Administrator

Administrator

የደቡብ ኮርያ የጦር ሃይል አባላት የሆኑ ወታደሮች በኮርያ ዘመቻ ወቅት የተሳተፉና በጽናት በመታገል ታላቅ ውለታ የሰሩ ኢትዮጵያውያን ዘማቾችን ለመርዳት የሚውል የገንዘብ ድጋፍ እያሰባሰቡ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡
የደቡብ ኮርያ ጦር በኦፊሻል የፌስቡክ ገጹ ላይ ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ኮፖጆላ የተባለው ድረገጽ ትናንት እንደዘገበው፣ የአገሪቱ 27ኛ ክፍለ ጦር አባላት የሆኑ ወታደሮች በአበል መልክ ከሚሰጣቸው ገንዘብ የተወሰነውን በማሰባሰብ በአለማቀፉ የእርዳታ ድርጅት በኩል ለኢትዮጵያውያን የኮርያ ዘማቾች ለመላክ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡
እ.ኤ.አ በ1951 በተጀመረው የሁለቱ ኮርያዎች ጦርነት፣ ከ6 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ዘማቾች ደቡብ ኮርያን በመደገፍ ለአምስት አመታት ያህል በጽናት መታገላቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ 122 ያህሉ ሲሞቱ 536 የሚሆኑት ደግሞ የመቁስል አደጋ እንደደረሰባቸው ገልጧል፡፡
ደቡብ ኮርያውያኑ ወታደሮች የሚያሰባስቡት ገንዘብ፣ በህይወት ለሚገኙ 350 ያህል ኢትዮጵያውያን ዘማቾች እንደሚደርስ የጠቆመው ዘገባው፣ ወታደሮቹ የኢትዮጵያውያን ዘማቾችን ፎቶግራፎች ይዘው በኩራት ስሜት ውለታቸውን እየዘከሩ የሚያሳየው ፎቶግራፍ፣ በጦሩ የፌስቡክ ድረገጽ ላይ መለቀቁንም አክሎ ገልጧል።

ለኦሮሚያ 2 ቢ ብር ተመድቧል - ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ
 
ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ፤ በኦሮሚያ ስድስት ወረዳዎች የምግብ ዋስትናቸው ያልተረጋገጠ ከ1 ሚ. በላይ ሰዎችን ለመደገፍ የ2 ቢ. ብር
ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡ ባለፈው ሳምንት በአዳማ ከተማ አዩ ኢንተርናሽናል ሆቴል ይፋ ባደረገው በዚህ ፕሮጀክት ላይ፤ የክልሉ ኃላፊዎች፣ የወረዳ ተወካዮች፣ የወርልድ ቪዥን ካንትሪ ዳይሬክተሮችና ፕሮጀክት ማናጀሮች ተገኝተዋል፡፡ አምስት አመት የሚዘልቀው ይሄው ፕሮጀክት የሚተገበርበት ገንዘብ የተገኘው ዩስኤይድ ለዚሁ ተግባር ከመደበው 175 ሚሊዮን ዶላር ላይ እንደሆነ በዕለቱ ተነግሯል። ወርልድ ቪዥን ላለፉት 40 ዓመታት በኦሮሚያ ክልል 24 ወረዳዎችና አምስት ዞኖች የምግብ ዋስትና ድጋፍና ሌሎች የተቀናጁ የልማት ስራዎችን በመስራት ከ6 ሚ. በላይ ህፃናትንና በጣም ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሲያገለግል መቆየቱም በዕለቱ ተገልጿል፡፡ ወርልድ ቪቪን ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ባጠናቀቀው የአምስት አመት የልማትና የምግብ ድጋፍ ፕሮግራም ከ1.5 ሚ. በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን የገለፁት የኦሮሚያ ክልል የደህንነት፣ የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት ደገፋ አሁንም ወርልድ ቪዥን በ6 ወረዳዎች የምግብ የጤናና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ ለመስራትና ወገኖችን ለመደገፍ ያቀረበውን ትልቅ ሀብት በአግባቡ መጠቀም አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡የወርልድ ቪዥን የልማትና የምግብ ድጋፍ ፕሮግራም (DFAP) ፕሮጀክት ዳይሬክተር አቶ ጉቱቴሶ እንደገለፁት፤ የዘንድሮው ፕሮጀክት በዋናነት የሚያተኩረው የምግብ ዋስትናቸው ባልተረጋገጠ የኦሮሚያ የአማራና የደቡብ ክልል አካቢዎች ሲሆን ይህን ፕሮጀክት ለማሳካት የ3.8 ቢ. ብር በጀት ማግኘታቸውን ጠቅሰው፣ የአማራው ከሁለት ሳምንት በፊት ይፋ መሆኑንና የደቡቡ በቅርቡ በሀዋሳ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡ የምግብ ዋስትናቸው ላልተረጋገጠ የሦስቱ ክልል አካባቢ ማህበረሰቦች ከምግብ ድጋፍ በተጨማሪ የተቀናጁ በርካታ ስራዎች ይከናወናሉ ያሉት አቶ ጉቱ ከነዚህም መካከል በግብርና፣በጤና፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በአኗኗር ዘይቤ በገጠር ስራ ፈጠራና በመሰል ስራዎች ላይ በማተኮር ድርቁን ተከትሎ የመጣውን የምግብ እጥረት እንዲቋቋሙ ይደረጋል ተብሏል፡፡

Saturday, 11 February 2017 14:08

የሙዚቃ ጥግ

 - ለውጥ ሁሌም ይከሰታል፡፡ የጃዝ ሙዚቃ አንዱ ድንቅ ነገር ያ ነው፡፡
   ማይናርድ ፈርጉሰን
- ጃዝ ወደ አሜሪካ የመጣው የዛሬ 300 ዓመት ከባርነት ጋር ነው፡፡
  ፖል ዋይትማን
- የጃዝ መንፈስ የግልፅነት መንፈስ ነው፡፡
  ሔርቢ ሃንኮክ
- ጃዝ ግሩም የመማሪያ መሳሪያ ይመስለኛል፡፡
  ጆን ኦቶ
- በቀን ሦስት ሰዓት ገደማ ጃዝ አዳምጣለሁ፡፡
  ሉዊስ አርምስትሮንግን እወደዋለሁ፡፡
ፊሊፕ ሌቪን
- ጃዝ በተፈጥሮው የብዙ የተለያዩ ዓይነት
ሙዚቃዎች ጥርቅም ነው፡፡
  ዴቪድ ሳንቦርን
- ስለ ጃዝ ማውራት ሁልጊዜም አስደሳች ነው።
  ክሊንት ኢስትውድ
- የጃዝ ሙዚቃ በጣም በርካታ አስደናቂ ዝነኞችን ፈጥሯል፡፡
  ዊንቶን ማርሳሊስ
- ጃዝ ከሌሎች የሙዚቃ ዘውጎች ተውሷልም፤ ለሌሎች የሙዚቃ ዘውጎች አውሷልም፡፡
  ሔርቢ ሃንኮክ
- ጃዝ ልክ እንደ ወይን ጠጅ ነው፡፡ በአዲስነቱ ለባለሙያዎች ብቻ ነው የሚሆነው፤ ሲቆይ ግን ሁሉም ይፈልገዋል፡፡
  ስቲቪ ላሲ
- የጃዝ ሙዚቃ የስሜቶች ቋንቋ ነው፡፡
  ቻርልስ ሚንጉስ
- ጃዝ የማሽን ዘመን የሐገረሰብ ሙዚቃ ነው፡፡
  ፖል ዋይትማን
- ጃዝ የዕለት ተዕለት ህይወትን አቧራ ያጥባል።
  አርት ብሌኪ
- ጃዝ የአሜሪካ ክላሲካል ሙዚቃ ነው፡፡
  ቢሊ ቴይለር

  ሃሊ ቤሪ - የኦስካር አሸናፊ

       ሃሊ ቤሪ በ21 ዓመት ዕድሜዋ የፊልም ተዋናይ ለመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኒውዮርክ ስትጓዝ ገንዘብ አልቆባት ክፉኛ ተችግራ ነበር፡፡ ፒፕል መፅሔት እንደዘገበው፤እናቷ ተጨማሪ ገንዘብ ለልጇ መላክ ተገቢ አይደለም ብላ ወሰነች፡፡ ራሷን እንዳትችል ማሳነፍ ነው በሚል እሳቤ፡፡
    በዚህ ወቅት ነው ሃሊ ቤሪ፣ከቤት አልባ ምስኪኖች ጋር በመጠለያ ውስጥ የኖረችው፡፡ ከሪደር ዳይጀስት ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ ቤሪ ስትናገር፡- “በዚያ ሁኔታ ውስጥ ማለፌ፣ራሴን እንዴት መምራት እንዳለብኝና በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ እንዴት መኖር እንደምችል አስተምሮኛል - በመጠለያ ውስጥ ወይም ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ገቢም ቢሆን፡፡ ምንጊዜም የራሴን መውጫ መፍጠር እንደምችል የማውቅ ሰው ሆኛለሁ” ብላለች፡፡ የሆሊውዷ ዝነኛ
ተዋናይት ሀሊ ቤሪ፣ የኦስካር አሸናፊ ናት፡፡

---------------------------------

                           ጄምስ ካሜሮን - የፊልም ዳይሬክተር

      ጄምስ ካሜሮን “The Terminator” የተሰኘውን የፊልም ስክሪፕት ሲፅፍ፣በቂ ገቢ አልነበረውም፡፡ ከእጅ ወደ አፍ የሚባል ነበር፡፡ እንደ IGN ዘገባ፤ለተወሰኑ ጊዚያትም በመኪና ውስጥ ለማደር (መኖር) ተገዷል -
ለቤት ኪራይ የሚከፍለው ገንዘብ ስላልነበረው፡፡
    በወቅቱ ካሜሮንን በእጅጉ ያሳስበው የነበረው ጉዳይ ግን ገንዘብ አልነበረም፡፡ “The Terminator” የተሰኘውን ስክሪፕቱን ዲያሬክት ማድረግ ብቻ ነበር የሚፈልገው - በዘርፉ በቂ ልምድ ባይኖረውም፡፡ የፊልም ጽሁፉን ለፕሮዱዩሰሮች ሲያቀርብ፣ብዙዎቹ ስክሪፕቱን ቢወዱለትም፣እሱ በዳይሬክተርነት መስራቱን ግን አይፈልጉም ነበር፡፡
   ካሜሮን ግን በሀሳቡ ፀና፡፡ በመጨረሻም ከፕሮዱዩሰር ጋሌ አኔ ሁርድ ጋር አጋርነት ፈጠረ፡፡ ፕሮዱዩሰሩ የፊልም
ፅሁፉን መብት ከገዛው በኋላ በዳይሬክተርነት መደበው፡ ፡ ካሜሮን ህልሙን እውን አደረገ፡፡ “The Terminator”
በመላው ዓለም ታይቶ፣77 ሚ. ዶላር ገቢ አስገኝቷል፡፡

----------------------------------

                                ጄነፈር ሎፔዝ - ድምፃዊትና ተዋናይት

      ጄኔፈር ሎፔዝ የ18 ዓመት ኮረዳ ሳለች ዳንሰኛ የመሆን ከፍተኛ ጉጉትና ፍላጎት ነበራት፡፡ እንደ ማንኛውም ለልጁ የወደፊት እጣፈንታ የሚጨነቅ እናት፣ሎፔዝ ኮሌጅ ብትገባላት ትወድ ነበር- እናቷ፡፡ ሆኖም ሎፔዝ አሻፈረኝ አለች፡፡ በዚህ ሰበብ በእናትና በልጅ መካከል አለመግባባት ተፈጠረና ከቤት ወጣች፡፡ ከቤት ከወጣች ጀምሮም በዳንስ
ስቱዲዮዋ ሶፋ ላይ ማደር ጀመረች ሲል ዘግቧል - ደብሊው መጋዚን፡፡
    “ቤት አልባ ነበርኩ፤ነገር ግን ይሄንን ነው የምሰራው ብዬ ለእናቴ ነግሬያታለሁ” ብላለች፤ ሎፔዝ ለደብሊው መጋዚን፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ በአውሮፓ የዳንስ ስራ አገኘች፡፡ ከዚያ በኋላ ሁሉም ነገር ተለወጠ፡፡ የ46 ዓመቷ ዝነኛ አቀንቃኝ፣ ተዋናይት፣ፕሮዱዩሰርና ዲዛይነር ጄኔፈር ሎፔዝ ባለፈው ዓመት 28.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን ፎርብስ ዘግቧል። ያኔ እንኳንስ እናቷ ራሷ ሎፔዝም፣ የዚህን ያህል ተወዳጅ፣ሚሊዬነር፣ስኬታማ ---እሆናለሁ ብላ መች አሰበች!?

----------------------------------

                              ቻርሊ ቻፕሊንና ወንድሙ

     ቻርሊ ቻፕሊንና ወንድሙ ከኑሮ ጋር ፊት ለፊት የተጋፈጡት ገና በለጋ የልጅነት ዕድሜያቸው ነበር፡፡ የአባታቸውን ድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ተከትሎ፣ እናታቸው የአዕምሮ ህክምና ሆስፒታል ውስጥ ገባች፡፡ ይኼን ጊዜ ታዳጊው ቻፕሊንና ወንድሙ ራሳቸውን ማስተዳደር ነበረባቸው - Charliechapline.com እንደዘገበው፡፡
    ሁለቱም ወላጆቻቸው በትርኢት ሙያ ውስጥ ስለነበሩ፣ ቻፕሊንና ወንድሙ የእነሱን ዱካ ለመከተል ወሰኑ፡፡ መንገዱ አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ የማታ ማታ ግን ቻርሊ ቻፕሊን ስኬት ተቀዳጀ፡፡ ዛ ሬም ድ ረስ ከ ድምፅ
አ ልባው የ ፊልም ዘመን ታላላቅ ተዋናዮች አንዱ በመሆን ይጠቀሳል - ኮሜዲያኑ ቻፕሊን፡፡

 የደራሲ፣ አርታኢና ሀያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ ልብ ወለድ ‹‹በፍቅር ስም›› የፊታችን ሰኞ ከቀኑ 11፡ 30 ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ይመረቃል፡፡ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ኢ/ር ጌታሁን ሄራሞ፣ ቴዎድሮስ አጥላውና አሸናፊ መለሰ በመፅሐፉ ላይ ዳሠሳ የሚያቀርቡ ሲሆን በሀይሉ ገ/እግዚአብሔር - ወግ፤ ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም - ግጥም እንደሚያቀርቡ የፕሮግራሙ አዘጋጅ ‹‹ተረት ፊልሞች›› አስታውቋል። መድረኩን የሚመራው ጋዜጠኛ ደረጀ ሀይሌ ነው
ተብሏል፡፡ ‹‹በዕለቱም በመፅሃፉ ሁለንተና ላይ ውይይት ይካሄዳል፡፡ እርስዎ መፅሃፉን ካላነበቡ እንብበው፣ ካነበቡ ተዘጋጅተው፣ እንዲያም ሲል እኔ ያነበብኩት የደራሲውን ቀደምት ልቦለዶች ነው ካሉ የመወያያ መድረኩ እርስዎንም ያሳትፋልና እንዳይቀሩብን›› ብሏል-ደራሲው በጥሪ ካርዱ ላይ ባሰፈረው ማስታወሻ፡፡

 የፊዚክስ መምህሩ ወጣት ወስናቸው አጥናፌ (ቦንጋ) አዲስ የከፍኛ የሙዚቃ አልበም ያወጣ ሲሆን ነገ በሚያስተምርበት የድል በር ት/ቤት አዳራሽ ይመረቃል ተብሏል፡፡ ‹‹ሀማሂኔ›› የሚል መጠሪያ የተሠጠው አልበሙ፤ ሙሉ በሙሉ ቪሲዲ ሲሆን 585 ሺ ብር እንደወጣበት ድምፃዊው ተናግሯል፡፡ አልበሙ የከፋ ማህበረሰብን ቋንቋ፣ ባህል፣ አለባበስ፣ የአኗኗር ዘይቤና አጠቃላይ መልክአ ምድርን የሚያሳይ መሆኑን መምህር ወስናቸው ጠቁሟል፡፡ ለቪሲዲው ተጠናቆ መውጣት የከፋ ዞን አስተዳደር ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉን የጠቆመው ድምፃዊው፤ የከፍኛ መፅሃፍ
ፀሐፊውና መምህር አባቱ አጥናፌ ጎበና፤ የከፍኛ ግጥሞቹን በማጠናከር ከፍተኛ እገዛ እንዳደረጉላት ተናግሯል፡፡
ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በፊዚክስ የመጀመሪያ
   ድግሪውን ያገኘ ሲሆን ከአንድ ዓመት በኋላ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪውን እንደሚያገኝ
የጠቆመው ድምፃዊው፤ ከዚህ ቀደም ‹‹ዋቤ ጉቴ›› የተሰኘ ነጠላ ዜማ መልቀቁን አስታውሷል፡፡ በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ ዶ/ር አሸብር ወ/ማሪያምን ጨምሮ የኪነ ጥበብ ቤተሰቦች እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር “የሂስ ጥበብ ሂደት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጥናታዊ ፅሁፍ ዛሬ
ከረፋዱ 3፡00 ጀምሮ በወመዘክር አዳራሽ ያቀርባል፡፡
   በጥናቱ ላይ በርካታ የስነ ፅሁፍ ባለሙያዎች፣ ደራሲያንና አንባብያን ተገኝተው ውይይት እንደሚደረግበት ተጠቁሟል፡፡ በውይይቱ ፍላጎት ያለው ሁሉ እንዲገኝና ሀሳብ እንዲያዋጣ ደራሲያን ማህበር ጥሪ አቅርቧል፡፡

  በአማረች ጎሹ የተዘጋጀው “ገዥነት” የተሰኘ አዲስ መፅሀፍ ገበያ ላይ ዋለ፡፡ መፅሀፉ በዋናነት ፍልስፍናዊ፣
ስነ- ልቦናዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጥናል ተብሏል፡፡ በ110 ገፆች የተቀነበበው መፅሐፉ፤ በ40 ብር
ለገበያ መቅረቡም ታውቋል፡፡

አብርሃም ግዛው ኢንተርቴይመንትና ስራዎች ድርጅት ከካሌብ ሆቴል ጋር በመተባበር ‹‹ድሮና ዘንድሮ›› የተሰኘ ዓለም አቀፍ የፍቅረኞች ቀንን ታሳቢ ያደረገ የመዝናኛ ፕሮግራም ማክሰኞ ይካሄዳል፡፡
    በፕሮግራሙ ላይ ታዋቂ ሰዎች፣ ረጅም ጊዜ በትዳር ያሳለፉ ጥንዶች የፍቅር ህይወታቸውን የሚያወጉበትና ልምድ የሚያካፍሉበት መድረክ መዘጋጀቱ የተገለፀ ሲሆን “የፍቅረኞች ቀን” በአገራችን መከበሩ ጥሩና መጥፎ ጎኑ ተነስቶ ውይይት ይደረጋል ተብሏል፡፡ በተጨማሪ አዝናኝ ገጠመኞች፣ ሙዚቃ፣ ትዊስትና ሳልሳ ዳንስ፣ ስታንዳፕ ኮሜዲና ሌሎችም የመዝናኛ ፕሮግራሞች ለታዳሚው እንደሚቀርቡ ለማወቅ ተችሏል።

ከአሜሪካ ታላላቅ ኩባንያዎች ግማሽ ያህሉ በስደተኞች የተቋቋሙ ናቸው

     ጎግል፣ አፕል እና ማይክሮሶፍትን ጨምሮ 127 የአሜሪካ ታላላቅ ኩባንያዎች፣ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ያወጡት የስደተኞች የጉዞ ገደብ የስደተኞችን ህጎችና ህገ-መንግስቱን የሚጥስ ነው በሚል የተቃወሙት ሲሆን በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በጋራ ክስ መመስረታቸው ተዘግቧል፡፡
በአብዛኛው በቴክኖሎጂ መስክ ላይ የተሰማሩት እነዚህ ኩባንያዎች፣ በጋራ በመሰረቱት ክስ፤ ስደተኞች በአሜሪካ ኢኮኖሚ ላይ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ በመጠቆም፣ ትራምፕ ስደተኞች ለተወሰነ ጊዜ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ መከልከላቸው በአገሪቱ ኩባንያዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ሊነሳ ይገባል በሚል በክሳቸው ማመልከታቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ መከልከላቸው የአገሪቱ ኩባንያዎች የውጭ አገራት ምርጥ ባለሙያዎችን እንዳይቀጥሩና እንዳያሰሩ እክል ይፈጥራል ያሉት ኩባንያዎቹ፤ ተመልሰው የመግባታቸው ጉዳይ አስተማማኝ ካለመሆኑ ጋር በተያያዘ ሰራተኞቻቸውን ወደ ሌሎች አገራት ለስብሰባና ለልምድ ልውውጥ ለመላክ እንደሚያስቸግራቸውም ገልጸዋል፡፡
ከአሜሪካ 500 ታላላቅ ኩባንያዎች መካከል 200 ያህሉ በሌሎች አገራት ስደተኞችና ከስደተኞች በተወለዱ ልጆች የተቋቋሙ መሆናቸውን ታዋቂው ፎርቹን መጽሄት በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ ማስታወቁን ያስታወሱት ኩባንያዎቹ፤” ይህም በንግድና ቢዝነሱ መስክ የጎላ ሚና የሚጫወቱትን ስደተኞች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ መከልከል ኢኮኖሚውን ማዳከምና አዳዲስ ኩባንያዎች እንዳይፈጠሩ እንቅፋት መፍጠር እንደሆነ ያመለክታል” ማለታቸውንም ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡