“የአባባ ተስፋዬ ተረቶች የስዕል አውደ ርዕይ” ባለፈው ማክሰኞ በብሔራዊ ቴአትር አርት ጋለሪ ተከፍቶ ለ4 ቀናት ክፍት ሆኖ የቆየ ሲሆን በዛሬው ዕለት ይጠናቀቃል፡፡ አውደ ርዕዩን መርቀው የከፈቱት አባባ ተስፋዬ፤በኔክስት ጄነሬሽን የበጎ አድራጎት ማህበር ህፃናትና ወጣቶች የተዘጋጀላቸው በሙካሽ የተጌጠ ካባ ተበርክቶላቸዋል፡፡ “በዓለም ላይ ብዙ አገራትን አይቻለሁ፤ሰርቶ ለመኖር እንደ ኢትዮጵያ የተመቸ አገር አላየሁም” ያሉት አባባ ተስፋዬ፤“አገራችሁንም ሥራንም ውደዱ፤እኔ አርቲስት ሆኜ እየሰራሁ  ሻሸመኔ ላይ በግብርና ሥራም ተሰማርቼ ነበር፡፡ ከግብርናው ባገኘሁት ትርፍም የራሴን ቤት ሰርቻለሁ፤መኪናም ገዝቻለሁ” በማለት የሥራን ጥቅም አስረድተዋል፡፡
በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረገው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩሉ፤“እኛ ዛሬ ላይ የደረስነው በቀደመው ትውልድ ታግዘንና ተረድተን ነው፡፡ ይህንን ውለታ ታሳቢ በማድረግ አባባ ተስፋዬን የሚዘክር መድረክ መሰናዳቱ መስፋፋትና መቀጠል አለበት” ብሏል፡፡
በአባባ ተስፋዬ ሳህሉ መኖሪያ ቤት ይዞታ ላይ ሊሰራ የታቀደው ቴአትር ቤትና የባህል ማዕከል ጋለሪ ህንጻ ዲዛይን በዕለቱ ቀርቦም ገለፃ ተሰጥቶበታል፡፡

በጀምስ ሬድፊልድ “The Celestine Prophecy” በሚል ርዕስ ተፅፎ በደራሲና ተርጓሚ አፈወርቅ በቀለ “የመጨረሻው መጀመሪያ” ተብሎ የተተረጐመው መጽሐፍ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ በ11 ሰዓት በዋቢሸበሌ ሆቴል አዳራሽ ይመረቃል፡፡ መጽሐፉ ለደራሲው አምስተኛ የትርጉም ሥራው ሲሆን በምረቃው ሥነስርዓት ላይ የሥነጽሑፍ ባለሙያዎችና ጥበብ አፍቃሪያን እንደሚታደሙ ታውቋል፡፡

 በብሩክ ከድር የተዘጋጀው “የአረቦች ፀደይ” የተሰኘ መፅሃፍ በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ፣ የፕሮፌሰር እሸቱ ጮሌ መታሰቢያ አዳራሽ ተመርቋል፡፡
መፅሀፉ እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተውና እስካሁንም ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቀው ንቅናቄ ያስከተለውን ዘርፈ ብዙ ምስቅልቅልና ሁለንተናዊ ገፅታውን ይዳስሳል፡፡
በ253 ገፆች በተቀነበበው “የአረቦች ፀደይ” መፅሃፍ ላይ አጭር ውይይት እንደተካሄደም ታውቋል፡፡

    በዓመቱ እስካሁን ያሳለፍነው መልካም ነበር፡፡ በስራ ነው ያሳለፍነው፡፡ ከአመት ወደ አመት የስራ አፈፃፀማችን እየተሻሻለ ነው፡፡ ሠራተኞቻችን ጤናቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ፣ እንዲማሩ ማድረጋችን፣ ተማሪዎችን ማስመረቃችን እንደቀጠለ ነው፡፡ በሌላ በኩል በየቦታው የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን የመፍታት ብቃታችን ከእለት ወደ እለት እየተሻሻለ ነው፡፡ ችግሮችን በጋራ በመፍታት ረገድ ጥሩ ክንውን ነበረን፡፡
በቀጣይ አመት ደግሞ የጀመርናቸው የ8 ሚሊዮን ብር የማስፋፊያ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶች ላይ ትኩረት ለማድረግ እንፈልጋለን፡፡ ወደ ውጭ መላክ ብቻ አይደለም ትልቅ የሚያደርገን ብለን ስለምናምን፣ ሀገር ውስጥ ያለውን ተጠቃሚ ፍላጐት ማሟላት መቻል አለብን፡፡ የሀገር ውስጥ ተጠቃሚው እያደገ ነው፡፡ ይሄን ፍላጐት ለማሟላት በአዲሱ አመት ጠንክረን እንሠራለን፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

  የስልጣን ዘመናቸውን 100ኛ ቀን ባለፈው ሳምንት ያከበሩት አዲሱ የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ፤ በባንክ ሂሳብ ደብተራቸው ውስጥ ያለው ገንዘብ 100 ሺህ ፓውንድ ብቻ መሆኑን በይፋ መግለጻቸውን ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ከዚህ ገንዘብ ውጭ ያላቸው ንብረት በጭቃ የተሰሩትን ሁለት ቤቶቻቸውን ጨምሮ አምስት የመኖሪያ ቤቶችና 270 ከብቶች ያሉበት የእርሻ ቦታ ብቻ መሆኑን እንደገለጹ የጠቆመው ዘገባው፤ሰውዬው ያላቸው ሃብት ከተራው የናይጀሪያ ህዝብ እጅግ የበዛ ቢሆንም፣ በመካከለኛና በከፍተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ዜጎች ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ገልጧል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ የግል ሃብታቸውን ይፋ ማድረጋቸው ከዚህ ቀደም አገሪቱን ሲመሩ ከነበሩና የህዝቡን ሃብት ወደ ካዘናቸው በማስገባት ከሚታሙ እጅግ ባለጸጋ ፕሬዚዳንቶች የተለዩ መሆናቸውን ለማሳወቅ ነው ተብሏል፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው፤ከቡሃሪ ሃብት 9 እጥፍ የሚበልጥ የ900 ሺህ ፓውንድ ባለቤት መሆናቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ቡሃሪ ስልጣን በያዙ ማግስት ከመንግስት ካዘና 100 ቢሊዮን ዶላር መንትፈው የግል ሃብታቸው አድርገዋል በሚል የሚታሙትን ሙሰኛ የአገሪቱ ባለስልጣናት ለፍርድ ለማቅረብ እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በ1980ዎቹ የአገሪቱ ወታደራዊ መሪ የነበሩት ቡሃሪ፤በስልጣን ዘመናቸው ከሙስና የጸዱ መልካም ሰው እንደነበሩ የጠቆመው ዘገባው፣ናይጀሪያን ለአምስት አመታት ያህል አንቀጥቅጠው የገዙት አምባገነኑ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳኒ አባቻ በአንጻሩ 3 ቢሊዬን ፓውንድ ሃብት እንደነበራቸውና አብዛኛውን ገንዘባቸውን በስዊዝ ባንክ እንዳስቀመጡት አስታውሷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

     ፖሊስ በአይፎን ተጠቃሚ የወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ ጀምሯል
             ማይክሮሶፍትም የወንጀል ተጠርጣሪን ኢሜል ባለመስጠቱ ተከሷል
   የአሜሪካ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ከአደንዛዥ ዕጽ እና ከጦር መሳሪያ ጋር በተያያዘ ለምናደርገው ምርመራ የሚጠቅሙ የጽሁፍ መልዕክቶችን አሳልፎ ሊሰጠን አልፈቀደም ያሉት ታዋቂው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል፤ፍርድ ቤት ቀርቦ ቅጣት የሚጣልበትን ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው መንግስትን መጠየቃቸውን ኒውዮርክ ታይምስ ዘገበ፡፡
የኤፍቢአይ እና የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣናት፤ አፕል በሚያመርተው አይፎን አማካይነት ከሰዎች ወደ ሰዎች የተዘዋወሩ አጭር የጽሁፍ መልክቶችን ለወንጀል ምርመራ አሳልፎ አልሰጥም ብሎ በእምቢተኝነት በመጽናቱ ህጋዊ እርምጃ ይወሰድበት ሲሉ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጥያቄ ማቅረባቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ወንጀል መርማሪዎች የአፕል ምርት የሆነውን አይፎን በሚጠቀሙ የአደንዛዥ ዕጽ እና የጦር መሳሪያ ወንጀል ድርጊቶች ተጠርጣሪዎች ዙሪያ ለሚያደርጉት ምርመራ የአጭር የጽሁፍ መልዕክቶቹ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው መናገራቸውም ተጠቁሟል፡፡
አፕል ከዚህ ቀደም ከፖሊስ ለቀረበለት ጥያቄ፣ የአጭር የጽሁፍ መልዕክቶቹ የተላለፉበት አይሜሴጅ የተሰኘ የመልዕክት መላላኪያ ሲስተሙ ነባር መረጃዎችን የሚያጠራቅምበት ቋት የሌለው በመሆኑ የተጠየቀውን መረጃ ስለማያገኝ አሳልፎ መስጠት እንደማይችል ማስታወቁን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ከአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ጋር በተያያዘ በተጠረጠረ አንድ ግለሰብ ዙሪያ ለሚደረግ የወንጀል ምርመራ ጠቃሚ የሆኑ የኢሜይል መልዕክቶችን አሳልፎ ሊሰጠው ባለመፍቀዱ ከማይክሮሶፍት ኩባንያ ጋር የፍርድ ቤት ክርክር እያደረገ እንደሚገኝም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

አሜሪካዊው ታዋቂ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ማይክል ጆርዳን፤ያለ ፈቃዴ ዝናዬን ተጠቅሞ ሃብት አፍርቷል ባለው አንድ ኩባንያ ላይ ለመሰረተው ክስ በካሳ መልክ እንዲከፈለው በፍርድ ቤት የተወሰነለትን 8.9 ሚሊዮን ዶላር ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሊለግስ እንደሆነ ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
የ52 አመቱ ጆርዳን፤ሴፍዌይ የተባለው የአሜሪካ የምግብ አምራችና አከፋፋይ ኩባንያ፣ ሳያስፈቅደኝ ምስሌን ለምርቶቹ ማስታወቂያ ተጠቅሟል፣ ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ካሳ ሊከፍለኝ ይገባል በሚል የመሰረተውን ክስ ሲመረምር የቆየው ፍርድ ቤት፤ 8.9 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈለው ወስኗል፡፡
ቺካጎ ውስጥ የተሰየመው ችሎት፤ውሳኔውን ማሳለፉን ተከትሎ ጆርዳን ለጋዜጠኞች እንደተናገረው፤ጉዳዩ ክብርን የማስጠበቅ እንጂ በካሳ ገንዘብ የማግኘት አለመሆኑን ጠቅሶ፣ ኩባንያው የሚሰጠውን 8.9 ሚሊዮን ዶላር የካሳ ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ለበጎ አድራጎት ተግባር እንደሚያውለው አስታውቋል፡፡ ነዋሪነቷ በኒውዮርክ ኢስት ሀምፕተን የሆነው አሜሪካዊቷ ሚሊየነር ሌስሊ አን ማንዴል በበኩሏ፤4 ሚሊዮን ዶላር በሚያወጣው እጅግ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቷ ውስጥ ለምታረባቸው 32 ወፎች፣ 100 ሚሊየን ዶላር ማውረሷን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ሚሊየነሯ በፈረመችበት ህጋዊ የውርስ ሰነድ ላይ፣ ወፎቼ ጎጇቸው በሳምንት ሁለት ጊዜ እየተጸዳላቸውና ከሱፐርማርኬት ደረጃቸውን የጠበቁ ጣፋጭ ኬኮች፣ ካሮትና ፈንድሻ እንዲሁም የተጣራ ውሃ እየተገዛላቸው በአግባቡ እየተመገቡ እንዲኖሩ እፈልጋለሁ ብላለች፡፡
እ.ኤ.አ በ2007 ሊዎና ሄልምስሌ የተባለች በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማረች አሜሪካዊት ሚሊየነር ለአንድ ውሻዋ 12 ሚሊየን ዶላር ማውረሷንም ዘገባው ጨምሮ አስታውሷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

  መጪው አመት በተለይም በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን ግንዛቤና እውቀት አዳብሮ ጥቅም ላይ የሚያውልበት ዘመን እንዲሆን በኢትዮያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ስም መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ዘወትር ቅዳሜ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በሚያወጣው ጽሁፍ በ2008 ዓ/ም ለህብረተሰቡ ይበልጥ መረጃ ሊያካፍል እንደሚችል እምነታችን ነው፡፡
ህብረተሰቡም በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ ያለውን ምላሽ እና ገጠመኝ እንዲሁም እውነታ ያካፍለን ዘንድ ከወዲሁ ግብዣ እናቀርባለን፡፡
መልካም አዲስ አመት
ሰላማዊት ክፍሌ ስራ አስኪያጅ
                    በአዲስ አመት በተለይም በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ እና በቤተሰብ ወይም ፍቅርን ለመጀመር ምን አቅደዋል? የሚለውን በሚቀጥለው እትም የምንመለከተው ይሆናል፡፡ በዚህ እትም ግን ፍቅርን ለመመስረት ምን ዝግጁነት ያስፈልጋል? የሚለውን ከተለያዩ መረጃዎች ካገኘናቸው በጥቂቱ እናስነብባችሁዋለን፡፡
አዲሱ አመት ሊጀምር ሰአት እየተቆጠረ የመጨረሻዋ የእኩለ ለሊት ሴኮንድ ደቂቃዋን እንዲሞላ ስታደርገው በዚያው ፍጥነት የነበረውን አሮጌ አስተሳሰብ በአሮጌው ሻንጣ አድርገህ ወርውረው፡፡ በምትኩም የተዘጋጀህበትን አዲስ የእቅድ ሻንጣ ክፈተው ይላል ያገኘነው የስነልቡና አዋቂዎች መረጃ፡፡
ባለፈው አመት የነበረኝ ብቸኝነት መለወጥ አለበት፡፡
ሕይወትን በሚመለከት ሌላውን ማለትም ሁለተኛውን ምእራፍ መጀመር አለብኝ
የማስብለት የሚያስብልኝ የኑሮ አጋር ያስፈልገኛል
በቤተሰብ በህብረተሰብ ውስጥ ተጠሪ ለመሆን የሚያስችለኝ ክብር መመስረት አለብኝ
አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ የምንባባልበት እድሜ ማለፍ የለበትም
በተፈጥሮ ህግ መሰረት እራስን ለመተካት መዘጋጀት አለብኝ በሚል ፕሮግራም ጉዞን በአዲሰ መልክ መጀመር ያስፈልጋል፡፡
ምናልባትም ያልተሟሉ ነገሮች እንኩዋን ቢኖሩ... ይህን አሟልቼ ይሀንን ተምሬ ይህንን ስራ ለውጬ ቤት ሰርቼ መኪና ገዝቼ ካልሆነ በስተቀር ወደ ትዳር አላመራም የሚል ካለ የመጣበትን መንገድ መለስ ብሎ መፈተሸ ይገባዋል፡፡
እድሜዬ ስንት ደርሶአል?
ምን ያህል ተምሬአለሁ?
ምን አይነት ስራ እየሰራሁ ነው?
ለወደፊት ያለሁበትን ደረጃ ለማሻሻል መንገዱስ እድሉስ ምንድነው?
አቅሙ አለኝ ወይንስ ምኞት ብቻ ነው?
በወደፊቱ የምመኘውን ነገር ካላገኘሁ እስከመቼውም ትዳር ሳልመሰርት ልቀር ነው ወይንስ?
ትዳር ሳልመሰርት ከቀረሁ ቀሪ ሕይወቴን እንዴት እገፋለሁ? ምንስ እጎዳለሁ?
ትዳር ብመሰርት ምን እጠቀማለሁ?
ላለኝ የወደፊት እቅድስ ትዳር መመስረቱ ምን ያህል ያግዘኛል ወይንስ ያስተጉዋጉለኛል?
በትክክል ብቸኛ በመሆኔ ተጠቃሚ ነኝ ወይንስ ተጎጂ ነኝ?
የሚሉትንና ሌሎች መሰል ነገሮችን እያሰላሰሉ ወደ ትክክለኛው ውሳኔ ላይ መድረስ ተገቢ ነው፡፡
ሚረር ሃውስቲንግስ የተሰኘው ድረ ገፅ በጆርናል ያወጣው እውነታ ደግሞ የሚከተለው ነው፡፡
በአዲስ አመት አዲስ ሰው ለመሆን አብሮ ከጎን የሚሆን ሰው ለማዘጋጀት በመጀመሪያ ግልጽ የሆነ አስተሳሰብ ሊኖር ይገባል፡፡
እስዋ ይህንን ነው የምትፈልገው ወይንም እሱ ሰው የሚለውን ነገር አይሰማም ወደሚለው ነገር ከመሄድ በፊት በግልጽ አስተሳሰብ... አዎን ይህ የሱ ባህርይ አይደለም ወይንም እሷ የምትፈልገው ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህ ምን ቢደረግ የተሸለ ይሆናል የሚለውን በቅንነት አስቦ መነጋገር ብልህነት ይሆናል፡፡
በችኮላ ወደ ፍርድ አትሂድ፡፡ አይታወቅም ያ እሱ እኮ ወይንም እሱዋ እኮ ያልናቸው ሰዎች ልክ ሊሆኑ ችላሉ፡፡ ስለዚህ በቅንነት ከታሰበ መፍትሔ ይገኛል፡፡ ለአዲስ አመት ይታሰብበት፡፡
ለቀጠሮ በጋበዝነው ሰው ወይንም ሴት ላይ የምናየውን ባህርይ እኛ ስለቀጠርን ብቻ ተለውጦ ማየት አለብን ብለን መቸገር የለብንም፡፡
የራስ የሆነ አቋም ያስፈልጋል፡፡ ለመጠየቅም መፍራት አይገባም፡፡ እንዴት ነው? ቀጠሮ መያዛችንን ወድደኸዋል/ሽዋል? ብሎ በመጠየቅ ትክክለኛውን መልስ ለማግኘት መሞከር ወደሚቀጥለው ሰፋ እና ከበድ ያለ ነገር ከመገባቱ በፊት መልሱን ለማወቅ ያስችላላ፡፡
የማይሆን ከሆነም በይሉኝታ ተሸብቦ ጊዜ መፍጀት ሳይሆን ወደሚጠቅመው ሌላ እርምጃ ማዘንበል ይጠቅማል፡፡
የምትወደው ወይንም ከምትወጂው ሰው በተቃራኒ ቦታ የምትቀመጪ/ጥ ከሆነ ሁኔታውን ማሻሻል ይገባል፡፡
አንድን ሰው ማየት ወይንም ማወቅ ቀልብህን የሚስበው ወይንም ቀልብሽን የሚስበው ከሆነ ዝም ብሎ በይሉኝታ ወይንም በሀፍረት ብቻ ከማለፍ ይልቅ ቀረብ ብሎ ማነጋገር ይበጃል፡፡
ምናልባትም ምን እንደሚፈልጉ ማውቅ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ምን አይነት መጽሐፍ ያነባል/ታነባለች? ምን አይነት ስፖርት ታዘወትራለች/ያዘወትራል? የመሳሰሉትን በመፈተሸ አብሮ ለመሳተፍ መሞከር ለመግባባት የሚያበቁ ውይቶችን ማድረግ ፍቅረኛን የማግኘት መንገዱን ይከፍታል፡፡
መልካም አዲስ አመት        

Published in ላንተና ላንቺ

  የቅርብ ተቀናቃኝ የነበረችው ኬንያ በዕጥፍ ብልጫ እያሳየች ነው…
   በዓለም ሻምፒዮናው የኬንያ ገቢ 7.2 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን የኢትዮጵያ ድርሻ ከ500 ሺ ዶላር በታች ነው፡፡
  በ31ኛው ኦሎምፒያድ ኬንያ 7 ወርቅ፣ 5 ብርና 5 ነሐስ፤ ኢትዮጵያ 3 ወርቅ፣ 3 ብርና 2 ነሐስ ያገኛሉ፡፡ ኢንፎስትራዳ

   የቻይናዋ ዋና ከተማ ቤጂንግ ባስተናገደችው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ተሳክቶለታል ለማለት ያዳግታል፡፡ ሁሌም የውጤት መለኪያ የቅርብ ተቀናቃኝ የነበረችው ኬንያ ነች፡፡ ባለፉት 2ሻምፒዮናዎች እና የለንደን ኦሎምፒክ ኬንያን መፎካከር ለኢትዮጵያ ያዳገተ መስሏል፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ባስመዘገበው ውጤት መርካት አይቻልም፡፡ በተለይ በወንድ አትሌቶች ያጋጠመው ሁኔታ ያስደነግጣል፡፡ በረጅም ርቀት አትሌቲክስ የኢትዮጵያ መሪነት ሙሉ ለሙሉ እየተነጠቀ ነው፡፡ ኬንያውያን ይቅርና ሞፋራህ ብቻውን ኢትዮጵያን ከኋላ ማስከተል ቀጥሏል፡፡ የውጤት ማሽቆልቆል ከምን የመጣ ነው? በተፎካካሪነት መድከምስ ለምን ይታያል? በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብዙ ክፍተቶች መኖራቸውን እየካዱ መቀጠል አያስፈልግም፡፡ በታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በከፍተኛ ደረጃ ተዘጋጅቶ መሳተፍ ይኖርበታል፡፡ ባለአቅምና ልምድ ተጠቅሞ የመዘጋጀትና የመሳተፍ ትኩረት ከሁሉም ባለድርሻ አካላትም ያስፈልጋል፡፡ በብራዚል ከተማ፤ ሪዮ ዲጄኔሮ 31ኛው ኦሎምፒያድ ሊካሄድ ከዓመት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል፡፡ በታላቁ ኦሎምፒክ መድረክ የኢትዮጵያን አትሌቲክ የሚያነቃቁ ውጤቶች ለማስመዝገብ ከወዲሁ መነሳሳት አለብን፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ባለ ድርሻ አካላት ብዙ ናቸው፡፡ ስፖርቱ የአትሌቲክስ የፌዴሬሽኑ ብቻ አይደለም፡፡ መገናኛ ብዙሃናት፤ የስፖርት ምሁራን፣ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ታላላቅ አትሌቶች፣ ክለቦች፣ አካዳሚዎች… ወዘተ መረባረብ አለባቸው፡፡ በፌዴሬሽኑ የአስተዳደር፣ የእድገት እና የስልጠና መዋቅር አገር አቀፍ መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡
በ15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ ሜዳሊያ ስብስብ ከበፊቱ ያልተሻለው በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ በወቅታዊ የስልጠና መዋቅር እየተሠራ አይደለም፡፡ በሌሎች አገራት ካለው የዕድገት ደረጃ አንፃር በጥናት የታገዘ ዝግጅት እንዳልተደረገም በገሃድ መታዘብ ተችሏል፡፡ በአትሌቶች ዝግጅት ላይ የአየር ሁኔታና ተስማሚነትን በአሣማኝ ሁኔታ የተካሄደ አልነበረም፡፡ በአመጋገብ በስነልቦና ጠንካራ ስራዎች እንዳልተሠሩም ይገለፃል፡፡ ወቅቱን የጠበቁ የአሰራር ስርዓቶች አለመዘርጋታቸውም ይስተዋላል፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ላይ ሌሎች ብዙ ችግሮችን መመልከት ይቻላል፡፡ ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ የሚያስፈልግ ነው፡፡ የዓለም ሻምፒዮናው ድክመት ቢያንስ በመጭው ኦሎምፒክ እንዳይደገም ብዙ መሠራት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ የቅርብ ተቀናቃኝ የነበረችው እና አሁን በዕጥፍ ብልጫ ማሳየት የጀመረችውን ኬንያ ምሳሌ ማድረግ ይቻላል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው በድምሩ 16 ሜዳልያዎች (7 የወርቅ፣ 5የብር፣ 5 የነሐስ) በማስመዝገብ ኬንያ ከዓለም 1ኛ ሆና ጨርሳለች፡፡ በከፍተኛ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ውድድር አፍሪካዊ አገር የሜዳልያ ሰንጠረዥን በመሪነት ሲያጠናቅቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡  ጃማይካ በ12 (7 የወርቅ፣ 2 የብርና 3 የነሐስ) ሜዳልያዎች፤ አሜሪካ በ18 (6 የወርቅ፣ 6 የብርና 6 የነሐስ) ሜዳልያዎች ታላቋ ብሪታንያ በ7 (4 የወርቅ፣ 1 የብርና 2 የነሐስ) ሜዳልያዎች እስከ 4 ያለውን ደረጃ አግኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በ3 የወርቅ 3 የብርና 2 የነሐስ በአጠቃላይ በ8 ሜዳልያዎች 5ኛ ደረጃ ነበራት፡፡ የሜዳልያው ውጤት ኬንያ ያላትን ዕጥፍ ብልጫ የሚያመላክት ነው፡፡ ባለፉት 15 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ኬንያ ያስመዘገበችው የወርቅ ሜዳልያ ብዛት 50 ሲደርስ የኢትዮጵያ 25 ነው፡፡
በሻምፒዮናው የአፍሪካ አገራት ከሰበሰቡት 31 ሜዳልያዎች ከፍተኛውን ድርሻ ኬንያና ኢትዮጵያ ይወስዳሉ፡፡ ከሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ሌላ የወርቅ ሜዳልያ ድል ያስመዘገቡት ኤርትራ እና ደቡብ አፍሪካ ናቸው፡፡  የደቡብ አፍሪካ የወርቅ ሜዳልያ በ400 ሜትር ወንዶች የተገኘው ነው፡፡ በተጨማሪ በ200 ሜትር ወንዶች የነሐስ ሜዳልያም ተመዝግቧል፡፡ ስለሆነም ደቡብ አፍሪካ ከአህጉሩ በውጤታማነት በ3ኛ ደረጃ ትጠቅሳለች፡፡ የሻምፒዮናው አስደናቂ ውጤት የተባለው ደግሞ በማራቶን ለኤርትራ የተገኘው የወርቅ ሜዳልያ ነው፡፡ ከ4ቱ አገራት ውጭ የሜዳልያ ውጤት ያስመዘገቡት ግን ጥቂት ናቸው፡፡ ግብጽ በጦር ውርወራ የብር ሜዳልያ፣ ቱኒዚያ በ3ሺ ሜትር መሰናክል የብር ሜዳሊያ፣ ሞሮኮ በ1500 የነሐስ ሜዳልያ እንዲሁም ኡጋንዳ በወንዶች ማራቶን የነሐስ ሜዳልያዎችን አግኝተዋል፡፡  አንዳንድ ዓለም አቀፍ የመረጃ ምንጮች ከኬንያና ከኢትዮጵያ ባሻገር የሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገራት የነበራቸውን ተሳትፎ ደካማ ብለውታል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው ከአፍሪካ አህጉር ከ27  በላይ አገራት የተወከሉት በ1 አትሌት ብቻ ነበር፡፡ ከምስራቅ አፍሪካ በስተቀር ከሌለው የአፍሪካ ክፍል በወንድ አትሌቶች ከፍተኛ የተሳትፎ ብቻ መቀነስ ተስተውሏል፡፡ አጭር ርቀት እና በሌሎች የሜዳ ላይ ስፖርቶች የሚታወቁት የሰሜንና  የምዕራብ አፍሪካ አገራትም አልሆነላቸውም፡፡ በተለይ ናይጀሪያ ጠንካራ ተሳትፎ አልነበራትም፡፡   
ኬንያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በሜዳልያ ስብስብ በአንደኛነት ጨርሳ ደረጃ አዲስ ታሪክ ማስመዝገቧ ድንገተኛ ክስተት አይደለም፡፡ የአገሪቱን አትሌቲክስ በበላይነት የሚመራው ተቋም የሚከተለው አቅጣጫ እንዳመጣው ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ሰሞኑን እንኳን በዓለም ሻምፒዮናው የተገኘውን ውጤት በኦሎምፒክም ለመቀጠል የተጀመሩ ስራዎች ማስረጃ ይሆናሉ፡፡ “አትሌቲክስ ኬንያ” የተባለው የኬንያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአገሪቱ ዋና ዋና የክልል ከተሞች የተደራጁ የስልጠና ቦታዎችንና  ቢሮዎችን ለመክፈት ወስኗል፡፡ በጦር ውርወራ እና በ400 ሜትር መሰናክል በተገኙ ድሎች በመነቃቃትም በአጭር ርቀትና በሜዳ ላይ ስፖርቶች ለመስራት ሃሳብ ቀርቧል፡፡ ፌዴሬሽኑም ለአትሌቶች የሚመጥን ዘመናዊ የስልጠና መዋቅር፤ የቴክኒክ ድጋፍ፣ የፋይናንስ ድጋፍ፣ እንዲሁም ዘመናዊ የስፖርት መሣሪያዎችና ፕሮፌሽናል ባለሙያዎችን ባካተቱ ግብረ ኃይል መስራት እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡ በአጠቃላይ ኬንያ በዓለም ሻምፒዮና ያገኘችው ስኬት ከመላው ዓለም አድናቆት አትርፎላታል፡፡ ከኢትዮጵያ ተቀናቃኝነት በላቀ ደረጃ እያመለጠች መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
የኬንያ አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮናው ከ7.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አጋብሰዋል፡፡ በአንፃሩ የኢትዮጵያ አትሌቶች ድርሻ ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በታች ነው፡፡ በኬንያ የዓለም ሻምፒዮና ስኬት በቂ ምርምርና ጥረት ማድረግ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስራ ነው፡፡ በተለያዩ ዘገባዎች ከቀረቡ ትንተናዎች ለመረዳት የሚቻለው ግን የአገሪቱ አትሌቲክስ በከፍተኛ የውጤት እና የዕድገት ደረጃ ላይ መሆኑን ነው፡፡ የኬንያ አትሌቶች ውጤታማነት በስምጥ ሸለቆ አካባቢ ከመኖራቸው ሁኔታ ጋር ተያይዞ በስፋት መነሳቱ የተለመደ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን በኬንያ አትሌቲክስ ዘመናዊና ምቹ የአሠራር መዋቅር መዘርጋቱን የሚገልፁ መረጃዎች አሉ፡፡ በኬንያ አትሌቲክስ ዘመናዊ የስፖርት መሠረተ ልማቶች በመላው አገሪቱ ተስፋፍተዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ድጋፍ ሰጪ ስፖንሰሮች መብዛታቸውም የአካዳሚዎችና የማሠልጠኛዎችን አቅም አሳድጓል፡፡  እንዲሁም የኬንያ መንግስት በወጣቶች ላይ ያተኮረ የአትሌቲክስ የእድገት አቅጣጫዎች ላይ በትኩረት መሥራቱም ይጠቀሳል፡፡ ለኬንያ አትሌቶች የተዘረጋው ጥሩ የስልጠና መዋቅር ከመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች የሚነሳ ነው፡፡ ከዚያም በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና በክለብ ደረጃ የስልጠና ሂደቱ ይቀጥላል፡፡  ፕሮፌሽናል አትሌቶችን በየጊዜው እንዲወጡ አስችሏል፡፡ የኬንያ አትሌቲክስ ተተኪዎችን ለማፍራት አቅሙ የዳበረውም በዚያ ምክንያት ነው፡፡ በተጨማሪም የሜዳልያ ስብሰባቸውን ለማብዛት በሌሎች የውድድር መደቦችም ላይ አተኩረውም ሰርተዋል፡፡ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው አሠልጣኞችና ማናጀሮችም ከሀገር ውስጥም ከውጭም በስፋት እየሰሩም ይገኛሉ፡፡ የስፖርት ምሁራን እና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም በየጊዜው በመጽሐፍ፣ በቪዲዮ ምስልና በጥልቅ ዘገባዎች በኬንያ አትሌቲክስ ከፍተኛ ምርምር በማድረጋቸውም ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የስፖርት ዳታዎችን  የሚያሰባስብና የሚያሰላ ግዙፍ ተቋም ኢንፎስትራዳ በኦሎምፒክ የሜዳሊያ ስኬት ቅድመ ትንበያ ተሰርቷል፡፡ በ2016 እ.ኤ.አ ሪዮዲጄኔሮ በምታስተናግደው 31ኛው ኦሎምፒያድ ላይ ነው፡፡ የሜዳልያ ትንበያውን ኢንፎስትራዳ በየጊዜው እየከለሰ ሲያሰራጭ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ተቋም 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናና በተገባደደ  ማግስት የሜዳልያ ትንበያውን በመከለስ አስታውቋል፡፡ በኢንፎስትራዳ የሜዳልያ ትንበያ መነሻነት የተሠሩ ትንታኔዎች እንደሚያመለክቱት በሪዮ ኦሎምፒክ አውስትራሊያ የወርቅ ሜዳልያዋ በእጥፍ እንደሚጨምር፤ አዘጋጇ ብራዚል 4 የወርቅ ሜዳልያዎችን እንደምታጣ፤ ፈረንሳይ ደረጃዋ ቢቀንስም ካለፈው ኦሎምፒክ በተሻለ ተጨማሪ የወርቅ ሜዳልያዎች እንደምታገኝ፤ ጀርመን ከፈረንሳይ የተሻለ ውጤት እንደምታስመዘግብ፤ ታላቋ ብሪታንያ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች እንደምትነጠቅ፤ ቻይና ውጤቷ እንደሚያሽቆለቁልና፤ ራሺያ በከፍተኛ ተፎካካሪነት እንደሚሳተፉ በዝርዝር ተተንትኗል፡፡ በ2012 እ.ኤ.አ ላይ ለንደን ባስተናገደችው 30ኛው ኦሎምፒያድ በድምሩ 104 ሜዳሊያዎች ያገኘችው አሜሪካ በኢንፎስትራዳ ትንበያ 10 የወርቅ ሜዳልያ ተቀንሶባታል፡፡ በሪዮዲጄኔሮ በምታገኘው አጠቃላይ የሜዳልያ ብዛት ከዓለም መሪነቱን ባትነጠቅም ታገኛለች የተባለው 95 የወርቅ ሜዳልያዎችን ነው፡፡ በ15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሜዳልያ ሰንጠረዡን በአንደኝነት የጨረሰችው ኬንያ 31ኛው ኦሎምፒያድ ላይ 17 ሜዳልያዎች (7 ወርቅ፣ 5 ብርና 5 ነሐስ) እንደምታገኝ ተገምቷል፤ ለኢትዮጵያ የተተነበየው ደግሞ 3 የወርቅ 3 የብርና 2 የነሐስ በአጠቃላይ 8 ሜዳልያዎች ነው፡፡ በሜዳልያ ስብስባቸው ኬንያ ከዓለም 13ኛ እንዲሁም ኢትዮጵያ 27ኛ ደረጃ እንደሚኖራቸውም ተጠቁሟል፡፡  
ኢንፎስትራዳ 31ኛው ኦሎምፒያድ ከመጀመሩ 1 ዓመት ቀደም ብሎ ይፋ ያደረገው የሜዳሊያ ትንበያ ነው አሜሪካ 1ኛ ደረጃ የያዘችው በ95  (41 የወርቅ፣ 20 የብር፣34 የነሐስ) ሜዳልያዎች ነው፡፡ ቻይና በ79 (33 የወርቅ፣ 28 የብር፣ 18 የነሐስ) ሜዳሊያዎች፣ ራሽያ በ71 (26 የወርቅ፣ 24 የብር፣ 21 የነሐስ)  ሜዳልያዎች፣  እንዲሁም ጀርመን በ47 (18 የወርቅ፣ 15 የብር እና 14 የነሐስ) ሜዳልያዎች እስከ አራት ያለውን ደረጃ አከታትለው ይወስዳሉ ተብሏል፡፡  

     2007 ራሴን ከውድድር ያገለልኩበት ዓመት ነው፡፡ በርካታ ስራዎችን እየሰራሁ ነው፡፡ በግብርና፣ በሆቴል፣ በተለያዩ ግንባታዎች ላይ ነን፡፡ በተለይ ግብርናችን ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው፡፡ የቡና ተክላችን 600 ሄክታር ደርሷል፡፡ የማር ምርት ጨርሰን በ2008 ወደ ገበያ እንገባለን፡፡ ለአገር ውስጥም ለውጪም ገበያ ይቀርባል፡፡ የወርቅ ማእድን ስራዎችም ጀምረናል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ያስመዘገብነውን ውጤት በተመለከተም እንደ ተመልካች አልቀበለውም፡፡ አንድ ወገንን ለመውቀስ አይደለም፤ አትሌቱም የስፖርት ቤተሰቡም የራሱ ድርሻ አለው፡፡ መንግስት ይኼን ጉዳይ አልባት ካልሰጠው ከብራዚል ስንመለስ የባሰ ነገር ገጥሞን ሁላችንም እንዳናዝን እሰጋለሁ፡፡ ከዚህ በላይ ብዙ ለማለት አልፈልግም፡፡
አዲሱ ዓመት ጥሩ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በተሰማራንባቸው ስራዎች እኛንም ተጠቅመን አገርንም ለመጥቀም እንስራለን፡፡ በዋናነት ግን መንግስት መልካም አስተዳደርን አስመልክቶ መቀሌ ላይ ያስተላለፈውን መልእክት እንደሚተገብረው ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር ትልቁ ችግር ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜያችንን ከስራ ይልቅ በቢሮክራሲ እያጠፋን ነው፡፡ መንግስት ይሄን መቅረፍ ከቻለ፣ እኛም ማደግ የምንችልበት ዓመት ይሆናል፡፡