Administrator

Administrator

  በደቡብ ሱዳን ለአራት አመታት ያህል በዘለቀው የእርስ በእርስ ግጭት ሳቢያ በአገራቸው እና ከአገራቸው ውጪ የተፈናቀሉ የአገሪቱ ህጻናት ቁጥር ከ2 ሚሊዮን በላይ መድረሱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማስታወቁን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ በታህሳስ ወር 2013 በተቀሰቀሰውና ይህ ነው የሚባል ዘላቂ መፍትሄ ሳይገኝለት ለአመታት በቀጠለው የእርስ በእርስ ግጭትና የፖለቲካ ቀውስ ሳቢያ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ የአገሪቱ ዜጎች ወደ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያና  ሱዳን እንዲሰደዱ ማድረጉን  የጠቆመው ዘገባው፤ ከእነዚህ ስደተኞች መካከልም ከ62 በመቶ ወይም ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ህጻናት መሆናቸውን ገልጧል፡፡
የእርስ በእርስ ጦርነቱ ሌሎች ከ1 ሚሊዮን በላይ ደቡብ ሱዳናውያን ህጻናትንም በአገራቸው ውስጥ ከመኖሪያ ስፍራቸው ማፈናቀሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅትና የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ማስታወቃቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡
የእርስ በእርስ ግጨቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያን መገደላቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ የተፈናቀሉ አጠቃላይ ዜጎች ቁጥርም 3.5 ሚሊዮን እንደሚደርስ አስታውቋል፡፡

መዝናኛው ኢንዱስትሪ የምታገኘውን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ ያቀደቺው ሳኡዲ አረቢያ፣ በአይነቱ ልዩ የሆነና የላስ ቬጋስን ያህል ስፋት ይኖረዋል የተባለውን ግዙፍ የመዝናኛ ከተማ ግንባታ ከስድስት ወራት በኋላ እንደምትጀምር መነገሩን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ከመዲናዋ ሪያድ በስተደቡብ አቅራቢያ በሚገኝ 334 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ስፍራ ላይ የሚቆረቆረውና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ወጪ የሚደረግበት ይህ ልዩ የመዝናኛ ከተማ፤ ለነዋሪዎችና ለውጭ አገራት ጎብኝዎች የተለያዩ የመዝናኛ፣ የስፖርትና የባህላዊ ትርዒቶች አገልግሎት እንደሚሰጥ ዘገባው አስታውቋል፡፡
እጅግ ማራኪ ፓርኮች እንደሚኖሩት የተነገረለት ይህ ግዙፍ መዝናኛ ከተማ፣ አለማቀፍ ተፈላጊነት እንደሚኖረውና ለአገሪቱ ከፍተኛ ገቢ ያስገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
ሳኡዲ አረቢያ አዳዲስ የገቢ አማራጮችንና የኢኮኖሚ መስኮችን በማስፋፋት ኢኮኖሚዋን ከነዳጅ ጥገኝነት ለማላቀቅ አቅዳ እየሰራች እንደምትገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ የዚህ ጥረት አንዱ አካል የሆነው የግዙፍ የመዝናኛ ከተማ ግንባታ ፕሮጀክት በአራት አመታት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክቷል፡፡

  የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በተለያዩ ብሄራዊ፣ አህጉራዊና አለማቀፍ ስብሰባዎች ላይ በተደጋጋሚ ሲያንቀላፉ የሚያሳዩ ፎቶግራፎችንና ቪዲዮዎችን በማህበራዊ ድረ ገጾች የሚያሰራጩና በታላቁ መሪያችን ላይ የሚያላግጡ ሰዎች ተሳስተዋል፣ ሙጋቤ በስብሰባዎች ላይ አይናቸውን ገርበብ ስለሚያደርጉ ያንቀላፉ ይመስላሉ እንጂ በጭራሽ አይተኙም ሲሉ የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ አስተባብለዋል፡፡
“ታላቁ መሪያችን አይኖቻቸው የብርሃን ጨረሮችን የመቋቋም አቅም ስለሌላቸው በተደጋጋሚ አይኖቻቸውን ገርበብ ስለሚያደርጉና ጎንበስ ስለሚሉ ያንቀላፉ ይመስላሉ እንጂ፣ ብዙዎች በማህበራዊ ድረገጾች እንደሚያብጠለጥሏቸው ስብሰባቸውን አቋርጠው አያንቀላፉም” ሲሉ የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ ጆርጅ ቻራምባ፣ ሄራልድ ለተባለው የአገሪቱ መንግስት ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡ እርጅና ተጫጭኗቸው አቅም ቢከዳቸውም በቀጣዩ አመት በሚካሄደው የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር ታጥቀው መነሳታቸውንና ስልጣናቸውን እንደዋዛ ለማንም እንማያስረክቡ ያስታወቁት የ93 አመቱ ፕሬዚዳንት ሙጋቤ፤ ሰሞኑን ለአይን ህክምና ወደ ሲንጋፖር ማቅናታቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሙጋቤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ፣ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ እና የአረብ-አፍሪካ ጉባኤን ጨምሮ በበርካታ አህጉራዊና አለማቀፋዊ ስብሰባዎች ላይ እንቅልፍ ወስዷቸው የሚያሳዩ አስቂኝ ፎቶግራፎችና የቪዲዮ ምስሎች በተለያዩ ድረገጾች ላይ በስፋት ተሰራጭተው ይገኛሉ፡፡

    የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ዜጎች የሆኑ ስደተኞችን አሳፍረው ከሊቢያ በመነሳት በሜዲትራኒያን ባህር ወደ አውሮፓ በመጓዝ ላይ በነበሩ ሁለት ጀልባዎች ላይ ሰሞኑን በደረሱ አደጋዎች በድምሩ 250 ያህል ስደተኞች መሞታቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ጀልባዎቹ ከመጫን አቅማቸው በላይ በርካታ ስደተኞችን አሳፍረው በመጓዝ ላይ ሳሉ ባለፈው እሁድና ሰኞ ከሊቢያ አቅራቢያ በሚገኙ የሜዲትራኒያን ባህር አካባቢዎች የመስጠም አደጋ እንዳጋጠማቸው የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው እሁድ ከሊቢያ አቅራቢያ አደጋ በደረሰባት ጀልባ 163 ያህል ስደተኞች መሞታቸውን የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን ባለፈው ማክሰኞ ማስታወቁን ገልጧል፡፡
የተወሰኑ ስደተኞች ከአደጋዎቹ ተርፈው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ለህልፈተ ህይወት ከተዳረጉት አፍሪካውያን ስደተኞች መካከል ህጻናት እንደሚገኙበትና የሴት ስደተኞች ቁጥርም በርካታ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ከ1 ሺህ 300 በላይ አፍሪካውያን ስደተኞች ከሊቢያ በመነሳት ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት በአስቸጋሪ የጀልባ ጉዞ ላይ ሳሉ ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ባለፈው ሳምንት ብቻ ከ6 ሺህ በላይ አፍሪካውያን ስደተኞች ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደተለያዩ የአውሮፓ አገራት መጓዛቸውን አስረድቷል፡፡
ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ወደ አውሮፓ የተጓዙ አፍሪካውያን ስደተኞች ቁጥር ከ43 ሺህ በላይ መድረሱንም የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

 ባለፈው ማክሰኞ…
ከወደ ዋይት ሃውስ አንድ አስደንጋጭና ያልተጠበቀ ዜና ወጣ…
አነጋጋሪው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዋይት ሃውስ ባወጡት መግለጫ፣ ከጆርጅ ደብሊው ቡሽ እስከ ክሊንተን፣ ከኦባማ እስከ ትራምፕ የአገዛዝ ዘመናት በአነጋጋሪነት የዘለቁትን ታዋቂውን የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ጄምስ ኮሚን ከስራ ገበታቸው ማባረራቸውን አስታወቁ፡፡
እ.ኤ.አ በ2013 በያኔው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ተመልምለው ኤፍቢአይን ለአስር አመታት በዳይሬክተርነት ሊመሩ የተመረጡት የ56 አመቱ ሪፐብሊካን ጄምስ ኮሚ፣ ገና ሶስት አመት ከመንፈቅ ብቻ እንደሰሩ፣ ባለፈው ማክሰኞ ባልተጠበቀው የትራምፕ ውሳኔ ታላቁን ተቋም ከመምራት ታገዱ፡፡
የትራምፕ አስተዳደር የኤፍቢአይ ዳይሬክተሩን ጄምስ ኮሚ ከስራ ለማባረር የወሰነው፣ በሄላሪ ክሊንተን የኢሜይል ቅሌት ዙሪያ ኤፍቢአይ ያከናወነውን ምርመራ በፊታውራሪነት የመሩት ሰውዬው፣ ምርመራውን በሚያከናውኑበት ወቅት በርካታ ስህተቶች መፈጸማቸውንና ብቁ አለመሆናቸውን በማረጋገጡ እንደሆነ አስታውቋል። ባለፈው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመጨረሻው ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ድንገት ብቅ ብለው ባወጡትና በወቅቱ ከተቀናቃኛቸው ዶናልድ ትራምፕ ጋር እልህ አስጨራሽ የፍጻሜ ፍልሚያ ላይ የነበሩትን ሄላሪ ክሊንተንን የማሸነፍ ዕድል የከፋ አደጋ ላይ የጣለ በተባለው የዳግም የኢሜይል የቅሌት ምርመራ ውሳኔ ብዙዎችን አስደንግጠው ነበር - አነጋጋሪው ኮሚ፡፡
ሄላሪን አደጋ ላይ የጣለውን ይህን አደገኛ ውሳኔ ለመላው አለም ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ ተፎካካሪያቸው ዶናልድ ትራምፕ፣ ጠላቴን ድባቅ መታልኝ ያሏቸውን ጄምስ ኮሚን፣ ለፍትህ የቆመ ጀግና ሲሉ በአደባባይ አሞካሽተዋቸው ነበር፡፡ ይህ ከሆነ ከወራት በኋላ ታዲያ፣ እነሆ ባለፈው ማክሰኞ ዶናልድ ትራምፕ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ሆነው ብቅ አሉና፣ ያሞካሹትን ሰው መልሰው ለማዋረድና ለመወረፍ ደፈሩ- “ታላቁን ተቋም በቅጡ የመምራት ብቃት የሌለው ሰው ነው!... በአፋጣኝ ስራውን ይለቅ ዘንድ ፈርደንበታል!” በማለት፡፡
ጄምስ ኮሚ ከዳይሬክተርነታቸው መነሳታቸው በይፋ መነገሩን ተከትሎ፣ ዶናልድ ትራምፕ አስደንጋጩን ውሳኔ ለማሳለፍ ያነሳሳቸውን ሰበብና የውሳኔውን ስረ መሰረት በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶችና ትንተናዎች እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡ ብዙዎች ውሳኔውን የሚያያይዙት ደግሞ ባለፈው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዘመቻ ወቅት ሩስያ ጣልቃ በመግባት ትራምፕን አግዛለች የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ ኤፍቢአይ የጀመረውን ምርመራ የሚመሩት ጄምስ ኮሚ ከመሆናቸው ጋር ነው፡፡
ብዙዎች እንደሚሉት፤ ትራምፕ በኮሚ ላይ ውሳኔውን ያሳለፉት፣ በምርመራው ሂደት እኔን ሊጎዱ የሚችሉ ድርጊቶችን ሊፈጽሙ ይችላሉ ከሚል ስጋት በመነጨ ነው፡፡
ጄምስ ኮሚ ኤፍቢአይን በዳይሬክተርነት በመሩባቸው አመታት፣ የተሸናፊዋን ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ የሄላሪ ክሊንተንን የኢሜይል ቅሌት ጨምሮ ቁልፍ የተባሉ የምርመራ ስራዎችን ያከናወኑ ሲሆን፣ ሰውዬው በሚይዟቸው አቋሞችና በሚያስተላልፏቸው አወዛጋቢ ውሳኔዎች በአንዳንዶች ብቁ መሪ በሚል ቢሞገሱም፣ ብልጣብልጥ በሚል የሚተቿቸውም አያሌ ናቸው፡፡
የሰውዬውን አወዛጋቢነት ከፍ ካደረጉት ሁነቶች መካከል አንዱ፣ ባለፈው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመጨረሻ ወሳኝ ምዕራፍ ሰሞን የሰሩት አነጋጋሪና አደገኛ የተባለ ያልተጠበቀ ድርጊት ነው። ሄላሪ ከትራምፕ ጋር በእልህ አስጨራሽ የምርጫ ፉክክር ውስጥ አልፈው ወደመጨረሻው ምዕራፍ በተሸጋገሩበት በዚያ ወሳኝ ወቅት ላይ ነበር፣ ጄምስ ኮሚ ድንገት ብቅ ብለው አነጋጋሪውን ውሳኔ ይፋ ያደረጉት፡፡
ኤፍቢአይ በሄላሪ ክሊንተን የኢሜይል አጠቃቀም ዙሪያ የጀመረውን ምርመራ ማስረጃ ስላልቀረበበት መዝጋቱን በሃምሌ ወር በይፋ ያስታወቁት ኮሚ፣ ሄላሪ ከትራምፕ ጋር ትንቅንቅ ላይ በነበሩበትና አንደኛቸው የሌላኛቸውን የቆየ ስህተትና የከረመ ድብቅ ጉድ እየፈለፈሉ በአደባባይ በማሳጣትና ደጋፊ በማሳጣት በተጠመዱበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ብቅ ብለው፣ በሄላሪ የኢሜል ቅሌት ዙሪያ ጀምረን ትተነው የነበረውን ምርመራ እንደገና ከፍተነዋል አሉ፡፡
የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፉክክሩ በተጧጧፈበትና ቀጣዩ የአሜሪካ መሪ ማን ይሆን የሚለው ጥያቄ መልስ ሊያገኝ የ11 ቀናት ዕድሜ ብቻ በቀረበት በዚያ ወሳኝ ወቅት ይፋ የተደረገው ድንገተኛው የኮሚ መግለጫ፣ ሄላሪንና ደጋፊዎቿን በድንጋጤ ክው ሲያደርግ፣ ትራምፕንና ደጋፊዎቹን አስፈነጠዘ። ጄምስ ኮሚ በወሳኝ ወቅት ላይ አጉል ሴራ ይዘው ከተፍ ያሉ መሰሪ ተብለው በሄላሪ ሰዎች ሲብጠለጠሉ፣ በትራምፕ ሰዎች ደግሞ ለእውነት ተሟጋች ድንቅ ባለሙያ ተብለው ተወደሱ፡፡
የኮሚ አነጋጋሪነት የሚጀምረው የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን በነበሩበት በጆርጅ ደብሊው ቡሽ የስልጣን ዘመን ነው፡፡ በወቅቱ ከኤሌክትሮኒክ ቁጥጥር ፕሮግራም ጋር በተያያዘ የሚያራምዱት አቋምና የሚያስተላልፉት ውሳኔ ብዙዎችን ያስገርም እንደነበር ይነገራል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፣ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተንና በሞኒካ ሊዊንስኪ ቅሌት ውስጥም የጄምስ ኮሚ ስም አብሮ ሲነሳ የሚኖር የአገሪቱ አነጋጋሪ የቅሌት ታሪክ አካል ነው፡፡
ጄምስ ኮሚ ባለፈው ረቡዕ ለኤፍቢአይ በጻፉት የስንብት ደብዳቤ፣ ትራምፕ ለምን ይህን ውሳኔ አስተላለፉብኝ የሚለውን ጉዳይ በማጣራት የማጠፋው ጊዜ አይኖረኝም ብለዋል፡፡

   ከደርባ ሲሚንቶ በስተቀር ከግሉ ዘርፍ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ብድር ወስዶ የሚሰራ ድርጅት እንደሌለ የተገለፀ ሲሆን፣ ባንኩ ከግል ኢንቨስተሮች ጋር ለመሥራት ፈቃደኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ ም/ፕሬዚዳንት፤ የግል፣ የመሰረተ ልማትና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ኃላፊ ሚ/ር ፒየር ጉስሌይን፣ በኢትዮጵያ ለ3 ቀን ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክተው ባለፈው ማክሰኞ በራዲሰን ብሉ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት፣ ከኢንዱስትሪና ከንግድ ሚኒስትሮች ጋር፣ እንዲሁም የግል ዘርፉን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ያደረጉት ውይይት ፍሬያማ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ሚ/ር ጉስሌይን፤ ድርጅታቸው በ2001 ዓ.ም ለደርባ ሲሚንቶ 55 ሚሊዮን ዶላር ያበደረ ብቸኛው የግል ባንክ መሆኑን ጠቅሰው፣ ደርባን ሲሚንቶን ሲጎበኙ፣ ጥራት ባለው እንቅስቃሴውና ለአህጉሩ የኢኮኖሚ ዕድገት በሲሚንቶ አቅርቦት እያደረገ ባለው አስተዋጽኦ መርካታቸውን ገልፀዋል፡፡
ሌሎች የግል ኢንቨስተሮች ከባንኩ ጋር የማይሰሩትና የማይበደሩት፣ ባንኩ፣ ለግሉ ዘርፍ እንደሚያበድር ግንዛቤው ስለሌላቸው እንደሆነ ጠቅሰው፣ “በተለይ በኤክስፖርት ዘርፍ ከተሰማሩ የግል ኢንቨስተሮች ጋር ለመስራት ገንዘብ አዘጋጅተን እየተጠባበቅን ነው፤ ኑ አብረን እንሥራ!” በማለት ጋብዘዋል፡፡
ም/ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ስላደረጉት ጉብኝት በሰጡት መግለጫ፣ ተደጋጋሚ ድርቅ፣ ዓለም አቀፍ የምርት ፍላጎት መቀነስና የሸቀጦች ዋጋ መውደቅ ቢያጋጥማትም፣ ኢትዮጵያ ጠንካራና እውነተኛ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ዕድገት ስላሳየች፣ የትራንስፎርሜሽን እቅዷን ታሳካ ዘንድ ባንኩ፣ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
“ባንኩ፣ ለአፍሪካ ያለው አመለካከት፣ ቅድሚያ በሚሰጣቸው አምስት ስትራቴጂዎች ይጠቃለላል” ያሉት ሚ/ር ጉስሌይን፣ “እነሱም፣ አፍሪካን የመብራትና የኃይል ተጠቃሚ ማድረግ፣ አፍሪካን መመገብ፣ አፍሪካን በኢንዱስትሪ ማበልጸግ፣ አፍሪካን አንድ ማድረግና የአፍሪካን ህዝብ ኑሮ ጥራት ማሻሻል ነው” ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መስራት የጀመረው ከ42 ዓመት በፊት በ1975 ሲሆን እስከ አሁን ወጪያቸው በአጠቃላይ 4.6 ቢሊዮን ዶላር የሆነ 130 ፕሮጀክቶች (በመሰረተ ልማት፣ በኃይል፣ በውሃና ሳኒቴሽን) በማህበራዊ፣ በእርሻና በግሉ ዘርፍ ተከናውነዋል፡፡ ባንኩ፣ በአሁኑ ወቅት በ2 ቢሊዮን ዶላር 26 ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡
ባንኩ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ባለው ተሳትፎ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የጠቀሱት ም/ፕሬዚዳንቱ፤ ኢትዮጵያና ጅቡቲን ለሚያገናኘው ስትራቴጂያዊ የኃይል አቅርቦት፣ ኢትዮጵያ - ኬንያን ለሚያገናኘው የመንገድ ፕሮጀክት፣ ለገጠር የኤሌክትሪክ አቅርቦትና መቀሌን ከዳሎል ለሚያገናኘው የኃይል ማሰራጫ መስመር፣ ባንኩ፣ 900 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረጉን ተናግረዋል። እንዲሁም ባንኩ፣ የምስራቅ አፍሪካን የኃይል ፕሮጀክት እየደገፈ ነው፡፡ እነዚህ ተግባራት፣ የገጠርና የከተማ ቤቶች፣ የኢንዱስትሪ ዞኖች፣ የማዕድን ማዕከላት ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ማስቻል፣ አፍሪካን ብርሃናማ ማድረግና ለአፍሪካ ኃይል (ፓወር አፍሪካ) ቅድሚያ መስጠት ይሆናል ተብሏል፡፡
አፍሪካን አንድ ማድረግ ወይም ማስተሳሰር በሚለው የባንኩ ስትራቴጂ፣ በትራንስፖርት ዘርፍ አገራዊና አኅጉራዉ ትስስርን ለመፍጠር ለምሳሌ የኢትዮ - ኬንያ ትራንስፖርት ኮሪደር ፕሮጀክት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቦሌን አለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ ደረጃ ለማሳደግ፣ ለበርካታ መንገዶች መገንቢያና ማደሻ፣ ባንኩ አንድ ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረጉ ታውቋል፡፡
የእርሻውን ዘርፍ ለመደገፍና ለማዘመን፣ 7, 000 ሄክታር የሚሸፍነውንና 77 ሚሊዮን ኪዩቢክ የመያዝ አቅም ያለውን የካጋ መስኖ ፕሮጀክት፣ በእርሻው ዘርፍ ዝናብ ላይ የሚታየውን ጥገኝነት ለመቀነስና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ባንኩ ለኢትዮጵያ 630 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል። እንዲሁም የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ አቅም ለማጎልበት በተለይም በሲሚንቶ ምርትና በማዕድን ዘርፍ 160 ሚሊዮን ዶላር በብድር ተሰጥቷል፡፡ እንዲሁም ባንኩ፣ ለውሃ አቅርቦትና ለሳኒቴሽን 340 ሚሊዮን ዶላር፣ ለበጀት ድጎማ፣ ለማኅበራዊ አገልግሎት፣ ለትምህርት፣ ጤናና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማሻሻልና ለመደገፍ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረጉ ተገልጿል፡፡ 

 መሰረቱን በአሜሪካ አገር ካሊፎርኒያ ከተማ ውስጥ ያደረገና በአራት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተቋቋመው ‹‹አሪፍ ዘፈን›› የቴክኖሎጂ ኩባንያ፣ የኢንተርኔት አልበም ሽያጭ በቴዲ አፍሮ አዲስ አልበም መጀመሩን አስታወቀ፡፡
የኩባንያው የማርኬቲንግና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሪት ምዕራፍ ክፍሌ ለአዲስ አድማስ እንደገለጸችው፤ ኩባንያቸው  በአይነቱ አዲስ የሆነውን ይህንን ቴክኖሎጂ ወደ አገር ውስጥ በማምጣት፣ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ በማሰብ ወደ ሥራው ገብተናል ብላለች፡፡ ኩባንያው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ባደረገው የሥራ ስምምነት መሰረት፣ አገልግሎቱን ለሚፈልጉ ደንበኞች ከስልካቸው ሂሳብ ላይ ተቆራጭ በማድረግ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል አሠራር መጀመሩን ወ/ሪት ምዕራፍ ተናግራለች፡፡ እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፤ ከገቢው 40 በመቶ የሚሆነው ለኢትዮ ቴሌኮም የሚከፈል የአገልግሎት ክፍያ ሲሆን ከቀሪው 60 በመቶ ላይ ቫትና የሾርት ኮድ ክፍያ ተቀናሽ ሆኖ ቀሪው ለባለመብቱ አርቲስት ተከፋይ ይሆናል፡፡ የአልበሙን ሽያጭ አርቲስቱ እራሱ በኢንተርኔት የሚከታተል ሲሆን የተሸጠውን ዘፈን መጠን፣ የተሸጠበትን ጊዜና ሰዓት ሁሉ በቀጥታ መከታተል የሚያስችል መሆኑ አሰራሩን ተመራጭ ያደርገዋል ብላለች፡፡  የአሰራር ሲስተሙ ደንበኛው በግዥ ያገኘውን ዘፈን ለሌላ 3ኛ ወገን ለማስተላለፍ እንዳይችል በሚያግድ መልኩ የተበጀ ሲሆን ይህም የቅጂ መብትን በማስከበሩ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብላለች፡፡ ለተጠቃሚውም ከአንድ አልበም ላይ የሚፈልገውን ሙዚቃ ብቻ መርጦ ለመግዛት የሚያስችል ከመሆኑ ባሻገር የሚፈልጋቸው ዘፈኖች በአንድ ቦታ ላይ (ጥቅል ውስጥ) ተሰባስበው መቀመጣቸው ለአጠቃቀም ምቹ ሁኔታን ስለሚፈጥር ተመራጭ ያደርገዋል ስትል አስረድታለች፡፡  
በአዲሱ የቴዲ አፍሮ አልበም ወደ ሥራ የገባው አዲሱ “አሪፍ ዘፈን” አፕሊኬሽን፤ የቅጅ መብትን በማስጠበቅና አድማጭም ጥራት ያለውን ትክክለኛ ክፍያ የተፈፀመበትን የሙዚቃ ሥራ መጠቀም እንዲችል የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ለሙዚቃ ኢንዱስትሪ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚገመት አለመሆኑን ወ/ሪት ምዕራፍ ገልፃለች፡፡ በቀጣይም ከሌሎች ድምፃውያን ጋር ስምምነቶችን በመፈፀም ዘፈኖቻቸውን በኢንተርኔት ለሽያጭ እንደሚያቀርቡም ሃላፊዋ አስታውቃለች፡፡

    አገር በቀሉ በላይአብ ሞተርስ የኪያ ሞተርስ ኮርፖሬሽን ሞዴል የሆኑትን ሁለት አውቶሞቢሎች ሪዮና ፒካንቶ የተባሉትን በአገር ውስጥ ገጣጥሞ ለገበያ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡
ከትናንት በስቲያ ማምሻውን በሸራተን አዲስ በተካሄደው መኪኖቹን የማስተዋወቅ ሥነ - ሥርዓት የበላይአብ ሞተርስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፈቃዱ ግርማ፣ በአሁኑ ወቅት  “ታይገር ኖዝ” የተባሉትን ሁለት የኪያ ሞዴል መኪኖች፡- ሪዮና ፒካንቶ ገጣጥመው ለገበያ ማቅረባቸውን ጠቅሰው፤ በ2010 የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ታዋቂ የሆኑትን ሴዳን የመኪና ሞዴል ማለትም ሴራቶ፣ ለስፖርት አገልግሎት የሚውሉና ዘርፈ ብዙ
አገልግሎት ያላቸውን መኪኖች ለማቅረብ ማቀዱን ገልጸዋል፡፡
ኪያ ሞተርስ ኮርፖሬሽን በአሜሪካ ቀዳሚ ከሆነው የመኪና አምራች ኩባንያ ከፎርድ ጋር በጋራ መሥራት ከጀመረ በኋላ፣ በዓመት 1.5 ሚሊዮን መኪኖችን እንደሚያመርት ጠቅሰው፣ ኪያ፣ በ8 አገሮች 13 የመኪና ማምረቻና መገጣጠሚያ፣  በ172 አገሮች መሸጫና አገልግሎት መስጫዎች ፣
ዓመታዊ ገቢው 14.6 ቢሊዮን ዶላርና 40,000 የሙሉ ሰዓት ተቀጣሪ ሠራተኞች እንዳሉትና የኪያ መኪኖች በ2013 “ኢንተርናሽናል ካር ኦፍ ይር አዋርድ” ማሸነፉን ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በ150 ሚሊዮን ብር ገጣጥሞ ለገበያ ያቀረባቸው መኪኖች ለኢትዮጵያ መንገዶች ፋሽን ናቸው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ መኪኖቹ ሰፊ የቀለም ምርጫ፣ ውበት፣ ጥንካሬ፣ ምቾት፣ በፈለጓቸው ጊዜ መገኘት የሚችሉ፣ በአውቶማቲክና በእጅ ማርሽ የሚሠሩ መሆናቸውን፣ የሚገጣጠሙት መኪኖች ለ150 የአንድ ፈረቃ ሰራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩን፣ ፈረቃው ከአንድ በላይ ከሆነ የሰራተኞቹ ቁጥር ከዚህ እንደሚበልጥና እነዚህን መኪኖች የሚገዙ ሰዎች በአገር ውስጥ ከሚሸጡ ተመሳሳይ መኪኖች ጋር ሲነፃፀሩ ከ15-20 በመቶ ቅናሽ ያገኛሉ፤ ሌሎችም ጥቅም አሏቸው በማለት አብራርተዋል፡፡
በላይአብ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የ11 ወንድማማችና የአንድ እህት የቤተሰብ ቢዝነስ ሲሆን “በላይ አብ” የሚለው ስም ለሟች አባታቸው ለአቶ በላይ ሀብተ ጊዮርጊስ መታሰቢያ የተሰየመ ነው፡፡ ኢንቨስትመንት ግሩፑ፣ 11 ኩባንያዎች ሲኖሩት፣ አምስቱ ትላልቅ ኩባንያዎች፣ በላይአብ ኤሌክትሪክና ዳታ ኬብል፣ በላይአብ ሞተርስ፣ ጎልደን ቱሊፕ አዲስ አበባ ሆቴል፣ ሊኮን ኮንስትራክሽን ግሬድ BC-2 ኮንትራክተርና ሌዊስ
ኮንስትራክሽን ማቴሪያልስ ሳፕላይ ኢንተርፕራይዝ ናቸው፡፡
እነዚህ አምስቱ ኩባንያዎች የተመሰረቱበት ካፒታል 579 ሚሊዮን ብር ሲሆን በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ካፒታላቸው መስሪያ ካፒታላቸውን ጨምረ ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ ኢንተርፕራይዞቹ ከ1ሺ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ 

• በሥርዓተ ጥምቀት፣ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ያደረገችው ስምምነት ሲኖዶሱን አወያየ
• “ኢትዮጵያውያን ከሊቃውንቶቻቸው ጳጳስ አይሹሙ” የሚለው ቀኖና፣ ከፍትሐ ነገሥቱ ይወጣል
• በግል አታሚዎች ስሕተት የተጨመረባቸው ፥ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት እንዲስተካከሉ ታዘዘ
• ስለ አቡነ ጳውሎስ እና ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም የሚያወራው ‘ተኣምረ ማርያም’ ይገኝበታል

በክርስትናው የነገረ መለኰት እና የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋራ፣ የቆየ የታሪክ ግንኙነትና የዶግማ አንድነት ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በትምህርተ ሃይማኖት ረገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁለቱ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት መካከል እየታየ ነው ያለው ልዩነት እንዲመረመር፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አዘዘ፡፡
የስብሰባው ምንጮች እንደተናገሩት፣ ምልአተ ጉባኤው ትእዛዙን የሰጠው፣ ምሥጢረ ጥምቀትን በተመለከተ፣ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ ሚያዝያ 20 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ በካይሮ የተፈራሙትን የጋራ ስምምነት የቅርብ መነሻ በማድረግ በተካሔደ ውይይት ነው፡፡
የካቶሊኩ ፖፕ ፍራንሲስ በቅርቡ ግብጽን በጎበኙበት ወቅት፣ ከኮፕት ቤተ ክርስቲያን ፖፕና የእስክንድርያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ጋራ የተወያዩ ሲሆን፤ ከተፈራረሙት ባለ12 አንቀጾች የጋራ ስምምነት ውስጥ፣ አንዱ የሌላውን ምእመን ጥምቀት ላለመድገም የተስማሙበት አቋም(shared baptism) እንደሚገኝበት ተገልጿል። በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት፣ የሥርዓተ ጥምቀቱ አፈጻጸምና የሃይማኖት ምስክርነቱ፣ መሠረታዊ ልዩነት እንዳለው የገለጹ ምንጮች፤ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን አካሔድ፣ የነገረ መለኰትና የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ባላቸውና ኦሪየንታል ተብለው በሚታወቁት፥ የኢትዮጵያ፣ የሶርያ፣ የአርመንና የሕንድ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት ቅዱስ ሲኖዶሶች ያልተመከረበት እንደኾነ አስረድተዋል፡፡
በሥርዓተ ጥምቀት ላይ የሚፈጠረው ልዩነት፣ በሌሎቹ የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በሚኖረው አንድነት ላይ ተጽዕኖ እንዳለው ምንጮቹ ጠቅሰው፥ በሥርዓተ ቊርባን፣ ከአዳማዊ የሃጢአት ውርስ አንጻር የድንግል ማርያም ቅድስና፣ የካህናቱ ሥነ ምግባር (ሲጋራ ማጤስ)፣ የመሳሰሉት ኻያ ያህል ልዩነቶች በውይይቱ ወቅት እንደተነሡ ከቀደሙት ታላላቅ አባቶች አስተምህሮ ጋራ ያላቸው መጣጣም ጥያቄ ማሥነሳቱን አመልክተዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ በየጊዜው በሚያካሒደው ስብሰባ፣ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋራ በትብብር መሥራቱ እንዲጠናከር፣ በተለይም ከግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ለቆየው ግንኙነት ትኩረት እንዲሰጠው ቢያሳስብም፣ በትምህርተ ሃይማኖት ረገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሚታዩት ተናጠላዊ አካሔዶች አንጻር ዶግማዊና ቀኖናዊ አንድነቱ እንዲመረመር ስምምነት ተደርሶበታል፤ የሊቃውንት ጉባኤውም፣ ልዩነቶቹን አጥንቶ ለቀጣዩ ዓመት የጥቅምት ምልአተ ጉባኤ እንዲያቀርብ መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ምልአተ ጉባኤው፣ ግብጻውያን በፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ በጣልቃ(ሥርዋጽ) የጨመሩት ነው የተባለው አንቀጽ በቀጣይ የመጽሐፉ ኅትመቶች እንዲቀር መወሰኑ ተገልጿል። “ኢትዮጵያውያን ከሊቃውንቶቻቸው ጳጳስ አይሹሙ” የሚለው ሥርዋጹ፣ በግብጾች
እንደሚነገረው፣ በኒቂያ ጉባኤ 42ኛ አንቀጽ ያልተወሰነ፣ ሐሰተኛ ቀኖና ነው፤ ተብሏል፡፡
በአራተኛው ክፍለ ዘመን፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ጥያቄና ፈቃድ በግብጽ ከተሾመው ቅዱስ ፍሬምናጦስ በኋላ እስከ 1951 ዓ.ም. ይሾሙ የነበሩት ጳጳሳት ግብጻውያን እንደነበሩ ያስታወሱት ምንጮቹ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ከሥራቸው ለማድረግ ከአገራቸው ነገሥታት ጋራ መክረው ያስገቡት መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከራሷ ልጆች የራሷን ፓትርያርክና ጳጳሳት መሾም ከጀመረች ግማሽ ምእት ዓመት የተቆጠረ በመኾኑ፣ ሥርዋጹ፣ በቀጣይ ኅትመቶች እንዲቀር ቅዱስ ሲኖዶሱ ወስኗል። በስንክሳር የሚያዝያ 10 ቀን ንባብ፣ ከንጉሥ ሐርቤ ጋራ በተያያዘ ያለውም ያለውን ታሪክ፣ በተመሳሳይ መልኩ ከኅትመት እንዲወጣ መወሰኑ ታውቋል፡፡     
በሌላ በኩል፣ በግል አታሚዎች እየታተሙ በሚወጡ የጸሎትና የሥርዓት መጻሕፍት ውስጥ ተጨምረዋል የተባሉ ተኣምራት፣ አግባብ ያልኾኑ የሕዝቦች መጠሪያዎች የመሳሰሉት፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅና ውጭ የተፈጸሙና አስተምህሮዋን የሚፃረሩ እንደኾኑ ቅዱስ ሲኖዶሱ እንደመከረበት ተገልጿል፡፡ በግል አታሚዎቹ የቀድሞዎቹን ትክክለኛ ቅደጂዎች በሚያፋልስ መልኩ ለኅትመት የዋሉት፥ የስንክሳር፣ የራእየ
ማርያምና የተኣምረ ማርያም መጻሕፍት የተጠቀሱ ሲሆን፤ የቀድሞውን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስንና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ከቀኖናዊ አሠራር ውጪ በማካተት የታተመው ‹ተአምረ ማርያም› በአስረጅነት ተነሥቷል፤ በሊቃውንት ጉባኤም ተጠንቶ እንዲቀርብ መወሰኑ ታውቋል፡፡


Saturday, 06 May 2017 10:38

የወር አበባ መዛባት...

 ባለፈው እትም ስለወር አበባ መዘግየት መምጣትና መቅረት በሚመለከት አንዳንድ ነጥቦችን አንስተን ከዶ/ር ሙስጠፋ ነጋሽ ያገኘነውን ማብራሪያ ለአንባቢ ማለታችን ይታወሳል። ከወር አበባ ጋር በተያያዘ ያለውን ጠቃሚ ነገር ዶ/ር ሙስጠፋ ነጋሽ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ኮሌጅ መምህርና የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት የሆኑት ለዚህ እትም የሰጡትን ቁምነገር ታነቡ ዘንድ እነሆ ብለናል። ከ University of Maryland School of Medicine ድረገጽ ያኘነውን ቁምነገርም እናስነብባችሁዋለን።
የወር አበባ በተለይም ፍሰቱን ካልጠበቀ የሚያስትለው ችግር አለ።
የወር አበባ መጠን ከአስር እስከ ሰማንያ ሊትር በአማካይ ደግሞ ሰላላ ሚሊ ሊትር ነው። ከዚህ በተጨማሪም የሚፈሰው ደም የመርጋት ሁኔታ ሊታይበት አይገባም። ይህ ከሆነ ግን የወር አበባ መብዛቱን የሚያመላክት ነው። ስለዚህም ከዚህ ጋር ተያያዥ በሆነ ምክንያት፡-
የደም ማነስ እና ከደም ማነስ ጋር የተያያዙ ሌሎች ችግሮችንም ያስከትላል።
ልብ ድካምና ኢንፌክስን ለመሳሰሉት ሕመሞች ያጋልጣል።
የስነአእምሮአዊ ችግር ከወር አበባ ጊዜውን አለመጠበቅና የመጠን መብዛት ሊከሰት ይችላል። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚቆጠረው አንዲት ሴት በአጠገብዋ ያለች ጉዋደኛ ወይንም እህትዋ የወር አበባዋ በትክክል የሚመጣና የሚሄድ ከሆነ እስዋ ግን እኔ ለምንድነው ይህ መዛባት የገጠመኝ በሚል ከመጨነቅ ሊከሰት ስለሚችል ነው። ስለ ዚህም ሐዘን፣ የስሜት መጎዳት፣ እንደድብርት የመሳሰሉት ችግሮችም ሊገጥሙአት ይችላሉ።
የወር አበባ መዛባት የሚያስከትለው ሌላው ችግር በተለይም በትዳር ላይ ላሉ ያልተጠ በቀ እርግዝና ነው። ከዚሀም የተነሳ ጽንሱን ወደማቋረጥ ስለሚሄዱ እና በተለያዩ ምክንያቶችም ለማህጸን ካንሰር የመጋለጥ እድሎችን ያስከትላል።
እንደ ዶ/ር ሙስጠፋ ነጋሽ ማብራሪያ ሴቶች የተለያዩ የእርግዝና መከላከያዎች በተለይም ፕሮጀ ስትሮን ያላቸው መከላከያዎችን ሲወስዱ የወር አበባ አይፈጠርም። በዚህም ምክንያት ብዙ ጊዜ እርግዝና ተፈጥሮ ይሆናል የሚል ስጋት በሴቶች ላይ ይስተዋላል። አንዳንዶች ደግሞ ደሜ ሆዴ ውስጥ እየተጠራቀመ ስለሆነ ሆዴን እየነፋኝ ነው የሚል ስጋት ይስተዋልባቸዋል። ነገር ግን ሁሉም ሰው ሊገነዘበው የሚገባው ነገር በመርፌ የሚወሰድ የእርግዝና መከላከያ የወርአበባ እንዳይፈጠር ማድረጉን ነው። ለዚህም ምክንያቱ አንዱን ሆርሞን ብቻ ስለሚይዝ ሲሆን በኪኒን መልክ የሚዘጋጁት ግን የወር አበባ በጊዜው እንዲመጣ የሚያስችሉ ሆነው የተዘጋጁ ናቸው። በእርግጥ በኪኒኒ መልክ የተዘጋጀ በመርፌ የሚሰጥ መከላከያ እንዳለ እሙን ነው። ስለዚህ የወር አበባ መጀመሪያ የመዛባትና መቅረት ችግሮች እስከ 49/አመት ባሉት እድሜ ውስጥ ከሆነ እርግዝና እና ከእርግዝና ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ችገግሮች መኖር ያለመኖራቸውን ማወቅ ተገቢ ይሆናል። በዚህ መልክ የሚከሰቱ ችግሮች ለሕይወት አስጊ ስለሚሆኑ እና ጊዜ ሊሰጣ ቸው ስለማይገባ በፍጥነት ወደሐኪም መሔድም ይመረጣል። ውርጃ የሚከሰት ከሆነ ኢንፌ ክሽን በመፍጠር ወደሰውነት ሊሰራጭ ከመቻሉም በላይ ማህጸንዋን ከጥቅም ውጭ ሊያደርግ ይችላል። ምናልባትም ከማህጸን ውጭ እርግዝና ከሆነ ከመጠን በላይ በሆድዋ ውስጥ ደም ስለሚፈስ ለሕይወት አስጊ ሊሆን ይችላል። በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ የሚወሰዱ የእርግዝና መከላከያዎችም የወር አበባ መዛባቱን ሊያስከትሉ የሚችሉ ሲሆን ይህንን በሚመለከትም መድሀኒቱን ካዘዙ ባለሙያዎች ጋር መመካከር ያስፈልጋል።
የወር አበባ እርግዝና ሲኖር፣
ጡት በማጥባት ወቅት፣
በመርፌ መልክ የሚሰጡ የእርግዝና መከላከያዎች ሲወሰዱ ሊቋረጥ ይችላል።
ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ተፈጥሮአዊ ሲሆኑ ተፈጥሮአዊ ያልሆነው ደግሞ፡-
እድሜው የወር አበባ መምጫ ሆኖ ሳለ ሳመጣ ሲቀር፣
ምንም የእርግዝና መከላከያ ሳይወሰድ፣
እርግዝና ሳይኖር፣
እድሜ ለወር አበባ መቋረጥ ሳይደርስ ከሆነ አሳሳቢ ይሆናል።
ስለዚህ አንዲት ልጅ ከ15-16/ ባለው እድሜዋ የወር አበባ ካላየች ወደሕክምና መሔድ ግድ ነው። የወር አበባ በትክክለኛው እድሜ ቢመጣም የመምጫ ጊዜውን የሚያዛባ ከሆነና የሚቋረጥ ከሆነም የህክምና ድጋፍ ያስፈልጋል።
በወር አበባ ምክንያት የሚመጣ ሕመምን በዘመናዊ ሕክምና ማስወገድ እንደሚቻል እና የተለያዩ የቤት ውስጥ እርዳታዎችም እንደሚያስወግዱት University of Maryland School of Medicine ድረገጽ ይገልጻል።
የመጀመሪያው የማህጸን አጥንት ተሸካሚ አጥንት ምርመራ ነው። ይህ የምርመራ ሂደትም ላፓራስኮፒ በሚባለው የምርመራ መሳሪያ የሚከወን ነው። ሌላው የህክምና ዘዴ የአልትራ ሳውንድ ምርመራ ነው። እንደዚሁም የደምና የሽንት ምርመራን በመውሰድ የተከሰተውን ችግር በዝርዝር ለማወቅ ይረዳል። የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች ህመምን ለመቀነስ እና የተዛባ የወር አበባን ለማስተካከል ይረዳል ስለሚባል በሕክምናው ይታዘዛል። በሳይንሱ አለም ሌሎች የተለያዩ የህክምና ዘዴዎችም ስላሉ ችግሩ የገጠማቸው ሴቶች ወደሕክምናው አለም ጎራ እንዲሉ ይመከራል።
የወር አበባ መዛባትን በሚመለከት የተለያዩ የአመጋገብና የአኑዋኑዋር ምክሮችም ይለገሳሉ።
በካልሲየም የበለጸጉ ምግቦችን መመገብ ማለትም ቅጠላቅጠልና ጥራጥሬዎች እንዲሁም አትክልቶችን መመገብ ጠቃሚ መሆኑን ድረገጹ ያትታል።
ፍራፍሬዎች እንጆሪን እና ቲማቲምን ጨምሮ ባጠቃላይም ከሰውነት ውስጥ (Antioxidant) መመረዝን የሚያስወግዱ ምግቦችን መመገብ ጠቃሚ ነው።
በኢንደስትሪ ውስጥ ተሰርተው የታሸጉ እና እንደስንዴ ዳቦ፣ ፓስታ እና ስኩዋር የመሳሰሉትን ምግቦች ማስወገድ የወር አበባ መዛባት እንዳይኖር ያደርጋል።
ስጋን በሚመለከት የሚመከረው መጠኑ ትንሽ የሆነ ቀይ ስጋ እና ትንሽ ፋት ቅልቅል የሆነ ስጋን በመጠኑ መመገብን ይመክራል ድረገጹ።
ተጋግረው የታሸጉ ምግቦች እንደ ኩኪስ ኬኮች የተጠበሰ ድንች እና በኢንደስትሪ የተሰሩ ምግቦችን ማስወገድ ይጠቅማል።
በምግቦች ውስጥ የወይራ ዘይት፣ የአትክልት ዘይት የሆኑትን ለማብሰያነት መጠቀም ጠቃሚ ነው።
አልኮሆል እና ሲጋራ የሚጠቀሙ ከሆነ ማስወገድ ተገቢ ነው።
ከ6-8/ ብርጭቆ ውሀ በቀን መጠጣት ይመከራል።
በቀን እስከ 30/ደቂቃ የአካል አንቅስቃሴ ማድረግ ይመከራል።
ከዚህ ውጭ እንደከሞሜላ ያሉ ተፈጥሮአዊ የሆኑ ቅጠላ ቅጠሎች እንደሻይ አፍልቶ መጠጣትም ሊጠቅም ስለሚችል ከተለያዩ መረጃዎች በማገናዘብ እርግጠኛ የሆኑበትን ነገር መጠቀም ይመከራራል።
ከወር አበባ ጋር በተያያዘ አንዱ አስቸጋሪ ነገር የባህርይ መለዋወጥ ነው። ዶ/ር ሙስጠፋ ነጋሽ እንደሚሉት ሴቶች የወር አበባቸው ሊመጣ አካባቢ ባህሪያቸውን ብቻም ሳይሆን ሰውነታቸውም ጭምር ይለዋወጣል። የጡት ወጠርጠር ማለት፣ ጭንቀት፣ መነጫነጭ፣ ትውከት የመሳሰሉት ነገሮች ይከሰታሉ። ከዚህም በተጨማሪ የስሜት መለዋወጥ እና መረበሽ እንዲሁም የሆድ መክበድ ሊገጥማቸው ይችላል። የማህጸን ፈሳሽም በዛ ሊል ይችላል። በእነዚህ መሰል ምክንያቶች የተነሳ ትእግስትን የሚፈታተን ነገር ሊገጥማቸው ስለሚችል የባህርይ መለዋወጥ ነገር ሊታይ ይችላል። ከዚህ ውጭ ግን ሕመም የሚሆንበትም አጋጣሚ አለ። ሴትዋ ከስራራ እስከመ ቅረት ወይንም ወደሐኪም ቤት ሄዳ ሕክምና እስኪደረግላት ድረስ የሚያደርሳት ከሆነ ሕመም ስለሆነ በጣም አስቸጋሪ ነው። ስለዚህም አብረው የሚኖሩ ሰዎች የትዳር ጉዋደኛም ይሁን ቤተሰብ ይህንን መረዳትና ጊዜው እስኪያልፍ በትእግስት መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ለዚህ ጉዳይ ምንም ግምት ሳይሰጡ ከሴትየዋ ጋር መጨቃጨቅ ወይንም ክብርን፣ ትኩረትን መንፈግ የበለጠ ስለሚያበሳጫት ሊጎዳት ይችላል። ይህ የገጠማት ሴት ደግሞ ምክንያቱን በመደበቅ ለመታገል መሞከር ሳይሆን ያለችበትን ወቅትና ሁኔታ በትክክል ማስረዳት መቻል አለባት። በግልጽ በመነጋገር ችግሩን መፍታት ይቻላል ይላሉ ዶ/ር ሙስጠፋ ነጋሽ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እና መምህር።