Administrator

Administrator

ዴሞስቴን የተባለ የግሪክ ፈላስፋ ህዝብ በተሰበሰበበት ንግግር ለማድረግ እየተሳነው ስለተቸገረ፤ የንግግር ልምምድ ለማድረግ ወደ አንድ ወንዝ አጠገብ ይሄዳል፡፡
ወንዙ በከፍተኛ ፍጥነት እየተወረወረ ቋጥኝ ላይ ያርፍና ኃያል ድምፅ ይፈጥራል፡፡ ዴሞስቴን ደግሞ ይህንን ድምፅ ለማሸነፍ እጅግ ነጎድጓዳማ ድምፅ ያወጣል፡፡
ወንዙ በቀጣይ ጩኸቱን ተያይዞታል፡፡ ፈላስፋውም የፉክክር ንግግሩን ያምባርቃል፡፡ ፈላስፋው ይህን ልምምዱን ለተወሰነ ወቅት ካካሄደ በኋላ ወደ ህዝብ መሰብሰቢያው አደባባይ ተመለሰ፡፡ ስብሰባው ተዘጋጀለት፡፡
ወደመናገሪያው መድረክ ወጥቶ፤
“የአቴና ህዝብ ሆይ!” አለና ቀጠለ፤ “ዛሬ ስለአቴና ችግር በሰፊው ልነገራችሁና ላስረዳችሁ ነው ፊታችሁ የቆምኩት!” አለ በጣም ጮክ ብሎ፡፡
ህዝቡ ጆሮ አልሰጥ አለው፡፡ እርስ በርሱ እያወካ፣ ጨርሶ መደማመጥ ጠፋ፡፡ ዴሞስቴን በተቻለው ድምፅ ጮሆ እየተናገረ ነው፡፡ ሰሚ ግን ጠፋ፡፡
በመጨረሻ፤ የሞት ሞቱን ጮሆ፡-
“የአቴና ህዝቦች ሆይ፤
የአንዲት አህያ ታሪክ ልነግራችሁ ነው፤ አሁን …”
ቀስ በቀስ የህዝቡ ጩኸት ቀነሰ፡፡ በመካያውም ፀጥ እርጭ አለ፡፡ ጀመረ ዴሞስቴ፡-
“ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንዲት የምትከራይ አህያ የነበረችው አንድ ሰው ነበረ፡፡
በዚያው ወቅት አንድ ነጋዴ የሚከራይ አህያ ፍለጋ ወደ ባለአህያው መጥቶ፤
“ባለ አህያ?” ይለዋል፡፡
ባለ አህያ - “አቤት፤ ምን ልታዘዝ?”
ተከራይ - “የሚከራይ አህያ ፈልጌ ነበር?”
ባለ አህያ - “ውሰዳታ!”
ተከራይ - “ስንት ነው ሂሳብ?”
ባለ አህያ - “ለስንት ቀን?”
ተከራይ - “ለሶስት ቀን”
ባለ አህያው ዋጋውን ነግሮ, አህያዋን አስረከበውና ተከራይ ቀብድ ከፍሎ፣ አህያዋን ይዞ ሄደ፡፡
አንድ ቀን አልፎ ሁለተኛው ቀን ላይ ባለ አህያው ተከራይ በሄደበት መንገድ ወደ ገበያ ለመሄድ ጉዞ ጀመረ፡፡ ፀሐዩ በጣም ያቃጥላል፡፡ ምንም የጥላ መጠለያ የሌለበት፣ ጭው ያለ ሜዳ ነው፡፡ የአህያዋ ተከራይ አህያዋን አቁሞ፣ ጥላዋን ተጠልሎ ተቀምጧል፡፡
ባለአህያው ቀረብ ብሎ፤
“አስጠጋኝና አብሬህ ጥላው ስር ልቀመጥ” አለው
ተከራዩ - “አይቻልም”
ባለአህያ - “አህያዋኮ የራሴ ናት”
ተከራይ - “ትሁና! ዛሬን ጨምሮ እስከ ሦስት ቀን ድረስ የራሴ ናት”
ባለአህያ - “እንዲያውም፣ አህያዋን እንጂ ጥላዋን አልተከራየኸኝም - ለጥላዋ አስከፍልሃለሁ!”
ተከራይ - “ለሱ ሌላ ውል መፈራረም ይኖርብናል”
በዚህ ሁኔታ ሲጨቃጨቁ ቆዩ … አለና ዴሞስቴን ንግግሩን አቆመው፡፡
ህዝቡ፡-
እባክህ ጨርስልን! የዚህን መጨረሻ ሳናዳምጥ በጭራሽ ወደ ቤታችን አንሄድም!! እያለ አደባባዩን በጠበጠ!
“የአቴና ህዝብ ሆይ!
እጅግ አሳሳቢ የሆነውን የአቴና ችግር ላሳውቃችሁ ስናገር አልሰማ ብላችሁ፣ የአንድ አህያ ተረት መጨረሻ ለማወቅ ጓጉታችሁ ትጮሃላችሁ! ታሳዝናላችሁ! የአህያዋን ተረት መጨረሻ የምነግራችሁ፣ የአገራችሁን አቴናን ጉዳይ ነግሬያችሁ ሳበቃ ነው” ብሎ ለመናገር የፈለገውን ነገር ልባቸው እንደተንጠለጠለ ጨረሰላቸው፡፡
*   *   *
የሚያዳምጥ ህዝብ ማግኘት መታደል ነው፡፡ የሰማውን በልቦናው አሳድሮ ወደተግባር የሚለውጥ ህዝብ ማግኘት ደግሞ የመታደል መታደል ነው፡፡ ይህንን ለማግኘት ተጣጥሮ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ግድ ይላል፡፡ የለውጥ መንገዱ አዳጊ ሂደት እንጂ፤ በዚህ ጊዜ ለውጥ አመጣለሁ ብሎ ቀን ቆርጦ፣ መሳሪያ መርጦ በመቀመጥ የሚሆን አይደለም፡፡ ለውጥን ለማምጣት ለዋጩ ራሱ መለወጥ አለበት፡፡ የለውጡም ዓይነት መወሰን አለበት፡፡ ለውጡ ሥር - ነቀልና የመጨረሻው ዓይነት ከሆነ፣ ትራንስፎርሜሽን ነውና የቁርጡ ቀን ነው፡፡
የሥር - ነቀል ለውጥ ካደረገ፤ ከዚህ ቀደም የነበረው ምንነቱ ወዲያውኑ ተወገደ፣ ሞተ፣ ማለት ነው” ይለናል፤ ፈላስፋው ኤፒኩረስ፡፡
ሉክሩቲየስ የተባለው ሌላው ፈላስፋም፤
“ምንም ዓይነት ለውጥ ይሁን ለውጥ ከመጣ የቀድሞው ተንኮታኮተ፤ ስለዚህም ተደመሰሰ” ይላል፡፡ ይህ ማለት መሰረታዊ ለውጥ ተከስቷል እንደ ማለት ነው፡፡
ዞሮ ዞሮ በሀገራችን በኢትዮጵያ ለውጥ ይመጣ ዘንድ ከልባችን መመኘታችን አግባብነት አለው፡፡ ሁኔታዎች በአንድ ጊዜ ይከሰታሉ የሚል የዋህነት ግን አይኖርብንም፡፡ በየዘርፉ ያሉትን ችግሮች አንድ በአንድ በማየትና በመመርመር መላ ማበጀት ከጅምላ ዘመቻ ወይም ከሁሉን ባንዴ ርብርብ ያወጣናል፡፡ በሂሳብኛ አነጋገር integration by parts ብልት ብልቱን፣ በመጠን በመጠኑ እየቀመሩ ማዋሃድ እንደማለት ነው፡፡ የአገር አንድነትም መላው ይሄው ነው፡፡
ባለሙያዎቹን ወደ ስራውና ወደ ማዕዱ ማቅረብ ዋና ነገር ነው፡፡ አትሙት ላለው መላ አለው! ባለሙያ ሥራውን በፍቅር ይሰራ ዘንድ አዎንታዊ ድባብ (working atmosphere) ይፈልጋል፡፡ ቀዳሚው ፍቅር ነው፡፡ ከፍትፍቱ ፊቱን ይሻል፡፡ ውስጣዊ የሥራ ፉክክር ያወፍራል እንጂ አያቀጭጭም፡፡ መንፈስን ያጠነክራል እንጂ አያኮሰምንም፡፡ ይህም የአመለካከት ጉዳይ ነው፡፡ የበኩሌን ባዋጣ ሙሉው ስዕል ምሉዕነቱ ይረጋገጣል ብሎ የማሰብ ጉዳይ ነው፡፡ መማር የወረቀት ቀበኛ መሆን አይደለም፡፡ የሥራ መሰላል እንጂ፡፡ በመሰላሉ ጫፍ ወጣን ማለትም ሁሉን ቁልቁል እያዩ መኩራራት አይደለም፡፡ we shall never starve ብሎ የመቁረጥ ወኔ የሚፈልግ አያሉ የረሀብ ቢፌ እፊታችን ተደቅኗል! በጭራሽ ርሃብ አናማርጥም! ሁሉንም እናስወግዳለን እንጂ! መድኃኒቱ የየመስካችንን ኃላፊነት በቆራጥነት መወጣት ነው፡፡ እኔ ቆሜ ይህች አገር አትሸራረፍም ማለት ነው! ለዳተኝነት ቦታ አልሰጥም፣ ፍርሃት ደጄን አይረግጥም፣ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ልከፍል ዝግጁ እሆናለሁ! ተበታትነን የትም አንደርስም! አጅ ለእጅ እንያያዝ! እንማከር፤ እንሰባሰብ፣ እንደራጅ!
“ካልተሳፈሩበት፣ ቶሎ ተሸቀዳድሞ፡፡
ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ!!
“የሚለውን አንዘንጋ! “ማነህ ባለሳምንት!” መባል አይቀርም፡፡ ያገኘነውን አጋጣሚ በወጉ መጠቀም ነው ብልህነት! አለበለዚያ፤ “ዕድለ-ቢስ ሰው፣ ግመል ላይ ተቀምጦ ውሻ ይነክሰዋል” የሚለውን ተረት እየተረትን፣ የሌሎች መጫወቻ ሆነን እንቀራለን፡፡ ምዕራባውያንና ምሥራቃውያን ወዳጆቻችን እንደ ወዳጅ የሚያስቡልን የሚመስሉት እስከጠቀምናቸው ድረስ ብቻ መሆኑን አንርሳ!   

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ታዋቂውን የልብ ሃኪምና የአዲስ የልብ ህክምና ማዕከል ባለቤት ዶ/ር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ የ62 ተከሳሾች ክስ ትናንት ማቋረጡን አስታወቀ፡፡
ከቂሊንጦ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ በፍ/ቤት ከተበየነባቸው 38 ተከሳሾች መካከል 26ቱ ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡
በእነ ማስረሻ ሰጠኝ የክስ መዝገብ ስር ከሚገኙት 38 ተከሳሾች መካከል አራቱ በሰው መግደል ወንጀል የተከሰሱ በመሆኑ ክሳቸው ባለበት እንዲቀጥል የተባለ ሲሆን ቀደም ሲል ስምንቱ ያህሉ በነፃ መሰናበታቸው ታውቋል፡፡
ቀሪዎቹ ክሳቸው የተቋረጠላቸው በተለያዩ የሽብር ወንጀሎች ተከሰው ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው ሲከታተሉ የነበሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡  

ዢ ጂፒንግ በወንዶች፣ አንጌላ መርኬል በሴቶች ቀዳሚነቱን ይዘዋል

    ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፤በ2018 የፈረንጆች አመት በተለያዩ መስኮች ተጠቃሽ አለማቀፍ ተጽዕኖ ፈጥረዋል ያላቸውን 75 የዓለማችን ሃያላን ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን በወንዶች የቻይናው ፕሬዚዳንትና የኮሙኒስት ፓርቲ ዋና ጸሃፊ ዢ ጂፒንግ፣ በሴቶች የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ መርኬል ቀዳሚነቱን ይዘዋል፡፡
ላለፉት አራት ተከታታይ አመታት፣ የፎርብስ የአለማችን ቁጥር አንድ ሃያል ሆነው የዘለቁት የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ዘንድሮ ቦታቸውን ለዢ ጂፒንግ አስረክበው፣ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ያሉ ሲሆን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሶስተኛነት ይከተላሉ፡፡
የአመቱ የአለማችን ቁጥር አንድ ሃያል ሴት የተባሉት የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ መርኬል፣ ከአለማችን ሃያላን የአራተኝነት ደረጃን መያዛቸውን የጠቆመው የፎርብስ መግለጫ፤ የአለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ጄፍ ቤዞስ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
የሮማው ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ፣ የማይክሮሶፍቱ መስራች ቢል ጌትስ፣ የሳዑዲው ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን አል ሳኡድ፣ የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲና የጎግል ኩባንያ መስራች ላሪ ፔጅ እንደ ቅደም ተከተላቸው፣ ከስድስተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ የአለማችን ሃያላን ዝርዝር ውስጥ 17 ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተካተቱ ሲሆን፣ ተራማጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የሳዑዲ አረቢያው ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን አል ሳኡድ፣ ከእነዚህ አዲስ ገቢዎች አንዱ ናቸው፡፡
በአመቱ የአለማችን ሃያላን ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱ ታዋቂ ግለሰቦች መካከል 13ኛ ደረጃን የያዘው የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዛከርበርግ፣ 36ኛ ደረጃን የያዙት የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጁንግ ኡን፣ 66ኛ ደረጃን የያዙት የአፍሪካ ቁጥር አንድ ቢሊየነር ናይጀሪያዊው አሊኮ ዳንጎቴ እና 73ኛ ደረጃን የያዙት የአሸባሪው ቡድን አይሲስ መሪ አቡበከር አል ባግዳዲ ይገኙበታል፡፡
ፎርብስ የፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪነት፣ ተሰሚነት፣ የሃብት መጠን፣ የስኬት ደረጃና የመሳሰሉትን መስፈርቶች በመጠቀም ከገመገማቸውና በዝርዝሩ ውስጥ ካካተታቸው የአመቱ ሃያላን መካከል የአገራት መሪዎች፣ የኩባንያ ባለቤቶችና የስራ ሃላፊዎች፣ የተቋማትና ቡድኖች መሪዎች ወዘተ ይገኙበታል፡፡

  77 በመቶ አሜሪካውያን ስብሰባውን ይደግፋሉ ተብሏል

    አይን እና ናጫ ሆነው የከረሙትና ከዛሬ ነገ ከቃላት ጦርነት ወደ ሚሳኤል ጦርነት ይገቡ ይሆን በሚል አለም በስጋት ተወጥሮ ሲከታተላቸው የነበሩት የአሜሪካው ዶናልድ ትራምፕና የሰሜን ኮርያው አቻቸው ኪም ጁንግ ኡን፣ ከሳምንታት በፊት ሁሉንም ፉርሽ አድርገው፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሰላም በማውረድ፣በአይነስጋ ተገናኝተው በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ሊመክሩ  መቀጣጠራቸውን ያስታወሰው ሲኤንኤን፤ ለመሪዎቹ ታሪካዊ ስብሰባ የተመረጠቺው ሲንጋፖር መሆኗን ዘግቧል፡፡
ሰሜን ኮርያ አስራቸው የነበረቻቸውን ሶስት አሜሪካውያን፣ ባለፈው ረቡዕ መልቀቋን ተከትሎ የወጡ መረጃዎች፣ በስልጣን ላይ እያሉ በጋራ ስብሰባ ላይ በመታደም በሁለቱ አገራት ታሪክ የመጀመሪያዎቹ የሚሆኑት ትራምፕና ኪም ለሚያደርጉት ስብሰባ በተመረጠቺዋ ሲንጋፖር፣ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የተፈቱትን አሜሪካውያን እስረኞች ለማምጣት ወደ ፒንግያንግ አምርተው የነበሩት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ፣ ከሰሜን ኮርያው መሪ ጋር በቀጣዩ ስብሰባ ዙሪያ መምከራቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ፖምፒዮ በበኩላቸው፤የመሪዎቹ ስብሰባ የሚከናወንበት ቦታና ጊዜ መወሰኑን ከመናገር ውጪ የትና መቼ የሚለውን በግልጽ አለመጠቆማቸውን ገልጧል፡፡
የሰሜን ኮርያው ኪም ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ፤”ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር የማደርገው ስብሰባ በኮርያ ልሳነ ምድር ሰላምን ለማስፈንና የተሻለ መጻይ ጊዜን ለመፍጠር የሚያስችል ታሪካዊ ክስተት ይሆናል” ብለዋል - በመንግስት መገኛኛ ብዙኃን፡፡
የአሜሪካ መንግስት ባለስልጣናት ከገለልተኛነቷና ከተሟላ የመሰረተ ልማት አውታሮቿ ጋር በተያያዘ ሲንጋፖርን ለስብሰባው ሳይመርጧት እንዳልቀሩም ዘገባው አመልክቷል፡፡ በተያያዘ ዜናም 77 በመቶ ያህል አሜሪካውያን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሜን ኮርያው አቻቸው ጋር ለመገናኘት መወሰናቸውን እንደሚደግፉና ትራምፕ በሰሜን ኮርያ ጉዳይ እየተከተሉት ያለውን አካሄድ የሚደግፉ ዜጎች ቁጥርም ከወራት በፊት ከነበረው ጭማሪ ማሳየቱን ሲኤንኤን በጥናቱ አረጋግጧል፡፡

 “ደስ የሚል ህይወትን ኖሪያለሁ፤ አሁን ግን መኖር በቃኝ፤ የመሞት መብቴን አክብሩልኝና በክብር አስናብቱኝ” ያሉት ታዋቂው አውስትራሊያዊ ሳይንቲስት ዴቪድ ጉዶል፤ የመሞት መብታቸው ተከብሮላቸው በተወለዱ በ104 አመት ዕድሜያቸው ከትናንት በስቲያ፣ ስዊዘርላንድ ውስጥ በሚገኝ ክሊኒክ ተገድለዋል፡፡
12 የልጅ ልጆችን ያዩት ሳይንቲስቱ፤ ራሳቸውን ለሞት ሲያዘጋጁ በነበሩበት ዋዜማ ምናልባት ሃሳባቸውን ይቀይሩ እንደሆን የመጨረሻ ቃላቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው፣ በህይወት መቀጠል አልፈልግም፣ ልክ ነገ ላይ ህይወት እንድታበቃ የማድረግ እድል ስላገኘሁ ደስተኛ ነኝ ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን ዩኤስኤ ቱዴይ ዘግቧል፡፡
ሳይንቲስቱ የስዊዘርላንድ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ሶዲየም ፔንቶባርቢታል የተባለ አደገኛ መድሃኒት የተሞላበት ስሪንጅ በሃኪሞች ከተሰጣቸው በኋላ፣ መርፌውን ራሳቸው ክንዳቸው ላይ እንዲወጉት ተደርጎ፣ በደቂቃዎች ውስጥ የመጨረሻው እንቅልፍ እንደወሰዳቸውና ከቅጽበት በኋላም ይወስዳቸው ዘንድ የፈቀዱለት ሞት እሹሩሩ እያለ ወደማይመለሱበት እንደወሰዳቸው ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የመሞት መብት እንዲከበር የሚታገል አለማቀፍ ተሟጋች ተቋም አባል የነበሩት የ104 አመቱ የዕድሜ ባለጸጋ ዴቪድ ጉዶል፤ ምንም እንኳን ከቅርብ አመታት ወዲህ ከዕድሜ መግፋት ጋር በተያያዘ የጤና ችግር ቢያጋጥማቸውም ለሞት የሚያሰጋ እንዳልነበርና ለመሞት የወሰኑት ህይወት በቃችኝ በሚል ብቻ መሆኑንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በእንግሊዝ፣ በአሜሪካና በአውስትራሊያ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ለረጅም አመታት ያገለገሉትና በሙያቸው ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ የአውስትራሊያን የክብር ሜዳልያ የተሸለሙት ሳይንቲስቱ፤ እ.ኤ.አ በ1979 ጡረታ መውጣታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ 30 ቅጾች ያሉትንና ከ500 በላይ ታዋቂ ሳይንቲስቶች የጻፏቸው የምርምር ስራዎች የተካተቱበትን ኢኮስስተምስ ኦፍ ዘ ወርልድ የተባለ መጽሃፍ በአርታኢነት ለንባብ ማብቃታቸውንም አመልክቷል፡፡
በፈቃዳቸው ይህቺን አለም የተሰናበቱት ዴቪድ ጉዶል፤ ሬሳቸው እንዳይቀበር፤ ሰልስትና አርባ ብሎ ነገር እንዳይደረግላቸው የተናዘዙ ሲሆን የሰውነት ክፍሎቻቸው ለሌሎች ሰዎች ህክምና እንዲሰጥላቸውና አስከሬናቸው እንዲቃጠልም ለቤተሰቦቻቸው አደራ ብለው እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡

    በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሰሜን ምዕራብ ክልል የኢቦላ ቫይረስ ዳግም በወረርሽኝ መልክ መቀስቀሱንና በአካባቢው ለህልፈተ ህይወት ከተዳረጉ 17 ሰዎች መካከል ሁለቱ በቫይረሱ ሳቢያ መሞታቸው መረጋገጡን የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ቢኮሮ ከተባለቺው የአገሪቱ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ኢኮ ኢምፔንጄ የተሰኘች የገጠር መንደር ውስጥ የሚኖሩ 21 ሰዎች ባለፈው ሳምንት መታመማቸውንና ከእነሱ መካከልም 17ቱ ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ የተቀሩት በሆስፒታል ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ገልጧል፡፡
ስምንት ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት የዳረገው የኢቦላ ቫይረስ በቁጥጥር ስር ከዋለ አንድ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአገሪቱ ታሪክ ዘጠነኛው የሆነው የኢቦላ ወረርሺኝ  ከሰሞኑ መከሰቱን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ አፋጣኝ ርብርብ ካልተደረገ ወረርሽኙ የከፋ ጥፋት ሊያስከትል ይችላል መባሉን አመልክቷል፡፡
የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ወረርሺኙን በአፋጣኝ ለመግታትና ለዜጎች አፋጣኝ ህክምና ለመስጠት ባለሙያዎችን መድቦ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ በመጠቆም፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ ችግሩን ለመፍታት ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተቀሰቀሰውን የኢቦላ ወረርሺኝ ለመግታት በአፋጣኝ ልዩ ግብረሃይል በማቋቋምና 50 ባለሙያዎችን በማሰማራት ከአገሪቱ መንግስትና ከለጋሽ ተቋማት ጋር በጥምረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጾ፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርቧል፡፡
ከሁለት አመታት በፊት በምዕራብ አፍሪካ አገራት የተቀሰቀሰውና በታሪክ የከፋው እንደነበር የሚነገርለት የኢቦላ ወረርሺኝ፤ በአካባቢው አገራት በድምሩ 11 ሺህ 300 ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉንና 28 ሺህ 600 ያህል ሰዎችም በቫይረሱ መጠቃታቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

82ኛው “ጦቢያ ግጥም በጃዝ” ረቡዕ ይካሄዳል
 82ኛው ዙር “ጦቢያ ግጥም በጃዝ” የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ በራስ ሆቴል ይካሄዳል፡፡ ግርማ ተፈራ - ሙዚቃ፣ አርቲስት ተፈሪ አለሙ - ትረካ፣ ሽመልስ አበራ - መነባንብ፣ ጌዲዮን ወ/ዮሐንስ - ዲስርና በኃይሉ ገ/እግዚአብሄር ወግ የሚያቀርቡ ሲሆን ትዕግስት አጀመ፣ አብረሃም አስቻለው፣ ውብአለም ተስፋዬና ናትናኤል ጌቱ ግጥሞቻቸውን እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡

 በስራ ፈጠራና በካይዘን ፅንሰ ሀሳብ ላይ ተመስርተው ባሰናዷቸው መፅሐፍት የሚታወቁት ዶ/ር አቡሽ አያሌውና እንድሪስ አራጋው “የኢንተርፕረነርሺፕ ሀሁ” የተሰኘ መፅሐፍ አዘጋጅተው ለገበያ አቀረቡ፡፡ መፅሐፉ፤ “የራስህን ቢዝነስ ለመጀመር አሁኑኑ ተነስ” በሚል ከንግድ ሀሳብ ፈጠራ እስከ ንግድ ሀሳብ እቅድ አነዳደፍ ድረስ በተግባር የተዋቀረ ትምህርት ይሰጣል ተብሏል፡፡
አንድ ሰው እንዴት ውጤታማ ቢዝነስ መጀመር ይችላል፣ በፍጥነት ገበያን ሰብሮ ለመግባት ምን መደረግ አለበት፣ የቱን አይነት የንግድ ህጋዊ አመሰራረቶች ቢመርጥ ይጠቀማል በሚሉትና መሰል ጉዳዮችም ላይ ሰፊ ሃሳብና አማራጭ ያቀርባል ተብሏል፡፡ በ330 ገፆች የተቀነበበው መፅሐፉ፤ በ175 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

   በኢንተሌክችዋል አለም አቀፍ ት/ቤት አዘጋጅነት ሲካሄድ የነበረውና ከ1 መቶ በላይ ት/ቤቶች የተውጣጡ 1 ሺህ ተማሪዎች የተሳተፉበት የሂሳብ ውድድር፤ አሸናፊዎችን በመሸለምና በኪነ ጥበብ ዝግጅቶች ተጠናቀቀ፡፡
ት/ቤቱ ከ1ኛ - 3ኛ የወጡ ተማሪዎችን እንደየክፍል ደረጃቸው ከ2 ሺህ እስከ 1 ሺህ ብር እና የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ሸልሟል፡፡ ለአሸናፊ ተማሪ ት/ቤቶችም ዘመናዊ ፕሪንተርና ኮፒ በአንድ ላይ የያዘ ማሽን በሽልማት አበርክቷል፡፡ ውድድሩ ዘንድሮ ከ6ኛ - 8ኛ ክፍል ባሉ ተማሪዎች መካከል ለስምንተኛ ጊዜ መካሄዱም ተገልጿል።
በዚህ ውድድር የግልና የመንግሥት ት/ቤቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ የሂሳብ ውድድሩን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማካሄድ እቅድ እንደነበራቸው የት/ቤቱ የአፍሪካ ህብረት ቅርንጫፍ መምህርና ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ካሳሁን አስራደው ተናግረዋል፡፡ ውድድሩ በየዓመቱ መካሄዱ የተማሪዎቹን የሂሳብ ትምህርት ፍላጎትና ችሎታ ያሳድጋልም ተብሏል፡፡

  በዶ/ር አማረ ተግባሩ የተፃፈው “ኃይሌ ፊዳና የግሌ ትዝታ” የተሰኘ መፅሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ መፅሐፉ በ1960ዎቹ መጨረሻ በዋናነት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እንዲሁም የመኢሶን መሪ በነበረው ኃይሌ ፊዳ ህይወት፤ ፖለቲካዊ ሚና እንዲሁም አጠቃላይ አብዮታዊ እንቅስቃሴ የሚያስቃኝ ነው ተብሏል፡፡
ስለ ኃይሌ ፊዳ ጨዋነት፣ አስተዋይነት፣ አርቆ አሳቢነትና ረቂቅነት የሚያወሳው መፅሐፉ፤ ለዛውን፣ ልዩ ፍቅሩንና ሥጦታውንም በተባ ብዕርና ባማረ ቋንቋ ይገልጽልናል ተብሏል፡፡ “የድህረ ዘውድ ኢትዮጵያ የሁሉንም ዜጋ ነፃነትና እኩልነት የሚያረጋግጥ፤ የደሀውንና የተበደለውን ወገን ዕድልና ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ አቅጣጫ ከቀየሱት ወጣቶች ግንባር ቀደም የሆነው ኃይሌ ፊዳ ነውና ይህን መልካም ማስታወሻ ስላበረከተልን የዶ/ር አማረ ተግባሩ ባለውለታ ነን …” ብለዋል ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ በመፅሐፉ ጀርባ ባሰፈሩት አስተያየት፡፡ በ236 ገፆች የተቀነበበው መፅሐፉ፤ በ111 ብር ከ50 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡