Administrator

Administrator

 ከሊዮ ቶልስይ ተረቶች ውስጥ እንዲህ የሚል ይገኝበታል።
አንድ ንሥር በዛፍ ላይ ጎጆትሠራለች። እዚያ ውስጥ ጫጩት ትፈለፍላች። አንዲት አሣማ ደግሞ ግልገሎቿን ይዛ ዛፉ ሥር ትመጣለች። ንሥሩዋ ሩቅ በርራ አድን  ልጆቿን ትቀልባለች። አሣማዋ ዛፉ ሥር እየኖረች እጫካው ውስጥ እየገባች እያደነች ውላ ማታ ለልጆቿ ምግብ ታመጣላቸዋለች። በዚህ ዓይነት ንሥርና አሣማ እንደ ጥሩ ጎረቤት እየተማመኑ፣ እየተዋረዱ፣ አንዳቸው ባንዳቸው ላይ ክፉ ላያስ ተስማምተው መኖራቸውን ቀጥላ። በመሰረቱ ንሥርና አሳማ ባንዳቸው ላይ ክፉ ላያስቡ ተስማምተው መኖራቸውን ይቀጥላሉ። በመሠረቱ ንሥርና አሣማ በተፈጥሯቸው አንዳቸው ያንዳቸውን ግልገል ካገኙ የማይምሩ ተፃራሪ ፀባይ ያላቸውና ሊጠፋፉ የሚችሉ ናቸው። አንድ ቀን አንዲት አሮጊት ድመት ወደ ሁለተሩ ሰፈር መጣች። የንስሯንም ጫጩቶች ጡት የሚጠቡትንም የአሳማዋን ግልገሎች፣ ልትበላቸው አሰበች።
ወደ ንሥሯ ሄዳ፤
“ንሥር ሆይ! ለምግና ለአደን ብለሽ ከእንግዲህ ሩቅ መንገድ እንዳትሄጂ። ይቺ አሣማ የምትተኛሽ አይምሰልሽ። መጥፎ ተንኮል እያሰበችብሽ ነው። የዛፉን ሥር እየበጣጠሰችው ነው። እንደምታይው በየቀኑ የሥሩን አፈር እየማሰች ነው” አለቻት። ንስርም ስለምክሯ አመስግናት ተለያዩ
ቀጥላ ደግሞ ወደ አሳማዋ ዘንድ ሄዳ፤
“አሣማ ሆይ! ዘንድሮ ጥሩ ጎረቤት አልተዋጣልሽም። ትላንት ማታ ንሥሯ ለጫጭቶቿ እንዲህ ስትል ሰማኋት፡- ወዳጄ ስለሆንሽ ሆዴ አልችል ብኝ ልነግርሽ መጣሁ” አለች። አሣማም፤ “ምን አለችኝ እባክሽ?” ብላ በጉጉት ጠየቀች።
ድመትም፤ “ምን ስትል ሰማኋት መሰለሽ፡-” ‘ልጆቼ፤ ከእንግዲህ አትራቡም። እንዲያውም ጥሩ ጥሩ ግልገል አሣሞች እያመታሁ እቀልባችኋለሁ። አይዟችሁ፤ ይቺ አሳማ የምትኖርበት ድረስ መጥታ ግልገሎቿን መሬት ላይ አፍስሳልናለች። እናታቸው ራቅ ብላ ስትሄድ ቆንጆ ቆንጆ ግልገሎቿን እያመጣሁ አበላኋቸው’” አለች።
ከዚህ ቀን ጀምሮ ንስር ወደ ሩቅ ቦታ እየሄደች ማደኗን አቆመች።
አሳማዋም ከዚህ ቀን ጀምሮ ወደ ጫካ መሄዷን አቆመች።
የንስርም ቻጩቶች፣ የአሳማም ግልገሎች ከቀን ወደ ቀን ለረሃብ እየተጋለጡ ሄዱ። ውሎ አድሮ፤ የንስር ልጆች አንድ በአንድ ከዛፍ ላይ እየተፈነቸሩ ይወድቁ ጀመር። የአሳማም ግልገሎች እናታቸው ለመኖሪያ ወደማሰችው ጉድጓድ ውስጥ ሞተው ይገኙ ጀመር።
አሮጊቷ ድመት የሞቱትን ጫጩቶችና ግልገሎች እያፈራረቀች “ተመጣጠነ ምግብ ማለት ይሄ ነው!”፤ እየተመገበች፤ ፌሽታ ስታደርግ ከረመች።
ንስርና አሳማ ሲያለቅሱ ሰነበቱ።
***
 ከላይ ዛፍ ከታች መሬት ለመኖሪያ ካተመቸ አገር አማን አትሆንም።
የህዝቡ ኑሮ አስተማማኝ አይንም። በዜጎች መካከል መተማመን አይኖርም። አንድም ፍትሃዊት እየጠፋ “በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ ይሆናል”። አንድም ደግሞ ቃልኪዳን ፈርሶ፣ የተደላደሉበት ተንሸራቶ “ያመኑት ፈረስ ጣለው በደንደስ” ይሆናል። ከላይ በተረቱ እንዳየነው፤ ተቻችለውና ተስማምተው ለመኖር የሚችሉትን በማቆር፤ እንጠቀማለን ለሚሉ አለመመቸት ተገቢ ነው።
እጅግ የከረሩ አቋሞች ሚያመጡትን ጉዳት አንዳንዴ ከህዝብና ከሀገር ጥቅም ጋር ማየት ተገቢ ነው። በፓርቲዎች ደረጃ ሲታሰብ የኔ ልማት የሌላው ጥፋት የሚል እሳቤ ብዙ አያራምድም። በአገርኛ አባባል፤ “ሞትሽ እውነት በሆነና ልጅሽን ማሳደጉ እኔ በቸገረኝ፤ አለች አሉት” እንደተባለው ማለት ነው።
በዓለም ላይ እንደታየው ብዙ ለሥልጣን ሚታገሉ የፖለቲካ ሃይሎች ሁኔታዎች በውጥረት ሲሞሉ ምክንያታዊ መሆናቸው እየላላ በአጭር ጊዜ መፍትሄ ላይ ይተማመናሉ።
ይኸውም በአብዛኛው ስሜታዊና ጉልበተኛነት የሞላ ሆኖ ነው የሚገኘው። ይሄ በፈንታው ሰላም ያሳጣናል። በሀገራችን በተካሄደው ምርጫ ህዝቡበነቂስ ቀጥቶ ድምጹን ለፈለገው ወኪሉ መስጠቱ ለዲሞክራሲዊ ጎዳና ጥርጊያውን የማመቻቸቱን ያህል፤ በቸልተኝነት በማንአለብኝም በሚሰሩ ስህተቶች መካከል ፍጻሜ እንዳናይ ከተደረግን፤ በዲሞክራሲያዊነት ስም ሀሳዊ- ዲሞክራሲ ይጫነናል።
አንድ ጸሐፊ ስለተሳትፎአዊ ዲሞክራሲ ሲጽፍ፤ “በጥረት ህዝብን ማሳተፍ የመቻሉን ያህል በጉልበት የተሳትፎውን ፍሬ መከልከል ከቶ አይቻልም” እንዳለው በሀገራችን ዲሞክራሲያዊ ንፍቀ-ክበብ እንዳይጨልም ማድረግ ወሳኝ ነገር ነው።
በየትኛውም መልኩ ሰላምንም፣ ዲሞክራሲንም ማጣት ሀገራችን ዛሬ ልትቋቋመው የማትችለው እዳ ነው። የተረገመን እግር፤ በቅሎም ጫማም ይነሳዋል እንደሚባለው ሲሆን ነው። ማለት ነው።
“ከቶውንም ትላንት የነበረውን ምርጫ ሆነ ፖለቲካዊ አካሄድ ዛሬ ለምንሰራው ስህተት፤ መሸፈኛ አልያም መጸጸቻ እስከመቼ ነው? ግትርነት፣ ጉልበትና ስሜታዊነት ባላንጣ ላይ ብቻ ሳይሆን የራስንም ወገን እንደሚያሳጣህ ቀደምት ጸሀፍት ይናገራሉ። ሸክስፒር እንዲህ ይጠይቀናል፡- “… እልህ እስከምን ይዘልቃል።”
የት ድረስ ነው ግትር ጽንፉ
በባላንጣ ሰበብ ምክንያት፣
የራሱን ወገን ማርገፉ?...”
ዲሞክራሲ ስንል በህዝብ መወከል፣ በፖለቲካ ጉልበት የሆነበት ግን የህዝብ ተአማኒ አገልጋይ የሚኮንበት አትበጀኝም ሲል ህዝብ በቃኸኝ፣ አትወክለኝም ሊል የሚችልበት፤ የሲቪልና የፖለቲካ መብት እንዲከበር የሚደረግበት፤ ህዝብ ህጋዊና ህገ-ወጥ የሆነውን ነገር በውል አውቆና መብቱን ተረድቶ ሊያስከብር የሚነሳበት መነሳቱን እንደወንጀል የሚቆጠርበት፣ የማይሰጥ-የማይነጠቅ ነጻነት የሚቀዳጅበት ማለት ነው።
ይህንን ስንልም ዲሞክራሲ ምሉዕ ይሆን ዘንድ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶቹንም ያካተተ መሆኑን ከቶም ሳንዘነጋ ነው።
ወደ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ የሚያራምደንን ምርጫ አንድ እርምጃ ብለን ለመጓዝ የምርጫውን ዘላቂ ውጤት፣ የድጋሚ ምርቸውን ወሳኝ ቁጥርና አግባብ ያለው ቆጠራ እንዲኖር ታዛቢዎች እውነተኛ ውሳኔ፣ የስሞታዎች የተጣራ ውጤት ወዘተ ተደምረው ነው ፍሬ የሚገኘው፤ ሁሉም ተፎካካሪ ወገኖች ትልቁን የሀገር ስብእና ዘላቂውን የህዝብ ጥቅም ቀዳሚ አድርገው ካስተዋሉ ነው። አለበለዚያ ቻይናውያን እንደሚሉት “የባህር-ዳርቻ የወፍና የባህር አሣ ሲታገሉ አሣ-አጥማጅ አይቀማውም።”

ቶሎ ማስረከብና ልዩ ዲዛይን ዋና መገለጫዎቼ ናቸው ብሏል

ባለፉት 27 ዓመታት በመንገድ ግንባታ ሥራ ልምድ እንዳካበተ የገለጸው ዲ ኤም ሲ ሪል ስቴት ወደ መኖሪያ ቤት ማልማት መግባቱንና ለነባር ደንበኞቹ ልዩ ቅናሽ ማቅረቡን አስታወቀ። ድርጅቱ ይህንን ያስታወቀው ከትላንት በስቲያ ለቡ መብራት ሃይል በሚገኘው የግንባታ ሳይት ለመገናኛ ብዙሃን ባደረገው የጉብኝትና የመግለጫ መርሃ ግብር ነው። ዲ ኤም ሲ ሪል እስቴት በዳንኤል ማሞ ኮንስትራክሽን (ዲ ኤም ሲ) ስር ካሉ አምስት ኩባንያዎች አንዱ ሲሆን በተለይም በሀዋሳ በአርባ ምንጭና በሌሎች አካባቢዎች ላለፉት 27 ዓመታት ያካበተውን የመንገድ ግንባታ ልምድ ወደ ሪል እስቴት ልማት በማምጣት ለቤት ፈላጊዎች ሲኖሩበት የሚደሰቱበት ቤት ለማስረከብ አዳዲስ ቴክሎጂዎችንና 24 ሰዓት የሚሰሩ ሰራተኖችን ይዞ ወደ ስራ መግባቱን የኩባንያው ሃፊዎች አብራተዋል።
ዲኤምሲ ወደ ሪል እስቴት ልማት ከመግባቱ በፊት በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመለየት አንድ ዓመት ተኩል የፈጀ ጥናት ማካሄዱ የተገለጸ ሲሆን በጥናቱም ከተለዩት ዋና ዋና ችግሮች ቤቶቹን ለነዋሪዎቹ በወቅቱ የማስረከብና የዲዛይን ችግር ቀዳሚዎቹ ናቸው ሲሉ ከኩባንያው ሃፊዎች አንዱ አቶ ፋንታሁን ግርማ ገልጸው ዲኤምሲ ይህን ለመቅረፍ አንድ ስላፕ በ10 ቀን የሚሞላ ቴክኖሎጂ ከጣውላና ከእንጨት የጸዳ አሉሙኒየም ፍሬም ወርክ ቴክሎጂን በመጠቀም እስከ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ባለ ጊዜ ውስጥ ለማስረከብ 24 ሰዓት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል። በለቡ መብራት ሃይል በ65ሺ 395 ካ.ሜ ዋናው መንገድ ላይ በሚገነባው ትልቅ የመኖሪያ መንደር ለነባር ደንበኞቹ እስከ 1 ነጥ አራት ሚሊዮን ብር ቅናሽ ማድረጉን የገለጸ ሲሆን በአንድ ህንፃ ላይ እስከ 200 አባዎራ እንደሚኖርና በየህንፃው ለ200 አባወራ አንድ ቤት በእጣ ለእድለኛ እንደሚሰጥም ተነግሯል።
ከስቱዲዮ እስከ ባለ 4 መኝታ ቤት ለገበያ ያቀረበው ኩባንያው ቤቶቹ ከ6 ሚሊዮን እስከ 20 ሚሊዮን የሚደርስ ዋጋ እንዳላቸው የተገለፀ ሲሆን ባለ 186 ካ.ሜ ባለ አራት መኝታ ቤት  ወዲያው ከፍሎ ለሚገዛ 6 ሚሊዮን ማለትም የ1 ስቱዲዮ መግዛ ያህል ቅናሽ ይደረጋል ብለዋል የዲ ኤም ሲ ሃላፊዎች።
ቤቶቹን በጊዜ ማስረከብ ስለመቻላቸው ለቤት ፈላጊዎች ዋስትናቸው ምንድን ነው በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ ሃላፊዎቹ ሲመልሱ ቤቶቹን በ2 ዓመት ከስድስት ወር ለማስረከብ ውል መገባቱን ነገር ግን ከአቅም በላይ የሆነና አስገዳጅ ጉዳይ ካጋጠመ  ከ3-6 ወር የጊዜ ገደብ ጭማሪ ኩባንያው እንደሚጠይቅ ሆኖም በዚህ ጊዜ ማስረከብ ካልቻለ የቤቱን ዋጋ 20 በመቶ ኩባንያው እንደሚቀጣ በውሉ ላይ መቀመጡን ሃላፊዎቹ አብራተዋል።
 ለደንበኞች ተዓማኒ ለመሆንም ሆነ በወቅቱ ባለማስረከብ ከሚመጣው ቅጣት ኩባንያው ራሱን ለመጠበቅ ለሰራተኞች በግንባታው ሳይት ላይ መኖሪያ፣ ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን አሟልቶ 24 ሰዓት ግንባታው መቀጠሉም ተብራቷል። ዲ ኤም ሲ ሪል ስቴት በአሁኑ ወቅት ቤቶቹን በካሬ 90 ሺህ ብር ለሽያጭ ያቀረበ ሲሆን በቀጣይ በፒያሳ፣ በቦሌና በሌሎች ተመራጭ ቦታዎች ቤቶቹን ለማልት መዘጋጀቱን ገልጿል።
ዲኤም ሲ ሪል ስቴት የሚገነባቸው ቤቶች በልዩ ዲዛይን የተገነቡና ለኗሪው አስደሳች ናቸው የተባለ ሲሆን በየአንዳንዱ ህንፃ ላይ አምስት አሳንሰሮች የሚገጠሙና ከአምስቱ አንዱ እስከ ዛሬ በሪል እስቴት ባልተለመደ መልኩ ትልልቅ እቃዎችን የሚያጓጉዝ ሰርቪስ ሊፍት ይኖረዋል ተብሏል። መናፈሻ፣ ጂም ፣ የመዋኛ ገንዳዎች፣ የመኪና  ማቆሚያ፣ የህፃናት መጫዎቻ ቦታና ሌሎችም ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶች የሚገኙበት ቅንጡ መንደር እንደሚሆን የገለጹት ኃላፊዎቹ በቀጣይ ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ያለውን ቁርኝት ለማጠናከር በማሰብ ጋዜጠኞቹ በተመቻቸው ጊዜ ቀረፃና ኤዲቲንግ የሚሰሩበት ትልቅና ዘመናዊ ስቱዲዮ በመገንባት ላይ መሆኑንም ዲኤምሲ ሪል እስቴት ሀሙስ ረፋድ ላይ ለቡ መብራት ሀይል በሚገኘው የሽያጭ ቢሮው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ  አብራሯል።

የትግራይ  ክልል በመላው ኢትዮጵያ እጅግ  ከፍተኛ ጉዳት ካስከተለውና  በደርግ ዘመነ መንግስት ከተከሰተው የ1977ቱ ረሃብ የከፋ አደጋ ውስጥ ለመግባት ጫፍ ላይ መድረሱን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ፤ 90 በመቶ የሚሆነው  የክልሉ ነዋሪ ህዝብ ለከፋ ረሀብና  ለሞት ተጋላጭ መሆኑን አመልክቷል።
በትግራይ የነበረው አውዳሚ የጦርነት አሻራና ድርቅ ያስከተለው ረሀብ አደገኛ ጥምረት መፍጠራቸውን የጠቆመው የጊዜያዊ አስተዳደሩ  መግለጫ፤  የፌደራል መንግስቱና አለም አቀፍ ተቋማት እያንዣበበ ያለውን  የረሀብና የሞት አደጋ ለማስቀረት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በዚህ መግለጫው፤በጦርነቱ ወቅት የትግራይ የኢኮኖሚ መሰረት መድቀቅ፣ የጤና ተቋማት መውደምና ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የክልሉ  ህዝብ መፈናቀል፣ በትግራይ ብዙዎች ድህነትን መቋቋም እንዳይችሉ አድርጓቸዋል ሲል ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም   የዝናብ እጥረት፣ የአንበጣ መንጋ መከሰትና የሰብአዊ እርዳታ መቋረጥ በክልሉ ያለውን ችግር አባብሶታል ብሏል ።  ይህንን በክልሉ ተከስቷል የተባለውን የረሃብ  አደጋ ለመቋቋም የሚያስችል  የገንዘብ አቅም  እንደሌለው የገለጸው  ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ የፌደራል መንግስትና አለም አቀፍ ተቋማት በክልሉ የተከሰተውን የረሀብና የሞት አደጋ ለማስቀረትና ለነዋሪው ሕዝብ ችግር መፍትሔ ለመስጠት  መስራት እንደሚገባቸው ገልጿል። አያይዞም፤  ችግሩ የማይፈታ ከሆነ  ሀገራዊና ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን ሊያውክ እንደሚችል አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ይኸው በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የተሰጠውና  ክልሉ ከ1977ቱ ጋር የሚስተካከል ድርቅና ረሃብ ቀውስ  ውስጥ  ሊገባ ጫፍ ላይ መድረሱን  የሚጠቁመው መግለጫ፤  ፈጽሞ ስህተት  መሆኑን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቋል።
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ  ዶ/ር ለገሰ ቱሉ    በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ  እንዳስታወቁት፤ በአገር ደረጃ እንዲህ አይነት ቀውስ ሲኖር መታወጅ ያለበት በፌደራል መንግስት በኩል የፌደራል የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት በኩል  ነው ያሉት ዶ/ር ለገሰ፤ ይህም ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ማእከል በማድረግ ተገምግሞ  ነው ብለዋል ። የፌደራል የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት በትግራይ ክልል አራት ዞኖች ድርቅ መከሰቱን ቢያረጋግጥም፣ ከ77ቱ ድርቅና ረሃብ ጋር ይስተካከላል የሚል መረጃ እስካሁን እንዳላወጣም ሚኒስትሩ  ጨምረው ገልጸዋል።
ዓለም አቀፋ አጋር አካላት እርዳታ ባቆሙበት ሰዓት  መንግስት ፕሮጄክቶቹን ሁሉ  አጥፎ ለትግራይ ክልል በበቂ ሁኔታ እርዳታ እያቀረበ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ በ100 ሺህ የሚቆጠር ታጣቂዎችን በባለሙያ ስም በአንድ ቦታ ሰብስቦ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተመደበ በጀት እየቀለቡ፣ በምን ሞራል ነው ስለ ትግራይ ህዝብ ረሐብና ስቃይ ማውራት የሚቻለው?” ሲሉም ጠይቀዋል። በህዝብ ሽፋን የሚደረግ የትኛውም አይነት ፕሮፓጋንዳ ተቀባይነት እንደማይኖረውም ገልጸዋል ።

በሽብርና በሙስና ወንጀሎች ክስ ቀርቦባቸው በእስር ላይ በነበሩት  በእነ አብዲ ሞሃመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) እና በእነ ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው መዝገቦች ቀርበው የነበሩ ክሶች እንዲቋረጡ መወሰኑን  ፍትህ ሚኒስቴር አስታወቋል ።
ክሶቹ እንዲቋረጡ የተደረጉትም  ለህዝብ ጥቅም ሲባል እንደሆነም ገልጿል ።
የሶማሌ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር አብዲ ሞሃመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) በ2011 ዓ.ም በክልሉ የተፈጠረውን ሁከት ተከትሎ፣ በቁጥጥር ስር ውለውና ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው  በ1ኛ የህገ-መንግስትና የሽብር ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ሲታይ  መቆየቱ የሚታወቅ ነው። ይኸው በፍርድ ሂደት ላይ የነበረው ክስ እንዲቋረጥ መወሰኑ ተገልጿል። የክስ መቋረጡን ተከትሎም ከስድስት ዓመታት በፊት ነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ  ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለው አስካሁን በእስር ላይ የቆዩት አቶ አብዲ ኢሌ ከእስር  መለቀቃቸውም ታውቋል።የቀድሞ የኢትዮጵያ ብረታ ብረት እና ኢነጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር የነበሩት  ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ከኮርፖሬሽኑ ሥራ ጋር በተያያዘ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው  በምዕራባዊ ትግራይ በኩል ባታር በተሰኘው አካባቢ  በህዳር 2011 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሙስና ወንጀል ክስ ክርክር ሲካሄድበት  የቆየ ሲሆን፤ ከራዳር እቃዎች የግዥ ሒደት ጋራ ተያይዞ በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ተብለው የ3 ዓመት ከ7 ወር የእስራት ቅጣት ተወስኖባቸውም ነበር።




ጋዜጠኞች የሚደርስባቸውን ጥቃት የሚከታተል ድረገፅ ሥራ ጀመረ

•  የሚዲያ ነጻነትን ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል

የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር (ኢአማ)፤ በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን የሚከታተልና የሚሰንድ ድረ-ገጽ፡- sojethiopia.org  ይፋ አደረገ፡፡

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (UNESCO) ድጋፍ፣ በኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር ተዘጋጅቶ ስራ ላይ የዋለው ይህ ድረ-ገጽ (ፖርታል)፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ በሦስት ቋንቋዎች፡- በአማርኛ ፣ ኦሮምኛና እንግሊዝኛ ተዘጋጅቷል ተብሏል፡፡

ማኀበሩ ከትላንት በስቲያ በማዶ ሆቴል በሰጠው መግለጫ፤ ድረ-ገፁ በጋዜጠኞችና በብዙኃን መገናኛ ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች፣ ወከባዎች፣ እስሮችና ግድያዎችን ለመመዝገብ፣ ለመሰነድና ሪፖርት ለማድረግ የሚያስችል ነው ብሏል፡፡ ድረገፁ በተጨማሪ፣ በማህበራዊ  ሚዲያና  በሌሎችም  መንገዶች  የሚደረጉ  ማንቋሸሽ ፣ ዘለፋ ፣ ስም  ማጥፋትና የመሳሰሉትን በመመዝገብ ፣ በማጣራትና ለቀጣይ ውትወታ ስራዎች ግብዐት በመሰብሰብ መገናኛ ብዙሃን ነፃነታቸው ተጠብቆ በኢትዮጵያ  የዴሞክራሲያዊ  ማህበረሰብ  ግንባታ ሂደት ላይ የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ያስችላል ነው የተባለው፡፡   

sojethiopia.org የተሰኘው ድረ-ገፅ፤ ጋዜጠኞች ስራቸውን በሚሰሩበት ወቅት የሚደርስባቸውን ወከባና  የመሳሰሉ ክስተቶች  ከመከታተልና ከመመዝገብ በተጨማሪ በተለየ ሁኔታ፤ ሴት ጋዜጠኞች በስራ ቦታቸውም ሆነ በጋዜጠኝነት ጉዞአቸው ላይ የሚደርሱባቸውን ፆታዊ ጥቃቶች ሚስጥራዊነቱ በተጠበቀ መንገድ የሚመዘግብና የመፍትሄ ሒደቶችን ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የሚበጅበት  ማዕቀፍ ነው፡፡


በኢትዮጵያ የጋዜጠኞችን እስርና የመብት ጥሰቶች በተመለከተ መረጃዎችን የሚያወጡት የውጭ ተቋማት መሆናቸውን የገለጸው የአርታኢያን ማህበር፤ አዲሱ ድረ-ገጽ እኒህን መረጃዎች ከውጭ ሳይሆን ከራሳችን በቀጥተኛ መንገድ ለማግኘት ያስችላል ብሏል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የሚያስተባብረውና ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ የሚያዘጋጀው “የመኢሶን ሰማዕታት” መጽሐፍ ላይ የሚደረግ ውይይት በነገው ዕለት ቀኑ 8፡00 ጀምሮ በጉለሌው የአካዳሚው ቅጽር ግቢ፣ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የኪነጥበባት ማዕከል ይካሔዳል፡፡
ከዶክተር የራስወርቅ አድማሴ ጋር የሚደረገውን የውይይት ቆይታ ዶክተር እንዳለጌታ ከበደ ይመሩታል፡፡

ሀገራችን በፖለቲካ፡ ኢኮኖሚና ማሕበራዊ ዘርፎች የገጠሟትን ተግዳሮቶች በመንቀስና ለችግሮችም የመፍትሔ ሀሳቦችን የያዙ በርካታ መጣጥፎችን ለአገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጦች በማበርከት የሚታወቁት ዶ/ር ታዬ ብርሃኑ፤ "ሕግ እና ሰብአዊነት" የተሰኘ  መጽሐፋቸውን ለሕትመት ብርሃን አብቅተዋል።
መጽሐፉ አሁን ያለንበትን ሀገራዊ ምስቅልቅል የወለደውን የኢፌዲሪ ሕገመንግሥትን በብርቱ የሚሄስ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ከገባንበት ፖለቲካዊ ቅርቃር ለመውጣት ፣ሥርነቀላዊ መዋቅራዊ ማሻሺያ ማምጣት የሚቻልበትን የመፍትሔ ሐሳብም ያመላክታል።
 "ሕግ እና ሰብአዊነት"  በ7 ምዕራፎች ተከፋፍሎ፣ በ234 ገጾች የተቀነበበ ሲሆን፤ በ300 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ መጽሐፉን ጃፋር የመጻሕፍት መደብር እንደሚያከፋፍለውም ታውቋል፡፡

የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) ከእስር መፈታታቸው ተሰማ፡፡

ከስድስት ዓመት በፊት ነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉትና እስካሁን በእስር ላይ የቆዩት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር፤ ከእስር የተለቀቁት ዐቃቤ ሕግ ክሱን በማንሳቱ መሆኑን ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡

ጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ  እስክንድር ገዛኸኝ እንደተናገሩት፤ የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ክሳቸው ተነስቶ የተለቀቁት በዛሬው ዕለት  መጋቢት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. መሆኑ ታውቋል።

ከአቶ አብዲ በተጨማሪም በተመሳሳይ በእሳቸው የክስ መዝገብ ጉዳያቸው ሲታይ የነበሩ የሌሎችም ተከሳሾች ክስ ተቋርጦ መለቀቃቸውን ጠበቃው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጠበቃና የሕግ አማካሪው እንደሚሉት፣ ዐቃቤ ሕግ ባለው ሥልጣን መሠረት የክስ ማቋረጫውን ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ፣ አቶ አብዲ ከመፈታታቸው ውጪ ለጊዜው የደረሳቸው ዝርዝር ማብራሪያ እንደሌለ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“አሁን ማረጋገጥ የምችለው አቶ አብዲ ዛሬ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ከማረሚያ ቤት መፈታታቸውን እንጂ ዐቃቤ ሕግ ስላቀረበው ጥያቄ የደረሰን ነገር የለም” ሲሉ  የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ከእስር መውጣታቸውን ጠበቃቸው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው ከዓመታት በፊት ጀምሮ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ሲመሩ የነበሩት አቶ አብዲ፣ በክልሉ ውስጥ ከተፈጸሙ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ግድያዎችና የመንግሥት ሀብት ብክነት ጋር ስማቸው ሲነሳ ቆይቷል።
 
በቀድሞው ርዕሰ መስተዳደር ላይ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከልም በ2010 ሰኔ እና ሐምሌ ወራት ውስጥ “በሶማሌ ክልል የእርስ በርስ ግጭት እንዲፈጠር ለማድረግ በማሰብ ‘ሄጎ’ በሚል ስያሜ የሚታወቅ ወጣቶች ቡድን አደራጅተዋል” የሚል ይገኝበታል።

በወቅቱ በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጂግጂጋ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸው፣ እንዲሁም ንብረትና አብያተ ክርስቲያናት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል።

ኢትዮ - ሮቦ ሮቦቲክስ፤ በነገው ዕለት ሐሙስ፣ የ2024 የአፍሪካ ሮቦቲክስ ቻምፒዮንሺፕ ውድድሩን በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል የሚጀምር ሲሆን፤ ቅዳሜ መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡ መርሃ ግብሩ  በአዲስ አበባ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄድ ዓመታዊ የሮቦቲክስ ወድድር መሆኑን የኢትዮ-ሮቦ ሮቦቲክስ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰናይ መኮንን ገልጸዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ  በነገው ዕለት የሚጀመረውን የሮቦቲክስ ውድድር አስመልክቶ ከማዕከሉ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ  አቶ ሰናይ መኮንን ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡ እነሆ፡-

****

እስቲ ታዳጊዎች ባለፉት 6 ወራት በናንተ ማዕከል ውስጥ ስለወሰዱት የሮቦቲክስ ሥልጠና አብራሩልኝ?

ታዳጊዎች ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ፕሮግራሚንግ፣ ዲዛይኒንግ እና ኢንጅነሪንግ ላይ ያተኮረ የሮቦቲክስ ስልጠናዎችን ወስደዋል፡፡ የመማር በተግባር መርህ ተከትለው በመስራት ለቬክስ ሮቦቲክስ ውድድር ተዘጋጅተዋል፡፡

ልጆቹ ከዚህ ሥልጠና በተጨባጭ የሚያተርፉት ምንድን ነው? በህይወታቸው ላይ ምን ይጨምራሉ?

በእነዚህ ጊዜያት የኢንጅነሪንግ ፣ የዲዛይኒንግ እና  የፕሮግራሚንግ ክህሎቶቻቸውን አሻሽለዋል፡፡ የራሳቸውን አዲስ ነገር የመፍጠርና የመሞከር እድል አግኝተዋል፡፡ በመጪው የዲጂታል ዘመን ውስጥ ብቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያደርጋቸዋል፡፡
ባለፈው ጥር ወር በቻይና በተካሄደ ውድድር ላይ ተሳትፋችሁ ተመልሳችኋል? ውድድሩ ምን ይመስል ነበር? ውጤቱስ? በመሰል ዓለማቀፍ  ውድድሮች ላይ መሳተፍ ፋይዳው ምንድን ነው? የኛ ልጆች ከቻይናዎቹ አቻዎቻቸው ጋር ሲወዳደሩ ምን ደረጃ ላይ ነው ያሉት?

ባለፈው ጊዜ በቻይና በነበረን ውድድር አበረታች ውጤት አይተናል፡፡ ለብዙ ተወዳዳሪዎች የመጀመሪያ ስለነበር፣ ከዚህ በኋላ በሌሎች አለም አቀፍ ውድድሮች ማለትም በአሜሪካና በካናዳ ለሚጠብቃቸው መሰል ውድድር የበለጠ ዝግጁ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ፡፡ ቻይናውያን እጅግ በጣም ከፍተኛ ዝግጅት አላቸው፤ በተለይም በትምህርት ካሪኩለማቸው ሮቦቲክስ እና ፕሮግራሚንግ የተካተተ ስለሆነ፤ ከኢትዮጵያውያን የበለጠ ውጤት በማምጣት በውድድሩ ላይ አንደኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡

እስቲ  ነገ ሐሙስ በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል ስለሚጀመረው  የ2024 የአፍሪካ ሮቦቲክስ ቻምፒዮንሺፕ በጥቂቱ ይንገሩኝ? በውድድሩ ሌሎች አፍሪካውያን ይሳተፋሉ እንዴ?

በነገው እለት በኢሊሌ ሆቴል የሚደረገው የአፍሪካን ሮቦቲክስ ቻምፒዮንሺፕ በአዲስ አበባ ለሁለተኛ ጊዜ የሚዘጋጅ አመታዊ የሮቦቲክስ ውድድር ሲሆን፤ በዚህ  ውድድር የተወሰኑ እዚሁ አዲስ አበባ የሚኖሩ አፍሪካውያን ተማሪዎች ይሳተፋሉ፡፡ ውድድሩን ይበልጥ ሌሎች አፍሪካዊ ተማሪዎች የሚሳተፉበት ለማድረግ ጠንክረን እየሰራን ነው፡፡

ኢትዮ - ሮብ ሮቦቲክስ ከተከፈተ ምን ያህል ጊዜ ሆነው? እስካሁን ምን ያህል ተማሪዎች አስመርቃችኋል?

አፍሪካን ሮቦቲክስ ቻምፒዮንሺፕ ያልነው፣ ሮቦቲክስ ስንጀምር በአፍሪካ የመጀመሪያዎች እኛ በመሆናችን ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃ የሚሆነው ደግሞ በ2011 ዓ.ም  እኛ ከብዙ አለም አቀፍ የሮቦቲክስ ኩባንያዎች  ጋር  ስንፈራረም፣ ሌሎች  የአፍሪካ አገራት  ቀድመው አልተፈራረሙም ነበር፡፡ ሁለተኛ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ አገር ከመሆንዋ አንጻር ለዚህ ውድድር ከሌላ አገር የበለጠ ተመራጭ ያደርጋታል፡፡

እናንተ ዘንድ  በሮቦቲክስ ሰልጥነው ትልቅ ቦታ የደረሱ ኢትዮጵያውያን  አሉ?

በ2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስልጠና  ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ  ወደ አሜሪካና ካናዳ ሄደው ስኮላርሺፕ ያገኙና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት እየተማሩ ያሉ፣ ከ100 በላይ ተማሪዎች በተለያዩ ጊዜያት አገራቸውን አስተዋውቀዋል፡፡ ለወደፊት ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ስራ አለም ሲገቡ የምናያቸው ይሆናል፡፡ አሁን በስራ ላይ ካሉት ውስጥ  ሳሙኤል አርአያ በኦንላይን ስራ የሚጠቀስ ጎበዝ ልጅ ነው፡፡

ከሮቦቲክስ ሥልጠና ሌላ ቋንቋም ታስተምራላችሁ አይደል?

የቋንቋና የሰልፍ ዲስፕሊን ኮርስም ለህጻናት እንሰጣለን፡፡ በቋንቋ ስልጠናችን ለተማሪዎች ለየት ባለ ሪድ ኤንድ ቴል ፕሮግራማችን፣ ልዩ ልዩ በልምምድ ላይ ያተኮረ  ስልጠና እንሰጣለን፡፡

ኦቪድ ሪልእስቴት፤ “አንድ ቀን፣ አንድ ህልም፣ አንድ ዕድል” በሚል መሪ ቃል በትላንትናው ዕለት ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት በስካይላይት ሆቴል፣ ለአንድ ቀን ብቻ የሚቆይ ልዩ የቤቶች ሽያጭ በታላቅ ቅናሽ (40 %) ያከናወነ ሲሆን፤ በዚህም የሽያጭ መርሃ ግብር አብዛኞቹ ቤቶች ተሸጠው መጠናቀቃቸው ታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች ቀርጾ ወደ ሥራ መግባቱን ያስታወቀው ኦቪድ ሪልእስቴት፤ እነዚህ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች ልማት ፕሮጀክቶች በ4 ምድብና ሳይቶች መካተታቸውን አስታውቋል፡፡

በትላንትናው ዕለት ለህዝብ የቀረበው አንደኛው ፕሮጀክት ጫካ መኖሪያ ቤት ሲሆን፤ ይህ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ጫካዎች ውስጥ በግንባታ ላይ የሚገኙ 1900 የተንጣለሉ ቤቶች ባለ1፣ ባለ 2 እና ባለ 3 መኝታ አፓርትመንቶችን የያዘ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ 9 ሄክታር በሚሸፍን ሰፊ የከተማው አረንጓዴ መስክ ላይ የሚለማ ነው ተብሏል፡፡

ሁለተኛው ሐረር ሆራይዘን ፕሮጀክት ሲሆን፤ ባለ 2 እና 3 መኝታ ቤት ዘመናዊ አፓርትመንቶችን የያዘ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ 8 ኪ.ሜ ርቀት ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

ሦስተኛው ኪንግስ ታወር ሲሆን፤ ባለ1፣ ባለ2፣ ባለ3፣ እና ባለ4 መኝታ አፓርትመንቶችን ይዟል፡፡  ኪንግስ ታወር ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን ያካተቱ 1740 ሰፋፊ መኖሪያዎችን ያካተተ መሆኑ ታውቋል፡፡

አራተኛው አፍሪካን ሃይትስ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ባለ1፣ ባለ2፣ ባለ3፣ እና ባለ4 መኝታ አፓርትመንቶችን ጨምሮ 324 ቤቶችን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡

ኦቪድ ግሩፕ በሥሩ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ በርካታ ድርጅቶችን ያቀፈ የኮርፖሬት ሆልዲንግ ነው፡፡
ኦቪድ ሪልእስቴት ለአንድ ቀን ባዘጋጀው ልዩ የቤቶች ሽያጭ
ፕሮግራም ላይ  ያቀረባቸው  ቤቶች በሙሉ መሸጣቸውን ገለፀ

ኦቪድ ሪልእስቴት፤ “አንድ ቀን፣ አንድ ህልም፣ አንድ ዕድል” በሚል መሪ ቃል በትላንትናው ዕለት ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት በስካይላይት ሆቴል፣ ለአንድ ቀን ብቻ የሚቆይ ልዩ የቤቶች ሽያጭ በታላቅ ቅናሽ (40 %) ያከናወነ ሲሆን፤ በዚህም የሽያጭ መርሃ ግብር አብዛኞቹ ቤቶች ተሸጠው መጠናቀቃቸው ታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች ቀርጾ ወደ ሥራ መግባቱን ያስታወቀው ኦቪድ ሪልእስቴት፤ እነዚህ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች ልማት ፕሮጀክቶች በ4 ምድብና ሳይቶች መካተታቸውን አስታውቋል፡፡

በትላንትናው ዕለት ለህዝብ የቀረበው አንደኛው ፕሮጀክት ጫካ መኖሪያ ቤት ሲሆን፤ ይህ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ጫካዎች ውስጥ በግንባታ ላይ የሚገኙ 1900 የተንጣለሉ ቤቶች ባለ1፣ ባለ 2 እና ባለ 3 መኝታ አፓርትመንቶችን የያዘ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ 9 ሄክታር በሚሸፍን ሰፊ የከተማው አረንጓዴ መስክ ላይ የሚለማ ነው ተብሏል፡፡

ሁለተኛው ሐረር ሆራይዘን ፕሮጀክት ሲሆን፤ ባለ 2 እና 3 መኝታ ቤት ዘመናዊ አፓርትመንቶችን የያዘ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ 8 ኪ.ሜ ርቀት ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

ሦስተኛው ኪንግስ ታወር ሲሆን፤ ባለ1፣ ባለ2፣ ባለ3፣ እና ባለ4 መኝታ አፓርትመንቶችን ይዟል፡፡  ኪንግስ ታወር ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን ያካተቱ 1740 ሰፋፊ መኖሪያዎችን ያካተተ መሆኑ ታውቋል፡፡

አራተኛው አፍሪካን ሃይትስ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ባለ1፣ ባለ2፣ ባለ3፣ እና ባለ4 መኝታ አፓርትመንቶችን ጨምሮ 324 ቤቶችን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡

ኦቪድ ግሩፕ በሥሩ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ በርካታ ድርጅቶችን ያቀፈ የኮርፖሬት ሆልዲንግ ነው፡፡

Page 9 of 703