Administrator

Administrator

የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት፣ በፑንትላንድ ዋና ከተማ ጋሮዌ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ እንዲዘጋ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ እንደማትቀበል ፑንትላንድ አስታወቀች።
የሶማሊያ  መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ እየገባ ነው በሚል በሞቃዲሾ የኢትዮጵያ አምባሳደር አገሪቱን ለቀው እንዲወጡና በከፊል ራስ ገዟ ፑንትላንድና ነጻነቷን ባወጀችው ሶማሊላንድ ያሉት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እንዲዘጉ ማዘዙን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡  
ከጎረቤት አገር ኢትዮጵያ፣ ነጻ አገር ነኝ ከምትለው ሶማሊላንድና በከፊል ራስ ገዝ ከሆነችው ፑንትላንድ ጋር ፖለቲካዊ እሰጣ ገባው ውስጥ የገባው የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት፣ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ሦስቱን መንግሥታት የተመለከተ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል። የፑንትላንድ አስተዳዳር ትላንት ዓርብ መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጠው መግለጫ ቆንስላው እንዲዘጋ የተላለፈው ትዕዛዝ፣ የሶማሊያን ሕገ-መንግሥት የሚጥስ ነው በማለት ተግባራዊ እንደማይደረግ አስታውቋል።
የፕሬዚዳንት  ሐሰን ሼክ ሙሐመድ አስተዳደር የኢትዮጵያው አምባሳደር ሙክታር ከድር ዋሬ፣ በ72 ሰዓታት ከአገር እንዲወጡ ትዕዛዝ ከማስተላለፉ በተጨማሪ፣ አዲስ አበባ በሐርጌሳና ጋሮዌ ያላት ቆንስላዎች በአንድ ሳምንት ውስጥ እንዲዘጉ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ይሁን እንጂ የሶማሊላንድና ፑንትላንድ በሚኒስትር ደረጃ ያሉ መሪዎች የፌደራል መንግሥቱ ውሳኔን እንደማይቀበሉ ተናግረው ነበር። ከዚህ በተጨማሪም የሶማሊያ መንግሥት በአዲስ አበባ የሚገኙትን አምባሳደሩን “ለአጠቃላይ ምክክር” ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ ማዘዙን የሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።
የሶማሊያ መንግሥት በመግለጫው፤ ኢትዮጵያ “በሶማሊያ ሉዓላዊነትና የውስጥ ጉዳይ” ጣልቃ ገብታለች ሲል ከሷል። ኢትዮጵያ ታኅሣሥ 2016 ዓ.ም. ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር ጠረፍ ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት መፈረሟ ሞቃዲሾን ያስቆጣ ሲሆን፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኑነትም አጠልሽቶት ቆይቷል።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ደግሞ የሶማሊያ መንግሥት ያደረገውን የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ በመቃወም ከፊል ራስ ገዝ የሆነችው ፑንትላንድ ለፌደራል መንግሥቱ እውቅና መስጠት አቁሚያለሁ ብላለች።
ይህ የፑንትላንድ ውሳኔ በሶማሊያ ፖለቲካ ውጥረት ፈጥሮ ባለበት ወቅት የፑንትላንድ የገንዘብ ሚኒስትር ባለፈወው  ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ለጉብኝት አዲስ አበባ ገብተው ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጋር መወያየታቸው ሶማሊያን አስቆጥቷል፡፡
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አሁን የኢትዮጵያን ዲፕሎማት ለማባረርና የቆንስላ ጽህፈት ቤቶቿ እንዲዘጉ ከውሳኔ ላይ የደረሰው የገንዘብ ሚኒስትሩን ጉብኝት ተከትሎ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
የፑንትላንድ አስተዳደር መንግሥት ትላንት ዓርብ  ባወጣው መግለጫ፤ የሶማሊያን ውሳኔ እንደሚቃወም ገልጾ፤ ፑንትላንድ የውጭ ፍላጎቷን ለማስጠበቅ ከማዕከላዊው የሶማሊያ መንግሥት እውቅና ውጪ በቀጥታ በራሷ አማካይነት ግንኙነቶችን እንደምታደርግም ጨምራ ገልጻለች።

ባሮክ ኤቨንት ኦርጋናይዘር አ.ማ፣ ከሚያዚያ 10 እስከ ሚያዚያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ  የፋሲካ  ባዛርና ኤክስፖ በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡

ለ20 ቀናት ገደማ ክፍት የሚሆነው ባዛርና ኤክስፖ፤ ሸማቹ በተመጣጣኝና ቅናሽ ዋጋ ከራሱ ከአምራቹና አስመጪው የሚገበያይበት ነው የተባለ ሲሆን፤ አምራቹም ከሸማቹ ከፍተኛ ገበያ የሚያገኝበት እንደሚሆን ተነግሯል፡፡

ከ2ሺ በላይ አስመጪና ሻጮች እንደሚሳተፉበት በተነገረለት በዚህ ባዛርና ኤክስፖ፤ በቀን እስከ 10ሺ የሚደርሱ ሸማቾች ይጎበኙታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዚህ ባዛርና ኤክስፖ ከዓውዳመት ሸቀጦች በተጨማሪ፣ በየቀኑ ታዋቂ ሙዚቀኞች፣ ተወዳጅ ሥራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡

የፋሲካ ባዛርና ኤክስፖ የፊታችን ሚያዚያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ባለሃብቶች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት በይፋ ይከፈታል ተብሏል፡፡

የደራሲ እያዩ ደባስ ሦስተኛ መጽሐፍ “ፓርታ” ለንባብ የበቃ ሲሆን፤ ደራሲው በመግቢያው ላይ እንዳሰፈረው፤ “ፓርታ ላልተጻፈው የሐሳብ ዕዳ ክፍያ ይሆን ዘንድ ነው። እነርሱን የመሆን የሐሳብ ዕዳ ውስጥ ለገባ አንድ አሳቢ፣ ሰውን ነጻ የማውጣት የቀናነት ትግል ነው።

መጽሐፉ የትችት፣ የመወቃቀስ፣ የሐሜትና የጥላቻ ግብ የለውም። ከሐሳብነት የተረፈ የመቆሚያ ሥፍራም የለው፤ ብሏል ደራሲው።

የዚህ መጽሐፍ ዋና ገጸ-ባሕርይ “ሐሳብ” መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፤ደራሲው የእድሜ ዘመን ንባብ ያላቸውን ታዋቂ ግለሰቦችን ገጸ ባህሪ አድርጎ በማምጣት፣ለሃሳብ የበረታ ድርሰት ከትቧል፡፡
 
“ፓርታ” በ273 ገጾችና 68 ምዕራፎች የተቀነበበ መጽሐፍ ሲሆን አሳታሚና አከፋፋዩ ጃዕፈር መጻሕፍት መደብር ነው ተብሏል፡፡ መጽሐፉ  በ400 ብር ለአንባቢያን ቀርቧል።

•  የመጀመሪያውን ዙር የመኪና ርክክብ አድርገዋል

አሚጎስ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበርና ኢትዮፒካር፣. የኤሌክትሪክ መኪኖችን በብድር ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ዛሬ ጠዋት መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም  የፈፀሙ ሲሆን፤ የብድር መስፈርቱን ላሟሉ ሰባት የ“ምሰሶ የታክሲ ማህበር” አባላት የመኪና ርክክብ አድርገዋል።

ስምምነቱን የፈፀሙት የአሚጎስ ም/ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ይልማና የኢትዮፒካር ባለቤት አቶ ሳሙኤል አዲስዓለም  ናቸው።

በስምምነቱ መሰረት፣ የ"ሆን ዞ" አውቶ ፋክተሪ የኢትዮጵያና ምስራቅ አፍሪካ ብቸኛ ወኪል የሆነው ኢትዮፒካር፣ የአሚጎስ አባላት የሚፈልጓቸውን የኤሌክትሪክ መኪኖች ምቹና ቀልጣፋ በሆነ መልኩ በብድር እንደሚያቀርብ ታውቋል፡፡

 ኢትዮጵያ እንደ ሃገር የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ብሎም የአየር ንብረትን ለመጠበቅ ይረዳ ዘንድ የኤሌክትሪክ መኪናን እንደ አማራጭ የመጠቀም ፖሊሲን እየተገበረች ሲሆን፤ በሃገራችን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ፍላጎትም እያደገ መምጣቱ ተነግሯል፡፡

የአለማችን ተጠቃሽ የኤሌክትሪክ መኪኖች አምራች የሆነው የ"ሆን ዞን" አውቶ ፋክተሪ የኢትዮጵያና ምስራቅ አፍሪካ ብቸኛ ወኪል ኢትዮፒካር ብራንድ፣ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት ለተጠቃሚዎች እያቀረበ ይገኛል፡፡

የዜጎችን ኑሮ ባማከለ መልኩ በባንክ ብድር አማራጭ የሚቀርቡት እነዚህ የኤሌክትሪክ መኪኖች፣ የፋብሪካ ዋስትና እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን፤ድርጅቱ መኪኖቹን መቶ በመቶ በብድር ብቻ ለተጠቃሚዎች ለማቅረብም እየሰራ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡

• ለመጀመሪያ ጊዜ በኦንላይን የተመዘገበ ሰርተፊኬት ተሰጥቷል
የአዲስ አበባ ሌጀንድ ኢንተርናሽናል ፕሮ ቴኳንዶ አሶሴሽን፤ የ2016 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹን የ3ኛ ደረጃ የዳኝነት ሥልጠናና ዓለማቀፍ የፕሮ ቴኳንዶ የመጀመሪያ ራስን መከላከል ስልጠና ተሳታፊዎች ትላንት መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም በወወክማ አዳራሽ አስመረቀ፡፡
ሥልጠናው ከአዲስ አበባና ከክልሎች ለተውጣጡ 28 ተሳታፊዎች ለ15 ቀናት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፤ ተመራቂዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦንላይን የተመዘገበ ሰርተፊኬት ማግኘታቸው ታውቋል፡፡
 
ከሰልጣኞቹ መካከል 19 ያህሉ ሥልጠናውን በተሟላ መልኩ አልፈዋል የተባለ ሲሆን ሁለቱ አለማለፋቸው ነው የተነገረው፡፡
በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ እንደተነገረው፤ ሳኦል ኹነቶች ለአራት ሰልጣኞች የስፖርት ማዘውተሪያ አዳራሽ ያመቻቸ ሲሆን፤ በቅርቡ ፒያሳ አካባቢ በኮሪደር ልማት ሳቢያ የስፖርት ማዘውተሪያ ለፈረሰበት አንድ ወጣት በቀጣይ ቦታ ለማመቻችት ቃል ተገብቶለታል።
የአዲስ አበባ ሌጀንድ ኢንተርናሽናል ፕሮ ቴኳንዶ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት ማስተር ሃይለየሱስ ፍስሃ በመርሐግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ የተሰጠው 3ኛ ደረጃ የዳኝነት ሥልጠና፣ ሌጀንድ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ የሠጠው የመጀመሪያ ኮርስ ነው፡፡
የሌጀንድ ኢንተርናሽናል ፕሮ ቴኳንዶ አሶሴሽን የአፍሪካ ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ የበላይ ጠባቂ ግራንድ ማስተር (ፒ ኤች ዲ በማርሻል አርት ሳይንስ) ሄኖክ ግርማ፣ለተመራቂዎቹ ሰልጣኞች ሽልማት ሰጥተዋል፡፡
 
ይህ በዚህ እንዳለ፣ የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ከሳኦል ኩነቶች ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ 2016/2024 ኦፕን ቶርናመንት፣ ከግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን፤ ውድድሩን አስመልክቶ ነገ ቅዳሜ በአራት ኪሎ ስፖ/ትም/ሥልጠና ማዕከል በሚገኘው ትልቁ ጅምናዚየም ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡

ይህ ‹‹ሆኖ መገኘት፤ እኔም ኃይሌ ነኝ›› የተሰኘ መጽሐፍ በኢትዮጵያ የድርጅቶች አገልግሎት ልህቀትን ለማሳደግ በማሰብ የተደረገ የእውቀት ሽግግር ጥረት ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ወደ ልህቀት የሚደረግን ጉዞ የሚያግዝ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም መንገድንም የሚያመላክት እንጅ፡፡

‹‹ሆኖ መገኘት›› ማዕከል የሚያደርገው የአገልግሎት ልህቀት ከፍ እያለ በተግባር እየታየበት ያለውን ኃይሌ ሪሶርቶችና ሆቴሎች ሲሆን የሥረ ነገር ማጠንጠኛውም ራሱ ሆኖ መገኘትን ያሳዬን ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ነው፡፡ መጽሐፉ የሥራ ባህል ምን ያህል ወሳኝ መሆኑን አጽኦት የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ የስራ ባህል ምንነትን እና ተግባራትን ከመቅረጽ አንጻር ያለውን ሚና ያትታል፡፡

ሆን ተብሎ ቢሆንም እና ባይሆንም ባህል እያንዳንዱ ከባቢ ላይ ተጽዕኖውን ያሳርፋል፤ የግለሰቦች ይሁን የድርጅቶችንም ግብር እና ምግባር ይቀርጻል፡፡ ይህን ሀቅ ስንቅ አድርጎ በመያዝ ኃይሌ ሪሶርቶችና ሆቴሎች  ከቃል በላይ የሆነ በተግባርም የተገለጸ አዲስ ባህልን ለመፍጠር ችሏል፡፡

በዚህ መጽሐፍ የምንነግራችሁ ንድፈ ሐሳብ አይደለም፤ ይልቁንም እየተኖረ ያለ እና በተግባር የተገለጸን እውቀት እንጅ፡፡ ይህም እውቀት የጋራ የሆነ እንጅ ለጥቂቱ ተገልጦ ብዙኃኑ ያላገኙት ትንቢት አይደለም፡፡ ለውጡም ከተግባርዎ፣ ከምግባርዎ፣ ከሥነ ልቦናዎም ዘንዳ የሚታጨድ እሸት ነው፡፡ ስሊዚህም እንዲህ እንላለን ‹‹ማንም ቢሆን ልክ እንደ ኃይሌ ማሰብን መልመድን እና መሥራትን ይችላል›› ስለዚህም ‹‹እኔም ኃይሌ ነኝ›› ፍልስፍና የስኬት ቁልፍ ለእርስዎ እነሆ!

“አንዲት እናት ልጆቿን ብቻዋን ታሳድጋለች፡፡ የአስተዳደግ ዘይቤዋ ከሌሎች ወላጆች ለየት ይላል፡፡ ልጆቿ ከሰፈር ልጆች ጋር ተቀላቅለው ሲጫወቱ አይቼ አላውቅምና ሁሌም ጥያቄ ይፈጥርብኝ ነበር፡፡ ልጆችሽ ከእድሜ እኩዮቻቸው ጋር ሲጫወቱ አይቼ አላውቅም አልኳት፡፡
“በልጅነቴ ብቸኛ ወንድሜን ያጣሁት ሰፈር ውስጥ በተወረወረ ድንጋይ ነው” ወዲያውም ስቅስቅ ብላ አለቀሰች፡፡
“በጣም አዝናለሁ፤ መጠየቅ አልነበረብኝም” አልኳት፡፡
“እነዚህን ብርቅዬ ልጆች እንደ ወንድሜ ማጣት አልፈልግም፡፡ ውጭ እንደ ሌሎች ልጆች ቢጫወቱ ይሞቱብኛል ብዬ እፈራለሁ፡፡” አለችኝ::
ህክምና ያላገኘ የልጅነት ጠባሳ ጊዜ ጠብቆ በትዳር ህይወትም ይገለጣ:ል፡፡”
**
በደራሲ ብርሃኑ በላቸው አሰፋ የተዘጋጀው “ክቡር ልጆች፣ የልጆች ስነ ልቦና ለመገንባት እና የስሜት ስብራት ለመጠገን የሚረዱ ቁልፍ መንገዶች ” የተሰኘው መጽሐፍ፤ የፊታችን እሁድ መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ሳር ቤት በሚገኘው በኢንተርናሽናል ኢቫንጀሊካል ቤተ ክርስቲያን እንደሚመረቅ ደራሲው ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ (ለመግቢያ የተጠቀምንበት ጽሁፍም ከመጽሐፉ የተቀነጨበ ነው፡፡)
መጽሐፉ፤ በልጆች ስነ ልቦና ላይ ጥናትን መሰረት ያደረገና ሀገራዊ ለዛ ያለው እውነተኛ ታሪኮችን የሚያስቃኝ ሲሆን፤ በተለያየ ተግዳሮት ውስጥ ለሚገኙ ልጆች የመፍትሄ ሃሳብ ይዞ መቅረቡም ተጠቁሟል፡፡ በዋናነትም ልጆች የሚስተዋልባቸውን የስነ ልቦና ጫና እና የስሜት ስብራት የሚተነትን ሲሆን፤ በጥናት ላይ የተደገፈ የመፍትሄ ሃሳብን በተጨባጭ እንደሚያመላክትም ተነግሯል፡፡
“ክቡር ልጆች“ በአማርኛና አፋን ኦሮሞ ተዘጋጅቶ የተቀረበ ሲሆን፤ በዋናነትም ለትዳር ለሚዘጋጁ፣ ለወላጆች፣ ለመምህራን፣ እንዲሁም በልጆች ላይ ለሚሰሩ ባለሙያዎችና ለሌሎችም ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ደራሲው በሆሊስቲክ ቻይልድ ዴቨሎፕመንት ሁለተኛ ዲግሪ ፣ በሶሽዮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪና በስነፅሑፍና ቋንቋ ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ሲሆን፤ ከልጆችና ወጣቶች እድገት ጋር በተያያዘ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በተጋባዥ እንግድነት እየቀረበ ሙያዊ ትንታኔዎችን በመስጠት ይታወቃል፡፡
 

ጠ/ሚኒስትሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለው እንዲታገሉ ጥሪ አቀረቡ

”60 ፓርቲዎች ሆናችሁ ልንደግፋችሁ ይቸግረናል“

ለሁለት ወር ግድም ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ያደረጉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ባለፈው ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም በመቶዎች ከሚቆጠሩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች  ጋር በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

የፓርቲ አመራሮቹ በውይይቱ ላይ ለጠ/ሚኒስትሩ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል የሰላምና ጸጥታ ችግር፣ የህግ የበላይነት አለመኖር፣ የፖለቲካ  ምህዳር መጥበብ፣ የሜጋ ፕሮጀክቶች ተጠያቂነትና  የዜጎች መፈናቀል ጉዳዮች ይጠቀሳሉ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ሃላፊን ጨምሮ አንዳንድ የፓርቲ አመራሮች የቢሮ፣ የአዳራሽና የፋይናንስ ችግር  እንዳለባቸው ጠቅሰው ላነሱት ጥያቄ፣ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ  ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

እኛ እንደ ፓርቲ ማድረግ የምንችላቸውን ነገሮች እናያለን ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ያንን ለማድረግ ግን ለፓርቲዎቹ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል - አሁን ያሉት 70 የሚደርሱ ፓርቲዎች 4 ወይም 5 ሆነው ሰብሰብ እንዲሉ፡፡

“አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ 66 ወይም 68 ገደማ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ለ68 ሊቀ መንበር ቦታ የለንም፤ ለ68 ሊቀ መንበር ቢሮ የለንም፤ 2-3-4-5 ሆናችሁ ብትሰባሰቡ --- ከብልጽግና ጋር 5 ወይም 6 ፓርቲ ብንሆን አንቸገርም ነበር፡፡”  ያሉት ዐቢይ፤ ”ለምሳሌ ዛሬ በውይይቱ ላይ ከእያንዳንዱ ፓርቲ አምስት አምስት ሰው ቢወከል፣ 25ቱም ሰዎች መናገር ይችሉ ነበር” በማለት አስረድተዋል፡፡

 “ስንበዛ መበተን ብቻ ሳይሆን በዚያው መጠን አቅማችንም ውስን ይሆናል፤” ሲሉም አክለዋል፡፡



ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ውይይቱን የቋጩትም  የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሰብሰብ እንዲሉ በመማጸን ነበር፡፡

“እባካችሁ ወደ 4 ወይም 5 ፓርቲ ሰብሰብ በሉ፡፡ ግዴለም ይጠቅማችኋል፡፡ እንደዚያ ከሆናችሁ ፓርላማውም ይከፈታል፤ የምታስቡትም ሥልጣን ይመጣል፡፡ በዋና ዋና ጉዳይ ከተግባባችሁ በጋራ ሆናችሁ ብትታገሉ---አትጠራጠሩ ፓርላማውንም እንከፋፈለዋለን፡፡” ብለዋል፡፡

“እናንተ ግን አሁን 60 ናችሁ፤ ይሄ ለህዝብም ያስቸግራል” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ”እኔ እንኳን ስማችሁን አላውቀውም፤እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብ--” ሲሉም ፓርቲዎቹ ሰብሰብ ብለው እንዲታገሉ መክረዋል፡፡

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ከዚህ ቀደምም የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለው በጋራ እንዲታገሉ ጥሪ አቅርበው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ክብርት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ከጃፓን መንግስት የተበረከተላቸውን የወርቅ ጨረር ያለውን ኒሻን  ሽልማታቸውን ተረከቡ።
 
ይህ እውቅናና ሽልማት እኤአ ከ1875 ጀምሮ ለውጭ ሃገር ዜጎች በጃፓን መንግስት የሚሰጥ አንጋፋና ክብር ያለዉ ነው::  ከኢትዮጵያ የወርቅ ጨረር ያለው ኒሻን ሽልማት ከጃፓን መንግስት ሲሰጥ ክብርት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ የመጀመሪያዋ ናቸው። በጃፓን እና በኢትዮጵያ መካከል በስፖርት ዲፕሎማሲ እና ልውውጥ ዘርፍ ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅዖ ፣ በሌሎች ሀገራት እና አካባቢዎች መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማሳደግ፣ ለአትሌቲክስ እድገት ፣ ለአገር ሰላም ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅና በመስጠት በዓለም አቀፍ መስኮች የላቀ ስኬት ምክንያት ሽልማቱን አግኝተዋል። ክብርት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ሽልማታቸውን ዛሬ መጋቢት 24/2026 በኢትዮጵያ ከጃፓን አምባሳደር  ሚስተር ሺባታ ሂሮኖሪ እጅ ተረክበዋል ።

ጥበበ ተርፋ ማመጫ፤ በሐረር ከተማ በ1941 ዓ.ም ተወለዱ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሐረር መድኃኒዓለም ት/ቤት እንዳጠናቀቁ ወደ አዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ት/ቤት (በአሁኑ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት) በመግባት ተመርቀዋል።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥነጥበብ ልምምድ ውስጥ ተዋጽዖአቸው ከፍ ያለ ሥፍራ የሚሰጠው ነበረ:: የሥዕል ሥራቸውን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ለዕይታ ያበቁ ሲሆን፣ በሙያው ስምና ዝና ያፈሩ አንጋፋ ሙያተኛ ነበሩ::

አቶ ጥበበ ተርፋ የሥራቸው አቅጣጫ ተወልደው ባደጉበት ሐረር ላይ በማተኮር የትላንቱንና የዛሬውን ገጿን በቀለማት እንቅስቃሴ ይገልጹ ነበረ። አቶ ታዬ ታደሰ ባዘጋጁት የሠዓልያን ታሪክ ውስጥ ጥበበ "የተለያዩ ቴክኒኮችን የሚጠቀሙ ሲሆኑ፤ የሚያደንቁት ግን ኤክስፕሬሽኒዝምን ነው" በማለት መጻፋቸው ይታወሳል::

ሠዓሊ ጥበበ ተርፋ ማመጫ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው ህይወታቸው ማለፉን ሰምተናል:: ለመላው ቤተሰብ፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ለአለ_የሥነጥበብ_ት/ቤት ማህበረሰብ፣ ለሙያ ጓዶቻቸውና አድናቂዎቻቸው መጽናናት እንዲሆንላቸው እንመኛለን።

ቀብራቸው ነገ ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በየካ ሚካኤል ቤተክርስትያን ከቀኑ 8:30 የሚፈጸም ይሆናል። ነፍስ ይማር።

(አገኘሁ_አዳነ_ድልነሣሁ)

Page 6 of 704