Administrator

Administrator

 ድርቁን ተከትሎ አስከፊ ረሀብ ሊከሰት እንደሚችል ተመድ አስጠንቅቋል
               መንግሥት የእርዳታ ጥሪ ቢያቀርብም እስካሁን ምላሽ አላገኘም
               እስከ 15 ሺህ ብር ይሸጡ የነበሩ ከብቶች፣ 500 ብር ድረስ እየተሸጡ ነው
                              
    በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል የድርቅ አደጋ በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ሰዎችን ያፈናቀለ ሲሆን ከሩብ ሚሊዮን በላይ ህፃናት ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ውጪ ማድረጉንም የተባበሩት መንግስታት የእርዳታና የሰብአዊ ድጋፍ ድርጅት (UNOCHA) ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በድርቅ ከተጎዱ አካባቢዎች አንዱ በሆነው የኦሮሚያ ክልል፣ ቦረና ዞን ያሉ አርሶ አደሮች በህይወት የተረፉ ከብቶቻቸውን በርካሽ ዋጋ እየሸጡ መሆኑን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
ድርቅ ባጠቃቸው የቦረና አካባቢዎች በጉዳዩ ላይ ጥናት በማድረግ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ በደህናው ጊዜ እስከ 15 ሺህ ብር ይሸጡ የነበሩ በሬዎች፤ በአሁን ወቅት ከ500 እስከ 1 ሺህ ብር ድረስ እየተሸጡ ሲሆን ከ500 እስከ 1 ሺህ 500 ብር ይሸጡ የነበሩ በጎችና ፍየሎች ደግሞ በ80 እና በ90 ብር እየተሸጡ ነው ተብሏል፡፡
ከብቶቹ በአብዛኛው በአካላዊ ቁመናቸው የተጎዱ በመሆኑ፣ ፈላጊ ስለሌላቸው አርብቶ አደሮቹ በርካሽ ዋጋ ለመሸጥ መገደዳቸውን ባለሙያዎቹ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡፡፡
የከብቶች ሞትም እንደቀጠለ መሆኑን የጠቆሙት አጥኚዎች በተለይ የመጠጥ ውሃ ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉን ገልፀው፤ መንግስት በቦቴ ውሃ እያቀረበ ቢሆንም በበቂ መጠን አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡
ወቅታዊ ሪፖርቱን ሰሞኑን ይፋ ያደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ፤ በተለይ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል የሚሊዮኖችን ህይወት አደጋ ላይ ለጣለው ድርቅ መንግስትና የእርዳታ ለጋሽ ተቋማት ውሃና ምግብ በማቅረብ እየተረባረቡ ቢሆንም ከአደጋው አስከፊነት አንፃር በቂ አይደለም ብሏል፡፡
በድርቁ ምክንያት 228 ሺህ ህፃናት ትምህርት ማቋረጣቸውን ይፋ ያደረገው ሪፖርቱ፤ ከእነዚህ ውስጥ 183 ሺህ 090 የሶማሌ ክልል ህፃናት ሲሆኑ 44 ሺህ 571 የሚሆኑት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡ በሁለቱ ክልሎች ማለትም በኦሮሚያ በድርቁ ምክንያት 141 ት/ቤቶች፣ በሶማሌ ክልል 437 ት/ቤቶች በድምሩ 578 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ምግብና ውሃ ፍለጋ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አባወራዎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውን የጠቆመው የተመድ የእርዳታና ሰብአዊ ድጋፍ ድርጅት ሪፖርቱ፤ ከተፈናቀሉት ውስጥ 163 ሺህ ያህሉ ለትምህርት የደረሱ ህፃናት መሆናቸውን አመልክቷል፡፡ እነዚህን ተፈናቃይ ህፃናት ለ75 ቀናት ሊመመገብ 5.9 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግም ተገልጿል፡፡
በእርዳታ አሰጣት ደንብ ለአንድ ሰው በቀን ውስጥ 5 ሊትር ውሃ መቅረብ ያለበት ቢሆንም በአሁን ወቅት ለአንድ ሰው በቀን እየቀረበ ያለው በአማካይ 2.1 ሊትር ውሃ መሆኑን የተመድ ሪፖርት ጠቁሞ፤ የውሃ ክፍፍሉም ፍትሃዊ አለመሆኑንና ከወረዳ ወረዳ እንደሚለያይ አስታውቋል፡፡
በአጠቃላይ ለ5.6 ሚሊዮን የተረጂዎች 1 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ እርዳታ እንደሚያስፈልግና ይህ እርዳታ በአፋጣኝ ካልተገኘ ሁኔታው ወደ አስከፊ ረሃብ ሊቀየር እንደሚችል አሳስቧል፡፡
ተመድ መንግስት ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመሆን የእርዳታ ርብርብ እያደረጉ ነው ቢልም መንግስት በበኩሉ፤ ለድርቁ አደጋ የእርዳታ ጥሪ ቢያቀርብም እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱን አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አፍሪካን በተመለከተ ባወጣው ሪፖርቱ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በድርቅ በተጎዱ፣ ከሠሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት፣ በአሁኑ ወቅት ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የእርዳታ ርብርብ እንደሚፈልጉ አስታውቆ፤ አለማቀፉ ማህበረሠብ እጁን እንዲዘረጋ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

 በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2016 ብቻ በአዲስ አበባ ከተማ ከ30 ሚ. ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያላቸው 20 አዳዲስ እጅግ ባለጸጋ ሚሊየነሮች መፈጠራቸውን “ናይት ፍራንክ” የተባለ አለማቀፍ የሃብት ጥናትና አማካሪ ተቋም ሰሞኑን ባወጣው የ2017 አለማቀፍ የሃብት ስርጭት አመታዊ ሪፖርት አስታውቋል፡፡ ተቀማጭነቱ በእንግሊዝ የሆነው ተቋሙ፤ በ89 የአለማችን አገራት ውስጥ በሚገኙ 125 ከተሞች ላይ ያደረገውን ጥናት መሰረት በማድረግ፣ ለ11ኛ ጊዜ ባወጣው ሪፖርቱ፤ በአዲስ አበባ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያላቸው አዳዲስ ሚሊየነሮች ቁጥር ከአንድ አመት በፊት ከነበረው በ10 በመቶ በማደግ፣ በ2016 አመት 20 መድረሱን የጠቆመ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር በመጪዎቹ ዘጠኝ አመታት በእጥፍ በማደግ 40 ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት አስታውቋል፡፡  
በአዲስ አበባ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016፣ ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያላቸው ሰዎች ቁጥር 800 መድረሱን የገለጸው ሪፖርቱ፣ ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያላቸው ሚሊየነሮች ቁጥር ደግሞ 40 ደርሷል ብሏል፡፡
ሪፖርቱ በአፍሪካ አህጉር በመጪዎቹ ዘጠኝ አመታት ከፍተኛ የሚሊየነሮች ቁጥር እድገት ይመዘገብባቸዋል ብሎ የጠቀሳቸው አገራት፡- ኢትዮጵያ፣ ሞሪሽየስ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ እና ሩዋንዳ ሲሆኑ፣ በመላው አለም ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያላቸው ሰዎች ቁጥር በዘጠኝ አመታት ጊዜ ውስጥ በ43 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጧል፡፡
ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016 በመላው አለም ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያላቸው 6 ሺህ 340 አዳዲስ ሚሊየነሮች መፈጠራቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ይህን ያህል የሃብት መጠን ያላቸው የአለማችን ሚሊየነሮች አጠቃላይ ቁጥር 193 ሺህ 490 መድረሱንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሚሊየነሮች ቁጥር ከአለማችን አገራት ከፍተኛውን ጭማሪ ታስመዘግባለች ተብላ የምትጠበቀው ቬትናም ስትሆን፣ በአገሪቱ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያላቸው ዜጎች ቁጥር በዘጠኝ አመታት ጊዜ ውስጥ በ170 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚገመትም ተነግሯል፡፡

Monday, 27 February 2017 08:14

የቢዝነስ ጥግ

- የእውነተኛ ሥራ ፈጣሪ የህይወት ዓላማ ዓለምን መለወጥ ነው፡፡
  ቢል ድራይቶን
- የንግድ ሥራ ፈጣሪ ከሆንክ፣ ከተለመደው ወጣ ብለህ ማሰብ አለብህ፡፡
  ዋይኔ ሮጀርስ
- ልጄ አሁን “ሥራ ፈጣሪ” ነው፡፡ ሥራ ከሌለህ እንደዚያ ነው የሚሉህ፡፡
  ቴድ ተርነር
- ሦስት ጊዜ የንግድ ሥራ ፈጥሬአለሁ፡፡ ሦስት ኩባንያዎችንም መስርቼአለሁ፡፡
  ማርክ አንድሬሰን
- ሁሉም ሰው ሥራ ፈጣሪ ሊሆን ይችላል፤ ሀብታም ሥራ ፈጣሪዎች የሚሆኑት ግን በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
  ሮበርት ኪዩሳኪ
- ዛሬ በንግድ ሥራ ፈጣሪነት ዘርፍ ብዙ አማራጮች አሉ፡፡
  ኢክላስ ዜንስትሮም
- ከራሴ ጋር እንዲህ ስል ተማከርኩ፡- “የንግድ ሥራ ፈጠራን እያስተማርኩ ነው፤ ስለዚህ ራሴ የንግድ ስራ ፈጣሪ መሆን አለብኝ”
  ዳን ሼችትማን
- ዶናልድ ትራምፕ የንግድ ሥራ ፈጣሪ ነው፡፡
  ስቲቭ ባኖን
- የንግድ ሥራ ፈጣሪ መሆን ከባድ ነው፡፡ በጣም በጣም ከባድ፡፡
  ዴቪድ ኤስ.ሮዝ
- የንግድ ሥራ ፈጠራ፤ በአስቸጋሪ ኢኮኖሚ ውስጥ ህይወታችንን የምንቆጣጠርበት መንገድ ነው፡፡
  ሎርል ግሬይነር
- ሥራ ፈጣሪዎች በሳምንት 40 ሰዓት መስራትን ለማስቀረት፣ በሳምንት 80 ሰዓት ለመስራት ፈቃደኞች ናቸው፡፡
  ሎሪ ግሬይነር
- የንግድ ሥራ ፈጠራ፤ ለችግሮች አትራፊ መፍትሄዎች የመፈለግ ጥበብ ነው፡፡
  ብሪያን ትሬሲ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት “ኮንዲዩሲቭ ኢንቫይሮመንት ፎር ኢንሃንስድ ኤክስፖርት ፐርፎርማንስ) በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው 21ኛ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ከትናንት በስቲያ ተከፈተ፡፡
አገር ውስጥ ያሉ የንግድ ሰዎችን ከውጭ አገር አቻዎቻቸው ጋር የንግድ ትስስር እንዲፈጥሩ፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማስተዋወቅና የአባላቱን አቅም ለማሳደግ የሚሰራው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት ባዘጋጀው 21ኛው የንግድ ትርዒት፤ 100 የውጭ አገራትና 80 የአገር ውስጥ በአጠቃላይ 180 ድርጅቶች የሚሳተፉ ሲሆን ከውጭ ኩባንያዎች 50 ያህሉ ከኢጣሊያ የመጡ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ከየካቲት 16 እስከ 22 ቀን 2009  በሚቆየው የንግድ ትርዒት፤ ከ27 የውጭ አገራት፣ ኢጣሊያ፣ ሕንድ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ሱዳን፣ ዱባይ … እንዲሁም ከአገር ውስጥ የተውጣጡ… 180 ኩባንያዎች በአገልግሎት፣ በንግድ፣ በማኑፋክቸሪንግ በትርዒቱ የሚሳተፉ ሲሆን የኢጣሊያ ኩባንያዎች ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር ተቀናጅቶ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው የም/ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሚዲያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን ማሞ ገልጿል፡፡
የንግድ ትርዒቱን በክብር እንግድነት መርቀው የከፈቱት የንግድ ሚ/ር ዴኤታው አቶ አሰድ ዚያድ ሲሆኑ የንግድ ም/ቤቱ የቦርድ አባላት፣ አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ አባላት፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ንግድ ም/ቤቱ በቅርቡ ዓለም አቀፍ የእርሻና ምግብ ትርዒት በሚያዝያ፣ የማኑፋክቸሪንግና ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን በሰኔ እንደሚያካሂድ ታውቋል፡፡ እንዲሁም የንግድ ም/ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መኮንን ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ ኤግዚቢሽን ማዕከል ለመገንባት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ‹‹ፋይራ ባርሴሎና›› ጋር መስማማቱን አስታውቀዋል፡፡   

• እንደኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች በሆስፒታል ውስጥ ከሚሞቱ እናቶች በሚወሰደው መረጃ መሰረት እስከ 20% የሚሆነው የእናቶች ሞት በደም መርጋት በሽታ ነው።
 ዶ/ር ሙህዲን አብዶ
የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት
ደም በሰውነት ውስጥ ትልቅ ተግባር ያለው ተፈጥሮ ነው። ደም በሰውነት ውስጥ በሕይወት ዘመን ሁሉ ካለምንም ችግር መመላለስ መቻል አለበት። ነገር ግን ጉዳት በሚደርስበት ገዜ ከሰውነት ውጭ እንይፈስ እና ተጎጂው ከጉዳት እንዳይወድቅ እራሱን ማዳን መቻል አለበት። ይህም የደም ስሩ በተቆረጠበት በኩል ካለአግባብ እንዳይፈስ በአካባቢው በመርጋት እና የተከፈተውን የደም ስር በመዝጋት ነው። ስለዚህም የደም መርጋት ጤናማ እና ሕይወት አድን ተፈጥሮአዊ ሂደት ነው። ነገር ግን ባልተፈለገ ሁኔታ ማለትም ከልብ ሕመም፣ ስትሮክ እና ከመድሀኒት ጋር በተያያዘ በሚደርስ ችግር የደም መርጋት ከተከሰተ ጠቃሚነቱ ቀርቶ ጎጂ ይሆናል።
በሰውነት ውስጥ የደም መርጋት ተከሰተ ሊባል የሚችለው የሚከተሉት ሁኔታዎች ሲስተዋሉ ነው።
• የደም ዝውውሩ በትክክለኛው መንገድ መሆን ሲገባው ነገር ግን ሲገታ፣
• በደም ውስጥ የደም መርጋትን አጋጣሚ የሚጨምሩ ነገሮች በሚጨምሩበት ጊዜ፣
• በደም ስር ውስጥ ያሉ ተፈጥሮአዊ አካላት በሚጎዱበት ወይንም አደጋ በሚደርስባቸው ጊዜ፣ ነው።
ከዚህ ውጭ ግን በተለያዩ ባእድ አካላት ሰውነት ሲመታ ወይንም ሲቆረጥ የሚኖረውን ደም መፍሰስ ለማስቆም የሚረዳው ደም መርጋት እንደችግር ሳይሆን እንደነፍስ አድን ይቆጠራል። ምክንያቱም በዚያ በተቆረጠው የደም ስር ጫፍ ላይ ተከስቶ የደም ፍሰቱን ስለሚገታ ነው። ነገር ግን ደም የሚያቀጥን መድሀኒት የሚወስዱ ሰዎች ከሌሎች በተለየ በአደጋ ጊዜ የደም ስራቸው በራሱ የሚያደርገውን የደም መርጋት ሂደት ሊያስተጉዋጉልበት ይችላል። የደም መርጋትን ሊያመጡ የሚችሉ ከሚባሉት ውስጥ የደም ግፊት፣ ኮሎስትሮል፣የልብ ሕመም፣የስኩዋር ሕመም፣ማጨስ እና በቤተሰብ ውስጥ የደም መርጋት ሕመም የነበረ ከሆነ ተጠቃሾች ናቸው። ከልብ ሕመም፣ስትሮክ እና ከደም ስሮች መዘጋጋት ጋር የሚያያዘውን የደም መርጋትን ለመከላከል የደም ግፊትን የስኩዋር ሕመምን እና ኮለስትሮልን መቆጣጠር ተገቢ ነው።
አንዲት ሴት በእርግዝና ላይ እና በወሊድ ወቅት ሊያጋጥሙዋት ከሚችሉ የጤና እክሎች አንዱ የደም መርጋት ነው። በዚህ ወቅት የደም መርጋት በሽታ እንዲከሰት የሚያደርጉ የተለያዩ አጋጣሚዎች በመኖራቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። በእርግዝና ጊዜ የሚከሰተው የደም መርጋት ጽንሱን አደጋ ላይ የመጣል አዝማሚያው ከፍተኛ ነው። እንደመረጃዎቹ ጥቆማ ለዚህ ደረጃ የሚያደርስበት ምክንያትም የደም መርጋቱ በእንግዴ ልጅ ውስጥ ስለሚፈጠር ወደልጁ የሚሄደውን የደም ፍሰት ሊዘጋ ስለሚችል ነው።
• በእርግዝና ጊዜ ሰውነት በራሱ ደም እንዳይፈስ ለመከላከል ሲል የሚያዘጋጃቸው የደም መርጋት ተፈጥሮአዊ ሂደቶች ይጨምራሉ።
• እርግዝናው ጊዜውን እየጨመረ በሚመጣበት ጊዜ ጽንሱ በማደጉ ምክንያት በሚፈጠረው ጭነት ምክንያት ደም መልስ የሚባለው አካል በትክክል ስራውን እንዳይሰራ የሚሆንበት አጋጣሚ ይኖራል።
• በእርግዝና ወቅት በምጥ ሰአት ወይንም በውርጃ ጊዜ በተለይም ደግሞ ከወሊድ በሁዋላ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የደም መርጋት ሂደቱን የሚያባብሱ ነገሮች አሉ። በተለይም...
o ከምጥ ጋር በተያያዘ የደም ስሮች መጎዳት፣
o በኦፕራሲዮን መውለድ፣
o የሰውነት ውፍረት፣
o ተገቢውን አካላዊ እንቅስቃሴ ካለማድረግ ...ወዘተ ጋር በተያያዘ ወላድዋ የደም መርጋት ሕመም ሊገጥማት ይችላል።
• የደም መርጋት ምልክት ደም መርጋቱ እንደተከሰተበት የስውነት ክፍል ወይንም አርተሪ እና ቬይን በተባሉ የደም ክፍሎች ይለያያል። ስለዚህም የልብ ሕመም ወይንም መጠነኛ ስትሮክ ሊያጋጥም ይችላል። የደም መርጋትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ምክንያቶች ተብለው ከሚጠቀ ሱት መካከል ውፍረት፣እንቅስቃሴ አለማድረግ፣መተኛት የመሳሰሉት ይገኙበታል። አንዲት ሴት በተለይም በኢትዮጵያ ስትወልድ ከሚደረግላት እንክብካቤ መካከል ምግብ ከለመደችው መጠንና አይነት በላይ መስጠት እና ለእረፍት መተኛት እንዳለባት ታዋቂ ነው።ይህ ግን በባለሙያዎች ዘንድ ተቀባይነት የለውም።
• .....እንደጥሩ ልማዳዊ ድርጊት ተደርገው ከሚወሰዱ መካከል ሴቶች ሲወልዱ የሚደረግላቸው እንክብካቤ ይገኝበታል። ነገር ግን የእንክብንቤው መንገዱ ልብ ሊባል የሚገባው ነው። የወለደች ሴት መታረስ አለባት ከሚል አስተሳሰብ ብዙ እንድትተኛ ቅባት ያላቸውን ምግቦች ከመጠን በላይ እንድትመገብ ይደረጋል። በተለይም መኝታው እንደእረፍት የሚቆጠርበት መንገድ ትክክል አለመሆኑን መረዳት ይገባል። እረፍት ማለት መኝታ አይደለም። ማረፍ ማለት ሰውነት እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ ለተለያዩ በሽታዎች እንዲጋለጥ ማድረግ ተብሎ ሊተረጎም አይገባም። ማረፍ ማለት ቀደም ሲል ከነበረው አስጨናቂ ነገር አእምሮን ገለል አድርጎ ጥሩ ጥሩ ነገር እያሰቡ አዲስ ስላገኙት ነገር በተለይም ስለወለዱት ልጅ ምቹ ነገርን እያሰቡ ቀድሞ ከነበረው ውጥረት የበዛበት የኑሮ እንቅስቃሴ እራስን ገለል አድርጎ በመጠኑ እየተንቀሳቀሱ ለተወሰነ ጊዜ እራስን ማደስ ተብሎ ቢታሰብ ይበጃል። ከወለዱ በሁዋላ መተኛት የሚለው እጅግ ጎጂ የሆነና የተሳሳተ አስተሳሰብ መሆኑን ሁሉም ቢረዳው መልካም ነው። ስለዚህ አንዲት ሴት ከወለደች በሁዋላ ለተወሰነ ጊዜ እረፍት አድርጋ በየአንድ እና ሁለት ሰአቱ ልዩነት ለአስራ አምስት እና ሰላሳ ደቂቃ ያህል ከአልጋ እየተነሳች ብዙ ሳትርቅ ከክፍል ክፍል ዞር ዞር ማለት እና አቅሙዋም በጨመረ ጊዜ በደንብ በቤቷ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ማለት ይጠበቅባታል። ወደምግቡ ሁኔታ ስንመለስም... በወለዱ ጊዜ የሚመገቡት ምግቦች ስብ እና ጣፋጭ የበዛባቸው እንዲሆኑ አይመከርም። ይልቁንም በፈሳሽ መልክ የተዘጋጁ ምግቦችን እንዲሁም መጠጦችን እየወሰዱ በወለዱ ጊዜ የሚሰሩ የአካል እንቅስቃሴዎችን በየደረጃው በባለሙያ ምክር መስራት ሊከሰት የሚችለውን የደም መርጋት ሊያስቀር ይችላል። በተለይም ኦፕራሲዮን ሆነው የወለዱ ሴቶች ከቁስሉ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ምክንያቶችን ለራሳቸው እየፈጠሩ ፍርሀት ሰለሚያድርባቸው እራሳቸውን ከእንቅስቃሴ ሊገድቡ ስለሚችሉ የደም መርጋት ክስተቱን ሊያባብሱ ይችላሉ። ስለዚህ ማንኛዋም ወላድ የመጀመሪያዎቹን ስምንት ሰአታት ካረፈች በሁዋላ በየደረጃው የሰውነት ክፍሉዋን ማንቀሳቀስ ይጠበቅባታል.....
• እርግዝናና መውለድ የደም መርጋትን ከሚያባብሱ ነገሮች መካከል ናቸው። የደም መርጋት ችግር በሕይወት ዘመኑዋ አንድ ጊዜ ማለትም በእርግዝና ወይም ወሊድ ወቅት ብቻ የተከሰተባት ሴት እና በሌሎች የጤና ሁኔታዎች ወይንም በዘር ምክንያት ችግሩ የተሰከተባት ሴት በእኩል አይን አይታዩም። ስለዚህ ከእርግዝናው ወይንም ከመውለድ ጋር በተያያዘ ብቻ የደም መርጋት ሕመም የገጠማት ሴት ለዚህ ሕመም የዳረጉዋት ምክንያቶች ከተስተካከሉና ሕክምናውን በተገቢው መንገድ ወስዳ ለሚቀጥለው እርግዝና ብቁ መሆንዋን ሐኪም ካረጋገጠላት የሚቀጥለውን ልጅ ብዙም ሳትቆይ ማርገዝ ትችላለች። የደም መርጋት ችግር በተለያዩ ምክንያቶች እና በዘር የወረሱ ወይንም በተደ ጋጋሚ የሚከሰትባት እናት ከሆነች ግን በቀላሉ ወደ እርግዝናው እንድትገባ አይፈቀድም። ተከታታይ የሆነ የህክምና ክትትል አድርጋ የደም መርጋቱ ችግር በከፍተኛ ሁኔታ መወገዱ ሲረጋገጥ እና ሐኪሞች ሲወስኑላት ግን ልጅ መውለድ ትችላለች። (ዶ/ር ሙሁዲን አብዶ - የጽንስና ማህጸን ሕክምና)
• በአጠቃላይ ግን በደም መርጋቱ ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት የታማሚው የጤንነት ሁኔታ ፣የደም መርጋቱ የተከሰተበት ቦታ እና በምን ያህል ፍጥነት ሕክምና እንዳገኘ የመሳሰሉት ሁኔታዎች ደረጃውን ይለያዩታል። ብዙ ሰዎች በተለይም በእግራቸው ላይ የደም መርጋት ሕመም እንደደረሰባቸው ላያውቁ ይችላሉ። ምናልባትም ምልክቱ በግልጽ የማይታይ ሆኖ ወይንም ችላ ተብሎ ሊሆን ይችላል። በዚህም የተነሳ ወደ 25% የሚሆኑ ታማሚዎች የደም ቡዋንቡዋቸው በደም መርጋት ስለሚዘጋ በድንገት ይሞታሉ።
• የደረት ሕመም፣ የሆድ እቃ የላይኛው ክፍል ሕመም፣ ክንድ፣አንገት ወይንም መንጋጋ አካባቢ ሕመምና ስቃይ፣የምግብ አለመፈጨት፣ የትንፋሽ ማጠር፣ላብ ማላብ፣የማቅለሽለሽ ወይንም የማስመለስ እና የመሳሰሉት ሕመሞች ሲከሰቱ በፍጥነት ወደህክምና መሔድ ይገባል። ነገር ግን እነዚህ ምልክቶች ታዩ ማለት ሁልጊዜ የደም መርጋት ምልክቶች ናቸው ማለት አይደለም።

    የአዘርባጃኑ ፕሬዚዳንት ኢሃም አሊየቭ የትዳር አጋራቸውን መህሪባንን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አድርገው መሾማቸውን ባለፈው ማክሰኞ በይፋ ማስታወቃቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
   ፕሬዚዳንቱ የ52 አመት ዕድሜ ያላቸውን ባለቤታቸውን በአገሪቱ የስልጣን እርከን ሁለተኛ ደረጃን በሚይዘውና ባለፈው መስከረም ወር ላይ በጸደቀው አዲሱ የተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ቦታ ላይ ማስቀመጣቸው ብዙዎችን እያነጋገረ እንደሚገን የገለጸው ዘገባው፣ ዘገባው ገልጧል፡፡ ባለፈው መስከረም ወር
ላይ በተከናወነው ህዝበ ውሳኔ በአገሪቱ የህገ መንግስት አንቀጾች ላይ ማሻሻያ መደረጉን ያስታወሰው ዘገባው፣
የፕሬዚዳንቱን የስልጣን ዘመን ከአመስት አመታት ወደ ሰባት አመታት ማሳደጉ፣ ከ14 አመታት በፊት የአባታቸውን ቦታ ተክተው አገሪቱን መምራት የጀመሩት ፕሬዚዳንት አሊየቭ ከስልጣን ላለመውረድ የያዙት አቋም መገለጫ ነው በሚል መተቸቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
   በምክትል ፕሬዚዳንትነት የተሾሙት መህሪባን በህክምና ሙያ ከዩኒቨርሲቲ መመረቃቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ከዚህ ቀደም በህግ አውጭነት መስራታቸውንና የአንድ በጎ አድራጎት ድርጅት ሃላፊ ሆነው ማገልገላቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
    ገና የ19 አመት ወጣት ሳሉ ከፕሬዚዳንት ኢሃም አሊየቭ ጋር ትዳር የመሰረቱት መህሪባን፣ በረጅም አመታት የትዳር ቆይታቸው ሁለት ሶቶች እና አንድ ወንድ ልጅ ማፍራታቸውን ዘገባው አክሎ ገለጧል፡፡

     ደቡብ ኮርያ በሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነት ከአለማችን አገራት የመጀመሪያውን ደረጃ መያዟን ኦፕንሲግናል የተባለው የቴሌኮም መረጃ ተቋም ሰሞኑን ያወጣውን የጥናት ውጤት ጠቅሶ ሲቢሲ ኒውስ ዘግቧል። ተቋሙ በ87 የአለማችን የተለያዩ አገራት የ2016 የፈረንጆች አመት የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነት ዙሪያ ባደረገው ጥናት፣ ከአለም አንደኛ ደረጃን በያዘቺው ደቡብ ኮርያ የሞባይል ኢንተርኔት ፍጥነት በሰከንድ 37.54 ሜጋ ባይት እንደሚደርስ አስታውቋል፡፡
በሰከንድ 34.77 ሜጋ ባይት ፍጥነት ያለባት ኖርዌይ በሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነት ሁለተኛ ደረጃን መያዟን የጠቆመው ዘገባው፣ ሃንጋሪ በ31.04 ሜጋ ባይት በሰከንድ ፍጥነት ሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን እንዲሁም ሲንጋፖር እና አውስትራሊያ በቅደም ተከተላቸው አራተኛና አምስተኛ ደረጃን መያዛቸውን ገልጧል፡፡
በጥናቱ ከተካተቱት የአፍሪካ አገራት በሞባይል ኢንተርኔት ፍጥነት አንደኛ ደረጃን የያዘቺው ደቡብ አፍሪካ ስትሆን፣ በሰከንድ 9.93 ሜጋ ባይት ፍጥነት ያላት አገሪቱ ከአለማችን አገራት ደግሞ የ48ኛ ደረጃን ይዛለች ተብሏል፡፡

     የናዚው መሪ አዶልፍ ሂትለር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገደሉ ትዕዛዝ አስተላልፈውበታል የተባለው ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ በአሜሪካ ሜሪላንድ ውስጥ በተካሄደ ጨረታ 195 ሺህ ፓውንድ መሸጡ ተዘግቧል፡፡
የሂትለር የጥፋት ሞባይል ተብሎ የሚጠራውና ከ70 አመታት በላይ ዕድሜ እንዳለው የተነገረለት ይሄው ቀይ ቀለም ያለው ስልክ፣ በስተጀርባው የሂትለር ስም፣ የንስር ምስል እና የስዋስቲካ ምክልት እንዳለበት የዘገበው ቢቢሲ፣ ስሙ ያልተገለጸ ተጫራች በስልክ ባቀረበው የመወዳደሪያ ዋጋ አሸንፎ እንደገዛው ገልጧል፡፡
ብርጋዴር ጄኔራል ራልፍ ራይነር የተባሉ እንግሊዛዊ የጦር መሪ እ.ኤ.አ በ1945 በርሊን ውስጥ የሚገኘውን የሂትለር ምሽግ በጎበኙበት ወቅት፣ ይሄው ታሪካዊ ስልክ ከሩስያ የጦር መኮንኖች በስጦታ መልክ እንደተበረከተላቸውም ዘገባው አስታውሷል፡፡

በምርጫ ቢሸነፉም ስልጣኔን አልለቅም ብለው ለሳምንታት ካንገራገሩ በኋላ በተደረገባቸው ጫና አገራቸውን ጥለው የተሰደዱት የቀድሞው የጋምቢያ ፕሬዚዳንት ያያ ጃሜህ ከአገሪቱ ካዘና ያለአግባብ የዘረፉት ገንዘብ 1 ቢሊዮን ዶላር ያህል መድረሱን አዲሱ የአገሪቱ መንግስት አስታወቀ፡፡
አዲሱ የአዳማ ባሮው መንግስት ሚኒስትሮች ያወጡትም መረጃ ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፣ ተሰናባቹ ያያ ጃሜህ ከተለያዩ የአገሪቱ የመንግስት ተቋማት በየሰበብ አስባቡ ያለ አግባብ ለግል ጥቅማቸው ያዋሉት ገንዘብ በድምሩ 1 ቢሊዮን ዶላር ያህል መድረሱ በምርመራ ተረጋግጧል፡፡
ጃሜህ ከማህበራዊ ዋስትና፣ ከስፖርት እና ከቴሌኮም ድርጅቶች ብቻ 50 ሚሊዮን ዶላር ዘርፈዋል፤ ለግል አውሮፕላናቸው ግዢ ያለ አግባብ ከመንግስት ካዘና 4.5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል፣ እጅግ በርካታ ገንዘብም ያለ አግባብ ለግል ጥቅማቸው እንዲውል ተደርጓል ብሏል ዘገባው፡፡
ከአገሪቱ የማህበራዊ ዋስትና ካዘና ወጪ የተደረገ 40 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ የት እንደገባ አለመታወቁን የጠቆመው ዘገባው፣ ገንዘቡ በጃሜህ ኪስ ውስጥ ሳይገባ አይቀርም ተብሎ መጠርጠሩንና ቅንጦት ወዳጁ ጃሜህ በየሰበብ አስባቡ ደጋፊዎቻቸውን ለማስደሰት ባደረጓቸው የእራት ግብዣዎችና የቅንጦት ተግባራት 67 ሺህ ዶላር ያህል ወጪ መደረጉም ተነግሯል፡፡
ይሄም ሆኖ ግን ተመድ ለተጠቀሱት አራት አገራት የሚያስፈልገውን 4.4 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ ያደረገው ጥረት ይህ ነው የሚባል ውጤት አለማግኘቱንና እስካሁን ድረስ ማግኘት የቻለው 90 ሚሊዮን ዶላር ያህል ብቻ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ጸሃፊው፣ አለማቀፉ ማህበረስብ በአፋጣኝ የድጋፍ እጁን እንዲዘረጋ ጠይቀዋል፡፡

   4.4 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፣ የተገኘው 90 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው

      አለማቀፉ ማህበረሰብ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ርብርብ ካላደረገ በስተቀር፣ በተለያዩ አራት የአለማችን አገራት ውስጥ የሚገኙ 20 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ለርሃብ አደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፈው ረቡዕ አስጠንቅቋል፡፡
በደቡብ ሱዳን ሁለት ግዛቶች 100 ሺህ ሰዎች የርሃብ ተጠቂ መሆናቸውን ከቀናት በፊት በይፋ ያስታወቀው የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ፣ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲሁም በሶማሊያ፣ የመንና ናይጀሪያ በመጪዎቹ ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ የከፋ ርሃብ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡ ከከፋ ድርቅና ከእርስ በእርስ ግጭቶች ጋር ተያይዞ በተጠቀሱት አገራት ይከሰታል ተብሎ የሚጠበቀውን የርሃብ አደጋ ለመከላከል አለማቀፉ ማህበረሰብ በመጪዎቹ ሶስት ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ ርብርብ በማደረግ 4.4 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ ማሰባሰብ እንዳለበትም ዋና ጸሃፊው ተናግረዋል፡፡
7.3 ሚሊዮን ያህል የመናውያን አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ያለው ተመድ፣ በደቡብ ሱዳን 5 ሚሊዮን ያህል ዜጎች የምግብ እርዳታ እንደሚፈልጉ፤ በሰሜን ምስራቃዊ ናይጀሪያ 5.1 ሚሊዮን ህዝብ የምግብ እጥረት ተጠቂ እንደሆነ፤ 2.9 ሚሊዮን ሶማሊያውያን አስቸኳይ የምግብ እና የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ገልጧል፡፡
ይሄም ሆኖ ግን ተመድ ለተጠቀሱት አራት አገራት የሚያስፈልገውን 4.4 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ ያደረገው ጥረት ይህ ነው የሚባል ውጤት አለማግኘቱንና እስካሁን ድረስ ማግኘት የቻለው 90 ሚሊዮን ዶላር ያህል ብቻ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ጸሃፊው፣ አለማቀፉ ማህበረስብ በአፋጣኝ የድጋፍ እጁን እንዲዘረጋ ጠይቀዋል፡፡