Administrator

Administrator

 የአንበሳ ጀግንነት ከአዳኝ ቀስት አያድነውም።
የአፍሪካውያን አባባል
ደስተኛ ህዝብ ታሪክ የለውም፡፡
የቤልጂየሞች አባባል
ጦርነት ላልቀመሱት ጣፋጭ ነው፡፡
የላቲኖች አባባል
ሽንፈት የሚመረው ስትውጠው ብቻ ነው፡፡
የቻይናውያን አባባል
እውነት የያዘን ሆድ በበላ እንኳን አይበሱትም፡፡
የሃውሳ አባባል
እሳት ያቃጠለው ሰው ሁልጊዜ አመድ ያስፈራዋል፡፡
የሶማሌያውያን አባባል
መጥበሻው ካልጋለ ማሽላው አይፈነዳም፡፡
የዮሩባ አባባል
ዝሆን ላይ የሚጮህ ሞኝ ውሻ ብቻ ነው፡፡
የአንጎላውያን አባባል
በግድ ድስት ውስጥ የገባ አጥንት ድስቱን መስመሩ አይቀርም፡፡
የቼዋ አባባል
አይጥ የገደለ ዝሆን ጀግና አይባልም፡፡
የካሜሩያውያን አባባል
ትዕግስት የገነት ቁልፍ ነው፡፡
የአልባንያውያን አባባል
ቤትህን ከመምረጥህ በፊት ጎረቤትህን ምረጥ፡፡
የሶሪያውያን አባባል
ፈረሱ ከሚጠፋ ኮርቻው ይጥፋ፡፡
የጣልያኖች አባባል
ምንም ዓይነት ምስጢርህን ከራስህ አትደብቅ፡፡
የግሪካውያን አባባል
የሥራ ፈት ምላስ ፈፅሞ ሥራ አይፈታም፡፡
የአፍሪካውያን አባባል

 መስራቹ ዙክበርግ የዓለማችን 9ኛው ባለጸጋ ሆኗል
    ታዋቂው የማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ በአለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትርፍ እያገኙ ካሉ 10 የዓለማችን እጅግ ትርፋማ ኩባንያዎች አንዱ መሆኑንና የኩባንያው መስራች ማርክ ዙክበርግም ከዓለማችን ቀዳሚ ቢሊየነሮች 9ኛውን ደረጃ መያዙን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ኤስ ኤንድ ፒ በተባለው የአክሲዮን ገበያን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ 274 ነጥብ 95 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ያካበተው ፌስቡክ፣ ከሰሞኑ የአክሲዮን ገበያ ትርፋማነቱ መጨመሩን ተከትሎ፣ ከአለማችን 10 እጅግ ትርፋማ ኩባንያዎች የስምንተኛ ደረጃን ይዟል፡
የኩባንያው ትርፋማነት መጨመሩን ተከትሎ፣ የኩባንያው መስራች የማርክ ዙክበርግ አጠቃላይ ሃብትም 42 ነጥብ 9 ቢሊዮን መድረሱን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
ከሳምንታት በፊት ይፋ የተደረገው የብሉምበርግ የአለማችን ቀዳሚ ባለጸጎች ዝርዝር ማርክ ዙክበርግን የዓለማችን 11ኛው ባለጸጋ ብሎት እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣አራት ቢሊየነሮችን ቀድሞ በ9ኛነት ደረጃ ላይ መቀመጡን ገልጧል፡፡

 አሸባሪ ቡድኖችን ሊቀላቀሉ ይችላሉ በሚል ሰግታለች
  የሞሮኮ መንግስት የአገሪቱ ወጣቶች ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር ሊቀላቀሉ ይችላሉ በሚል ስጋት ለመዝናናት ወደ ቱኒዝያ የሚያደርጉትን ጉዞ መከልከሉን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ወቅቱ የሞሮኮ ወጣቶች ለመዝናናት በብዛት ወደ ቱኒዝያ የሚጓዙበት እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ የአገሪቱ መንግስትም የተወሰኑ ወጣቶች አጋጣሚውን ተጠቅመው ወደ ሊቢያ በማምራት ከአሸባሪና ጽንፈኛ ቡድኖች ጋር ሊቀላቀሉና የሽብርተኝነት ስልጠና ሊወስዱ ይችላሉ በሚል ስጋት፣ ሁሉንም የአገሪቱ ወጣቶች ወደ ቱኒዝያ እንዳይሄዱ መከልከሉን ገልጧል፡፡ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከጽንፈኛ ቡድኖች ጋር የሚቀላቀሉ የአገሪቱ ወጣቶች ቁጥር እያደገ መምጣቱ ስጋት የፈጠረበት የሞሮኮ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ወጣቶቹን ከጥፋት ተግባር ለመታደግ ውሳኔውን አስተላልፏል ብሏል ዘገባው፡፡በቅርብ ጊዜ ውስጥ ብቻ 1 ሺህ 600 ያህል ሞሮኳውያን ወደ ሶርያ በማቅናት ጽንፈኛ ቡድኖችን መቀላቀላቸውንና ስልጠና መውሰዳቸውን የገለጸው ዘገባው፣ የአገሪቱ መንግስትም የችግሩን አሳሳቢነት በማጤን የጉዞ እገዳ ውሳኔውን ማስተላለፉን አስታውቋል፡፡
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤አሸባሪውን አይሲስ የሚቀላቀሉ ሞሮኳውያን ቁጥር እያደገ መምጣቱን በመግለጽ፣ ለመዝናናት ወደ ሞሮኮ የሚሄዱ ዜጎቹን የሽብር ጥቃት ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ማስጠንቀቁንም ዘገባው አክሎ አስታውሷል፡፡በቱኒዝያ የመዝናኛ ስፍራ በተከሰተው የሽብር ጥቃት 38 የተለያዩ አገራት ዜጎች ለሞት መዳረጋቸውን ተከትሎ፣ እንግሊዝን ጨምሮ በርካታ የአለማችን አገራት ዜጎቻቸው ወደ ቱኒዝያ እንዳይሄዱ መከልከላቸውንም ዘ ኢንዲፔንደንት አስታውሷል፡፡

 አንጋፋው የሆሊውድ የፊልም ተዋናይ ጆርጅ ክሉኒ፤ የአፍሪካን አስከፊ ግጭቶች በገንዘብ የሚደግፉና ከጦርነቱ የሚጠቀሙ ወገኖችን በመከታተል ለፍርድ ለማቅረብ የሚያስችል አዲሰ ፕሮጀክት ባለፈው ሰኞ መጀመሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ክሉኒ ከአሜሪካዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ጆን ፕሬንደርጋስት ጋር “The Sentry” በተባለ ፕሮጀክት ላይ በጋራ ለመስራት የተቀላቀለ ሲሆን ፕሮጀክቱ በግጭት ቀጠናዎቹ ውስጥና ውጭ ያለውን የገንዘብ ፍሰት በመመርመር፣ ለፖሊሲ አውጭዎች ውጤታማ እርምጃ መውሰድ የሚያስችላቸውን ግብአቶች ለመስጠት ያለመ ነው ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ መረጃ በማሰባሰብ፣ የመስክ ጥናት በማካሄድና የትንተና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጦርነቶች እንዴት በገንዘብ እንደሚደገፉና ትርፍ እንደሚገኝባቸው ለማጋለጥ ያቀደ ሲሆን ሰዎች በድረገፅ የሚያውቋቸውን መረጃዎችና ምስጢሮች ስማቸውን ሳይገልፁ እንዲጠቁሙ ያበረታታል፡፡  የ54 ዓመቱ ክሉኒ እና ፕሬንደርጋስት ለሮይተርስ እንደገለፁት፤ የዚህ ፕሮጀክት ዓላማ፤ “የጦርነት አትራፊዎች ከወንጀላቸው ያገኙት የነበረውን ጥቅም መንፈግ ነው” ብለዋል፡፡ “ከጦርነቱ የሚጠቀሙ ሰዎች ላደረሱት ጉዳት ዋጋ ሲከፍሉ ሰላም ለማስፈንና ሰብዓዊ መብት ለማስከበር አቅም ይፈጠራል” ብሏል የሁለት ጊዜ ኦስካር አሸናፊው ክሉኒ በሰጠው መግለጫ፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ከመጀመራቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የተጀመረው ፕሮጀክት፣ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ ከሰሜን ምስራቅ እስከ ማዕከላዊ አፍሪካ ያሉ ግጭቶችን በገንዘብ የመደገፍ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ይመረምራል ብሏል ሮይተርስ፡፡
አዲሱ ፕሮጀክት ክሉኒ ከእነብራድ ፒትና ማት ዴመን የመሳሰሉ ተዋናዮች ጋር በመሰረተው “Not on our watch” የተሰኘ ድርጅትም ድጋፍ እንደሚደረግለት ታውቋል፡፡ የቀድሞው የአሜሪካ ፀጥታ ም/ቤት የአፍሪካ ዳይሬክተር የነበሩት ፕሬንደርጋስት እና ክሉኒ በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ላይ ሲሰሩ የአሁኑ የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡    

   የአንጋፋው ሰዓሊ ለማ ጉያ እና የሴት ልጁ የሰዓሊ ነፃነት ለማ የስዕል ስራዎች በጋራ የሚቀርቡበት የስዕል ኤግዚቢሽን ዛሬ ከጠዋቱ 5 ሰዓት ጀምሮ ይከፈታል፡፡
የልጅና የአባት የስዕል ኤግዚቢሽኑ የሚከፈተውና ለእይታ የሚቀርበው በአዲስ አበባ በሚገኘው የኦሮሚያ የባህል አዳራሽ ሲሆን፤ ኤግዚቢሽኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር አቶ አሚን አብዱልቃድር እንደሚከፍቱት ታውቋል፡፡

 የአንጋፋው ደራሲ አበራ ለማ “ቅንጣት - የኔዎቹ ኖቭሌቶች” የተሰኘ አዲስ የልብወለድ መፅሃፍ ሰሞኑን ለገበያ ቀረበ፡፡ በ264 ገፆች የተመጠነው መፅሃፉ፤ በ70 ብር እንደሚሸጥ ታውቋል፡፡
ነዋሪነቱን በኖርዌይ ያደረገው ደራሲው፤ በበርካታ የአጫጭር ልቦለድና የግጥም መድበሎቹ የሚታወቅ ሲሆን ከቀደምት ሥራዎቹ መካከል፡- “ኩል ወይም ጥላሸት” (የግጥም መድበል)፣ “ሸበቶ” (የግጥም መድበል)፣ “ሕይወትና ሞት” (የአጫጭር ልቦለዶች መድበል)፣ “ሞገደኛው ነውጤ” (ኖቭሌት) እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
በ1980ዎቹ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ዋና ፀሃፊ ሆኖ ያገለገለው አበራ ለማ፤ በአሁኑ ሰዓት በኖርዌይ ደራስያን ማህበር የመጀመርያውና ብቸኛው ጥቁር እንዲሁም በአፍ መፍቻው ቋንቋ የሚፅፍ አባል ደራሲ ነው ተብሏል፡፡

“የቤት ሥራ” የቴሌቪዥን ድራማ በቅርቡ መታየት ይጀምራል
   በጋዜጠኛና ፀሐፌ ተውኔት ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ተደርሶ፣ በካሌብ ዋለልኝ የተዘጋጀው “ከትዳር በላይ” የተሰኘ ዘመናዊ ኮሜዲ ቲያትር የፊታችን ረቡዕ  ከ11፡30 ጀምሮ በብሄራዊ ቴአትር ይመረቃል፡፡ ቲያትሩ በየሳምንቱ ዘወትር ረቡዕ በተመሳሳይ ሰዓት በዚሁ ቴአትር ቤት እንደሚታይ ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል በቴዎድሮስ ተ/አረጋይ እና በሰዓዳ መሃመድ ተደርሶ፣ በኢሳያስ ግዛው የሚዘጋጀው “የቤት ሥራ” የቴሌቪዥን ድራማ፣በያዝነው ወር መጨረሻ ላይ በኢቲቪ-1 መታየት እንደሚጀምር ተገለፀ፡፡ በቴዎድሮስ የትያትር ኢንተርፕራይዝ ፕሮዱዩሰርነት የሚቀርበው የቲቪ  ድራማ፤ በትዳርና በቤተሰብ ግንኙነት ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው ተብሏል፡፡ በድራማው ላይ አርቲስት ሽመልስ አበራ፣ ሰላም ተፈሪ፣ ስዩም ተፈራ፣ ቶማስ ቶራ፣ ጀምበር አሰፋ፣ ሳምሶን ታደሰ (ቤቢ) እንደሚተውኑበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

  በወግ ፀሐፊነቱ የሚታወቀው በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር የጻፋቸው በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጣጥፎች የተካተቱበት “ኑሮ እና ፖለቲካ- ቁ 3” የተሰኘ አዲስ መፅሃፍ ትትሞ ለንባብ ቀረበ፡፡ መፅሃፉ ቀላል የማይባሉ አዳዲስ ሥራዎች እንደተካተቱበት የጠቆመው ደራሲው፤ ቀድሞ የተሰሙና የተደመጡትም እንኳ በደጋሚ እንዲነበቡ ተደርገው በደንብ መቃናታቸውንና አዳዲስ ነገር እንደተጨመረባቸው ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡ በ157 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ለአገር ውስጥ በ40.50፣ለውጭ አገር በ15 ዶላር ይሸጣል፡፡  ደራሲው ከዚህ ቀደም “መንታ መልኮች”፣ “ኑሮ እና ፖለቲካ” (ቁጥር 1 እና 2) የሚሉ መጻህፍትን ያሳተመ ሲሆን በተለያዩ የፕሬስ ውጤቶች ላይ በአሽሙር የተጠቀለሉ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ወጎችን በማቅረብም ይታወቃል፡፡

“ቦቃፍ ቡሬ” የተሰኘ አዲስ የኦሮምኛ ኮሜዲ ፊልም፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ባለፈው ሳምንት ሐምሌ 12፣ በኦሮምያ የባህል ማዕከል በተከናወነ ደማቅ ስነ-ስርዓት የተመረቀ ሲሆን በሲዲ ለሽያጭ እንደቀረበም ታውቋል፡፡
በታምራት አዳሙ ተጽፎ በታዴማ ሚዲያ ኤንድ ኢቨንት ኦርጋናይዘር ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰርነት እና በኢሉ ኮ ፕሮዳክሽን ተሰርቶ የቀረበውን #ቦቃፍ ቡሬ#፣ ዳይሬክት ያደረገው ራሱ ታምራት ሲሆን የአንድ ሰዓት ከ30 ደቂቃ ርዝማኔ አለው፡፡ሰርቶ ለማጠናቀቅ 7 ወር በፈጀው በዚህ ፊልም ላይ አንጋፋው ተዋናይ አድማሱ ብርሃኑና ኦሊ ነጋ በመሪ ተዋናይነት የተጫወቱበት ሲሆን ሌሎች ከ15 በላይ አንጋፋና ወጣት ተዋንያንም ተሳትፈውበታል ተብሏል፡፡

 በመስከረም አበራ የተፃፉ የተለያዩ ፖለቲካዊ መጣጥፎችን ያካትተው “ስለ ስልጣን” የተሰኘ አዲስ መፅሃፍ ሰሞኑን ታትሞ ለንባብ ቀረበ፡፡ መፅሃፉ በ7 ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን  “የብሄር ፖለቲካችን”፣ “የአቶ መለስ ትዝታዎች”፣ “ቅይጥ ፖለቲካዊ ጉዳዮች” እና ሌሎችም ርዕሶችን አካትቷል፡፡
በ230 ገፆች የተቀነበበው “ስለ ስልጣን”፤ በ57 ብር ከ65 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡
ፀሃፊዋ በተለያዩ የፕሬስ ውጤቶች ላይ ፖለቲካዊ መጣጥፎችን በማቅረብ ትታወቃለች፡፡