Administrator

Administrator

    በዶ/ር ሱባህ ኤ የሱፍ በእንግሊዝኛ የተሰናዳው “Sharing Costss Nothing” ሰሞኑን ለገበያ የዋለ ሲሆን በተለያዩ የጤና ጉዳዮች ላይ እንደሚያጠነጥን ታውቋል፡፡ መፅሀፉ በዋናነት ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ  የሚያያቸው ነገር ግን ትኩረት ሰጥቶ ወደ ህክምና የማይመጣባቸው እንደ ስቅታ፣ ነስር፣ የመንገድ ጉዞ ህመም፣ የከፍታ በሽታ (Mountain Sikness)፣ ሀንግ ኦቨር፣ እና በጎጂ የጤና ልማዶች ላይ አተኩሮ የተዘጋጀ ነው፡፡ መፅሀፉ ለአገር ውስጥ በ45 ብር ፣ ለውጭ አገራት በ10 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡

    የገጣሚ መብራቱ መሀመድ “ሽሽት” የተሰኘ የግጥም መድበል ዛሬ ከ9፡30 ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር ይመረቃል፡፡ በመፅሀፉ ውስጥ የተካተቱት ግጥሞች በዋናነነት ሰው ከሀገሩ፣ ከህሊናው፣ ከፖለቲካ፣ ከዓለም፣ ከፍቅር፣ ከእውነት፣ ከጥበብና ከፈጣሪው ይሸሻል ወይ?
ቢሸሽስ የት ይደርሳል፣ ማንስ ነው መጠጊያው? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ያጠነጥናሉ ተብሏል። በምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ ወጣትና አንጋፋ ገጣሚያን ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን ከመፅሀፉ የተመረጡ ግጥሞች ለታዳሚው ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ በ83 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ30 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበርና መስከረም ፕሮሞሽን በመተባበር ያዘጋጁት “አገር አቀፍ ተጓዥ የንግድ ትርኢትና ባዛር” ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ተከፈተ፡፡ “አካል ጉዳተኞችን ማሳተፍ የህዳሴው አካል ነው” በሚል መርህ የመጀመሪያውን የንግድ ትርኢትና ባዛር ሜክሲኮ አደባባይ የከፈተው ማህበሩ፤ በተለያዩ የክልል ከተሞች ለ1 ዓመት እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
ከተቋቋመ 23 ዓመታትን ያስቆጠረውና በአገር አቀፍ ደረጃ 16ሺህ አባላት ያሉት ማህበሩ፤ የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበርና በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሶ፤ አካል ጉዳተኞች አካል ጉዳተኝነታቸው ሳይገድባቸው የሚያመርቷቸውን ምርቶች ከገዢ ጋር ለማገናኘትና ለማበረታታት ባዛሩ መዘጋጀቱን የማህበሩ ሃላፊዎች ባለፈው ረቡዕ በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡
በንግድ ትርኢትና ባዛሩ ላይ አካል ጉዳተኖች ያመረቷቸው ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የእጅ ስራዎች፣ ቦርሳዎች፣ ቀበቶዎች፣ የሶፋ ጨርቆች፣ የህትመትና የማስታወቂያ ስራዎችና ሌሎችም እቃዎች ለእይታና ለሽያጭ እንደሚቀርቡ ተገልጿል፡፡

በምግብ ማብሰል ሙያ አለማቀፍ እውቅናን ያተረፈው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሼፍ ማርከስ ሳሙኤልሰን፤“ፌስቱፌስ አፍሪካ; የተባለው የፓን-አፍሪካን ሚዲያ ተቋም ለሚያዘጋጀው አመታዊው የ“ፌስ ሊስት” ሽልማት በ“ግሎባል አምባሳደር አዋርድ” ዘርፍ ለሽልማት መመረጡን ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡
ተቋሙ በተሰማሩበት የሙያ መስክ የላቀ ተግባር ለፈጸሙ፣ ለወጣቱ ትውልድ አዲስ መንገድን ለከፈቱና የፓን-አፍሪካኒዝምን በጎ ገጽታ  በተመለከተ በሚደረጉ ውይይቶች ተጽዕኖ ለፈጠሩ ጀግኖች በየአመቱ የሚሰጠው የ“ፌስ ሊስት” ሽልማት ዘንድሮም ለ5ኛ ጊዜ በመጪው ሃምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ኒውዮርክ ሲቲ ውስጥ በሚካሄድ ስነስርዓት ለሼፍ ማርከስ ሳሙኤልሰንና ለሌሎች አራት ታዋቂ ግለሰቦች ይበረከታል ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ተወልዶ በስዊድን ያደገውና በአሁኑ ሰዓት ነዋሪነቱ በኒውዮርክ ሲቲ የሆነው ሼፍ ሳሙኤልሰን፤በሙያው አለማቀፍ ዝናን እንዳተረፈ የገለጸው ተቋሙ፣ሬድ ሮስተር የተባለ የራሱን ሬስቶራንት ከፍቶ ትርፋማ ቢዝነስ እያከናወነ እንደሚገኝና በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ለሁለት ጊዚያት ያህል የ3 ኮከብ ደረጃ የተሰጠው በእድሜው ትንሹ ሼፍ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በዋይት ሃውስ ለኦባማ በኣለ ሲመት በተዘጋጀ የክብር የእራት ስነስርዓት ላይ በተጋባዥነት ምግብ በማብሰል የሚታወቀው ሼፍ ሳሙኤልሰን፣ ለጥቁር አፍሪካውያን የስኬት ተምሳሌት መሆኑንና በሙያው የተለያዩ ታላላቅ ሽልማቶችን ማግኘቱንም መግለጫው አስታውቋል፡፡
ለ2016 የ“ፌስ ሊስት” ሽልማት የተመረጡት ሌሎቹ ዝነኞች፣ የግራሚ ተሸላሚው ድምጻዊ ዋይክሌፍ ዣን፣ ዋይቴከር ግሩፕ የተባለው ኩባንያ ፕሬዚዳንት ሮዛ ዋይቴከር፣ የታዋቂው ኢሰንስ መጽሄት ዋና አዘጋጅ የሆነቺው ቫኔሳ ዲ ሊካ እና የኩራሞ ካፒታል ኩባንያ መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዋሌ አዲኦሱን መሆናቸውንም ተቋሙ አስታውቋል፡፡


   የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዮሪ ሙሴቬኒ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣኔን ለመቀማት ሲያሴሩ ደርሼባቸዋለሁ ያሏቸውን 30 ያህል የአገሪቱ ከፍተኛ የጦር መሪዎችና ባለስልጣናት ማሳሰራቸውን ተከትሎ በአገሪቱ ውጥረት መንገሱ ተዘገበ፡፡
ከአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በመተባበር በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ለመጣል አሲረዋል የተባሉት የጦር መሪዎችና ባለስልጣናቱ፣ ባለፈው ሳምንት መታሰራቸውን ያስታወሰው አሶሼትድ ፕሬስ፤ ይህን ተከትሎም ድርጊቱን የተቃወሙ ታጣቂዎች በመንግስት ፖሊሶች ላይ ተኩስ መክፈታቸውንና ውጥረት መንገሱን ገልጧል፡፡
የአገሪቱ ፖሊስ ከመፈንቅለ መንግስት ሴራው ጋር ንክኪ አላቸው ያላቸውን በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትንና ደጋፊዎችን ማሰር መቀጠሉን የጠቀሰው ዘገባው፤ 12 ያህል የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊ ታጣቂዎች፣ ኡጋንዳ ፒዩፕልስ ኮንግረስ የተባለው ፓርቲ አባል የሆኑትንና በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉትን ዳን ኦላ ኦዲያ የተባሉ ግለሰብ ለማስለቀቅ፣ባለፈው እሁድ በፖሊስ ላይ ተኩስ በመክፈት ብጥብጥ መፍጠራቸውን ጠቁሟል፡፡  
ባለፈው የካቲት ወር በተካሄደው የአገሪቱ ምርጫ የሙሴቬኒ ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡትና የምርጫውን ውጤት በመቃወም ብጥብጥ አስነስተዋል በሚል ወደ ወህኒ የተወረወሩት ፎረም ፎር ቼንጅ የተባለው ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ዶ/ር ኪዛ ቢሲጂ፤ባለፈው ረቡዕ በአገር ክህደት ተከሰው በናካዋ ከተማ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት፣ በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት ነግሶ እንደነበር ዘገባው አመልክቷል፡፡
መፈንቅለ መንግስቱን የጠነሰሱት ኪዛ ቢሲጄ የተባሉ የአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር እንደሆኑ መነገሩን የጠቆመው ዘገባው፣ ግለሰቡ በአገር ክህደት ከተከሰሱት ቢሲጂ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጾ፣ ቢሲጂ በመንፈንቅለ መንግስቱ ሴራ እጃቸው ሊኖርበት እንደሚችል መጠርጠሩን አስታውቋል፡፡
ቪኦኤ በበኩሉ፤ የአገሪቱ መንግስት ባለስልጣናቱን በመፈንቅለ መንግስት ሴራ ጠርጥሮ ማሰሩ በቀጣይም ከፍተኛ ብጥብጥ ሊፈጥርና አገሪቱን ወደ ከፋ ቀውስ ሊከታት እንደሚችል እየተነገረ እንደሚገኝ ዘግቧል፡፡

  ታዋቂው ማይክሮሶፍት ኩባንያ፣ሊንክዲን የተባለውን ዝነኛ የማህበራዊ ድረገጽ በ26.2 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት ስምምነት ላይ መድረሱን እንዳስታወቀ ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ኩባንያው በታሪኩ ከፍተኛውን ግዢ የሚፈጽምበት ነው በተባለው በዚህ ስምምነት ወደ ማህበራዊ ድረገጽ አለም በይፋ ይቀላቀላል ያለው ዘገባው፤ ማይክሮሶስፍት ሊንክዲንን መግዛቱ ከፌስቡክና ከጎግል ጋር ለሚያደርገው የቴክኖሎጂ ፉክክር ትልቅ አቅም ይፈጥርለታል መባሉንም ገልጧል፡፡
በቢዝነስ ላይ በተሰማሩ ተጠቃሚዎች ዘንድ የሚዘወተረው ሊንክዲን የማህበራዊ ድረገጽ፤ከ400 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት የጠቆመው ዘገባው፣ ማይክሮሶፍት ግዢውን እስከ መጪው ጥር ወር ድረስ አጠናቅቆ ሊንከዲንን በእጁ ያስገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቋል፡፡
የሊንክዲን ተጠቃሚዎች ቁጥር ባለፉት አመታት በአማካይ በ19 በመቶ እድገት በማሳየት፣ 433 ሚሊዮን ያህል መድረሱን የጠቆመው ሮይተርስ፤ በትርፋማነቱም እንደማይታማና በማይክሮሶፍት ባለቤትነት ስር መተዳደሩ የበለጠ ውጤታማ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚታመን አስረድቷል፡፡
ማይክሮሶፍት ከአምስት አመታት በፊት ስካይፒን በ8.5 ቢሊዮን ዶላር፣ የኖኪያ የሞባይል ቀፎ አምራችነትንም በ7.2 ቢሊዮን ዶላር መግዛቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ሁለቱ ግዢዎች በታሪኩ ከፍተኛ ወጪ ያወጣባቸው ተብለው ተመዝግበው እንደነበርም ገልጧል፡፡

- እስካሁን 6 ክብረ ወሰኖችን አስመዝግቧል
- ከወራት በፊት የአመቱ ምርጥ አትሌት ተብሏል

በአሜሪካ የ3ኛ ክፍል ተማሪ የሆነውና የ8 አመት ዕድሜ ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ታዳጊ ታም ጋቬናስ፤ ባለፈው ሳምንት በኒውዮርክ በተካሄደው የኬንዝ ዶላን መታሰቢያ የ5 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር አዲስ የአለም ክብረወሰን ማስመዝገቡን ያሁ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ታዳጊው የ5ሺህ ሜትር ሩጫውን በ18 ደቂቃ በማጠናቀቅ፣በዚህ ዕድሜ ርቀቱን ፈጥኖ የጨረሰ የዓለማችን ባለተስፋ ታዳጊ አትሌት ተብሏል ያለው ዘገባው፤ታዳጊው ከሶስት አመታት በፊትም በዚያው በአሜሪካ በተካሄደ የ5 አመት ዕድሜ ያላቸው ታዳጊዎች የሩጫ ውድድር ላይ በ800 ሜትርና በ1ሺህ 500 ሜትር አዲስ የዓለም ክብረወሰን ማስመዝገቡን አስታውሶ፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሽልማቶችን ማግኘቱንና መነጋገሪያ መሆኑን አስታውቋል፡፡  
ባለፈው አመት በ800 ሜትር፣ በ1ሺህ 500 ሜትርና በ400 ሜትር ውድድሮች አዳዲስ ብሄራዊ ክብረ ወሰኖችን ያስመዘገበው ታዳጊው፤ከወራት በፊትም በአሜሪካ በተካሄደው ዩኤስኤቲኤፍ አመታዊ የታዳጊ አትሌቶች ሽልማት፣የአመቱ ምርጥ አትሌት ተብሎ መሸለሙም ታውቋል፡፡  
ታም ጋቬናስ በኢትዮጵያ እንደተወለደና ዕድሜው ሶስት አመት ሳይሞላው፣ ሜሪ ሊዛ ጋቬናስ በተባለቺው አሜሪካዊት አማካይነት በጉዲፈቻ ወደ አሜሪካ መወሰዱን ያስታወሰው ያሁ ኒውስ፣ አሳዳጊው የተፈጥሮ ክህሎቱን በማጤን ለስኬት እንዲታትር ታበረታታው እንደነበር ጠቁሟል፡፡

     በባንግላዴሽ ባለፈው ሳምንት የታጠቁ ሃይሎች በፈጸሙት ተከታታይነት ያለው ጥቃት፣ በበርካታ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያዎች መፈጸማቸውን ተከትሎ የጽንፈኛ ቡድኖችን እንቅስቃሴ ለመግታት የተጠናከረ እርምጃ መውሰድ የጀመረው የአገሪቱ መንግስት፤ ከ11 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎችን ማሰሩን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
የአገሪቱ መንግስት ሰሞኑን በርካታ ዜጎችን በመግደል ከፍተኛ ጥፋት ካደረሱ ጽንፈኛ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን 150 ታጣቂዎችና በአገሪቱ በተከሰቱ ብጥብጦች በተለያዩ ወንጀሎች ተሳትፈዋል በሚል የጠረጠራቸውን ከ11 ሺህ በላይ ግለሰቦች ማሰሩን ዘገባው ገልጧል፡፡
የአገሪቱ ፖሊስ አብዛኞቹ በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ጃማቱል ሙጅሃዲን የተባለው አክራሪ ቡድን አባላትና ለጥፋት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው ቢልም፣ ባንግላዴሽ ናሽናሊስት ፓርቲ የተባለው የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ ግን፣ የመንግስት እስር በአባላቶቼ ላይ ያነጣጠረ ነው፤ 2 ሺህ 100 አባላቶቼና ደጋፊዎቼ ታስረውብኛል ማለቱ ተዘግቧል፡፡
በባንግላዴሽ ባለፈው አንድ አመት ብቻ 35 ያህል ተመሳሳይ የሽብር ጥቃቶችና ግድያዎች መፈጸማቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ በአገሪቱ በህቡዕ የሚንቀሳቀስ አንድ አክራሪ ጽንፈኛ ቡድንም ከእነዚህ ጥቃቶች መካከል ሃያ ሶስቱን ለመፈጸሙ ሃላፊነት መውሰዱን ገልጧል፡፡

    የዚህ ዓምድ ትኩረት ሥነ-ጥበብ፤ በዋነኝነትም የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ነው። በተለይም ዘመንኛው (Contemporary) የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ላይ አጽንኦት በመስጠት ወቅታዊና በመታየት ላይ ያሉ ትርዒቶችን ይዳስሳል፡ ገለጻ ያቀርባል፡ ያትታል፡ ይመረምራል፡ ሂስ ያቀ ርባል። ግለሰቡን
ሳይሆን ስራውን በመተቸት የሂስ ባሕልን ለማዳበር ይጥራል፡፡ የዓምደኛውን እይታ መሬት በያዙና ሚዛን በሚደፉ አመክንዮች በማስደገፍ ግለሰብ አንባቢ ስለ ሥነ-ጥበብና ስለ ኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ግንዛቤ እንዲጨብጥ፣ የዕይታ ባሕሉ (Visual Culture) እንዲዳብር፡ የሥነ-ጥበብ አድናቆቱ
ከፍ እንዲል፡ ሥነ-ጥበብን የሕይወት ዘዬው (Life Style) አድርጎ እንዲወስደው መንገድ ለመክፈት ይጥራል። በማኅበረሰብና በሃገር ደረጃም ልክ እንደ ኤኮኖሚያዊ፡ ፖለቲካዊ፡ ማኅበራዊ፡ ባሕላዊና ትውፊታዊ እንዲሁም ታሪካዊ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ሥነ-ጥበብን የሰፊው የሕይወት መር (Mainstream) አካል እንዲሆን ይተጋል።

የትርዒቱ ርዕስ፡ የውስጥ ዳና ሠዓሊ፡ ሙሉጌታ ታፈሰ (ዶ/ር) የትርዒቱ አይነት፡ የግል፤ የቀለም ቅብ ስራዎች ብዛት፡ 41 የቀለም ቅብ፤ 11 የፓስቴል ኪነ- ንድፍ(Pastel Drawing)፤ 1 የቅይጥ (Mixed
Media) ስራዎች የቀረበበት ቦታ፡ ሌላ ጋለሪ(ጦር ኃይሎች፣ ቻይና ኤምባሲ አካባቢ፣ ለመጎብኘት ከረቡዕ-እሁድ ከጠዋቱ 4:00-ምሽቱ 12:00 ሠዓት ለአቅጣጫ+251911300756)፡ አዲስ አበባ
ጊዜ፡ ሰኔ 04-ሰኔ 20: 2008 ዓ.ም ዳሰሳ አቅራቢ፡ ሚፍታ ዘለቀ (የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ)       

ጥቆማ-ልብ የሚል ልብ ላለው!
ሰፊው የማኅበረሰብ ክፍል ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና በሚልባት፤ ሃብታሙ ሺዎችን ሚሊዮን፡ ሚሊዮኖችን ለማብዛትና ቢሊዮኖችን ለማካበት ነብሱን በሳተባት፤ ምሁሩም የጋን ውስጥ መብራቱን በታቀፈባትና መንግስትም ከልማት አቅጣጫ ብቻ ልጓሙን ባጠበቀባት አዲስ አበባችን ሠዓልያንና ለሥነ-ጥበብ ሕልውና የሚተጉ ተቋማት ለዘመንኛ ኑሮአችን የሰላ አተያይ እንዲኖረን የሚያግዙና ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ትርዒቶችን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ በቀጣይ ሳምንታት የተወሰኑት ላይ ዳሰሳ የማቀርብ ሲሆን ከዚህ ጥድፊያና ግርግር ከተሞላበት የኑሮ እሽክርክሪት ጥቂት ጊዜ ቆርሳችሁ፣ ትርዒቶቹን ቀድማችሁ ብትመለከቷቸው ዳሰሳዎቼን ለመረዳትም ሆነ ሥነ-ጥበብን የሕይወታችሁ ዘዬ(Life Style) አድርጋችሁ ለመውሰድ ማለፊያ ልምምድ ይሆናችኋልና የትርዒቶቹን ቦታዎች ልጠቋቅማችሁ፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዝየም፡ ጊዜያዊ የሥዕል ማሳያ አዳራሽ- በሠዓሊ ፍቅሩ ገብረማሪያም-እስከ ሐምሌ 07 የሚቆይ የግል ትርዒት፤ በአልያንስ ኢትዮ-ፍራንሴስ-በሠዓልያን አዲስ ገዛኧኝ፡ ደረጀ ደምሴ፡ ሱራፌል አማረና ታምራት ገዛኧኝ-እስከ ሰኔ 19 የሚቆይ የቡድን ትርዒት፤ በጉራምዓይኔ የሥነ-ጥበብ ማዕከል-በሠዓሊ ደረጀ ደምሴ-እስከ ሰኔ 30 የሚቆይ የግል ትርዒት፤ በጋለሪያ ቶሞካ-በሠዓሊ ተስፋ ሰለሞን-እስከ ነሐሴ 05 የሚቆይ የግል ትርዒት፤ በላፍቶ አርት ጋለሪ እስከ ሐምሌ 17 የሚቆይ የግል ትርዒት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ቦታዎቹን ለማታውቁ በ+251911702953 መረጃ ታገኛላችሁ፡፡ ታዲያ ይህ ጥቆማ ልብ የሚል ልብ ላለው! ብቻ ሳይሆን ለሥነ-ጥበብ ፋይዳ ቦታ የሌላቸውንና ነብሳቸውን እንዲያው በቅብዝብዝ ለሚያባዝኗት ሰዎች መረጃውን ለማቀበል ድልድይ ለመሆን ልብ ላለው ጎበዝ ሁሉ ይሁን! ወደ ዛሬው ዳሰሳ እንለፍ?
ሠዓሊ ዶ/ር ሙሉጌታ ታፈሰ ማነው?
ልከኛ ሰው ነው፡፡ ዶ/ር ሙሉጌታ ታፈሰ ጉምቱ ሠዓሊ ነው፤ የሥነ-ጥበብ ሃያሲና የሥነ-ጥበብ ቲዎረቲሽያን፡ ፈላስፋና ተመራማሪ ነው፡፡ በ1953 ዓ.ም አዲስ አበባ እስጢፋኖስ ቤ/ክ አካባቢ ተወለደ፡፡ በ1972 ዓ.ም በያኔ ስያሜው አዲስ አበባ ሥነ-ጥበብ ት/ቤት በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ተመርቆ፣ በት/ቤቱ፣ ለቀጣይ ሁለት አመታት አስተምሯል፡፡ ቡልጋሪያ ሶፊያ ከተማ ከሚገኘው Higher Institute of Fine Arts (1983 ዓ.ም) እንዲሁም ቤልጅየም፡ አንትወርፕ ከተማ ከሚገኘው National Higher Institute for Fine Arts (1989 ዓ.ም) የማስተርስ ዲግሪዎቹን፣ በ(2004 ዓ.ም) ደግሞ ከስፔኑ La laguna University የፍልስፍና ዶክትሬት ዲግሪውን በከፍተኛ ማዕረግና ክብር ተቀብሏል። በውጪ ሃገራት ትምህርቱን ሲከታተልና ኑሮውን ሲመራ በቆየባቸው በእነዚህ ሰላሳ አመታት ውስጥ በተደጋጋሚ ወደ ሃገሩ እየተመላለሰ፣ ለአዲስ አበባችን የሥነ-ጥበብ እድገት የበኩሉን ለማበርከት ትምህርታዊ ገለጻዎችንና ውይይቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ታዲያ በነዚህ ኃላፊነቶችና መሰጠቶች ታጅቦ፣ ሁሉ ለአፍታ ቸል የማይለው ጉዳይ ቢኖር የስቱዲዮ ሠዓሊነት ጥማቱና ይህን ለማሟላት ከቶም እማይቦዝነው ሙያዊ ስነ-ስርዓቱ ነው፡፡ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ነዋሪነቱን የቤልጅየሟ አንትወርፕ ከተማ ያደረገው ሠዓሊ ሙሉጌታ ታፈሰ፤ ከአክሪሊክና ዘይት ቀለም እስከ ሕትመትና ድብልቅ ቁስ ጥበባት የሚጠቀምና ስራዎቹ በከፍተኛ ባለሙያዎች ተመዝነው ሚዛን በመድፋት በዓለም-አቀፍ ደረጃም ክብርና እውቅናን ያገኘ ሠዓሊ ነው፡፡ በሃገር ውስጥና በዓለም-አቀፍ መድረኮች አያሌ የቡድንና የግል ትርዒቶች ስራውን ያቀረበ ሲሆን በግለሰብና በሕዝባዊ፡ ሃገራዊና፡ የባሕል ተቋማት ስርም ስራዎቹ ተሰብስበው ይገኛሉ፡፡ በቤልጅየም የሚገኘው የWARP Contemporary Art Platform ዳይሬክተር የሆነውና የሥነ-ጥበብ አጋፋሪው ስቲፍ ቫን በሊንገን፤ ‘ከበርካታ ሰበዞችና ሁኔታዎች ሃሳብ እየመዘዘ እንካችሁ የሚል ዘላን አእምሮ ያለው ነው’ ሲል ይገልፀዋል፡፡
“ስራዎቹ ልዕለ-ዓለማዊ (universal) በመሆናቸው ሁላችንም ወደምናውቀው ግን ደግሞ ሌላ ወደ ሆነ ዓለም  እንድናተኩር በር ከፋች ናቸው፡፡ የማስመሰል ቅመሞች ሳይነሰነሱ፤ ስራዎቹ የሰው ልጅምን ሆነ የሌሎች ነገሮችን ወካይ ቅርፆችን በተለየ መንገድ እንድንመለከት ዳግም ይፈጥራቸዋል፡፡ ተፈጥሯዊነትን ባይከተልም፣ ሰራዎቹ ዋቢ የሚያደርጉት የሰው ልጅን ቅርፅ ነው፡፡ የሚፈጥራቸው ቅርፆች ድብቅ እምቢተኝነት እንዲያመላክቱ፣ ለተለምዷዊ የእውቀትና የመረዳት ልምዶች በእጄ እንዳይሉ በማድረግ ነው የሚያስቀምጣቸው፡፡ ድብቅ በሆነው የሥራዎቹ ህልውናዎች ውስጥም አንድ ልብ ብሎ የሚያስተውል ሰው፣ የተብላላ ሀሳብ እንደሚያገኘው ሁላ በሂደቶች መሐል ለሚስተዋሉ እውነቶች ከፍ ያለ ትኩረት ይሰጣል፡፡ የሚያስቀምጣቸው ጉልህ ምስሎች ወደ አንድ ራሱን ወደቻለና በእይታ ለምንዳስሰው ዓለም ትኩረት እንድንሰጥ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ስራዎቹ ብጥስጣሽ ስሜትና ሀሳቦችን ሹክ የሚሉ ቢሆንም ተመላልሰን ስንመለከታቸው ግን አንደኛው ከሌላኛው ጋር የሚዛመድበትን የአንድነት ክር መምዘዝ ያስችለናል። በአጭር የሚቀርና አንድና አንድ ነገር ብቻ አመላክቶ የማለፍ የሥነ-ጥበብ ቀቢፃዊነትን በስራዎቹ አናይም፡፡ ይልቅስ፤ የሚያነሳት አንዷ ሀሳብ ሌላ፣ ሌላኛዋ ደግሞ ሌላኛውን እየነካችና እየቀሰቀሰች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በጋራ የምናጋራቸውን ሀሳቦች፣  ስሜቶችንና እውነቶችን ማእቀፍ ውስጥ የሚከቱ ስራዎችን ነው የሚሰራው” ይላል - በቢልገን፡፡
ከላይ የተገለፀውን ሀሳብ በዝርዝር ከማየታችን በፊት ከሰዓሊው መደንግግ የተወሰኑ ሃሳቦችን በአጭሩ እንመልከት፡
“የምሰራቸው ምስሎች የሚወለዱት ሊገለፅ ከማይቻለው የህይወት ትንቅንቅ ነው፡፡ አሻራቸውም በሞገዳዊ እንቅስቃሴአቸው ይገለፃል”
“ስራዎቼ ቅፅበታትን ይወክላሉ፡፡ የሰው ልጅ እንቅስቃሴዎች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ”
“በመገለጥ ወይም በብርሃን የተሞላ አካባቢና ህይወት የመፍጠር ፍላጎት ሁሌም በውስጣችን ይኖራል፤ ስሜት የማይሰጥ ቢሆንም እንኳን ሥዕል መስራት አስፈላጊ ነው”
“ስራዬን ፎቶ ግራፍን በምናይበት አይን ስንመለከተው፣ የዕውነታን እቅጩን ሳይሆን ትንሽ ለወጥ አድርጌ ወይም የእቅጩነት ደረጃውን ቀንሼ እቀዳለሁ/አስመስላለሁ፡፡ እውነታዊነት ያቀፋቸው ሰፊ አማራጮች ረጋ ባለ ሆኔታ ያስፈነድቁኛል፡፡ እነሱኑ ነው በስራዎቼ ልዘግብ ወይም ልገልጥ የምሞክረው፡፡”
 እውነታዊነት፡-
በብዙኃን የሀገራችን የሥነ-ጥበብ አድናቂዎችና በጥራዝ ነጠቆች ጭምር Realism እና Realistic በተወዘጋገቡ መረዳቶች አሉ፡፡ በመሰረቱ Realistic ወይም እውነታዊ ማለት በእውነታ ያሉ ነገሮችንና በተፈጥሮ የሚገኙትን መድገም ወይም አስመስሎ መስራት ሲሆን የማስመሰሉ ደረጃ ወደ ውሸትና ማታለል ያዘነበለ፣ ‘እዚያ ሲደርሱ እዚያ ብሎ ነገር የሌለበት’ የሌለውን አለ በማለት የሚሰራ የአሳሳል ፍልስፍና ነው። Realism ወይም እውነታዊነት ደግሞ ከነባራዊው ዓለም ፣ ከእለት ተዕለት ኑሮ እና እውነታ በመነሳት የሚሳል፣ የሚፃፍና የሚመረመር ፍልስፍና ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ተጓዳኝ ፍልስፍናዎች በኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብና ዕድገቱ ላይ አሉታዊም ሆነ አወንታዊ ተፅዕኖ ያሳደሩ በመሆናቸው፣ ሌላኛው ሥነ-ጥበባችን ላይ ወለፈንዲ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆነው ኢ-ምስላዊ ወይም አብስትራክት አርት ጋር በማያያዝ ሰፋ ያለ ሀተታ ለማቅረብ ጊዜና ሁኔታዎች እስኪፈቅዱ በይደር እናቆየውና ወደ እውነታዊነት እንመለስ፡፡
አዎ … እውነታዊነት የሰው ልጆችን የህይወት አቅጣጫ ለመቀየስ፣ ለማስመልከት፣ ለማስጤንና ለማስገንዘብ ሲሞክር የቆየ ፍልስፍና ነው፡፡ በተለይ በሥነ-ጥበቡ ዓለም፤ ለምንኖረው ሕይወት ጥራትና ደረጃ የበኩሉን ለማድረግ የሚታገል ትልቅ ፍልስፍናዊ መሰረት ያለው አሳሳል ነው፡፡ ሠዓሊ ዶ/ር ሙሉጌታ ታፈሰ፤ ለዘመናት ምናልባትም ሥነ-ጥበባዊ አቅጣጫውን በንቁ ንቃተ ህሊናው መግራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁኑ ጊዜ ድረስ ለእውነታዊነት ሲያቀነቅን መኖሩ የፍልስፍናውን ጥልቀት ከመረዳት የመነጨ ይመስለኛል። ‘እኔ ሥነ-ጥበብን እንድከውን የሚያደርገኝ ኃይል፣ አካባቢዬ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሥራዎቼ የበኩሌን ጥረት ለማድረግ የሚያስችሉኝ እንደሆኑ ስለማምንበት ነው’ የሚለው አስተያየቱ ‘እውነታዊነት ምሴ ነው’ ከማለት የተለየ አይመስለኝም፡፡ ሥዕል የሚሰራው ድንቅ ስሜቶችን ከመፍጠር ወይም ከWOW!!! የዘለለ ፋይዳ በሥነ-ጥበብ ማዕቀፍ ውስጥ የተቋጠረ ቃልኪዳን መኖሩን በመረዳቱ ለመሆኑና እውነታዊነት ለዚህ መረዳቱ አይነተኛ ቋንቋ እንደሆነው የሚያስረዱ አተያዮቹንና ሥራዎችን እንደ ምሳሌ እያነሳን እንቀጥል፡፡
የድምፅ ምናብ፡ የድምፅ ጎርፍ = ሰብዓዊነት  
በዚህ ትርዒት ከቀረቡት ሥራዎች መሀል ስምንቱ ድምፅ፣ ድምፃዊያንና ሙዚቃ ላይ ያተኩራሉ፡፡ ሠዓሊ ዶ/ር ሙሉጌታ ታፈሰ፤ እውነታዊነትን ለዚህ ትኩረቱ መግሪያ ካደረገበት አመክንዮ እንነሳ፡፡ የሰው ልጅ በዓለም ላይ ሲኖር መደሰት ይገባዋል ፡ ትንሿ መብቱም ነች፤ ደስታ። ጉልበታቸውን ለክፉ በማዋል ደስታን ነጣቂዎችም በዓለም ላይ ሞልተዋል፡፡፡ ኧረ እንደውም ዓለም እራሷ በእነዚህ ነጣቂዎች እየተነዳች ያለች ነው የምትመስለው። ሙዚቃ ደስታን ትቸራለች፡፡ ለተነጠቀብን ደስታም እንደ ሙዚቃ ያለ መፅናኛ የለም፡፡ ከተቀማ ደስታ የተወለደውን ብሉዝ  ማንሳት ይቻላል፡፡ አዎ… የብሉዝ ሙዚቃ የጥቁርነትና የነጭነት፤ በግፍ የመግዛትና በግፍ አልገዛም ባይነትና እምቢተኝነት ትንቅንቅ የተፈጠረ ነው፡፡ ይህ የመብት ጥያቄ የእውነታዊነት ፍልስፍና ከሚሞግተውና ከሚቆምለት እውነታ መሀከል አንዱ ነው፡፡ ሠዓሊ ዶ/ር ሙሉጌታ ታፈሰ ይህን ሙግት ወደ ሥዕል ያመጣው የጣፈጠና ከላይ ኩሬተር ወይም አጋፋሪ ስቲፍ እንዳለው፤ “የሚፈጥራቸው ቅርፆች ድብቅ እምቢተኝነትን እንዲያመለክቱ…” በማድረግ ነው። በትርዒቱ ውብ የሥዕሎች አሰቃቀል (Display) ግዘፍ እንዲነሱ ሆነው የተሰቀሉት አምስት ስዕሎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ የብሉዝ የሙዚቃ ስልት ንጉስ ማይልስ ዴቪስን የሳለበትንና ከማይልስ ዴቪስ ስዕል በስተቀኝ የተሰቀሉት አነስተኛ መጠን ግን ደግሞ ልብ የሚደልቅ ግዝፈት ያላቸውን የሌሎች ጥቁር ሙዚቀኞችን ሥዕሎች ስንመለከት፣ ድብቅ እምቢተኝነትን የማመላከቻው ማጣቀሻ ይሆናሉ፡፡ አምስቱም ሙዚቀኞች በየበኩላቸው፤ በዘመናቸው ለተፈጠሩ አካባቢያዊና የአካባቢው የዘረኝነት ችግሮች ቀጥተኛ መፍትሔ ባይሆኑም መፅናኛ ብቻ ተደርገው ቢወሰዱ፤ የሙዚቃቸውን ዋጋ ሊያሳንስ የሚችሉ..... ከዚህ ሁሉ  አልፎ ተርፎም እስከዛሬ ድረስ እያዳመጥናቸው ለነፍሳችን ምግብ የሚሆኑ ሙዚቃዎችን ትተውልናል፡፡ ሙዚቃቸውም፣ ከሙዚቃቸው የሚወጣውና የሚያወጡት ድምፅ፣ በሙዚቃቸው ድርሳን የሚያቀነቅኑት ሀሳብ፣ በዜማቸው የሚቃኘው ተመስጦ ሁሉ የድምፅን ምናብ እንድናስብ የሚያስገድድ ኃይል አላቸው፡፡ እንደ ሠዓሊ ዶ/ር ሙሉጌታ ታፈሰ  አተያይ ድምፅ፤ ‘የስልጣኔ አንዱ የደም ስር ነው’ የደም ስርነቱና የመዘወርነቱ ኃይልና መነሻ ስልጣኔ ነው፡፡ ለምሳሌ ብሉዝን ብንወስድ የሰው ልጅ ስልጣኔ ካመጣው አንድ ጣጣ ማለትም አንዱ ሌላኛውን በመጨቆን፣ ለመክበር የሚደረገውን ጭቆና ከመቃወምና ከመቋቋም የተወለደ ሙዚቃ ነው፡፡ በዚህም ብሉዝ የተራማጁ ስልጣኔ የፈጠረው ነው ማለት ይቻላል። ድምፅ ሰውን ስሜታዊ ያደርጋል፡፡ የሰውን ሀሳብ ከመረዳት የሚመነጭና መልሶም ሰውን የመርዳት አቅም ያለው ነው፡፡ በተለይም በብሉዝ የሚፈጠረው ድምፅ ምናብን ይፈጥራል፡፡ ያልሸነፍ ባይነት  ምናብ በድምፅ ይፈጠራል። ይህ ሲጠራቀም ደግሞ የድምፅ ጎርፍ ፈጥሮ በጊዜው በተለመደውና ነጮች ጥቁሮችን ይጨቁኑበት ለነበረው የመረዳት ልምድ፣ እምቢ ባይነትን በማነሳሳት፣ጥቁሮች ለመብታቸው እንዲነሱ ረድቷል። ከዚህ አኳያ ሠዓሊ ዶ/ር ሙሉጌታ ታፈሰ፤ ይህንን የድምፅ ምናብ ፈጥረውና የድምፅ ጎርፍ ከስተው፣ በወቅቱ የነበረውን የጥቁር ሰው የህይወት አቅጣጫ ለመቀየስ፣ በሙዚቃቸው የበኩላቸውን ለሞከሩት ሙዚቀኞች ታላቅ ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ሰብዓዊ ክብር ሰጥቷል  ባይ ነኝ። የጥቁሮች መብት ታጋይ የነበረው ማልኮም ኤክስንም ከድምፅ ማጉያ ጋር አድርጎ፣ የጎላ የታጋይ ሰብዕናውን በሌላ ሥዕሉ ያሳየናል፡፡
የሰብዓዊነት መገለጫ፡ ሰዎች ለሰዎች መስጠት ካለባቸው ክብር ባሻገር የሰሩት ስራ አክብሮት ለሰው ልጆች ህይወት እሴት መጨመሩን ማስመልከትና አክብሮቱን የሚሰጥበትንም ፍልስፍናዊ መሰረት ጠንቅቆ ማወቅ ነው። ይህን በማድረግ ሰዓሊው የእውነታዊነት አሳሳልን ብቻ ሳይሆን ፍልስፍናውንም በጥልቀት የሚመረመር መሆኑን መረዳት እንችላለን፡፡ ይህ እንዴት ቢባል፣ አንድም ይሄን ሁሉ ላደረጉ ሙዚቀኞች ሊሰጥ የሚገባውን ክብር በማስታወሱ፣ በሌላ በኩልም ሥዕሎችን ከመሳል ባለፈ የእውነታዊነት ፍልስፍናን መሬት በረገጡ እሳቤያዊ መሰረት ማስደገፍ መቻሉ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከሀገራችን ባሻገር በዓለም ላይ ላሉ ቁጥራቸው በጣም አነስተኛ ለሆኑ ብቁ ሰዓሊያን ብቻ የሚቻል የጥበብና የፍልስፍና አቋቋም በመሆኑ፣ ለሠዓሊ ዶ/ር ሙሉጌታ ታፈሰ ላቅ ያለ ክብር እንድንሰጠው ያስገድደናል፡፡  
ትንሽዬ ምርቃት፡     ምርቃቷ ራሷ ምርቃት የምትመስለዋን BH የተሰኘች ሁለት መዳፍ ተጋጥመው የማትሞላ ስራን ይመለከታል፡፡ ስራዋ በአንዷ ገፅ የተከፈተና ውስጧ በዘመናዊ የጆሮ ኩክ መጥረጊያ ጥጥ የተደፈነች ሳጥን ነች፡፡ በቅርበት በግልፅ ባይታይም ራቅ ስንል ግን የአድማጮችን ጆሮ የምትኮረኩረውና ከመንፈስ ዘልቃ የብሶት ኩክ ጠራርጋ የምታወጣዋ የብሉዝ አቀንቃኟ ቢሊ ሆሊደይን ምስል ያሳያል፡፡ በዚህ ስራ ሶስት ነገሮችን ልብ ይበሉ፡፡ ሙዚቃ፣ የጆሮ መጥረጊያ ኩክ፣ ከዚያ ስዕል፡፡ ለእኔ ይህ ሥዕል የConceptual Art ልከኛ አብነት ነው፡፡
መድብላዊነት (Pluralism)
የአንድ ሰው አፈጣጠርና አኗኗር ራሱን ሆኖ እንዲኖር “እጣ ፋንታ”ውን ወይም “አካሄድ”ን ያካትታል። እኛነታችን አንድም ከራሳችን ጋር አብሮ ይወለዳል፤ አንድም ከአካባቢያችንም ሆነ ከአኗኗራችን እኛነታችንን እናገኛለን፡፡ በአንድ እኛነታችን ብዙ መድብሎች ነን። ውስጣዊ ማንነታችን ከውጫዊ አለም እየተላተመ፣ በማያቋርጥ ሂደት እኛነታችንን እንገነባለን፡፡ እናፈርሳለን። በዚህ ትርዒት የቀረቡት የተወሰኑት ስራዎች እዚህ ሀሳብ ላይ ያተኩራሉ፡፡ አንድ ምስል ከሌላኛው ጋር የሚስተጋበርበት (Converse የሚያደርግበት )፣ ራሳችን ከራሳችን የምንሟገትበት መድብላዊነትን ከሰው ልጅ አፈጣጠርና ኑሮ አንፃር ያስቃኘናል፡፡ ውስጣዊውና የውጭ መስመርን (Inside Track) በዚህ ልብ ብለን ማየት እንችላለን፡፡
በስሜት የተሞሉ እንቅስቃሴዎች ወይም አኳኋኖች
አብዛኞቹ የሠዓሊ ዶ/ር ሙሉጌታ ታፈሰ ስራዎች፣ አንቅስቃሴ በተለይም በሰው ልጅ እንቅስቃሴ ላይ ያተኩራሉ፡፡ ሰዓሊው ከእንቅስቃሴ ባሻገር አኳኋኖችን እንዴት ለስሜትና ለሀሳብ ቅርብ አድርጎ እንደሚያስቀምጥ ከእውነታዊነት ጋር አያይዘን በአንድ ስራው ውስጥ እንመልከት፡፡ ይህ ስራ “የተንበረከከ” የሚሰኝ ሲሆን እጅግ ህመም በተሞላበት ስሜት መሸነፍን፣ እጅ መስጠትን የሚያሳይ ነው፡፡ የሰው ልጅ ህይወት ከአለፍ ባገደም በዝቅጠት የተሞላ ነው፡፡ በዘመንኛ አኗኗራችን ይህ እውነታ በአያሌው ይስተዋላል፡፡ ሆኖም ይህንን ዝቅጠታችንን በተለያዩ መንገዶች ለመሸፋፈን እየሞከርን፣ ቀጥ ብለን የቆምን እንደሆንን ሁሉ በEGO ወይም በእኔነት መንፈስ ተወጥረን እንገዳደራለን፡፡ ይሁን… መቼስ፤ ሰው ያለ EGO አይኖር፡፡ ሆኖም አኗኗራችን አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ የስሜትና የሀሳብ ውዥንብር ሲከሰትብን እጅ እንድንሰጥ፣ እንድንሸነፍ ሲያስገድደን ምናለ በ’ጄ ብንል? በ’ጄ ማለትና መሸነፍ አንድም ትልቅነት አለያም መማርና ማነስ ሲሆን፤እንዲህ መሆን የሚችል ሰው ወደ ውስጡ የመስመጥ፣ ውስጡን የመመልከት አቅም ያለው እንደሆነም ልብ ይሏል፡፡ እውነታን መቀበልና መማር ለሌላ እድልና ትምህርት ዝግጁ መሆን የሚያስችል ጥበብ እንደሆነም መገንዘብ ይቻላል። ሠዓሊ ዶ/ር ሙሉጌታ ታፈሰ፤ እውነታዊነትን እየሰበከ እንደሆነ ለማሳያ ልዩ ቦታ ያላት ስራ ናት፡፡
ጭምብል-Mask
ሁለት ጭንብል ተኮር ስራዎች በዚህ ትርዒት ተካተዋል። ብላክ ማስክ እና ዋይት ማስክ የተሰኙ። ጭንብል ስሜትና ሀሳብን ለመግለፅም ሆነ ለመደበቅ ይውላል፡፡ ይህ በመላው ዓለም ያለ ታሪክ፣ ባህልና እውነት ነው፡፡ የጥቁርና የነጭ ጭንብሎች፣አያሌ የገሀዱ ዓለም ነፀብራቆችን ይወክላሉ፡፡ ነጮች ጥቁሮችን ለመበዝበዝ ጥቁር ጭንብል ለብሰዋል፡፡ እስካሁንም ይህንኑ ያደርጉታል፡፡ ጥቁሮችም ከነጮች ለመቃረም ነጭ ጭንብል በመልበስ ወስክ ወስክ ይላሉ፡፡ (ጥቁሮች ስል ኢትዮጵያውያንንም መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡ ይህንኑ እውነት ፍርጥርጥ አድርጎ ነው ሠዓሊ ዶ/ር ሙሉጌታ ታፈሰ  በጭንብል ስራዎቹ የሚያስገነዝበን። ይመችህ!
ቅርበትና ርቀት-Perspective
የሠዓሊ ዶ/ር ሙሉጌታ ታፈሰ  ሥነ-ጥበባዊ ሰዋሰው ከሚያዘነብልባቸው አናስራት (elements) መሃከል ቅርበትና ርቀት አንዱ ነው፡፡ ሁሌም በነገሮች መሀል ነው የምንገኘው፡፡ ወደ እኛ የሚቀርቡም ሆነ ከኛ የሚርቁ ነገሮች መሃል ነው የምንኖረው፡፡ ታዲያ የቀረበውም ቅርብ፣ የራቀውም ሩቅ የሚሆነው እኛ ከቆምንበት አንፃር ስንለካው ነው፡፡ ቻይናዊው ሠዓሊ አይ ዌይ ዌይ፤ከቆመበት ሆኖ የመሃል ጣቱን ሲያሳየን፣ ጣቱ ግዙፍ ሆኖ በአንፃሩ ደግሞ ከርቀት የሚታየው የቤጂንግ ቤተ-መንግስትን አሳንሶ ያሳየናል፡፡ የአይ ዌይ ዌይን ስሳቅ ትተን ወደ ውስጣዊውና የውጭ መስመርን (Inside Track)  ስንመጣ፣ ከቅርበትና ርቀት አንፃር ስንመለከተው፣አሁንም ወደ እውነታ የሚቀርቡ እሳቤዎችን ነው የምናገኘው። የሰው ልጅ ቦታን ይፈጥራል፡፡ ከፈጠራቸውና ከሚኖርባቸው ቦታዎች ጋር ያለው ግንኙነት ከቦታዎቹ ጋር ያለውን ስሜታዊና ሀሳባዊ ተዛምዶም ጠቋሚ ነው። ሠዓሊ ዶ/ር ሙሉጌታ ታፈሰ፤  scenery ወይም ከባቢን በቅርበትና ርቀት ሲሰራ፣ በነፃነት የሚጨፍርና  የሚቦርቅ ነፃነቱን እንዲሁም የቅርቡን ይበልጥ እያቀረበና ሩቁንም እያራቀ፣ ስለ ቦታ ያለንን ስሜት፣ግንዛቤና ሃሳብ ጥልቅ ወደ ሆነ መረዳት ያሻግርልናል፡፡ ስለዚህ ትርዒት ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ እስከዚህም ላነበባችሁኝ ምስጋና ይገባችኋል፡፡ ምናልባት የመጨረሻ ነጥብ፡፡ እሱም የሠዓሊ ዶ/ር ሙሉጌታ ታፈሰን ጥበባዊ ጉዞ ጠያቂ ነው፡፡ ለመዳሰስ እንደሞከርኩት፤ሠዓሊ ዶ/ር ሙሉጌታ ታፈሰ ብዙ ሰው ነው፡፡ የአዕምሮውንም ዘላንነት እናያለን፡፡ ታዲያ ይህ ዘላን አእምሮው መቼ ነው ኢትዮጵያ ላይ የሚያርፈው? ኢትዮጵያን ፈፅሞ መተው የማይችለው ሠዓሊ ዶ/ር ሙሉጌታ ታፈሰ፤ ኑሮው ኢትዮጵያ ውስጥ ባለመሆኑ የሥራዎቹ ትኩረት ይበልጡን ዓለም አቀፋዊ ይዘትና ሰብዓዊነት ላይ እንዲሆን ያስገደደው ይመስላል። የኢትዮጵያ አፈር፣  የኢትዮጵያ  ሰማይ፣  የኢትዮጵያ ኑሮ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ህይወት በስራዎቹ በቂ ትኩረት አለማግኘታቸው ስለ ሠዓሊው ሳስብ የሚከነክነኝ ብቸኛው ጉዳይ ነው፡፡ ለነገሩ በብዙ አቅጣጫዎች ስንመለከተው፣ለእሱ አይነት የአኗኗር ዘይቤና ሰብዕና (በነገራችን ላይ በጣም ጭምትና ትሁት ሰብዕና ያለው ሰው ነው)ምቹ ያልሆነ ማህበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊ… ወዘተ ንቅዘት በሞላበትና የሥነ-ጥበባችን ማዕቀፍ ጤነኛ አካሄዶችን በማይከተልበት ሀገር መጥተህ ኑርና፣ ኢትዮጵያን የተመለከቱ ሥራዎች እየሰራህ ለሀገራችንም ቤዛ ሁን የሚል ሃሳብ ማንሳት ጭራሹንም የያዘውን ለማስጠፋት የሚደረግ ሙከራ ሊመስልብኝ ይችላል፡፡ ግን እንደው... ዝም ብሎ ቅር የሚል ነገር አለ አይደል? ለዚያ ነው ያነሳሁት፡፡ ስለ ሠዓሊ ዶ/ር ሙሉጌታ ታፈሰ በይበልጥ ለማወቅ www.mulugetatafesse.com’ን ይጎብኙ ፡፡ ቸር እንሰንብት!   

13 የአገሪቱ ታዋቂ ሳይንቲስቶች በአባልነቷ መቀጠሏን ደግፈዋል
የእንግሊዝን የአውሮፓ ህብረት አባልነት ቀጣይ ዕጣ ፋንታ የሚወስነው ህዝበ ውሳኔ በመጪው ሳምንት የሚካሄድ ሲሆን፣ ከአባልነቷ ትውጣ የሚለው አብላጫ ድምጽ የሚያገኝና ውሳኔው ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ፣ 800 ሺህ ያህል እንግሊዛውያን ከስራ ገበታቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ተዘገበ፡፡
ሴንተር ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ቢዝነስ ሪሰርች የተባለው የአገሪቱ የጥናት ተቋም ያወጣውን የጥናት ውጤት ጠቅሶ ዘ ቴሌግራፍ እንደዘገበው፣ በአገሪቱ ህዝቦች ቀጣይ ዕጣ ፋንታ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ የሚፈጥር ነው የተባለው ይህ ህዝበ ውሳኔ፣ እንግሊዝን ከህብረቱ አባልነት ውጭ ካደረገ፣ በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ ተሰማርተው ህይወታቸውን ይመሩ የነበሩ 800 ሺህ ያህል ዜጎች ስራ አጥ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
በአለማቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ 13 እንግሊዛውያን ሳይንቲስቶችም፣ እንግሊዝ በህብረቱ አባልነቷ ትቀጥል የሚለውን የውሳኔ ሃሳብ እንደሚቀበሉት ለቴሌግራፍ ጋዜጣ በላኩት ይፋ የአቋም መግለጫ ደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡
በቀጣዩ ህዝበ ውሳኔ ላይ በህብረቱ አባልነቷ ትቀጥል ብለው ድምጻቸውን እንደሚሰጡ ያስታወቁት ሳይንቲስቶቹ፣ አገሪቱ ከህብረቱ አባልነቷ መውጣቷ ሳይንሳዊ ምርምሮችንና ጥናቶችን የሚያደናቅፍ መሆኑን ገልጸው፣ ህብረቱ ተመራማሪዎችና ሳይንቲስቶች በትብብር እንዲሰሩ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ላቅ ያለ ሚና ሲጫወት እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡