ጨጨሆ የባህል አዳራሽ የተመሰረተበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በአገሪቱ ላይ በባህል፣ በቱሪዝምና በበጐ ሥራ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ሰዎች ሽልማት ሰጥቷል፡፡
“የጨጨሆ ባህል ሽልማት” በሚል ርእስ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ አንጋፋው የማስታወቂያ ባለሙያ ውብሽት ወርቃለማው የአስር ሺህ ብር እና የዋንጫ ሽልማት ሲያገኙ፣ በውዝዋዜ የምትታወቀውና በቅርቡ ከአሜሪካ ወደ ሀገር ቤት የተመለሰችው እንዬ ታከለ የአስር ሺህ ብርና የዋንጫ ሽልማት አግኝታለች፡፡ እንዲሁም ከአራት ሺህ በላይ የባህል ግጥምና ዜማ የሰራው ሙሉጌታ አባተ፤ተመሳሳይ ሽልማት ሲያገኝ፣ተወዛዋዥዋ ዳርምየለሽ ተስፋዬም ተሸላሚ ሆናለች፡፡
በሽልማት ፕሮግራሙ ላይ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ በቆዳ የተሰራ ምስላቸው የተበረከተላቸው ሲሆን የቱሪዝም አባት የሚባሉት አቶ ሃብተስላሴ ታፈሰም ተሸልመዋል፡፡
የሽልማት ፕሮግራሙ ልዩ ተሸላሚ የሆነው የመቄዶኒያ የአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን ማዕከል መስራች ወጣት ቢኒያም በለጠ ደግሞ 20 ሺህ ብር ተበርክቶለታል፡፡ አርቲስት መሰረት መብራቴ፤የጨጨሆ የባህል አዳራሽ አምባሳደር ሆና ለአንድ ዓመት ለመስራት ተፈራርማለች፡፡

Published in ዜና

እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ!!
ሁልጊዜ በልቤ የምፀልየውና አውራውን ፓርቲ ኢህአዴግን አብዝቼ አደራ የምለው፣አንዳንድ መብቶችን ጨርሶ እንዳይነካብን ነው፡፡ (ለመንካት ባያስብ ሁሉ ደስ ይለኛል!) ይሄን የምለው ዝም ብዬ አይደለም፡፡ እንደ ልብ እየታተሙ የሚወጡትን መፃህፍት ለመቆጣጠር የሚያስችል የመፃህፍት ፖሊሲ ይወጣል የሚባል ነገር ሽው ስላለኝ ነው፡፡ የመፃህፍት  ፖሊሲ ከሚባለው ነገር ጋር ችግር የለብኝም፡፡ ስሙን አሳምሮ ግን ወደ ቁልቁለት እንዳይሰደን ነው - ፍርሃቴ፡፡  ወደ ሳንሱር እንዳይመለስ ነው ስጋቴ፡፡ (እስካሁን ያልተሸራረፈ መብት ቢኖር … መፃህፍትን  የማሳተም መብት
ይመስለኛል!)  እናም ኢህአዴግ ------ በግጥም ተሰደብኩ፣ በትያትር ተነቀፍኩ፣ በቀልድ
ተፌዘብኝ፣ በዘፈን ተብጠለጠልኩ፣በመጽሐፍ ገበናዬ ወጣ -- ወዘተ በሚል አትንኩኝ ባይነት ወደ
አፈናና እገዳ እንዳይገባ ይጠንቀቅ (እስከዛሬ አልሞከረውም አልወጣኝም!)  በአዲሱ ዓመት ምን
እንዳሰብኩ ልንገራችሁና ወደ ፖለቲካ ቀልዶቻችን እንሂድ፡፡
የቲቪ የፖለቲካ ሾው የመጀመር ዕቅድ አለኝ፡፡ እግረመንገዴን የIdea ኮፒራይት ማስመዝገቤ
እንደሆነ ልብ በሉልኝ፡፡ ቀልዳችንን የምንጀምረው ከፈረንጆቹ ነው፡፡ በእነሱ ጀምረን በኛ
እናሳርገዋለን፡፡ (በአገሬ ፖለቲካዊ ቀልድ እኮራለሁ!)
********   
በቀድሞው የሶቭየት ህብረት ዘመን ነው፡፡ ሁለት የእስር ቤት ጓደኛሞች የታሰሩበትን ምክንያት እርስ በርስ ይጠያየቃሉ፡፡ አንደኛው እስረኛ፤ “በምን ምክንያት ነው ያሰሩህ? በፖለቲካ ነው ወይስ በተራ ወንጀል?” ሲል የወህኒ ቤት ጓደኛውን ይጠይቀዋል፡፡ “በፖለቲካ ነው እንጂ፡፡ አየህ---እኔ ቧንቧ ሰራተኛ ነኝ፡፡ አንድ ቀን ወደ ወረዳው የፓርቲ ጽ/ቤት ጠርተው የፍሳሽ ማስተላለፊያውን ቱቦ እንድጠግንላቸው ነገሩኝ፡፡ እኔም ችግሩን በደንብ ተመለከትኩና፤‹ሲስተሙ በሙሉ መለወጥ አለበት› አልኳቸው፡፡ ወዲያው ወሰዱና የ7 ዓመት እስር

አጠጡኛ፡፡;
********   
በህንድ ዴልሂ አንድ ሹፌር ከፓርላማው ፊት ለፊት በትራፊክ መጨናነቅ መንገድ ተዘግቶባት ቆሟል፡፡ በመሃል አንድ ሰው ድንገት የመኪናውን መስተዋት ያንኳኳል፡፡ ሹፌሩ መስኮቱን አውርዶ፤ “ምንድነው የተፈጠረው?” ሲል ጠየቀ፡፡ “ሽብርተኞች፤የህንድ ፖለቲከኞችን በሙሉ አፍነው፣ የ100ሚ. ዶላር ክፍያ ጠይቀዋል፡፡ ገንዘቡ ካልተሰጣቸው ሁሉም ላይ ነዳጅ አፍሰው እሳት ሊለቁባቸው ነው፤ እናም በየመኪናው እየዞርን እርዳታ እያሰባሰብን ነው” “እያንዳንዱ ሰው በአማካይ ስንት እያዋጣ ነው?” ጠየቀ ሹፌሩ፡፡ ሰውየውም፤ “2 ሊትር ገደማ ነው” መለሰ፡፡
********   
     አንድ ብላቴና አባቱ ዘንድ ይሄድና “ፖለቲካ ምንድነው?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ አባትም፤ “ልጄ፤ እስቲ በዚህ መንገድ ለማስረዳት ልሞክር፡- እኔ የቤተሰቡ ቀለብ አቅራቢ ነኝ፤ ስለዚህ ካፒታሊዝም በለኝ፡፡ እናትህ ገንዘቡን ስለምታስተዳድር መንግስት እንበላት፡፡ እኛ እዚህ ያለነው ያንተን ፍላጎቶች ለማሟላት ስለሆነ … አንተን ህዝብ እንልሃለን፡፡ ሞግዚቷን ደግሞ እንደ ሰራተኛው መደብ እንቁጠራት፡፡ ህፃኑ ወንድምህን መጪው ዘመን እንበለው፡፡ እስቲ  ይሄን አስብና ስሜት ይሰጥ እንደሆነ እየው” በማለት አስረዳው፡፡
ብላቴናው አባቱ የነገረውን እያሰላሰለ ወደ መኝታው ሄደ፡፡ የዚያኑ ዕለት ሌሊት ህፃን ወንድሙ ሲያለቅስ ሰምቶ ከእንቅልፉ ተነሳ፡፡  ወንድሙ ጋ ሄዶም የሆነውን ተመለከተ፡፡ የሽንት ጨርቁ በሽንትና በሌላም ተበለሻሽቶ ነበር፡፡ እየተጣደፈ ወደ ወላጆቹ መኝታ ክፍል አመራ፡፡ እናቱ ጥልቅ እንቅልፍ ላይ ነበረች፡፡ ሊቀሰቅሳት አልፈለገም፡፡ ወደ ሞግዚቷ መኝታ ክፍልም ደግሞ ሄደ፡፡ በሩ ተቆልፏል፡፡ በቀዳዳ ሲያጮልቅ፣ አባቱን ከሞግዚቷ ጋር ተኝቶ ተመለከተው፡፡ ከዚያም ተስፋ ቆርጦ ወደ መኝታ ክፍሉ ተመለሰ፡፡ በነጋታው ብላቴናው ለአባቱ፤ “አባዬ፤ አሁን ፖለቲካ ምን ማለት እንደሆነ የገባኝ ይመስለኛል” ይለዋል፡፡
አባትም፤“ጎሽ ልጄ፤ ስለ ፖለቲካ የገባህን በራስህ ቋንቋ ንገረኝ” አለው፡፡ ልጅም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ካፒታሊዝም ከሰራተኛው መደብ ጋር አንሶላ ሲጋፈፍ፣ መንግስት ለጥ ብሎ ይተኛል፡፡ ህዝቡን ዞር ብሎ የሚያየው የለም፡፡ መጪው ዘመንም በጥልቅ አረንቋ ውስጥ
ተዘፍቋል”
********   
እስቲ አሁን ደግሞ አንድ ሁለት አገር በቀል የፖለቲካ ቀልዶችን እንመልከት (በአገር ቀልድ መኩራት ይልመድባችሁ!) በሀይሉ ገብረእግዚአብሔር ዝነኛ ወግ ፀሐፊ ነዋ! ምርጥ የፖለቲካ ስላቆችንም ይጽፋል፡፡ “ኑሮና ፖለቲካ” በሚል ርዕስ 3 የመፃህፍት ጥራዞች ላይ ደርሷል፡፡  መፃህፍቱን አድናችሁ ታነቡ ዘንድ እየጠቆምኩ፣ ለዛሬ ከፌስቡኩ ላይ ያገኘኋትን የጨረሰች የፖለቲካ ስላቅ ልጋብዛችሁ፡፡ አንድ የገዢው ፓርቲ አባል “ምርጫ በማሸነፉ” ደስ ተሰኝቶ ሚስቱ ጋ ደወለ አሉ፡፡ “ሄሎ ማሬ!”
“አቤት ውዴ!”
“ምርጫውን እኮ አሸነፍኩኝ!”  አለ ደስታ ባመጣው ፈገግታ ታጅቦ፡፡ “እውነት?” እሷም ደስታ የሚያደርጋትን አሳጥቷት ባለማመን ጠየቀች፡፡ ጥያቄዋ ግን ባልን አስቆጣው፡፡
“እ!? ምን አልሽ አንቺ!”
“እውነት አሸነፍክልኝ ወይ ነው ያልኩት”
አሁንም ደስታዋ አላበራም፡፡
“አንቺ ሴት ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር መዋል ጀመርሽ ማለት ነው!?” ንዴት የሚያደርገውን

እያሳጣው፡፡
“ምን እያልክ ነው እንዴ?” ግራ ቢገባት ጠየቀች፡፡
“እዚህ ጋ ‹እውነት› የሚለውን ቃል ምን አመጣው!? ‹አሸነፍኩ› ማለት ያው  አሸነፍኩ ነው!

አይገባሽም እንዴ!”
********   
የእኛ አገር የቀልድ ምንጭ ይገርመኛል፡፡ ከትራጄዲ ውስጥ ነው የሚፈጠረው፡፡ ለዚህ እኮ ነውቀልዶቻችን መራራ የሆኑት - በተለይ የፖለቲካዎቹ፡፡ ለምሳሌ በ97 ምርጫ ማግስት የተፈጠሩ ቀልዶችን ብዛት ስናይ፣ የግንቦት 2007 ምርጫን ተከትሎ ምንም ቀልድ አልተፈጠረም ማለት ይቻላል፡፡ (እንደ 97ቱ ቀውጢ አልነበረማ!) ለማንኛውም ግን አንድ የሰማኋትን ቀልድ ከእነ አካቴው ከመርሳቴ በፊት እንደ ታሪክ ልዘግባት፡፡  ገዢው ፓርቲ ምርጫውን 100 በመቶ አሸነፈ ተብሎ የተወራ ሰሞን ነው (ምርጫ ቦርድ መሰረተ ቢስ ነው ብሏል!) ቀልዷ ግን ከቦርዱ ማስተባበያ በፊት ስለተፈጠረች … እንስማት (ቀልድና
ቁምነገር አይደባለቅም!) እናላችሁ … አንዲት እናት ለዕድርተኛቸው የልጃቸውን በትምህርት እሳት መሆን በኩራት ይደሰኩራሉ፡፡ “ይገርምሻል … ሂሳብ 100 ከመቶ፣ ሳይንስ 100 ከመቶ፣ አማርኛ 100 ከመቶ፣
እንግሊዝኛ 100 ከመቶ …!!” ዕድርተኛዋ ተገርመውና ተደንቀው ይሄዳሉ፡፡ ብዙ ተለያይተው… አንድ ቀን ይገናኛሉ - ዕድርተኛሞቹ፡፡ አንደኛዋ ዕድርተኛ እንዲህ አሉ፤ “አንቺ፤ያ ኢህአዴግሽ አደገልሽ??”
(100በመቶባመጣእኮነው!)አዲሱንዓመት የፍቅር፣የደስታ፣የሰላም፣የመቻቻል፣የሥልጣኔ፣የዲሞክራሲ፣የፍትህ፣የመልካም
አስተዳደር፣የልማት፣የብልጸግና፣----ያድርግልን!! (ረዥሙ ምርቃት ተብሎ በጊነስ እንዲመዘገብልኝ
ጥረት ጀምሬአለሁ!)

የአለም ኢኮኖሚ እድገት ከተገመተው በታች ይሆናል ተብሏል
             አዝጋሚው የቻይና ኢኮኖሚ በአለማችን ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል
                           አህጉረ እስያ በአለም ኢኮኖሚ መሪነቷ ትቀጥላለች ተብሎ እንደሚጠበቅ አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክርስቲያን ላጋርድ ማስታወቃቸውን ዘ ሂንዱ ታይምስ ዘገበ፡፡
አለማቀፉ የኢኮኖሚ እድገት ከዚህ በፊት ተገምቶ ከነበረው አነስ ባለ መጠን በመካከለኛ ደረጃ ላይ ሆኖ እንደሚቀጥል የገለጹት ክርስቲያን ላጋርድ፣ በአለማችን የኢኮኖሚ እድገት መሪነቱን የያዘችው እስያ፤ ምንም እንኳን የእድገት መጠኗ እየቀነሰ ቢሆንም በመሪነቷ ትቀጥላለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ለሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ኢንዶኔዥያ ያመሩትና ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆኮ ዊዶዶ ጋር በአለማቀፉ የኢኮኖሚ ሁኔታ ዙሪያ የመከሩት ላጋርድ፣ ባለፈው ማክሰኞ በአገሪቱ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ አለማቀፉ የኢኮኖሚ ሁኔታ ኢንዶኔዢያን በመሳሰሉ ያላደጉ አገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ ገልጸዋል፡፡
የአምናው የአለማችን የኢኮኖሚ ዕድገት 3.4 በመቶ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ አይ ኤምኤፍ ባለፈው ሃምሌ ወር ላይ የዘንድሮው የአለማችን የኢኮኖሚ ዕድገት 3.3 በመቶ ሊያድግ ይችላል ብሎ መገመቱንና ዕድገቱ ግን ያነሰ ሊሆን እንደሚችል ዳይሬክተሯ መናገራቸውን አስረድቷል፡፡ አምና 2.4 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበችው አሜሪካ፤ ዘንድሮ በ2.5 በመቶ ታድጋለች ተብሎ መገመቱን የጠቀሰው ዘገባው፣ ባለፈው አመት 7.4 በመቶ ያደገችው ቻይና በበኩሏ፤ የዕድገቷ መጠን ቀንሶ 6.8 በመቶ ሊደርስ ይችላል ተብሎ እንደተገመተ ጠቁሟል፡፡
ያደጉ አገራት ኢኮኖሚ በተወሰነ መጠን ማገገም ይታይበታል ቢባልም፣ በማደግ ላይ ያሉ ኢኮኖሚዎች ግን ከነበሩበት ደረጃ ዝቅ ይላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ክርስቲያን ላጋርድ ተናግረዋል፡፡
ቢቢሲ በበኩሉ፤ ክርስቲያን ላጋርድ አዝጋሚው የቻይና ኢኮኖሚ በአለማቀፉ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን ዘግቧል፡፡
“የቻይና ኢኮኖሚ እድገት በሌሎች የአለማችን አገራት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ፣ ከዚህ በፊት ከተገመተው በላይና የከፋ ሊሆን እንደሚችል ሁኔታዎች ያመለክታሉ፡፡ ስለሆነም ቻይና የጀመረቻቸውን የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ማስቀጠል ይገባታል” ብለዋል ላጋርድ፡፡
በቻይና ኢኮኖሚ ላይ የሚታዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ነዳጅና ማዕድናትን የመሳሰሉ ሸቀጦች ዋጋ እንዲቀንስ ማድረጉን የጠቆመው ዘገባው፣ በዚህም ሸቀጦቹን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ብራዚልና ሩሲያን የመሳሰሉ አገራት ክፉኛ እየተጎዱ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

     የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ሚስት ግሬስ ሙጋቤ፤ ከሃራሬ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች የተዘረፉ ልባሽ ጨርቆችንና አልባሳትን ያለአግባብ ለፖለቲካ ደጋፊዎቻቸው በማከፋፈላቸው ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሆነ ተዘገበ፡፡
የሃራሬ ከተማ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ፖሊስ የወረሰባቸውን ልባሽ ጨርቆችና አልባሳት ቀዳማዊ እመቤት ግሬስ ሙጋቤ፣ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው አከፋፍለዋል በሚል ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ተከትሎ፣ የዚምባቡዌ መደበኛ ያልሆኑ ዘርፎች ድርጅት በሴትየዋ ላይ ክስ እንደሚመሰርት ማስታወቁን ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ህገወጥ የጎዳና ላይ ነጋዴዎችን እንቅስቃሴ ለመግታት በሚል ልባሽ ጨርቆችና ጫማዎች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ መከልከሉን ያስታወሰው ዘገባው፣ የሃራሬ ከተማ ፖሊስም በቅርቡ ባደረገው አሰሳ፣ በሺህዎች ከሚቆጠሩ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች በርካታ ቶን የሚመዝኑ ልባሽ ጨርቆችና ሌሎች ቁሳቁሶችን መንጠቁን ገልጧል፡፡
ቀዳማዊ እመቤት ግሬስ ሙጋቤ፣ ባለፈው ሳምንት በሰሜናዊ ዚምባቡዌ በተከናወነ የፖለቲካ ቅስቀሳ ላይ፣ ፖሊስ ከነጋዴዎቹ የነጠቃቸውን 150 ቦንዳ ልባሽ ጨርቆችና አልባሳት ዛኑፒኤፍ ለተባለው ፓርቲያቸው ደጋፊዎች በነጻ ሲያከፋፍሉ መታየታቸውን የጠቀሰው ዘገባው፤ ድርጊቱን ያወገዘው የዚምባቡዌ መደበኛ ያልሆኑ ዘርፎች ድርጅትም ክስ ለመመስረት እየተዘጋጀ መሆኑን ማስታወቁን አስረድቷል፡፡
ቀዳማዊ እመቤት ግሬስ ሙጋቤ፤ የግል ንብረታቸው ያልሆነን ልባሽ ጨርቅና አልባሳት ለደጋፊዎቻቸው ማከፋፈላቸው ህገወጥ ድርጊት በመሆኑ፣ ይሄን ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ በአፋጣኝ ክስ እንመሰርታለን ብለዋል፣ የድርጅቱ ዳይሬክተር ፕሮሚዝ ክዋናንዚ፡፡
ግሬስ ሙጋቤ ከነጮች የተወረሱ ሰፋፊ መሬቶችን የግል ይዞታቸው በማድረግ በአገሪቱ አቻ እንደማይገኝላቸው የጠቆመው ዘገባው፣ ልባሽ ጨርቆቹን ሲያከፋፍሉ በደስታ ተውጠው ገዝተው እንዳመጡላቸው ለደጋፊዎቻቸው ሲናገሩ እንደነበርም አመልክቷል፡፡
በርካታ የአገሪቱ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች በፖሊስ እየታደኑ እየተደበደቡና ንብረቶቻቸው እየተወረሰባቸው መሆኑንና  በ17 ያህል ነጋዴዎች ላይ ክስ መመስረቱንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

 ጆሃንስበርግ 23‚400፣ ካይሮ 10‚200፣ ሌጎስ 9‚100 ሚሊየነሮች አሏቸው
            አፍሪካ በድምሩ 670 ቢ. ዶላር ሃብት ያካበቱ 163 ሺህ ሚሊየነሮች አሏት

   የደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ በአፍሪካ አህጉር በርካታ ሚሊየነሮች የሚገኙባት ቀዳሚ ከተማ መሆኗን አፍርኤዥያ ባንክ እና ኒው ወርልድ ዌልዝ የተሰኙ ተቋማት ሰሞኑን ይፋ ያደረጉትን አህጉራዊ የጥናት ውጤት ጠቅሶ ቢቢሲ ዘገበ፡፡ “የወርቅ ከተማ” ተብላ የምትጠራው ጆሃንስበርግ፤ 23 ሺህ 400 ሚሊየነሮች የሚኖሩባት የአፍሪካ የባለጸጎች ከተማ መሆኗን የገለጸው ዘገባው፣ ደቡብ አፍሪካ በአህጉሩ ከሚገኙ ሚሊየነሮች 30 በመቶው የሚገኙባት አገር መሆኗንም አስታውቋል፡፡
10 ሺህ 200 ሚሊየነሮች ያሏት የግብጽ መዲና ካይሮ፤ በሚሊየነሮች ብዛት ከአህጉሩ ከተሞች ሁለተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን 9 ሺህ 100 ሚሊየነሮች ያሏት የናይጀሪያዋ ሌጎስ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
ባለሃብቶቹ በዝርዝሩ ውስጥ ለመካተት ቢያንስ 1 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ሊኖራቸው እንደሚገባ የጠቆመው ዘገባው፣ አፍሪካ በድምሩ 670 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ያካበቱ 163 ሺህ ሚሊየነሮች እንዳሏትም አክሎ ገልጿል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

    የፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ መንግስት ሞሃመድ ሙርሲን ከመንበረ መንግስቱ አስወግዶ ስልጣን ከያዘ በኋላ በአገሪቱ የመጀመሪያው በሚሆነውና ከሚጠበቀው ጊዜ ዘግይቷል በሚል ሲተች ቆይቶ በጥቅምት ወር ሊካሄድ ቀን በተቆረጠለት የግብጽ ፓርላማ ምርጫ፣ በውጭ አገራት የሚገኙ ዜጎች ድምጽ እንዲሰጡ መፈቀዱ ተዘገበ፡፡
ኦል አፍሪካን ዶት ኮም ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በርካታ ግብጻውያን በሚኖሩባቸው 139 የተለያዩ የአለማችን አገራት በሚቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች፣ ዜጎች ድምጻቸውን እንዲሰጡ ለማስቻል አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡
በምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሃምዲ ሳንድ ሎዛ የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ በ139 አገራት ውስጥ በሚገኙ የግብጽ ኤምባሲዎች የምርጫ ጣቢያዎች ተቋቁመው ዜጎች ድምጽ እንዲሰጡ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ዘገባው ገልጧል፡፡
ማክሰኞ በተጀመረው የአገሪቱ የምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ፣ 2 ሺህ 745 ያህል ዜጎች በተወዳዳሪነት መመዝገባቸውንና ምዝገባው ለ10 ቀናት ያህል እንደሚቆይ የግብጽ ከፍተኛ የምርጫ ኮሚሽን ያስታወቀ ሲሆን፣  55 ሚሊዮን ያህል ዜጎች ድምጽ ለመስጠት መመዝገባቸውንም አሃራም የተባለው የአገሪቱ ድረገጽ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት የምርጫ ኮሚሽን፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ምርጫው በጥቅምት ወር አጋማሽ እንደሚካሄድና የድምጽ አሰጣጡም ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ማስታወቁን የጠቆመው የቴሌግራፍ ዘገባ፣ አገሪቱ ከሰኔ ወር 2012 አንስቶ ፓርላማ እንደሌላትና ምርጫ እንድታካሄድ የተወሰነው ቀደም ብሎ ቢሆንም በፕሬዚዳንቱ ቸልተኝነት መዘግየቱን አመልክቷል፡፡
ፕሬዚዳንት አል ሲሲ፤ ከነባር የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ለመቀላቀልም ሆነ አዲስ ፓርቲ ለመመስረት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቆየታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ በቀጣዩ ምርጫም ዋነኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደማይወዳደሩ ጠቁሟል፡፡
ምርጫው ከተያዘለት ጊዜ እንዲራዘምና ባለፈው መጋቢት ወር እንዲካሄድ ቢወሰንም፣ የአገሪቱ ፍርድ ቤት አንዳንድ የምርጫ ህጎች ህገመንግስቱን የሚጥሱ ናቸው በማለት ምርጫው ዳግም እንዲራዘም መወሰኑን ዘገባው አስታውሷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

     ‹‹መማር ምንድነው?›› የሚል ጥያቄ ከጀርባው አዝሎና አግተልትሎ የሚያመጣቸው እና ለትካዜ የሚዳርጉ ጥያቄዎች ከህሊናዬ በር ቆመው ያለ ዕረፍት ባንኳኩኝ ጊዜ ሁሌም የሚታወሰኝ፤ የዜን ቡዲስት የሆኑ የአንድ ጃፓናዊ መነኩሴ ታሪክ ነው፡፡ የዚህን መነኩሴ ስም አላስታወስኩትም፡፡ ታሪካቸው የቀረበበት መጽሐፍ ርዕስም ሆነ የደራሲው (የአርታኢው) ስም ትዝ አይለኝም፡፡ ሆኖም፤ የመጽሐፉ አንድ ምዕራፍ ሆኖ የቀረበው የመነኩሴው ታሪክ፤ “How I become a Buddhist Monk” (እንዴት የዜን መነኩሴ ለመሆን በቃሁ) በሚል ርዕስ መቅረቡን አስታውሳለሁ፡፡  
በመነኩሴው የትረካ ዘዬ እና አቀራረብ በእጅጉ መደነቄንም አስታውሳለሁ፡፡ መነኩሴው፤ በእኔ ባይ የትረካ አንጻር ታሪካቸውን ሲያወጉን፤ ከመመንኮሳቸው በፊት ለእምነቱ የነበራቸውን ዝቅ ያለ አመለካከት አይደብቁንም፡፡ የዚህ ጽሑፍ አንባቢ፤ በዜን ቡዲዝም ላይ ሊኖረው የሚችለው ጥርጣሬ ወይም ንቀት ወይም  ጥላቻ ባለው ተራኪ ዓይን የሚቀርብ ትረካ ነው፡፡ በወቅቱ ስለዜን ቡዲዝም የነበራቸውን አመለካከት፤ የወቅቱን ስሜት በሚመጥን ቃላት ይገልፁታል፡፡ ይህ ስልት ሐይማኖቱን ከማይቀበሉ አንባቢዎች ጋር በቀላሉ ያዛምዳቸዋል፡፡ ሐይማኖታዊ ጉዳይን የሚያትት ፀሐፊ በእምነት በማይመስሉት ሰዎች ህሊና ሊቀሰቅሰው የሚችለው ለክርክር የመዘጋጀት ዝንባሌ እንዲወገድ አድርገው መተረክ ችለዋል፡፡ በሌላ አገላለፅ፤ የመሰበክ (የመበለጥ) ስሜትን ከአንባቢያቸው የማራቅ ብቃት ይዘዋል፡፡
እንዲህ ያሉ ስነልቦናዊ ሸለቆዎችን፣ አጥርና ግድግዳዎችን በማስወገድ፤ ፀሐፊውና አንባቢው ጫጫታና ግርግር በሌለበት ስፍራ ለብቻቸው ለመወያየት የሚችሉበትን ዕድል ለመፍጠር በሚያግዝ የትረካ ስልት ያወጉናል፡፡ የሐሳብ ግብይቱ፤ ደላላና የገበያ ግፊያ ወዘተ በሌለበት ቦታ እንዲከናወን ማድረግ ችለዋል፡፡ የአንባቢው እና የፀሐፊው ህሊና ለብቻቸው የሚገናኙበትን መንገድ አውቀውታል፡፡ ታሪኩን ሲነግሩን፤ ከኛ እንደ አንዱ ሰው ሆነው እንጂ መነኩሴ ሆነው አይደለም፡፡ በዚህ መንገድ የግል ህይወታቸውን ሲያጫውቱን፤የዜን ቡዲዝም አዕማደ ሐይማኖት ሊባሉ የሚችሉ ሐሳቦችን በተራ የህይወት ክስተቶች ውስጥ እያሳዩን ይጓዛሉ፡፡ መነኩሴው ዘመናዊ ትምህርት ተምረዋል፡፡ በኋላ የዜን መነኩሴ ለመሆን የበቁት፤ ከዜን መምህራን እግር ስር ሆነው ተምረው ነው፡፡ በእርግጥ፤ ዜንን መሆን እንጂ መማር አይቻልም፡፡ ዜንን መንገድ እንጂ ሐይማኖት ለማለት አይቻልም፡፡ ለወሬ እንዲመቸን ‹ሐይማኖት›› እና ‹‹ትምህርት›› እያልን እንቀጥል፡፡    
ዜንን ‹‹መማር››
የዜን መምህራን ሲያስተምሩ፤ ለተማሪ ህሊና የሚያስቸግሩ ፅንሰ ሐሳባዊ ጉዳዮችን ከመተንተን አያነሱም፡፡ ተማሪው በሐይማኖቱ የሚከበሩ እና የሚታመኑ ነገሮችን ከመቀበል እንዲጀምር አይጠበቅም፡፡ ከተማሪው የሚጠበቀው፤ ህሊናው ለሚያመላልሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት መጣጣር ብቻ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያግዝ አስተዋይ ዓይንና ልብ ይዞ ለመገኘት መስራት ብቻ ነው፡፡ ታዲያ ማየትና ማስተዋልን ሐብት የማድረግ ነገር እንዲህ ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡
ለጥያቄዎቹ መልስ ለማግኘት የሚችል ተማሪ፤ በጥያቄዎቹ በደንብ ግራ መጋባት ይኖርበታል፡፡ ለጥያቄዎቹ መልስ ለማግኘት የማይቦዝን ሰው መሆንም አለበት፡፡ ለጥያቄው መልስ ለማግኘት፤ ‹‹እጅህን ቆርጠህ ስጠኝ›› ቢሉት፤ እጁን ቆርጦ ለመስጠት የማያመነታ ሰው መሆን አለበት፡፡ እንዲህ ያለ ህሊና ያለው ሰው ይማራል፡፡ ገበያ ተልኮ ዙሪያ ገባውን  እያየ ተልዕኮውን የሚረሳ ሰው አይሆንም፡፡
አንድ ሰው ከሞት ፊት በቆመ ጊዜ የሚኖረው ዓይነት ህሊና ሊኖረው ይገባል፡፡ ሰው ከሞት ፊት ሲቆም፤ እስከዚያች ቅፅበት ድረስ ቁም ነገር የመሰሉ ነገሮች ሁሉ እርቃናቸውን ቆመው ይመለከታል፡፡ ትናንት - ከነግሳንግሱ፤ ነገም - ከነሠራዊቱ ይሸሻል፡፡ ህሊናን በግራ በቀኝ እየጎተቱ የሚያዋክቡት ነገሮች በቅፅበት ይጠፋሉ፡፡ በትናንት (ትዝታ) እና በነገ (ተስፋ) መካከል ያለው የገመድ ጉተታ ያማል፡፡ ገመዱ ተበጥሶ ከሁለት ሲወድቅ፤ ወደ ግራ ወይ ወደ ቀኝ፤ ወደ ላይ ወይ ወደ ታች ለማየት የማይቻልበት የእይታ አንፃር ይፈጠራል፡፡
ከሞት ፊት በቆመ ሰው ዘንድ የሚፈጠረው የትኩረት ኃይል፤ የመሬት ዙሪትን ለማቆም የሚችል ኃይል ይሆናል፡፡ በአንዲት አተም ውስጥ ከታመቀ ኃይል የሚነፃፀር የትኩረት ኃይል ይኖረዋል፡፡ እንደ ዝንጀሮ መዝለል የሚወደውና ማትኮር የተሳነው ህሊና፤ በፀጥታና በትኩረት ይጓዛል፡፡
ነገሩ፤ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ቢወድቅ እንደ ጨው ከሚያሟሟ የአሲድ ገንዳ ሊወድቅ በሚችልበት ሁኔታ በቀጭን ገመድ ላይ ለመራመድ የሚሞክር ሰው ነገርን ይመስላል፡፡ በዚህ ለመራመድ የሚወስን ሰው፤ እግሩን አንስቶ ሲያሳርፍ ሚዛኑን ቢስት ሊፈጠር የሚችለውን ነገር ያውቀዋል፡፡ መምህሩ፤ ሙዳ ሥጋ ወደ ገንዳው ጥሎ፤ ትኩረት አጥቶ ቢወድቅ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ያሳየዋል፡፡ ማንኛውም ሰው በዚች ገመድ ለመራመድ ከመወሰኑ በፊት ብዙ ያስባል፡፡ ይቸገራል፡፡ ሆኖም፤ በህይወቱ ተወራርዶ ከወሰነ፤ አንዲት ነቁጥ ክፍተት የሌለው ውሳኔ አድርጓል፡፡ ትኩረቱም ነፋስ የሚያስገባ ነቅ የሌለው ጥቅጥቅ ያለ ትኩረት ይሆናል፡፡
ሞት ከፊታችን በቆመ ጊዜ፤ ‹‹አይ እኔ ይቅርብኝ ዛሬ አልሄድም›› ብሎ መመለስ አይቻልም፡፡ ቁርጡ ሰዓት መጥቷል፡፡ ስለዚህ መሄድ ብቻ ነው፡፡ እንዲህ ባለ ትኩረትና ውሳኔ የመጣ ጥሩ ተማሪ ነው፡፡ እንዲያውም፤ ከዚህ ነጥብ የደረሰ ተማሪ መምህር አያስፈልገውም፡፡ መምህር የሚያስፈልገው ከዚህ ነጥብ ለመድረስ ነው፡፡ የመምህሩ ሥራ ከጫፍ ቆሞ፤ እሱ እስከቆመባት ሥፍራ ድረስ የመጣ ሰውን መቀበል አይደለም፡፡ ለመጓዝ የቆረጠ ሰውን ተቀብሎ፤ ከጉዞ የሚያዘናጉ ነገሮችን እንዲለይ እያደረገ፤ መንገድ ከሚያስቱ ነገሮች እንዲጠበቅ እየረዳ፣ ሳይሄድ የሄደ እንዲመስለው የሚያደርግ አጭበርባሪ ፈተናን እያመለከተ፤ የጦር ዕቃ እያስታጠቀና እያስጨከነ፤ ተማሪው የእውነትን አሰር ተከትሎ ከፍፃሜ እንዲደርስ መርዳት ነው ሥራው፡፡ ‹‹What the student is ready፣ the teacher will arrive›› ይላሉ፡፡
መነኩሴው፤ ከእንዲህ ዓይነት መምህር ሄደው የገጠማቸውን ሲተርኩ፤ ታሪኩ ሳይመነኩሱ እንደተጀመረ ሳይመነኩሱ ይጠናቀቃል፡፡ ታሪኩ፤ መንኩሰው መናገር ከሚጀመሩበት እርከን ሲደርስ ትረካው ይደመድማል፡፡ የመነኩሴው ትረካ የሚጀምረው፤ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ዓመት ላይ ነው፡፡ እናም በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በማተት ትረካው ይነሳል፡፡ አሁን ከጃፓኖች እንተዋወቅ፡፡
ከጃፓኖች እንተዋወቅ
ጃፓን ሽንቶይዝም፣ ቡዲዝም እና ክርስትናን የሚከተሉ ዜጎች አሏት፡፡ ዓለም ጃፓናውያንን የሚያውቃቸው፤ ለ250 ዓመታት ክርችም አድርገው የዘጉትን በር እንዲከፍቱ የሚያስገድድ የታሪክ ክስተት በገጠማቸው ጊዜ፤ መበለጣቸውን ተረድተውና በፍጥነት የአውሮፓን ሥልጣኔ ቀስመው፤ ሐገራቸውን ከኃያል የዓለም መንግስታት ተርታ ለማቆም ባደረጉት እጅግ አስገራሚ እርምጃ ብቻ አይደለም፡፡ ጃፓኖች ለንጉሦቻቸው በሚሰጡት ወሰን የሌለው ክብር ወይም አምልኮ፤ የሐገራቸው፣ የንጉሳቸው ወይም የግል ክብራቸው የተነካ በመሰላቸው ጊዜ ሆዳቸውን በጩቤ እየቀደዱ (ሃራኬሪ እያደረጉ) ህይወታቸውን በማጥፋት ልማዳቸው ጭምር ነው፡፡
የሳሞራይ (የመኳንንት) ልጅ የሆነ አንድ ጃፓናዊ ፈፅሞ በጠላት ሊማረክ አይችልም፡፡ በጦርነት ሲዋጋ በብርቱ ቆስሎ ቢወድቅና አዕምሮውን ስቶ በወደቀ ጊዜ እንኳን በጠላት እጅ ተማርኮ ቢገኝ፤ የጃፓንን የሥነ ፍጥረት ክብር እንዳዋረደ ይቆጠራል፡፡ በብርቱ ቆስሎ የተማረከ ሰው፤ ታክሞ ድኖ የማረከው የጠላት ኃይል በነፃ ቢያሰናብተው፤ ወደ ወገኖቹ ጦር ተመልሶ የገዛ ሽጉጡን ጠጥቶ ይሞታል፡፡ ወይም ሳንጃውን ከሆዱ ቀርቅቦ ራሱን ይገድላል፡፡
የጃፓን የሽንቶ ሐይማኖት የሚያስተምራቸው፤ ከጃፓን ውጪ ያለው የዓለም ህዝብ በሙሉ በሥነ ፍጥረት ዝቅተኛ ከሆነ ምንጭ የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ከሰማይ አማልክት የተወለዱት ጃፓናውያን ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህ ዘራቸውን የተቀደሰ አድርገው ይመለከታሉ፡፡ ‹‹አንድ ቀን የዓለም ገዢዎች እንሆናለን የሚል ሐሳብ አላቸው›› በሚል የሚታሙት ጃፓኖች፤ ‹‹የአማልክት የበኩር ልጅ፤ የእግዚሃር ልጅ›› እያሉ ለሚጠሯቸው ነገስታቶቻቸው፤ መማር እና መዘመን የማይለውጠው የአክብሮት ስሜት ወይም አምልኮ አላቸው፡፡ እንኳን እነሱ፤ ሌላ የውጭ ሐገር ሰው ባለማወቅ የንጉሱን ክብር የሚነካ ድርጊት አድርጎ ሲያዩ፤ በቸልታ ወይም ‹‹ባያውቅ ነው›› በሚል ስሌት አያልፉትም፡፡ በዚህ በኩል ያላቸውን ነገር ለማሳየት ሊነሳ የሚችለው ታሪክ ብዙ ነው፡፡
ዓለም በጀግንነቱ የሚያደንቀው፤ እውቁ የጃፓን ጀነራል ኖዢ፤ በህዝቡ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነው እና ‹‹ሜይዢ ቲኖ›› እያሉ የሚጠሩት  ንጉሠ ነገስት ሙትሱሂቶ፤ በመቶ ጊዜ ‹‹ከደጉ ንጉሴ በኋላ የተረፈኝ ህይወት ምን ይረባኛል›› ብሎ፤ ሃራኬሪ አድርጎ ሞቷል፡፡ ጃፓንን ለአርባ አምስት ዓመታት፤ ከ1867 እስከ 1912 ዓ.ም ድረስ የገዛው ሜይዢ፤ ሐገሪቱ በትምህርት እና በኢንዱስትሪ ዘርፍ እንድትገሰግስ አደረገ፡፡ የዓለምን ገበያ በኢንዱስትሪ ምርቶችዋ አጥለቀለቀችው፡፡ ‹‹በርሽን ክፈች›› ይሏት የነበሩት ምዕራባውያንን፤ በጥራት በብዛት እና በዋጋ የሚያስከነዳ ምርት ማቅረብ ያዘች፡፡ ከጃፓን ጋር መወዳደር የተሳናቸው ሰዓት እና ብርጭቆ የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች በኪሳራ መዘጋት ጀመሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ምዕራባውያኑ በራቸውን በጃፓን የንግድ ዕቃ ላይ ለመዝጋት ተንቀሳቀሱ፡፡
እንግሊዝና አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ምዕራባዊ መንግስታት የጃፓን የንግድ ዕቃ ወደ አገራቸው እንዳይገባ በራቸውን መዝጋት ጀመሩ፡፡ እንዲያ በአጭር ጊዜ ከመሬት ተነስታ፤ በተሳሳተ ስሌት እና በትምክህት ተጠልፋ መልሳ የወደቀችው ጃፓን፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከጀርመን ናዚስት መንግስት እና ከጣሊያን የፋሽስት አገዛዝ ጋር በማበር ቆመች፡፡ አንዳንዶች ‹‹የጃፓን መንግስት ሃራኬሪ አደረገ›› ሲሉ ተቹ፡፡ ጃፓን ኃይሏ እየገነነ ሲመጣ፤ ማንቹሪያን እና በሰሜናዊ ቻይና የሚገኙ ግቶችን ወረረች፡፡ ከቻይና ጋር የጀመረችው ጦርነት ለስምንት ዓመታት ቀጠለ፡፡ ሁላችን እንደምናውቀው፤ በአሜሪካም ላይ ጥቃት ሰነዘረች፡፡ ታህሳስ 7 ቀን 1941 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ‹‹ፐርል ሀርበር›› በሚባለው የአሜሪካ ወደቦች ላይ ድንገተኛ የአውሮፕላን ጥቃት በመጣል ከፍተኛ ጉዳት አደረሰች፡፡ አሜሪካ ከእንግሊዝ እና ከፈረንሳይ ጋር በአውሮፓ የጦር ግንባሮች ተሰልፋ ነበር፡፡ የአሜሪካ ሠራዊት ሥራ ስለበዛበት፤ ለጃፓን ጥቃት ፈጣን የአፀፋ ጥቃት አላደረገም፡፡ ሆኖም ትንሽ ፋታ ሲገኝ፤ ተከታታይ የአየር ጥቃት በመሰንዘር የጃፓንን ፋብሪካዎች፣ ወደብ እና መርከቦች በመደብደብ ከፍ ያለ ጉዳት አደረሰ፡፡ እንግዲህ የመነኩሴው ታሪክ የሚነሳው፤ ከዚህ የጃፓን የታሪክ ምዕራፍ ነው፡፡
ጦርነቱ እየተጠናከረ ነው፡፡ ስለዚህ የጃፓን መንግስት ዜጎችን በብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ለጦርነት መመልመል ጀመረ፡፡ ሆኖም ለብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት የሚመለመሉት የማህበረሰብ ሳይንስ ተማሪዎች እንጂ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች አልነበሩም፡፡ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች፤ ለጃፓን የኢኮኖሚና የኢንዱስትሪ ዕድገት ተፈላጊ በመሆናቸው፤ የሰው ኃይል እጥረት እንዳይከሰት በማሰብ ለውትድርና አገልግሎቱ የሚመለመሉት የማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ተማሪዎች ብቻ ነበሩ፡፡
ባለታሪካችን የሆኑት መነኩሴ፤ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለውትድርና አገልግሎት የቀረበውን ጥሪ ለመቀበል ወደ ካምፕ ገቡ፡፡ በወቅቱ የ12ተኛ ክፍል ተማሪ የነበሩት መነኩሴ፤ የተመረጡ የጠላት ዒላማዎችን አጥፍቶ ለመጥፋት ግዳጅ ሲሰለጥኑ ቆይተው፤ ግዳጅ በመጠባበቅ ላይ ሳሉ፤ ስልጠና ወስደው ለተልዕኮ ዝግጁ ሆነው ወታደራዊ ግዳጁን ለመቀበል በጉጉት መንፈስ እየተጠባበቁ ሳሉ፤ ጃፓን አልማውም ሆነ ገምታው የማታውቀው ጥቃት ደረሰባት፡፡
የጃፓን የአየር ጥቃት የእግር እሣት ሆኖ ያንገበገባት፤ በቦንብ ጣይ አውሮፕላኖች ተከታታይ ጥቃት የቁጭት ንዳዱ ያልበረደላት አሜሪካ፤ ለዓለምም ሆነ ለራሷ አዲስ የሆነ ቦንብ የታጠቀ የጦር ጀት ወደ ጃፓን ላከች፡፡ ያ ጀት የአቶሚክ ቦንብ የታጠቀ ነበር፡፡ የሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ከተማዎች በአቶሚክ ቦምብ ተመቱ፡፡ በዓለም የጦርነት ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ ውድመት ደረሰ፡፡ በሂሮሽማ ከተማ፤ በአንዲት ቅጽበት፤ 224 ሺህ ጃፓናውያን እንደ ቅጠል ረገፉ፡፡ በዚህ ጊዜ ጃፓናውያን ፍፁም የሚጠየፉት እና ከሞት በበለጠ የሚጠሉት ነገር መጣ፡፡ መሸነፍን አምኖ እጅ ከመስጠት ይልቅ ሞትን ለሚመርጠው የጃፓን ህዝብ የሚያንገሸግሽ ፈተና ቀረበለት፡፡
 በወቅቱ የነበረው የጃፓን ንጉስ ሂሮሂቶ መወሰን ነበረበት፡፡ ‹‹ጃፓንን የአማልክት ልጆች የሚኖርባት የተቀደሰች ምድር ነች፡፡ የትኛውም ህዝብ ጃፓንን ድል ሊያደርጋት አይችልም›› የሚል፤ ሐይማኖትን መሠረት ያደረገ እምነት ያለው የጃፓን ህዝብ ከፈተና ወደቀ፡፡ ‹‹አማቴራሱ›› ከምትባል የፀሐይ ሴት አማልክት የተወለደ ነው የሚሉት ንጉሳቸው ተቸገረ፡፡ እነርሱ ከከፍተኛ ቦታ ቆመው ወደ ታች ሊመለከቱት የማይፈልጉት ንጉሳቸው፤ በከተማ ጉዳናዎች ሲያልፍ ከፎቅ ላይ ሆነው  ወደ ታች እንዳያዩት በር እና መስኮቶችን ዘግተው የሚያሳልፉት ንጉስ ሂሮሂቶ አንዳች ነገር ገጠመው፡፡ እንኳን ቀልቡን ሳይስት፤ በብርቱ ቆስሎ ህሊናውን ስቶ ለጠላት እጅ መስጠት የማይሻው የጃፓን ህዝብ ንጉስ፤ በጃፓን ህዝብ ፊት መወሰን ይኖርበታል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ባለታሪካችን አውሮፕላን አስነስቶ በተመረጠ የጠላት ኢላማ ላይ በመውደቅ ለሐገሩ ጃፓን የሚውልላትን ውለታ እያሰላሰለ፤ ሞቱን አስቀድሞ ሞቶ ለግዳጅ የሚንቀሳቀስበትን ቀን ይጠባበቅ ነበር፡፡ 

Published in ጥበብ

  ቀደም ሲል ….
   …. ለህይወት የሞት እንቅርት ያንጠለጠለ፣ ለወጣትነት የእርጅና ባላጋራ የፈጠረ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ብቻ ይመስለኝ ነበር፡፡ የማሚት እሹሩሩ የእርጅና ፍርሃት፣ የአጋፋሪ እንደሻው የሞት ሽሽት፣ የክንፈ የጊዜ መባከን ቁጭት፣ የእትዬ አልታዬ ከወርቅ ጥርሳቸው አንሰው ድብዝዝ ማለት … ያ … ሁሉ ትርክት ለእርጅና እና ሞት መሰዋት … የስብሃት ብቻ የደራሲነት አምልኮት ይመስለኝ ነበር፡፡
ወጣቶች በሩን ቆለፉ
ተዋደዱ ተቃቀፉ ተጣደፉ
አንቀላፉ
ኩኩሉ!
ሌሊቱን ለብሶ እርጅና ደረሰ
ቀኝ እጁን ሰደደ
ውብ ጡት ዳሰሰ
    ወጣቶች ጠወለጉ
    ጠወለጉ ጠወለጉ
    ሲነጋ ተያዩ
    አለቀሱ አለቀሱ
እሜት መሬት ያለ ቅሬት
ሳታላምጥ ዋጥ - ስልቅጥ!
    ዋይ ዋይ
    ዋይ ዋይ (ሌሊቱም አይነጋልኝ፤ ገፅ 23)
ለወጣቱ ስብሐት ህይወት አንድ ሌት መተኛት ናት፡፡ ዳግም መንቃት የሌለባት፤ የሚገፋፋው ሳይታወቅ የሚጣደፉባት፡፡ እንዴት? ህይወት ለአንድ ወጣት እንዲህ ናት? በልጅነት የወተት ጥርስ ወጣትነትን ታኝካለች? በአፍላነት የቀዘቀዘ ዕድሜን ጠርታ ጉያዋ ትከትታለች? ….
… ለእኔ በህይወት ጅማሬ ላይ ልጅነት ልቅ ነች - ያልተገራች፡፡ መተከዣ ጊዜ ያላበጀች፡፡ እንዲሁም በአፍላነት ላይ ወጣትነት እርጅናን አያዋየውም፡፡ መቼ ነው አይለውም፡፡ በህይወት እንደተሞኘን አለን፤ በየዕድሜ ዕርከን ላይ ህይወት አልቦ - ዘላለማዊነት ታፀናለች፡፡ ለልጆች ልጅነት ልብ የማይባል ዘላለማዊነት ነው፤ ለወጣቶች የወጣትነት ፀሐይ መቼም የማትጠልቅ ግትር ናት፡፡ ዕድሜ የሰጠንን ስናልፈው ወደኋላ እንጂ ወደፊት እንዳናየው ተጋርዶብናል … የወጣቱ ስብሐት ገፀባህሪ ማሚት እሹሩሩ ግን በአፍላ ብርሃማነት ላይ የእርጅና ከል ደርባ ትንቀሳቀሳለች፡፡
.......“እርጅና ሳስበው ያስጠላኛል፡፡ አየህ አሁን ወጣት ነኝ፣ ቆንጆ ነኝ፤ ወንዶች ውኃ ይሆኑልኛል፣. የጠየኩትን ይከፍሉኛል፡፡ ግን ቁንጅና እንደ ፍሬ ነው፡፡ እየበሰለ ሲሄድ በጣም ያስጎመጃል፡፡ አንድ ሀሙስ ቆይቶ ይበሰብሳል፡፡ ይረግፋል፡፡ መልኬ ሲጨማደድ፣ ቁንጅናዬ ሲረግፍ ምን እሆናለሁ? …” (ሌቱም አይነጋልኝ፤ ገፅ 186)
ህይወት የኋልዮሽ እያዩ ወደፊት የሚሾፍሯት ናት፡፡ እንደቴፕ አጠንጥነው የሚያደምጡት፡፡ ወጣቱ ስብሀት ግን እንደትንቢት መድረሱ የሚያጠራጥረውን እርጅና አምና የምትብሰከሰክ ወጣት ገፀ ባህሪ መፍጠር ችሏል፡፡ እርሱ እራሱ፣ ከወጣትነት ትኩሳት ጋር የዕድሜ አመሻሽ ውጭ አዳብሏል? ብለን እንድንጠይቅ ግድ ይላል፡፡ እንዴት? አለበለዚያስ ለገፀባህሪው ይሄን ሸክም ከየት አመጣው? …
ስብሐት ትኩሳትን ሲፅፍ ገና ሃያ አምስት አመቱ እንደነበር መግቢያው ላይ ይገልፃል፡፡ ይሁንና ከወጣትነት አሻግረው እርጅናን ከሚማትሩ አፍላዎች በተጨማሪ ከአዛውንትነት ድንዛዜ ጋር እየተጎተቱ ከተጎራባች፡ ወጣቶች “እሳት” የሚጫጫሩ ገፀባህሪዎችንም ፈጥሯል፡፡ የሌቱም አይነጋልኝ “አልተገናኘንም” የእነዚህ አይነቶቹ ተወካይ ናቸው፡፡ የቅፅል ስማቸው ትዕምርትም በዕድሜ መተላለፍን ወካይ ነው፡፡ በእርጅና ተጨምድደው ወደ ሞት እየተጓዙ፣ ወደ ህይወት ከሚንቀለቀሉት መፅናኛ ትኩሳት ከየመሸታ ቤቱ ይሸምታሉ፡፡
ሌላዋ የዚህ ሰልፍ ተሳታፊ ገፀባህርይ እትዬ አልታዬ ናቸው፡፡ ስብሀት “ፊታቸው የሚስቅ መዳፍ ይመስላል” ይላቸዋል፡፡ ብርሃኑ ከተሰኘ መሸተኛ ደንበኛቸው ጋር ይቀላለዳሉ፡፡ “ሙቀት፣ ሙቀት፣ ሙቀት” ሲሉት፡-
“ያረቄና ያንቱ ፍቅር ሙቀት” አላቸው፡፡ ሁለቱ ሁሌ እንደተቃለዱ ነው፡፡
“አይ አንተ! ምነው የዛሬ ሰላሳ ዓመት ተገኝተህ በሆነ?”
“ያኔማ አይመችም ነበር፡፡ የለሁም ነበር” አላቸው
“እሱ ላይ ነው ጉዱ ይኸውልህ! እኔ ደግሞ አሁን የለሁም”
እትዬ አልታዬ በህይወት መተላለፍን መሰረት አድርገው “አልተገናኘንም” ሲሉ ነው፡፡ ግን ህይወት እንዲህ ናት? በአመሻሽ ድንግዝግዝ፣ አጥበርባሪ ተጎራባች ለማየት ይዳዳታል? መተላለፍና አለመገናኘት ሆዷን ይበላታል? …
… እዚህ ላይ ነው ስብሐትን ግሪካዊው ደራሲ ኒኮዝ ካዛንትዛኪዝ (Nikos Kazantzakis) የሚዳበለው፡፡ ቀደም ሲል የስብሐት ብቻ የሚመስለኝ የህይወትና ሞት፣ የወጣትነትና እርጅና ጉዳይ የካዛንትዛኪዝ መሆኑን ካወቅሁ ጥቂት ዓመታት አልፈዋል፡፡ የደራሲውን “ZORBA THE GREEK” የተሰኘ ልቦለድ ካነበብኩ በኋላ መሆኑ ነው፡፡ እዚህ ልቦለድ ውስጥ አንድ “አልተገናኘንም” ዕጣ ፈንታቸው የሆነ ገፀባህርይ አሉ፡፡ ስማቸው አሌክሲስ ነው፡፡ መቶ ዓመት ቢሞላቸውም ሴቶችን መቋመጥ አላቆሙም፡፡ አይናቸው ማጠራጠር ይዟል፡፡ ደጃፋቸው ላይ ወንበር አውጥተው ይቀመጣሉ፡፡ በአጠገባቸው ልጃገረዶች ሲያልፉ ይጣራሉ፡፡
“ማነሽ አንቺ?”
“የፂኒዮ (ወይም) የማስተራንዶኒ ልጅ ነኝ”
“እስቲ ቅረቢና ልንካሽ፣ አይዞሽ አትፍሪ” ልጃገረዶቹ ከሀፍረት ጋር ፊታቸውን ያቀርባሉ፡፡ አሌክሲስ እጃቸውን ሰድደው ለስለስ ባለ ሁኔታ፣ በእጃቸው እያጣጣሙ ይዳስሱና እንባቸው ኮለል ብሎ ይወርዳል፡፡ ተራኪው ዞርባ አንድ ቀን ጠየኳቸው ይላል፡፡
“አያቴ ስለምን ያለቅሳሉ?”
“የማለቅስበትን ጉዳይ መረዳት ተስኖህ ነውን የእኔ ልጅ? እኔ ወደሞት ሳዘግም ከበስተኋላዬ ስንት ልጃገረዶች ቀሩ መሰለህ”
በዓሉ ግርማ ከስብሐት ገብረእግዚአብሄር ወስዶ (ባይገልፅም) ያደራጃቸው ገፀባህርይ እትዬ አልታዬ፤ “ደራሲው” ውስጥ የአሌክሲስን ብሒልና መብሰክሰክ ሲደግሙት እናያለን፡፡
“… የደረሰ ጎረምሳ ሲያዩ ምን ይላሉ መሰለህ? ‹ይኸ ሎጋ ወደ ህይወት፣ እኔ አልታዬ ወደ መቃብር፡፡ በመንገድ ተላለፍን እቴ!› ብለው እንትፍ እንትፍ ይሉበታል” (ደራሲው ገፅ፡ 156)
የአመሻሽ ህይወት የራሷ የሆነ የጀንበር ሙቀት የላትም? የወጣቶችን “ከፍ ዝቅ” የመናቂያ ልቦና አልተሰጣትም? ዕድሜ በማይፈቅደው፣ አካል በማይሸከመው መወብራት ትመታለች? ወይስ የመረጋጋት መከዳታበጃለች? ጐኗን ታሳርፋለች? ….
ስብሐት ባልበረደ የማታ ጀንበር የሚመሰሉ ሌላ ገፀባህርይም አለው፡፡ “ትኩሣት” ውስጥ ጃምቪድ የተሰኘ ገፀባህርይ ታሪካቸውን የሚያወሳው አያቱ፤ በመቶ ስምንት ዓመታቸው የሰው ሚስት ወሽመው ባሏ ሲመጣባቸው በመስኮት ሲዘልሉ እግራቸው የተሰበረ፡፡ ለጉድ የተፈጠሩት እኚህ አዛውንት፤ ከወጣት በላይ ፈጥነው እግራቸው ይድንና ወደ ወትሮው የአፍላ መዛለላቸው ይመለሳሉ፡፡
የካዛንትዛኪዝም ዞርባ ከወንድ አያቱ ተስፈንጥሮ ሴት አያቱንም በዕድሜ አለማወቅ ሽሙጥ ይጎበኛል፡፡ የልጅ ልጆቻቸውና እኩዮቻቸው አንዲት ሴት በዘፈን የሚያሸበለብሉበትን ቅዳሜ እየጠበቁ አያቱ ይኳኳላሉ ይላቸዋል፡፡ በሰማኒያ ዓመት ዕድሜያቸው በምስጢር የፍቅር አጋር መቃበዛቸው ትክክል አለመሆኑን ወጣቱ ዞርባ ከስድብ ጋር ስለነገራቸው፣ በዚህ ተስፋ መቁረጥ መኖራቸው ይሟጠጣል፡፡ ወደ መቃብር የሚያመሩት የልጅ ልጆቻቸው ከልባቸው ተራግመው ነው፡፡ ዞርባ ይሄንን ተርኮ ሲጨርስ እንዲህ ይላል፡- “ሴት ልጅ በሰማኒያ አመቷ እንኳን ጨርሶ የማይጠግግ አንድ የቁስል ክፍተት አላት፡፡ ብዙ ቁስሎቿ ተፈውሰው ቢጠፉም፣ ያ ልዩ ቁስሏ ግን እንደተከፈተ አብሯት ወደ መቃብሯ ይወርዳል፡፡” ስብሐት ይሄንን “የሴቶች ቁስል” ከካዛንትዛኪዝ ጋር በመጋራት ይሆን ማሚት እሹሩሩ ከእርጅና አድማስ አሻግራ ስለመፈቀር እንድታሰላስልና እንድትጨነቅ ያደረጋት? “… ያኔ እንግዲህ ወንዶች አይፈልጉኝ” ትላለች፡፡ ክንፈን የመሰለ ወጣት ስትመለከት ለማነጋገር ትሞክርና እንደሚያዳግታት ታስባለች፡፡ በዚህ ጭንቀት ያርዳታል፡፡ ለሁለት ጫፍ ዕድሜ (ለወጣትነትና እርጅና) አንድ አይነት ምላሽ የሚሰጥ አካል እንዴት ሊኖር ይችላል? ለወጣቷ ማሚት እና ለአሮጊቷ ማሚት ክንፈ አንድ ነው? እንደምን? …
ይሄንን ጉዳይ ካዛንትዛኪዝም በ “ዞርባ ዘግሪክ” ውስጥ ሲደግመው አስተውያለሁ፡፡ ዳሜ ሆርቴን (Dame Hortense) የተሰኘች የጥንት ኮማሪት ገፀባህርይ አለችው፡፡ በወጣትነት ዘመኑዋ፣ የክሬት አብዮት በፈነዳበት ወቅት ታፈቅረው የነበረውን ጣሊያናዊ የባህርይ ኃይል ወታደር፣ በስተርጅና ዘመኗ ከአፏ ባለማጥፋቷ በቀቀኗም ስሙን መጥራት ልማዷ አድርጋ፣ “ካናቫሮ” ትላለች፡፡ ሆርቴን የደረሰችው የማሚት እሹሩሩ የገና ለገና ፍርሃት ውስጥ ነው፡፡ ማሚት እሹሩሩም ብትሆን ክንፈን የምሽት ስንቅ ማድረጓ ስለማይቀር፣ በቀቀን የሚኖራት ከሆነ ሥሙ በልምድ ድግግሞሽ ውስጥ ተስተጋቢ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ማሚት እሹሩሩንና ዳሜ ሆርቴን ካወሳን አይቀር የሚመሳሰሉበትን አንዳንድ ነጥብ አንስተን ወደ ድምዳሜ እናምራ፡፡ ሁለቱም እርጅናን ይፈራሉ፤ ሁለቱም ከእርጅና ፍርሃት ጋር እንዳይጋፈጡ የሚከላከሉባቸው አፍቃሪዎች አሏቸው፡፡ ለማሚት ክንፈ፣ ለሆቴን ዞርባ፡፡ ክንፈ ማሚት ከእርጅና ጋር እንዳትጋፈጥ ማታለያ የፍቅር ቅጭልጭልታዎችን ያበጃል፡፡ ዞርባም እንደዚያው፡፡ ሆርቴን በእርጅናና ሞት ፍርሃት ስትርድበት ጊዜ መግዣ ሀሳቦችን ያቀርባል፡፡ “መልካሙ ሐኪም፣ ቮሮኖፍ አንድ አስደናቂ ምርምር አድርጎ እርጅናን የሚያጠፋ፣ ወጣትነትን የሚያመጣ መዳኒት አግኝቷል፡፡ እሱን በበርሜል ሞልቼ አመጣልሻለሁ” ይላታል፡፡ ሆርቴን በተስፋ ተሞልታ እርጅናን በመተው፣ ስለ ሰርግና ስለ ቬሎ ማውራት ትጀምራለች፡፡
ማሚት እሹሩሩና ዳሜ ሆርቴን የሚገናኙበት ሌላ የህይወት መስቀልኛ መንገድም አለ፡፡ ሁለቱም ካደፈ፣ ከጎደፈ ህይወት ውስጥ እንደ ዕንቁ የሚያበራ የወገናዊነት ስራ ሲሰሩ ይስተዋላሉ፡፡ ማሚት ሴተኛ አዳሪነቷን፣ ውበቷን ተጠቅማ ተጣመው ሊያድጉ የተዘጋጁ ወጣት ችግኞችን ታቀናለች፡፡ ክንፈ እና እንዲሁ አንድ ሌላ ወጣት በፍቅር ሳቢያ ችላ ያሉትን ትምህርት እንዲያጠብቁ ብሎም ጠንካራ ተማሪ እንዲሆኑ ስትነግራቸው ይስተዋላል፡፡ ሆርቴን ደግሞ ልጅነቷን፣ ወጣትነቷን አይተው በፍቅር የነሆለሉ አራት የባህር ኃይል አድሚራሎች በክሬት ህዝብ፣ ላይ መድፋቸውን እንዳይተኩሱ ትከላከላለች፡፡ “No Boom-boom!” ትላቸዋለች፡፡ በዚህም ህዝቡን ከእልቂት ታድጋለችና ዞርባ ቦምቦሊና (Bouboulina) ይላታል፡፡ ቦምቦሊና የግሪክ ጀግና ሴት ስም ነው፡ ሆርቴን ብቻ ሳትሆን ማሚትም “ቦምቦሊና” አይደለችም? ጀግንነት ከአንድ ግንባር ብቻ ይገኛል ያለው ማነው? ይሄንን ስብሐትም ሆነ ካዛንትዛኪዝ ቀድመው የተረዱት ይመስላል፡፡
ቀደም ሲል ….
…. ለሕይወት የሞት ነቁጥ፤ ለወጣትነት የእርጅና ሚዲያት አዳብለው የሰው ልጅን እጣፈንታ የሚያዝጎረጉር ደራሲ ስብሀት ገብረእግዚአብሔር ብቻ ይመስለኝ ነበር፡፡ ቆይቶ ኒኮዝ ካዛንትዛኪዝ በ “ዞርባ ዘ ግሪክ” ብዘገይም በንባብ መጣልኝ፡፡ ሞት የህይወት፣ እርጅና የወጣትነት ንቅሳቶች ተደርገው የቀረቡበት የጥበብ ሥራ በሌላው የጀርመናዊው ደራሲ ኸርማን ኸሠ ልቦለድ “Narcissus and Goldmund” ውስጥ ተንፀባርቋል፡፡ ወደፊት እንዳመቸን እንፈትሸዋለን፡፡ ከዚያ በፊት ግን ዞርባን ከስብሐት ህይወት ጋር አንፅረን የምንዳስስበት እንዲቀድም ወድደናል የዚያ ሰው ይበለን፡፡
ማስታወሻ
“ዞርባ ዘ ግሪክ” የተሰኘውን ልቦለድ የእኛው ተፈሪ መኮንን ወደ አማርኛ እንደመለሰው አውቃለሁ፡፡ ከዚያም አለፍ ብሎ ከሁለት አመታት አስቀድሞ ከአሳታሚዎች ጋር ንግግር ጀምሮ ነበር፡፡ እስካሁን የመፅሀፉ ድምፅ አልተሰማም፡፡ የአማርኛ ስነ ፅሁፍን በአንድ እርከን የሚያሳድግ ሥራ እንደሆነ በእራሱ አምናለሁ፡፡ ታዲያ የት ዘገየ? ወይንስ ጨነገፈ? እንኳን መጨንገፉ መዘግየቱም ጉዳቱን የሚያንረው ሥራ ነው፡፡ ቶሎ! ቶሎ! ቶሎ! እንለዋለን ተፈሪ መኮንንን፡፡

Published in ጥበብ

     ስለ አማርኛ ነክ ጉዳዮችና ስለ ኢትዮጵያ ኮከብ የሚል ሁለት መጻህፍቶቹን አይቼለታለሁ፡፡ ዛሬ መጻህፍቶቹ አይደሉም እንድጽፍበት ያስገደዱኝ፡፡ ስለ ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ “ወሪሳ” መጽሐፍ የተመለከተበት የአዲስ አድማስ ነሐሴ 16 ቀን 2007 ዓ.ም የጥበብ ዳሰሳ ጽሑፍ እንጂ!
ጸሐፊው በመቅድሙ ስለ ሕልም ምንነት፣ አስፈላጊነትና የእለት ተዕለት ትሥሥር ለመጥቀስ ይሞክራል፡፡ የዓለማየሁ ገላጋይ “ወሪሳ” ሕልም እና ትንቢት እንደሆነ እንዲሁም፣ ደራሲው በልቦለዱ “ነብይ ነው” ይለናል፡፡ ሃያሲውን ደግሞ ሕልም ፈቺ!!... ሳበሳ…
ዓለማየሁ ገላጋይ ነብይ አይመስለኝም፣ የአሁኑን ነባራዊ ሁኔታ የሚቀነብብ ደራሲ እንጂ፡፡ አሁንን የምናይበት አይናችን ስለተንሸዋረረና አሁን ላይ የሚሰማን ስሜት በስንፍና፣ በመንፈስ ደብዛዛነት እንዲሁም በሐቀኝነት ቅቤ ስላልጠገበ፣ አሁንን የሚገልጹ ጥቂት “ሕልመኞች” ነብይ ናቸው ሲባል መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ (ሌሊሣ ግርማ “ግልብ” ሲል የሚጠራው ትውልድ!!)
በእኔ እይታ “ወሪሳ” በአሁን ላይ እየተኖረ ያለ ትዕይንት እንጂ ያልታየ (የነገ ትንቢት) መዝገብ አይመስለኝም! (ካልመሰለኝ ደግሞ አይደለም እንዳልል አምባገነን የሆንኩ ያስመስልብኛል፡፡) ሃያሲው፤ ሒሳዊ  ነብይ ሆኖ ለመቅረብ የሞከረ ይመስል (ነው አላልኩም ይመስል እንጂ)፤ ትላንትን እንደ ውርጅብኝ ደረቅ ኩነት ሲወርድብን፣ አሁን ላይ ነብይ ነኝ ብሎ የሚለፍፍን ዜና ነጋሪን ይመስላል፡፡ (ትላንትናን አይቼዋለሁ፡፡ ዛሬን በሚገባ ተረድቼዋለሁ፤ ነገን ማየት እችላለሁ፤ ነብይ ነኝ  አይነት የሁለት ሰዓት ዜና!)
አብነት ስሜ፤ “ኢትዮጵያ ክፋትና ክፉ አሸንፎ የሚኖርባት አገር ነች” ይለናል፡፡ ይህንንም የኋላ ታሪኮችን እየጠቀሰ፣ #ኃይለ ሥላሴ ከሞቱ ጸሐይ ትጨልማለች፤ መንግሥቱ ሥልጣን ከለቀቀ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች እያልን ዘምረናል” ብሎ ሲተርክልን፣ “ኢህአዴግ ከሌለ ኢትዮጵያ ብትንትኗ ይወጣል” የሚለውን የአሁን ንቅዘት ሊጠቅስልን አልደፈረም፤ (ፈርቶ ነው እንዳንል ስለ ጀግና እና ስለ ጥበበኛ ምንነት ከርሱ ውጭ የገለጸልን የለም!! ራሡ ፈራጅ ራሱ ወራጅ ይሉሃል ይሄ ነው!!)
“ክርስትናን ከማንም ቀድመን ተቀበልን እንላለን፡፡ ሁለት ሺህ ዓመት ግን ሰይጣን ነው በእግዚአብሔር ስም ሲገዛን የኖረው፡፡” ሲል የሁለት ሺህ ዓመት ታሪክ ፈራጅ ሆኖ በሰይጣን ስም ሲገዝተን ማንም ከሳሽ የለውም (ንቁና ስውር አዕምሮ አሉ ብሎ ሲተርክ፣ ፈራጅ ሕሊና ያለው መስሎ ነበር፡፡)
“ጀግና ብንሆንማ መሪያችን ደመወዝ የምንከፍለው አገልጋይ ብቻ ይሆን ነበር”  ቆንጆዎቹን የሚመሥል ነጥብ ያነሳና፣ “ጀግና ጠቢብም ነው፤ እኛ ጥበብ የሚባል ነገርም አልነበረንም” ሲል አሁንም “ፈራጅ ወራጅነቱ” ቁልቁል ያንከባልለዋል! ኢትዮጵያ አሁን እንዲህ “የእሳት ልጅ አመድ” የሚል ተረት በእውን ደርሶባት፤ ኢትዮጵያ አሁን እንዲህ “ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል …” ብኂል አካፍቶባት፤ አሁን ላይ ፈራጁ በዛባት!  ወራጁም … እንዲሁ!
ኢትዮጵያ ጥበብ አልነበራትም ስትባል በቀላሉ ያልተማሩ እናቶቻችን ጠላ ሲጠምቁ ዓለም አሁን የገነነበትን የመጠጥ ኢንደስትሪ ጥበብ ይዛ የቆየች ነች፤ ትላንትን ጥበብ አልባ የማድረጉ “አላባዊያን” በዝተው፤ ይሕንን ጥበብ ዘመን በሚፈልግበት መንገድ ማሸጋገር የኛ ድርሻ ሆኖ ሳለ፤ የኛን እርግማንና ጨለምተኝነት የትላንትናዎቹ ላይ ቀባናቸው፡፡
በድንጋይ ላይ ጽሑፍን፣ በብራና ላይ ትምህርትን፣ በታሪክ ላይ ጀግንነትን ሲከትቡልን እኛ አሳልፈን የሰጠናትን ኢትዮጵያን በምጸትና በዋዛ ፈረድንባት! እውቀት እንግሊዝን ማወቅና ማንነት ላቲኖችን መቅዳት ሆኖ በተሰበከበት አሁን ላይ የትላንትናዎቹን ጀግኖች በባዶነት ወዝ ቀባናቸው፡፡ ፈራጅ ወራጅ!!
“ይሕ ህዝብ ምን አለ?” ተብሎ ንጉሥ ሲጠይቅ፣ “ዝም አለ” ሲባል የሚፈራ ህዝብ፤ አሁን በጡዘትና በስካር እንዲሁም በባዕዳን መንፈስ ተይዞ የሚሰቃየውን ሕመምተኛ ሕዝብ፤ ብሎም የትላንትናዋ “ታንጉት” ላይ ሲሰለፍባት አልታወቀውም፡፡ ባሕሏን፣ ወጓን፣ ሃይማኖቷንና ቀየዋን አክባሪ፣ አድባሯን ተማጻኝ እንስት፤ አሁን በፐርምና በፈንገስ የምትሰቃየውን እንስት፣ በነጭ አማልክት የምታጓራውን ሴት ቀብቶ፤ የትናንትናዋን ክብርት ሲፈርድባት (ሲደፍራት) ማንም ወቃሽና ከሳሽ አላስቀመጠም፡፡
እሱ ምን ያድርግ ንቁውና ሥውሩ ሕሊናው ተምታቶበት!!
እነ በላይ ዘለቀ አይነት ጀግኖች የወጡባትን ምድር፣ እንደነ ዘርዓይ ድረስ፣ እነ አብዲሳ አጋ፤ ታከለ ወልደሃዋርያት … አይነት ጀግኖች ----- እነ አቡነ ጴጥሮስ፣ እነ ገብርዬ፣ እነ አሉላ አባ ነጋ፣ እነ ሞገስ አሰግዶም፣ እነ ባልቻ … እያልኩ ሰዎችን መጥቀስ ብጀምር ጽሑፌን ባይደክመውም አንባቢን ማድከም እንጂ፣ አብነት ስሜ የጠቀሳቸውን ጥቂት አምባገነን መሪዎች ለመመከት ከላይ የጠቀስኳቸው ከበቂ በላይ ይመስሉኛል፡፡
ሶርያ፣ ግብፅ፣ ኤፌሶን (ቱርክ) ኢየሩሳሌም፣ አንጾኪያ፣ ነብያ፣ ኤርትራ፣ ሊቢያና መሰል ጥንታዊ ቦታዎች አሁን እየፈራረሱ ናቸው፡፡ ቀደምት የክርስትና መስበኪያና መማሪያም  ጉባዔዎች ነበሩ፤ አሁን በሰይጣን ማዕረግ ስር በተሾሙ ግለሰቦች እየተበላሉ ነው፡፡ ዓለምን የሚገዛት ዲያቢሎስ፣ ቅጥረኞቹን ባከበረበትና ባጀገነበት ዘመን፤ የትላንትናዎቹ የጸረ ዲያቢሎስ ጀግኖች ቢሰደቡ፣ ቢፌዝባቸውና ስማቸው ቢከስም አያስደንቅም!!
እኔም ክፍል አንድ ሐሳቤን እዚህ ላይ ልቋጭ፡፡ በቀጣይ ጽሁፌ ስለ መሪነት፣ ስለ ተመሪነት ጥበብ እና ትርጓሜ፣ የተረጋገጠልኝንም ሆነ የተገለጠልኝን ሀሳብ አካፍላለሁ፡፡ ዘለአለማዊነት ለሐሳብ ልዩነት እያልኩ! ሳምንት እቀጥላለሁ፡፡ ቸር እንሰንብት!

Published in ጥበብ
Saturday, 05 September 2015 10:14

የኢንቬስተሩ ችሎት!

 በሽንጠ - ረጅሙና ሁለተኛው ፎቅ ለይ በተንጣለለው ቢሮዋቸው ላይ እስከ ዳር በተነጠፈው ቀይ ምንጣፋቸው ላይ ትንቡክ ትንቡክ ትንቡክ እያሉ በመሄድ ወንበራቸው ላይ ተቀመጡ፡፡ ወደ ግራ ሲያዩ አዲስ አበባ በከፊል አረንጓዴ፣ በከፊል ደግሞ ዝንጉርጉር ህንፃዎችዋን አሳየቻቸው፡፡ ሞቋቸው ስለነበር ኮታቸውን አወለቁና የፀሀፊዋን መጥሪያ ተጫኑ፡፡ ቀይ አፍንጫ ጎራዳ፣ የደም ገንቦ ወጣት መጣች፣ ሽቁጥቁጥ ናት፡፡ አይኖችዋ የተሸከሙት የውበት እሳት ግን ከሩቅ ይለበልባል፡፡ አዩዋትና አጎነበሱ፣ አለቃ እርሷ የሆነች ይመስል፡፡
ወደ ቀኝ መለስ ሲሉ በመስታወት የተለበጠው፣ የመጽሐፍት መደርደሪያ ውስጥ የተሰለፉትን መጽሐፍት አዩ፡፡ አብረሃም ሊንከን፣ ጆንኤፍ ኬኔዲ፣ ዩሊሰስ ግራንት… በተርታ ተሰልፈዋል፡፡ ቀልባቸውን ብዙ አላቆዩም፡፡
“እኔ የምልሽ ይህ ሁሉ ደብዳቤ ምንድነው?”
“እንትኖቹ ናቸዋ ያመጡት?”
ገለጥለጥ አደረጉና አዩት፡፡ የኮንዶሚኒየም ዕጣ የወጣላቸው ሰዎች ያመጡት የእርዳታ ጥየቃ ወረቀት ነው፡፡
“ሰዎቹ ራሳቸው ነው የመጡት?”
“አንዳንዶቹ ለዘበኞች ነው የሰጡት”
“ታዲያ ይህ ሁሉ ሲመጣ አንቺ መመለስ አልነበረብሽም? …. ከልክ በላይ በዝቷል አትይም ነበር?”
የእጅዋን መዳፍ እያፋተገች፤ ‹እሳቸው ደሀ አባት ናቸው፣ ለሀገራችን እግዜር የጣለልን መልዐክ ናቸው፡፡› እያሉ እምቢ አሉ፡፡ … ድሮም የደሀ ጠላት ደሀ ነው እያሉ የተናገሩ ሁሉ አሉ፡፡”
እና ቢሆንስ … የሀገር ሁሉ ደሀ እኔ ላይ መውደቅ አለበት እንዴ? … እኔ ብቻ ነኝ እንዴ ሀብታም? … መድኃኒዓለምን አደረጉኝ እንዴ? … አንድ ቤዛ አደረጉኝ እኮ!”
ዓይናቸውን መለስ ሲያደርጉ በአንድ ታዋቂ ጋዜጣ ላይ የሰጡትን ቃለ ምልልስ ርዕስ አዩት፤ “የሀገሬን ህዝብ መርዳት አይታክተኝም!” ይላል፡፡
ብዙ ሰዎች በቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ አይተዋቸው ስልክ ደውለው ነበር፡፡ በተለይ እንደ ቶልስቶይ “ለድሆች ኖሬ፣ ከድሆች ጋር እሞታለሁ” ያሉትን ሲያደንቁ ነበር የዋሉት፡፡ እንደዚህ እንዲናገሩ የመከራቸው የቢሯቸው የሰው ሀብት አስተዳደር ኩራባቸው ነበር፡፡  
“ምን ዓይነት ሀገር ነው? … አንዴ ቃል ካፍ ካመለጠ….” ሲሉ ፀሐፊዋ ስርጉት “ጋሼ ይሄ ሀገር እኮ መከራ ነው፣ ልቡ የማይታወቅ ህዝብ ነው! … የሰውን ቆዳ ካልገፈፍኩ የሚል፣ ሥራ የማይወድ! በልመና ተወልዶ በልመና ያደገ! … እርሶ እግዜር የባረካትን ሀገር ትተው መጥተው በመስጠት ተወልደው በመስጠት ያደጉ … እንደጌታ ፍጥረት የሚታዩ ቱጃሮች ያሉበትን ሀገር … እዚህ ዓመዳም ሀገር … እኔ እዚያ ሄጄ ጎዳና ተዳዳሪ ብሆን ይሻለኛል፡፡”
“… ምናጣሽ እዚህ …” አሏት ድንገት … እንደቅል የሚያበራ መላጣቸውን እያደራረቁ፡፡
“… መኪና የለኝ ፣ ቤት የለኝ፣ ኑሮ መከራ ነው፡፡ …
ዓይናቸው ወደ ግራ መለሱ፤ አዲስ አበባ በራስዋ ሳቅና እንባ መሀል ተንጠልጥላለች፡፡ ስለዚህ ነገር ብዙ አያውቁም፡፡ እርሳቸው ከሥራ በኋላ ከሆነ ሸራተን አሊያም ሂልተን ነው ውሎዋቸው፡፡
“በይ የኔ ቆንጆ … ሂጂና ከመካከላቸው የባሰ ችግር ያለባቸውን… አሳማኝ የሆኑትን ለይልኝ!...”
“እሺ …” ብላ ሰነዱን ይዛ ሄደች፡፡
… አሁን የኔ ሀብትም ሀብት መሆንዋ ነው? የአሜሪካን ሀብታሞች አላዩ!... አንድ ሪል እስቴት፣ …. አንድ የስፖንጅ ፋብሪካ፣ አንድ የቀለም … ከዚያ ሌላ ሁለት ህንፃዎች… አንድ የትምህርት ተቋም … ብቻቸውን ሳቁ፡፡
ድምፁ አስደንግጧት በሩን ከፍታ “… ፈለጉኝ?” አለቻቸው፡፡ ርቀቷ ከአድማስ ብቅ ያለች ፀሐይ አስመሰላት፡፡ ችግር አለመኖሩን በምልክት ነገሯትና መልሳ ዘጋችው፡፡
“ምን አሳቃቸው?” ብላ መልሳ ደብዳቤዎቹን መክፈት ጀመረች፡፡
የመጀመሪያው… “የደሆች አባት … ጋሽዬ ቴሌቪዥን ላይ ያየሆት ቀን ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፣ ከነቅላትዎ ጌታችንን ቁርጥ! … እሱን ነው ያሰብኩት … አንጀቴን በሉኝ … ፈጣሪ እኛን እንደወደደን አወቅሁ …”
ሌባ ምናቸው ነው መድኀኒዓለምን የሚመስለው?.... ዓሳማ ይመስል አብጠው፣ ማጅራታቸው ራሱ ያንድ ሰው ወገብ ያህል የለ!… እሳቸው በመስቀል ቢሰቀሉ መስቀሉ አይሰበርም!...
ይሄ ደ‘ሞ ሞላጫ ድርሰት ነው!
“የደሀ አባት መሆንዎን ሰምቼ ነው፡፡ በቀበሌ ቤት ስኖር ለልማት ተብዬ ተነሳሁ፣ በዚያ መሀል አንድ የቆርቆሮ መጠለያ በመከራ ተሰጠኝና ስኖር፣ ከሁለቱ ልጆቼ አንዱ በብርድ ታምሞ ሞተብኝ፡፡ ያለ አባት ያሳደኩት ልጅ ነበር፡፡ … ቀን ቀን እንጀራ ጋግሬ ስሸጥ እውላለሁ፣ ማምሻም ከሞት የተረፈ ልጄን እህል አቅምሼ እንጀራ ለመሸጥ ብርድ ሲመታኝ ያመሻል፤ ኑሮዬ የመከራ ነው … ዕጣው እንደ ጥሩ ነገር ደረሰኝ … ይኸው እንቅልፍ አልወስድ ብሎኝ ልሞት ነው፡፡ … በየወሩ የሚከፈለውን ከየት አምጥቼ ነው የምሰጠው?”
የኔን እናት ህይወት ይመስላል፤ ከዚህ የተሻለ ህይወት አልነበራትም፡፡ አባቴ ጨካኝ ባይሆን ይሄኔ ያለ እናት አልቀርም ነበር፡፡ የሰው ቤት ገረድ ሆና አስተምራኝ ሞተች፡፡…
ወደ ወረቀቶቹ ተመለሰች፡፡
“ለአብዮታዊት ኢትዮጵያ በቆራጥነት ተሰልፌ፣ ሀገሬን ከመገንጠል አደጋ ለመታደግ ስታገል አንድ አይኔንና እግሬን ያጣሁ ነኝ፡፡ የደርግ ወታደር ሳልሆን የኢትዮጵያ ወታደር ነኝ፡፡ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የጦር አካዳሚ ምሩቅ ነኝ፡፡ ዛሬ መኖሪያ ቤት እንኳ የለኝም፡፡ ይኸው ኮንዶሚኒየም ተመዝግቤ ዕጣ ቢወጣልኝ የምከፍለው አጥቻለሁ፡፡
ሻለቃ፡፡”
ለእኒህማ ጨምረው ነው የሚሰጧቸው፡፡ አባታቸው የጃንሆይ ክብር ዘበኛ ስለነበሩ ወታደር ሲያዩ ይባባሉ… አለችና ሳቀች፡፡
ሌላው የኢትዮጵያ አባት፤
“እኔ የልጆች አባት ነኝ፤ ድንገት በተፈጠረ የመኪና አደጋ ወህኒ ቤት እገኛለሁ፡፡ ልጆቼን የማስተዳድርበት አንድ አይሱዙ መኪና አደጋ ደርሶበት፣ የብዙ ሰዎች ሕይወት ጠፍቶ የማልወጣው ዕዳ ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ እባክዎ ከዚህ አደጋ ውስጥ ልጆቼን ይታደጉልኝ! ልጆቼም ከትምህርታቸው ተደናቅፈው ቤት ሊውሉ ነው፡፡”
ሳቀች፡፡ አባትዋ የሞቱት በመኪና አደጋ እንደሆነ ሰምታለች፡፡ ብዙም ነፍስ አታውቅም ነበር፡፡ እናትዋን አባርረው ሌላ ሚስት አግብተው እንደነበር ሁሌ የምትሰማው ነገር ነው፡፡ ግን ሆድዋ ባባ፡፡
ሌላኛውን ገለጠች፡፡
“…ለሀገሬ ልማት ሌትና ቀን አልተኛም፤ እጄን ኪራይ ሰብሳቢነት ውስጥ ስላላስገባሁ ደሀ ነኝ፡፡ የምኖረው በቀበሌ ቤት ነው፡፡ ከኔ ጋር የሚሠሩ ዛሬ ሕንፃ አላቸው፤ መኪና ያሽከራክራሉ፡፡ ሠፈራቸው ቦሌ ነው፡፡ እኔ ግን ይኸው ዛሬም ሕዝብን በእውነት ለማገልገል በሕዝቡ መሀል እዳክራለሁ፡፡
ከሁሉ ይልቅ ሕዝቡ ራሱ “ለነፍስህ ነው ለሥጋህ” እያለ መግቢያ መውጫ ያሳጣኛል፡፡ እውነት ዋጋ ታስከፍላለች፡፡ ልማታችን ይቀጥላል! እርስዎ እንደልማታዊ ባለሀብት ጉዳዬን ይዩልኝ”
ከት ብላ ሳቀች፡፡ ረጅም ሣቅ፡፡ ድንቅ ድርሰት!
እያንዳንዱን አገላብጣና መርጣ፣ ለአለቃዋ ይዛላቸው ሄደች፡፡ ስልካቸው ላይ አቀርቅረዋል፡፡ መላጣቸው ቦግ ብሎ ጥቁር ሰማያዊ ሸሚዛቸው ላይ ያለው ነጭ ሸንተረር ደመቀባት፡፡
“ይቅርታ!”
“ግቢ ግቢ … ለየሻቸው?”
“አዎ!”
“የሚያሳምኑ አሉ?”
“እርስዎ ይዩት”
ወረቀቱን አስቀምጣላቸው ወጣች፡፡
ሁሉንም ተራ በተራ እያዩ ሳቁ፡፡ አንዳንዱም አሳዘናቸው፡፡ የተወሰኑት ላይ ፈረሙ፡፡
ከዚያ ስርጉት ተቀብላቸው እያገላበጠች እያየች ሳለ፤ ጥቁሩ፣ ፈገግተኛውና ወፍራሙ የሰው ሀብት አስተዳደር ኃላፊ ኩራባቸው ብቅ አለ፡፡
“እሺ የኔ ቅመም!”
“አለሁልህ”
አንገትዋን አቅፏት፤ “እንዴት ሆነ?”
“ካቀረብካቸው ውስጥ ሦስቱን ለዓመል አሥቀርቼ ሁሉንም ሰጠኋቸው”
“ከዚያ ፈረሙበት በይኛ!”
ቀዝቀዝ ያለች መስላ “የ…ስ” አለችው፤ “አደገኛ ልቦለድ ፀሐፊ ነህ፤ አስለቀስከኝኮ!”
“አንቺን ካስለቀሰሽ፣ ጌቶችን ይታይሽ!”
“የተወሰኑ ሰዎች ግቢ አስገብቻለሁ”
“ምን የሚያደርጉ?”
“ዘበኞች እንዲሰሙዋቸው …ጌቶች ጋ ውሰዱን የሚሉ… የኮንዶሚኒየም ዕጣ የወጣላቸው … ቂቂቂ!”
“አንተ ግን የቴአትር ደራሲ መሆን ነበረብህ!”
“ሆንኩ‘ኮ አስለቀስኩሽ አይደል… ምን ትፈልጊያለሽ! አሁን ለሰዎቹ ትንሽ ሣንቲም ሰጥቼ ላባራቸው፤ የሂሳብ ክፍሉ አቤ ገንዘቡን ሲያወጣ እየመጡ እንዲቀበሉ ሰዎች አዘጋጅቻለሁ፡፡ ያንቺ ሰላሣ ፐርሰንትም ይሰጥሻል!”
“የምን አሜሪካ ነው ታዲያ!” አለችና ሳቀች፡፡
“አሜሪካ መሄድ ቂልነት ነው! እሳቸውም አሜሪካ ሄደው የቀናቸው፣ ትላልቅ ዘመዶች ስለነበሯቸውና ትልቅ ዩኒቨርሲቲ ስለተማሩ ነው፡፡ ሊንከን … ግራንት … ኬኒዲ … የሚሉት ወድደው መሠለሽ፡፡”
“ወንድ ነህ… ግጭ!”
እጅ ለእጅ ተገጫጩ፡፡
“ሕልማችን ተሳካ! ልማቱ ሠመረ!”
ተሣሣቁ፡፡           

Published in ልብ-ወለድ
Page 12 of 16