Administrator

Administrator

ገነት ንጋቱ የኪነጥበበ ፕሮሞሽን እና ፊልም ፕሮዳክሽን በደራሲና አዘጋጅ ገነት ንጋቱ የተሰራውን “ሐማርሻ” ፊልም እንደሚያስመርቅ አስታወቀ። ድርጊታዊ የሆነው የ95 ደቂቃ የቤተሰብ ፊልም ተሠርቶ እስኪጠናቀቅ አንድ ዓመት ወስዷል፡፡ ግንቦት 18 በአዲስ አበባ የግል ሲኒማ ቤቶች በማግስቱ ግንቦት 19 ከምሽቱ 11 ሰዓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር በሚመረቀው ፊልም ላይ ገነት ንጋቱ፣ ተዘራ ለማ፣ ካሌብ አርአያስላሴ፣ ዘላለም ይታገሡ፣ ምስራቅ ታዬ እና ሌሎችም ተውነዋል፡፡

በዮሐንስ ሞላ የተደረሱ ሰባ ሁለት ግጥሞች የተካተቱበት “የብርሐን ልክፍት” የግጥም መጽሐፍ ከትናንት ወዲያ ተመረቀ፡፡ ከቀኑ 11 ሰዓት በዋቢ ሸበሌ ሆቴል የተመረቀው ባለ 107 ገፅ መጽሐፍ ለሀገር ውስጥ ገበያ በ28 ብር ለውጭ ሀገራት ደግሞ በ18 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡

ዱም ሚዲያና ፕሮሞሽን ወርሃዊ የሥነ ጽሑፍ ምሽቱን ትናንት አቀረበ፡፡ ከምሽቱ 11 ሰዓት “ብእር በዜማ” በሚል ርእስ በአምባሳደር መናፈሻ የቀረበው ወርሃዊ የሥነጽሑፍ ምሽት በከረምቤ ባሕላዊ የሙዚቃ ቡድን ጣእመዜማዎች የታጀበ ነው፡፡ በምሽቱ አልአዛር ሳሙኤል፣ ምልዕቲ ኪሮስ፣ ሰለሞን ሰሀለ፣ ሰናይት አበራ፣ ገነት አለባቸው፣ አንዱዓለም አሰፋ፣ እንድርያስ ተረፈ እና ሌሎች የሥነጽሑፍ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡

‹መለስ ዋንጫ› በሚል መታሰቢያ በሚደረገው የ2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ደደቢት ለመጀመርያ የሻምፒዮናነት ክብሩ እየገሰገሰ ነው፡፡ ደደቢት ፕሪሚዬር ሊግን መሳተፍ ከጀመረ ዘንድሮ ገና በአራተኛው የውድድር ዘመኑ ላይ ቢሆንም ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት በዋንጫ ተፎካካሪነት በደረጃ ውስጥ ቆይቷል፡፡ ሊጠናቀቅ ከ2ወር ያነሰ እድሜ በቀረውና 14 ክለቦችን በሚያሳትፈው ሊግ ደደቢት ባደረጋቸው 20 ጨዋታዎች 43 ነጥብ እና 23 የግብ ክፍያ በመያዝ ይመራል፡፡ ከተመሰረተ 16ኛ ዓመቱን የያዘው ደደቢት ባለፈው የውድድር ዘመን በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን ዘንድሮ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ ተሳታፊ ሆኖ እስከ ሁለተኛ ዙር መገስገስ የቻለ ነው፡፡ ደደቢት በውድድር ዘመኑ እስከ ባለፈው ሳምንት ባደረጋቸው 20 ጨዋታዎች በ13 ሲያሸንፍ፤ በአራት አቻ ተለያይቶ እና በ3 ተሸንፎ በተጋጣሚዎቹ ላይ 43 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡

ታዳጊ ህፃናትን በማሰልጠን ከ16 ዓመት በፊት የተጀመረው ክለቡ ገና በወጣትነት እድሜው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱ ሲታወቅ በቀጣይ የውድድር ዘመን በኩባንያ ደረጃ ራሱን ችሎ ለመንቀሳቀስ እየሰራ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ውስጥ የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን አሸንፎ በዓለም ክለቦች ዋንጫ ላይ አፍሪካን ለመወከል ራእይ የያዘው ደደቢት በኢትዮጵያ ክለቦች ከፍተኛ ውድድር ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት በሻምፒዮናነት ፉክክር ከሚጠቀሱት 3 ክለቦች አንዱ ሲሆን ለወቅቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እስከ 9 ተጨዋቾች በማስመረጥም ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ በ2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና በ37 ነጥብ እና በ17 የግብ ክፍያ 2ኛ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ34 ነጥብ እና 10 የግብ ክፍያ እንዲሁም ሃዋሳ ከነማ በ33 ነጥብና በ8 የግብ ክፍያ 3ኛ እና 4ኛ ደረጃን አከታትለው ይዘዋል፡፡

ኢትዮፉትቦል ድረገፅ በዘንድሮው ውድድር ማን ሻምፒዮን ሊሆን ይችላል በሚል ከ13521 አንባቢዎቹ በሰበሰበው ድምፅ ኢትዮጵያ ቡና 60.79 በመቶ ድርሻ በመያዝ የመጀመርያውን ግምት ሲወስድ፤ ጊዮርጊስ በ27 በመቶ፤ መብራት ሃይል በ7.2 በመቶ፤ አርባምንጭ በ2.66 በመቶ እንዲሁም ደደቢት በ1.83 በመቶ የድምፅ ድርሻ በተከታታይ ደረጃ የሻምፒዮናነት ግምት ወስደዋል፡፡ ደደቢት በቀሪ የሊግ ጨዋታዎች ያለሽንፈት መጓዙ በታሪክ የመጀመርያውን የሻምፒዮንነት ዋንጫ የሚያነሳበትን እድል ይፈጥርለታል፡፡ በኢትዮጵያ ከፍተኛው የክለቦች ውድድር በፕሪሚዬር ሊግ ደረጃ መካሄድ ከጀመረ ዘንድሮ 66ኛ ዓመቱን የያዘ ሲሆን 16 ክለቦች የሻምፒዮናነት ክብር አጣጥመዋል፡፡

ከእነዚህ ክለቦች ለ25 ጊዜ ሻምፒዮን በመሆን የከፍተኛ ውጤት ክብረወሰን የያዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡ የቀድሞው መቻል ክለብ በ11 ጊዜ ሻምፒዮናነት ሁለተኛ ደረጃ ሲይዝ፤ ጥጥ 5 ጊዜ፤ የአስመራው ሃማሴን 4 ጊዜ፤ መብራት ኃይልና ቴሌ 3 ጊዜ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና፤ ሲምንቶ እና ሃዋሳ ከነማ እያንዳንዳቸው ሁለት ጊዜ የኢትዮጵያ ሊግ ውድድር ሻምፒዮን በመሆን ከ3 እስከ 6 ያለውን የውጤታማነት ደረጃ ይዘዋል፡፡ በፕሪሚዬር ሊጉ ታሪክ እያንዳንዳቸው አንድ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን የበቁ ሰባት ክለቦች የሚጠቀሱ ሲሆን እነሱም የብሪቲሽ ሚሊታሪ ሚሽን፤ ርምጃችን፤ ቀይባህር፤ ምድር ባቡር፤ ኦጋዴን አንበሳ፤ ኦሜድላ እና ትግል ፍሬ ናቸው፡፡ ደደቢት የዘንድሮውን ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮናነት ከወሰደ የኢትዮጵያ ሊግ ሻምፒዮን ለመሆን 17ኛው ክለብ አንዴ ሻምፒዮን ከሆኑ ክለቦች ደግሞ ስምንተኛው ይሆናል፡፡ የ2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ‹መለስ ዋንጫ› ላይ በወራጅ ቀጠና አራት ክለቦች ይገኛሉ፡፡ በ4 ነጥብና በ35 የግብ እዳ 14ኛውንና የመጨረሻውን ደረጃ የያዘው ውሃ ስራዎች መውረዱ ሲረጋገጥ፤ 11 ነጥብ እና 17 የግብ እዳ አስመዝግቦ በ13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከነማም አጣብቂኝ ውስጥ ነው፡፡ ሃረር ቢራ በ19 ነጥብ እና በ11 የግብ እዳ 11ኛ፤ ሙገር በ17 ነጥብ በ12 የግብ እዳ 12ኛ ደረጃ ላይ በመሆን በወራጅ ቀጠናው እየዳከሩ ናቸው፡፡

ከአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ከ2ኛ ዙር ማጣርያ የመልስ ጨዋታ በኋላ የተሰናበተው ቅዱስ ጊዮርጊስ በኮንፌደሬሽን ካፕ የ16 ክለቦች ጥሎ ማለፍ የመጀመርያ ጨዋታ ነገ በአዲስ አበባ ስታድዬም የግብፁን ክለብ ኢኤንፒፒአይ ያስተናግዳል፡፡ ጊዮርጊስ በኮንፌደሬሽን ካፑ ጥሎ ማለፍ የመጀመርያ ጨዋታውን በሜዳው ሲያደርግ ተጋጣሚውን በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፉ በመልሱ ጨዋታ ከሜዳ ውጭ ሲጫወት የማለፍ እድሉን ያጠናክርለታል፡፡ ጊዮርጊስ ከግብፁ ክለብ ኢኤንፒፒአይ ጋር በአፍሪካ ደረጃ ሲገናኝ የነገው ግጥሚያ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን ሁለቱ ክለቦች በ2006 እኤአ ላይ በሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመርያ ዙር በደርሶ መልስ ሁለት ጨዋታዎች ተገናኝተው ነበር፡፡

ያኔ የመጀመርያው ጨዋታ ካይሮ ላይ ተደርጎ ያለምንም ግብ አቻ የተለያዩ ቢሆንም በመልሱ ጨዋታ ጊዮርጊስ በሜዳው ኢኤንፒፒአይን 1ለ0 አሸንፎ ወደ ሁለተኛ ዙር ለመሸጋገር ችሏል፡፡ ነገ ከኢኤንፒፒአይ ከሚያደርገው ፍልሚያ በፊት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከግብፅ ክለቦች ጋር 9 ጊዜ ተገናኝቶ 2 ድል ኦምስት አቻ እና 2 ሽንፈት ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡

10 ጎሎች አግብቶ 7 ተቆጥሮበታል፡፡ በአፍሪካ የክለብ ውድደሮች የግብፅ 7 ክለቦች ከ5 የኢትዮጵያ ክለቦች ጋር 23 ግጥሚያዎች ላይ ተገናኝተዋል፡፡ በእነዚህ 21 ግጥሚያዎች የግብፅ ክለቦች ከኢትዮጵያዎቹ አቻቸው ጋር ተጋጥመው 8 ጊዜ ሲያሸንፉ፤ በ11 አቻ ተለያይተው በ4 ተሸንፈዋል፡፡ 39 ጎሎች አግብተው 18 ጎሎችን አስተነማግደዋል፡፡ ከኢትዮጵያ 5 ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ ኢትዮጵያ ቡና ባንኮች፤ ደቢት እና መቻል ጋር የተገናኙት 7 የግብፅ ክለቦች ዛማሌክ፤ ሳዋህል፤ አልሃሊ፤ ኢትሃድ፤ሜክዋሊን፤ ኢኤንፒፒአይ እና ኦሎምፒክ ነበሩ፡፡

በ2012 -13 የውድድር ዘመን የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ዛሬ እና ነገ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቁ በየሊጐቹ የሻምፒዮናነት ፉክክሩ ብዙም አጓጊ ያልነበረ ቢሆንም የታየው የገቢ መነቃቃት የአውሮፓ እግር ኳስ ትርፋማነትን አሳይቷል፡፡በስፖንሰርሺፕ እና በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚገኙ ገቢዎች መሟሟቅ የተጨዋቾች የደሞዝ ክፍያ እና የዝውውር ገበያውን ሂሳብ እያሳደገ ነው፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ማን ዩናይትድ በውድድሩ የተሳትፎ ታሪኩ 20ኛውን ፤ በስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ ባርሴሎና በውድድሩ የተሳትፎ ታሪኩ 22ኛውን፤ በጀርመን ቦንደስ ሊጋ ባየር ሙኒክ በውድድሩ የተሳትፎ ታሪኩ 23ኛውን፤ በጣሊያን ሴሪኤ ጁቬንትስ በውድድሩ የተሳትፎ ታሪኩ 29ኛውን እንዲሁም በፈረንሳይ ሊግ 1 ፓሪስ ሴንትዠርመን በውድድሩ የተሳትፎ ታሪኩ 3ኛውን የሻምፒዮናነት ክብራቸውን አግኝተዋል፡፡ አምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ዘንድሮ በተለይ በማልያ ስፖንሰርሺፕ ገቢ እና በቴሌቭዥን የስርጭት መብት የሚያገኙት ገቢያቸው ጨምሯል፡፡ በውድድር ዘመኑ ከማልያ ስፖንሰርሺፕ አምስቱ ምርጥ ሊጎች በድምሩ እስከ 315 ሚሊዮን ፓውንድ ሰብስበዋል፡፡

ከዚሁ ገቢ በሚወዳደሩበት 20 ክለቦች 11 የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያዎችን ያሰራው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በ117.3 ሚሊዮን ፓውንድ ገቢ የአንበሳውን ድርሻ ወስዷል፡፡ በቴሌቭዥ ንስርጭት መብት ደግሞ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ለቀጣዮቹ 3 የውድድር ዘመናት 6 ቢሊዮን ፓውንድ ለማግኘት ውሉን ሲያድስ የጀርመኑ ቦንደስ ሊጋም በተመሳሳይ ወቅት 2.5 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ለመሰብሰብ እንደተዋዋለ ታውቋል፡፡

በአንድ የውድድር ዘመን በሚያስገኘው የገቢ መጠን ከአውሮፓ አምስት ታላላቅ ሊጎች የሚመራው የእንግሊዙ ፕሪሚዬር ሊግ ከ2.11 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ በመሰብሰብ ነው፡፡ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ ደግሞ በየዓመቱ 1.40 ቢለዮን ፓውንድ ገቢ እየሰራ ሁለተኛ ደረጃ አለው፡፡ የስፔኑ ላሊጋ 1.37 ቢሊዮን ፓውንድ፤ የጣሊያኑ ሴሪኤ 1.29 ቢሊዮን ፓውንድ እንዲሁም የፈረንሳዩ ሊግ 1 በ900 ሚሊዮን ፓውንድ ዓመታዊ ገቢ በማስመዝገብ ተከታታይ ደረጃ አላቸው፡፡

በውድድር ዘመኑ በስታድዬም ተመልካች ብዛት ግንባር ቀደሙ የጀርመን ቦንደስሊጋ ሲሆን የሊጉ አንድ ጨዋታ በአማካይ የሚያገኘው የተመልካች ብዛት 42429 ነው፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 35903 ፤ የስፔን ላሊጋን 29353፤ የጣሊያን ሴሪኤ 24752 እንዲሁም የፈረንሳይ ሊግ1 19168 ተመልካችን ብእያንዳንዱ ጨዋታ በአማካይ ያገኛሉ፡፡ የእንግሊዙ ፕሪሚዬር ሊጉ ነገ ሲገባደድ በተመሳሳይ ሰዓት የሚደረጉ ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች ይጠበቃሉ፡፡

ጨዋታዎቹ በ3ኛ ደረጃ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ማጣርያን ተሳትፎ ለማግኘት በአንድ ነጥብ ተበላልጠው ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትን አርሰናልና ቶትንሃም የሚያተናንቁ ናቸው፡፡ ቶትንሃም ከሊጉ ላለመውረድ የሚጫወተውን ሰንደርላንድ ሲገጥም ኒውካስትል ዩናይትድ ከአርሰናል ይገናኛል፡፡ በጣሊያን ሴሪኤ ሲዬና ከሚላን በሚያደርጉት ጨዋታም የሻምፒዮንስ ሊግ እጣ ይወሰናል፡፡ ኤሲ ሚላን በባላቶሊ እየተመራ በሴሪኤው ሶስተኛ ደረጃ ይዞ ለመጨረስ ከባድ ፈተና ይገጥመዋል፡፡ በስፔን ላሊጋ በ እስከ አራት ባለው የሊጉ ደረጃ ለመጨረስ ሁለት ፍልሚያዎች ይጠበቃሉ፡፡በእነዚህ ጨዋታዎች ጌታፌ ከቫሌንሽያ እንዲሁም ሲቪያ ከሪያል ሶሲየዳድ ይገናኛሉ፡፡ በጀርመን ቦንደስ ሊጋ ፍራይበርግ ከሻልካ 4 ዛሬ ይጫወታሉ፡፡

  • በሰብ ሰሃራ አፍሪካ በጥንዶች መካከል በአማካኝ እስከ 15ኀ በመቶ የሚሆኑት የኤችአይቪ ውጤታቸው የተለያየ ሆኖ ይገኛል፡፡
  • በብዙ ጥናቶች እንደሚታየው ሴቶች 60 ወንዶቹ 40 ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ሆነው ይገኛሉ፡፡
  • ሳይንቲስቶችንም ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ጥንዶች ውጤታቸው አንዳቸው ፖዘቲቭ አንዳቸው ደግሞ ኔጌቲቭ ይሆናሉ፡፡

በዚህ እትም ለንባብ የበቃው የአንድ ተሳታፊን ጥያቄ መሰረት ያደረገ ጉዳይ ነው፡፡ ለጥያቄው ማብራሪያ እንዲሰጡ የጋበዝናቸው ዶ/ር እያሱ መስፍን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ፋክልቲ መምህር እና የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ቀጥሎ የምታነቡት ተሳታፊዋ የላኩትን ጥያቄ ነው፡፡ ውድ ኢሶጎች... .....እኔ ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭ ስሆን ባለቤ ግን ኔጌቲቭ ነው፡፡እኔ እስከአሁን ድረሰ ምንም የኤችአይቪ መድሀኒት ተጠቃሚ አይደለሁም ፡፡ የግብረስጋ ግንኙነት የምንፈጽመውም በኮንዶም ነው፡፡ ነገር ግን ልጅ ለመውለድ በጣም ስላማረኝ አንድ ነገር አሰብኩ፡፡ ይኼውም ከግንኙነት በሁዋላ በኮንዶም ውስጥ ያለውን የዘር ፈሳሽ ባለቤ ወደእኔ ማህጸን ውስጥ እንዲያፈሰው እና ማርገዝ እንድችል ነው፡፡

ነገር ግን የፈለግነውን ነገር ከማከናወናችን በፊት መጠየቅ የምፈልገው... በጠቆምኩት መንገድ ሙከራ ብናደርግ ልጅ ማርገዝ እችላለሁ? ልጅ ማርገዝ ብችልስ ምን ያህል ጤናማ ይሆናል? ልጅ ከአረገዝኩ በሁዋላ የፀረ ኤችአይቪ መድሀኒት ተጠቃሚ መሆን ይጠበቅብኛል? ለእነዚህ ጥያቄዎች እና ተያያዥ ለሆኑት ሁሉ መልስ እንደማገኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ .. ዶ/ር እያሱ መስፍን ከአሁን ቀደም ለዚሁ እትም የባለትዳሮችን በኤችአይቪ ቫይረስ ውጤት መለያየት በሚመለከት መልስ ሰጥተዋል፡፡ .....ከጥንዶች ወይም ከባለትዳሮች መካከል አንዳቸው ፖዘቲቭ ሌላኛው ደግሞ ኔጌቲቭ በመሆን የኤችአይቪ ውጤት መለያየት ሲኖር በእንግሊዝኛው ዲስኮርዳንስ ይባላል፡፡ይህ በአሁኑ ጊዜ በጥንዶች መካከል ቁጥሩ እየጨመረ የመጣ ነው፡፡

በተለይም በሰብ ሰሃራ አፍሪካ በጥንዶች መካከል በአማካኝ እስከ 15ኀ በመቶ የሚሆኑት የኤችአይቪ ውጤታ ቸው የተለያየ ሆኖ ይገኛል፡፡ ጥንዶች በጋር እየኖሩ የተለያየ ውጤት የሚኖርበት ምክን ያት የተለያየ ነው፡፡አንዱ በቅርብ ጊዜ የተጋቡ ከሆኑ ወይንም አንዱ ፖዘቲቭ ሆኖ ገና ወደሌላው እስኪተላለፍ በሚወስደው ጊዜ ምክንያት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለረጅም ጊዜ በትዳር አብረው እየኖሩም አንዱ ፖዘቲቭ ሌላው ደግሞ ኔጌቲቭ የመሆን ነገር ይታያል፡፡ በኤችአይቪ የመያዝ ሁኔታ ከሰው ሰውም ይለያያል፡፡ አንዳንዶች በቫይ ረሱ ያለመያዝ ሁኔታ ሲታይባቸው ሌሎች ደግሞ ቶሎ የመያዝ ሁኔታ ይኖራቸዋል፡፡ እንደገናም በደም ውስጥ ያለው የቫይረስ መጠንም ቁጥሩ ከፍ ያለ ከሆነ ወይንም ብዙ ቆይቶ ብዙ የተጎዳ ከሆነ ለመተላለፍ ከፍ ያለ እድል ይኖረዋል፡፡

የኤችአይቪ መድሀኒት ሙሉ በሙሉ በትክክል የሚወስዱ ሆነው ነገር ግን ሳይከላከሉ ወይንም በኮንዶም ሳይ ጠቀሙ የወሲብ ግንኙነት የሚያደርጉ ከሆነ አሁንም ቫይረሱ የመተላለፍ እድል ይኖረ ዋል፡፡ ነገር ግን በተለያዩና በማይታወቁ ምክንያቶች ለሳይንቲስቶችም ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ጥንዶች አንዳቸው ፖዘቲቭ አንዳቸው ደግሞ ኔጌቲቭ ሆነው አብረው ይኖራሉ፡፡ አብረው በሚኖሩ ጥንዶች በአማካኝ ከአንድ መቶ እስከ ሁለት መቶ ግንኙነት ውስጥ በአንዱ ኤችአይቪ ቫይረስ እንደሚተላለፍ ይገመታል፡፡ ስለዚህም ጥንዶች ምንም ኮንዶም የማይጠቀሙ ከሆነ በአመቱ መጨረሻ ከመቶው አስሩ በቫይረሱ ሊያዙ ይችላሉ፡፡ ይህን ንም ለመከላከል በማንኛውም ጊዜ በወሲብ ግንኙነቱ ወቅት ኮንዶም እንዲጠቀሙ ግድ ነው፡፡..... ኢሶግ፡ የዘር ፈሳሽን ከኮንዶም ወደማህጸን በማስገባት ማርገዝ ይቻላልን? ዶ/ር ኢያሱ፡ ይህ ጥያቄ የብዙዎች ከኤችአይቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ጥያቄ ነው፡፡

የወንድ የዘር ፍሬ መቅስቈቂ ሰስቁቁ በተፈጥሮው ጭራ ያለው መዋኘት ወይንም መንቀሳቀስ የሚችል ነው፡፡ ስለዚህም ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረለት ካለበት ስፍር ዋኝቶ በመንቀሳቀስ እርግዝና እንዲፈጠር ያስችላል፡፡ ለምሳሌ ሙሉ በሙሉ ወሲባዊ ግንኙነት ሳይፈጸም ወይንም ክብረንጽህና ሳይገሰስ በብልት አካባቢ የዘር ፈሳሹ በመፍሰሱ ብቻ እርግዝና የሚከሰትበት አጋጣሚ አለ፡፡ ስለዚህ በኮንዶም ውስጥ የፈሰሰ የዘር ፈሳሽ ወደማህጸን የሚገባበት አጋጣሚ ከተፈጠረ ማርገዝ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ወደ ጠያቂዋ ሁኔታ ስንመለስ ወሲባዊ ግንኙነት የምትፈጽመው በኮንዶም ሲሆን ኮንዶም የተዘጋጀው ደግሞ ባብዛኛው እርግዝ ናን ለመከላከል ሲሆን በሚሰራበት ጊዜ በወንድና በሴት ዘር መካከል እንዳይገናኙ እንደግድግዳ ከመከላከል በተጨማሪ የሚጨመርበት የኬሜካል ውሁድ አለ፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች የወንዱን የዘር ፍሬ መዋኘት እንዳይችል ወይንም እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ አቅሙን የማዳከም ስራ ይሰራሉ፡፡

ስለዚህ በዚህ መልክ የተጠራቀመው የዘር ፈሳሽ ውጤታማ ላይሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ ማርገዝ ከተቻለ በሚረገዘው ልጅ ጤና ላይ ምንም የሚያስከትለው ጉዳት ወይንም የጤና ችግር የለም፡፡ ኢሶግ፡ የወንድም ይሁን የሴት የዘር ፍሬ ከፈሰሰ በሁዋላ ምን ያህል የቆይታ እድሜ ይኖረዋል? ዶ/ር ኢያሱ፡ የወንድና የሴት የዘር ፍሬዎች ቆይታ ይለያያል፡፡ ከግንኙነት በሁዋላ የወንዱ የዘር ፈሳሽ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በመዋኘት ከማህጸን በር አልፎ ከማህጸን ቱቦ ይደርሳል፡፡ ሁኔታዎች ለመቆየት ከተመቻቹለትም እስከ 72/ሰአት ድረስ ቆይታ ያደርጋል፡፡ የሴቷ የዘር ፍሬ ግን ሁኔታዎች በተሙዋሉበት ከ24-48 ሰአት ድረስ ብቻ መቆየት ይችላል፡፡ ኢሶግ፡ አንዲት ሴት በኮንዶም የተጠራቀመ የዘር ፈሳሽን ወደ ማህጸን በግልዋ ማስገባት ትችላለች? ዶ/ር ኢያሱ፡ የዘር ፈሳሽን ወደማህጸን ማስገባት የሚል አሰራር በግለሰብ ደረጃ የለም፡፡ ምናልባትም ሰዎች የተፈጥሮን አቀማመጥ ካለመረዳት የሚያስቡት ሊሆን ይችላል፡፡

በመጀመሪያ ብልት አለ፡፡ ከዚያም የማህጸን በር ይገኛል፡፡ ከዚያ በሁዋላ የማህጸን ቱቦ ጋ ደርሶ ፈሰሽን ማስገባት ሲቻል ነው እርግዝና ይኖራል የሚባለው፡፡ ብዙዎች የሚያስቡት ልክ ከብልት ቀጥሎ የሚያገኙትን አካል ማህጸንን እንደሚያገኙ አድርገው ከሆነ ስህተት ነው፡፡ ከማህጸን ቱቦ መድረስ የሚቻለው ክኒካል በሆነ የህክምና አሰራር እንጂ በግል አይደለም፡፡ በእርግጥ የወንድ የዘር ፈሳሽ በብልት እና በማህጸን በር አካባቢ በመፍሰሱ ብቻ የመቆየት እድሉን ካገኘ እራሱ ዋኝቶ እርግዝና እንዲከሰት የሚያደርግበት አጋጣሚ ስለሚስተዋል ይህንን እድል መጠቀም ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሊታወቅ የሚገባው የምንጠቀምባቸው ኮንዶሞች ፀረ ስፐርም ያልሆኑና የማያዳክሙ አይነት መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ኢሶግ፡ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወይንም የተለያየ ውጤት ያላቸው ሰዎች ልጅ ለመውለድ ምን ማድረግ አለባቸው? ዶ/ር ኢያሱ፡ ይህንን ፍላጎት ለማሟላት ብዙ መፍትሔዎች አሉ፡፡ ወሲባዊ ግንኙነት ከኮንዶም ውጪ ከተደረገ ከአንዱ ሰው ወደሌላው እንዲሁም ወደሚረገዘው ልጅ ቫይረሱ መተላለፉ እርግጥ ነው፡፡

ነገር ግን ይህንን የመተላለፍ እድል ለመቀነስ መደረግ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የቫይረሱ መጠን በሰውነትዋ ውስጥ አድጎ ከሆነ ወይንም የመከላከል አቅሙዋ ቀንሶ ከሆነ የፀረ ኤችአይቪ መድሀኒት በመውሰድ በደምዋ ውስጥ የሚገኘውን የቫይረስ መጠን እንዲቀንስ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም አንዳቸው ለሌላኛው የሚያስተላልፉትን ቫይረስ ከመቀነስ ባሻገር ጤነኛ ልጅ ለመውለድ ያስችላቸዋል፡፡ በእርግጥም ቫይረሱ የመተላለፉን አደጋ ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል ባይባልም እጅግ ይቀንሰዋል፡፡ ስለዚህ ወደሕክምናው በመሄድ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠቅማል፡፡ የፀረ ኤችአይቪ መድሀኒቱን ወስዶ በደም ውስጥ ያለውን ቫይረስ መቀነሱ ከታወቀ በሁ ዋላ የወር አበባ ቀንን በመቁጠር ማርገዝ በሚቻልባቸው ቀናት ብቻ ያለኮንዶም ግንኙነት ማድረግ እንደ አንድ አማራጭ ሊያዝ ይችላል፡፡ ይህ ግን ውስን ለሆነ ቀን እንደመጨረሻ አማራጭ የሚወሰድ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

በእኛ አገር ባይኖርም ባደጉ አገሮች እንደ አማራጭ ከሚወሰዱ መንገዶች መካከል የወንድ የዘር ፍሬ ተወስዶ በማሽን የሚታጠብበት ነው፡፡ የወንዱ የዘር ፍሬ ከቫይረሱ ከጸዳ በሁዋላ በመርፌ ወደ ሴቷ ማህጸን እንዲገባ በማድረግ ልጅ መውለድ የሚቻልበት መንገድ አለ፡፡ በአጠቃላይ ግን ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩም ሆኑ ማንኛውም ሰው እርግዝናን ሲያስብ አስቀድሞ ሐኪምን ማማከር እንደሚገባ መዘንጋት የለበትም፡፡

ዴሞስቴን የተባለ የግሪክ ደስኳሪ፣ በታሪክ አንደበተ-ርቱዕ ከሚባሉት አንዱ ተደናቂ ፈላስፋ ነው! ዴሞስቴን አያሌ ጊዜ ለአቴና (ግሪክ) ህዝብ ንግግር አድርጓል፡፡ ንግግሩ ተደማጭ ይሆን ዘንድ አንደበቱን ለመግራት፣ ምላሱን ለማስላት፣ ወንዝ ወርዶ ከምላሱ ሥር ጠጠር እያደረገ ከወንዙ ጅረት ጋር የሚፎካከር የጩኸት ድምጽ በማውጣት የአንደበት አቅሙን አካብቷል፡፡ እንግዲህ፤ ዴሞስቴን በተደጋጋሚ የአቴና ህዝብ ወራሪዎች እየመጡበት መሆኑን ተናግሮ የሚሰማው አጥቷል፡፡

በመጨረሻም፤ ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ሄዶ መድረኩ ላይ ወጥቶ መናገር ጀመረ፡፡ “አንድ ተረት ብነግራችሁ ለመስማት ዝግጁ ናችሁ?” ሲል ጠየቀ፤ ደስኳሪው ዴሞስቴን፡፡ “አዎ!” አለ ህዝቡ፡፡ (ተረት የማይማርከው ህዝብ የለም፡፡) “አንድ አህያ የሚያከራይ ሰው ነበር” ሁላቸውም ጆሮአቸውን ወደ ባለ አህያውና አህያው ታሪክ አቀኑ፡፡

“አንድ አህያ ተከራይ መጥቶ፤ የበረሃ ጉዞ ስላለብኝ፤ አህያህን አከራየኝ?” አለው ለባለአህያው፡፡

“እሺ፤ እንስማማ?!”

አለው አከራይ፡፡ ተስማሙና አህያውን ይዞ ሄደ፡፡ በነጋታው የበረሃ መንገዱን ተያያዘው፡፡ እንዳጋጣሚ የአህያው አከራይም ወደዚያው በረሃ ይሄድ ኖሮ መንገድ ላይ ተገናኙ፡፡ አብረው መጓዝም ቀጠሉ፡፡

ቀትር ላይ ደከማቸውና ጭው ባለ በረሃና ቃጠሎ፤ ሆጨጭ ባለው አሸዋ ላይ እረፍት አደረጉ፡፡ በአህያዋ ጥላ ሥር የተከራየው ሰው አረፍ አለ፡፡ ይሄኔ ባለ አህያው፤ “አህያዋን እንጂ ጥላዋን አላከራየኸኝም ተነስ” አለና ሙግት ጀመረ፡፡ ተከራዩ ደግሞ፤ “አህያዋን ስከራይ በአህያዋ በኩል የሚመጣ ጥቅም ሁሉ የእኔ ነው” አለ፡፡ ሙግቱ ተፋፋመ፡፡

ዴሞስቴን ወደ ህዝቡ ዞሮ፤ “እህስ፤ ጥላው የማነው?” ሲል ይጠይቃል፡፡ ከፊሉ ህዝብ፤ “የባለ አህያው ነው!” ሲል ጮኸ፡፡ ከፊሉ “የተከራዩ ነው!” ሲል ጩኸቱን አሰማ፡፡ ከፊሉ ደግሞ፤ “አዲስ ድርድር ያሻል!” አለ፡፡ ከፊሉ፤ “ዳኛ ጋ ይሂዱ!” አለ፡፡ ይሄኔ ዴሞስቴን፤ “የአቴና ህዝብ ሆይ! አሳሳቢውን የሀገራችንን መወረር ነገር ስነግራችሁ ጆሮአችሁን አልሰጥ አላችሁኝ፡፡ የአንዲት አህያ ጥላ ታሪክ ግን ይህን ያህል አጯጯሃችሁ! እጅግ ታሳዝናላችሁ!”

ብሏቸው ሄደ፡፡ ህዝቡም፤ “ታሪኩን ጨርስልን! መጨረሻቸው ምን ሆነ?”

እያለ ጩኸቱን ቀጠለ፡፡ ዴሞስቴን ግን መንገዱ ቀጠለ፡፡

                                                         * * *

የምንጮህበትን እንወቅ፡፡ የሀገር ጉዳይ፣ የሥርዓቱ ጉዳይ፣ የፓርቲ ህግጋትና አካሄድ ጉዳይ፤ ምኑ ቅጡ … ትላልቁ ስዕል እያለ፤ በትናንሽ የካርቱን ስዕሎች መታለል የለብንም፡፡ ከዚያ ይሰውረን! ሥጋታችን፤ የሥልጣን ገዋ (Power vacuum) እንዳይፈጠር እንጂ፤ የሰው ገዋማ ችግር የለም፡፡ ማንም ይተካል፡፡ የተንሳፈፈ የፖለቲካ አቅጣጫ፤ አሳሳቢ ነው፡፡ በጥቃቅን ነገር ላይ እንድናተኩር ያደርጋል፡፡ ያዘናጋል፡፡ በማናቸውም ዕምነት ላይ አምላኪ እንድሆንና እንድናተኩር፣ እንድንጨቃጨቅም ያደርጋል፡፡ ኦባማ፤ “ህዝባችን በሀገር ውስጥ ገቢ ላይ ዕምነቱን እንደገና እንዲያዳብር እናድርግ” አለ አሉ፡፡ ለካ ያሜሪካ ጉዳይ እንደኛ ነው፤ ብንል ማን ይከለክለናል? ግን ያ ተቋም ብቻ ነው ተጠያቂው ሥርዓቱም? ብንልም ያባት ነው፡፡ ከላይ የጠየቅነው ዴሞስቴን የአቴናን ንጉሥ ሲሞግት፤ “በፈቃዱና አውቆ ስህተት የሚሠራ አለን? ያ ከሆነ ሰውየው የሚያናድድና ለቅጣት የሚዳረግ ነው፡፡ ሆነ ብሎ ሳይሆን ሳያውቅ ስህተት ቢሠራስ? እሱ መቀጣት ሳይሆን ይቅርታን ሊያገኝ ይችላል፡፡

ስህተት የፈፀመውም ሆነ ጥፋት የሠራው በሥራው ተመስጦ፣ ካለማስተዋል የተነሣ ቢሆንና ስኬት የእሱ ባትሆንስ?!” በለስ ያልቀናውን ሰው አናዝንበትም፤ አናጠቃውምም፡፡ አብረነው እናዝናለን እንጂ፡፡ ይሄ ሁሉ በእኛ ህግ ጥላ ሥር የሚፈረድ ብቻ አይደለም፡፡ የለም፤ ተፈጥሮ፤ ባልተፃፈ ህግዋ ያስቀመጠችው ነው። ህገ-አዕምሮ የሚዳኘው ነው፡፡ ስለዚህ ኤስፒለስ (ዴሞስቴን በህዝብ ጥያቄ የሽልማት ዘውድ ይጫንለት የተባለውን ሃሳብ የተቃወመው ንጉሥ፣ በእስተዛሬው አገዛዙ፤ በጭካኔውና በግፉ ሰውን ሁሉ በመብለጡ፣ እንደክፉ -ዕጣ ፈንታ የዘረዘራቸውና እኔን የከሰሰባቸው በሙሉ የራሱ መጠየቂያ ናቸው…” ይልና ኦ ደጉ ባለሞገሱ አምላክ ሆይ! እባክህ ምህረትህ አይለያቸው! እነሆ ለእኒህ ሰዎች የተሻለ መንፈስ፣ የተሻለ ስሜት ስጣቸው፡፡

ሆኖም ጨርሶ የማይድኑ ከሆነ፤ እነሱው በእነሱው ላይ በባህርም በየብስም፣ ያለወቅቱ የመጣ መርገምትንና የመንፈስ መንኮታኮትን፤ ይፈርዱ ዘንድ ተዋቸው፡፡ እኛም የተረፍነው በደግነትህ ደህንነት፣ ቸርነትህን ለተጐናፀፍነውና ካሰፈሰፈው መዓት በማያወላውል መልኩ በፈጣሪ እርምጃ እንድን ዘንድ ለታደልነው፤ ከዚህ የማስጠንቀቂያ ደወል በኋላ፤ ፀጋህን አላብሰን፡፡” ስለ ሥርዓት ስናስብ የካምቦዲያው አብየታዊ መሪ ሲሞን ቦሊቫር “በፍፁም ሥልጣን የናጠጡ ገዢዎች ሥር መኖር፤ ለማናቸውም ሹም ያላንዳች ተቃውሞ አሜን ብሎ መኖር ነው፡፡ የጨቋኙ ገዢ ፍቃደ - ልቡና የላዕላይ ህጉ የበታች ሹማምንት እንደልብና በዘፈቀደ በተደራጀ የጭቆና ስልት እንዲበዘብዙ የሚፈቅድላቸው፤ መሆኑን ልብ እንበል ይለናል፡፡

ቦሊቫር፣ ለኮንግሬሱ ባደረገው ንግግር ፓርላማውን ሲያስጠነቅቅም “ነፃነታችንን ማስጠበቅና ማቆየት አዳጋች ነው፡፡ ምክንያቱም አንድም ሦስትም የሆኑት ሦስቱ ዋና ዋና ጠላቶቻችን፣ ማለትም ድንቁርና፣ ጭቆናና ሙስና (Triple yoke of Ignorance, Tyranny and corruption) የህዝቡን ዕድገት ስላቀጨጩት ነው! እንዳሻቸውም ሁሉን እንዲከውኑ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ባርነት የጨለማ ሴት - ልጅ ነው፡፡ ዕውር ህብረተሰብ የገዛ መንኮታኮቱ ዕውር መሣሪያ ነው፡፡ ክፉ ምኞትና ክፉ ሴራ የህዝቡን ዝግጁ አማኝነትና ልምድ - አልባነት በመንተራሱ ጥቅም አካብተውለታል። ከቶውንም የፖለቲካዊ፣ ኢኮኖማያዊ ወይም የሲቪል የመረዳት - አቅም - ማጣት ህዝቡን ለዚህ ዳርጎታል፡፡ ውዥንብሩን፣ ድንግርግሩንና ቅዠቱን ሁሉ ዕውነታ ነው ብሎ ማሰብ፤ ማንኛውንም ዓይነት ሊቼንሣ፤ ከነፃነት ጋር ማምታታት፤ ሀገር መክዳትን በጀግንነት ስም ማወጅ፣ ፍትህን የበቀል ካባ ማልበስ ሆኗል ዘመናዊው ሥልጣኔ፡፡ “ነፃነት”፣ ይላል ሩሶ፤ “እጅግ በጣም ምርጥና ምራቅ የሚያስመጣ ምግብ ያለበት ቢፌ ነው፡፡ ሆኖም ጥሩ አርጐ ፈጭቶ ከሰውነት ለማዋሃድ እጅግ አዳጋች ነው፡፡

ይለናል፡፡ አንድ ዕውቅ - ሌባና አጭበርባሪ ሹም፤ ዴሞስቴንን፣ “ለሊት በሻማ እየፃፈ ቁጭ ብሎ ያድራልና ሊከለከል ይገባል”፤ ሲል ከሰሰው፤ ይባላል፡፡ ዴሞስቴንም፤ “አዎን በቅጡ የማውቀው አንድ ነገር አለ፡- ብርሃን ሁሉ ከአገር ቢጠፋ አንተ ደስታህ ነው፡፡ ለስርቆት የሚመችህ ያኔ ነዋ! እላንት የአቴና ህዝቦች ሆይ! አይግረማችሁ! እስከዛሬ ከታዩት ያገር ካዝና ዘረፋና ሌብነቶች ሁሉ፤ ያሁኑ አያስደንቅም፡፡ ምክንያቱም ሌባው ሁሉ የተሠራው ከነሐስ ነው፡፡ አገሩ የተሠራው ግን ከሸክላ ነው፡፡

ማንኛቸው እንደሚፈርሱ እናንተ ለዩ!” አለ፡፡ ትናንሽ ዕድሎችና ቀዳዳዎች፤ አብዛኛውን ጊዜ የታላላቅ ገንዘብ - ማፍሪያ ኢንተርፕራይዞች ምንጮች (መነሻዎች) ናቸው፡፡ ምንጮቹ የሚደፈኑት ሥርዓቱ አይቷቸው ራሱን ሲመረምር ነው!! ይላሉ ሌሎች ፀሐፍት፡፡ ችግሩ፤ “ሌባው ሁሉ የተሠራው ከንሐስ ነው፡፡ አገሩ የተሠራው ግን ከሸክላ ነው!!” በሼክስፒር ድርሰት ብሩተስና ግብረ-አበሮቹ በህብረት ንጉስ ጁሊየስ ቄሣርን በጩቤ ጠቅጥቀው በገደሉት ወቅት፤ የልብ ወዳጄ የሚለው ብሩተስ እንደወጋው ያየው ሟቹ ቄሣር “አንተም ብሩተስ?

(eftu Brute?) እንዳለው ይታወሳል፡፡ ቀጥሎ ከወጊዎቸ አንዱ ባለሟል የጠየቀውም አይረሴ ነው፡- “ቀጥሎ ምንድን ነው ሥራችን?!” (በገነነ ቃለ-አንክሮና በደም ጉምዥት)

እንዴት ሰነበታቸሁሳ!

ስሙኝማ…እኔ የምለው…የሸሻችሁት ነገር በየቦታው ሲመጣባችሁ አያናድዳችሁም! በተለይ የህዝብ ትራንስፖርት መኪናዎች ውስጥ… አለ አይደል… ሰላም የማይሰጣችሁን ነገር ስትሰሙ… “የት ብሄድ ነው ሰላሜ የማይረበሽብኝ!” አያሰኛችሁም? የምር…ለምሳሌ መስማት የማትፈልጉት የሬድዮ ፕሮግራም አለ እንበል፡፡ ቤት ውስጥ እሱን ፕሮግራም የከፈተ የቤተሰበ አባል እንደ ‘ፐብሊክ ኤነሚ ነምበር ዋን’ ይቆጠራል፡፡ ታዲያላችሁ…የሆነ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ገብታችሁ ቁጭ እንዳላችሁ ያ ፕሮግራም በሰፊው ይለቀቅላችኋል፡፡ “እሱን ፕሮግራም ለውጥ” አትሉት ነገር የሚወዱት ሰዎች እዛው ታክሲ ውስጥ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እናላችሁ በሦስት ብር ከሰባ መንገድ የሠላሳ ሰባት ብር ‘አንታይ አሲድ’ ገዝታችሁ ትገባላችሁ፡፡ ወይ ደግሞ የሆነ የሙዚቃ ካሴት ተከፍቷል፡፡

ታዲያ ካሴቱ ላይ ያሉት ዘፈኖች በሙሉ የሾፌሩ የ‘አገሩ ዘፈኖች’ ይሆናሉ፡፡ እና ሾፌሩ “የአገሬ ለምለም መስክ ታወሰኝ…” ምናምን ታወሰኝ ከሚለው ዘፈን ጋር አብሮ ይዘፍናል፡፡ (ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ያው ሁላችን የትውልድ አካባቢያችንን “ለምለሟ…” “አረንጓዴዋ…” “የምድር ገነት…” ምናምን ማለት እንወዳለን፡፡ ቅልጥ ያለ ‘ሚስኢንፎርሜሽን’ ይላችኋል ይሄ ነው፡፡ አሀ ልክ ነዋ…የአንዳንዶቻችን የትውልድ መንደር ደረቅና አቧራ ከመሆኑ የተነሳ እኮ ዘመዶቻችን አረንጓዴ ቀለምን የሚያወቁት በኢትዮዽያ ባንዲራ ላይ ብቻ ነዋ! ቂ…ቂ…ቂ…) ገንዘባችሁን ከፍላችሁ በምትንቀሳቀሱበት ታክሲ የማትፈልጓቸውን ነገሮች እያቃራችሁም ለመዋጥ ትገደዳላችሁ፡፡ እናማ… አስቸጋሪ ነው፡፡

እናማ በየቦታው ስትሄዱ የሸሻችሁትን ነገር እንድታዩ ወይም እንድትሰሙ ትገደዳላችሁ፡፡ ኮሚኩ ነገር እነኛ ነገሮች ከስፍራው ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም፡፡ አንዳንድ ቦታማ ከሌኒን ቤተመንግሥት በስጦታ መጥተው የተረሱ የሚመስሉ መፈክሮች ግድግዳ ሞልተው ያፈጡባችኋል፡፡ የምር ግራ የሚገባኝ ነገር…ዓለም የወዝ አደሮች መሆኗ ሲቀር (እንክት አድርጐ ነዋ!) የመፈክር ለውጥ አይደረግም እንዴ! (በወዲያኛው ዘመን…“ተፈጥሮን በቁጥጥራችን ስር እናውላለን” የሚለውን መፈክር አራት ኪሎ ተሰቅሎ ሲያዩ “ድንቄም!” ያሉት ሰውዬ ሸቤ ገብተው ነበር ይባላል፡፡ ዘንድሮ “ድንቄም!” የሚያስብሉ መአት መፈክሮች አሉ፡፡ “ድንቄም!” ማለቱ…አለ አይደል…“ደግሞ ከእነማን ጋር ያስፈርጀን ይሆን!” እየተባለ ሁሉም ነገር ‘ሆድ ውስጥ’ ተከርችሞበት ቀረ እንጂ! እናላችሁ…ገንዘባችሁን ከፍላችሁ አገልግሎት የምትፈልጉበት ቦታ ሁሉ የሸሻችሁት ነገር አለቦታው መጥቶ ይደነቀርባችኋል፡፡

ቀሺሙ ምግብ ሁሉ የሙሉ ልብስ ዋጋ በሚያወጣበት በዚህ ዘመን ለመመገብ አንዱ ሬስቱራንት ትገባላችሁ፡፡ የቤቱ ባለቤቶች የፈለጉትን ሙዚቃ እስከጥግ ለቀውታል፡፡ እናንተ ምግባችሁን በሰላም፣ ጭቅጭቅ ምናምን በሌለበት ሁኔታ ነው መብላት የምትፈልጉት፡፡ እናላችሁ… የሆነ “ጉድ ስላደረግሽኝ የእጅሽን አትጪ…” ምናምን የሚል ‘ደምፕ’ ያደረገቻችሁን እንትናዬን (ነው የሚባለው… አይደል!) የሚያስታውስ ዘፈን እያምባረቀ ምግቡ እንዴት ብሎ ከጉሮሮ ይወርዳል! አይደለም አጥንቱ ሊጋጥ፣ አጥሚቱም አይወርድ! ቂ…ቂ…ቂ… ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ ‘ደምፕ’ የመደራረግን ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን ስሙኝማ፡፡ ዘንድሮ ሙሉ ለሙሉ ‘ደምፕ’ መደረግ ቀርቷል አሉ፡፡ እናላችሁ…ነገርዬው እንደ አውሮፓ አሰልጣኞች ነገር ሆኗል አሉ፡፡

አለ አይደል…ማንቺኒ ዘንድሮ ማን ሲቲ፣ ለከርሞ ሞናኮ ደግሞ በሌላኛው እንደገና ማን ሲቲ ሊመጡ ይችላሉ፡ እና በዘንድሮ ግንኙነት “የአገሬ ወፍ ጠራችኝ…” ብላ በዛው ሄዳ የምትቀር እንትናዬ የለችም ይላሉ፡፡ ጨዋታው “የወሰደ መንገድ ያመጣል መልሶ…” አይነት ሆኗል፡፡ የእነ እንትናን ኪስ ይጭነቀው እንጂ ምን ችግር አለ! እናላችሁ…ይሄ የሚኒባሶች ነገር…አርጀት ያሉ ሚኒባሶች ወላ ሬዲዮ፣ ወላ ካሴት ማጫወቻ ስለሌላቸው ይመቹኛል፡፡ ሌሎች የሚታዩ ነገሮች ቢኖሩ የማርሹ እጀታ ተነቅሎ እንዳይወድቅ ጠፍንጎ ያሰረው ፕላስቲክ ገመድ፣ ዳሽ ቦርዱን “ወይ ንቅንቅ!” ብሎ አጣብቆ የያዘው ፕላስተር…የተሰነጠቀው የጎን መስታወት “መለያየትማ የለም!” በሚል መሀል ለመሀል ያያዛቸው የሚያብለጨልጨው አሚር ማጣበቂያ፣ የኋላ ማሳያ መስታወቷን ‘በስቅላት እንደተቀጣች’ አይነት አንጠልጥሎ የያዛት ሲባጎ…ምናምን ናቸው፡፡ የማትፈልጉት “አፈር የፈጨሁብሽ፣ እትብቴ የተቀበረብሽ መንደሬ…ናፍቆትሽ አላስቆም አላስቀምጥ አለኝ…“ምናምን አይነት ‘ሲንቴቲክ’ ዘፈን የለ…(ይሄን የሚዘፍነው ሰው የቅርብ ሞዴሏን ሌከሰስ የሚያሽከረክር እንደሆነ ግንዛቤ ይግባልንማ!) “ሳይከፍል የሚወርድ ባለጌ ነው፣” አይነት ነገር የለ…በቃ ሰላም፡፡ እናላችሁ…በየሄዳችሁበት አካባቢ ሌላ ቦታ የሸሻችሁት ነገር ይገጥማችኋል፡፡

ሠራተኞቹ ከንጉሥነት አልፈው እንደ ንጉሠ ነገሥትነት በሚቃጣቸው መሥሪያ ቤት “ደንበኛ ንጉሥ ነው” የሚል መፈክር ግድግዳ ላይ ተለጥፎ ስታዩ የፈረንሣይ አብዮት አጀማመር ምክንያትን ለማወቅ ላይብረሪ መሄድ ነው የሚያምራችሁ፡፡ ልክ ነዋ…ምናልባትም ያንን አብዮት ያስነሳው ሰው “ደንበኛ ንጉሥ ነው” ተብሎ ግድግዳ ላይ በተሰቀለ መፈክር ስለተሾፈበት የተናደደ ሊሆን ይችላላ! እናላችሁ…በሚኒባስ ታክሲዎች መሄድ የመንገድ ጉዳይ ብቻ መሆኑ ቀርቷል፡፡ እናማ… የተለያዩ እምነቶችን ‘መልእክቶችን’ በተለያዩ አቀራረቦች ወደ እናንተ ይለቀቁላችኋል፡፡ እናማ… እንደ ሹፌሩ እምነት የሚተላልፋላችሁ ‘መልእክት’ ያንኑ አይነት ይሆናል፡፡ የምር ግን አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ ሁሉ ሰው የየራሱ እምነት አለው…መስማት የማይፈልገውን ሊሰማ መገደድ የለበትም፡፡ የምር ግን…ሚኒባስ ታክሲዎችም ሆኑ ሌሎች የህዝብ መጓጓዣዎች የቤተ እምነቶችን ሚና ሲይዙ አሪፍ አይደለም፡፡

(በተደጋጋሚ “እሱን ነገር ዝጋው…” ምናምን በሚባል አተካሮ ችግሮች ሲከሰቱ ተመልክተናል፡፡) እናላችሁ…አንዳንዶቹ በተለያዩ መልኮች የሚቀርቡት መልእክቶች “ወዮልህ! ቀኑ ደርሶልሀል፣ እኛ ዘንድ ካልተጠጋህ…” የሚሉ አይነት ‘ማስፈራሪያዎች’ ናቸው፡፡ የመሥሪያ ቤት የአለቃ “ወዮልህ!…” የቤት ውስጥ የትዳር አጋር “ወዮልህ/ወዮልሽ…” አምልጣችሁ የለየለት “ወዮልህ!... ሚኒባስ ውስጥ ሲገጥማቸሁ አስቸጋሪ ነው፡፡ እናላችሁ…አገልግሎት ፍለጋ በምትሄዱባቸው ቦታዎች የማይመቿችሁን ነገሮች ስታዩ…አለ አይደል…አስቸጋሪ ነው፡፡ ስሙኝማ…ኮንዶሚኒየም የቤት ችግር ለማቃለል አሪፍ ነው፡፡ በርካታ ‘ብሎኮች’ ያሉባቸውን የኮንዶሚኒየም መንደሮች ስታዩ… አለ አይደል… “እነኚህ ባይሠሩ ኖሮ ይሄን ሁሉ ህዝብ ምን ይውጠው ነበር!” የሚያሰኝ ነው፡፡ ግን የኮንዶሚኒየም ኑሮን አስቸጋሪ የሚያደርጉ የእኛ ባህርያት አሉ፡፡ አቅራቢያችሁ ካለው መኖሪያ ወይ የሀይማኖት መዝሙርና ሰበካ፣ ወይ ቅልጥ ያለ የ‘ፖርኖ’ ራፕ ሙዚቃ፣ ወይ በርጫ አፎቻቸውን ‘ወደ አንድ ያዋሃደላቸው’ አሥር ሰዎች በአንድ ጊዜ ሲያወሩ…ብቻ ምን አለፋችሁ የማይሰማ ነገር የለም፡፡

በየኮንዶሚኒየሙ የሚኖሩ ወዳጆቻችን የሚያወሩን ወሬዎች አንዳንዴ የሆነ ተከታታይ የቤተሰብ ‘ሶፕ ኦፔራ’ ታሪክ ይመስላሉ፡፡ እናላችሁ… በየቦታው ውጥረቱ ሲበዛባችሁ…የሸሻችሁት ነገር መገኘት በማይገባው ቦታ ሲገጥማችሁ… አለ አይደል… ጎመን ቀቅል አሉኝ ምን ጊዜ ሊበስል ይኽንን ቀንጥሼ እዘልቀው ይመስል፣ ማለት ይመጣል፡፡ የምር እኮ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አይደለም እኛ ግለሰቦቹ አገር ራሷ እንኳን ይህንን ‘ቀን ጥሳ ታልፍ እንደሁ’ ግራ እየገባን ያለ ጊዜ ላይ እየደረስን ነው፡፡ እግዚአብሔር ጠፍቶብኝ ብፈልግ አጣሁት ንገሩልኝ ሰዎች ቀን ያገኛችሁት ይሉ ነበር አባቶቻችን ሲቀኙ፡፡ ያን ያገኛችሁ ሰዎች ለእግዚአብሔር ብዙ አቤቱታ አላቸው ብላችሁ ንገሩልንማ! ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…የዚች አገር፣ ቀን የወጣልን፣ ቀን ያልወጣልን፣ ቀን የሚወጣልን፣ ‘ዕድላችን’ ሆኖ ቀን የማይወጣልን፣ ቀን እንዳይወጣልን የዓይናችን ቀለም መሰናክል የሆነብን ሰዎች ተብለን ምደባ ሊወጣልን የሚችል ይመስለኛል፡፡ እናማ አገልግሎት እናገኛለን ብለን በምንሄድባቸው ቦታዎች፣ በምንሳፈራቸው የህዝብ ትራንስፖርት መኪናዎች ለተጨማሪ የ‘አንታይ አሲድ’ ወጪ ማውጣት የለብንም! ደህና ሰንብቱልኝማ!

ዕውቁ የስነልሳን ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባየ ይማም “ቋንቋ መግባቢያ ብቻ ሳይሆን የማንነት መግለጫም ነው” ይላሉ፡፡ ይህን ፍሬ ሃሳብ የሚሽር ሌላ ማስረጃ እስካልቀረበ ድረስ የፕሮፌሰሩ አባባል ፍጹም እውነት ነው፡፡ ያለፉት የኢትዮጵያ መንግስታት ሲወቀሱበት የኖሩትና ከሚወቀሱባቸው የ “ተጨቁነናል” ቅሬታዎች አንዱም ይኸው የቋንቋ ጉዳይ ነው፡፡ እርግጥ ነው በቋንቋ እንዳይጠቀሙ ቀጥተኛ ተጽእኖ ማድረግና በሌላ አሸማቃቂ ዘዴዎች ጫና ማድረግ በማንነት ላይ የሚደረግ አደገኛ ዘመቻ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባለፉት መንግስታት ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎች ተገቢ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ (የደርግ መንግሥት በ15 የብሔረሰብ ቋንቋዎች የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ በማካሄድ ከሌሎች ቀዳምያን መንግሥታት ልዩ መሆኑን ሳንዘነጋ)፡፡ የተባበሩት መንግስታት አካል የሆነው ዩኔስኮም ሆነ ሌሎች ዓለምአቀፍ ተቋማት በራስ ቋንቋ የመናገር መብት የሰብአዊ መብት አንዱ አካል አድርገው ይወስዱታል፡፡

ለተግባራዊነቱም ተገቢው ህጋዊ ጥበቃ መደረግ አለበት ብለው ይከራከራሉ፡፡ በ1987 ዓ.ም የፀደቀው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገመንግሥት አንቀጽ አምስትና ሰላሳ ዘጠኝም ይህንን እውነት እንዲያረጋግጡ ሆነው ተቀርፀዋል፤ ምንም እንኳ እያንዳንዱ ክልል በመረጠው ኢትዮጵያዊ ቋንቋ የመጠቀም መብት ቢኖረውም የፌዴራሉ መንግሥት የስራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑን በግልጽ ይደነግጋል - ይኸው ህገመንግስት፡፡ አማርኛ ዛሬ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ከመሆን አልፎ ብዙዎች በሚሰግዱላትና በሚያመልኳት አሜሪካ ዋና ከተማ (ዋሽንግተን ዲሲም) ህጋዊ የሥራ ቋንቋ መሆን ችሏል። ከአፄ ዮሐንስ ውድቀት በኋላ ከአማራ የወጡ ግለሰቦች የፖለቲካ ስልጣን ይዘው በመቆየታቸው አማራ የሆነውን ሁሉ እንደጨቋኝ የማየት አባዜ በተለይ በየዋኃን ፖለቲከኞች ዘንድ ሲስተዋል የቆየ እውነት ነው፡፡ አሁንም የኢትዮጵያውያን አንድነት በማይዋጥላቸው በአንዳንድ ግለሰቦች ዘንድ ይኸው የቸከ ዘፈን መደመጡ ቀርቷል ማለት አይቻልም፡፡ ግን መስተዋል ያለበት ዐቢይ ቁም ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡

በመሰሪነታቸውና ህዝብን ከህዝብ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት በመነጣጠል ሴራ የሚታወቁት እንግሊዛውያን፣ ቋንቋቸው የከፋፋዮች ሃብት ስለሆነ ተብሎ ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ አልተጣለም፡፡ እንግሊዞችን አምርረው የሚጠሉት ቻይናውያንና አረቦች ሳይቀሩ እንግሊዝኛ ቋንቋን ትኩረት ሰጥተው ይማራሉ፡፡ ቻይናውያን ለምን እንግሊዝኛን መማር እንደሚፈልጉ ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ “የጠላታችንን ምስጢር ለማወቅ እንዲረዳን ነው” የሚል ነው፡፡ እርግጥ ነው ህዝብ የህዝብ ጠላት ሆኖ አያውቅም፡፡ እንደ ሂትለር ያሉ ልበ ድፍን መሪዎች ግን አንዱን ህዝብ በሌላው ላይ በማዝመት እንደ ቅንስናሽ ሂሳብ (ፍራክሽን) እርስበርሱ ሊያጣፉት ይችላሉ፡፡ ሆኖም እንዲህ ያለውን ጅምላ መንጋነት በመቃወም ማንኛውም ህዝብ የማንኛውም ህዝብ ጠላት አለመሆኑን በተግባር ማሳየት ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቂ እውቀትና ልበ ሰፊነት ያስፈልጋል፡፡ በቂ ዕውቀትና ልበሰፊነት ካለ የህዝብን ወይም የገዥ መደብንና የቋንቋን መሠረታዊ ልዩነት ማወቅ አያስቸግርም፡፡ በየትኛውም ዘመንና በየትኛውም አገር ቢሆን ሰውን ሰው እንጂ ቋንቋ ጨቁኖት አያውቅም፡፡

ይልቁንም የሰብአዊ መብት ተቀናቃኞች ሰፊው ህዝብ ረግጠው መግዛት ሲጀምሩ የህዝብን ቋንቋም አብረው ይደፈጥጣሉ፡፡ ቋንቋ ብዙ ጊዜ እንደተባለውና እንደሚባለው የመግባቢያ መሳሪያ ነው፡፡ መሳሪያ በመሆኑም በአግባቡ ከተገለገሉበት ያግባባል፡፡ ያለወግ ከተጠቀሙበት ግን በግለሰቦችም ሆነ በህዝቦች መካከል ሊኖር የሚችለውን ግንኙነት ያበላሻል፤ ቋንቋን የጦር መሳሪያ ነው ብለን እንውሰደው፤ የጦር መሳሪያ በአግባቡ ከተጠቀሙበት አገርን ከወራሪ ሃይል መከላከል ያስችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰው ያስፈልጋል፡፡ ዝም ብለን ብናስቀምጠውም ዕቃ ነውና ሊበላሽ ይችላል እንጂ በራሱ ጊዜ አገርን ከጥቃት ሊከላከልልን አይችልም፡፡ ቋንቋም እንደዚሁ ነው። በአግባቡ ካልተጠበቀና ካልተገለገሉበት ይጠፋል፣ ማንነትንም ሊያጠፋ ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ በህገመንግስቷ እንዳረጋገጠችው፤ ፌዴራላዊ መንግስቱ የዕለት ከዕለት ሥራውን የሚያከናውነው በአማርኛ ቋንቋ ነው፡፡

ህገ መንግስቱ “ተረቅቆ ፀደቀ” የሚባለው ከህዝብ በተውጣጡ ህጋዊ ወኪሎች አማካይነት ነው። ለዚህም ይመስለኛል መግቢያው ላይ “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ወደንና ፈቅደን ይህን ህገመንግሥት አጽድቀናል” ብሎ የሚጀምረው፡፡ ይህን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ወደውና ፈቅደው ያረቀቁትንና ያፀደቁትን ህገመንግስት አክብሮ የማስከበር ኃላፊነት የእያንዳንዱ ዜጋ ቢሆንም በተለይ የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት ድርብ ኃላፊነት አለባቸው ባይ ነኝ። አንደኛ ወክለውት የመጡት ብሔር ወይም ብሔረሰብ፣ ወይም ህዝብ ስላለ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ወኪሎች ስለሆኑ ነው። ለነገሩ ህገመንግስቱን የማክበር የዜግነት ግዴታም አለባቸው፡፡ ግን በተለይ ቋንቋን በተመለከተ ህገመንግስቱን እያከበሩት ሳይሆን በተለያየ መንገድ (የፖለቲከኞችን አባባል ልጠቀምና) እየሸራረፉት ነው - አስረጂዎቼን ላቅርብ፡፡ የሕግ አውጭው ህገወጥ ድርጊት ህግ አውጭው አካል የተዋቀረው ከዚያው ከፈረደበት “ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ” እየተባለ ከሚጠራው ነው፡፡ ያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ ወክሎ ሲልክ “ህገመንግሥቱን አክብሮ መብትና ጥቅሜን ያስከብርልኛል” ብሎ እንጂ ወር ሙሉ ቁጭ ብሎ የመንግስት ደሞዝ እንዲበላ ወይም ስብሰባ ባለ ጊዜ ብቻ በአጀንዳው ላይ አመነበትም አላመነበትም እጅ አውጥቶ የጐደለ ድምጽ መሙያ እንዲሆን አይደለም፡፡

በረቂቅ አዋጅነት የሚቀርብለትን ጉዳይ ጠንቅቆ ማወቅ፣ አውቆም ተገቢው ህጋዊ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡ የፓርቲ ዲሲፕሊን ስላለ ብቻ እሷኑ በመፍራት “ሃሳቡን የምትደግፉ” ሲባል ከእንቅልፉ ነቅቶም ቢሆን እጁን መምዘዝ ህገወጥነት ነው፡፡ በንቃት ባለመሳተፉ የተጣለበትን ህዝባዊ ውክልና አልተወጣማ! ለምሳሌ ይኸው ህግ አውጭ ያፀደቃቸውን ህገወጥ ስሞች ልጥቀስ “የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት” ይባል የነበረውን ተቋም “የቤቶች ኤጀንሲ”፣ “የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን” ይባል የነበረውን “ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ” ብሔራዊ ቤተመጻሕፍት ወመዘክርን “ብሔራዊ ቤተመጻሕፍትና ቤተመዛግብት ኤጀንሲ” ተብሎ ከሚኒስትሮች ም/ቤት ወይም ከአንድ ሚኒስቴር ጉራማይሌ ስም ሲቀርብለት ያለምንም ማቅማማት ተቀብሎ ያፀድቃል፡፡ ይህን ሲያደርግ ሳይ ነው ህግ ለማውጣት ህግ መጣስ የለበትም የምለው፡፡ ህግ አውጭው የፌዴራል መንግሥቱ የመጨረሻው ባለስልጣን እስከሆነ ድረስ ራሱ ያወጣቸውን የሃገሪቱን ህግና ሥርዓት በማክበር ነው ተግባሩን ማከናወን ያለበት። የፌዴራሉ መንግሥት የስራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑን ማወቅና መቀበል፣ ተቀብሎም በስራ መተርጐም አለበት፡፡

“የምናምን ኤጀንሲ” ተብሎ ረቂቅ ሲቀርብለት “ኤጀንሲ አማርኛ ስላልሆነ ለቋንቋ ባለሙያዎች ይተላለፍና አቻ ትርጉም ይፈለግለት” ሲል አናስተውልም፡፡ ሆን ተብሎ አማርኛን ጉራይማይሌ ለማድረግ እንጂ “ኤጀንሲ” ለሚለው ቃል አቻ ትርጉም ጠፍቶለት አይደለም። በተለመደው “ድርጅት” ማለት ይቻላል፡፡ ይህ አይመጥነውም ከተባለም ከአገሪቱ ህዝብ ቋንቋዎች መፈለግና መጠቀም ተገቢም ህገመንግስታዊም ነው። ምክንያቱም ህገመንግስቱ አንቀጽ አምስት ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎች እኩል ህገመንግስታዊ ዕውቅና እንዳላቸው ስለሚደነግግ ነው፡፡ ለእንግሊዝኛ ቋንቋ ግን አንድም የህጋዊነት ቦታ አይሰጥም፡፡ የዛሬ አምስት ዓመት በአፍሪካ ደረጃ የተከበረውን የሁለት ሺህ ዓመት መጠናቀቅ አስመልክቶ ልዩ ልዩ ጉዳዮችን ስታዘብ ነበር፡፡ ከታላላቆቹ የመንግስት መሪዎች ጀምሮ ወደታች እስከ መጨረሻው እርከን ያሉ ንዑሳን ባለስልጣናት ድረስ ሁለት ሺህን የሚጠሩት “ሚሊኒየም” እያሉ ነበር፡፡ እንዲያውም ፕሬዚዳንት ግርማ “ሚላኒየም” የሚል ስም አውጥተውለት ነበር፡፡

ልክ ኤች አይ ቪ ኤድስን “ኤች ቪ አይ” ብለው እንደሚጠሩት ማለት ነው፡፡ በወቅቱ ከተገረምሁባቸው የመንግስት ተቋማት አንዱ የሰባ ሁለት ዓመቱ (ያኔ ስልሳ ሰባት ዓመቱ ነበር) አዲስ ዘመን ጋዜጣ “የሚሊኒየም ገጽ” ብሎ ቋሚ አምድ ሲከፍት በኦሮሚፋ የሚታተመው በሪሳ ጋዜጣ ግን “በርኩሜ” የሚል ቆንጆ ቃል ተጠቅሞ ማየቴ ነው፡፡ በርኩሜን “ቆንጆ ቃል” ያልሁት ትርጉሙ ሺህ ዓመት ማለት ሲሆን ኢትዮጵያዊም ህገመንግስታዊም ቃል ስለሆነ ነው፡፡ የበዓሉን ዓላማም በአግባቡ ገልጿል፡፡ ከዚህ በላይ አፍሪካውያን “የራሳችን በዓል ነው” ብለው የወሰኑትን ጉዳይ ኢትዮጵያዊ ቃል ቢጠፋ እንኳ (አልጠፋም እንጂ) ከሌላ አፍሪካዊ ቋንቋ መጠቀም ይቻል ነበር፡፡ ለምሳሌ በርኩሜ በጣም ገላጭና አጭር ቃል ሲሆን ሺህ ዓመት፣ ዓምኣት፣ ወዘተ ማለት ይቻል ነበር፡፡ ነገሩ “ሳይቸግር ጤፍ ብድር” መሆኑ ነው። ወይም እኒያኑ “የምናመልካቸውን” ፈረንጆች ለማስደሰት ሊሆን ይችላል፡፡ እናም ህዝብን ወክሎ የተቀመጠው ህግ አውጭ የሚያወጣቸው ህጐች በይዘት ብቻ ሳይሆን በቋንቋም ህገመንግስቱ የሚደነግገውን ስርዓት ጠብቀው መውጣታቸውን የመቆጣጠር ህጋዊ ኃላፊነት አለበትና ተግባራዊ ሊያደርገው ይገባል ባይ ነኝ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ህገወጥ መግለጫ ነፍሳቸውን ይማርና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ኢትዮጵያን ወክለው ሲናገሩ የፈረንጅ አፍ ይቀናቸው ነበር፡፡ አንዳንድ ሰዎችም እንግሊዝኛቸውን ሲያደንቁላቸው ሰምቻለሁ፡፡ ግን እንግሊዝኛ መናገርኮ የአዋቂነት መለኪያ ሊሆን አይችልም፡፡ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ የኬንያ፣ የደቡብ ሱዳንና በአገራችንም የጋምቤላ ገበሬዎች ከቋንቋ ምሁራን የተሻለ እንግሊዝኛ ይናገራሉ፡፡ ግን ያው እንደ አማርኛ ተናጋሪው፣ እንደ ኦሮምኛ ተናጋሪው ወይም እንደ ሱማሊኛ፣ አፋርኛ፣ወይም ስልጢኛ ተናጋሪው ገበሬዎች እንጂ የሊቃውንት ቁንጮዎች አይደሉም፡፡ በኮሙኒዝም ወቅት በአውሮፓ የኬጂቢ ከፍተኛ ወኪል የነበሩት የዛሬዋ ሩሲያ ፕሬዚዳንት ፑቲን እንግሊዝኛ አቀላጥፈው ይናገሩ ነበር፤ አሁንም ችሎታው አላቸው፡፡ በእንግሊዝኛ ችሎታቸውም ነው የሃያሉ የስለላ ተቋም ከፍተኛ ባለሙያ ሆነው የተመደቡት፡፡ ግን የሩሲያ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሰየሙ በኋላ በሩስኪ ቋንቋ ውስጥ ቢሞቱ እንኳ አንዲት የእንግሊዝኛ ቃል አይጨምሩም፡፡ ምክንያቱም የሩሲያ የሥራ ቋንቋ ሩስኪ እንጂ እንግሊዝኛ አይደለማ! ጀርመኖች በራሳቸው ቋንቋ ካልሆነ መንገድ የጠፋበት እንግዳ ሰው ቢጠይቃቸው እንኳ በቋንቋቸው ካልሆነ አይጠቁሙም፤ ፈረንሳዮችም ለቋንቋቸው እጅግ ጠንቃቆች ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያምም ቢሆኑ እንግሊዝኛ ቋንቋ በደንብ መናገር እየቻሉ ከማንኛውም አገር መሪ ጋር ሲነጋገሩ በብሔራዊ ቋንቋቸው እንደነበር የረጅም ጊዜ አስተርጓሚያቸው አቶ ግርማ በሻህ ለግል መገናኛ ብዙኃን መግለጻቸውን አስታውሳለሁ፡፡ እንዲያውም “አንድ ጊዜ ፕሬዚዳንቱ ከሆነ አገር መሪ ጋር ሲወያዩ የተሳሳተ ትርጉም በመስጠቴ ግርማ! እንደዚያ አይደለም ያልሁት፡፡ አሁንም እንዲህ ብለህ አስተካክለህ ንገረው ብለው አርመውኛል” ብለዋል፤ የብዙ ቋንቋዎች ተናጋሪ የሆኑት አቶ ግርማ በሻህ፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚያሻው ነገር ፕሬዚዳንት መንግስቱ በአማርኛ የሚናገሩት እንግሊዝኛ አልችል ብለው ሳይሆን ለሀገራቸውና ለራሳቸው ክብር በመስጠታቸው መሆኑን ነው። “ራሱን ያቀለለ አሞሌ ባለ ዕዳ አያከብረውም” የሚባለው የዚህ ዓይነቱ የማንነት ጉዳይ ሲያጋጥም ይመስለኛል፡፡ በደርግ ዘመንማ እንዲያውም የከፍተኛ ትምህርት ሁሉ በብሔራዊ ቋንቋ እንዲሰጥ ዝግጅቱ ጦፎ እንደነበር በቂ ማስረጃዎች አሉ፡፡

የቀድሞው ንጉሥ ኃ/ሥላሴም ቢሆኑ እንግሊዝኛ አጥርተው ይናገሩ እንደነበር “አዶልፍ ፓርለስክ” የተባለ ቸኮዝሎባኪያዊ “የሐበሻ ጀብዱ” በተባለው መጽሐፉ ላይ ገልጿል፡፡ ግን ንጉሡ የትም ቦታ ይናገሩ የነበረው በብሔራዊ ቋንቋቸው አማርኛ ነበር፡፡ አማርኛ ግራ ይገባው የጀመረው በዘመነ ኢህአዴግ ይመስለኛል፡፡ አንድ ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው ረቂቅ መሪ ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂዶ ነበር፡፡ በውይይቱ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ተሳትፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሙሉ ንግግራቸውን በእንግሊዝኛ ነበር ያደረጉት፡፡ ግን ለማን? ለምን ዓላማ? ግልጽ አይደለም፡፡ ስለ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር (ከቋንቋ ጋር በተያያዘ) ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ግን የአገራችን አባባል “ሙት ወቃሽ አታርገኝ” ይላል፡፡ እኔም ለአባባሉ ልገዛና በዚሁ ልለፋቸው፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥራቸውን የጀመሩት “የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሌጋሲ ያለምንም ማወላወል አስፈጽማለሁ” በማለት ቃል ገብተው ነው፡፡ እውነትም በደንብ ተክተዋቸዋል፡፡

ለመሆኑ “ሌጋሲ” የሚለው ቃል አቻ ትርጉም የለውም? “ውርስ፣ ፈለግ፣ ዕቅድ፣ ራዕይ፣ ውጥን” ማለት ሊሆን አይችልም ይሆን? አማርኛ ቃል ቢጠፋለትስ ወላይትኛ፣ ጌዴዎኛ፣ ሲዳምኛ ወዘተ ሊገኝለት አይቻልም? ከሁሉ የገረመኝ በስራቸው የሾሟቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ማዕረግ ነው (እሳቸው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ ነው የተሾሙት እንጂ ምክትል ጠ/ሚኒስትራችን አንድ ብቻ ናቸው ብለውናል) የዚህ ዓይነት ሹመት ህገመንግስታዊ ነው አይደለም? የሚለውን ፍሬ ነገር እናቆየውና የማዕረጋቸው ማጀቢያ ቃል በእጅጉ ያስፈራል፡፡ ምክንያቱም “የዚህ ክላስተር አስተባባሪ፣ የዚያ ክላስተር አስተባባሪ” የሚል ነው፡፡ ካልጠፋ ስም “ክላስተር”ን ምን አመጣው? ለዓመታት የኖርነው በዘግናኝ ጦርነት ውስጥ ነው፡፡ ከደርግም ሆነ ዛሬ ሁለት መንግስታት ካቋቁሙት የዚያኔዎቹ አማጽያን ይሰጥ የነበረው መግለጫ “ደርግ ወይም ሻዕቢያ ወይም ወያኔ ሰላማዊውን ህዝብ በክላስተር ቦንብ ጨፈጨፈ” የሚል ነበር፡፡ ስለሆነም ክላስተር የማህበራዊ አገልግሎት አስተባባሪነትን ሳይሆን አስፈሪነትን፣ ነፍሰ ገዳይነትን፣ ስጋትንና መከራን ነው ሊያስታውሰን የሚችለው፡፡ ለዚህ ሳይሆን ይቀራል በአንዳንድ አካባቢዎች “የአባት ክፉ የስም ድሃ ያደርጋል” የሚባለው? መሪኮ የሁሉ ነገር መሪ ነው፡፡

ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በርኩሜን ወይም ሺህ ዓመታችንን ስናከብር ከባለቤታቸው ክብርት ወይዘሮ አዜብ ጋር በባህላዊና ብሔራዊ ልብሳቸው ተንቆጥቁጠው ነበር ያከበሩት፡፡ ከማግስቱ ጀምሮ የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት እንዲሁም የወረዳና የቀበሌ ሹማምንት ሳይቀሩ በዚሁ ባህላዊ ልብስ መዋብ ጀመሩ፡፡ ለማንነታቸው ትኩረት በመስጠታቸውም ሊወደሱ እንጂ ሊወቀሱ አይገባም፡፡ እንደዚህ ሁሉ ለቋንቋችንም መሪዎች ሲጠነቀቁ ቢታዩ፣ ሌላው ባለስልጣንና ድምሩ ህዝብ ለራሱ ሃብት ትኩረት ሊሰጥና በማንነቱ ሊኮራ ይችላል፡፡ ጉራማይሌ ቋንቋ ያመጣው ጣጣ ብዙ ነው። የልጆች፣ የንግድ ተቋማት፣ የግል ት/ቤቶችና አንዳንድ አደባባዮች ሳይቀሩ “በኢትዮጵያዊ ስም ብትጠሯቸው ትከስራላችሁ” የተባሉ ይመስል ከተማችንን አስጠሊታ አድርገዋታል፡፡

ጀግኖች ወላጆቻችን አጥንታቸውን ማገርና ግድግዳ አድርገው ሃገራችንን በባዕዳን ባያስወርሯትም፣ እኛ ግን ወደንና ፈቅደን ለባዕዳን መጤ ባህልና አስተሳሰብ ህሊናችንን ለጭዳነት አቅርበናል፡፡ “ዲያስፖራ አደባባይ፣ ቦብማርሌይ አደባባይ፣ ካርል ሃይንዝ አደባባይ፣ ቸርችል ጐዳና፣ ካኒንግሃም መንገድ ወዘተ” በመንግሥት የተሰየሙ የባዕዳን መታሰቢያዎች ናቸው፡፡ እርግጥ ነው እነዚህ ሰዎች ለሀገሪቱ በአጠቃላይ፣ ወይም ለመሪዎች በተለይ የከፈሉት ውለታ ሊኖር ይችላል፡፡ ግን በተለያየ መንገድ ለሀገራቸው መስዋዕት የሆኑ ጀግኖቻችንን የት አገር ወስደን እንዲታወሱ እናድርግ? የኢፌዴሪ ህገመንግስት፤ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ አማርኛ ነው ይላል፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫ ደግሞ አዲስ አበባ ነው።

ታዲያ በፌዴራሉ መንግሥት ጉያ ስር የተወሸቁ አንዳንድ የግል ት/ቤቶች “አማርኛ መናገርና ድንጋይ መወርወር ክልክል ነው” እስከማለት ሲቀናጡ፣ አገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴርና የፍትሕ ተቋማት አሏት ወይ አያሰኝም? በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማርኮ ዓለምአቀፍ ተቀባይነት ያገኘ ሰብአዊ መብት ነው። ስለሆነም እባካችሁ መሪዎቻችን፤ ቋንቋችሁንና ቋንቋችንን አፍቅሩ! በማንነታችሁ ኩሩ! የሀገሪቱን ህግጋት አክብሩ! አለዚያ አትወክሉንማ!!