ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር እሰራለሁ ያለው ከአንጀቱ ነው ከአንገቱ?
በመጪው ጉባኤ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ባይፈታስ? (ሂስ ያደርጋላ!)
ተቃዋሚዎች አንዳንዴ በኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ይጋበዙ እንጂ!!


ኢህአዴግ በመቐለ ከተማ ባደረገው 10ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ የግንባሩ  ሊቀመንበር ሆነው በድጋሚ የተመረጡት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ (በድጋሚ ያልተመረጠውን ንገሩኝ?!) ከተቃዋሚዎች ጋር በጋራ ለመስራት እንደሚፈልጉ ጠቅሰው  ለተቃዋሚዎች ልባዊ የሚመስል ጥሪ ሲያስተላልፉ ሰማሁ፡፡ አንዳንዶች ግን ከአንጀት ይሁን ከአንገት ገና አልታወቀም ይላሉ፡፡ በእርግጥ ምክንያት አላቸው፡፡
ለምሳሌ አንዳንድ ተቃዋሚዎች----- በ2002 ምርጫ ማግስት፣ኢህአዴግ እንዲሁ ተመሳሳይ ቃል ገብቶ እንዳልፈጸመው በማስታወስ፣ያሁኑም ከቀድሞው አይለይም በማለት ነገሩን ዋዛ ፈዛዛ ያደረጉት ይመስላሉ፡፡ (በነሱም መፍረድ ይቸግራል!) ቀኝ ዘመም የሆኑ የፖለቲካ ተንታኞችም፤ኢህአዴግ በየ5 ዓመቱ እንዲህች ያለች “ፉገራ” ለምዷል ሲሉ በነገር ወጋ አድርገውታል፡፡ (የሂስ ሃንግኦቨር ላይ ስለሆነ ግን አይሰማቸውም!)
ኢህአዴግ የ2002 ምርጫን በ96. ምናምን ፐርሰንት ባሸነፈ ማግስት፤ “ተቃዋሚዎች ፓርላማ ባይገቡም (ያኔ እንኳን አንድ ለመድኀኒት ያህል ገብቶ ነበር!) በአገሪቱ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉበት መድረክ ይፈጠራል” ሲል አውራው ፓርቲ በአደባባይ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ “ባለፉት 5 ዓመታት ግን እንኳንስ በአገሪቱ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ ዕድል ሊሰጠን ቀርቶ ህገ መንግስታዊ መብታችን ተጥሶ፣ህልውናችን ለአደጋ የተጋለጠበት ጊዜ ነበር; በማለት አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ገዢውን ፓርቲ አምርረው ይወቅሳሉ (አምርረው ይረግማሉ ቢባል ይቀላል!)
በአጭር ቋንቋ “እንኳን በአገሪቱ ጉዳዮች ሊያሳትፈን በዓይኑ እንኳን ሊያየን አይወድም ነበር” ይላሉ፤ተቃዋሚ ፓርቲዎች፡፡ እናም በኢህአዴግ 10ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ ጠ/ሚኒስትሩ ያስተላለፉትን ጥሪ “ፌዝ” ነው ባይ ናቸው፡፡ (ነቄ ነን እንደማለትም ይመስላል!) እስቲ ለማንኛውም ጠ/ሚኒስትሩ በጉባኤው መጠናቀቂያ ላይ ያሉትን ሙሉ ቃል እንመልከተው፡-
“ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ከኢህአዴግ ጋር ለመስራት በፈቃዳችሁ ልክ፣ ኢህአዴግ ከእናንተ ጋር ተባብሮ በሚያስማሙን ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት፣ በሚያለያዩን ጉዳዮች ላይ ለመተጋገል የወሰነ በመሆኑ፣ በዚህ አጋጣሚ መላው የአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለአገራችን የህዳሴ ጉዞ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ጥሪዬን ለማቅረብ እወዳለሁ”
እንግዲህ እንደምታዩት… ጥሪው በሸጋ ቋንቋ የቀረበ፣በትህትና ቅላጼ የተቃኘ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ተቃዋሚዎች የኢህአዴግን ባህሪ በልተነዋል እያሉ ነው (ዳግም አንሸወድም ነው ነገሩ!) እኔ ደግሞ አሁን የምሩን ቢሆንስ? ስል ጥርጣሬ ገባኝ፡፡ (ቋንቋ መግባቢያ መሆኑ ቀረ?!)
እኔ የምለው ግን ኢህአዴግ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ራሱን ሲገመግምና በራሱ ላይ ሂስ ሲያደርግ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጉዳይ አንስቶ ይሆን? (አንስቶም ከሆነ አልነገረንም ብዬ ነው!) እርግጥ ነው ------ የመልካም አስተዳደርንንና የኪራይ ሰብሳቢነትን ችግር ያህል ቅድሚያና ትኩረት ይሰጠዋል ብለን አንጠብቅም፡፡ ግን መነሳቱ የግድ ነው (ኢህአዴግ---የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መሰረት እንዲይዝ እተጋለሁ ሲል ሰምቼ እኮ ነው!) … እናላችሁ ተቃዋሚዎች በየጊዜው የሚያሰሙትን ምሬትና እሮሮ------ የሚያወጡትን መግለጫ------ ራሱ ሲወስዳቸው ከነበሩት እርምጃዎች (ምላሾች) አንፃር ገምግሞ “ትክክል ነኝ… በጀመርኩት እቀጥላለሁ” አሊያም “በተቃዋሚ አያያዝ ላይ የማሻሽለው ነገር አለኝ” ብሎ ሂስ ማድረግ ያለበት ይመስለናል (እኛ ከኢህአዴግ ባናውቅም!)
በነገራችን ላይ… የተቃዋሚዎች እሮሮና ምሬት እኮ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ለምን አልተሳተፍንም የሚል አይደለም፡፡ (እዬዬ ሲዳላ ነው አሉ!) ይልቁንም በአመራሮቻችንና በአባላቶቻችን ላይ ከፍተኛ ወከባና ድብደባ… እስርና ግድያ እየተፈፀመብን ነው የሚል ውንጀላ ነው፡፡ ይሄን ተከትሎ ደግሞ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት … መንግስትን/ኢህአዴግን በመብትና ነጻነት አፈና እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ደጋግመው በመውቀስ በዓለም ፊት እያሳጡት ነው፡፡ (የኒዮሊበራል አቀንቃኝ መሆናቸው አልጠፋኝም!) አነሰም በዛም የአገር ገጽታን እንደሚያጠለሽም ኢህአዴግ አይስተውም፡፡ (አሁንም ቢሆን ለግምገማ አልረፈደም!)
በነገራችን ላይ በቅርቡም እኮ (በግንቦቱ ምርጫ ማግስት ማለቴ ነው!) ኢህአዴግ አንድ ቃል ገብቶ አልፈጸመም፡፡ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አወያያለሁ ብሎ ነበር፡፡ (እሱም አያርመውም ልበል?!) እስካሁን ግን ውይይቱ ስለመካሄዱ የሰማነው ነገር የለም (መቼም በምስጢር አይካሄድም አይደል?!) ይህቺ የማወያየት ነገር እኮ በቅርቡ በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድም ቅሬታ አስነስታ ነበር፡፡ (“ኢህአዴግ የማሳተፍ ተነሳሽነት ይጎድለዋል” ልበል?!) እናላችሁ … የጠ/ሚኒስትሩ የፖሊሲ አማካሪ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ፤ ከንግዱ ህብረተሰብ ጋር ባደረጉት ግልፅነትና ድፍረት የተንፀባረቀበት የውይይት መድረክ ላይ፤ “እውነት እንደ አጋር የምትቆጥሩን ከሆነ፣ ለምን በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ ላይ ለውይይት አልተጋበዝንም?” ሲሉ ጠየቁ (የፈለገ ተሸምድዶ ቢገባ የማይመለስ ቦንብ ጥያቄ እኮ ነው!)
በራሱ ቋንቋ ልጠቀምና ኢህአዴግ በንግዱ ህብረተሰብ ላይ ያለውን ብዥታ በጊዜ አጥርቶ በአጋርነት አብሮ ለመስራት ካልቆረጠ፣የሚፈለገውን ውጤት ያስመዘግባል የሚል እምነት የለኝም (በሱ አለመቁረጥ የምንጎዳው ደግሞ እኛ ነን!) በተመሳሳይ ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ በሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ያለውን ብዥታም ማጥራት ይኖርበታል፡፡ (ብዥታው ሲጠራ ብቻ ነው ጠ/ሚኒስትሩ ያሉት በጋራ የመስራት ነገር እውን የሚሆነው!)
አንዳንዴ የኢህአዴግ ነገር የገባኝ ሲመስለኝ ለራሴ እንዲህ እላለሁ፡፡ ነገርየው አግባብ ባይሆንም  እንኳን-----ተቃዋሚዎችን ጠጋ ብሎ፤“አገሪቷን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ እስከማሰልፍ አታካልቡኝ … ቀዝቀዝ በሉ!” ቢላቸውስ እላለሁ (የስልጣን ፉክክር ከልማት በኋላ እንደማለት ነው!)
ሌላው ደግሞ ምን መሰላችሁ ----- (በእርግጥ አንገብጋቢ ላይሆን ይችላል!) ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዳንዴ እንኳን በኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ቢጋበዙ ምናለበት? የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲና ሌሎች ወዳጅ የአፍሪካ ፓርቲዎች ይፏልሉበት የለም እንዴ? በዚህም ተባለ በዚያ ግን ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች ለአገሪቱ የተሻለ እድገት ለማምጣት እንደሚፎካከሩ ፓርቲዎች እንጂ እንደ ታሪካዊ ጠላት የሚተያዩበት ዘመን ማብቃት አለበት፡፡ በመተካካቱ ሂደትም “የጥላቻ ፖለቲካ በኛ ይብቃ” ብለው ለአዲሱ ትውልድ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ማውረስ አለባቸው፡፡ እንግዲህ----በኢህአዴግ 10ኛው ጠቅላላ ጉባኤ መጨረሻ ላይ ከተሰጡ መግለጫዎች እንደተረዳነው፤ በመልካም አስተዳደር ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት አልተቻለም፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት ልክ አጥቶ ተባብሷል፡፡ ሙስና ተንሰራፍቷል፡፡ አድርባይነት በዝቷል፡፡ ህዝቡ ትዕግስት በደርዘን የታደለ ሆኖ እንጂ በአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት በእጅጉ ተማሯል፡፡ እኔ እንደውም ትንሽ አብርጄው ነው እንጂ የኢህአዴግ አመራሮች ሲናገሩት እኮ በሥልጣን ላይ የሚቀጥሉ ሁሉ አይመስሉም (ራሳቸውን ሲገመግሙ ለነገ አይሉም!) … ለዚህም ነው ኢህአዴግ፤ “የመልካም አስተዳደር ጉዳይ በተለይ ግልፅነትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ የሞት ሽረት ትግል አደርግበታለሁ” ሲል ያስታወቀው፡፡ ይሄ ግን ለእንደኔ ያለው አገሩን ወዳድ ተራ ተርታ ዜጋ ብዙም አይገባም፡፡ (የችግሩን ጥልቀትና ስፋት አያሳይማ!) በዚያ ላይ በአብዛኛዎቹ የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤዎች ማጠናቀቂያ ላይ ተመሳሳይ መግለጫዎችን ስንሰማ ነው የኖርነው፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት … አድርባይነት … ሙሰኝነት … የአመለካከት ---- ወዘተ ችግሮች ብርቃችን አይደሉም፡፡ ጥያቄው----ችግሮቹ ምን ያህል ሥር ሰደዱ? የሚለው ነው፡፡
ለዚህ መላ ይሆነን ዘንድም የስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ቢያግዘን ሸጋ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገታችንን በቁጥር እያሰላ ባለሁለት አሃዝ ዕድገት ተመዝግቧል እንደሚለን ሁሉ … (ቁጥር በግድ አስለምዶን የለ!) የመልካም አስተዳደር ጉድለቱን … የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሩን መጠን…. የሙስናውን ጥልቀትና ስፋት … የአድርባይነቱን ሁኔታ …. ዲሞክራሲን በማሳደግ ይሁን በማቀጨጭ የተገኘውን ለውጥ … አስልቶ ወይ ለክቶ በፐርሰንት ይንገረን፡፡ (ለወሬ እንኳን አልተመቸንም እኮ ነው!)
ከምሬ እኮ ነው … ቆይ ያለፈውን የመልካም አስተዳደር ጉድለት እንዴት ከዘንድሮው አነፃፅረን ልዩነቱን እንወቅ! አያችሁ----ሌላው ቢቀር የመልካም አስተዳደር ጉድለቱ ባለአንድ አሃዝ ነው ወይስ ባለሁለት የሚለውን ማወቅ እኮ ቀላል አይደለም፡፡ እኔ የምለው ግን --- በመልካም አስተዳደር ሥር ነቀል ለውጥ አልመጣም ነው የተባለው አይደል? (ሥርነቀሉ ይቅር --- ኢምንት ለውጥስ ተመዝግቧል?) ለማንኛውም ----- በቁጥር እንነጋገር እያልኩ ነው (ተጨባጭ ይሆንልናል እኮ!)
አንድ የመጨረሻ ሃሳብ ሰንዝሬ ወጌን ልቋጭ፡፡ ኢህአዴግ በራሱ ላይ በሚያደርገው ምህረት የለሽ ሂስ በእጅጉ አደንቀዋለሁ፡፡ ለሌላ ተቺ እንኳን ክፍተት ሳይሰጥ እኮ ነው ራሱን  የሚቀጠቅጠው፡፡ (የሂስ ተመክሮውን ለወዳጅ አገራት ማጋራት አለበት!) ችግሩ ግን ምን መሰላችሁ? ግምገም ብቻ ነው፡፡ ሂስ ብቻ፡፡ በጥፋቱ ተጠያቂ ተደርጎ የሚባረር ሹመኛ፣ሚኒስትር፣የፓርቲ አመራር ወዘተ----አይተን አናውቅም፡፡ (ያፈጠጡ ያገጠጡ ሙሰኞች ካልሆኑ በቀር!)
እኛ አገር ደግሞ አንድ ባለሥልጣን የሚመራው መ/ቤት የፈለገ ውድቀትና ኪሳራ ቢደርስበት (እንደሰለጠኑት አገራት) አልቻልኩም ብሎ በገዛ ፈቃዱ ከሃላፊነቱ አይለቅም፡፡ (ነውር ነው!) እናም ከእነ አለመቻሉ እየተገመገመ ይቀጥላል፡፡ ግለ ሂስ እስካደረገ ድረስ የከፋ እርምጃም አይወሰድበትም፡፡ ይልቁንም ሁሌ እንደምንሰማው ----- አመራሩ በጅምላ ኃጢያቱን ተሸክሞት ቁጭ ይላል፡፡ ራሴን ገምግሜአለሁ፣ጥፋቴን አምኛለሁ፣ከስህተቴ ተምሬ---ቀምሬ---በመጪዎቹ 5 ዓመታት አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት ተነስቼአለሁ ----- ይለናል ፊታችን ቆሞ፡፡ ማን? የኢህአዴግ አመራር! (ሙሉ አመራር ከሥልጣን ይውረድ አይባል?!)
ይሄ ሳይሆን አይቀርም ከዓመት ዓመት እየተጫወተብን ያለው ችግር፡፡
እናላችሁ-----በየጊዜው በኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ማብቂያ ላይ የምንሰማው የአቋም መግለጫ ወይም ውሳኔ ----- ፈረንጆቹ New year’s Resolution እንደሚሉት ዓይነት ነገር እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡ አንድ ሰው አዲስ ዓመት መጥቢያ ላይ ለራሱ የሚገባው የውሳኔ ቃል ሊባል ይችላል፡፡ ለምሳሌ በአዲሱ ዓመት ሲጋራ አቆማለሁ----መጠጥ የደረሰበት አልደርስም----ትምህርት እቀጥላለሁ---ወዘተ---ብሎ ለራሱ ቃል ይገባል፡፡ ነገር ግን በዓመቱ መጨረሻ ላይ ቃል ከገባው ውስጥ አንዱንም ላይፈጽም ይችላል፡፡ ሆኖም የሚጠይቀው------የሚወቅሰው ማንም የለም፡፡ ከህሊናው በቀር፡፡ ቃሉን ባለማክበሩም ቅጣት የለበትም፡፡ ለነገሩ ግለሰቡ ማድረግ ያለበትን ባለማድረጉ የሚጎዳው ራሱ ብቻ ነው፡፡ የኢህአዴግ ሪዞሉሽን ግን ይለያል፡፡ በ95 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ስም የሚደረግ ስለሆነ በአግባቡ ሳይፈጸም ሲቀር፣ ያ ሁሉ ህዝብ ለችግር ይዳረጋል፡፡ ለመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ለኪራይ ሰብሳቢነት፣አድርባይነት ለሚያስከትላቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች ወዘተ ይጋለጣል፡፡ በዚህም የተነሳ የኢህአዴግ ሪዞሉሽን ወይም ውሳኔ በልዩ ጥንቃቄ እንዲሁም ተጠያቂነትና ሃላፊነት በተሞላበት መልኩ ተፈጻሚ ሊሆን ይገባል፡፡
ለማንኛውም ግን ያሰብነውን ------ ያቀድነውን ------- የጀመርነውን ------ ሁሉ ያሳካልን፡፡ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

ዘረኝነት፣አክራሪነት፣ኪራይ ሰብሳቢነት፣አድርባይነት፣----አያውቅም

  አንድ ወዳጄ ያወጋኝን ላውጋላችሁ፡፡ ሳልጨምር ሳልቀንስ፡፡ በቅርቡ ቤተሰቡን ይዞ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ ነበር፡፡ በሰላም ነው፡፡ ለሽርሽር፤አየር ለመለወጥ!! (ችግሩ ግን አየር አናስለውጥ የሚሉ ኪራይ ሰብሳቢዎች በሽ ናቸው!) በነገራችን ላይ ይሄ ወዳጄ ለፍረጃ አይመችም፡፡ ለምን መሰላችሁ? ልማታዊም ኒዮሊበራልም አይደለም! በቃ ዝም ብሎ ሰው ነው!! (የፍረጃ አባዜ የተጠናወታቸው ምን ይዋጣቸው?!)  
እናላችሁ … ጥሮ ግሮ በሸመታት የቤት መኪናቸው፣ እሱና ውድ ባለቤቱ እንዲሁም ሁለት ህፃናት
ሴት ልጆቹ ከአዲስ አበባ ወጣ ብለው እየተጓዙ ነው፡፡ መኪናውን የምትሾፍረው ባለቤቱ ነበረች፡፡ (በሳኡዲ ዛሬም ሴቶች መኪና መንዳት አይፈቀድላቸውም አሉ!) ቤተሰቡ ትሪፑን ኢንጆይ አድርጎታል፡፡ እየሳቁና እየተጫወቱ ይጓዛሉ፡፡ አንድ የሆነ ቦታ ላይ ሲደርሱ ግን ትራፊክ ተጨናነቀና መጓዝ ሳይሆን መንፏቀቅ ተጀመረ፡፡ (እንደ ዲሞክራሲያችን!) በዚህ መሃል ታዲያ እንደ አንበሳ የሚያጓራ፣የመንግሥት ታርጋ የለጠፈ V8 ቶዮታ ድንገት ከኋላቸው ደርሶ፣ እንኩ ቅመሱ አላቸው፡፡ (V8 ለመንፏቀቅ አይሆንማ!) ግጭቱ ከባድ ባይሆንም  
ወዳጄና ቤተሰቡ ግን ቢያንስ ድንገተኛ በመሆኑ መደንገጣቸው አልቀረም፡፡ (ገጪው እንደ ደህና
ካልቾ ሊቆጥረው ይችላል!)  ወዳጄ እንደነገረኝ፤የመንግስት ታርጋ በለጠፈው V8 መኪና ውስጥ የነበሩት ሰውዬ፣ የአካባቢው
ባለሥልጣን ናቸው፡፡ (ልማታዊ ይሁኑ ኪራይ ሰብሳቢ እስካሁን አልተረጋገጠም!) መኪናው
የሚዘወረው ግን በሹፌር ነበር፡፡ (በደሞዙና በኑሮ ውድነቱ አሳቦ ኪራይ ሰብሳቢ ሊሆን እንደሚችል
ጠረጠርኩ!) ወዳጄ ከኋላ የደረሰበትን የግጭት ወይም የ“ካልቾ; መጠን ለመገምገም ያህል ከመኪናው ወረደ፡፡ (ገጪው ሳይወርድ ተገጪው ዱብ አለ!) የመኪናዋን ኋላ በመዳፎቹ እየደባበሰ ጉዳቷን መፈተሽ
ያዘ፡፡ ዓይኑን ወደ V8ቱ በትዝብት ሲልክ፣ መንዲስ የሚያህሉት ባለሥልጣን (ማለቴ የህዝብ አገልጋይ!) ከመኪናቸው ሲወርዱ ተመለከተ፡፡ (#ልማታዊ መሆን አለባቸው” ብሎ በልቡ ደመደመ!)  ከመቅጽበት ግን የቱ ጥግ ላይ ተሸሽጎ እንደነበር ያላወቀው አንድ ትራፊክ ፖሊስ ከች አለና፣ ባለሥልጣኑን ከልማታዊነታቸው አስተጓጎላቸው፡፡ (እንዴት? ማለት ጥሩ!) ባለሥልጣኑን በፖሊስ ሰላምታና አስማት በሚመስል ሃይል ገፋፍቶ ወደ መኪናቸው አስገባቸው፡፡ በድጋሚ የፖሊስ ሰላምታ ሰጠ፡፡ ይሄኔ መኪናው እያጓራ ተፈተለከ፡፡  ወዳጄ አፍታ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በተከሰተው ነገር አራስ ነብር ሆነ፡፡ (ከአንበሳ እንደማይበልጥ ግን አልጠፋውም!) የፈለገ ባለሥልጣን ቢሆኑ እንዴት ከኋላ ገጭተውኝ በክብር ይሸኛሉ? ወዳጄ ለራሱ ያቀረበው ጥያቄ ነበር፡፡ (ከጥያቄ ይልቅ እንቆቅልሽ ቢባል ይቀላል!) በደመነፍስ ወደ ትራፊክ ፖሊሱ ለመሄድ እግሩን ሲያነሳ፣ፖሊሱ ከደረት ኪሱ ደረሰኝ እያወጣ  ወደሱ ሲመጣ ተመለከተው፡፡ አጠገቡ ደርሶ የፖሊስ ሰላምታ ከመስጠቱ በፊት ወዳጄ በድንፋታ ተናገረ፡- “እንዴት የገጨንን መኪና ዝም ብለህ ትለቀዋለህ?” “አልገጨህም … መንገድ ዘግተህበት ነው” ፖሊሱ ፍርጥም ብሎ መለሰ፡፡ (እንደ ወዳጄ አገላለጽ)  “አይተሃል ግን ከኋላ መጥቶ እኮ ነው…” ፖሊሱ ግን አላስጨረሰውም፡፡
“አንተ ቆመህበት ነዋ!” ይኼኔ ቁጣዬ ወደ ግርምት ተለወጠ - ይላል፤ ወዳጄ፡፡ብዙ ንዴቶችን ቀናንሼ መጨረሻውን ብነግራችሁ ይሻላል፡፡ “የማታ ማታ እኛው ተገጭተን … እኛው የቅጣት ደረሰኝ ተቆረጠልን” ሲል ወዳጄ የገጠመውን በምሬት አጫውቶኛል፡፡ ቅጣቱን ለመክፈልም በነጋታው ብዙ ኪሎ ሜትር ነድተው ወደዚያው ስፍራ መመለስ ነበረባቸው፡፡ (መመለሱ ራሱ ሌላ ቅጣት ነው!) ቆይ አሁን ይሄ ከምንድነው የሚመደበው? በሥልጣን መባለግ? የመልካም አስተዳደር ችግር? አድርባይነት? አጎብዳጅነት? ኪራይ ሰብሳቢነት ወይስ ምን ---- ? ግዴለም ከምንም ይመደብ፡፡ ግን መፍትሄውስ ምንድን ነው? (አዲሱ #የማህበራዊ ተጠያቂነት ቲያትር; ይሞከራ!) እኔ ግን ምን እላለሁ መሰላችሁ? በአጠቃላይ ለዘርፈ ብዙ ችግሮቻችን መፍትሄው የማህበራዊ ተጠያቂነት ቲያትር ወይም የፖለቲከኞች የእርስ በርስ መገማገም አሊያም የካይዘን ንድፈ ሃሳብ ወዘተ አይደለም፡፡ ለአፍሪካ የሚበጃት ሮቦት መራሽ መንግስት ነው፡፡ ያለምክንያት አይደለም፡፡ ቢያንስ ሮቦት አህጉሪቷን ተብትበው ከያዟት ዘረኝነት፣የሃይማኖት አክራሪነት፣ካንሰር ከሆነው ሙሰኝነት፣ ከሥልጣን ጥመኝነት፣ወዘተ --- የጸዳ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር ሮቦት የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም እንደ አፍሪካ አምባገነን መንግስታት ህገመንግስት አይደልዝም፡፡ በራሳችን አገር ዜጎች ከምንቃጠል ሮቦት መራሽ መንግስት አሰርተን በሮቦት ብንመራ አይሻለንም?! ከምሬ እኮ ነው ---- አነጋገሬ ዘይቤያዊ ወይም ተምሳሌታዊ እንዳይመስላችሁ ----- ቀጥተኛ ነው፡፡ ለአፍሪካ የሚበጃት
ሮቦት መራሽ መንግስት ነው፡፡ አፍሪካውያን ከመዝረፍና እርስ በርስ ከመተላለቅ በቀር ሌላ ሙያ
የለንም፡፡ ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት የተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግልና መስዋዕትነት ለዚህ ነበር?
በነገራችን ላይ የሮቦት ቴክኖሎጂ ከምናስበው በላይ እየረቀቀ ሄዷል፡፡ ስለዚህ ሃሳብ አይግባችሁ፤ሳይንቲስቶቹ ሮቦት መራሽ መንግስት በመፍጠር ያግዙናል፡፡ በቅርቡ ያየሁት አንድ የሆሊውድ ፊልም - “Robcop” ይሰኛል፡፡ ፊልሙ ሲጀምር፤አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣን፤“operation Freedom Tehran” በሚል ስያሜ በሮቦት ወታደሮች ኢራንን ነፃ ለማውጣት ስለተጀመረ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ማብራሪያ ሲሰጡ ይታያል፡፡ ከዚህ ቀደም በቬትናም፣ አፍጋኒስታንና ኢራን በተደረጉ ጦርነቶች በርካታ አሜሪካውያን ህይወታቸውን እንዳጡ የጠቆሙት ባለስልጣኑ፤ ከአሁን በኋላ ግን የአንድም አሜሪካዊ ወታደር ህይወት ሳይጠፋ ተልዕኮአችንን በስኬት እንፈፅማለን - ይላሉ፡፡ (በሮቦት ወታደሮች ማለት ነው!) በእርግጥም ቀጣዩ ትዕይንት እሳቸው
የተናገሩትን ያረጋግጣል፡፡ በቴራን የአሜሪካ ሮቦት ወታደሮች ከታጣቂዎችና ከአጥፍቶ ጠፊዎች ጋር
ሲፋለሙ በፊልሙ እንመለከታለን፡፡ ሮቦቶች በውጭ አገራት ወታደራዊ ተልዕኮ ብቻ አልተወሰኑም፡፡ በአሜሪካም ወንጀለኞችን አድኖ የመያዝ ኃላፊነት ለሮቦት ፖሊስ (Robcop) ተሰጥቶም እናያለን፡፡ ሮቦት ፖሊስ ከሰው በተለየ ፕሮግራም የተደረገውን አንድም ሳያዛንፍ በስኬት ያከናውናል፡፡ ወዳጄ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ እንደገጠመው ዓይነት ትራፊክ ፖሊስ አይደለም ሮቦት ፖሊስ፡፡ የአገሪቱ የመጨረሻ ከፍተኛ
ባለሥልጣንንም ቢሆን ወንጀል እስከሰራ ድረስ ጨርሶ አይምረውም፡፡ ወንጀለኛ መሆኑን ሴንስ ካደረገ በማንኛውም ወንጀለኛ ላይ እንዲወስድ ፕሮግራም የተደረገውን እርምጃ በዚያ ባለሥልጣን ላይ ይወስዳል፡፡ እሱ የሚያውቀው ወንጀለኛነቱን ነዋ፡፡ የዚህን ዓይነት ሃቅ አልናፈቃችሁም? አፍሪካ ለዘመናት የተራበችውን ሃቅ የምታካክሰው በሮቦት ሰራሽ መንግስት ብቻ ነው፡፡  ለነገሩ በገሃዱ ዓለምም ሮቦቶች በተለያዩ ጦርነቶች ጥቅም ላይ እንደዋሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እ.ኤ.አ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ከ800 በላይ ሮቦቶች በኢራቅና አፍጋኒስታን ጦርነቶች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ብራዚል የ2014 የዓለም ዋንጫን ስታዘጋጅ ደግሞ ፕሮግራሙን በአስተማማኝ ደህንነት ለማካሄድ የሮቦት ፖሊሶች እርዳታ አስፈልጓት ነበር፡፡ እናም መቀመጫውን ማሳቹሴትስ ያደረገ Irobot የተባለ ኩባንያ፣ 30 የሮቦት ፖሊሶችን እንዲሰራላት የ7.2 ሚ.ዶላር ስምምነት አድርጋ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ ባይገርማችሁ ሮቦቶቹ በፍጥነት የሚንቀሳቀሱ፣ 360 ድግሪ መሽከርከር የሚችሉ፣ከ2 ሜትር ከፍታ ኮንክሪት ላይ ወድቀው ንክችት የማይሉ ብርቱ ስሪቶች
ነበሩ ተብሏል፡፡ ሮቦቶች በአህጉራችን አፍሪካም አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ከራርመዋል፡፡ በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ በኪንሻሳ ያለውን የትራፊክ መጨናነቅና የአሽከርካሪዎች ህግ መጣስ ዕልባት ለማበጀት በሚል እ.ኤ.አ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ 3 የሮቦት ትራፊክ ፖሊሶች ተመድበው፣ የትራፊክ
ፍሰቱን መቆጣጠር እንደጀመሩ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡ ሮቦት ትራፊኮቹ፤በሶላር ሃይል የሚንቀሳቀሱ ሲሆን የቅኝት ካሜራ ተገጥሞላቸው፣ የትራፊክ ፍሰቱን እየቀረጹ ለፖሊስ ቢሮ ይልካሉ፡፡ በዚህም የአገሪቱ ፖሊስ ዋና ሃብት እንደሆኑ የፖሊስ ሃላፊዎች ተናግረዋል፡፡ ሮቦቶቹ በተመደቡ ማግስት ዘ ጋርዲያን ያነጋገረው የመዲናዋ ታክሲ ነጂ፣ ቀደም ሲል በኪንሻሳ የትራፊክ ህግ እየጣሱና ወንጀል እየፈጸሙ የሚያመልጡ በርካታ አሽከርካሪዎች እንደነበሩ አስታውሶ፤ከዚህ በኋላ ግን ማምለጥ አይሞከርም ብሏል፡፡ አብዛኞቹ አሽከርካሪዎች እንደ ቀድሞው መንቀዥቀዥ እንደተዉም የታክሲ ሹፌሩ ተናግሯል፡፡ የሮቦት ትራፊክ ፖሊሶች ከማንም በላይ የሚያስፈልገን እኮ ለኛ ነው፡፡ (እጃችንን እንዳጣጠፍን በትራፊክ አደጋ ስንት ህይወት ተቀጠፈ?) ዱባይም በ2017 ዓ.ም (ከሁለት ዓመት በኋላ ማለት ነው) በጎዳናዎቼ ላይ ሙሉ አገልግሎት የሚሰጡ የሮቦት ፖሊሶች አሰማራለሁ ብላለች፡፡   ጦቢያ የሚያስፈልጋት ግን Robcop ብቻ አይደለም፡፡ (ክፍተታችን እኮ ብዙ ነው!) ምናልባት በአገልግሎት ዘርፍ የሚሰማሩ ሮቦቶችም ሳያስፈልጉን አይቀርም፡፡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጡ ሮቦቶች ያስፈልጉናል፡፡ የመንግሥትን ቢሮክራሲ በቲያትር ለመበጣጠስ መሞከር አይቻልም፡፡ (ቢቻልማ ኖሮ በ25 ዓመት ውስጥ ብጥስጥሱ ይወጣ ነበር!) እናም በዚህ ረገድም ሮቦቶች ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ ሮቦት ዳኞችም (RobJudge እንዲሉ) የፍትህ ስርዓታችንን ሊያሻሽሉልን ይችላሉ፡፡ ሮቦት ፖለቲከኞችስ? (Robpolitician እንደማለት) ዋናው ችግራችን
ፖለቲካ አይደለም እንዴ!! በእጅጉ ያስፈልገናል እንጂ፡፡ ዋናው ነገር ምን መሰላችሁ ----- ሮቦቶች ስሜት አልባ ስለሆኑ ጭፍን የፖለቲካ ጥላቻ፣ ጠባብነት፣ ዘረኝነት  ወይም አክራሪነት በመሳሰሉ ጎታችና አሉታዊ (Negative) አስተሳሰቦች አይጠቁም፡፡ ስለዚህ የፖለቲካውን መድረክ ሙልጭ አድርገው ያጸዱልናል፡፡ በእርግጥ አንድ ነገር መጠንቀቅ አለብን፡፡ በሆነ የቴክኒክ ችግር የሮቦት ዘር በሰው ልጅ ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝር ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል የግድ ይላል፡፡ ችግሩ ቢከሰት ወዲያው የምናከሽፍበትን  ዘዴ ወይም መሣሪያ በቅጡ ልንካንበት ይገባል፡፡ ያለዚያ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት አሉ እንደተባለው፤“We have become the victim of our own success” ማለታችን አይቀርም::

Page 16 of 16