Administrator

Administrator

Saturday, 01 August 2015 14:26

የፀሐፍት ጥግ

(ስለ ተፈጥሮና ውበት)
ተራሮቹ እየተጣሩ ነው፤ እናም መሄድ አለብኝ፡፡
ጆን ሙይር
ውበት እውነት ነው፤ እውነትም ውበት፡፡
ጆን ኪትስ
ማናቸውም ውብ ነገሮችን የማየት ዕድል አያምልጣችሁ፡፡ ውበት የእግዚአብሄር የእጅ ፅሁፍ ነውና፡፡
ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን
ዛፍ ብሆን ኖሮ ሰውን የምወድበት ምክንያት አይኖረኝም ነበር፡፡
ማጊ ስቲፍቫተር
ተፈጥሮ የሚጎበኝ ሥፍራ አይደለም፡፡ ቤታችን ነው፡፡
ጌሪ ስኒደር
አንገቴ ላይ አልማዝ ከማደርግ ይልቅ ጠረጴዛዬ ላይ ፅጌረዳ አበባ ቢኖረኝ እመርጣለሁ፡፡
ኢማ ጎልድማን
ቅድመ አያትህ እንደ ምግብ ያልተቀበሉትን ምንም ነገር አትብላ፡፡
ማይክል ፓላን
በዓለም ላይ ያለውን ውበት መመልከት፣ አዕምሮን የማጥሪያ የመጀመሪያው እርምጃ ነው፡፡
አሚት ሬይ
ተፈጥሮን በጥልቀት ተመልከት፤ ያን ጊዜ ሁሉንም ነገር የተሻለ ትረዳለህ፡፡
አልበርት አነስታይን
በምድር ላይ ገነት የለም፤ ነገር ግን የገነት ሽርፍራፊዎች አሉ፡፡
ጁሌስ ሬናርድ
ከእያንዳንዱ ደመና ጀርባ ሌላ ደመና አለ፡፡
ጁዲ ጋርላንድ
ምድር ባዶ እግራችሁን ስትዳስሳችሁ እንደሚያስደስታትና ነፋስ ከፀጉራችሁ ጋር መጫወት እንደሚናፍቀው አትርሱ፡፡
ካሊል ጂብራን
ፊታችሁን ለመመልከት በመስተዋት ትጠቀማላችሁ፤ ነፍሳችሁን ለመመልከት በጥበብ ሥራዎች ትጠቀማላችሁ፡፡
ጆርጅ በርናርድ ሾው

  ከህንድ ጦርነቶች በአንዱ እንዲህ ሆነ አሉ፡፡
የፈረሰኛው ብርጌድ የወራሪዎቹን ጐሣ ድባቅ መታና ደመሰሰ፡፡ የተረፈው የጐሣው መሪ ብቻ ነበር፡፡
የፈረሰኛው ብርጌድ አለቃ ለተረፈው መሪ እንዲህ አለው፡-
“እጅግ አድርገህ በጀግንነት ስለተዋጋህ ነብስህን አተርፍልሃለሁ - አልገድልህም!”
ያም የወራሪዎቹ ጐሣ መሪ፤ ስለተደረገለት ምህረት ምሥጋና ለማቅረብ ቃላት ሲፈልግ ሳለ፣ ከተራራው አናት መዓት የህንድ መንጋ መጥቶ የፈረሰኛውን ብርጌድ ይደመስሰዋል። የተረፈ አንድ ሰው ቢኖር የብርጌዱ አለቃ ብቻ ነው፡፡ አሁን እንግዲህ ቦታ ተለዋወጡ - የብርጌዱ አለቃና የወራሪዎቹ መሪ፡፡
የወራሪዎቹ መሪ ለተረፈው የብርጌዱ አለቃ በፈንታው እንዲህ አለው፡-
“እኔ እንዳንተ ደግ አልሆንልህም፡፡ ሞት አይቀርልህም፡፡ ግን ሦስት ምኞት እንድትናገር እድል እሰጥሃለሁ”
የብርጌዱ አለቃም፤
“የመጀመሪያ ምኞቴ፤ ፈረሴን ለማየት እንድትፈቅድልኝ ነው” አለ፡፡ ተፈቀደለትና ፈረሱ መጣለት፡፡ ከዚያም የብርጌዱ አለቃ ለፈረሱ የሆነ ነገር በጆሮው ሹክ አለው፡፡ ፈረሱ ፈረጠጠ፡፡
ይሄኔ የብርጌዱ አለቃ፤ “ትንሽ እንጠብቀው” አለ፡፡
ተፈቀደለት፡፡
ዕውነትም ፈረሱ ከአንድ ሰዓት በኋላ ተመለሰ፡፡ አንዲት በጣም ውብ የሆነች ልጃገረድ ይዞ ነው የመጣው፡፡
የብርጌዱ አለቃ ለጐሣው መሪ፤
“ይቺን ልጀገረድ ሰጥቼሃለሁ” አለው፡፡
የወራሪዎቹ መሪ ልጃገረዲቱን ወስዶ ፍቅሩን ገልጦላት ተመለሰና፡-
“ሁለተኛው ምኞትህ ምንድን ነው?” አለው፡፡
የብርጌዱ አለቃም፤
“ፈረሴ ይምጣልኝ” አለ፡፡
ተፈቀደለትና ፈረሱ መጣለት፡፡
አሁንም በጆሮው የሆነ ነገር ሹክ አለው፤ ፈረሱ ጋለበ፡፡
“ትንሽ እንጠብቀው” አለ አለቃ፡፡
ፈረሱ ከአንድ ሰዓት በኋላ ሌላ ምን የመሰለች ቆንጆ ልጅ ይዞ መጣ፡፡
አለቃም ለጐሣው መሪ፤
“ይቺንም ልጅ መርቄ ሰጥቼሃለሁ” አለው፡፡
የወራሪዎቹ ጐሣ መሪ ልጅቱን ወሰደ፡፡ ሲዝናና ቆይቶ ተመለሰና፤
“ሦስተኛው ምኞትህስ ምንድን ነው?” አለው፡፡
“ፈረሴን እንዳገኘው ይፈቀድልኝ”
ተፈቀደለትና ፈረሱ መጣ፡፡
የብርጌዱ አለቃ ፈረሱ ላይ ወጣ፡፡ እርካቡን ኮለኮለና መጭ አለ፡፡ ማን ያስቁመው? ለዐይን ተሰወረ!
*                  *                     *
ከጉልበተኝነት ብልህነት ይበልጣል፡፡ ደግ ላደረጉልን ክፉ መመለስ መበለጥ እንጂ መሻል አይደለም፡፡ ምኞቶቻችን ተጨባጭ ይሁኑ፡፡ ተጨባጭ ቢሉም ለሀገርና ለህዝብ ፋይዳ ያላቸው ማለት ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ምድራዊ ገነት ብትሆንልን ማንም የሚጠላ የለም፡፡ ሆኖም ምኞታችን አቅማችንን ያገናዘበ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በብዙ ጉዳዮች ከልኩ በላይ መወጣጠር (Over - stretched እንዲል) መሰነጣጠቅም ሆነ መሰባበርን ማስከተሉን እንገነዘባለንና፡፡
“ሲያርስ ነካክቶ፣ ሲዘራ አፈናጥሮ፣ ጥፋተኛ እኔን አድርጎ” የሚባል ተረት አለ፡፡ በቅጥ - በቅጡ ያልሰሩት ሥራ፣ በአግባቡ ያላዘጋጁት ነገር፤ በኋላ ሰበባችንን በሌሎች ላይ እንድንላክክ ያደርገናል ማለት ነው፡፡ ሁሉንም መነካካትም አንዱን ሳናበስል እንድንቀር ያደርገናል፡፡ የጎረቤቶቻችንን አያያዝ በተመለከተ አንድም በዲፕሎማሲ መስክ፣ አንድም ሉዓላዊነትን በማስከበር ረገድ፤ አሳምረን መጓዝ ያስፈልገናል፡፡ የኃያላን መንግሥታትን ድጋፍ የማይሻ አንድም የሶስተኛው ዓለም አገር ባይኖርም፤ “በራቸውን ከፍተው እየተኙ፣ ሌባ ሌባ ይላሉ” የሚለውን አባባል ማስተዋል ወቅታዊ ነው፡፡ በሌላ ወገንም ድጋፍን ከልኩ በላይ አጋኖ ማሰብ፤ “አንገቷን ደግፈው ቢያስጨፍሯት፤ ያለች መሰላት” የተባለውን መዘዝ ያመጣል፡፡
ፈረንጆቹ There is no free lunch የሚሉት (ምንም ነገር በነፃ አይገኝም እንደማለት) የዋዛ ነገር አይደለም፡፡ የሚያስከፍለን ነገር መኖሩ ገሀድ ነው፡፡ ግን ቅናሹን ዋጋ ማስተዋል አለብን፡፡ ሁሉን በሚዛን መጫወት ከአጓጉል ቡጢ ያድናል፡፡ እኛን ከሌላ አፍሪካ አገራት ምን ይለየናል? ልዩ የሚያደርገን የኢኮኖሚ ጥሪት አለን ወይ? የፖለቲካ መረጋጋታችን አስተማማኝ ነወይ? እዚያው ሞላ እዚያው ፈላ (Volatile) የሆነው የምሥራቅ አፍሪካ አባዜ ምን ያህል አይመለከተንም? “ሠርጌን አሙቅልኝ” የሚባለው ዓይነት የፖለቲካ ዘፋኝ፤ ጠንቋይ፣ ከዶክተር አይለይም በሚልባት አፍሪካ፣ የተሟሟቀ ልማት አለኝ ማለት ይቻላልን? የአፍሪካ የመከላከያ ኃይል ምን ያህል የአፍሪካ ህብረት ታዛዥ ይሆናል? የድንበረተኛ አገሮች ፍቅርስ ወረት ነው ዘላቂ? ራሳቸውን ያላረጋጉ አገሮች እንደ አሜባ የከበቧት አገራችን፤ እንዳትዋጥ እንዳትሰለቀጥ መጠንቀቋ ዋና ጉዳይ ሆኖ ለሌሎች መጠቀሚያና ማነጣጠሪያ እንዳትሆን፣ መሬት የያዘ ዕሳቤ አላትን? ብሎ መጠየቅ ያባት  ነው ! ዙሪያችን ያሉትን ሁሉ በነቃ ዐይን፣ በዐይነ - ቁራኛ መመልከት፤ ያለ፣ የነበረ ወደፊትም የሚኖር፣ መላ ነው፡፡ አለበለዚያ፤ “የጨው ገደል ሲናድ፤ ብልጥ ያለቅሳል፣ ሞኝ ይልሳል” ይሆንብናል፡፡  

       ከአዘጋጁ፡-
በአውስትራሊያ የሚታተም “አሻራ” የተሰኘ መጽሔት በቁጥር 2 ዕትሙ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያምን በተለያዩ ጽሑፎች ዘክሯል፡፡ እኛ ግን ለዛሬ ልጃቸው ዶ/ር መቅደስ መስፍን ወልደማሪያም ከመጽሔቱ ጋር ያደረገችውን ቃለምልልስ መርጠን ከመለስተኛ የአርትኦት ሥራ በኋላ ለአንባቢያን አቅርበነዋል፡፡

         ዶ/ር መቅደስ መስፍን ወልደማሪያም ማን ናት?
               (የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ልጅ)

   ራስሽን ለአንባቢ በማስተዋወቅ ውይይታችንን ብትጀምሪልን?
ስሜ መቅደስ መስፍን ይባላል፡፡ የፕሮፌሰር መስፍን የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፡፡ የምኖረውም አሜሪካን አገር ማሳቹቴስ ግዛት ነው፡፡ ወደ አሜሪካ ከመጣሁ ከ20 ዓመት በላይ ሆኖኛል፡፡
በኢትዮጵያ እያለሁ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት በናዝሬት ትምህርት ቤት ሲሆን በከፍተኛ ትምህርት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ፋክሊቲ ምሩቅ ነኝ፡፡ አሜሪካን ሃገር ከመጣሁ በኋላም በቦስተን ዩኒቨርሲቲ በ Public Health የማስተርስ ዲግሪ አግኝቻለሁ፡፡ በዚሁ ሙያ ከኢሚግራንቱ ጋር በተገናኘና በኤችአይቪ መከላከል (HIV Prevention) ለረዥም ጊዜ ሥሰራ ቆይቻለሁ። አሁን ደግሞ በግል አንዳንድ ስራ ለመጀመር እየተዘጋጀሁ ነው፡፡
በቅርቡ በአንድ አጋጣሚ “Eforall 2015 Finalists” በሚል ከተዘረዘሩት 18 ሰዎች ውስጥ ስምሽን አይቻለሁ። ለመሆኑ ይህ Eforall የተሰኘው ድርጅት ምን እየሰራ ያለ ድርጅት ነው? ያንቺ ስም በFinalist ዝርዝር ውስጥ የሰፈረው ምን ሰርተሸ ነው?
(Entrepreneurship for all) ወይም በአጭሩ (Eforall) የተሰኘው ድርጅት አነስተኛ የቢዝነስ ሃሳቦችን የሚያበረታታ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ነው፡፡ ይህ ተቋም ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነት የቢዝነስ ሃሳብ አፍልቀው ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያደርጉትን ጥረት የሚያበረታታ ድርጅት ነው። አሰራሩም በመጀመሪያ ወደ ተግባር የሚለወጥ ቢዝነስ ሃሳብ አለን የሚሉ ሰዎችን ሃሳባቸውን ዘርዝረው በማመልከቻ መልክ ያቀርባሉ፡፡ ድርጅቱም የቀረቡለትን ማመልከቻዎች በተለያዩ መመዘኛዎች አወዳድሮ የበለጠ አሳማኝ ሆነው ያገኛቸውን ተቀብሎ ዕቅዳቸውን ወደ ተግባር የሚለውጡበትን መንገድ በተለያየ መልክ ያግዛል። እኔም እንዲሁ አንድ ያሰብኩትን ነገር ለመሞከር ጥናት እያደረኩ ባለሁበት ወቅት ነበር ድንገት ከዚህ ድርጅት የተደወለልኝ። ከዚህ በፊት ስለዚህ ድርጅት ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ደውለው “እያደረግሽ ያለውን ሙከራ እያየን ነው። እኛ እንዲህ ዓይነቱን በግል ተነሳሽነት የሚደረጉ ጥረቶችን የምናበረታታ መንግስታዊ ያልሆንን ድርጅት ነን፡፡” ብለው ራሳቸውን ካስተዋወቁኝ በኋላ፤ ለምን ሃሳብሽን በዝርዝር ገልጸሽ ማመልከቻ አታስገቢም? በርግጥ ያመለከተ ሁሉ ላንቀበል እንችላለን፡፡ ውድድሩ ጠንካራ ነው፡፡ ግን መሞከርሽ አይከፋም” ብለው ምክር ሰጡኝ። እኔም ሃሳባቸውን ተቀብዬ እንደተባልኩት አደረግኩ። በኋላም ከ80 ያህል አመልካቾች መካከል አስራ ስምንታችንን ብቻ ተቀበሉን፡፡ እንዳሉትም ውድድሩ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ማመልከቻ አስገብቶ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን በየግዜው እየጠሩ ሃሳብክን በባለሙያ ፊት እንድታስረዳ ያደርጉሃል። ለሚቀርብልህ ጥያቄ ሁሉ አሳማኝ መልስ መስጠት አለብህ፡፡ ምክንያቱም እነሱን ካላሳመንክ ሌላውንም ማሳመን አትችልም ከሚል እምነት ነው፡፡ ትክክልም ይመስለኛል። አንዴ ከተቀበሉ ግን ራስህን ችለህ እስክትቆም ድረስ በሁሉም መልክ ያግዙሃል ይረዱሃል፡፡ ብዙ ልፋት ያለው ነገር ነበር። ሆኖም ግን ከ18 ተመራጮች መካከል ሆኜ ቀጣዩን ማለትም ወደ ተግባር የሚገባበትን ጎዳና ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነኝ፡፡ Eforall 2015 Finalists ስም ዝርዝር ውስጥ ስሜ የተጠቀሰው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ከመነሻዬ በደፈናው በግል አንዳንድ ስራ ለመጀመር እየተዘጋጀሁ ነው ያልኩትም ይህንኑ ነበር፡፡
ወደ ፕ/ር መስፍን እንመለስ፤ ፕሮፌሰርን እንደ አባት እንዴት ትገልጫቸዋለሽ? አሁን ላለሽ ማንነት የሳቸው አስተዋፅኦ ምን ያህል ነው? ፕሮፌሰር በትምህርት ላይ ባላቸው ጠንካራ አቋም ይታወቃሉና በዚህ ረገድ በልጅነት ዘመን በጥሩም በመጥፎም የተከሰተ ትዝታም ካለ?
እንዳልከው በትምህርት ላይ ያለው አቋም ጠንካራ ነው፡፡ ያም ሊሆን ይችላል እኛም ብዙ አላስቸገርንም። የሚፈለገውን ውጤት ስለምናመጣ ብዙም በቁጣም ሆነ ውጤት ከማጣት ጋር በተያያዘ የማስታውሰው ነገር የለም፡፡ ከሱ ይልቅ ትዝ የሚለኝ በሃይስኩል እያለን የነበረበት የስራ ውጥረት ነው፡፡ ከስራ ወጥቶ ትምህርት ቤት መጥቶ ነው ወደ ቤት የሚወስደን፤ አንዳንዴ ግን ስለሚቆይብን ብቻችንን ትምህርት ቤት ውስጥ የመቆየት ነገር ነበር (ሳቅ)፡፡
ሌላስ እንደ አባት የሚገለጽ ባህሪ የላቸውም? ቁጡ! የሚፈሩ?
ብዙ ጊዜ ጓደኞቹ አባቴ ይቆጣል! አባቴን እፈራዋለሁ … ሲሉ ይገርመኝ ነበር፡፡ እኛ ጋ እንደዚህ አይነት ነገር የለም፡፡ ከአፉ አውጥቶ ካልተናገረ በስተቀር ምንም የምናውቀው ነገር አልነበረም። የሚነግረን ነገር ካለም ረጋ ብሎ ነው የሚነግረን። ግርፊያ፤ ዱላ፤ ቁጣ … የሚባል ነገር የለም፡፡ ጥፋት እንኳ ብታጠፋ ቁጭ አድርጎ የሚነግርህ ነገር ማጥፋትክን እንድትጠላው ነው የሚያደርግህ፡፡ እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ደግሞ ብዙም አልነበረም፡፡
ሌላው ልነግርህ የምፈልገው “ቅድሚያ ለእንስት” (Ladies First) በሚለው መርህ ላይ ያለውን እምነት ነው፡፡ እኔ ልጅም ሆኜ አሁን ጓደኞቼ አብዛኞቹ ወንዶች ናቸው፤ ብዙ ግዜ “ቅድሚያ ለእንስት” (Ladies First) በሚለው መርህ ላይ እንከራከራለን፤ ለምንድነው ቅድሚያ ለሴት የሚሰጠው ዓይነት ክርክር ማለቴ ነው፤ ይህ መርህ ግን ለአባባ አፋዊ ሳይሆን የውስጥ እምነቱ ነው፡፡ ለሴት ልጅ ክብር አለው፡፡
አንድ አጋጣሚ ልንገርህ፡- ወደ አሜሪካ ልመጣ ስል፤ ኢሚግሬሽን ለፓስፖርት ይሁን አሜሪካ ኤምባሲ ለቪዛ ይሁን አሁን ዘንግቼዋለሁ፤ ከሱ ጋር አብረን ሄደን ነበር። በቀኑ በጣም ብዙ ባለ ጉዳይ ስለነበር መቀመጫም አልተገኘም፡፡ በኋላ ቀደም ብለው መጥተው ወንበር አግኝተው ከተቀመጡት ሰዎች መካከል እሱን የሚያውቁ ሰዎች እንዲቀመጥ ተነሱለት፡፡ እሱ ደግሞ “አንቺ ተቀመጪ አለኝ”። እንዴ …? የተነሱት ላንተ ነው እኔ አልቀመጥም አልኩ፡፡ እሱ ግን “አንቺ ቆመሽ እኔ አልቀመጥም” ብሎ አስቀምጦኛል፡፡ ይህ የሚያሳየው ለሴት ልጅ ያለውን ክብር ነው፡፡
እኔና እህቴን አስቀምጦ ሲመክረን ብዙ ግዜ ሴት ልጅ ከጾታዋ ጋር በተያያዘ ሊደርስባት የሚችለውን ችግር ካስረዳን በኋላ መፍትሄው ደግሞ ትምህርት እንደሆነ አያይዞ ነበር የሚነግረን፡፡ በዚህ መልኩ ነበር የትምህርት ወሳኝነት ውስጣችን የሚያሰርፀው፡፡
ፕ/ር ብዙ የሚታወቁባቸው ጠንካራ የሰብዕና መገለጫዎችና ተያይዞም ችሎታዎች አሏቸው፡፡ ወዳንቺ የመጣው የትኛው ነው?
በልጅነቴም ብዙ ሰዎች በመልክ ትመስይዋለሽ ነው የሚሉት፡፡ ሌላ ሌላው ባብዛኛው ለሌላ ሰው የሚታይ ወይም ሌላው ሊናገረው የሚችል እንጂ ራስህ ስትናገረው ይከብዳል፡፡ ከሱ የተማርኩት የሚመስለኝ አንድ ነገር ፡- አልችለውም ብሎ ተስፋ መቁረጥ የሚባል ነገር የለብኝም። ማድረግ እችላለሁ (I can do it!) ብዬ ነው የምነሳው! የጀመርኩትን ግብ ሳላደርስ ተስፋ ቆርጦ ያለመቆም ዕልህ አለብኝ። ይህም ከሱ የመጣ ይመስለናል። እሱ በዚህ እድሜው እንኳ አንድ ነገር ከጀመረ ጫፍ ሳያደርስ ምንምና ማንም አያቆመውም፡፡
ሌላው ከሱ ወሰድኩ የምለው ጥቃትን በይሁንታ ወይም በያልፋል አይነት ትዕግስት አመለቀበልን ነው። አሁን ለምሳሌ እሱ የታሰረ ጊዜ እንደኔው ቤተሰባቸው ወይም አባታቸው የታሰሩባቸው ጓደኞቼ የሆነውን ተቀበሎ የማለፍን ነገር ሲያወሩ፣ ለኔ በፍጹም አይዋጥልኝም ነበር። የኔ ጥያቄ በመጀመሪያስ ለምን ይሆናል? ለምን ይታሰራል? ነው፤ አግባብ ያልሆነ ነገር ሲፈጸምብህ ወይም መብትህ ሲነካ ታግለህ መብትን ማስከበር እንጂ ስለ ምህረትና ስለ መሳሰሉት ነገሮች ማሰብ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ይህም እምነቴ ከሱ የተገኘ ይመስለኛል፡፡
ከፕ/ር የምታደንቂላቸው ችሎታና ባህሪዎች ጥቂቱን ልትጠቅሺልኝ ትችያለሽ…?
በመጀመሪያ የተፈጥሮ ስጦታ በመሆኑ ክሬዲት የሚሰጠው ባይሆንም የሱ ጭንቅላት የተለየና በጣም የሚደንቅ ነው፡፡ በትንሽ ጊዜ ውስጥ አንድን ነገር ከተለያየ አቅጣጫ አይቶ ላንተ የማይታይህን ነገር አይቶ የሚያቀርብበት ችሎታው ሁሌም ያስገርመኛል። አንድ አወያይ ሃሳብ ከተነሳ ያ ሃሳብ ብትንትኑ ወጥቶ ካልቀረበ አይረካም፡፡ የሰው ሃሳብ በትዕግስት ያደምጣል። እሱም ያለመሰልቸት ያስረዳል፡፡ ባጠቃላይ ሃሳብን የመመርመር ችሎታና ትዕግስቱን አደንቃለሁ፡፡ ሌላው ደግሞ ያመነበትን ነገር ፊት ለፊት ከመናገር የሚያቆመው የለም።
አሁን ባለንበት ህብረተሰብ አንድን ሀሳብ ተቃውመህ አልያም ወጣ ያለና የተለየ ሃሳብ ይዘህ ስትቀርብ እንደ ጠላት ወይም እንደ ድፍረት የመውሰድ ነገር እየተለመደ ነው፡፡ የታየህን ነገር በግልጽ ስትናገር ሃሳብህን እንደተለየ ሃሳብ ተቀብሎ በዚያው ስሜት ከመመዘን ይልቅ ከጥላቻ እንደመነጨ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ እንዲህ ዓይነት ልምድ እየገዘፈ በሄደበት ህብረተሰብ ውስጥ እንደ አባባ አይነት ሃሳቡን በግልጽ የሚናገር ሰው ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች ይገጥሙታል፡፡
በሦስት መንግስታት ውስጥ ሲያልፉ በተለያየ አጋጣሚ በትረ ስልጣኑን ከያዙት አካላት ጋር በነበራቸው አለመግባባት ቤተሰባችሁ ስጋት ውስጥ የወደቀበት የምታስታውሺው ትዝታ ካለ? በተለይ መንግስቱን ውረድ ባሉበት ወቅት ምን ተሰማሽ?
በመጀመሪያ የታሰረው እኔ ገና የ11 ወይም የ12 ዓመት ልጅ ሆኜ ይመስለኛል፡፡ የረብሻው ምክንያት በጊዜው ባይገባኝም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረበሸ ተብሎ እሱም ታስሮ ቤት ውስጥ የነበረው ግርግር ትዝ ይለኛል፡፡ ያኔ ደግሞ አዋቂ ሲያወራ ልጅ ወደ ውጭ ወይም ወደ ጓዳ የሚባልበት ዘመን ነበርና ስለታሰረበትና ስለረብሻው ምክንያት ብዙም የማስታውሰው ነገር ባይኖርም እንዲሁ ብቻ መታሰሩ ቤተሰቡን እንዳሳሰበ ትዝ ይለኛል፡፡
ሌላው እንዳልከው መንግሥቱ ኃይለማሪያምን ውረድ ባለበት ወቅት የተፈጠረው ነው፡፡ ያን ሁኔታ አሁንም ድረስ ሳስበው ይገርመኛል፡፡ በጊዜው እኔ እዚሁ አሜሪካን ሀገር ነበርኩ፡፡ ይህ በሆነበት ዕለት ወይም ማግስት ይመስለኛል አንድ ለሱም ለኔም ወዳጅ የሆነ ሰው ደውሎ “መስፍንን ሰሞኑን አግኝተሸዋል? “ሲል ጠየቀኝ፡፡ አይ ሰሞኑን አላገኘሁትም ብዬ ከመለስኩ በኋላ ነገሩ ስለከነከነኝ ምነው? ምን የተፈጠረ ነገር አለ? ብዬ ጠየቅኩት፡፡
“አይ አሁንም፣ በቃ መንግሥቱን ውረድ ብሎት አሁን ያለበት አይታወቅም፤ (He is in hiding)” አለኝ። በመጀመሪያ በጣም ደነገጥኩ፤ ተደብቋል የሚለው ነገር ከአባባ ተፈጥሮና ባህሪ ጋር በፍጹም የሚስማማ አልሆነልኝም፡፡ ልቀበለው አልፈለኩም፡፡
በመሆኑም ወዲያው ደውዬ ለማረጋገጥ ፈለኩ። ላገኘው አልቻልኩም፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ያው ወዳጃችን መልሶ ደውሎ “ተደብቋል ያልኩሽ ቀልዴን ነው፡፡ መንግሥቱን ግን ውረድ ብሎት መንግሥቱ ሳይበሰጫጭ አልቀረም” ከጉዳዩ ክብደት አንፃር ቀልዱ ባይገባኝም፣ ተደበቀ የሚለው ነገር እውነት አለመሆኑን መቀበል አልከበደኝም፡፡
በኋላም ደውዬ ሳገኘው ተረጋጋሁ፡፡ እንደተፈራው አልሆነም፤ መንግስቱም አገር ጥሎ ጠፋ፤ ሁሉም በዚሁ አበቃ፡፡ እንደሰማሁ ግን በጣም በጣም ነበር የደነገጥኩት።
የእሳቸው ልጅ በመሆንሽ ምን ይሰማሻል?
ይሄ ምን ያጠያይቃል ብለህ ነው? (ሳቅ) የሱ ልጅ በመሆኔ በጣም! በጣም ነው የምኮራው፡፡ በነገራችን ላይ እናቴም ያልተዘመረላት ጀግና እንደሚባሉት አይነት ነች። ከነዚህ ሰዎች መፈጠሬ ለኔ ክብሬም ኩራቴም ነው፡፡
እኔ ብቻ ሳልሆን ሁላችንም ኢትዮጵያዊያኖች እዚህ የደረስነው ብዙ ዋጋ ተከፍሎ ነው፡፡ ለሃገራቸው ድንቅ ስራ ሰርተው፤ ግዙፍ መስዋዕትነት ከፍለው ለዛሬው ማንነታችን ያበቁንን አባት እናቶቻችንን ውለታ ተሸክመን ነው የምንኖረው፡፡ እኔም ከሱ በመፈጠሬ ደስታዬ ወሰን የለውም፡፡

  የሰንበት ት/ቤቶቹ እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው እን
                         ‹‹መልካም ዜጋ የምታወጣው ተቋም በሙስና መጎዳቷ ለሀገርም ጉዳት ነው”፤ ወንጀሉ ላይ መንግሥት መዋቅሩን                         ጠብቆ ይገባል፤ በሃይማኖቱ መሸፈን አይችሉም››        ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም


        ከመልካም አስተዳደር ዕጦት እና ከተጠያቂነት ሥርዐት መጥፋት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ ሰፍኗል በተባለው ምዝበራ እና ሙስና  መንግሥት መዋቅሩን ጠብቆ ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወስድ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ከትላንት በስቲያ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራሮች ጋር በተካሔደው ውይይት፣ መንግሥት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በሰላም እና በልማት ጉዳዮች ላይ አብሮ እንደሚሠራ የጠቀሱት የሚኒስቴሩ ከፍተኛ ሓላፊዎች፣ ‹‹ የሕዝብ ሀብት ለህዝብ ጥቅም መዋል አለበት፤ በሕዝብ ገንዘብ እንዲቀለድ አንፈልግም፤ መንግሥት ሰላምንና የሕግን የበላይነት ከማረጋገጥ አኳያ ደረጃውን ጠብቆና የሙስና ወንጀል መፈጸሙን አጣርቶ ርምጃ ይወስዳል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ሙዳየ ምጽዋቱን ማን ነው የሚጠቀምበት፤ ሕዝብ ይጥላል፤ ጥቂት ሰዎች መኪና እና ቤት ይሠሩበታል፤›› በማለት የአለመግባባት መንሥኤዎችን የዘረዘሩት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሙሉጌታ ውለታው፣ የሚዘርፉት ሃይማኖት ሳይኖራቸው በሃይማኖት ስም የሚነግዱ ግለሰቦች እና አካላት እንደኾኑ ገልጸዋል፡፡ በሚፈጽሟቸው ወንጀል ነክ ጉዳዮችም ‹‹መንግሥት ለምን ጣልቃ ይገባል አይባልም፤ ከሀገረ ስብከቱ ጋር ኾኖ ይከታተላል፤ ወንጀለኛውን ይይዛል፤ ይቀጣል፤ ያጸዳል፤›› ብለዋል፡፡
የግልጽነት እና የተጠያቂነት አሠራር ዘመኑ የሚጠይቀው እና መንግሥትም በአቋም ያስቀመጠው መኾኑን ያወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች ሙስናና ብልሹ አሠራር እንዲወገድ፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና ሃይማኖት እንዲጠበቅ የጀመሩትን እንቅስቃሴ አድንቀዋል፡፡ ‹‹እንቅስቃሴአችኹን ከሁከት በራቀ፣ ስልታዊ በኾነና በሰላማዊ መንገድ ቀጥሉ፤ መንግሥትም ድጋፍ ያደርግላችኋል፤›› ሲሉም አበረታተዋቸዋል፡፡
የሰንበት ት/ቤት አባላት ሰላም ፈላጊዎች እንደኾኑ የገለጹት የአንድነቱ አመራሮች በበኩላቸው፣ ለቤተ ክርስቲያን ሰላም መደፍረስ ዋነኛ ምንጩ የመልካም አስተዳደር ዕጦት እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ እንደ አመራሮቹ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ እና ቅዱስ ፓትርያርኩ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለማስወገድና ተቋማዊ ለውጥን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን በየጊዜው ቢያሳልፉም ትግበራው አስተዳደራዊ መዋቅሩን ከላይ እስከ ታች በኔትወርኪንግ በተቆጣጠሩ ሙሰኞች ስለሚታገት ተፈጻሚ ለመኾን አልቻለም፡፡
ሙሰኞቹ÷ በሙዳየ ምጽዋት፣ በስእለትና በስጦታ ምእመኑ የሚሰጠውን ገንዘብ ለራሳቸው ዓላማና ጥቅም እያዋሉ፤ የአድባራቱን መሬትና ሕንፃ ከዋጋ በታች እያከራዩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ጥቅሞችና መብቶች ከገቢያቸው በላይ ሕገ ወጥ ሀብት ያካብታሉ፤ በሦስትና በአራት ሺሕ ብር ደመወዝ ኤሮትራከር ይገዛሉ፤ ሕንፃ ይሠራሉ፡፡
ይኹንና የተጠያቂነትና የግልጽነት አሠራር ባለመኖሩ ሲነቃባቸውና ተቃውሞ ሲበረታባቸው የበለጠ ወደሚዘርፉበት ቦታ በዕድገት እንደሚዘዋወሩ ጠቅሰው፣ ለዚኽም በጎጠኝነትና በጥቅም ትስስር ተሞልቷል ያሉት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ፅ/ቤት ተጠያቂ ነው ብለዋል፡፡ “ሀገረ ስብከቱ ሌባን አሳልፎ አይሰጥም፤ በሹመት እና በዝውውር ጉቦ እየተከፈለ አብሮ ይበላል፤” በማለት የወቀሱት አመራሮቹ፣ “የሕዝብ ንብረት እየባከነ ስለኾነ መንግሥት ጣልቃ ይግባልን፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሀብታቸው ተሰፍሮ ተቆጥሮ ይታወቃል፤ አሠራሩ እዚኽም ይምጣልን፤” ሲሉ አመልክተዋል፡፡
ሙሰኞችን በመቃወማቸውና እውነቱን በመናገራቸው አሸባሪዎች ተብለው ለእስር እንደሚዳረጉ  አመራሮቹ ጠቁመው፣  የጸጥታ አካላት ርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ኹኔታቸውን በሚገባ እንዲያጣሩና ፍትሐዊ አሠራር እንዲከተሉ ጠይቀዋል። ከአስተምህሮ ውጭ የኾኑ ግለሰቦችን የማጋለጥ ድርሻ የእነርሱ መኾኑን ገልጸው፣ በዚኽም በአክራሪነት መፈረጃቸው አግባብነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡
“አክራሪነትና ጽንፈኝነት በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ መኖሩ የሚያከራክር አይደለም፤” ያሉት ሚኒስትሩ ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም፣ ኾኖም ጥያቄው በሃይማኖት አጥባቂነት እስከተነሣ ድረስ ከአክራሪነት ስለሚያርቅና ከሙስና ስለሚጠብቅ የሚደገፍ መሆኑን ጠቁመው የፍረጃው አካሔድ ስሕተት መኾኑን አብራርተዋል። እንደ ሚኒስትሩ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ የማይፈቅደውን የአክራሪነት አስተሳሰብና ተግባር በሃይማኖት ሽፋን የሚያራምዱ ግለሰቦች ለተቋሙ ደኅንነት ሲባል መለየት አለባቸው፡፡
ሕዝብ ከተግባርም እንደሚማር ዶ/ር ሺፈራው ገልጸው፣ አትስረቅ እያሉ በሌላቸው ገቢ የሚልዮን ብር መኪኖችን የሚነዱ አካላት፣ ለሀገር መልካም ዜጋ የምታወጣውን ተቋም በማማሰን በሕዝብ ላይ ተጽዕኖ እየፈጠሩ ናቸው ብለዋል፡፡ ይህም ለሀገር የሚጎዳ በመኾኑ ድንጋይ በመወርወር ሳይኾን በምእምኑ ሰላማዊ እንቅስቃሴ በቀጣይነት መጋለጥ እንደሚገባቸው መክረዋል፤ የሰንበት ት/ቤት አባላትም ከቤተ ክርስቲያኒቷ አልፎ ለሀገርና ለዓለም የሚበቁ ሊቃውንቷን በማስተባበር ለመልካም አስተዳደር መስፈን የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፤ መንግሥትም ‹‹መዋቅሩን ጠብቆ በወንጀሉ ላይ ይገባል፤ በሕግም ይጠይቃቸዋል፤ በሃይማኖቱ መሸፈን አይችሉ፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
በሚኒስቴሩ የስብሰባ አዳራሽ በተደረገው በዚኹ የግማሽ ቀን ምክክር ማጠናቀቂያ ላይ፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የዋና ክፍል ሓላፊዎች የተገኙ ሲኾን ሚኒስትሩም “የወጣቶቹን ጥያቄ እንደ ቀላል አትዩት፤ በአስቸኳይ ፍቱ” ሲሏቸው ተደምጠዋል፡፡
ቀደም ሲል ሚኒስቴሩ፣ ከሀገረ ስብከቱ የአድባራት አለቆች፣ ካህናት እና ሰባክያነ ወንጌል ጋር ተመሳሳይ ምክክር ያደረገ ሲሆን፤ ይኸውም በቅርቡ በሃይማኖት ተቋማት በሰላም አብሮ መኖር እና ጤናማ ግንኙነቶች ማስፈንን በተመለከተ በጋራ እንደሚካሔድ ለሚጠበቀው ውይይት ቅድመ ዝግጅት እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በአገር አቀፍ ደረጃ የንባብ ባህል እንዲዳብር “ከመንግሥት እና ከባለድርሻ አካላት ምን ይጠበቃል?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት የሚያስችል አውደ ጥናት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ሥነ - ፅሁፍና ፎክሎር ትምህርት ክፍል ጋር በመተባበር በትላንትናው ዕለት በብሄራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መፃህፍት ኤጀንሲ አዳራሽ አውደ ጥናት አካሂዷል፡፡ በአውደ ጥናቱ ላይ አቶ ደረጀ ገብሬ (ረ/ፕ) “የንባብ ባህልን ለማዳበር የባለድርሻ አካላት ሚና” በሚል ርዕስ እንዲሁም ዶ/ር ሙሉ ሰው አስራቴ፤ “የልሳነ ብዙ የቋንቋ ትምህርትና ፖሊሲ የንባብ ባህልን ለማዳበር የሚኖረው ተግዳሮት እና ዕድል” በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ሃሳቦችን ማቅረባቸው ታውቋል፡፡

  በአሌክስ አብርሐም በተፃፈው “ዶ/ር አሸብር” የተሰኘው የወግ ስብስቦች መፅሃፍ ላይ በነገው ዕለት ከ8 ሰዓት ጀምሮ በወ-መዘክር አዳራሽ ውይይት ይካሄዳል፡፡ ለውይይት መነሻ የሚሆን ሃሳብ የሚያቀርበው ደራሲና ጋዜጠኛ አለማየሁ ገላጋይ ነው ተብሏል፡፡
የመፅሃፍ ውይይቱ እናት ማስታወቂያ፣ የጀርመን የባህል ማዕከልና ወመዘክር በጋራ የሚያዘጋጁት እንደሆነ ታውቋል፡፡

በሰለሞን ተሾመ ባዬ የተዘጋጀው “ፎክሎር ምንነቱና የጥናቱ የትኩረት አቅጣጫ” የተሰኘ መፅሃፍ የፊታችን ሐሙስ ከቀኑ 10 ሰዓት በብሄራዊ ሙዚየም እንደሚመረቅ ተገለፀ፡፡ በምረቃ ሥነ - ሥርዓቱ ላይ የተለያዩ ምሁራን የውይይት ሃሳብ የሚያቀርቡ ሲሆን ምሁራኑ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው፣ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራና አቶ እንዳለ ጌታ ከበደ እንደሆኑ ታውቋል፡፡ የመፅሀፉ ይዘት፡- የፎክሎር ፅንሰሀሳብን በሳይንሳዊ መንገድ ማብራራት፣ በአገራችን የሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን ቃላዊ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ባህሎችን መሰረት ያደረገ ትንተና መስጠት እና ሌሎችን ያካትታል ተብሏል፡፡ በ335 ገፆች የተዘጋጀው መፅሀፉ፤ በ120 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

ነፃነት ኪዳነማርያም የተፃፈው “የአሥመራው ታዳኝ” የተሰኘ ታሪካዊ ልብወለድ መፅሃፍ በነገው ዕለት ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ መስቀል አደባባይ በሚገኘው ኢዮሐ ሲኒማ ይመረቃል፡፡ የመፅሀፉ ዋጋ 60 ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም “ዋሻው” የተሰኘ ለአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የአኒሜሽን ፊቸር ፊልም ሰርቶ ለተመልካች ማቅረቡ ይታወሳል፡፡  

   በእስራኤል በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቁ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ናቸው
    ኢትዮጵያዊው ምሁር ዶ/ር አንበሴ ተፈራ በእስራኤል የመጀመሪያው ከፍተኛ የዩኒቨርሲቲ መምህርና የፋካልቲ አባል በመሆን በቴል አቪቭ ዩኒቨርሲቲ ስራ መጀመራቸውን ጂዊሽ ኒውስ ድረገጽ ሰሞኑን ዘገበ፡፡
ዶ/ር አንበሴ በቴል አቪቭ ዩኒቨርሲቲ የእብራይስጥ ባህል ጥናት የትምህርት ክፍል የሴሜቲክ ቋንቋዎች ከፍተኛ መምህር ሆነው እያስተማሩ እንደሚገኙ የጠቆመው ዘገባው፣ ምሁሩ ከ15 አመታት በፊት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሲያገኙም በእስራኤል የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ እንደነበሩ አስታውሷል፡፡
በ1962 የተወለዱት ዶ/ር አንበሴ፤ የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሊንጉስቲክስ በተቀበሉበት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአምስት አመታት ያህል በመምህርነት ማገልገላቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ እየሩሳሌም ውስጥ ከሚገኘው ሂብሩ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን መቀበላቸውንና በዩኒቨርሲቲው አማርኛ ቋንቋን ሲያስተምሩ እንደቆዩም አክሎ ገልጿል፡፡  
ዶ/ር አንበሴ፤ ሶስት መጽሃፍትንና ከ20 በላይ ጥናታዊ ጽሁፎችን ለህትመት ያበቁ ሲሆን፣ ከማስተማርና ከጥናትና ምርምር በተጨማሪም ለ13 አመታት ያህል ለእስራኤላውያን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች አማርኛ ቋንቋን በማስተማርና በትምህርት ሚኒስቴር የአማርኛ ጥናቶች ብሄራዊ ሱፐርቫይዘር ሆነው በማገልገል እንደሚታወቁ ዘገባው ጠቁሟል፡፡

Saturday, 01 August 2015 14:06

በሚቀጥለው ቅዳሜ …

ወደ ኢትዮጵያ ጠቅልዬ ልመለስ ነው ስል በአሜሪካ ያሉ ሚዲያዎች መጥተው ነበር ቺካጐ ትሪቡን “አዲስ አበባ ዎን፤ ቺካጐ ሎስት” ብሎ ፅፏል በኢትዮጵያ በደቡብ በሸዋ፣ በጐንደር ገጠሮች 30 ት/ቤቶች አሠርቷል
በአያት አካባቢ ሪል ኢስቴት እየሠራ ነው “አይዞን” የተባለ 12 ዘፈን የያዘ አዲስ አልበሙን በቅርቡ ያወጣል
ጋንግስተሮች በ30 ሞተርሳይክሎች እያባረሩ ሊገሉት ሲሉ አምልጧልከአርቲስት ዘለቀ ገሠሠ ጋር ያደረግነውን ግሩም ቃለ ምልልስ በሚቀጥለው ሳምንት ያንብቡት