በአብነት ስሜ መጽሐፍት አርታኢነት የምናውቃቸው አደዳ ኃይለ ሥላሴ የተባሉ ጸሐፊ፤ ባለፈው ሳምንት የአዲስ አድማስ እትም ላይ ባወጡት የምላሽ ፅሁፍ፣ የእኔን አስተያየት ከግለሰብ ትውውቅ (ትንቅንቅ) ባልተናነሰ “ምናብ” ተችተዋል፡፡ አብነት ስሜ፤ ነሐሴ 16 ቀን 2007 ዓ.ም በወጣው የጋዜጣው እትም፤ በዓለማየሁ ገላጋይ “ወሪሳ” መጽሐፍ ላይ ኂሳዊ ፅሁፍ ማስነበባቸው የሚታወስ ሲሆን እኔም በሳምንቱ ለአዲስ አድማስ አስተያየቴን ልኬ ነበር፡፡ ከአንድ ሳምንት በኋላ አስተያየቱ ለንባብ በቃ፡፡ ቀጣይ ክፍል እንዳለውም ጠቁሜ ነበር፡፡ ጽሁፉን ብልክም ግን በአዲስ ዓመት እትም ላይ ጽሑፉ አልወጣም፤ በአዲሱ ዓመት ሁለተኛ እትም ላይም እንዲሁ የለም፡፡
መስከረም 8 ቀን 2008 ዓ.ም በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ፤ አይዳ የተባሉት ፀሃፊ፤ በአብነት ስሜ ላይ ተጽፎ ለነበረው አስተያየት (ሒስ/ኂስ…?) ምላሽ ሰጡ፡፡ አስተያየት ሰጪዋ፤ ሌላውን ለማስተማር ውድ ጊዜያቸውን በመሰዋታቸውና ለመወያየት በመፍቀዳቸው ይመሰገናሉ፡፡ እኔም ትምሕርት ወስጄበታለሁ፡፡ ስላስተማሩን፣ ስለዘከሩንና ስላወያዩን በድጋሚ እናመሰግናቸዋለን፡፡ ይቀጥሉበት!
ሆኖም ግን የጽሑፌን ሐሳብ ያገኙት አልመሰለኝም፡፡ እኔ ወደ መግባባት ነጥብ ለመድረስ እንጂ ነገሩ የአተካራ ቅብብሎሽ ሆኖ፣ ዘረ-ሐሳባችንን ጠጠርና እሾሕ ላይ ለመዝራት አልነበረም፡፡ በበኩሌ አብነት ስሜ የሰሯቸውን የጽሑፍ ትሩፋቶች እውቅና ላለመስጠት አሊያም ጸሐፊውን ከእውቀት አጠር ቀዬ ለመመደብ አልሜ አልፃፍኩም፡፡ ዋና ትኩረተ- ነጥቤ፤ ሕልምና የከዋክብት ቆጠራን ከዓለማየሁ ገላጋይ ‹‹ወሪሳ››ም ሆነ ከገሃዱ ዓለም ውዥንብራችን ጋር ሳንደባልቅ ወደ ነባሩ፣ ተጨባጩና መፍትኄ ወደሚሻው የሕይወት መስመራችን እንድንመለስ ነበር አስተያየቴን ያሰፈርኩት፤እንጂ ልሳደብ አይደለም፡፡
አደዳ የተባሉት አስተያየት ሰጩ፣ ባቀረቡት ጽሑፉ ላይ ያልገባኝ ነገር ቢኖር፣ “ተሳድበሃል” መባሌ ነበር፡፡ የአቶ አብነትን መፅሃፍ “አማርኛ ነክ” ያልኩት በስሕተት ነው፡፡ እታረማለሁ፡፡  ሁልጊዜ ታትመው የሚወጡ መጽሐፍትን የማየት ፍላጎቱም ፈቃዱም ስላለኝ፣ አብነት ስሜን በኢትዮጵያ ኮከብ መፅሐፍ አውቄው፤ በ“የቋንቋ መሰረታዊያን” ላይ ደገምኩት፡፡ መጽሃፉን “አይቼለታለሁ” ማለቴ በርዕስ ደረጃ በመሆኑ፣ “ስውሩ” አዕምሮዬ ሊያስታውስ የቻለውን “አማርኛ”ን ከ”ቋንቋ” ጋር በማላተም፣ የቋንቋ መሰረታውያን ማለት ሲገባው፣ “አማርኛ ነክ ጉዳዮች” በሚል በስሕተት ፃፍኩ፡፡ ለዚህ እታረማለሁ፡፡ ይቅርታ!
ሌላው ግን አስተያየት ሰጪዋ፤ “በቀቀናዊ ማንነት”ን የገለጹበት መንገድና “አብነት ስሜ እኮ በእነ ዶክተር ዮናሰ አድማሱና ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ የተደነቁ…” በሚል አስተያየት፣ ፀሃፊውን ኀፂር ለማድረግ የመሞከር ኢ-ሳይንሳዊ ሂደት፣ከእውቀት ሰጪነቱ ይልቅ የቲፎዞ አሸብሻቢነት ሰብዕናን ያመላክታል፡፡
የኔ ሐሳብ በግልጽ እና በቀጥታ
የዓለማየሁ ገላጋይ ‹‹ወሪሳ›› ሕልምም፣ ትንቢትም አይደለም! ያለንበትን ነባራዊ ገጽታ ያለ ኮከብ ቆጠራ እርዳታ፣ ያለ ሕልም ፈቺ ሰባኪነት አሳይቶናል፡፡ አብነት ስሜም ሕልምን በመፍታት መፍትሄ እናፈላልግ ከማለት፣ ለእኔ ሳይንሳዊውና ቀላሉ ያውም ቀጥተኛው መንገድ፣ ነባራዊውን፣ ሳንተኛና ሳንቃዥ የሚታየንን ሐቅ እንፈትሸው፣ እናሳየው፣ እንግለጠው፣ እንወያይበት፣ እንመካከርበት እንለወጥበት የሚለው ነው፡፡
የእውነቱን ትዕይንት ሕልም አድርጎ በማቅረብ፣ “ሕልም እንፍታ፤ ኮከብ እንቁጠር፤ ለችግራችን መፍትሄ እንስጥ” ይሉናል፡፡ “ኮከብ ቆጠራን እናሳድግና እጣፈንታችንን እንወስንም” ይላሉ፡፡ እኔ በዚህ አልስማማም! በዚህም ምክንያት በአብነት ስሜ የቀረቡት ሐሳቦችም ከምጠብቃቸው በታች ሆነውብኛል፡፡ እናም ሲፈርዱ ያየኋቸው ታላቅ ሰው፣ ወረዱብኝ አልኩኝ፤ እንጂ ፈፅሞ አልተሳደብኩም፡፡
ኮከብ ቆጠራ (አስትሮሎጂ) ላይ ትልቅ የተሳሳተ አመለካከት እየገነባን እንደሆነና ያንንም የአብነት ስሜን የእውቀት ክምችትም ሆነ ሙያዊ ክህሎት ሳላሳንስም ሆነ ሳላከብድ የግል አስተያየቴን መስጠቴ፤ “ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ” ብኂል፤ “አብነት አይኄስ፣ እርሱ አዋቂ ነው” ብለው መልስ የሰጡት አደዳ፤ ሰማይ በመብረቅ እንደሚታረስና ንጉስም እንደሚገረሰስ እኔ ደቂቁ አልነግራቸውም፡፡
“አንተ አላዋቂ ነህ!” አይነት ብኂል እየተለመደ መጥቷል፡፡ ሐሳብን ደበላልቆ ማምታትም አዋቂነትም ሆኗል፡፡ “ቲፎዞነት” ቋሚ መተዳደሪያ “ሱቅ በደረቴ”ን አንግቧል፡፡ አነጣጥሮ መተኮስና መጣል ጀግንነትን ተክቷል፡፡ “ኧረ ገዳይ!” እና “ዘራፍ!” ፉከራዎች፣ በእውቀት ጭንብል እየተሸፈኑ ተስፋፍተዋል፡፡  መልስ የፃፉትን አደዳ ኃይለ ሥላሴን፤ አልበርት ፓይክ ማናቸው ብዬ እንዳልጠይቃቸው፣ መጠየቅ መሳደብ እንዳይመስላቸው ፈራሁ፡፡ ቢመስላቸውም ግን የሚያውቁትን እንዲያካፍሉን እንጠይቃለን፡፡ (አልበርት ፓይክ የሰይጣን አምልኮትን ያወጀበት መጽሐፍ ‹‹ሞራልስ ኤንድ ዶግማ››ን ልብ ይሏል፡፡)
ዝነኛ ታዋቂዎች፤“ነጻ ፈቃድን፣ ከኮከብ ቆጠራ”፤ ታሪክን ከተረት፤ “እውነትን ከሕልም” ጋር በማላተም የሰውን ልጅ መዳረሻ ሲገድቡት፣ ጨቅላ መንፈስን በእሽሩሩ ሕመም ሲያክሙት ይታያሉ፤ ትውልድን በዚያው መስመርና በውስብስብ አቅጣጫ ሲነዱት ሃይ የሚላቸው የለም፡፡ በዚህ ሁኔታ #ንጉሱ ራቁቱን ነው” ያለው ሕጻን፣ በ“አዋቂዎች” መረገጡ አያስገርምም…፡፡ የሰው ልጅ ነጻ ፈቃድና ምርጫ እያለው፣ የኮከብ ቆጠራ አይነት ሳይንሳዊ ጥንቁልናን እንደ አዋቂነት በመውሰድ ሕዝቡን ያወዛውዙታል፡፡ ሕልምህን እንፍታልህና ችግርህን እናስወግድልህ እያሉ ያደነዝዙታል!! የሰው ልጅ በሁለት ምርጫዎች ኮርቻ ላይ ቆሞ የሕይወትን ፈረስ የሚጋልብ ፍጡር ነው፡፡ ለፍጥረታት አይገዛም! ፈጣሪም አይደለም! የሰማይ ከዋክብት ይቅሩና የሰማይ ከዋክብት ፈጣሪ እንኳ እጣ ፈንታውን እንዳይወስንለት በምርጫ የተሳፈረ ፈረሰኛ ነው፡፡(ፈረሱ ካልተገራ አስቡት መደነባበሩን!!)
ወደ ምድር መምጣትን በምርጫችን ባናደርግም፤ ወደ መጣንበት መምረጥን ግን ምርጫችን እናደርጋለን፡፡ ወደማታውቀው መጥተህ ወደምታውቀው ለመሄድ መኖር ታላቅነት ነው፡፡ ይሕን ታላቅነት ኮከብ ቆጣሪዎች ሲያከስሙት፣ ሲጫወቱበት  ያስቆጫል፡፡
 እኔ እንደ አስተያየት ጸሃፊዋ ወደ ታች ወርጄ፣ “በቀቀናዊንም” ሆነ “ባለጌነትን” እየጠቀስኩ፣ አንባቢን በወረደ ፍርድ ሸንጎ ላይ አልገትርም፡፡ እውቀት፣ ጥበብ፣ ሥልጣኔንና ነባራዊ ሁኔታን ተገንዝቦ፣ ባልተወሳሰበና ባልተደባለቀ ስሜት ማሕበረሰብን እያስተማርን፣ ብርቱ ትውልድ እናፍራ ነው አስተያየቴ፣ ፍላጎቴ- ጠሎቴም አንዲሁ!  
በኔ በኩል ሳይንሳዊ ጸሐፊያን፣ ታሪክን ከተረት ጋር አይደባልቁም፤ ውሳኔያቸውን በአማልክት፣ በፍጥረታት ሰልፍ አይገድቡም፤ ሕልምንም ከእውኑ ዓለም እይታ ጋር መለየት መቻል አለባቸው፤ ነገሮችን ማወሳሰብ የለባቸውም፤ የራሳቸውን ችግር ከፈጣሪ፣ ከከዋክብትም ሆነ ባለፈ ታሪክ ላይ ብቻ ተንጠልጥለው አይጋፉም፡፡ ነጻ ፈቃዱም ሆነ ምርጫው በአሁን ላይ ባሉ ጊዜያት ተወስኖ፣ አሁን ያለው ትውልድ ብቻ አንድ ተጨባጭ ለውጥ ላይ እንዲያተኩር መንገዱን ይከፍቱለታል፡፡ ከተፈጣሪ ያውም ከግዑዛን አካላት መፍትኄ አያስሱም፤ ከሕልምም ሆነ ከከዋክብት ዛሬያቸውንና  ነጋቸውን አይዳስሱም፡፡ (ከታወርን ግን ልንዳስስ እንችላለን!)
ለሕልምም ሆነ ለጥንቆላ ጊዜ አይሰጡም፡፡ ፈጣሪን ይማጸናሉ፡፡ ፈጣሪን ሕግጋቱን፣ ሐሳቡን በመረዳት ንጽሕና፣ ቅድስና እና ሥልጣኔን ይሰብካሉ፡፡ ሕልም በስራ ብዛት ይታያል (መክብብ 5፡3፡፡) ሕልም በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ፈቃድ፣ ራዕይና እቅድ ተመስሎ ተቀምጧል፡፡ “ሕልሜን ለማሳካት…” ስንል በሕይወታችን የምንፈልገው ግብ ላይ ለመድረስ ማለት ነው፡፡ ይሕም አብነት ስሜ የሚጠቅሰው ተኝተን፣ በ“ስውሩ” የአዕምሮ ክፍል (የተደበቀውን የምናየው ክፍል) ላይ የምናገኘው ሳይሆን ከእውኑ ዓለም በቀጥታ የምንረዳውን ትዕይንት መፍታትና ማፍታታት ብሎም ወደ መፍትሄ መሮጥ ነው፡፡
ችግርን ከተደበቀው የአዕምሮ ክፍል ማግኘት ይሻላል ወይንስ ከሚታየው የገሃድ ዓለም? እሳቸው ከተደበቀው የአዕምሮ ክፍል ከሚሉት ፈልገው መውጣታቸው ፈቃዳቸው ቢሆንም፤ የዓለማየሁ ገላጋይንም ሆነ የጉዱ ካሳን የእውን ዓለም ገጽታ፣ ከሕልምና ከኮከብ ቆጠራ ጋር ማዛመዱ ስለተምታታብኝ ነው! እጣ ፈንታን ከከዋክብት አጥር መፈለግ ይሻላል ወይንስ በእጃችን ካለው የተፈጥሮ ምርጫ? መልሱ ምርጫ ነው! ምርጫዎች ሁሉ ግን መልስ አይሆኑም!!
ሕልም የለም ብዬ አላምንም፡፡ ሆኖም እኔ  ሕልም ፈቺው፤ ሕልሙን ማየት የሚኖርበት ጊዜ  ላይ አተኩራለሁ፡፡ ይሕን ለማገዝ፡- ፈርኦን ሕልም አይቶ የዓለም ሕልም አዋቂዎችን አሰልፎ፤ “ሕልሜን ፍቱልኝ” አላላቸውም፤ “ሕልሜን እዩልኝ” እንጂ! የአዋቂዎች ጥበብ፤ ሕልም መፍታት ብቻ ሳይሆን ቀድሞ ሕልም ማየት ነው! ዓለማየሁ ገላጋይ ደግሞ ሕልምን ሳይሆን እውነትን አየ- አብነት ስሜ ሕልም አደረገው! ሕልሙንም ልፍታ ብሎ ወንዝ ወረደ!! ጋሻ ጃግሬው ከኋላው ነው!!
ዮሴፍ ተመርጦ ሕልም ፈቺ ሲሆን ሕልሙ አልተነገረውም፤ ራሱ ሕልሙን አይቶ ራሱ ፈታው፡፡ ሕልም ተነግሮት የሚፈታልንን አንፈልግም፤ ብዙ “ሕልም ፈችዎች” ተሰልፈዋልና! የሚያስፈልገን ዮሴፋዊ የሕልም ጠቢብ ነው፡፡ (አብዛኛው “ጸሐፊ” የእነ ሲግመንድ ፍሮይድ አስተምህሮቶችን በሚዛናዊ አይን ሳይሆን በቀጥታና በዝና ጭምር ብቻ እየተረጎመ፣ እነሱንም በመጥቀስ “አዋቂ ነኝ” የሚል ሰብዕናን መገንባት የተለመደ ሆኗል) አደዳ ኃይለ ሥላሴ፤ ሲግመንድ ፍሮይድን ያውቁታል? እንዴት? በምን?
ሰራተኛ ሕዝብ ግን በሕልም አይታወክም፤ በስራ ያምናል! ከቅዠቱም ሆነ “በስውር አዕምሮ” ተኝቶ ከሚያልመው ይልቅ በእውን ላለው ሐቅ ዋጋ ይሰጣል፡፡ (ሆድ ያባውን ከስውር አዕምሮ ጋር ያጣመረው ድንቅ ይላል)፡፡
ሰው ሲሰክር ተደብቆ የነበረውን ሐሳብ ነው የሚያወራው፡፡ ተክሉ አስኳሉ፤ ኢ-ንቁ አዕምሮ (ስውሩ አዕምሮው) ከሕልም ጋር የሚዛመድበትን ነገር ፍሮይድን ጠቅሶ፣ ግሩም ጽሑፉን “የዓመጻ መንገድ” በተባለው ልጨኛ ስራው አስነብቦናል፡፡ “የዓመጻ መንገድ”ን አንባቢንም፣ አስተያየት ሰጪንም ሆነ የተከበሩ አብነት ስሜን እንዲያነቡት እጋብዛለሁ፡፡ በጋራ እንወያይበት ዘንድም እጠይቃለሁ፡፡
በእውኑ ቀጥተኛና ግልጽ መንገድን የመረጠ ግለሰብ ጣፋጭ ሕልም ያያል፡፡ ጠቢቡ እንዲህ እንዲል፤ “ልጄ ሆይ÷ እነዚህ ከዓይኖችህ አይራቁ፤ መልካም ጥበብንና ጥንቃቄን ጠብቅ፡፡ ለነፍስህም ሕይወት ይሆናሉ፤ ለአንገትህም ሞገስ፡፡ የዚያን ጊዜ መንገድህን ተማምነህ ትሄዳለህ፤ እግርህም አይሰነካከልም፡፡ በተኛህ ጊዜ አትፈራም፤ ትተኛለህ÷ እንቅልፍህም የጣፈጠ ይሆናል፡፡ (መጽሐፈ ምሳሌ፤ ምዕራፍ3፡21-23)  
ብዙ ሕልም ባለበት ዘንድ እንዲሁም ብዙ ቃል ባለበት ስፍራ፣ በዚያ ብዙ ከንቱ ነገር አለ፤ አንተ ግን እግዚአብሔርን ፍራ፡፡ (መክብብ 5፡7)  
ሳይንሳዊ አዋቂዎች፤ ታሪክን ከአፈ ታሪክ ንግርት ወይንም ተረትነት ማላቀቅ አለባቸው፤ የሰውን ልጅ እጣ ፈንታ ከኮከብ ቆጠራ ገደብ መነጠል አለባቸው፤ ከቅዠቱ ዓለም ወጥተው የእውኑን መዳሰስ አለባቸው፡፡ ልክ ዓለማየሁ ገላጋይ በ‹ወሪሳ›› እንዳደረገው!
በትንቢት፣ በነብይ፣ በሕልምም ሆነ በከዋክብት ጥናት አስፈላጊነት ላይ ተቃውሞ የለኝም፡፡ ሆኖም ትንቢት ተናጋሪ ግምት ሰጪ፣ ነብይም ሐሳዊ ሲሆን ሕልም ነጋሪም የተነገረን፤ የተተረጎመን ሕልም ልፍታ ብሎ ሲደባልቅና የከዋክብትን ጥናት ለጥንቁልና ሲያውለው፣ ችግሩ ወደ ጥልቁ “መውረድ”ን ያከናንበናል!
አስተያየት ሰጪው፡- “በወሪሳ አንድምታዊ ትርጓሜ ላይ አብነት በቁጣ ተሞልቶ (ፓሺኔት ሆኖ) የጻፈው ይመስለኛል፡፡ ይኸ ለሀገሩና ለወገኑ ካለው ጥልቅ ፍቅርና መቆርቆር የመነጨ ስሜት ሊሆን ይችላል፡፡” ሲሉ በሳይንሳዊ መንገድ እውቀትን ለመጨበጥ ስንመካከር፣ ስሜታዊነትና ቁጣ የመግባባት ጸር መሆናቸውን ዘንግተውት ከአዋቂነት ሰብዕና ጋር አደባልቀውታል፡፡
የ”ሔሰ” እና የ”ኄሰ” ጉዳይ
ሔሰ፤ ሐየሰ፤ መንቀፍ ማጸየፍ፣ ማነወር፣ መክሰስ፣ መስደብ፣ መቆጣት፡፡
ኄሰ፤- ነቀፈ- ሐዪስ፡ ሔሰ፡፡ ሲሉ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ይተረጉሙታል፡፡ አስተያየት ሰጪዋ አደዳ፤ ሒስ/ኂስ በሚል ለመነጣጠል በመሞከር፣ አዋቂነታቸውን ለማሳየት ይሞክሩና፤ እንደለመድነው ድንግርግር ወዳለው የተደባለቀ ማንነት ይዶሉናል፡፡ ትንቢትና ነቢይን እንደዚሁ ሊተረጉሙልን ሞክረዋል፡፡
 የሚገርመውም ትንቢት የመጪውን ነገር ብቻ ሳይሆን የአሁኑን ነገር መናገርም ሊሆን ይችላል ካሉን በኋላ፤ የአለቃ ኪዳኔ ወልድ ክፍሌ ትርጉምን ሲጻረሩ እንመለከታለን፡፡ ዓለማየሁ ገላጋይንም የአሁን ዘመን ተናጋሪ “ነብይ” ካደረጉት በኋላ፤ ለነብዩ ሕልም ፈቺ ያስፈልገዋል ይላሉ፡፡ ነብዩ እየተናገረ ሕልም ፈቺው ምን ያወራል? ሕልም ፈቺውስ ከጥንቆላና ከኮከብ ቆጠራ እንዲሁም ከቅዠት ጋር ምን ይሰራል? የተምታታባቸው ያልኩት በዚህ ምክንያት እንጂ ስድብ አይደለም!!
አንባቢ ልብ እንዲለው የምፈልገው ነገር ቢኖር አብነት ስሜ፣ በ”ወሪሳ” መጽሐፍ ላይ በሰጠው አስተያየትና ስለ ኮከብ ቆጠራ (አስትሮሎጂ) “ልፈፋው”፤ ለመሞገት ሞከርኩ እንጂ በሌላ ጉዳይ ላይ ሐሳቤን አልሰነዘርኩም፡፡ የስድብ ቃልም ሆነ ዘለፋ ተጠቅሜ ከሆነ ከመረገምም ባሻገር ሕግ ፊት እንዲያቆሙኝ ይሁን፡፡ ይሕንንም ለማመሳከር ከዚህ በፊት የወጣውን ጽሑፌን በማንበብ፣ የአብነት ስሜን አስተያየትም ሆነ የአደዳ ኃይለ ሥላሴን ምላሽ ከማንበቤ በፊት፤ የዓለማየሁ ገላጋይ “ወሪሳ”ን በሚገባ በመረዳት፣ የአብነት ስሜን አስተያየትና የእኔን አስተያየት በመዳኘት፣ ፍርዱን ለሕሊና ሰጥቻለሁ! ከሕሊና ፍርድ አያመልጡምና፡፡
አዲስ አድማሶች፤በዚህ አጋጣሚ ይህን አይነት የሐሳብ ልውውጥ መድረክ ማመቻቸታቸውን በማመስገን፤ከዚህ በፊት “ቀጣይ ክፍል” በሚል የጻፍኩትን ጽሑፍ እንዲያወጡልኝ በትሕትና እጠይቃለሁ! እናንብብ፣ እንጠይቅ፣ እናመዛዝን፣ እንወያይ፣ እንሳተፍ፣ እንምረጥ- እንሻሻል!!
ከዝግጅት ክፍሉ
የጋዜጣችን ዓላማ የውይይት መድረክ በመክፈት ሃሳቦች በሰለጠነ መንገድ እንዲንሸራሸሩ ማድረግ ሲሆን በዚህም ሂደት አንባቢያን እውቀትና ግንዛቤን ይቀስማሉ፤የውይይት ባህልም ይዳብራል ብለን እናምናለን፡፡
 ፀሃፊው አቶ ተስፋዬ፤የላኩልን “ቀጣይ ክፍል” እኛ ዘንድ መኖሩ እውነት ነው፡፡ ሆኖም ርዕሰ ጉዳዩ ከሞላ ጐደል ከላይ በቀረበው ጽሁፍ የተዳሰሰ በመሆኑ ቀጣዩን ክፍል ማስተናገድ አንባቢያንን ስለሚያሰለች በዚሁ ቋጭተነዋል፡፡

Published in ህብረተሰብ

    ነገ ደመራ ነው፤ ተነገ በስቲያ ደግሞ የመስቀል በዓል፡፡ “እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሰን” መባባል የወግ ነው፡፡ ጉዳዩ የመሚለከተን ሆኖ ሲገኝ የችቦ መዋጮአችንን ይዘን ነገ የሚተረኮሰው ደመራ ላይ ብርሃን ወካይ እሣታችንን እናዋጣለን፡፡ ቢመለከተንም ካላመቸን ደግሞ በየደጃፋችን ላይ ደጃፍ ወካይ ደመራ መተኮስ የሚያስችል አማራጭ አለን፡፡
እንግዲህ ነገ…
…ከሰአት በኋላ ደብርና አድባራት የሚወክሉ፡፡ ዲያቆናት ዝማሬአቸውን ይዘው ብቅ ይላሉ፡፡ ቀሳውስቱም ከሽብሸባ ጋራ ደምቀው ጐዳናውን ያደምቃሉ፡፡ ይሄ እለት የመስቀልን በዓል ባህሉ አድርጐ ለኖረ ማህበረሰብ ልዩ ትርጉም አለው፡፡ ለባዕዶችም እንዲሁ፡፡ ከአዲስ ባህል ጋር መተዋወቂያቸው ነው፡፡ አንዳንድ ባዕዳን ግን ይሄን ደማቅ የመስቀል በዓል ሥነ - ሥርዓት የሚወዱት አይመስልም፡፡ ለምሳሌ ሮማን ፕሮቻዝካ የተሰኘ ጀርመናዊ ጋዜጠኛ ጽፎት ደበበ እሸቱ የተረጐመው “ኢትዮጵያ የባሩዱ በርሜል” የተሰኘ መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ የሚል ነገር አንብቤአለሁ፡-
“ኦብዘርቫቶር ሮማኖ የተባለ የህትመት ውጤት እንኳን በእውነት በጣም ቀና በሆነ አመለካከትና ትዕግስት በሰፈነበት ሁኔታ ስለ ኃይማኖታዊው ሥርዓትና ኋላቀር ስለሆነው የአገልጋዮች ሁኔታ መፅሐፍ አውጥቷል፡፡ ያንን ንፅህና የጐደለውንና ማይማን የሆኑት የጉባኤ አባላት ክምችት የሚያቀርቡትን ከዚያ ኋላቀር ከሆነው ዳንሳቸው ጋር አረመኔያዊነትና የመናፍስት አምልኮ ቅልቅል የሆነውን ባህል እንዴት “የሃይማኖታዊ ሕብረተሰብ ባህላዊ ሀብት” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል”
የፕሮቻዝካ አስተያየት የንፁህ አእምሮ ፍርድ እንዳልሆነ የምናውቅ እናውቀዋለን፡፡ ይሄ ሰው በጋዜጠኝነት አገራችን ገብቶ በሰላይነት ሲያገለግል በመገኘቱ ተይዞ የተባረረ ነው፡፡ በእምነት ሥርዓታችን ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ላይ ያለው ድምዳሜ የጥላቻና የበቀል ፍላጐትን ያንፀባረቀ የሆነው ለዚህ ነው፡፡ እሱን ትተን ወደ ደማቁ በዓላችን እናዝግም፡-
እንግዲህ ነገ የምናከብረው የደመራ በዓል ማስታወሻነቱ ለንጉስ ቆስጠንጢኖስ እና ለእናቱ ለንግሥት እሌኒ ኃይማኖታዊ ተግባር ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቸነከረበት ሥፍራ መስቀል ከተቀበረበት ሥፍራ በቁፋሮ እንዲገኝ ሁኔታውን ያመቻቸች ንግሥቷ ነበረች፡፡ ከሦስት መቶ አመት በኋላ መሆኑ ነው፡፡ ሥፍራው ቆሻሻ መጣያ ሆኖ በመቆየቱ ደብዛ አልነበረውምና ንግሥቲቱ ግራ ቢገባት ደመራ አስደምራ አንድ ዳውላ እጣን ጨመረችበት፡፡ የእጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ አርጐ ቁልቁል በመውረድ መስቀሉ የሚገኝበትን ትክክለኛ ሥፍራ ጠቆመ፡፡ በዚህ ጥቆማ መሰረት ግማደ መስቀሉ በቁፋሮ ተገኘ፡፡ ነገ ይሄን እለት ደመራ በመደመር እንዘክራለን፡፡ “ኢዮሃ አበባዬ!” እንላለን፡፡
ደመራው የቀሳውስት ድግ ታጥቆ፤ በሽርጉዳችን የኰራ መምሰሉ የግድ ነው፡፡ እስኪለኮስ ድረስ በጊዜያዊ ማጊያጊያጫ ባንዲራ ይታጠቃል፡፡ አደይ አበባ ይጐናፀፋል፡፡ ዝማሜውን በአርምሞ ይቃኛል፡፡ አመሻሹ ላይ መኰፈሱና አበባ መጐናፀፉ አብቅቶ እሳት ይተኮሣል፡፡ ሆታ እና እልልታ ከደመራው ቀድሞ ይጋያል፡፡ ኦሆሆሆሆይ! እናንተን ቱሪስት ማድረጌ ነው ይሄን ሁሉ የምዘበዝበው? አንዳንዴ እንዲህ ነው፡፡ የኖቤል ተሸላሚ ሕንዳዊውን ባለቅኔ ራቢንድራናት ታጐርን የሆንኩ መሰለኝ፡፡ ታጐር አንድ ቅኔ አለችው፡፡ “ጊታንጃሊ” ሲል ሰይሟታል፡፡ የዚች ቅኔ ግብ ተፈጥሮን መተንተን ነው (ተፈጥሮ ለኛ ባዕድ የሆነች ይመስል) እናም ዛፉን፣ ፀሐዩን፣ ቢራቢሮውን፣ አበባውን፣ አየሩን…እያማለለ! ያቀርብልንና ቅኔውን ሲቋጭ “እ-ህ? ምን እኔን ፈዘህ ታደምጣለህ? ውጣና እራስህ ተመልከተው እንጂ” ይላል፡፡ እንዲያ ነው፡፡ የእኔም ድርጊት የደመራን ሥነ - ሥርዓት እየዘገቡ እዚያው ላለው ሰው ማቅረብ መሰለ፡፡ ይሁን!
ለዚህ ፅሁፍ መነሻ ወደሆነኝ ርዕሰ ጉዳይ ላምራ…
…ደመራ መተኰሱ ከጨለማ ዘመን ወደ ብርሃን መሸጋገራችንን የሚዘክር ብቻ አይደለም፡፡ መጪው ዘመን እንዴት ያለ ባህርይ እንዳለው መተንበያ ጭምር ነው፡፡ መጀመሪያ ደመራው ነዶ ካለቀ በኋላ ዝናብ የሚያጠፋው ከሆነ እንደመልካም ገጠመኝ ይቆጠራል፡፡ “እሰይ፣ እሰይ” ይባላል፡፡ መጪው ጊዜ ላይ ተስፋ ይጣላል፡፡
ደመራው ነዶ ከማለቁ በፊት ደግሞ አወዳደቁም ሌላው ትንበያ ነው፡፡ የደመራው አወዳደቅ አቅል መጪውን ጊዜ የሚተነብይ ተደርጐ ይወሰዳል፡፡ ከደመራው በስተደቡብ ቆመን ወደ ሰሜን ስንመለከተው፣ በስተቀኛችን (ወደ ምሥራቅ) ከወደቀ፣ መጪው ጊዜ ጥጋብና ሰላም ነው ይባላል፡፡ እንዲያ ሳይሆን ቀርቶ ደመራው በስተግራችን (ወደ ምዕራብ) ከወደቀ የጨፍጋጋ ዘመን መጠቆሚያ ነው፡፡ ረሃብና ጦርነት በጨካኝ እጆቻቸው ያስተናግዱናል፡፡
ታገል ሰይፉ “ቀፎውን አትንኩት” ሲል እንደገጠመው ያለ ነው፡፡ የሰው ልጅ በመጪው ጊዜ ላይ ያለው ተሳትፎ ተቀጥቦ የተሰጠውን መቀበል ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሰላምን በማምጣት፣ ጦርነትን በማስቀረት፣ ጥጋብን በማስፈን፣ ረሃብን በማስወገድ በኩል የሰው ልጅ ድርሻ አልተቸረውም፡፡ እንደ አራስ ልጅ ተንጋሎ ከመሣቅና ከማልቀስ ውጭ ነገሮችን እንደሚመቸው አድርጐ የመለወጥ ብቃትም ሆነ ሐላፊነት የለውም፡፡ ተቀጥቦ የተሰጠውን ይቀበላል እንጂ ቢወጣ ቢወርድም ጦርነቱ አይቀርም፤ በጠላትነት ተነስቶ ቦምብ ቢያከማችም፣ ቢጠመድም፣ ቢያፈነዳም ሰላሙ አይስተጓጐልም፡፡ ሺህ ምንተሺህ ትራክተር ጠምዶ ቢያርስም፣ እርዳታ ተቀብሎ ቢያከማችም የተባለው ረሃብ አይቀርም፡፡ ደግሞም የተመረተውን ሁሉ እሳት ውስጥ ቢማግድም አንዴ ደመራው ወደ ቀኝ ወድቋልና ጥጋቡ ግድ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ደመራ ነክ ትንበያ፣ ለማህበረሰብ ትልቅ ጫና ሳይኖረው አይቀርም፡፡ የሰው ልጅ መጪውን አይቶ ካላመለጠ፣ አዘናነቡን ተመልክቶ ካልተጣለለ፣ እጥረት ሰግቶ በቁጠባ ካልዳነ… ምኑን የሰው ልጅ ሆነው? የመጣው እንደመጣ እያወቀ ዝም ብሎ ከጠበቀ ምኑን ከእንስሳ ተለየው? የደመራ አወዳደቅ እንደ አዝማሪ ግጥም አቀባይ “ተቀበል” ያለንን ካዘመርን አደጋ አለው፡፡
ከመስቀል ደመራ ባሻገር የመስቀል ዶሮ እርድንም እንደዚያው መጪውን ጊዜ ተንባይ አድርጐ የሚወስድ የህብረተሰብ ክፍል አለ፡፡ አራጁ ፊቱን ወደ ሰሜን መልሶ ሲባርክ፣ የዶሮው አወዳደቅ እንደ ደመራው ሁሉ ፊቱን ወደ ምሥራቅ አዙሮ በግራው፣ ክንፉ በኩል ከሆነ፣ ጥጋብና ሰላም ይሰፍናል፡፡ በተቃራኒው ከሆነ ደግሞ እንዲሁ ዕጣ - ፈንታችን እንደተጣመመ ይቆጠራል፡፡
ምልኪ የዘመናዊ ህዝብ መተዳደሪያ ሊሆን እንደማይገባው እሙን ነው፡፡ “እንዲህ ስለሆነ እንዲህ ይሆናል” የሚል ምልኪ ከተፈጥሮ ጋር በቅጡ የማይተዋወቅ ጭፍን ሕዝብ አሚነ - ስብከት ነው፡፡ የእንዲህ ያሉ ምልኪዎች ጅማሬ ከክርስቶስ ልደት በፊት አምስት መቶ ዘመን አስቀድሞ ወደኖረው ግሪካዊ ፈላስፋ ፓይታጐረስ ይወስደናል፡፡ ፓይታጐረስ ከተጠይቃዊ አስተሳሰብ ባሻገር መላቅጣቸው የጠፋ የምልኪ ትዕዛዛትን ለደቀመዛሙርቱ አስተላልፎ ነበር፡፡ እርሱ እንደሚለው፤ መጪው ጊዜ እንዲሰምር መደረግ የሌለባቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ አተርን ጠርጥሮ መብላት፣ ነጭ አውራ ዶሮን ማረድ፣ መስቀለኛ ብረት መርገጥ፣ አበባን መቀንጠስ፣ በባዶ አውራ ጐዳና መዘዋወር፣ ከመኝታ ሲነሱ የገላን ሰንበር ከአልጋ ምንጣፍ ላይ እንዳለ መተው፣ ከቤት ሲወጡ ግራ እግርን ማስቀደም… ፈጽሞ የተከለከሉ ነበሩ፡፡ ነገሮች ወደ መጥፎ አዝማሚያ የሚሄዱት በእነዚህ ነገሮች መከናወን እንጂ በሌላ እንዳልሆነ አስረግጦ ያስተምር ነበር፡፡ እህስ? የእኛ ደመራና የዶሮ ዕርድ ከዚህ ምልኪ አይመደብ ይሆን? …፡፡ እስኪ ለማንኛውም እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሰን ብለን እንለያይ፡፡
  

Published in ህብረተሰብ

131 ዜጎቿን ያጣችው ኢራን፤ ሳኡዲ አረቢያን ተጠያቂ አድርጋለች
እስካሁን በአደጋው 717 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል

በሳዑዲ አረቢያ በሀጂ ስነስርዓት ላይ ከትናንት በስቲያ 717 ሰዎች በሞቱበት አደጋ የአገሪቱ ባለስልጣናት እየተወዛገቡ ሲሆን፤ የኢራን መንግስት 131 ዜጐቹ መሞታቸውን በመግለጽ የሳዑዲን መንግስት ተጠያቂ አድርጓል፡፡
ከመካ በ5 ኪ.ሜትር ርቀት በሚገኘው ሚና የሚባል አካባቢ፣ በሰይጣን ላይ ድንጋይ የመወርወር ሃይማኖታዊ ስነ ስርአት ላይ በተፈጠረ ግርግር ነው አደጋው የተከሰተው ተብሏል፡፡ የብዙዎችን ህይወት በቀጠፈው አደጋ፤ 863 ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ለሃጂ ስነስርዓት በሄዱ ኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰ አደጋ ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም፡፡
የኢራን መንግስት መሪ አያቶላ ሆሚኒ፤ አደጋው የተፈጠረው በሳዑዲ መንግስት ዝርክርክ አሰራር ነው፤ ለአደጋው ሙሉ ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት ብለዋል፡፡
የሳኡዲ የጤና ሚኒስትር ካሊድ አል-ፍሌህ በዚህ አይስማሙም፡፡ አደጋው የተከሰተው በምዕመናን ጥፋት ነው ብለዋል፡፡ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መንሱር አልቱርኪ፤ ተመሳሳይ ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ብዙ ምዕመናን፤ በተመሳሳይ ሰአት በጠባብ መተላለፊያ ላይ የፈጠሩት ግርግር የአደጋው መንስኤ ነው ብለዋል - ቃል አቀባዩ፡፡
የሀጂ ኮሚቴ ሊቀመንበር ልዑል መሃመድ ቢን ናይፍ በበኩላቸው፤ የአደጋው መንስኤ በአስቸኳይ ተጣርቶ እንዲቀርብላቸው ትዕዛዝ የሰጡ ሲሆን፣ የሀገሪቱ ንጉስ ሰልማን ግን የሀጂ ጉዳይ ድርጅቱ እንደገና እንዲዋቀር አዘዋል፡፡
በአደጋው ከሞቱት መካከል፣ 131 የኢራን፣ 14 የህንድ፣ 18 የቱርክ፣ 7 የፓኪስታን፤ 3 የአልጄሪያ እና 3 የኢንዶኔዢያ ዜጎችን ጨምሮ፣ ቁጥራቸው ያልተጠቀሰ የናይጄሪያ፣ ኒጀር፣ ቻድ፣ እና ሴኔጋል ዜጎች የአደጋው ሰለባ ሆነዋል ተብሏል፡፡
በሳኡዲ የብዙዎችን ህይወት የቀጠፈ አደጋ በአንድ ወር ውስጥ ሲያጋጥም ያሁኑ ሁለተኛው ነው፡፡ ከቀናት በፊት በመካ ታላቁ መስጊድ ላይ፤ የግንባታ ክሬን ወድቆ፣ 109 ሰዎች መሞታቸው ይታወቃል፡፡
ከትናንት በስቲያ ያጋጠመው አደጋ ከተሰማ በኋላ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ ባንኪሙን እና የካቶሊክ ፓፓስ ፍራንሲስ የሀዘን መልዕክታቸው ካስተላለፉት ቀዳሚዎቹ ሆነዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ1990 ካጋጠመውና 1426 ሰዎችን ለህልፈት ከዳረገው ተመሳሳይ አደጋ ቀጥሎ የሰሞኑ የበርካታ ምዕመን ህይወት የተቀጠፈበት አደጋ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡


Published in ዜና

ደንበኞች በሞባይል ቁጥራቸው ሂሳብ መክፈት ይችላሉ

    አንበሳ ባንክ ቤልካሽ ቴክኖሎጂ ሶሉሺንስ ከተባለ ድርጅት ጋር በመሆን በሱቆችና መደብሮች ገንዘብን በሞባይል ለማዘዋወር የሚያስችል አዲስ ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ አዋለ፡፡
የባንኩና የቤልካሽ ቴክኖሎጂ ሶሉሺንስ የሥራ ኃላፊዎች ሰሞኑን በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ደንበኞች በሚቀርባቸውና ለሸመታ በሚዘዋወሩባቸው ሱቆች የሞባይል ስልካቸውን በመጠቀም የገንዘብ ዝውውር እንዲያደርጉ፣ ገንዘብ እንዲልኩና እንዲቀበሉ፣ በሱቆቹ ገንዘብ (ተቀማጭ) ገቢ እንዲያደርጉ፣ ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ የሚያደርግ የሄሎካሽ አሠራር ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ደንበኞች በሞባይል ቁጥራቸው የባንክ አካውንት መክፈት የሚችሉበት አዲስ አሠራር  መጀመሩን የተናገሩት የሥራ ኃላፊዎቹ፤ ደንበኛው በሚሰጠው የግል የሚስጢር ቁጥር ገንዘቡን ማስቀመጥ፣ ማዘዋወርና መላክ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ እስከአሁን 200 ወኪሎች ወደተግባር መግባታቸውን የተናገሩት ኃላፊዎቹ፤ በቀጣይ አድማሳቸውን በማስፋት፣ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች አገልግሎታቸውን ለማዳረስ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
አንበሳ ባንክ ባለፈው ዓመት ካፒታሉን 6.2 ቢሊዮን ብር ያደረሰ ሲሆን 510 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል አለው፡፡
ቤልካሽ ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ አዳዲስ የፋይናንስ ሥራ አገልግሎቶቹን ለህብረተሰቡ በማስተዋወቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን እስከአሁን ሄሎ ዶክተር፣ ሄሎ ካሽ፣ ሄሎ ሎየር እና ሄሎ ሥራ የተባሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በሥራ ላይ አውሏል፡፡

Published in ዜና

ወንዞችም ይሞላሉ ተብሏል
   በመጪዎቹ የበጋ ወራት ወቅቱን ያልጠበቀ ከፍተኛ ዝናብ አዲስ አበባና አካባቢዋን ጨምሮ በአብዛኛው የሃገሪቱ ክፍሎች የሚጠበቅ ሲሆን ጐርፍም ሊከሰት ይችላል ተብሏል፡፡
የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ትናንት ባቀረበው የትንበያ ሪፖርት፤ በኤሊኖ ክስተት ምክንያት ካለፉት አመታት በተለየ የክረምቱ ዝናብ ዝቅተኛ እንደነበር ጠቅሶ የዝናቡ ስርጭት በመጪዎቹ የበጋ ወራት ያይላል ብሏል፡፡
ከጥቅምት ጀምሮ የሚጠበቀው ዝናብ፤ በደቡብና በደቡብ ምስራቅ የሃገሪቱ ክፍሎች ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የተባለ ሲሆን በተለይ በቦረና ጉጂ፣ ባሌ፣ ሶማሌና በደቡብ የኢትዮጵያ ክልሎች ዝናብ መዝነቡ ለአርብቶ አደሩ የግጦሽ ሣርና የመጠጥ ውሃ ከማስገኘቱ አንፃር ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡
በድርቁ ክፉኛ ተጐድቶ የነበረው የአፋር ክልልም በበጋው በቂ ዝናብ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአንፃሩ በበጋው ወቅት ደረቅ መሆን ይጠበቅባቸው በነበሩ የሀገሪቱ ሰሜን፣ ሰሜን ምስራቅ፣ መካከለኛው እና ምስራቅ አካባቢዎች ላይ የሚዘንበው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፤ የደረሱ ሰብሎች ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል ተብሏል፡፡ ለአርሶ አደሩም በየጊዜው መረጃ በመስጠት ምርቱን በጊዜ እንዲሰበስብ ማድረግ ይገባል ተብሏል፡፡
በአጠቃላይ ቀጣዩ የበጋ ወቅት ከዚህ በፊት ከተለመደው ውጪ ዝናባማና እርጥበታማ ሆኖ እንደሚዘልቅ የጠቆመው ኤጀንሲው፤ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ከወትሮው በተለየ ጐርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብም ያጋጥማል ብሏል፡፡
ጐርፍ ያስከትላል ተብሎ በሚጠበቀው ከባድ ዝናብ መነሻነትም በዋቢሸበሌ፣ ገናሌና ኦሞ ወንዞች ላይ ከወትሮው በተለየ ሙላት ያስከትላል ተብሏል፡፡ በበጋው ወቅት ደረቅ መሆን ሲገባቸው ዝናብ የሚዘንብባቸው አካባቢዎች፣ ከሚፈጠረው ደመናና ዝናብ የተነሣ፣ ከከፍተኛ ቅዝቃዜና ውርጭ ስጋት ነፃ ሊሆኑ እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡
የበጋውን ወቅት ወደ ክረምትነት ይቀይረዋል የተባለው የአየር ፀባይ መዛባት (የኢሊኖ ክስተት) ወደ አመቱ አጋማሽ አካባቢ ቀስ በቀስ እየቀነሰ ወደ መደበኛው የአየር ፀባይ ይለወጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም የሜቲዎሮሎጂ ትንበያ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡  

Published in ዜና

   ከ1988 እስከ 1997 ድረስ ባሉት ዓመታት ያለህጋዊ ፈቃድ ለተያዙ ከ34 ሺህ በላይ ቦታዎች፣ መንግስት የይዞታ ማረጋገጫ ሊሰጥ ማቀዱን፣ የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ፅ/ቤት ገለፀ፡፡
የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች የስራ ሂደት መሪ አቶ ማርቆስ አለማየሁ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ይዞታዎቹ ለቀጣይ ልማት የማይፈለጉና በ1997 ዓ.ም በተነሳው የአየር ፎቶግራፍ ውስጥ የተካተቱ መሆን አለባቸው፡፡
ከ44 ሺህ በላይ ለሆኑ ፍቃድ የሌላቸው ቦታዎች፣ የይዞታ ማረጋገጫ ለመስጠት መታቀዱን የገለፁት አቶ ማርቆስ፤ እስካሁን ድረስ 11ሺህ ለሚሆኑ ማረጋገጫው እንደተሰጣቸው ጠቁመው ዘንድሮ ከ30ሺህ በላይ የሚሆኑትን እንደሚያስተናግዱ ገልፀዋል፡፡
መንግስት ቀደም ያሉ ዓመታትን የመረጠው የቤት ልማት ፕሮግራሙ ያልተጀመረበት ጊዜ በመሆኑ ነው ያሉት የሥራ ሂደት መሪው፤ በአሁኑ ወቅት ግን ህብረተሰቡ በተዘጋጀው የቤት ልማት ፕሮግራሞች  ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ከ1997 በኋላ የተካሄዱ ማንኛውም አይነት የመሬት ወረራዎች ተቀባይነት የላቸውም ያሉት አቶ ማርቆስ፤ መንግስት ከተጠቀሰው ጊዜ በኋላ በተሰሩ ቤቶች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ ገልፀዋል፡፡
ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ በከተማዋ ለረጅም ዓመታት ሰነድ አልባ የሆኑ ይዞታዎች ሰነድ እንዲያገኙ ሲሰራ መቆየቱን በመግለፅም ከ2002 ጀምሮ ከ66 ሺህ በላይ ይዞታዎች ሰነድ እንዲያገኙ መደረጉን የሥራ ሂደት መሪው ጠቁመዋል፡፡

Published in ዜና
Saturday, 26 September 2015 08:22

ለአዲስ አድማስ አዘጋጅ

     ባለፈው ቅዳሜ በወጣው የአዲስ አድማስ ዕትም ላይ፤ አደዳ ኃይለ ሥላሴ፤ “በአብነት ስሜ ላይ ለተሰነዘሩ ትችቶች የተሰጠ ምላሽ” በሚል ርዕስ የጻፉትን አነበብኩ። ደግሜም አነበብኩት። በዚሁ ጋዜጣ ላይ ወሪሳ ስለተባለው የአለማየሁ ገላጋይ መጽሐፍ አብነት ስሜ ባቀረቡት ሂሳዊ ጽሁፍ ላይ ለተሰጠ አስተያየት ምላሽ  ነው።
አንድ በ1960 ገደማ የደረሰብኝን ገጠመኝ አስታወሰኝ። በወቅቱ ዩኒቨርስቲ የህግ ተማሪ ነበርኩ። በአማርኛ ጋዜጦች በተለይ በ “አዲስ ዘመን” ሳምንታዊ አምድም ነበረኝ። አንዴ ለዚያ አምድ ያዘጋጀሁት ጽሁፍ አይወጣም ተብሎ ታገደ። አጋጁ ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ነበሩ። የማስታውቂያ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስቴርና የሳንሱር ሐላፊም ነበሩ። ከኔ ጋር ተቀራርብናል። አንድ ቀን ጠየኳቸው፤
 “ብላታ ይኸ የዘመኑ ሰው ብዙ እርስዎ ባልነበሩበት የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሊጽፍ ይችላል። አንዴት ለክተው ነው ያልፋል ይወድቃል የሚሉት?” አልኳቸው።
መለሱልኝ፤“ልጄ ሙት ቀላል ነው!” አሉኝ በጥሞና፤ “እኔ ካልገባኝና ካልተረዳሁት አያልፋትም!”
 ይህ የአደዳ ጽሁፍ ያንን አስታወሰኝ። መልእክቱ ካልገባን ካልተረዳን፥ (ሁሉንም ልናውቅና ልንረዳ አንችልምና)  ዞር- ዞር ብሎ መጠየቅና ማፈላለግ ነው። ካፈላለጉት ምንጩ (ጮቹ) እዚያው አሉልን። ሊገመት በሚችለው ምክንያት ሁሉ ብላታን እንዲያ አላልኩም። ልላቸው ተገቢም አልመሰለኝም።
ለምንናገረው፤ለምንጽፈው ሐላፊነትና ተጠያቂነት ለጀማው አንባቢ አለብን። ከሁሉም  በላይ ግን ተጠያቂነቱ ለራሳችን  መሆን   አለበት። ለራሳችን ታማኝ ከሆንን ለጀማውም ታማኝነቱ ከዚያ ይፈልቃል።  የሐምሌትን  በተዘዋዋሪ መንገድ መጥቀስ መሞክሬ ነው፡-
“This above all: to thine own self be true,
And it must follow, as the night the day,
Thou canst not then be false to any man.”
ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን እንዴት እንደተረጎመው በቃሌ ማስታወስ አልቻልኩም። በሒስና ኂስ መካከል ያለውንም ልዩነት ተማርኩ። እንደኔ  እንደኔ፣ ይህ የአደዳ ጽሁፍ አልፎ አልፎ ደጋግሞ ቢወጣ ጥሩ ይመስለኛል። “ጠንቀቅ ነው ደጉ!”  የሚል ይመስለኛል። ቀይ መብራት እንዳንጥስ ደውል ሆኖ ሊያገልግል የሚችል ይመስለኛል። እኔኑ ጨምሮ!
ከአክብሮት ጋር
አሰፋ ጫቦ
Corpus Christi Texas USA

Published in ባህል

    ከዕለታት አንድ ቀን ሚያሚ ለሚባለው ጋዜጣ፣ የቀብር ሥነስርዓት ክፍል ስልክ ተደወለ አሉ፡፡
ደዋይዋ ሴት ናት፡፡
“የአንድን ሰው የህይወት ታሪክ በመቃብሩ ላይ ፅፎ ለመቅረፅ ምን ያህል ይፈጃል?” አለች ሴትዮዋ፡፡
የጋዜጣው ሠራተኛ በትህትና፤
“ለአንድ ቃል አምስት ዶላር ያስፈልጋል እመቤት”
“ጥሩ” አለችና ሴትዮዋ ከጥቂት ጊዜ እረፍት በኋላ፤
“እርሳስ ይዘሃል?”
“አዎን እመቤት”
“ወረቀትስ ከአጠገብህ አለ?”
“አዎን እመቤት”
“እሺ እንግዲያው የምታፅፊለትን ቃል ልምረጥ”
“መልካም”
“እንግዲያው የእኔ እመቤት፤ ቦጋለ ሞቷል” ብለህ ፃፍ፡፡
“ይኸው ነው? በቃ?” አለ ፀሐፊው ባለማመን፡፡
“አዎን ይሄው ነው” አለች ሴትዮዋ
“እመቤቴ በስህተት አንድ ቁም ነገር ሳልነግርዎ ዘንግቻለሁ”
“ምንድን ነው የዘነጋኸው?”
“ከአምስት ቃላት በታች መናገር ክልክል ነው፡፡ አምስት ወይም ከአምስት በላይ መጠየቅ ነበረብዎ”
“እሺ፤ ጥቂት ደቂቃ እንዳስብ ፍቀድልኝ” ብላ ፍቃዱን ጠየቀች፡፡”
ጥቂት ደቂቃ አሰበችና
“እሺ እርሳስና ወረቀት ይዘሃል?”
“አዎን፤ እመቤት፤ ይዣለሁ!”
“እንግዲያው ፃፍ”
“እሺ እመቤት”
“እንግዲያው ቦጋለ ሞቷል - የሚሸጥ ካዲላኩ መኪናው እንዳለ አለ - አሁንም አልተሸጠም” ብለህ አክልበት አለችው፡፡
*   *   *
እንደሁኔታው ተስተካክሎ ቀዳዳዎችን መጠቀም አስተዋይነት ነው፡፡ መንገዶች ሁሉ በአንድ በኩል ብቻ ነው የሚሄዱት ብሎ ግትር አለመሆን ታላቅነት ነው!
ዕውቀት እያነሰ በመጣ ቁጥር ሐሜትና ስለሰው መተቸት እጅግ የሚዘወተር ነገር እየሆነ ይመጣል፡፡ በዚህም ሳቢያ ችግርን በመላ ከመፍታት ይልቅ ከአፍ አፍ ማዛመት ዋና ሥራ እየሆነ ይሄዳል፡፡
“በነገር በተተበተበ ማህበረሰብ ውስጥ ለብልሆች ስድቦች የጋራ ይደረጋሉ፡፡ ሐሜትንም ከሰው ሰው ይለዋወጡታል፡፡ (insults are shared and gossip is exchange) ይሄ የሆነበት ምክንያት ሐሜትን ማዛመት ከመቅለሉም የበለጠ አዝናኝና አስደሳች በመሆኑ ሲሆን፣ መቼም ቢሆን መቼ የሌሎችን ስህተት መለየትና ታርጋ መስጠት የራስን ህፀፅ ከማየት የቀለለ በመሆኑ ነው” ይሉናል ፀሐፍት፡፡
በየጊዜው ስለሚዲያዎች ክፉ ክፉው ይወሳል፡፡ ሚዲያዎች እንደአስፈሪ ጠላቶች መታየታቸው በየትኛውም ሥርዓት የሚከሰት ጉዳይ ነው፡፡ ያለነገር አይደለም፡፡ መረጃዎች ህብረተሰብን ያነቃሉ፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ ይህ ግን በአዎንታዊም በአሉታዊም ውጤት ሊፈረጅ ይችላል፡፡
“ፈላጭ - ቆራጭ መንግሥታት ሁነኛ ጫና በግል ሚዲያዎች ላይ ማሳረፋቸው የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የህዝብ ፍላጐት ብዙውን ጊዜ የሚቀሰቀሰው በድራማዊ ክስተቶችና ስማቸው በገነነ የተከበሩ ሰዎች እንዲሁም ሚዲያውን እንደራሳቸው ቤት ርስተ - ጉልት ባደረጉ ግለሰቦች ነው ይለናል - ዳንኤል ካህኔማን (Thinking, Fast and Slow)”
የአዕምሮአችንን ውሱንነት መዘንጋት የሚከሰተው እናውቃለን ብለን ባመንበት ነገር ያለን ለከት የለሽ በራስ መተማመን እና የድንቁርናችንን ሙሉ ገጽታ ለመረዳት ብቃት ማጣት እንዲሁም የምንኖርበትን ዓለም በጥርጣሬ መሞላት ልብ አለማለት ነው! በመጨረሻ የአገራችን የኢኮኖሚ ጣጣ ዛሬም መንገድም ኖሮ፣ አበባም ኖሮ፣ ባቡርም ኖሮ፤ ምን ሆነ? የሚለው ነው፡፡ ሙሰኛና ሙሰኛ ጀርባቸውን በሚተሻሹበት አገር ልማት ይኖራል ወይ? የሚለው ጥያቄ መልሱ አንድና አንድ ነው
ሹም ለሹም ይጐራረሳሉ፤
ድሃ ለድሃ ይላቀሳሉ!!
የልማት መርሀ - ግብር ሙስናን አይሽረውም እንደማለት ነው!!

Published in ርዕሰ አንቀፅ

         በዚህ ጽሑፍ የማነሣቸው ርእሰ ጉዳዮች በአራት የተከፈሉ ናቸው፡፡ አንደኛው፡-  ስለ ዩኒቨርስቲ አጠር ያለ መሠረታዊ ሐሳብ እና የአካዳሚያዊ ነጻነት መርሖዎች፤ ኹለተኛ፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመንግሥት መዳፍ ሥር ስለ መውደቅ፤ ሦስተኛው፡- የፕሬዝዳንት ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬን ገጸ ሰብእና (persona) በኹለት ወጎች ሥር ማብራራት ሲኾን፣ አራተኛው፡- የርእሰ ጉዳዮቹ ማጠቃለያ ነው፡፡

(ሀ) ዩኒቨርስቲ እና አካዳሚያዊ ነጻነት
ከኹሉ አስቀድሞ አንባቢ ልብ እንዲልልኝ የምፈልገው፣ በዚህ ጽሑፍ የቀረቡት አስተያየቶች እና ምልከታዎች እንደ አንድ በፍልስፍና መስክ የተሰማራ ሰው መጠየቅ ያለባቸውን ነገሮች ለመጠየቅ ያለሙ ናቸው፡፡ ይህም ሐሳቦቹ እና ምልከታዎቹ በአጠቃላይ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ከመከጀል ብቻ ሳይኾን ሳንጠይቃቸው ብናልፍ ትክክል አይኾንም ከሚል እምነት በመነሣት ነው፡፡
የዚህ ጽሑፍ አንደኛው ዓላማ የሚያጠነጥነው፣በዩኒቨርስቲ ምንነት ዙሪያ በመኾኑ ስለ ዩኒቨርስቲ ጠቅለል ያለ ዕሳቤ እና በተጨማሪም ዩኒቨርስቲን፣ “ዩኒቨርስቲ” የሚያሰኙትን ርእይ፣ ተልእኮ እና ግብ ማሳየት ነው፡፡
የዩኒቨርስቲ  ዋነኛው ርእይ እና ተልእኮ፣ ዕውቀት ማፍለቅ ሲኾን፣ ያፈለቀውንም  ለተማሪዎች ማስተላለፍ እና መተግበር ነው፡፡ ይህም ማለት የዩኒቨርስቲ ዋነኛው ተግባር ከዘመን ዘመን እየተሸጋገረ አኹን ላይ የደረሰውን ዕውቀት መጠበቅ እና መከባከብ እንዲኹም በተሟላ መልኩ ለትውልዱ ማሳወቅ እና ማስተላለፍ ነው፤ በተጨማሪም ከዚህ በፊት ያልነበረውን ሐሳብ እና ዕውቀት መፍጠርም ነው፡፡
ዩኒቨርስቲ የአንድ ሀገር ምሁራዊ ህልውና እና የሥልጣኔ ዕድገት መገለጫ በመኾኑ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ከሌሎች ተቋማት በተሻለ የሕግ እና የነጻነት መብት ሊሰጠው ይገባል፡፡ እዚህ ላይ ትልቁ የጀርመን ፈላስፋ ካርል ያስፐርስ ስለ ዩኒቨርስቲ ምንነት ሲገልጹ፤ ዩኒቨርስቲ በመንግሥት ቁሳዊ እና ፋይናንሳዊ ድጎማ የሚተዳደር ቢኾንም ከሌሎች ተቋማት ለየት የሚያደርገው የራሱን ርእይ እና ተልእኮ ቀርጾ የሚተገብር እና የሚንቀሳቀስ አንጻራዊ ነጻነት ያለው በመኾኑ ነው፡፡ ለዚህም ነው፣ የዩኒቨርስቲ መምህራን የመንግሥት ደመወዝተኛ ቢኾኑም እንደ ሌሎቹ የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች (civil servants) የመንግሥትን ፖሊሲ ለማስፈጸም የተቀጠሩ አገልጋዮች የማይኾኑት፡፡
በተጨማሪም የዩኒቨርስቲ ዐቢይ ተልእኮ የምንለው፣ ተቋሙ እውነት ላይ ለመድረስ ማንኛውም ጉዳይ የሚጠየቅበት እና የሚመረመርበት ማእከል መኾኑ ነው፡፡ ይህንንም ተልእኮ በአግባቡ ለመወጣት ዩኒቨርስቲ በልዩ ልዩ ተቋማት ሥር ለሚያካሒደው ጥናት እና ምርምር ያልተገደበ ነጻነት እና  መብት ይኖር ዘንድ ግድ ይላል፡፡ ዩኒቨርስቲ ነጻነቱን በማስቀደም ነው፣ የዕውቀት መዲና እና መፍለቂያ ኾኖ  ከዘመን ዘመን እየተሸጋገረ የመጣው፡፡ የዩኒቨርስቲ ነጻነትን ባነሣን ቁጥር የአካዳሚያዊ ነጻነት ጥያቄ ቁልፍ የኾነ ድርሻ ያለው መሠረታዊ ሐሳብ እንደ ኾነ ግልጽ ነው፡፡
(ለ) አካዳሚያዊ ነጻነት
አካዳሚያዊ ነጻነት ማለት ማንኛውም መምህር በሥራ ገበታው ላይ ሊኖረው የሚገባውን ነጻነት እና መብት የሚደነግግ  የሕግ መርሕ ነው፡፡ አኹን በዓለም ላይ በሰፊው ተቀባይነት ያገኙት የአካዳሚያዊ ነጻነት መርሖዎች፣ የዛሬ አንድ መቶ ዓመት ገደማ በአሜሪካን ሀገር በጉዳዩ ዙሪያ የጥናት ስብሰባ ከተደረገ በኋላ ተሳታፊዎቹ የሚከተሉትን አራት ነጥቦች አቅርበው፣ ሕጋዊ ከለላ ለማሰጠት በመቻላቸው እነሆ እስከ አኹን ድረስ ወሳኝ የኾኑ የአካዳሚያዊ ነጻነት መርሖዎች እና አዕማድ ኾነዋል፤ ፍሬ ሐሳቦቹም እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
1. የመመራመር እና የማሳተም ነጻነት
ማንኛውም መምህር በፈለገው እና በመረጠው ርእስ ምርምር እና ጥናት የማካሔድ ሙሉ መብት አለው፡፡ በተጨማሪም በምርምር ያገኘውን ውጤት ያለምንም ዕንቅፋት እና ገደብ የማሳተም መብት አለው፡፡
2. መምህር በክፍል ውስጥ ስለሚኖረው ነጻነት
ማንኛውም መምህር ለሚያስተምረው ትምህርት ይኾናል የሚለውንና የሚበጀውን የማስተማርያ ጽሑፎችን የማካፈል እንዲኹም ማንኛውንም ትምህርት ነክ የኾኑ ጉዳዮችን በውይይት እና በጥያቄ ያለምንም ጫና ለተማሪዎቹ ሊያቀርብ ይችላል፡፡
3. በትምህርት ተቋም ቅጽር ውስጥ የሚኖር መብት/Intramural Right)  
ማንኛውም መምህር አቅሙና ችሎታው እስከ ፈቀደ ድረስ የአንድን የዩኒቨርስቲ አስተዳደር እና አመራር ሳይፈራ እና ሳይሸማቀቅ የማሔስ እና የመተቸት ሙሉ መብት አለው፡፡
4. ከትምህርት ተቋሙ ቅጽር ውጭ ስላሉ ጉዳዮች የሚኖር መብት(Extramural Right)
ማንኛውም መምህር በሥራ ገበታው ላይ እያለ የሀገሩን የአስተዳደር፣ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ጉዳዮችን የመተቸት ሙሉ መብት አለው፡፡
እነዚህ ከላይ የተገለጹት መርሖዎች በሕግ ማህቀፍ ሥር መካተታቸው፣ በአካዳሚው ዓለም ውስጥ ለተሰማሩ መምህራን ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑና እንዲኹም ለወከባና ለእንግልት እንዳይዳረጉ መከታ ይኾናቸዋል፡፡
፪.
 አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ለመቆጣጠር የተደረገው ሒደት
ኢሕአዴግ ስለ ፖለቲካ ስትራቴጅና አቅጣጫ  በ1997 ዓ.ም. ባወጣው ሰነድ ላይ፤ ስለ ሀገሪቱ ምሁራን የሚከተለውን ግምጋሜ አቅርቧል፡፡ ግምጋሜው የታየበትን መነጽር፣ ከዚህ በታች ስለምናቀርበው የዩኒቨርስቲው በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መዋል መንደርደሪያ ይኾነናል፡፡
እንደ ኢሕአዴግ አመለካከት፣ምሁሩ ምንጊዜም ወደ ሥልጣን ማማተሩ ስለማይቀር በተቻለ መጠን የሥልጣን  መወጣጫ መንገዱ ተዘግቶ መያዝ አለበት፡፡ ይህን ለማሳካት ምሁሩ የንዋይ ፍላጎቱ በተቻለ መጠን እንዲሟላለት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በመኾኑም በሙያው ዙሪያ ባሉ ሳንካዎችና ጥቅማጥቅሞች ተጠምዶ ወደ ሀገራዊ ጥያቄዎች ሳይሻገር በእዚያው ማጥ እየዳከረ እንዲኖር ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ከዛሬ ስድስት መቶ ዓመት በፊት፣ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቅ፣ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ ከደረሷቸው መጻሕፍት መካከል ‘መጽሐፈ ምስጢር’ ብለው በሰየሙት ድርሳናቸው ውስጥ፣ ሳይማሩ እናስተምራለን ብለው ስለተነሡ የቤተ መንግሥት ባለሟሎች የሚከተለውን ብለው ነበር፡፡ ከአባ ጊዮርጊስ የወሰድነው ጥቅስ ሊቁ ለሌላ ጉዳይ የተናገሩት ቢኾንም ለያዝነው ርእስ የመንፈስ ቅርበት አለው ብለን ስለምናምን በዚሁ አገባብ የጠቀስነው መኾኑን ለአንባብያን እያስታወስን ጥቅሱን ያጎረሱንን መሪጌታ ሳናመሰግን አናልፍም፡፡
“እሉ እሙንቱ [መነኮሳት] እለ ቀዲሙ የዐየሉ ገዳመ አድባረ ወበዐታተ ወድኅረ ይትዋሐውሑ በአዕጻዳተ ነገሥት፡፡ ቀዲሙ  ከመ ኢይትመሀሩ መጻሕፍተ ነቢያት ወሐዋርያት በንኡሶሙ ወጽኡ ገዳመ ወተግኅሡ እምዐጸደ ቤተ ክርስቲያን እንተ ይእቲ  እመ ኩልነ ዘኢይነጽፍ ሐሊበ አጥባቲሃ፡፡ ወድኅረኒ  ኢይፈጽም ገድሎሙ በጽማዌ ውስተ ገዳም  ቦኡ ውስተ አብያተ ነገሥት ወበዊኦሙ ከመ ኢያርምሙ መሀሩ ዘኢትምህሩ ወሰበኩ ዘኢያእመሩ፡፡ ይልህቅኑ ሕፃን ዘእንበለ ሐሊበ አጥባተ እሙ ይሌቡኒ መነኮስ ዘኢተምህረ መጻሕፍተ ነቢያት ወሐዋርያት ከመ ይኩን መመህረ ለሰማዕያን ፡፡ ለሀወት ገዳም በኃጢአቶሙ ወለሀዋ አድባረ ምኔታት ወኢረኪቦቶሙ፡፡
“ለሀወት ቤተ ክርስቲያን በእንተ ዘነሠቱ አናቅጺሃ ነቢያተ ወነክነኩ አዕማዲሃ ሐዋርያተ፡፡ ወሠርዑ ሎሙ ሕገ ወሥርዓተ ዘኢይወጽአ እምእስትንፋሰ አፉሁ ለእግዚአብሔር ፡፡”
ትርጉም፡-
“እነዚህ [መነኮሳትም] ቀድሞ በበርሀ በተራሮችና በዋሻዎች የሚዘዋወሩ በኋላ ግን በነገሥታት ዐፀዶች  ውስጥ የሚመላለሱ ናቸው፡፡ ቀድሞ በታናሽነታቸው ጊዜ የነቢያትና የሐዋርያትን መጻሕፍት እንዳይማሩ የጡቶቿ ወተት የማይደርቅ የኹላችን እናት ከኾነች ከቤተክርስቲያን ዐፀድ ርቀው ወደ ገዳም ወጡ፡፡ ኋላም ገድላቸውን በገዳም ውስጥ ኾነው በጭምትነት እንዳይፈጽሙ ወደ ነገሥታት ቤት ይገባሉ፤ገብተውም ዝም እንዳይሉ ለራሳቸው ያልተማሩትን ያስተምራሉ፤የማያውቁትንም ይሰብካሉ፣ሕጻን ያለ እናት ጡት ያድጋልን? መነኩሴስ ለሚሰሙ ሰዎች አስተማሪ ይኾን ዘንድ ያልተማረውን የነቢያትና የሐዋርያትን መጻሕፍት ያስተውላልን?
“ቤተ ክርስቲያን ስለ ኃጢአታቸው አለቀሰች፡፡ የገዳማት ተራሮችም እነርሱን ባለማግኘታቸው አለቀሱ፤ቤተ ክርስቲያን ነቢያት በሮቿን ስላፈረሱ፣ ምሰሶዎቿ ሐዋርያትንም ስለነቀነቁ አለቀሰች፡፡ ከእግዚአብሔር አንደበት ያልወጣውንም ሕግና ሥርዓት ለራሳቸው ሠሩ፡፡”
ከላይ በጥቅስ ከተቀመጠው የአባ ጊዮርጊስ ትዝብት የሚከተሉትን ፍሬ ነገሮች ነቅሰን ማውጣት እንችላለን፡፡ የአመራረጣችን መሠረት፣ ባለንበት ወቅት አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንዴት ሙሉ በሙሉ በመንግሥት መዳፍ ሥር እንደ ወደቀ  የጥቅሱ መንፈስ ማሳያ ኾኖ ስላገኘነው ነው፡፡ አኹን በሥልጣን ላይ ያለው ሥርዓት፣ ከገጠር ወደ ከተማ እንደ መጣው ኹሉ፣ የአባ ጊዮርጊስም ‘ምሁራን’ ከበረሓ ወደ ቤተ መንግሥት የመጡ በመኾናቸው ተመሳሳይነታቸው ከፍ ያለ ነው፡፡
የቅዱሱን ተግሣጽ በኹለት ምድብ በመክፈል በመጀመሪያ፣ የትዝብታቸውን መነሻ ቀጥለን ደግሞ፤ ድርጊቱ ያስከተለውን አሉታዊ ዉጤት እናያለን፡፡
ሀ. የትዝብታቸው መነሻ፡-
የተወሰኑ ምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት በመፈለግ ወደ ዋሻ፣ አድባራት እና በረሓ ገቡ፡፡ መንፈሳዊ ተጋድሎ አልኾንላቸው ሲል በረሓውንና ዋሻውን ለቀው ወደ ቤተ መንግሥት ጠጋ አሉ፤ ወደ ቤተ መንግሥቱም አዘውትረው መመላለስ ጀመሩ፡፡ ከማዘውተራቸው ብዛት የቤተ መንግሥቱን አመኔታና ይኹንታ ተቀዳጁ፡፡ የሹማምንቱን ቅቡልነት ቢያገኙም በየበረሓው ወጣትነታቸውን በከንቱ አባክነው በዘመኑ ከቤተ ክርስቲያን ብቻ ይገኝ የነበረውን ትምህርት ሳያገኙ ስለቀሩ፣ የቤተ መንግሥት ባለሟልነታቸውን ተጠቅመው፣ ያልተማረውን ምእመን እናስተምራለን ብለው ተነሡ፡፡   
ለ. ድርጊቱ ያስከተለው አሉታዊ ውጤት፡-
አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፤ኹኔታው ያስከተለውን አሉታዊ ውጤት በኹለት ዘይቤ (Metaphor) ያስረዳሉ፡፡ እነዚህም፡- “በሮቿ ተሰበሩ” እና “አዕማዷ ተነቃነቁ” የሚሉት ናቸው፡፡
በሮቿ ተሰበሩ፡-
“በሮቿ ተሰበሩ” ከሚለው ዘይቤ ውስጥ በዛ ያሉ ምልከታዎችን መንቀስ ይቻላል፡፡ በር ስንል የሚፈለገው የሚገባበት፣ መግባት የሌለበትን ደግሞ  መቆጣጠሪያ ሥርዓት መኾኑን ነው የሚያመለክተው፡፡ በመኾኑም የተናጋና የተሰበረ በር ያለው ተቋም፤ ማንም እንዳሻው የሚገባበትና የሚወጣበት፣ ሥርዓት አልባ ጎዳና ኾኗል ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ልዕልና አስጠብቃ መዝለቅ ተስኗታል እንደማለትም ነው፡፡
አዕማዷ ተነቃነቁ፡-
የአንድ ቤት ዐምዱ ወይም ምሶሶው ከተነቃነቀ፣ጨርሶ የመፈራረሱ ጉዳይ ተቃርቧል ማለት ነው፡፡ በአባ ጊዮርጊስ ዕይታ፤ የቤተ ክርስቲያኒቷ ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊት በአጠቃላይ አስተምህሮዋ ተናግቷል ማለታቸውን ያሳያል፡፡ በተፈጠረው አግባብ የለሽ አካሔድና ቀውስ የቤተ ክርስቲያኒቷ አበው አዘኑ፤ አለቀሱም፡፡
ወደ ጥንተ ነገራችን ስንመለስ፤የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ አቀራረብ፣ አኹን በዩኒቨርስቲው ቅጥር ውስጥ የሚካሔደውን ኹኔታ በሚገባ ለመረዳት እንደ መነጽር ይኾነናል፡፡ ከኹሉ አስቀድሞ፣ የአባ ጊዮርጊስ ‘መምህራን’ እናስተምራለን ብለው የተነሡት ራሳቸው ሳይማሩ ያልተማሩትን ሰዎች ለማስተማር ነው፡፡ በእኒህ ኹለት ዓመታት ውስጥ፣ በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ እናሠልጥን ብለው የተነሡት የመንግሥት ሹመኞች ራሳቸው በሚገባ ሳይማሩ፣ አልተማሩም የሚሏቸውን ሳይኾን፣ የተማሩትን ክፍል ለማስተማር መነሣታቸው ነው፡፡ ከዚኽ አንጻር አባ ጊዮርጊስ የታዘቧቸው መምህራን ከአኹኖቹ እናስተምር ባዮች በእጅጉ የተሻሉ ኾነው እናገኛቸዋለን፡፡ ይኸውም የቀድሞዎቹ፣ ራሳቸው ባይማሩም እናስተምር ያሉት ያልተማሩትን ሲኾን የእኛዎቹ ግን እናስተምር ብለው የተነሡት የተማሩትን በመኾኑ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ በዚህ ዘመን ቢኖሩ ኀዘናቸው ምን ያኽል በበረታ ነበር!!
አባ ጊዮርጊስን በእጅጉ ያሳዘናቸውና ያስገረማቸው፣ ቤተ መንግሥት በፍጥረቷ የአስተዳደር መንገድ መቀየስ እንጂ የዕውቀት ምንጭ ወይም የምሁርነት ምኩራብ ሳትኾን፣ ዐዋቂዎች ነንና እናስተምር እያሉ የሚነሡባት ማእከል ኾና ስላገኟት ነው፡፡ አኹን ወዳለንበትም ጊዜ ስንመጣ፣ ብዙዎችን እያሳሰበ ያለው በየዩኒቨርስቲው እናሠልጥን እያሉ የሚመጡት ሰዎች አኳኋን ነው፡፡ ልክ እንደ አባ ጊዮርጊስ ‘ምሁራን’ አስቀድመው ወደ በረሓ ከወጡ በኋላ ተመልሰው ቤተ መንግሥቱን በቁጥጥራቸው ሥር አዋሉ፡፡ ከዚያም ቤተ መንግሥቱም ዩኒቨርስቲውም አይቅርብን ብለው የዩኒቨርስቲውን መምህራን እናስተምራለን ብለው ብቅ አሉ፡፡
የአባ ጊዮርጊስ ኀዘን የበረታው፣ እኒኽ ‘ምሁራን’ ቤተ ክርስቲያን እንደ በሮቿ የምታያቸውን የነቢያት አስተምህሮ ስለሰበሩና በምሰሶ የተመሰሉትን የሐዋርያትን ዶግማና ቀኖና ስላነቃነቁ ነው፡፡ ብዙዎችን ታዛቢዎች በእጅጉ እያሳሰባቸው ያለው በአስተማሪነትና በአሠልጣኝነት ስም፤ ዩኒቨርስቲው የዕውቀት፣ የጥበብ፣ የምርምርና የመሳሰሉት ዕሴቶች ገዳም ኾኖ ሳለ፤ ሊቃነ ማእምራኑ (ፕሮፌሰሮቹ) ያስቀመጧቸውን ሚዛኖች (በሮች) በመስበር አዕማዷን ስላነቃነቁት ነው፡፡የቤተ ክህነቱ በር እንደተሰበረው ኹሉ፣ የየኒቨርሲቲውም በር ተሰብሯል ስንል ዩኒቨርስቲው ተማሪዎቹንም ኾነ መምህራኑን  መርጦ የመቀበል መብቱ ተገፍፎ፣ በፖለቲካ ትእዛዝ እንዲሞላ በመደረጉ፣ ማንም እንዳሻው የሚገባበትና የሚወጣበት ኾኗል ማለታችን ነው፡፡ የአዕማዷን መነቃነቅ በምናነሣበት ጊዜ በዋናነት የምናቀርበው፣ ዩኒቨርስቲው የነበረው የማስተማር ሥነ ዘዴ ተሽሮ፣ ከፖለቲካ ኃይሉ በመጣ ማዘዣ፣ እነርሱ ይበጃል የሚሉትን አካሔድ ተግባራዊ እንዲያደርግ መገደዱን ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚኾነው፣ ከቢፒአር እስከ ቢኤስሲ እና አንድ ለአምስት አደረጃጀትን መምህራኑ ሳይመክሩና ሳይዘክሩበት፣ ዩኒቨርስቲው እንዲከተል መደረጉ ነው፡፡  የአባ ጊዮርጊስ ‘ምሁራን’፣ የመንግሥትን ኃይልና ቤተ ክርስቲያንን ገና በሚገባ ያልተቆጣጠሩ ሲኾን፣ የአኹኖቹ ምሁሮች ግን ሥልጣንን ሙሉ በሙሉ ለያዙ ኃይሎች ተጠሪዎች ናቸው፡፡ በመኾኑም ከንኡሳን (ደቃቂን) ሓላፊዎች  እስከ ዐቢይ አለቃው - ፕሬዝዳንቱ፣ ድረስ ለቤተ መንግሥቱ የፖለቲካ ቀኖና ተገዥና  ተኣማኒ በኾኑ እሺ ባዮች እንዲያዝ ተደርጓል፡፡  
እውነተኛ ዩኒቨርስቲያዊ ይትበሃል ተሽሮ፣ የበረሓ ጀግኖች እንዳፈተታቸው የሚናኙበት ኾነ፡፡ የመማር ማስተማር ሒደቱንም፣ ዩኒቨርስቲያዊ ልዕልናው ስለ ተገፈፈ ሳይንሳዊና ሞያዊ አሠራሩ ተሻረ፡፡ በቦታውም ከፖለቲካው ጽሕፈት ቤት በሚመነጭ ኢሕአዴጋዊ ትእዛዝ በሩን አፈረሱት፤ ዐምዱንም አነቃነቁት፡፡ ካርል ያስፐርስ የገለጹት ‘አማናዊው ዩኒቨርስቲ’ እና እውነተኞቹ ምሁሮቿ ስለ እነዚህ ሰዎች አድራጎት አብዝተው ያዝናሉ፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ሲቋቋም፣ ሊቁ ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ፣ የበሩን ኹለት አዕማድ ‘በዕውቀት’ እና ‘በሠናይ’ (Virtue) በመመሰል የዘመሩለት፣ ማንም ሰው ሊያየው በሚችለው መልኩ መሠረቱ ተናጋ፤ ውድቀቱም ተቃረበ፡፡



“ከ100% በላይ ተጠናቋል” … ምን ማለት ነው?

    አንድ ወዳጄ ሰሞኑን ስልክ ደወለልኝና፤ “ፋብሪካው ከ100% በላይ ተጠናቋል ይባላል ወይ?” አለኝ፤ የመገረም ቅላፄ በሚያስተጋባ ድምፅ፡፡
“ምን ማለት ነው? እንዴት?” አልኩት፤ በመገረም ሳይሆን ግራ በመጋባት፡፡
“የሆነ ዜና ላይ ሰምቼው እኮ ነው … የሶላር ማምረቻ ምናምን መሰለኝ”
እኔ ከመናገሬ በፊት ሌላ አስገራሚ መረጃ አከለልኝ፡፡
“ደሞ እኮ ገና ሥራ አልጀመረም!”
“ምኑ ነው ታዲያ ከ100% በላይ ተጠናቋል የተባለው?”
ለአፍታ ያህል በጥልቅ ሀሳብ ውስጥ ሰጠምኩ፡፡
“ግን የት ነው የሰማኸው…. ከየትኛው ሚዲያ?” ከጥልቅ ሃሳብ ውስጥ መንጥቆ ያወጣኝ ከአንደበቴ ያፈተለከው የራሴ ጥያቄ ነበር፡፡ ወዳጄ መለሰልኝ፡፡
“ከመንግስት ሚዲያ ነው … ኢዜአ ወይም ኤፍ ኤም …” (ያው የመንግስት ሚዲያ የመንግስት ነው ብሎ መለሰኝ!)
እኔ የምላችሁ ግን …  “ፋብሪካው ከ100% በላይ ተጠናቋል” ሲባል… እውነት ምን ማለት ነው? ኢህአዴግ ስንት በታማበት የግንቦቱ ምርጫ እንኳን ከ100 ፐርሰንት በላይ ውጤት አምጥቷል አልተባለም! (ቦርዱማ 100% የተባለውንም አስተባብሏል!)
አሁን እኔ ለማወቅ የጓጓሁት ምን መሰላችሁ? ፋብሪካ ወይም ኮሌጅ አሊያም ሆስፒታል… ከ100% በላይ ተጠናቋል ሲባል… ምን እንደሚመስል ነው፡፡
እውነቴን እኮ ነው የምላችሁ … ከ100% በላይ የተጠናቀቀ ምንም ነገር ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ ቆይ ግን? በምርጫስ ቢሆን … እገሌ ፓርቲ ከ100% በላይ በሆነ ድምፅ (ከየት መጥቶ?) አሸነፈ ይባላል እንዴ? (እዚህም ባይሆን እነ ሰሜን ኮሪጠ አካባቢ!) እኔ እንግዲህ ከወዳጄ መረጃ የተረዳሁት ምን መሰላችሁ? ከ100% በላይ ተጠናቋል ከተባለ፣ (ጦቢያ ምድር ማለቴ ነው!) “ሥራ አልጀመረም” ማለት ነው፡፡ (በምን ቋንቋ እንዳትሉኝ!)
መቼም ይሄን ዜና ያጠናቀረው ጋዜጠኛ፣ ቢያንስ “ቅጥ አምባሩ የጠፋ ዘገባ” በሚል ዘርፍ ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡ ለነገሩ እንዲህ አይነት ልማታዊ ጋዜጠኞች በሽበሽ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የEBC ጋዜጠኞች፤ የመንግስትን የልማት ስራዎች ወይም ስኬቶች ያለ ቅጥ በማጋነን፣ በመለጠጥና በማስፋት … ማንም የሚያህላቸው እንደሌለ በአስር ጣቴ ልፈርምላችሁ እችላለሁ፡፡ (ኧረ ኢህአዴግም ይፈርምላቸዋል!) እኔ የምለው ግን… “የግነት ጋዜጠኝነት” የሚባል ኮርስ አለ እንዴ? የኢህአዴግ ካድሬዎች እንዲህ ያለውን የ“ልማታዊ ጋዜጠኞች” ግነት፣ ለልማት ካላቸው ውስጣዊ መነሳሳትና መቆርቆር የመነጨ ነው … በሚል ሊገመግሙት ይችላሉ፡፡ ግምገማቸው ትክክል ነው … አይደለም የሚለውን ለመወሰን ግን አስቸጋሪ ነው፡፡ (“ውስጣዊ መነሳሳት” እና “መቆርቆር” የሚሉት ሃሳቦች መለኪያቸው ምንድን ነው?)
በነገራችን ላይ በየዓመቱ መስቀል ሲመጣ ትዝ የሚለኝ ... EBC ለበዓሉ ከመጡ የውጭ ቱሪስቶች ጋር የሚያደርገው ኢንተርቪውና ከዚያ ውስጥ የሚሰራው ግነት የበዛበት ዜና ነው፡፡ ይሄ እንኳን ዓላማው የአገር ገፅ ግንባታ በመሆኑ ችግር የለውም፡፡ ግን እኮ ዓላማው እንደተባለው ከሆነ፣ መቅረብ ያለበት ለኛ ሳይሆን ለውጭ ሰዎች ወይም ለኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ነበር፡፡ (እኛማ አረረም መረረም እየኖርነው ነው!)
ወደ “ልማታዊነት” ጉዳይ ልመልሳችሁ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየሚዲያው ተከታትላችሁልኝ ከሆነ … ከመንግስት ባለስልጣናት እስከ ወረዳ አስተዳደር፣ ከከፍተኛ ባለሀብት እስከ ጥቃቅንና አነስተኛ ነጋዴዎች … ወዘተ ድረስ ምንም ሲናገሩ “… ልማታዊነት” የምትለዋን ቃል በግድ መደንገር አለባችሁ የተባሉ ይመስላሉ፡፡ “ልማታዊነት” ቃሉን ደጋግሞ በመጥራት ብቻ የሚመጣ ከመሰላቸው ቀለጡ፡፡ (አስማት እኮ አይደለም!)
እውነቱን ለመናገር ይሄ አካሄድ ግን ጤናማ አይደለም፡፡ ልማታዊ የመንግስት አመራሮችንም ሆነ ልማታዊ ባለሀብቶችን ፈፅሞ አይፈጥርልንም (ልማታዊ ደስኳሪዎችን እንጂ!)
ከዚያ ዘለል ካለም እንደ EBC ጋዜጠኞች ያሉ “የልማት ተቆርቋሪዎችን” ይፈጥርልን ይሆናል፡፡ ችግሩ ግን በአሁኑ ዘመን ጦቢያ የሚያስፈልጋት … በተግባር የሚሰራላት እንጂ የሚደሰኩርላት አሊያም የሚቆረቆርላት አይደለም፡፡ ልማታዊ ለመሆን ካድሬ መሆን አያስፈልግም (ለነገሩ ካድሬ ልማታዊ ሆኖ አያውቅም!) ልማታዊነት እኮ በተሰማራንበት ዘርፍ ውጤታማ ስራ ማከናወን ነው፡፡ ኪሳራ ሳይሆን ትርፍ ማስመዝገብ፡፡ ከመንግስትም ሆነ ከህዝብ የተሰጠንን ኃላፊነት በብቃት መወጣት ነው - ልማታዊነት!!
የተሰጣቸውን ትልቅ ኃላፊነት ሳይወጡ ቀርተው፤ “ልማቱ ወደፊት እንዲገሰግስ አስበን፣ ልማቱ እንዳይደናቀፍ ሰግተን፣ ልማቱ እንዳይቋረጥ ጓጉተን … ወዘተ” ሰበብ ድርደራ አያዋጣም፡፡
እንደውም ከተቻለ ከካድሬ በቀር ሌላው የመንግስት አገልጋይና ሹመኛ ሁሉ “ልማታዊ” የሚለውን ቃል ያለቦታው እንዳይደነጉር መመሪያ ቢጤ ቢወጣ ሸጋ ነበር፡፡ (በልማታዊነት ስም ሆድ አባብቶ ኃላፊነትን መሸሽ ተለምዷል!)
እናላችሁ … ሁሉም በተሰማራበት ሙያና በተሰጠው ኃላፊነት ቢለካ ነው የሚበጀው  “ልማታዊ …” የሚለውን ቃል በየንግግሩ መሃል በመሸጎጥ፣ እርስ በርስ መሸዋወድ ይብቃን! “ልማታዊ ነኝ” ያለ ሁሉ፤ ልማታዊነቱን በስራው ፍሬ፣ በውጤቱ ያስመዝን፡፡ ያኔ “ሀቀኛው ልማታዊ” እና “ሃሳዊው ልማታዊ” በግልፅ ይለያል፡፡ (ልማታዊነትን በመደስኮር የለማ አገር አላየንም!)
 ፖለቲካዊ ወጌን ከመቋጨቴ በፊት ሰሞኑን ለተለያዩ ሚዲያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የፀረሙስና ኮሚሽነሩ አቶ ዓሊ ሱሌይማን፤ ለአንድ ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ እስቲ እንቆዝምበት፡፡
ከጋዜጠኛ የቀረበላቸው ጥያቄ እንዲህ ይላል፡- “ፀረሙስና ኮሚሽን፤ በከፍተኛ ባለስልጣናትና ባለሀብቶች ከሚፈፀሙ ሙስናዎች ይልቅ በትንንሽ ሙስናዎች ላይ የሚያተኩረው በፍራቻ የተነሳ ነው እንዴ?”
እሳቸውም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ሰው ይፈራል ባይባልም፣ የምንፈራበትም የማንፈራበትም ጉዳይ አለ፡፡ ትልቁ ነገር ግን ፍርሃቱ የግል ጉዳይ አይደለም፡፡ ልማት እንዳይደናቀፍ በመስጋት ነው፡፡ ልማቱን ላለማደናቀፍ በማለት ትንሹን ነገር አስበን፣ ትልቁ ነገር እንዳይሰናከል የምናደርገው ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ በተረፈ ግን በራሳችን እንዲህ ብናደርግ እንዲህ ይመጣብናል የምንለው ነገር የለም፡፡”
እንዴ… ከዚህ በላይ ምን ይምጣ?! በትልቅ ስጋት … በከባድ ፍርሃት … እንዳሉ ያስታውቃሉ እኮ (ግን ያው ለልማቱ ሲሉ ነው!) “ልማቱ እንዳይደናቀፍ…” እየተባለ በሚደረገውም በማይደረገውም የተነሳ … አገሪቷ እንዳትደናቀፍ ሰጋሁ፡፡ (እንዴት አልሰጋ?!)
እኔ የምላችሁ… ቆይ ግን ልማት ምንድን ነው? ልማትና ሙስናስ? ትላልቆቹ ሙሰኞች በህግ ሲጠየቁ እንዴት ነው ልማቱ የሚደናቀፈው? ቁንጮዎቹ ሙሰኞች ይሄን ያህል አስፈሪ ሆነዋል ማለት ነው? በቁጥርስ ስንት ይሆናሉ? በመቶኛ ሲሰሉስ? ግን ግን እንዲህ የሚያስፈሩ እስኪሆኑ ድረስ ለምን ተጠበቁ? መቼ ነው “ልማቱ እንዳይደናቀፍ …” ከሚል ስጋት የምንወጣው?
ምናልባት እንዲህ ጉዳዩን እየበታተንን ስንፈትሸው አንዳች መላ፣ አንዳች ዘዴ ብልጭ ይልልን ይሆናል፡፡
በዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ ላይ ጭንቅ ጥብብ ለማለት፣ የግድ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር መሆን አይጠበቅብንም፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡ እናም እሳቸውንም ቢሆን ከሸክሙን እናግዛቸው (ለብቻቸውማ እዳ የለባቸውም!) መልካም ደመራ! መልካም መስቀል!

Page 3 of 16