Administrator
ለአቡነ ሐራ ድንግል አንድነት ገዳም ዛሬ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር ይካሄዳል
• ገዳሙን ለመታደግ 100 ሚ.ብር ያስፈልጋል
ለአቡነ ሐራ ድንግል አንድነት ገዳም፣ በዛሬው ዕለት ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ፣ በካፒታል ሆቴል ዓለማቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር የሚካሄድ ሲሆን፤ገቢው በገዳሙ ይዞታ ላይ ለሰፈሩ ነዋሪዎች ካሣ በመክፈል ይዞታውን ለገዳሙ ለማስመለስ ነው ተብሏል፡፡ የገዳሙ ገቢ ማሰባሰቢያ ኮሚቴ እንደገለጸው፤ ገዳሙን ለመታደግና ለማስፋፋት በአጠቃላይ 100 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡
ገዳመ ወንያት አቡነ ሐራ ድንግል የአንድነት ገዳም፣ በ1574 የተመሰረተና የጻዲቁ አባት አቡነ ሐራ ድንግል ገድልና ገቢረ ተዓምራት የሚካሄድበት ገዳም ነው - ይላሉ የገዳሙ መነኮሳት፡፡
ከ400 ዓመት በላይ ታሪክ ያለው ይህ ትልቅ ገዳም በሰሜን ጎጃም፣ ባህርዳር ዙሪያ የሚገኝ ሲሆን፣ ጻዲቁ አቡነ ሐራ ድንግል፣ ከፈጣሪያቸው በተገባላቸው ቃልኪዳን መሠረት፣ ደዌን ሲፈውሱና ተዓምራትን ሲሰሩ የቆዩበትና አሁንም የሚሰሩበት ጥንታዊ ገዳም መሆኑን፣ የገዳሙ ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ገቢረ ተዓምር የሚሰራበት ታሪካዊ ገዳም፣ ትልቅ ችግር እንደተጋረጠበት መነኮሳቱ ተናግረዋል፡፡
“ለፈውስና ለድህነት ከመላው አገሪቱ ወደ ገዳሙ የሚመጡ ምዕመናን ድህነትና ፈውስ ካገኙ በኋላ፣ ገዳሙን ተጠግተው ቤት በመሥራት እዚያው እየኖሩ፣ ገዳሙ ይዞታውን እየተነጠቀ ከመጣበቡም በላይ፣ የገዳሙን ቅድስና የሚያረክሱ ተግባራት እየተፈጸመበት ይገኛል፡፡” ይላል፤ የኮሚቴው መግለጫ፡፡
የገዳሙ መነኮሳት የታሪክ ዶሴና ማስረጃ ላይ ተንተርሰው እንደሚናገሩት፤ ዓጼ ዮሐንስ በነቀርሳ ተይዘው በአቡነ ሐራ ድንግል ጸበል በመዳናቸው ነበር ለገዳሙ የአንድ ሰዓት የእግር መንገድ ያህል ስፋት ያለው ቦታ ለገዳሙ የሰጡት፡፡ ደርግ ሥልጣን ሲይዝ በገዳሙ 800 የሚደርሱ መናንያን እንደነበሩ የሚያስታውሱት መነኮሳቱ፤ በወቅቱ “መሬት ላራሹ” የሚል አዋጅ በመታወጁ የገዳሙን ይዞታ አርሶ አደሮች እየተቆጣጠሩት እንደመጡና መናንያኑ ገዳሙን ጥለው መኮብለላቸውን ያስረዳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በገዳሙ ይዞታ ላይ ከ250 በላይ አባወራዎች ሰፍረው እንደሚገኙ የሚገልጹት መነኮሳቱ፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ ለመንግሥት በተደጋጋሚ አቤቱታ ካቀረቡ በኋላ፣ መንግሥት ነዋሪዎቹን አንስቶ ሌላ ቦታ ለማስፈር ፈቃደኛ ቢሆንም፣ ለነዋሪዎች ካሣ ለመክፈል በጀት እንደሌለው በመግለጽ፣ ገዳሙ ካሣውን እንዲከፍል መወሰኑን ይናገራሉ፡፡
ሆኖም የሚከፈለው ካሣ ከገዳሙ አቅም በላይ በመሆኑ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል የሚለው የገዳመ ወንያት አቡነ ሐራ ድንግል አንድነት ገዳም የገቢ ማሰባሰቢያ ኮሚቴ፤ ባለፈው ሐሙስ በጠቅላይ ቤተክህነት አዳራሽ፣ ስለ ገዳሙ አሁናዊ ሁኔታና ስለ ገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደተነገረው፣ የአማራ ክልል ካቢኔ ለገዳሙ ሁሉንም ይዞታውን ባይሆንም 60 ሄክታር የሚደርስ ቦታ እንዲመለስለት የወሰነ ሲሆን፤ ገዳሙ በበኩሉ ለአርሶ አደሮቹ የሚገባቸውን የመሬት ካሣ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ ይህን የመሬት ካሣ ለመክፈልና ለገዳሙ የማስፋፊያ ልማት ለማከናወን፣ ዛሬ ቅዳሜ ሚያዝያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል፣ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት፣ ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊቱ 6 ሰዓት የሚቆይ ዓለማቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር እንደሚያካሂድ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡ ለአርሶ አደሮቹ የመሬት ካሣውን ለመክፈልና የገዳሙ ይዞታ ከተለቀቀ በኋላ በሥፍራው ለሚከናወኑ ልማቶች በአጠቃላይ 100 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው የገለጸው የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴው፤ በመላው ዓለም የሚገኙ የቤተክርስትያን ልጆችና የጻድቁ አቡነ ሐራ ወዳጆች በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ በንቃትና በትጋት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት በገዳሙ የሚገኙ መናንያን ቁጥር 5ሺ እንደሚደርሱና በጾም ወቅት የጸበልተኛው ቁጥር ከ50 ሺ በላይ መሆኑን የጠቆመው የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴው፤ እኒህን ሁሉ በአግባቡ የሚያስተናግድ በቂ መጠለያና የልማት ሥራዎች ማከናወን አስፈላጊ እንደሆነ በአጽንኦት ተናግሯል፡፡
"ስብሐቲዝም የሀሳብ ውይይት" እሁድ ይካሄዳል
ስብሐቲዝም የሀሳብ ውይይት የፊታችን እሁድ ሚያዝያ 20 2016 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት(ወመዘክር) አዳራሽ ውስጥ ይካሄዳል።
የሕላዌ እንቆቅልሽ " የተሰኘ መጽሐፍ ነገ ይመረቃል
"የሕላዌ እንቆቅልሽ " የተሰኘ መጽሐፍ ነገ ይመረቃል
የደራሲ ማንደፍሮ ማሩ "የሕላዌ እንቆቅልሽ" የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ቅዳሜ ሚያዝያ 19 2016 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 ጀምሮ በወመዘክር አዳራሽ ይመረቃል።
"ፋሽን" መጽሐፍ ቅዳሜ ይመረቃል
በደራሲ ባየህ ንጉሴ የተዘጋጀው “ፋሽን” የተሰኘ በፋሽን እና ሞዴሊንግ ላይ ትኩረቱን ያደረገ መጽሐፍ ቅዳሜ ሚያዝያ 19/2016 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) አዳራሽ ጥሪ የተደረገላቸው
የጥበብ ቤተሰቦች እና እንግዶች በተገኙበት ይመረቃል ይመረቃል።በስድስት ምዕራፍ የተከፈለው መጽሐፉ ስለ ሞዴሊንግ አይነቶች፣ ሞዴል የመሆን ትሩፋቶች እና ተግዳሮቶች፣ የቁንጅና ውድድር፣ ሻምፖ እና ኮድሽነር አመራረጥ፣ ፖርትፎሊዮና ሌሎችም ዝርዝር ጉዳዮችን ይዟል።
ዘመን ባንክ የሠራተኞቹን ዕውቀትና ክህሎት ለማሳደግ ከሊንክድኢን ለርኒንግ ጋር የአጋርነት ስምምነት ፈጸመ
ዘመን ባንክ የሠራተኞቹን ዕውቀትና ክህሎት ለማሳደግ፣ በዓለም ትልቁ የኢንተርኔት የመማሪያ መድረክ ከሆነው ሊንክድኢን ሊርኒንግ ጋር የአጋርነት ስምምነት ተፈራረመ፡፡
የዘመን ባንክ የሰው ሀብት ምክትል ዋና ኦፊሰር አቶ ታከለ ዲበኩሉ ስለ ስምምነቱ ሲገልጹ፤ “ዘመን ባንክ ለሰራተኞቹ ቀጣይነት ያለው የመማርና የሙያ እድገት ባህልን ለማሳደግ ቁርጠኛ ነው። ከሊንክድኢን ለርኒንግ ጋር ያደረግነው ስምምነት፣ ይህንን ቁርጠኝነት የሚያጎላ ከመሆኑም በላይ ሠራተኞቻችን በፋይናንስ ዘርፉ የሚጠይቀውን ችሎታ፣ እውቀትና ክህሎት እንዲያሳድጉ የሚረዳ ነው፡፡" ብለዋል፡፡
የሊንክድኢን ታለንት ሶሉዩሽን ዋና ኃላፊ ማቲው ግሬይ በበኩላቸው፤ ”ከዘመን ባንክ ጋር ያደረግነው ስምምነት የሰራተኞቹን የክህሎትና የእውቀት ክፍተቶችን ለማሟላት እድሉን የሚሰጠን ከመሆኑም በላይ ሊንክድኢን ለርኒንግ በአፍሪካ ተመራጭ የክህሎት ልማት መድረክ ሆኖ መቀጠሉን ስለሚያሳይ እጅግ ተደስተናል። የዘመን ባንክ የሰው ሃብት ስትራቴጂ በቀጣይ አመታት ይበልጥ እንዲጎለብትና ውጤታማ እንዲሆን አብረን እንሰራለን።" ብለዋል፡፡
የእነዚህ ኮርሶች ወጪ ሙሉ በሙሉ በዘመን ባንክ የተሸፈነ ሲሆን፤ የባንኩ ሠራተኞች ሥልጠናውን በነፃ እንደሚያገኙ ታውቋል፡፡
አይናቸውን ለማብራት 400 ሺህ ዶላር ያስፈልጋል
የሰሜን ጎጃሙ ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳም ትልቅ ችግር ተጋርጦበታል ተባለ
አንድ ሰው - ለአንድ ወገን!!...
ሀርመኒ ሂልስ ት̸ ቤት ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቀን አከበረ
አፍሮ-ኤዥያ ዓለማቀፍ የጤና ኤክስፖ በቅርቡ በመዲናዋ ይካሄዳል
*በኤክስፖው ከ30ሺ በላይ ለሚሆኑ ጎብኚዎች ነጻ የህክምና ምርመራ ይሰጣል
አፍሮ-ኤዥያ ዓለማቀፍ የጤና ኤክስፖ፣ እዚህ አዲስ አበባ በኤግዚቢሽን ማዕከል፣ ከግንቦት 9-11 ቀን 2016 ዓ.ም ለሦስት ቀናት ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በኤክስፖው ላይ ከ400 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች፣ ከ30ሺ በላይ ጎብኚዎችና ከ2ሺ በላይ የጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡
የጤና ኤክስፖውን አስመልክቶ አዘጋጆቹና አጋር ተቋማት ዛሬ ከሰዓት በኋላ 8 ሰዓት ላይ በራማዳ ሆቴል የሚዲያ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ሰፊ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደተመለከተው፣ በጤና ኤክስፖው ላይ የፓናል ውይይቶች፣ ዎርክሾፖችና ኤግዚቢሽኖችን ጨምሮ በርካታ ኹነቶች ይቀርባሉ፡፡ የጤና ባለሙያዎች የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበትና የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር የሚካሄድበት እንዲሁም የትስስርና የትብብር ዕድሎች የሚፈጠርበት መድረክ እንደሚኖርም ተጠቁሟል፡፡
ኤክስፖው በጤና አጠባበቅ ኢንዱስትሪ ውስጥ የህዝብ ጤናን፣ ፋርማሲዩቲካልስን፣ የህክምና ቴክኖሎጂንና ሌሎች በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችንና ዘርፎችን እንደሚሸፍን የተገለጸ ሲሆን፤ ይህ ሁሉን አቀፍ አቀራረብም ተሳታፊ ድርጅቶችና ጎብኚዎች በተለያዩ መስኮች ከአዳዲስ ዕድገቶችና ፈጠራዎች ጋር እንዲተዋወቁ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡
“ድልድዮችን እንገንባ፣ ህይወትን እናድን” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው በዚህ ዓለማቀፍ የጤና ኤክስፖ፤ ከ30ሺ በላይ ለሚሆኑ ጎብኚዎች ነጻ የጤና ምርመራ የሚከናወን ሲሆን፤ ለጤና አጠባበቅ ባለሙያዎችም ነጻ ሥልጠና እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡
ለሦስት ቀናት በሚቆየው የአፍሮ- ኤዥያ ዓለማቀፍ የጤና ኤክስፖ ላይ ከህንድ፣ ዱባይ፣ ታይላንድ፣ ቱርክ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ማላይዥያና ሌሎችም አገራት የተውጣጡ በጤና ላይ የሚሰሩ ተቋማትና ባለሙያዎች እንደሚሳተፉበት ተጠቁሟል፡፡
ኤክስፖው ከወትሮው በተለየ በቢዝነስ ላይ ብቻ የሚያተኩር ሳይሆን፣ ተቋማት ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ልዩ ዕድል የሚያገኙበት እንደሆነም ተነግሯል፡፡
ይህን ዓለማቀፍ የጤና ኤክስፖ ኤፍዚ ማርኬቲንግና ኮምዩኒኬሽን ኃ.የተ.የግ. ማህበር ከሰላም ኸልዝ ኮንሰልታንሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሲሆን፤ ሳልማር ኮንሰልታንሲ፣ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር፣ የኢፌዲሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብና መድሃኒት ባለሥልጣን እንዲሁም የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በአጋርነት እንደሚሳተፉበት ታውቋል፡፡