Administrator

Administrator

የይሓ ቤተ መቅደስ አስደናቂ ቅርስ ነው። ከዚሁ አጠገብ ሌላ ሕንጻ በጥንት ዘመን ተገንብቶ እንደነበር የፍርስራሽ ምልክቶች ይጠቁማሉ። ነገር ግን፣ በቂ ምርምር ሳይካሄድበት እስከ 2009 ድረስ ቆይቷል።
ቀደም ሲል በተደረጉ አነስተኛ ጥናቶች አማካኝነት የተወሰኑ መረጃዎች መገኘታቸው ግን አልቀረም። እንዲያም ሆኖ፣ የይሓ ግንባታ በየመን አገር ከሚገኙ ጥንታዊ ሕንጻዎች ጋር ይመሳሰላል በማለት ነበር የቅርስነቱን ለመግለጽ የሚሞክሩት።
የይሓ ሕንጻ ግን ከተገመተው በላይ ሆኖ ነው የተገኘው። ባለፉት ዐሥር ዓመታት በተካሄዱ ጥናቶች አማካኝነት የተገኙ መረጃዎች… የይሓ ሕንጻ በግዝፈቱም በአሠራር ጥበቡም በዘመኑ አቻ እንዳልነበረው ያረጋግጣሉ ተብሏል።
ጥንታዊነቱም ከእስካሁኖቹ እንደሚቀድም ተጠቅሷል። ከ2800 ዓመት በፊት የተገነባ ነውና።
ምንም እንኳ የጥናቱ ውጥን፣ “ከየመን ጥንታዊ ሕንጻዎች የተኮረጀ” እንደሆነ በመገመት የተጀመረ ቢሆንም፣ በቁፋሮ የተገኙ የሕንጻው የግንባታ ቁሳቁስ ሲታዩ ግን፣ በዐይነታቸውና በመጠናቸው እንዲሁም በአሠራር ጥበባቸው እጅግ የላቁ ሆነው ተገኝተዋል።
እናም፣ የይሓ ሕንጻ የቅርስነት ክብር ከየመን ግንባታዎች ጋር ስለተዛመደ አይደለም ተብሎ ተነገረለት። ራሱን የቻለ ትልቅ ግኝት እንደሆነም ታመነበት።
የዚህን ግኝት ግዙፍነትና ጥንታዊነት ለመገንዘብ፣ ከዝነኛው የይሓ ቤተ መቅደስ ጋር በማነጻጸር ብናየው ሳይሻል አይቀርም።
በጥበብ የተራቀቀው የይሓ ቤተ መቅደስ!
የይሓ ቤተ መቅደስ የዛሬ 2500 ዓመት ገደማ የተገነባ ሳይሆን አይቀርም ተብሎ ነበር የተገመተው። አለምክንያት አይደለም። በየመን ከሚገኙ ተመሳሳይ ግንባታዎች በፊት የኢትዮጵያ ሊቀድም አይችልም ከሚል ሐሳብ ጋር ተያይዞ የመጣ ግምት ነው።
በደንብ ከተጠና በኋላ ግን፣ የሕንጻው ዕድሜ ከተገመተው በላይ እንደሆነ ታውቋል። የይሓ ቤተ መቅደስ 2800 ዓመት ያስቆጠረ ታሪከኛ ቅርስ እንደሆነ ታምኖበታል ብለዋል ታዋቂው የአፍሪካ የቅርስ ተመራማሪ ዴቪድ ፍሊፕሰን።
Epigraphic comparisons… suggested a date for the Great Temple no earlier than 500 BC, but more recent views on the chronology of southern Arabian epigraphy and architecture favour an age some three centuries earlier. (Foundations of an African Civilisation (AKSUM & THE NORTHERN HORN), David W. Phillipson, 2012. ገጽ 26)።
ታዲያ የኢትዮጵያ የሥልጣኔ ታሪክ እያደር ይደምቃል ቢባል ይበዛበታል?
18.6 ሜትር በ15 ሜትር ስፋት ያለውና በ14 ሜትር ቁመት የተገነባው ቤተ መቅደስ፣ በአምስት ምሶሶዎች ላይ የቆመ ደጀ ሰላም የተሰራለት ጥንታዊ ግንባታ ነው። ቤተ መቅደሱና ደጀ ሰላሙ፣ በጥበብ የተራቀቀ አስደናቂ የሥልጣኔ ቅርስ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም።
የቅርስ ተመራማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ መንገደኛ ተመልካቾችም የሕንጻውን ጥበብ በቀላሉ አይተው ሊመሰክሩ ይችላሉ። እጅግ በተራቀቀ ጥበብ እንደተገነባ  ከፍሊፕሰን አገላለጽ መረዳት ይቻላል። “built of large, extremely finely dressed, rectangular blocks  of silicified sandstone” በማለት ጽፈውለታል።
የይሓ ቤተ መቅደስ ያን ሁሉ ዘመን ተሻግሮ እስከ ዛሬ የዘለቀው በግንባታው ጥበብና በአናጺዎቹ የሙያ ልሕቀት እንደሆነ ሌሎች አጥኚዎችም ተናግረዋል።
እናም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ክብሩ እየተገለጠ በአድናቆት ሰማይ የነካው የይሓ ቤተ መቅደስ፣ ከአጠገቡ ሌላ ተፎካካሪ ቅርስ ይመጣለታል ወይም ይመጣበታል ተብሎ አልተገመተም ነበር።
ግን እንደተገመተው አልሆነም፤ ከተገመተው በላይ እንጂ።
ከአጠገቡ ሌላ አንጋፋ ቅርስ ተገኝቶለታል። “ግራት በዓል ገብሪ” ይሉታል - ቦታውን። ጥንታዊ ግዙፍ ሕንጻ ከ2800 ዓመት በፊት ተገንብቶ የነበረው እዚህ ቦታ ላይ ነው ብለዋል የቅርስ ተመራረማሪዎች።
ሕንጻው 60 ሜትር በ50 ሜትር ስፋት አለው። ባለደረጃ መድረክ ላይ የተሠራ ይመስላል።
መድረኩ የስድስት ሜትር ቁመት አለው። እዚያ ላይ ነው ሕንጻው የሚጀምረው።
ከፊት ለፊት የሕንጻው መግቢያ በስድስት ግዙፍ ምሶሶዎች ጸንቶ የቆመና ግርማ ሞገስን የተላበሰ ነው። ምሶሶዎቹ 10.5 ሜትር ርዝመት እንደነበራቸው አጥኚዎቹ ይገልጻሉ። ውፍረታቸው ደግሞ 85 ሴንቲሜትር በ95 ሴንቲሜትር ነው።
የአንዱ ምሶሶ ክብደት፣ ከ200 ኩንታል ይበልጣል።
የሕንጻው የግድግዳ ውፍረት 2 ሜትር ገደማ ነው።
የምሶሶዎች ትልቅነትና የግድግዳው ውፍረት ከህንጻው ግዙፍነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡ (Journal of Architectural Engineering Technology፣ Published: 29-May-2023፣ Volume 12 Issue 4፣ Preliminary Structural Analysis for the Archaeological Reconstruction of the Ancient Palace Grat Be’al Gibri in Yeha, Ethiopia)
በቁፋሮ የተገኙትን መረጃዎች የመረመሩ አንጥኚዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ ሕንጻው ከአምስት እስከ ዘጠኝ የሚደርስ ፎቅ ነበረው። የሕንጻው መልክና ቅርጽ ምን እንደሚመስል ለማሳየትም የምስል ንድፍ አቅርበዋል።  
ይህም ብቻ አይደለም።
የእስካሁኑ የቁፋሮ ግኝት አስደናቂ ቢሆንም፣ ያለ ቁፋሮ በማግኔቲክ ዘዴ በዙሪያው የተደረጉ የቅኝት ጥናቶች ደግሞ ሌላ ተጨማሪ መረጃ ይዘው መጥተዋል። በቁፋሮ የተገኘው ጥንታዊ የሥልጣኔ ቅርስ ቀላል ባይሆንም፣ ገና በቁፋሮ ያልተገለጠው ጥንታዊ ግንባታና ቅርስ እንደሚበልጥ ተመራማሪዎች ተናግረዋል። ለቁፋሮም ጓጉተዋል።
በእርግጥ የቁፋሮ ጥናት ለማካሄድ ገና ብዙ ውጣውረድ እንደሚኖር ያውቃሉ። አካባቢው ላይ የመኪና መንገድ ለመሥራትና የአውቶቡስ መነሃሪያ ለመገንባት እንደታሰበ ሰምተዋል።
ለእነዚህ ሥራዎች አማራጭ ቦታ ካልተገኘላቸው ለቅርሶች አደጋ ነው፤ ለምርምርም እንቅፋት ነው።
ሌላው ችግርስ ምንድነው?
ትልቁ ችግር ጦርነት ነው። በጀርመንና በኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች ከ2009 እስከ 2020 ሲካሄድ የነበረው ጥናት በጦርነት ምክንያት ለረዥም ጊዜ ተቋርጧል። በቅርቡ ወደ ጥናታቸው ለመመለስ እየሞከሩ እንደሆነ ቢገለጹም፣ ወደ ሥራ ለመመለስም ራሱን የቻለ ትንሽ “ጥናት” ማካሄድ፣ የቅድመ ዝግጅት “ሥራ” ማከናወን የግድ ነው።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ከጥንታዊ ሥልጣኔና ከአስደናቂ ቅርሶች ጋር ተያይዞ፣ ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት የምንሰማው ወሬ፣ ከጦርነት አደጋና ጦስ ጋር እየተዛመደ ነው። ከእንደዚህ ዐይነት የጦርነት አደጋና ጦስ ተገላግለን የምናየው መቼ ይሆን?
በሥዕል ያጌጡ የሃይማኖት መጻሕፍት በአባ ገሪማ ገዳም  
ከመቶ ዓመት በፊት የእንግሊዝ ሙዝዬም የቅርሶች የበላይ ጠባቂ የነበሩት ወሊስ በጅ፣ በዘመናቸው ከሚጠቀሱ የቅርስ ምሁራ መካከል ቀዳሚ ባለዝና ናቸው። ጥንታዊ የኢትዮጵያ ድርሳናትንና መዛግብትን ተርጉመው አሳትመዋል። የነገሥታት የዜና መዋዕል ድርሳናትን በማሰባሰብና በማጠናቀር በእንግሊዝኛ ሁለት ዳጎስ ያሉ መጻህፍት አበርክተዋል። ክብረነገሥት የተሠኘውንም መጽሐፍ ከግዕዝ ወደ እንግሊዝኛ ተርጉመዋል።
ሰውዬው እንዴት ጊዜ እንደሚበቃቸው ባይታወቅም፣ በጥንት በባቢሎን ቋንቋ የተጻፉ መዛግብትንም ተርጉመዋል። የባቢሎን ቅርሶችን የሚዳስስ መጽሐፍም አሳትመዋል። ምን ይሄ ብቻ!
የግብፅ ጥንታዊ ጽሑፎች በብዛት ወደ እንግሊዝኛ ተርጉመዋል፡፡ በጥንታዊ የግብፅ ሃይማኖትና እምነት ዙሪያ፣ በርካታ መጻሕፍትን ለንባብ አብቅተዋል።
እንዲያውም፣ የግብፅ ጥንታዊ ቋንቋና አጻጻፍ ላይ የመጀመሪያውን መዝገበ ቃላት አዘጋጅተው ለታሪክ ተመራማሪዎች አቅርበዋል - በ1500 ገጽ።
በአጠቃላይ፣ ከ25 በላይ ግዙፍ መጻሕፍት በወሊስ በጅ ተዘጋጅተው ታትመዋል።
የሆነ ሆኖ እኚሁ ዝነኛ የእንግሊዝ ሙዚዬም ኀላፊ የኢትዮጵያን ታሪክን በሚመለከት የዛሬ 95 ዓመት ባሳተሟቸው ሁለት መጻሕፍት ላይ፣ ጥንታዊ የግዕዝ ድርሳናትንና መዛግብትን እየዘረዘሩ አብራርተዋል።
በብራና ላይ የተጻፉ መዛግብት በዘመን ብዛት ከአገልግሎት ውጭ እንደሚሆኑ በመግለጽ፣ በዚህም ብዙ የኢትዮጵያ ቅርሶች ጠፍተዋል በማለት ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
እንዲያም ሆኖ እጅግ የሚያስደንቁና በጥበብ የተጻፉ የግዕዝ መጻሕፍት በየቦታው እየተገኙ የተመራማሪዎችን ቀልብ እንደማረኩ ወሊስ በጅ ገልጸዋል፡፡ በተለያዩ ገዳት ውስጥ የውጭ ሰው ያላያቸው በርካታ መጽህፍት እንደሚኖሩ አልጠራጠርም ሲሉም ጽፈዋል።በዚሁ አጋጣሚም ነው፣ በሥዕል ያጌጡ የሃይማኖት መጻሕፍት ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት።በግዕዝ የተጻፉና በሥዕል ያጌጡ የሃይማኖት መጻሕፍት (illuminated manuscripts)  በኢትዮጵያ መኖራቸውን ሲገልጹ፣ ከ16 ክፍለ ዘመን ወዲህ የአውሮፖ መጻሕፍትን በማየት እንደተጀመረ ተናግረዋል።
As soon as the Abyssinians became acquainted with the Portuguese and Italian missionaries in the 16th century they discovered the existence of illuminated Books… and in the 17th century the native scribes and artists began to decorate their manuscripts with coloured pictures.
በሥዕል ያጌጡ የሃይማኖት መጻሕፍት በኢትዮጵያ የተዘጋጁት ከ1500 ወዲህ ከአውሮፓውያን በመኮረጅ ነው ሲሉ ዕውቁ ተመራማሪ ግምታቸውን ቢናገሩ አይገርምም፡፡
 ሌላ አማራጭ አልታያቸውም፡፡ ነገር ግን፣ ግምታቸውን እንደ እርግጠኛ ዕውቀት የቆጠሩት ይመስላል፡፡
ለነገሩ፣ ለበርካታ ዓመታት ይህን ግምታዊ ድምዳሜ የሚያፈርስ የጥናት ግኝት ጎልቶና ጎልምሶ አልወጣም፡፡ የድምዳሜያቸው ግን ትክክል አልነበረም፡፡
ዋሊስ በጅ፣ ምንም እንኳ እጅግ ዐዋቂ የታሪክ ምሁር ቢሆኑም፣ እዚህ ላይ ተሳስተዋል።
በእርግጥ በጣም የሚያስወቅስ ስህተት አይደለም። በወቅቱ የተገኘውን መረጃ ነው የጻፉት፡፡ ከዚያ ወዲህ፣ ባለፉት መቶ ዓመታት በርካታ ጥናቶች ተካሂደዋል። ብዙ አዳዲስ መረጃዎች ተገኝተዋል።
በሥዕል ያጌጡ የሃይማኖት መጻሕፍት ጥንት ከ1500 ዓ.ም በፊትም በኢትዮጵያ ነበሩ። ይህን የሚያሳዩ ጥንታዊ ቅርሶች በምሁራ ዘንድ መጠቀስ የጀመሩት ባለፉት 60 ዓመታት ነው፡፡
አንዲት እንግሊዛዊ ተመራማሪ “የአባ ገሪማ ገዳም መነኮሳ ጥንታዊ የሃይማኖት መጻህፍት አስይተውኛል” ብለ መጻፏ ለለሎች አጥኚዎ በር ከፋች ሆኗል፡፡
የተመራማሪዋን ጥቆማ በመስማት የፈረንሳይና የእንግሊዝ ተመራማሪዎች በየፊናቸው መጥተዋል፡፡ በሥዕል ያጌጡ ጥንታዊ የሃይማኖት መጻህፍትን በፎቶና በማይክሮ ፊልም ሰንደዋል፡፡
በየበኩላቸው ባደረጉት ጥናትም፣ በሥዕል ያጌጡት የሃይማኖት መጻሕፍት በኢትዮጵያ የአንድ ሺ ዓመት ዕድሜ ሳይኖራቸው አይቀርም ሲሉ ተልጸዋል፡፡ የተመራማሪዎች ጥናት በዚህ አልተቋረጠም፡፡ የቅርሶቹን ዕድሜ በሳይንሳዊ ዘዴ በስሌት ለማረጋገጥ ናሙናዎችን ወስደው መርምረዋል፡፡
ነገር ግን፣ የምርመራዎቹ ውጤት ከጠበቁት ውጭ ስለሆነባቸው ለማመን በእጅጉ አመነቱ። እንደገና ተጨማሪ የናሙናዎች ጥናት ያካሂዱት የእንግሊዝ የኦክስፎርድ ተመራማሪዎች ናቸው፡፡ የጥናታቸው ውጤት ከቀድሞ ግምታቸው በእጅጉ የሚበልጥ ነው።
በግዕዝ የተጻፉና በሥዕል ያጌጡ የሃይማኖት መጻሕፍት በኢትዮጵያ ውስጥ ከአውሮፓ የሚቀድም ረዥም ታሪክ እንዳላቸው የተረጋገጠውም ይህን በመሰለ ረዥም የጥናት ምልልስ ነው።
በሥዕል ያጌጡ የሃይማኖት መጻሕፍት ከአውሮፓ የተኮረጁ አይደሉም። እንዲያውም፣ በአባ ገሪማ ገዳም የተገኙት በሥዕል ያጌጡ መጻሕፍት በጥንታዊነታቸው በመላው ዓለም ተወዳዳሪ የላቸውም ተብሏል።
በእርግጥ፣ እነዚህ የጥናት ግኝቶች ከመቶ ዓመት በፊት አይታወቁም ነበር። እናም ዝነኛው የእንግሊዝ ሙዝዬም የቅርሶች ዋና ኀላፊ፣ የዛሬ 95 ዓመት ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ የተሳሳተ ሐሳብ ቢያሳትሙ አይገርምም።ዋናው ነጥብ ግን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች ከገመቱትና ከጠበቁት በላይ ጥንታዊ ቅርሶች መገኘታቸውና ቅርስነታቸው እያደር የሚደምቅ መሆኑ ነው።


 
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሊቨርፑል ኖቲንግሃም ፎረስትን 1 ለ 0 ሲያሸንፍ ቼልሲ ከብሬንትፎርድ ጋር 2 አቻ ተለያይቷል፡፡
 
የሊጉ መሪ ሊቨርፑል በዋንጫ ፉክክሩ ላይ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ባገኘበት ጨዋታ ዳሪዊን ኑኔዝ ባለቀ ደቂቃ ቡድኑን አሸናፊ ማድረግ ያስቻለ ግብ አስቆጥሯል፡፡
 
በፕሪሚየር ሊጉ ምሽት 12 ሰዓት በተደረጉ ሌሎች ጨዋተዎች ቶተንሃም ክሪስታል ፓላስን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ፣ ኒውካስትል ዩናይትድ ዎልቭስን 3 ለ 0 ረትቷል፡፡

አንድ ታዋቂ የንጉሥ አጫዋች፤ የንጉሱ ባለሟሎች፣ መሣፍንቱና መኳንንቱ እንዲሁም ባለሌላ ማዕረግ ባለሥልጣናት በሚገኙበት፣ ከግብር በኋላ በሚካሄደው የመዝናኛ ሰዓት እንደ ሁልጊዜው ጨዋታ ያመጣል፡፡ ከመጠጡ ገፋ ተደርጎ የሚጠጣበት ሰዓት በመሆኑ ሳቁና ውካታውም ለከት የለውም፡፡ እንደልብ ይጮሃል፡፡ ከአፍ ለቀቅ ይባላል፡፡ ታዲያ ያ አጫዋች፣ በጥያቄ መልክ ነው ለዛሬ ቀልዱን ያቀረበው፡፡
አጫዋች፡- “ከዝቅተኛ መደብ ያለ ሰው ለምሳሌ ኩሊ፣ እንጨት - ፈላጭ፣ መንገድ - ጠራጊ ወዘተ ሲሰክር ምን ይባላል?” አንዱ ባለሟል ይመልሳል፡- “ጢምቢራው ዞረ! ተንጀባረረ ነዋ የሚባለው” ሁሉም ሳቀ፡፡
አጫዋች፡- “ትክክል ነው፡፡ እሺ፤ በመካከለኛው መደብ ያለ ሰው፤ ለምሳሌ ዝቅተኛ የመንግስት ሰራተኛ፣ ትናንሽ ነጋዴ፣ ወታደር ወዘተ ሲሰክር ምን ይባላል?”
አንዱ ይመልሳል፡- “ጣጥ አለ! ጢዝ አለ! ድብን አለ!” ይባላል አለ፡፡ ሁሉም ሳቁ፡፡
አጫዋቹም፡- “በትክክል ተመልሷል!” አለና ወደ ጥያቄው አመራ፡፡ “እሺ የመካከለኛው መደብ አባላት እንደ መካከለኛ ነጋዴ፣ መኮንኖች፣ የመ/ቤት የቢሮ ኃላፊዎች፣ ምሁራን ሲሰክሩስ ምን ይባላሉ?”
አንድ ትልቅ ሰው ይነሱና ይመልሳሉ፡- “ሙክክ ብሏል! እሳት ገብቶታል! እንግሊዝ ይደባልቃል!” አሉ፡፡
አጫዋቹም፡- “በትክክል ተመልሷል!” አለና ወደሚቀጥለው ጥያቄ ሄደ፡፡ “እሺ የከፍተኛው መደብ አባላት ማለትም መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ፣ ሚኒስትሮቹ፣ ስመ-ጥሮቹ ነጋዴዎቹ ወዘተ ሲሰክሩ ምን ይባላሉ?”
ከመኳንንቱ አንዱ ተነሱና መለሱ፡- “ሞቅ ብሏቸዋል! ጨዋታ ጨዋታ ብሏቸዋል! ትንሽ ወሰድ አድርገዋል! ትንሽ መሸት አድርገው ነበር!” ይባላል አሉና ተቀመጡ፡፡ ሁሉም ሳቁ፡፡
አጫዋቹ፡- “ብራቮ! በትክክል ተመልሷል!  ወደ መጨረሻው ጥያቄ እንሄዳለን፡፡ ንጉሱ ሲሰክሩስ ምን ይባላሉ?”
ሁሉም ፀጥ አሉ፡፡ እጅ የሚያወጣ ሰው ጠፋ፡፡ “ሞክሩ! ሰዓት አላችሁ” ቢል ትንፍሽ የሚል ጠፋ፡፡ ስለዚህም አጫዋቹ፤
“እሺ፤ እኔ እራሴ እመልሰዋለሁ” አለና “ንጉሡ ሲሰክሩ ‘አልጠጡም፤ ግን ደስ ብሏቸዋል’ ነው የሚባለው” አለ፡፡ ሰው በሳቅ ሞተ፡፡
ንጉሡ ስለድፍረቱ ተናደው አጋፋሪው ፀጥታ እንዲያስከብር አዘዙ፡፡
ንጉሥ፡- “አሁን ላጠፋኸው ጥፋት የማያወላዳ ቅጣት ያስፈልግሃል!”
አጫዋች፡- “ምን አጠፋሁ ንጉሥ ሆይ?”
ንጉሥ፡- “አስቀህብኛል!”
አጫዋች፡- “የሳቁት የእርስዎ ሰዎች’ኮ ናቸው፣ የተሰበሰበው ህዝብ’ኮ ነው፤ ንጉሥ ሆይ?!”
ንጉሡ የባሰውን ስለተናደዱ ግንባራቸው ላይ ያሉ ስሮቻቸው ሁሉ እንደቀንድ ቆሙ፡፡ ማንም ያልገመተው ፍርድም ፈረዱ፡፡
“1ኛ ስለ አጫዋቼ - አሁን ላጠፋኸው ጥፋት ሞት ተፈርዶብሃል፡፡ ሆኖም የምትሞትበትን መንገድ የመምረጥ እድል ሰጥቼሃለሁ!
2ኛ የሳቃችሁ ባለሟሎቼና ሹማምንቶቼ በሙሉ፤ የንብረታችሁን አንድ አራተኛ ለእኔ ገቢ ታደርጋላችሁ!
አሁን አጫዋቼ፤ የምትመርጠውን አሟሟት ተናገር” አሉ፡፡ አጫዋቹም ተነስቶ፤
“ንጉሥ ሆይ፤ እኔ የምመርጠው አሟሟት አርጅቶ መሞትን ነው!”
ንጉሡ ከት ብለው ስቀው “የመረጥከው የሞት አይነት ተፈቅዶልሃል!” አሉትና ወደ መኳንንቱና መሳፍንቱ ሲዞሩ፤ ሁሉም ደንግጠውና አኩርፈው ቆመዋል፡፡ ንጉሡም “በዚህ በአሁኑ ቀልድ ከእኔ ጋር ባለመሳቃችሁ የንብረታችሁ ሩብ ይወረሳል ብዬ ፈርጄ የነበረው ተሻሽሎ ግማሽ ንብረታችሁን እንድትሰጡኝ ፈርጃለሁ!”
ሁሉም ለጥ ብለው እጅ ነሱ - አጫዋቹም ጭምር፡፡
***
ቢስቁበት የሚቆጣ፣ ቢስቁለትም የሚቆጣ ንጉሥ፣ የበላይ ኃላፊ፣ የፖለቲካ መሪ ወይም ግለሰብ አይጣል ነው፡፡ ከእኔ ጋር ካሳቅህ ትቀጣለህ፤ በራስህ ከሳቅህም ትቀጣለህ የሚል ደግሞ የበለጠ የከፋ ነው፡፡ ከቅኝቴና ከዜማዬ ውጪ የዘፈነ ወዮለት እንደማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለ ፍርሃት በዳመነበት አካባቢ ልባዊ አስተያየት፣ ግልፅነት፣ ሀቀኛ ግምገማ፣ እውነተኛ ሪፖርት አይኖርም፡፡ ስቆ መጠራጠር፣ አልቅሶም መጠራጠር ይበዛልና፡፡ የበላይን ፈገግታ እያዩ መሳቅ አብዛኛው ማግጠጥ ነው! ራስን መሆን ያቅታል፡፡ በየትኛዋ ደቂቃ ከወንበሬ እነሳ ይሆን እያሉ መወያየት ከምንጩ የዲሞክራሲ አካለ - ጎደሎ ነው! ፍርሃት፣ ቂም፣ ተንኮል፣ ሤራ፣ አስቀድሞ - ፍርድ (prejudice) ባለበት ዲሞክራሲ አይኖርም፡፡ ዲሞክራሲ ከሌለ ደግሞ እውነተኛ ሰላም፣ እውነተኛ ፍትህ፣ እውነተኛ ልማት ማምጣት እጅግ ሩቅ ህልም ነው፡፡
ከንጉሡ ጋር የሚስቁ ምሁራንና ባለሟሎች፣ ከአለቃ ጋር የሚስቁ የበታች ኃላፊዎችና ምንዝሮች፡- ለጊዜው በአርጩሜነት ቢያገለግሉ እንጂ አገርን ከጥፋት፣ ኢኮኖሚን ከድቀት፣ ህዝብን ከመራቆት አያድኑም፡፡ ይልቁንም ራሳቸው በተሻለ አርጩሜ የሚቀጡበት ቀን ሊመጣ እንደሚችል ከላይ ካነበብነው የአጫዋቹ ታሪክ ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡
 ማጫፈርና ማሟሟቅ ተስፋን አያመላክትም፡፡ መጠፋፋትን እንጂ ተደጋግፎ ማደግን አይጠቁምም፡፡ “በደህናው የማይጠቅም ሞቶ በህልም ይታያል” እንደሚባለው ካለፉ በኋላ ነበሩ ማለት ብቻ ይሆናል ትርፉ፡፡ ህዝብ ወይም ባለሟሉ ሲስቅ የሚስቅ ንጉሥ ወይም ባለስልጣን ማግኘት መታደል ነው፡፡ በእርግጥም በብዛት አያጋጥምም፡፡ አገራችን ለአቻ ሥራ አቻ ሰው (The Right Man at the Right Place) ዛሬም የተሳካላት አይመስልም፡፡ የሹም ሽር መብዛት፣ የእሥር መበርከት፣ የውይይት አለመቀጠል፣ የእቅዶች የአንድ ሰሞን ሞቅ ሞቅ ሆኖ መቅረት፣ የተወሰኑ ውሳኔዎ በቀላጤ መሻር፣ ባለሙያን አለማክበር፣ የበኩር ልጅን ምን ሰራህ አለማለት፣ የእንጀራ ልጅን የሰራውን አለማመስገን፣ ራስ ሳይጠና ጉተና ማሳደግ፣ ህዝቡን ለመለወጥ ከመጣር ይልቅ የራስን መንገድ ጥርጊያውን ማሳመር ወዘተ ሁሉ የሚያሳዩት ለአቻ ሥራ አቻ ሰው ማጣትን ነው፡፡ አለመታደልን ነው፡፡ “የምትኖር ሚስትና የሚያኖር ባል አንድ ገበያ እየዋሉ አይገኛኙም” እንደሚባለው ነው፡፡ እንዲህ ባለው ሰውና ሙያ ባልተገናኙበት አገር እበላ-ባዩ፣ አጫዋቹ፣ አንጓቹና አንጋቹ ይበዛል፡፡ በሥራ ከማገዝ ይልቅ በወሬ ማናቆር ይበረክታል፡፡ በእሾም ይሆናል ተስፋ ለራስም ለወገንም የማይበጅ የሲስቁ ልሳቅ ጥረት ይበዛል፡፡ “በጥገኝነት” እና በአድር - ባይነት “እኔ መንገዱን ላሳይ እችላለሁ” የሚሉ አብሪዎች አያሌ ይሆናሉ፡፡ ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ የሆኑት መንታ መንታ ይፈለፈላሉ፡፡ ይህም “ጥርስ የሌላት፣ ጥርስ ያላትን ነክሳ፣ አነካከስ ታስተምራለች” የሚለውን ተረት ያስታውሰናል፡፡ ዞሮ ዞሮ “የእናት ዓለም ጠኑ”ው ገራፊ ገብረየስ እንዳለው፤
“እድሜ ለእኔ፣ እኔ 40 ስገርፍ እያየ ከአንድ እስከ አርባ ቁጥር ተማረ!” መባሉ አይቀርምና አለመታደል ነው!
እንኳን ለ128ኛው የአድዋ ድል በዓል አደረሰን!!

Saturday, 02 March 2024 21:00

አ ድ ዋ 1 2 8

የፌደራል መንግስትና  የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ አደራዳሪዎች በተገኙበት   በቀጣይ ሳምንታት  በፕሪቶርያው ስምምነት ዙሪያ ዳግም ለውይይት ሊቀመጡ ነው ተባለ።  የካቲት 18 እና 19 ቀን 2016 ዓ.ም  የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ  መሰብሰቡንና የተለያዩ ውሳኔዎች ማሳለፉን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ረዳኢ ሀለፎም ከትግራይ ቴሊቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል። ካቢኔው ባካሄደው ስብሰባ፣ የአስተዳደሩን ስራዎች ለመስራት አስቸጋሪ የነበሩ መመሪያዎችን ማሻሻሉን ጠቁመዋል። በሁለቱ ወገኖች መካከል በፕሪቶርያ የተደረገው  ስምምነት ባለመተግበሩ ሣቢያ  የክልሉ ህዝብ ላይ የሚደርሰው መከራና ስቃይ ሊቆም አልቻለም ያሉት  የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ረዳኢ ሀለፎም፤  የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከፌደራል መንግስቱና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በስምምነቱ አፈጻጸም ዙሪያ በተደጋጋሚ መምከሩን ገልጸዋል።
በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ አደራዳሪ አካላት በተገኙበት በፌደራል መንግስትና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል በቀጣይ ሳምንታት ውይይት እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።
የአፍሪካ ህብረት፣ የመንግስታቱ ድርጅት፣ የአሜሪካንና የደቡብ አፍሪካ መንግስታት ተወካዮች ተሳታፊ የሚሆኑበት የፕሪቶርያውን ውል አፈጻጸም የተመለከተ ውይይት ለማካሄድ ቀጠሮ መያዙን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የካቲት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መናገራቸው ይታወሳል።

የፒያሳ ነዋሪዎች በ3 ወራት ጊዜ ውስጥ አካባቢውን እንዲለቁ ተነግሯቸዋል

በአዲስ አበባ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ፣ የፒያሳና አራት ኪሎ ነዋሪዎች ለልማት ከመኖሪያቸው እንደሚነሱ የክፍለ ከተማው አስተዳደር  ገልጿል።
አስተዳደሩ  በማህበራዊ ትስስር ገፁ ላይ እንዳስታወቀው፤ ሁለቱን አካባቢዎች መልሶ በማልማትና ነዋሪዎችን በማስነሳት ዙሪያ ሰሞኑን  ከነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርጓል። ውይይቱ፣ በንግድ የሚተዳደሩ ነዋሪዎች ንግዳቸውን በሚቀጥሉበትና ሌሎች ነዋሪዎች በመልሶ ማልማቱ ዕቅድ በሚስተናገዱበት ኹኔታ ላይ ያተኮረ ነበር ተብሏል።
ነዋሪዎችን ለልማት የማንሳቱን ሂደት የሚከታተል ከአመራሩና ከነዋሪዎች የተውጣጣ ኮሚቴም እንደተዋቀረ ተገልጧል። በተለይ የፒያሳ ነዋሪዎች በሦስት ወራት ውስጥ አካባቢውን እንዲለቁ እንደተነገራቸው ምንጮች ጠቁመዋል። ነባር ነዋሪዎቹን የማስነሣቱ ስራ በሦስት ወራት ውስጥ ተጠናቆ የግንባታ ስራው ይጀመራል ተብሏል።በተያያዘ ዜናም፣ ከቀበና እስከ አራት ኪሎ  እንዲሁም  ፒያሳ ደጎል አደባባይ ድረስ  የመንገድ ኮሪደር ግንባታ ሥራው ሠሞኑን  ተጀምሯል፡፡
 የከተማ አስተዳደሩ  ካቢኔ የካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው የ3ኛ ዓመት 8ኛ መደበኛ ጉባኤ፣ ግንባታቸው እንዲጀመር ውሳኔ ካስተላለፈባቸው አምስት  የከተማዋ የመንገድ ኮሪደሮች መካከል በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኘውና  ከቀበና አደባባይ - አራት ኪሎ - ፒያሳ ደጎል አደባባይ ኮሪደር አንዱ ነው።
 የመንገድ ኮሪደር  ግንባታው በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገባ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የአራት ኪሎው  ባለፈው ረቡዕ  ተጀምሯል፡፡

የግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ቦሩ ”የሥራ መልቀቂያ አስገቡ“ በሚል የተሰራጨው መረጃ ሃሰተኛ መሆኑን የባንኩ ባለድርሻ አካላት ገለጹ፡፡

የግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ቦሩ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን የሚገልጹ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች መሰራጨታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሆኖም  መረጃው ሙሉ በሙሉ ሃሰተኛ ነው ብለዋል - ለባንኩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት የሥራ መልቀቂያ አስገቡ በሚል የተሰራጨው ሃሰተኛ መረጃ የባንኩን ጥቅም እንደሚጎዳ የጠቆሙት የባንኩ ባለድርሻ አካላት፤ ሃሰተኛ መረጃውን ያሰራጩ ማህበራዊ ሚዲያዎችንና ግለሰቦችን በህግ እንደሚጠይቁ አመልክተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ  አዲሱ ገበያ ሸገር መናፈሻ አካባቢ የተገነባውና  ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የግንባታ ወጪ  ተደርጎበታል የተባለው  ናሁሰናይ ኢንተርናሽናል ሆቴል፤ ከነገ ወዲያ  ቅዳሜ የካቲት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ይመረቃል።

የሆቴሉ ባለቤቶች አቶ እሱባለው ናሁሰናይና  ባለቤታቸው ወ/ሮ ሒሩት ምህረቴ እንዲሁም የሆቴሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ካሳሁን በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ሆቴሉ  ደረጃውን የጠበቀ፣ ምቹ ስፍራ ላይ የተገነባና ለደንበኞቹ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችል መልኩ የተደራጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሆቴሉ  46 የመኝታ ክፍሎች  ያሉት ሲሆን፤ እንግዶች ምግባቸውን እዚያው እያበሰሉ የሚመገቡበት የተሟላና የተደራጀ የገስት ሃውስ ክፍሎችንም ያካተተ ነው። አገልግሎቱንም  ከአካባቢው አንፃር ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ለማቅረብ  በሚያስችል መልኩ መደራጀቱ ተጠቁሟል፡፡

የሆቴሉ ግንባታ  ሦስት ዓመታትን  እንደፈጀ የተገለፀ ሲሆን፤ ናሁሰናይ ኢንተርናሽናል ሆቴል ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምር ከ70 እስከ 100 ለሚሆኑ  ሠራተኞች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተነግሯል፡፡

ሆቴሉ  ከነገ ወዲያ ቅዳሜ  የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት እንደሚመረቅ ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ከተማ  አዲሱ ገበያ ሸገር መናፈሻ አካባቢ የተገነባውና  ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የግንባታ ወጪ  ተደርጎበታል የተባለው  ናሁሰናይ ኢንተርናሽናል ሆቴል፤ ከነገ ወዲያ  ቅዳሜ የካቲት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ይመረቃል።

የሆቴሉ ባለቤቶች አቶ እሱባለው ናሁሰናይና  ባለቤታቸው ወ/ሮ ሒሩት ምህረቴ እንዲሁም የሆቴሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ካሳሁን በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ሆቴሉ  ደረጃውን የጠበቀ፣ ምቹ ስፍራ ላይ የተገነባና ለደንበኞቹ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችል መልኩ የተደራጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሆቴሉ  46 የመኝታ ክፍሎች  ያሉት ሲሆን፤ እንግዶች ምግባቸውን እዚያው እያበሰሉ የሚመገቡበት የተሟላና የተደራጀ የገስት ሃውስ ክፍሎችንም ያካተተ ነው። አገልግሎቱንም  ከአካባቢው አንፃር ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ለማቅረብ  በሚያስችል መልኩ መደራጀቱ ተጠቁሟል፡፡

የሆቴሉ ግንባታ  ሦስት ዓመታትን  እንደፈጀ የተገለፀ ሲሆን፤ ናሁሰናይ ኢንተርናሽናል ሆቴል ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምር ከ70 እስከ 100 ለሚሆኑ  ሠራተኞች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተነግሯል፡፡

ሆቴሉ  ከነገ ወዲያ ቅዳሜ  የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት እንደሚመረቅ ተገልጿል።