Administrator

Administrator

የምድር አውሬ ሁሉ መነገጃና መሰባሰቢያ አንድ ገበያ ነበር ይባላል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አውሬ ሁሉ እገበያ ሲውል፤ አያ ጅቦ ቀርቶ ኖሯል፡፡ ማታ ሁሉም ከገበያ ሲመለስ ከጎሬው ብቅ ይልና መንገድ ዳር ይቀመጣል፡፡ ዝንጀሮ ስትመለስ ያገኛትና ገበያው እንዴት እንደዋለ ይጠይቃታል፡፡ “እቸኩላለሁ ጦጢት ከኋላ አለችልህ እሷን ጠይቃት” ብላው ሄደች፡፡ ጦጢት ስትመለስ ጠብቆ “ገበያው እንዴት ዋለ?” አላት፡፡ “መሽቶብኛል፡፡ ገና ብዙ ሥራ አለብኝ” ብላው አለፈች፡፡ ቀጥላ ሚዳቋ መጣች፡፡ ያንኑ ጥያቄ ጠየቃት፡፡ “እንኮዬ አህይት እኋላ አለች - እሷን ጠይቅ!! እኔ እነዝንጀሮ ቀድመውኛል፤ ልድረስባቸው” ብላው ሄደች፡፡ አህያ ስትንቀረደድ መጣች፡፡ ገበያው እንዴት እንደዋለ ጠየቃት፡፡ “ቆይ አረፍ ብዬ ላውራልህ” ብላ አጠገቡ ተቀመጠች፡፡

“ይሄ ተገዛ! ያ ተሸጠ!” ስትለው አመሸች፡፡ አያ ጅቦ ቀጠለና “ለመሆኑ እኔ እምዘለውን መዝለል ትችያለሽ?” አላት፡፡ “አሳምሬ” አለችው፡፡ እሱ የሞት ሞቱን ዘለለ፡፡ እሷ ግን እዘላለሁ ብላ ገደሉ ውስጥ ወደቀች፡፡ አያ ጅቦ ወርዶ ሆዷ ዘንጥሎ መብላት ጀመረ፡፡ እመት ውሻ በዛ ስታልፍ ስጋ ሸቷት መጣች፡፡ “ነይ ውረጂና እየመተርሽ አብይኝ” አላት፡፡ ወርዳ እየመተረች ስታበላው የአህያዋን ልብ አገኘችና እሱ ሳያያት ዋጥ ስልቅጥ አደረገችው፡፡ ቆይቶ “አንቺ ልቧ የታል?” ሲል ጠየቃት፡፡ ውሺትም፤ “ልብ ባይኖራት ነው እንጂ ልብ ቢኖራት መቼ ካንተ ዘንድ መጥታ ትቀመጥ ነበር?!” አለችው፡፡ “ታመጪ እንደሁ አምጪ፤ አለዛ አንቺንም እበላሻለሁ!” አለ፡፡ “አያ ጅቦ፤ ያለ ቂቤ? ያለ ድልህ? ደረቁን ልትበላኝ?” “ቅቤና ድልሁ ከየት ይመጣል?” አለ ጅቦ በመጎምጀት፡፡

“ከእመቤቴና ከጌታዬ ቤት አመጣለሁ” “ሄደሽ የጠፋሽ እንደሆን ማ ብዬ እጠራሻለሁ?” “እንኮዬ -ልብ- አጥቼ” ብለህ ጥራኝ፡፡ “በይ እንግዲያው ሄደሽ አምጪ” ብሎ ላካት፡፡ ቅርት አለች፡፡ ሲቸግረው “ኧረ እንኮዬ ልብ አጥቼ?” ሲል ጮሆ ተጣራ፡፡ ውሻም፤ “ከጌታዬና ከእመቤቴ ቤት ለምን ወጥቼ!” አለችው፡፡ ከዚያም የስድብ መዓት ታወርድበት ጀመር፡፡ ጅቦም፤ “አንቺም እጉድፍ እኔም እጉድፍ፡፡ አገኝሻለሁ ስንተላለፍ” አላት፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ውነትም ጉድፍ ስትለቃቅም አገኛት፡፡ ዐይኗ ፈጠጠ፡፡ “ዐይንሽ እንዴት እንዲህ አማረልሽ?” ሲል ጠየቃት፡፡ “በዐሥር የአጋም እሾክ ተነቅሼ!” አለችው፡፡ “እስቲ እኔንም ንቀሺኝ?” ተስማምታ ከጌታዋ አጥር ዓሥር የአጋም እሾህ ሰብራ አምጥታ ዐይኖቹን ቸከቸከችው፡፡ “ኧረ አመመኝ” ሲል፤ “ዝም በል ሲያጌጡ ይመላለጡ ነው፣ ማማር እንዲያው ይገኝ መሰለህ?” ትለዋለች፡፡ ሁለቱንም ዐይኖቹን አጥፍታ፤ “በል ና ሠንጋ ጥለው የሚሻሙ ጅቦች ጋ ልቀላቅልህ” ብላ፤ ውቂያ ላይ ያሉ ገበሬዎች ማህል ከተተችው፡፡ ወስዳ ጤፍ መውቂያ ሙጫቸውን እየመዘዙ ሊገድሉት ያራውጡት ጀመር፡፡ ውሻ ሆዬ እነሱ ሲሯሯጡ ዳቧቸውን ይዛ ወደቤቷ መጭ አለች!!

                                                           * * *

ያሰቡትን ቸል ሳይሉ ከፍፃሜ ማድረስ አስተዋይነት ነው፡፡ ያለኩያ ጓደኛ መያዝ፤ ነገርን ሳያመዛዝኑ ፈጥኖ አምኖ መቀበል ከጥቃት የሚያደርስ ቂልነት ነው፡፡ አታላይ ለጊዜው የመብለጥለጥ ምኞቱን ቢያረካም፣ የፈፀመው ደባ እንደሚደርስበት የዥቡን አወዳደቅ ማስተዋል በቂ ነው! ብልህ በዘዴ ከአደጋ ያመልጣል፡፡ ኃይለኛ የሆነ ጠላት ቢገጥመው እንኳ በጥበብ ለመርታት ይችላል፡፡ ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡ አንዱ ሲሠራ ሌላው ሲያፈርስ፣ አንዱ ሲታሰር ሌላው ሲተበተብ፤ የሁኔታዎች መወሳሰብ ይከሰታል፡፡ ከውስብስቡ ሁኔታ ለመውጣት እጅግ አስፈላጊው ነገር ትዕግሥትና ስክነት ነው፡፡ ባላንጣ፤ ሀገር ያልተረጋጋበትን ሰዓት መምረጡ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ በብልህነት ማውጠንጠን፣ አርቆ - ማስተዋል፤ ነገሮች ተደራርበው ግራ እንዳይጋቡን ይጠቅመናል፡፡ የሙስና ላይ ዘቻው አንድ ረድፍ ነው፡፡ የቤት ችግር ሠልፍ፣ ለቤት የተመዘገበ ሰው ያገኘው ኮንዶምኒየም በሌላ ተወስዶበት ለአቤቱታ ቤት - ደጁን ማጥለቅለቅ፤ እናቱ የሞተችበትም፤ ወንዝ የወረደችበትም እኩል ማልቀሳቸው፤ መንግሥት ላይ ዕምነት ማሳደር ባንድ ወገን፣ መንግሥት በትክክል ሊቆጣጠረው ባይችልምስ የሚል ፊናንሳዊ ስጋት በሌላ ወገን፤ አፍንጫችን ሥር ያሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ በጦርነት ድንፋታ ንፋስ ከታጀቡ ደግ አይሆንም፡፡

ስለጦርነት ከተነገሩት ድንቅ አነጋገሮች ሁሉ የሚከተለው ይገኝበታል - “ጦርነት ነፃነትህን ስለሚወስድብህ አስፈላጊ የሆነ ምርጫ ላይ ለመዋጋት ወይም ላለመዋጋት ልትወስን ትችላለህ፡፡ አንዴ ጦርነት ከገባህ ግን የምርጫ ኃይልህ አከተመ” (ጊልበርት ሙሬይ) ሁሉም ነገር ጥንቃቄንና ዝግጁነትን ይጠይቃል፡፡ የተረጋጋ ህዝብን ይጠይቃል፡፡ መንገዶች ሁሉ ወደአንድ አቅጣጫ እንዳይሄዱ፤ እመነገጃውና እመገበያያው የሚገቡትን ባለይዞታዎች በጥሞና መያዝ ይገባል፡፡ የህዝብን አመኔታ የሚያጠናክር አዎንታዊ እርምጃ ሀገራዊ ስሜትን ለማድመቅ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ቤትም አገርም አለኝ የሚል ህዝብ እንዲኖረን ያስፈልጋል! “በሰው ልጅ ላይ የወረደ ታላቅ መርገምት ጦርነት ነው፡፡

በሰላም ጊዜ የሚፈፀሙት የጭካኔ ወንጀሎች፤ በሰላም ጊዜ የሚካሄዱት ሚስጥራዊ ሙስናዎች አሊያም የሀገሮች ሃሳብ - የለሽ የገንዘብ ዝርክርክነቶች ሁሉ፤ ጦርነት ከሚያደርስብን ሠይጣናዊ ጥፋት ጋር ሲወዳደሩ እንክልካይ ነገሮች ይሆናሉ” ይለናል፤ ሲድኒ ስሚዝ፡፡ የህዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ የወቅቱ ጥሪ ነው፡፡ የመንግሥት ጥንቃቄ የተሞላ እርምጃም የወቅቱ ጥሪ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊና ዲፕሎማሲያዊ ሂደትን ሥራዬ ብሎ ማቀናጀት ብልህነት ነው!! ዕውነት ገና ጫማውን እያሰረ፣ ውሸት ዓለምን ዞሮ ይጨርሳል የሚለውን አባባል አንርሳ!! በመላና በጥበብ የመምራት ክህሎትን የሚጠይቅ ወቅት ነው፡፡ “አዞው ወደውሃ ሲስብ፣ ጉማሬው ወደ ሣሩ ይስባል” የሚለው የወላይታ ተረት ጉዳያችንን ያሳስበናል፡፡

ከ10 በላይ አቃቤ ህጐችም ይከሰሳሉ ተባለ

በቅርቡ ከስልጣን የተነሱት የፍትህ ሚኒስትር አቶ ብርሃነ ኃይሉና ከአስር በላይ አቃቤ ህጐች በሙስና፣ በሽብርተኝነትና በግድያ ወንጀል በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የተመሰረተን ክስ ያለአግባብ አቋርጠዋል በሚል በፖሊስ ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ምንጮች ገለፁ፡፡ ፖሊስ በሚኒስትሩና በአቃቤ ህጐቹ ቢሮ ባካሄደው ከፍተኛ ብርበራ በርካታ መዝገቦችን ማግኘቱንና ለምርመራ መውሰዱን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በፖሊስ ብርበራ የተገኙት መዝገቦች ያለአግባብ ተቋርጠው እንዲዘጉ የተደረጉ ክሶች ናቸው ተብሏል፡፡

ተከሳሾች ላይ በቂ ማስረጃ ማቅረብ ካልተቻለ ክሶቹን አቋርጦ መዝገቡን መዝጋት የፍትህ ሚኒስትርና የአቃቤ ህጐች ስልጣን መሆኑ ቢታወቅም ከሙስና፣ ከሽብርተኝነትና ከግድያ ጋር የተያያዙት እነዚህ በፖሊስ ብርበራ የተገኙ ከደርዘን በላይ የሆኑ መዝገቦች ግን፣ በቂ ማስረጃ እያለ፣ ያለ አግባብ የተቋረጡ ናቸው ተብሏል፡፡ ምርመራው ተጠናቆ እንዳበቃ በሚኒስትሩና በአቃቤ ህጐቹ ላይ ክስ እንደሚመሰረትም ምንጮች ጠቁመዋል። ለሰራተኞች አቤቱታ ምላሽ ባለመስጠትና በሥራ ድልድል በደል ፈጽመዋል በሚል ቅሬታ ይቀርብባቸው የነበሩት የፍትህ ሚኒስትሩ፤ በተለይ የጥብቅና ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ይታያሉ የተባሉ ችግሮችን እንዲፈቱ አራት የማሳሰቢያ ደብዳቤዎች ተጽፎላቸው እንደነበር ምንጮች ገልፀዋል፡፡ በሚኒስትሩ ላይ ከባለጉዳዮችም የተለያዩ ቅሬታዎች ይሰነዘሩ ነበር ያሉት ምንጮች፤ የታራሚዎች የይቅርታ ጥያቄን ማዘግየትና ተገቢ ምላሸ አለመስጠት በዋናነት እንደሚጠቀስ ገልፀዋል፡፡

በቅርቡ በተካሄደው የኢህአዴግ ዘጠነኛ ጉባኤ ላይ ከፓርቲው መሪዎችና አባላት ለሚኒስትሩ የቃል ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸው እንደነበር ምንጮች ገልፀው፣ ፓርላማም የመ/ቤቱ በርካታ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡ በኢህአዴግ ዘጠነኛ ጉባኤ ላይ የአገሪቱ ዋና ችግር በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ የሚታይ እንደሆነ መገለፁ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ሶስት ሚኒስትሮች በወንጀል ተጠርጥረው ከስልጣን የወረዱ ሲሆን፣ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጁነዲን ሳዶ ከአገር መኮብለላቸው ይታወሳል፡፡

የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልኡክ ጽ/ቤት ሃላፊ የነበሩት አምባሳደር ዣቪየ ማርሻል ባደረባቸው የአጭር ጊዜ ህመም ቤልጅየም ብራሰልስ በሚገኘው ቅድስት ኤልሳቤጥ ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው፣ ባለፈው ቅዳሜ ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም በተወለዱ በስልሳ አንድ አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡ አምባሳደር ማርሻል ከተሾሙበት እ.ኤ.አ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ሶስት አመት ተኩል የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልኡክ ጽ/ቤትን በአምባሳደርነት መርተዋል፡፡ በአምባሳደርነት ባገለገሉበት በዚህ ወቅትም በአውሮፓ ህብረትና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነትና የልማት ትብብር በከፍተኛ ደረጃ እንዲጠናከር ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል፡፡ አምባሳደሩ በ1988 ዓ.ም የአውሮፓ ኮሚሽንን የተቀላቀሉ ሲሆን በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በሞሮኮ እንዲሁም በሶሪያ በሚገኙት የህብረቱ ልኡክ ጽ/ቤቶች በአማካሪነት አገልግለዋል፡፡

ከ1999 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ደግሞ በሱዳንና በዚምባብዌ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ነበሩ፡፡ በግብርና ስራ ተሰማርተው ከነበሩ ቤልጅየማዊ ቤተሰቦች በኮንጐ ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ውስጥ በ1952 ዓ.ም የወለዱትና የግብርና ባለሙያ የሆኑት አምባሳደር ማርሻል፣ ለግብርና ሙያና ለአርሶ አደሮች ልዩና ስስ ልብ ነበራቸው፡፡ የኢትዮጵያን የገጠር አርሶ አደሮች ለመርዳት በሙሉ ሃይላቸውና በከፍተኛ ስሜት ያደረጉት ጥረት የአርሶ አደሮችንና የኢትዮጵያ መንግስትን ድጋፍና ከበሬታ አስገኝቶላቸዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ህዝቦች፣ ለዱር እንስሳቶቿና ለተፈጥሮ አካባቢዋ የነበራቸው ፍቅር ወሰን አልነበረውም፡፡ ለዱር እንስሳትና ለአካባቢ ጥበቃ ያደርጉት የነበረው ጥረት፣ የላቀና በምሳሌነት የሚጠቀስ ነበር፡፡ ልማት፣ ሰላምና የአካባቢ ጥበቃ ያላቸውን የእርስ በርስ መስተጋብር እንዲጋሩ የአውሮፓና የሌሎች ሀገራት አምባሳደሮችን በማስተባበር የሰሜን ተራሮችን፣ በምዕራብና ደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ደኖችንና የቡና እርሻዎችን እንዲጐበኙ አድርገዋል፡፡ አምባሳደር ማርሻል ምንም እንኳ በቢሮ ውስጥ ከመቀመጥ ይልቅ በባሌ ወይም በሰሜን ተራሮች ላይ ድንኳን ተክለው ቢሰሩ በእጅጉ እንደሚያስደስታቸው የታወቀ ቢሆንም በስራ አመራራቸው፣ የስራ ባልደረቦቻቸውን በማስተባበርና በማነቃቃት ረገድ የባልደረቦቻቸውን አድናቆትና ከበሬታ ያስገኘ ችሎታ ነበራቸው፡፡ አምባሳደር ማርሻል ባለትዳርና የአንድ ወንድና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት ነበሩ፡፡

ስለተለያዩ በሽታዎች ንቃተህሊና ተፈጥሮ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲኖር ወይንም ስለበሽታዎቹ ትኩረት ተሰጥቶ ተገቢው ሕክምና እንዲደረግ ለማሳሰብ የተለያየ ቀለም ያላቸው ሪቫኖች አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ፒንክ ሪቫን ነው፡፡ ፒንክ ሪቫን ኣለም አቀፍ እውቅና ያለው በጡት ካንሰር ላይ ንቃተህሊናን እንዲፈጥር ታልሞ የተሰራ ልዩ ምልክት ነው፡፡ ይህ ሪቫን ለእይታ ሲቀርብ ወይንም ስለሪቫኑ ሲነገር በጡት ካንሰር ለተጠቁ ሰዎች የሞራል ድጋፍ ይሆናል ተብሎ ይታመናል፡፡ ፒንክ ሪቫን በስፋት የሚነገርለትና ወደ እይታም ሆነ ወደ ጆሮ በስፋት የሚቀርበውና የሚሰማው የብሔራዊ የጡት ካንሰር ወር በሚከበርበት ወቅት ነው፡፡ ፒንክ ቀለም የተመረጠለት ሪቫን ከጡት ካንሰር ጋር ተቆራኝቶ መልእክት እንዲያስተላልፍ ሲደረግ 22/ ዓመት ሆኖታል፡፡ በዚያን ጊዜ መቀመጫውን በኒውዮርክ ከተማ ያደረገው ሱዛን ጂ ኮሜን komen ፋውንዴሽን እ.አ.አ በ1991/የጡት ካንሰር በሽታን ተቋቁመው ከበሽታው ነፃ መሆን ስለቻሉ ሰዎች የተዘጋጀ ውድድር ላይ ለተሳታፊዎች ሪቫኑ ከተበተነ በ ት ቀን ወዲህ ሪቫኑን መጠቀም ልማድ ሆኖ ቀርቷል፡፡

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ፒንክ ሪቫን እ.ኤ.አ በ1992 ወይንም ከ21 ዓመታት በፊት ሰፊ እውቅና ተሰጥቶት የብሔራዊ የጡት ካንሰር ንቃተ ህሊና መፍጠሪያ ልዩ መለያ መሆን ችሎአል፡፡ የኤችአይቪ ኤይድስ ምልክት ከሆነው ቀይ ሪቫን ሐሳብ ተወስዶ ለጡት ካንሰር የተሰራው ፒንክ ሪቫን አሌክሳንድራ ፔኒ እና ከጡት ካንሰር በሽታ አገግማ ለመዳን በበቃችው ኤቭለን ላውደር ምክንያት ተፈጥሮ በመላው ኒውዮርክ እንዲሰራጭ ትላልቅ ለሆኑ የኮስሞቲክስ ኩባንያዎች ተሰጥተዋል፡፡ አሌክሳንድራ የሴቶች ጤናን አስመልክቶ በሚዘጋጀው የ..ሰልፍ.. መጽሔት ዋና አዘጋጅ ስትሆን ኤቭለን ደግሞ የ..ኤስ ላውደር.. ኮስሞቲክስ ኩባንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ናት፡፡

ፒንክ ሪቫን ከሰማያዊ ሪቫን ጋር አብሮ ሲደረግ አጋጣሚው በጣም ጥቂት ቢሆንም በወንዶች ላይ ስለሚከሰተው የጡት ካንሰር አመላካች ይሆናል፡፡ ከ17/ ዓመታት በፊት የጆን ደብሊው ፋውንዴሽን መስራችና ፕሬዚዳንት የሆኑት ናንሲኒክ ሪቫኑን በሁለት ቀለም አቀናጅተው ሲፈጥሩ ..ወንዶችም የጡት ካንሰር ይይዛቸዋል.. የሚለውን ነጥብ ለማሳሰብና ግንዛቤውንም ለመፍጠር ሲሉ ነው፡፡ የፒንክ ሪቫን ቀለም ፒንክ የሆነበት ምክንያት ምእራባውያን አገሮች በሰነጾታ የሴቶች ተሳትፎን የሚገልጹበት በመሆኑ እና ቀለሙ ሴቶችን ስለመንከባከብ እንዲሁም ቆንጆ መሆንን ስለሚያመላክት ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፒንክ ቀለም ጥሩ መሆንንና ተባባሪ መሆንን ይገልጻል ተብሎም ይታመናል፡፡ ፒንክ ሪቫን ሲወሳ ፡- በጡት ካንሰር ላለመያዝ መጠንቀቅ፣ በበሽታው የተያዙ ለወደፊቱ ተስፋ እንዲያደርጉና የጡት ካንሰር በሽታን ለማጥፋት ንቅናቄ እንዲደረግ ያሳስባል፡፡

በጡት ካንሰር ላይ የሚሰሩ የተለያዩ ተቋማት ስራቸውን ከጡት ካንሰር ጋር ይበልጥ ለማቆራኘት ፒንክ ሪቫንን ይጠቀሙበታል፡፡ ፒንክ ሪቫንን ፡- መግዛት፣ ማድረግ ወይንም ለእይታ ማብቃት ...ሪቫኑን የያዘው ሰው ወይንም ተቋም ስለሴቶች ያላቸወን ጥንቃቄና እንክብካቤ ያሳያል፡፡ በየአመቱ ጥቅምት ወር ላይ በሺዎች ወይንም በመቶዎች የሚቆጠሩ ምርቶች በፒንክ ሪቫን ይወከላሉ ወይንም ደግሞ ፒንክ ቀለም እንዲኖራቸው ይደረጋሉ፡፡ በተጨማሪም ከምርቶቹ ሽያጭ ከሚገኘው ገቢ የተወሰነውን ስለጡት ካንሰር ስለሚደረግ ምርምርና ስለበሽታው ስለሚኖረው የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴ እንዲውል ይደረጋል፡፡ የዛሬ ሰባት አመት 15/ሺህ ከብር የተሰሩ ሳንቲሞች ሮያል ካኔዲያን ሚንት የተሰኘው የካናዳ ሳንቲም አምራች ተቋም ሰርቷል፡፡ የሳንቲሞቹ አንደኛው ጎን የንግስት ኤልሳቤጥ ምስል የተቀረጸበት ሲሆን በሌላኛው ጎኑ ደግሞ ሪቫን ተቀርጾበታ፡፡

በዚህ ብቻ ያልተገታው የፒንክ ሪቫን ሳንቲሞች ስሪት የ25/ሳንቲም ዋጋ ያላቸው 30/ሚሊዮን ሳንቲሞች በአንዱ ጎናቸው ፒንክ ሪቫን ተቀርጾባቸው ለተለመደው የግብይት ስርአት እንዲውሉ ተሰራጭተዋል፡፡ በአንድ ጎኑ ቀለም ያለው ሳንቲም ሲቀርብ ፒንክ ሪቫን በታሪክ ሁለተኛው እንደሆነ ይነገራል፡፡ የጡት ካንሰርን በሚመለከት ስላለው አለም አቀፍ እውቅና ይህንን ህል ካልን የጡት ካንሰርን አመጣጥና ሕክምናውን ለአንባቢዎች ባልንበት ባለፈው እትም ዶ/ር አበበ በቀለ እንደገለጹት ሕመሙ በኢትዮጵያ ውስጥ መታከም የሚችል ሲሆን ነገር ግን ሕክምናው ውስን በሆነ ሆስፒታል መሰጠቱ አንዱ ጎጂ ነገር ነው፡፡ የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ጎጂ ወይንም ገዳይ ነው የሚለውን ለመገመትም አስቸጋሪ የሚሆኑ ነገሮች እንደሚኖሩና ለዚህም እንደማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው ብዙ ሰዎች ሕክምናውን በአቅራቢያቸው ስለማያገኙ እና ሕመሙም ወደተቀረው የሰውነት ክፍላቸው ከመሰራጨቱ አስቀድሞ እርምጃ የማይወስዱ ብዙዎች መሆናቸው ነው ብዋል፡፡

ዶ/ር አበበ በቀለ አክለው እንደገለጹትም ጡት ላይ ያበጠ ነገር ሁሉ ካንሰር አለመሆኑን ነው፡፡ ሰዎች በዚህ መደናገጥ አይገባቸውም፡፡ ሆኖም ግን ያበጠ ነገር ባእድ መሆኑን ካለመዘንጋት በፍጥነት ወደሐኪም ዘንድ መቅረብ ይጠቅማል፡፡ ጉዳዩ ከሐኪም ዘንድ ከደረሰ በሁዋላ ካንሰር ነው አይደለም ለማለት በመጠኑ ከእባጩ ሴል ላይ በመርፌ ለምርመራ ይወሰዳል፡፡ ነገር ግን ብዙ ሰዎች ሰውነን መርፌ ከነካው በሽታው ወደሌላ አንሌ ይሰራጨል ከሚል የተሳሳተ ግምት ሕክምናውን እስከነጭርሱም ትተውት ይሄዳሉ፡፡ ይሄ ሙሉ በሙሉ የተሳሳተ ውሳኔ መሆኑን ሁሉም ሊያውቀው ይገባል፡፡ ይህ ምርመራ መደረጉ የግድ መሆኑን እና ሰዎች እንደሚሉት አይነት ጉዳት የማያመጣ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ህክምናውን በተገቢው ማድረግ ይገባል፡፡ ምርመራውን ለማድረግ የሚፈጀው ጊዜ ከሁለት ደቂቃ ያልበለጠ ሲሆን ምላሹም በ24 ሰአት ውስጥ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ታማሚዎች ሳይረበሹ ምርመራውን ሐኪም በሚያዘው መሰረት ካካሄዱ መዳን ወይንም እድገቱን በመግታት መቆየት ይቻላል፡፡

ጡት ካንሰር ሁሉንም ሴቶች ወይንም ሰው አይይዝም፡፡ ነገር ግን ሁለት መንገዶች አሉት፡፡ 1/እድሜ፡- ማንኛዋም ሴት ከሰላሳ እና ሳላሳ አምስት አመት በፊት ሲሆናት የጡት ካንሰር እንዲያውም አይታይባትም ማለት ይቻላል፡፡ ከሰላሳ አምስት እስከ 50/ አመት አካባቢ ከሰላሳ ወይንም ከሰላሳ አምስት ሴቶች አንዱዋ ላይ ጡት ካንሰር ይታያል፡፡እድሜ ወደ ሰባ ሰማንያ ሲደርስ ከስምንት ሴቶች አንዷ ላይ የጡት ካንሰር ይከሰታል፡፡ ስለዚህ ሴት መሆንና በእድሜ መግፋት ለጡት ካንሰር ሊያጋልጥ ይችላል፡፡ 2/ሆርሞን፡- ሴቶች ላይ ኢስትሮጂንና ፕሮጀስትሮን የተባሉ ሆርሞኖች ይገኛሉ፡፡ የሰውነት ክፍል በብዛት ለኢስትሮጂን እየተጋለጠ ከሄደ ለጡት ካንሰር የመጋለጥ እድሉም የሰፋ ይሆናል፡፡ ኢስትሮጂን በብዛት ያላቸው ሴቶች የወር አበባ ከ13/አመት በፊት የሚያዩ ወይንም የወር አበባቸው ሳይቋረጥ እስከ ሀምሳ እና ሀምሳ አምስት አመት ድረስ የሚቆይባቸው ናቸው፡፡ ልጅ ሳይወልዱ የሚኖሩ ወይንም መጀመሪያ ልጃቸውን ከሰላሳ አመት በሁዋላ የሚወልዱ እንዲሁም ወልደው ጡት ያላጠቡ ሴቶች እና ለተለያየ ምክንያት ኢስተትሮጂንን ለሕክምና ወይንም እንደምግብ የወሰዱ ሴቶች ብዙውን ጊዜ ለጡት ካንሰር ሕመም ይጋለጣሉ ብለዋል ዶ/ር አበበ በቀለ፡፡ ....ባለፈው ሳምንት እትም ዶ/ር አበበ ፈለቀ ተብሎ የተጻፈው ዶ/ር አበበ በቀለ በሚል እርምት እንዲነበብ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡..

በነርቭ ሕመም እየተሰቃየ ለሚገኘው አርቲስት ፍቃዱ አያሌው የሕክምና ገንዘብ ለማሰባሰብ ታስቦ ባለፈው ግንቦት 16 የተከፈተው የስዕል አውደርእይ እስከ ፊታችን ረቡዕ እንደሚቀጥል አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡ አርቲስቱን በባንኮክ ለማሳከም 450ሺ ብር እንደሚያስፈልግ ታውቋል፡፡ አርባ አርቲስቶች ሥራቸውን በአውደርእዩ አሳይተው ሽያጩን በቀጥታ ለሰዓሊው መታከሚያ ለማዋል አቅደው የነበረ ሲሆን አሁን የአርቲስቶቹ ቁጥር 68 መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአውደርዕዩ ላይ ከሚሳተፉ አንጋፋና ወጣት ሰዓሊያን መካከል ዘርይሁን የትም ጌታ፣ ታደሰ መስፍን፣ መዝገቡ ተሰማ፣ ወርቁ ጐሹ፣ ብርትኳን ደጀኔ፣ ሮቤል ተመስገን፣ ሃይሉ ክፍሌ ይገኙበታል፡፡ በአውደ ርዕዩ ላይ የቀረቡ ስእሎች ከአንድ ሺህ እስከ አስራ አምስት ሺህ ብር በመሸጥ ላይ እንደሆኑ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ ሥነጥበባትና ዲዛይን ትምህርት ቤት የ2001 ዓ.ም የከፍተኛ ማእረግ ተመራቂ የሆነውን አርቲስት ፍቃዱ አያሌውን ባንኮክ፣ ታይላንድ ለማሳከም ከ450ሺህ ብር በላይ የተጠየቀ ሲሆን ይህንኑ ከግምት በማስገባት አውደርእዩ የተዘጋጀበት የአዲስ አበባው ጣይቱ ሆቴል ባለቤቶች በቀን ሁለት ሺህ ብር ይከራይ የነበረውን አዳራሽ ለ12 ቀናት በነፃ ፈቅደዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ከጀርመን የልማት ተቋም (GIZ) ድጋፍ ተጠይቆ ምላሽ እየተጠበቀ ሲሆን ሰዓሊው ከእለት ወደ እለት ህመሙ እየጠናበት እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ሠዓሊ ፍቃዱን መርዳት የሚፈልጉ በስልክ ቁጥር +2510919193132 እና +251911635840 ደውለው መርዳት እንደሚችሉ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡

በ8ኛው የቢግ ብራዘር አፍሪካ ሪያሊቲ ሾው ከሚሳተፉት 28 ተወዳዳሪዎች ሁለት ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙበት ታወቀ፡፡ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን የ26 ዓመቷ መምህር እና የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነችው ቤቲ እና በደቡብ አፍሪካ ነዋሪና ተማሪ የሆነው የ23 ዓመቱ ቢምፕ ናቸው፡፡ መላው አፍሪካ በቀጥታ ስርጭት በሚያየው ውድድር በመሳተፌ ልዕልት አድርጎኛል ያለችው ቤቲ በውድድሩ ካሸነፈች በሽልማት ገንዘቡ የትራቭል ኤጀንሲ ማቋቋም እፈልጋለሁ ብላለች፡፡ በቢግ ብራዘር አፍሪካ ላይ በመሳተፍ የማገኘው ልምድ አጓጉቶኛል ያለው ቢምፕ በበኩሉ ፤ ውድድሩ ሃገሩን ለማስጠራት የሚችልበት መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ገልፆ፤ ማሸነፍ ከቻለ በአዲስ አበባ የመዝናኛ ክለብ የመክፈት ሃሳብ እንዳለው ተናግሯል፡፡ ከመምህርነት ሙያዋ ባሻገር በአስተርጓሚነት የምትሰራው ቤቲ በቢግ ብራዘር አፍሪካ ኢፊሴላዊ ድረገፅ እራሷንነ ስትገልፅ ብልህ፤ በራስ መተማመን ያላት፤ ወሳኝ ሁኔታዎች በቁርጠኝነት የምጋፈጥ ነኝ ብላለች፡፡

ቀጠሮ አክባሪ፤ ምክንያታዊ እና ብዙ የሚያወሩ ሰዎችን እንደምትጠላ የምታሳውቀው ቤቲ መፅሃፍ የማነበብ ዝንባሌ እንዳላት አመልክታ ከሁሉ ማንበብ የምትወደው የግል ማስታወሻዋን እንደሆነ ገልፃለች፡፡ አፍሪካውያን ማንኛውንም ነገር ማሳካት እንደሚችሉ ለዓለም ህዝብ ያሳዩ ህዝቦች ናቸው የምትለው ቤቲ በደብረዝይት ያለው ኩሪፍቱ ሪዞርት ተወዳጅ መዝናኛዋ እንደሆነ ገልፃ የዓለም ሙዚቃ እና ፊልም ወዳጅ በመሆኗ ሆሊውድን ለማየት ሁሌም ያጓጓኛል ብላለች፡፡ ትውልዱ በአዲስ አበባ ቢሆንም አሁን በሚማርበት ደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ቢምፕ በበኩሉ ራሱን ታማኝ፤ ግልፅ፤ አስተማማኝ እና ሃላፊነት ተቀባይ አድርጎ ይገልፃል፡፡ አፍሪካውያን ጓደኞች እንግዳ ተቀባዮች እና ብዙ አስደናቂ የባህል መስቦች ያሏቸው ህዝቦች ናቸው የሚለው ቢምፕ በቢግ ብራዘርስ ላይ በመካፈል በቲቪ መታየቱን መላው ቤተሰቡ ስለወደደለት ደስ ብሎኛል ብሏል፡፡

በገጣሚና ጋዜጠኛ በረከት በላይነህ የተፃፈው “የመንፈስ ከፍታ” የተሰኘ የግጥም መድበል ሰኞ በ11፡30 በዋቢሸበሌ ሆቴል ይመረቃል፡፡ በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች የተከፋፈለው “የመንፈስ ከፍታ”፡ የገጣሚው 48 ያህል ወጥ ግጥሞችና፣ ጃላላዲን ሩሚን ጨምሮ ሌሎች የታወቁ የፋርስ ገጣሚያን የፃፏቸው 31 ትርጉም ግጥሞች ተካተውበታል፡፡ በምረቃ ስነስርአቱ ላይ ታዋቂ ወጣትና አንጋፋ ገጣሚያን ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የመጽሐፉ ዋጋ 30 ብር ነው፡፡ ገጣሚው በቅርቡም “ንፋስ አፍቃሪዎች” የተሰኘ የግጥም ሲዲ አሳትሞ ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡

በየሁለት ሳምንቱ በመፃሕፍት ላይ የንባብ እና የውይይት መድረክ በማድረግ የሚታወቀው ሚዩዚክ ሜይ ዴይ የመወያያ ሥፍራውን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ሬዲዮ ፋና አካባቢ ወደሚገኘው ብሔራዊ ቤተመፃሕፍትና ቤተመዛግብት ድርጅት (ወመዘክር) አዛወረ፡፡ ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቤተመፃሕፍትና ቤተመዛግብት አዳራሽ ለውይይት የሚቀርበው መጽሐፍ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ በ1993 ዓ.ም ያሳተመው የኮሌጅ ቀን ግጥሞች” የተሰኘ የግጥም መድበል እንደሆነ ታውቋል፡፡

በመጽሐፉ ከተሰነዱት ግጥሞች መካከል የኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) “በረከተ መርገም” እና የዮሐንስ አድማሱ “እስቲ ተጠየቁ” ይገኙበታል፡፡ መነሻ ሃሳብ በማቅረብ ለሶስት ሰዓታት የሚዘልቀውን ውይይት የመሻ ሃሳብ በማቅረብ የሚመሩት የሥነጽሑፍ ባለሙያው የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ ገዛኸኝ ፀጋው ናቸው፡፡

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ከዋይት ሃውስ ከወጡ ወዲህ ባለፉት 12 አመታት በተለያዩ ቦታዎች ንግግር በማቅረብ ብቻ 106 ሚሊዮን ዶላር ማግኘታቸው ሲኤንኤን ዘገበ፡፡ ቢል ክሊንተን በአንድ መድረክ ንግግር ለማቅረብ በአማካይ 200ሺ ዶላር ይከፈላቸዋል፡፡ የቀድሞው ፕሬዝዳንት በንግግር አዋቂነታቸው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተፈላጊ ናቸው፡፡ በናይጄርያ ሌጎስ በአንድ መድረክ የተከፈላቸው 700ሺ ዶላር በተመሳሳይ የስራ ድርሻ የተገኘ ትልቁ ክፍያ እንደሆነ ታውቋል፡፡

ቢል ክሊንተን በንግግር አዋቂነታቸው አምና ከፍተኛ ተፈላጊነት እንደነበራቸው የሚገልፀው ሲኤንኤን በመላው ዓለም በ73 መድረኮች በመስራት 17 ሚሊዮን ዶላር እንደተከፈላቸው ገልጿል። ቢሊ ክሊንተን 42ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩ ናቸው፡፡ በበጎ አድራጊነት፤ በንግግር አዋቂነት ፤ በዴሞክራት ፖለቲከኛነት እና በጥብቅና ሙያቸው ከፕሬዝዳንትነት ከወረዱ በኋላ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸው ቢል ክሊንተን 80 ሚሊዮን ዶላር ሃብት እንዳላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከኤሌክትሮኒክስ ሙዚቃ ዲጄዎች፣ ሆላንዳዊ ዲጄ ቲዬስቶ 75 ሚሊዮን ዶላር መሪነቱን እንደያዘ ሴለብሪቲ ኔትዎርዝ ገለፀ። ለግሉ በገዛው ጄት አውሮፕላን በመላው ዓለም በመዘዋወር የሚሰራው የ44 ዓመቱ ዲጄ ቲዬስቶ፣ በአማካይ ለአንድ ምሽት ስራ እስከ 250ሺ ዶላር እየተከፈለው ባለፈው ዓመት ብቻ ሃያ ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል። ቲዮስቶ፣ በሙዚቃ መሸጫ ሱቅ እየሰራና ፒዛ እየተላላከ ይኖር እንደነበር አስታውሶ፣ ዲጄነትን የጀመረ ጊዜ ባንድ ምሽት ሃምሳ ዶላር ብቻ ይከፈለው እንደነበር ገልጿል።

ከዲጄነት ጎን ለጎን፣ እንደ ሌሎቹ ዲጄዎች በሙዚቃ ፕሮዲውሰርነትና በአቀናባሪነት እየሰራ አምስት ሙሉ አልበሞችን እና ሶስት የሪሚክስ አልበሞችን ለገበያ አብቅቷል፡፡ ባንድ ምሽት በአማካይ ከ100ሺ እስከ 500ሺ ዶላር ከሚከፈላቸው ታዋቂ የኤሌክትሮኒክስ ሙዚቃ ዲጄዎች መካከል አንዳንዶቹ፣ የግል ጄት አውሮፕላንና ውድ ቪላ እየገዙ ለቅንጦት ኑሮ ገንዘባቸውን ሲያፈሱ ይታያሉ። ሴሌብሪቲ ኔትዎርዝ ባወጣው የዲጄዎች ደረጃ፣ ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ የወጡት ከሃምሳ እስከ ስድሳ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ሃብት ያላቸው ዲጄዎች ናቸው።