Administrator

Administrator

Saturday, 27 May 2023 20:01

"የደፈረሱ አይኖች"

እሁድ በ20/09/2015 ዓ.ም ከቀኑ በ8:00 ሰአት ታላላቅ እንግዶች በተገኙበት ይመረቃል።
እርስዎም እንዲታደሙ ተጋብዘዋል።
"የደፈረሱ አይኖች"
ደራሲ:- ውድ ነህ ክፍሌ
አዘጋጅ:- ሳሙኤል ተስፋዬ
Saturday, 27 May 2023 17:45

ሀገር ነው የራበን

እንደ ሐገር ባህል ልብስ~
አምሮ እንደ ተሠፋ
ያኖረን አስውቦ~ህብረ ቀለም ሰጥቶ~
ፍቅር እምነት ተስፋእንደ ጉም ብን ብሎ~
ሳናውቀው ከጠፋበየእምነት በዐሉ~
አንድ ማዕድ ተቋድሰን
በልተን ካደግንበት~ ፍቅር ተጎራርሰን
ነገር ሳይሆን እሳት~ ተጫጭረን ፍሙን
የጉርብትናን ልክ~ የጎረቤት ጥቅሙን
ካጣጣምነበት ደጅ~
የአብሮ መኖር ጣዕሙን
በሰልፍ የመረጥነው~ የጣልንበት ተስፋ
ቤት መስጊድን ማፍረስ~
እስኪደርስ ከከፋ
ዝናብ ፀሀይ ንቀን~በሠልፍ የመረጥነው
ወላሂ ማርያምን~ የሚል ሠው ካስጠላው
ቻው አብሮ መኖሩ~ቻው ሀገር ማለቱ
ደህና ክረሚ ዐለም~መኖር ምናባቱ
ይቅር ምናባቱ~ተራ ብልጭልጩ
የሠው ልጅ ነበረ~ከምንም በላጩ
አረ ሁሉም ነገር~ይቅርብን ይቅርብን
ሀገር ላይ ቁጭ ብለን~ሀገር ነው የራበን
ተስፋችን ተሟጦ~ትግስታችን አልቆ
እምነታችን በግፍ~ከውስጣችን ደርቆ
ባይተዋርነቱ~ ወደ ዳር እየገፋን
የሀገር ረሀብ ጠኔ~በአፍጢማችን ደፋን
መስጊድ እያፈረሱ~
ሰውን ከትውልዱ ቀዬ እየነቀሉ
ትርጉሙ ከሆነ~ ያገር ማልማት ቃሉ
ይቅር ምናባቱ~ መበልፀግ ማደጉ
ሰው ነው ያገር ግርማው~ ያገር ሞገስ ወጉ
ይቅር ምናባቱ~ ያሁን የዘመኑ~
መኪና ጋጋታ
እንሂድ በጋሪ~እንደ እቃ ተጭነን~
በኳትሮ ትሬንታ
ይቅርብን ውሃውም~
ደፍርሶ እሚመጣው
በርሜል እየገፋን~
ከቢርካ እንደ ጥንቱ~
በፍቅር እንጠጣው
ይቅርብን ያሁኑ~
የእስፓልት መንገዱ
ውሸት ነው አይመችም~
በፍቅር ካልሄዱ
አሁን ያለው ሁሉ~
ይቅርብን ይቅርብን
ፆም አድረን እንኑር~
ሀገር ነው የራበን
ያሁን ቴክኖሎጂ~
ተክሎ ጎጂ ሆኖ~ለችግር ካበቃ
ያሁኗን ወስዳችሁ~
ኋላ ቀሯን ሀገር~መልሱልን በቃ።
(ከድር አሊ)


ለሴቶች ብቻ

     እንደ ቀልድ የተጀመረ ፍቅር ነው። በልምምድ። በአስራዎቹ እድሜዋ፤ ሲሞዝቅ አየችው፤ በድምፁ ተማረከች። ነጥሎ መለመላት፤ አደገኛ talent scout ነበር። ድምፅዋን ወደደላት። የምትደመጥ ድምፃዊ አደረጋት።
አብረው መስራት ጀመሩ። ለመደችው። ለመዳት። “መለያየት ሞት” የሚሆን እስኪመስላቸው። እናስ?  መለያየትን ለመርታት አብረው ሆኑ። ውሃ አጣጭ። 60ዎቹ መጀመሪያ ላይ መሆኑ ነው።
ቆይቶ፤ ባህሪውን መልመድ አቃታት። ነገር ግን ፍቅር የማትለምደውን ባህርይ ተሸክሞ የመዝለቅ ያህል ነው ብላ አስባ አብራው ቀጠለች። ከIke Turner ጋር።
ከምታውቀው በላይ በደንብ በሱስ ተዘፈቀ። ፍቅሩን ወይንም ጥላቻውን በይው… በራሱ መንገድ  ይገልፅላት ጀመር። በደንብ አድርጎ ይነርታታል። አጥንቷ በተደጋጋሚ እስኪሰበር ደብድቧታል።
ትኩስ ቡና ፊቷ ላይ ሲደፋ [ደረጃ 3 ቃጠሎ የሚባለውን] የሚያሟላ ጉዳት ደርሶባታል።
ከቀልቧ ሆና አሰበችው። ፍቅር ይገድላል። ሊገድላት የሚችል ፍቅር እጇ ላይ አስራ ነበር የምትኖረው።
ከዕለታት ባንዱ ፈታችው። ተጠናቀቀ። 1978 [እኤአ]።
 Ike Turner እና Tina Turner የሚባለው ጥምረት አድሮ በሚያሳቅቅ ትዝታ (Trauma) ፤ የለፋችበት የስራ ሕይወት ደግሞ “ቲና ተርነር” በሚል ባሏ በሰጣት የመድረክ ስም/ብራንድ እና ቦርሳ በማይሞላ ገንዘብ ተጠናቀቀ።
የቲንኤጅ ፋንታሲዋ የነፍስና የስጋ መናጢ አደረጋት።
እናስ? እናማ…
መክሊቷን ጠንክራ ሰራችበት። ዳግም አንሰራራች።
ለስጋዋ ምቾት አሰበችበት። ፍቅር የሚባለው ጉድ It no longer worked — ለሷ።
ዓመታት ነጎዱ። ዝናዋም ተመልሷል።
በአንደኛው በረራዋ የጀርመን ሙዚቃ ፕሮዲዩሰር ከአየር ማረፊያ እንዲቀበላት ይደረጋል።  ስትወርድ አየችው። ሰውዬውን።
ልቧ መታ። በሀይል። ደነገጠች። አላባት። እጆችዋ ለመጨበጥ እስከማይችሉ፤ አላባት።
አስቢው!
1985 ላይ ነው። ቲና 47 ዓመት ሞልቷት ነበር። ሰውዬው ገና 30 ነው።
አሁን የቲንኤጅ ፋንታሲ ላይ አይደለችም። በፈተና ያለፈና የደደረ ነፍስ ነው ያላት። ለአፍላ ፍቅር የሚመች እድሜም አይደለም። የሴትልመንት እና የነርቸሪንግ እድሜ ነው።
ግን በቃ ሆነ። ፍቅር አገረሸ። እንደ አዲስ። አፈቀረች።
ሰውዬውስ? አፍቅሯት ነበር። ስሜቱ አለው። ገና አፍላ እድሜ ላይ ነው። ቀድሞ መውደዱን ሲገልፅ እንዴት ትመነው? ወዳ አይደለማ! በቡጢ አጥንት የሚሰባብር ፍቅር ውስጥ ኖሯ፤ መውደድ ለምኔ ብላ ስሜቷን ስትመገብ የኖረች ቪክትም ናታ!  አታምነውም።
“I didn’t believe him,” she shared. “But I didn’t want to say no because I wanted to continue the relationship.” ትላለች።
ተጨማሪ 27 ዓመት ዴዲኬትድ የሆነ ዴቲንግ አደረጉ። አጃኢብ የባህር ማዶ ሰው ሥነልቡና!
አመነችው።
ስዊዘርላንድ ተሰደደችለት። ያውም የ‘እናት ሀገር አሜሪካ’ ዜግነቷን መልሳ ፤ አልፈልግም፤ ዜግነቴ ፍቅሬ፤ ልቤ ያለበት ቦታ ነው ብላ ነዋ!
2013 ላይ ተሞሸሩ። Tina Turner 73 ሞልቷታል። Bach ደግሞ 57 ዓመቱ ነበር። ተሞሸሩ። ጋብቻዋን ሳታጣጥም፤ ደም ግፊቷ የኩላሊት ችግር ከሰተባት። ኩላሊት ያሻት ነበር።
Bach ያቀረበላት ስጦታ ኩላሊቱን ነበር። ስኬታማ ቀዶ ህክምና አደረገች። ዳነች። 2017 ላይ። ከቀዶ ህክምና ስትነቃ Bach በዊልቼር ሆኖ ክፍሏ ገባ።
“ፊቱ ላይ ፍቅር አየሁ!” ትላለች። ከበፊቱ ይልቅ አምሮበት ታያት። ውበቱ ጎላባት።
ፍቅር ኃያል ነገር! ታዲያ መቼስ ከስቲም ባዝ አልወጣ?! ከቀዶ ህክምና ክፍል አገግሞ እንጂ — ለምን ሊቆነጅ ይችላል? ማምሻዋን በፍቅር ኖረች። ሰሞኑን  አረፈች።
------------
እምልሽ…  So much to tell እኮ ስለዚህች ሴት ጉዞ። So much to analyze እኮ እዚህ ውስጥ። መዓት የሥነልቡና ቲየሪ ላነሳልሽ እችላለሁ — ይሄን ጉዞ ለመፈከር። ግን ለምን እኔን ታነቢያለሽ? ዛሬ ማታ እየተኛሽ ለምን አታስቢውም?
“What’s Love got to do with it? “
እውን እንዲያ ነውን? ተርነርም ሀሳቧን ሳትቀይር ትቀራለችን?
(ሱራፊል አየለ)


 በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ገለምሶ ከተማ ሰሞኑን የተሰማው ወሬ አግራሞትን የሚያጭር ነው። ሌሊት በጨለማ በመጓዝ የምናውቀው ጅብ በቀትር ከተማይቱ ውስጥ ወደ ሚገኝ አንድ የግል ክሊኒክ ሰተት ብሎ መግባቱ ተሰምቷል።
በገለምሶ ከተማ በሚገኘው ሚልኪ ክሊኒክ የሕክምና ባለሙያ የሆነው አዱኛ አባይነህ፣ የሆነውን እንዲህ በማለት ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ አስረድቷል።
“ጠዋት ወደ አራት ሰዓት አካባቢ ይሆናል። የክሊኒካችን በር ክፍት ነው። እኛም ገና ሥራ አልጀመርንም ነበር። ጅቡ በቀጥታ በተከፈተው በር ገብቶ ወደ ላብራቶሪ ክፍል አመራ።”
የክሊኒኩ ነርስ የሆነው አዱኛ፣ ሰዎች ጅቡን ሲያዩ ተደናግጠው ለመደብደብ ዱላ ማንሳታቸውን ይናገራል።
የክሊኒኩ ባለቤት ግን ሰዎች ጅቡን እንዳይመቱ ተከላከሉ።
“ወደ አምስት ሰዓት አካባቢ የክሊኒኩ ቅጥር ግቢ በሰው ተሞልቶ ነበር። በዚህ ጊዜ በአካባቢው የሚገኙ የትራፊክ ፖሊሶችን ጠርተን ሕዝቡ እንዲረጋጋ አደረግን።”
ጅቡ ግን ላብራቶሪ ክፍል ከገባ በኋላ ጭንቅላቱን አቀርቅሮ እንደተኛ ነበር ይላል፤ አዱኛ። ሁኔታው የታመመ እንጂ ጉዳት ለማድረስ የመጣ አይመስልም ነበር።
“ጅቡ ታሞ እንደሆነ ጠረጠርን። ከዚያም የእንስሳት ሐኪም ጋ ደወልን። እርሱም የፀረ-እብድ ውሻ በሽታ (አንቲ ሬቢስ) መርፌ ስጠው አለኝ። ከዚያም በኋላ መድኃኒት ቤት ሄጄ ገዝቼ ቀስ ብዬ በመርፌ ወጋሁት” ይላል፤ ነርስ አዱኛ።
ነርስ አዱኛ ለጅቡ መርፌውን ለመውጋት ባሰበ ጊዜ ለደኅንነቱ ሰግቶ ነበር። ነገር ግን ጅቡ በጣም ተዳክሞ ለመንቀሳቀስ በማይችልበት ሁኔታ ስለነበረ፣ ሲወጋ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አላደረገም ብሏል። ቢሆንም ግን ለደኅንነቱ የሰጋው ነርስ፤ ጅቡ ተኝቶበት ከነበረው ስፍራ አቅራቢያ የነበረውን ማቀዝቀዣ በከለላነት ተጠቅሞ ነበር መርፌውን የወጋው።
በክሊኒኩ ውስጥ ለአንድ ሰዓት ያህል የቆየው ጅብ፣ መርፌውን ከተወጋ ከ20 ደቂቃ በኋላ ተነስቶ መውጣቱን አዱኛ ይናገራል። “ጅቡ የታመመ ስለሚመስል እኛ አንድ ባዶ ክፍል ልናስገባው ነበር። ነገር ግን እንዳሰብነው አልሆነም። ልክ መርፌውን ከወጋነው ከደቂቃዎች በኋላ ከተኛበት ቦታ ተነስቶ ወጥቶ ሄደ።”
በግል ክሊኒክ መርፌ የተወጋው ጅብ ዳግም አለመመለሱን የህክምና ባለሙያው ያስረዳሉ። ክሊኒኩ ጅቡ ያረፈበትን የላብራቶሪ ክፍል በሚገባ ካጸዱ በኋላ ወደ ቀድሞ ሥራው ተመልሷል። እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ በአካባቢው የተለመደ አለመሆኑንና የአካባቢው ነዋሪዎች መደነቃቸውን የህክምና ባለሙያው አቶ አዱኛ ይናገራሉ።

ትውስታ አድማስ

                    የትኛው “ጉንዳን” እንሁን?


          ”--የፖለቲካችን አሰላለፍ ጭራና ራስ ሆኗል። ሁለቱም ተስማምቶ መሀል ላይ መገናኘት ሲችሉ እርስ በርስ መናከስን መርጧል፡፡ አንድ አካል አንድ አምሳል መሆናቸውን ረስተው፣ አንዱ ጫፍ በሌላኛው ጫፍ ላይ ይነሳል፡፡ መሀላቸው እንዳይበጠስ እንደ መጠንቀቅ ይሳሳባሉ፡፡ ከተበጠሱ በኋላ እንደ መማርና እንደ መጠገን፣ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ይዘምታሉ፣ይፋለማሉ፡፡--”
               - በክብሮም በርሀ-


         ጉንዳኖች ተዓምረኛ ፍጥረቶች ናቸው፡፡ ከምንም በላይ ህብረታቸው የሚደንቅ ነው፡፡ ጉንዳኖች በህብረት “እኔ ነኝ ያለ” ወንዝ ማቋረጥ ይችላሉ። ጉንዳኖች በታታሪነታቸው የሚታወቁ አስገራሚ ፍጥረታት ሲሆኑ፤ የሠው ልጅን የማስተማር ብቃቱ አላቸው፡፡ የፍጥረታት ሁሉ ንጉስ ተደርጎ የተሾመው “ሰው”፣ በመጨረሻ ላይ ለጉንዳን እጁን ብቻ ሳይሆን እግሩን ይሰጣል፡፡  ጠቢቡ ያሬድ ከጉንዳን መማሩ ይነገራል፡፡ በትምህርት ተስፋ ቆርጦ የነበረው ያሬድ፤ ዛፍ ስር ሆኖ “ወድቆ መነሳትን” ተምሯል፡፡ በውጤቱም፣ ከውድቀት ተነስቶ ታሪክን ሰርቷል፡፡ ተንጠራርተን ጉንዳን ብለን የምንሰድባቸው ቻይናውያን ሳይቀር እንደ ያሬድ ከጉንዳን የተማሩ ይመስላል፡፡ የቻይናውያን የጥንካሬ ዋነኛ መስፈርታቸው  “ወድቆ መነሳት” ነው፡፡ አሸዋ ላይ ወድቆ ዶግ አመድ የሚሆን ብርጭቆ ከቁስ አይቆጥሩትም፡፡ እርግጥ ነው እኛ የምናውቃቸው የቻይና ዕቃዎች፣ አሸዋ ላይ “አሸዋ” የሚሆኑ ናቸው፡፡ የመድሎው ዓይነት፣ ወደ አደጉ ሀገሮች የሚልኳቸው ዕቃዎች ደግሞ “ተሰብረው የማይሰበሩ” መሆናቸው ይነገራል፡፡ አቤት ልዩነት፣ አቤት መናናቅ!
ወደ ነገራችን ስንመለስ፣ “The Story of Philosophy” በተሰኘው የዊል ዱራንት መፅሐፍ ገፅ 245 ላይ ሾፐንሀወር የተባለ ፈላስፋ፣ ቡልዶግ የተባለ የአውስትራልያ ጉንዳንን በተመለከተ ይነግረናል። የፈላስፋ ነገር ለማንም ሰው የማይታይ ይታየው የለ፡፡ ጉንዳኑ በሁለት ከተከፈለ በ”ጭራ”ና በ”ራስ” መሀከል  ለግማሽ ሰዓት ያክል የሚዘልቅ ፍልሚያ ይካሄዳል፡፡ “ጭራ” ሲናደፍ፣ “ራስ” ደግሞ በጥርሱ ይናከሳል፡፡ በውጤቱም ከሁለት አንዱ ይሆናል፤ ወይ ሁለቱም ይሞታሉ አልያ ደግሞ በሌላ ጉንዳን ይበላሉ፡፡ ቻይናውያን፤ “ነብሮች ሲፋለሙ ከተራራ ሆነህ ተመልከት” ይላሉ፡፡ አንደኛው መሞቱ ሌላው ደግሞ ማጣጣሩ ስለማይቀር፣ ሁለቱንም ነብሮች ለመግደል ይቀላል፡፡ እናም፣ እርስ በርሱ የተበላላ ጉንዳን፣ በሌሎች ጉንዳኖችን የሚበላው በቀላሉ ነው፡፡
እኛም ሆንን ጉንዳኖች በተፈጥሮ ቁጥጥር ስር መሆናችን አንድ ያደርገናል፡፡ ማናችንም ብንሆን ከተፈጥሮ ህግጋት ማምለጥ አይቻለንም፡፡ ተፈጥሮ ደግሞ ላጣጣማት ማር፣ ላጠመማት ምሳር ነች። ተፈጥሮን ተጠቅሞና ተጠቦ መኖር ጣፋጭ ነው። ተፈጥሮን አጣቦና ተጣቦ መኖር ደግሞ ተቀርቅሮ መሞትን ያስከትላል፡፡ ተፈጥሮን ተጠቅሞ በፍቅርና በሰላም መኖር፣ ራስን ከህሊና ያወዳጃል፡፡ ተፈጥሮን አጣሞና ግዴለሽ ሆኖ መኖር ደግሞ የገዛ አንገት ላይ እጀ-ገመድ ያስገባል፡፡ ዋናው ነገር አጠቃቀማችን ነውና፡፡
ራስን በጭራ ላይ አዝምቶ የገዛ ነፍስ ማድከም ስራ የሚመስለው ሰው አለ፡፡ የጉንዳኑ ራስ  ጭራን ማጥፋት ቀላል ይመስሏል፡፡ በአንፃሩ ጭራም በራስ ላይ የበቀል በትር ያሳርፋል፡፡ ዳሩ ግን፣ ሁለቱም አይተርፉም፡፡ ሁለቱም ለመበላት ራሳቸውን ይከሽናሉ፡፡
የፖለቲካችን አሰላለፍ ጭራና ራስ ሆኗል። ሁለቱም ተስማምቶ መሀል ላይ መገናኘት ሲችሉ እርስ በርስ መናከስን መርጧል፡፡ አንድ አካል አንድ አምሳል መሆናቸውን ረስተው፣ አንዱ ጫፍ በሌላኛው ጫፍ ላይ ይነሳል፡፡ መሀላቸው እንዳይበጠስ እንደ መጠንቀቅ ይሳሳባሉ፡፡ ከተበጠሱ በኋላ እንደ መማርና እንደ መጠገን፣ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ይዘምታሉ፣ይፋለማሉ፡፡
የፖለቲከኞች ጫፍ መርገጥ (ራስና ጭራ መሆን) ሳያንስ፣ ዳር ቆሞ ሞታቸውን የሚጠባበቅ አይታያቸውም፡፡ ይህ ወገብ በሌለውና ጭራና ራስ ብቻ በሆነው አካል የሚሞከር አይደለም፡፡ “ቆም ብሎ ለማሰብ” መጀመሪያ መቆም፣ ከዛ ደግሞ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለመቆም ወገብ ግድ ሲሆን ለማሰብ ደግሞ ከጭራ ጋር የተሰናሰለ ራስ ያስፈልጋል። ሁለቱም በሌለበት ግን መቆምም ሆነ ማሰብ የሚታሰብ አይደለም፡፡
ፖለቲከኞቻችን በጀመሩት “እልህና ወኔ” ከቀጠሉ፣ የአውስትራልያው ቡልዶግ ጉንዳን፣ “ጭራና ራስ” መሆናቸው አይቀርም፡፡ በጭራና ራስ ተደስቶ የሚያድር ባይኖርም ወገብ ሳይኖራቸው ወገብ፣ እግር ሳይኖራቸው እግር፣ ፍቅር ሳይኖራቸው ልብ ሆኖ የሚያኖራቸው ህዝብ አለ፡፡ የሚያስቀው ነገር የተገላቢጦሽ ሆነና፣ “የምናኖርህ ህዝባችን ሆይ” ብለው መፎከራቸው ነው፡፡ የሚደንቀው ነገር የማኖረው “እኔ ነኝ”፣ “እኔ ነኝ” ማለታቸውና በዚሁ መጣላታቸው ነው፡፡ የሚሰቀጥጠው ነገር፣ እነሱ ጭራና ራስ መሆናቸው ሳያንስ ወገብ ሆኖ የሚያገለግላቸውን ህዝብ፣ “ጭራና ራስ” ለማድረግ መወሰናቸው ነው፡፡ ተስፋ የሚያስቆርጠው ነገር ሁሉም ጭራና ራስ ሆኖ ሲያበቃ፣ ሁሉንም ጠራርጎ የሚበላ “ዳር ተመልካች” እና “እበላ ባይ” መኖሩን አለማየቱ ነው፡፡ ካልተበሉ በቀር አያምኑም ማለት እኮ ነው፤ “ፈንጅ አምካኝ ከስህተቱ አይማርም” እንደሚባለው ማለት ነው፡፡
ስለሆነም፣ ጥያቄው ቀላል ነው፡፡ ጥያቄው፡- “የትኛውን ጉንዳን እንሁን?” ነው፡፡ ያ ተባብሮና የህብረት ሰንሰለት ፈጥሮ፣ ወንዝን የሚያቋርጠው ጉንዳን ወይስ ያ “ጭራና ራስ” ሆኖ፣ ራሱን በራሱ የሚበላውና ራሱን የሚያስበላው? እሳትና ውሃ ቢቀርብ እጃችንን የምንሰደው ምኑ ላይ ነው?
***
(ምንጭ፡- አዲስ አድማስ ዌብሳይት፤30 ኦክቶበር 2016)

የስኬታማ ህይወት ትልቁ እንቅፋት፣ የመውደቅ ፍርሃት ነው፡፡ እንቅፋቱ ውድቀት ራሱ ሳይሆን ፍራቻው ነው፡፡ እንደውም መውደቅ የበለጠ ያጠነክራችኋል፤ የበለጠ ቁርጠኛ  ያደርጋችኋል፡፡ የመውደቅ ፍርሃት ወይም ውድቀትን መጠበቅ ግን ሃሳባችሁንም ሆነ ተግባራችሁን ያሽመደምደዋል፡፡
አንድ ወጣት ጋዜጠኛ በአንድ ወቅት የIBM መሥራች ለነበረው ቶማስ ጄ. ዋትሰን (ሰር) እንዲህ ሲል ጠይቆት ነበር፤ “እንዴት በፍጥነት የበለጠ ስኬታማ መሆን እችላለሁ?” ዋትሰን ሲመልስም፤ “በፍጥነት ስኬታማ ለመሆን የምትሻ ከሆነ የውድቀትህን መጠን ከፍ አድርገው” ብሏል፡፡
ወደፊት ለመጓዝ ድፈሩ፡፡ በጥረታቸው ሚሊዬነር ለመሆን የበቁ ሰዎች ቁማርተኞች አይደሉም፡፡ ነገር ግን ወደ ግባቸው ለመድረስ   አደጋዎችን  ለመጋፈጥ ፈጽሞ አያመነቱም፡፡ ምናልባት ባለጸጋ ለመሆን ዝግጁ መሆናችሁን የሚያረጋግጠው ትልቁ ነገር፣አደጋዎችን መጋፈጥን በተመለከተ ያላችሁ አመለካከት ነው፡፡
ምንጊዜም ስኬታማነታችሁን አደጋ ላይ ከሚጥሉ ሁኔታዎች ጋር ስትጋፈጡ ተከታዩን ጥያቄ ለራሳችሁ አቅርቡ- “በእርምጃዬ ብገፋበት የሚደርስብኝ የመጨረሻው አስከፊ ነገር ምንድን ነው?” ከዚያም በነዳጅ ሃብት የበለጸገው ቢሊዬነሩ ጄ.ፖል ጌቲ የሚለውን ተግብሩ - “ያ አደገኛ ነገር ምንም ይሁን ምንም ፈጽሞ እንደማይከሰት እርግጠኛ መሆን!”
ሃቁ ምን መሰላችሁ? መውደቅን የማይፈራ ማንም የለም፡፡ ሁሉም ማጣትና ድህነትን ይፈራል፡፡ ሁሉም ስህተት መፈጸምና  መሰናከልን አይሻም፡፡ ሚሊዬነሮች ግን አውቀውና  ሥራዬ ብለው ይህን ፍርሃት ይጋፈጡታል፡፡ እናም ያሻቸውን ከማድረግ የሚያስቆማቸው ማንም የለም፡፡ ታዋቂው ገጣሚ ዋልዶ ኤመርሰን፤ “የምትፈራቸውን ነገሮች ማከናወንን የህይወትህ አካል አድርገው፡፡ የምትፈራቸውን ነገሮች ከሰራህ ያለ ጥርጥር ፍርሃት ይሞታል፡፡” ይላል፡፡  
በድፍረት ስትንቀሳቀሱ አንዳች የማታዩት ኃይል ለድጋፍ አጠገባችሁ ይቆማል፡፡
እያንዳንዱ የድፍረት እርምጃ ደግሞ የወደፊት ወኔያችሁንና አቅማችሁን ያሳድገዋል፡፡ ስኬት እንደምትጎናጸፉ እርግጠኛ ባልሆናችሁበት ሁኔታ ወደፊት ለመጓዝ እርምጃ ስትወስዱ  ፍርሃታችሁ ጠፍቶ ድፍረታችሁና ልበ ሙሉነታችሁ ይጨምራል፡፡
 የማታ ማታም አንዳችም ነገር የማትፈሩበት ደረጃ ላይ ትደርሳላችሁ፡፡
“APPOLLO 13”በተሰኘው ምርጥ ፊልም ላይ ሽንፈትን በተመለከተ የናሳ ስፔስ ቁጥጥር ሃላፊ ኢዩጂኒ ክራንትዝ የተናገረው ምርጥ አባባል ተጠቃሽ ነው፡፡
የህዋ ጣቢያው ሰራተኞች ስለ መንኩራኩሯና ጠፈርተኞቹ መጥፋት ማሰብ በጀመሩ ወቅት ጮክ ብሎ፤ “ሽንፈት አማራጭ አይደለም” ብሏቸዋል፡፡
እንግዲህ የናንተ ሥራ ሚሊዬነር ለመሆን ቁርጠኝነት ማሳየት ነው፡፡ የናንተ ሥራ ቁርጥ ያሉ ግቦችን መቅረጽ ነው - ከዚያም በጽሑፍ አስፍራችሁ በየዕለቱ መተግበር፡፡ ሁልጊዜም ግባችሁን ለማሳካት ስትንቀሳቀሱ ታዲያ፣ “ሽንፈት አማራጭ አይደለም” የሚለውን ልታስታውሱ ይገባል፡፡ ይሄ አመለካከት ነው፣ ከምንም ነገር የበለጠ ዘላቂ ስኬትን የሚያረጋግጥላችሁ፡፡
***
ውድቀትን ወደ ድል መቀየር ይቻላል!
በህይወት ጉዟችን  ሽንፈት ወይም ውድቀት ሲገጥመን ሁለት አማራጮች አሉን፡፡ አንድም ወድቆ ወይም ተሸንፎ መቅረት ነው አሊያም ከውድቀታችን ተምረን ለቀጣዩ  ድል መትጋት ነው፡፡ ወድቆ መቅረት ትክክለኛው አማራጭ አይደለም፡፡
የስኬት መንገዳችንን  ለመጥረግ ሊያጋጥሙ የሚችሉ መሰናክሎችን ወይም ፈተናዎችን ከወዲሁ ማጥናትና መፈተሽ ብልህነት ነው፡፡፡ የሥነልቦና ዝግጅት ለማድረግና አማራጮችን በፍጥነት ለመውሰድ ያስችለናል፡፡
ብዙ ውጤት የጠበቅንበት ሥራ ባላሰብነው መንገድ ሳይሳካ ቢቀር (ፌይል ቢያደርግ) ምንድነው ማድረግ የሚጠበቅብን? ያልተሳካበትን ምክንያት በፍጥነት መርምረን፣  ከስህተቱ  መማርና  ለቀጣይ የስኬት ጉዟችን መትጋት ይገባናል፡ሁልጊዜም ራሳችሁንና ሥራችሁን ለመገምገም ድፍረት ይኑራችሁ፡፡ ጥቃቅን ስህተቶችና ክፍተቶችን እየተከታተላችሁ ከማረምና ከመድፈን ችላ አትበሉ፡፡ በራሳችሁ ሥራ ላይ ርህራሄ የለሽ ሃያሲ በመሆን ራሳችሁንና ሥራችሁን ከከፋ ጉዳትና ውድቀት መታደግ ትችላላችሁ፡፡
በሥራችሁ ላይ ችግር ሲገጥማችሁ ወይም ኪሳራ ሲደርስባችሁ ሰበብ ለመደርደር አትሯሯጡ፡፡ በዕድላችሁ ለማማኸኘትም አትሞክሩ፡፡ “እኔ እኮ አይሆንልኝም፤ዕድሌ ነው”  አትበሉ፡፡ ሰበብ በመደርደርም ይሁን በዕድል በማማኸኘት  ማንም የፈለገበት ውጤት ላይ አልደረሰም፡፡ የሚያዋጣው የችግሩን መንስኤ  በቅጡ መርምሮና ፈትሾ የመፍትሄ እርምጃ በመውሰድ ለተሻለ ውጤት  መትጋት ብቻ ነው፡፡
ያለማችሁትን ግብ ለማሳካት ጽኑና አይበገሬ  ሁኑ፡፡ በትናንሽ እንቅፋቶች ተስፋ ለመቁረጥና ለማቆም አትጣደፉ፡፡ አዳዲስ ያልተሞከሩ መላዎችንና ዘዴዎችን ተግብሩ፡፡ አዳዲስ አሰራሮችን ሞክሩ፡፡ ነገር ግን ውጤት ከማያመጣ ነገር ጋር የሙጥኝ ብላችሁ አትክረሙ፡፡
ውዱን ህይወትና ጊዜያችሁን በከንቱ ማባከን ሌላ ጥፋት ነው፡፡ የመጀመሪያው ዕቅዳችሁ (plan A) ካልተሳካ ወደ ሁለተኛው ዕቅዳችሁ (Plan B) ተሻገሩ፡፡
ልብ በሉ፤ ሁሉም ችግር በጎ ጎን አለው፡፡ ያንን በጎ ጎን ፈትሾ ማግኘት ግን የናንተና የናንተ ብቻ ሃላፊነት ነው፡፡
ከአቅም በላይ የሚመስል ትልቅ ፈተና ወይም ተግዳሮት ሲገጥማችሁ ከመደንገጥና ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ  አዕምሮአችሁን ክፍት አድርጋችሁ የመፍትሄ ሃሳቦችን አስሱ፡፡ የተሻለ ልምድ ያላቸው አዋቂዎችንና ባለሙያዎችን አማክሩ፡፡ በእርግጥም ከተጋችሁ  ውድቀትን ወደ ድል መቀየር ትችላላችሁ፡፡
(ምንጭ፡- ”ህይወትና ስኬት”)


 ከብዙ አመታት በፊት ሁለት ለአካለ ትግል የደረሱና በተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥ ይታገሉ የነበሩ ጓዶች ነበሩ፡፡ ከተወሰነ ወቅት በኋላ የነበሩበትን ፓርቲ ትተው ዓላማቸውን ቀይረው በጊዜው ወደነበረው መንግሥት ገቡ፡፡ በዚያ መንግሥት ውስጥም እንደ አንድ ኮሚቴ ሆነው እንዲሰሩ በመወሰኑ በኮሚቴ ሃላፊነት አንድ ሻምበል ተመድቦላቸው የፖለቲካ ጥናታቸውን ቀጠሉ፡፡ ተጠመቁ፡፡ አመኑ፡፡ መልካም ኑሮ ያገኙ መሰሉ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከሁለቱ ወጣቶች አንደኛው ወደ ወዳጅ አገር ወደ ኩባ ለአጭር ጊዜ ስኮላርሺፕ አገኘና ሄደ፡፡
ተምሮ፣ ተመራምሮ፣ የፖለቲካ ንቃቱን አዳብሮ፣ አንቱ ተብሎ፣ በስኮላርሺፕ የሚቆይበት ጊዜ አልቆ ወደ እናት አገሩ ተመልሶ መጣ፡፡ ወደ እናት ኮሚቴው ለመግባትም አገር ውስጥ ይጠብቀው ወደነበረው ጓደኛው  ሄደና አገኘው፡፡
ሆኖም ሰብሳቢያቸው የነበረው፤ የኮሚቴያቸው መሪ ሻምበል ዛሬ የለም፡፡ ከኩባ የመጣው ወጣት እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የቆየውን ወጣት “ኧረ የሆነስ ሆነና ጓድ ሻምበልስ ወዴት አለ?” ሲል ጓደኛውን ጠየቀ፡፡
ጓደኛውም እያመነታ፤
“ለካ አልሰማህምና! ጓድ ሻምበል እኮ ታስሯል” ይለዋል ሲፈራ ሲቸር፡፡
ከኪዩባ የመጣው ወጣት ክው አለ፡፡ ግራ ገባው፡፡ “እንኳን አሰሩት” እንዳይል ነገ ምን ሊከተል እንደሚችል፣ ጓድ ሻምበል ይፈታ አይፈታ፣ ተፈቶም ወደ ኮሚቴው ይመለስ አይመለስ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ በአንፃሩ “እሱን የመሰለ ጓድ እንዴት ይታሰራል?” ብሎ እንዳይሟገት ደግሞ ገና እሥሩ አላበቃም፡፡ በማን ላይ እንደሚቀጥል ስለማይታወቅ ያስፈራል፡፡ ስለዚህ ጥንቃቄ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ጓደኛው ምን ይል ይሆን እያለ እየጠበቀ አፍ-አፉን ያየዋል፡፡
ያም ከኩባ ተመላሽ ሲጨንቀው ቆይቶ እንዲህ አለ፡-
“አቤት የአብዮታችን ፍጥነት!!”
****
አለመተማመንና ጥርጣሬ የነገሰበት ወቅት የፍርሃት እናት ነው፡፡ ሰው የልቡን አያወራም፡፡ ጓደኛና ጓደኛ በጎሪጥ ይተያያል፡፡ መከዳዳት የእለት - የሰርክ ጉዳይ ይሆናል- እንደውም ይለመዳል፡፡ ጠብታዋ ነገር ሰፍታ ጎርፍ ትሆናለች፡፡ በጦርነት ከሚረታው በወሬ የሚረታው ይበልጣል፡፡ የበታች የበላዩን ይፈራል እንጂ አያከብርም፡፡ ይታዘዛል እንጂ አያምንም፡፡ የበላይ የበታቹን በትንሽ-በትልቁ ይጠራጠራል፡፡ ያሴርብኛል እንጂ ያግዘኛል የሚል እምነት የለውም፡፡ አለቅየው ቅንጣት ታህል ጥፋት ሲያይ ከምድር-ከሰማይ ጉዳይ ጋር አገናኝቶ በእኔ ላይ የተቃጣ ተንኮል ነው ሲል ይደመድማል፡፡ ሁሉ ነገር ወዴት እንደሚያመራ ስለማይታወቅ በጥንቃቄና በፍርሃት መካከል ልዩነት ይጠፋል፡፡ ሰላምታው ስድብ፣ ስድቡ ሰላምታ የሚመስልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ፈሪው ከፍርሃቱ ብዛት ጀግና ይሆናል፡፡ እንቅፋቱ ሁሉ ለሞት ያበቃኛል ስለሚል የተከላከለ መስሎት አጥቂ ይሆናል፡፡ “የሚያባርረኝ ጣሊያን እንቅፋት መትቶት በሞተ አርበኛ ነህ አሉኝ እንጂ እኔስ አርበኛ አደለሁም!” እንዳለው የሃገራችን ሰው መሆኑ ነው፡፡ ጀግናው ደግሞ ከጥንካሬው ብዛት ፈሪ ይሆናል፡፡ ትንኟን በአቶሚክ ቦንብ ይገድላል፡፡ ለዚህም አላጨበጨባችሁልኝም ብሎ አገር ምድሩን ያኮርፋል፡፡ መጨካከን እንደ ዋዛ ይለመዳል፡፡ ስርቆትና ምዝበራ “ቢዝነስ ተሰራ” ይሰኛል፡፡ ከእያንዳንዱ ሃብት ጀርባ ያለው ወንጀል እንደ ጥበበኛነትና እንደ ጀብድ እንደሚቆጠር ሁሉ፤ በእያንዳንዱ መሸናነፍ ጀርባ ያለው ደግሞ እንደ አላማ ፅናት፣ ቆራጥነት፣ መስዋእትነት ይታያል፡፡ በዚህን አይነት ሰአት ብዙ ክስተት የድንገቴና የዱብ-እዳ እንጂ በሂደት የመጣ አልመስል ይላል፡፡ አብዛኛው ነገር የማይታይ ፍልሚያ (The invisible conflict እንዲል መፅሐፍ) አይነት ይሆናል፡፡ ህቡኡ የአደባባይ አዋጅ ፣ የአደባባይ አዋጁ ህቡእ የመምሰል ባህሪ ያመጣል፡፡ ወዴት እየሄድን ይሆን? የሚለው ጥያቄ የሁሉ ሰው ጥያቄ ይሆናል፡፡ የአለቃም የምንዝርም! አንድ ጊዜ አንድ አብዮት አደባባይ ለመሰለፍ የወጡ አሮጊት “የዛሬው ሰልፍ አላማ ምንድን ነው?” ብሎ ጋዜጠኛ ቢጠይቃቸው፤ “ቆይ እንጂ አትቸኩል ገና ሹሞቹ መጥተው መች ነገሩን!” አሉት አሉ፡፡ የሚያገባንን ጉዳይ ሁሉ መስማት መቻል አለብን፡፡ በሃገር ደረጃ የተለየ ችግር የሚፈጥር ካልሆነ በቀር፡፡
ህዝብ በየጊዜው የሚካሄደውን ነገር ማወቅ ይፈልጋል፡፡ በየወቅቱ የሚደረገውን ሃገራዊም ሆነ ከሃገር ጋር የተያያዘ አለም-አቀፍ እንቅስቃሴ እንዲገባው ይፈልጋል፡፡ አፍንጫው-ስር የሚከናወን ድርጊት ላይ አፍጦ አርቆ ማስተዋል እንዳያቅተው፣ ሩቅ ሩቅ እያየ የቆመበት ምንጣፍ ከእግሩ ስር ተስቦ እንዳይወሰድ፤ ማንኛውም ኢንፎርሜሽን ሊነገረው ይገባል፡፡ አለበለዚያ ስለነገ ያለው ተስፋና ግምት በፍርሃትና ጥርጣሬ የተሞላ ይሆንና “አቤት የአብዮታችን ፍጥነት!” ሲል የሚገኝ የራሱ አቋም የሌለውና “ዛሬን እንደምንም ልደር ብቻ” የሚል ዜጋ መፈልፈል ይሆናል እጣችን፡፡ ታመመ ሲሉ ሞተ ፣ ወደቀ ሲሉ ተሰበረ ማለት ቅርብ በሆነበት ዘመን፣ ህዝብ ላለማመን ቅርብ ቢሆን አይገርምም፡፡ አጋጣሚን መሾሚያ መሸለሚያ የሚያደርግ የሚበዛበት ጊዜ ቢፈጠርም አይገርምም፡፡ ሔልሙት ክሪስት የተባለ አንድ ደራሲ፤ The rottener the time the easier it is to get promoted  እንዳለው ነው፡፡ (ጊዜው የበለጠ እየነተበ በመጣ ቁጥር በቀላሉ መሾምና እድገት ማግኘት እየበዛ ይሄዳል እንደማለት ነው፡፡) የቢሮክራሲ ንቅዘት፣ የአመለካከት ክስረት፣ የአዛዥነት አስተሳሰብ፣ የእሺ-ባይነት ኩራት፣ ከሁሉ-በላይ ነኝ የሚል ስሜት፣ የጌታና የሎሌ ግንኙነት፣ የመቻቻል ድህነት፣ የሙስና ጌትነት ወዘተ ሁሉም የተሳሰሩና የተሳሰረ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንዲሁም ታሪካዊ ምንጮች ያሏቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ የህዝብ ጥርጣሬና ፍርሃት ሲከሰትና ነገ ምን ይፈጠር ይሆን? እያለ መስጋትና መጠየቅ ሲበዛ፣ እነዚህን ምንጮች በጥሞና መመርመር ያሻል፡፡ እንደ ሲዳማ ህዝባዊ አባባል “አይጧ ከሌለች ጉድጓዱ ከየት መጣ?” ማለት አለብን፡፡     ዘመን ባንክ፤ አዲሱን የዋና መሥሪያ ቤቱን ህንጻ ዛሬ ያስመርቃል

         የዛሬ 15 ዓመት፣ በ87.2 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል፣ የባንክ ኢንዱስትሪውን  የተቀላቀለው ዘመን ባንክ፣ አዲሱንና ዘመናዊውን ባለ 36 ወለሎች የዋና መሥሪያ ቤቱን ህንጻ በዛሬው ዕለት  ያስመርቃል፡፡
የዘመን ባንክ  አመራሮች  ከትናንት በስቲያ ሐሙስ፣ በአዲሱ የዋና መሥሪያ ቤት ህንጻ  መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ የባንኩን ያለፉ ዓመታት የሥራ አፈጻጸምና የአዲሱን ህንጻ መጠናቀቅ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባ የፋይናንስ ማዕከል ተብሎ በሚታወቀው ሰንጋ ተራ አካባቢ የተገነባው

የዘመን ባንክ  የዋና መሥሪያ ቤት ህንጻ አምስት ዓመታትን የፈጀ ሲሆን፤የግንባታው አጠቃላይ ወጪ ወደ 1.5 ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ተነግሯል፡፡
የዋና መ/ቤቱ ህንጻ መጠናቀቅ ተበታትነው የቆዩትን የባንኩን የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ወደ አንድ ህንጻ በመሰብሰብ ለደንበኞቹም ሆነ ለራሱ ወጪ ቆጣቢ፣ ቀልጣፋና ምቹ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችለው ተገልጧል፡፡
አዲሱ ህንፃ ባንኩ በየዓመቱ ለህንጻ ኪራይ ሲያወጣው የነበረውን ከ40 ሚ. ብር በላይ እንደሚያስቀርለት የተናገሩት የዘመን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ዘበነ ፤” አዲሱ ህንጻ ለባለአክሲዮኖቻችን ሃብት፣ ለደንበኞቻችን ደግሞ ዋስትና ነው” ብለዋል፡፡የባንኩ ዘመናዊ ህንጻ ሁሉንም የግንኙነት አማራጮችን በቴክኖሎጂ ያቀፈ፣ የመረጃ መሰብሰቢያና ማደራጃ እንዲሁም መተንተኛ ማዕከላት ያሉት ነው ተብሏል፡፡
በ2300 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ያረፈው ህንጻው፤ እስከ 200 የሚደርሱ ተሳታፊዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው የስብሰባ አዳራሾች፣ እያንዳንዳቸው 13 ተሳፋሪዎችን የሚያጓጉዙ አሳንሰሮች፣ 200 ተሽከርካሪዎችን ማቆየት  የሚያስችሉ የምድር ቤትና ፎቅ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችን ይዟል፡፡


ግንባታውን ያከናወነው China W

u Yi CO. LTD የተሰኘ የቻይና መንግሥት ተቋራጭ ኩባንያ መሆኑ ታውቋል፡፡


ባለፈው 2021/22 በጀት ዓመት የባንኩ ትርፍ ከታክስ በፊት 2.1 ቢሊዮን ብር እንደነበር ያስታወሱት የባንኩ አመራሮች፤ ይህም ባንኩ ከተመሰረተ ጀምሮ ካስመዘገበው ትርፍ ከፍተኛው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ያለፉት አምስት ዓመታት የትርፍ ድርሻ በአማካይ 40 በመቶ መድረሱንም አክለው ገልጸዋል፡፡
የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ በአሁኑ ሰዓት ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፤የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱና የተከፈለው ካፒታል መጠን 4.7 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተመልክቷል፡፡ 100 የሚደርሱ ቅርንጫፎች ያሉት ዘመን ባንክ፤ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ጠቅላላ ሃብት እንዳለው  ታውቋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ መረጃው ያልተጣራና ከአንድ ወገን ብቻ የተገኘ ነው ብሏል

        በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ እየተካሄደ ያለው ዜጎችን በግዳጅ የማስነሳትና ቤቶችን የማፍረስ ሂደት 100ሺ ቅሬታዎች እንደቀረቡበት ተገለፀ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ መረጃው ያልተጣራና ከአንድ ወገን ብቻ የተገኘ ነው ሲል አስተባብሏል፡፡የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ በሸገር ከተማ “ህገወጥ ግንባታ” በሚል እየተካሄደ ካለው የቤት ፈረሳ ጋር በተያያዘ ከአንድ መቶ ሺ በላይ አቤቱታዎች እንደቀረቡለት ገልጿል፡፡
ተቋሙ በተያዘው በጀት አመት ከ133ሺ በላይ አቤቱታዎችን መቀበሉን ገልፆ፤ ከዚህ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ውስጥ እየተካሄደ ካለው የቤት ፈረሳ ጋር የተያያዙ አቤቱታዎች እንደሆኑም አመልክቷል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ “ህገወጥ ግንባታ” ናቸው እያለ ለሚያፈርሳቸው የመኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች ምትክ ቦታ እንደማይሰጥና ለተፈናቃዮችም ጊዜያዊ መጠለያ እንዳልተዘጋጀላቸው የገለፀው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ይህ ሁኔታም ተቋሙን እጅግ እንዳሳሰበውና መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክቷል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በከተማው እየፈረሱ ያሉት ቤቶች በህገወጥ መንገድ የተገነቡና የግንባታ ፈቃድ የሌላቸው ቤቶች መሆኑን ጠቁሞ፤ እርምጃው የህግ የበላይነትን ከማስከበር ጋር የተያያዘ ነው ብሏል፡፡
በህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የተገለፀውና 100ሺ ቅሬታዎች ቀረቡበት የተባለው ጉዳይም ከእውነት የራቀ፣ ውይይት ያልተደረገበትና፣በአግባቡ ያልተጣራ እንዲሁም ከአንድ ወገን ብቻ በተገኘ መረጃ ላይ የተመሰረተ ነው ሲል አስተዳደሩ አስተባብሏል፡፡ ከ16 አገራት የተውጣጡ 130 ኩባንያዎች ይሳተፉበታል

       5ኛው ʺአግሮፉድ ኢትዮጵያ እና ፕላስትፕሪንትፓክ ኢትዮጵያʺ ዓለማቀፍ የንግድ ትርኢት፣ ከሰኔ 1- 3 ቀን  2015 ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡በንግድ ትርኢቱ ላይ የግብርና፣ ምግብ ማቀነባበሪያ፣ የምግብ ግብዓት ንጥረነገሮች፣ ፕላስቲክ፣ ህትመትና ማሸጊያ ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም  መፍትሄዎች ይቀርባሉ ተብሏል፡፡
የንግድ ትርኢቱ አዘጋጆች ባለፈው ሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም  በስካይ ላይት ሆቴል ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
አዘጋጆቹ በመግለጫው ላይ እንደጠቆሙት፤ በንግድ ትርኢቱ ላይ  ከ16 አገራት የተውጣጡ  130 ድርጅቶች የሚሳተፉ ሲሆን  አገራቱም ኢትዮጵያን ጨምሮ ኦስትሪያ፣ ቡልጋሪያ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ህንድ፣ ጣሊያን፣ ዮርዳኖስ፣ ኬንያ፣ ኮሪያ፣ ኩዌት፣ ኔዘርላንድስ፣ ታይዋን፣ ታይላንድና ቱርክ ናቸው፡፡ ትርኢቱን ከ3ሺ  በላይ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በንግድ ትርኢቱ ላይ ከቻይና የመጡ ከ60 በላይ ኩባንያዎች የሚሳተፉ  ሲሆን፤ ከኩዌት የመጡ  8 ድርጅቶችም ተሳታፊ  እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡
“በኩዌት አምርቱ” የንግድ ትርኢቱ  የወርቅ ስፖንሰር  ነው ተብሏል፡፡  
5ኛው አግሮፉድ ፕላስትፕሪንትፓክ ኢትዮጵያ ዓለማቀፍ የንግድ ትርኢት የተዘጋጀው፣  በጀርመኑ የንግድ ትርዒት ስፔሽያሊስት ፌር ትሬድ መሴ እና በኢትየጵያው አጋሩ  ፕራና  ኢቨንትስ ትብብር ነው፡፡

Page 1 of 646