Saturday, 26 September 2015 08:01

የኪነት ጥግ

(ስለፊልም ስክሪፕት)
- ከጥሩ የፊልም ፅሁፍ መጥፎ
ፊልም መስራት እችላለሁ፤
ከቀሽም የፊልም ፅሁፍ ግን አሪፍ
ፊልም መስራት አልችልም፡፡
ጆርጅ ክሉኒ
አንድን ፊልም እሰራለሁ ወይም
አልሰራም ብዬ እንድወስን
የሚያደርገኝ የፊልም ፅሁፉ
አይደለም፡፡
ዣን ሉዊስ ትሪንቲኞንት
- አሁን አሁን የታሸገበትን ፖስታ
በማየት ብቻ የፊልም ፅሁፉ
አሪፍ መሆንና አለመሆኑን ማወቅ
እችላለሁ፡፡
ፒተር ኦ‘ቱሌ
- የፊልም ፅሁፍ ከማንበቤ
በፊት ምንም አይነት ውል
አልፈራረምም፡፡ ጥሩ ከሆነ
ደግሞ የ20 ዶላርም ይሁን የ1 ሚ.
ዶላር እሰራዋለሁ፡፡
ማርቲን ፍሪማን
- ልክ እንደ ፊልም ፅሁፍ ሁሉ፣
ለራስህ የቢዝነስ ዕቅድ ሊኖርህ
ይገባል፡፡
ፕሬይቲ ዚንታ
- ፀሐፊ ነኝ አልወጣኝም፤ በፊልም
ውስጥ ግን ለረዥም ጊዜ
ቆይቻለሁ፤ እናም የፊልም ፅሁፍ
መፃፍ እችላለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡
ቤኒቺዮ ዴልቶሮ
- ፊልም ለመስራት ከመወሰኔ
በፊት እናቴ ሁል ጊዜ የፊልም
ፅሁፉን ታነበዋለች፡፡
ቼሎ ግሬስ ሞርቴዝ
- መፅሀፍ በእጄ መያዝ እወዳለሁ፡
፡ አንድ ሰው የፊልም ፅሁፍ
ሲልክልኝ ታትሞ እንዲሰጠኝ
እጠይቃለሁ፡፡
ማርዮ ካንቶኔ
- ሊፃፍ ወይም ሊታሰብ የሚችል
ከሆነ፤ ፊልምም መሆን ይችላል፡፡
ስታንሌይ ኩብሪክ
- ከተሰሩት ማናቸውም ፊልሞች
ላይ እሰርቃለሁ፡፡
ኳንቲን ታራንቲኖ
- ዘይቤ (style) ማለት፤ ሁሉንም
ዘይቤዎች መርሳት ነው፡፡
ጄሌስ ሬናርድ
- ሁልጊዜም ፊልም ሰሪ የመሆን
ፍላጎት ነበረኝ፤ የመጀመሪያ
ፊልሜን እስክሰራ ድረስ ግን
ምስጢር አድርጌ አቆይቸዋለሁ፡
አንግሊ


Published in ጥበብ
Saturday, 19 September 2015 09:43

አስማት ውበት

     አስማት የሆነ ውበት ያላት ሲባል እንደ ዘበት ነበር የምሰማው… ለካሰ ያንዳንዱን ሴት ውበት ለመግለፅ ቃላት ሲጠፉ፣የዘመኑ ልጆች ለዘመኑ ውብ ልጃገረዶች የሰጡት የዘመኑ ምርጥ ቃል ነው፡፡….ሳራ አስማት ውበት የተቸራት ልጅ ናት…. ይህችን ውብ አበባ…የመኖር አዙሪት በኔ ምህዋር አስገብቷት……የፍቅር አማልክት ከተተንከረከከዉና ከጋመው እሳት ውስጥ…..ከሚፋጅና ከሚለበልብ ምድጃ ውስጥ…..ከፍም እሳት ውስጥ…“.እንቁ ” አስቀምጠው…  “በምላስህ አውጣና ውሰዳት” ብለው ፈርደውብኝ፣ በምላሴ ያወጣዃትና…..ትኩስ እንባዬን አንገቷ ስር አፍስሼ እንደምወዳት የነገርኳት ልጅ ናት፡፡
….አስማት የሆነ ውበት ላላት ልጅ የሚከፈል ዋጋ ብዙ ነዉ…..እንቆቅልሹም…ማለቂያ የለውም…..
መጀመሪያ አብረን ያመሸን እለት፣ ኮተቤ ብረታብረት ካለዉ የአያቶቿ ቤት ልወስዳት ሄጄ ከመኪና ወርጄ፣ ለሰላምታ እጆቼን ስዘረጋ፣ አይኖችዋን ጨፍና እቅፌ ዉስጥ ገባችና፣ ፊቷን አንገቴ ስር ቀብራ ለሰኮንዶች  ጸ……….ጥ ስትል…..ስስ ጸጉርዋ ፊቴን እየለሰለሰው፣ ሙቀቷን እንዳልሞቀዉ ሲከለክለኝ….በዚያች ጸ…..ጥ ባለችበት ቅጽበት…አንደበት የነበረውና ሞገድ እየረጨ ልቤን ያናገረዉ…..ጡቷ…ነበር!!…..እርግጠኛ ነኝ ጡት መያዣ አላደረገችም፡፡
ረዥም ቤዥ ከለር የሆነ ቀሚስ፣ ቡላ ጫማና ቡላ ቦርሳ…በቃ…እንደ ዋዛ ጸጉርዋን ወደ ኋላ ለቃዋለች….ሽቶ አልተቀባችም…ሊፕስቲክ----ኩል-----ጌጣጌጥ አልነካትም….ጸጉርዋን እንኳን በሻምፖ አልታጠበችውም…በወተት ነው መሰለኝ የሚያጥቧት አያቷ ----- “.ወተት ወተት የምትል ልጅ፣ ቀስተ ደመና የሚረጩ አይኖች ያሏት”….
ወተት ለሆነች ልጅ የሚሆን ጸጥ ያለ ሬስቶራንት ሳስብ……..ቫቲካን  አርኮባሊኖ ትዝ አለኝ፡፡ እዚያ እራት በልተን ወደ ሰፈርዋ ስሸኛት…ዳንስና ብላክ ሌብል እንደምትወድ….የከተማውን ምርጥ የምሽት ክለቦች እየጠራች----ገድልዋን ታብራራ ጀመር….እንትን ሆቴል ዊስኪውን እንዴት አርገዉ ለሴት ልጅ አጣፍጠዉ እንደሚሰጡ ብትቀምሰው…እንትን ክለብ ያለው ዲጄ ሪትም ሲያነብ ብትሰማው….እያለች ተረከችልኝ፡፡ ቅድም ሳገኛት እጅ ያልነካት ትመስል የነበረችዉ ባለ ወተት ልጅ…አሁን ደግሞ….ሰዶምና ገሞራ ውስጥ የመኖሪያ ፈቃድ ያላት መሰለችኝ….
ወደ ቤቴ ስገባ ለራሴ እንዲህ ብዬ ነገርኩት…“አስማት የሆነ ውበት ካላት ልጅ ጀርባ ብዙ ነገር አለ…አርፈህ ተቀመጥ”…..
ብዙ ቀን ዝም አልኳት….ዳሩ…ያችን የመሰለች ልጅ እኔ ፈለኳት አልፈለኳት ምን ይጎልባታል…? ጉዳይዋ ነዉ…? ይግረምህ ብላ ደወለችና…
“ይቅርታ ጠይቀኝ” አለችኝ….
“ለምኑ?” አልኳት….
“ለምኑ ይላል እንዴ….ይቅርታ ጠይቀኝ እኮ ነዉ የምልህ….!!”ተኮሳተረች….
“እሺ…ይቅርታ…!!” አልኳት….
“…ይቅር ብያለሁ….ስራ ስትጨርስ አግኘኝ…እፈልግሃለሁ….;አዘዘችኝና….ዘጋችዉ፡፡
…..ሳገኛት…በነጭ መደብ ላይ ጥቁር ጠቃጠቆ የበዛበት በጣም አጭር ቀሚስ ለብሳ…መሰላል ላይ የቆመች ያስመሰላትን ባለ ረዥም ታኮ ጫማ አድርጋ ነበር…አይኖችዋን ተኩላቸዋለች…ሊፕስቲክ ተቀብታለች…ጥፍሮችዋን ተሰርታለች…ጸጉርዋ ያብረቀርቃል…አንገቷ…ጣቶቿ…ክንድዋ…በጌጣጌጥ ኳኳታ የሚያቃጭል…ደወል ልጅ ሆና አገኘኋት…ከሁሉም በላይ የሽቶዋ መአዛ ጥንካሬና የቀሚሷ እጥረት ትእግስቴን የሚፈታተን ነበር…ዛሬ ደግሞ ጡት መያዣ አድርጋለች፡፡
የላምበረትን ቁልቁለት ስንያያዝ፤ “ዛሬ መደነስ እፈልጋለሁ” አለችኝ፡፡ ሴቶች የወንድን ልብ የሚያዩበት ልዩ መነጽር አላቸዉ….ሺ ጥያቄዎች ቢኖሩኝም የተሸነፈላትን ውስጤን አይተዋለች፡፡ እንደዛ ባይሆን ኖሮ፣ እንደ ዋዛ ወዲህ ና! ወዲያ ሂድ! አትለኝም ነበር፡፡ አልባኒ እራት እየበላን ሰአቱን ገፋንና፣ ጉዞ ወደ ባይላሞስ ሆነ…..ጎበዝ መደነስ መቻል መሰረታዊ ነገር ነው ለካ….ሰዎች አንገት ማስገቢያ ያህል የሚሉት ቢሆንም፤ቃሉ ለዳንስ ከሰራ/ ዳንስ መቻል ያስፈልጋል….ስራዋ ዳንስ ሳይሆን አይቀርም….እስኪያዞረኝ አወዛገበችኝ፡፡…እንደ ህጻን ልጅ ሰውነቴን እየታከከች እንደ ሀረግ ዞረችኝ፡፡…አ….ቤ…..ት… የሰው አይን ሊበላኝ ነበር…ምን ይሆን የሚያዩት….? እስዋ ለጋ ወጣት፣ እኔ ጎልማሳ…እስዋ አጠር ያለች፣ እኔ ረዥም …እስዋ ብላክ ሌብል፣ እኔ ውሃ መጠጣቴን ነዉ?…ብቻ አምላክ አብረሃምን “ቀና ብለህ ቁጠር” ያለውን ክዋክብቶች የሚያክሉ አይኖች አይተውኛል….እስዋን ሳይሆን እኔን ማየታቸውን ነዉ የማውቀዉ….
እስዋ ደንሳና ሰክራ ደከመች….እኔ ተወዛውዤና ተሳቅቄ ደከመኝ፡፡ ግን ደረጃውን ደግፍያት አውርጄ….መኪና ዉስጥ ተሸክምያት አሳፍሬ…ወደ ቤቴ እሽኮኮ ብዬ አስገብቼ…እንደ ሞተ ሰዉ የተዘረጋችውን ልጅ ማስተኛት የውዴታ ግዴታዬ ነበር፡፡….ጠዋት ስራ መሄድ ስለነበረብኝ  ስነሳም አልነቃችም…የሴትን ልጅ ቁንጅና ማረጋገጫ ናሙና የሚወስድበት ትክክለኛው ሰዓት ጠዋት ውሃ ሳይነካት ነው፡፡…ከንፈሮችዋን ሳታላቅቅ…ፈገግ ያለች ከመሰለች…ድምፅ ሳይወጣት ያንሾካሾከች ከመሰለች…ደምዋ ግጥም ብሎ ጸዳልዋ ከበራ….ያች ሴት በርግጥ ውብ ናት….ሳራ ሞታም የምታምር ይመስለኛል….
ቢሮዬ ገብቼ ለራሴ እንዲህ አልኩት፤“ትቅርብህ…!!.ከነውበትዋ… ከነልጅነትዋ…ትቅርብህ…!!.” …ጥያቄ ምልክት ነፍሴ ላይ አትማ…ግራ አጋብታኝ ብወዳትም ትቅርብኝ!!!
…….ሳምንታት አለፉ……..
….ግን አልቀረም…መ/ቤቴ ህንጻ ስር ካለው ካፌ ሆና በሰው አስጠራችኝ፡፡ እውነቱን ለመናገር ናፍቃኝ ነበር…ድርያ ለብሳለች፤ከስስ አላባሽ ሻርፕ ጋር፡፡ …ጸጉርዋን በሻሽ ሸብ አርጋዋለች….ነጠላ ጫማ ነበር ያደረገችው…ሌላው የሴት ልጅ ውበት ናሙና መውሰጃ ሰዓት አልባሌ ልብሰ የለበሰች ጊዜ ነዉ፡፡…ያኔ ውብ ሆና ከታየች፣ ያለ ጥርጥር በመላዕክት እጅ ተሰርታለች፡፡…አቤት ስታምር!…ግንባርዋ ላይ ሳምኳት…ጨፍና ነበር…
“…..ከረዥም ቀሚስ ውስጥ…ካለ መኳኳል ውስጥ…ካለ ማጌጥ ውስጥ…ቤተክርስትያን ከመሳለም ውስጥ…አንገት ከመድፋት ውስጥ…ትህትናና ጨዋነት ያለ….ይመስልሃል!!...በተቃራኒው.....ካጭር ቀሚስ ዉስጥ…ከማጌጥና ከመኳኳል ውስጥ…ከመደነስ ከመዝፈን ውስጥ..ነውርና ክፋት ያለበት ይመስልሃል…!!.ይህ ግን ስህተት ነዉ!!” አለችኝ፡፡
በርግጥ ጸጥ አሰኘችኝ….ቀጠለችናም…“ለመሆኑ አንድ ደስ ያለህ ቦታ ውሰደኝ ብልህ የት ትወስደኛለህ…?” ብላ ጠየቀችኝ…
“…ቤተ ክርስትያን” አልኳት…
“…ሃይማኖትህ ምንድነው….?”
#…ሀይማኖቴ እግዚአብሄርን ማመን ነው…እግዚአብሄርን መፍራት…ለሱ ክብር መኖር…;አልኳት፡፡
“…ውሰደኝ የምልህ ቀን ትወስደኛለህ…” ብላኝ… ያዘዘችዉን ጁስና በርገር ይዛ ..“ሸኘኝ” አለችኝ፡፡ ሰፈርዋ ስሸኛት ነፍሴ “ኢፍ ላቪንግ ዩ ኢዝ ሮንግ…አይ ዶንት ዋና ቢ ራይት…” የሚለውን ዜማ አንጎራጎረችላት…ደርሳ ልትወርድ ስትል…“ልሳምሽ?”…ብዬ ጠየቅኳት…“ለምን ታስፈቅደኛለህ…?”.ብላ ጮሃ ወረደች፡፡ ..እዳዉ ገብስ ነዉ…ሮጬ ያዝኳትና ከንፈሬ የደረሰበት ሁሉ ሳምኳት፡፡
….ልጅና አዋቂ ሆና…ጨዋና ዱርዬ ሆና…ጥሩና መጥፎ ሆና…እንጃ ብቻ ብዙ እንቆቅልሽ ሆናብኝ….ግራ አጋብታኝ…ወደድኳት…!! …ግን ጥሩና መጥፎዋ ምንድነው….? ባልገባኝ ነገር እኔ “የምፈልገው አይነት ሴት” አደርጋታለሁ ብዬ እልህ ተጋባሁ…በርግጥ “ከነፋስ ጋር” ነበር እልህ የያዘኝ…ምን ልሁንልህ…? እንዴት አይነት ሴት ልሁንልህ? እንድትለኝ…ፈለግሁኝ፡፡ …በደግነት….በፍቅር…በመታዘዝ….በመሸነፍ….የምፈልጋት አይነት ሴት አደርጋታለሁ ብዬ ቆረጥኩኝ…፡፡ በርግጥ ወድጃት ነበር…እንድትደውል ሳልጠብቅ ቀንና ማታ ስደውል…ሰንበትና አዘቦት ቀን ሳልለይ እስዋ… ና!!... ያለችኝ ቦታ ሁሉ ስገኝ…ሳከብራት…ስታዘዛት…ሳፈቅራት…ስናፍቃት….ጊዜው ሮጠ፡፡ እስዋ እንቆቅልሽ እንደሆነችብኝ…..ሳራ እንቆቅልሽ እንደሆነች-----ጊዜው ሮጠ…ከሳራ ጋር ፍቅርና እልህ ይዞኝ….ጊዜው ሮጠ፡፡
**************      **************
አንድ እሁድ ረፋዱ ላይ ሚጢጢዬ ቁምጣ በስስ ፓክ አውት ለብሳ ቤቴ መጣችና “ቸርች እንሂድ” አለችኝ….. በርግጥ ደንግጬ ነበር፤ግን ረጋ ብዬ “..ሳርዬ…እንደዚህ ለብሶ ደጀ ሰላም መሄድ ድፍረት ነዉ..ልብሰ ትቀይሪና እንሄዳለን” አልኳት…ህጻን ልጅ እንደማባበል ተጠንቅቄ….
“…ለመሆኑ መድሃኒአለም ነዉ ወይስ ዩጎ ነዉ የምትወስደኝ…?”
“…እግዚአብሄር ወደ ሚመለክበት ወደ ፈለግነዉ እንሄዳለን….ከአምላክ እንጂ ከተቋሙ ምን አለን…” ስላት አፍታም ሳትቆይ…
“…በቃ ከከተማ እንውጣ” አለች….
“…ሳ……ሪ!…?”.አልኳት ጮክ ብዬ
“…ዋ…..ት!……?”አለች እስዋም ጮኻ
“…ቤተ ክርስትያን ካልሄድን ከከተማ እንውጣ….ማለት….በጣም የሚቃረን ነገር እኮ ነው…ሊተካካ አይችልም!!”
“…ሁለቱም የነፍስን ጉድለት ለመሙላት የሚኬድበት መስሎኝ….ነው…”
“የነፍስ ጉድለት”…..የሚለውን ቃል ከአንደበትዋ ስሰማዉ የባሰ ደነገጥኩ….
“…ለማንኛዉም ልብስሽን ቀይሪ ስሞትልሽ….የኔ ቆንጆ….;
“አልቀይርም……ኡ…….ፍፍፍፍፍ…..አስጠላኝ አሁንስ…!!.ከዚህ ቤት እንውጣ….”
“….ምኑ ነው ያስጠላሽ…..ቤቱ ነው…ወይስ የኔ ንግግር?;
“…ሁሉም ነገር…!!.መመከር ሰለቸኝ!! መታረም ደከመኝ…!!መቼ ነው እኔ ትክክል የምሆነው….?“
“…ሳሪ የምትናገሪውን ታውቂያለሸ….?”
“….አውቃለሁ….ሁሉም ነገር አስጠላኝ አልኩህ’ኮ…..!!;
“….ሳሪዬ….እያናደድሽኝ ነዉ….;
“…ገደል ግባ!!”
ብልጭ አለብኝ “….በዛ…..ሳራ በዛ…..; አፈጠጥኩባት….“…ገደል ግባ አልኩህ’ኮ….!!.አትሰማም….??”
ዘልዬ ጸጉርዋን ጨምድጄ….“አንቺ እኔን ነው ገደል ግባ ያልሽኝ…?;.አልኳት…እስዋ መች ከቁብ ቆጥራኝ…እስዋን ትቼ ስልክዋን ግድግዳው ላይ ከሰከስኩት….“አንቺ እኔን ነዉ ገደል ግባ ያልሽኝ…?” አስጓራችኝ፡፡….ግድግዳዉን በቦክስ ነረትኩት….ፊቴ ያገኘሁትን ዕቃ ሁሉ ሰባበርኩኝ…አፌን ሀሞት ሞላው ---”ውጭልኝ!!....በጄ ሰበብ ሳትሆኝ….ዉጪ…..!!!...; ጮህኩባት…
…..ኮስተር ብላ…“ግደለኝ!!”...ብላ አፈጠጠች…
….ዛሬስ….ለየላት….ለካስ ከእብድ ጋር ነዉ….ስወዛገብ የከረምኩት…..ማልቀስ ሁሉ ዳዳኝ….
“…….መምታት አትችል…መጨከን አትችል…..መሳደብ አትችል….ማሳመም አትችል…..ሁሌ ፍቅር…ሁሌ ትህትና….” ማልቀስ ጀመረች….ከዚህ በኋላ ምንም አላልኩም…እስዋ ብቻ ነበረች የምታወራው…
….ባጭሩ………በጣም ባጭሩ…………
….አያቶቿ ቤት ነው እስዋና ታናሽ እህቷ የሚኖሩት…በ15 አመት ታላቋ የሆነው የወላጅ እናትዋ ወንድም….እሽኮኮ ባረጋት ቁጥር ሽንቷን ጭርር እያደረገችበት….እንዳላሳደገ….ከአፉ አውጥቶ አጉርሶ ያሳደገውን…የሳራን ለጋ ገላ፣ ገና በ14 አመትዋ….ወሲብ ባሰከረው ቁጣ፣ በፈርጣማ ክንዱ ፈጥርቆ….ቀደደው፡፡…ለዚህ ነው ሳራ ….ከትህትና ….ከእንክብካቤና….ከፍቅር…ቀጥሎ…. ምህረት የለሽ ጭካኔ….የሚከተል የሚመስላት….ለዚህ ነው በሁሉም ነገርዋ ግድ የለሽ ሆና የቀረችው….
…መሆን የሚገባው…ሳራን አቅፌ እንባዋን ማበስና ቃላት በስለት ሰብስቤም ቢሆን እስዋን ማፅናናት ነበር…ነገር ግን…
…በለቅሶዋ መሃል  ትዝ ያለችኝ…ትንሽ እህትዋ ነበረች….“እህትሽ የት ነው ያለችው….? እስዋስ….እስዋስ…? ሳራ….!!”ብዬ ጮህኩ….ደመ ነፍሴ የሆነ ነገር ነገረኝ….
….አፍጥጣ እያየች….“እህቴ ምን ሆነች…?ቹቹ ምን ሆነች…?”ብላ….በጥያቄ አዋከበችኝ…
“…ለእናትሽ መንገር ነበረብሽ…!! ለአያቶችሽ መንገር ነበረብሽ…!! ስለ ቹቹ ማሰብ ነበረብሽ….!!” የምይዘዉ የምጨብጠው ጠፋኝ….
…ቹቹ ጋ ደወልኩ… “የት ነሽ ቹቹዬ….?”
“..አጎቴ ቤት ነይ ብሎኝ …በምልክት የነገረኝ ቦታ እየደረስኩ ነው….” “…ቹቹ….ተመለሽ…!!አጎትሽ ቤት…እንዳትገቢ….!!ያለሽበት ቁሚ …!!መጣን….” ተያይዘን…ወደ ቹቹ በረርን፡፡…ድንግርግር ያላትን ብላቴና ይዘን ወደ ኮተቤ….ስንሄድ…ሳራ… “ትወደኛለህ..አይደል …??”.አለችኝ
“….አጥንቴ ፈሳሽ እስኪሆን ድረስ እወድሻለሁ….!!” አልኳት…“ሳርዬ፤ ለአጎትሽ የሚሆን ትህትና አይኖረኝም….እፋረደዋለሁ!!.....አንቺን ግን መምታት….መሳደብ…….አልችልም፡፡ እያሳመምኩሽ መሳም…እያሳመምኩሽ ማቀፍ…እያሳመምኩሽ….አልችልም” አልኳት፡፡….. በህይወቴ “ከባድ ነው” ብዬ ያመንኩበት ችግር ውስጥ እየሰመጥኩ እንዳለሁ ገባኝ፡፡…ደስ እያለኝ የምገባበት…የሳራ ፍቅር!!
…..አስማት የሆነ ውበት ካላት ሴት ልጅ ጀርባ ብዙ ጣጣ አለ፡፡

Published in ልብ-ወለድ

 የዛሬ 2 ሳምንት ከገጣሚ ወንድዬ ዓሊ ጋር ቀልጠፍ ያለች ቃለ - ምልልስ ጀምረናል፡፡ ውይይታችን ድንበር ሳይሻገር በሀገራችን ጥበባት ዙሪያ ሲሽከረከር ነበር፡፡ ዛሬም እዚሁ ሀገራችን፣ ይልቁንም በጥበባት ትኩስ ምጣድና እንጀራ፣ በፉንጋውና ቆንጆው፣ በአይነ ልሙና አይነ ኮከቡ ለጥበባችን እልፍኝ ድምቀት፣ ለዘመናችን ውበት ይሆነን ዘንድ እመኛለሁ፡፡
                     

    ግራጫው፤ አማረም አረረም በየሣምንቱ አዳዲስ የግጥም መድበሎች ይወጣሉ፡፡ ገልጠህ ስታነባቸው ግን ራሳቸው ለራሳቸው የደፉትን ባርኔጣ ያህል የማይመዝን ሥራ ሆኖ ስታገኘው አንዳች ነገር ሰውነትህን ይወርረዋል፡፡ ልብህ ይሰበራል፡፡ እነዚህ በአቻ ግፊት ወይም ገጣሚ በመሆን ውስጣዊ ረሀብ ያሳተሙት ናቸው፡፡
በየመሀሉ ደግሞ ከፍላት እንዳመለጠች በቆሎ ጠጣር ነገር ይዘው ብቅ ያሉ ነገር ግን ቅድም ባነሳናቸው የሕትመት ጐርፍ ተውጠው፣ ትኩረት የተሳናቸውም አሉ፡፡ ለምሣሌ ዕድሜውን በወጣት ሣጥን ውስጥ የማላስቀምጠው ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ፣ ወጣቶቹ ቴዎድሮስ ፀጋዬ፣ በዕውቀቱ ስዩም፣ ታገል ሰይፉ፣ ወንድወሰን ካሳ፣ አሌክስ አብረሃም፣ ወዘተ…
ዶክተር በድሉንና አሌክስ በሺህ የሚቆጠሩ የፌስ ቡክ ደቀመዛሙርት አሏቸው፣ ግን አድናቆቱ ባብዛኛው ጥልቀት የለውም፡፡ ምርቱን ከገለባው ከሚለዩ ደፋር ሃያሲዎች ጋር አልተፋጠጡም፤ በዚያው እንዳይቀጥሉ ነው ስጋቴ፡፡ ጅምላ ፍካሬና የጀሌ ጩኸትን ያህል የጥበብን ሰው የሚያደነዝዝ ነገር የለም፡፡
ቴዎድሮስ ፀጋዬ መካከል ላይ ያለ ብርቱ ልጅ ነው፡፡ ወንድወሰን ካሳ ዓይናፋር ሳይሆን አይቀርም፤ እርሱ አይጮህም፣ የጮኸለትም የለም፡፡ ይህ የእኔ ግንዛቤ ነው፡፡
ቅርፁና ይዘቱ ምንም ይሁን ምንም፣ ሙገሣው ካፖርት የደረበላቸውና ሙቀት ያደነዘዛቸው ገጣሚያን፤ ከፈዘዘ ማለዳቸው ሲባንኑና ምድርን ሲረግጡ፣ ሌላ መካሻ ይዘው እንደሚመጡ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ለስነ ግጥም ተወልደው ከሆነ ቢፈዙም አይጠፉም፡፡
አየህ ሙገሳ የመሸታ ያህል ስካር አለው፤ የሚያድርና የሚሰነብት “ሀንጐቨር” አለው፡፡ ከዚያ መላቀቅ ቀላል አይምሰልህ!
ሰው ለጥበብ ይወለዳል?...ወይስ ራሱ በፍቅር ጥበብን ይወልዳል?...ምናልባትስ ከትምህርት ቤት ይሸምት ይሆን?
በኔ አተያይ ከነብዙ አባዜው ጥበብ መወለድን ይጠይቃል፤ መታደልም ነው፤ ግና በትምህርት፣ በንባብና በሕይወት ተሞክሮ መበልፀግ ግድ ይለዋል፡፡ ለጥበብ ተወልደን ራሳችንን የምንኮተኩትባቸው በርካታ ነገሮች ያስፈልጉናል፡፡ እነዚያ ነገሮች ሲያንሱን ነገር ዓለሙ ይሳከርብናል፡፡ ዕውቀት መሬት ያስረግጠናል፣ በተለይ ንባብ፣ ከሚያነብበው በላይ የሚናገር ሰው ግልብነቱ ያፈጥጥበታል፡፡
ጥበብን ወዳፈቀረው እንምጣ፡፡
ማኅበራዊ ሕይወታችን እስቲ እንየው፡፡ ያፈቀረ ሁሉ ጥሩ ባል ወይም ሚስት ሊሆን/ልትሆን ይችላል/ትችላለች? አይሆንም፡፡ ኪነጥበብን የተማረ ሁሉ ገጣሚ አሊያም ሰዓሊ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን የጥበብ ፍቅርና ትምህርትን የተጐናፀፉ ሰዎች ግሩም ሃያሲያንና መምህራን በአጠቃላይ ቱንቢ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ መጣመማችንን ወይም ቀጥተኛነታችንን እየመዘኑ የሚነግሩን እነሱ ናቸው፡፡ ጥቂቶች ናቸው እንጂ በእኛም ሀገር ብርቱ ሰዎች አሉን እኮ፡፡ ስም ልጥራ እንዴ? እነ ብርሃኑ ገበየሁን የመሰሉ፡፡
የኃይለ ቃልና ምናብ ምንጭህን ንገረኝ እስቲ?
በአእምሮዬና በልቡና የተጐሰጐሱ፣ በጥበብ ጥማት ለቃተተች ነፍሴ ዋርካ የሆኑኝን ሰዎችም ሆኑ የሕይወት መንገዴን መቸቶች መዘርዘር አይቻለኝም፡፡ ፊውዳል ነክ፣ ነገር ግን የባላገር ሥልጡን የሆነው ቆምጫጫ አባቴ፣ ባህሪዬን በጥበብ የሳለው ይመስለኛል፡፡ ለአባቱ የተፃፈውን ከ“ወፌ ቆመች” ውስጥ “ዱባና ንፍሮ”ን በከፊል እንመልከት፡-
ቶፋ ሙሉ ዱባ - ታሽቆ             እቀምሰው ብል   - ከምክኑ            የዱባ ቁርጥ - ተንፈቅፍቆ             እበላ ብል - ከክሽኑ!
እንቅብ ስፍር -  ንፍሮ
ዛሬስ አልጥምህ አለኝ…ሌማቱ
ኩስኩስቱን ሙሉ - ተነፍሮ            ዱባ ከንፍሮ - ብልቱ
እሳቱ ላይ - በእንክርት፣             እንዳልበላው - መታከቴ
ዛሬም አለ -  ከመደቤ ፊት ለፊት፡፡         ድንገቱ ዛሬ - ኩራቴ
ሁሌም - በየቀኑ                 እየታየኝ የራብ ሞቴ
ባየው ባየው - እሱኑ                 አዬ - ሆድ!
ቶፋውም                    ኩስኩስቱም
እንክርቱም፡፡     
ያደግሁበት ማኅበረሰብ የጥበብ ብልጽግና ከግዕዙ፣ ዐረቡ፣ ኦሮሚፋው፣ አፋሩ ተዳቅለው የጐመሩበት፣ በአጭሩ “ወሎኛ” በመሆኑ እጅግ ገላጭ የሆኑትን ሥነ - ቃላት እየሰማሁ ማደጌ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ደግሜ፣ ደግሜ፣ ደጋግሜ ማንበቤ፤ ጠቅሞኛል፡፡ በብሉይ መጽሐፍት ሲሶዎን ከያዙት ግጥሞች ለነፍስ የሚሆን አንዳች ስንቅና ክርክር የማይታጣባቸው መዝሙረ ዳዊትንና ኢዮብን፣ መኃልይ መኃል..ንማንበቤ ጠቅሞኛል፡፡
በዓለማችን ላይ ያሉ ታላላቅ ባለቅኔዎች ያደግንበት ዋርካ፣ አለ… የነፍሳችንን ክሮች ተርትሮ የገባ፣ የልብ ማህተም አለ ይላሉ፣ አንተስ ፈር ቀዳጅህ ማነው?
በእኔ ዕድሜ የሚገኝ ሰው በከበደ ሚካኤል ታሪክና ምሳሌ ያልተማረ የለም፡፡ እሳቸው አፊዎት፣ (በእንግሊዝኛው የኔ ትውልድ Inspiration ናቸው፡፡ በውስጥህ አፈር ለብሶ የፈዘዘውን ዘር እንድታበቅል የሚረዱ የጥበብ ጠብታዎች አባት ናቸው፡፡ የሥነ ግጥም አተያዬን (እንደ አብዮት) የገለባበጠው ግን ፀጋዬ ገብረመድህን ነው፡፡ “እሳት ወይስ አበባ” መድበሉን ገና እስከዛሬ አውቄ አልጨረስኳትም፡፡ ሁሌ ተማሪዋ ነኝ፡፡ በእውነት እልሃለሁ ውስጤ የተቀበረውን የገጣሚነት መንፈስ ያኳሹት ግን ኦቴሎ፣ ሐምሌት፣ ማክቤዝ የሚባሉት የዊልያም ቬክስፒር ትርጉሞች ናቸው፡፡ የቴዎድሮስን ድራማ ሣይማ ልቤ ቀለጠች፣ እንግዲህ ጋሽ ፀጋዬ ነው፤ ኃይለቃልን፣ ፍንገጣን፣ በራስ ላይ ማመፅን፣ የስነ ግጥም ፍልስፍናን ያስተማረኝ፡፡ ከእሱ ሲቀጥል የደበበ ሰይፉን የግጥም መጽሐፍት እወዳቸዋለሁ፣ በመጠኑ አቃንተውኛልና፡፡ (በጽጌረዳ ብዕር ከታተመው በቀር)
አስቸርህ ባጣ (ለፀጋዬ ማስታወሻ የተፃፈ)
በአየር - ደንገላሳ፣
በጨረር - የሳንሳ፣
በነፋስ ትከሻ - በገሞራው እስትንፋስ
ለመንጠቅ - አንደዜ! - ስውር ጥበብ ላስስ፣
ትንሽ ልፋሰሰው! - ዛቴን እዚህ ትቸው
በሰማያት ጀርባ - በማይጐረብጠው፡፡
በል - ንሳ - በልልኝ
በል- ንሳ - በልልኝ
ማዕበልን አቅፌ - መብረቅን፣ ጨብጬ
እቶንን - ደርቤ - አውሎ ተጫምቼ
በደመናት - ዋሻ
ውበት - መናገሻ፣
በነጐድጓድ ወንበር፣ - ሁሉንም ንገረኝ- ጉባኤ እንቀመጥ፣
አክናፍ ወቅኔያት፣ - ይንጠቁኝ ልብነነው- ባቴ እዚሁ ይቅለጥ፡፡
ልቀቀው! - አይተንፍግ - ታምቆ እስከመቼ?- ገሞራው ይፈንዳ
ሽቅቡን ወደ ላይ - ሽቅብ የሽቅቡን - እኔነቴን ይንዳ፡፡
(ከ“ወፌ ቆመች” በከፊል የተወሰደ)
የሀገራችን የስነ ጽሑፍ ምሁራን ለማስተማሪያ ባዘጋጁቸው መጽሐፍት አንተን “ገጣሚ” ብለው ነው ያስተዋወቁን፡፡ ምናልባት በዝርው የፃፍካቸውን መፃህፍት የማያውቁም ስላሉ … ይሆናል፡፡ አንተ ምን እንድትባል ነው የምትፈልገው?
እኔ እንጃ! በርግጥ ከ“ወፌ ቆመች” በኋላ፣ የታሪክ መጻሕፍትን፣ ግለ ታሪኮችንና (እንደፈለገ - ብርሃኑ ያሉ) ጽፌያለሁ፡፡ በርካታ የአርትዖት ስራዎችን ሠርቻለሁ፣ ጥናትና ምርምሮችም እንደዚሁ፡፡
ያሻችሁን በሉኝ፡፡ እኔ ግን የሥነጽሑፍ ወዝአደር መሆኔን አውቃለሁ፡፡
አሁን የአዲስ ዘመን ጐህ ላይ ነን፣ ስለቀጣዩ ዘመን መጠየቅ ያሠኛልና፣ ወደፊት ምን ታስባለህ?
ሁለት ነገሮች ቢሳኩልኝ ደስ ይለኛል፡፡ “ወፌ ቆመችን” ለብቻዋ፣ አሊያም ከ“ውበት እና ሕይወት” ጋር አዳምሬ ማሳተም እፈልጋለሁ፡፡
ሌላው ተዝረክርከው ከተቀመጡትና ቁጥራቸውን በቅጡ ከማላውቀው ግጥሞቼ መካከል መርጬ፣  በዚህ ዘመን ከተለመዱት ጥራዞች በተለየ ጠብደል ያለ ጥራዝ ባሳትም ምኞቴ ነው፡፡ ሌላውን ስንደርስ እናየዋለን፡፡ ሁሉንም ለማየት ያብቃን! 

Published in ጥበብ
Saturday, 19 September 2015 09:41

ውይ ህዝብ!

  “ይሄው፤ ከመጠጥ ጋር ተቆራረጥኩ! ምንም…ም…ን…ም ነገር ከእዚህ በኋላ ወደ እሱ አይመራኝም፡፡ እራሴን ለመቆጣጠር ጊዜው አሁን ነው፤ በርትቼ መስራት አለብኝ…ደሞዝ ሲከፈልህ ደስተኛ ነህ፤ ስለዚህ እንቅልፍ ምቾት ሳትል በሀቀኝነት፣ ከልብህና በጥንቃቄ መስራት ይገባሀል፡፡ መለገም አቁም! ሳይሰሩ ደሞዝ መውሰድ ለምደሀል፤ ይህ ደሞ ወዳጄ…ትክክል አይደለም…በጭራሽ ትክክል አይደለም…”
ይህን የመሳሰሉ ትምህርቶችን ለራሱ ከሰጠ በኋላ፣ ዋና ትኬት ተቆጣጣሪው ፖድቲያጊን፣ ሊቋቋመው የማይችለው የስራ መነሳሳት ተሰማው፡፡ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ያለፈ ቢሆንም ትኬት ተቆጣጣሪዎቹን ቀስቅሶ፣ በባቡር ፉርጐዎቹ ውስጥ ከእነሱ ጋር ወዲያ ወዲህ እያለ ትኬቶችን መፈተሽ ጀመረ፡፡
“ት..ት…ት..ትኬት….እ..እ…እ…እባካችሁ!” የትኬት መቁረጫዎቹን እያማታ መጮኸ ያዘ፡፡ የፀሐይን መጥለቅ ተከትሎ በቀረው ጭላንጭል ብርሃን ውስጥ የተደበቁ፣ እንቅልፍ የጣላቸው የፊት ገፆች ሁሉ አናታቸውን እየነቀነቁ ትኬታቸውን ማቀበል ጀመሩ፡፡
“ት…ት…ት…ትኬት…ይቅርታ!” እያለ ፖድትያጊን በፀጉራም ኮትና በአልጋ ልብስ እንዲሁም በትራስ የታጠረውን፣ ኩስምን ያለ የሁለተኛ ማዕረግ ተሳፋሪ ያናግር ጀመር፡፡ “ይቅርታ፤ ትኬት!”
ጣረ ሞት የመሰለው ሰውዬ መልስ አልሰጠም፡፡ እንቅልፍ ውስጥ ሞቷል፡፡ ዋና የትኬት ተቆጣጣሪው የተሳፋሪውን ትከሻ በቀስታ መታ መታ አደረገና ትዕግስት በማጣት ተናገረ፡፡
“ት..ት..ት…ትኬት….እ…እ…እ…እባካችሁ!”
ተሳፋሪው ፖድትያጊን ላይ አይኑን አፈጠጠበት፡፡ “ምን?...ማነው?...ኸ?”
“ግልፅ በሆነ ቋንቋ ነው የተጠየቁት፤ ት..ት…ት…ትኬት……እ…እ…እ…እባክዎን!
ጣረ ሞት የመሰለው ሰውዬ፣ የስቃይ ፊት አሳይቶ “የፈጣሪ ያለ!” ሲል አቃሰተ፡፡ “የአምላክ ያለ! በቁርጥማት እየተሰቃየሁ…ሶስት ሌሊቶችን አልተኛሁም! ለመተኛት ስል አሁን ገና ነው ማደንዘዣ የዋጥኩት፤ አንተ ደግሞ እዚህ… ትኬት! ምህረት የለሽነት ነው፤ ሰብዓዊነት ማጣት ነው! መተኛት ለእኔ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ብታውቅ ኖሮ፣ በዚህ በማይረባ ነገር አትረብሸኝም ነበር…ጭካኔ ነው፤ ከንቱ ነገር ነው! ምንድነው ከትኬቴ የምትፈልገው! የማይረባ ነገር ነው!”
ፖድትያጊን መልስ መስጠት እንዳለበትና እንደሌለበት ያስብ ጀመር፤ ከዚያም መልስ መስጠት እንዳለበት ወሰነ፡፡ “ይሄ መጠጥ ቤት አይደለም፤ አትጩህ!”
“በጭራሽ፤ መጠጥ ቤት ውስጥ ሰዎች የተሻለ ሰብዓዊ ናቸው…” ተሳፋሪው አሳለ፡፡ “ምናልባት ሌላ ቀን እንድተኛ ትፈቅድልኝ ይሆናል! ተዓምር ነው! ብዙ ውጭ ሀገራት ተጉዣለሁ፤ ማንም ትኬት ብሎኝ አያውቅም፤ አንተ ግን ሰይጣን የላከህ ይመስል ደግመህ ደጋግመህ…”
“ውጪ ከተመቸህ እዛ መሄድ ነዋ!”
“ጅልነት ነው ጌታዬ! አዎ! ተሳፋሪውን በጭስ፣ በታፈገ አየርና በብርድ መግደላችሁ ሳያንስ በህግና ደንብ ልታንቁት ነው፤ እንጦሮጦስ ግቡ! ትኬት እንደሆነ አለው፤ የአምላክ ያለህ! ምንድነው እንዲህ ማስጨነቅ! ለድርጅቱ የሚጠቅመው ቢሆን ጥሩ…ይሄኔ ግማሹ ተሳፋሪ ያለ ትኬት ነው የሚጓዘው!”
“ይስሙ ጌታዬ” ፖድትያጊን በብስጭት ጮኸ፡፡ “መጮህና ህዝቡን መረበሽ ካላቆሙ፣ በሚቀጥለው ጣቢያ ላስወርዶት እንዲሁም ስለሁኔታው ሪፖርት ለማድረግ እገደዳለሁ!”
“የሚያሳፍር ነገር ነው!” ሲል ‹ህዝቡ› በንዴት ተናገረ፡፡
“የታመመን ሰው ማሰቃየት ምን ይጠቅምሃል … ኧረ ትንሽ ተመልከትና እስቲ ርህራሄ አድርግ”
“ሰውዬው እራሱ ተሳዳቢ ነው’ኮ” ፖድትያጊን ትንሽ ፍርሃት ገብቶት ተናገረ፡፡
“ጥሩ…ትኬቱን አልወስድም…ደስ እንዳላችሁ…እርግጥ ነው፣ በደንብ እንደምታውቁት ይህንን ማድረግ ግዴታዬ ነበር…ግዴታዬ ባይሆን ኖሮ ጥሩ…የባቡር ጣቢያውን ተቆጣጣሪ ጠይቁ…የምትፈልጉትን ሰው ጠይቁ…”
ፖድትያጊን ትከሻውን በምንግዴነት ሰብቆ ከበሽተኛው ራቀ፡፡ መጀመሪያ ላይ ትንሽ ቅሬታና መጐዳት ተሰምቶት ነበር፡፡ ሁለት ወይም ሶስት ፉርጐዎችን ካለፈ በኋላ ግን የትኬት ተቆጣጣሪው ሆዱ የማያውቀው የሆነ አይነት አለመረጋጋት ተሰማው፡፡
“በሽተኛውን መቀስቀስ አስፈላጊ አልነበረም” ሲል አሰበ፡፡ “ምንም እንኳ የኔ ችግር ባይሆንም…ያለ ምክንያት፣ በግድየለሽነት ያደረግሁት መስሏቸዋል፡፡ ግዴታ አለብኝ…ካላመኑኝ፣ የባቡር ተቆጣጣሪውን አመጣላቸዋለሁ፡፡”
ባቡር ጣቢያ ደረሱ፡፡ ባቡሩ ለአምስት ደቂቃ ቆመ፡፡ ሶስተኛው ደውል ከመደወሉ በፊት፣ ፖድትያጊን መጀመሪያ ወደገባበት ሁለተኛ ማዕረግ ፉርጐ ገባ፡፡ ከኋላው ቀይ ኮፍያ ያደረገ የባቡር ጣቢያ ተቆጣጣሪ ተከትሎታል፡፡
“ይህ እዚህ ጋ ያለ ሰው” ፖድትያጊን ጀመረ፤ “ትኬቱን መጠየቅ እንደማልችል ተናግሯል…ስለጠየኩትም ተበሳጭቷል፡፡ እባክዎን እርሶ ተቆጣጣሪ ስለሆኑ እንዲያብራሩለት እለምናለሁ…ጌታዬ፤ ትኬት የጠየቅኩት በደንቡ መሰረት ነው ወይስ እራሴን ለማስደሰት?” ፖድትያጊን ጣረሞት የመሰለውን ሰውዬ ያናግረው ጀመር፤ “ጌታዬ፤ ካላመኑኝ የጣቢያ ተቆጣጣሪውን ይጠይቁት”
ታማሚው የተወጋ ያህል አይኑን አፍጥጦ በድንገት ተነሳ፤ ወዲያው የስቃይ ፊት አሳይቶ ወንበሩ ላይ ሰመጠ፡፡ “የአምላክ ያለ! ሌላ ኪኒን ውጬ ትንሽ ሸለብ ሲያደርገኝ፣ አንተ ደግሞ እንደገና እዚህ…እንደገና! ልለምንህ፤ ትንሽ እራራልኝ!”
የባቡር ጣቢያ ተቆጣጣሪውን መጠየቅ ይችላሉ…ትኬትዎን መጠየቅ እንደምችል ወይም እንደማልችል”
“ይህ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ነው! ውሰድ ትኬትህን …ውሰድ! በሰላም እንድሞት ከፈቀድክልኝ አምስት እጥፍ እከፍላለሁ! ታመህ አታውቅም? ጨካኞች!” “ይህ ግፍ ነው!” የወታደር የደንብ ልብስ የለበሰ ግለሰብ መበሳጨት ያዘ፡፡ “ለዚህ ንዝንዝ ምንም ማብራሪያ ላገኝለት አልችልም፡፡”
የባቡር ጣቢያ ተቆጣጣሪው በብስጭትና የፓድትያጊንን እጀታ እየጎተተ፤ “በቃ ተው …” አለ፡፡ ፓድትያጊን በምናገባኝነት ትከሻውን ሰብቆ፣ የባቡር ተቆጣጣሪውን ተከትሎ ቀስ ብሎ ማዝገም ጀመረ፡፡
“እነሱን ማስደሰት አይቻልም” ሲል፣ በግራ መጋባት አሰበ፡፡ “ለራሱ ስል ነው የባቡር ተቆጣጣሪውን ያመጣሁት፤ እንዲያስረዳው ብዬ እንዲሁም እንዲረጋጋ፤ ነገር ግን እሱ … ተሳደበ!”
ሌላ ጣቢያ ደረሱ፡፡ ባቡሩ ለአስር ደቂቃ ቆመ፡፡ ሁለተኛው ደውል ከመደወሉ በፊት፣ ፓድትያጊን በመዝናኛ ባር ውስጥ ቆሞ የጠርሙስ ውሃ እየጠጣ ሳለ፣ ሁለት ግለሰቦች ወደ እሱ መጡ፤ አንደኛው የኢንጅነር የደንብ ልብስ የለበሰ እና ሌላኛው የወታደር ካፖርት፡፡
“እየውልህ፤ የትኬት ተቆጣጣሪ!” ኢንጅነሩ ፖድትያጊንን ያናግረው ጀመር፡፡ “ለበሽተኛው ተሳፋሪ ያሳየኸው ባህሪ፣ ተመልካች የነበረውን ሰው ሁሉ አሳፍሮታል፤ ስሜ ፑዝትስኪ ይባላል፤ ተሳፋሪውን ይቅርታ ካልጠየክ፣ የትራፊክ ማናጀሩ ጓደኛችን ስለሆነ ቅሬታችንን ለእሱ እናቀርባለን፡፡”
“ጌቶች! ለምን ግን እኔ … ለምን ግን እናንተ …” ፖድትያጊን ደነገጠ፡፡ “ማብራሪያ አንፈልግም፡፡ ነገር ግን እያስጠነቀቅንህ ነው፤ ይቅርታ የማትጠይቅ ከሆነ፣ ጉዳዩን ወደ ህግ ፍርድ እንዲያገኝ እናደርጋለን፡፡” “በእርግጠኝነት እኔ … ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ በእርግጠኝነት …. ለማረጋገጥ …”
ከግማሽ ሰዓት በኋላ፣ ፖድትያጊን የራሱን ክብር ሳያዋርድ ተሳፋሪውን ይቅርታ የሚጠይቅበትን ቃላቶች መርጦ ወደ ፉርጎው ተጓዘ፡፡ “ጌታዬ” በሽተኛውን ጠራው፤ “አድምጠን ጌታዬ ….”
በሽተኛው ነቃና ተስፈንጥሮ ተነሳ፡- “ምንድነው?”
“እኔ … ምን ነበር? …. መበሳጨት አይገባህም …”
“ኡኽ! ውሃ …” በሽተኛው ልቡን ይዞ ቃተተ፡፡ “ሶስተኛ ማደንዘዣ ውጬ እንቅልፍ ሲወስደኝ … እንደገና! የአምላክ ያለ! መቼ ነው ይሄ ስቃይ የሚያቆመው!”
“እኔ የመጣሁት … ይቅርታ ….”
“ኦኽ! … በሚቀጥለው ጣቢያ አውርደኝ ከእዚህ በላይ አልችልም … እኔ መሞቴ ነው …”
“ይህ ጭካኔ ነው፤ አሳፋሪ!” በብስጭት ‹ህዝቡ› አላዘነ፡፡ “ዞር በል! ለእዚህ ግፍህ ትከፍላለህ፡፡ ዞር በል!” ፖድትያጊን እጁን በሀዘን እያመናጨቀ፣ በረጅሙ ተንፍሶ ከፉርጎው ወጣ፡፡ የተቆጣጣሪዎች ክፍል ገብቶ ጠረጴዛ ላይ ተቀመጠና፣ ድክም ብሎት ይነጫነጭ ጀመር፤ “ውይ ህዝብ! በምንም ነገር ሊደሰት አይችልም! አንድ ሰው የመጨረሻ አቅሙን ተጠቅሞ መልፋትና መስራቱ ትርጉም የለውም፡፡ ሰውን ወደ መጠጥ እና ስድብ ይገፋፋሉ … ምንም ካላደረግህ ይበሳጫሉ፤ ግዴታህን መወጣት ስትጀምር ይበሳጫሉ፡፡ ከመጠጣት ሌላ መፍትሄ የለውም፡፡”  ፖድትያጊን በአንድ ትንፋሽ ጠርሙሱን ከጨለጠ በኋላ፣ ስለ ስራ፣ ግዴታና ታማኝነት መጨነቅ አቆመ፡፡

Published in ጥበብ

     ሰሞኑን የዘመናትን ጫፍ የሚያንፀባርቁ ሁለት ታሪካዊ ፊልሞች አየሁ፡፡ አንዱ ሁለት ሺህ ዓመታት ሊያስቆጥር የሚዳዳው የይሁዲዎች ታሪክ ነው፡፡ ሌላኛው ሁለት ዓመት ሊደፍን ጥቂት የሚቀረው የአፍጋኖች ውጣውረድ፡፡ የመጀመሪያው ፊልም “ጆሴፈስ” የተሰኘ ይሁዲ የሮማ ታሪክ ፀሐፊ አንድ በጦርነት የጠፋችን ከተማ በታሪክ ለመከተብ የሚያደርገውን ጥረት የሚተርክ ነው፡፡ ጆሴፈስ ከኢየሱስ ዘመን ጋር ተለጣጥቆ የኖረ የታሪክ ሰው በመሆኑ፣ ያንን ጊዜ ለማሰስ የሚሞክሩ ተመራማሪዎች ዋነኛ ማጣቀሻ ያደርጉታል፡፡ በቅርቡ ሳህለሥላሴ ብርሃነ ማሪያም የተረጐሙት “የኢየሱስ ህይወት” የተሰኘ ድንቅ መጽሐፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ሰሙ ይነሳል፡፡ እናም የሚል ርዕስ ባለው በዚህ የአሜሪካኖች ፊልም ላይ ጆሴፈስ፤ ያቺ የይሁዲዎች ከተማ በሮማውያን ስለተከበበች፣ ነዋሪዎቿ ከምርኮ ለመትረፍ እንዴት እርስ በእርስ ተገዳድለው እንዳለቁ ይተርክልናል፡፡
“Good kill” የተሰኘው ሌላኛው አሜሪካዊ ፊልም ደግሞ በሰው አልባ ጄት የአፍጋኖችን አሸባሪዎች ለማጥፋት የተደረገውን ውጣ ውረድ በእውነት ላይ ተመስርቶ ያስጐበኘናል፡፡ አሜሪካና አሜሪካውያን በዚህ ታድለዋል፡፡ የገዛ ታሪካቸው አጥሮ ቢያስቸግራቸውም በሌሎች ህዝቦች ላይ ተመርኩዘው እስከ ሆሜር ዘመን ተስፈንጥሮ ለመማማር አላዳገታቸውም፡፡ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር እየቆረጡ ለማለት እንችላለን፡፡
እኛ ከደጃፋቸው ሞፈር ከሚቆረጥ ተላላ ህዝቦች መካከል ነን፡፡ ሆሜር ፈልጐን መጣ እንጂ አልፈለግነውም፤ ኤዞፕ ትንሽ ሥጋችን እንደመርፌ ወጋችው እንጂ እኛን አላስቃሰተንም፤ ማክዳ በእንቆቅልሽ ያመጣችውን አልተጠቀምንበትም፤ ዞሳካለስ “The Great Merchant” (ታላቁ ነጋዴ) ለምን እንደተባለ ጥበብ አላደረግንም… ልብ አላልነውም እንጂ መሬትን የገረፈው፣ ሸሽቶ የቤተክርስቲያን ደወል የደወለው፡፡ ንጉስ ሁሉ የጥበብ ግብአት ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ታሪኩ በጥሬው ጥበብ ሲሆን እንመለከታለን፤ ነገር ግን ፍላጭ ድንጋይ መፍለጫ የሚሆነውን ያህል እንኳን አልተጠቀምንበትም፡፡ አንድ የገረመኝን ታሪክ ላውጋችሁ፡፡
በራስ ዓሊ ዘመን ነው፡፡ የሰሜንና የትግራይ ገዢ የነበሩት ደጃች ውቤ አምፀው፣ ራስ ዓሊን ሊወጉ ተነሱ፡፡ አጠገባቸው አቡነ ሰላማን በመያዛቸው ህዝቡ ከጐናቸው እንደሚሰለፍ አልተጠራጠሩም፡፡ ደብረታቦር አጠገብ አጅባር ላይ ተዋጉ፡፡ በጦርነቱ ከወታደሩ መደበላለቅ የተነሣ መረጃ ተሳከረ፡፡ ሁለቱም የጦር መሪዎች የተሸነፉ ስለመሰላቸው በየፊናቸው ወደ ኋላ ሸሹ፡፡ ከተማ ተቀምጦ ወሬ ከሚጠባበቀው ሰው መካከል አንዱ ለሌላው ሲያወራ ነው አሉ፡-
“ራስ ዓሊ እና ደጃች ውቤ ተዋጉ” ይላል፡፡
“እህሳ?” ሲባል
“ራስ ዓሊ ሸሹ፣ ደጃች ውቤ ተማረኩ፣ ተያዙ” አለ
“በወግ አታወራም?” ሲባል …
“እነሱ በወግ ያልሆኑትን እኔ ምን ብዬ በወግ ላውጋው?” አለ አሉ፡፡
ሰውየው እውነቱን ነወ፡፡ ሁለቱ ተዋጊዎች በወግ አልሆኑም፡፡ ለካ በየፊናቸው ሲሸሹ፣ ደጃች ውቤንና አቡኑን ብሩ አሊጋዝ አግኝቶ ማርኳቸዋል፡፡
ይቺ ታሪክ ብቻዋን አስቂኝ ፊልም፣ ቴአትር፣ ልቦለድ አይወጣትም? አልተጠቀምንባትም እንጂ ታሪኳ ለማሳቅ የተፈጠረች ያህል እያንከተከተች ቀጥላለች፡፡ እንዲህ…
ደጃች ውቤ ከተማረኩ በኋላ ራስ ዓሊ ወደ መንበራቸው ተመለሱ፡፡ ታሪኳ “አሳዛኝ” የምትሆነው ራስ ዓሊ ደጃች ውቤን ቢበቀሉ ነበር፡፡ ራስ ዓሊ ግን አላደረጉትም፡፡ ደጃች ውቤን ማሩና ወደ ግዛታቸው ላኳቸው፤ ያውም ባሪያ ሰጥተው፡፡ ታሪክ ፀሐፊው አለቃ አፅሜ፤ እራሳቸው እየሳቁ ሳይሆን አይቀርም እንዲህ ይሉናል፡-
“ደጃች ውቤ ከግዛቱ ሲደርስ ለዚያ ባሪያ ስም አወጣ፡፡ ሲቻለው ማሪ ዓሊና ፈጣሪ ብሎ ሰየመ፡፡”
ይቺን ታሪክ ለመፃፍ የሚነሳ የባለምናብ ሰው ድርሻ አድካሚ እንደማይሆን ግልጽ ነው፡፡ የራስ ዓሊ እና የደጃች ውቤ ባህርይ አልቆ የተፈጣጠመ ነው፡፡ ትንሽም ከባቢያዊ ሁኔታውና የአካባቢው ሰዎችን መሳል ሳያተጋው አይቀርም፡፡ ሁለቱን መኳንንቶች የከበቡት ሰዎች እንዴት ያሉ ነበሩ? ምን፣ ምን መከሩ? ደጃች ውቤ እንዴት ተሳስተው ለጦርነት ቆረጡ? ራስ ዓሊ እንዴት ተቋቁመው ምህረት አወረዱ? ይቺን፣ ይቺን ማሰብ በቂ ነው፡፡
እንደው ያለአግባብ ምኞት ላይ ስንወድቅ ነው እንጂ እንኳን ጥቃቅኖቹ የታሪክ ሁነቶች ቀርቶ አንኳር አንኳሮቹም በቅጡ ወደ ጥበብ አልተለወጡም፡፡ አፄ ቴዎድሮስ የተሻለ በጥበብ ፀሐፊያን ቢቀነቀኑም በቂ ነው ከማለት የሚያደርስ አይደለም፡፡ የፀጋዬ ገብረመድህን እና  የግርማቸው ተክለሀዋርያት “ቴዎድሮስ” ቴአትሮች፣ የአቤ ጉበኛ “አንድ ለእናቱ” የብርሃኑ ዘሪሁን “የቴዎድሮስ እንባ” እና “የታንጉት ሚስጥር”፣ የጌትነት እንየው “የቴዎድሮስ ራዕይ” ….. ከአንድ እጅ ጣት አልዘልቅ ያሉ ሆኑ፡፡ ከውጭ የባሪየር ቲ. “ቴዎድሮስ” ባለ አምስት ገቢር ድራማ አለ፡፡ ይሄው ነው፤ ቴዎድሮስን ያህል አወዛጋቢ ንጉስ በምናብ የታገዙ ብዙ ምስሎችን አለማትረፉ ኪሳራው የእኛ ነው፡፡ ስለ አፄ ቴዎድሮስ ካነበብኩት አንድ የገረመኝን እዚህ ላይ ጣል አድርጌ ልለፍ፡-
ምድር ቁና በሆነችበት ወቅት መቅደላ ላይ ነው፡፡ የንግስና ጀንበር ባዘቀዘቀችበት በዚህ ጊዜ አፄ ቴዎድሮስ እንግሊዛዊያኑን እስረኞች ፈተው ወደ ዘመዶቻቸው ላኳቸው፡፡ ከሸዋና ከጎጃም እየመጡ የታሰሩትንም ከአቶ ዳርጌና ከደጃዝማች ብሩ ጎሹ ጋር አድርገው ፈቱ፡፡ የቀሩትን አምስት መቶ የሚሆኑትን ባላባቶች “አንድ አንድ አረር እየሰጡ በመቅደላ ገደል ሰደዷቸው” ይላሉ አለቃ አፅሜ፡፡ “ይሄንን ድንቅ /ጉድ/ ለማየት ሁለት መነኮሳት ቆመዋል፡፡ አቶ ቴዎድሮስ አዩዋቸውና፡-
“አባቶቼ ከዚህ ስፍራ ለምን መጣችሁ?” ሲሉ ጠየቋቸው፡፡
“አይ እንዲሁ ለማየት ብለን ነው” አሉ
“እንግዲያውስ በጣም እዩት” ብለው ገደል ሰደዷቸው፡፡
የአፄ ቴዎድሮስ አወዛጋቢ ባህርይ ለፀሐፊ እጅግ አድርጎ የሚመች ነው፡፡ መነኮሳቱ ቆመው አሰቃቂውን ትዕይንት መመልከታቸው ጥፋት ነው? እንዴት? ጥፋትስ ከሆነ መቀጣት የነበረባቸው ወደ ገደል በመሰደድ ነበር? ለምን? … እዚህ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉ ምላሻቸው መንቶ ነው፡፡ አዎ፣ አይደለም … ልክ ነው፣ ልክ አይደለም … በሚል፡፡ መነኮሳቱ ቆመው አሰቃቂውን ትዕይንት ማየታቸው የውስጣቸውን ጭካኔና ክፋት ይገልጣል፡፡ ልንል እንችላለን፡፡ እንደ መነኩሴነታቸው ሲሆን አፄውን ሳይፈሩ ለመገዘትና ሰውን ወደ ገደል ከመወርወር ለመታደግ መድፈር ነበረባቸው፡፡
 ካልሆነ ደግሞ ፊታቸውን ሳይመልሱ አካባቢው መሸሽ በተገባቸው ነበር፡፡ እነሱ ግን ከእዚህ አንዱን እንኳን አላደረጉም፡፡ እናስ? በዛም በዚህም መከራከር አይቀርምና ይሄን ቁራጭ ታሪክ ወደ ጥበብ ለመለወጥ የተነሳሳ ሰው ግራ ቀኙን፣ ላይ ታቹን እየዳሰሰ … ስራውን ሊያስፋፋ ይችላል፡፡
ታሪክ የጥበብ ግብአት የመሆኑ ጉዳይ ከዚህ እስከዚህ ተብሎ የሚደመደም አይደለም፡፡ ታሪክን ለጥበብ መነሻ ቢያደርጉትት፣ ማዳበሪያ ቢያደርጉት፣ ለመደምደሚያ ቢያጩት ስራውን ማጠርቃቱ እሙን ነው፡፡ ግን ምን ይሆናል… ታሪክ ለእኛ ሞኝ ደጃፍ ያለ ሞፈር ሆኖብናል፡፡
 ይሄን ከማሳሰብ ጋር አንድ የአስቂኝ ድራማ፣ ፊልም ወይም ልቦለድ መነሻ የሚሆን ቁራጭ ታሪክ ነግሬ ላብቃ፡፡፡
በሸዋ ነው፡፡ መርድ አዝማች ኃይሌ እንደሞቱ ሣህለ ሥላሴ በአልጋው ተቀመጡ፡፡ አፍታም ሳይቆይ ከአቶ ሰይፉ ጋር ቂሙ የማይበርድ ጦርነት ሆነ፡፡ “በዚያን ዘመን፣ በዚያች ወራት የነበረ ሰው እንዴት ያሳዝናል” ይላሉ ታሪክ ፀሐፊው፡፡
ታላቅ ሽብር ሆነ፡፡ ልጅ ሲወለድ ስሙ ሽብሩ ወይ አሳርአየሁ ይባል ነበረ፡፡ የሸዋ መንግሥት ለሁለት ተከፈለ፡፡ አቶ ሰይፉ ቴዎድሮስን ከጠላ እና አባ ሰላማን ከነቀፈ ጋራ ሆኑ፡፡ መርዕድ አዝማች ኃይሉ ደግሞ ቴዎድሮስንና አባ ሰላማን የወደደን ተከተሉ፤ እንደዚህ ጦርነት፣ ሽብር፣ ዘረፋ፣ መጋደል ሆነ፡፡ በየአውራጃው የአጣ ምን አጣ፣ የአገኘ ምን አገኘ ተባለ፡፡
ዳኛ ጠፋ፤ “በቴዎድሮስ አምላክ፣ በሰላማ አምላክ፣ በኃይሉ አምላክ፣ በበዛብህ አምላክ” ቢሉ የሚሰማ ጠፋ፡፡ አንድ ባላገር ወንበዴዎች ሲደበድቡት የሚለው ቢያጣ፤ “በድብልቅልቁ አምላክ” አለ ይባላል፡፡
ይቺ ቁራጭ ታሪክ አስቂኝ ብቻ ሳይሆን አሳዛኝም ትሆናለች፤ እንደያዥው ማለቴ ነው፡፡  

Published in ጥበብ

 መግቢያ
አብነት ስሜ፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በነሐሴ 16 እና 23 ቀን 2007 ዓ.ም የወጣ “ወሪሳ-የዓለማየሁ ገላጋይ ትንቢታዊ ድምፆች” የተሰኘ ኂሳዊ ንባብ ማቅረቡ ይታወሳል። ለዚህ ጽሁፍ ምላሽ ነው ብለው ተስፋ በላይነህ የተባሉ ጽሑፍ አቅራቢ “አብነት ስሜ ራሱ ፈራጅ ራሱ ወራጅ” የሚል መጣጥፍ አቅርበዋል። ይኸ ጽሑፍ የዚያ ምላሽ ነው። አብነት ወሪሳ በተባለው ልቦለድ ላይ ያቀረበው የአስተያየት ብእሮግ፣ አንድም እንዲህ ማለት ይሆናል፤ አንድም እንዲህ ነው በሚል አካሔድ የቀረበ አንድምታዊ ትርጓሜ ነው። አንድም ማለት ቃል በቃል ወይም ማለት ነው። አብነት ለዚህ አስረጂ ከሀገራችን የአንድምታ ትርጓሜ ባህል አንድ ምሳሌ ጠቅሷል፤ [የፈርዓን ልጅ ገላዋን ትታጠብ ዘንድ ወደ ዐባይ ወንዝ ወረደች። የፈርዖኑ ልጅ የተርሙት ወደ ዐባይ ወንዝ መውረድ አራት አንድምታዊ ትርጓሜዎች ተሰጥተውታል፤ አንድም ለህክምና ጠበል፤ አንድም ለድብቅ ፍቅር፤ አንድም ለጉማሬ አምልኮ፤ አንድም ለውሀ ዋና ትምህርት ብሎ።] ተቺው ይህንንም ጥበብ ቢተቹ መልካም ነበር። ነቢዩ ሙሴን ከባህር ያወጣች ሰው እንዴት ጉማሬ አምላኪ ትባላለች ብለው ቢሞግቱም ሸጋ ነበር።
በወሪሳ ውስጥ የተካተቱት ማኅበራዊ ጉዳዮች የገሀዱ ዓለም ነፀብራቆች ናቸው። እነዚህ ጉዳዮች ማኅበራዊ ህፀፆች፣ እንከኖች፣ ቁስሎች ወይም ህመሞች ተብለዋል። የተጻፈው ይሄ ነው። ብእሮገኛው የተሸፋፈነ ቁስል አይድንም፤ ይገለጥ ነው ያለው። ይኸ ቁስል ሲነካ ሊቆጡ የሚችሉ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስቀድሞ ተናግሯል። ለዚህ አንድ ሰው ተገኝተዋል። ከዚህ በመቀጠል እኒህ ሰው ባቀረቡት መጣጥፍ ላይ አስተያየት አቀርባለሁ።

      ሒስ እና ኂስ
በተለይ በፈጠራ ጽሑፍ ላይ አስተያየት ሲሰጥ ሒስ እና ኂስ የተሰኙ ቃላት በመተካካት ጥቅም ላይ ሲውሉ ይታያል። ሒስ ነቀፋ፣ ነውር፣ ክስ፣ ስድብ፣ ጸያፍ ማለት ነው። ኂስ ደግሞ ማሻሻያ፣ ማብለጫ፣ ማላቂያ ማለት ነው። ለምሳሌ ይኄይስ የተሰኘው ቃል ይሻላል፤ ይበልጣል የሚል ፍች አለው። ዝርዝር ማብራሪያውን በኪዳነወልድ ክፍሌ መዝገበቃላት (ገጽ 443 እና 477) ውስጥ ማግኘት ይቻላል። በድርሰት ላይ የሚሰጥ አስተያየት ከሒስ ይልቅ ኂስ ቢሆን የሚመረጥ ይመስለኛል። አብነት የሞከረው ኂሳዊ ንባብ ለማቅረብ ነው።
ነቢይ እና ትንቢት
ነቢይ የመጪውን ብቻ ሳይሆን ያለፈውን እና የአሁኑንም የሚናገር ሰው ነው። ዝርዝሩን በደስታ ተክለወልድ መዝገበቃላት (ገጽ 832) ውስጥ ማየት ይቻላል። ትንቢት በነቢይ የሚነገር ቃል ነው። ቃሉ የመጪውን ጊዜ ብቻ ሳይሆን ያለፈውን እና የአሁኑንም ያካትታል። ነቢይ ሌላው ዝም ያለውን የሚናገር ማለት ነው። ትንቢት የታየ ብቻ ሳይሆን የተነገረ ነገር ማለት ነው። ያ የታየ ነገር ደግሞ የወደፊቱን ብቻ ሳይሆን ያሁኑንም ያለፈውንም ያካትታል።
አብነት፣ ደራሲውም እንደ ነቢይ ይታያል ያለው ደራሲው ሌላው ዝም ያለውን ይናገራል ለማለት ብቻ ነው። ስለመጪው ዘመን  ትንቢት ተናግሯል አላለም። ስለአሁኑም ዘመን ትንቢት መናገር ይቻላል። ነቢይ የሚለው ቃል አሻሚ እና አወዛጋቢ ከሆነ ነባይ የሚለውን ተለዋጭ ቃል ብንጠቀመውም ይቻላል። ነባይ ተናጋሪ በሚለው ፍችው ብቻ ተገድቦ ማለት ነው። ትንቢት የሚለውን ቃልም የተከሰተ ወይም የተገለጠ ወይም የተነገረ በሚለው መተካት ይቻላል። ትችት አቅራቢው ይህንን የተረዱት አይመስልም።
ህልም
አብነትን “ራሱ ፈራጅ ራሱ ወራጅ” በማለት የጻፉት ግለሰብ፣ “ጸሐፊው [አብነት] ስለ ህልም ምንነት፣ አስፈላጊነት እና የዕለት ተዕለት ትስስር ለመጥቀስ ይሞክራል” ብለው ጽፈዋል። አብነት በጽሑፉ ስለ ሕልም ጻፈ እንጅ ለመጻፍ አልሞከረም። የጻፈው አሉባልታ አይደለም። እሱ የጻፈው ካነበበው፣ ከመረመረው፣ ካጠናው እና ካስተዋለው ነው። ስለ ሥነህልም ከ50 በላይ መጻሕፍትን እንዳነበበ አውቃለሁ። በሀገራችን የህልም አፈታት ላይ የተጻፉ ሁለት የዲግሪ ማሟያ ጥናቶችን እንዳማከረ አውቃለሁ። በሀገራችን የህልም አፈታት ላይ በተዋበ ብእሩ ያዘጋጀው ዳጎስ ያለ መጽሐፍም እንዳለው አውቃለሁ። እንኳን የአብነት ስሜ ይቅርና የሲግመንድ ፍሮይድ የህልም እና መሰል ትወራዎችም ተፈትነዋል፣ ተፈትሸዋል፣ ተተችተዋል። የአብነትን ሐሳብ ማብጠልጠል እና መተቸት ተገቢ ሊሆን ይችላል። ስድብም እንኳን ቢሆን በሚመጥነው ሰው ቢሆን ይሻል ነበር። ለነገሩ አብነት የተለየ ሐሳብም አላራመደም፤ የህልም ትንታኔ ነባር ዕውቀት ነው።
ትወራዊ ማእቀፍ (Theoretical Framework) እና ጽንሰ-ሐሳባዊ ማእቀፍ (Conceptual Framework) አንድነት እንዳላቸው ሁሉ ልዩነትም አላቸው። አብነት የተጠቀመው ሁለተኛውን ነው። ልቦለድን-እንደ-ህልም-መፍታትን አብነት በተጠቀመበት መልኩም ባይሆን ያንግን የመሳሰሉ የሥነልቦና ሊቃውንት አራምደውታል። በሀገራችንም ሚካኤል ሺፈራው የተባሉ አስተዋይ ኀያሲ፤ “ምስጢረኛው ባለቅኔ” በተባለው ድንቅ መጽሐፋቸው ውስጥ በተግባር አውለውታል። ይህን ዘዴ አብነትም በራሱ መንገድ ተጠቅሞታል።
አብነት በ1986 ገና የቅድመ-ምረቃ ተማሪ እያለ የልቦለድ ገፀባህርያትን በሥነልቦናዊ ማእቀፍ ውስጥ የሚተነትን የጥናት ወረቀት እንዳቀረበ አውቃለሁ። በዚህ ወረቀቱ የአበራ ለማን “እቴሜቴ” እና የስብሐት ገብረእግዚአብሔርን “አሮጊት” አኂሷል።  የጥናቱ ወረቀት የተደነቀ እንደነበረ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነጽሑፍ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑትን አቶ ዘሪሁን አስፋውን መጠየቅ ይቻላል።
አስትሮሎጂ
አብነት ልቦለድን ለማኄስ እና ለመተንተን ህልምን፣ ሥነልቦናን እና አስትሮሎጂን ያጣመረ ጽንሰሐሳባዊ ማእቀፍ ነው የተጠቀመው። ይህን በዋናነት በሀዲስ ዓለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” እና በዓለማየሁ ገላጋይ “ወሪሳ” አሳይቶታል። ይህን የሥነኂስ ስልት ጉልበቱን እና ድክመቱን በመንቀስ ጥርት አድርጎ የሚጽፍ ቢኖር እሰየው ነበር። ብእሮገኛውን ግን በድፍኑ “ግልብ” ማለት ነውር እና አላዋቂነት ነው የሚሆነው።
ልቦለድን እንደ ህልም ማየት አዲስ ነገር አይደለም። የዘመናችን ሊቃውንት “Collective Memory” እና “Collective Thought” ላይ ብዙ ተራቅቀዋል። ልቦለድን በሥነልቦናዊ ማእቀፍ ውስጥ ማየትም የተለመደ ነው። የአስትሮሎጂ ሊቃውንትም አስራሁለቱን ኮከቦች ሲያብራሩ፤ አልፎ አልፎም ቢሆን ከአፈታሪክ፣ ከልቦለድና፣ከተውኔት ገፀባህርያት ይጠቅሳሉ። ይህን ደግሞ አብነት አልደበቀንም። በየኢትዮጵያ ኮከብ እና በፍካሬ ኢትዮጵያ መጽሐፉ ውስጥ ተናግሮታል። አብነት በተለየ ያደረገው ነገር የልቦለድ ገፀባህርያትን በአስትሮሎጂ ማእቀፍ ውስጥ መተንተንን ነው። ይህንንም በድብቅ አላደረገውም። በ2001 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀ ዐውደ ጥናት ላይ “የጉዱ ካሳ ኮከብ” በሚል ርእስ ጥናት አቅርቧል። ጥናቱን “ቼይር” ያደረጉት ዶ/ር ዮናስ አድማሱ ነበሩ። በወቅቱ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘን፣ ደረጀ ገብሬን ጨምሮ ብዙ የሥነ ጽሑፍ መምህራን ነበሩ። ያኔ ሙከራው መደነቁን እንጂ አቅራቢው “ግልብ” መባሉን አልሰማሁም።
እኔ አብነት ስሜን “ወደር እና እንከን የሌለው ጸሐፊ ነው” አላልኩትም። ዕውቀት በተፈጥሮው ሁሌም እንከን ይኖረዋል። ሳይንስና ዕውቀት ፍጹም አይደሉም። ሙሉ በሙሉ ውድቅ ሊሆኑ፣ ሊሻሻሉ እና ፈርሰው ሊገነቡ ይችላሉ። አንድ የሥነጽሑፍ እና የሥነልሳን ተማሪ የሆነ ኀያሲም ከዚህ ውጭ አይሆንም። መምህራንም ሆኑ ምሁራን ፍፁም አይደሉም። ነገር ግን፣ የሚጽፈውን ነገር ጠንቅቆ የሚያውቅን ታታሪ ሰው፣“ግልብ” የሚል ጸሐፊ የአእምሮው ጤንነት ያጠራጥራል።
በወሪሳ አንድምታዊ ትርጓሜው ላይ አብነት በቁጣ ተሞልቶ (passionate ሆኖ) የጻፈው ይመስለኛል። ይኸ ለሀገሩ እና ለወገኑ ካለው ጥልቅ ፍቅርና መቆርቆር የመነጨ ስሜት ሊሆን ይችላል። እዚህ ላይ ቅሬታ ያለው አስተያየት ሰጪ ተጠየቃዊነት ያለው ጭምት ወይም አካዳሚያዊ አስተያየት ቢሰጥ እደሰታለሁ እንጂ አልከፋም። እሱ የተጠቀመውን ጽንሰሐሳባዊ ማእቀፍም በአካዳሚያዊ ባህል ፉርሽ የሚያደርግ ጽሑፍ ባነብ የምበሳጭ ሰው አይደለሁም። ከአፍላጦን ጀምሮ እስከ ሆኪንግ ድረስ ያልተሳሳተ ምሁር የለም። ፍፁምነት ቢኖር ኖሮ የዓለማችን ሳይንስና ዕውቀት እንደ ድንጋይ ቆሞ ይመለክ ነበር። ሳይንስ ዘወትር እየታረመ እና እየጠራ የሚጓዝ ትሁት መንገደኛ ነው።
ኅሊና
አስተያየት ሰጪው፣ በመጣጥፋቸው በአንቀጽ 11 ላይ ጸሐፊውን “እሱ ምን ያድርግ ንቁውና ስውሩ ኅሊናው ተምታቶበት!!” ብለውታል። ይህን ሐረግ እንደመሰለኝ አብነት “ክሱት እና ስውር ዕውቀት” ከሚለው ላይ አንሻፈው ወስደውት ነው። ይኸ ሐሳብ በሥነልቦና የጥናት ዘርፍ ውስጥ በስፋት የታወቀ ነው። ልዩነቱ አብነት የተጠቀመው አማርኛ ብቻ ነው። ክሱት የተገለጠ እና ፊት ለፊት ያለ ማለት ነው። ስውር ደግሞ ኅቡእ ወይም የተደበቀ ማለት ነው። አእምሮአችን የሚደብቃቸው ብዙ ሐሳቦች አሉ። በሀገራችን ብሂልም፣ “ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” ይባላል።  ሆድ ያባውን ማለት ሆድ የደበቀውን ማለት ነው። ሆድ ያባው አእምሮ የደበቀው ማለት ነው። ሆድ ወይም ልብ የተሰኙ ቃላት አእምሮ ማለትም ይሆናሉ። ሰዎች በመጠጥ ሞቅታ ብቻ ሳይሆን በህልም ወይም ደግሞ በፈጠራ ጽሑፋቸው ውስጥ ሆዳቸው ያባውን የ“ስውሩን አእምሮ” ድብቅ ነገር ያወጣሉ ተብሎ ይታመናል። ይህንን በነፍሮይድ፣ በነካርል ያንግ እና ከነሱ በቀጠሉ ምርምሮች ውስጥ ማንበብ ይቻላል። ይሄ ነገር በሌላ አገላለጽ በሁለተኛ ቋንቋ ችሎታችን ፍዝ (passive) እና ንቁ (active) ቃል የምንለው ነው። አብነት ይህን ዕውቀት ነው የጠቀሰው። አንድ ሰው ፍዝ እና ንቁ ቃላቱ ተደባለቁበት ተብሎ አይወቀስም። ተስፋ የተባሉት ጸሐፊ፤ “ንቁና ሥውሩ ሕሊናው ተምታቶበት” በሚል ሐረግ ዘለፋ የመሰላቸውን ጽፈዋል። ይኸ ስድብ አይደለም፤ አሳዛኝ ስህተት ብቻ ነው።
እንስሳት ከሞላ ጎደል የሚመሩት በደመነፍስ ነው። የሰው ልጅ በደመነፍስም በኅሊናም ይመራል። ኅሊና ሐሳብ ማለት ነው። ሰውን ከእንስሳ የሚለየው ክፉና ደጉን፣ ጎጂና ጠቃሚውን ደመነፍሳዊ ባልሆነ መንገድ መለየት ስለሚችል ነው። በደመነፍስ ውስጥ ነፃ ፈቃድ የለም። ደመነፍስ “ፕሮግራምድ” የሆነ “ኦቶማቲክ” ባህሪ ነው፤ ማሰብን አይፈልግም። ከምድር ላይ ፍጡሮች በተለየ ነፃ ፍቃድ ያለው የሰው ልጅ ብቻ ነው። ነፃ ፈቃድ በሌላ ቋንቋ ኅሊና ማለት ነው።
ተስፋ የተባሉት ጸሐፊ፤ “ኅሊና” የሚለውን ቃል ምንነት አልተረዱትም። አንድን ሰው፣ “ኅሊና የለህም?” የምንለው፣ “ሰው አይደለህምን? አታመዛዝንም? ክፉና ደጉን አታውቅምን?” ለማለት ነው። መጣጥፈኛው በእርጋታ የጻፉ አይመስለኝም፤ ወይም ደግሞ ጥራዝ ነጠቅና ዕውቀት-አጠር እንዳይሆኑ እሰጋለሁ።
ጀግና እና ጀግንነት
ዲሞክራሲ ህዝባዊ-አገዛዝ ነው፤በዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ሥልጣን ከህዝብ ይመነጫል። ህዝብ መሪውን ወይም አስተዳዳሪውን ይመርጣል እንጂ መሪ ህዝቡን አይመርጥም። ንግሥና በዘር፣ በጉልበትና በብልጠት ካልሆነ በህዝብ ምርጫ አይደረግም። አብነት የጻፈው መሪውን የሚመርጥ ህዝብ ጀግና ነው ብሎ ነው።
አስተያየት ሰጪው ግን አብነት የጻፈበትን ዐውድ አላስተዋሉትም። እሳቸው ያደረጉት ነገር (ትህትና ቢጎድለውም) በቀቀናዊ ነው ለማለት እገደዳለሁ። ኢትዮጵያ እና ጀግና የሚሉትን ቃላት እንደሰሙ፣ “በላይ ዘለቀ፣ ዘርዓይ ድረስ፣ አብዲሳ አጋ ...” እያሉ መዘርዘር ጀመሩ። ጸሐፊው እነዚህን ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች፣ ጀግኖች አይደሉም አላለም። አብነት የታሪክ ትምህርቱን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነው። ተሳዳቢው ጸሐፊ ግን በአመለካከት ውዥንብር ውስጥ ገብተዋል። የሁለተኛ ክፍል መስኮት ላይ ለሦስት ሰዓት እንደተቀመጠች በቀቀን፣ ኢትዮጵያ እና ጀግና የሚሉትን ቃላት ሲሰሙ የደመነፍስ የስም ጥሪ አካሒደዋል። እኚህ ሰው አሳ ባዩ ቁጥር፣ “አሳ በጊል ይተነፍሳል” እያሉ ደጋግመው የሚጮሁ ዓይነት ናቸው። ወይም ደግሞ ፈረንጅ ባዩ ቁጥር፣ “The quick brown fox jumped over the lazy dog” እያሉ በደመነፍስ የሚዘምሩ በቀቀናዊ ሰው እንዳይሆኑ እሰጋለሁ።
አምባገነን
በወሪሳ ውስጥ የሰፈሩ ሰውና የልቦለዱ ተራኪ አምበርብር የተባሉትን ገፀባህሪ ሊገላገሉ ይፈልጋሉ።  ይህንን ነው አብነት ከአምባገነናዊ “ተውሳክ” ገዥዎች ጋር ያመሳሰለው። ለዚህ ምሳሌ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን እና መንግስቱን ጠቅሷል። ተሳዳቢው ጸሐፊ ግን፣ “[አብነት] ኢህአዴግ ከሌለ ኢትዮጵያ ብትንትኗ ይወጣል የሚለውን የአሁን ንቅዘት ሊጠቅስልን አልደፈረም።” ብለዋል።  ይኸ “በቀቀናዊ ድንጋሬ” ነው። አንደኛ ነገር የቀረ ምሳሌ አለ ተብሎ አንድ የኂስ አቅራቢ አይዘለፍም። ሁለተኛ ነገር ተሳዳቢው ያመጡት ምሳሌ አብነት ከጻፈው ሐሳብ ጋራ አይገናኝም። ይኸ ተራና “መርዘኛ” አካሔድ ይመስላል። አብነት ኢህአዴግን አልተሳደበምና አስተዋይ አይደለም ብሎ መጻፍ ምን ማለት ነው? ምን ዓይነት መዘላበድ ነው! አንባቢንስ አብዝቶ መናቅ አይሆንም? እኔ ዕድሉ ያልገጠማቸው አንባቢያን የአብነትን የኂስ ጹሑፍ እንዲያነቡት ከመጋበዝ ሌላ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ነገር ከመጻፍ ብገታ ይሻለኛል።
ማንበብና መጻፍ
ተሳዳቢው ጽሑፍ አቅራቢ አንብቦ መረዳትም ሆነ ጽፎ ማስረዳት የተሳናቸው ይመስሉኛል። ልቅም አድርገው ማንበብ እና ጥርት አድርገው መጻፍ አልቻሉም። ኂስ አቅራቢው  ግን ከሞላ ጎደል በቅጡ አንብቦ የተደራጀ ጽሑፍ እንደጻፈ ኅሊና ያለው አንባቢ ሁሉ መፍረድ ይችላል። አብነት የአጻጻፍ ቴክኒኮችን በቅጡ የተማረ እና ያነበበ ሰው ነው። በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛ የሚጽፈው ነገር የበሳል ድርሰትን መርህ የተከተለ እንደሆነ አውቃለሁ። አብነት የበሳል ድርሰት ተማሪ እና ጸሐፊም ብቻ አይደለም። በሳል ድርሰትን (Advanced Composition) በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ደጋግሞ እንዳስተማረ አውቃለሁ። ተሳዳቢው ጸሐፊ ከዚህ መማር ሲገባቸው የድንጋሬ ጦራቸውን ሰብቀው መፎከራቸው ትዝብት ላይ እንዳይጥላቸው እፈራለሁ።
የሐሳብ ልዩነት
ትችት አቅራቢው፣ በመጣጥፋቸው መጨረሻ ላይ፣ “ዘላለማዊነት ለሐሳብ ልዩነት እያልኩ ሳምንት እቀጥላለሁ” የሚል ቃል አስፍረዋል። እሳቸው ያቀረቡት የሐሳብ ልዩነት አይደለም። ጥሩ የኂስ ሙከራ ያደረገን ጸሐፊ ጉድለቱን ነቅሶ በማውጣት  ጠንካራ ጎንም ካለው ያንን በማሳየት ወደተሻለ ጎዳና መምራት ወይም አማራጭ ሐሳብ ማራመድ እንጂ አፍ እንዳመጣ መሳደብ የሐሳብ ልዩነት አይባልም። የሐሳብ ልዩነት ካላቸው “እኔ ደግሞ ይህንን ነገር የማየው በዚህ አቅጣጫ ነው” ብለው ይጽፉ ነበር። አስቀድመው የኂስ ጽሑፉን በቅጡ አላነበቡትም፤ አልገባቸውም። ይህን አድርገው የኂስ ጽሑፉን ሙሉ በሙሉ እንኳን ፉርሽ ቢያደርጉት አደንቃቸው ነበር። ሐሳብን እያሳከሩ ዘለፋ መጻፍ የሐሳብ ልዩነት አይባልም።
ኂስ እና ስድብ ይለያያሉ። ስድብ የባለጌ ነው፤ኂስ የጨዋ ነው። አብነት የጻፈውን ጥልቅ ኂሳዊ ንባብ ብዙ አንባቢዎች እንደወደዱት ለመረዳት ችያለሁ። የአብነት ኂሳዊ ንባብ ችግር እና ድክመት ካለው በሥነጽሑፍ እና በተቀራራቢ የዕውቀት ዘርፎች ላይ በቂ ልምድ እና ዕውቀት ያላቸው ጸሐፊዎች አስተያየት እንዲሰጡበት ማድረግም የሚቻል ይመስለኛል።
ጥበብ በኢትዮጵያ
አብነት ባለፉት የጭለማ ዘመናችን ከጥበብ ርቀን ነበር ብሎ የጻፈውን ተቺው በሌላ ተርጉመውታል። ኢትዮጵያ ውስጥ የጠላ ኢንዱስትሪ ነበር፤ ስለዚህም ኢትዮጵያውያን ጥበበኞች ነበሩ ይሉናል። ጸሐፊው “አላዋቂ ሳሚ ----” ዓይነት ሆነውብኛል።
አብነት በሌሎች መጻሕፍቱና በየጊዜውም በሰጣቸው ቃለመጠይቆች ኢትዮጵያ አስትሮኖሚን ጨምሮ የብዙ ጥበባት ጀማሪ ነች እያለ በማስረጃ አስደግፎ ተናግሯል። ተቺው ያቀረቡት ሐሳብ ግን ለሰሚው ግራ ነው። “በኃላፊነት ይጠጡ” እንደሚባለው “በኃላፊነት ይጻፉ” የሚል ማስታወሻም ቢኖረን ሳይጠቅም አይቀርም።
“አማርኛ ነክ” ምንድን ነው?
የመጣጥፉ አቅራቢ ገና ሲጀምሩ፤ “ስለ አማርኛ ነክ ጉዳዮች እና ስለ ኢትዮጵያ ኮከብ የሚል ሁለቱን መጻህፍቶቹን አይቼለታለሁ።” በማለት ጽፈዋል። ዐረፍተ ነገሩ በመዋቅሩም ሆነ በይዘቱ የተጣረሰ ነው። “ስለ አማርኛ ነክ ጉዳዮች” ምን ማለት ነው? ያሳዝናል።  አብነት የጻፋቸው መጻሕፍት የኢትዮጵያ ኮከብ፣ ፍካሬ ኢትዮጵያ፣ የቋንቋ መሠረታዊያን፣ ሳይኪ እና ኪዩፒድ እና አሁን በቅርቡ ደግሞ ጠቢባን ምን አሉ የተባሉ ናቸው። “ስለ አማርኛ ነክ ጉዳዮች” የጻፈው መጽሐፍ የለም። ባለመጣጥፉ ሊሉ የፈለጉት ምናልባት የቋንቋ መሠረታዊያን የሚለውን ከሆነ ይኸም መጽሐፍ “አማርኛ ነክ” አይደለም። መጽሐፉ የቋንቋን ሳይንስ መሠረታዊ እሳቤዎች የሚያብራራ እንጂ “አማርኛ ነክ” መጽሐፍ አይደለም። የመጣጥፉ አቅራቢ ዐረፍተ ነገር ሳያጠሩ ለትችት ባይቸኩሉ ደግ ነበር።
አላዋቂ ሐኪም ታማሚን የመግደል መብት የለውም። አላዋቂ መሀንዲስም “ዲሞክራሲያዊ መብቴ ነው” በሚል ህዝብን አደጋ ላይ የሚጥል ድልድይ ሲገነባ ዝም መባል የለበትም። ተረቱም ከመጠምጠም መማር ይቅደም ይላል። ተቺው “አይቼለታለሁ” የሚል ቋንቋም ተጠቅመዋል። ይኸ የጠራ ሐሳብ አይደለም። ይዩልኝ ብሎ የለመናቸው ያስመስላል።
የሁለት ሺህ ዘመን ታሪክ
መጣጥፈኛው ተስፋ፤ ኂሳዊ ንባብ ያቀረበውን ጸሐፊ፣ የሁለት ሺህ ዘመንን ታሪክ በአንድ ዐረፍተ ነገር የሚጨፈልቅ “ፈራጅ” ብለውታል። ይኸም ማስተዋል የጎደለው ግርድፍ አስተያየት ነው። ጸሐፊው የኢትዮጵያ ኮከብ በተባለው መጽሐፉ የዓለምን ታሪክ በየሁለት ሺህ ዘመን ከፍሎ አቅርቦልናል። በኂሳዊ ብእሮጉ ያመለከተው የኢትዮጵያ የሁለት ሺህ ዓመት ታሪክ ከዚያ ጋር የተገናኘ ነው። እሱ የጭለማ ዘመን ብሎታል። ከዚያ በፊት ባለው ዘመን ኢትዮጵያ ታላቅ እንደነበረች የታሪክ ጸሐፍትን እየጠቀሰ ተናግሯል። እንዲያውም በቅርቡ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በወጣ “ምጽአተ ኢትዮጵያ” በተባለው ብእሮጉ፤የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ከገናናው የአትላንቲስ ዘመን ጋር አገናኝቶታል። አብነት የኢትዮጵያን የ26 ሺህ ዓመት ታሪክ የዳሰሰበት “ውዳሴ ኢትዮጵያ” የተባለ መጽሐፍ እንዳለውም አውቃለሁ።
ማጠቃለያ
አብነት ስሜ የጻፈው የብእርወግ ነው። ተስፋ በላይነህ የጻፉት ግን የብእርወሬ ይመስላል። ተስፋ የተከበሩ እና አስተዋይ ሰው ሊሆኑ ይችላሉ፤ ይሄ መጣጥፋቸው ግን በቅጡ የተደራጀ አይደለም፤ የችኮላ ሥራ ሳይሆን አይቀርም። ሊናገሩ የፈለጉትን ጥርት ባለ ቋንቋ አልገልጹትም። በመጣጥፋቸው ውስጥ የሚያስከፋ ስድብ እንዳይኖር አልተጠነቀቁም። ይሄ ነገር ደግሞ ምላሽ ያስፈልገዋል ብዬ ስላመንኩ ይህን ጽፌአለሁ።

Published in ጥበብ
Saturday, 19 September 2015 09:36

ርቀትና ቅርበት ሊላተሙ ነበር

  የበዕውቀቱ ስዩም ግጥሞች
                
    የአማርኛን ግጥም አንዳንድ ወጣት ብዕሮች አስቀይመውታል። ቤት ለመታ፣ ከጫፉ ዜማ ላንጠባጠበ ስንኝ  -ሳይመሰጡ- ወረቀታቸውን ይደቅናሉ። ፍም እኮ ጤዛ ያሰገዋል፤ ብዙዎቹ ፍምና ጤዛ ቀርቶ፥ ስጋት ሳይሆን ፍዝነትና የፈሰሰን ውሃ መርጠዋል። ይነበባል፤ ይረሳል። ጥቂት ወጣቶች ግን ብርቅ ናቸው፤ አንዱ በዕውቀቱ ስዩም ነው። ግጥሞቹ ገለልተኛ አይደሉም፤ ይናደፋሉ። ልማድ የረበበት ፍዝነት ስለሚኮላ፥ ፈርጥ ግጥሙ ያውከናል፤ በደምሳሳው በውብ ቋንቋና በሚያባንን ምስል ይመሰጣል። ያሳተመው ሶስት የግጥም መጻሕፍት እንቁ ናቸው። “ኗሪ አልባ ጐጆዎች” ፥ “የሳት ዳር ሀሳቦች” እና እነዚህን ሳይበትን አዳዲስ ግጥሞች የታከለበት በአንድ ጥራዝ የታተመው “ስብስብ ግጥሞች” ናቸው። ይህ 127 ግጥሞች የታመቀበት ልዩ መጽሐፍ የሚመጥነው ሂሳዊ ግምገማና ጥናት ሳይገላልጠው መጋረዱ አግባብ አይደለም። (ነገ እሁድ የበዕውቀቱ ስብስብ ግጥሞች በወመዘክር ለግምገማ ይቀርባል) በአመዛኙ አጭርና እምቅ ቅኔ ናቸው። “ግጥም ... ለእኛ ፍለጋ (ኀሠሣ) መኾኑን እናምናለን፤ ያልተንዛዛ ልቅሶ፥ ያልቆረፈደ ተርብ፥ ያልተዝረከረከ ፍልስፍና መኾኑን እናምናለን፤ ለገጣሚ ብቻ የተሰጠ መክሊት እንደ ኾነም እናምናለን።” [ገፅ፥2] ቢልም በዕውቀቱ ስብስቡ አንድ በአማርኛ ሥነግጥም የግሉን ድንበር ያሰመረ ብርቅ ብዕር መከሰቱን ይመሰክራል።
የነገን ውይይት ላለመሻማት ያክል፥ ስብስብ ግጥሞቹን በመዝለል፥ ከጥቂት አመታት በፊት በበኩር ስራው“ኗሪ አልባ ጐጆዎች” የተቀነበቡ ግጥሞች ብቻ ለማንበብ በሞከርኩት እንደመም።  
ህልም አለህ ይላሉ
ራዕይ ያዘለ
ኮከብ አለህ አሉ
ትንቢት የታደለ
ህልምህን ንገረኝ
ኮከብህን አሳየኝ
ተርጉሜው ልፅናና
መነሻዬን ልወቅ መድረሻዬን ላጥና
ባንተ ዕጣ ፈንታ ውስጥ ርስት አለኝና:።
<ጋርዩሽ> የመሰለ የበዕውቀቱ ግጥም ግልፅ ባይሆንም ደብዛዛ አይደለም። ግጥም እድሜ እንዳይሰበስብ የሚያመነምነው ግልፅነቱ ነው፤ በአንድ ንባብ ያበቃለታል። አጠራጣሪነት - ambiguity - የፍች አሻሚነት ግን ግጥምን ያከርመዋል። “ህልም አለህ ይላሉ” አንድምታው እንደ ገጠመኛችንና ዕውቀታችን ዥንጉርጉር ነው። ይህ ግጥም አንድ ጠገጉ የነሳርተር ህልውናነትን -existentialism- ይፃረራል። ሰው ለእድገቱም፥ ለውድቀቱም እራሱ ብቻ ነው ተጠያቂ የተባለው፥ ሰው የሌላው ሁኔታ ሊጐዳውም ሊበጀውም አቅም አለው፥ የመሰለ እሳቦት ተላልፎበታል። ተራ ሰው አይደለም የኛን ህይወት የሚገዛ፤ ራዕይና ኮከብ ዕጣ ፈንታው የሆነው ነው መነሻና መድረሻችንን የሚለካልን። አፃፃፉ ዝርው ልሙጥ ሳይሆን ቅኔያዊ ነው፤ ዜማም አለው። ሲቋጭ አንድ ትርፍ ቃል ሊያጣርስበት ነበር:: “መነሻዬን ልወቅ መድረሻዬን ላጥና / ባንተ ዕጣ ፈንታ ውስጥ ርስት አለኝና ”ውስጥ  የሚለው ቃል ዜማውን ቧጭሮታል:: ቀለም ተቆጥሮ ሳይሆን ሲደመጥ ያስታውቃል:: ይህን እሳቦት - በሌላ ግለሰብ ዕጣችን መወሰኑ - “የኔ ነፃ ፈቃድ ” በሚለው ውብ አጭር ግጥሙ ተስተጋብቷል። የ “ጋርዩሽ”  ግን ህልም፥ ኮከብ፥ ርስት ... ምን ይወክላሉ ? አጠራጣሪነቱን አስፍቶታል::
ከሃምሳ ሰባት ግጥሞቹ እንደ “ጋርዩሽ” ለአጠራጣሪነት፥ ለድርብርብነት የሚያደሉ አምስት ብቻ ናቸው:: “ዘመን ሲታደስ”፥ “የመፃተኛው ዝማሬ” ፥ “መሽቷል አትበል” ፥ “የመፃተኛው አገር” እና “ህይወትና ሞት” ናቸው። ሌሎቹ ግልፅና ቶሎ ይደርሱናል፤ አናክልባቸውም።
ብዙ ግጥሞቹ -የበዕውቀቱም መለያ- የምናውቀውን፣ የለመድነውን በስንኞች ያነቃቃና ድንገት መድረሻው ላይ አቅጣጫውን በሀይል ሰብሮ ወይም መጨረሻ ላይ ተቀልብሶ ያባንነናል:: ለአብነት “ጣይና አንሺ” ይነበባል::
ደሞዙን ቢጥል
አንስተው ጠጡበት
ባርኔጣውን ቢጥል
ወስደው ደመቁበት
ከዘራውን ቢጥል
ተመረከዙበት
በሄደበት ሁሉ
እየተከተሉ
በጣለው ሲያጌጡ
በጣለው ሲያተርፉ
ራሱን ሲጥል ግን
አይተውት አለፉ::
ሲኖርህ ጭፍራ አለህ፤ ስታጣ ግን ብቻህን ትቀራለህ የመሰለ ሀቅ ከመለመዱ ብዛት ሰለፈዘዘ ለግጥም አይመችም። የማይመቸው ለተራ ገጣሚ ነው። በዕውቀቱ ግን ፊልም እንቅስቃሴ ይከተላል፤ ካሜራ ከስፍራ ስፍራ ያስዘልላል። አራት አምስት ነገሮች ሲወድቁ ሌላው አፈፍ ሲያደርጋቸው ዘና ብለን ሳለ፥ የዋሁ ሰው አዱኛ ከድታው ድኅነት ሲጥለው እንባንናለን። የሰውን ክህደት ከመዘርዘር ተቃራኒውን ተግባር - በቸርነቱ - መሰላል አበጅቶለት ነው ወጥተን፥ ወጥተን የመጨረሻ መርገጫ ምስማር ተተክሎበታል። ይወጋጋል፥ መድማትም አለ።
ይህን የመሰለ የሚቀለበሱ ግጥሞች አሉት። ይሄድ ይሄድና አዘናግቶ እንግዳ ሀቅ ይደቅናል። ይህ አፃፃፍ ለባለቅኔው ይመቸዋል። ሃሌታ ንባባችንን ይናደፋል። ያደፈጠው ከመጨረሻ ስንኞች ተስፈንጥሮ ከወጣ በኋላ ግን፥ በሁለተኛ ንባብ ጥፍሩ ለመሰባበር ይዳዳል። ባነበብነው ግጥም  “ራሱን ሲጥል ግን / አይተውት አለፉ”  የመሰለ ግርምት፥ እንደተጫረ ክብሪት እንደገና አይጫርም፤ ዳግም የማይጫሩ ግጥሞች አሉት። “ለብርሃኖች”፥ “የሁለት ዘመን ሰዎች”፥ “አዳምና ሚስቱ”፥ “አንሺና ወዳቂ”፥ “አዳምና ጥበቡ” ... የመሳሰሉ። ሁለት ጊዜ ባይቀጣጠሉም ለአዲስ አድማጭ ሲነበቡ፣ በውይይት መሃል ሲታወሱ ወይም የሆነን ፅሁፍ ሲያደምቁ ማነቃቂያ ናቸው። መቀልበስ ግን አደጋ አለው፤ ተደምመን ስናነበው ድንገት ይፈዛል:: ሰው ለምን መነመነ፥ ሞገገ ? ስንፍና፥ እጦት፥ በደል ... ሳይሆን ሲቀለብሰው የሌላው “ቦርጭ” ሆነ፤ ግጥሙን አዘመመው። “የሁለት ዘመን ሰዎች” መቀልበሱ አረገበው።
በዕውቀቱ ሲይዝለት ግጥም መቀልበሱን ከጥልቅ እሳቦት፥ ከጥያቄ ቀስቃሽ አጠራጣሪነት ያጠላልፈዋል። ሲጠላለፍ ተደጋግሞ ይነበባል፤ ከግርምታው ልቆ ይንዠረገጋል። አንድ ያልታተመ ግጥሙ ትዝ ይለኛል።
አልወጣም ተራራ ደመናን ልዳብሰ
ቀስተ ደመናውን ቁልቁል ልቀለብስ
አልዋስም እኔ
ካቡነ ተክሌ ክንፍ
ከያዕቆብ መሰላል፤
እኔ መውጣት ሳስብ
ሰማዩ ዝቅ ይላል::
ምስልና ዜማው ይመስጣል። የተክልዬ ገድል፥ የያዕቆብ ህልም ከአእምሯችን ይፍታታል። አልገባኝም፥ ምን ማለቱ ነው ? ... ተራራ፥ ደመና፥ ዝቅ የሚለው ሰማይ ከምናባችን የምናክለውን አንዳች ሀቅ፥ ሥነተረት ወይም አስተውሎት ይማጠናሉ። እንደ አረሆም የሚዘፈን፥ እንደ እንባ የሚፈልቅ መደናገርም አለ። ግጥም ሲረቅ እንዲህ ነውና።
“ፍቅረኛዬ የተኛችበት አንሶላ ሲራገፍ፥ ነጫጭ ቢራቢሮ ይራገፋሉ” ይል ነበር አንድ ገጣሚ። በዕውቀቱም ስለ ፍቅር ተቀኝቷል።
ለሱ
ሰው ብቻ አይደለችም
ጠፈር ናት ባካሏ
መሬት ናት በነፍሷ
ዕድሜ ልኩን ቢሮጥ
አያመልጥም ከሷ::
ይህ ውብ አጭር ግጥም የፍቅርን ፍፁም ወረራ ያደምቃል። ፍቅር ወጥመድ ሆነ። “ዕድሜ ልኩን ቢሮጥ/ አያመልጥም ከሷ”  የሚለው ስንኝ ግጥሙን ቅኔያዊ ውበት ቀብቶ ከመስነፍ አስጣለው:: በዕውቀቱ ፍልስፍናን አልያም የተመስጦ አስተውሎቱን የሚመጥን የፍቅር ግጥሞች የሉትም:: የተሻለው “የይቅርታ ማህላይ” ነው።
ማነው የፈለገኝ?
በማይነጋ ሌሊት
በማይመሽ ቀን መሐል
ተዘርሬ ስገኝ
ከተውሺኝ በኋላ ርቃን ቀርታ ነፍሴ
እንኳንስ ከሰው አውድ ተነጠልሁ ከራሴ::
እንዲህ የተጐዳ አፍቃሪ አለ፤ ሀዘኑ የበረታ። ሀዘኑ ስለበዛ አይወቀስም። እውስጡ የተደበቀ ዕልልታ አገኝ ብሎ ነው ሀዘኑን ለማንጠፍ የሚተጋው። ግጥሙ ተወሳስቦ ሥር ሊሰድ ሲል ተበተነ። ምናልባት የገጣሚው ብዕር እመድረሻው መጠማዘዝ፥ ማስደንገጥ ስለለመደ ይሆናል ያመፀበት። “ጽንፍ የለሽ ይቅርታን ውሰጂ ከከንፈሬ”  ከሰው አውድና ከራሱ ለተነጠለ አይመጥንም። እርግጥ ለቀዘቀዘ ኩርፍያ ከንፈር አስታራቂ ነው፤ ለጥላቻ ቅጣት። እናቱ የምታክል የቤት አከራይ፥ እቅፍ አድርጋ ከንፈሩን ብትስመው፥ ተከራይ ባይተዋርነት ይሰመዋል:: ይህ ጥላቻ፥ ያኛው ፍቅር። “ብታውቂ” ፥ “ሹክሹክታ” ፥  “ፍካሬ ዕውነት” እና “ይስጥሽ”  ወደ ተመስጦ አጐንብሰው ይነሳሉ፤ አጐንብሰው ሊቀሩ ሲችሉ።  
በዕውቀቱ ብዙ ሰው እንደ ሀቅ የተቀበለውን አዟዙሮ በተሻለ ሀቅ ይተከዋል፤ ያክልበታል። ለልጁ ስም አቤልን ሲመርጥ ሀይልን የተጠየፈ ማኅበረሰብ፥ ጥላቻው የምር ነው። ቃየልም እንደ አቤል ሰለባ ነው፤ አጥፊው ፈጣሪ ነው የመሰለ የማይደፈር ሀቅ ገጣሚው ቀስቅሷል፤ “ቃየል ጠጠር ነበር ለባለወንጭፉ” ።  ፈላስፋው ድዮጋን በጠራራ ፀሐይ ፋኖስ ይዞ ሰው መፈለጉ ሲደንቀን፥ በዕውቀቱ ግን  “በከንቱ ይጮሃል ሰው የት አለ ብሎ / ሰው ሰራሹን ፀሐይ በጣቱ አንጥልጥሎ” በማለት እንደ ፈላስፋው ረቀቀ። ሰው የፈጠረውን ፋኖስ አንጠልጥሎ፥ ሰው የመፈለግን አባዜ ተሳልቆበታል። ያሬድ ተስፋ እንዳይቆርጥ፥ ትል ዛፍ ለመውጣት ያደረገውን ጥረት አያቶቻችን ተርከውልናል። በዕውቀቱ ግን የትሉን ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን፥ የምትበላውን ቅጠል የልብ ትርታዋን በማጤን አከለበት። ድልም ሽንፈትም ባንድ ላይ ተላወሰ። ርዕሱ እንኳን ቅኔያዊ ሆነ “ከዛፍ የተቀሠመ ዜማ”።
ባለቅኔው ቋንቋው ይጥማል፤ ምስሎቹ አይሰለቹም፤ አዲስነት የተለመደውን ያነቃል። ስርዓተ ነጥብ ግን ለመጠበቅ ደንታ የለውም። መሸፈት ከመረጠ፥ የግድ ስርአት መከተል የለበትም።  ግን ስንኝ፥ ሲከተለው ስንኝ፥ ሲከተለው ስንኝ ... ይከማቹና አንድ ልዩ ውበት ይነፈጋል:: በአንጓና በአንጓ መካከል የሚኖር ክፍተት፣ የተዘለሉ ባዶ መስመሮች የሚፈጥሩት ቅኔያዊ ዝምታ - poetic silence - ይነፈጋሉ። ነጠላ፥ ድርብ ሰረዝ፥ አራት ነጥብ... ይህ ለቅፅበት መቆም - pause - ለአንባቢ ምናብ እንደ ፌርማታ የሚወርድና የሚወጣ ስሜት ይሁን እሳቦት ያስተላልፋሉ። ይህን ቅኔያዊ ዝምታ ለማብራራት ሌላ ወረቀት ያስፈልጋል:: ለጊዜው የ “ፍካሬ ህልውናን”  ቅኔያዊ ዝምታ፥ ድንበር አልባ ከሆኑትና ፀጥታን ካላቆሩት ከ “ጥጡና ፈታይዋ”፥ “መልክዓ እናት” እና “ታዕምረኛ አባ” ጋር ማነፃፀር በቂ ነው።  
በሰማንያ ስምንት አመቷ ያረፈችው በሥነጽሑፍ የኖቤል ተሸላሚ ፖላንዳዊት ባለቅኔ -Szymborska - “ቁጥር ፍለጋ ተራ ከሚጠብቁ ዜሮዎች ይልቅ፥ ብቻቸውን የቀሩ ነፃ ዜሮዎች እመርጣለሁ::” ብላ ነበር። ዜሮና ዜሮ መደርደር። በዕውቀቱ ግን ለዜሮ በተመስጦ ቁጥር ይፈልጋል። ግጥሞቹ በአመዛኙ እሳቦት ዋልታ ዙርያ ነው የሚጠነጠኑት። አስተውሎትና ግንዛቤ ያደነድናቸዋል:: ዳሩ ግን ጥልቅ ስሜት እንባችንን፥ ልቦናችንን፥ ሰብዓዊነታችንን ... በዚህም ምክንያት ደጋግመን እየቆየን የምንመለስበት ግጥም ስብስቡ ውስጥ እምብዛም አይነበብም።  “ዕረፍቴን አስሳለሁ”  በመጠኑም ቢሆን እሳቦቱ በስሜት ርሷል። ሎሬት ፀጋዬ “ማነው ምንትስ”  ወይም “ትዝታ” ፥ ደበበ ስይፉ ስለእናት ስለአባት የተቀኘውን፥ ደረጀ በላይነህ “ጠቢቡ” በማለት ለደበበ ሠይፉ የዘረፈውን ያነበበ ይህ ጥልቅ ሰብዓዊነት ከበዕውቀቱ ስዮም ይጠበቃል። ጭራሽ በዕውቀቱ ግጥሞቹ ከእናት በስተቀር ሴትን እንደ ከሃዲ፥ አረጋዊያን ደግሞ ለወጣቱ የማይጥሙ፥ ባዶ ስልቻ አቀባይ አድርጐ ስለተቀኘባቸው የሚያጠያይቅ ነው። ግጥሞቹ ለአእምሮ እንጂ ለልቦና ስለማይቀርቡ የተቀኘባቸው ግጥሞች ውይይትን ይጋብዛሉ። ተልጦ ተልጦ የተፃፈ የተላገ ነው። ስንጐርስ በእጃችንና በአፋችን መካከል ያለውን ርቀት ማን ይለካል? ጠቃሚ ርቀት አለ፤ ከንቱም ርቀት አለ። የበዕውቀቱ ግጥሞች የተላጉ ቢሆንም፤ ከጥልቅ ስሜት ቢሸሹም፥ ጠቃሚ ርቀትን አሳይተውናል። እንድያውም ርቀትና ቅርበት የተላተሙ እስኪመስለን ድረስ - በተለይም በአጫጭር ግጥሞቹ። እንግሊዝ ከጃፓኖች የተዋሱት ሃይኮ Haiku የሚባል የአፃፃፍ ስልት አለ። ሰለሞን ደሬሳ “ዘበተ እልፊቱ” ወለሎታት ውስጥ ገፅ 93 መውጫ አበጅቷል። <ሃይኩ በ17ኛው መቶ የበሰለ ሶስት መስመሮች በ 5 7 5 (ባማርኛ አፃፃፍ) ፊደላት (በላቲን አፃፃፍ) ሲይላብላት የሚደረደር የጃፓን ወለሎ። ሃይኩ አብዛኛውን ጊዜ የሚነሳው ተፈጥሮን ከማትኰር ሲሆን መድረሻው የወለልቱው የውስጥ ስሜት ነው።> ይህን የውስጥ ስሜት፥ ጭፍግግነት መቧጠጥ የበዕውቀቱ ሁለተኛው መለያው ነው:: የደበበ “ዘመዴን ስስመው” የመሰለ ሃይኩ። (ደበበም በዕውቀቱም ወደ አራት ስንኞች ቢያደሉም የግጥሙ መንፈስና ጥልቀት ነው ከሃይኩ የሚያፋትጋቸው፥ ቀለም ሳይቆጠር) ለማብራራት ያክል አንድ በእንግሊዘኛ የተፃፈ ሃይኩ ብዙም ካልታወቀ ገጣሚ - Thomas Williams - ትዝ ይለኛል።
Dark blue butterfly
Blending quietly into
The gathering storm
----------------------------------
ደማቅ ሰማያዊ ቢራቢሮ
ያለኮሽታ ሊዋኸድ ነው
መሰብሰብ የጀመረን ማዕበል ሰብሮ።  
ጥበብ አንዳንዴ በንፅፅር ሊገለጥ ይችላል። የዚህን ምስር የሚያህል ግጥም፥ ድንበሩን ሊደረምስ የሚችል ንቁ የሆነ ውስጣዊ ንፅፅር አለ። ከማያበቃው የባህር ዝምታ፣ ከማዕበል በፊት ከረጋው ዝምታ ጋር ተነፃፀረ። ጥቃቅን ከሆነው የቢራቢሮ ክንፍ ነው ገጣሚው የጀመረው። ይህን የሃይኩን ቅፅበት - the Haiku moment - እንደ ሰማይ ስባሪ አጐላው። የሳሙኤል ጆንሰንን ሀቅ አስታወሰን፤ “ምንም ጉዳይ ለሱ ኢምንት አይደለም፤ ትንሿን ነገር በጥልቅ አስተዋይነት ላጤነ።”  በአንክሮ ማጤን የበዕውቀቱ ስዩም አንድ ባህርይ ነው።
እኛኮ ለዘመን
ክንፎች አይደለንም
ሰንኮፍ ነን ለገላው
በታደሰ ቁጥር የምንቀር ከኋላው ።
ዘመንና ሰንኮፍ ተነፃፀረ። ዘመን ሲታደስ፥ ዕልልታ በየሰው ልብ ሲያጐነቁል፥ በበዕውቀቱ ሃይኩ ርቀትና ቅርበት ተላትመውበታል። ለዘመን ብጉንጅ ነን፤ ወሸላ፥ ከነሰንኮፉ የሚወጣ ቁስል።
አገር ድንኳን ትሁን
ጠቅልዬ የማዝላት
ስከፋ እንድነቅላት
ስረጋ እንድተክላት።
ይህ ሃይኩ የነፃነት ራዕይ ነው፤ የዕውነት መገቻ። ሀገሩን ለሚቸረችር ሳይሆን፥ ያለእሷ መኖር ለሚመዘምዘው። የኑረዲን ዒሳን “ዒሻራን” ያስታውሰናል። “አንድ ትልቅ አገር፣ ከትንሽ መንደር ላይ / ተጣጥፎ ተኝቶ / ሲጨናነቅ አየሁ፣ ለእግሮቹ መዘርጊያ / ሽራፊ ቦታ አጥቶ ።” ለበዕውቀቱ ሀገር ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስ፥ ለኑረዲን ሀገር ከአንድ ስፍራ ተኝቶ የረጋ፥ ሁለቱም ግን የነፃነት -ግለሰባዊ ቢሆንም- ጉጉት ነው የወረራቸው።
በነፍሴ ሰማይ ላይ
ቢሰርቅ ጣምራ ፀሐይ
አንዱን ጋርጃለሁ
ሌላው ደምቆ እንዲታይ።
መንታ ብርሃን ሳይሆን ለነፍስ እምነትና ክህደት፥ ህይወትና ሞት ጥንድ ብርሃኖች ሆነው አንዱ መጋረድ አለበት ሌላው እንዲጐላ። ሁለት የወለደች ድሃ እናት አንዱን ትምህርት ቤት ትልካለች፤ አንዱን እቤት ታስቀራለች። ውስጡ ሲቦረቦር ጭላንጭሉ የሚያጓጓ ሃይኩ።
Poetry is writing in borrowed time የሚል አንብብያለሁ። ቀንና ሌሊት አልበቃ ብሎ ነው ሥነግጥምን ለመጻፍ ጊዜን መዋስ ያለብን ? እንግሊዛዊ ዝነኛ ገጣሚ Philip Larkin ሰናፍጭ የምታክል ግጥሙ ታሳስበናለች። “ሲነጋ  የተረዳሁት ጉዳይ አለ / ጊዜ ልክ መጥረቢያ፥ እንጨት ውስጥ ሲሰነቀር፥ የሚያሰማው ወለለት ነው።” ይላል። መጥረቢያ እንጨት ውስጥ ሲሰነቀር ከመፈለጡ በፊት ያለው እፍታ፥ የትንፋሽ ጊዜ ሳይሰወር በገጣሚው ከተነጠቀ መቀኘቱ ድንቅ ይሆናል። አለበለዝያ  በየአረቄ ቤት የሚፈሰውን ጊዜ መዋስ ያስፈልጋል። የበዕውቀቱ አጫጭር ግጥሞች ማገዶ ሲሰነጠቅ የፈጀውን አፍታ፥ ጥቂት ፈርጥ ደቂቃዎች ላይ የፈሉ ናቸው።
በደምሳሳው የበዕውቀቱ የተወሰኑ ግጥሞች ቢናደፉም ለአጭር ጊዜ ነው። ለሁለተኛ ለሶስተኛ ዙር አቅም ያንሳቸዋል። ሃይኩ ወይም ሩባዕያት ግጥሞቹ ግን ትንፋሻችን እስኪያልቅ እናነባቸዋለን። ለማነፃፀር ያክል፥ ዕውቅ አሜሪካዊት ደራሲ Sylvia Plath ጭንቅላቷን የጋዝ ምድጃ ውስጥ አግብታ ራሷን ትገድላለች። አስቀድሞ ህክምና ላይ እያለች፥ የሥነልቦና ጠቢብ “እናትሽን የመጥላት ስሜትሽን በግጥም ተንፍሽው” ሲላት ትደሰት ነበር። የበዕውቀቱ ግጥሞች እንደ የስልቪያ ጥላቻ -ያልሰከኑ ግን ያልፈነዱ- ናቸው። ወጐቹን የሚያነብ ሩቅ ሊዘልቅ እንደሚችል ይገነዘባል። ሌላ ማነፃፀሪያ ደግሞ እናቷን እጅጉን የምትጠላ ወጣት ነበረች። ቤንዚን አርከፍክፋ ክብሪት በራሷ ላይ ለኮሰች። እየተቀጣጠለች እቤት ውስጥ እናቷን አፈላለገች። ሥጋ አጥንቷ የሚነድ ማገዶ ሆና፥ እናቷ ላይ ተጠመጠመች፤ አብረው ፍም ሆነው ወደቁ። ለጣቂና በጉጉት የሚጠበቀው በዕውቀቱ ግን የነገውን አቅጣጫ ማን ያውቃል ባይ ነውና፣ ያልታተመ ግን አደባባይ የተነበበ  ብርቅ ግጥሙ መቆያ ይሁነን።
ያንን ገለባ ልብ
ከድጅ የወደቀው፣
አድራሻህ ወዴት ነው
ብለህ አትጠይቀው፤
የነገው ነፋስ ነው
መንገዱን የሚያውቀው።
***ድኅረ ንባብ*** በዕውቀቱ በበኩር ስራው -“ኗሪ አልባ ጐጆዎች”- አንድ ብርቅ ገጣሚ መከሰቱን አብስሯል። ዛሬ በ“ስብስብ ግጥሞቹ”  እና ገና ባልታተሙት ቅኔዎቹ እጅጉን መርቀቁን፥ ጥበባዊ ብስለቱ ይመስክራል። እንዴት? ጥያቄው ዘመነኛ ግጥሞቹን ለሂሳዊ ግምገማ በማጋለጥ መመለስ ይኖርበታል፤ ሀቁ በዕውቀቱ ድንቅና የተካነ ገጣሚ መሆኑ ነው።

Published in ጥበብ

    አዲሱን 2008 አመት ከተቀበልን እነሆ አንድ ሳምንት ሊቆጠር ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ወቅት ያለፈውን አመት ከንውኖቻችንን የምንፈትሽበት ለመጪው አዲስ አመት ደግሞ እቅድ አቅደን ተግባራዊ ለማድረግ የምንቀሳቀስበት ግዜ ነው፡፡ ለመሆኑ የእርስዎ የ2008 ዓ/ም አመታዊ እቅድ ምንድነው? ለዚህ እትም እቅዶቻቸውን እንዲያካፍሉን የጋበዝናቸው ሰዎች የሚከተለውን ብለዋል፡፡
የመጀመሪያዋ ተናጋሪ እራሔል ስጦት ትባላለች፡፡ እራሔል በመስከረም/2008 መጨረሻው ላይ ትወልዳለች፡፡ እቅዱዋን እንደሚከተለው አካፍላናለች፡፡
“... አሁን ያረገዝኩት ሁለተኛ ልጄን ነው፡፡ የምወልደው በ2008/መስከረም መጨረሻው ላይ ይሆናል፡፡ ያው 2008/ዓ/ም መጀመሪያው ላይ ነው፡፡ ከዛ በኋላ እንግዲህ ልጅ ማሳደግ ነው የሚሆነው፡፡ ሁለት ልጅ ይሆናሉ ሁለት ልጅ ሲሆን ደግሞ ጫናው ይጨምራል ብዬ አስባለሁኝ ያንን በሚገባ ለመወጣት አሁን እየተዘጋጀሁ ነው፡፡ ስለዚህ የ2008 እቅዴ ልጆቼን ማሳደግ ነው ማለት ነው፡፡ የመጀመሪያ ልጄ ትምህርት ቤት አልገባችም ፡፡ገና ሁለት አመቷ ነው ህፃናት መቆያ ውስጥ ነው ያለችው፡፡..
ጥ፡ ብዙ ግዜ እንደሚታየው በዚህ እድሜ ልጆች ተደራርበው ሲወለዱ ትልልቆቹ ይቀናሉ፡፡ ለመሆኑ አንቺ ይህንን እንዴት ልታስተናግጂው ተዘጋጅተሻል?
“...ብዙ ዝግጅቶችን እያደረኩኝ ነው እንዳትቀና የእሷን ነገር እንዳትጠቀም አዳዲስ ነገሮችን እንድትለምድ ከመኝታ ጀምሮ እያስተካከልኩ ነው፡፡ ብዙዎቹ አዲስ ልጅ ተወልዶ የእነሱን እቃ ሲጠቀሙ አይወዱም የሚል ነገር አለ፡፡ እና ከዚህ የተነሳ ቀድማ እንድትዘጋጅ ብዙ ነገር እያደረኩኝ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ያለውን ደግሞ በሂደት ማየት ነው፡፡”
ጥ፡ ስለዚህ 2008 እቅዱ ልጅ ማሳደግ ብቻ ሳይሆን ይህንንም ጉዳይ በብቃት መወጣት ይሆናል እና ስታስቢው ከባድ አይመስልሽም?  
“...በጣም ከባድ ይመስለኛል ብዙ ጓደኞቼም ጋር ያለውን ነገር ሳይ ሌሎች ሰዎችም የሚሉትንም     ስሰማ ይሄ ነገር በቤት ውስጥ ከባዱ ነገር ይመስለኛል፡፡ አዲስ የሚወለዱት ልጆች በጣም ብዙ     እንክብካቤ ስለሚፈልጉ ብዙ ግዜሽን የምትሰጭው ለእነሱ ነው፡፡ በዚህ መሀል ትልልቆቹ በጣም ነው የሚቀኑት ስሜታቸውም ሊጎዳ ይችላል እና የእነሱን ስሜት በማይጎዳ መልኩ ለእነሱም     በቂ ግዜ እየሰጠሸ የተመጣጠነ ነገር መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ እኔም በዚህ እረገድ እየተዘጋጀሁበት ነው፡፡”
ጥ፡ ይህንን በሚመለከት ከባለቤትሽ ጋር ትመካከራላችሁ?
“...አዎ እኔ እንደውም አሁን ከዚህ በኋላ ትኩረቴ በሙሉ አዲስ ወደሚወለደው ልጅ ስለሚሆን መኝታ ክፍል ስቀይርላት እራሱ ከአባቷ ጋር የበለጠ እንድትቀራረብ ሆኗል በፊት ከእኛ ጋር ነበር የምትተኛው አሁን ግን የእራሷ ክፍል ከአባቷ ጋር እንድትተኛ አድርጌያለሁ፡፡ ስለዚህ አሁን ሌላ ክፍል ማደሩንም ተለማምዳለች ከአባቷ ጋር ያላት ቅርርብም ከበፊቱ     ጨምሯል፡፡”
ጥ፡ ይህ እንግዲህ በቀላሉ የሚታይ ነገር አይደለም እና በሁለት ሺህ ስምንት እንዲህ ለሚወልዱ ሁሉ ምን መልእክት ታስተላልፊያለሽ?
“...ያው በጣም ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን አዲስ ለሚወለደው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለትልልቆቹም ትኩረት መስጠት እና በተቻለን መጠን እነሱንም ማስደሰት እንዳለብን እመክራለሁ፡፡ በተጨማሪም ደግሞ በቅናት ተነሳስተው ትንንሾቹንም እንዳይጎዱ በጣም በጥንቃቄ መከታተል አለብን፡፡ የእራሳቸው ወንድም ወይም እህት ስለሆኑ ምንም አያደርጓቸውም በሚል መዘናጋት የለብንም፡፡ በጣም ስለሚቀኑ ልጆችም ስለሆኑ ብዙ ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ...የምንሰማውም ብዙ ነገር አለ፡፡ ስለዚህ ሁለት ሺህ ስምንት አከታትለው ለሚወልዱ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እመክራለሁ፡፡..”
---------------///--------------
“...በትረማሪያም እባላለሁ፡፡ያው በቅርብ ግዜ ነው ቤተሰብ የመሰረትኩት አንድ ልጅ አለችኝ ስለዚህ በእሷ ማቆም አልፈልግም፡፡ ምናልባትም በአዲሱ አመት እንደ እግዚያብሄር ፍቃድ ለእሷ     ወንድም ወይም እህት መጨመር እፈልጋለሁ ከባለቤቴም ጋር ውይይት እያደረግን ነው ስለዚህ በቀጣዩ አመት አንድ ውሳኔ ላይ እንደርሳለን ብዬ አስባለሁ እና ይሄ አንዱ እቅዴ ነው፡፡ ከዛ በተጨማሪ ደግሞ የባለቤቴን የእራሴን እንዲሁም የልጄን ጤንነት በመንከባከብ ለማሳለፍ አስባለሁ፡፡”
ጥ፡ እንዴት ነው ባለቤትህን የምትንከባከባት? በተለይ በእርግዝናዋ ወቅት እንዴት ነበር የምታግዛት?
“...እቤት ውስጥ እኔ ማንኛውንም ስራ እሰራለሁ በእኛ መካከል የወንድ የሴት የሚባል ስራ የለም፡፡ ሁለታችንም ስራ ነው የምንውለው ከስራ ስንመለስ በአብዛኛው እንደውም እኔ ነኝ የምሰራው ማለት እችላለሁ ምክንያቱም በእርግዝና ግዜ ይደክማታል ስለዚህ እረፍት ታደርጋለች፡፡ እቤት ውስጥ የምታግዘን ሌላ ልጅ አለች ከእሷ ተረዳድተን ብዙውን ስራ እንሸፍናለን፡፡ ልብስ በማጠብ ቢሆን፣ ምግብ በማብሰል ቢሆን፣ የሚገዛዙ ነገሮችን በመግዛት ቢሆን ሁሉንም ነገር ለመሸፈን ጥረት አደርጋለሁ እና ብዙም ጫና አልፈጥርባትም፡፡ የሚቀረኝ እንጀራ መጋገር ብቻ ነው እንጂ ሽንኩርት ከትፌ አቁላልቼ በሚገባ ወጥ እሰራለሁ፡፡”
ጥ፡ የስነተዋልዶ ጤናን በመጠበቁስ እረገድ በ2008/ ምን እቅድ አለህ?
“...ስነተዋልዶ ጤናን በተመለከተ ያው እንግዲህ እራሴን እጠብቃለሁ፡፡ ከምንም ነገር ጋር ንክኪ የለኝም እራሴን ጠብቄ ነው የምኖረው እና በዚህ እረገድ ችግር ይገጥመኛል ብዬ አላስብም፡፡”
ጥ፡ አንዳንድ ግዜ ተፈጥሮ በእራሱ የሚያመጣቸው የተለያዩ የጤና ችግሮች አሉ እና በዚህ ዙሪያስ ምን     አስበሀል?
“...እሱን ያው በተለያየ ግዜ የስነተዋልዶ ጤናን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ያለሁበትን ሁኔታ በቀጠሮ እየሄድኩ እታያለሁ፡፡ ለባለቤቴም ክትትል የሚያደርግላት ባለሙያ አለ ለልጄም እንደዛው፡፡ ይሄ መለመድ ያለበት ነገር ነው፡፡ ቅንጦት ወይም ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ብቻ የሚያደርጉት ነገር አይደለም፡፡ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ ነው እንደውም   የሀገራችን ብሂል...በተለያየ ግዜ የማናቃቸው ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ ምንም አይነት የህመም ምልክት ሳያሳዩ ስር ሰደው ትልቅ ችግር የሚሆኑ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ሴቶች ሁልግዜ የወር አበባ ከመምጣቱ በፊት እና መጥቶ ከሄደ በሁዋላ ጡታቸውን በእራሳቸው እጅ እንዲመረምሩ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሴቶች ይህንን ልምድ ማድረግ አለባቸው፡፡ እና ሌሎችም የጤና ሁኔታዎቻችንን ነቅተን መከታተል ይኖርብናል፡፡ በተመሳሳይ በደማችን ውስጥ ያለው ስኳር በምን ሁኔታ? መቼ? መጠኑ ከፍ እንዳለ ላናውቀው እንችላለን ስለዚህ ምልክቶቹ እስኪታዩ መጠበቅ የለብንም፡፡ ሌላ የአይን ህመም ሊሆን ይችላል፣ የደምግፊት ወይም ሌሎች በሽታዎች ሊሆኑ ይችላሉ ባላወቅነው ሁኔታ በጤናችን ላይ ችግር ሊያደርሱብን ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በተለያየ ግዜ በአመት አንዴ ወይም ሁሌ ፕሮግራም አድርገን የጤናችንን ሁኔታ መከታተል ተገቢ ነው፡፡ ሰዎች ምናልባት ከሀብት ጋር አንዳንዶችም ከቅንጦት ጋር ሊያይዙት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ይሄ ቅንጦት ወይም ሲመቸን የምናደርገው ነገር አይደለም፡፡ በአመት ለምንበላው ወይም ለምንለብሰው እንደምንጨነቀው ሁሉ ቅድመ ምርመራ ማድረግንም ልናስብበት ይገባል፡፡..
                                                                         
     “... አዲሱ ደረሰ እባላለሁ፡፡”
ጥ፡ አዲሱ... እንዴት ነው እጅህ ላይ ቀለበት አላይም አላገባህም እንዴ?
መ፡ አዎ አላገባሁም
ጥ፡ ይቆያል ወይስ እንዴት ነው?
መ፡ “....(ሳቅ)..... የሚቆይ ይመስለኛል፡፡ በአሁኑ ሰአት ሙሉ ትኩረቴን ያደረኩት በስራዬ እና   በትምህርቴ ላይ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ግን ዋናው ምክንያት እሱ አይደለም፡፡ ያው መጋባት የሚያገባ ሰው መኖርን ይጠይቃል እና ዋናው ምክንያት እሱ ይመስለኛል፡፡ ግን መጀመሪያ ላይ እንደነገርኩሽ ምናልባትም ለመጪዎቹ ሶስት ዓመታት ሙሉ ትኩረቴ በስራዬ እና በትምህርቴ ላይ እንዲሆን ስለምፈልግም ነው፡፡”
ጥ፡ ትዳርን በ2008/ አላሰብከውም፡፡ እናስ መቼ ይሆናል ብለህ ታስባለህ?
መ፡ “አሁን ባለፈው ግንቦት ወር ላይ ነው ሰላሳኛ አመቴን ያከበርኩት ስለዚህ የሴት ጓደኛ ለመያዝ ብቻ ሳይሆን ትዳር ለመመስረት የምችልበት እድሜ ላይ ነው ያለሁት እና ሀሳቡ አለኝ፡፡ ብዙ ሰዎች በሀያዎቹ መጀመሪያ እድሜ ላይ ሆነው ትዳር እየመሰረቱ ባለበት ግዜ ላይ ሰላሳ አመት ላይ ሆኖ ጓደኛ ስለመያዝ ማውራት በእራሱ የሆነ ጫና ይፈጥራል፡፡ እና የትዳሩን ነገር በእቅድ ይዞ ቢያንስ የፍቅር ግንኙነት መጀመር በሚለው ሀሳብ ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ፡፡ ከላይ እንዳልኩት የመጀመሪያው ምክንያት ያው ገና ከጅምሩ ከፍተኛ የሆነ መግባባት የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ ከተጋባን በኋላ እየተወያየን ነገሮችን እናስተካክላለን የሚባለው ነገር ለእኔ አይዋጥልኝም፡፡ ምክንያቱም ለእኔ ትዳር ወደኋላ የማልመለስበት መንገድ ነው፡፡ ከተጋቡም በኋላ ሌላ አማራጭ አለ የሚባለው ለእኔ አይታየኝም ስለዚህ ሁልግዜም ጥንቃቄ እና ትኩረት ያስፈልገዋል ባይ ነኝ እና ለዚህም ይመስለኛል እስካሁን የቆየሁት...ይሄ አመለካከቴ ወደ ፍራቻ ተቀይሮ እንደሆነም አላወኩም (...ሳቅ)”
ጥ፡ ከጋብቻውም ውጪ ቢሆን ለአዲሱ አመት ምን አቅደሀል?
መ፡ “ከምንም በላይ በህይወታችን ለሚፈጠሩ አጋጣሚዎች አእምሮአችንን ክፍት አድርገን መጠበቅ አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ በሁለት ሺህ ስምንት ማግባት አለባችሁ ባይባልም እንኳን ቢያንስ መንገዱን ለመክፈት ከለሌሎች ሰዎች ጋር በተለይም ከሴቶች ጋር መቀራረብ ወይም ግልፅ ውይይት ማድረግ ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ፡፡.. ----


Published in ላንተና ላንቺ

    ከስድስት አመታት በላይ በጠፈር ላይ የቆየቺው ሉናር ሪኮኔሳንስ ኦርቢተር የተባለች የናሳ የጠፈር መንኮራኩር፣ ይሄን አጀብ የሚያሰኝ ዜና ይፋ አድርጋለች - ጨረቃ እያደር መጠኗ እያነሰና እየተኮማተረች መሄዷን ቀጥላለች፡፡
የጠፈር መንኮራኩሯ በተገጠመላት የረቀቀ ካሜራ ያነሳቻቸው ፎቶግራፎች፣ የጨረቃ መጠን ከዚህ በፊት ከነበረው እያነሰ መምጣቱን አመላክተዋል ሲል የዘገበው ሮይተርስ ነው፡፡
የጨረቃን ሶስት አራተኛ ክፍል መሸፈን በቻለው በዚህ ካሜራ የተነሱት ጥራት ያላቸው ፎቶግራፎች፣ በጨረቃ ላይ ከ3ሺህ በላይ ሰፋፊ ስርጉድ ስፍራዎች እንዳሉ የጠቆሙ ሲሆን ከአምስት አመታት በፊት የተነሱ ፎቶግራፎች ግን፣ በጨረቃ ላይ የነበሩት ስርጉድ ስፍራዎች 81 ብቻ እንደነበሩና የቁጥራቸው መብዛት ከጨረቃ መጠን እየቀነሰ መምጣት ጋር የተያያዘ ነው መባሉን ዘገባው አስታውቋል፡፡
የናሳ የጠፈር ተመራማሪዎች የጨረቃ መጠን እያነሰ የመጣው ከመሬት  ስበት ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ተጽዕኖ ነው ማለታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በራሷ በጨረቃ ውስጥ የሚታዩ የሙቀት መጠን ለውጦችም ለመጠኗ መቀነስ አስተዋጽኦ አበርክቷል ሲሉ መናገራቸውን አክሎ ገልጧል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

    ከስድስት አመታት በፊት ለተካሄደው የ2009 የኖቤል ሽልማት የአመቱ ተሸላሚዎችን የመረጠውን የተቋሙ የሰላም ኮሚቴ በጸሃፊነት የመሩት ጌር ሉንደስታድ፣የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ለኖቤል የሰላም ተሸላሚነት በመምረጣቸው መጸጸታቸውን እንደገለጹ ቢቢሲ ዘገበ፡፡በወቅቱ ኮሚቴው ኦባማን ለኖቤል የሰላም ሽልማት በዕጩነት ሲመርጣቸው፣ ለዚህ ትልቅ ሽልማት የሚያበቃ ጉልህ ስራ አልሰሩም በሚል ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበር ያስታወሱት ሉንደስታድ፣ሽልማቱ መነቃቃትን ፈጥሮላቸው ተጨባጭ ስራ ይሰራሉ ብሎ በማመኑ ኦባማን ተሸላሚ እንዳደረጋቸው ሰሞኑን ለንባብ ባበቁት የግለ ታሪክ መጽሃፋቸው ገልጸዋል፡፡ ኦባማ ግን ኮሚቴው እንደጠበቀው ለአለም ሰላም ይህ ነው የሚባል ጉልህ ተግባር አልፈጸሙም ያሉት ሉንደስታድ፣ በወቅቱ ኦባማን የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ለማድረግ በነበራቸው ተሳትፎ መጸጸታቸውን በግልጽ ጽፈዋል፡፡ኦባማ የ2009 የዓለም የኖቤል የሰላም ተሸላሚ መሆናቸውን በሰሙበት ቅጽበት ነገሩን ለማመን መቸገራቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ብዙዎቹ የኦባማ ደጋፊዎችም የሽልማቱን ዜና የተሳሳተ ሳይሆን አይቀርም ብለው ተጠራጥረውት እንደነበር ጠቁሟል፡፡
ጌር ሉንደስታድ እ.ኤ.አ ከ1990 እስከ 2015 መጀመሪያ በኖቤል የሽልማት ድርጅት የሰላም ኮሚቴ ጸሃፊ በመሆን ማገልገላቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ተሸላሚዎችን በመምረጡ ሂደት ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደነበራቸው ጠቁሟል፡፡ የዘንድሮው የአለም የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ከ20 ቀናት በኋላ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ
Page 4 of 16