Administrator
ደደቢት ሴፋክሴዬንን በሜዳው ይፋለማል
የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በዓለም 107ኛ፤ በአፍሪካ 17ኛ፤ በምስራቅ አፍሪካ 2ኛ ነው
16 ክለቦች በሚሳተፉበት የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ዛሬ እና ነገ በአንደኛ ዙር ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታዎች በመላው አህጉሪቱ ሲካሄዱ የምስራቅ አፍሪካዎቹ ከተሞች አዲስ አበባ፤ ዳሬሰላም እና ናይሮቢ ትልልቅ ግጥሚያዎችን ያስተናግዳሉ፡፡ የአምናው የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ደደቢት በነገው እለት የቱኒዚያውን ክለብ ሲኤስ ሴፋክሴዬን በአዲስ አበባ ስታድዬም የሚፋለም ይሆናል፡፡ የቱኒዚያው ክለብ ሲኤስ ሴፋክሴዬን ከሳምንት በፊት በአፍሪካ ክለቦች ሱፕር ካፕ በግብፁ ክለብ አልሃሊ 3ለ2 ተሸንፎ ዋንጫ አምልጦታል፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን የአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ ዋንጫን ያሸነፈው ሲኤስ ሴፋክሲዬን በሱፕር ካፑ የደረሰበትን ሽንፈት በነገው የአዲስ አበባ ጨዋታ ለማካካስ ትኩረት ማድረጉን የቱኒዚያ ጋዜጦች ዘግበዋል፡፡ ደደቢት በአፍሪካ ደረጃ ብዙም ልምድ ባይኖረውም በደጋፊው ፊት ከባድ ተፎካካሪ ሆኖ በመጫወት በከፍተኛ የግብ ልዩነት ለማሸነፍ ከቻለ የማለፍ እድሉን ሊያሰፋ ይችላል፡፡ በሌሎች የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች በዛሬው እለት ናይሮቢ ላይ የኬንያው ክለብ ጎሮማሃያ ለሁለት ጊዜያት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ያሸነፈውን የቱኒዚያውን ኤስፔራንስ ሲገጥም፤ ዳሬሰላም ላይ ደግሞ የታንዛኒያው ክለብ ያንግ አፍሪካንስ የአምናው የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ከነበረውና ከሳምንት በፊት የሱፕርካፕ ዋንጫ ያገኘውን የግብፁን ክለብ አልሃሊን ያስተናግዳል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከተመሰረተ ከ70 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ክለቦች ከፍተኛ ውድድር ፕሪሚዬር ሊግ ባለፈው የውድድር ዘመን በፉክክር ደረጃው ከዓለም 107ኛ፤ ከአፍሪካ 17ኛ እንዲሁም ከምስራቅ አፍሪካ 2ኛ ማግኘቱን የእግር ኳስ ስታትስቲክስ እና ታሪክ ዓለም አቀፍ ፌደሬሽን (IFFHS) አመለከተ፡፡ ተቀማጭነቱን በስዊዘርላንዷ ከተማ ሉዛን ውስጥ ያደረገው የእግር ኳስ ስታትስቲክስ እና ታሪክ ዓለም አቀፍ ፌደሬሽን (IFFHS) ለዓለም የእግር ኳስ ሊጎች ደረጃ የሚያወጣው በአገር ውስጥ የሊግ እና የጥሎ ማለፍ ውድድሮች በመመዘን፤ በአህጉራዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የየአገሩ ክለቦች ያላቸውን ፉክክር ደረጃ እና ውጤት በማስላት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ከዓለም የክለብ ውድድሮች 107ኛ ደረጃን ያገኘው 157 ነጥብ በማስመዝገብ ነው፡፡ በምስራቅ አፍሪካ በክለቦቿ የሊግ ውድድር አንደኛ የሆነችው 230 ነጥብ በማስመዝገብ ከዓለም 91ኛ ደረጃ የወሰደችው ሱዳን ስትሆን፤ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ከያዘው ሁለተኛ ደረጃ በመቀጠል፤ የኬንያ ፕሪሚዬር ሊግ በ123 ነጥብ ከዓለም 114ኛ፤ የታንዛኒያ ፕሪሚዬር ሊግ በ114.5 ነጥብ ከዓለም 118ኛ፤ የብሩንዲ ፕሪሚዬር ሊግ በ114 ነጥብ ከዓለም 119ኛ፤ የኡጋንዳ ፕሪሚዬር ሊግ በ114 ነጥብ ከዓለም 120ኛ እንዲሁም የሩዋንዳ ፕሪሚዬር ሊግ በ108 ነጥብ ከዓለም 125ኛ ደረጃ በማግኘት ተከታታይ ደረጃ አላቸው፡፡ የእግር ኳስ ስታትስቲክስ እና ታሪክ ዓለም አቀፍ ፌደሬሽን (IFFHS) የዓለም አንደኛ ምርጥ ሊግ ብሎ የሰየመው 1155 ነጥብ ያስመዘገበውን የስፔኑ ፕሪሚዬራ ሊጋ ሲሆን፤ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በ1128 ነጥብ፤ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ በ1058 ነጥብ፤ የጣሊያን ሴሪ ኤ በ927 ነጥብ፤ የብራዚል ሴሪኤ በ896 ነጥብ፤ የአርጀንቲና ፕሪሚዬራ ዲቪዥን በ868 ነጥብ፤ የፈረንሳይ ሊግ 1 በ796 ነጥብ፤ የሩስያ ፕሪሚዬር ሊግ በ739.5 ነጥብ፤ የኮሎምቢያ ፕሪሚዬር ሊግ በ724.5 ነጥብ እንዲሁም የሮማንያ ፕሪሚዬር ሊግ በ722.5 ነጥብ ከ2 እስከ 10 ያለውን ደረጃ አግኝተዋል፡፡ በአፍሪካ በምርጥ የፉክክር ደረጃው አንደኛ የተባለው 469.5 ነጥብ በማስመዝገብ በዓለም 31ኛ ደረጃ የወሰደው የቱኒዚያ ሊግ ነው፡፡ ግብፅ በ361.5 ነጥብ ከዓለም 46ኛ፤ ሞሮኮ በ361 ነጥብ ከዓለም 47ኛ፤ ናይጄርያ በ332.5 ነጥብ ከዓለም 53ኛ፤ ማሊ በ322 ነጥብ ነጥብ ከዓለም 56ኛ፤ ደቡብ አፍሪካ በ316.5 በዓለም 61ኛ፤ አልጄርያ በ315.5 ነጥብ ከዓለም 62ኛ፤ አንጎላ በ314.5 ነጥብ ከዓለም 64ኛ እንዲሁም ካሜሮን በ295 ነጥብ ከዓለም 70ኛ በመመዝገብ በአፍሪካ ምርጥ ሊጎች የደረጃ ሰንጠረዥ ከ2 እስከ 10 ተከታትለው ተቀምጠዋል፡፡ ጋና፤ ኮትዲቯር፤ ኮንጎ ዲ ሪፖብሊክ፤ ሱዳን፤ ዛምቢያ፤ ዚምባቡዌ፤ ኮንጎ ኪንሻሳ፤ ኢትዮጵያ፤ በርኪናፋሶ፤ ቦትስዋና እና ኬንያ ከ11 እስከ 20 ደረጃ ያገኙ የአፍሪካ ሊጎች ሆነዋል፡፡
ኢንዱራሊ የመኪናና የሞተር ብስክሌት ውድድር ነገ ይካሄዳል
የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት አሶሴሽን ያዘጋጀው የኢንዱራሊ የመኪናና የሞተር ብስክሌት ውድድር ነገ በቃሊቲና አቃቂ አካባቢ ገላን ገበሬ ማህበር ክልል ውስጥ እንደሚካሄድ ታወቀ ፡፡ የሞተር ስፖርት አሶሴሽኑ የበላይ ጠባቂ የሆኑት የተከበሩ አቶ አባዱላ ገመዳ ውድድሮቹን በስፍራው ተገኝተው እንዲያስጀምሩ ጥሪ ተደርጎላቸዋል፡፡ ኢንዱራሊ በ2006 ዓ.ም ለማካሄድ በዕቅድ ከያዛቸው ውድድሮች መካከል አንዱ መሆኑን የገለፁት የአሶሴሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኤርምያስ አየለ በቀጣይ ወራት ሁለት የከተማ እና አንድ የከተማ ውጭ ውድድሮችን እንደሚዘጋጁም ተናግረዋል፡፡
በኢንዱራሊ የመኪናና የሞተር ብስክሌት ውድድር ላይ 15 መኪናዎችና 27 ሞተርብስክሌቶች እንደሚካፈሉ የሚጠበቅ ሲሆን ከተወዳዳሪዎቹ መካከል 4 ኢትዮጵያዊያን፤ 9 የጣልያናውን፤ 1 ጅቢቲያዊና 1 ህንዳዊ ይገኙበታል፡፡
የመኪናው ውድድር በአራት ምድብ ተከፍሎ እንደሚካሄድ ያመለከተው የሞተር ስፖርት አሶሴሽኑ መግለጫ ባለ 2000 ሲሲ ቱርቦ መኪናዎች በአንደኛው ምድብ፤ ከ1601 እስከ 2000 ሲሲ በሁለተኛው ምድብ፤ ከ1301 እስከ 1600 ሲሲ በሶስተኛው ምድብ፤ በአራተኛው ምድብ ደግሞ እስከ 1300 ሲሲ ጉልበት ያላቸው መኪናዎች ይወዳደሩበታል፡፡ የውድድር መኪናዎቹ የተለያየ ጉልበት ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ ዓይነታቸውም እንደሚለያይ የገለፀው አሶሴሽኑ ፎርድ፤ ፔጆት፤ ላንቻ ዴልታ፤ ሚትሱቢሺ፣ ቶዮታ፣ ኦፔል፣ ሱዙኪና ሊፋን መኪናዎች መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
በተጨማሪ በሚካሄደው የሞተር ብስክሌት እሽቅድምድም ላይ 4 ኢትዮጵያዊያን፤ 7 ፈረንሳዊያን፤ 5 ጣሊያናዊያን፤ 6 ጅቡቲያዊያን፤ 2 አሜሪካዊያን፤ 1 እንግሊዛዊ እና 1 ጀርመናዊ እንደሚሳተፉ ሲታወቅ መወዳደርያዎቹ ሞተር ብስክሌቶች ከ125 እስከ 600 ሲሲ ጉልበት ያላቸው ናቸው፡፡
የኢንዱራሊ የመኪናና የሞተር ብስክሌት ውድድሩን ከጀላዳ ራይደርስ ጋር በመተባበር እንዳዘጋጀው የገለፀው የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት አሶሴሽን ቢጂአይ አምበር ቢራ፤ ኮባ ኢምፓክት፣ አልታ አውቶ ካር ኬር ጋራጅ፤ ዩኒቨርሳል ፕላስቲክ ፋብሪካ፣ ናሽናል ሞተርስ፣ አምቦውሃ ፋብሪካና አምቼ ኢቪኮ በስፖንሰርነት እንደደገፉት አመልክቷል፡፡
የዲናው የሰንበት ውሎ
ዲናውና ሁለተኛ ልጁ ሉዊስ ስላሴ በአሜሪካን ሙዚየም ኦፍ ናቹራል ሂስትሪ
በ1970 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ የተወለደውና በልጅነቱ ወደ አሜሪካ ያቀናው ዲናው መንግስቱ፣ እድገቱ በቺካጎ ሲሆን ከጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪውን፣ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በስነጥበብ ሁለተኛ ዲግሪውን ተቀብሏል፡፡
‘ዘ ቢዩቲፉል ቲንግስ ዛት ሄቨን ቢርስ’፣ ‘ሀው ቱ ሪድ ዘ ኤር’ እና ‘ቺልድረን ኦፍ ዘ ሪቮሊዩሽን’ በተሰኙት የረዥም ልብወለድ መጽሃፍቱ በሃገረ አሜሪካ ከፍተኛ ታዋቂነትን ያተረፈው ደራሲ ዲናው መንግስቱ፣ ሮሊንግ ስቶንንና ዎልስትሪት ጆርናልን በመሳሰሉ ታዋቂ ጋዜጦችና መጽሄቶች ለንባብ በሚያበቃቸው ስራዎቹም ይታወቃል፡፡ በርካታ የስነጽሁፍ ሽልማቶችንም ለማግኘት በቅቷል፡፡
በ2007 ያሳተመው የመጀመሪያ መጽሃፉ የአመቱ የኒዮርክ ታይምስ ታላቅ መጽሃፍ ተብሎ የተመረጠለት ዲናው፣ ዘ ኒዮርከር ጋዜጣም በ2010 ከአርባ አመት ዕድሜ በታች ያሉ ምርጥ ሃያ ደራሲዎቼ ብሎ ከጠቀሳቸው መካከል ተካትቷል፡፡ ሎስአንጀለስ ታይምስ በ2008 የምርጥ መጽሃፍ ተሸላሚ አድርጎታል።
በ2007 የናሽናል ቡክ አዋርድ ፋውንዴሽን ሽልማትን የተቀበለ ሲሆን፣ በተመሳሳይ አመትም ‘ቺልድረን ኦፍ ዘ ሪቮሊዩሽን’ በሚለው መጽሃፉ የጋርዲያንን ፈርስት ቡክ አዋርድ ያገኘ ተደናቂ ደራሲ ነው፡፡
ደራሲ ዲናው መንግስቱ ለመጨረሻ ዕጩ ተሸላሚነት ከታጨባቸው ታዋቂ ሽልማቶች መካከልም፣ የዳይላን ቶማስ ሽልማት፣ የኒዮርክ ፐብሊክ ላይብራሪ ያንግ ላዮንስ ሽልማት፣ ግራንድ ፕሪክስ ዴስ ሌክትሬ ዲ ኤሌ ሽልማት ይጠቀሳሉ፡፡
‘ኦል አዎር ኔምስ’ የሚል ርዕስ የሰጠው አራተኛ መጽሃፉ በቅርቡ ለህትመት የሚበቃለት ዲናው፣ ነዋሪነቱን ከባለቤቱ አና ኢማኑኤሌ እንዲሁም ከሁለት ወንድ ልጆቹ ጋብሬልና ሉዊስ ስላሴ ጋር በዋሽንግተን ዲሲ አድርጓል፡፡
ዲናው የአንድ ሰንበት ውሎውን ገጽታ፣ ለኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛ ጁሊ ቦስማን በራሱ አንደበት እንዲህ ተርኮላታል፡፡ ኒዮርክ ታይምስም የዲናውን ውሎ ባሳለፍነው ሳምንት የዕለተ ሰንበት እትሙ ለንባብ አብቅቶታል፡፡
እነሆ!
‘አላርም’ አንፈልግም!
ከቤተሰባችን አባላት ሁሉ ሰነፉ ሰው እኔ ነኝ፡፡ ማልጄ ከአልጋዬ መውረድ አልወድም፡፡ እኔና ሚስቴ ከእንቅልፋችን የሚቀሰቅሰን አላርም አንሞላም። ቀስቅሰው መንጋቱን የሚነግሩን ሁሌም ማልደው የሚነቁት ልጆቻችን ሉዊስ ስላሴና ጋብርኤል ናቸው። ንጋት አስራ ሁለት ሰዓት አካባቢ ከአልጋቸው ብድግ ይሉና የመኝታ ቤታችንን በር በርግደው ከተፍ ይላሉ፡፡ እየተሯሯጡ እኔና እናታቸው የተኛንበት አልጋ ላይ ይወጣሉ፡፡
“በሉ ተነሱ! ረፍዷል!” ብለው ይቀሰቅሱናል፡፡ እኔና ሚስቴ ግን፣ በተለይ በሰንበት ተኝተን ማርፈድ ነው የምንፈልገው፡፡
“እባካችሁ ተውን! ትንሽ እንተኛ አትረብሹን!” እንላቸውና የተወሰነ ጊዜ ተኝተን እንቆያለን፡፡
ከዚያ ሚስቴ ቀድማኝ ትነሳና ለቤተሰቡ ቁርስ ታዘገጃጃለች፡፡ ቁርሳችንን የምንበላው ከአልጋችን ሳንወጣ ነው፡፡ አሪፍ የሆነ ወፍራም ስፕሬሶ እናዘጋጃለን፡፡ እዛው አልጋዬ ውስጥ እንደተጋደምኩ ስፕሬሶዬን እጠጣለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው፣ ከእንቅልፌ ሙሉ ለሙሉ ነቅቼ ከአልጋዬ መውረድና የሰንበት ውሎዬን ‘ሀ’ ብዬ መጀመር የምችለው፡፡
ወደ ኬክ ሩጫ
የእለቱ የአየር ሁኔታ የከፋ ካልሆነ በቀር፣ የመጀመሪያው የእሁድ ተግባራችን ልጆቻችንን በተገቢው ሁኔታ ማለባበስና ለሰንበት ሩጫ መዘጋጀት ነው፡፡ የቤተሰቡ የሰንበት ሩጫ መነሻውን ከምንኖርበት አፓርታማ ደጃፍ አድርጎ፣ ከሰፈራችን አቅራቢያ የሚገኝ አንድ ኬክ ቤት በር ላይ ይጠናቀቃል፡፡ የፈረንሳይ ዜጎች የሚያስተዳድሩት ይህ ኬክ ቤት፣ በከተማዋ ምርጥ ኬኮችን ከሚያቀርቡ አሉ የተባሉ ስመጥር ኬክ ቤቶች አንዱ ነው፡፡
የእኛ ቤተሰብም ዘወትር እሁድ ማለዳ ወደዚህ ኬክ ቤት የሰንበት ሩጫ የምናደርገው፣ ‘ቁራሳ’ የሚባለውን ጣፋጭ ኬክ ለመሸመት ነው፡፡ ፓሪስ ውስጥ ነዋሪ እያለንም ማልደን ወደ ኬክ ቤት መሄድና ቁራሳ መግዛት የተለመደ ተግባራችን ነበር፡፡ እዚህ ከመጣን በኋላም፣ በሰንበት ማለዳ ከልጆቻችን ጋር ወደ ኬክ ሩጫ ማድረጋችንን አልተውነውም፡፡
እንስሳ መሆንን የሚያስመኝ የእንስሳት ፍቅር!
ኬካችንን ገዝተን ወደ ቤታችን ከተመለስንና አጣጥመን ከበላን በኋላ፣ የጠርሙስ ጭማቂዎችንና በግቢያችን ከሚገኙ የተለያዩ የቤት እንስሳቶች የሳምንቱን ተረኛ የቤት እንስሳ እንመርጣለን። ተረኛው እንስሳ ቀኑን ሙሉ ከእኛ ጋር በሄድንበት ሁሉ ይዘነው ስንዞር የሚውል ነው። ጭማቂዎቻችንን፣ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችንና ተረኛውን እንስሳ ይዘን ረፋድ ላይ ከቤት እንወጣለን - ወደ ጉብኝት፡፡
በየሳምንቱ የምንጎበኛቸውን ቦታዎች እንመርጣለን፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ አንድ እሁድ የጎበኘነው፣ በኒውዮርክ ሲቲ የሚገኘውንና በአለማችን ትልቁ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም መሆኑ የሚነገርለትን “አሜሪካን ሙዚየም ኦፍ ናቹራል ሂስትሪ” ን ነበር፡፡ ልጆቻችን በግቢያችን ለምናሳድጋቸው ለሁሉም እንስሳት ልዩ ፍቅር ነው ያላቸው፡፡ በተለይ ታናሽዬው ሉዊስ ስላሴ ለእንስሳት ያለው ፍቅር እጅግ የሚገርም ነው፡፡ እንስሳትን አብዝቶ ከመውደዱ የተነሳ፣ ቀሪ የህይወት ዘመኑን እንስሳ ሆኖ ማሳለፍ እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡
ጋደም ብሎ ንባብ
የዕለቱን ጉብኝት ካጠናቀቅን በኋላ፣ ሉዊስ ቢያንስ ለአንድ ሰዓት ያህል መተኛት ስላለበት ወደቤታችን እንመለሳለን፡፡ እሱ ከእንቅልፉ እስኪነቃ ቤቱን ስናዘገጃጅ እንቆያለን፡፡ ከዚያም እኔና የመጀመሪያው ልጄ ጋብርኤል አልጋችን ላይ ጋደም ብለን ማንበብ እንጀምራለን፡፡ እኔ የዕለተ ሰንበት ጋዜጦችን ማገላበጤን ስቀጥል፣ ጋብርኤል ደግሞ በአይፓዱ ጌም ይጫወታል፡፡
ሳትወልድ ብላ!
ምሳ ሰዓት እየደረሰ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ለትንሹ ልጃችን ሾርባ እናዘጋጃለን፡፡ እኔና ሚስቴ ምግብ ላይ እስከዚህም ነን፡፡ ልጆቻችንን ግን በአግባቡ ነው የምንመግበው፡፡ ሳትወልድ ብላ ይባል የለ!... ልጆች ሲኖሩሽ ብዙ ምግብ አትበይም፡፡ ታላቁ ልጅ ምግብ ላይ አደገኛ ነው፡፡ ምግብ በሰዓቱ ካልደረሰ ጉዳችን ይፈላል፡፡ እንደ ሙዝ ያሉ ቢጫ ቀለም ያላቸውን ምግቦች የበለጠ ይወዳል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በመጠኑ የተወሰነ ፒዛ መብላት ጀምሯል፡፡
የተሲያት ብስኩት
ዘወትር እሁድ ከሰዓት በኋላ አንድ የተለመደ ፕሮግራም አለን - ብስኩቶችን መጋገር፡፡ ሁለቱም ልጆቻችን ብስኩቶችን መጋገር ይወዳሉ፡፡ እሁድ ከሰዓት በኋላን ኩኪስ በመጋገር ተጠምደው ነው የሚያሳልፉት፡፡ ሊጥ አብኩተው፣ እንቁላል በጥብ
ጠው ኩኪስ ሲጋግሩና ሲጠብሱ ነው የሚውሉት፡፡
የምሽት እንግዳ
ፓሪስ እያለን ሁሌም እሁድ እሁድ ማታ የሆነ እንግዳ ወደ ቤታችን ጎራ ማለቱ አይቀርም ነበር። ለነገሩ እዚህ ከመጣን በኋላም፣ ቢያንስ ከሁለት እሁድ በአንዱ የሆነ እንግዳ ሳናስተናግድ አንቀርም። ብዙ ጊዜ ለእሁድ ማታ ራት የተጠበሰ ዶሮ ነው የምናዘጋጀው፡፡
በነገራችን ላይ እኔ ራሴ የተዋጣልኝ ምግብ ሰሪ ነኝ፡፡ ቶማስ ኬለር የሚባለው ታዋቂ የምግብ አብሳይ በሚጠቀምበት አዘገጃጀት መሰረት ነው የዶሮ ጥብስ የምሰራው፡፡ ዘይት ወይም ቅቤ የሚባል ነገር አይገባበትም፡፡ በተቻለ መጠን ጥብሱ ደረቅ ያለ መሆን አለበት፡፡ በዚህ መልኩ ሲዘጋጅ የዶሮዋ ቆዳ በሚገርም ሁኔታ ስለሚደርቅ ሲበላ ኩርሽም ኩርሽም ይላል፡፡ ዋው!... እንዴት እንደሚጣፍጥ ልነግርሽ አልችልም!
እንግዶች ከመጡ ጥሩ አድርገን ስናስተናግድ እናመሻለን፡፡ ልጆቻችንም ገላቸውን ታጥበው የሌሊት ልብሶቻቸውን ይለብሳሉ፡፡ ልጆቹ በአብዛኛው ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ነው የሚተኙት፡፡ ቤታችን ውስጥ ያለውን ሰው በሙሉ ደህና እደሩ ብለው ይሰናበቱና ወደ አልጋዎቻቸው ያመራሉ፡፡ እንቅልፍ እስከሚወስዳቸው ድረስ አንድ ሁለት አጫጭር ታሪኮች ያሏቸው የህጻናት ፊልሞችን ያያሉ፡፡ ከፊልሙ በሚወጣው የህጻናት ጫጫታ ታጅበው ማንቀላፋት ይወዳሉ፡፡
እሁድ ስታልቅ
እሁድ ቀን ከሚስቴና ከልጆቼ ጋር ዘና ስል መዋል እንጂ፣ በስራ ተጠምዶ መዋልም ሆነ ማምሸት አይመቸኝም፡፡ እሁድን ዘና ብዬ በእረፍት አሳልፌ፣ ሰኞን በነቃ ትኩስ ስሜት መቀበል ነው የምፈልገው። አንዳንዴ ግን፣ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ በመጠኑም ቢሆን ልሰራ እችላለሁ፡፡ ለምሳሌ በጆርጅ ታውን ማክሰኞ ማክሰኞ ተማሪዎችን አስተምራለሁ፡፡ ስለሆነም ለማስተምረው ትምህርት መዘጋጀት ሲያስፈልገኝ፣ እሁድም ቢሆን የተወሰነ ሰዓት አምሽቼ መዘጋጀቴና ከመሸ ወደ አልጋ ማምራቴ አይቀርም፡፡
የሰንበት እንግዶቻችንን በወጉ አስተናግደን ከሸኘን በኋላ፣ ከሚስቴ ጋ አልጋችን ላይ ጋደም ብለን ፊልም እያየን አይስክሬም እንበላለን፡፡ ለምሽቱ የምናየውን ፊልም ከሚስቴ ጋር ተነጋግረን ነው የምንመርጠው፡፡
ፊልሙ የእሷ ምርጫ ከሆነ፣ በአንድ ደራሲ ወይም አርቲስት ህይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን ዶክመንታሪ ፊልም መሆኑ አይቀርም። ምርጫው የእኔ ከሆነ ግን፣ እምብዛም ዋጋ የሌለው ፊልም መሆኑ ግድ ነው፡፡
ታላቅ የጥናት ጉባኤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል፣ የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች የሚያከብር ሲሆን በትላንትናው ዕለት በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ ግቢ፣ በእሸቱ ጮሌ አዳራሽ ታላቅ የጥናት ጉባኤ ተጀምሯል። ዛሬም ይቀጥላል የተባለው የጥናት ጉባኤው 40ኛ ዓመቱን የሞላው “የመጀመሪያው” አብዮትና ተከታይ ክስተቶች በኢትዮጵያ የታሪክ ትርጉም ላይ ያሳረፏቸው ተፅዕኖዎች የሚፈተሽበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
የፕሮግራሙ አዘጋጆች ለአዲስ አድማስ በላኩት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ በሁለቱ ጉባኤ ቀናት 25 የታሪክ ባለሙያዎች የጥናት ወረቀት የሚያቀርቡ ሲሆን ከታሪክ ጋር በተያያዙ ተግዳሮቶችና ዕድሎች ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት የሚደረግበት የመጀመሪያው አጋጣሚ እንዲሆን ተጠቁሟል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ አካዳሚክ ማህበረሰቡ፣ የታሪክ ባለሙያዎች፣ ለታሪክ ልዩ ቅናት ያላቸው የህብረተሰብ አካሎችና ጋዜጠኞች በሚገኙበት በዚህ ጉባኤ፤ ፍላጎት ያላቸው ሁሉ እንዲታደሙ አዘጋጆቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“ቅጥልጥል ኮከቦች” ትያትር ለተመልካች ቀረበ
በፀሃፌ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ ተፅፎ በተሻለ አሰፋ የተዘጋጀው “ቅጥልጥል ኮከቦች” ትያትር ባለፈው እሁድ ተመርቆ ተከፈተ፡፡
የትያትሩ ጭብጥ በህክምና ስነ ምግባር ጥሰትና በምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ የሚያተኩር ሲሆን ትያትሩ ተመርቆ ከመከፈቱ በፊት በባለሙያዎች እንደተገመገመ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በትያትሩ ላይ አርቲስት ሽመልስ አበራ (ጆሮ)፣ መሰረተ ህይወት፣ ስናፍቅሽ ተስፋዬ፣ ሱራፌል ተካና ሌሎችም ይተውኑበታል፡፡
ትያትሩ ዘወትር እሁድ ከ8 ሰዓት ጀምሮ ለተመልካች እንደሚቀርብም ታውቋል፡፡ ፀሃፌ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ ከዚህ ቀደም ከአስር በላይ ትያትሮችን ፅፎ ለተመልካች አቅርቧል፡፡
“ስኳር እና ፍቅር” ተመረቀ
የገጣሚና ሙዚቀኛ ቴዎድሮስ ነጋሽ ሁለተኛ የግጥም መድበል “ስኳር እና ፍቅር” በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት አዳራሽ ተመረቀ፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የደራሲው ቀደምትና አዳዲስ ስራዎች ከሙዚቃ ጋር ታጅበው የቀረቡ ሲሆን ባይላሞር የዳንስ ቡድን በሳልሳ ዳንስ ፕሮግራሙን እንዳደመቀው ታውቋል፡፡
የሃዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ሲምፖዚየም ያካሂዳል
ባለፈው ዓመት በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ስር የተቋቋመው የሃዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ዛሬና ነገ ሁለተኛ ዓመታዊ ሲምፖዚየሙን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ጊቢ እንደሚያካሂድ ተገለፀ፡፡
በሲምፖዚየሙ ላይ ሰባት ባህል ተኮር ጥናታዊ ፅሁፎች በአገር ውስጥና በውጭ ተመራማሪዎች ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ ባለፈው ዓመት የተቋቋመው የባህል ጥናት ተቋሙ፣ ከጀርመኑ “ኢትዮ ስፔር” ጋር በመተባበር፣ በአካባቢው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ያሉትን የተለያዩ ቅርሳ ቅርሶች በዲጂታላይዜሽን ሥርዓት አደራጅቶ በመያዝ ለትውልድ ለማስተላለፍ እገዛ እንደሚያደርግ የተናገሩት የተቋሙ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ፈቃዴ፤ ተቋሙ የአብነት ት/ቤቶች ባህላዊ አስተምህሮቱን ጠብቀው እንዲዘልቁ የማጠናከሪያ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡
የሃዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም የአካባቢውን ባህል፣ ወግ፣ ልማድ፣ ትውፊትና ኪነ-ጥበብ ለመጠበቅና በርካታ ትውፊታዊ ሃብቶች ያሏቸው ቅኔና ግዕዝ በምርምር ታግዘው፣ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ የማድረግ ዓላማ ይዞ መቋቋሙ ይታወሳል፡፡
“አላቲኖስ” የአድዋ ድልን 120ኛ ዓመት በዓል በጣይቱ ሆቴል ያከብራል
አላቲኖስ ፊልም ሰራዎች ማህበር ከኤድሚክ ፊልምና ቲያትር ካምፓኒ ጋር በመሆን የአድዋ ድልን 120ኛ ዓመት ክብረ በዓል “የዓድዋ ስነ-ጥበብ” በሚል መሪ ቃል በነገው ዕለት ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በጣይቱ ጃዝ አምባ እንደሚያከብር አስታወቀ፡፡ ማህበሩ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ እንደጠቆመው፤ የአድዋን ሥነ-ጥበባዊነት የሚያጎሉ ጥናታዊ ዲስኩሮች በፊልም፣ በቲያትር፣ በሙዚቃ፣ በሥነ-ፅሁፍና ፍልስፍና ምሁራን አማካይነት ይቀርባሉ፡፡ ታዋቂ አርቲስቶችም አድዋን የሚያጎሉ ኪነጥበባዊ ትርዒቶች እንደሚያቀርቡ ተገልጿል፡፡ የአድዋ ጀግኖች እና አርበኞች ታሪክ በአርአያነት ለትውልድ እንዲሻገር ይዘከራሉ ብሏል- የአላቲኖስ መግለጫ፡፡
የቀልድ - ጥግ
የፖለቲካ ቀልዶች
ትርጓሜ
“የፖለቲካ ቀልዶች ችግር አንዳንዴ እንደባለቤቶቻቸው ሊመረጡ መቻላቸው ነው”
* * *
የፖለቲከኛ ትርጉም
ፖለቲከኛ ማለት ጀልባዋን ራሱ ነቅንቆ፣ አናግቶ ሲያበቃ፤ ከዚያ እያንዳንዱን ሰው እባህሩ ላይ ማዕበል ተነስቷል ብሎ ለማሳመን የሚችል ሰው ነው!
* * *
የየምርጫ ጣቢያ ትርጉም
የምርጫ ጣቢያ ማለት ገንዘባችሁን የሚያጠፋላችሁን ሰው የምትመርጡበት ቦታ ነው!
* * *
አንድ የሩሲያ መሪ ወደ አሜሪካ መጥቶ የአሜሪካን ወታደሮች እንዲጎበኝ ይጋበዛል። በዚሁ መሠረት ወደ አሜሪካ ጣና ወታደሮቹን ይጐበኝ ጀመር፡፡
የአሜሪካው መሪ፡- “ወታደሮቼ ለእኔና ለአገሬ በጣም ታማኝ ናቸው” አለው ለሩሲያዊው፡፡
የሩሲያው መሪ፡- “እስቲ አንዱን ወታደር ጥራልኝና ጥያቄ ልጠይቀው” አለ
አንድ ወታደር ተጠራና መጣ፡፡
ይሄኔ ሩሲያዊው ወደ አሜሪካኑ ዞሮ፤
“እስቲ ታማኝነቱን ለማረጋገጥ ከገደል አፋፍ ውድቅ በለው” አለው፡፡
የአሜሪካው መሪም ለወታደሩ “በል ከዚህ ገደል ወደ መሬት ተወርወር” አለና አዘዘ፡፡
ወታደሩም፤ “አላደርገውም ጌታዬ” አለው
መሪው፤ “ለምን?”
ወታደሩ፤ “በእኔ ሥር የሚተዳደሩ ብዙ ቤተሰቦች አሉኝ ጌታዬ” አለ፡፡
ሩሲያዊው ሳቀ፡፡ “ይሄንን ነው ታማኝ ወታደር አለኝ የምትለው? ቆይ የእኔን አገር ወታደር አሳይሃለሁ፤ ጋብዤሃለሁ ናና እይ” አለው፡፡ በግብዣው መሠረት አሜሪካዊው መሪ የጉብኝት አፀፋውን ለመመለስ ከሦስት ቀን በኋላ ወደ ሞስኮ በረረ፡፡ የሩሲያን ወታደር ከባድ ሰልፍ ጐበኘ፡፡ ከዚያም ወደ ሩሲያዊው መሪ ዞሮ፤
“በል እስቲ አንተም አንድ ወታደር አስጠራና ስለታማኝነቱ እኔም ጥያቄ ልጠይቀው” አለው፡፡
አንድ ወታደር ተጠራ፡፡
የሩሲያው መሪ ለወታደሩ፤
“በል ከዚህ ገደል ተወርወር!” አለና አዘዘው፡፡
ወታደሩ ሳያቅማማ ሰላምታ ሰጥቶት ወደ ገደሉ ተወረወረ፡፡ የአሜሪካው መሪ በጣም ተገርሞ ወደ ገደሉ ጫም ሄዶ ቁልቁል ተመለከተ፡፡ እንዳጋጣሚ የተወረወረው ወታደር አንድ የዛፍ ቅርንጫፍ ላይ አርፎ ኖሮ መሬት ሲደርስ ለሞት አልተዳረገም። የአሜሪካው መሪ ወታደሩ እንዲመጣ ጠየቀ፡፡ ወታደሩን ተሸክመው አመጡለት፡-
“አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፡፡ የእኔ ወታደር ወደ ገደል ተወርወር ብለው፤ የምረዳቸው ቤተሰቦች ስላሉኝ አላረገውም አለኝ፡፡ አንተ ግን ተወርወር ስትባል ተወረወርክ ምክንያትህ ምንድነው?”
ወታደሩም፡-“እኔም የምረዳቸው ቤተሰቦች ስላሉኝ ነው”
የአሜሪካው መሪ በመደነቅ ፡- “እንዴት?”
ወታደሩም፡- “ምቢ ብል እኔን ብቻ አይደለም የሚገሉኝ፡፡ ቤተሰቤንም ጭምር ነው!”
ማረሚያ ቤት ለአቶ አሥራት ጣሴ የሰጠው ምላሽ
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣው አዲስ አድማስ ዕትም ላይ የቀድሞው የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ የነበሩትና በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ ሳይካተቱ የማዕከላዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ አስራት ጣሴ፤ “የሙስና አዋጁ እንደገና ሊፈተሽና ሊታይ ይገባል” በሚል ርዕስ “በእስር በቆየሁባቸው 10 ቀናት ውስጥ ስለ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የታዘብኳቸው” በማለት ከከፍተኛ ሪፖርተር አለማየሁ አንበሴ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ተመልክተነዋል፡፡ ይሁን እንጅ አቶ አስራት ጣሴ ስለማረሚያ ቤቱ የተናገሩት ወደ አንድ ፅንፍ ያዘመመና የተቋሙን ገፅታ ሙሉ በሙሉ በሚያበላሽ መልኩ የቀረበ ሲሆን ማረሚያ ቤቱን በተመለከተ ትክክለኛው መረጃ ለህብረተሰቡ ይደርስ ዘንድ ምላሻችንን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
1ኛ/ በእስር ቤት ቆይተዎ ምን ታዘቡ? ተብለው ለተየጠቁት ጥያቄ
“በእውነት በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በቆየሁባቸው ስምንት ቀናት በዚች ሀገር የፍትህ ስርዓት እንዴት ፈታኝ እንደሆነ ተረድቻለሁ” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡ (ገፅ 14)
በአሁን ሰዓት መንግስት ዜጎች የፍትህ ተደራሽነት ይኖራቸው ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ተግቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት ከቅርብ ዓመታት በፊትም የፍትህ አካላትን በማዋቀር “ፍትህ ለሁሉም ይዳረስ” በሚል መሪ ቃል፣ የፍትህ አካላት በከፍተኛ ሁኔታ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከፍትህ አካላትም መካከል የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አንዱ ሲሆን መንግስት በሰጠው ተልዕኮ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኙ የህግ ታራሚዎችንና የቀጠሮ እስረኞችን ተቀብሎ በመጠበቅ፣የታረመና የታነፀ ዜጋ ለማድረግ ፍትህ በማስጠበቅ የህግ ታራሚዎችም አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በፈፀሙት ወንጀል ተፀፅተው ከእርምት በኋላ ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ አምራች ዜጋ ለመፍጠር እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡ አቶ አስራት ጣሴ ግን በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ውስጥ ተአማኒነት ያለው አስተያየት ለመስጠት በቂ የእስር ጊዜያትን ሳያሳልፉና ሁኔታዎችን ሳያጤኑ በአጠቃላይ የማረሚያ ቤቱን ስም በሚያጎድፍ መልኩ “ፍትህ የለም” ብለው መናገራቸው አግባብነት የሌለውና ከእውነት የራቀ ነው፡፡ በመሰረቱ ማንኛውም ሰው ነፃ አስተያየት የመስጠት መብት ቢኖረውም እነዚህ አስተያየቶች ግን በማስረጃና በደጋፊ እውነታዎች መመስረት ሲገባቸው፣ ተጠያቂው ግን “በዚች አገር ፍትህ እንዴት ፈታኝ እንደሆነ ተረድቻለሁ” በሚል ያለምንም መገለጫ ከእውነት በራቀ መልኩ የተናገሩት ንግግር ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ስለዚህ አስተያየቱ ከአሉባልታ የማይሻገርና መንግስት ግልፅ የሆነ አሰራር እየተከተለ ባለበት ጊዜ የማረሚያ ቤቱን ፍትህ የማረጋገጥ ጉዞ በሚያሰናክል መልኩ የቀረበ በመሆኑ የሚስተካከል ቢሆን፡፡
2ኛ/ “የማረሚያ ቤት አያያዝ ባልተፃፈ ህግ የሚመራበት ሁኔታ እንዳለም ተረድቻለሁ” በማለት ትዝብታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ (ገፅ 14)
ነገር ግን የፌደራል ማረሚያ ቤቶች መቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 365/95 በተሰጠው ስልጣን እንዲሁም ደንብ ቁጥር 138/99 የታራሚዎች አያያዝ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው ደንብ መሰረት፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኙ የህግ ታራሚዎችና የቀጠሮ እስረኞችን ተቀብሎ ከውስጥና ከውጭ ሊደርስ ከሚችል ጥቃት በመጠበቅ፣ መሰረታዊ ፍላጎታቸውን በማሟላትና አርሞና አንፆ አምራች ዜጋ የማድረግ ኃላፊነት አለበት ሲል የሚደነግግ ነው፡፡
ከዚህም በመነሳት ታራሚዎች የፍርድ ግዜያቸውን ጨርሰው እስከሚወጡ ድረስ ማረሚያ ቤት የራሱ የሆነ ህግና ደንብ አውጥቶ የህግ ታራሚዎችንም ሆነ የተቋሙ ሰራተኞችን ያስተዳድራል፡፡
ነገር ግን አቶ አስራት ጣሴ፣ በማረሚያ ቤት ውስጥ ምንም አይነት የተፃፈ ህግ እንደሌለና በመተዳደሪያ ደንብ ሳይመራ በዘፈቀደ ማረሚያ ቤቱ ደስ ባለው ህግ እንደሚተዳደር አድርገው መናገራቸው አግባብነት የሌለውና በእርግጥም ስለሚሰጡት አስተያየት ግልፅ እውቀት የሌላቸው መሆኑን ያሳያል፡፡ የህግ ታራሚዎችን ለማስተዳደር በወጣው ደንብ አንቀጽ 27 ላይ በግልፅ እንደሚደነግገው፣ አሁንም ያለው አሰራር እንደሚያሳየው፣ ማንኛውም የህግ ታራሚ ወደ ማረሚያ ቤት በሚገባበት ጊዜ የማረሚያ ቤቱ የስነስርአት ደንቦች በቃልና ግልፅ በሆነ ቦታ ሁሉም ታራሚ በሚመለከተው ሁኔታ የማስቀመጥና በዝርዝር የሚገለፅበት አሰራር አለ፡፡ አቶ አሥራት ግን በማረሚያ ቤቱ ጥበቃ የተደረገላቸውን መረጃ የማግኘት መብት በማጥላላት፣ምንም ዓይነት የተፃፈ ህግ የለም በሚል ያቀረቡት አስተያየት በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ያለውን አሰራር የማያመለክት ከመሆኑም በላይ የህግ ታራሚዎችም መመሪያው በሚፈቅደው የዝውውር፣ የአመክሮ፣ የቅበላና የድልደላ መመሪያዎች እየተዳደሩ የሚገኙ ሲሆን ይህም ጉዳይ በአፋጣኝ ታርሞ የሚቀርብ ቢሆን፣
3ኛ/ ህገ-መንግስቱ ላይ ሰው በሰውነቱ ሊያገኛቸው የሚገባ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተብለው በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡
ሰብአዊ መብት ተብለው ከተቀመጡትም የመናገር፣ የመፃፍ፣ የማንበብና የመማር ወ.ዘ.ተ ይገኙበታል፡፡ ይሁን እንጂ አቶ አስራት ጣሴ የካቲት 15 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣው አዲስ አድማስ እትም ላይ ለህግ ታራሚዎች የግል ጋዜጦችና መፅሔቶች ያለመግባታቸውን ሰብዓዊ መብትን እንደመጣስ ይቆጠራል ብለዋል፡፡ (ገፅ 14)
እርግጥም የማንበብን መብት መንፈግ ሰብዓዊ መብት እንደመጣስ የሚቆጠር ቢሆንም ማረሚያ ቤቶች ባለው ደንብና መመሪያ መሰረት ታራሚዎችን ሲያስተዳድሩ ስነ-ፅሁፎች፣ ጋዜጦችና መፅሄቶች እንዳይገቡ የሚከለክል ሳይሆን የእርምት ሂደቱ ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድርና በታራሚዎች መካከል ጤናማ ግንኙነት የሚያበላሽ መሆን ስለማይገባው፣ ወሲብ ቀስቃሽ የሆኑና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የሚፃረሩ ይዘት ያላቸው መፅሄቶች፣ መፅሀፎችና ጋዜጦች እንዳይገቡ ይደረጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወንጀል ሰርታችኋል ተብለው በፍርድ ቤት የተወሰነባቸው በእርምት ላይ የሚገኙ የህግ ታራሚዎች፣ ለእርምታቸው መሰናክልን ሊፈጥሩ ይችላሉ ተብለው የታመነባቸው ጋዜጦችና መፅሔቶች እንደየአስፈላጊነቱ የማይገቡ ቢሆንም በአጠቃላይ መፅሀፎች እንዳይገቡ አልተከለከለም፡፡
ይህ ደግሞ ሰብዓዊ መብትን መጣስ ሳይሆን ወንጀለኛ ተብሎ የተፈረደበት የህግ ታራሚን ተመልሶ ወደ ጥፋት እንዳይገባ ለማድረግ እንደሆነና የማንበብ መብቱን ለመንፈግ እንዳልሆነ አንባቢያን እንዲረዱ እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም የማንበብ መብታቸው ቢነፈግ ኖሮ፣ የተለያዩ መፃህፍቶችና መማሪያ ፅሁፎች እንዲሁም ለማረም ማነፅ የሚያግዙ በራሪ ፅሁፎች ወደ ማረሚያ ቤት ባልገቡ ነበር፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ በማረሚያ ቤት ውስጥ ቤተ-መፃህፍት ማቋቋም ባላስፈለገ ነበር፡፡
በአጠቃላይ አስተያየት ሰጭው ተራ የፖለቲካ ተወዳጅነትን ለማትረፍና ህግ ታራሚዎች ላይ የፖለቲካ ቅስቀሳ ለማድረግ የተጠቀሙት መንገድ እንጂ በቂ መረጃና ደጋፊ መገለጫ ችግሮችን አንስተው ህብረተሰቡን ወይም ማረሚያ ቤቱንም ለለውጥ ትግሉ አጋዥ የሚሆን አስተያየት እንዳልሰጡ ተገንዝበናል፡፡ ግለሰቡ በእውቀት ላይ የተመሰረተ አስተያየት ባለመስጠታቸውና ዘለፋና አሉባልታ ላይ በማተኮራቸው ሊታረሙና ለሰጡትም አስተያየት አንባብያንን ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባቸዋል፡፡
የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር