው ወጪ 3 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል ተብሎ ቢጀመርም ወጪው እየጨመረ መጥቶ 5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ዘገባው ገልጧል፡፡
1 ሺህ መኪኖችን የማስተናገድ አቅም ያለው የመኪና ማቆሚያ ስፍራ በሚኖረው በዚህ ህንጻ ግቢ ውስጥ 7 ሺህ ያህል ዛፎች መተከላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ግንባታው በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡

   ቻይና ባለፈው ወር በተመድ ማዕቀብ ከተጣለባት ሰሜን ኮርያ ጋር ስታከናውነው የቆየቺውን የተለያዩ የውድ ማዕድናት ምርቶች ግዢና የነዳጅ ሽያጭ ለማቋረጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የንግድ ማዕቀቦችን መጣሏን አስታወቀች፡፡ ሮይተርስ እንደዘገበው፤ሰሜን ኮርያ የውጭ ንግድ ምርቶች ሁለት ሶስተኛውን ያህል በመግዛት የምትታወቀው ቻይና፣ የሰሜን ኮርያ ዋነኛ የወጪ ንግድ ምርቶች የሆኑትን ወርቅና ሌሎች ውድ ማዕድናት ላለመግዛት ወስናለች፡፡ የቻይና መንግስት ከሰሜን ኮርያ የግዢ ማዕቀብ ከጣለባቸው ምርቶች መካከል ብረት፣ ወርቅ ቲታኒየም እንደሚገኙበት የጠቆመው ዘገባው፣ ሰሜን ኮርያ በ2013 ለውጭ ገበያ ካቀረበቺው ምርት 65 በመቶ የሚሆነውን የገዛቺው ቻይና እንደሆነች አስታውሷል፡፡
ቻይና ከዚህ በተጨማሪም ለሰሜን ኮርያ የአውሮፕላን ነዳጅ መሸጥ እንደማይቻል ከሰሞኑ ባወጣቺው ማዕቀብ ወስናለች ያለው ዘገባው፣ ማዕቀቡ በሰሜን ኮርያ የወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል መባሉን ገልጧል፡፡
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማና የቻይናው አቻቸው ዢ ጂፒንግ ባለፈው ሳምንት ዋሽንግተን ውስጥ በተካሄደው አለማቀፉ የኒውክሌር ደህንነት ጉባኤ ላይ ተገናኝተው በሰሜን ኮርያ የኒውክሌር እንቅስቃሴ ላይ ቻና ለመፍጠር መስማማታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ አሜሪካ ቻይና በሰሜን ኮርያ ላይ የጣለቺውን የንግድ ማዕቀብ በደስታ እንደተቀበለቺውም አክሎ ገልጧል፡፡

ባለፈው እሁድ ማለዳ ላይ...
አለማቀፉ የምርመራ ጋዜጠኞች ጥምረትና ሱደች ዜቱንግ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ፣ አለምን ያስደነገጠ ቁልፍ አለማቀፍ የቅሌት መረጃ ይፋ አደረጉ፡፡
የፓናማ ሰነዶች የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ቁልፍ መረጃ፣ ባለፉት አራት አስርት አመታት በድብቅ የተከናወኑ የዓለማችን ገናና ፖለቲከኞች፣ ባለሃብቶችና ታዋቂ ግለሰቦችን የገንዘብ ቅሌት ለአለም ያጋለጠ አነጋጋሪ አጀንዳ ሆኗል፡፡
ያሳለፍነው ሳምንት የዓለማችን ታላላቅ መገናኛ ብዙሃን ቀዳሚ ትኩስ ዜና የፓናማ ሰነዶች ቅሌት ነበር፡፡ ይሄው ቅሌት የዓለማችን ስመ ገናና ፖለቲከኞችና ባለጸጎች በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ወደ ሌሎች አገራት ማሸሻቸውንና ግብርን ለማምለጥ ሲሉ በውጭ አገራት በድብቅ ባቋቋሟቸው ኩባንያዎችና የንግድ ተቋማት ረብጣ ትርፍ ማጋበሳቸውን ያሳያል፡፡
በአለማችን የመረጃ ማፈትለክ ታሪክ እጅግ ትልቁ ነው የተባለውና ሞዛክ ፎንሴካ ከተባለው የፓናማ የህግ አገልግሎት ተቋም አፈትልኮ የወጣው ይህ ቁልፍ ሚስጥር፣ 11 ሚሊዮን ያህል የቅሌት መረጃዎችን የያዘ ሲሆን፣ በ76 የአለማችን አገራት ከሚገኙ መገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ 107 ያህል ጋዜጠኞችም ከአንድ አመት በላይ ለሚሆን ጊዜ በመረጃዎቹ ላይ ጥናት ሲያደርጉ ነበር ተብሏል፡፡  
እስካሁን በተገኘው መረጃ የ12 አገራት የወቅቱና የቀድሞ መሪዎች፣ ከ60 በላይ የአገራት መሪዎች ቤተሰቦችና ተባባሪዎች እንዲሁም ፖለቲከኞች በዚህ ቅሌት ውስጥ እንደተሳተፉ የታወቀ ሲሆን፣ ከቅሌቱ ጋር ንክኪ ያላቸው ኩባንያዎችና ተቋማት ቁጥርም 214 ሺህ ያህል እንደሚደርሱ ታውቋል፡፡ አነጋጋሪው መረጃ እ.ኤ.አ ከ1977 እስካለፈው ታህሳስ ወር የተከናወኑ ታላላቅ ቅሌቶችን የያዘ ሲሆን ጥብቅ ሚስጥሩን ለአመታት በእጁ ይዞ የቆየው የፎንሴካ የህግ ተቋምም መረጃው ከውጭ አካላት በተደረገበት ምንተፋ አምልጦት እንደወጣ በማስታወቅ፣ በቅሌቱ ተባባሪ ነው በሚል የቀረበበትን ውንጀላ አስተባብሏል፡፡
የፓናማ ሰነዶች ቅሌት በመገናኛ ብዙሃን ይፋ መደረጉን ተከትሎ በቅሌቱ ውስጥ ስማቸው ከተጠቀሱት የአገራት መሪዎች መካከል አስደንጋጩን ተቃውሞ ቀድመው ያስተናገዱት የአይስላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲግሙንዱር ዴቪድ ጉንላጉሰን ናቸው፡፡ በመሪያቸው ቅሌት ክፉኛ የተቆጡት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ አይስላንዳውያን አደባባይ ወጥተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን እንዲለቁ የጠየቁ ሲሆን፣ በብሪቲሽ ቨርጂን አይስላንድስ የንግድ ኩባንያ አቋቁመው ረብጣ ዶላር እያፈሱ ነው የተባሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩም በነጋታው ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል፡፡
የሩስያው ፕሬዚደንት ብላድሚር ፑቲን በቅሌቱ ስማቸው ከተነሳ የአለማችን መሪዎች አንዱ ቢሆኑም፣ የአገሪቱ መንግስት ግን በመሪዬ ላይ የተሰነዘረ መሰረተ-ቢስ ውንጀላ ነው ሲል አጣጥሎታል፡፡ በመሰል ቅሌት የተጠቀሱት የዩክሬኑ ፔትሮ ፖሮሼንኮም ረቡዕ ዕለት ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ራሳቸውን ከደሙ ንጹህ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ አሜሪካውያን ፖለቲከኞችና ታላላቅ ባለስልጣናት ምንም እንኳን እስካሁን ድረስ በቅሌቱ ስማቸው ባይነሳም፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ግን፣ የአገራቸው ታላላቅ ባለጸጎች ከመሰል ቅሌት ነጻ እንዳልሆኑ ረቡዕ ዕለት ተናግረዋል፡፡ በፓናማ ሰነዶች ቅሌት ውስጥ በራሳቸው አልያም በቤተዘመዶቻቸውና የስራ አጋሮቻቸው ተሳትፈዋል ተብለው ከተጠቀሱ አፍሪካውያን መካከል ኮፊ አናን፣ ጃኮብ ዙማ፣ ጆን ኩፎር እና ጆሴፍ ካቢላ ይጠቀሳሉ፡፡
በቅሌቱ ውስጥ አሉበት ከተባሉት ታዋቂ ሰዎች መካከልም፣ አሜሪካዊቷ ድምጻዊት ቲና ተርነር፣ አዲሱ የፊፋ ፕሬዚዳንት ጊያኒ ኢንፋንቲኖ፣ ታዋቂው የቦሊውድ የፊልም ተዋናይ አሚታባህ ባቻን፣ ታዋቂው የሆሊውድ ተዋናይ ጃኪ ቻን እና የአለማችን እግር ኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ይገኙበታል፡፡

    ኢዮሃ አዲስ ኢንተርቴይንመንትና ኤቨንት፤ በ9.5 ሚሊዮን ብር ጨረታ ያሸነፈው “ኢዮሃ ፋሲካ ኤክስፖ” ትላንት ተከፈተ፡፡ በኤክስፖው ላይ ከ450 በላይ የውጭና የአገር ውስጥ የንግድ ድርጅቶች መሳተፋቸውን የጠቆሙት አዘጋጆቹ፤ከ80 በላይ እውቅ ድምፃዊያንም ጐብኚውን እንደሚያዝናኑ የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ አዩ አለሙ ተናግረዋል፡፡
በኤክስፖው ልጆቻቸውን ይዘው ለመጐብኘት የሚመጡ ወላጆች፣የልጆቻቸው ጉዳይ እንዳያሳስባቸው ሲባል፣ ከ“ፀሐይ መማር ትወዳለች” አዘጋጆቹ ዊዝኪድስ ወርክሾፕ ጋር ኢዮሃ ስምምነት በመፍጠር፣ ወላጅ ልጆቹን አስረክቦ ከገባ በኋላ ሲጨርስ ከዊዝኪድስ ወርክሾፕ መረከብ እንደሚችል ወ/ሮ አዩ ገልፀዋል፡፡
በኤክስፖው 23ቱ ቀናት የተለያዩ ዘመናዊና ባህላዊ የውዝዋዜ እንዲሁም በርካታ የተሰጥኦ ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን ከዘመናዊ አውቶሞቢል ጀምሮ የተለያዩ ሽልማቶች መዘጋጀታቸውም ታውቋል፡፡ ጎብኚው በመረጃ እጦት እንዳይቸገር፣“ሁሉም ቤት” የተባለ የመረጃ አፕልኬሽን መዘጋጀቱም ታውቋል፡፤
የፋሲካው ኤክስፖ እስከ ሚያዝያ 22 የሚቆይ ሲሆን በመቀጠልም ኢዮሐ በቴክኒካል ፕሮፖዛል ያሸነፈውና የበጎ አድራጎት ስራን ለመስራት እየተዘጋጀበት ያለው የቀይ መስቀል ኤግዚቢሽን ከሚያዚያ 28 እስከ ግንቦት 2 ቀን 2008 ዓ.ም እንደሚያካሂድና ገቢው ሙሉ ለሙሉ በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች እንደሚውል ለማወቅ ተችሏል፡፡   

Saturday, 09 April 2016 10:09

የኪነት ጥግ

 (ስለ ቴሌቪዥን)
ሁሉም ቴሌቪዥኖች ትምህርታዊ ናቸው፡፡ ጥያቄው፡- ምንድን ነው የሚያስተምሩት ነው?
ኒኮላስ ጆንሰን
ሰዎች እርስ በእርስ ከመተያየት ይልቅ ሌሎች ማናቸውንም ነገሮች መመልከት እንደሚመርጡ ቴሌቪዥን አረጋግጧል፡፡
አን ላንደርስ
ቴሌቪዥንን በጣም ትምህርታዊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ለማለት እገደዳለሁ፡፡ አንድ ሰው ቴሌቪዥን በከፈተ በደቂቃ ውስጥ  ወደ ቤተ መፃህፍት ሄጄ አንድ ጥሩ መፅሃፍ አነባለሁ፡፡
ግሮቾ ማርክስ
ቲያትር ህይወት ነው፡፡ ሲኒማ ጥበብ ነው፡፡ ቴሌቪዥን የቤት ቁስ ነው፡፡
ያልታወቀ ደራሲ
ቴሌቪዥን? ከዚህ መሳሪያ ምንም ጥሩ ነገር አይወጣም፡፡ ቃሉ ግማሽ ግሪክና ግማሽ ላቲን ነው፡፡
ያልታወቀ ደራሲ
ቴሌቪዥን በቤትህ ውስጥ ልታገኛቸው በማትችላቸው ሰዎች እንድትዝናና ይፈቅድልሃል።
ዴቪድ ፍሮስት
ቴሌቪዥን 90 በመቶው እንቶ ፈንቶ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን የሁሉም ነገር 90 በመቶው እንቶ ፈንቶ ነው፡፡
ጌኒ ሮዴንቤሪ
የቴሌቪዥን አንዱ ትልቁ አስተዋፅኦ ነፍሰ ግድያን ወደ ትክክለኛ ቦታው ወደ ቤት መልሶ ማምጣቱ ነው፡፡
አልፍሬድ ሂችኮክ
ኤሌክትሪክ ባይኖር ኖሮ ሁላችንም ቴሌቪዥንን በሻማ ብርሃን እንመለከት ነበር፡፡
ጆርጅ ጎባል
በቴሌቪዥን የተፈጠረ ሰው በቴሌቪዥን ሊጠፋ ይችላል፡፡
ቴዎዶር ኤች ዋይት
ቴሌቪዥንን ለማዝናናት ብቻ ሳይሆን ሰዎች የተሻለ ህይወት እንዲመሩ ለማገዝ ልጠቀምበት እሻለሁ፡፡
ኦፕራ ዊንፍሬይ
ቴሌቪዥንን እንወደዋለን፤ ምክንያቱም ቴሌቪዥን የሌለበትን ዓለም ያመጣልናል፡፡
ሆዋርድ ዚን

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አይጥና አንድ እንቁራሪት በቀጠሮ ይገናኛሉ፡፡
አይጥ፤
“እመት እንቁራሪት፤ አንዳንዴ ከውሃ ወጥተሽ መሬት ላይ ፀሐይ ስትሞቂ ሳይሽ ‘ምነው ከዚች ጋር ጓደኝነት ብንጀምር?’ እያልኩ ልቤ ስፍስፍ ይላል፡፡”
እንቁራሪትም፤
“ሆድ ለሆድ የመነጋገር ነገር ጠፍቶን ነው እንጂ እኔም እኮ ባየሁሽ ቁጥር ‘ምነው ጓደኛ በሆንን’ እያልኩ አስባለሁ፡፡”
አይጥ መልሳ፤
“አየሽ አንቺ ውሃም ውስጥ፣ መሬትም ላይ፣ ኗሪ ነሽ፡፡ እኔ ግን መሬት ላይ ብቻ ኗሪ ነኝ”
እንቁራሪት፤
“እንደሱ ብለሽ ራስሺን አታሳንሺ፡፡ ይልቁንም፤ ምንጊዜም እንዳንለያይ እንስማማ፡፡ እግራችንን በገመድ እንሠር” አለቻት፡፡
አይጥም፤
“እጅግ የብልህ ዘዴ አመጣሽ፡፡ በቃ ገመድ እኔ ከየትም ከየትም ብዬ አመጣለሁ” አለች፡፡
እንደተባለው እግሮቻቸውን አቆራኝተው በገመድ አስተሳሰሩ፡፡
መሬት ላይ ባሉ ጊዜ ሁሉ ወዳጅነታቸው ግሩም ድንቅ ሆኖ ቆየ፡፡ እንቁራሪት ወደ ውሃ ውስጥ ገብታ ዋና ስትጀምር ግን ጣጣ መጣ፡፡
አይጥ ወዴት እንደምትገባ መላው ጠፋት፡፡ አይጥ ከመስመጥ በቀር ምንም ምርጫ አልነበራትም፡፡ አይጥ ተንደፋድፋ ሰመጠች፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ሬሣዋ ውሃው ላይ ሲንሳፈፍ ታየ፡፡
ታሪኩ ግን በዚህ አላበቃም፡፡ አሞራ ከሰማይ የአይጥን ሬሣ ፍለጋ መጣ፡፡ አይጢቱን ላፍ አድርጐ ወደ አየር ሲምዝገዘግ፤ እግሯ አብሯት የታሠረውም እንቁራሪት ተንጠልጥላ ወደ ሰማይ ወጣች፡፡ “ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ” ሆነ ነገሩ፡፡ ሁለቱም የአሞራ ራት ሆኑ!!
***
ጊዜን፣ ቦታን፣ ማንነትንና ተግባራዊ አንድነትን ያላገናዘበ መቀናጆ፤ መጨረሻው ክፉ ውድቀት ነው፡፡ ተያይዞ መንኮታኮት ነው፡፡ እንደ እንቁራሪት ውሃ ውስጥ፣ እንደ አይጥ መሬት ላይ የሚኖሩ፣ አንድ ዓይነት ነን ብሎ ማሰብ አጉል ህልም ነው፡፡ አስቀድሞ ነገር የወዳጅነቱ (የህብረቱ) ፋይዳ ምንድነው? ግቡስ ምን ነው? ምንስ ለመሥራት ነው? ሀገራዊ አንድነትን ስናስብ ሀገራዊ ፋይዳውን ማጤን፣ ለሁሉም ወገን ያለውን ፍሬ - ነገር ማሰላሰል፣ ተግባራዊ ሂደቱን መመርመርና ልብ ለልብ መነጋገር ቁልፍ ነገር ነው፡፡
የእንቁራሪትን የምድር - የውሃ ኑሮ በወጉ ማጥናት፤ አንዴ አይጥ አንዴ የሌሊት ወፍ ነኝ የምትለውንም አይጥ፤ ውስጧን ማመዛዘን እጅግ ወሳኝ መሆኑን አንዘንጋ፡፡ ከልዩ ልዩ መልካችንና ከልዩ ልዩ ይዞታችን ተነስተን ልንፈጥር የምንችለውን አገራዊ አንድነት ስናሰላው ልባዊ ግንኙነት ካላደረግን፤ ወይ “እባብ ለእባብ ይተያያል ካብ ለካብ”፣ “ወይ እርስ በእርሱ ሥጋን በኩበት ጠበሱ”፣ አሊያም “ድንጋይ በድንጋይ ላይ ቆሟል”፤ የከፋ መልክ ከያዘም ከታሪክ እንደምንማረው “ለምሣ ያሰቡንን ለቁርስ አረግናቸው” ዓይነት መበላለት ሊያስከትል የሚችል ሁኔታ ሊመጣ ይችላል፡፡ ከአድሮ ቃሪያ አካሄድ ይሰውረን፡፡
ከታሪካችን ካየናቸው ችግሮች አንዱ የሒስ ባህል አለመኖር ነው፡፡ ማንም ስህተቱን መቀበል ቀርቶ፣ ስህተት ከናካቴው አልታየም በሚባልበት አገር፣ ግትርነት መንሰራፋቱ አይታበሌ ነው፡፡ አማካሪ ምክርን ሂሳዊ ቢያደርግ ብዙ መንገድ መጓዝ ይቻላል፡፡ “ተባባሪ ዋይታ” ችግር አይፈታም፡፡ ይልቁንም እዬዬን ያገር ባህል ያደርጋል!
አልፎ ተርፎም፤ ብሶት እስኪጠራቀም፣ አድሮም እስኪገነፍል፣ ሲሸፋፍኑ መኖር እንደ ፖለቲካ ዘይቤ ይያዛል፡፡ እንዲህ ያለ ዘይቤ ሀገርን ያቆረቁዛል፡፡ ነጋ ጠባ ያንኑ ሐተታ ከማነብነብ አንዳንዴ “እህ?” ብሎ ማዳመጥ፣ ስለ አካሄዴ ምክራችሁን ለግሱኝ፣ ያልተዋጠላችሁን ጠይቁኝ ማለት ያባት ነው፡፡ አሁን ይህ ባህል የተጀመረ ይመስላል፡፡ ዋናው ዘላቂነቱ ነው!
ዛሬ በህይወት የሌሉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፤ በ97 ዓ.ም ምርጫ ማግስት በነበሩት ችግሮች ላይ ሒስ ሲያቀርቡ፤
“ዋናውና መሠረታዊ ችግር ንቀት ነው፡፡ ተጠቃዋሚዎች በምርጫው አዲስ አበባን ሲያሸንፉ ገዢውን ፓርቲ ናቁ፡፡ ገዢው ፓርቲ ገና ከመነሻው ተቃዋሚዎች በምንም ረገድ አያሸንፉም የሚል ንቀት አድሮበት ነበር” ብለው ተናግረዋል ይባላል፡፡
በሁለቱም ወገን የታየው ንቀት ከፊውዳላዊ ተዓብዮ የመነጨ ነው፡፡ የመደብ መሠረታችን ይብዛም ይነስ በእያንዳንዱ የህይወት ዱካችን ላይ አሻራውን ማሳረፉ አይቀሬ ነው፡፡ ንቀት ካለን ለትግል ያለን ዝግጁነት ለቋሳ ይሆናል፡፡ ንቀት ካለን ወደ ማንጐላጀት እንጂ ወደ ንቁነት አንራመድም፡፡ ንቀት ካለን ጊዜን በአግባቡ አንጠቀምም፡፡ ንቀት ካለን የአገሩ ቁንጮ እኛ ብቻ ነን የሚል ዕብሪት ይጫነናል፡፡ ምንም አይነት ሒስ አንቀበልም፡፡ የተሠሩትን ስህተቶች ጨርሶ እንዳልነበሩ ስለምንቆጥር፣ ጥፋቶችን ከማየት ይልቅ ሌሎች ላይ ማላከክን ሥራዬ ብለን እንይዘዋለን፡፡
ይህ በፈንታው ሁሉን ኮናኝ፣ ሁሉን ረጋሚ ያደርገናል፡፡ ይሄኔ እንግዲህ ጨዋታው ሁሉ “Do damned don’t damned” የሚሉት ይሆናል ፈረንጆቹ! ሠራህም ትረገማለህ፣ አልሠራህም ትረገማለህ፡፡ ይሄኔ አገር ከሩጫ ወደ መራመድ፣ ከመራመድ ወደ መዳከር፣ ከመዳከር ዝሎ ወደ መቆም ትመጣለች፡፡ ፍትሐችን ልፍስፍስ፣ ዲሞክራሲያችን ወንካራ፣ መልካም አስተዳደሩ “አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” የሚል፣ ልማቱ ህልም እልም፣ ለውጡ አገም - ጠቀም፣ የህዝብ ቁጥር ከአፍ እስከገደፉ፣ የሥራ አጡ መጠን አበስኩ ገበርኩ ወዘተ. ይሆንና ነገን መፍራት ግድ ይሆናል፡፡ ነገን የሚሠራ ሰው ጥርጣሬ ፎቅ ይሠራበታል! ከዚህ ይሰውረን!
ጥርጣሬ የልብ ለልብ መነጋገር ጠር ነው፡፡ የብሔራዊ መግባባት ሃሳብ እስከዛሬ ሲብላላ ኖረ እንጂ ከልብ አልተሞከረም፡፡ የህግ የበላይነትን አምኖ፣ የዲሞክራሲን መላ በአግባቡ ተረድቶ፣ የዜጐች እኩል ተጠቃሚነትን ተማምኖ፣ ባህላዊ የመግባቢያ መንገዶችን ፈትሾ በቁርጠኝነት ከታጓዙ፣ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡ እስከዛሬ አልተሞከረም፤ እንሞክረው፡፡ “አባቴ፤ ብዙ መንገድ አለ፡፡ በየቱ እንሂድ? ባልተሄደበት” አሉ የሚባለው ለዚህ ነው፡፡  

“ደምሴ ዋኖስ፤ ግጥሙም፣ ዜማውም ሃሳቡም የኔ ነው ማለቱ አሳዝኖኛል”

  ዕውቅ ኮሜዲያኖች ተሰባስበው በህብረት የሰሩትና በህጻናት ሳይቀር ተወዳጅነትን ያተረፈው የታላቁ ህዳሴ ግድብ “8100A” የተሰኘው ማስታወቂያ ሰሞኑን የባለቤትነት ውዝግብ አስነስቷል፡፡
ውዝግቡ የተነሳው ባለፈው እሁድ በማስታወቂያው ላይ የተሳተፈው ኮሜዲያን ደምሴ ዋኖስ፣ በኢቢሲ የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ የማስታወቂያው ሃሳብ አመንጪም ሆነ የግጥሙና ዜማው ባለቤት “እኔ ነኝ” ብሎ መናገሩን ተከትሎ ነው፡፡
 “ደምሴ ዋኖስ ለምን እንደተሳሳተ ባላውቅም፣ ግጥሙም፣ ዜማውም ሃሳቡም የኔ ነው ብሎ  መናገሩ አሳዝኖኛል” ያለው የምዕራፍ ፕሮሞሽን ባለቤት ወልደሩፋኤል ዓለሙ (ቢኒ ምዕራፍ) በበኩሉ፤ የ“8100A” ማስታወቂያን ሃሳብ ያፈለቅሁት እኔ ነኝ ሲል አስረግጦ ይናገራል። እንዲያም ሆኖ ሁሉም ባለሙያ የየራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን አልካደም፡፡ “እንደ መነሻ እኔ ብሰራውም የተሻለ ለዛና ውበት እንዲኖረው ሁሉም የየራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል” ብሏል - ቢኒ ምዕራፍ፡፡ ተጀምሮ እስኪያልቅ ግን የራሱ ሃሳብ መሆኑን ማስረጃዎች እየጠቀሰ ያስረዳል፡፡እስከ ዛሬ የምንሰማቸው የባለቤትነት ውዝግቦች በትያትር ወይም በፊልም ጽሁፎች አሊያም  በዘፈኖች ዙሪያ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ተራው በማስታወቂያ ሃሳብና ግጥም ላይ ሆኗል፡፡  
ለመሆኑ የባለቤትነት ውዝግብ መነሻው ምን ይሆን? ማስታወቂያው ያለ ክፍያ በነጻ የተሰራ በመሆኑ የጥቅም ጉዳይ መንስኤ ሊሆን አይችልም። ዝናም እንዳይባል ሁለቱም ባለሙያዎች ታዋቂ ከመሆናቸው አንጻር ብዙም የሚያስኬድ አይመስልም፡፡ ጉዳዩን የውዝግቡ ባለቤቶች  ካልነገሩን በቀር መላ ምታችን የትም አያደርሰንም፡፡ የአዲስ አድማሱ ደረጀ በላይነህ፤ 200 ያህል የሙዚቃ ክሊፖችን እንዲሁም በርካታ የሬዲዮና ቴሊቪዥን ማስታወቂያዎችን እንደሰራ ከሚገልጸው ቢኒ ምዕራፍ ጋር ውዝግብ ስለተነሳበት የህዳሴ ግድብ ማስታወቂያና እግረመንገዱን በሥራዎቹ ዙሪያ ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጓል።
“8100 A” የተሰኘው የህዳሴ ግድብ ማስታወቂያ የባለቤትነት ጥያቄ አስነስቷል፡፡ ማነው የሃሳቡ አፍላቂ? እስቲ ስለ ጉዳዩ በዝርዝር ንገረኝ…እንዴት ነው ሥራው የተጀመረው?
በመጀመሪያ ለሕዳሴው ግድብ ማስታወቂያ ለመስራት ለሚፈልጉ ሰዎች ጥያቄ ሲቀርብ ነበር፣ “ለምን  በኮሜዲያን አልሰራውም?” የሚል ሀሳብ በውስጤ የተፈጠረው፡፡ በዚህ መልክ መሥራት የፈለኩትም ለግድቡ ሥራ የሕዝብ ተሣትፎን ለመጨመር፣ ሕዝቡ እየተዝናና ማየትና መስማት ያስፈልገዋል በሚል ነበር፡፡ ተሣተፉ ሲባል አስገዳጅ እንዳይመስል፣ ለዛ ባለው ሁኔታ ውስጥን እንዲቆሰቁስ ነው ያንን መንገድ የመረጥኩት፡፡ በዚህ ስሜት ውስጥ እያለሁ “በሦስት ብር!...በሦስት ብር!” የምትለዋ ሃሳብ ከነዜማዋ መጣችልኝ፡፡  ከዚያም ወደ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ አስተባባሪ ጽ/ቤት ደውዬ አቶ ዮናስ የሚባሉ ሰው አገኘሁና ሃሳቡን ነገርኳቸው፣ እሳቸውም ሂድበት (go ahead) አሉኝ፡፡ በመቀጠል ያማከርኩት ኮሜዲያን ማርቆስን ነው፣ እርሱም “በጣም አሪፍ ነው፣ ፍልፍሉን አማክረው!” አለኝ። በዚህ ሂደት ላይ እያለሁ ደምሴ ዋኖስና ሌሎቹም ተጨመሩና በተለምዶ ቺቺኒያ እሚባለው ሠፈር “ግራንድ ሬስቶራንት” ተገናኝተን መከርን፡፡ በተለይ ኮሜዲያን እያዝናኑ ሃሳቡን ወደ ሕዝቡ የማድረስ ተሰጥኦ እንዳላቸውና ሙያቸው ለዚያ የተመረጠ እንደሆነ አወራኋቸው፡፡
ከዚህ ቀደም በትወናና በሌላ መልክ ከተሠሩት ማስታወቂያዎች በተለየ ሕዝቡ ውስጥ ለመግባት፣ በግጥምና ዜማ ታጅቦ በክሊፕ መልክ ቢሠራ ለሚለው ሃሳቤ የእነርሱን አስተያየት ጠየቅኋቸውና በቴፕ ሪከርደር የቀዳሁትን አሰማኋቸወ፡፡ በዚያ ተስማሙና እንቅስቃሴው ቀጠለ፡፡ በሚቀጥለው ቀጠሮዋችን ስንገናኝ፣ ግጥሙ ላይ ትንሽ ማሻሻያ ተደረገና ወደ ድምጽ ስቱዲዮ ገባን፡፡ ስቱዲዮ ስንገባ ዘሪሁን እሸቱ ከሚባል ጐበዝ የሙዚቃ አቀናባሪ ጋር ለሁለተኛ ጊዜ ግጥሙን አሻሻልነው፡፡ አሰፋ ተገኝ የሚባል ኮሜዲያን አንድ ሁለት ስንኞች ጨመረ፡-
አገራችን አድጋ እኛም እንድንኮራ
በራሳችን ገንዘብ ግድቡ ይሠራ፡፡ ---- የሚል፡፡
ኮሜዲያን ማርቆስ በበኩሉ፤
አይገድብም  ቢሉ እንገድበዋለን
ጥቅም የለውም ቢሉ እንጠቀማለን
ብር አለቀ ቢሉ ገና እናዋጣለን
አንዴ ጀምረናል እንጨርሰዋለን …የሚለውን አከለ፡፡  
እኔ ደግሞ፡-
ጊዜው የሩጫ ነው ፈጣን ነው ዘመኑ
መኪና ለመያዝ ሞባይሎን ይጫኑ፡፡… የሚሉትን ስንኞች አበረከትኩ፡፡ ዜማው ላይ ደግሞ “በ3 ብር በ3 ብር” የሚለውን አከልኩበት፡፡ ደምሴ ዋኖስ “8100” የሚለውን ዜማ ጨመረ፡፡ ከዚያም እነ ማይ ክርስቶስና ሌሎቹም ተጨማመሩና ሥራውን ከፍ አደረግነው፡፡ ለነገሩ እንደ መነሻ እኔ ብሠራውም የተሻለ ለዛና ውበት እንዲኖረው ሁሉም የየራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ ለዚህ ሥራቸው ደግሞ ትልቅ አክብሮት እሰጣለሁ፡፡
አንዳንዴ ግን እኛ ሀገር ያለ አግባብ የሰዎች የሥራ ዋጋ ሲነጠቅና ሲዛባ ይታያል፡፡ ባለፈው እሁድ የሆነውም ይኸው ነው፡፡ ደምሴ ዋኖስ በምን እንደተሳሳተ ባላውቅም፣ ግጥሙም፣ ዜማውም ሃሳቡም የኔ ነው ብሎ በቴሌቪዥን መስኮት መናገሩ አሳዝኖኛል፡፡ “ኮሜዲያን ጋር ሄጄ ሠራሁት፣ ቀረፃውን ምዕራፍ ፕሮሞሽን ሰራው” ነበር ያለው። እንዲህ ባይደረግ መልካም ነው፡፡ ሰው ለሠራው ሥራና ለደከመው ድካም ተገቢውን ዋጋ ማግኘት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡
ወደ ዋናው ጉዳይ ስንመጣ እንዳልኩህ፣ ይህንን የ8100 A ማስታወቂያ የሠራሁት እኔ ነኝ፡፡ ይህንን እውነት ዛሬም ወደፊትም በልበሙሉነት እናገራለሁ። እንደምታውቀው የሕዳሴው ግድብ ሥራ የሚሰራው በነፃ ነው፡፡ ማንም ሰው ከግድቡ ሥራ ክፍያ አይጠብቅም፡፡ እኔም ለማስታወቂያው ሥራ የሚያስፈልገውን ሙሉ ወጭ ሸፍኜ ነው የተሰራው። የግድቡ አስተባባሪ ጽ/ቤት ያገዘን ትራንስፖርት በማዘጋጀት ብቻ ነው፡፡ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የኮሜዲያኑን ወጭ ሁሉ የቻልኩት እኔ ነኝ፡፡ ፕሮዳክሽኑም የኔ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ግምት ሊሰጠው ይገባ ነበር፡፡
እስቲ ስለ ክሊፕ ሥራዎችህ አጫውተኝ… ለመሆኑ አርቲስቶች የቪዲዮ ክሊፕ ለማሠራት ወዳንተ ሲመጡ እንዴት ነው የምትቀበለው?
በመጀመሪያ አንድ ድምፃዊ ወደ እኔ ሲመጣ ሙዚቃውን ይዞ እንዲመጣ እጠይቃለሁ፤ ከዚያም ሙዚቃውን አዳምጣለሁ፡፡ ግጥሙና ዜማው ቆንጆ ሆኖ ካገኘሁት እዚያው መሥራት እንደምንችል አበስረዋለሁ፡፡ ከዚያም ወደ ዋጋው እንገባለን፡፡ ግጥምና ዜማው ቅንብሩ ጥሩ ካልሆነ፣ አስተያየት  እሰጣለሁ፡፡ ግጥሙ ይሄ ይጐድለዋል፣ ዜማውም እንዲህ ተደርጐ ቢስተካከል… የሠራልህን ሰው አነጋግረው እለዋለሁ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ግጥሞች ላይ ሀሳብ መሥጠት ስለምችል፤ ጠቅላላ የዘፈኑ ቅርጽ እንዲህና እንዲያ ቢሆን ገበያ ወስጥ መግባት ትችላለህ፤ ግጥሙ ብዙ አቅም የለውም፣ ሃሳቡ ብዙ የደረጀ አይደለም፤ ዜማዎቹም ውስጥን ኮርኳሪ አይደሉም ብዬ ሃሳብ እሰጣለሁ፡፡
ግጥሙና ዜማው የሚያረካ ከሆነ ዋጋ እንስማማና ስክሪፕት ወደ መፃፉ እንገባለን፤ አንድ አምስት ቀናት ወስጄ በጥሞና ለመሥራት እሞክራለሁ፡፡ ምን መሠለህ? ክሊፕ ይነስም ይብዛ የሀገር መልክ አለው። እዚያ ድረስ ዘልቄ እጨነቃለሁ፣ አምጣለሁ። የሙዚቃ ክሊፕ ሥራ በጣም ከባድ ሥራ ነው፡፡ ስክሪፕት ከፃፍኩ በኋላ ቀጣዩ ከዘፋኙ ጋር በስክሪፕት ጉዳይ መነጋገር ነው፡፡ በዚያ ከተስማማ የቀረፃውን ቀን እንቆርጣለን፣ ካልተስማማ፣ ሃሳብ ይሰጠኝና ሃሳባችንን ለማጣጣም እንሞክራለን፡፡ ከዚያ በኋላ የቀረፃው መቸት ከታሪኩ ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ እንሞክራለን፡፡
እኛ ሀገር እንደምታውቀው የበጀት ችግር ስለሚኖር ክሊፖች ያን ያህል አመርቂና ውብ አይሆኑም፡፡ በጀት ሲኖረው፣ ከቦታ አመራረጥ ጀምሮ አለባበስና የምትጠቀምባቸውን ቁሳቁሶች ሁሉ የተሻሉ ታደርጋቸዋለህ፡፡ በጀት ከሌለህ ርቀህ ሳትሄድ፣ ለቀረፃው ተስማሚ ባልሆነ ሁኔታ ስለምትሠራ ክሊፖቹ የልብ የማያደርሱና የጥበባቸው ልክና ከፍታ የተዛነፈ ይሆናል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን የዘፋኙን የልብ ምኞት ለማድረስ ባለን ቁሳቁስና ሁኔታ የተሻለ ነገር ለመሥራት ዕውቀትና አቅማችንን ሁሉ ሳንሰስት እንጠቀማለን፡፡
በአጋጣሚ ግጥሙ ቀሽም፣ ዜማው ደካማ፣ ቅንብሩ ልፍስፍስ ቢሆን ምን ታደርጋለህ?
በተለይ አሁን አሁን ግጥም፣ ዜማና ቅንብር በሚገባ የማጣጥምበት ጆሮ አለኝ፡፡ ስለዚህ አጣጥሜ አድማጩን የማይመጥን ከሆነ ዘፋኙ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል፣ ምናልባትም ለቴሌቪዥን መስኮት እንኳ እንደማይደርስ እነግረዋለሁ፡፡ እኔ ነጋዴ ብቻ አይደለሁም፣ ውስጤ ያላመነበትንና የሚቆረቁረኝን ነገር መሥራት አልፈልግም፡፡ ይህን ሳደርግ ደግሞ ዘፋኙን በፍቅር አግባብቼ ነው፡፡ ከቻለ ዜማውንና ግጥሙን እንዲያስተካክል፣ ያንን ካደረገ ብቻ እንደምሠራለትም እነግረዋለሁ፡፡
አይሆንም ብለህ የመለስካቸው ድምፃውያን አሉ?
እጅግ በጣም ብዙ! ብዙ አሉ፡፡ ከነዚያ ውስጥ አስተካክለው የመጡ አሉ፡፡ አንድ ሦስት ያህል ዘፋኞች ደግሞ ግጥሙና ዜማው ላይ ሃሳብ ሰጥቼ፣ አግዣቸው ዳግመኛ የሠሩ አሉ፡፡ ሳይመጡም የቀሩ ብዙ አሉ፡፡
በክሊፕ ሥራ ላይ አስገራሚ ገጠመኞች ይኖሩሃል ብዬ አስባለሁ…
ክሊፕ ስንሠራ ከአዲስ አበባ ከተማ ርቀን ወጥተን የምንሠራበት ጊዜ አለ፡፡ አንድ ጊዜ ከከተማ ወጥተን ምንም ነገር የሌለበት ሜዳማ ሥፍራ ልንሰራ ሄደን፣ ሁሉን ሰርተን ከጨረስን በኋላ የሆኑ ወጣቶች መጡና ለቦታው መክፈል አለባችሁ አሉን፡፡ “ለምንድነው የምንከፍለው?” ስንል “ሳሩን ረግጣችሁታል ይደርቃል” አሉን፡፡ ክፈሉ አንከፍልም ሃይለኛ ፀብ ተነሳ፡፡ ድንጋይ አንስተው መኪና ሊሠብሩብን፣ ሆነ፡፡ ከዚያ እኔ ሾፌሩንና ልጆቹን ካስገባሁ በኋላ ለማግባባት ሞከርኩ፡፡ መኪናው እየሄደ ነበር፣ ልክ ልጆቹ ድንጋዩን ሲጥሉ ተንደርድሬ መኪና ውስጥ ገባሁ፡፡ አመለጥን፡፡ መኪናው በድንጋይ ቢመታም መስታወቱ አልተነካም፡፡ የድንጋይ እሩምታ አወረዱብን፡፡ አንዳንዴ እንዲህ ይገጥምሃል፡፡
አንዴ ደግሞ እንዲህ ሆኗል፡፡ ይህ በቅርብ የገጠመኝ ነው፡፡ አንድ ጋራዥ ውስጥ የሚሠራ ሥራ ነበር፡፡ ገፀ ባህሪው ስደት ሄዶ ወደ ኋላ በምልሰት ስለ ሀገሩ የሚያስብበት ቦታ ስለነበር እዚያ ለመሥራት ባለጋራዡ ፈቀደልኝ፡፡ እዚያ ጋራዥ ውስጥ ቀረፃ ጀምረን ሳለ ድንገት ግርግር ተነሣ፡፡
“ማነው? ምንድነው?” ስንል “ማን ፈቀደላችሁ?” ተባለ፡፡ ለካ የፈቀደልን ጋራዡን ተከራይቶ የሚሠራው ሰው ነው፡፡ ለነገሩ ሥራው ማንንም አይጐዳም፣ ዘፈኑም ሀገርህ ውስጥ መሥራት ብትችል፣ የሕሊና ነፃነት ታገኛለህ፤ ውጭ ሄደህ ሰው ቤት ከምትሠቃይ የሚል ነበር፡፡ ለባለጋራዡ ይህን ሃሳብ ስነግረው፤ “ይህማ እዚህ መሠራት አለበት፣ ወገኖቻችንን ከስደት ለመታደግ ሁላችንም መረባረብ አለብን” ብሎ ነበር የፈቀደልን፡፡ ከኋላ የመጣው ሰውዬ ግን “ማነው?” ብሎ ብረት ላጥ አድርጐ አውጥቶ ግንባሬን ሊለኝ ሲል፣ አጠገቤ የነበሩት የሥራ ባልደረቦቼ ተንደርድረው ያዙት፡፡ ከዚያ በኋላ ትንሽ በጥፊ ነገር ላስ አደረገኝ፡፡ ከዚያ ግርግር ላለመፍጠር ተጠነቀቅሁ፡፡ ሃሳቡን ያለመረዳት ይሆናል በሚል ላግባባው ሞከርኩ፡፡ ሰውየው ጤናማ አስተሳሰብ አልነበረውም፡፡ እናም “ና” ብዬ ጠርቼው የቀረጽኩትን ሁሉ ሠረዝኩት፡፡ “ሌላ ጊዜ ሲገባህ እንገናኝ ይሆናል!” ብዬው ትተነው ሄድን፡፡ ከዚህም የባሰ ሁኔታ ሊገጥምህ ይችላል፡፡
ሌላው ገጠመኝ ደግሞ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ውጭ ጉዳይ ጀርባ ጫካ ነገር ውስጥ እየቀረጽን እያለ ድንገት፣ መሬት ለመሬት እየተሳቡ የሚመጡ ሰዎች አየን፡፡ የፖሊስ ጃኬት የለበሱ ነበሩ፡፡ “ምንድነው?” ስንል “ቁም ባለህበት! እንዳትንቀሳቀስ!” ተባልን። ዘፋኝ የለ፣ ተወዛዋዥ የለ፣ ሁላችንንም አፋፍሰው ወደ ውጭ ጉዳይ ይዘውን ሄዱ፡፡ እዚያ ተወስደን አንድ ሰዓት ያህል አለቃቸው እስኪመጣ ጠበቅን። ከተወዛዋዦቹ አንዱ የማረሚያ ቤት ተወዛዋዥ ስለነበረ እዚያ ቦታ መቅረጽ ችግር የለውም፣ መታወቂያዬን አሳያለሁ ብሎን ነበር፡፡ በኋላ ግን ወቀሳው በእርሱ ባሰ፡፡
በመጨረሻ “እዚህ ቦታ ላይ ቀረፃ አይካሄድም፤ ይህ ደግሞ ለጋራ ደህንነታች ነው፣ ይቅርታ አድርጉልን! እናንተ ያገራችን የጥበብ ሰዎች እንደሆናችሁ እናውቃለን” ብለው አስተምረው ለቀቁን! እንደዚህም ሆነን እናውቃለን!


• መንግስት በዓመት ለውጭ እዳ ከ900 ሚሊዮን ዶላር በላይ ይከፈላል
• የወለድ ክፍያው ብቻ በዓመት ወደ 300 ሚ. ዶላር ይጠጋል
• የአገር ውስጥና የውጭ ጠቅላላ እዳ 770 ቢ. ብር ሆኗል

     ባለፉት አምስት አመታት በፍጥነት እየገዘፈ የመጣው የመንግስት የውጭ እዳ 20 ቢ. ዶላር እንደደረሰ ሰሞኑን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያስረዳል፡፡ በስድስት ወራት ውስጥ ለውጭ እዳ ክፍያ 450 ሚ. ደላር ተከፍሏል፡፡ ከዚህም ውስጥ 140 ሚ. ዶላር የወለድ ክፍያ ነው፡፡
በ2001 ዓ.ም የመንግስት የውጭ እዳ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በታች እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን፤
በታህሳስ ወር የእዳ ክምችቱ ሃያ ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ከዚያ ወዲህ ባሉት ወራት እስከ ሰኔ የበጀት መዝጊያ ድረስ የሚመጡ ብድሮች ሲጨመሩበት፣ እዳው ወደ 22 ቢሊዮን ዶላር ሊጠጋ ይችላል፡፡
በአምስት አመታት ውስጥ ወደ አራት እጥፍ ከገዘፈው የእዳ ክምችት ጋር፤  እዳ ከነወለዱ
ለመመለስ አገሪቱ የምታጣው ገንዘብም በእጅጉ ጨምሯል፡፡ በ2001 ዓ.ም፣ እዳ ለመመለስ ኢትዮጵያ የከፈለችው 80ሚ. ዶላር አይሞላም ነበር፡፡የዘንድሮው ክፍያ ከ900 ሚ. ዶላር በላይ ይሆናል፡፡
 ከዚህም ውስጥ የብድር ወለድ ለመክፈል የሚውለው ገንዘብ ወደ 300 ሚ. ዶላር ይጠጋል ተብሎ
ይገመታል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ግን የወለድ ክፍያው ከ30 ሚ ዶላር በታች ነበር - አምና 250 ሚ.ዶላር፡፡ በሌላ በኩል፤ የመንግስት የአገር ውስጥ ብድርም እንዲሁ፤ በአምስት ዓመታት ውስጥ፣ ከመቶ
ቢሊዮን ብር ወደ 350 ቢሊዮን ብር ጨምሯል፡፡ እስከ ታህሳስ ወር ድረስ ጠቅላላ የመንግስት የአገር ውስጥና የውጭ እዳ 770 ቢ. ብር እንደደረሰ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ይገልጻል፡፡        ካንሰር እያደገ የመጣ የጤና ችግር መሆኑንና በአገሪቱ በየአመቱ 44 ያህል ሺህ ሰዎች በካንሰር ሳቢያ ለሞት እንደሚዳረጉ፤ 77 ሺህ የሚደርሱ ሰዎችም በካንሰር እንደሚጠቁ “አናዶሉ ኤጀንሲ” ዘገበ፡፡በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የካንሰር መከላከልና ቁጥጥር ፕሮግራም የቴክኒክ አማካሪ ዶክተር ኩኑዝ አብደላን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የካንሰር ችግር በመስፋፋት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚከሰተው የሞት መጠን 5.8 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍነውም በካንሰር በሽታ ሳቢያ የሚከሰት ሞት ነው፡፡ በአገሪቱ ለካንሰር ተጋላጭ በመሆን ረገድ ሴቶች ቅድሚያውን እንደሚይዙና ይህም እጅግ አሳሳቢእንደሆነ ለ“አናዶሉ ኤጀንሲ” የተናገሩት ዶክተር ኩኑዝ አብደላ፣ በካንሰር ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል በሚል ሪፖርት ከተደረጉት መካከል ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ብለዋል፡፡ በአገሪቱ በአዋቂ ሴቶች ላይ ከሚከሰቱት የካንሰር አይነቶች መካከል ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው የጡት ካንሰር እንደሆነም አስረድተዋል፡፡መንግስት ካንሰርን ለመከላከልና ለማከም ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ በተመረጡ 118 ሆስፒታሎች የማህጸን በር ካንሰር ምርመራና ህክምናን ለማስፋፋት እየተሰራ እንደሚገኝ፤ የመድሃኒት አቅርቦትና ለካንሰር ህክምና የሰው ሃይል ማሟላትም ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙበት ገልጿል፡፡

    አርጀንቲናዊው የአለማችን የእግር ኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ፤ ከዚህ በፊት ይጠቀምበት የነበረውን ጫማውን በግብጽ ለበጎ አድራጎት የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ በሚደረግ ጨረታ ላይ ለሽያጭ እንዲቀርብ በስጦታ መልክ ማበርከት እንደሚፈልግ መናገሩ በርካታ ግብጻውያንን ማበሳጨቱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ሜሲ መልካም ነገር በማሰብ ጫማውን በስጦታ ለማበርከት እንደሚፈልግ በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ቢናገርም፣ ጉዳዩ በግብጻውያን ዘንድ በንቀት መተርጎሙንና ሰሞንኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ የአገሪቱ ፓርላማ አባል የሆኑ ግለሰብም አልአሲማህ በተባለው ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው የሜሲን ድርጊት በማውገዝ፣ለሜሲና ለአርጀንቲና የራሳቸውን ጫማ እንደሚሰጡ መናገራቸውን ገልጧል፡፡
የግብጽ እግር ኳስ ማህበር ቃል አቀባይ አዝሚ መጋሄድ በበኩላቸው፤ የሜሲን ድርጊት በማውገዝ፣ግብጻውያን የእሱን ድጋፍና እርዳታ እንደማይፈልጉና ጫማውን ራሱ እንዲጫማው አልያም የድሆች መናኸሪያ ለሆነች የአርጀንቲና ምንዱባን እንዲሰጥ መክረውታል፡፡
የእግር ኳስ ተጫዋቹ ድርጊት በግብጽ ላይ የተደረገ ብሄራዊ ንቀት ነው በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመው የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም ሊሆን የቻለው ጫማ በግብጽና በሌሎች የአረብ አገራት እንደ አንድ የንቀት ምልክት ተደርጎ የሚታይ በመሆኑ ነው ብሏል፡፡