በግጭት ምክንያት የሚደርሰው የመንገድ ንብረቶች ውድመት እየተባባሰ መምጣቱን በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ መብት ጥበቃና አስተዳደር ገለፀ፡፡
አስተዳደሩ ያለፈው ዓመት የስራ አፈፃፀሙን አስመልክቶ ከትላንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ በበጀት ዓመቱ በ569 የመንገድ ንብረት ላይ አደጋዎች ደርሰው ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን የጠቆመ ሲሆን ከነዚህም አደጋዎች ውስጥ 244 ያህሉ አደጋዎች በቀለበት መንገድ ላይ መከሰታቸውንና የንብረቶቹ ውድመት በገንዘብ ሲተመን፣ ከ1.3 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነም የአስተዳደሩ ንዑስ የስራ ሂደት መሪ አቶ አስመላሽ ኪዳነማርያም ተናግረዋል፡፡
ቀሪዎቹ 325 አደጋዎች በሌሎች ዋና ዋና መንገዶች ላይ የተከሰቱ ሲሆን ግጭቶች ያደረሱት ጉዳት በገንዘብ ሲተመን ከ3.6 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በአብዛኛው ለጉዳት የሚዳረጉት የመንገድ ላይ ንብረቶች የመንገድ ዳር መብራቶች፣ የእግረኛ  መከላከያ አጥሮች፣ የመንገድ ማካፈያ፣ መከላከያ ግንብና የትራፊክ ምልክቶች ሲሆኑ በግጭት ምክንያት ከሚደርስባቸው ጉዳትና ውድመት ባሻገር በህገ ወጥ ግለሰቦችም ስርቆት እንደሚፈፀምባቸው ተገልጿል፡፡ በበጀት ዓመቱ በግጭትና በስርቆት ምክንያት በመንገድ አካላቶች ላይ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት መድረሱንም አቶ አስመላሽ አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ አስመላሽ ገለፃ፤ ባለስልጣኑ በግጭት ጉዳት የሚደርስባቸውን ንብረቶች በክትትል ካሳ ከማስከፈልም በተጨማሪ በመንገድ ላይ በሚያጋጥሙ ህገ-ወጥ ተግባራት ላይ የቁጥጥርና የክትትል ስራ የሚያከናውን ሲሆን በዚህም ክትትልና ቁጥጥር በዋና መንገዶች ላይ የግንባታ መስሪያዎች ያከማቹ 105 ግለሰቦች ላይ የገንዘብ መቀጫ ጥሏል፡፡
የመንገድ ላይ ንግድ፤ በግንባታ ስም እግረኛ መንገድን ማጠር፣ ከባድ መኪናን ለረጅም ጊዜ አቁሞ መጥፋት፣ ህገወጥ ማስታወቂያዎችን መለጠፍ፣ ማንጠልጠልና መትከል፣ በባለስልጣኑ ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሲሆን እነዚህን ህገ ወጥ ድርጊቶችን ባከናወኑ አካላት ላይ እርምጃ መውሰዱንም ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
ህብረተሰቡ የመንገድ ላይ ንብረቶችን እንደራሱ ንብረት እንዲጠብቅና ህገ-ወጦችን እንዲጠቁም ባለስልጣኑ የግንዛቤ ስራዎችን የሚራ ሲሆን በህገ-ወጦች የሚፈፀሙ ጥፋቶችን እንዲጠቆም 917 ነፃ የስልክ መስመርን ማስተዋወቁንም ገልፀዋል፡፡
“ምንም እንኳ ባለስልጣኑ በመንገድ አካላት ላይ የደረሱ ውድመቶችን ካሳ ሙሉ በሙሉ ማስከፈል ቢችልም የግጭቱ መጠን ግን ከ2006 የበጀት ዓመት ጨምሯል ያሉት ኃላፊው፤ በ2007 የደረሱት የመንገድ ንብረት አደጋዎች ቀደም ካለው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ126 አደጋዎች ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
ባለስልጣኑ በ2008 የበጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ለመከወን የዓምናውን ልምድ መነሻ በማድረግ ቀመር ማውጣቱንም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና
Saturday, 19 September 2015 09:06

“ሲልቪ” በትክክል የማናት?

ይህ ፅሁፍ የነበረውን እምነት በማስቀጠል አጀንዳ፣ወይም አዲስ እምነት በመስጠት አብዮት አልተፃፈም፡፡ ያለውንና የተገኘውን፣የተደረሰበትን እውነታ ግን እናጋራችኋለን፤ ከዚህ የተለየ አላማ የለውም፡፡
ሁላችንም በይፋ ሲልቪን የምናውቃት፣አርትኦት በጨቆነው፣በመጀመሪያው የ1990 እትም፣ በስብሐት ገብረእግዚአብሔር (ነፍስኄር) “ትኩሣት” ልብወለድ ውስጥ ይመስለኛል፡፡ ሲልቪን ማስታወስ በራሱ “መብራት አጥፍተው፣አይን ከድነው...የተመኙትን ወንድ እያሰቡ ከሌላ ሰው ጋር መተኛትን” ያሳስባል፡፡ ወይም ሲልቪ፡- ወሲብና ጥበብ፣ወሲብና ምናብ፣ወሲብና ፋንታሲ ናት፡፡
ቀደም ብሎ ታዲያ አዳም ረታ በ1986 እንደፃፈው የጠቀሰልንን አጭር ልብወለድ በ’እቴሜቴ ሎሚሽታ’ መፅሐፍ ውስጥ እናገኛለን። ልብወለዱ “ሁለት ተኩል የውስጥ ሱሪዎች ለአዲስ አበባ” የሚል ነው። ሌላም ደሞ ስራ አለው፡- “ጭጎላ፡ ወደ ፊት ወደ ሁዋላ” የተባለ፡፡ ይኸም አጭር ልብወለድ በ1979 ዓ.ም (ግንቦት) ተፅፏል፡፡ በ’አለንጋ ምስር’ መድበል ውስጥ ይገኛል፡፡
ሌላው በተጨማሪ የምጠቅሰው፣ የሀዲስ ዓለማየሁ የረዥም ልብወለድ ስራ የኾነው “የልም እዣት” ነው፡፡ የልም እዣት ከ1964 በፊት ተሰናድቶ እንደነበር በመቅድማቸው ሀዲስ ገልፀዋል፡፡ ዋንኛው የስብሐት ስራ የኾነውን #ትኩሳት; የተፃፈበትን ጊዜ ግን ክፍቱን ተውነው፡፡ (መልካም ቆይታ)
አሁን ቀደም ብለን በስብሐት ስራ ውስጥ የተዋወቅናትን ሲልቪን ነው የምንፈልጋት፡፡ በጠቀስኳቸው የአዳም አጭር ልብወለዶች ውስጥ ሲልቪ የምትገኘው በደራሲው የራሱ ይትበሃልና ተውኽቦ የተነሳ ሳትደምቅና ሳትጎላ ነው፡፡ ወይም እዚያ ጋ “ጊዜ ዝግ አላለም”፡፡
በ “ሁለት ተኩል የውስጥ ሱሪዎች ለአዲስ አበባ” ውስጥ ከገፅ 260 አንስቶ (ቀደም ብለን ከገፅ 259 ጀምረንም እስከ ገፅ 261 እናከትማለን)፡፡
አዳም በዚህ ስራው በ”ምልሰት የምናውቀውን የአፃፃፍ አገባብ በ”ወሰጅ” ተጠቅሞታል - ምን ማለቴ ነው፦ በዋናነት ራሱ ትረካው ያሁን ግዜ ከመሆን ይልቅ ትውስታ ሲሆን፣በመሃል ደመቅ ባለ የፊደል ትየባ የሚመጣውም፣ ትውስታ በመሆን ፈንታ የአሁን ጊዜ ነው። (አጠቃላዩ ትረካው ትውስታ ነው፤ምልሰቱ ደሞ ያሁን ጊዜ) እናም በዚህ አጭር ልብወለድ፣ “በአሁን ጊዜ-ምልሰት” ውስጥ ተራኪው ገፀባህሪ፣ አንዲት ሎሚሽታ የተባለችን ሴት መኪና ላይ ይተዋወቃል፡፡ በግልፅ በእንግዳዋ ሴት ይሳባል፤ .... በመጨረሻ ከታክሲው የምትወርድበት ግዜ ሲደርስና ቀድሞ ሊያሳልፋት ወርዶ የታክሲው በር ጋ ሲጠብቃት፣ስትወርድ የተከፋፈቱ ጭኖቿን አየ፡፡ “..ባለትዳር መሆኑንም ረሳ”፡፡ በዚህ ሁኔታ ከዚያ የተንደረደረ ከቤቱ ሲደርስ፣ ባለቤቱ ማርታን ልብሷን ስትቀይር ያገኛታል፡፡ “..ወደ አልጋ ያቻኩላት ጀመር”፡፡ ግራ የገባት ሚስቱ “ምን ሆንክ?” አለችው። አልሰማትም፡፡ .......
እነዚህን እንደ ነጥቦች ብንይዛቸውስ -----
•--- ተራኪው  ሎሚሽታን፣ “ፊቷ ማርታን የሚመስል ነገር እንዳለው” ተናግሯል (ገፅ  259)
•....”ሎሚሽታ የተባለችው ሴት የማርታ ልጅነት ነበረች”
•ለማርታ ሰውነት “.ጤንነት የተጠቀመባት” .....እና
•ለሎሚሽታ ሰውነት ደሞ “..የጭኖቿ ልስላሴና ርዝመት”፣ የሚል የአመሳስሎ አገላለፁ ....
እዚህ ትረካ ላይ አትኩሮታችን የሚያርፍበት የጊዜ ነጥብ ፣ “..ወደ አልጋ ያቻኩላት ጀመር” የሚለው ላይ ያርፋል።
በሁለተኛው ትረካው፣ “ጭጎላ ወደ ፊትና ወደ ኋላ” ውስጥ ባለታሪካችን ገፀባህሪይቱ መሶበወርቅ፣ በዕድሜ ከባለቤቷ አንፃር ወጣት ናት። ባሏ የፀባይ ችግር ባይኖርበትም በመካከላቸው ባለ የእድሜ ርቀት ብቻ ተመርራበታለች፤ልቧም ከሱ ሊረጋላት አልቻለ። ከግቢያቸው አንድ ተከራይ ሰሞኑን መጥቷል፡፡ ልትዘረጋው ያሰበችውን የግንኙነት ድልድይ ሌላኛ ጫፍ ተቀብሎ ህልሟን እውን ለማድረግ ግን ተከራዩ አልፈቀደም፡፡ ያውም አዲስ ሙሽራ ነው፡፡
ታዲያ የትረካው የመጨረሻ ቀን፣ ተከራዮቹ እጮኛማቾች የሚዳሩበት ቀን ነው፡፡ ጫጉላ የሚገቡበትም፡፡ ባለቤቷን ጨምሮ ደጋሹም እንግዳውም ግቢ ውስጥ ናቸው፡፡ እሷ ግን ከመኝታ ቤቷ አልወጣችም፡፡ ከሆነ ሰዐት በኋላ በቀጥታ ወጥታ የባሏን እጅ ከእንግዶች መካከል ከአግዳሚው ወንበር ላይ አንስታ በችኮላ ወደ መኝታ ቤቱ ታመጣዋለች፡፡ አቻኩላውም ወደ አልጋው፡፡ ግራ የገባው ባልም እየተንከረፈፈ ተከተላት-- ሆነም፡፡
የሲልቪን ምስል ተገንብተው የሚሰሩት ጭረቶችን በትኜ ላስቀምጣቸው፡
•ባል ከሚስቱ የስጋ ፈቃድን ይሁንታ ከረጅም ግዜያት በኋላ ያገኘው በዚያች ቀን ነው፡፡
•ያ ቀን ያ ተከራይ / በመሶብ ምኞት ውስጥ ያለው ወጣት፣ ከሙሽራው ጋር የተጫጨበት እለት፣ ያውም ልክ ጯጉላ የሚገባበትን ሠዐት እየጠበቀ ነው፡፡
•ልክ ባሏን ጎትታ ወደ ቤት እንዳገባችው፣ ፊቱን ወደ አፍላ እጮኛሞቹ ቤት ፊቱን የሰጠውን መስኮት በሰፊው ከፈተችው፤ባልም በዚህ ድርጊት የኾነ ዕቅድ እንዳለ ጠረጠረ፤ “ብር አምባር ሰበረልዎ” የሚለውም ዘፈን ወለል ብሎ ገባ፤የእጮኛማቾቹ ቤት ጣርያና ግድግዳም ታየች።
•ባሏን ስትስም ለራሷ እንዲህ ትላለች፤ “አሁን ሙሽራው ሙሽሪቱን እየሳማት..” ነው፡፡
•ይህን ስታደርግ ጀምሮ አይኖቿ የተጨፈኑ ናቸው፡፡ከዚህም ያትኩሮታችን ድምቀት የሚወስደው ቦታ፤የትረካው ማብቂያ የሆነው “...እጅ አዙር ፍቅር ...እጅ አዙር ጫጉላ “ የሚለው አገላለጽ ሊሆን ይችላል፡፡
ይህን እጅ አዙር ፍቅርና ግንኙነት፣በሀዲስ ዓለማየሁ ስራ “የልምእዣት” ውስጥም እናገኘዋለን፡፡ እሱን ልጥቀስ፡- (ከገፅ 408--409)
“ ....አሁን ግን በሱዋ ምክንያት አመንዝራ ልሆን ነው፣ውቤ “ ይለዋል በሽህ፡፡
# ..ጉዴን ልንገርህ ....” ብሎ ይጀምርለታል፡፡
“ ብቻችንን በሆን ቁጥር እንዲህ ባለ ፈተና ውስጥ ወድቄ ስገኝ፣ፍትወት ራሴን መግዛት እስኪሳነኝ ድረስ ያቃጥለኝና፣የምሆነውን ያሳጣኝና እስዋን - እንደ ታቦት የማከብራትን ቅዱስዋን ታቦት ማርከስ ሆኖ ስለሚታየኝ፥ ወዲያውም ለምን እንደሆነ አላውቅም ስለምፈራት እስዋን ቶሎ ቤትዋ አድርሼ የግብረ-ዝሙት ስራ መተዳደሪያቸው አድርገው ወደሚኖሩ ሴቶች እሮጣለሁ! እዚያ እሷን እያሰብሁ፣እሷን ከአሳቤ ሳላጠፋ፣ ከነሱ ጋር ስቆይ ከስዋ ጋር ያለሁ እየመሠለኝ፣ከዚያ በፊት አግኝቼ የማላውቀውን ደስታ አገኛለሁ፡፡........”
ይህን “እጅ አዙር የፍቅርና የፍትወት ግንኙነት” ሁሉም ባለታሪኮቻችን የፈለጉት ለየራሳቸው የተለያየ ምክንያት ነው፡፡
በሽህ፦..ስለሚያከብራት፣ ስለሚፈራትና ሊያረክሳት ስለማይፈልግ
መሶበወርቅ፦የልጅነት ወግ ማእረጓን በደንቡ መሠረት ለማስመለስ ስለተመኘችና እኩያዋንም ወጣት በዚያች ቅፅበት ያገኘችው እየመሰላት ....... ወዘተ፡፡
ውድ አንባቢዎቼ፤ በመጨረሻ አንድ ሌላ ጥቆማዬን ልመርቅላችሁ፡- የዳንኤል ወርቁ ካሳ “የማዕበል አሦች” (1995) ረዥም ልብወለድ ውስጥ ተመሳሳይ ነገር ማግኘቴን አስታውሳለሁ፣የምታነቡት ከሆነ እንደምታገኙት እርግጠኛ ነኝ፡፡ ግን ሲልቪ የማናት?



Published in ጥበብ

   አብርሃም ግዛው ኢንተርቴይመንትና ፕሬስ ስራዎች ድርጅት ከኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ልዩ የመስቀል በዓል ፕሮግራም ያካሂዳል፡፡ በኢቴቪ 3 ከቀኑ 11፡30 እስከ ምሽት 1፡30 ሰዓት ድረስ በሚተላለፈው በዚሁ ፕሮግራም ላይ የእርድ፣ የደመራ ማብራት፣ እና የአገር ሽማግሌዎች የምርቃት ስነስርዓት የሚካሄድ ሲሆን ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃዎች፣ የኮሜዲ ዝግጅትና የመስቀል በዓል አከባበር ታሪካዊ ዳራ እንደሚቀርቡም ጋዜጠኛና ፕሮሞተር አብርሃም ግዛው ተናግሯል፡፡
በእለቱ ታዋቂ ሰዎች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይታደማሉ ተብሏል፡፡ አብርሃም ግዛው ኢንተርቴይመንትና ፕሬስ ስራዎች ድርጅት “የጥበብ ብልጭታ” የተሰኘና በብስራት ኤፍኤም የሚተላለፍ የኪነ ጥበብ ፕሮግራም አዘጋጅ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን የመስቀል በዓልን ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ማዘጋጀቱም ታውቋል፡፡

Published in ዜና

• ባለፈው ዓመት በትራፊክ አደጋ የ448 ሰዎች ህይወት አልፏል
• 22 ተሳፋሪዎች፣ 19 አሽከርካሪዎች፣ የተቀሩት እግረኞች ናቸው

  ለአሽከርካሪዎች የወጣው ደንብ፤ ማንኛውም ሹፌርም ሆነ ከጐን የተቀመጠ ተሳፋሪ፤ የአደጋ መከላከያ ቀበቶ (Seat belt) ሳያስር በጉዞ ላይ ከተገኘ 120 ብር እንደሚቀጣ የሚጠቁም ሲሆን ለሁለቱም ወገን ተጠያቂው አሽከርካሪው ነው ይላል፡፡ እስካሁን ግን ህጉ ከአሽከርካሪዎች በቀር ተሳፋሪ ላይ ሳይተገበር ቆይቷል፡፡ ተሳፋሪዎች እንኳንስ ቀበቶ ሊያስሩ ቀርቶ አብዛኞቹ መኪኖች የአደጋ መከላከያ ቀበቶ ከእነአካቴው የላቸውም፡፡ ተሳፋሪው ቀበቶ የማሰር ልማድ ቢያዳብር ኖሮ፣ በተለያዩ ጊዜያት በሚደርሱ በርካታ አሰቃቂ አደጋዎች ላይ የሟቾችን ቁጥር መቀነስ ይቻል ነበር ይላል - ፖሊስ፡፡
ተወዳጇ አርቲስት ሰብለ ተፈራም በዘመን መለወጫ ዕለት፣ መስከረም 1 ቀን 2008 ዓ.ም በደረሰባት ድንገተኛ የመኪና አደጋ ወቅት ቀበቶ አስራ ቢሆን ኖሮ የተሻለ የመትረፍ ዕድል ሊኖራት ይችል ነበር ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንደገለፀው፤ ትራፊኮች የአሽከርካሪን ብቻ ሳይሆን ከጐን የሚቀመጡ ተሳፋሪዎችንም ቀበቶ እንዲያስሩ ቁጥጥር አለማድረጋቸው  ስህተት ነው፡፡
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ስለጉዳዩ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ “በወቅቱ ቀበቶ የማሰርን ጉዳይ በአሽከርካሪው ላይ ብቻ ያጠበቅነው አብዛኞቹ መኪኖች ከእርጅና ጋር በተያያዘ ቀበቶ ስላልነበራቸው ነው” ብለዋል፡፡
ዘንድሮ ግን ህጉ በጥብቅ ተግባራዊ መደረግ እንደሚጀምር የጠቁሙት ኢንስፔክተሩ፤ አሽከርካሪዎች በህጉ መሰረት የተሳፋሪውንም ቀበቶ አሁኑኑ እንዲያስተካክሉ አሳስበዋል፡፡
“ህይወትን ከአደጋ መከላከል ለራስ ነውና በተለይ በግል ተሽከርካሪ የሚጠቀሙ ግለሰቦች ቀበቶ ማሰርን ካሁኑ መላመድ ይኖርባቸዋል” በማለት ኢንስፔክተሩ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
ባለፈው ዓመት (2007 ዓ.ም) በአዲስ አበባ በትራፊክ አደጋ ምክንያት 448 ሰዎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 22ቱ ተሳፋሪዎች፣ 19ቱ አሽከርካሪዎች፣ የቀሩት እግረኞች እንደነበሩ የትራፊክ ፖሊስ መረጃ ያመለክታል፡፡


Published in ዜና
Saturday, 19 September 2015 09:02

የታሪክ ባህሪያትና ዓላማ

(በፕ/ር መስፍን “አዳፍኔ” መነሻነት

   በአማርኛ ቋንቋ ከሚጽፉ እጅግ ጥቂት ኢትዮጵያዊያን ምሁራን መካከል አንጋፋው ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አንዱ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ በሚጽፏቸው በሳል ጽሁፎችና በሚያነሷቸው አዳዲስ ጉዳዮች የምሁርነትን ልክ አሳይተውናል ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ በተለይ ባለፉት አስር ዓመታት በየሁለት አመቱ ልዩነት ማለት ይቻላል በተከታታይ ግማሽ ደርዘን የሚሆኑ መጽሀፍትን አስነብበውናል፡፡ ባለፈው ዓመትም (በ2007) ‹አዳፍኔ፡ፍርሃትና መክሸፍ› በሚል ርዕስ አዲስ መጽሀፍ አሳትመዋል፡፡
‹አዳፍኔ› ፕሮፌሰሩ በ2005 ዓ.ም ያሳተሙት ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› መጽሀፋቸው ተከታይ ክፍል ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ሁለት አስረጂዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ አንደኛው ከጭብጥ አኳያ ብዙ ተመሳስሎሽ አላቸው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ‹አዳፍኔ› ከያዛቸው አስር ምዕራፎች ውስጥ ሶስቱ (ይህም የመጽሀፉን ዘጠና ስድስት ገጾች ወይም 40 በመቶ ያህል ይሸፍናል ማለት ነው) በ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› ላይ በተለያዩ ጸሀፍት ለተሰነዘሩ ትችቶች ምላሽ የሰጡበት (በመጽሀፉ እንደተገለጸው የ‹ ትችቶች ትችት›) ነው፡፡
በዚህ መጣጥፍ አዘጋጅ አተያይ፤የመጽሀፉ ዋነኛ መገለጫዎች (መልኮች) ሁለት ናቸው፤እነዚህ ሁለት መገለጫዎችም የመጽሀፉ ውበቶች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው መጽሀፉ በይዘቱ ሰፋ ያለ መሆኑ ነው፤ከዚሁ ጋር የተያያዘው ሁለተኛው፣ መጽሀፉ በቅርጹና አቀራረቡ የራሱ የሆነ አዲስ ቀለም ይዞ መምጣቱ ነው፡፡ አዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ እጅግ በርካታ ጉዳዮችን ይዳስሳል፤ታሪክ፣ባህል፣ስልጣንና አገዛዝ (ፖለቲካ)፣ኢኮኖሚክስ፣ስነመንግስትና አስተዳደር (አገር፣ህዝብና መንግስት)፣ሀይማኖት፣ትምህርትና ዕውቀት እንዲሁም ዕውነት፣ ስነ-ልቦና፣ፍልስፍና እና በሌሎች የጥናት ዘርፎች ዙሪያ የሚሽከረከሩ ጽንሰ ሀሳቦችን ያነሳል፡፡ ሌላው የመጽሀፉ መልክ ለጥናትና ምርምር፣ለጥልቅ ውይይትና ክርክር የሚጋብዙ ሀሳቦችን ማንሳቱና በዚሁ በተቃኘ አቀራረብ መዘጋጀቱ ነው፡፡
ወጣቱ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ በመክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ መጽሀፍ ዙሪያ ያለውን አተያይ ከሁለት አመታት በፊት ገደማ በአንድ መጣጥፉ አስነብቦናል፡፡ ዲያቆን ዳንኤል በመጣጥፉ ካነሳቸው በርካታ ቁም ነገሮች አንዱ የክሽፈት ታሪክ እንጂ የታሪክ ክሽፈት የሚባል ሊኖር አይችልም የሚለው አንዱ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፤ በአዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ መጽሀፋቸው ‹የትችቶች ትችት› በሚለው ምዕራፍ ውስጥ ለዚህ መልስ ሰጥተዋል፤ ነገር ግን መልሱ አጥጋቢ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡  መልስ የተሰጠበት አግባብ የተደራጀና ግልጽ አይደለም፡፡ እንዲያም ሆኖ የአዳፍኔ ዋነኛ ጭብጥ በክሽፈት ታሪክና በታሪክ ክሽፈት ዙሪያ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሀሳቦቹ እዚህም እዚያም ተበታትነው የቀረቡ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ አንባቢ የጠራ ግንዛቤ እንዳይኖረው ያደርጋል የሚል ስጋት አለኝ፡፡
በዚህ መጣጥፍ አቅራቢ እምነት፤ የክሽፈት ታሪክ እና የታሪክ ክሽፈት የሚሉት ሁለት ሀሳቦች ብዙ ጉዳዮችን ያዘሉ በመሆናቸው በጥልቀት መታየት አለባቸው፡፡ በመሆኑም  አዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ ስለ ክሽፈት ታሪክና ስለ ታሪክ ክሽፈት ያነሳቸውን ሀሳቦች በማሰባሰብ ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡ መጽሀፉ ከአደረጃጀት አንጻር በዚህ ሁኔታ ቢቀርብ መልዕክቱን በይበልጥ ለመረዳት ያስችላል፤በመጽሀፉ በተነሱት ጉዳዮች ላይ በአንባቢያን የሚቀርቡ የውይይትም ሆነ የክርክር ሀሳቦች ቅርጽ እንዲይዙ ለማድረግም ያግዛል፡፡
የታሪክ ምንነት፣ባህሪያትና ዓላማ
የታሪክ ፍልስፍና ዘይቤ አባት በመባል የሚታወቀው አውግስ ሚኖስ፤ የታሪክ ምንነትና ዓላማን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡-
ታሪክ መንግስት መቆሙንና መፍረሱን፣ ህዝቦች ማደጋቸውንና መውደቃቸውን ያትታል፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት አምላክ ባቀደው መሰረት የሰውን ዘር ወደ እውነተኛው ብርሃን ለመምራትና ለማዳን ሲል ነው፡፡
የፕሮፌሰር መስፍን የታሪክ ምንነትና ዓላማ አረዳድም ከአውግስ ሚኖስ ጋር በይዘቱ አንድ ነው፣ቋንቋው ቢለወጥም፡፡ እንደፕሮፌሰሩ አገላለጽ ታሪክ ማለት፡-
“…..ለአንድም ሰኮንድ የማያቋርጥ የኑሮና የአኗኗር ጅረት ነው፡፡ ……..ታሪክ የአንድ ህዝብ የስራ መዝገብ ነው፡፡” (ገጽ 98-99)
የታሪክ ዓላማ ደግሞ ህዝቡ ያለፈውን ዘመን ከፍታና ዝቅታ አስታውሶ፣ የአሁኑ ትውልድ ካለፈው ትውልድ በጎ ጎኖች ትምህርት ወስዶ፣ ከችግሮቹ ተምሮ፣ በኑሮው መሻሻል እንዲያሳይ ማድረግ ነው (ገጽ 28፣29 )፡፡  
በአጠቃላይ፡- ታሪክ ማለት የትናንት ዕውነትን (በጎም ሆነ በጎ ያልሆኑ) መመርመር ነው፡፡የታሪክ ዓላማ የሰው ልጅ የትናንት በጎ ተግባራቱን አዳብሮ፣ከስህተቱ ደግሞ ተምሮ የዛሬና የነገ ህይወቱን እንዲያቀና ማድረግ ነው፡፡ በዚህም አውግስ ሚኖስ የታሪክን አስፈላጊነትና ዓላማ ከመለኮታዊ ሀይል ዓላማ ጋር ያዛምደዋል፡፡ በዚህም የታሪክ ዓላማ የፈጣሪ አላማ ነው፡፡
ስለታሪክ ባህሪያት
በግሌ የታሪክ ባህሪ ከአምላክ ባህሪ ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡ ታሪክ አምላካዊ ባህሪዎችን ሁሉ ይወርሳል፡፡ ታሪክን ከአምላካዊ ባህሪ ጋር ለማንጸር ያደረግሁት ጥረት ያልተመቻቸው የአምላክን ባህሪ የማያውቁ ናቸው ባይ ነኝ፡፡ ለመሆኑ የአምላክ ባህሪያት ምንድናቸው? የታሪክ ባህሪያትስ ?
በመሰረቱ የአምላካዊነት መሰረት ሀቅ ነው፤የታሪክ መሰረቱም እንዲሁ ሀቅ (እውነት) ነው፡፡ ፈጣሪ የሰው ልጆችን ጨምሮ በአጠቃላይ በፍጡራን ላይ ፍጹም ስልጣን አለው፤ታሪክም ይህ ስልጣን አለው፡፡ የፈጣሪ ዓላማ የሰው ልጆች ሁሉ በቀና መንገድ እንዲያልፉ ማስተማር ነው፤የታሪክ ዓላማም እንደዚሁ ነው፡፡ ወደር የለሽ ትዕግስትና ሆደ-ሰፊነት አምላካዊ ባህሪ ነው፤ዓላማውም ሰዎች በራሳቸው ከጥፋት መንገድ እንዲታቀቡ፣ካለፈው ስህተታቸው እንዲታረሙ ጊዜ መስጠት ነው፡፡ የታሪክ መንገድም ይህ ነው፡፡ በመሰረቱ ዕውነትን (ታሪክን) መበረዝ ወይም ማጥፋት የሚቻል ሊመስለን ይችላል፡፡ መሪዎችም ይህን ለማድረግ የቻሉ ሊመስለን ይችላል፡፡ ግን በጥልቀት ከመረመርነው አልቻሉም፡፡ የፈጣሪን ትዕግስት ዓላማ ያልተረዱም በስህተት ላይ ስህተት እየፈጸሙ፣ በመጨረሻም ከነጭራሹ የፈጣሪን ስልጣን ሲመኙ፣ሲብስም ህልውናውንም ሲክዱ፣መቀበሪያቸውን ጉድጓድ እየማሱ እንደሆነ ሳይታወቃቸው፣የትዕግስቱ መብዛትም በቆፈሩት ጉድጓድ እንዲቀበሩ ያደርጋቸዋል፡፡ የታሪክም መንገድ ይህ ነው፡፡ ታሪክ ከስህተት ለመማር እድል ይሰጠናል፡፡ ይህን ማድረግ ያልቻሉ ግን በቆፈሩት ጉድጓድ ይቀበራሉ፡፡ በታሪክ ማህደር እንደተዘከረው፤ በታሪክ ላይ የዘመቱ ሁሉ መጨረሻቸው መጥፋት ነበር፡፡ በእርግጥም በዘመናት ሂደት ያለፉ፣ታሪክ ላይ ያመጹ አገዛዞችና ነገስታት አነሳስና አወዳደቅን ለመረመረ ይህ ይገለጥለታል፡፡ ታዲያ የፈጣሪ የቅጣት በትር ፍጹም ፍትሃዊ እንደሆነው ሁሉ የታሪክ ቅጣትም ጊዜ ወይም ቦታ የማይቀይረው፣ ለማንም የማይወግን ፍጹም ፍትሃዊ ነው፡፡ ትናንትም ይሁን ዛሬ በታሪክ ላይ ያመጹ ሁሉ በጥፋታቸው ልክ ተቀጥተዋል፤ነገም እንዲሁ እንደሆነ ይቀጥላል፡፡

    አቶ ደቻሳ ጅሩ ይባላሉ፡፡ ትውልዳቸው ከበቆጂ 20 ኪ.ሜ ርቃ ከምትገኘው ሽርካ ከተማ ነው፡፡ ተማሪ በነበሩ ጊዜ የማራቶን ሯጭ ለመሆን መሞከራቸውን የሚናገሩት አቶ ደቻሣ፤ ለስፖርቱ ከፍተኛ ፍቅር ቢኖራቸውም አትሌት መሆን ግን አልቻሉም፡፡ በላቀ ደረጃ የተማሩ የእርሻና ደን ጥምር ተመራማሪ ናቸው፡፡ ከጅማ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲፕሎማቸውን በእርሻ አግኝተዋል፡፡ ከአለማያ ዩኒቨርሲቲ በእጽዋት ሳይንስ ቢ.ኤስ.ሲ ድግሪ ሠርተዋል፡፡  በጣሊያን ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ በምግብ ሥርዓት  አድቫንስድ ዲፕሎም አግኝተዋል፡፡ ከአውስትራሊያው የሜልቦርን ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የማስትሬት ዲግሪያቸውንም በ “አግሮ ፎረስተሪ” ተቀብለዋል፡፡ ከእርሻና ደን ጥምር ምርምራቸው ባሻገር አቶ ደቻሣ አትሌቲክስን በጣም ልዩ ትኩረት ይሰጡታል፡፡ በፍቅርና በፍላጐት አትሌቶችን ይከታተላሉ፡፡ የኢትዮጵያን ሯጮች የስልጠና እና የውጤት ሁኔታዎችን ባገናዘቡ ጥልቅ ምርምሮችንም እያደረጉ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የሳይንስና የምርምር አቅጣጫዎች እንዲሁም ጥበባዊ ዕይታዎች ላይ ያተኮረ የመፅሃፍ ዝግጅታቸው ከ500 ገፆች በላይ ሆኗል፡፡ ለህትመት ለማብቃትም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ናቸው፡፡ ከ40 ዓመታት በላይ በተቀናጀ ግብርና ምርምር (በአዝርዕትና በእንስሳት) ላይ በመስራት ከፍተኛ ልምድ ማካበታቸው ትልቅ አቅም መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ይህን ልምዳቸውንም በስፖርቱ በተለይም በአትሌቲክስ ላይ ለመተርጐም ይፈልጋሉ፡፡  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ወደ ሳይንስና ምርምር መጠጋት እንዳለበትም የሚመክሩት አቶ ደቻሣ፣  በሥነምህዳር እና በአየር ተስማሚነት የኢትዮጵያን አትሌቲክስ የሚያሳድግ ጥልቅ ምርምር ማድረጋቸውን ያስረዳሉ፡፡ ስፖርት አድማስ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የለውጥ አቅጣጫ ላይ ያተኮረውን ምርምራቸውን  በመንተራስ ከአቶ ደቻሣ ጅሩ ጋር ሰፋ ያለ ቃለምልልስ አድርጓል፡፡ የቃለምልልሱን የመጀመሪያውን ክፍል እንደመግቢያ ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

     

        የእርሻና ደን ምርምር ተመራማሪነት ሙያዎን ከስፖርቱ ጋር እንዴት ያዛምዱታል?
ጥያቄህን የምገነዘበው ወጣና ለየት ባለ መንገድ ነው፡፡ ሃሳቤ እንደመጫኛ ረጅም ሆኖ ይያያዛል፡፡ እንደሰፌድ ላይ እህል ብትን ያለ የተቆራረጠ ሊሆን ይችላል፡፡ በአጠቃላይ አስተሳሰቤን በድር ልትመስለው ትችላለህ፡፡ በእርሻና ደን ጥምር ምርምር ባተኮረው ሙያዬ የረጅም ዓመታት ልምድ ውስጥ አግኝቻለሁ ራሴን ባይ ነኝ፡፡
ከስፖርቱ ጋር ያለው ትስስር በ60ዎቹ ተማሪ  በነበርኩ ጊዜ የተቆሰቆሰ ፍላጐት ነው፡፡ ያኔ ማናችንም ወንድ ተማሪዎች ስንዘፍን እንደ ጥላሁን ስንሮጥ እንደ አበበ ቢቂላ መመኘትና ማለም የጸና ፍላጎታችን ነበር፡፡ በወቅቱ  የሙዚቃ አርቲስቶቻችን ‹‹ጥላሁን ገሰሰ ይድርሻል፤ አበበ ቢቂላ ያገባሻል›› እያሉ በመዝፈን አትሌቱን ሙሽራ ያደርጉታል፡፡ በተለይ ይህን የመሰለው ሁኔታ ይማርከኝ ነበር፡፡ ጐበዝ ተማሪ ስለነበርኩ ያኔ ከትምህርቱ ጐን ለጐን በስፖርትም ጐበዝ የመሆን ፍላጐት ስለነበረኝ በንቃት በመሳተፍ አልፌበታለሁ፡፡
በከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ተማሪነቴ ደግሞ በተለይ በጂዮግራፊ ትምህርት በጣም ጐበዝ ነበርኩ፡፡ ስለ አየር ንብረት እና መልከዓ ምድር ሁኔታዎች ላይ በነበረኝ የምርምር ፍላጐት እታወቅ ነበር ለአስተማሪዎች ከባድ ጥያቄዎችን የማንሳት ልምዱም ነበረኝ፡፡ ኮሌጅ ስገባ ደግሞ በሜትሮሎጂ ዙሪያ ከፍተኛ ፍላጐት አሳይ ስለበር፡፡
አንዳንድ አስተማሪዎች በሜትሮሎጂም ትምህርት እንድገፋበት ይመክሩኝም ነበር፡፡ የአየር ንብረት እና የመልዕክዓ ምድር ሁኔታዎች ከስፖርቱ ጋር ከፍተኛ ተያያዥነት እንዳላቸው ማንም ይረዳዋል፡፡
በእርግጥ የእርሻና ጥምር ደን ምርምር ባለሙያ እንደመሆኔ በዚህ ዋና የግብርና ዘርፈ- ብዙ ተግባራትን አከናውናለሁ፡፡ ሞያው ቴክኖሎጂን ከማፍለቅ በዘለለ ለማህበረሰቡ ስልጠና መስጠት እና ግኝቱን ማስረጽንም ያካትታል፡፡ የሙያው ይዘትና ተግባር ከላይ እንደገለጽኩት ሆኖ፡-  እርሻና ደን ጥምር (አግሮፎርስተሪ) ምርምር  ሲገለጥ ሳይንስ አርትና ቢዝነስ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡  አካባቢን የሚያስጠብቅ፤ የኢኮኖሚ ፋይዳ ያለውና ማህበረሰቡ ተቀብሎት የሚተገበር የምርምርና የማስፋፊያ የስራ ሂደት ነው፡፡ የእርሻና ደን ጥምር ምርምር ባለሞያ የሆነ ሰው ሳይንቲስት ብቻ አይደለም አርቲስትም ነው ማለት ይቻላል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቁሪ ሆኖ ደንንና ፋይዳውን በዋናነት ትኩረት በመስጠት በማስቀደም ይንቀሳቀሳል፡፡ ሰብልና እንስሳትን አካቶ በተጣመረ/በተቀናጀ/ መልኩ ማየትን መስራትንም ይችላል፡፡ ከ40 ዓመታት በላይ በሙያው ያገለገልኩት በዚህ ዓይነት ቁርጠኛ አቋም ነው፡፡ በአጠቃላይ ባለሁበት ሙያ ፈረሱን ሯጭ፣ በሬውን ጐታች፤ ላሟን ወተት ስጭ፤ ከብቱን ስጋ ስጭ፣ ዶሮዋን እንቁላል ጣይ…ወዘተ ለማድረግ ብዙ ምርምሮችን በማድረግ ሠርቻለሁ፡፡ እነዚህን የምርምር አቅጣጫዎች በሰው ልጅ ላይ ለመተግበር በስፖርቱ ለውጥ የሚፈጠርባቸውን ሁኔታዎች ለመተባበር እንደሚቻል ፍፁም እምነት አለኝ፡፡  
በሳይንሳዊ ልማት ያተኮረው ሙያዎ ተቀራራቢነት በሌለው የአትሌቲክስ ዘርፍ ላይ እንዴት ይተረጐማል? በስፖርቱ ላይ ጠለቅ ያለ ሳይንሳዊ ግምገማና አስተያየት መስጠትስ አይከብድም ወይ?
ጥያቄህን በጥያቄ ልመልሰው? ‹‹አትሌቲክስን ኢ-ሳይንሳዊና ጸረ-ልማት ያደረገው ማነው›› አላግባብ? ስለምንለያየው እንጂ አትሌቲክሱም ሳይንሳዊ ልማት ነው፡፡ በእርግጥ ሳይንሳዊ ግምገማ እና አስተያየት መስጠት ይከብዳል ማለትህ ልክ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ማንኛውም የምርምር መስክ ከባድ ነው፡፡ የባለሙያው ኃላፊነት ከባድንቱንና ውስብስብነቱን ማቅለል እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የወደፊት አቅጣጫዎች ስርነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልግ አስተያየቶች ይሰጣሉ፡፡ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብና ውጤታማ ለመሆን ስፖርቱ ያለበት ደረጃ አስተማማኝ አይደለም፡፡ ከፌዴሬሽኑ እና ከአትሌቶች ባሻገር የለውጥና የዕድገት አቅጣጫዎችን በመቀመር ወሳኝ ሚና መጫወት ያለባቸው ባለድርሻ አካላት እነማን መሆን አለባቸው?
በርግጥ ስር ነቀል ለውጥ የሚለው አካሄድ ትንሽ የሚከብድ ይመስለናል፡፡ የባሰ ችግር ሊፈጥር ስለሚችል ነው፡፡ የዛፍ ሰው ስለሆንኩ መሰለኝ፣ ከስሩ መንቀል መጣል የሚያዋጣ አይመስለኝም፡፡ ማን ማንን ይተካል፣ የቱን ግንዛቤ ብናዳብረው የተሻለ ይሰራል በሚለው መንገድ ለውጥን ማሰብ ይሻላል፡፡ ስለስፖርቱ የወደፊት አቅጣጫዎች ምላሽ ሰጪዎቹ ከሞያው ጋር ይበልጥ አግባብነት ያላቸው የፌዴሬሽን ባለሙያዎች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ከፌዴሬሽኑ፣ ከስፖርት ኮሚሽኑ እና ከአትሌቶች ባሻገር ግን የላቀ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ብዙ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል አትሌቲክሱ ሳይንሳዊ በሆኑ አቅጣጫዎች መመራት አለበት፡፡ እንደሰማሁት የአትሌቶች የሙያ ማህበር መቋቋሙ አንድ ትልቅ እምረታ ነው፡፡  በማንኛውም የሙያ ማህበር እንደምናየው ግን መሆን የለበትም፡፡ ከመዋጮ ክፍያ እና መብትና ግዴታ ከማስጠበቅ ባሻገር በስፖርቱ ዕድገት ማህበሩን ውጤታማ ተግባር እንዲወጣ ማስቻል ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ከተለመደው የፌዴሬሽኑ መዋቅር ውጭ ለስፖርቱ ለውጥና ዕድገት ወሳኝ ግብአቶችን የሚሰጡትን ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስተባባሮ መንቀሳቀስ ግድ ነው፡፡ ባለሙያዎቹ በየመስኩ ያላቸውን እውቀትና ልምድ በማገናዘብ ጠቃሚን መረጃዎች የሚያቀርቡበት ሂደት መፈጠር አለበት፡፡ ለአሰልጣኞችና ለአትሌቶች ድጋፎችን በመስጠት እንዲሳተፉ ማድረግ ነው፡፡  ከዓለም ጋር ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ፣ በየጊዜው ተተኪ አትሌቶችን በተሟላ ብቃት ለማውጣት የሚቻለው በዚህ ዓይነቱ አቅጣጫ ብቻ ነው፡፡ በከፍተኛ ምርምር እና ቅንጅታዊ ስራዎች  ላይ ሁሉም ወሳኝ ባለድርሻ አካላት አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ የግብርና፤ የጤና፣ የስነምግብ፣ የስነልቦና፣ የአየር ሃይል፣ የአየር መንገድን፣ የሜትሮሎጂ ባለሞያዎች የሚያካትት መዋቅርን ፌዴሬሽኑ ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከባለሞያዎቹ ጋር በዚህ ጉዳይ ስንወያይ ሁሉም የበኩላቸውን  ማድረግ እንደሚፈልጉ ይገልጻሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ ለፍላጐታቸው ትኩረት ሰጥቶ አቅማቸውን መጠቀም አለበት፡፡
እርስዎን ጨምሮ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ያሏቸውን ባለሙያዎች ወደ ስፖርቱ ማቅረብ የሚቻለው እንዴት ነው?
የመጀመሪያው ርምጃ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ፣ የአትሌቶች ማህበርና የስፖርት ኮሚሽኑ ሌሎቹን ባለድርሻ አካላት አሰባስበው ለውጥ ሊፈጥሩ የሚችሉበትን መድረክ መፍጠር ነው ይህን አስመልክቶ በአገር አቀፍ ደረጃ ምክክር የሚደረግበትን የስብሰባ መድረክ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡   
ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤት ማሽቆልቆል ፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ተጠያቂ ነን፡፡ ይህ ስል የአስተዳደሩንና የአመራሩን ድክመት ወደ ጐን በመተው አይደለም፡፡ እንደዜጋ ያገባናል የምንል የሁሉም ዘርፍ ባለሙያዎች ግን ተጠያቂ ከመሆናችን በፊት አብረን የምንሠራበት ዕድል አልነበሩንም፡፡ እንደሚባለው አብረን መብላት እንጂ አብረን መስራት የማንችል ሆነናል፤- ለስራ ያለን ትኩረት ግለሰባዊ ነው፡፡ የቡድን ስራ ውጤታማ እንደሚያደርግ ፍልስፍናው በስኬት ላይ መንጸባረቁ እንደማይቀር የምንገነዘብ ይመስለኛል፡፡ የምክክር መድረኩ ተዘጋጅቶ ከዚያም ሁሉም ባለሙያ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዴት ማቅረብ እንደሚችል ከሌሎች ጋር ተማክሮ መወሰን ይጠበቅበታል፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በተናጠል ድጋፍ የሚያደርግለት አማካሪ አካል ያስፈልገዋል፡፡
የአትሌቶችን ውጤታማነት በመፈታተን ለከፍተኛ ውጣውረድ የሚዳርጓቸው በርካታ ሁኔታዎች አሉ፡፡ የጤና በስነልቦና ያለመረጋጋትን ጨምሮ፤ የግል ብቃት፤ ከአሰለጣጠንና አቀባብል ጉድለትና ከመሳሰሉት የሚመነጩ ክፍተቶች ብዙ ናቸው፡፡….(ይቀጥላል)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ከዘመን ዘመን ስላሸጋገርከን ምስጋና ይግባህ፡፡
አንድዬ፡— አጅሬው ደግሞ መጣህ!… ዘንድሮስ ፈጠንክ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ዓመቱን ሙሉ ስጨቀጭቅህ ከምኖር ለምን አንድ ጊዜ ዝርግፍ አይወጣልኝም ብዬ ነው፡፡ መቼም የተሸከምነው ሸክም እኮ አንድዬ… የተሸከምነው ሸክም!
አንድዬ፡— እሺ፣ አሁን ደግሞ ምን አድርግ ልትለኝ ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንደዬ፣ አሁን እንኳ ለየት ያለ ነው፡፡ ምን መሰለህ… አሥርቱ ትዕዛዛትን እንደገና አይተህ ወይ አሻሸልልን፣ ወይ ሙሉ ለሙሉ ለውጥልን፡፡
አንድዬ፡— (ከት ብሎ ሳቀ)  ብላችሁ፣ ብላችሁ ደግሞ በዚህ መጣችሁ! ምኑን ነው የማሻሽልላችሁ! ቃሌ እንደማይለውጥ ጭራሹኑ ረሳችሁት!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንደዬ ብዙ ትዕዛዞችህን፣ — እንደውም ሁሉንም ልንል ማለት አልቀረንም — መፈጸሙ እየከበደን ስለመጣ ማሻሻያ ይደረግልን፡፡
አንድዬ፡— ነገርኩህ፣ ቃሌ አይለወጥም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ጊዜው ተለውጧላ! ጊዜው ተለውጧል!
አንድዬ፡— ጊዜማ ያው ነው፡ እየተለዋወጠ ያስቸገረኝ ጊዜው ሳይሆን የእናንተ ባህሪይ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ያኔ አንተ እነኛን ትዕዛዛት ለሙሴ የሰጠኸው ጊዜ የነበረው ዓለምና የአሁኑ ዓለም ተለዋውጧል እኮ!
አንድዬ፡— ታዲያ እናንተ ትዕዛዛቴን መፈጸም ካልቻላችሁ ተዉት እንጂ፡ ያውም ለእናንተ  ‘ስፈጥራቸው የሠራሁት ስህተት ነበር እንዴ!’ እያልኩ ራሴኑ እንድጠይቅ ላደረጋችሁኝ  ብዬ  ነው ዓለም የሚመራባቸውን ትዕዛዛት የምለውጥ!
ምስኪን ሀበሻ፡— እሺ አንድዬ፣ ቢያንስ ትዕዛዛቱን ለጊዜው እኛ ላይ እንዳይሠራ አግድልንና የሽግግር ጊዜ ስጠን፡
አንድዬ፡— የምን ጊዜ አልከኝ?
ምስኪን ሀበሻ፡— የሽግግር ጊዜ…
አንድዬ፡— እሱ ደግሞ ምንድነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ በቃ ስለእኛ ነገር ዓለሙን ትተኸዋል! አየህ እኛ ዘንድ ለሁሉ ነገር የሽግግር ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ አሥር ዓመት ለሞላውም፣ ሀያ ዓመት ለሞላውም የሽግግር ጊዜ ለምዶብናል፡፡ ይኸው ከስንትና ስንት ዓመት በፊት ጀመርናቸው ያልናቸው ነገሮች ላይ ሁሉ ገና ሽግግር ላይ አይደለን፡፡ አንድዬ ትንሽ ቂ…ቂ…ቂ… ብል ቅር ይልሀል!
አንድዬ፡— ቂ…ቂ..ቂ…. ደግሞ ምንድነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— ሳቅ ነዋ አንድዬ!
አንድዬ፡— ተስቆ ተሙቷል፡፡ በል ሳቅህን ለብቻህ ስትሆን ትስቃለህ፡፡ አንዳችሁ በአንዳችሁ እየሳቃችሁ አይደል ወደ እኔ ለአቤቱታ የምትግተለተሉት! አሁን ወደ ጉዳይህ…የመጨረሻ ቃሌ ትዕዛዛቱ አይለወጡም ነው፡፡ ጨረስን አይደል!
ምስኪን ሀበሻ፡— አልጨረስንም አንደዬ፣ አለጨረስንም፡፡ ገና መች ጀመርንና!
አንድዬ፡— ስነግርህ ስማ እንጂ…ነው ወይስ እልፍኜ ድረስ እያስተጋባ የሚረብሸኝ ጭቅጭቃችሁን ቁጭ ብዬ ላዳምጥ!
ምስኪን ሀበሻ፡— በጭራሽ አንድዬ፣ በጭራሽ! ግን ለምሳሌ ‘የሰው ሚስት አትመኝ’ ምናምን የሚለው ትዕዛዝ በአሁኑ ጊዜ አንተስ ስታየው ልክ ነው? አንተ መጀመሪያ የመመኘት ባህሪይን ባትፈጥርልን ኖሮ እኛስ እንመኝ ነበር!
አንድዬ፡— እና ምን ይሁን ነው የምትለው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ምኞት ብቻ ሀጢአት መሆኑ ልክ አይደለማ! ትንሽ አኮ የምንተነፍሰው ምኞት የተባለ ነገር ስላለ ነው፡፡ እሱኑ ወስደህብን ምን እንሁን?
አንድዬ፡— ታዲያ ደግ ደጉን ነገር ተመኙ እንጂ የሰው ሚስት ምን ያስመኛችኋል?
ምስኪን ሀበሻ፡— ዘመኑ ነዋ አንድዬ… ደግሞ አንድዬ፣ አትታዘበኝ እንጂ ገና ሲያዩዋት ልብ ቷ የምታደርግ የሰው ሚስት ከመመኘት የበለጠ ምን ደስታ አለ! አንድዬ ዘመናዊነት የሚለካው አንድም የሰው ሚስት በመመኘት፡ ከተቻለ ደግሞ እነሆ በረከት…
አንድዬ፡— እነሆ ምን?
ምስኪን ሀበሻ፡— እነሆ በረከት…ምን መሰለህ አንድዬ፣ ይሄ አንሶላ መጋፈፍ የሚባል ነገር አለ አይደል… አንዳንዴ እንደ ቅኔ ልናስመስለው እነሆ በረከት እንለዋለን፡፡ ለነገሩ አንድዬ ዘንድሮ የሚገፈፍ አንሶላም አያስፈልገንም፡፡
እሱንማ እኔ መኖሬን ረስታችሁ ‘ሰው ባያይ እሱ ያየናል ብላችሁ ሳትሰጉ፣ በአደባባይ ተያይዛችሁት የለ እንዴ! … በፊት እኮ የአካል እንቅስቃሴ የምታደርጉ እየመሰለኝ መለስ ብዬም አላይም ነበር፡፡ በኋላ ላይ አይደል እንዴ ጉዳችሁን ያወቅሁት!
ምስኪን ሀበሻ፡— ይኸው አንድዬ፣ ይኸው! አኔም የምልህ እኮ ይህንኑ ነው፡፡ እነዛ የምታያቸው እኮ ገሚሶቹ የሌሎች ባሎች ሚስቶች፣ ገሚሶቹ የሌሎች ሚስቶች ባሎች ናቸው፡፡ አንድዬ እንደውም አንድዬ፣ ራሳቸው ሚስት፣ ባል የሚባሉት ቃላት የትርጉም ለውጥ ያስፈልጋቸዋል፡፡
አንድዬ፡— እውነት!
ምስኪን ሀበሻ፡— እንክት ነዋ፣ አንድዬ!… ለምሳሌ ሚስት የሚባለውን ቃል ትርጉም ‘ለግል ይዞታነት ብቻ ሳይሆን እንደ ተጫባጭ ሁኔታው አንዳንዴም ‘አውትሶርስ’ በማድረግ…
አንድዬ፡— አንደኛውን ለይቶላችኋልና! አንደኛውን የጋራ በለኝና እረፈው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አየህልኝ አይደል አንዴዬ! ይሄኔ እንዴት እየሆኑ ነው ብለህ አለፍ፣ አለፍ እያልክ ብየታየን ኖሮ እንዲሀ አትለኝም ነበር፡፡ አንድዬ…ሚስቱን ተነጠቆ የቺን ታክል የማይሰማው  ባል የሞላበት ዘመን ነው እኮ፡፡
አንድዬ፡— ለእናንተ አሥሩን ትዕዛዛት ማሻሻል ሳይሆን ማድረግ ያለብኝ ሌሎች ለእናንተ ብቻ የሚሆኑ አንድ መቶ አሥር ትዕዛዛት መጨመር ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ምነው አንድዬ፣ ምነው፡! አሁን ያለው ሸክም ከበደን እያልንህ እንደገና መቶ አሥር ትዕዛዛት!
አንድዬ፡— አንድ የማውቅላችሁ ነገር ቢኖር ሸክም እንደምትችሉ ነው፡፡ የእናንተ ሸክም ሌላው ትከኛ ላይ ቢሆን የሰዉ ሁሉ ትከሻ ተሳባብሮ፣ ተሰባብሮ እኔንም ‘ምን ብዬ ነው ትከሻ የሚል የአካል ክፍል የፈጠርኩት!’ ብዬ ጸጸት ይገባኝ ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ደግሞ አንድዬ ያኔ ትዕዛዙን ስታወጣ በወንዶች ላይ አድልዎ ፈጽመሀል፡፡ በዚሀ ዘመን ቢሆን ኖሮ በጸረ ወንድንት ትከሰስ ነበር፡፡
አንድዬ፡— ክሰሱኛ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ኸረ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን!
አንድዬ፡— አንተው ነህ ያልከው፡፡ እሺ፣ ምን ማለት ነበረብኝ፡
ምስኪን ሀበሻ፡— የሰው ሚስት አትመኝ ከሚለው አስከትለህ የሰው በባል አትመኚ ብለህ መጨመር ነበረብሀ!
አንድዬ፡— እንደዛ ባይባልስ የታወቀ አይደለም እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አይደለም አንደዬ፣ የታወቀ አይደለም፡፡ ዘንድሮ እኮ ከሚስት ነጣቂ እኩል ባል ነጣቂ ሞልቶልሀል፡፡
አንድዬ፡— ለመነጣጠቅማ ጊዜና ቦታ አታጡም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ኸረ ጊዜም ቦታም አያስፈልገንም…
አንድዬ፡— ማለት…
ምስኪን ሀበሻ፡— ማለትማ አንድዬ…መኪናው በለው፣ ቢሮው በለው፣ የህንጻ ጣራና ምድር ቤት በለው፣ የግምብ ጥግ በለው… ብቻ ልበለህ ሁሉ ቦታ ላየ ነው ሚስትምባልም የሚነጠቀው፡፡
አንድዬ፡— ግራ አጋባኸኝ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንደዬ ክፉ አታነግረኛ! በቃ እዛው ይነጠቃል፣ እዛው እንትን ይባላል…አለቀ ደቀቀ፡፡ ነገም ሌላ ቀን ነው፡፡
አንድዬ፡— ለመራቢያ የሰጠኋችሁን የሰውነት ክፍሎች መረባረቢያ አደረጋችኋቸዋ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ በትክክል ተመልሷል፡፡ አሁን ገና የእኛ ቋንቋ እየገባህ ነው፡፡  አንድዬ፣ ግን የአሥርቱን ትዕዛዛት ነገር አስተካክልልንና ስትራቴጂ ነድፈን፣ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት ተረባርበን ለስኬት በማብቃት የምእተ ዓመቱን ግብ እናሳካለን፡፡
አንድዬ፡— ቆይ፣ ቆየኝማ እስኪ ያለከውን ድገምልኝ፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እኔም ቃል በቃል ለመድገም ያስቸግረኛል፡፡
አንድዬ፡— ባያስቸግርህ ነበር የሚገርመኝ፡፡ ሦስት ምዕራፈ የሚወጣውን ነገር በአንድ አራት ነጥብ ብቻ ነው እኮ የጨረስከው!
ምስኪን ሀበሻ፡— ዘመን ነዋ፣ አንድዬ! ከዘመኑ ጋር እሄድ ብዬ ነው፡፡
አንድዬ፡— በል አሁን ብዙ የቁም ነገር ጥያቄ ይዘው የሚጠብቁኝ ስላሉ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ መቼ ጨረስኩ! እንደውም አልጀመርኩም፡፡
አንድዬ፡— ሳምንት ተመለስ…
ምስኪን ሀበሻ፡— ይመችህ አንድዬ፣ ይመችህ!
አንድዬ፡— ሆሆይ… ቀስ ብለህ እኮ ቢራ ልጋብዝህ ልትለኝ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ብልህ አትገረም፡፡ እንደ አምላክ የሚያደርገን በዝተናል፡፡
አንድዬ፡— በል ደህና ሰንብት፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ዓመት በዓል ወቅት፣ አንድ አባት ልጁን ይዞ ወደ አንድ ሆቴል ቤት ጎራ ይላል፡፡ ለልጁ ለስላሳ ለሱ ነጭ አረቄ አዞ መጠጣት ይጀምራል፡፡ ያን አረቄ በላይ በላዩ ሲጨማምርበት ወደ ሞቅታው ተጠጋ፡፡
አረቄውን ልትቀዱለት የምትመላለሰው ቆንጆ ሴት እየተሞናደለችና ሽንጧን እያተራመሰች ስትመላለስበት ዐይኑ ከሱዋ አልላቀቅ አለ፡፡
“አንቺም ጠጪ፣ ለኔም አምጪ” ማለት ጀመረ፡፡ ቆንጆይቱም መጎንጨት ጀመረች፡፡ ሞቅ አላቸው ሁለቱም፡፡ ተጠቃቀሱና ተራ በተራ ወደ ጓዳ ገቡ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ልጅየው ለስላሳውን ትንሽ በትንሽ እየጠጣ ሲያስተውል ቆይቷል፡፡ አባቱ ሳይመለስ ብዙ የቆየ ስለመሰለው፣ ወደሄደበት አቅጣጫ ሄደ፡፡ አንድ ክፍል ውስጥ ተኝተዋል ለካ! ደንግጦ ቶሎ ወደ ቦታው ተመልሶ ተቀመጠ፡፡
አባትዬው ተመለሰ፡፡ አንድ ደግሞ ሂሳብ ከፈለና ወጡ፡፡
ቤት ደርሰው የሚበላ ቀርቦ በልተው እንደጨረሱ ጨዋታ መጣ፡፡
እናት - “እሺ ዙረታችሁ እንዴት ነበር?” አለች ወደ ልጁ እያየች፡፡
ልጁም - “መጀመሪያ ወደ ሆቴል ሄድን”
እናት - “እሺ?”
ልጅ - “አባዬ አረቄ አዘዘ፡፡ ለእኔ ለስላሳ ሰጠኝ”
እናት - “ከዛስ?”
ልጅ - “ከዛማ አባዬ ደጋገመ”
አባት - “በቃህ እንግዲህ! ወሬ አታብዛ”
እናት - “ተወው እንጂ ይንገረኝ”
ልጅ - “ከዛ የምታስተናግደንን ሴትዮ ጋበዛት”
እናት - ጉጉቷ ጨመረ፡፡ “እሺ ከዛስ?”
ልጅ - “ከዛ ሴትዮዋ ወደ ጓዳ ሄደች”
አባት - “አንተ ልጅ! ሁለተኛ ሽርሽር አልወስድህም!”
እናት - “ተወው ይጨርስልኝ!”
ልጅ - “ከዛ አባዬም ወደ ውስጥ ገባ”
እናት  - በችኮላ፤ “እሺ? ከዛስ?”
ልጅ - “አባዬ ሲቆይብኝ የት ሄደ ብዬ ወደዛ ሄድኩ”
እናት - “ከዛስ?”
ልጅ - “ከዛ አይቼ ተመለስኩ”
እናት - “ምን አየህ?”
ልጅ - አመነታ!
እናት ሁኔታው ገብቷት - “አይዞህ ንገረኝ”
ልጅ፤ እናቱንም አባቱንም አየና፤
“ያየሁትማ አንቺና ዘበኛችን እንደምትተኙት ዓይነት ነው!” አለ፡፡  
*           *          *
የሌላውን ዐይን ጉድፍ ለማሳየት ከመጣጣር የራስን ጉድፍ አስቀድሞ ማየት፣ አስቀድሞ ማውጣት ታላቅ ብልህነት ነው፡፡ ሁሉም ለስህተት በሚጋለጥበት ሁኔታ ውስጥ እያሉ አንዱ ባንዱ ላይ ጣቱን ቢቀስር ውጤቱ ሲቀሳሰሩ መዋል ነው፡፡ በንጉሡ ዘመን የወጣ አንድ ካርቱን ስዕል ባሳየው ምስል፣ ባለስልጣናት ወይም ሚኒስትሮች በትልቅ የኮንፈረንስ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠዋል፡፡ እያንዳንዳቸው፣ አንዱ ባንዱ ላይ በሌባ ጣቱ ይጠቁማል፡፡ ማንም በማንም ላይ ጣቱን ሳይቀስር የሚታይ የለም፡፡ ሁሉም ጥፋተኛ ነው እንደማለት ነው፡፡ ግምገማዎች ምን ያህል ሀቀኛ ናቸው? ስህተትን ለማረም የሚያስችል ምን ያህል ቅን ልቦና አለ? የተገመገሙት ሁሉ እርምጃ ይወሰድባቸዋልን? ያንንስ ማን ይቆጣጠራል? ግምገማ ከእከክልኝ ልከክልህ ነፃ ነውን? ከየአንዳንዱ ግምገማ ምን ያህል ተምረናል? የሚገመገምና የማይገመገም፣ ይነኬና አይነኬ ሰው የለምን? ግምገማ ራሱ መገምገም የለበትምን? ባለፈው ዘመን የኮሚቴ መብዛት ትልቅ ችግር ሆኖ ተሰበሰቡና አሉ፤ ይህንኑ የሚያጠና ኮሚቴ አቋቁመው ተለያዩ! ሀገራችን አባዜዋ ብዙ ነው፡፡ አንድ ተገምጋሚ፤ ስለሀገራችን የስድስት መስመር የህዝብ መዝሙር ፃፍ ተብሎ አሥር ገፅ ያህል የዓላማ ፅሁፍ ተሰጠው፡፡ ቢለው ቢለው ያን ሁሉ ዓላማ በስድስት መስመር ማጠናቀቅ እንደማይመች ታወቀውና፤
“እንኳን ስድስት መስመር፣ መቶም አይበቃሽ እንደው በደፈናው፣ ዕንቆቅልሽ ነሽ    !”ብሎ ደመደመ ይባላል፡፡
በግምገማ ንፍቀ - ክበብ ዋና ጉዳይ የሚሆነው አዎንታዊነት (Positivism) ነው፡፡ በአዎንታዊነት ውስጥ ተስፋ አለ፡፡ በአሉታዊነት ውስጥ ጨለምተኝነት ነው ያለው፡፡ ሰውን ማነፅ አገርን ማልማት ነው፡፡ ሙያን ማክበር ሙያተኛን ማበልፀግ ነው! ይህም አዎንታዊነት ነው፡፡ መንገድ መሥራት ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ሀዲድ መዘርጋት ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ባቡር ማስኬድ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ በባቡር መሄድ ደግሞ ስልጣኔ ይፈልጋል፡፡ የባቡሩን መነሻና መድረሻ ደግሞ መረጃ ጆሮ ነው የሚፈልገው፡፡ አዎንታዊነት ውስጥ ሟርትን እንዳንከት መጠንቀቅ ያንድ የሰለጠነ ህዝብ ብልህነት ነው፡፡ ብዙ የሰራን እያስመሰልን ውስጡ ውስብስብ መክተት አሉታዊነት ነው! አገር ገንዘብ ይኖራት ዘንድ ሁለት ሶስት ያለው ቢላ መጠቀምም አሉታዊነት ነው፡፡ አገር አቀናለሁ ብሎ ደፋ - ቀና የሚለው ዜጋ፣ በንፁህ ስሜት፣ በቀና ልቦና ሲወድቅ ሲነሳ፤ ሌላው ወገን በአጭር - አቋራጭ (Short-cut)፣ አየር ባየር ከባለሥልጣን በመመሳጠር፣ በቀጭን ቢሮክራሲያዊ ትዕዛዝ ወዘተ… ሀብቱን ሲያከማችና ፎቁን ሰማይ ሲያስነካ ማየት ዘግናኝ ነው! ጉዳይ አስፈፃሚ የሆነ ባለዘመድ (መንገድ አዋቂ) ከባለ ጉዳዩ በላይ የሚያገኝበት አገር ውስጥ ለአስተዋይ ሰው ከኮሜዲው ትራጀዲው ማየሉ አይገርምም፡፡ በየቀኑ ነገር የባሰበት ዜጋ፤ “ደረቁ ከበደኝ እያልኩ፣ እርጥብ ትጨምርበታለች” የሚለው ለዚህ ነው! ከዚህ ያውጣን!!

Published in ርዕሰ አንቀፅ

    በአሁኑ ወቅት እጅግ አሳሳቢ እየሆነ ለመጣው የኩላሊት ህመም መፍትሄ ይሆናል በሚል በዘውዲቱ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ በመገንባት ላይ ለሚገኘው የህክምናና የዕጥበት ማዕከል የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ፎረም ተካሄደ፡፡ ትናንት በግሎባል ሆቴል በተካሄደው በዚህ ፕሮግራም ላይ ለማዕከሉ ግንባታ የሚረዳ ገቢ ለማሰባሰብ በማህበረሰቡ ላይ በጎ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና የመንግስት ባለስልጣናት ተገኝተዋል፡፡

Published in ዋናው ጤና

 የአርቲስት ሰብለ ተፈራ( እማማ ጨቤ) የቀብር ስነስርዓት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን የውጭጉዳይ ሚኒስቴር ዶር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ታዋቂ ግለሰቦች  አድናቂዎቿ በተገኙበት የቀብር ስነስርዓቷ ተፈፀመ፡፡
ለወዳጅ ዘመዶቿ እንዲሁም አድናቂውቾ መፅናናትን እንመኛለን፡፡

Published in ዜና
Page 7 of 16