“ቤቲ እና አማረ” የተሰኘው ሳይንሳዊ ልቦለድ ፊልም ከትላንት በስቲያ ምሽት በጎይተ ኢንስቲትዩት የፊልሙ ተዋንያንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመርቋል፡፡ ይህ ሳይንሳዊ ልቦለድ ፊልም ለመጀመሪያ ጊዜ ዓምና በሞስኮ የፊልም ፌስቲቫል ላይ ለእይታ ቀርቦ አድናቆት ማትረፉን የተናገሩት አዘጋጆቹ፤ፊልሙ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሳይንሳዊ ልቦለድ ፊልም እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

      አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያው ውይይት አልተሳተፈም
   የቲያትርና ሥነ ጥበባት ስርዓተ ትምህርትን ወጥ ለማድረግ ባለፈው ነሐሴ ወር መገባደጃ ላይ በወልቂጤ ከተማ ውይይት ያደረጉት የአገሪቱ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች፤ ለዳግም ምክክር በመስከረም መጨረሻ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ በመጀመሪያው ውይይት ላይ የወልቂጤ፣ ጎንደር፣ አዲግራት፣ አክሱም፣ መቀሌና ወሎ ዩኒቨርሲቲዎች የተካፈሉ ሲሆን አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
ለውይይቱ ቢጋበዝም ሳይገኝ ቀርቷል ተብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት በቲያትርና ስነ ጥበባት የትምህርት ዘርፍ ተመርቀው እየወጡ ያሉ ተማሪዎች እኩል ተወዳዳሪ መሆን አልቻሉም ያሉት ዩኒቨርሲቲዎቹ፤ ይህንን ችግርም ለመፍታት በስርአተ ትምህርቱ ላይ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ መካተት እንዲሁም መታጠፍ ያለባቸው የትምህርት አይነቶች
እንዳሉም የትምህርት ባለሙያዎቹ ተወያይተዋል፡፡ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የቲያትርና ስነ ጥበባት መምህር አቶ ምንያህል ተሾመ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በስርአተ ትምህርቱ ላይ
የመሰረታዊ የትምህርት አይነቶች አለመካተት እንዲሁም አንድ ላይ መሆን የሚገባቸው ኮርሶች መበታተን የትምህርት ክፍሉ መሰረታዊ ችግሮች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ስርአተ ትምህርቱን በተለያየ መንገድ እየተገበሩት እንደሚገኙ የጠቆሙት መምህሩ፤ የስርአተ ትምህርቱ ወጥ መሆን ተመርቀው የሚወጡትን ልጆች እኩል ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከማስቻሉም በላይ በጤና ወይም በሌላ ምክንያት ዩኒቨርሲቲ መቀየር የሚፈልጉ ተማሪዎች ትምህርቱን ከየትኛውም ዩኒቨርሲቲ መከታተል እንዲችሉ ዕድል ይሰጣቸዋል
ብለዋል፡፡ የወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ዳንኤል ጉማታው በበኩላቸው፤ የስርአተ ትምህርቱ የጋራ መደረግ ሁሉም ተማሪ ተቀራራቢ እውቀት
እንዲኖረው ለማድረግ አይነተኛ መፍትሄ እንደሆነ ጠቁመው ብቁ ተማሪዎችን ለማፍራት ግን ስርአተ ትምህርቱን ከማሻሻል በተጨማሪ በዘርፉ ያሉ ሌሎች ችግሮችን ሊፈቱ ይገባል ብለዋል፡፡ የወሎ ዩኒቨርሲቲ የቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ስራውን የጀመረው መድረክ ሳይኖረው ነው ያሉት መምህሩ፤ አሁንም ድረስ መድረኩ ገና በግንባታ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የፊልም ኮርሶች በስርአተ ትምህርቱ መካተታቸውን ጠቁመው
ኮርሶቹ እየተሰጡ ያሉት ግን ያለ ካሜራ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ በአማካይ በየዓመቱ ከ30 እስከ 40 ተማሪዎችን ከቲያትር ጥበባት የትምህርት ክፍል የሚያስመርቁ ቢሆንም በአገሪቱ ያሉት ቲያትር ቤቶች አራት ብቻ መሆናቸው ሌላው ችግር ነው ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች፡፡ እነዚህንና መሰል ችግሮቹን ያነሱት ዩኒቨርሲቲዎቹ፤ በያዝነው ወር መጨረሻ በመቀሌ ተገናኝተው ስርአተ ትምህርቱን የጋራ ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ትምህርቱን በመስጠት ላይ የሚገኙት 7 ዩኒቨርሲቲዎች ሲሆኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ጥሪ ቢደርሰውም ባልታወቀ ምክንያት በውይይቱ ላይ እንዳልተገኘ አስተባባሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

አትጠራጠሩ፤ቀልድ የማያውቁ ፓርቲዎች ለዛ ቢስ ናቸው!

    ባለፈው ሳምንት ለእናንተ ብቻ ሹክ ባልኳችሁ መሰረት፤ዘንድሮ የፖለቲካ ቶክ ሾው (በቲቪ) የመጀመር ዕቅዴ ከተሳካ፣ በአገሪቱ አሉ የተባሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች  (ነቄዎቹን ነው ታዲያ!) እየጋበዝኩ ቀልዳቸውን እንደማስኮመኩማችሁ ከወዲሁ ቃል እገባለሁ፡፡ (አትስጉ! እንደ ፖለቲከኞች ቃል አባይ አይደለሁም!)
በእርግጥ ከአቅሜ በላይ የሆነ ችግር ሊገጥመኝ እንደሚችል አልክድም፡፡ (ብዙ “አጼ በጉልበቱዎች” አሉ እኮ!) ለምሳሌ ኢቢሲ ዓይነውሃዬን ብቻ አይቶ፣ “የፖለቲካ ቶክ ሾው አይቻልም; ቢለኝ ምን አደርጋለሁ? (ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ የህዝብ ንብረት ነው አይደል?!) እንዲያም ሆኖ ግን ምርጫ የለም፡፡ “አንድዬ ያክብርልኝ፤እቤቴ በቲቪ መስኮት አልጣችሁ” ብዬ ከቴሌቪዥን ጣቢያው ውልቅ ብቻ ነው፡፡
መቼም ቶክ ሾው ተከለከልኩ ብዬ ብቻዬን የተቃውሞ ሰልፍ አልወጣ!! ልውጣም ብል እኮ ላይሳካ ይችላል፡፡ ወይ የምንፈቀድልህ ከቀበና ጃንሜዳ ድረስ ነው ይሉኝና በሳቅ ያፈርሱኝ  ይሆናል፡፡ (ፓርቲ እመስላለሁ እንዴ?) እኔ እኮ ተቃውሞ ያለኝ ግለሰብ እንጂ ተቃዋሚ ፓርቲ አይደለሁም፡፡ (የህዝብ አጀንዳ ሳይሆን የራሴን አጀንዳ ነው የማራምደው!) እናም ተቃውሞዬን ማሰማት የምፈልገው ------ ቤተመንግስቱ ደጃፍ ላይ ብቻ ነው፡፡ ዋናው የአገሪቱ መሪ፣ ወደ ቤተመንግስቱ ሲገቡ ወይም ግቢያቸው ውስጥ ነፋስ ለመቀበል ሲዘዋወሩ፣ አይተው በደሌን እንዲጠይቁኝ  እንጂ ጭር ባለ ሜዳ የመቃወም ሃራራ የለብኝም፡፡ (ዓላማዬም ትግል ሳይሆን የፖለቲካ ቶክ ሾው በቲቪ የማቅረብ ህገመንግስታዊ መብቴ እንዲከበርልኝ መጠየቅ ብቻ ነው!)
ወይ ደግሞ የመከልከል አባዜ የተጠናወተው የሚመለከተው አካል፤(ኢህአዴግ በ10ኛው ጠቅላላ ጉባኤ “ኪራይ ሰብሳቢዎች;-- ያላቸውን ማለቴ ነው!)፤ “በቂ የጸጥታ ኃይል ስለሌለ ሰልፉን ለሌላ ጊዜ አስተላልፈው” ሊሉኝ ሁሉ ይችላሉ፡፡ ይሄን ጊዜ አንድ ግለሰብ መሆኔን ማስታወስ ደግሞ ከጥቅሙ ይልቅ ጉደቱ ያመዝናል፡፡ (#ካፈርኩ አይመልሰኝ” አለ አበሻ!)  
ወዳጆቼ፤እስካሁን የነገርኳችሁ ሁሉ የቀድሞ ዘመን ስጋት እንጂ የዛሬ ስጋት እንዳይመስላችሁ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ብዙዎቹ ስጋቶች የአዲሱ ዓመት  እንደማይሆኑ ተስፋ አድርጉ፡፡ ለምሳሌ ልማቱ ተጠናቆ ከመጪው እሁድ ጀምሮ ባቡሩ አገልግሎት መስጠት ስለሚጀምር፣ ከዚህ በኋላ መስቀል አደባባይ ለተቃውሞ ሰልፍ የሚከለከልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ (ቋሚ የልማት ጣቢያ ነው ካልተባለ በቀር!)
የብሮድካስቲንግ ባለሥልጣንም ባለፈው ዓመት ከ20 የማያንሱ አዳዲስ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችና ቻናሎች እንደሚከፈቱ መግለጹን አስታውሳለሁ፡፡ (እንደውም ዘግይቷል!)
 እናም----ከብዙ ሁኔታዎች አንጻር ኢቢሲ የፖለቲካ ቶክ ሾው እንደማይከለክለኝ እተማመናለሁ፡፡ ከከለከለኝም ደግሞ ችግር የለም፡፡ (በኋላ የሚቆጨው ራሱ ነው!) ከአዳዲሶቹ ጣቢያዎች አንዱ፣ እጄን ስሞ ይቀበለኛል፡፡ (ከኢቢሲ ጋር አልቆረብኩ!)
አሁን ዋናው ነገር ምን መሰላችሁ?  በየፓርቲያቸው በይፋም ሆነ ውስጥ ለውስጥ  የተነገሩና የተፈጠሩ ቀልዶችን፣ ቆመንለታል ለሚሉት ህዝባቸው ለማጋራትና ዘና ለማድረግ ፈቃደኛ የሆኑ ፓርቲዎችን ወይም ፖለቲከኞችን መመልመል ነው፡፡
ለመሆኑ በራሱ ላይ አብዝቶ የሚቀልድ የአገራችን ፓርቲ የትኛው ይሆን? ኢህአዴግ፣ ሰማያዊ፣ ኢዴፓ፣ (ብዙ መከራ ስላየ ተስፋ ያለው ይመስለኛል!) መድረክ፣ ወይስ ማን ይሆን?
  እርግጠኛ ነኝ ----- ከኢህአዴግም ከተቃዋሚዎችም ብዙ በሳቅ የሚያፈርሱ ቀልዶችን እንሰማለን፡፡ (የቶክ ሾው ሞቶ፡- ቀልድ የማያውቁ ፓርቲዎች ለዛ ቢስ ናቸው! የሚል ነው) አንዴ ይጀመር እንጂ በህዝብ የተፈጠሩ ቀልዶችም ይጎርፋሉ፡፡ ይኸውላችሁ--- አዲስ የቀልድ ባህል በመጀመር ዘና ከማለታችንም ባሻገር የከረረውን ፖለቲካችንንም ለዘብ እናደርገዋለን፡፡ ጨዋታ አዋቂና ቀልደኛ ሰው እኮ ምን ቢበሽቅ ፈጥኖ አይሳደብም፤ አንዳንዴ ተርቦ ወይ ቀልዶ ያልፋል፡፡ ቀልድ የማያውቅ ከሆነ ግን ቶሎ ያመራል፡፡ ለጠብ ይጣደፋል፡፡ በ21ኛው ክ/ዘመን ደግሞ ዱላ ከኋላ ቀሮች ተርታ ያሰልፋል፡፡ እናም በቀልድ እናባብለው ብዬ እኮ ነው (ኋላ ቀርነታችንን!!)
አሁን የአሜሪካ የፖለቲካ ቀልዶች ምን እንደሚመስሉ እንቃኝ ዘንድ አንድ ሁለት ሦስቱን ልጋብዛችሁ፡፡ ለአገር በቀሉ የፖለቲካ ሾው መዳረሻ ይሆኑናል፡፡ ወደ ቀልዶቹ፡-
*          *        *
የዋይት ሃውስ ጨረታ
የዋይት ሃውስን አጥር ለማደስ 3 ኮንትራክተሮች ይጫረታሉ፡፡ አንደኛው ከቺካጎ፣ ሌላኛው ከቴኒዝ፣ ሦስተኛው ከሚኔሶታ የመጡ ናቸው፡፡ ሦስቱም ከአንድ የዋይት ሃውስ ሹም ጋር ተያይዘው የአጥሩን ሁኔታ ለማየት ይሄዳሉ፡፡
የሚኔሶታው ኮንትራክተር ወዲያው ሜትሩን አወጣና አጥሩን ለካው፡፡ ከዚያም በእርሳስ ሂሳቡን ጫር ጫር አደረገና፤ “ሥራው 900 ዶላር ገደማ ይፈጃል፤ 400 ዶላር ለቁሳቁስ፣ 400 ዶላር ለሰራተኞቼ፣ 100 ዶላር ትርፍ ለእኔ” ሲል አስረዳ፡፡
የቴኒዙም ኮንትራክተር ለካክቶ ሲያበቃ፣ የሰራውን ሂሳብ ተናገረ፤ “ይሄን ሥራ በ700 ዶላር እሰራዋለሁ፡፡ 300 ዶላር ለቁሳቁስ፣ 300 ዶላር ለሰራተኞቼ፣ 100 ዶላር ትርፍ ለእኔ”
 አሁን ተራው የቺካጎው ኮንትራክተር ነው፡፡ እሱ ግን የለካውም ሆነ ያሰላው ሂሳብ የለም፡፡ ወደ ዋይት ሀውሱ ኃላፊ ጠጋ አለና በሹክሹክታ፤ “2,700 ዶላር!” አለው፡፡ ሹሙም በመጠራጠር እያየው፤ “እንደሌሎቹ ስትለካ እንኳን አላየሁህም፤ እንዴት ነው ይሄን የሚያህል ቁጥር ላይ የደረስከው?” ሲል ጠየቀው፡፡ የቺካጎው ኮንትራክተር አሁንም በሹክሹክታ፤ “1ሺ ዶላር ለእኔ፣ 1ሺ ዶላር ለአንተ፣ በቀረው ገንዘብ የቴኒዙን ኮንትራክተር ቀጥረን አጥሩ ይታደሳል፡፡” በማለት አስረዳው፡፡ የዋይት ሀውሱ ሹሙም ምንም ሳያቅማማ፤ “ጨርሰናል!” ሲል መስማማቱን ገለፀለት፡፡
(ወዳጆቼ፤ የበጀት ማነቃቂያ ዕቅዱም ተግባራዊ የሆነው በዚህ መንገድ ነው፡፡)
*        *      *
ባለቀ ሰዓት ማሊያ መቀየር?!
በህይወት ዘመኑ ሁሉ  የሪፐብሊካን ፓርቲን በመደገፍ የሚታወቅ ጽኑ ሰው ታሞ አልጋ ይዟል፡፡ ህመሙ እየተባባሰ ሊሞት ማጣጣር ጀመረ፡፡ ከመሞቱ በፊት በነበረች ሽርፍራፊ  ደቂቃ እንደምንም ትንፋሹን አሰባሰበና፤ #ከአሁን ሰዓት ጀምሮ ሪፐብሊካንን ትቼ የዲሞክራት  ደጋፊ ሆኛለሁ; ሲል አስታወቀ - በኑዛዜ ቃና፡፡ (ዕድሜ ልኩን ኢህአዴግ ወይም ሞት ሲል የነበረ አባል፣ባለቀ ሰዓት ላይ ተቃዋሚ ሆኛለሁ ሲል አስቡት!)
አጠገቡ የነበረ ጓደኛው በእጅጉ እንደተናደደበት ገጽታው ይመሰክራል፡፡ ሥሩ ተገታትሮ ከደቂቃ በፊት ማሊያ ለውጫለሁ ያለውን የቀድሞ የሪፐብሊካን ደጋፊ ባልንጀራውን አፋጠጠው፤ “እኔ ፈጽሞ የምትለው ነገር አልገባኝም፤ ህይወትህን ሙሉ ፍንክች የማትል ብርቱ የሪፐብሊካን ደጋፊ ነበርክ፤ አሁን ምን ተገኝቶ ነው ድንገት ተነስተህ ዲሞክራት ለመሆን የፈለግኸው?!”
በሞት ጣር ላይ የነበረው ሰውዬ ለመልስ የሚሆን ትንፋሽ አላጣም፤ “ለምን መሰለህ … የእኛ ፓርቲ ሰው ከሚሞት የእነሱ ቢሞት ስለምመርጥ ነው!” አለው፡፡
 (እቺ በሃበሽኛ ስትተረጎም … “ጠላትን ደስ አይበለው!”)
*          *        *
“ገንዘቤን ቁጭ አድርጋት”
አንድ ሌባ አንድ ትልቅ ሰውን አሳቻ ቦታ ላይ ሽጉጥ  ይደግንበትና፤ “ያለህን ገንዘብ በሙሉ ቁጭ አድርጋት!” ሲል ያስፈራራዋል፡፡ በድንገተኛው የዘረፋ ጥቃት የተደናገጠው ሰውዬም፤ “በእኔ ላይ ይሄን ልትፈጽም አትችልም … እኔ የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ነኝ” ይለዋል፡፡ ሌባውም መለስ ብሎ፤ “እንዲያ ከሆነማ … በል ገንዘቤን ቁጭ አድርጋት” አለው፡፡
(የኮንግረስ አባል ከሆንክማ የራሴው ገንዘብ ነው እንደማለት …!)
*          *        *
ተጋባዡ ፖለቲከኛ
የጎልፍ ክለብ እራት ላይ አንድ ፖለቲከኛ ንግግር እንዲያደርግ ይጋበዛል፡፡ ፖለቲከኛው መድረክ ላይ ወጥቶ ንግግሩን ሲጀምር፣ ጥቂት ታዳሚዎች አጋጣሚዋን በመጠቀም ሹልክ እያሉ ወደ ባሩ አመሩ … አልኮል ለመጎንጨት፡፡
ከአንድ ሰዓት በኋላ ሌላ አንድ ታዳሚ ወደ ባሩ መጥቶ ይቀላቀላቸዋል፡፡ ወዲያው ቀድመው የወጡት ታዳሚዎች በጥያቄ ያጣድፉታል፡-
“አሁንም ሰውየው ንግግሩን አልጨረሰም?”
“አዎ፤ አልጨረሰም”
“ለመሆኑ ምንድነው የሚዘባርቀው?”
“ምን አውቃለሁ፤ ገና ራሱን አስተዋውቆ አልጨረሰም እኮ”
(ኮንሰርት የሚያቀርብ መሰለው እንዴ?)

    ቲ ጂ ኤም ዲ በሚል ስያሜ የተመሰረተው የ “ሪል ውሃ” አምራች ኩባንያ፤ ያለበት 44 ሚ.ብር የግብር ዕዳ በምርመራ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ገለፀ፡፡ ኩባንያው ከ1999 ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ ታደለ ዳለቻ በተባለ ግለሰብ ስራ አስኪያጅነት ሲመራ የቆየ ሲሆን ከ2002 እስከ 2003 ዓ.ም አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ይመሩት እንደነበር የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የትምህርትና ኮሙዩኒኬሽን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ በላይ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ በመቀጠል ድርጅቱ አቶ መሃመድ ለተባሉ ግለሰብ የተሸጠ ሲሆን የኩባንያው እንቅስቃሴ ሲጠና ቆይቶ፣ 44 ሚ ብር የግብር እዳ እንዳለበት መታወቁን ይህንንም እዳ ግለሰቡ እንዲከፍሉ የሚጠይቅ ደብዳቤ በ2005 ዓ.ም ከባለስልጣኑ መ/ቤት እንደተፃፈላቸው ምክትል ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡ ግለሰቡ “ኩባንያውን ስገዛው ይሄ ሁሉ እዳ እንዳለበት አላውቅም’ የሚል ምክንያት አቅርበዋል” ያሉት አቶ ፋሲካ፤ አንድ ኩባንያ በሽያጭ ሲዘዋወር ክሊራንስ ሳይወጣበት ስለማይዘዋወር የሰውየው ምክንያት ተቀባይነት ያለው አልነበረም ብለዋል - አቶ ፋሲካ፡፡ በኋላ ግን ኩባንያውን የገዙት ግለሰብ ወደ ባለስልጣኑ በመቅረብ፤ “ያለበትን እዳ ቅድሚያ 25 በመቶ ከፍዬ ቀሪውን ቀስ በቀስ እከፍላለሁ” እያሉ ሲያዘናጉ ቢቆዩም፣ ኩባንያው ግን እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ ማምረት አለማቆሙን ባለስልጣኑ ደርሶበታል ብለዋል ም/ዳይሬክተሩ፡፡ ኩባንያው ክስ ያልተመሰረተበት ጉዳዩ ውስብስብ በመሆኑ ነው ያሉት አቶ ፋሲካ፤ በአሁኑ ወቅት የግብሩ ዕዳ በከፍተኛ ምርመራ ላይ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡የሪል ውሃ ማምረቻ ድርጅት ከ190 በላይ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን ያለፉትን ሁለት ወራት ደመወዝ ያልተከፈላቸው መሆኑንና የሪል ውሃ ማምረቻው የሚገኝበት የቡራዩ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ፅ/ቤትም ለዓመታት ከሰራተኞቹ ደመወዝ የሚቆረጠው የስራ ግብር አልደረሰኝም ማለቱን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግቧል፡፡

Published in ዜና

ሸራተን ከ5 ኮከብ በላይ ይገባኛል አለ

  በቅርቡ ይፋ በተደረገው የአዲስ አበባ ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምደባ ሸራተን አዲስ፣ ኢሊሊ ዓለም አቀፍ ሆቴልና ካፒታል ሆቴልና ስፓ፤ 5 ኮከብ የተሰጣቸው ሲሆን ሸራተን አዲስን ጨምሮ 20 ሆቴሎች በኮከብ አሰጣጡ ላይ ቅሬታ አቅርበው ምላሽ እየተጣበበቁ ነው፡፡
ባለ 5 ኮከብ ደረጃ ይሰጣቸዋል ተብሎ የተጠበቁት ሂልተን አዲስና ራዲሰን ብሉ ሆቴል ባለ 4 ኮከብ ሆነዋል፡፡
5 ኮከብ የተቀዳጁት ኢሊሊ እና ካፒታል ሆቴል በተሰጣቸው ደረጃ ደስተኛ መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን ሸራተን አዲስ ግን ከ5 ኮከብ በላይ ይገባኛል የሚል ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ካፒታል ሆቴል 12 በሚደርሱ መስፈርቶች መመዘኑን የጠቆሙት የሆቴሉ ሴልስና ማርኬቲንግ ማናጀር አቶ ሚካኤል ተካ፤ ከመቶ 85.68 በማግኘትም ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ለመሆን መብቃቱን ገልፀዋል፡፡ ሆቴላችን የ5 ኮከብ ባለቤት መሆኑ በአለማቀፍ ደረጃ ያለው ተቀባይነት እንዲጨምርና ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲዘልቅ ይረዳዋል ያሉት ማናጀሩ፤ ሆቴሉ ወደፊት ሊጀምር ያቀዳቸው ሌሎች አገልግሎቶች ሲሟሉ፣ ወደ “ግራንድ ሌግዠሪ” ደረጃ ማደግ እንደሚችል መዛኞቹ መጠቆማቸውን ተናግረዋል፡፡
ሆቴላቸው 5 ኮከብ ማግኘቱ እንዳስደሰታቸው የተናገሩት የኢሊሊ ዓለም አቀፍ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር አብዱሰላም ባሬንቶ በበኩላቸው፤ የተሰጠው ደረጃ ሆቴሉ በእንግዶች ዘንድ ይበልጥ ተመራጭ እንዲሆን እንደሚረዳና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለማቅረብ እንደሚያተጋቸው ገልፀዋል፡፡ የሸራተን አዲስ ሆቴል አንድ የስራ ሃላፊ በስልክ በሰጡን አስተያየት፤ ሆቴሉ በኮከብ ደረጃ አሰጣጡ ላይ ያሉትን ቅሬታዎች ለሚመለከታቸው አካላት አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው ጉዳዩ፣ እልባት ሲያገኝ ውጤቱ ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የባህልና ቱሪዝም የህዝብ አለማቀፍ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ገዛኸኝ አባተ በበኩላቸው፤ በኮከብ ደረጃ ምደባው ላይ 20 ሆቴሎች ቅሬታ ማቅረባቸውን ጠቁመው፤ ቅሬታቸው ምላሽ ማግኘቱንና በሚቀጥለው ሳምንት ይፋ እንደሚደረግ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ ሆቴሎች 95 ያህሉ ለምዘና ተመርጠው የነበረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ፣ 38ቱ ከ 1 ኮከብ እስከ 5 ኮከብ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት፤ ከ5 ኮከብ በላይ “ግራንድ ሌግዠሪ” ያገኘ ሆቴል የለም፡፡ የኮከብ ደረጃ ከተሰጣቸው መካከልም 3ቱ ባለ 5 ኮከብ 11ዱ ባለ 4፣ 13ቱ ባለ 3፣ 10ሩ ባለ 2 ኮከብ ደረጃ ሲያገኙ አንድ ሆቴል ባለ 1 ኮከብ ደረጃ ተሰጥቶታል፡፡ ለሁሉም ሆቴሎች ተመሳሳይ 12 የመመዘኛ ነጥቦች የተዘጋጁ ሲሆን ባገኙት የመቶኛ ውጤት መሠረት ደረጃው ተሰጥቷቸዋል ተብሏል፡፡ የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምዘናው ከተጀመረ 5 ወራት ገደማ ያስቆጠረ ሲሆን በአሁን ወቅት በክልል ከተሞች ለሚገኙ ሆቴሎች ተመሳሳይ የምዘና ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የሆቴል ምዘናው የሚከናወነው በተባበሩት መንግስታት የአለም ቱሪዝም ድርጅት ሲሆን ለስራው የሚውለው በጀት የተገኘው ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) እንደሆነም ታውቋል፡፡

Published in ዜና

ባቡሩ ነገ ማለዳ ስራውን ይጀምራል
   በነገው ዕለት ስራ ለሚጀምረው የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት የሃይል አቅርቦት የማሟላት ሃላፊነቱን የወሰደው “ቻይና ኤሌክትሪክ ፓዎር ኢኩፒመንት ኤንድ ቴክኖሎጂ” የተባለው ኩባንያ የሃይል አቅርቦቱን ያልተቆራረጠና አስተማማኝ አደርጋለሁ ሲል ቃል መግባቱን ዥንዋ ዘገበ፡፡
የኩባንያው ምክትል ጄኔራል ማናጀር ቼን ዊ፤ ኩባንያው በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ አምስት ቦታዎች የገነባቸውን የቀላል ባቡሩ የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ንኡስ ጣቢያዎች ባስጎበኙበት ወቅት እንዳሉት፣ ምንም እንኳን ኩባንያው የጊዜ መጣበብና በአገር ውስጥ ገበያ የቁሳቁስ አቅርቦት እጥረት ቢያጋጥመውም ንኡስ ጣቢያዎቹን በወቅቱ ገንብቶ የጨረሰ ሲሆን፣ የባቡር ኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦቱን አስተማማኝ ለማድረግ በቻለው አቅም ሁሉ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ቻይና ኤሌክትሪክ ፓዎር ኢኩፒመንት ኤንድ ቴክኖሎጂ ኩባንያ በአዲስ አበባ ያስገነባቸው የቀላል ባቡር የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ንኡስ ጣቢያዎች አምስት ሲሆኑ በቃሊቲ፣ አያት፣ ሚኒልክ፣ መስቀል አደባባይ፣ እግዚያብሄርአብ ቤተ ክርስቲያንና በጦር ሃይሎች አካባቢ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል ተሳፋሪዎች በጉዞ ወቅት እስከ 10 ኪሎ የሚመዝን እቃ ብቻ ይዘው ለመጓዝ እንደሚፈቀድላቸው የተገለፀ ሲሆን አንዳንድ በባቡሩ ላይ እንዳይጫኑ የሚከለከሉ እቃዎች እንደሚኖሩ ታውቋል፡፡
የባቡር ትራንስፖርቱ ክፍያ እስከ 4 ኪሎ ሜትር ሁለት ብር፣ እስከ 8.8 ኪሎ ሜትር 4 ብር እንዲሁም ከመነሻ እስከ መጨረሻ ፌርማታ 6 ብር ነው ተብሏል፡፡ ትኬት ሳይዙ መጓዝ ከፍተኛ ቅጣት እንዳለውም ተጠቁሟል፡፡

Published in ዜና

    በሽብር ተከሰው ጉዳያቸው በፍ/ቤት እየታየ የሚገኘው የዞን 9 ጦማሪያንና በስደት ላይ የሚገኙ  የጦማሪያኑ ቡድን አባላት፤ የዓለም አቀፉ ጋዜጠኞች ጥበቃ ኮሚቴ (CPJ) የ2015 አለማቀፍ የፕሬስ ነፃነት ሽልማት አሸናፊ ሆኑ፡፡
ሲፒጄ፤ የማሌዥያ፣ ፓራጓይና ሶሪያ ጋዜጠኞችም የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ እኒህ ጋዜጠኞች በሥራቸው ሂደት የሞት ማስፈራሪያና ዛቻ እንደረሰባቸው የጠቆመው ኮሚቴው፤ በአካላዊ ጥቃት፣ በህጋዊ እርምጃ፣ በእስር ወይም በስደት ክፉኛ መሰቃየታቸውንም በመግለጫው ጠቁሟል፡፡  
“የዞን 9 ጦማሪያን በሀገሪቱ ያሉ ነፃ ፕሬሶችና መገናኛ ብዙሃን በመንግስት ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ ተፅዕኖዎች እንዲሁም በገንዘብ አቅም መዳከም የማህበረሰቡን ችግር አጉልተው ማውጣት በተሳናቸው ሰዓት፣ የማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል” ሲል ሲፒጄ በሪፖርቱ አወድሷቸዋል፡፡
የዞን 9 ጦማሪያን ከሦስት ዓመት በፊት በ9 ወጣት ፀሐፊያን የተመሰረተ የጡመራ መድረክ መሆኑን የገለፀው ሲፒጄ፤ 4ቱ ጦማሪያን በእስር ላይ እንደሚገኙና ሁለቱ በቅርቡ ከእስር መለቀቃቸውን እንዲሁም 3ቱ የጦማሪያኑ አባላት በስደት ከሀገራቸው ውጪ እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡
አራቱ በእስር ላይ የሚገኙት የዞን 9 አባላት አቤል ዋበላ፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ አጥናፍ ብርሃኔና  ናትናኤል ፈለቀ ሲሆኑ ማህሌት ፋንታሁንና ዘላለም ክብረት ከወራት በፊት ከእስር መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡ በሌለችበት በሽብር የተከሰሰችውን ሶሊያና ሽመልስን ጨምሮ እንዳልክ ጫላና ጆማኔክስ ካሳዬ በስደት ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
መንግስት በ2007 ዓ.ም 6 ያህል ጋዜጠኞችን ከእስር መልቀቁን የጠቀሰው ሲፒጄ፤ ዛሬም ግን በርካታ ጋዜጠኞች ከስራቸው ጋር በተያያዘ በእስር ላይ እንደሚገኙ ጠቁሞ፣ ኢትዮጵያ ከዓለም ጋዜጠኛ አሳሪ 10 አገራት መካከል በ4ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አመልክቷል፡፡
የሲፒጄን ሪፖርቶች እንደማይቀበል በተደጋጋሚ የገለፀው የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ በፃፈው ፅሁፍ ምክንያት አሊያም ከሙያው ጋር በተያያዘ የታሰረ አንድም ጋዜጠኛ አለመኖሩን መግለፁ ይታወሳል፡፡ 

Published in ዜና

  መመሪያ ያልተሰጠበት የደብሩ የሚሊዮን ብሮች የበጀት ጥያቄ እንዲዘገይ አዟል
 •  የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅና ምክትላቸውን እያወዛገበ ነው


    የአራዳው መናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር፣ እያሠራው የሚገኘው የሁለገብ ሕንፃ ግንባታ፣ ተደርጎለታል ባለው የዲዛይን ማሻሻያ ሳቢያ በልዩነት የሚያስፈልገው ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪና ከባለሀብቶች ጋር በመተባበር ለማስገንባት ያቀዳቸው የሌሎች ሁለት ሕንፃዎች ግንባታና በጀት እንዲጸድቁለት ያቀረባቸው ጥያቄዎች፣ ለፓትርያርኩ ቀርበው መመሪያ ያልተሰጠባቸው በመሆናቸው “በአሉበት ሁኔታ እንዲቆዩ” የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አዘዘ፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባኤ፣ በደብሩ ግንባታዎችና የበጀት ይጸደቅልኝ ጥያቄዎቹ ላይ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ለአፈጻጸም ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሳይላኩለት የቆዩበት ምክንያት እንዲብራራለትም ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከትላንት በስቲያ ለሀገረ ስብከቱ በጻፈው ደብዳቤ ጠይቋል፡፡
የደብሩ ሰበካ ጉባኤ፣ የልማት ዕቅዶቹ በሀገረ ስብከቱ በኩል እንዲጸድቁለት ባለፈው ዓመት ሚያዝያ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. መጠየቁን ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ባስታወሰበት ደብዳቤው፤ ዲዛይኑ ለተሻሻለው ሁለገብ ሕንፃ ማሠሪያ እንዲሁም በስተምሥራቅ የሚገኙት ሱቆች ፈርሰው በምትካቸው ባለሁለት ፎቅ ሕንፃ መሥራት ይቻል ዘንድ የብር 6 ሚሊዮን በጀት በደብሩ እንደተመደበ፣ በጥያቄው ላይ ለመወሰን ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተሰበሰበው የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ቃለ ጉባኤ መረዳቱን ጠቅሷል፡፡
በዕለቱ፣ በምክትል ሥራ አስኪያጁ መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር በተመራው የአስተዳደር ጉባኤው ስብሰባ፣ በደብሩ የቀረበው የበጀት ይጸድቅልኝ ጥያቄ፣ “ከባድና ከሀገረ ስብከቱ አቅም በላይ” ሊሆን እንደቻለ ተጠቁሟል፡፡ ወጪው ከ61 ሚሊዮን ወደ 152 ሚሊዮን ያደገው የዲዛይን ክለሳ ጥናት፤ በገለልተኛ ባለሞያዎች ተገምግሞ፣ ውጤቱ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እንዲላክና በዚያው በኩል እንዲጸድቅ፤ የሁለት ተጨማሪ ሕንፃዎች ግንባታ ውሎችም ለአስተዳደር ጉባኤው ቀርበው እንዲታዩና የውሳኔው ቃለ ጉባኤም በምክትል ሥራ አስኪያጁ ሸኚ ደብዳቤ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እንዲላክ ከስምምነት ተደርሶበት እንደነበር ጠቅላይ ጽ/ቤቱ አውስቷል፡፡
ይኹንና ውሳኔዎቹም ኾኑ የውሳኔዎቹ ቃለ ጉባኤ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ እንዳልተላከ ጠቅሶ፣ ለሦስት ወራት ሳይላክ የዘገየበት ምክንያት ከተጨባጭ ማስረጃ ጋር እንዲብራራለት የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት አዟል፤ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ደብርን ጨምሮ የ48 አድባራትን የመሬትና የገቢ ማስገኛ ተቋማት አጠቃቀምና የኪራይ አፈጻጸም ያጣራው አጥኚ ኮሚቴም፣ ጉዳዩን ተከታትሎ እንዲያስፈጽም በደብዳቤው ግልባጭ መታዘዙን ጠቅላይ ጽ/ቤቱ አስታውቋል፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ የቃለ ዐዋዲ ድንጋጌ አንቀጽ 12 ንኡስ አንቀጽ 8፣ ቋሚ ንብረትንና ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቁ ጉዳዮች በሥራ ላይ ሊውሉ የሚችሉት ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ ሲያገኙ ብቻ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ አልፎ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት እንደመኾኑ፣ በአጥቢያ ሰበካ ጉባኤያቱ ለሀገረ ስብከቱ የሚቀርቡ ጥያቄዎች በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ አማካይነት ለፓትርያርኩ እየቀረቡ አመራር ሲሰጥባቸው፣ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በመመሪያው መሠረት ማስፈጸም ይኖርበታል፡፡
በዚሁ አግባብ፣ በሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሰብሳቢነት የተላለፈው ውሳኔ፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ አማካይነት ለፓትርያርኩ ቀርቦ መመሪያ እስከሚሰጥበት ድረስ የደብሩ የግንባታና የበጀት ይፅደቁልኝ ጥያቄዎች በአሉበት ሁኔታ እንዲቆዩ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሀገረ ስብከቱን አዟል፡፡
ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ይህን ይበል እንጂ፤ ደብሩ በጥያቄው መሠረት ግንባታውን እንዲቀጥል የሚገልጽ ነው የተባለ ደብዳቤ፤ በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ለደብሩ አስተዳደር አስቀድሞ መጻፉን የሀገረ ስብከቱ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ የደብሩም ዋና ጸሐፊ እንደኾኑ የጠቀሱት ምንጮቹ፣ በአንድ በኩል ጥያቄ አቅራቢ በሌላ በኩል ውሳኔ ሰጪና አፅዳቂ በመኾን የፈጸሙት ተግባር የተጠያቂነት መርሆዎችንና የአስተዳደር ጉባኤውን ውሳኔ ከመፃረሩም በላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከምክትል ሥራ አስኪያጁ ጋር እየተካረሩ ለመጡት አለመግባባቶችም አንድ መንሥኤ መኾኑን አስረድተዋል፡፡
የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር፣ በሕንፃዎች፣ በሱቆችና በባዶ መሬት አጠቃቀምና የኪራይ አፈጻጸም፣ የአሠራር ችግር እንዳለባቸው ከተዘረዘሩት 15 ገዳማትና አድባራት አንዱ እንደኾነ፣ በፓትርያርኩ ትእዛዝ የተሠየመው ኮሚቴ ባካሔደውና በጠቅላይ ጽ/ቤቱ አማካይነት ለቋሚ ሲኖዶስ በቀረበው ጥናታዊ ሪፖርት ተጠቅሷል፡፡
እንደ ሪፖርቱ፣ የደብሩ ሁለገብ ሕንፃ፣ የዲዛይን ማሻሻያ በሚል ወጪው ከ61 ወደ 171 ሚሊዮን ብር ያደገ ሲኾን አዲስ ተቆጣጣሪ መሐንዲስም በደብሩ ዋና ጸሐፊ ጠቋሚነት ያለጨረታ ተቀጥሯል፡፡ ሀገረ ስብከቱና ሊቀ ጳጳሱ ለአዲሱ የዲዛይን ጥናትና ከብር 110 ሚሊዮን በላይ ላሳየው የዋጋ ጭማሪ ዕውቅናና ፈቃድ ባልሰጡበት ሁኔታ ግንባታው መቀጠሉም አግባብነት እንደሌለው በሪፖርቱ ተገልጧል፡፡
ቋሚ ሲኖዶስ፣ ጥናታዊ ሪፖርቱን ሙሉ በሙሉ በመቀበል ውሳኔዎችን ማሳለፉን ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በደብዳቤው ገልጾ÷ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብርን ጨምሮ በተዘረዘሩት 15 ገዳማትና አድባራት ተፈጸመ በተባለው ኢ-ፍትሐዊ አሠራር፣ በተናጠልም ኾነ በጣምራ ተጠያቂ የሚኾኑ የአመራር አካላት ከተሰበሰቡት ማስረጃዎች ጋር በንጽጽር እንዲቀርቡለት፤ የሕንፃዎቹ፣ የሱቆቹና የባዶ መሬቶቹ የኪራይ አፈጻጸምና የመካናተ መቃብሩ አጠቃቀም የሚመሩበት መተዳደርያ ደንብ፣ የጨረታ ደንብ፣ የአከራይና ተከራይ የውል ሰነድ በማእከላዊነት በባለሞያዎች ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ፤ ጥናቱ ባልሸፈናቸው ሌሎች ገዳማትና አድባራት ላይም እንዲቀጥል መታዘዙንም አስታውቋል፡፡

Published in ዜና

    ከ200 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት 12ኛው አለማቀፍ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ከትላንት በስቲያ ጀምሮ እየተካሄደ ነው፡፡ በኤግዚቢሽኑ ላይ ከ120 በላይ የሃገር ውስጥ ኩባንያዎች ተሣታፊዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ከ17 የተለያዩ የአለም ሀገራት የተውጣጡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሠማሩ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ከውጪ ከተገኙት መካከል የጣሊያን፣ የቱርክ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስና የቻይና ኩባንያዎች ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡ ለ12ኛ ጊዜ የሚካሄደው ኤግዚቢሽኑ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሠማሩ አምራቾችን፣ አሠሪዎችን፣ የሪልእስቴት ኩባንያዎችን፣ የግንባታ ማሽነሪ አስመጪዎችን፣ የፋይናንስ ተቋማትንና በዘርፉ ተዋናይ የሆኑ አካላትን በአንድ ቦታ የሚያገናኝ ይሆናል ተብሏል፡፡ ኤግዚቢሽኑ የፊታችን ሠኞ ይጠናቀቃል፡፡

Published in ዜና

     ከተለያዩ የአለም ክፍሎች የተውጣጡ በአቬሽን ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን የሚያሳትፍ “አይማ አፍሪካ” የተሰኘ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ፣ ከፊታችን ማክሰኞ ጀምሮ ለ3 ቀናት ይካሄዳል፡፡ ጉባኤው በተለይም በአገሪቷ ያለውን የኤርፖርት የመሰረተ ልማት እድገት ለማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ጠቁሟል፡፡ የድርጅቱ የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ወንድም ተክሉ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ ከሌሎች የኤርፖርት አገልግሎት ሰጪና መሰረተ ልማት አቅራቢ ድርጅቶች ጋር የንግድና የወዳጅነት ትስስር ለመፍጠር ጉባኤው መልካም አጋጣሚ ይሆንለታል፡፡ በጉባኤው ላይም ድርጅታቸው፣ “የአሁኑ እና የወደፊቱ የኤርፖርት መሰረተ ልማት” በሚል ርዕሰ ገለፃ እንደሚያቀርብ ኃላፊው አክለው ገልፀዋል፡፡
የአይማ (AIMA – Airport infrastructure maintenance repair & over hall (Mro) aviation) ጉባኤ በአለም ለ20ኛ ጊዜ፣ በአፍሪካ ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ከ200 በላይ ተሳታፊዎች ይገኙበታል ተብሏል፡፡  

Published in ዜና
Page 6 of 16