Administrator

Administrator

 “የወጣው መስፈርት አንድን ግለሰብ ታሳቢ ያደረገ ነው”
       “በ4 ወር እንኳን አንድ ድርጅት በምስራቅ አፍሪካ ያሉም ቢተባበሩ ሥራው አያልቅም”

   የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ጥር 1 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሦስት ሳይቶች የሚገኙ 40/60 ቤቶችን የአሉሙኒየም በርና መስኮት ከነመስታወቱና ከነሙሉ ገጠማ ስራው እንዲሰራለት ያወጣው የ1 ቢሊዮን ብር ጨረታ ሠነድ ቅሬታ አስነስቷል፡፡
በጨረታው ሠነድ ላይ የወጣው መስፈርት ለአንድ ድርጅት የወገነ፣ የወቅቱን የምንዛሬ እጥረት ያላገናዘበና በአጠቃላይ ሌሎች ተፎካካሪ ድርጅቶችን ከጨዋታ ውጭ የሚያደርግ ነው ሲሉ  በአልሙኒየም አስመጭነትና ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ቅሬታቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ለአንድ ግለሰብ እንዲመች ሆኖ የተሰናዳው የጨረታ ሠነድ እንኳን በ4 ወር በ4 ዓመት በአንድ ድርጅት ተሰርቶ  ሊያልቅ ቀርቶ በምስራቅ አፍሪካ ያሉ በአልሙኒየም ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ቢተባበሩ እንኳን ሥራው እንደማያልቅ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ኢንተርፕራይዙ ባወጣው የጨረታ ሠነድ ተጫራች ድርጅቶች የአልሙኒየም ክምችት (ስቶክ) እንዲኖራቸውና ከኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢዎች የተሰጠ የብቃት ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ መጠየቁን የገለፁት ድርጅቶቹ ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ድርጅቶች ቶሎ ቶሎ እቃውን እያስገቡ ማከማቸት እንደማይችሉ፣ አንድ ዕቃ ታዝዞ እስኪገባ የሚፈጀውን ጊዜ ግምት ውስጥ ሳያስገቡ ሠነዱን በዚህ መልኩ ማዘጋጀታቸው አንድን ድርጅት ለመጥቀም ሆን ብሎ የተሰራ ሴራ ነው ሲሉ ያማርራሉ፡፡
ከደረጃ መዳቢዎች የተሰጠ ሠርተፍኬት አቅርቡ መባሉን በተመለከተም፤ “እኛ እቃውን ከውጭ የምናስመጣ እንደመሆናችን ከኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢዎች የሚሰጠን ሠርተፍኬት እንደሌለ ይታወቃል” ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ከውጭ አገር የሚሰጥ ተመጣጣኝ ሠርተፍኬት እንዲያቀርቡ አለመጠየቃቸውም ሆን ተብሎ ተፎካካሪዎችን ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ የተሰራ በመሆኑ ሠነዱን ቢገዙም በጨረታው እንደማይሳተፉ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
የጨረታው ሠነድ አንድ ድርጅትን ለመጥቀም ታስቦ ለመውጣቱ ምን ማረጋገጫ አላችሁ በሚል ከአዲስ አድማስ ለተነሳው ጥያቄ፣ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሲመልሱ፣  ታሳቢ የተደረገው ድርጅት ከውጭ በሚመጣ አልሙኒየም ተረፈ ምርት ሪሳይክል እያደረገ የሚያመርት በመሆኑ ክምችትም የኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢዎች ሠርተፍኬትም እንዳለው ይታወቃል በአጠቃላይ የታዘዘው የአልሙኒየም አይነትና ቀለም ሳይቀር ለዚሁ ድርጅት የታሰበ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደምም ከአምስት ዓመታት በፊት በክራውንና በሰንጋ ተራ ለተገነቡ ቤቶች ተመሳሳይ የ1 ቢሊዮን ብር ጨረታ ወጥቶ ይሄው ድርጅት ማሸነፉንና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያላጠናቀቀው ሥራ እንደነበር ገልፀው፤ ጭራሽ እነዚህን ቤቶች በአራት ወር (በ120 ቀናት) አንድ ድርጅት በጥራትና በፍጥነት ያጠናቅቃል ማለት ዘበት ነው ብለዋል፡፡
የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ በአራት ወር አልሙኒየም በሮች ከነመስታወታቸው ተገጥመው እንዲጠናቀቁለት ጨረታ ያወጣባቸው ሦስት ሳይቶች ሲሆኑ፤ እነዚህም ሳይት አንድ ቦሌ ቡልቡላ የሚገኝ ሲሆን፤ በዚህ ሳይት 15 ባለ 15 ወለል (G+15)  ቤቶች፣ በሳይት ሁለት ቦሌ በሻሌ 22 ባለ 15 (G+15)፣  15 ባለ 13 ወለል (G+13)፣ 21 ባለ 9 ወለል (G+9) ቤቶች፣ በሳይት ሦስት ደግሞ ቦሌ አያት፡- 16 ባለ 15 ወለል (G+15)፣   34 ባለ 13 ወለል (G+13)፣ 10 ባለ 8 ወለል (G+8) ቤቶች ሲሆኑ እነዚህን ብሎኮች በ120 ቀናት የአልሙኒየም በር ከነመስታወቱ ለመግጠም አልሙኒየሙ በካሬ ተባዝቶ፣ ለ120 ቀናት ሲካፈል ድርጅቱ በቀን 3637 ካሬ ሜትር አልሙኒየም መስራት እንዳለበት የገለፁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ይህ በህልምም በእውንም የማይታሰብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ አንድ ጠንካራ የሚባል ድርጅት በቀን ከ30 ካ.ሜ በላይ አልሙኒየም ቆርጦ አስተካክሎ፣ መስታወት ገጥሞና ሠርቶ ማጠናቀቅ እንደማይችል የጠቆሙት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ይሄ በቤት ችግር እየተሰቃየ መቶ ፐርሰንት ከፍሎ በጉጉት ለሚጠብቀው ህዝብ ተጨማሪ መዘግየትን እንደሚፈጥር ገልፀው፤ ኢንተርፕራይዙ እነዚህን ሕገ-ወጥ አሰራሮች በጥሞና ተመልክቶ፣ የጨረታ ሠነዱን እንዲያስተካክል ጠይቀዋል፡፡ ምላሽ የማይሰጣቸው ከሆነም መብታቸውን በህግ እንደሚያስከብሩ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልፀዋል፡፡  
የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ኃላፊዎች በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡን ላለፉት ሁለት ሳምንታት በተደጋጋሚ ቢሮአቸው ብንመላለስም ኃላፊነት ወስዶ ምላሽ የሚሰጥ ባለመገኘቱ የኢንተርፕራይዙን ሀሳብ ማካተት አልቻልንም፡፡

በጦርነትና የግጭት ቀጠናዎች ውስጥ አደገኛና አስቸጋሪ ህይወት እየገፉ የሚገኙ የአለማችን ህጻናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ከ357 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ሴቭ ዘ ችልድረን ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዓለማቀፍ ሪፖርት ማስታወቁ ተዘግቧል፡፡
በጦርነትና በግጭት ቀጠናዎች ውስጥ ከሚገኙት የአለማችን ህጻናት፣ ግማሽ ያህሉ ወይም 165 ሚሊዮን የሚደርሱት ከፍተኛ ግጭት በሚከሰቱባቸው አካባቢዎች ውስጥ እንደሚኖሩ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ህጻናት ለዚህ ችግር በመጋለጥ ረገድ ቀዳሚነቱን እንደሚይዙና አፍሪካውያን ህጻናት እንደሚከተሉ በመግለጽ፣ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ከሚኖሩ አምስት ህጻናት፣ ሁለቱ ግጭት ወይም ጦርነት በሚከናወንበት አካባቢ በ50 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ውስጥ እንደሚኖሩ አመልክቷል፡፡
በርካታ ህጻናት በጦርነትና በግጭት ቀጠናዎች ውስጥ እንደሚገኙባቸውና ለህጻናት እጅግ አደገኛ ናቸው ተብለው በሪፖርቱ ከተጠቀሱት የአለማችን አገራት መካከል ሶሪያ ቀዳሚነቱን ስትይዝ፣ አፍጋኒስታንና ሶማሊያ በተከታታይነት ተቀምጠዋል፡፡
በህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የማቁሰል ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ እንደመጡ የዘገበው ዘ ኢንዴፔንደንት፤ የተባበሩት መንግስታት በማስረጃ አስደግፎ የሚመዘግባቸው መሰል ጥቃቶች ቁጥር ባለፉት ሰባት አመታት ውስጥ በ3 እጥፍ ማደጉንም አስታውሷል፡፡
በግጭቶችና በጦርነቶች ሳቢያ ከመኖሪያ አካባቢያቸው እየተፈናቀሉ ለተለያዩ ስቃዮችና እንግልቶች የሚዳረጉ የአለማችን ህጻናት ቁጥር እያሻቀበ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ ከ65 ሚሊዮን በላይ የዓለማችን ህጻናት ምንም አይነት ቋሚ የመኖሪያ ቤት እንደሌላቸው አመልክቷል፡፡

   የአገሪቱ መሪ፤ ሚኒስትሮች ከባልደረቦቻቸው ጋር ፍቅር እንዳይጀምሩ አስጠንቅቀዋል

   ከሰሞኑ ይፋ ከተደረገባቸው የወሲብ ቅሌት መረጃ ጋር በተያያዘ፣ አገራዊ የመነጋገሪያ አጀንዳ የሆኑት የአውስትራሊያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ባርናቢ ጆይስ፤ የፓርቲ መሪነትና የሚኒስትርነት ስልጣናቸውን ይለቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የተዘገበ ሲሆን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማልኮም ተርንቡልም፤ ሚኒስትሮች ተመሳሳይ ድርጊት ፈጽመው ከተገኙ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ማስጠንቀቃቸው ተዘግቧል፡፡
የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ባርናቢ ጆይስ፣ በቅርቡ የ24 አመት ትዳራቸውን በማፍረስ፣ የስራ ባልደረባቸው ከሆነች አንዲት ሴት ጋር በፈጠሩት የድብቅ የፍቅር ግንኙነት፣ ሴትየዋን ማስረገዛቸውን የሚያጋልጥ የወሲብ ቅሌት መረጃ ከሰሞኑ ይፋ መደረጉንና ጉዳዩ ትልቅ አገራዊ አጀንዳ መሆኑን የዘገበው ዘ ቴሌግራፍ፤ ይህን ተከትሎም የአገሪቱ ፓርላማ ከትናንት በስቲያ ባደረገው ስብሰባ፣ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ተከስተዋል ያላቸውን ሌሎች ተጨማሪ የሙስና ድርጊቶችን በመመርመር፣ ሚኒስትሩ ከስነምግባር ውጭ የሆነና ክብርን የሚያጎድፍ ጸያፍ ተግባር በመፈጸማቸው፣ በፈቃዳቸው ስራቸውን እንዲለቅቁ ወይም እንዲባረሩ የሚጠይቀውን የውሳኔ ሃሳብ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን አመልክቷል፡፡
“በምክትል ሚኒስትሩ ድርጊት እጅግ አዝኛለሁ፤ ይሄም ሆኖ ግን ከአሁን በኋላ ባለትዳርም ሆነ ወንደላጤ ማንኛውም ሚኒስትር፣ የስራ ባልደረባው ከሆነች ሴት ጋር በፍጹም የፍቅር ግንኙነት መመስረትም ሆነ አንሶላ መጋፈፍ አይችልም” ሲሉ በይፋ ያስጠነቀቁት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማልኮም ተርንቡል፤ ድርጊቱ በቀጣይም እንደ አንድ ከባድ የስልጣን ብልግና ወይም የሙስና ወንጀል ተወስዶ እንደሚያስቀጣም አስታውቀዋል፡፡
ምንም እንኳን በአገሪቱ የሚኒስትሮች ስነምግባር ደንብ ውስጥ ከስራ ባልደረባቸው ጋር የፍቅር ግንኙነት በሚጀምሩም ሆነ በሚያማግጡ ሚኒስትሮች ዙሪያ የሚያትት ምንም አይነት አንቀጽ ባይኖርም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ከአሁን በኋላ መሰል ድርጊት የፈጸመ ሚኒስትር፤ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጠብቀው በማስጠንቀቅ፣ ድርጊቱን በግልጽ የሚያወግዙና ተገቢ ቅጣት የሚጥሉ ህጎችና መመሪያዎች በቀጣይ ወጥተው፣ ተግባራዊ እንደሚደረጉም ተናግረዋል፡፡
24 አመታትን በትዳር አብረዋት ከዘለቋት ባለቤታቸው፣ አራት ሴት ልጆችን ያፈሩት የ50 አመቱ የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፤ የስራ ባልደረባቸው ከሆነች ሌላ ሴት ጋር በድብቅ እፍ ክንፍ ማለታቸውና ማስረገዛቸው ባለፈው ሳምንት ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ ጉዳዩ የአገሪቱን ፖለቲካ ፓርቲዎችም ጨምሮ በርካታ ዜጎችን እያነጋገረ እንደሚገኝም ዘገባው አስታውሷል፡፡  

 ለወራት በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውና ብዙ ሲወራለት የቆየው አዲሱ የሳምሰንግ ስማርት ፎን ምርት ጋላክሲ ኤስ9 በመጪው ሳምንት በባርሴሎና በሚካሄደው አለማቀፍ የሞባይል ትርዒት ላይ በይፋ ተመርቆ በገበያ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አዲሱ ጋላክሲ ኤስ9 የመሸጫ ዋጋው 739 ፓውንድ ያህል እንደሚሆን የዘገበው ቴክራዳር ድረገጽ፣ ሞባይሉ 6 ጊጋ ባይት ራም እንዳለውና 64 ጊጋ ባይት መረጃ መያዝ እንደሚችል እንዲሁም ባለ 12 ሜጋፒክስል ሁለት ካሜራዎች እንደተገጠሙለት አመልክቷል፡፡
ውሃንና ቆሻሻን የመከላከል አቅሙ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ የተነገረለት ኤስ9 ያለ ገመድ ቻርጅ መደረግ የሚችል እንደሆነም ዘገባው አስረድቷል፡፡
ኩባንያው ሞባይሉ በይፋ በተመረቀ በቀናት እድሜ ውስጥ ከደንበኞች የግዢ ትዕዛዝ መቀበል እንደሚጀምርና በቀጣዩ ወር አጋማሽ ላይ ምረቱን ለገዢዎች የማድረስ ስራ ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው አመልክቷል፡፡

  በአፍጋኒስታን ባለፈው የፈረንጆች አመት 2017 በተካሄዱ ብጥብጦች፣ ከ10 ሺህ በላይ በሚሆኑ የአገሪቱ ንጹሃን ዜጎች ላይ የግድያ ወይም የመቁሰል አደጋ መድረሱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በአፍጋኒስታን በአመቱ 3 ሺህ 438 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን የጠቆመው ተመድ፤7 ሺህ 15 ያህል የሚሆኑትም ለመቁሰል አደጋ መዳረጋቸውን ያመለከተ ሲሆን በዜጎች ላይ ከተፈጸሙት ግድያዎች ወይም የማቁሰል ድርጊቶች መካከል ከስድሳ በመቶ በላይ የሚሆኑት የተፈጸሙት በጸረ-መንግስት ሃይሎች በተደረጉ የቦንብ ጥቃቶች መሆኑንም አመልክቷል፡፡ በአመቱ በአፍጋኒስታን ንጹሃን ዜጎች ላይ ከተፈጸሙት ጥቃቶች መካከል ታሊባን 42 በመቶ፣ አይሲስ 10 በመቶ ድርሻ እንደነበራቸው ያስታወሰው መግለጫው፤ በአሜሪካ የአየር ድብደባዎች ለሞትና ለመቁሰል አደጋ የሚጋለጡ ዜጎች ቁጥርም እያደገ ነው ብሏል፡፡
በ2017 የፈረንጆች አመት አፍጋኒስታናውያን ህጻናትና ሴቶች በከፍተኛ ሁኔታ የጥቃት ሰለባ መሆናቸውን የጠቆመው መግለጫው፤በአመቱ 359 ሴቶች መገደላቸውንና 865 ሴቶች ደግሞ መቁሰላቸውን፤ 861 ህጻናት መገደላቸውንና 2 ሺህ 318 መቁሰላቸውን አስታውቋል፡፡

የደን ሽፋንን በተፋጠነ የዛፍ ተከላ በማሳደግ፣ የአየር ብክለትን ለመዋጋት ቆርጦ የተነሳው የቻይና መንግስት፤ ከስራ ገበታቸው ተሰናብተው የነበሩ 60 ሺህ ወታደሮችን መልሶ በመቅጠር በችግኝ ተከላ ስራ ላይ ሊያሰማራ ማቀዱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ከዚህ በፊት በመደበኛ ውትድርና ሙያ ላይ ያገለግሉ የነበሩና ከስራ ገበታቸው የተሰናበቱት እነዚህ ወታደሮች፤ የቻይና መንግስት በአገሪቱ የተለያዩ ግዛቶች ሊያከናውናቸው ባቀዳቸው ሰፋፊ የደን ልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ በችግን ተከላ ስራ ላይ እንደሚሰማሩ የጠቆመው ዘገባው፤በተለይም የኢንዱስትሪ ጭሶችን በብዛት በማውጣት ከፍተኛ የአየር ብክለትን በሚያስከትሉ አካባቢዎች ብዛት ያላቸው ዛፎችን ለመትከል መታቀዱን አመልክቷል።
ቻይና በዘንድሮው የፈረንጆች አመት ብቻ 84 ስኩየር ኪሎ ሜትር በሚሸፍን ቦታ ላይ በርካታ ዛፎችን የመትከል እቅድ ይዛ በስፋት እየተንቀሳቀሰች እንደምትገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ በደን ይሸፈናል ተብሎ የታቀደው ቦታ ስፋት ከአየርላንድ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት ጋር ተመጣጣኝ መሆኑን አስረድቷል።
 አገሪቱ የደን ሽፋኗን አሁን ከሚገኝበት 21 በመቶ፣ በመጪዎቹ ሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ ወደ 23 በመቶ ከፍ ለማድረግ ማቀዷንና የደን ሽፋኑ እ.ኤ.አ እስከ 2035 ድረስ 26 በመቶ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክቷል፡፡

  በጀርመኑ የቴክኒክ ተራድኦ ድርጅት (ጂአይዜድ) እና ሲኤንኤፍኤ በተሰኙ ዓለም አቀፍ ተቋማት እገዛ በአርሲ ዞን ሁሩታና ሳጉሬ ወረዳዎች፣ከ60 ሺ ዩሮ በላይ በሆነ ወጪ፣ ዘመናዊ የግብርና ግብአቶች ማስፋፊያ ማዕከላት ተገነቡ፡፡
ሰሞኑን የተመረቁት እነዚህ የግብርና ማዕከላት፣ ዘመናዊና ጥራት ያላቸው የሰብል ዘሮችን፣ የአረም መከላከያ መድሐኒቶችና የእንስሳት ህክምና ምርቶችን በሰለጠኑ ሠራተኞችና በተመጣጣኝ ዋጋ፣ ለአርሶ አደሮች ያቀርባሉ ተብሏል፡፡
ማዕከላቱን የተራድኦ ድርጅቶችና የአካባቢው ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች በእኩል መዋጮ ያስገነቧቸው ሲሆን ከአገልግሎት ሽያጭ የሚሰበሰበው ገቢም ለወጣቶቹ እንደሚሆን ተነግሯል፡፡ አንድ ማዕከል ለ25 ሺህ ያህል አርሶ አደሮች እንደሚያገለግል የተጠቆመ ሲሆን ማዕከላቱ ግብአቶችን ከማቅረብ ጐን ለጐን፣ለአርሶ አደሮች የምክርና ስልጠና አገልግሎት እንደሚሰጡ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገልጧል፡፡    

 የ“ፊታውራሪ” የሙዚቃ ክሊፕ የሽፋን ፎቶ በ400 ሺህ ብር ተሽጧል

    በቅርቡ በገበያ ላይ የዋለው “እስኪ ልየው” የተሰኘው የድምጻዊት ሄለን በርሄ የሙዚቃ አልበም ባለፈው ሳምንት አርብ ምሽት በማማስ ኪችን በተከናወነ ልዩ ፕሮግራም የተመረቀ ሲሆን፣ በእለቱ በይፋ ተመርቆ ለእይታ የበቃውና በአልበሙ ውስጥ ከተካተቱት 14 ሙዚቃዎች አንዱ የሆነው የ“ፊታውራሪ” የሙዚቃ ክሊፕ ፎቶ ግራፍ ለጨረታ ቀርቦ በ400 ሺህ ብር ተሽጧል፡፡
ኡቡንቱ አርት ማኔጅመንት እና ንጉስ ኢንተርቴንመንት በጋራ ያዘጋጁትና የካቲት 2 ቀን 2010 ዓ.ም ምሽት ወሎ ሰፈር በሚገኘው ማማስ ኪችን በተከናወነው የአልበሙ የምረቃ ፕሮግራም ላይ በርካታ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የድምጻዊቷ አድናቂዎችና ተጋባዥ እንግዶች የታደሙ ሲሆን፣ ድምጻዊቷ አዳዲስና ቆየት ያሉ ተወዳጅ ሙዚቃዎቿን በአስገራሚ ብቃት በማቀንቀን ታዳሚውን ስታዝናና አምሽታለች፡፡
ድምጻዊት ሄለን በርሄ፣ በአዲሱ አልበም ውስጥ የተካተተውን የኔ ቆንጆ የተሰኘ ተወዳጅ ዜማ ያበረከቱላትን ታዋቂውን የዜማ ደራሲና የማንዶሊን ተጫዋች አቶ አየለ ማሞን ጨምሮ ለአልበሙም ሆነ ለሙዚቃ ክሊፑ ስኬታማነት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን በተደጋጋሚ ስታመሰግን አምሽታለች፡፡
ምነው ሸዋ ኢንተርቴንመንት ፕሮዲዩስ ያደረገውና 350 ሺህ ብር ያህል ወጪ እንደተደረገበት የተነገረለት እንዲሁም ከ50 በላይ ተዋንያን የተሳተፉበት “ፊታውራሪ” የሙዚቃ ክሊፕ በምሽቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ለእይታ በበቃበት ቅጽበት፣ በዩቲዩብ ድረገጽ የተለቀቀ ሲሆን፣ የፕሮግራሙ ታዳሚያን አድናቆታቸውን በሚገርም ሁኔታ ሲገልጹ ተስተውለዋል፤ በዩቲዩብም ብዙ ተመልካቾች እያዩት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የ“ፊታውራሪ” የሙዚቃ ክሊፕ የሽፋን ፎቶ ግራፍ በምሽቱ ለጨረታ የቀረበ ሲሆን፣ የድምጻዊቷ አድናቂዎችና በዝግጅቱ ላይ የታደሙ የሙዚቃ አፍቃሪያን ፎቶግራፉን በእጃቸው ለማስገባት ረጅም ፉክክር ካደረጉ በኋላ፣ በስተመጨረሻም 400 ሺህ ብር ያቀረቡት የማማስ ኪችን ባለቤት ጨረታውን አሸንፈዋል፡፡
በአልበሙ የምረቃ ስነስርዓት ላይ ጸደኒያ ገብረ ማርቆስ፣ ጌትሽ ማሞ፣ ዳግማዊት ጸሃዬና አስገኘው አሽኮ (ዴንዳሾ)ን ጨምሮ ሌሎች ተጋባዥ ድምጻውያን የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ለታዳሚያን አቅርበዋል፡፡

 “የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ ሕያው መሆን አለበት”

     የክራርና የዋሽንት መምህርና የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ መስራች የነበሩት አርቲስት መላኩ ገላው በሰማንያ ዓመት ዕድሜያቸው አሜሪካ ውስጥ አርሊንግተን - ቨርጂንያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አርፈዋል።
አርቲስት መላኩ ገላው በጣልያን የወረራ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 1929ዓ.ም ከአባታቸው ከአቶ ገላው ተክሌና ከእናታቸው ከእማሆይ ትኩነሽ ተሰማ በላስታ ላሊበላ ተወለዱ፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ የተፀነሰው የሙዚቃ መሳሪያ የመጫወት ፍቅር ከልጅነት ባለፈ በ1956 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲና የኦርኬስትራ ኢትዮጵያን በመቀላቀል በክራርና በዋሽንት ተጫዋችነት፣ ከዚያም ከ1959 ዓ.ም ጀምሮ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በሁለቱም ባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች በመምህርነት ከ28 ዓመታት በላይ አገልግለዋል።
በተለይ በኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ከተስፋዬ ለማ፤ ከአሜሪካዊው መሲንቆ ተጫዋች ቻርለስ ሳተን እና ከአርቲስት ጌታ መሳይ አበበ ጋር በመሆን የባህል አምባሰደርነታቸውን በዓለም ለማስመስከር ችለዋል፡፡ በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤትም የባህል የሙዚቃ መሳሪያ መጫወት በማይበረታታበት ጊዜ የራሳቸውን የማስተማር ልምድ በመጠቀም ትምህርቱን መስጠት እንደጀመሩና መሰረት እንደጣሉ ተማሪዎቻቸው ይመሰክራሉ፡፡ ታላላቅ የሚባሉ የሙዚቃ ባለሙያዎችን እንደ ጥላሁን ገሠሠ፤ ብዙነሽ በቀለ፤ ሂሩት በቀለንና ሌሎች አንጋፋ ድምፃውያንን በዋሽንትና በክራር በማጀብ የሙያ ድርሻቸውን የተወጡ ባለሙያ ነበሩ፡፡ ለአርቲስት ጌታ መሳይ አበበም “የሽምብራው ጥርጥር” የሚለውን የሙዚቃ ድርሰት በመስጠትም ይታወቃሉ፡፡ የእጅጋየሁ ሽባባውን የአገው ባህላዊ ሙዚቃንም በልዩ መልክ በማጀብ የዋሽንት ችሎታቸውንም አስመስክረዋል፡፡
ኑሯቸውን በአሜሪካ ካደረጉበት ጊዜ አንስቶ በግላቸው በርካቶችን ክራር በማስተማር የቆዩ ሲሆን በአቶ ተስፋዬ ለማ በተቋቋመው ሙዚየም ውስጥ የባህል ሙዚቃ መሳሪያዎችን በማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ከማበርከታቸውም በተጨማሪ ከቀድሞ የሙዚቃ አጋሮቻቸው ከተስፋዬ ለማ፤ ቻርለስ ሳተን እና ጌታ መሳይ አበበ ጋር በመሆን “ዞሮ ገጠም” የሚል ሙዚቃን በመስራት ለባህል ሙዚቃ ህዳሴ የበኩላቸውን ተወጥተዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 ለባህል የሙዚቃ መሳሪያ ዕድገት ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽዖ የፊደል ዕድሜ ዘመን ተሸላሚ ክብርን አግኝተዋል፡፡ “የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ ሕያው መሆን አለበት” የሚለውን ጽኑ አቋማቸውን ህይወታቸው እስካለፈችበት ጊዜ ድረስ ሌሎችን በማስተማርና በተለይም ሙያውን ለልጆቻቸው በማውረስ ታላቅ ታሪክ የሰሩ የባህል ሙዚቃ አምባሳደር ሆነው አልፈዋል፡፡
አርቲስት መላኩ ገላው ባለትዳርና የ7 ልጆች አባት ሲሆኑ 12 የልጅ ልጆችም አይተዋል፡፡ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 3 ቀን 2010 ዓ.ም በአርሊንግተን ቨርጂኒያ ቤታቸው በ80 ዓመት ዕድሜያቸው ሕይወታቸው አልፏል፡፡ አስክሬናቸውም በመጪው እሁድ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የሚሸኝ ሲሆን ቀብራቸውም የፊታችን ሰኞ የካቲት 12 ቀን 2010ዓ.ም በፈረንሳይ ደብረ ፀሀይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ከቀኑ በ9ሰዓት እንደሚፈጸም ከቤተሰቦቻቸው የተገኘ መረጃ ያስረዳል፡፡

  “አዝማሪና ውሃ ሙላት” በተሰኘው የደራሲ ከበደ ሚካኤል ግጥም ውስጥ የምናቃቸው ዝነኛ መስመሮች ለዛሬ የመረጥናቸው ናቸው፡፡

        አዝማሪና ውሃ ሙላት
        አንድ ቀን አንድ ሰው ሲሄድ በመንገድ
        የወንዝ ውሃ ሞልቶ
                ደፍርሶ ሲወርድ
        እዚያው እወንዙ ዳር
                እያለ ጐርደድ
        አንድ አዝማሪ አገኘ
                ሲዘፍን አምርሮ
        በሚያሳዝን ዜማ
            ድምፁን አሳምሮ፡፡
        “ምነው አቶ አዝማሪ
        ምን ትሠራለህ?”
        ብሎ ቢጠይቀው፤
        “ምን ሁን ትላለህ፣
        አላሻግር ብሎኝ
        የውሃ ሙላት
        እያሞጋገስኩት
        በግጥም ብዛት
        ሆዱን አራርቶልኝ ቢያሻግረኝ ብዬ”
        “አሁን ገና ሞኝ ሆንክ ምነዋ ሰውዬ
        ነገሩስ ባልከፋ
        ውሃውን ማወደስ
        ግን እንደዚህ ፈጥኖ
        በችኮላ ሲፈስ
        ምን ይሰማኝ ብለህ
        ትደክማለህ ከቶ
        ድምፁን እያሽካካ መገስገሱን ትቶ
        እስኪ ተመልከተው ይህ አወራረድ
        ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ”

        ተግሳጽም ለፀባይ ካልሆነው አራሚ
        መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚ!
*   *   *
በተደጋጋሚ ሀገራችን ባለፈችበት የለውጥ ሂደት ውስጥ የተገነዘብነው ዋና ነገር ገዢው “ያቀድኩትን ልተግብርበት እረፉ”፤ ሲል፤ ተገዢው “ኧረ ይሄ ነገር አልተሟላልኝም እያለ ሲያማርር፤ በመሀል ውዱ ጊዜ ማለፉ ነው፡፡ የጠፋው ጊዜ ከሰነበትን በኋላ ተመልሶ መፀፀቻችን ይሆናል፡፡ የተወሳሰበው ችግር መፍትሄ ማግኘት ቀርቶ የባሰ የተወሳሰበ ሆኖ ይገኛል፡፡ የባሰ ምስቅልቅሉ ይወጣል፡፡ መፍትሄ መስጠት ያለባቸው አካላት የውስጥም የውጪም ግፊትና ውጥረት ስላለባቸው፤ ሌሎች ችግሮችን ማስተናገድ አልሆነላቸውም። ቢወተወቱ አያዳምጡም፡፡ “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይነቃም” የሚለው ተረት የበለጠ ይገልፀዋል፡፡ ለማደግም ሆነ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችለው መደማመጥ ነው። ሁሉንም ነገር ዐይኔን ግንባር ያድርገው ብለን አንችለውም፡፡ ካለመደማመጥ በተጨማሪ የሚደረገውንም ሆነ የተደረገውን አላውቅም፤ ማለትና መስማትም ማየትም እምቢ ካልን፣ ጉዟችን የዕውር የድንብር ይሆናል፡፡
ጊዜ እየረፈደ ከመጣ በኋላ ሁኔታውን ለመቀልበስ ብንሞክር ፍሬ-አልባ ሙከራ ይሆናል። ዛሬም ዐይናችንን ከፍተን ቆም ብለን እናስብ፡፡ ውጥረት ውስጥ ከመግባታችን በፊት የውጥረቱን መፈጠሪያ ቧንቧዎች እንዝጋ፡፡ አሁንም ደግመን ደጋግመን እናዳምጥ። ሀገራችን ከእንግዲህ ተጨማሪ ችግር የምትሸከምበት ጫንቃ የላትም፡፡ ካልተጠነቀቅን ሀገርም እንደ ሰው ተሰባሪ ናት፡፡ የ1966ን አብዮት አንርሳ፡፡ ገዢዎች መግዛት ሲያቅታቸው፣ ተገዢዎች አንገዛም ሲሉ፣ ሀገር ለአብዮት የበሰለ ሁኔታ ላይ እንደደረሰች አንዘንጋ፡፡ ሲመሽ ጉሮሮ ለጉሮሮ ከመተናነቅ፣ ፊት ለፊት ተገናኝቶ መነጋገር ነው፤ ወደ መፍትሄው የሚያስጠጋን። እስከ መቼ “ዴሞክራሲያችን ለጋ ስለሆነ ነው” እያልን ምክንያት እንሰማለን? እስከ መቼ “የመልካም አስተዳደር ችግር ነው” እያልን እንዘልቀዋለን? እስከ መቼስ “የፍትህ ሰጪ አካላት የአፈፃፀም ችግር አለ” እያልን እንጓዛለን? የድህነት ችግርስ እስከመቼ ነው ቁልፍ ነው እየተባለ የምንቀጥለው? ከሃያ በላይ ዓመታት ተጉዘን፣ ምንም ለውጥ አለማምጣታችን፣ የሚያሳፍረን ጊዜ አይመጣምን? ዛሬም መብራት ይጠፋል፡፡ ዛሬም ውሃ ይጠፋል፡፡ ዛሬም ኔትዎርክ ይቸግራል፡፡ ዛሬም ኑሮ አዘቅት ውስጥ እየከተተን ነው፡፡ እነዚህ የብሶትና የምሬት ምንጮች እስከ መቼ እንደተጫኑብን ይኖራሉ? እናስብ! ምንጣፉ ከእግራችን ስር ተስቦ እስኪወሰድ አንጠብቅ! “ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም” ከአርባ ዓመት በኋላ መድገም አሳፋሪ ይሆናል፡፡ “ፋታ ስጡኝ”  ለማለትም ጊዜ የለም! የነካነው ሁሉ ወርቅ ይሆናል ብለን እንደ ሚዳስ አስማት (Midas Touch) የምናስብበት ጊዜ አልፏል፡፡
“እስቲ ተመልከተው ይህ አወራረድ
ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ”
የሚለውን ዛሬም ማስተዋል ይበጃል፡፡ መልካም ጊዜ ይመጣ ዘንድ ሁላችንም እንመኛለን!