Administrator

Administrator

ጠ/ሚኒስትሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለው እንዲታገሉ ጥሪ አቀረቡ

”60 ፓርቲዎች ሆናችሁ ልንደግፋችሁ ይቸግረናል“

ለሁለት ወር ግድም ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ያደረጉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ባለፈው ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም በመቶዎች ከሚቆጠሩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች  ጋር በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

የፓርቲ አመራሮቹ በውይይቱ ላይ ለጠ/ሚኒስትሩ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል የሰላምና ጸጥታ ችግር፣ የህግ የበላይነት አለመኖር፣ የፖለቲካ  ምህዳር መጥበብ፣ የሜጋ ፕሮጀክቶች ተጠያቂነትና  የዜጎች መፈናቀል ጉዳዮች ይጠቀሳሉ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ሃላፊን ጨምሮ አንዳንድ የፓርቲ አመራሮች የቢሮ፣ የአዳራሽና የፋይናንስ ችግር  እንዳለባቸው ጠቅሰው ላነሱት ጥያቄ፣ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ  ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

እኛ እንደ ፓርቲ ማድረግ የምንችላቸውን ነገሮች እናያለን ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ያንን ለማድረግ ግን ለፓርቲዎቹ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል - አሁን ያሉት 70 የሚደርሱ ፓርቲዎች 4 ወይም 5 ሆነው ሰብሰብ እንዲሉ፡፡

“አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ 66 ወይም 68 ገደማ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ለ68 ሊቀ መንበር ቦታ የለንም፤ ለ68 ሊቀ መንበር ቢሮ የለንም፤ 2-3-4-5 ሆናችሁ ብትሰባሰቡ --- ከብልጽግና ጋር 5 ወይም 6 ፓርቲ ብንሆን አንቸገርም ነበር፡፡”  ያሉት ዐቢይ፤ ”ለምሳሌ ዛሬ በውይይቱ ላይ ከእያንዳንዱ ፓርቲ አምስት አምስት ሰው ቢወከል፣ 25ቱም ሰዎች መናገር ይችሉ ነበር” በማለት አስረድተዋል፡፡

 “ስንበዛ መበተን ብቻ ሳይሆን በዚያው መጠን አቅማችንም ውስን ይሆናል፤” ሲሉም አክለዋል፡፡ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ውይይቱን የቋጩትም  የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሰብሰብ እንዲሉ በመማጸን ነበር፡፡

“እባካችሁ ወደ 4 ወይም 5 ፓርቲ ሰብሰብ በሉ፡፡ ግዴለም ይጠቅማችኋል፡፡ እንደዚያ ከሆናችሁ ፓርላማውም ይከፈታል፤ የምታስቡትም ሥልጣን ይመጣል፡፡ በዋና ዋና ጉዳይ ከተግባባችሁ በጋራ ሆናችሁ ብትታገሉ---አትጠራጠሩ ፓርላማውንም እንከፋፈለዋለን፡፡” ብለዋል፡፡

“እናንተ ግን አሁን 60 ናችሁ፤ ይሄ ለህዝብም ያስቸግራል” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ”እኔ እንኳን ስማችሁን አላውቀውም፤እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብ--” ሲሉም ፓርቲዎቹ ሰብሰብ ብለው እንዲታገሉ መክረዋል፡፡

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ከዚህ ቀደምም የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለው በጋራ እንዲታገሉ ጥሪ አቅርበው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ክብርት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ከጃፓን መንግስት የተበረከተላቸውን የወርቅ ጨረር ያለውን ኒሻን  ሽልማታቸውን ተረከቡ።
 
ይህ እውቅናና ሽልማት እኤአ ከ1875 ጀምሮ ለውጭ ሃገር ዜጎች በጃፓን መንግስት የሚሰጥ አንጋፋና ክብር ያለዉ ነው::  ከኢትዮጵያ የወርቅ ጨረር ያለው ኒሻን ሽልማት ከጃፓን መንግስት ሲሰጥ ክብርት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ የመጀመሪያዋ ናቸው። በጃፓን እና በኢትዮጵያ መካከል በስፖርት ዲፕሎማሲ እና ልውውጥ ዘርፍ ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅዖ ፣ በሌሎች ሀገራት እና አካባቢዎች መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማሳደግ፣ ለአትሌቲክስ እድገት ፣ ለአገር ሰላም ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅና በመስጠት በዓለም አቀፍ መስኮች የላቀ ስኬት ምክንያት ሽልማቱን አግኝተዋል። ክብርት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ሽልማታቸውን ዛሬ መጋቢት 24/2026 በኢትዮጵያ ከጃፓን አምባሳደር  ሚስተር ሺባታ ሂሮኖሪ እጅ ተረክበዋል ።

ጥበበ ተርፋ ማመጫ፤ በሐረር ከተማ በ1941 ዓ.ም ተወለዱ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሐረር መድኃኒዓለም ት/ቤት እንዳጠናቀቁ ወደ አዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ት/ቤት (በአሁኑ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት) በመግባት ተመርቀዋል።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥነጥበብ ልምምድ ውስጥ ተዋጽዖአቸው ከፍ ያለ ሥፍራ የሚሰጠው ነበረ:: የሥዕል ሥራቸውን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ለዕይታ ያበቁ ሲሆን፣ በሙያው ስምና ዝና ያፈሩ አንጋፋ ሙያተኛ ነበሩ::

አቶ ጥበበ ተርፋ የሥራቸው አቅጣጫ ተወልደው ባደጉበት ሐረር ላይ በማተኮር የትላንቱንና የዛሬውን ገጿን በቀለማት እንቅስቃሴ ይገልጹ ነበረ። አቶ ታዬ ታደሰ ባዘጋጁት የሠዓልያን ታሪክ ውስጥ ጥበበ "የተለያዩ ቴክኒኮችን የሚጠቀሙ ሲሆኑ፤ የሚያደንቁት ግን ኤክስፕሬሽኒዝምን ነው" በማለት መጻፋቸው ይታወሳል::

ሠዓሊ ጥበበ ተርፋ ማመጫ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው ህይወታቸው ማለፉን ሰምተናል:: ለመላው ቤተሰብ፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ለአለ_የሥነጥበብ_ት/ቤት ማህበረሰብ፣ ለሙያ ጓዶቻቸውና አድናቂዎቻቸው መጽናናት እንዲሆንላቸው እንመኛለን።

ቀብራቸው ነገ ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በየካ ሚካኤል ቤተክርስትያን ከቀኑ 8:30 የሚፈጸም ይሆናል። ነፍስ ይማር።

(አገኘሁ_አዳነ_ድልነሣሁ)

በሰርቢያ ቤልግሬድ በተካሄደው የ45ኛው ዓለም   አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአምስት ምድቦች ማለትም  8ኪ.ሜ. ከ20 ዓመት በታች  ወንዶች  ፣ 6 ኪ.ሜ. ከ20 ዓመት በታች  ሴቶች  ፣ 4x2 ኪ.ሜ የድብልቅ ሪሌ ሴት/ወንድ  ፣ የ10 ኪ.ሜ. የአዋቂ ሴቶች እና አዋቂ ወንዶች  በተካተቱበት ውድድር ከ51 አገራት  የመጡ 485 የሚሆኑ አትሌቶች ተፎካክረውበታል።  በዚህም ውድድር ኢትዮጵያ በ14 ሴት እና በ14 ወንድ በ28 አትሌቶች የተወከለች ሲሆን በ ሁለት ወርቅ ፣በስድስት ብር እና በሁለት ነሃስ በአጠቃላይ በ10 ሜዳሊያ ከአለም የሁለተኛነት ደረጃ በመያዝ ውድድሩርን ጨርሳለች ፡፡

ግሪን ዌቭ አሊያንስ ከኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በአረንጓዴ ልማት ዙሪያ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት በዛሬው ዕለት  ረፋዱ ላይ ፈጸመ፡፡

ስምምነቱን የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ም/ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬነሽ መኩሪያና የግሪን ዌቭ አሊያንስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ረድኤት ያዘው በባለሥልጣኑ መ/ቤት አዳራሽ ተፈራርመዋል፡፡

የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬነሽ መኩሪያ በፊርማ ሥነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በጠ/ሚኒስትሩ ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረውን አረንጓዴ ልማት ለማስቀጠል መንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት አጋርነት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህ ረገድ የዛሬው ስምምነት ፋይዳው የላቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣን መ/ቤቱ  ከመጋቢት 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የአየር፣ የውሀ፣ የአፈርና የድምጽ  ብክለትን ለመቀነስ የሚያስችል የ6 ወራት ዘመቻ መጀመሩን የገለጹት ወ/ሮ ፍሬነሽ፤ በአጋርነት መሥራት ዘመቻውን ውጤታማ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

የግሪን ዌቭ አሊያንስ መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ አርቲስት ሚኪያስ ነጋሳ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የሚያከናውናቸው ሥራዎች ሰፊ ከመሆናቸው አንጻር መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት አጋርነት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዛሬ የተከናወነው ስምምነት የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴውን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት የዓባይ ግድብ 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ያዘጋጀዉን የመታሰቢያ ቴምብር በዓሉን በማስመልከት በተዘጋጀዉ የፓናል ዉይይት መድረክ ላይ ይፋ አደረገ።
የአባይ ግድብ የመታሰቢያ ቴምብሩን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣የዉሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ እና የአባይ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በጋራ መርቀዋል።
የመታሰቢያ ቴምብሩ ከዛሬ ጀምሮ ለ192 የአለም አገራት እንደሚሠራጭ ተገልጿል።

የደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማ "የዓለማችን ምስጢራት" የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ከሰሞኑ ለአንባቢያን ቀርቧል።

ይህ አዲስ መጽሐፍ የፊታችን መጋቢት 28 2016 ዓ.ም በወመዘክር አዳራሽም ይመረቃል ተብሏል።

"ግጥም ሲጥም "ለሁሉም ክፍት የሆነ የኪነጥበብ  መድረክ ተመልሷል። በዚህም ሳምንትም የቦታ ለወጥ አድርጎ ነገ ረቡዕ መጋቢት 25 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 12:00 ጀምሮ ገርጂ በሚገኘው ደስክ አዲስ ውስጥ ይካሄዳል ተብሏል።

"እንዲህ ያለም የለ"መጽሐፍ ረቡዕ ይመረቃል

የገጣሚ ሀብታሙ ሀደራ "እንዲህ ያለም የለ" የተሰኘ የግጥም ስብስብ መጽሐፍ የፊታችን ረቡዕ መጋቢት 25 2016 ዓ.ም ከ10:30 ጀምሮ በወመዘክር አዳራሽ ይመረቃል።

  • • ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ሳሚ ዳንና ጃኪ ጎሲ ይሳተፉበታል

           ታዋቂ የኢትዮጵያ ድምፃዊያን የሚሳተፉበት “የኢትዮጵያ ሙዚቃ ቀን” በእስራኤል ቴላቪቭ እንደሚካሄድ  አፍሮ ስታይል ኢንተርቴይመንት አስታወቀ፡፡  
    የእስራኤል የነፃነት ቀንን ምክንያት በማድረግ፣ ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ፣ም የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን በቴላቪቭ የሚካሄድ ሲሆን፤ አፍሮ ስታይል ኢንተርቴይመንት ባዘጋጀው በዚህ  ኮንሰርት ላይ ጎሳዬ ተስፋዬ፤ ሳሚ ዳንና ጃኪ ጎሲ እንደሚጫወቱ ተገልጿል። ታዋቂ የጃማይካ ዳንስሆል አርቲስትም በኮንሰርቱ ላይ  እንደሚሳተፍ  ተጠቁሟል።
    የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀንን ለማክበር የተሰናዳው መርሐግብር ከሚያዚያ 29 እስከ ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም  የሚቆይ ሲሆን፤ በተለያዩ የሙዚቃ ዝግጅቶችና በእስራኤል ከተሞች በሚካሄዱ ጉብኝቶች የሚታጀብ ይሆናል ተብሏል።
    ከሚያዚያ 29 እስከ ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም በእየሩሳሌም ከተማ ጉብኝቶች የተዘጋጁ ሲሆን፤ ግንቦት 5  በሃንገር 09 አዳራሽ ቴላቪቭ ላይ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ቀን ልዩ  ኮንሰርት እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፡፡  በተመሳሳይ ቀን የቴላቪቭ ከተማን ለማስጎብኘትም ታቅዷል።  ግንቦት 8 ቀን 2016 ዓ.ም በሚር ያቆብ አዘጋጅነት በቴላቪቭ ሐንገር 09 አዳራሽ፣ የሬጌ ሙዚቃ ዝግጅትና ዳንስ እንደሚቀርብም ታውቋል።

Page 9 of 706