Administrator

Administrator

በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በ14 .5 ሚሊዬን ዶላር የተገነባ ዘመናዊ የፕላስቲክ ቧንቧና መገጣጠሚያ ማማረቻ ፋብሪካ የፊታችን ቅዳሜ ይመረቃል፡፡
ፋብሪካውን “ኢ ዜድ ኤም ትሬድ እና ኢንቨስትመንት” የተሰኘው ኢትዮጵያዊ የንግድ ኩባንያና የቻይናው ዓለም አቀፍ ድርጅት ሪፎ በጋራ እንደገነቡት ተገልጿል፡፡
የፋብሪካውን ምርቃት አስመልክቶ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና የኩባንያዎቹ ከፍተኛ አመራሮች በዛሬው ዕለት በጋራ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፤ ፋብሪካው በዘርፉ ያለውን የአቅርቦት እጥረት ለመፍታትና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት ያለመ ነው ተብሏል።
ፋብሪካው ወደ ስራ ሲገባ 2ሚሊዬን ሜትሪክ ቶን ፒፒአር ቱቦዎችና 1 ነጥብ 9 ሚሊዬን የፒፒአር መገጣጠሚያዎች ፣ 1 ሚሊዬን ሜትሪክ ቶን የፒቪሲ ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችና 9 መቶ ሺህ የፒቪሲ መገጣጠሚያዎች እንዲሁም 3 ነጥብ 5 ሚሊዬን ሜትር በላይ የፒቪሲ ኮንዲዩት የማምረት ዓመታዊ አቅም አለው ተብሏል፡፡
ፋብሪካው በአሁኑ ሰዓት የሙከራ ምርት እያመረተ ሲሆን ፥ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ከ600 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ተጠቁሟል፡፡
በ3 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ፋብሪካው፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዘመናዊ የፕላስቲክ ቧንቧና መገጣጠሚያ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በመሆን እውቅና ማግኘቱም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
የቻይናው ሪፎ ኩባንያ በዘርፉ የ27 ዓመት ልምድ ያካበተና በመላው ዓለም እየሰራ እንደሚገኝ፣ በኢትዮጵያም ልምዱን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግሩንና ብራንዱን ይዞ እንደመጣ የተገለጸ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊው ኢ ዜድ ኤም በበኩሉ፣ ላለፉት 6 ዓመታት የሪፎን ምርቶች ብቸኛ ወኪል አስመጪ ሆኖ ሲሰራ እንደቆየ የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ እስመለአለም ዘውዴ፣ ምርቱን በማስመጣት ብቻ በአገር ውስጥ ያለውን ፍላጎት ማሟላት ስላልተቻለ በአገር ውስጥ ማምረቱ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አብራርተዋል።
ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር፣ 50 በመቶ ምርቱን ለጎረቤት አገራት ምርት እንደሚልክም ተገልጿል፡፡

•  የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስን ዲጂታላይዝ የሚያደርጉ መላዎችንም አስጀምሯል


ኢትዮ ቴሌኮም፤ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣንና የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጋር በመተባበር፣ የነዳጅ አቅርቦት የአሰራር ስርዓትንና የነዳጅ ኩፖንን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችል እንዲሁም ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርና ከመንገድ ደህንነትና ኢንሹራንስ ፈንድ አገልግሎት ጋር የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን አገልግሎትን ዲጂታላይዝ የሚያደርጉ ሶሉሽኖችን በይፋ አስጀምሯል፡፡


ኩባንያው በዛሬው ዕለት የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለትን በተማከለ የዲጂታል ሥርዓት ለማከናወን የሚያስችል የነዳጅ አቅርቦት ትስስር አስተዳደር ሶሉሽን /Fuel Supply Chain Management System/ በማበልጸግ ተግባራዊ ማድረጉን ያስታወቀ ሲሆን፣ ይህም ሶሉሽን በነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ ያሉ ዘልማዳዊ የአሰራር ሂደቶችንና በወረቀት ላይ የተመሰረቱ አሰራሮችን ለማዘመን፣ ግልጽነት ያለው የነዳጅ አቅርቦትና ግብይትን ለማስፈን፣ ትክክለኛ ዳታ በወቅቱ ለማግኘት እንዲሁም በሂደቱ ውስጥ ለሚያስፈልጉ መሳሪያዎች ግዢ የሚውል የውጪ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው አመለክቷል፡፡


በተጨማሪም፤ የዘርፉ ተዋናዮች ማለትም የነዳጅ ጣቢያዎችና ቀጥተኛ ተጠቃሚ ደንበኞች፣ የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች፣ የኢትዮጵያ የፔትሮሊየም አቅራቢ ድርጅት እንዲሁም የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አጠቃላይ የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የሚከናወኑ እንቅስቃሴዎችን ለመከታተል፣ የነዳጅ አቅርቦት ትዕዛዝን በዲጂታል መላ ለመስጠት/ለማቅረብ፣ ትዕዛዝ ለመቀበል እንዲሁም አስፈላጊውን ዳታ በወቅቱ ለማግኘት (real-time data access) ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል፡፡


በሌላ በኩል፤ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የማንዋል የነዳጅ ኩፖን ሽያጭ አገልግሎት አሰራርን ወደ ወረቀት-አልባ የዲጂታል ኩፖን በመቀየር አዲሰ አሰራር ያስተዋወቀ ሲሆን፤ ይህም ዘመናዊ አሰራር የነዳጅ ኩባንያዎች የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን፣ የነዳጅ ማደያዎችን የአገልግሎት አማራጭ ለማሳደግ፣ ግብይቶችን ለማሳለጥ፣ የገንዘብ ፍሰትን ለማሻሻል፣ የሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን ለመቀነስ፣ የተጠቃሚዎችን መጠን ለመጨመርና ሽያጭ ለማሳደግ፣ የዲጂታል ኩፖን ዳታዎችን ለመቆጣጠር እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀ ግብይት ለማካሄድ የሚያስችል የዲጂታል ሶሉሽን ማስተዋወቁን በመግለጫው አመልክቷል፡፡   


በተመሳሳይ ሁኔታ፤ ኩባንያው የሦስተኛ ወገን የመድን አገልግሎትን በዲጂታል ስርአት አማካኝነት ለመስጠት የሚያስችል ሶሉሽን ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርና ከመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ ጋር በመተባበር ይፋ አድርጓል። ይህም የኢንሹራንስ አገልግሎት አሰጣጥ ተግዳሮቶችን በማስቀረት በተለይም የተማከለ መረጃ እንዲኖር ለማስቻል፣ ክፍያን በወቅቱና በዲጂታል መንገድ ለማከናወን፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል፣ የተሟላ ሪፖርት በወቅቱ ለማግኘትና ወረቀት-አልባ አገልግሎት ለመስጠት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል፡፡


በተጨማሪም ይህ የዲጂታል ሶሉሽን ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን ለመቀነስ፣ ተገልጋዮች የሚያደርጉትን ምልልስና ውጣ ውረድ በማስቀረት ባሉበት ሆነው በቀጥታ (online) እንዲስተናገዱ ለማድረግ፣ በኢንሹራንስ ሂደቶች ውስጥ የሚከሰቱትን ተግዳሮቶች ለመቀነስ እንዲሁም የእድሳትና ባለቤትነት ለውጥ አሰራርን ዲጂታላይዝ ለማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ኢትዮቴሌኮም ጠቁሟል፡፡

12ኛው ዓለማቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ኮንፈረንስ በህዳር ወር ይካሄዳል

12ኛው ዓለማቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ኮንፈረንስ “ኢትዮጵያ ለግብርና ምርት ፍላጎትዎ አስተማማኝ ምንጭ” በሚል መሪ ቃል፣ ህዳር 11 እና 12 ቀን 2016 ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል እንደሚካሄድ ተገለፀ።

ኮንፈረንሱን የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር፣ ከኢፌዲሪ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንደሚያዘጋጁት ተጠቁሟል።

የኮንፈረንሱን አጠቃላይ ዝርዝር ሁኔታ አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ረፋድ ላይ የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር፣ ርብቃ ህንፃ 7ኛ ፎቅ ላይ  በሚገኘው ፅ/ቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

ለሁለት ቀናት በስካይላይት ሆቴል በሚካሄደው ኮንፈረንስ ላይ 400 የአገር ውስጥ ላኪዎች፣ የእርሻ ግብአትና ማሽነሪ አቅራቢዎች፣ የጉምሩክ አስተላላፊዎች፤ እንዲሁም ከ20 የተለያዩ አገራት የሚመጡ ከ100 በላይ ዓለማቀፍ ምርት ገዢ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል። ከእነዚህ አገራትም ውስጥ ቤልጂየም፣ ቻይና፣ ግብፅ፣ ህንድ፣ እስራኤል፣ ጃፓን፣ ፓኪስታን፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ሲንጋፖር፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ቱርክ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ ዩክሬን፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ኡዝቤኪስታን፣ ጣሊያን፣ ናይጀሪያና ቡርኪናፋሶ ይገኙበታል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር አመራሮች በመግለጫው ላይ እንዳመለከቱት፤ ዓለማቀፍ ገዢዎችን፣ የአገራችን የዘርፍ ምርት ላኪዎችን፣ የእርሻ ምርት ግብአት አቅራቢዎችን፣ ከፍተኛ የመንግስት ተቋማትና የተለያዩ  አገልግሎት ሰጪዎችን  በአንድ መድረክ በማገናኘት የንግድ ትስስር መፍጠር ከኮንፈረንሱ ዓላማዎች አንዱ ሲሆን፤ ተሳታፊዎች በዘርፉ ያለውን  ዓለማቀፍ የንግድ አጠቃላይ ሁኔታ (የአቅርቦት ፍላጎትና ዋጋ አዝማሚያዎች) በተመለከተ የተሟላ መረጃ እንዲያገኙ ማስቻልም ሌላው  የኮንፈረንሱ ዓላማ ነው ተብሏል።

ኮንፍረንሱን የሀገር ውስጥ ላኪዎች የንግድ ግንኙነታቸውን በላቀ ሁኔታ ለማጠናከር እንዲሁም አዳዲስ የንግድ ግንኙነቶችን ለመመስረት እንደሚጠቀሙበት የተገለፀ ሲሆን ፤ በተጨማሪም ቀጣይ  የሽያጭ ውሎችን ለመፈራረም ከፍተኛ ዕድል ይፈጥርላቸዋል ተብሏል፡፡

ሀገሪቱ ዘርፉን እንድታሳድግ በመንግሥት የታቀደውን ዕቅድ ከማሳካት አንፃርም ኮንፈረንሱ ከፍተኛ አስዋፅኦ እንደሚያበረክት የማህበሩ አመራሮች ጠቁመዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ 14 ፅሁፍ አቅራቢዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ፅሁፎች እንደሚያቀርቡም ታውቋል፡፡

የማህበሩ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው የግብርና ምርቶች የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ ምርቶች መካከል  ተጠቃሽ ሲሆኑ፤ አገሪቱ በ2015 በጀት ዓመት 147, 205 ቶን ቅባት እህሎች ወደ ውጭ በመላክ 253,344,754 ዶላር ገቢ አግኝታለች፡፡ በዚሁ በጀት ዓመት 377,261 ቶን የጥራጥሬ ምርቶች ወደ ውጭ ተልከው፣ 310,568,278 ዶላር ገቢ መገኘቱም ታውቋል፡፡

ባለፈው ዓመት በህዳር ወር 11ኛው የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ኮንፈረንስ በሸራተን አዲስ ሆቴል መካሄዱን ያስታወሰው የማህበሩ መግለጫ፣ በኮንፈረንሱ ላይ ከ435 በላይ ገዢዎች፣ ላኪዎች፣ አስመጪዎችና አገልግሎት ሰጪዎች መሳተፋቸውን እንዲሁም ከ250 በላይ ጥሪ የተደረገላቸው የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በስኬት መጠናቀቁን አውስቷል፡፡

 

 የቴሌግራም ቻናልችንን  በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Tuesday, 14 November 2023 06:34

addisadmassnews.com Issue1243

በአልባኒያ ሊግ ዘጠኝ ግቦችን በማስቆጠር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የነበረው ጋናዊው አጥቂ ራፋኤል ድዋሜና በጨዋታ መሐል ሕይወቱ ማለፉ ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡
ተጫዋቹ የተሰለፈበት ኢግናቲያ ክለብ ከፓርቲዛኒ ጋር እየተጫወተ ባለበት ወቀት በ23ኛው ደቂቃ አካባቢ ተዝለፍልፎ የወደቀ ሲሆን፤ አፋጣኝ የሕክምና ክትትል ቢደረግለትም በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል፡፡
ዳዋሜና ራሱን ስቶ ከወደቀ በኋላ በህክምና ባለሙያዎች እርዳታ ከሜዳ እንዲወጣ ከተደረጓ በኋላ ሕይወቱ ማለፉን ነው የአልባኒያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የገለጸው፡፡
የ28 ዓመቱ ራፋኤል ድዋሜና በስፔን፣ ስዊዘርላንድ፣ ኦስትሪያ እና ዴንማርክ ባሉ ክለቦች በመጫወት የተሳካ ጊዜ አሳልፏል።
በዚህ የውድድር ዘመን በአልባኒያ ሊግ ዘጠኝ ግቦችን በማስቆጠር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነበር ሲሆን፤ በፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ህይወቱም ዘጠኝ ጊዜ ለሀገሩ ጋና ተጫውቷል።
ተጫዋቹ ከልብ ሕመም ጋር በተያያዘ በ2021 ከእግር ኳስ ራሱን እንዲያገል ከህክምና ባለሙያዎች ምክር ቀርቦላት እንደነበር ዶቼ ቬለ ዘግቧል፡፡

  ኮሎኔል መንገሻ ወልደ ሚካኤል (8) ከአባቴ ጋር አንድ ኮርስ ሲሆኑ ያገኘኋቸውም አዲስ አበባ ነበር። አባቴ የልዩ ኃይሉ አዛዥ ሆኖ ድሬደዋ የሚሠራበት ወቅት እሳቸው እዚያው ከተማ የመድፈኛ ጦር የትምህርት መኮንን ሆነው  ለአንድ ዓመት ቆይተዋል። በወቅቱም ከአባቴ ጋር ብዙ ተቀራርበው እንደነበር ቃለ-ምልልስ ስናደርግ አጫውተውኛል። ከዚያ ወዲያም በደብዳቤ ያስታወሱትን ሁሉ ጽፈው ልከውልኛል። ድሬደዋ በእረፍታቸው ወቅት በአባቴ ላንድሮቨር ሆነው አብረው ይዝናኑ እንደነበር ነግረውኛል።
“በዚያ ወቅት አባትሽ ጂቡቲ ገና ነፃ ሳትሆን ሀረር፣ ጅጅጋና  ኦጋዴን በመሯሯጥ እጅግ ይባክን ነበር። አንዳንዴ በጣም በጠዋት ቀድሞ ይነሳና ከተባሉት ሥፍራዎች ሲዞር ውሎ ማታ ይገባል። የተሰጠውን ግዳጅ ለመፈጸም ሁሌ እንደተሯሯጠ ነበር።” ኮሎኔል መንገሻ ወልደሚካኤል።


ኮሎኔል መንገሻ ወልደሚካኤል አባቴን ሲያነሱ “ውድ ወንድሜ ጀግናው ዳግማዊ ቴዎድሮስ” በማለት ነው በደብዳቤአቸውም ሆነ በቃላቸው የሚጠቅሱት። በተለምዶ አብሮ ትምህርት የጨረሰ ሰው ይናናቃል-ይባላል። እሳቸው ግን በጣም የጠራ ቅንነት ቢኖራቸው ነው እንዲህ ማለታቸው። ክፋቱ ግን ከአባቴ ጋር ምንም አብረው አልሠሩምና ስለ አባቴ የሚያቁት ነገር በጣም የተወሰነ መሆኑ ላይ ነበር።
አባቴን ከጂቡቲ ጉዳይ ጋር በማያያዝ ለመጀመሪያ ጊዜ ያነሱልኝ ሰው ግን እሳቸው ነበሩ። አባቴ ጂቡቲን በተመለከተ “በመሯሯጥ እጅግ ይባክን” የነበረው ምን እያደረገ እንደሆነ ግን ፈጽሞ አያውቁም። ምን ዓይነት ተግባር እንደፈጸመ ማወቅ አልቻሉም። በጠዋት ተነስቶ ማታ መግባቱን ግን አስተውለዋል። አብረው እየዞሩ እየጠጡና እየተዝናኑም አላጫወታቸውም። ከባድ ሚስጥር እንደነበር ግልጽ ነው። እናም አልተወው ነገር አክብደው ነው የገለጹት። እናኔም ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር ለመቀላቀል እንድትችል ይደረግ ከነበረው የፖለቲካ፣ የፕሮፓጋንዳ እና የውጭ ጉዳይ የዲፕሎማሲ ጥረት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ጽሁፎችንም በሄሊኮፕተሮች ይበትኑ እንደነበር ሰምቻለሁ። ለዚሁ ተግባር ይሆናል አባቴ  ሲሯሯጥ የነበረው ብዬ ገመትኩ።


ይህንን እንደዚህ ደምድሜ ካለፍኩ ወዲያ ብዙ ቆይቶ በሌላ ቃለ-ምልልስ ካልጠበኩትና ከጉዳዬም ጋር ግንኙነት ይኖረዋል ብዬ ካልገመትኩት ሰው ፍንጩን የሚያብራራ አቢይ ነጥብ አገኘሁ። የመደምደሚያ ግምቴም ብዙም ከእውነቱ አለመራቁን አረጋገጥኩ። አንዳንዴ ሰዎች የሚሰጡት ትንሽ ፍንጭ ከሌላ ሰዎች መረጃ ጋር ሲዋሃድና ሲጣመር ይጎላና ይገዝፋል።
አቶ እጅጉ ደሴ (40) በኢትዮጵያ የአየር መንገድ አስተዳደር ውስጥ አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ሆነው ያገለገሉ ናቸው። ስለበረራ ድህንነቱ የአባቴ አገልግሎት- ስናደርግ በአጋጣሚ የጅቡቲውን ነገር አነሱብኝ። አባቴ አየር መንገዱን ከለቀቀ ወዲህ አንዴ እራት ጋብዘውት እቤታቸው ይወስዱታል። በእራቱ ግብዣ ላይ ሲጨዋወቱ በአጋጣሚ የጅቡቲው ነገር ተነሳ። ጅቡቲ ከላይ እንዳሰፈርኩት ተጠቃላ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት የሆነችው እ.ኤ.አ በ1888 ዓ.ም ላይ ነበር። ፈረንሳይ በጀነራል ቻርለስ ደጎል እየተመራች በነበረበት ወቅት፤ እ.ኤ.አ በ1967 ዓ.ም ላይ፤ የጅቡቲ ህዝብ አንድ የብያኔ ህዝብ እድል አገኘ። ቀደም ሲልም ሌላ እድል ተሰጥቶት ከፈረንሳይ ጋር ለመቆየት መርጦ ነበር። ይህን ጊዜ ግን ጄኔራል ደጎል ከጃንሆይ ጋር ጥሩ ቅርበትና መልካም ግንኙነት ነበራቸውና ከብያኔ ህዝቡ ወደ ፈረንሳይ ጅቡቲን በምትለቅበት እለት ኢትዮጵያ በምትኩ ብትገባ ምንም እንደማይቃወሙና እርምጃም እንደማይወስዱ አረጋግጠውላቸው ነበር።
ጂቡቲ የአፋርና የኢሳ ብሔር ህዝቦች ይኖሩባታል። ኢትዮጵያ በአፋሮቹ ከኢትዮጵያ መቀላቀል መፈለግ ስታምን፣ ሱማሊያ ደግሞ በኢሳዎቹ ከሶማሊያ መቀላቀል ታምናለች። ለጅቡቲ ህዝብ ድምጽ አሰጣጥም ኢትዮጵያና ሶማሊያ የራሳቸውን ቅድመ ቅስቀሳና ጥረት አድርገዋል። ሱማሊያ ከቅስቀሳው ባሻገር የእራሷን ሰው ለምርጫ ወደ ጁቡቱ ሱማሌያ ስታግዝ፣ ኢትዮጵያ ከፕሮፓጋንዳ ቅስቀሳ ውጭ አልዘለቀችም ነበር። ውጤቱ ደግሞ ለሁለቱም አልሆነም፤ የጅቡቲ ህዝብ በፈረንሳይ እጅ  ሆኖ ወደ ነጻነት ለማምራት በድምጹ ወሰነ።በወቅቱ ጃንሆይ የደጎልን የይግቡ አረንጓዴ መብራት እንዳገኙ የ3ኛ ክፍለ ጦርና የክብር ዘበና ጦርን ከጅቡቲ ድንበር በተጠንቀቅ አሰፈሩ።  አባቴ በድንበሩ ተጠንቀቅ ላይም ከ3ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ከጄ/ል አበበ ገመዳ ጋር አብሮ ነበር። ይህንን ነበር አይቶ እጅጉ ደምሴን ያጫወታቸው።


በቦታው ሆነው የጃንሆይን “የወደፊት ቀጥሎ” ትዕዛዝ ሲጠባበቁ ከሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ገደማ ላይ እራሳቸው ጃንሆይ በስልክ/ሬዲዮ ጄኔራሉን አስቀርበው፣ “አበበ አትግባ!” አሏቸው። ጄነራሉ ስልኩን ሰምተው ስቅስቅ እንዳሉ ገልጾ፤ “ሁለተኛ ኢትዮጵያ እንደዚህ አይነት እድል አያጋጥምሽም! ደጎል እኮ እኛ ስንወጣ እናንተ ግቡ ብሏል!” ብሎ በምሬትና ቁጭት አባቴ እንዳጫወታቸው አቶ እጅጉ ደምሴ ገለጹልኝ።
ጃንሆይ ለምን አትግባ አሉ? ለሚለው ጥያቄም አቶ እጅጉ ደምሴም መልሱን በደንብ ደርሰውበታል። ቀደም ሲል አልጀሪያና ሞሮኮ ተጋጭተው ሊዋጉ ጦራቸውን በየድንበራቸው በማዘጋጀት ላይ እያሉ በአጋጣሚ ጃንሆይ በወቅቱ በይይቤሪያ በጉብኝት ላይ ሆነው ሁኔታውን አወቁ። ከዚያ አልጀርስና ካዛብላንካ ተመላልሰው መሪዎችን አነጋግረው፣ የሁለቱንም ጦር ከድንበራቸው እንዲያፈገፍጉ በማድረግ ጦርነቱን አስቀሩት። ሱዳንንም ከተቃዋሚ ቡድን ጋር አስታርቀው ነበር።


ስለዚህም ጃንሆይ “የሰላም የኖቤል ሽልማት” ያገኛሉ ተብሎ በተስፋ ላይ ነበሩ።  በዚያ ወቅት ጅቡቲን ከወረሩ ያ የኖቤል ሽልማት እድል መቅረቱም ሆነ ለዚህ ነው ጦሩን እንዲመለስ ያደረጉት። ሻምበል ጌታቸው ወ/ማርያም የክብር ዘበኛ ጦር፣ ያኔ ድንበሩ ድረስ መሄዱንና የጃንሆይን የኖቤል ሽልማት ጉዳይ ትክክለኝነት ማወቃቸውን በደንብ አረጋግጠውልኛል። ዶ/ር ሰለሞን አበበ (41) ደግሞ የኖቬል ሽልማትን ጉዳይ እንደ አንድ ምክንያት ተቀብለው  በተጨማሪም ጃንሆይን ከጅቡቲ ህዝብ መሃል በፈረንሳይ ደሞዝተኝነት የሚተዳደረው ብዙ ነበርና ያንን ማስተዳደሩና ደመወዝ መክፈሉን ፈርተው የውሃና የመብራት ችግሩን ብቻ እንኳን ምን ያህል ወጪ እንደሚጠይቅ አውቀውና መክረው ያደረጉት ነው ብለው ያምናሉ። ጦሩ ድንበር ላይ በተጠንቀቅ መቆሙን በተመለከተም እሳቸው በወቅቱ ሀረር ክፍለ ሀገር የልማት አስተዳዳሪ ሆነው ይሰሩ ስለነበር በደንብ ማወቃቸውን አረጋግጠውልኛል።


 ዶ/ር ሰለሞን የተወለዱትና ያደጉት ሀገር ሲሆን በተለያዩ ክፍለ ሀገራት በአስተዳደርና ልማት ስራ አገልግለው ከዚያም በተመድ የስደተኛ አስተዳዳሪነት በየሀገሩ ተዘዋውረው አሁን ዳላስ ቴክሳስ ውስጥ በጡረታ ይኖራሉ። በዚህ በዳለስ ከተማ ባለው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ በአባትነት መካሪ፣ አስተባሪና አስታራቂ በማገልገል  ተወዳጅነት አላቸው።


በሌላ ምዕራፍ ላይ የጠቀስኳቸው ኮሎኔል ዘሩ እጅጉ (921) ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ በስራ አባቴን የተገናኙት ድሬዳዋ ሆኖ ነበር። እሳቸው በዚህም ወቅት በመረጃ ሥራው ላይ ነበሩ። ድሬዳዋ አየር ኃይል ማሠልጠኛ ሲቋቋም እሳቸውም በሙያቸው መምጣታቸውን ያስታውሳሉ። የፕሮፓጋንዳ ሥራውን በተመለከተ በጣም የቀረበና የበለጠ ትዝታ አላቸው። በዚህ ወቅት አባቴ የሚመራው ልዩ ኃይል የሱማሌን መንግስት ለማናወጥ ብዙ የፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ ሥራን መስራቱን በደንብ ያስታውሳሉ። ጽሁፎችን በአየር ላይ ሆነው ለመበተን አባቴና አባባሎቹ እስከ በረራ ድረስ ጠልቀው ይገቡ እንደነበር ገልጸው፤ አባቴ ጦሩን ይዞ ሲንቀሳቀስ እሳቸው መረጃ በመስጠት የጠበቀ የስራ ግንኙነት ትብብር እንደነበራቸውና እሳቸው እራሳቸውም በሙያቸው የተካፈሉበት ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ አረጋግጠውልኛል።

 ከእለታት አንድ ቀን፣ አያ ዝንጀሮ፣ የአንበሳን ሚስት ሊያሽኮረምም አስቦ አንበሳ በሌለበት ወደ ሚስትየው ይሄዳል፡፡ የአንበሳ ሚስት የዝንጀሮን መላ ሰውነት ቃኝታ ስታበቃ፣
“አያ ዝንጀሮ፤ አይንህ ለምን ቀላ?” ብላ ትጠይቃለች፣ አይኑን አተኩራ እያየች፡፡
ዝንጀሮም፤
“የዐይኔ መቅላትማ የጀግንነት ምልክት ነው” ይላታል፡፡
ቀጥላ ወደ እጁና ወደ እግር ጥፍሩ እያስተዋለች፤
“ጥፍርህስ እንዲህ ረዝሞ ለምን አደገ?”  ትለዋለች፡፡
“ፍሬ ለመፈልፈል እንዲረዳኝ ብዬ ያሳደግሁት ነው፡፡ እኔ‘ኮ ምንም ነገር ያለ አንዳች ብልሃት አልሰራም!”
የአንበሳ ሚስት ከፊቷ የሚጎማለለውን ዝንጀሮ ዘወር ዘወር ብላ ተመለከተችና፤
“መቀመጫህስ በምን ምክንያት ተመለጠ?” ብላ ጠየቀችው፡፡
“እሱ ዓለም የሚያውቀው ነገር እኮ ነው፡፡ መቀመጫዬ የተመለጠው ህይወቴ በጦር ሜዳ ውሎና በጀብድ የተሞላ እንደመሆኑ፤ ከፈረስ ፈረስ ስዘል ነው” አለና መለሰላት፡፡
በመጨረሻም፤
“ይገርማል አያ ዝንጀሮ፤ ዛሬ ከቁመትህ ሁሉ በጣም የገረመኝ ደግሞ የጎፈርህ መንዠርገግ ነው፡፡ የአንበሳን ጎፈር መሰለኮ”
“ይሄማ ጠላትን መከላከያ ነው፡፡ ከሩቅ ግርማ - ሞገሴን እያየ የዱር አውሬው ሁሉ የሚሸሸኝ እኮ በዚህ በጎፈሬዬ ምክንያት ነው!”
አያ ዝንጀሮ እንዲህ እየፎከረ የአንበሳን ሚስት ሲያማልል ሲጎማለል፤ ድንገት አያ አንበሶ ከተፍ አለ፡፡ ከዚያም ጥያቄ ይጠይቀው ጀመር፤
“አያ ዝንጀሮ፤ ምነው ዐይንህ ቀላ?”
ዝንጀሮ ድምፁ ሁሉ ኮሰመነና ልቡ ከዳው፡፡
“ዐይኔ የቀላው በድህነት ምክንያት ነው” አለ፡፡
አንበሳ ቀጠለና፤
“ጥፍርህስ ለምን አደገ?”
“መሬት የምቧጥጥበት ነው ጌታዬ!”
“መቀመጫህን ደሞ ምን መለጠው?”
“ከተራራ ተራራ የምንፏቀቅበት ነው!”
“ፀጉርህንስ ምን እንዲህ አንጨፈረረው?”
“ለብርድ፤ ለብርድ ነው ያሳደግሁት ጌታ አንበሶ!”
አንበሳም ክፉኛ እየተኩራራ፤
“ሂድ ጥፋ ከዚህ! አስኮናኝ!” አለው፡፡
ዝንጀሮ እግሬ አውጪኝ አለ፡፡
አንበሳም ወደ አንበሲት ዞሮ፤
“አንቺም ሁለተኛ ከእንደዚህ ያለ ተልካሻ ቡክን ጋር እየዋልሽ አታዋርጂኝ!” አላት፡፡
***
“እዩኝ እዩኝ ያለች ደብቁኝ ደብቁኝ ትላለች” ነው ነገሩ፡፡ ያልሆነውን ነን ማለትን የመሰለ ክፉ በሽታ የለም፡፡ ለአንዴና ለዛሬ ብቻ ያልሆነውን ነን በማለት ለማጭበርበር እንችል ይሆናል፡፡ ነገ ግን ማንነታችን ይጋለጣል፡፡
 “ጓሣና ድንግል አላንድ ጊዜ አይበቅል” የሚለውን ተረት አለመርሳት ነው፡፡ ለታይታ የምናደርገው ሁሉ የአፍታ ስም ብቻ ነው የሚተርፈን፡፡ በሆይሆይታና በግርግር የምንፈጥረው ማናቸውም ትልቅነት በቀላሉ እንደሚናድ ካብ ነው፡፡ በትህትናና በሥርዓት የተሰራ ነገር ሁሉ ግን ፍሬያማ ይሆናል፡፡
ልባምነት ጽናትና ጥንካሬ ያለው፣ እርጋታ ውስጥ እንጂ ችኩልነት  ውስጥ አይደለም፡፡ ችኩል ጅብ ቀንድ ይነክሳል ይሏልና፡፡
“አደባባይ ሲበዛ የክት ልብስ ይጠፋል” የሚለውን አነጋገር መቼም ቢሆን አለመዘንጋት ነው፡፡ ብዙ ጉራ በመንዛትና አደባባይ በመታየት ውስጥ ብዙ ስህተቶችን እናፈራለን እንጂ ደርዛችን እፍኝ ታህል አትሆንም፡፡
“የማትሰግር በቅሎ ጌጧ ይበዛ” ነውና መመሪያ ብናበዛ፣ ገለፃ ብናዘወትር፣ ያላንዳች አማራጭ አዲስ ሀሳብ፤ ያንኑ ያንኑ ዲስኩር ደጋግመን ብንደሰኩር፣ ራሳችንን ከማድመጥ በቀር ወደፊት አንራመድም፡፡የሀገር ጉዳይ ሁሌም ረዥም መንገድ ነው፡፡ ብዙዎች የሀገር ችግሮች አቋራጭ የላቸውም፡፡ መሳለጫ መንገድም የላቸውም።
 አጫጭር አቋራጮችን ስንፈልግ መቸኮል ይመጣል፡፡ ሥረ-ነገሩን ትተን ላይ ላዩን ብቻ መነካካት ይበዛል፡፡ ሥር የሰደደ፣ “ለዘር ለቀለብ ይበቃል” የሚል ነገር ይጠፋል፡፡ በጭብጥ እህል ጠብ መጫር ይበዛል፡፡ “ስንቃችሁ ግማሽ ቁና፤ ነገራችሁ አህያ እማይችለው” የሚባልበት ወቅት ይሆናል፡፡
“የአዕምሮህ ዛጎሉ ውጪ ፀሐይ የሚሞቅ ከሆነ፣ ከውስጥም ዕንቁው አለመኖሩ ይታወቃል” እንዲሉ፤ ውዱንና ትልቅ ዋጋ ያለውን ቅርስ አለማርከስ ተገቢ ነው፡፡ በምናደርገው ነገር ውስጥ ሁሉ መላ፤ ጥበብና ስልት ካልታከለበት ፍሬያማ አይሆንም፡፡
ስለ ፖለቲካ ሸንጎ የሚያውቁ ፀሐፍት እንዲህ ይመክራሉ፡-
“ስለ ማሸነፍህና ድልህም ቢሆን ብዙ ጥሩምባ ከመንፋት ተቆጠብ፡፡ ስለ ራስህ በምትናገረው ሁሉ ቁጥብና ትህትናን የተላበሰ ሁን፡፡ ብዙ የምትሰራና እድገቱ ሁሉ የኔ ነው የምትል አትሁን፡፡ ማር ሲበዛ ይመራልን አትርሳ፡፡ ለተገቢው ነገር ብቻ ትኩረትን ሳብ፡፡
በተለመደና በአሰልቺ ልሳንና ዲስኩር አትናገር፡፡ ልሳንህ ሁኔታዎችን የሚገዛ መሆን አለበት፡፡ የመጥፎ ዜና ተሸካሚ ላለመሆን መጣር አለብህ፡፡ ከመናገርህ በፊት ሁለት ሶስቴ አስብ ይሏል፡፡
ህዝብን አለመናቅ የጥበብ መጀመሪያ ነው፡፡ ያልተመለሱ ጥያቄዎች የነገ ቂም እርሾ ናቸው፡፡ ለሚሰሩ ሰዎች ምስጋናና ሽልማትን አትንሳ፡፡ የሰዎችን ሽልማትም በግፍ አትውሰድ፡፡ የበታቾችን ማንጓጠጥ የመሪዎች ታላቅ ህፀጽ ነው፡፡ የፈጠራዎች ሁሉ እናት መስተዋት ነው፡፡
ሌሎች እንደሚያዩን አድርጎ ራሳችንን ያሳየናልና፡፡ ራሳችንን የምናይበት መስታወት ከእጃችን መለየት የለብትም፡፡ ስሜቱን የማይቆጣጠር መሪ ለአደጋ የተጋለጠ ነው፡፡ መንፈሱን ከጊዜው ጋር ካላጣጣመም የመምራት መላው ሰንካላ ይሆናል፡፡ ማንኛውም መሪ ነገን የሚያስብ ጭንቅላት ሊኖረው ይገባል፡፡
ራሳችንን ለሌሎች የደስታ ምንጭ ለማድረግ መሞከር ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ወዝና ለዛ ያለው መሆን አለብን፡፡
ዣን ዴ ላብሩዩር የተባለ ፀሀፊ፤ “የፖለቲካ ሸንጎን የሚያውቅ ገጽና መልኩን (gesture) ለመቆጣጠር የሚችል፤ አይኑን መግራት የሚያውቅ ሰው ነው፡፡ ብቁና የማይደፈር፤ ከቶም የማይገሰስ ነው፡፡
መጥፎ ምግባራትን ማሟሸሽ፣ ለጠላቶቹ ፈገግ ማለት፤ ቁጣውን ማለዘብ፣ ስሜቱን መሸፈን፣ የልቡን በልቡ መያዝና አንዳንዴ የማይፈልገውን ከስሜቴም ውጪ ለመናገር መገደድን የሚችል ሰው ነው” ይለናል፡፡ እነዚህን ሁሉ ሳይገነዘብ የሚጓዝ፣ “ሙዙን ስታይ፣ መዘዙንም እይ!” የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር የዘነጋ ነው!


ቋሙ በአፍሪካ የአይቲ ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑ ተጠቁሟል


       በአፍሪካ የአይቲ ማዕከል ለመሆን ራዕይ ሰንቆ በአዲስ መልክ እየተዋቀረና እየተደራጀ መሆኑ የተነገረለት የአይቲ ፓርክ ኮርፖሬሽን፤ ከሁለት ሳምንት በኋላ በይፋ  ሥራ እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡ በአይቲ ፓርኩ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ  የሆነው  የግል  የዳታ ማዕከል አገልግሎት መስጠት መጀመሩም ተጠቁሟል፡፡
ይህ ይፋ የተደረገው ባለፈው ረቡዕ ጠዋት በሸራተን አዲስ ሆቴል፣ “የዳታ ማዕከል አገልግሎት ሥነምህዳር ዕድሎችን ለፋይናንስ ዘርፉና ለቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪው ማመቻቸት” በሚል ርዕስ፣ ለግማሽ ቀን በተካሄደ ጉባኤ ላይ ሲሆን፤ ጉባኤውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የአይቲ ፓርክ ኮርፖሬሽንና የዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል  በትብብር እንዳዘጋጁት ታውቋል፡፡
የአይቲ ፓርክ ኮርፖሬሽኑን  የሚያስተዳድረው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር በለጠ ሞላ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር እውን በማድረግ ረገድ አይቲ ፓርኩ ጉልህ ሚና የሚጫወት ይሆናል፡፡ ከዚህ አንጻር ጉባኤው ወቅታዊና ተገቢ መሆኑን ሚኒስትሩ አስምረውበታል፡፡
የአይቲ ፓርክ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሔኖክ አህመድ በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ፣ የኮርፖሬሽኑ ትልቁ ዓላማው ቢዝነስ መሥራት የሚያስችል ሥነምህዳር መፍጠር መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም ሁሉም በጋራ የሚጠቀምበት ሪሶርስ በአንድ ቦታ ያቀርባል ብለዋል፡፡
 ራዕያችን የአፍሪካ የአይቲ ማዕከል መሆን ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ይህን ለማሳካትም  የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማምጣትና አቅምን በማሳደግ ዓለማቀፍ ተወዳዳሪነትን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
በዛሬው ጉባኤ ላይ  በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የግል የዳታ ማዕከል፣ በአይቲ ፓርክ ገንብቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የጠቆመው ዊንጉ አፍሪካ የዳታ ማዕከል ኩባንያ፤ በምሥራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊላንድና ታንዛንያን  ጨምሮ በአራት አገራት በዘርፉ አስተማማኝ አገልግሎት እየሰጠ  የሚገኝ ስመ-ጥር ኩባንያ ነው ተብሏል፡፡   
ኩባንያቸው በቀጣናው ተጠቃሽ  የዳታ ማዕከል አገልግሎት አቅራቢ መሆኑን የገለጹት የዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል  ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ተሾመ፤ በኢትዮጵያም ዓለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አስተማማኝ የዳታ ማዕከል መገንባቱን ጠቁመው፤ በዋናነት  የፋይናንስ ዘርፉና የቴክኖሎጂ ተቋማት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡ዊንጉ አፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ሥራ ከጀመረ 18 ወራት ማስቆጠሩን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ የዚህ ጉባኤ አንዱ ዓላማ እነዚህ የፋይናንስና ቴክኖሎጂ ተቋማት ከፍተኛ ወጪ አውጥተው፣ የየራሳቸውን የዳታ ማዕከል ከመገንባት ይልቅ በኛ ማዕከል ቢጠቀሙ፣ የበለጠ እንደሚያዋጣቸው መረጃና ግንዛቤ ለመስጠት ነው ብለዋል፡፡ ጉባኤው አጋርነትና ትብብር የመፍጠሪያ መድረክ እንደሚሆንም ጨምረው አመልክተዋል፡፡
የዳታ ማዕከሉን ከሚመሩት ውስጥ 90 በመቶው ኢትዮጵያውያን መሆናቸው የገለጹት የኩባንያው አመራሮች፤ ማዕከሉ ለወጣት ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጂ ኢንጂነሮች ትልቅ የሥራ ዕድል መፍጠሩን አውስተዋል፡፡የዘርፉ ዓለማቀፍ ተዋናዮች በአጋርነት አብረውን እንዲሰሩ መሳብ ችለናል ያሉት አመራሮቹ፤ የመንግሥት ደንብና መመሪያዎች ወጥተው እንደተጠናቀቁ እኒህ ተዋናዮች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ገልጸዋል፡፡ ማይክሮሶፍት፣ ቲክቶክና ሜታ (የቀድሞው ፌስቡክ) የመሳሰሉ ግዙፍ ዓለማቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ወደዚህ አገር እንዲመጡም እየሰራን ነው ብለዋል - የዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል ኩባንያ  አመራሮች፡፡ የዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል፣ በ50 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መገንባቱ  ይታወቃል፡፡በዚህ ለግማሽ ቀን በሸራተን አዲስ በተካሄደው ጉባኤ ላይ፣ የአይቲ ኢንዱስትሪው መሪዎች፣ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የፋይናንስ ተቋማት አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡


 በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኩል በህጋዊ ሽፋን ያለ በቂ ቀረጥ እየገባ ያለ  ኮንትሮባንድ ምርት መበራከቱ በአገር ውስጥ አምራቾች እና ህጋዊ ነጋዴዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ነው ተባለ፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የድሬዳዋ ቅርንጫፍ በኩል ያለበቂ ቀረጥ ከፍተኛ የሆነ ምርት በፍራንኮ ቫሉታ እየገባ ነው የሚሉት አምራቾች እና ነጋዴዎች ይህ ሁኔታ በስራቸው ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረና ከስራቸው እያፈናቀለን  ነው ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ  ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ተደጋጋሚ አቤቱታ አሰምተናል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲባባስ እንጂ ምንም የመርገብ ምልክት አልታየበትም ብለዋል፡፡
እንደመረጃ ምንጮች በተለይ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ የግንባታ እቃዎች እና መሰል ሌሎች ሸቀጦች መዳረሻቸውን መሃል አገር አድርገው በድሬዳዋ ጉምሩክ በሚወጣ ዲክላራሲዎን ምንም በሚባል ቀረጥ እየገቡ በገበያ ውስጥም ከፍተኛ ጫና ፈጥረዋል ሲሉ አክለዋል፡፡
ይህ ሁኔታ የአገር ውስጥ አምራች እና ህጋዊ ምርት አስገቢዎችን ብቻ ሳይሆን አገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን በቢሊዎን ብሮች የሚቆጠር የመንግስት የቀረጥ ገቢም እንድታጣ ምክንያት ሆኗል ሲሉ ነው ያከሉት፡፡
በማሳያነት የቆርቆሮ እና አርማታ ብረት ህገወጥ እንቅስቃሴን የሚጠቅሱት ቅሬታ አቅራቢዎች የጉምሩክ ኮሚሽን ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ መሰረታዊ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች ማህበር አመራሮች ጋር ስለችግሩ መምከሩን መግለጹ የችግሩን መኖር አመላካች ነው ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን ኮሚሽኑ ስለጉዳዩ መወያየቱን ቢገልፅ የችግሩን መኖር በይፋ አላመነም ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎች በጥቅሉ ያሉ ችግሮችን እፈታለው ብሎ መግለጹ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን በማህበራዊ ገጹ ስለውይይቱ ባጋራው መረጃ የኢትዮጵያ መሰረታዊ ብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ  ኢንዱስትሪዎች ማህበር ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ፣ ዘርፉ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘትና ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ እያበረከተ የሚገኘው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ማለታቸውን ጠቅሶ ከጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮች ጋር የተደረገው ውይይትም እየገጠሙ የሚገኙ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዝ ተናግረዋል ሲል አክሏል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙሌ አብዲሳ በበኩላቸው የሐገር ውስጥ የብረት አምራቾች የሚያነሱትን ጥያቄ ለመመለስ ኮሚሽኑ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡
እንደ ቅሬታ አቅራቢዎች ገለፃ ከፍተኛ የሆነ የብረት ምርት በፍራንኮ ቫሉታ እየገባ መሆኑን ጠቅሰው ይህ እጅግ አነስተኛ ቀረጥ እየተከፈለበት የሚገባ ምርት ገበያውንም በማጥለቅለቅ የአገር ውስጥ አምራቾችን በእጅጉ እየጎዳና አንዳንዶቹም ስራ ለማቆም እንዲገደዱ እያደረገ ነው ተብሏል፡፡
አዲስ አድማስም የተለያዩ የጉምሩክ ሰነዶችን ማየት የቻለ ሲሆን፡፡ ሰነዶቹ  የተለያዩ ግለሰቦች የተለያየ መጠን ያለው ብረት ከመደበኛው ማስቀረጫ መጠን እጅጉ ያነሰ ቀረጥ ተከፍሎባቸው የብረት ምርቱ እንደገባ ያሳያል፡፡
እስከ 300 ሺ ቶን ብረት በአንድ የጉምሩክ ሰነድ በአንድ ግለሰብ እንዲገባ መፈቀዱን የጠቀሱት የመረጃ ምንጮች፡፡ በተመሳሳይ 120 ሺ ቶን፣ 150 ቶን በሌላ ግለሰብ እንዱም ሌሎች በርካታ የብረት ጭነቶች በተለያዩ ግለሰቦች ስም በድሬዳዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ በኩል እንዲገቡ ይሁንታ ያገኙበት ሰነዶችምን በመረጃነት ቀርበዋል ።
ባለፉት ጥቂት ወራት የወጡት የጉምሩክ ሰነዶች እንደሚያሳዩት ግለሰቦቹ የከፈሉት የጉምሩክ ቀረጥ መጠንም በኪሎ ግራም ከ92 ሳንቲም፣ 74 ሳንቲም እና 50 ሳንቲም ብቻ መሆኑን የተረዳን ሲሆን፡፡በአንጻሩ በተመሳሳይ ወቅት በህጋዊ መልኩ የገባ ብረት በኪሎ ግራም 35 ብር አካባቢ እንደተከፈለባቸው  ያገኘናቸው የጉምሩክ ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ በመሆኑም በህጋዊ የጉምሩክ ሰነድ እጅግ ባነሰ የቀረጥ መጠን እየገቡ የሚገኙት ብረቶች የሁለት አስገቢዎች ብቻ ተሰልቶ እንኳን ለአገሪቱ መግባት የነበረበትን ከ 14 ቢሊየን ብር በላይ ያሳጣ ነው ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎች ያብራራሉ፡፡በጉዳዩ ከትናንት በስቲያ  መግለጫ የሰጠው የመሰረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ  ኢንዱ ስትሪዎች ማህበር ልዩ ልዩ የማጭበርበሪያ ዘዴ እና ህጋዊ ሽፋን በመጠቀም እየገባ የሚገኝ የተለያየ የብረት ምርት በአምራች ኢንደስትሪው ህልውና ላይ አደጋ ጋርጧል ሲል አስታውቋል፡፡
የማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ በመግለጫው እንደተናገሩት 76 የሚሆኑ የማህበሩ አባላት አርማት ብረት (Reienforcment bar)፥ ጋልቫናይዝድ ቆርቆሮ (Galvanized sheet)፥ ቱቦላሬና የበርና የመስኮት ዘንጎች( Tubular sections)፥ እንዲሁም ልዩ ልዩ የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ምርት ውጤቶች ለመሰረተልማት የጀርባ አጥንት የሆኑ የኮንስትራክሽን ግብአቶችን እንደሚያስመጡ ገልጸዋል። አያይዘውም በአገራችን የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የብረት ማምረት አቅም  10 ሚሊዮን ቶን በአመት መድረሱንና  በአንጻሩ ፍላጎት ደግሞ እስከ 2 ሚሊዮን ቶን በአመት እንደሚሆን ይገመታል ብለዋል።
ይህም ሆኖ ያለቀላቸው ምርቶች ከውጭ አገር በህጋዊ መንገድና ስርአትን ባልተከተል መንገድ የሚገቡ በመሆኑ በገበያው ላይ ኢ-ፍትሃዊ የንግድ ውድድር በመፍጠር ኢንዱስትሪዎች ላይ የህልውና አደጋ  እንዲጋረጥባቸው እያደረጉ ይገኛል ሲሉ ነው ያከሉት።
እነዚህን ምርቶች የሚያመርቱ የአገር ውስጥ አምራቾችን ከገበያ ውጭ ሊያደርጉ የሚችሉ የኮንትሮባንድና ሌሎች ህግን ሽፋን አድርገው የሚፈፀሙ ህገ ወጥና ምንጫቸው ያልታወቁ ምርቶች ከማምረቻ ዋጋ በታች በሆነ ዋጋ የሚሸጡና ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች ገበያውን እየተቆጣጠሩት በመምጣታቸው በተለያዩ መድረኮች ድምፃችንን በማሰማትና ለሚመለከታቸው ሁሉ አቤቱታችንን በደብዳቤ ጭምር እያሳወቅን ቆይተናል ያሉት የማህበሩ ዋና ስራ አሰስኪያጅ።
በአሁኑ ወቅት ለቆርቆሮ ለቱቦላሬ ምርት የሚያገለግሉ የጥቅል ጥቁር ብረቶችና የአርማታ ብረት ምርቶች በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት  በስፋት እየታየ እንደሚገኝ መረጃዎች እየደረሱን ይገኛሉ ሲሉ ነው ያከሉት።
ማህበራቸው የዘርፉን አጠቃላይ ሁኔታ የመቃኘትና የመከታተል ኃላፊነቱን በመወጣት ሂደት ላይ ሳለ በቀርቡ  ለማመን የሚያስቸግሩ መረጃዎች እየደረሱት መሆኑን አቶ ሰለሞን ጠቅሰው፤  እነዚህ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በቢሊዮኖች የመንግስትን ገቢ ሊያስቀሩ የሚችሉና የአገር ውስጥ አምራቾችን ሙሉ ለሙሉ ሊያዘጉ የሚችሉ ችግሮች ሆነው አግኝተናቸዋል ብለዋል። በመሆኑም በዚህ መንገድ ፈፅሞ ሊታመን በማይችልና በየትኛውም ዓለም ሊኖር በማይችል ዋጋ የብረታ ብረት ምርቶች እንደተገዙ ተደርጎ የጉምሩክ ቀረጥ ለማስፈፀም ማቅረብ ምን ያህል የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚጎዳ የሚታወቅ ሲሆን በተለይ ደግሞ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ አፍስሰው በማምረት ተግባር ላይ የተሰማሩትን የአገረ ውስጥ አንዱስትሪዎች አሽመድምዶ ከገበያ ውጭ ሊያደርጋቸው የሚችል ድርጊት እንደሚሆን ለማንም ግልፅ ነው ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ገልጸዋል።ኢትዮጵያ ከሜዳዋ ውጪ ማሊን 2ለ0 አሸነፈች

የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ኢትዮጵያ ከሜዳዋ ውጪ ማሊን 2ለ0 አሸንፋለች።

የማሸነፊያ ጎሎቹንም ንግስት በቀለ በ57ኛው፣ እሙሽ ዳንኤል በ68ኛው ደቂቃ ለኢትዮጵያ አስቆጥረዋል።

የመልሱ ጨዋታ እሁድ ህዳር 9 በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ይደረጋል።

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Page 5 of 677