Administrator

Administrator

Saturday, 09 February 2013 12:15

ራሳችሁ ላይ አነጣጥሩ!

ብዙዎቹ መከፋቶችና መጥፎ ስሜቶች የሚመነጩት ከፉክክር ወይም ራስን ከሌሎች ጋር በማነፃፀር ነው፡፡ ሌሎች ከኛ የተሻለ ሥራ ሰርተው ስናይ ስለራሳችን መጥፎ ስሜት ይሰማናል፡፡
ትኩረታችንን ድክመቶቻችን ላይ ባደረግን ቁጥር ስለራሳችን ፈፅሞ ጥሩ ስሜት ሊሰማን አይችልም፡፡ ሌሎች ከኛ የበለጠ መልከመልካምና ቆንጆዎች በመሆናቸው ብቻ እንከፋለን፡፡ ሌሎች ከእኛ የበለጠ ገንዘብ፣ አውቶሞቢሎችና መኖርያ ቤቶች ስላላቸው በመጥፎ ስሜት እንዋጣለን፡፡
የሥራ ባልደረቦቻችን እድገት አግኝተው እኛ በማጣታችን ሆድ ይብሰናል፡፡ ሌሎች ከኛ የበለጠ ደስተኞች በመሆናቸው ብቻ ከጥሩ ስሜት እንፋታለን፡፡
አያችሁ - ራሳችሁን ከሌሎች ጋር ማነፃፀር ካልተዋችሁ በቀር ሁልጊዜም ከእናንተ የተሻለ ሰው ማግኘታችሁ አይቀርም፡፡
እናም መቼም ቢሆን ጥሩ ስሜት አይሰማችሁም ማለት ነው፡፡ ማብቂያ በሌለው የፉክክር ወጥመድ ውስጥ ከመውደቅ ይልቅ ራሳችንን ነፃ በማውጣት ህይወትን ለምን በመረጥነው መንገድ አንመራም? ሌሎች ከእኛ የሚሻሉባቸው ጉዳዮች ላይ ከማተኮርና ስለራሳችን መጥፎ ስሜት እንዲሰማን ከማድረግ ይልቅ ለምን ከሌሎች መማርና ክህሎታችንን ማሻሻል ላይ አናተኩርም?
የህይወት ቀዳሚ ግብ ማደግ እንጂ መፎካከር አለመሆኑን ማወቅ ብልህነት ነው፡፡
አትኩሮታችሁን ምንጊዜም ራስን በማሳደግና ምርጡን በማለም ላይ ልታውሉት ይገባል፡፡ ይሄ ከተሳካላችሁ የማታ ማታ ትልቁን ሽልማት መቀዳጀታችሁ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ2004 የአቴንስ ኦሎምፒክ ላይ በወንዶች የ110 ሜትር የመሰናክል ውድድር፤ ለቻይና የመጀመርያውን ወርቅ ያስገኘላት ቻይናዊው አትሌት ሊዩ ዚያንግ ነበር፡፡ ይሄ አትሌት በኦሎምፒክ ለቻይና አዲስ ታሪክ አስመዘገበ፡፡ የአራት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮንና በውድድሩ ተፎካካሪው የነበረው አለን ጆንሰን ከውድድሩ ቢወጣ ኖሮ ውጤትህን ይለውጠው ነበር ወይ ተብሎ የተጠየቀው ዚያንግ፤ “በፍፁም! እኔ የራሴን እቅድ ብቻ ነው የምከተለው፤እናም የላቀ ውጤት ማስመዝገቤ አይቀርም ነበር“ በማለት ነው የመለሰው፡፡ አያችሁ ይሄ አትሌት ከማን ጋር ነው የምሮጠው ብሎ እንኳ አይጨነቅም፡፡ ምርጥ ውጤት ለማምጣት ብቻ በትኩረት ይተጋል እንጂ!
ምንጭ- (The Lost Secrets of Manifestation)

Saturday, 09 February 2013 12:11

የፖለቲካ ጥግ

ነፃ ምርጫ እንድታካሂዱ ፈቅጄላችኋለሁ፤ ነገር ግን ከታማኝ አገልጋዬ ከሪቻርድ በስተቀር ማንንም እንድትመርጡ አልፈቀድኩላችሁም፡፡
ሔነሪ ሁለተኛው (የእንግሊዝ ንጉስ የነበሩት የአዲስ ቢሾፕ ምርጫን አስመልክቶ የተናገሩት)
የአሜሪካ ፕሬዚዳንትም እንኳን አንዳንዴ እርቃናቸውን መቆም አለባቸው፡፡
ቦብ ዳይላን (አሜሪካዊ ዘፋኝና የዘፈን ግጥም ደራሲ)
ለፖለቲከኞች ፍቅርም ጥላቻም የለኝም፡፡
ጆን ድራይደን (እንግሊዛዊ ገጣሚ፣ ፀሐፌ ተውኔትና ሃያሲ)
አገር ለመለወጥ ነበር ያለምነው፤ እሱን ትተን ዓለምን ለወጥን፡፡
ሮናልድ ሬጋን (የአሜሪካ ፕሬዚዳንትና አክተር የነበሩ)
ፓርላማ በለንደን ውስጥ የሚገኝ ምርጥ ክለብ ይመስለኛል፡፡
ቻርለስ ዲከንስ (እንግሊዛዊ ደራሲ)
እንግሊዝ የፓርላማዎች እናት ናት፡፡
ጆን ብራይት (እንግሊዛዊ ፖለቲከኛ)
ፓርላማ ወንዱን ወደ ሴት፤ ሴቷን ወደ ወንድ ከመቀየር በቀር ሁሉን ማድረግ ይችላል፡፡
ሔነሪ ኸርበርት ፔሞብሮክ (የእንግሊዝ መኳንንት)
ፖለቲከኛ ማለት ከሰው በቀር ሁሉ ነገር እላዩ ላይ የተቀመጠበት አህያ ነው፡፡
ኢ.ኢ ኩሚንግ (አሜሪካዊ ገጣሚና ሰዓሊ)
ም/ፕሬዚዳንት፤ የመንግስት አውቶሞቢል ትርፍ ጐማ ማለት ነው፡፡
ጆን ናንሲ ጋርነር (የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩ)
በተመለከተ የተናገሩት)

 

ለጠራራ ፀሐይ “ዝርፊያ” የጠራራ ፀሐይ “ዘለፋ!”
ዛሬ ወጋችንን በእንቆቅልሽ ብንጀምር ምን ይመስላችኋል? ታዲያ የፖለቲካ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ለነገሩ ፖለቲካችን መቼ ከእንቆቅልሽ ወጥቶ ያውቃልና ነው!! (ኑሮአችንስ ቢሆን?) አሁን ለማንኛውም “እንቆቅልሽ?” ብያችኋለሁ “ምን አውቅልሽ” ካላችሁኝ ልቀጥል፡፡ “በአገራችን ብዛታቸው እንደቆጠራቸው ሰው አይነት ከፍና ዝቅ የሚሉት ምንድን ናቸው?” ምናልባት ጠጠር የሚልባችሁ ከሆነ (እንደ ጦቢያ ፖለቲካ ማለቴ ነው!) ፍንጭ ልስጣችሁ እንዴ? (ፍንጭት ግን አልወጣኝም!) ፍንጭ ከሰጠኋችሁማ ምኑን እንቆቅልሽ ሆነ! ስለዚህ በቁርጠኝነት ሙከራችሁን ቀጥሉ፡፡ ወጋችንን ወደ መቋጨቱ ገደማ ስንደርስ ታዲያ መልሱን ሹክ እላችኋለሁ (በምስጢር!)
እስቲ ፖለቲካ በፈገግታችንን ከምድረ አሜሪካ እንጀምረው፡፡ የቤቱ አዛውንት (አያት ነገር ይመስሉኛል) በድንገተኛ የልብ ህመም ራሳቸውን ይስቱና ቤተሰባቸው ተደግናጦ በብርሃን ፍጥነት ሆስፒታል ያደርሷቸዋል፡፡ እዚያም ሲደርሱ ጥብቅ የህክምና ክትትል (IC) የሚሰጥበት ክፍል እንዲገቡ ይደረጋሉ፡፡ (የፖለቲካ IC ቢኖር ጥሩ ነበር!) ከረዥም ሰዓት በኋላ የመረመራቸው ሐኪም ብቅ ይልና፤ “ሽማግሌው አዕምሮው ሞቷል፤ ልቡ ግን ይመታል” በማለት ለትልቁ ልጃቸው ይነግረዋል፡፡ (እንቆቅልሽ አይመስልም?) ልጅም፤ “እንዴ ዶ/ር፤ በቤተሰባችን ውስጥ እኮ አንድም የዲሞክራት ፓርቲ አባል ኖሮ አያውቅም!” አለው - ለዶክተሩ፡፡ (አያችሁልኝ የፈረንጅን ነገር ፍለጋ!) አዕምሮአቸው ሞቶባቸው ልባቸው የሚሰራ ዲሞክራቶች ናቸው ለማለት እኮ ነው፡፡
እስቲ ወደ ዋና አጀንዳችን ደግሞ እንግባ፡፡ እኔ የምላችሁ ግን… ኢቴቪ እዳውን ከፈለ እንዴ? (እዳችንን ማለቴ ነው!) ለምን መሰላችሁ የጠየቅኋችሁ? ኢቴቪ “አይለቀውም… አይለቀውም!” የሚል ነገር አባባሽ ቢያገኝ ኖሮ እኮ… የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎችን የማስተላለፍ ባለመብት ነኝ ከሚለው ተቋም ጋር ቡጢ መግጠሙ አይቀርም ነበር ብዬ ነው፡፡ ደግነቱ አላገኘም፡፡ በነገራችሁ ላይ ኢቴቪ ክፍያ ሳይፈፅም ጨዋታውን ሲያስተላልፍ “እጅ ከፍንጅ” መያዙን እንደ ትልቅ “ሼም” መቁጠር አለብን እንዴ? (ኢቴቪ እኮ ለህዝብ ጥቅም ብሎ ነው - እንደ ኢህአዴግ!) አንድ የህትመት ሚዲያ ላይ ደግሞ “ኢቴቪ የአገር ገፅታን አበላሸ” የሚል ወቀሳ ተሰንዝሮበት አንብቤአለሁ (So what? ራሱ የገነባውን ገፅታ፤ ራሱ አፈረሰ!) እኔ ግን የቲቪ ስክሪናችን ላይ ከመጣው “ሂሳብ አልተከፈለም” የሚል “አሳጭ ፅሁፍ” ይበልጥ የገረመኝ ራሱ ኢቴቪ በራሱ ሚዲያ የሰጠው በቁጣ የታጀበ “ዘለፋ” ነው (ካፈርኩ አይመልሰኝ ይሏል ይሄ ነው!) እናላችሁ… አንድ ምሽት በ2 ሰዓት ዜና ላይ ኢቴቪ ድንገት ንዴቱን አወረደው፡፡

በጠራራ ፀሃይ ተፈፀመ ላለው “ዝርፊያ” ተመጣጣኝ ምላሽ ሰጠ፡፡ አንዳንዶችም ለጠራራ ፀሃይ “ዝርፊያ” የጠራራ ፀሃይ “ዘለፋ” ሲሉ የኢቴቪን ጀግንነትና ወኔ አደነቁ፡፡ እንደኔ እንደኔ ግን ያልተገባ አድናቆት ነው፡፡ ለነገሩ ያኛውም ወገን (ባለመብቱን ማለቴ ነው) ትንሽ ሳያበዛው የቀረ አይመስለኝም! ስንት ሺ ዩሮ ነበር የጠየቀው? (ግድብ እየገነባን መሆኑን አያውቅም እንዴ?) ካላወቀም ጥፋተኛው ራሱ ኢቴቪ ነው የሚሆነው!!
ቆይ አንድ ነገር ልንገራችሁ፡፡ ኢቴቪ ያንን የውጭ ተቋም “ክፍያ አስወደድክብኝ” በሚል ዘራፍ ያለበት ወዶ አይደለም፤ ለምዶበት ነው (ማነው ልማድ ሲሰለጥን ተፈጥሮ ይሆናል ያለው?) አሃ… የጦቢያን ነጋዴ “ለሆዱ ያደረ”፣ “ስግብግብ” ምናምን እያለ መዝለፍ ለምዶበት እኮ ነው! ይሄውላችሁ ዋጋ (ክፍያ) ተወደደብኝ ያለ ወይም ደግሞ “ስንጥቅ ሊያተርፍብኝ ነው” ብሎ የጠረጠረ ደንበኛ፤ ምን ያደርጋል መሰላችሁ? ብስጭቱን ጓዳው ትቶ ለድርድር ይተጋል (ያለ አመሉ?) እናላችሁ… ኢቴቪ “ነቄ” ቢሆን ኖሮ “ውዱን ክፍያ” አስቀንሶ ያለአንዳች ብስጭትና ዘለፋ ሥራውን ይቀጥል ነበር (Business as usual ብሎ!) ድርድሩም ባይሳካም ደግሞ ችግር የለውም (የዓለም መጨረሻ እኮ አይደለም!) መቼም ዘለፋው የተሰነዘረበት ተቋም፤ ነገሩን ሰምቶት ከሆነ እንዴት ግራ እንደሚጋባ አስቡት፡ (እንቆቅልሽ ነው የሚሆንበት!)
አያችሁ… የአፍሪካን ዋንጫ ጨዋታዎች ለኢቴቪ ለማስተላለፍ ከ1ሺ ፐርሰንት በላይ የዋጋ ጭማሪ አድርጓል የተባለው ተቋም፤ Local (ኢትዮጵያዊ ማለቴ ነው) ቢሆን ኖሮ እኮ ችግር የለውም ነበር፡፡ (ገበና ለገበና እንተዋወቃለና!) ይኸኛው ግን ዓለም አቀፍ ተቋም ነው - Strictly በነፃ ገበያ መርህ የሚመራ!! (ነፃ ገበያና ዕዝ ኢኮኖሚን ማጣቀስ አያውቅም - እንደ ኢህአዴግ!) እናም በዋጋው የተስማማ ከፍሎ አገልግሎት ያገኛል፤ ያልተስማማ ይቀርበታል፡፡ (እጅ ጥምጠዛ እኮ የለም!) አያችሁ… ኢቴቪ እዚህ አገር ነጋዴ “ዋጋ አስወደደ” በሚል ወዶ እስከሚጠላ እንደሚብጠለጠል አሳምሮ ያውቃል! (ምን ማወቅ ብቻ?) እናም በአገር ውስጥ ልማድና ደንብ ዓለም አቀፍ ቢዝነስ ለማካሄድ ዳዳው፡፡ እኔማ “እንኳንም በዚህ አለፈልን!” አልኩኝ፡፡ እንዴ… ኢቴቪ ቢነሳበት ኖሮ እኮ ወዶ እስኪጠላ በማይሰማው ቋንቋ “ያስታጥቀው” ነበር - ያውም በተረትና በምሳሌያዊ አባባል የበለፀገ! “የኒዮሊበራል ቅጥረኛ!”፣ “ፀረ-አፍሪካ!”፣ “የኢምፔሪያሊዝም ግልገል” ወዘተ…ወዘተ ሊለው ይችል ነበር እኮ፡፡ (አንድዬ አተረፈና!) ትንሽ የቆጨኝ ግን ኢቴቪ ተቋሙን “ኪራይ ሰብሳቢ!” ሳይለው መቅረቱ ነው!! ትክክለኛ የኪራይ ሰብሳቢ ምሳሌ እኮ ይሄ ተቋም ነው (መብቱ ቢሆንም!)
እኔ የምላችሁ… ፅሁፌ መግቢያ ላይ ያቀረብኩትን የእንቆቅልሽ ጥያቄ ፈታችሁት? ይሄውላችሁ… በአገራችን ብዛታቸው እንደ ቆጣሪው ከፍና ዝቅ የሚሉት ምን መሰሏችሁ? የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው!! እንቆቅልሹ ግን የእኔ ፈጠራ እንዳይመስላችሁ! (ኮፒራይቱ የአንድ ቱባ ፖለቲከኛ ነው!) ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በመመስረት በሊ/መንበርነትና በፕሬዚዳንትነት ወደ ሁለት አስርት ዓመታት ገደማ የመሩት (ያውም ምክትላቸው ከነመኖራቸውም ሳይታወቁ) ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ናቸው ባለቤቱ! በቅርቡ በአገሪቱ ውስጥ ስንት ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳሉ ሲጠየቁ ምን አሉ መሰላችሁ? “እሱ እንደቆጣሪው ይለያያል!” (የአመቱ ምርጥ የፖለቲካ እንቆቅልሽ!)
“እውነት ግን የተቃዋሚዎች ብዛት ምን ያህል ነው?” ማነው የሚጠየቀው - ኢህአዴግ ነው ምርጫ ቦርድ? ሌላው ቢቀር እኮ መረጃው ለኢቴቪ ጥያቄና መልስ ይሆነናል፡፡ (ድንገት ከተጋበዝን ብዬ እኮ ነው!) ግን ለምንድነው በኢቴቪ የተቃዋሚዎች ጥያቄና መልስ የማይጀመረው? (ኢቴቪ የጋራ ንብረታችን ነው ብዬ እኮ ነው!)
የኢህአዴግ ፅ/ቤት ኃላፊ የተከበሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን በቅርቡ የሰጡት መግለጫ ተቃዋሚዎችን ጭስስ እንዳደረጋቸው ታዝባችሁልኛል? 28ቱ ፓርቲዎች ባለፈው ሳምንት በሰጡት ምላሽ ኢህአዴግ ነፍሴን “አግላይ!” ብለውታል (ብርቁ ነው እንዴ ማግለል!) እሱማ ይሄኔ እግሩን ዘርግቶ Mission Accomplished ይላል፡፡ እኔን ደግሞ “ጭስስ” የሚያደርገኝ ምን መሰላችሁ? የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማጠንጠኛው “ብሽሽቅ” መሆኑ ነው!
በነገራችሁ ላይ ፕሮፌሰር በየነ ስለተቃዋሚዎች ብዛት የሰጡትን እንቆቅልሻዊ መልስ የሚያጠናክር አባባል 28ቱ ፓርቲዎች በሰጡት መግለጫ ውስጥ አግኝቻለሁ፣ እንዲህ ይላል፡-
“ኢህአዴግ ለራሱ ፖለቲካዊ ጥቅም የሚበጀው ሲሆን 75 የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ይናገራል” የሚለው መግለጫው፤ ሲያሻው ደግሞ ተቃዋሚዎች ውስጣቸው መፈተሽ አለበት በማለት የምርጫ ቦርድን ሥልጣን ይወስዳል ሲል ኢህአዴግን ይኮንናል፡፡ (አቤት የእንቆቅልሻችን አበዛዝ!)

Saturday, 09 February 2013 11:55

እንጨዋወት

‘ሲስተም ፌይለር’…

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የካቲት ተጋመሰሳ! (“ገንዘብ መቁጠር ሲያቅትህ ወር ቁጠር…” ያልከኝ ወዳጄ…አሁን፣ አሁን እየገባኝ ነው!)
ስሙኝማ…ግራ እየገባን ያለ ነገር አለ፡፡ ይሄ ቴክኖሎጂ ምናምን የሚሉት ነገር..አለ አይደል ጥቅሙ ሥራን ማቅለልና መልክ ማስያዝ፣ የእኛንም መጉላላት ለማስቀረት አይደል እንዴ! ዓለም ስንት ሥራ እየሠራ ባለበት ሰዓት እኛ ሚጢጢዋ ነገር ሁሉ አቃተችን ማለት ነው!
የምር እኮ…ግራ እያጋባን ነው፡፡ “አገልግሎታችን ሁሉ ኮምፒዩተራይዝድ ሆኗል፣ ከእንግዲህ መጉላላት የለም…” ምናምን ተብሎ ደስ ሲለን ለአገልግሎት ስንሄድ ምን ይባላል መሰላችሁ…“ኮምፒዩተሩ አልሠራ አለ!” (ስሙኝማ…ይቺ አባባል ምን ትመስላለች መሰላችሁ…በቃ ልክ እርስ በእርስ ጣት መጠቋቆም እንደምንወደው ሁሉ ኮምፒዩተሩ ላይም ‘ጣታችንን የምንጠቁም’ ነው የሚመስለው፡፡ አልሠራ ያለው ኮምፒዩተሩ ነው እንጂ ኮምፒዩተሩን የሚያንቀሳቅሰው ወይም ሰው አይደለም፡ አሪፍ አይደል!)
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ ‘ሲስተም’ የሚሉት ነገር ልክ የሆነ ወርድና ስፋት ያለው እየመሰለን መጥቷል፡፡ አሁን፣ አሁን “ሲስተሙ አልሠራ አለ” የሚሉት ነገር ከአንዳንድ ለምድር ለሰማይ ከከበዱ መሥሪያ ቤቶች ስንሰማ…ግር የሚል ነገር አለ፡፡ መጀመሪያ ‘ሲስተሙ’ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት በቂ ሙከራ አልተደረገበትም ማለት ነው! ልክ ነዋ…ነገሮች “ባገኝ ባጣ…” አይነት ነገር እየሆኑብን ነዋ! በ“ባገኝ ባጣ…” አለ አይደል… ከሆነ ይሆናል ካልሆነ አይሆንም…‘ፉል ስቶፕ’!
‘ሲስተም’ ምናምን የሚባሉ ነገሮች ግን የራሳቸው የቀረጻ፣ የሙከራ፣ የማረጋጋጫ ምናምን ነገሮች አሏቸው አይደል እንዴ! እና አንድ ነገር ገና ከመጀመሩ “ሲስተም አልሠራ አለ…” ምናመን ነገር ሲባል…ቴክኖሎጂ ላይ እምነት እንድናጣ ነው የሚያደርገን፡፡ የመዘመናችን ነገር ከ‘ፌስ ቡክ’ አላልፍ ብሎ ግራ የገባን ነው የሚመስለው፡፡ (ስሙኝማ…እንዴት ነው አሪፍ የሆነው ነገር ሁሉ ወደ እኛ ሲመጣ የሆነ ጭራና ቀንድ የሚያበቅለው! አሁን ለምሳሌ ‘ፌስቡክ’ የሚሉትን ነገር…ካወቅንበት የሚገኝበት ዕውቀትና መረጃ በምንም ሊለካ የማይችል ነው፡፡ ሆኖም በ‘የፌስቡክ’ ገጽ የሚለጠፉትን ምስሎች፣ የሚጻፉትን መልእክቶች ምናምን ስታዩ የምር አስቸጋሪ ነው፡፡ አለ አይደል…“‘ደመ መራራነታችን’ ይሄን ያህል ጠልቆ በፌስቡክም ገባ እንዴ!” ምናምን የሚያሰኝ ነው፡፡) እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…‘ሲስተም’ የሚባለውን ነገር “ሀይ!” የሚልልን ይጥፋ! ልክ ነዋ… “እሰይ ስለቴ ሰመረ፣ ኑሮዬ ዘመነ” ምናምን ብለን ለመዝፈን ሲቃጣን ምን ይሆናል መሰላችሁ…‘ሲስተም ፌለር’ ይገጥማል! ስሙኝማ…አንዳንድ ጊዜ “‘ሲስተሙ’ም እንደ እኛ ክፉ፣ እንደ እኛ ‘ምቁ’ ሆነ እንዴ ምናምን ያሰኛል፡፡ የምር…ካነሳነው አይቀር… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ምን መሰላችሁ፣ ‘ደመ መራራነት’ በዛ፡፡ በዛው ልክ ክፋት በዛ፣ ምቁነት በዛ ጥላቻ በዛ!
ኮሚክ ነገር እኮ ነው…የእኛ የግለሰቦቹ ክፋት ‘ፍሬኑ ተበጥሶ’ ሲንደረደር...አንዳንዴ ክፋት የግለሰቦች ጉዳይ ብቻ መሆኑ ቀርቶ…አለ አይደል…የሆነ ‘ኦርጋናይዜሽናል ቻርት’ የተሠራለት ነው የሚመስለው፡፡ ክፋት፣ ምቀኝነት፣ ጥላቻ ምናምን የተባሉ ነገሮች…የሆነ በስርአት የተዋቀረ አይነት መልክ ያላቸው ሲመስል አስቸጋሪ ነው፡፡
ሀሳብ አለን…‘ኒኦ ክፋቲዝም ምናምን የሚባል የ‘ቦተሊካ’ ስርአት ተፈልስፎ በመጽሐፍ መልክ ይውጣልንማ! አሀ… የራሳችን ‘ዳስ ካፒታል’ የሚኖረን ደረጃ ላይ ደርሰናላ! (በነገራችን ላይ ‘ኒኦ—ክፋቲዝም’ የእኛንና የወዳጅ አገር ‘አፎች’ን በማገናኘት የተፈጠረ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…ያው በምግብ ‘ሚስቶ’ የምንለው አይነት መሆኑ ነው፡፡ ‘ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች’ አይነት ሚስቶ እንትኖች ኦፊሴላዊ እውቅና አላቸው አይደል፡፡) እናማ… ክፋት ይህን ያህል እየተዋሀደን መምጣቱ ካልቀረ አርማ ወጥቶለት፣ ‘ሲንግል’ ተለቆለት፣ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ ተመድቦለት (ቂ…ቂ…ቂ…) ‘መልክ’ ይውጣለትማ!
ደግሞ ሌላ እየበዛ የመጣ ነገር አለላችሁ…ስስት! የምር… በአጥር ተንጠልጥሎ “እከሊት፣ ከእራት የተረፈች ትንሽ ሹሮ ቢጤ አለችኝ፣ ነይ አባይኝማ…” ምናምን ማለት በአርኪዮሎጂስቶች ዋሻ ውስጥ በ‘አራሚክ’ ቋንቋ ተጽፎ ይገኝ እንደሁ እንጂ…እንኳን ልንሰማው “እንዲህ ይባል የነበረበትም ዘመን ነበር እንዴ!” የምንልበት ዘመን ደርሰናል፡፡ ልጄ…ዘንድሮ እንኳን “ሹሮ አባይኝ” ሊባል ቀርቶ…አለ አይደል…የሌላ ሰው ሹሮ ላይ ሁላችንም የይገባኛል ጥያቄ ያለን ነው የሚመስለው፡፡ ‘መስጠት’ የሚለው ቃል ሙሉ ለሙሉ ‘መውሰድ’ በሚለው ስለተተካ…ከ“እራት የተረፈች ሹሮ…” መጋበዝ “ሲያምርሽ ይቅር” የሚባል ነገር ሆኗል፡፡
እናላችሁ…ነገርዬው ሁሉ…አለ አይደል…“እንካ” ማለት እየቀረ “አምጣ” ማለት ብቻ እየገነነ የመጣ ይመስላል፡፡ የእኛ የግለሰቦቹን እንኳን ተዉትና…አንዳንዴ ከተለያዩ ክፍሎች የሚወጡ መመሪያዎች፣ ደንቦች ምናምን ላይ እንኳን ከጀርባቸው የሆነ “አምጣ” የሚል ጩኸት የገደል ማሚቶ ትሰማላችሁ፡፡ እናማ…“ይቺ ያው እንደተለመደው ለገንዘብ የወጣች ነች…” እያልን ማማታችን ከቁጥር ይግባልንማ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ጅብ ሆዬ እሜቲት አህያ የሆነ ነገር ተሸክማ ስትሄድ አይቶ ምን አላት አሉ መሰላችሁ…“አንቺም ሲሳይ፣ የተጫንሽው ሲሳይ…” ብሎ አረፈላችሁ፡፡ እናማ…አንዳንድ ጊዜ ጫና ሲበዛብን የተጫንነው ነገር ይኑርም አይኑርም…“አንቺም ሲሳይ፣ የተጫንሽው ሲሳይ…” የምንባል ይመስለናል፡፡
እናላችሁ…አሁን፣ አሁን አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ያለው የተገልጋይ ሰልፍ የካምቦሎጆውን የጊዮርጊስና ቡና ግጥሚያ ‘አርማጌዶን’ ሊያስንቅ እየተጠጋ ነው፡፡ እናማ…የከምፒዩተርም ይሁን የግለሰብ…‘ሲስተም’ የሚባለው ነገር “ሀይ” ይባልልንማ! ብዙ ነገሮች እየናፈቁን ነው፡፡ የምር…ዘወር እያልን ከጀርባችን የማናይበት ጊዜ እየናፈቀን ነው፡፡ የመሸበት መንገደኛ እግሩ ታጥቦ እንዲያድር የሚደረግበት አይነት መተማማን…አለ አይደል… ‘የድንጋይ ላይ ጽሁፍ’ እየሆነ በመጣበት ጊዜ የምናምነውና የሚያምነን ሰው እየናፈቀን ነው፡፡ “እንዲህ ያለ ዘመን ዘመነ ግርምቢጥ…” ምናምን እንደሚባለው ሁሉ…አይደለም ጓደኛ ጎረቤት ምናምን፣ የሥጋ ዘመድ ተሁኖ እንኳን መተማማን እየጠፋ ነው፡፡ እምነታችንን ጥለን “ይቺን ገንዘብ በአደራ አስቀምጭልኝ…” “ገበያ ደርሼ እስክመጣ ልጆቹን ጠብቅልኝ…” ምናምን የምንልበት ዘመን እየናፈቀን ነው፡፡
በፊት ጊዜ ገድገድ ሲያደርጋችሁ፣ ሲያደናቅፋችሁ “እኔን ይድፋኝ!” ምናምን የሚል የማታውቁት ሰው መአት ነበር፡፡ አዎ “ብታምኑም፣ ባታምኑም” እንደሚባለው……እንዲህ የሚባልበት ጊዜ ነበር! (ከዚህ በፊት እንዳወራነው…አለ አይደለ… “ነበር” የሚለው ቃል እየበዛ ሲሄድ አሪፍ ምልክት አይደለም፡፡) አሁን፣ አሁን ግን አይደለም የማታውቁት ሰው፣ የምታውቁት ‘ሹሮ ተበዳዳሪ’ እና ‘ቡና አጣጪ’ እንኳን ሲያደናቅፋችሁ… “ምን ያወላክፈዋል፣ እያየ አይሄድም!” ምናምን ነው የሚላችሁ፡፡ እናማ… እንደው ገድገድ ሲያደርገን እጁን ሰደድ አድርጎ “እኔን!” የሚል ህብረተሰብ ናፈቀን፡፡
ጓደኛሞች ናቸው፡፡ አንደኛው የሆነ ዕቃ ጓድኝየው ጋር በአደራ ለማስቀመጥና ላለማስቀመጥ ሲያመነታ ጓደኝየው ምን ይለዋል…“እመነኝ ሀሳብ አይግባህ፣ ዕቃውን በሚገባ እጠብቅልለሁ” ሲለው ያኛው ደግሞ “አይደለም አንተን የገዛ ወንድሜንም አላምንም…” ይለዋል፡፡ ጓደኝየው ምን ቢል ጥሩ ነው …“ልክ ነህ፣ እኔም የአንተን ወንድም አላምነውም፡፡” ከማይታመንና አደራ ከማይጣልበት ዘመድና ወዳጅ ይሰውረንማ!
በየመሥሪያ ቤቱ በር ላይ ፈገግ የሚሉ የጥበቃ ሠራተኞች ማየት ናፈቀንማ፡፡ “አቤት ጌታዬ ምን ልርዳዎት…” ማለት ቀርቶ ዱላውን እየወዘወዘ “ወዴት ነው፣ መግባት አይቻልም” የሚል የጥበቃ ሠራተኛ በዝቷል፡፡
ስሙኝማ…እንደ እኛና ቢጤዎቻችን ግራ የገባው ምስኪን ምን አለ አሉ መሰላችሁ…
ግንብ ላይ ብሠራ እባቡ መከራ፣
በዛፍ ላይ ብሠራ አሞራው መከራ፣
በምድር ላይ ብሠራ እረኛው መከራ፣
የት ውዬ የት አድር ብዬ፡፡
እናላችሁ…ብዙ ነገር እየተበላሸ ‘ሲስተም ፌይለር’ የሚሉት ነገር እግር ተወርች እያሠረን ስለሆነ “ሀይ!” ይባልልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

“የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ሁሉ ተባበሩ”
ካርል ማርክስ “የዓለም ሠራተኞች ተባበሩ፤ ከሰንሰለቱ በስተቀር የሚቀርባችሁ ነገር የለም ብሎ ነበር”፤ እኔም እላለሁ፤ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ሁሉ ተባበሩ፣ ከእስራት ሰንሰለቱ በስተቀር የሚቀርባችሁ ምንም ነገር የለም፡፡ (All Ethiopian oppositions Unite! You have nothing to lose but your chains) ማርክስን መጥቀሴ ማርክስሲት ሆኜ አይደለም፤ አባባሉ እውነትነት ያለው ሆኖ ስለአገኘሁት እንጂ! ለነገሩ ማርክስን በደንብ ሳያውቁ ማርክሲስትም ሆነ ፀረ-ማርክስሲት መሆን አይቻልም።
28 የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋ፣ ምርጫው ፍትሐዊና ገለልተኛ እንዲሆን ያቀረቧቸው ጥያቄዎች በአግባቡ ሳይመለሱ ወደ ምርጫው እንደማይገቡ በሙሉ ድምፅ ወስነዋል። ይህ ትብብር ቀጣይነት የሚኖረው ከሆነ በእውነቱ በጣም ታሪካዊ ሊባል የሚችል ነው። የዛሬው ጽሑፌ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ሆኖ በቀጣይ ቢደረጉ መልካም ነው ብዬ በማስባቸው ነገሮች ላይ የራሴን ሐሳብ ለመሰንዘር ነው።
ኻያ ስምንት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች “ምንም ውጤት በሌለው ምርጫ አንሳተፍም፣ የአገር ሀብትም በማባከኑ ወንጀል ላይ ተሳታፊ አንሆንም” ብለው ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸው በራሱ ትልቅ ነገር ነው።

በእኔ እይታ ከዚህ ረብ የለሽ የምርጫ ሂደት ራስን ማግለል ከሰላማዊ ዐመፅ - አልቦ ትግል አማራጮች አንዱ ነው - ከዐምባገነን መንግሥት ጋር አለመተባበር! ይህ በራሱ ግን በቀጣይ እርምጃዎች እስካልተደገፈ ድረስ ውጤቱ “ምንም” የውሳኔ አማራጭ ሊሆን ይችላል። ማርክስ “የፕሮግራም ጋጋታ ብቻውን ለውጥ አያመጣም” ብሏል።

ይህ ሐቅ አሁንም ይሠራል። ወደ ውጤት የማይቀየር ዘጠና ዐይነት ፕሮግራም መኖሩ ምንም አይፈይድም። ትግሉን ለማካሄድ መሠረታዊ በሆኑ ተጨባጭ አጀንዳዎች ላይ ብቻ ተመርኩዞ፣ ባለው ላይ እየተደመረ የሚሄድ የተመረጠ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መኖር አለበት። ወደ ምርጫ መግባት አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ተመራጭ የትግል ስልት አይደለም። ከዚህ አንጻር አሁን ወደ ምርጫ አለመግባቱ ቀዳሚው ተመራጭ ስልት ሆኖ ተገኝቷል ማለት ነው። ከዚህ በኋላስ ምን እናድርግ የሚል ጥያቄ መምጣቱ የሚጠበቅ ነው። በተስፋ መቁረጥ፣ አንገት ደፍቶ መቀመጥ “ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት ተሰልፈናል” ከሚሉ ኅይሎች የሚጠበቅ ነገር አይደለም። በዚህ ጊዜ ትክክለኛው አማራጭ የሚሆነው ሰላማዊ፣ ዐመፅ አልቦ ትግል ለማካሄድ መነሣት ነው።
ይህ ሰላማዊ፣ ዐመፅ አልቦ ትግል ጄን ሻርፕ “ከዐምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ” በሚለው መጽሐፉ ላይ እንዳስቀመጠው 198 ደረጃዎች አሉት። ሰሞኑን በጋራ በተደረሰበት ውሳኔ አንዱን ብቻ ነው በተወሰነ መልኩ የተጠቀምነው፤ ገና 197 ደረጃዎች ይቀራሉ ማለት ነው። እንግዲህ ተግቶ ደረጃ በደረጃ አንድ በአንድ መተግበር ያስፈልጋል።
ይህ ትግል ጥብቅ ዲሲፒሊን የሚጠይቅ፣ ነገሮች ባልታሰበ ኹኔታ ወደ ዐመፅና ብጥብጥ እንዳያመሩ መጠንቀቅን የግድ የሚል፣ ሐላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች ብቻ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ነው። እንደ ማኅተመ ጋንዲ ያለ የሞራል ልዕልና ያለው መሪ፣ እንደ ሕንዶች ያለ ሥርዐት ያለውና በአንድ ላይ ያለልዩነት የሚሰለፍ ሕዝብ መፈጠር ይኖርበታል። ይህ እንዲኾን ከተፈለገ በመጀመሪያ እንደ ሕዝብ ያሉብንን ልዩነቶች ለማጥበብና ለማመቻመች ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል።
ቀጥሎ መሠራት ያለበት ስለሰላማዊ ዐመፅ አልቦ ትግል በስፋትና በጥልቀት ማስተማር፣ ለዚህ መርሕ በተግባር መገዛት እንዲቻል ማለማመድ ያስፈልጋል። በዚህ ዙሪያ ሙስሊም ወንድሞቻችን እስካሁን እያሳዩት ያለው ሰላማዊ ተቃውሞ የሚደነቅ ነው። አገር በቀል የሰላማዊ ትግል ስልት በመሆኑ ለእኛ ጥሩ ትምህርትና ሞዴል ሊሆን የሚችል ነው። ይህ በራሱ የሚያሳየው ነገር አለ፤ ሕዝባችን በአግባቡ የሚመራውና አምኖ ሊከተለው የሚችል መሪ ድርጅት ካገኘ ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ አያዳግተውም።
እዚህ ላይ መሠመር ያለበት አንድ ዋና ነጥብ ግን አለ፤ ይህ ዐይነቱ የፖለቲካ ትግል እርስ በርስ ለስድብና ለዱላ የሚገባበዙ የፖለቲካ መሪዎች የሚመሩት ሊሆን አይችልም። በትምህርት ብዛት ወይም በፖለቲካው ብዙ ዘመን በማስቆጠርም አይደለም። “እገሌ ወደ ፓርላማ የገባው ኢሕአዴግ ስለደገፈው ነው፤ እገሌ ደግሞ የኢሕአዴግ ተለጣፊና ተቀላቢ ነው” እያሉ በማውራትና በማስወራትም የሚሳካ አይደለም። ተጨባጭ አጀንዳዎችና የፖለቲካ ስትራቴጂዎች ላይ የተመሠረተ፤ ሊታይ የሚችል ተጨባጭ እንቅስቃሴ ማድረግ ግድ የሚል ነው።
ትርጉም የሌለው ስብሰባ በየጊዜው በማካሄድም አይደለም። ስብሰባ በራሱ ቁም ነገር አስገኝቶ አያውቅም። ፖለቲካዊ ትግል ማካሄድ ማለት በየጊዜው ስብሰባ ማካሄድ ማለት አይደለምና። የፖለቲካ አመራሮቹ፣ ፖለቲካውን በተገቢው ሁኔታ ለመምራት ወገባቸውን ጠበቅ፣ ምራቃቸውን ዋጥ አድርገው መነሣት ይኖርባቸዋል።
ሕገ መንግሥቱን ለማስከበር በሚደረገው ትግል ሐላፊነት ወስደው ለመምራት፣ መታሰርም ካለ ለመታሰር ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል። “እኔ ሜዳ ሜዳውን ነው መታገል የምፈልገው እንጂ መታሰር እፈራለሁ” የሚል የፖለቲካ መሪ ካለ አቋሙን መመርመር፣ ካልኾነም ራሱን ከአሁኑ ከፖለቲካው ማግለል አለበት። ከዚህ በኋላ በፖለቲካው የሚኖሩና ለፖለቲካው የሚኖሩ ሰዎች መንገዳቸው አንድ ላይ መሆን የለበትም። ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ መንግሥት ባለበት አገር፣ ሕገ መንግሥቱን ለማስከበር መነሣት በራሱ ወንጀል ሆኖ እስር ቤት ሊያስወርድ እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም።
ራሳቸውን ከምርጫው ያገለሉት ፓርቲዎች ቀጣይ ርምጃ መሆን ያለበት፣ ሕዝቡን ሰብስቦ ማነጋገር ነው። በምርጫው ላይ ለመሳተፍ “የምርጫው ሜዳ ይስተካከል፣ ምርጫ ቦርድም ገለልተኛ ይሁን” ብለን የጠየቅነው ጥያቄ፣ የኢሕአዴግ መንግሥትና ምርጫ ቦርድ የዝሆን ጆሮ ሰጥተውታል። ይህ ጥያቄአችን ተቀባይነት አግኝቶ ተፈጻሚ እስኪኾን ድረስ ሕዝቡ ሰላማዊ ትግል እንዲያካሂድ መጥራትና መምራት ያስፈልጋል። ፓርቲዎቹ አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን ይዘው ሰልፍ መውጣት፣ አመራሮቹም ለተቃውሞ መንገድ ላይ ተኝቶ ማደርና መቀመጥ መጀመር ይኖርባቸዋል። ሕዝቡ የፓርቲዎቹን ቁርጠኝነት ሲገነዘብ በልበ ሙሉነት ለመደገፍ ይነሣል፤ መብቱን ለማስከበርም በጽናት መቆም ይጀምራል።
የፓርቲዎቹ አመራሮች እንዲህ በሚያደርጉበት ጊዜ ሊታሰሩ ስለሚችሉ ሌላ ተጠባበቂ አመራር ማዘጋጀት፣ እንደገና ያ አመራር ሲታሰር ደግሞ እንደዚሁ ሌላ እየተተካ ጥያቄው እስኪመለስ ድረስ መቀጠል ያስፈልጋል። አንድ እውነት አለ፤ ሁላችንም ለመታሰርና ለመሞት እስከተዘጋጀን ድረስ፣ ኢሕአዴግ ሁሉንም ማሰር፣ ሁሉንም መግደል ፈጽሞ አይችልም። እነ አንዷለም እና እነ በቀለ ገርባ የታሰሩት ሌሎቻችን ዝም በማለታችን ነው። ይህ ሥርዐት የመለወጡ ቁርጠኝነት በሁላችን ዘንድ እስከሌለ ድረስ በተወሰኑ ሰዎች ትግል ብቻ ለውጥ ይመጣል ማለት የዋህነት ነው።
ኢሕአዴግ ሁኔታዎች አስገድደውት ካልሆነ በስተቀር በእኩልነት ሜዳ፣ በገለልተኛ ዳኛ ሥር ሆኖ በምርጫ አይወዳደርም። በማያጠራጥር ሁኔታ ቢሸነፍም ሥልጣኑን በሰላም አያስረክብም። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ማለትም እኩል የመወዳደሪያ ሜዳና ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ በትክክል እስኪኖር ድረስ በምርጫ የመሳተፉ ጉዳይ መታሰብ የለበትም። በዚህ ጉዳይ ላይ ፓርቲዎቹ ቁርጠኛ አቋም ከያዙ ገዥው ፓርቲ በምርጫ ቦርድ በኩል “በምርጫ ስላልተሳተፋችሁ” ብሎ የፓርቲዎቹን ሕጋዊ ሰርተፊኬት ወደ መቀማቱ እንደሚገባ ምንም ጥርጥር የለውም።
በዚህ ጊዜም ቢሆን ትግሉ ወደ ህዝባዊ ንቅናቄ እንዲሸጋገር ተግቶ መሥራት እንጂ መደናገጥ አያስፈልግም። የግብጽ ሙስሊም ወንድማማች ፓርቲ ሕጋዊ ዕውቅናውን በሙባረክ መንግሥት በኩል ቢያጣም እውነተኛውን ህልውናውን ግን አላጣም ነበር። ሌላው ቀርቶ አባላቱ በግል እየተወዳደሩ የፓርላማውን አሥራ አምስት በመቶ መቀመጫ እስከመያዝ የደረሱበት ጊዜ ሁሉ ነበር።
ከዚህ የምንረዳው አንድ የፖለቲካ ፓርቲ የምስክር ወረቀቱ ሲቀማ የሚጠፋ ከሆነ ሲጀመር የፖለቲካ ፓርቲ አልነበረም ማለት ነው። የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ህልውና በጠንካራ ሕዝባዊ መሠረት ላይ እንጂ በሰርተፊኬት ላይ መቆም የለበትም። ስለዚህ ህልውናውን አላግባብ በሚያጣበት ወቅትም ቢሆን ትግሉ ባለው ሕዝባዊ መሠረት መቀጠል የሚችል፣ ከሰርተፊኬት በላይ የሆነ አቅም ያለው ኅይል መሆን መቻል ይኖርበታል። አንድ ፖለቲካዊ ፓርቲ ጽኑ ሕዝባዊ መሠረት፣ ጠንካራ አደረጃጀትና አመራር ከሌለው በስለላ፣ በጦር፣ በኢኮኖሚና በመዋቅር በደንብ የተደራጀን መንግሥት ማሸነፍና ሥርዐት መለወጥ አይችልም።
ከሁሉም በላይ በእኛ አገር ያለውን ተጨባጭ ፖለቲካዊ ሁኔታ በደንብ ማጤን ያስፈልጋል። የአገራችን ችግር የሥልጣን ጥያቄ ብቻ አይደለም። ትግሉ የርእዮተ ዓለም ትግል መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል። ሁለት አብረው ሊሄዱና ሊታረቁ የማይችሉ የአብዮታዊ ዴሞክራሲና የሊበራል ዴሞክራሲ ትግል ነው እየተካሄደ ያለው።
ኢሕአዴግ መሠረቱ ማርክስሲት ድርጅት ስለሆነ ይህን ቅራኔ በሚገባ ይረዳዋል። ዋናው ነጥብ ኢህአዴግ በትክክል በሁሉም ነገር እስካልተሸነፈ ድረስ በምርጫ ስለተሸነፈ ብቻ ሥልጣኑን ያስረክባል ማለት እንዳልሆነ በደንብ መታወቅ አለበት። ኢሕአዴግ ሁልጊዜ በምርጫ የሚወዳደረው እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ሆኖ ነው። እንደሚሸነፍ ቢያውቅ፣ ማወቅ ሳይሆን ቢጠረጥር እንኳ ወደ ምርጫ ውድድር አይገባም።
ስለዚህ ከገዢው ፓርቲ ጋር በምርጫ ለመወዳደር የሚቻለው በመጀመሪያ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ እንዲሁም እኩል የውድድር ሜዳ ሲፈጠር ብቻ ነው። ኢህአዴግ ይህን አምኖ እስኪቀበል ድረስ ግን ሰላማዊ ትግሉን ብቻ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል። ኢሕአዴግን ወደዚህ ደረጃ ሳያመጡ ከእርሱ ጋር በምርጫ መወዳደር እርሱን ከማጀብ፣ የእርሱን ድል ከማድመቅ ውጪ ትርጉም አይኖረውም። በማጀቡ ሂደት ከአሁን በፊት እንደታየው የተወሰኑ የተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጮችን ወደ ፓርላማ ማስገባት ይቻል ይሆናል። የሥርዐት ለውጥ ግን በዚህ መንገድ አይመጣም ፤ እስከአሁን የተጓዝንበት ልምድ የሚያሳየውም ይሄንኑ ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነጽሑፍ ትምህርት ክፍል ለረጅም አመታት በመምህርነት ያገለገሉት ዶ/ር ዮናስ አድማሱ በተወለዱ በ69 ዓመታቸው በትላንትናው ዕለት ከዚህ አለም በሞት ተለዩ፡፡
ህዳር 6 ቀን1935 ዓ.ም ከእናታቸው ከወ/ሮ ጌጤነሽ (ውባለ ጐንደር) ቸኮል እና ከአባታቸው ከቶ አድማሱ ሃዳስ ማርያም በአዲስ አበባ ደጃች ውቤ ሠፈር የተወለዱት ዶ/ር ዮናስብቻቸውን በሚኖሩበት ቤታቸው ውስጥ ህይወታቸው አልፎ እንደተገኙ ምንጮ ጠቁመዋል፡፡ ፖሊስ አስከሬኑን ለምርመራ ወደ ሆስፒታል ሊወስድ እንደወሰደ የጠቆሙ ምንጮች፤ የቀብር ስነስርአታቸው የሚፈፀምበት ቀን እንደተወሰነ ገልፀዋል፡፡

ትዳር ያልመሰረቱትና ልጆች የሌላቸው ዶ/ር ዮናስ፤ በቅርቡ በህይወት በሌለው በታናሽ ወንድማቸው በዶ/ር ዮሐንስ አድማሱ የተዘጋጀውን የዮፍታሔ ንጉሴ የህይወት ታሪክ ጥናታዊ ጽሑፍ አርመው በመጽሐፍ መልክ እንዲታተም በማድረግ ለምርቃቱ በመዘጋጀት ላይ እንደነበሩ ታውቋል፡፡ 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የታተመው መጽሐፉ፤ የካቲት 13 ቀን 2005 ዓ.ም ለምርቃት ስነስርዓቱ ቀጠሮ ተይዞለት እንደነበር ተገልጿል፡፡
በቋንቋና ስነጽሑፍ መምህርነታቸው የሚታወቁት ዶ/ር ዮናስ፤ ከ5 አመት እስከ 9 አመት ባለው የልጅነት ጊዜያቸው የቤተክህነት ትምህርትን፣ ከዚያም በኮከበ ጽብሃ የቀዳማዊ ሃይለስላሴ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
አጭር የመምህርነት ስልጠና ከወሰዱ በኋላም ለአንድ አመት በቀድሞ የወለጋ ክ/ሀገር በአንደኛ ደረጃ መምህርነት እንዳገለገሉ የህይወታ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
በኋላም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመግባት በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነጽሑፍ የትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በ1959 ዓ.ም አግኝተዋል፡፡ ከ1960 ጀምሮ ለአንድ ዓመት በዲፓርትመንቱ በመምህርነት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ በ1962 ዓ.ም የትምህርት እድል አግኝተው ወደ አሜሪካ በመጓዝ በሎስአንጀለስ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ድግሪያቸውን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ወስደዋል፡፡ ከዚያም ወደ ሃገር ውስጥ ተመልሰው በሙያቸው ማገልገል ቢጀምሩም በ1970 ዓ.ም በቀይ ሽብር ምክንያት በድጋሚ ተሠደው ወደ አሜሪካ በማቅናት እዚያው የዶክትሬት ድግሪ ትምህርታቸውን ተከታትለው ከደርግ ውድቀት በኋላ በ1988 ዓ.ም ወደ ሀገር ውስጥ በመመለስ እስከ ህልፈተ ጊዜያቸው ድረስ በመምህርነት ሲያገለግሉ መቆየታቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

 

ከአገራችን ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል፡፡ አንድ ቁራ የሚበላው አጥቶ ከቦታ ቦታ ይዘዋወራል፡፡ አየር ላይ ሲንከራተት አንድ አሞራ ያጋጥመዋል፡፡ አሞራ፤ “አያ ቁራ ወዴት እየሄድክ ነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ቁራም፤ “የምበላው ነገር ባገኝ ብዬ ብዙ ዞርኩኝ፤ ግን እስካሁን አላገኘሁም” ሲል ይመልሳል፡፡ አሞራ፤ “እዚያ ማዶ በሬ አርደው ቅርጫ ሲያደርጉ ተመልክቻለሁ፡፡ እሰቲ ሂድና አካባቢው ላይ አንዣብ፡፡” ቁራ፤ “እግዚሃር ይስጥህ ወደዚያው ሄጄ የእለት ጉርሴን ብፈልግ ይሻላል፡፡” ቁራ አንደተነገረው በሬ ወደታረደበት መንደር ይሄዳል፡፡ በአየር ላይ ሆኖ ያንቋርራል፡፡ ቅርጫ የሚካፈሉት ሰዎች ያዩትና ድንጋይ እያነሱ እየወረወሩ ያባርሩታል፡፡ ቁራው ይሸሽና ዞሮ ዞሮ መጥቶ ደሞ ዛፍ ላይ ያርፋል፡፡

ሰዎቹ ያዩትና በቅዝምዝም ዱላ ሊመቱት ያምዘገዝጉበታል፡፡ የድንጋይ እሩምታ ይለቁበታል፡፡ ሸሽቶ ወደ አየር ይበራል፡፡ ይሄኔ አሞራ ያገኘዋል፡፡ አሞራ፤ “አያ ቁራ ጠግበህ በላህ?” ይለዋል፡፡ ቁራ፤ “ምን እበላለሁ ሰዎቹ አይናቸውን እኔ ላይ ተክለው በየትኛውም መንገድ ብሞክር ድርሽ አላስደርግ አሉኝ!” አሞራ፤ “እንግዲያው እንዲህ እናድርግ፡፡ አንተ በድንጋይ ቢወረውሩ የማያገኙህ ቦታ ሁንና ጩህባቸው፡፡ አንተን ለመምታት ወዳንተ ዞረው ሲያተኩሩ እኔ አካባቢው ላይ አድፍጬ እቆይና በአሳቻ ሰዓት ደህናውን ብልት መንትፌ እሮጣለሁ፡፡

ከዚያ እንካፈላለን!” ቁራ በዚህ ይስማማና ከፍ ብሎ በአየር ላይ ሆኖ ጩኸቱን ያቀልጠዋል፡፡ አሞራ እንደገመተው ሰዎቹ እየተሯሯጡ ድንጋይም፣ እንጨትም፣ እያነሱ ወደ አየር እያጐኑ መከላከል ቀጠሉ፡፡ ትርምስ ሆነ፡፡ አሞራ ሆዬ አስቀድሞ በቅርጫው አቅራቢያ ሣር የሚግጡ በጐች ዘንድ ይመጣና አንዱ በግ ላይ አርፎ ድምፁን ፀጥ አድርጐ ይጠብቅ ኖሯል፡፡ በጉ መናገርም፤ ከላዬ ላይ ውረድም፤ ለማለት ባለመቻሉ ዝም ብሎ ሣሩን ይግጣል፡፡ አሞራ ትርምሱ በጣም የተጧጧፈበትን አሳቻ ሰዓት ጠብቆ እንዳለው አንዱን ደህና ሙዳ መንትፎ ክንፌ አውጪኝ ይላል፡፡ ቁራ አሁንም ጩኸቱን ቀጥሏል፡፡ አሞራ ወደማይደረስበት አቅጣጫ በረረ፡፡ ቁራ እንዳንቋረረ ቀረ! “ጩኸትን ለቁራ፣ መብልን ለአሞራ” ይሏል ይሄው ነው፡፡ *** የእለት ሳሩን አቀርቅሮ የሚግጥ በግ ሆኖ የአሞራ መቀመጫ ከመሆን ያድነን፡፡

ቀና ብለን ውረድ ለማለት የማንችለው፣ ገፍተን የማናባርረው፤ ሮጠን የማናመልጠው ባላጋራ፣ መረማመጃ ከመሆን ያውጣን፡፡ እንደ ቁራ ከመጮህ፣ እንደባለቅርጫ ህዝብ ሙዳችንን ከመመንተፍ ያትርፈን፡፡ ከሚዲያ ጩኸትና ዘራፌዋ፣ ከማይናከስ አንበሳ አበሳ፣ ሁኔታዎችን ሳያመዛዝን ጥልቅ ከሚል አድር - ባይ ይሰውረን፡፡ “ቅንዝንዝንና፣ የቀን ጐባጣን ስቀህ አሳልፈው፣ ቢያምርህ ሰው መሆን” የሚለውን የሻምበል ዮሐንስ አፈወርቅን ግጥም ልብ እንል ዘንድ ልብ ይስጠን፡፡ የሀገራችን የመማር ማስተማር ሂደት አሳሳቢ ነው፡፡ የራስ እድገት፣ ሀገራዊ እድገትና ሙያዊ እድገት ነው የመማር-መማማር አላማ፡፡ ይህ በእርግጥ እየሆነ ነወይ፤ ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ በተለይ የሳይንስ ነክና ሂሳብ ነክ ትምህርቶች ስምረት አስፈሪ ነው፡፡ በፍላጐት መመደብ ቅንጦት ከሆነ ሰንብቷል፡፡

የተማሪ ሁኔታ ተስፋ ያስቆረጠው መምህር ቁጥር ጥቂት አይባልም፡፡ ከናካቴው ማስተማሩን ለመተው ያኮበኮበው መምህር በቋፍ ያለ መሆኑን ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ “ዝናቡ የትጋ ስንደርስ ነው የመታን?” ብለን እንደ ቹኒአቸቤ የምንጠይቅበት ሰዓት ነው፡፡ ትምህርት አስቀያሚ የሆነው ከመቼ ጀምሮ ነው? በምን ምክንያት? የትውልድ መሰረት የሆነው ትምህርት ቅጥ ካጣ ነገ ምን መሳይ ሊሆን ነው? ብዛት ነው ጥራት የሚያዋጣን? (Academic excellence or mass production? እንዲል ፈረንጅ፡፡

በጌቶች የሚሠራ ወጥ ወይስ ለብዙሃኑ ታዳሚ የሚሰራ የድግስ ወጥ ነው የሚያዋጣን? እንደማለት ነው፡፡ ተምረን ምን ልንሆን ነው? የኮብል - ስቶን ትውልድ እያልን የምንሳለቀው እስከመቼ ነው? ተማሪና አስተማሪ አንድ ገበያ እየዋለ ምን አይነት ሥነምግባራዊ ግንኙነት ሊኖር ነው? የተማሪ አስተማሪ ግምገማ በት/ቤት አዋጣን ወይስ አላዋጣንም? ይሄ ሁሉ ሆኖ ዛሬ የት ደርሰናል? ሃይማኖትና ትምህርት ለየቅል አይደሉም ወይ? በቅን ልቦና ያልተወያየንባቸው ጥያቄዎች አቤት ብዛታቸው? ያም ሆኖ አሁንም አልመሸም፡፡ ብንወያይበትና እውነቱን ፍርጥ ብናደርገው ይበጀናል፡፡ ጥናት ቢቀርብበት ፍሬ እናገኝበታለን፡፡ አለበለዚያ ሥጋቱና ዋስትና ማጣቱ ይገድለናል! “ሰዎች ሁሉ ስጋትና ዋስትና - ማጣት አላቸው፡፡ በዚህ ዋስትና - ማጣታቸው ላይ ከተጫወትክ ታሸንፋለህ፡፡ ሆኖም ሥልጣንን በተመለከተ ሁሉም ነገር የደረጃ ጉዳይ ነው፡፡

በጣም ትልቅ ሥልጣን ያለው ሰዉ የበለጠ ዋስትና - ማጣት የሚሰማውና የባሰበት ሥጉ ሰው ነው፡፡ ስለዚህም ሌሎችን የሚያጠቃውና አደገኛ የሚሆንባቸው በበለጠና በከፋ ደረጃ ነው፡፡ ስለዚህ ከእንዲህ ያለው ሰው ጋር ስትጫወት ስስ ብልት አይተህ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ጥቂት ጥቃት እጅግ በጣም ይሰማዋል! ይህንን አትርሳ” ይለናል ሮበርት ግሪን፡፡ አሞራ፤ ቁራ መጮህ እንደሚቀናው አውቋልና እሱን እያስጮኸ ሙዳውን ይወስዳል፡፡ “የኛ ተግባር መማር መማር መማር!” የሚለውን አሮጌ መፈክር ባንዘነጋው መልካም ነው፡፡ከት/ቤትም መማር፣ ከኑሮም መማር ይጠብቅብናል፡፡ በመምረጥና በማጽደቅ መካከል ልዩነት መኖሩን እንማር፡፡ የኳስ ቲፎዞ በመሆንና የፖለቲካ ቲፎዞ መሆን መካከል ልዩነት መኖሩን እንማር፡፡ “ትላንትማ ቤትህ ደጃፍ ላይ እንቅፋት የመታህ ድንጋይ ዛሬም ከመታህ ድንጋዩ አንተ ነህ፤ የሚለውን የቻይኖች አባባል አንዘንጋ፡፡

በሀገራችን ብዙ ነገሮችን ለመተግበር ከጥናትና እቅድ ይልቅ በዘመቻ ማመናችን የቆየ ባህል ነው፡፡ የዘመቻ ሥራ ደግሞ ያንድ ሰሞን ሆይሆይታ ነው፡፡ ዘራፍ ይበዛዋል፡፡ ስለሆነም “የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ መሆኑ አይታበሌ ነው! ለሚዲያ ፍጆታ፣ አሊያም ለውጪ መንግሥታት ተቋማት ጆሮ-ገብነት ብለን በአንድ ወቅት እንደቁራ የምንጮኸውን ጩኸት፣ ነገ ደግመን የማንሰማው ከሆነ፤ የጊዜ፤ የሰው ኃይልና የአቅም ብክነት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ የምንጮኸውን ከልባችን እንጩህ! የምንሰራውን ከልባችን እንሥራ! ይሄን አቀድኩ ይሄን እስካሁን ፈፀምኩ ለማለት ብቻ የምንጣደፍበት ደርዝ-አልባ ጉዞ ከንቱ ነው፡፡ “በችኮላ ቅቤ ያንቃል፤ ቀስ በቀስ ድንጋይ ይዋጣል” የምንለው ያለነገር አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ÷ ካህናት እና ምእመናን ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባት ሊኾን ይገባል የሚሉትን ዕጩ በመጠቆም እንዲሳተፉ ጠየቀ፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው፣ ስለ ስድስተኛው ፓትርያሪክ የምርጫ ሂደትና የተመረጡት ፓትርያሪክ ስለሚሾሙበት ቀን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ካህናትና ምእመናን ግልጽ ለማድረግ ከትላንት በስቲያ በጽ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ ባስተላለፈው ጥሪ÷ በሀገር ውስጥ ያሉ ካህናት÷ አገልጋዮች መኾናቸውን፣ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ደግሞ የአጥቢያው ቤተ ክርስቲያን አባላት መኾናቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ በመያዝ በአስመራጭ ኮሚቴው ጽ/ቤት በአካል በመቅረብ፣ ከሀገር ውጭ የሚገኙትም በፋክስ ቁጥር 011 - 1567711 እና 011-1580540 ከየካቲት 1 - 8 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ዕጩአቸውን እንዲጠቁሙ ጠይቋል፡፡

አራት ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ሁለት የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎችን፣ ሁለት የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችን፣ አንድ የሰንበት ት/ቤት፣ አንድ የማኅበረ ቅዱሳንና ሦስት የምእመናን ተወካዮችን በአጠቃላይ 13 አስፈጻሚዎችን በአባልነት በያዘውና ታኅሣሥ 10 ቀን 2005 ዓ.ም በቅ/ሲኖዶስ በተቋቋመው አስመራጭ ኮሚቴ ወጥቶ በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ መጽደቁ በተገለጸው መሪ ዕቅድ እንደሚያመለክተው÷ የስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ሂደት የሚጀምረው ለአንድ ሱባኤ/ሳምንት በሚቆይ የጸሎት ጊዜ ነው፡፡ ከትላንት የካቲት 1 ቀን እስከ የካቲት 8 ቀን 2005 ዓ.ም በሚዘልቀው በዚህ የጸሎት ሱባኤ÷ ቤተ ክርስቲያኒቱ ቅን/ርቱዕ መሪ እንድታገኝ፣ እግዚአብሔር የወደደውንና የፈቀደውን በመንበሩ ያስቀምጥ ዘንድ ካህናቷና ምእመናንዋ አምላካቸውን በጸሎት እንዲማፀኑ በዐዋጅ ታዝዘዋል፡፡በምርጫው ለመሳተፍ የሚችሉት መራጮች÷ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች፣ የጥንታውያን ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት፣ ምእመናን፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ናቸው፡፡

ታኅሣሥ 8 ቀን 2005 ዓ.ም ቅ/ሲኖዶሱ ባጸደቀው የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ አንቀጽ 7 ንኡስ አንቀጽ 1 - 7 ላይ በተዘረዘረው የመራጮች ማንነት÷ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያና የድርጅት ሓላፊዎች፣ የየሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ በሀገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ ገዳማት አበምኔቶች፣ እመምኔቶች እና የታላላቅ አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ከየሀገረ ስብከቱ ሰበካ ጉባኤያት የተወከሉ አራት የካህናት፣ አራት የምእመናንና አራት የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች ጠቅላላ ብዛታቸው ከእያንዳንዱ ሀገረ ስብከት 12 ሰዎች፣ የመንፈሳዊ ኮሌጆች መምህራንና ተማሪዎች ተወካዮች ከየኮሌጆቹ ሁለት ሁለት ሰው፣ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ ዕውቅና የሰጠቻቸውና ከቤተ ክርስቲያኗ ጋራ አብረው በመሥራት ላይ የሚገኙ ማኅበራት ተወካዮች ከየማኅበራቱ አንድ አንድ ሰው እንደኾኑ ተደንግጓል፡፡

በዚህ ድንጋጌ መሠረት በስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ የሚሳተፉ መራጮች አጠቃላይ ቁጥር 800 ሲሆን ይህም ባለፉት አምስት ፓትርያሪኮች ከተሳተፉት መራጮች ብዛት ጋራ ሲነጻጸር ‹‹በእጅጉ የላቀ ነው›› ተብሏል፡፡ በሀገር ውስጥ በሚገኙት የ53ቱ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ሰብሳቢነት በሚመራ የአስተዳደር ጉባኤ ውሳኔ የሚለዩት መራጮች ዝርዝር እስከ የካቲት 16 ቀን ለአስመራጭ ኮሚቴው እንዲላክ፣ መራጮቹም እስከ የካቲት 19 ቀን 2005 ዓ.ም አዲስ አበባ እንዲገቡ መታዘዙን የኮሚቴው መግለጫ ጠቅሷል፡፡

በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ እንደተደነገገው፣ ምርጫው ታዛቢዎች ይኖሩታል፡፡ እኒህም÷ ከአራቱ አኀት አብያተ ክርስቲያናት (ግብጽ፣ አርመን፣ ሕንድ እና ሶርያ) ከእያንዳንዳቸው አንድ አንድ ሰው፣ ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር አንድ፣ ከአፍሪቃ አብያተ ክርስቲያናት ም/ቤት አንድ፣ በቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ከቤተ ክርስቲያኗ ምእመናን የሚመረጡ ታዋቂ የአገር ሽማግሌዎች ሦስት፣ በመንግሥት የሚወከሉ ሦስት ሰዎች እንደኾኑ ተገልጧል፡፡አስመራጭ ኮሚቴው እስከ የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ የዕጩዎች መመዘኛ መሠረት አጣርቶ ለምርጫ የሚያቀርባቸውን ዕጩ ፓትርያሪኮች ማሳወቅ ይጠበቅበታል፤ ለምርጫ የሚቀርቡት ዕጩዎች ብዛትም አምስት ነው፡፡

ለዕጩ ፓትርያሪክነት የሚጠቆመው ሊቀ ጳጳስ፣ ጳጳስ ወይም ኤጶስ ቆጶስ÷ ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ የኾነ፣ የውጭ አገር ዜግነት ካለውም የውጭ ዜግነቱን ሰርዞ ወደ ኢትዮጵያዊነቱ የተመለሰ፣ ዕድሜው ከ50 ዓመት ያላነሰ ከ70 ዓመት ያልበለጠ፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የአብነት ትምህርቶች ቢያንስ በአንድ ጉባኤ የተመረቀ ቢቻል ሁለገብ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ያለው ኾኖ ከከፍተኛ የመንፈሳዊ ትምህርት ተቋማት ወይም በዘመናዊ ትምህርት ቢያንስ ዲፕሎማ ወይም ዲግሪ ያለው፣ ሙሉ አካል ያለውና ጤንነቱ የተሟላ፣ የቤተ ክርስቲያኗ ቋንቋ የኾነውን ግእዝን የሚያውቅ ኾኖ ቢቻል ከዓለም አቀፍ ቋንቋዎች አንዱን የሚያውቅ፣ በቅድስና ሕይወቱና በግብረ ገብነቱ የተመሰገነ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በመፈጸም በቂ የአስተዳደር ችሎታና ልምድ ያለው መኾን እንደሚገባው በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ ላይ በሰፈረው መመዘኛ ተደንግጓል፡፡ ከአምስቱ ዕጩዎች መካከል ለዕጩ ፓትርያሪክነት ይኹንታ የሚሰጣቸውን አባቶች ለመወሰን የመጨረሻ ሥልጣን ያለው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ነው፡፡ ምልአተ ጉባኤው ከየካቲት 16 ቀን ጀምሮ ተሰብስቦ ከተወያየ በኋላ የካቲት 19 ቀን 2005 ዓ.ም አምስቱን ዕጩ ፓትርያሪኮች ለሕዝቡ ይፋ እንደሚያደርግ በኮሚቴው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል፡፡

የ፮ኛው ፓትርያሪክ ምርጫ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም እንደሚከናወን፣ ለፓትርያሪክነት የተመረጠው አባት በዓለ ሢመት ደግሞ የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም እንደሚፈጸም ኮሚቴው ያስታወቀ ሲኾን ምርጫው ኀሙስ፣ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ተካሂዶ በዚሁ ዕለት ከምሽቱ 12፡00 ላይ የተመረጠው አባት በብዙኀን መገናኛ አማካይነት ለሕዝብ ይፋ እንደሚኾን ገልጧል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ሲኖዶስ መመራት ከጀመረችበት ከ1951 ዓ.ም ወዲህ ስድስተኛ ፓትርያሪክ በመኾን ለመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሚመረጠው አባት ሹመት (በዓለ ሢመት) የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ኮሚቴው አስታውቋል፡፡ በዓለ ሢመተ ፕትርክናውም የሚከናወነው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያን መሪዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ካህናትና ምእመናን በተገኙበት እንደሚኾን በመግለጫው ላይ ተመልክቷል፡፡

አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) በማተሚያ ቤት ዕጦት ምክንያት ለተቋረጠው የፓርቲው ልሳን ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዝግጅቶች እና እርዳታዎችን አሰባስቦ የማተሚያ ማሽን ለመግዛት ማቀዱን አስታወቀ፡፡ ፓርቲው በትናንትናው ዕለት በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ለአንድ ዓመት ከሁለት ወር ያህል የመንግሥት በሆነው ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት እየታተመ በየሣምንቱ ማክሰኞ ለገበያ ይቀርብ የነበረውን “ፍኖተ ነፃነት” የተባለ የፓርቲው ጋዜጣ ወደ አንባቢው ለመመለስ በውጭ እና በአገር ውስጥ ከሚገኙ ደጋፊዎቹ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ ገንዘብ በማሰባሰብ አንድ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የማተሚያ ማሽን ለመግዛት አቅዷል፡፡

በዕለቱ የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እንደተናገሩት፤ በሕጋዊ መንገድ የተቋቋመ ማንኛውም ፓርቲ የራሱን ልሣን የማሳተም መብት እንዳለው ሕጉ ቢደነግግም፤ መንግሥት ማተሚያ ቤቶች ላይ በሚያደርገው የተለያዩ ጫናዎች ምክንያት በተፈጠረ ፍርሀት ጋዜጣ ብቻ ሳይሆን ደረሰኝ ማሳተም እንደተቸገሩ ተናግረዋል፡፡

በማተሚያ ቤት ዕጦትም ለአባላቱና ለኅብረተሰቡ መረጃ በመስጠት የሚገለገሉበትን ጋዜጣ ማተም እንደተቸገሩ ገልጸዋል፡፡ በማተሚያ ቤት ምክንያት ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ የተጣለውን እገዳ ለመታገል የማተሚያ ማሽኑን መግዛት እና የሕትመት ውጤቱን ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ነጋሶ፤ ከአስፈላጊነቱ ዓላማ በመነሳት የተለያዩ ጥናቶችን ሲያካሂዱ ቆይተው ማሽኑ ከአጋዥ መሣሪያዎቹ ጋር አንድ ሚሊዮን ብር እንደሚያወጣ እንደተረዱ ገልጸዋል፡፡

ማሽኑን ለመግዛት ከአቅራቢ ድርጅቶች ጋር መነጋገር መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህንን የፓርቲውን ዓላማ እና ፍላጎት ለማሳካት የሚደረገውን የገቢ ማሰባሰብ ፕሮጀክት ለማከናወን ሦስት ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን የገለፀው ‹‹የፍኖተ ነፃነት›› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነብዩ ኃይሉ ስለ ገቢ ማሰባሰቢያ እቅዱ እንዳብራሩት፤ መጽሐፍትን በመሸጥ፣ ከ30 ብር እስከ 1ሺሕ ብር ለሚለግሱ ኩፖን፣ ከተጠቀሰው ገንዘብ በላይ መለገስ ለሚፈልጉ የቃል ኪዳን ሰነድ መዘጋጀቱን እና ዓላማውን የሚደግፍ ማንኛውም ሰው በባንክ ሂሳብ ቁጥራቸው ገቢ ማድረግ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በኢንተርኔት ኦን ላይን ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚቀጥሉት አራት ወራት የገቢ ማሰባሰቡን ሥራ እንደሚቀጥሉ ጠቁሟል፡፡

ዶ/ር ነጋሶ በበኩላቸው፤ “ፍኖተ-ነፃነት” ለአባላቱና ለህብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግም ቢሆን ሃሳቡን ማስተላለፍ ከፈለገ ሊገለገልበት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ፓርቲዎች በማተም ሥራ ላይ ሲሠማሩ ቀረጥ መክፈል እንደሌለባቸውም በህጉ ማስቀመጡን ገልፀው፤ ማሽኑ የሌላ ሰው የህትመት ሥራ እንደማይሠራና “ከፍኖተ-ነፃነት” በተጨማሪም በኦሮምኛና በሌሎች የአገሪቱ ቋንቋዎች የሚሠራጩ የራሱን ኒውስሌተሮች የመስራት ሃሳብ እንዳለው ዶ/ሩ ገልፀዋል፡፡ የገቢ ማሰባሰቡ ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ አራት ወራት እንደሚቀጥልም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተያያዘ ዜና የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና የቋንቋ ምሑር ዶ/ር ኃይሉ አርአያ “ቋንቋና የቋንቋ ፖሊሲ” በሚል ርእስ ነገ ረፋድ ላይ በአንድነት ጽ/ቤት ጥናት እንደሚያቀርቡና ውይይት እንደሚካሄድ የተገለፀ ሲሆን ህብረተሰቡ በውይይቱ ተካፋይ እንዲሆን ግብዣ ቀርቧል፡፡

“... እንግዲህ የእናቶች ጤና ሲባል በቅድሚያ እናቶችን ለጉዳት የሚዳርጋቸው የእናቶቹ ወደ ሆስፒታል ያለመምጣት ችግር ነው፡፡ ይህ ምክንያቱ የተለያየ ሲሆን አሁን አሁን ግን መንግስት የጤና ኤክስንሽን ሰራተኞችን ለህብረተሰቡ ቅርብ በሆነ ሁኔታ እያሰማራ እና እናቶቹም ስለጤናቸው እንዲማሩ እየተደረገ ስለሆነ የተሻለ ነገር አለ ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን አሁንም ብዙ መስተካከል የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉ አይካድም፡፡ እናቶች ለህክምና ወደሆስፒታል ሲመጡም አገልግሎት የሚሰጥባቸው መሳሪያዎች በበቂ ሁኔታ መገኘት ይገባቸዋል፡፡ የህክምናው ባለሙያ ክህሎትና የመሳሰሉት ሁሉ የእናቶችን ጤንነት ለመጠበቅ አንዱም ሳይዛባ በተሟላ መንገድ መገኘት ይገባቸዋል፡፡ ... የጤና ባለሙያው በቂ የሆነ ችሎታ ኖሮት በበቂ መሳሪያ እየታገዘ ህክምናውን እንዲሰጥ ሁኔታዎች መሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ካልሆነ የእናቶች ወደሆስፒታል መምጣት አለመምጣት ምንም ልዩነት የለውም፡፡ ምናልባት ልዩነት ሊባል የሚችለው ወደሐኪም ሳይሄዱ ከእቤት መሞት ወይንም ሐኪም ቤት ሄዶ መሞት በሚል ሊገለጽ የሚችል ብቻ ነው...” ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ /የጽንስና ማህጸን ሕምና እስፔሻሊስት የእናቶችና ሕጻናትን ሞት በመቀነስ ረገድ የደብረማርቆስ ሆስፒታል ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር እየሰራ መሆኑን ዶ/ር አብነት ሲሳይ በደብረማርቆስ ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ገለጹ፡፡

እንደ ዶ/ር አብነት ገለጻ የደብረማርቆስ ሆስፒታል ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጋር ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ አይክ ኢትዮጵያ ከሚባል ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር የእናቶችን እና ሕጻናትን ጤንነት በሚመለከት ለሚሰራው ስራ ከተመረጡ ሁለት ሆስፒታሎች አንዱ ሆኖአል፡፡ ደብረማርቆስ ከአማራ ክልል ከትግራይ ደግሞ አድዋ ሆስፒታል ተመርጠው ከተወሰኑ ወራት ወዲህ ስራ የጀመሩ ሲሆን ከሕብረተሰቡ ጋር በተቀናጀ ሁኔታ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ ንቃተ ህሊናን የማዳበር ስራ ተሰርቶአል፡፡ በጤና ተቋም ወይንም ወደ ሆስፒታል በመቅረብ የሚወልዱ እናቶች ቁጥር 20ኀ የማይሞላ በመሆኑ ይበልጡኑ እናቶችን ለማዳን ወደ ህብረተሰቡ መውረድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቶአል፡፡ ወደህብረተሰቡ ለመድረስ ደግሞ የጤና ኤክስንሽን ሰራተኞች ዋናዎቹ ድልድዮች በመሆናቸው በደብረማርቆስ ዙሪያ ያሉትን ሙያተኞች ጠርተን የፕሮግራሙን አላማ ከማስረዳት ጀምሮ የጤና ኤክስንሽን ሰራተኞቹ እናቶችን ከጤና ኬላ ወደ ጤና ጣብያ እንዲያስተላልፉ ከዚያም ከፍ ወዳለ ሆስፒታል የመቀባበልን ሁኔታ በተቀናጀና ስርአት ባለው መንገድ እንዲሰራ አስፈላጊ መሆኑን እንዲገነዘቡ በማድረግ ስራው ተጀምሮአል፡፡

እናቶች ብዙውን ጊዜ በእርግዝና ጊዜ ክትትል ሲያደርጉ ቢቆዩም ለመውለድ ወደሆስፒታል ወይንም ክትትል ሲያደርጉ ወደቆዩበት ጤና ተቋም የሚሄዱት በጣም ጥቂቶች የመሆናቸው ጉዳይ አሳሳቢ በመሆኑ ይህንን ሁኔታ መልኩን በመቀየር እናቶች በወሊድ ጊዜ ወደሆስፒታል ለመሄድ የሚያስችላቸውን ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ የሚያስችላቸውን ዘዴ መምከር ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህንንም በተገቢው ለማስፈጸም እንዲያስችል ከኢሶግ እንዲሁም ከአይክ ጋር የሚሰራው ስራ የእርግዝና ክትትል ስታደርግ የቆየች እናት በመሀከል ብትሰወር ወደየት እንደደረሰች ፣ወልዳ ይሁን ወይንስ? በምን ምክንያት ? የሚለውን ለይቶ ማወቅና እናቶች ያሉበትን ሁኔታ በሚገባ ተረድተው ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ለማስቻል የሚደረግ ክትትልን ይጨምራል፡፡ የደብረማርቆስ ሆስፒታል ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጋር በመተባበር 5/ጤናጣቢያዎችን ባካተተ መልኩ የእናቶችንና የጨቅላዎችን ሞትና ደህንነት ሁኔታ በክትትል ይመዘግባል ፡፡ በዚህም መሰረት ከአንድ ወር በፊት ስለነበረው አሰራር በዶ/ር... ያለምወርቅ እንደቀረበው ሪፖርት ከሆነ በጤናጣቢያዎቹ ለሚኖረው አገልግሎት አንድ አምቡላንስ ተመድቦ አስፈላጊ በሆነበት ቦታና ሰአት እናቶችን ወደሆስፒታል ማመላለስ ተጀምሮአል፡፡ ሆስፒታሉ በየወሩ ከየጤናጣብያዎቹ ጋር በየወሩ በስብሰባ የሚገናኝ ሲሆን ችግሮችንም ከስር ከስሩ እየተከታተሉ መፍታት የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶአል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጤናጣብያዎቹ ለእናቶች ማበርከት ያለባቸውን አገልግሎት ጠንቅቀው እንዲያውቁና እንዲተገብሩ ለማስቻል ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በየወሩ በሚኖረው ዳሰሳ የእናቶችን እና ጨቅላዎችን ሞት በተመለከተ በማዋለጃ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በሆስፒታሉ በተለያዩ ክፍሎችም ያለው ሁኔታ በሪፖርት እንዲካተት ይደረጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የእናቶችንና ጨቅላዎችን ሞት በመመዝገቡ ረገድ በሆስፒታሎችና በጤና ጣቢያዎች ያለውን ብቻም ሳይሆን እናቶች በቤታቸው እንዳሉ የተከሰተ ነገርም ካለ በቀበሌና በኤክስንሽን ሰራተኞች አማካኝነት እንዲመዘገብ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶአል፡፡ በደብረማርቆስ ሆስፒታል እንደውጭው አቆጣጠር በኦክቶበር ወር 150/አንድ መቶ ሀምሳ እናቶች የወለዱ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ከጤና ጣብያዎች እስከ ሰማንያ ኪሎ ሜትር ከሚደርስ እርቀት በቅብብል የመጡና እራሳቸውም ወደ ሆስፒታሉ የመጡ ይገኙበታል፡፡ በአጠቃላይ ወደ 27 የሚሆኑ እናቶች ወደሞት አፋፍ ደርሰው የነበሩ ሲሆን ነገር ግን በሆስፒታሉ የተመዘገበ የእናቶች ሞት የለም፡፡ ለሞት አፋፍ እንዲደርሱ ከሚዳርጉዋቸው ምክንያቶችም አንዱ ደም መፍሰስ ሲሆን ሁለት እናቶች የማህጸን መተርተር የደረሰባቸው ናቸው፡፡ ሁለት እናቶች ደግሞ ከማህጸን ውጭ ያረገዙ ሲሆን ውርጃም የሚጠቀስ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ እናቶች ከወለዱ በሁዋላ የሚከሰት የደም መፍሰስ አብዛኛውን ለሞት አፋፍ የመድረስ ሁኔታ ማለትም 25 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ከእርግዝና ጋር ተያይዞ የሚከሰት የደም ግፊትም ያጋጠመ ሲሆን አስፈላጊውን ሕክምና በማግኘታቸው ከሞት ተርፈዋል፡፡ ከዚህ ውጭ የትራንስፖርት፣ የምግብ እጥረት እና የቤተሰብ እቅድ ዘዴን ባለመጠቀም ምክንያት እና ብዙ የወለዱ እናቶችም ለከፋ አደጋ ተጋልጠው ተገኝተዋል፡፡ ወደ ሀያ የሚሆኑ እናቶች በልጅነታቸው ግርዘት የተፈጸመባቸው ሲሆን በጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ምክንያት በምጥ ጊዜ ለሚከሰቱ ሕመሞች የተጋለጡም አሉ ፡፡

ለሞት አፋፍ የደረሱ እናቶች እድሜ ከ20-40 የሚደርሱ ሲሆኑ የልጅነት ጋብቻም ለችግር ከሚያጋልጡ መካከል ናቸው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ለመቅረፍም ህብረተሰቡን በማስተማሩ ረገድ በአቅራቢያው ያሉት የጤና ባለሙያዎች የበኩላቸውን ድርሻ ተወጥተዋል፡፡ በደብረማርቆስ ሆስፒታል የእናቶችን እና የጨቅላ ሕጻናትን ሞት ምክንያት ለማወቅ በሚደረገው አሰራር ያጋጠሙ ችግሮችን በሚመለከት የሕመምተኞች የቅብብል ሁኔታ አንዱ ሲሆን ሌላው የኤሌክትሪክ መስመር አለመኖር ነው፡፡ በማዋለድ ረገድ አንዳንድ ተጨማሪ መሳሪያዎች እንደቫኪዩም የመሳሰሉ ማለት ነው እጥረቱ እንዳለ ተገንዝበናል፡፡ ነገር ግን መፍትሔውን በሚመለከት አንዳንድ ጤና ጣቢያዎች ያለባቸውን የቅጽ እጥረት እራሳቸው በመፍጠር ተገቢውን መረጃ አያይዞ ወደሆስፒታል የመላክ አሰራር ተጀምሮአል፡፡ የኤሌትሪክ አገልግሎትንም በሚመለከት ለአንዳንድ ጤና ጣቢያዎች በቻርጀር የሚሰራ መብራት ለመስጠት ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡ የህክምና መርጃ መሳሪያዎችም በተቻለ መጠን በጎደለበት ቦታ እንዲሰጥ ሆስፒታሉ የራሱን መፍትሔ ዘርግቶአል፡፡ በአጠቃላይም ከጤናጣቢያዎቹ ጋር በወር አንድ ጊዜ አጠቃላይ ስብሰባ የሚደረግ ሲሆን በሆስፒታሉ ከሰራው ጋር የሚገኛኙት የሚመለከታቸው ባለሙያዎች በሙሉ ወደጤናጣቢያዎች እየወረዱ የጎደለውን ነገር የማየት ስራ እንዲሰራ ከስምምነት ተደርሶአል፡፡ ከሆስፒታሉ ጋር በትብብር የሚሰሩ ሳላይት ጤና ጣቢያዎችን በምን መንገድ ማጠናከር እንደሚገባ እና ያለውን ክፍተት ማሟላት እንዲሁም ምላሾችን በተገቢው በመመርመር አስፈላጊውን ማድረግ በሆስፒታሉ የተዋቀረው ቡድን ስራ መሆኑ የታመነበት ስለሆነ የእናቶችንና ጨቅላዎችን ሞት ምክንያት ከማወቅ አንጻር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ እሙን ነው እንደ ዶ/ር ያለምወርቅ፡፡

የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከአለምአቀፉ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጋር በመተባበር በሚያደርገው እገዛ በኢትዮጵያ ከ9/መንግስታዊ ሆስፒታሎችና 45/ ጤና ጣብያዎች ጋር በመተባበር የእናቶችን ሞት ሁኔታ ለማወቅ ለሚሰራው ስራ እንዲረዳ በየሆስፒታሎች መረጃ ለመሰብሰብ እንዲያስችል አንዳንድ ኮምፒዩተር ገዝቶ አከፋፍሎአል፡፡ ዶ/ር አብነት ሲሳይ ከደብረማርቆስ ሆስፒታል የኮምፒዩተሩን አገልግሎት ሲገልጹ ከአሁን ቀደም ባለው አሰራር የህመምተኞች ካርድ በአካል የሚቀመጥ ሲሆን ከቦታ ጥበት የተነሳ ከተወሰነ ጊዜ በሁዋላ እንዲቃጠል ይደረጋል፡፡ አሁን ግን ኮምፒዩተሩን በማግኘታችን ...ለምሳሌ የዛሬ ሶስት አመት አንዲት እናት ታክማ የነበረ እና ሐኪሙዋ በሌለበት እንደገና ለሕክምና ብትመለስ በኮምፒዩተር የተያዘ መረጃ ካለ በቀላሉ ችግርዋን ለመረዳት እና በወቅቱ ባለው ሐኪም ለመረዳት ትችላለች፡፡ ስለዚህ የህሙማኑን መረጃ በተሙዋላ መንገድ ለረጅም ጊዜ ለማስቀመጥ የሚረዳ በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡