Administrator

Administrator

ባለፈው 1 ዓመት የታተሙ መፃህፍት ይወዳደራሉ
     በረዥም ልቦለድ፣ በግጥምና በልጆች መፃህፍት ዘርፍ የሥነ ፅሁፍ ሥራዎች ተወዳድረው ሊሸለሙ ነው።
ኖርዝ ኢስት ኤቨንትስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃህፍት ኤጀንሲ ጋር በትብብር ያዘጋጁት ሆሄ የሥነፅሁፍ ሽልማት ፕሮግራም፤ አሸናፊ ደራስያንን ከመሸለም ባሻገር የንባብ ባህል እንዲስፋፋ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ላበረከቱ ክበባትንና ቤተ መፃህፍትም የሚመሰገኑበትና ዕውቅና የሚያገኙበት ይሆናል ተብሏል፡፡
የሽልማት ፕሮግራሙ አዘጋጆች ከትናንት በስቲያ በጎተ ኢንስቲትዩት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ለውድድር የሚቀርቡት መፃህፍት ከመስከረም 1 ቀን 2008 እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ የታተሙ መሆን አለባቸው፡፡ ተወዳዳሪ መፃህፍቱ በዳኞች ኮሚቴ በተዘጋጀላቸው መስፈርቶች መሰረት የሚመዘኑ ሲሆን በዳኞች ኮሚቴ ከሚሰጠው ውጤት በተጨማሪ አንባቢያን በነፃ የስልክ መልዕክትና በድረ ገፅ የሚሰጡት ድምፅም የተወሰነ ነጥብ ይኖረዋል ተብሏል። አጠቃላይ ውጤቱ የሚታወቅ ይሆናል፡፡
በውድድሩ መሳተፍ የሚፈልጉ ደራሲያን ከታህሳስ 4-19 2009 ዓ.ም ሞርኒንግ ስታር ሞል ላይ በሚገኘው የድርጅቱ ቢሮ፣ በጎታ ኢንስቲቲዩትና በቡክላይት መፅሀፍ መደብር መመዝገብ እንዳለባቸው የጠቆሙት አዘጋጆቹ፤ የሽልማት ስነ ስርዓቱ በሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡


      እናት የማስታወቂያ ስራዎች ድርጅት ከጀርመን የባህል ማዕከልና ከወመዘክር ጋር በመተባበር “አማካሪው አልፍሬድ ኤልግ በምኒልክ ቤተ-መንግስት” በሚል ርዕስ በዮናስ ታረቀኝ ወደ አማርኛ በተተረጎመው ታሪካዊ መፅሀፍ ላይ በነገው ዕለት ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በወመዘክር አዳራሽ ውይይት ይካሄዳል፡፡
ለውይይቱ የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት አቶ ብርሀኑ ደቦጭ ሲሆኑ በውይይቱ የመሳተፍ ፍላጎት ያለው ሁሉ እንዲገኝ ተጋብዟል፡፡

የኖቤል ተሸላሚዎችን አነጋግረዋል
     የአመቱ የኖቤል የስነጽሁፍ ተሸላሚ በመሆን የተመረጠውና “ስራ ስለሚበዛብኝ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ አልገኝም” በማለቱ የዓለማችን መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው አሜሪካዊው ድምጻዊና የሙዚቃ ግጥም ደራሲ ቦብ ዳይላን፣ ባለፈው ረቡዕ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር በዋይት ሃውስ እንዲገናኝ የቀረበለትን ግብዣ ባለመቀበል በስነስርዓቱ ላይ ሳይገኝ መቅረቱ ተዘግቧል፡፡
ኦባማ የዘንድሮ የኖቤል ተሸላሚ አሜሪካውያንን ከሽልማት ስነስርዓቱ በፊት በዋይት ሃውስ ለማግኘት ባለፈው ረቡዕ በያዙት ቀጠሮ፣ ሌሎች ተሸላሚዎች በስፍራው ቢገኙም ልማደኛው ዳይላን ግን ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የውሃ ሽታ ሆኖ በመቅረት ዳግም የመገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሊሆን እንደበቃ የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ይጠቁማል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ዳይላን ተሸላሚ መሆኑ ይፋ የተደረገ ሰሞን፣ “ከምወዳቸው ገጣሚያን አንዱ የሆነው ዳይላን ሽልማቱ ይገባዋል” በማለት የእንኳን ደስ አለህ መልዕክት ያስተላለፉለት ሲሆን  እ.ኤ.አ በ2012 ታላቁን የአገሪቱ የነጻነት ሜዳይ ሽልማት አበርክተውለት እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ምንም እንኳን ዳይላን ባይገኝም፣ ኦባማ በዕለቱ የፊዚክስ ኖቤል ተሸላሚዎቹን ዳንካን ሃልዳኔን  ማይክል ኮስተርሊዝን፣ የኢኮኖሚክስ ተሸላሚውን ኦሊቨር ሃርትን እንዲሁም የኬሚስትሪ ተሸላሚውን ሰር ጄ ፍሬዘር ስቶዳርትን  በዋይት ሃውስ በክብር ተቀብለው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈውላቸዋል፤ ለስራቸውም እውቅና ሰጥተዋቸዋል፡፡

የሚከተለው ተረት በአበሻም አለ፡፡ የህንዱ ግን ትንሽ ለየት ይላል፡፡ እነሆ፡-
ከዕለታት አንድ ቀን አይጦች ከባድ ሰብሰባ አደረጉ፡፡ የስብሰባው ዓላማ በየጊዜው በድመት የሚደርስብንን ጥቃት እንዴት እንከላከል? የሚል ነው፡፡
ሀሳብ ብዙ ከተብላላ በኋላ እንድ ዘዴ ለመዘየድ ተወሰነ፡፡ ይኸውም፤ ‹‹ድመት ሁልጊዜ ባልታሰበ ሰዓት እየመጣ አይጦችን የማጥቃት ስልት ስላለው፤ ይኼ እንዲሰናከል ማድረግ የሚቻለው፤ ድመት አንገት ላይ ቃጭል በማሰር ነው፡፡ ይህም የሚጠቅመው ድመት አድፍጦ ሲመጣ ቃጭሉ እየጮኸ እንዲያጋልጠው ነው! ተባለ፡፡ ያኔ እኛም በየጎሬያችን ጥልቅ እንላለን፡፡››
 ሁሉም አጨበጨቡ፡፡
‹‹ለዘመናት ስንታመስ የነበረበት ሁኔታ ዛሬ መላ ተመታለት!›› በሚል ሆታውና ዕልልታው ደራ!
በመካከል ግን አንድ አስተዋይ አይጥ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ አነሳ፡-
‹‹ለመሆኑ በድመት አንገት ላይ ቃጭሉን የሚያስር ጀግና አይጥ የቱ ነው?
እስቲ አስተያየት እንስጥበት››
ፀጥ ፀጥ ሆነ፡፡ ‹‹ማነው ደፋር?›› አለና ቀጠለ አስተዋዩ አይጥ፡፡ ወደ አንዱ አይጥ ዞር ብሎም፤
‹‹አንተ ትሻል ይሆን? ሲል ጠየቀው፡፡ አይጡም፤
‹‹እኔ የአይጥ ቅድመ- አያቶቼ ከባድ ግዝት አለብኝ፡፡ እድመት አጠገብ ከደረስክ የተረገምክ ሆነህ ቅር ብለውኛል!›› አለ፡፡
ሁለተኛው አይጥ ተጠየቀ፡፡ እሱም፤
‹‹እኔ ወደ ድመት ከተጠጋሁ የሚጥል በሽታ አለብኝ፡፡ እዛው ክልትው ነው የሚያደርገኝ!›› አለ
‹‹አንተስ?›› ተባለ ሶስተኛው፡፡
‹‹እኔ ከዚህ ቀደም በድመት ተይዤ ድመቶች ችሎት ቀርቤ፤ ሞት ተፈርዶብኝ ነበር፡፡ ዕድሜ ለእናንተና አባቴ፣ ጥበብ አስተምረውኝ ስለ ነበር አስቀድሜ የሞትኩ መስዬ ለጥ አልኩ፡፡ ልፍስፍስ ብዬ ተኛሁ፡፡ ቢያነሱኝ፣ ቢሸከሙኝ፣ ቢያገላብጡኝ ትንፍሽ ሳልል ወድቄ ቀረሁ፡፡ ሞቷል ብለው በማሰብ ቃሬዛ ሊያመጡ ሲሄዱ እኔ ፈትለክ አልኩ! ስለዚህ አሁን ድመት ሰፈር በምንም መልኩ ቢሆን ዝር ማለት የለብኝም!›› አለ፡፡
ሁሉም አይጦች በየተራ እየተነሱ ከባድ ከባድ ሰበቦችን እያቀረቡ ተቀመጡ፡፡  
አንድ አይጥ አንድ አዲስ ሀሳብ አመጣ፡-
‹‹ለምን ድመቱ ሲያንቀላፋ ሄደን ቃጭሉን አናጠልቅለትም?›› አለ፡፡
አስተዋይ አይጥ ግን ሀሳቡን ተቃወመና እንዲህ አለ፡-
‹‹የህንድ ድመት የአነር ዝርያው ይበዛል፡፡ የህንድ አነር በአፈ-ታሪክ እንደሚታወቀው፤ ሲተኛ አንድ ዓይኑን ጨፍኖ፣ አንድ ዐይኑን ገልጦ ነው፤ ይባላል፡፡ ስለዚህ አድፍጠን ብንሄድ እንኳ በሚያየው ዐይኑ ይይዘናል›› አለ፡፡
 ‹‹ታዲያ ምን በጀን?›› አሉት ሌሎቹ፡፡
አስተዋዩ አይጥም፤
‹‹የሚሻለው አንድ የአነር ጥናት ያጠኑ የገዳም አባት አሉ፡፡ እሳቸውን እንጠይቅ›› አለ፡፡
ሁሉም ተስማሙና ወደ ጠቢቡ ሄዱ፡፡ ጠቢቡም፤
‹‹አይጦች ሆይ! የአነር-ክልስ ድመት የዋዛ እንዳይመስላችሁ፡፡ ፀባዩ ህብረ-ቀለም ነው፡፡ ዓይኑን የሚጨፍነው ወተት ከሰጣችሁትና ሲጠግብ ብቻ ነው፡፡ በዛች ደቂቃ ብቻ ነው ቃጭሉን ልታጠልቁለት የምትችሉት!›› አሉ፡፡
ጥያቄው ግን ቀጠለ፡-
‹‹ወተቱንስ እንዴት ነው የምናቀርብለት? ማንስ ነው የሚያቀርበው?››
‹‹ወተቱንማ መጀመሪያ ንፁህ ወለል ላይ አፍስሳችሁ እናንተ ትበርራላችሁ፡፡ እሱን ሲልስ ቀጣዩን ወተት በሳህን ትገፉና ትጠፋላችሁ፡፡ ወደ ዋናው የወተት መድረክ ሲገባ ትጠብቁታላችሁ፤ ሲጠግብ ዓይኑን ይጨፍናል፡፡ ያኔ ነው የቃጭሉ ማንጠልጠል ሰዓት!››
አሏቸው፡፡
እንደተባለው አደረጉ፡፡ ቀናቸው፡፡
ግን ክፋት አይቆምምና ያ ድመት ሌላ ጊዜ ጓደኛውን ይዞ መጣ፡፡ እሱ ባንድ ጉድጓድ በኩል ቃጭሉን እያንቃጨለ ይመጣል፡፡ በሌላኛው የጉድጓዱ ጫፍ ግን ቃጭል የሌለውን ድመት ይልከዋል፡፡ አገር አማን ነው ብለው በዛኛው ጉድጓድ ብቅ የሚሉት አይጦች ዋጋቸውን አገኙ!
* * *
እንግዲህ ባለ ቃጭልና ቃጭል አልባ ድመት በሀገራችን በብዛት አለ፡፡ አንድ ችግር ሲፈታ ሌላ ችግር ይፈልቃል። ጀርሙ ከሥሩ- ስላልተነቀለ ነው! የጋንግሪን ልክፍት ይመስላል፡፡ ስብሰባዎች ይካሄዳሉ፡፡ ጠማጁና ተጠማጁ ይፋጃሉ፡፡ አንዱ የልማት መላ ሲፈጥር፣ ሌላው የጥፋት መላ ያደራጃል፡፡ እስከ ሚቀጥለው ስብሰባ ይሄው እርቅ- ወ-ጠብ ሥርዓት ይሆናል፡፡ ይቀጥላል፡፡ ‹‹ማንም ከማንም አይማርም›› ይላል ሎሬት ፀጋዬ፡፡
‹‹ተምረህ ተምረህ ደንቆሮ ሆነሃል!›› ይላሉ ገጣሚና ፀሀፌ-ተውኔት መንግሥቱ ለማ! አንድን ግምገማ እንዴት ነገሬን በሆድ አምቄ ፈተናውን ልለፈው? ከሆነ ጥረታችን፤ ለውጥ ወደሚቀጥለው ዓመት ግምገማ ያልፋል እንጂ የተመኘነው የተሻለ ሥርዓት አይመጣም! መቅሰስ እንጂ እራት አይሆንልንም፡፡
ብዙ በሥልጣን የባለገ ሰው መቀነሳችን ቀናነት ካለው፤ ጎጂ አይደለም፡፡ የምንተካውንም በቅንነት ማሰብ ግን ወደድንም ጠላን ይጠበቅብናል፡፡ በዕሙናዊ ባህሉ ግምገማን የመሰለ ነገር የለም! በሒሳብ ገፅታው ግን ማናቸውንም አምባገነናዊ ጥፋት ለመፈፀም በሩ ክፍት ነውና ያሳስባል፡፡ ከትናንት በስቲያ ምን ነበርን? ትናንትስ? ዛሬስ? ብለን መጠየቅ ያባት ነው፡፡ ክልሎች እርስ በርሳቸው ሲጋጩ ከርመው፣ ዛሬ ችግሩ ተፈታ ስንል የትላንቱ መሰንበቻ ግጭታቸው መረጃ ተደብቀን ነበርን? ብሎ መጠየቅ ዛሬን እንድንገመግም ያግዘናል፤ የአመራሮቻችንንም ሀቀኛ ባህሪ እንድናገናዝብ ቀኝ እጅ ይሆነናል፡፡ የአመራሮች ችግር ተፈታ ስንል የህዝቦች ምሬትና ያልተፈቱ ጥያቄዎች መፍትሔ ማግኘት ጉዳይ መላ ይኖረዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን! ዕውን ተስፋችን ተስፋ አለውን!?
የሀገራችን ዓለማቀፋዊ ግንኙነትንም ከክልል ልቀንና ባሻገር አይተን ዕጣ-ፈንታችን ምን ይሆን? የበለፀገችው አሜሪካ ከእኛ ከድሆቹ እኩል ‹‹ምርጫ ተጭበርብሯል›› በሚባልበት ዘመን ወዴት እየተጓዝን ነው? ብሎ መጠየቅ ክፍት አእምሮ ያላቸው አገሮች ጥያቄ ሊሆን ይገባል! ያለ ዓለማዊ ግንኙነት ብቻችንን ደሴት ሆነን አንኖርምና የዓለምን ጠረን ማሽተት፣ መልኩን ማየት፣ ጣዕሙን መቅመስ፤ አካሉን መንካት ብቻ ሳይሆን በስድስተኛ ህዋሳችንም ቢሆን (with our sixth sense too) ለማጣጣም መሞከር አለብን፡፡ በአለም ላይ በሚከሰት ሂደት ሳቢያ እያንዳንዱ ሀገር ብቻ ሳይሆን በውስጡ የሚኖር ህልው ከጉዳይ መፃፍ አለበት፡፡ የህዝብ ብዛት መጨመር ለህልውናችን ምን ያህል አስጊ ነው የምንለውን ያህል፤ የህዝብ ቁጥር መቀነስስ ታላላቅ ሀገሮችን አያሳስባቸውም ወይ? ወደብ ያላቸውና የሌላቸው አገሮችስ በውሃ ላይ ካለ ባህራዊ ኃይል ጋር ምን ያህል ህልውናቸው ስጋት ላይ ነው? ታላላቅ አገሮች የንግድ ግንኙነታቸው ሲዛባ እኛን አይመለከተንም ወይ? ሰደትን የገቢ ምንጭ ያደረጉ እንደኛ ዓይነት አገሮችስ ኢኮኖሚያቸው ምን ይውጠው ይሆን? (ለምሳሌ እንደሜክሲኮ የአንበሳውን ድርሻ ለስደት ድርጎ (Remittance) ያደረጉ አገሮች የሚሰማቸው በቀል ነው የጎረቤት አገር ፍቅር?...) የራስን ኢኮኖሚ በራስ ማስተዳደር ይቻላልን? ማስተዋል የሚያሻቸው አያሌ ሂደቶች የሥጋቶቻችን እኩያ ናቸው! ጥገኛ ኢኮኖሚ የራሱን አደጋ ማስተዋል አለበት። ከአፍንጫ ሥር የራቀ መሆን አለበት፡፡
በአሜሪካና በአውሮፓ አያሌ ዛፎች አሉ፡፡ በነዚህ ዛፎች ላይ ደግሞ አያሌ የወፍ ጎጆዎች አሉ፡፡ ከአፍሪካም፣ ከእስያም፣ ከላቲን አሜሪካም የመጡ ወፎች ያረፉባቸው ዛፎች አያሌ ናቸው፡፡ የዘር፣ የቀለም፣ የሃይማኖት፣ የአመለካከት ወዘተ ባለቤት የሆኑትን ወፎች ለመግፋት ወይም ለማባረር የዓለም ኃያላን መሪዎች ያኮበከቡ በሚመስልበት በአሁን ወቅት ዕሳቤያችን ምን መሆን አለበት? ብሎ ማሰብ ደግዬ መንገድ ነው፡፡ ቀኝና ግራ ሳይባል የአክራሪዎች መንገድ ሊከሰት የሚችልበት አሳቻ ሁኔታ ሊታይ ይችላል፡፡ ‹‹ዛፉን ሳይሆን ዛፉ ላይ ያለውን ጎጆ እይ›› የሚለው አባባል የሚያሻን እዚህ ላይ ነው፡፡ ልቡና ይሰጠን!

ከአፍሪካ አንደኛ ነው

        ኢትዮጵያዊው ያሬድ ንጉሴ ዲሳሳ በዓለም ሻምፒዮና በብራዚላዊያን ጂጁትሱ ስፖርት ለግማሽ ፍፃሜ በመድረስ በ4ኛ ደረጃ ያጠናቀቀ ሲሆን ውጤቱ ለኢትዮጵያም ለአፍሪካም በታሪክ የመጀመሪያው ነው፡፡ በ2016 የዓለም ጂጁትሱ ሻምፒዮና ያሬድ ንጉሴ በመጀመሪያው ዙር ጀርመናዊ ተጋጣሚውን በማሸነፍ ሲሆን፤ በ2ኛው ዙር ደግሞ ከሩሲያው ተጋጣሚ ጋር ተገናኝቶ በስፖርቱ አዳዲስ ህጎች ጋር በተገናኘ ያስመዘገበው ውጤት ተሰርዞበት ለግማሽ ፍፃሜ መድረስ ችሏል። በጂጁትሱ የዓለም ሻምፒዮና የያሬድ አሰልጣኝ ሆነው የተሳተፉት በዓለማቀፉ የጂጁትሱ ፌዴሬሽን የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ የሆኑትና ስፖርቱን በኢትዮጵያ በማስተዋወቅ ፈር ቀዳጅ የሆኑት ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ ናቸው፡፡ ዶ/ር ፀጋዬ ከጀርመን ለስፖርት አድማስ በሰጡት አስተያየት የያሬድ ውጤት ከስምንት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የተዋወቀውን የጂጁትሱ ስፖርት በከፍተኛ ደረጃ የሚያነቃቃና በአፍሪካ ደረጃ ግንባር ቀደም ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል ስኬት ነው ብለውታል፡፡
በግማሽ ፍፃሜው በ56 ኪ.ግ ኮሎምቢያዊውን ተጋጣሚ ያገኘ ሲሆን በዚሁ ፉክክር ላይ በስፖርቱ በቅርቡ በተቀየሩ አዳዲስ ህጎች ሳቢያ የነበረው ብልጫ ተወስዶበት የነሐስ ሜዳሊያው ለጥቂት አምልጦታል፡፡ ያሬድ ንጉሴ የጁቬንቱስ ክለብ ሰልጣኝ ሲሆን ከዚህ በፊት በጀርመን ዱሱልዶፍ በተካሄደ አለማቀፍ ውድድር ተሳትፎም ያውቃል። ባለፈው ሰሞን በፖላንድ በተካሄደው የዓለም የጂጁትሱ ሻምፒዮና ያሬድ ንጉሴ በ4ኛ ደረጃ ማጠናቀቁ ከፍተኛ አድናቆት ያተረፈበት ሲሆን፤ ከአፍሪካ በ1ኛ ደረጃ ከመላው ዓለም በ5ኛ ደረጃ እንዲቀመጥ አስችሎታል፡፡ በሻምፒዮናው ላይ ከነበረው ተሳትፎ በኋላ በአቡዳቢ በሚካሄድ ሴሚናር ከመጋበዙም በላይ በጂጁትሱ  ስፖርት ከፍተኛ ደረጃ ካላቸው ብራዚላዊ አሰልጣኝ ጋር የሚሰራበት ዕድል ተፈጥሮለታል፡፡ በዚሁ የዓለም ሻምፒዮና ላይ 600 የጂጁትሱ ስፖርተኞችና 200 አሰልጣኞቻቸው ተካፋይ ነበሩ፡፡ በቀጣይ በፖላንድ በሚካሄደው የ2017 ወርልድ ጌምስ አፍሪካን በመወከል የሚሳተፍ ይሆናል፡፡ ወርልድ ጌምስ፣ ካራቴ፣ ሞተር ስፖርት፣ ዳርት፣ ጂዶ፣ ጂጁትሱና ሌሎች ስፖርቶችን የሚያካትት አለማቀፍ የውድድር መድረክ ነው፡፡
ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ ነዋሪነታቸው በጀርመን ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የጂጁትሱ ስፖርትን በማስፋፋት ፈርቀዳጅ ሚና የተጫወቱ ናቸው። በታላቁ የጀርመን የመኪና አምራች ኩባንያ መርሴዲስ ቤንዝ በፕሮጀክት ማኔጅመንትና በዳይቨርሲቲ ማኔጅመንት ለ15 ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን ከፕሮጀክት ማኔጅመንት ጋር በተያያዘ በርካታ መፅሀፍቶችን ያዘጋጁና በተለያዩ ጊዜያትም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የተለያዩ ስልጠናዎችና ወርክሾፖችን ይሰጣሉ፡፡ ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ጂጁትሱ ዩኒየን ምክትል ሊቀመንበር ዓለማቀፉ ጂጁትሱ ማህበር አባልና የምስራቅ አፍሪካ ዞን ተወካይ እንዲሁም በዓለማቀፉ የጂጁትሱ ፌዴሬሽን የስነ ምግባር ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የጂጁትሱ ስፖርትን ለማስፋፋት ከ8 ዓመታት በፊት በፍትህ ሚኒስቴር የተቋቋመ ማህበር መኖሩን ለስፖርት አድማስ የገለፁት ዶ/ር ፀጋዬ በአዲስ አበባ፣ በድሬደዋ፣ በሐረርና በሀዋሳ የጁዶ ጂጁትሱ ማህበራት ተቋቁመው እንደሚንቀሳቀሱና በአጠቃላይ እስከ 500 የጂጁትሱ  ስፖርተኞችን በማቀፍ እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡      
የጂጁትሱ ስፖርት የማርሻል አርት አይነት ስፖርት ሲሆን የመጣል የመወርወር የመጥለፍና የተለያዩ የምት ስንዘራ ቴክኒኮችን የሚተገብር ስፖርት ነው፡፡ ይህ ስፖርት በአሁኑ ወቅት ብራዚላዊያን ጂጁትሱ በሚል መጠሪያ በዓለማቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ ሲሆን ዓለማቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በ2020 እ.ኤ.አ ከሚካሄደው የቶኪዮ ኦሎምፒክ በኋላ የኦሎምፒክ ስፖርት ለማድረግ ትኩረት እየሰጠው ነው፡፡

 ሙሴቪኒ በበኩላቸው፤ ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ ወንዶችን አውግዘዋል

     የኡጋንዳ ርዕሰ መዲና ካምፓላ የካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ኪዚቶ ሉዋንግዋ፤የአገሪቱ ሴቶች በወንዶች ላይ ድብደባ መፈጸማቸውን እንዲያቆሙ መጠየቃቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ሚፒንጊ በተባለቺው የአገሪቱ አውራጃ ከሚቀርቡ አስር የቤት ውስጥ ጥቃት አቤቱታዎች መካከል ግማሹ፣ በሚስቶቻቸው የተደበደቡ ባሎች ጉዳይ መሆኑን የአገሪቱ ፖሊስ ሪፖርት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ነው ጳጳሱ፣”ሴቶች ወንዶችን መደብደብ ያቁሙ” ሲሉ መልዕክት ያስተላለፉት ብሏል - ዴይሊ ሞኒተር፡፡ ጳጳሱ አክለውም፣”ወንዶች የቤተሰብ መሪ (ሃላፊ) እንደሆኑ አምነው መቀበል አለባቸው፤ ባሎቻቸውን መውደድና ማክበርም ይጠበቅባቸዋል” ሲሉ መናገራቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
በአንጻሩ የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩሪ ሙሴቬኒ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችል አዲስ ዘመቻ መጀመራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤መንግስታቸው ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ ባሎችን እንደሚያወግዝ ማስታወቃቸውን አመልክቷል፡፡

 - ከ500 በላይ በሚሆኑ ኩባንያዎች የባለቤትነት ድርሻ አላቸው
       - ኦባማ ባለቤታቸው ለፕሬዚዳንትነት እንደማትወዳደር አስታወቁ

      ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሙሉ ትኩረታቸውን አገር በመምራት ስራቸው ላይ ለማድረግና የጥቅም ግጭት ስጋትን ለማስወገድ በማሰብ፣ ወደ ዋይት ሃውስ ሲገቡ የንግድ ስራቸውን ሙሉ ለሙሉ እንደሚያቆሙ ባለፈው ረቡዕ ማስታወቃቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
“ሙሉ ትኩረቴን አገሪቱን ለመምራትና አሜሪካን እንደገና ታላቅ አገር ለማድረግ ስል ግዙፉን የቢዝነስ ስራዬን ሙሉ ለሙሉ አቋርጣለሁ፡፡ እርግጥ ነው ፕሬዚዳንት ሆኜ ቢዝነስ እንዳልሰራ የሚከለክለኝ ህግ የለም፤ነገር ግን  በንግድ ስራዬና በስልጣኔ መካከል የጥቅም ግጭት እንዳይኖር ማድረግ እንዳለብኝ ይሰማኛል” ብለዋል፤ትራምፕ ባለፈው ረቡዕ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፡፡
አገር የመምራቱ ተልዕኮ የበለጠ ዋጋ አለው ያሉት ትራምፕ፣ ከተሰማሩባቸው በርካታ የቢዝነስ መስኮች ሙሉ ለሙሉ መውጣት የሚያስችሏቸው ህጋዊ ሰነዶች እየተዘጋጁ እንደሚገኙና ጉዳዩን በተመለከተ በቅርቡ ይፋዊ መግለጫ እንደሚሰጡም ተናግረዋል፡፡ ትራምፕ ከዚህ ቀደምም የቢዝነስ ስራቸውን የመምራት ሃላፊነቱን ለሶስቱ ልጆቻቸው ዶናልድ ጄአር፣ ኤሪክ እና ኢቫንካ እንደሚያስረክቡ ተናግረው እንደነበር ዘገባው አስታውሷል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ከሚታወቁበት ትርፋማ የሪልእስቴት ኢንቨስትመንታቸው በተጨማሪ፣ በአሜሪካና በተለያዩ የአለማችን አገራት በአያሌ የንግድ ዘርፎች ውስጥ የተሰማሩ ሲሆን ከ500 በላይ በሚሆኑ ታላላቅ ኩባንያዎችም የባለቤትነት ድርሻ እንዳላቸውም ይታወቃል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በዲሞክራቷ ዕጩ ሄላሪ ክሊንተን ሽንፈት የተናደዱ አሜሪካውያን ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ከአራት አመታት በኋላ በሚደረገው ምርጫ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ በፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ ዘመቻ መጀመራቸው የሚታወስ ሲሆን ባለቤታቸው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ግን ሚሼል ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት እንደማይወዳደሩ አስታውቀዋል፡፡ ኦባማ ከሮሊንግ ስቶን መጽሄት አዘጋጅ ጃን ዌነር ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ፣ ባለቤታቸው ሚሼል ፖለቲከኛ የመሆን ፍላጎት እንደሌላቸው በመጥቀስ፣ በፍጹም ለፕሬዚዳንትነት አትወዳደርም ማለታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ መጽሄቱን ጠቅሶ ባለፈው ረቡዕ ዘግቧል፡፡

 በሰከንድ 130 ኳድሪሊዮን ስሌቶችን የመስራት አቅም አለው ተብሏል
       የጃፓን ኮምፒውተር ሳይንስ ባለሙያዎች በዓለማችን በፍጥነቱ አቻ አይገኝለትም የተባለውንና በአንድ ሰከንድ 130 ኳድሪሊዮን ስሌቶችን የመስራት አቅም ያለውን እጅግ ፈጣን ኮምፒውተር ለመስራት ማቀዳቸው ተዘግቧል፡፡
139 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ ይደረግበታል የተባለውና ስራው በመጪው የፈረንጆች አመት 2017 ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ፈጣን ኮምፒውተር፤አገሪቱ ያለ አሽከርካሪ የሚንቀሳቀሱ መኪኖችንና ሮቦቶችን በአዲስ ፈር ቀዳጅ ፈጠራ ለመስራት የያዘቺውን ዕቅድ የሚያግዝ ነው መባሉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ናሽናል ኢንስቲቲዩት ኦፍ አድቫንስድ ኢንደስትሪያል ሳይንስ ኤንድ ቴክኖሎጂ በአገሪቱ ተቋም የሚተገበረው የፈጣን ኮምፒውተር ፕሮጀክቱ፣ የጃፓን መንግስት አገሪቱን ብቃት ያላቸው ማሽነሪዎችን በማምረት ረገድ አለማቀፍ መሪነቱን ከያዙት ደቡብ ኮርያና ቻይና ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ የያዘው እቅድ አካል መሆኑንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የጃፓኑ ኮምፒውተር በስራ ላይ ሲውል በአሁኑ ወቅት የአለማችን ፈጣን ኮምፒውተር የሆነውን የቻይናውን “ሰንዌይ ቲያሁላይት” በመተካት የቀዳሚነቱን ስፍራ ይይዛል ተብሏል፡፡

 500 ሺ ያህል ህዝብ በጦርነት አገሩን ጥሎ ተሰዷል
       የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በእርስ በእርስ ግጭት ከምትታመሰዋ የማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር ግማሽ ያህሉን የሚሸፍነውና ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የአገሪቱ ህዝብ የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው አስታወቀ፡፡ አገሪቱን ከ3 አመታት በፊት ከገባችበት የእርስ በእርስ ግጭት ለማውጣትና ወደ መረጋጋት ለመመለስ የሚደረገው ጥረት የተሻለ ለውጥ ቢመዘገብበትም፣ ባለፈው መስከረም ወር በተፋላሚ ሃይሎች መካከል ዳግም ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ የሰብዓዊ ቀውሱ መባባሱንና የእርዳታ ፍላጎቱ መጨመሩን የተመድ የሰብዓዊ ጉዳይ ትብብር ቢሮ ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ በአገሪቱ በሚንቀሳቀሱ የሰብዓዊ ድርጅቶች ላይ ሳይቀር ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑ፣ ለዜጎች እርዳታ እንዳይደርስ እንቅፋት ጥሯል ያለው ዘገባው፤ የአገሪቱን የ2017 የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎት ለማሟላት 400 ሚሊዮን ዶላር  ገንዘብ እንደሚያስፈልግ መገለጹንም ጠቁሟል፡፡
በአገሪቱ ለሶስት አመታት በዘለቀው የእርስ በእርስ ግጭት ሳቢያ 400 ሺህ ያህል ዜጎች በአገር ውስጥ ሲፈናቀሉ፣ ሌሎች ግማሽ ሚሊዮን ያህል ዜጎች ደግሞ ወደ ጎረቤት አገራት ቻድ፣ ካሜሩንና ኮንጎ መሰደዳቸውን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

 ኮሙኒስቱ አብዮተኛ ፊደል ካስትሮ ኩባን ለአምስት አሰርት ዓመታት የገዙ አምባገነን  መሪ ሲሆኑ ከታላቋ ብሪቴይን ንግስት ኤልዛቤትና ከታይላንዱ ንጉስ ቀጥሎ ለረዥም ጊዜ በስልጣን ላይ የቆዩ የዓለማችን ሦስተኛው መሪ ነበሩ፡፡ በከፍተኛ ህመም አስገዳጅነት የዛሬ 10 ዓመት ሥልጣናቸውን ለወንድማቸው ያስረከቡት ካስትሮ፤ ባለፈው አርብ በ90 ዓመታቸው ማለፋቸው ይታወቃል፡፡  
ከ40 ዓመት በላይ የግድያ ሙከራዎች፣ ወረራና የኢኮኖሚ ማዕቀብ የተደረገባቸው ፊደል ካስትሮ፤ ከስልጣን መንበራቸው ንቅንቅ ሳይሉ ዘጠኝ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ተፈራርቀዋል - ከአይዘንአወር እስከ ክሊንተን፡፡
ፊደል ካስትሮ በዓለም ረዥሙን ንግግር በማድረግ ክብረወሰን ይዘዋል፡፡ እ.ኤ.አ ሴፕተምበር 26 ቀን 1960 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለ4 ሰዓት ከ29 ደቂቃ ንግግር አደርገዋል። በዚህም ረዥም ንግግራቸው የዓለም ድንቃ ድንቅ ክስተቶችን  በሚመዘግበው “ጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ” ስማቸው ሰፍሯል፡፡ በእርግጥ ካስትሮ በአገራቸው ኩባ ከዚህም የላቀ ክብረወሰን አላቸው፡፡ በ1986 ዓ.ም በሃቫና ሦስተኛው የኮሙኒስት ፓርቲ ኮንግረስ ሲካሄድ ለ7 ሰዓታት ከ10 ደቂቃዎች ያህል ንግግር አድርገዋል፡፡  
ፊደል ካስትሮ ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት የጀመሩት ገና በለጋ ዕድሜያቸው ነበር ማለት ይቻላል። የ12 ዓመቱ ታዳጊ ካስትሮ በወቅቱ ለሁለተኛ ጊዜ ለተመረጡት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት በፃፈው ደብዳቤ፤በድጋሚ በመመረጣቸው ደስታውን ገልጾ፣የ10 ዶላር ኖት እንዲልኩለት ጠይቆ ነበር - ‹‹የ10 ዶላር ኖት ከዚህ ቀደም አይቼ አላውቅም›› በማለት፡፡
ደቡብ አፍሪካ ከዘረኛው የአፓርታይድ አገዛዝ ለመላቀቅ ያደረገችውን የነፃነት ትግል በአጋርነት የደገፉት ፊደል ካስትሮ፣ከኔልሰን ማንዴላ ጋር አንድ መፅሃፍ በትብብር ጽፈዋል፡፡  ርዕሱም፡- ‹‹HOW FAR WE SLAVES HAVE COME!›› ይሰኛል፡፡
ካስትሮ ከብዙዎቹ አምባገነን መንግስታት በተለየ በኩባ በስማቸው የተሰየሙ መንገዶች፣ ህንፃዎች ወይም ሰፈሮች የሉም፡፡ ይሄን ያደረጉትም አምልኮተ-ሰብዕ ለመፍጠር ባለመፈለጋቸው ነው ይባላል። ህልፈታቸውን ተከትሎ በኩባ ለ9 ቀናት ብሄራዊ ሀዘን የታወጀላቸው ካስትሮ፤ አሁን ከሞታቸው በኋላ መንገድ ወይም አደባባይ በስማቸው ሊሰየምላቸው እንደሚችል ተነግሯል።  
ከሀብታም ቤተሰብ እንደተወለዱ የሚነገርላቸው ካስትሮ፤ በስልጣን ላይ ሳሉ እዚህ ግባ በማይባል ዝቅተኛ ደሞዝ እንደሚተዳደሩ በመግለጽ በድህነት የሚማቅቅ ህዝባቸውን ሲያሞኙ ኖረዋል፡፡ እውነታው ግን ከድህነት ጋር የማይተዋወቁ፣ የቅንጦት ህይወት ያጣጣሙ ሚሊየነር መሆናቸው ነው፡፡ ሁነኛ የመረጃ ምንጮች እንደሚጠቁሙት፤ ጠቅላላ የሃብታቸው መጠን 900 ሚ.ዶላር ነው፡፡ በዚህም ሃብታቸው የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶችን እነ ቢል ክሊንተን፣ ባራክ ኦባማና ጆርጅ ቡሽን ይበልጣሉ፡፡
የኩባ የስለላና ደህንነት ቢሮ እንደሚለው፤ ፊደል ካስትሮ በስልጣን ዘመናቸው ከ600 በላይ የግድያ ሙከራ በአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲአይኤ ቢደረግባቸውም ከሞት  ተርፈው ለግማሽ ክ/ዘመን ገደማ ኮሙኒስት አገራቸውን ገዝተዋል። ካስትሮ ከሞት ጋር ድብብቆሽ መጫወት የጀመሩት ገና በወጣትነት የአብዮተኝነት ዘመናቸው ሲሆን በወቅቱ ሁለት ጊዜ ሞተዋል ተብሎ በኩባ ፕሬሶች ተዘግቦ ነበር። “ከግድያ ሙከራ መትረፍ የኦሎምፒክ ውድድር ቢሆን ኖሮ የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ እሆን ነበር” በሚለው ዝነኛ ንግግራቸው የሚታወቁት ካስትሮ፤የማታ ማታ በሰው እጅ ሳይሆን በተፈጥሮ እርጅና ህይወታቸው አልፏል። ሲአይኤ የኩባን ፕሬዚዳንት ለመግደል ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም ይላሉ - መረጃዎች፡፡ እንደ ነፍሳቸው የሚወዱትን ሲጋር ከመመረዝ እስከ በአልሞ ተኳሽ ማስገደል እንዲሁም በሚወዱት የቸኮሌት ሚልክሼክ ውስጥ የተመረዘ ክኒን ከመጨመር እስከ ጫማቸውን በመርዘኛ ኬሚካል መበከል ድረስ... እና ሌሎችም የግድያ ሙከራዎች ቢደረግባቸውም አንዱም ለውጤት አልበቃም፡፡