ጋዜጠኛ የደስደስ ተስፋ በቅርቡ ያሳተመው “እንጀራ ከመከራ” የተሰኘ የግጥም መድበል በዛሬው ዕለት ከቀኑ 9 ሰዓት በሀገር ፍቅር ትንሿ አዳራሽ ይመረቃል፡፡ በ72 ገፆች የተቀነበበው መድበሉ፤ በ25 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

  በህፃናትና ቤተሰብ የምክር አገልግሎት ሙያዋ በምትታወቀው አሜሪካዊቷ ኤልዛቤት እስኮላንድ ተፅፎ በአርቲስት ፈለቀ አበበ የተተረጐመው “አሻንጉሊቴ ረብሻ አይወድም” የተሰኘ የልጆችና የቤተሰብ መጽሐፍ ሰሞኑን በገበያ ላይ ዋለ፡፡
መጽሐፉ ልጆችን አሳታፊ የሥነምግባር መማሪያ መጠይቆችን ከስዕሎች ጋር የያዘ ልቦለድ ታሪክንና ለወላጆች ስለ ህፃናት እንክብካቤ የሚያስተምር ጠቃሚ ምክሮችን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡ በቡክ ላይት መፃህፍት አሳታሚነት ለህትመት የበቃው መጽሐፉ፤ በ30 ብር እንደሚሸጥ ታውቋል፡፡
በተዋናይነቱ የሚታወቀው አርቲስት ፈለቀ አበበ፤ ከዚህ ቀደም “ብርሃንና ጥላ” የተሰኘ የግጥም መድበልና “ፊልም ቦይ” የተሰኘ ትርጉም መጽሐፍን ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡

 በታዋቂው አሜሪካዊ ደራሲ ማልኮልም ግላድዌል “Outliers - The Story of Success” በሚል ርዕስ የተጻፈው መጽሐፍ፤ በተርጓሚ አካሉ ቢረዳ #ወጣ ያለ - የስኬት ታሪክ” በሚል ወደ አማርኛ ተመልሶ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡
ግላድዌል በጥናትና ምርምር ላይ ተመስርቶ በሚያዘጋጃቸው ድንቅ መጻህፍቶቹ በመላው ዓለም የሚታወቅ ደራሲ ሲሆን በተለይ The Tipping Point በተሰኘ የመጀመሪያ መጽሐፉ ከፍተኛ ዝናን ተቀዳጅቷል፡፡
በ214 ገጾች የተሰናዳው “ወጣ ያለ; የተሰኘው መጽሃፉ፤በ100 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
ተርጓሚው ከዚህ ቀደም በርከት ያሉ በስኬት ላይ የሚያጠነጥኑ መጻህፍትን ወደ አማርኛ ተርጉሞ ያሳተመ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አሜሪካ በጃፓን ጥላ ሥር፣ የባለጸጎች አዕምሮ ምስጥር፣ ባቢሎናዊው የሐብት ልኡል፣ የዓለም ታላቁ የንግድ ጥበበኛና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

  በዶክተር ምህረት ደበበ በተፃፈውና በቅርቡ ለንባብ በበቃው “ሌላ ሰው” የተሰኘ ልቦለድ መጽሐፍ ሃሳብ ላይ የአንባቢያን ውይይትና የመጽሐፍ ማስፈረም ዝግጅት ዛሬ ከቀኑ 9፡30 ጀምሮ በደሳለኝ ሆቴል ይካሄዳል፡፡ መጽሐፉም ለሽያጭ ይቀርባል ተብሏል፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም “የተቆለፈበት” የተሰኘ በተደጋጋሚ የታተመ ልብ ወለድ መጽሐፍ ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡

     ክሮሲንግ ባውንደሪ” የተሰኘ ዓለም አቀፍ የትውን ጥበባት ፌስቲቫልና ጉባኤ በመጪው መስከረም ወር አጋማሽ ላይ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የቲያትር ባለሙያዎች ማህበር አስታወቀ፡፡
በፌስቲቫሉ ላይ ከሐገር ውስጥ 9 ትያትሮች የሚቀርቡበት ሲሆን ከውጪ ሀገራትም ከአፍሪካ  እንዲሁም ከአሜሪካና ከእስራኤል የሚመጡ የቴአትር ቡድኖች ስራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል፡፡ ፌስቲቫሉ በክውን ጥበባት ላይ የሚካሄድ ዓለም አቀፍ ጉባኤንም ያካትታል ተብሏል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ ከተለያዩ ሀገራት የተጋበዙ የዘርፉ ምሁራን ጥናታዊ ፅሁፎችን እንደሚያቀርቡ ተጠቁሟል፡፡
በፌስቲቫሉ ላይ የሚካፈሉት ትያትሮች በብሄራዊ ቴአትር፣ በሀገር ፍቅር፣ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ፣ በኦሮሞ ባህል ማዕከል፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝና በአስኒ አርት ጋለሪ ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡
የትውን ጥበባት ፌስቲቫሉን የኢትዮጵያ የቲያትር ባለሙያዎች ማህበር፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከብሄራዊ ቴአትርና ከሰንዳንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁት ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ከኢትዮጲስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር በነገው ዕለት ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ “የደጅ አዝማች ከበደ ተሰማ የታሪክ ማስታወሻ (ከ1904 -1934 ዓ.ም) በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ውይይት እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡
ለውይይቱ መነሻ ሃሳብ የሚያቀርቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነጥበብ እና ዲዛይን ት/ቤት  የስነጥበብ ታሪክ መምህር የሆኑት አቶ አበባው አያሌው ሲሆኑ በወመዘክር አዳራሽ በሚካሄደው በዚህ ውይይት ላይ የሥነፅሁፍ ወዳጆች እንዲታደሙ አዘጋጆቹ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Saturday, 05 September 2015 10:04

ሦስቱ ጥያቄዎች

   አንዳንድ ነገሮችን ለመፃፍ በጣም እቸገራለሁ፡፡ ይመስለኛል አንድም ስለምፅፈው ነገር በደንብ ስለማላውቅ ነው፤ አልያም የማውቀው ነገር ለመፃፍ አይመችም፡፡፡ ስለዚህ መፍትሄው ምንድነው አቅልሎ መጀመር ብቻ ነው፡፡ ከጥያቄ በላይ ቀላል ነገር የለም፡፡
ጥያቄ፡- ምንድነው ጥበብ?
ጥያቄውን አውቀዋለሁ፡፡ ከጥያቄው ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚገናኙ መልስ መሳይ ነገሮች አሉ፡፡ በተለያየ ሰው አንደበት የተነገሩ፣ በተለያየ ተጓዥ የተቀመጡ መዳረሻዎች …
ግን የትኞቹም እንቅጩን አይጨብጡም፡፡ ዙሪያ ገባውን ይዞሩ ይሆናል እንጂ፡፡ ከፍልስፍና ዘርፎች ውስጥ በቁንፅል ብቻ የተጠና ባይተዋር እንደሆነ ድፍን ሆኖ የተቀመጠ ነገር ቢኖር “ጥበብ ምንድነው?” የሚለው ጥያቄና ፍቺው መሆኑን እኔ እና ቤቴ እናምናለን፡፡
የተመረመረበት አጋጣሚ በጣም ውሱን በመሆኑም ምክኒያት እንደ “መለኮታዊ” ሚስጢር ተደርጎ መወሰዱም አልቀረም፡፡  
ምንድነው ጥበብ? ከሚለው የሚቀድሙ ሦስት ጥያቄዎች እንዳሉ ፈላስፎች ይስማማሉ፡፡ አንደኛው ጥያቄ - ጥበብ የሆነውን ፈጠራ ካልሆነው የሚለየው መለኪያ ምንድነው? የሚለው ነው፡፡
ቀጥሎ የጥበብ አላማው ምንድነው? የሚለው ጥያቄ ቢሆንም ሁለተኛው ጥያቄ ራሱ በራሱ ውስጥ ሌላ መጠይቆች ይፈጠራል እንጂ የመጀመሪያውን የ “ጥበብ ምንድነው?” ጥያቄን ቀዳዳ አይደፍንም፡፡
የጥበብ አላማው … ማስተማር ነው፣ ፕሮፓጋንዳ ነው ወይንስ ውበትን መጨበጥ? አላማው የትኛው እንደሆነ የመረጠ ሁሉ ደግሞ ለምን እንደመረጠ በተያያዘ ፅንሰ ሀሳብ ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ ማያያዝ የሚችለው “የጥበብን ምንነት” ማወቅ ከቻለ ብቻ ነው፡፡ ሁለተኛው ጥያቄ ራሱ እንደ ቁንጫ ብዙ የጥያቄ እጮች ፈልፍሎ … ነክሶን ሳይገደል እንዳያመልጥ ተጠንቅቀን (በአውራ እና ሌባ ጣታችን ድብን አድርገን ይዘነው) ወደ ሦስተኛው ጥያቄ እናልፋለን፡፡ በሁለት አለኝ!
ሦስተኛው ጥያቄ … ራሱ ጥበበኛው ወይንም የጥበብ ፈጠራ ወኪሉ ማነው ወይንም ምን አይነት ሰው ነው የሚለው ነውን?
እናም እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ስል እስክሪፕቶዬን ባነሳሁበት ጊዜ ሁሉ ፅሁፍ እንቢ ይለኛል፡፡ መያዣ መጨበጫ የሌለውን ነገር ለመግለፅ እንደመሞከር ስለሚሆንብኝ ነው፡፡
አሁንም ከቀላሉ መጀመር ይሻላል፡፡ በቀላሉ ለመግለፅ ከሞከሩት አሳቢዎች መሀል በአንደኛው በእሱ ትከሻ ላይ በመንጠላጠል ኒውተን እንደመሰከረው “ሩቅ ለማየት” ሳይበጀኝ አይቀርም፡፡
ኮሊንግውድ የተባለ የእንግሊዝ ፈላስፋና ታሪክ ተመራማሪ ጥበብን “ገለፃ ነው” ሲል ይገልፀዋል፡፡ ግን “ገለፃ ሲባል መጠንቀቅ ይገባናል” ይላል ኮሊንግውድ “ገለፃ ማለት ምናባዊ አመለካከት እስከታከለበት ድረስ ብቻ የጥበብ አዝማሚያ ይኖረዋል” ይለናል፡፡
“The Principles of Art” በተሰኘው መፅሐፉ እንደሚያስረዳው፤ “ጥበብ … ተፈጥሮን በቀጥታ ከመቅዳት (Representation)፣ ለኑሮ አገልግሎት ሲባሉ ከሚከወኑ እደ ጥበባት (craft)፣ ማህበረሰብን ለማስደሰት ወይንም ለማጫወት ከሚከወኑት (Amusement) ወይንም የአስማት (ምትሀት) (Magic) ትርዒቶች … ውጭ (በላይ) ነው” ይለናል፡፡
የሀሳብን ተፈጥሮ ከላይ ከተጠቀሱት (ጥበብ አይደሉም) ከተባሉት ጋር ያለውን መመሳሰልና ልዩነት ከተነተነ በኋላ … ምናብ የታከለበት “ገለፃ” ምን ማለት እንደሆነ ለማስረዳት ይሞክራል፡፡
ቋንቋ በሌጣው ስንገለገልበትና ቋንቋን ደግሞ ስሜትንና ሀሳብን ስናስተነትንበት የተለያዩ ምንነት አለው … ስሜት፣ ምናብ፣ ሀሳብና ቋንቋ ሲቀላቀሉ በተናጠል እያንዳንዳቸው ከሆኑትም በላይ የሆነ አውታር ተቀይጦ እንደሚፈጠር ያሳያል፡፡ ይህም የቋንቋ አውታር ራሱን የቻለና … የራሱ የመግባቢያ ህጎች ያሉት ከመሆኑም በላይ በራሱ ህግ እንጂ በንጥረ ነገሮቹ ማንነት ብቻ የሚዳኝ አይደለም ይለናል፡፡
The  origin of art he says, can in man’s physical nature (that is, sensation or its emotions) nor in the intellect (concepts)
እናም የጥበብ ፈጣሪ የጥበብ መገለጥን አገኘ (Has an artistic experience) የሚባለው መስተሀልዩ አንዳች አጋጣሚ የጫረበትን ግርድፍ መነካት (Impression) ወደ ሀሳብ ሲቀይረው … ቀጥሎም በዚህ ሀሳቡ ላይ ምናብን ሲያክልበት (ሊያክልበት ሲችል) ነው፡፡
ምናልባትም ይህ የኮሊንውድ እይታ በተለምዶ “ሮማንቲሲስት” ተብለው ከሚጠሩት የጥበብ ንቅናቄ አራማጆች ጋር የሚያስማማው እንደሆነ ይገመታል፡፡ ከሮማንቲክ ዘመን ገጣሚያን አንዱ የሆነው ወርድስወርዝ … የግጥምን መፈጠር መንስኤው የስሜት መገንፈል፣ ወይንም ፈንቅሎ መውጣት መሆኑን ይገልፃል፡፡
“The spontaneous overflow of powerful feelings originating from emotions recollected in traquility”
ለወርድስወርዝ ጥበብ ማለት የስሜት መገለፅ ማለት ነው፤ ግን ስሜትን ቅርፅና ይዘት ሰጥቶ እስትንፋስ የሚዘራበት “ምናብ” (Imagination) ነው፡፡ የኮሊንግውድን ሀሊዮት ተመርኩዤ የት እንደደረስኩ …. ወይንም በዚህ እይታ ላይ ቆሜ ምን እንደሚታየኝ ለማወቅ  አልችልም፡፡ ምናልባት ምንም ስለማይታየኝ፡፡ እንዲያውም ከቆምኩበት እንግሊዛዊው ፈላስፋ ትከሻ ላይ የሚያሟልጨኝ አንድ ጥያቄ ሲረገዝ ይሰማኛል፡፡ ምናብ እና ምኞትን … ወይንም ምናብ እና ቅዠትን እንዴት ነው እምለያቸው? … በአንደኛው መታወቂያ ወረቀት ሌላኛው ሾልኮ በአርቲስቱ ሀሳብ ውስጥ ዘው ቢል እንዴት ይለያቸዋል?
ግን ኮሊንግውድ ለዚህም መልስ አለው፡- ምኞት (Fancy) በጊዜ እና ቦታ የታጠረ፣ ባይከሰትም ሊከሰት የሚችል … ያልወጣ የሎተሪ እጣ አይነት ነው … ይላል፡፡ ምናብ ግን ከጊዜና ቦታ የተፋታ ግን በጊዜ እና ቦታ መቼም የማያደበዝዛቸውን መሰረታዊ (Vital) የማይለወጡ የህይወት ንጥረ ነገሮችን (Archives) ይዞ ህልሙን የሚያደራ ነው፡፡ ከዚህ ቋሚ መነሻዎች ውጭ በጊዜና ቦታ የተገደቡትን … ወደ ቋሚ ከጊዜና ቦታ ወረተኝነት የማይናወጥ ዘላለማዊነት ለመድረስ ይንጠራራል፡፡
“It dessolves, diffuses, dissipates, in order to recreate; or where this is impossible, yet still, at all events it struggles, to idealize, to unity.”ይህ ሁሉ ጣጣ እንግዲህ የሚከናወነው በአንድ ግለሰብ የማስተዋልና የመፍጠር አቅም ውስጥ ነው፡፡ በአንድ የህይወት ጊዜ ቆይታ ውስንነት ገደብ፡፡
ምን ቢያደርግ ነው አንድ ሰው ራሱን ወደ አርቲስት ቀይሮ … አርቲስቱ ደግሞ በአንድ ገለፃ፣ በአንድ መግለጫ አውታር አማካኝነት ይኼንን ከጊዜም ከቦታም በላይ የሆነ ሁሉንም ነገር በኢምንት ፈጠራ ውስጥ ዘላለማዊ አድርጐ ማስቀመጥ የሚችለው? ስንል … ከቆምንበት የኮሊንግውድ ትከሻ አዳልጦን መውደቅ ይዳዳናል፡፡ ምናልባት እንዳንወድቅ ሊደግፈን ይችል እንደሆን በእርግጥ ባላውቅም አንድ ሠዓሊ በፅሁፍ አስቀምጦልን የሄደው አባባል (ለእኔ) ከመውደቅ ድጋፍ ሲሆነኝ ይሰማኛል፡፡ ይህ ሰዓሊ ቪንሰንት ቫንጎ ይባላል፡፡ ይሄንን ጥበብን በምናብ የማስገኘት አስቸጋሪ እንደሆነ እያወቀ አስቸጋሪነቱን ተሻግሮ መፍጠር የሚቻለው “በፍቅር” ብቻ ነው ይለናል፡፡ አንድን አጋጣሚ፣ ክስተት ወደ ጥበባዊ መነካት (Artistic experience) የሚለውጠው ተመልካቹ … የተመለከተውን ነገር ማፍቀር ሲችል ብቻ ነው ባይ ነው፡፡ ማፍቀር ሲችል ብቻ ነው የነገርየው እውነተኛ ማንነትም ሊገለፅለት የሚችለው ይለናል፡፡ “It is by loving a thing, that one can perceive it better and more accurately”
“መነካት” ማለት የአንድን ነገር ውበት ማየት ማለት ነው፡፡ ለመነካት ግን ማፍቀር ይቀድማል፤ እንደማለት፡፡ እንደ ሰዓሊው ቫንጐ እይታ፡፡
ኦስካር ዋይልድም ያለው ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡ እሱ ግን መነሻውን “ውበት” ነው ያደረገው፡፡ “ማንኛውንም ነገር የምናየው መጀመሪያ ውበቱ ሲገለፅልን ነው” ይላል፡፡ ቫንጎ ከፍቅር፣ ዋይልድ ከውበት ይነሳል፡፡
በኮሊንግውድ የጥበብ ፍልስፍና ላይ ቆሜ ቫንጎን እና ኦስካር ዋይልድን ተመርኩዤ … ሌሎቹን መጀመሪያ ላይ የጠየቅሁዋቸውን ጥያቄዎች እያሰላሰልኩ … ለመልስ እየጓጓሁ … ምናልባት እስከሚቀጥለው የፅሁፍ ድፍረት ጊዜዬ ለመቆየት እችላለሁ፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 05 September 2015 10:03

ገጣሚ ወንድዬ አሊ ስለ ግጥም…

“የአገራችን ግጥም በተስፋና በፅልመት መካከል ያለ ግራጫ ሆኖ ይታየኛል!”
             እንባና ሳቅን አሥማምቶ፣ ያለ ሸንጎና ፍርድ በሀረጋትና ስንኞቹ ትከሻ ለትከሻ ትቅቅፍ ህይወትን አዲስ የሚያደርግ ሰው - ገጣሚ ነው፡፡ ሰማይና ምድርን አሳስሞ ባንድ መኝታ ላይ የሚያጋድም ተዓምረኛም እንደዚሁ … ገጣሚው ነው፡፡ የመላዕክት ክንፎችን ላንብብ፣ የእግዜርን ጓዳ ልፈትሽ ብሎ መጋረጃ ገለጣ የሚደፍር ገጣሚ ነው፡፡
የጠፋን ነገር አሥሶ፤ የራቀን ነገር አቅርቦ የሚያሳይ ንሥር ዓይን ያለው ገጣሚ ከአደባባይ ሲጠፋ፣ … “የት ገባ?” ማለት ያገር ነው፡፡ “የወፌ ቆመች” እና የ “ውበት እና ህይወት” የግጥም መጽሐፍት አባት የሆነው ወንድዬ ዓሊ-የት ጠፋ? የአዲስ አድማስ ፀሐፊና ሃያሲ ደረጀ በላይነህ፣ ከገጣሚ ወንድዬ ዓሊ ጋር በሕይወቱና በግጥም ጥበብ ዙሪያ ተከታዩን ውይይት አድርገዋል፡፡

    ወንድዬ፡- ከአሥር ዓመታት በላይ በግሌ እየሰራሁ ነው፤ ቤቴ ቢሮዬም ሆኗል፡፡ ሥራ ለመቀበል፣ ለማስረከብም ካልሆነ ወይንም የጥናት ወረቀት ከሌለ በስተቀር ከቤቴ አልወጣም፡፡ በየቀኑ ከ12 - 16 ሰዓታት ድረስ እሰራለሁ፤ ይኼ አሰረኝ፡፡ በተለይ ደግሞ ሥነ ጽሑፍ የሕይወትህ ጥሪ - እንጀራህም ሲሆን የበለጠውን እርጋታና ፀጥታ ፍለጋ ከአደባባይ ትጠፋለህ፡፡
በጠፋህባቸው ዓመታት ምን ምን ሰራህ ታዲያ?
በትምህርት (ሙያዬ ልበል ይሆን) ደረጃ ኮሚዩኒኬሽን አጠናሁ - በማስተርስ ደረጃ፡፡ በዚህ ረገድ ከበራሪ ወረቀቶች አንስቶ እስከ ትልልቅ ጥናቶችና መጻሕፍት ዝግጅት ድረስ (እንደ ደንበኞቼ ፍላጎት) ስሰራ ከረምኩ፡፡ አጫጭር ዘገባዊ ፊልሞችም አሉ፣ ሦስት አራት የሚሆኑ፡፡ ይዘታቸውን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ (ኤችአይቪ፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ የልጆች አስተዳደግ፤ የህይወት ክህሎት) እስከ ግለታሪክ ዝግጅቶችና ህትመቶችን ይጠቀልላሉ፡፡ ለነገሩ ኮሚዩኒኬሽን ስትማር ብፌ እንደተመገብክ ቁጠረው፣ ሳይኮሎጂው፣ ስነ ሰብዕ (Anthropology)፣ ስነ - ጽሁፍ እንዲሁም ወደፍልስፍናና አንዳንድ ደረቅ ሳይንሶችም ትጠጋለህ፡፡ ልባም ከሆንክ በንባብና ጥናት አሳድገህ ባለብዙ ፈርጅ ባለሞያ ትሆናህ፡፡ ይህ ደግሞ ኮሚዩኒኬሽን በመማር የሚገኝ ትሩፋት ብቻ ሳይሆን የምንማርበት ተቋም ሥርዐተ ትምህርት፣ የመምህራኑ አቅምና መሰጠት እንዲሁም ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቆይታቸው እውቀትን ለመበዝበዝ ባላቸው ዝንባሌና ጥረት የሚወሰን ይሆናል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ጠነን ያለ፣ ምናባዊ ሸጋ ቋንቋ የሚጠቀም ገጣሚ ነው - ይሉሃል፡፡  ምን ዓይነት ግጥሞች ነው የምትወድደው?
ከስነ ግጥም ዓይነቶች ይልቅ የሚገደኝ ምንጫቸውና አፈጣጠራቸው ነው፡፡ ሰይፉ መታፈሪያ፤ “ግጥም ምንጩ ግለሰባዊ፣. ባፈጣጠሩ ዐይነ - ልቡናዊ፣ ባቀነባበሩ ጭምቅ፣ በቋንቋው ስልታዊ ነው” የሚለው አባባላቸው ይጥመኛል፡፡
ጋሼ ጸጋዬ ደግሞ ማቲው አርኖልድን ጠቅሶ፤ “ሥነ ግጥም ያው የገዛ ሕይወቱ ሂስ ነው” ይላል፡፡ ይህም ግሩም ነው፡፡ ሥነ ግጥም የገዛ ህይወት ሂስ ከመሆኑ ጋር የምደምረው ቁም ነገር አለኝ፤ ይኸውም ከደበበ ሰይፉ የተማርኩት ነው፡፡ “ባድማ ልቡን አድምጦ የሚጽፍ ጸሐፊ ከማህበረሰቡ የተጣላ ነው፡፡” የሚለውን አነጋገሩን እወድለታለሁ፡፡
ከጸጥታና እርጋታ ባሻገር በራስህ ዓለሙን ረስተህ፣ ዓለሙም አንተን ሸጉሮብህ (ቀርቅሮብህ) የምትጽፈው ግጥም የምድረበዳ ምኞት ዓይነት ነው፡፡ በጠየቅኸኝ መሰረት፤ ባብዛኛው የምወደው የግጥም ዓይነት ምሰላን ትርጉም ያላቸውን ይመስለኛል፡፡ የአንድ ቀን ክስተት ተንተርሰው የሚገጠሙ የአዝማሪ ዓይነት ግጥሞችን ብዙም አልወድም፡፡ የአንድ ቀን ገጠመኝ ግን ወደ ህይወት ምሰላ ተለውጦ፣ ሁለንታዊነትን ተላብሶ፣ ሳነብበው ደስ ይለኛል፡፡ ውበት እና ሕይወት ውስጥ “በጥላዬ” የሚለውን ግጥም የጻፍኩት ኃይሌ ገብረስላሴ በኦሎምፒክ መድረክ አንደኛነቱን ለቀነኒሳ ባስረከበበት ቀን ውድድሩን በቴሌቪዥን ካየሁ በኋላ ነበር፡፡ ግና በግጥሙ ውስጥ ኃይሌም ቀነኒሳም የሉም፣ ህይወት ግን ነበረች፡፡ እኔም ነበርኩ፡፡
“ጥላዬ”
የቀደመው ቀረ
   ጀማሪው ፊተኛ
   ፊተኛው ከኋላ
   የኋላው አንደኛ፡፡
    ያልዘቀጠው ወጣ
    የወጣው ዘቀጠ፡፡…
ፊት የወጣች ፀሐይ
    በ-ምዕራብ ሰማይ
    መጥለቂያው በር ላይ፡፡
አዲሷ ከምሥራቅ
    በንጋት አልፋ ላይ
በማለዳ ‘ርከን ላይ፡፡
    እርከኑ እስቲሰበር
    በጭለማ በትር፡፡
የቀደመው ሲቀር፣
የወጣው ሲዘቅጥ፣
ምዕራብ ሲጠልቅበት፣
ጐህ ሲቀድ ለምሥራቅ፣
እነሱን ሲታዘብ … በወጣ … ዘቀጠ
ከገቡበት መቅረት
ከወጡበት መግባት
እንዴት ባመለጠ!?
“ውበትና ሕይወት”ን ካሳተምክ ዘጠኝ ዓመታት አለፉ፤ አሁንስ ግጥም፣ ትጽፋለህ?
ባልጽፍማ ሞቼአለሁ ማለት ነው፡፡ “ውበት እና ሕይወት” በ1998 ዓ.ም ታተመች፡፡ “ወፌ ቆመች” ረቂቁ ለኩራዝ አሳታሚ ድርጅት የተሰጠው በ1982 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ነበር፡፡ የታተመችው በ1984 ዓ.ም ይመስለኛል፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮተቤ የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ እንደተጨማሪ ማስተማሪያ ሆነች፡፡
“ወፌ ቆመች ቅጽ 2 (ውበት እና ህይወት)” ስትታተም ድፍን አገሩ በነፃ ፕሬሶች የተጥለቀለቀበት ጊዜ ነበር፡፡ ስለዚህ ድምፅዋ ሳይሰማ ከገበያ ጠፋች፤ ተሸጠች፡፡ አዳዲሶቹን ግጥሞች “ወፌ ቆመች ቅጽ 3” ለማሳተም የዘመኑን ነገር እያደባሁ ነው፡፡
በዚህ ዘመን በግጥም ሥራዎች ረገድ ምን ገረመህ?
ያልተዘመረላቸው ጀግኖች እንዳሉ ሁሉ ያልተዘመረላቸውም መጻህፍት መኖራቸው! … የኔ መጽሐፍ “ውበት እና ሕይወት” እንኳ በጎምቱ አንባቢዎች እጅ ብቻ ገብታ ለአዲሱ ዘመን ገጣሚያን የስልትና የፍልስፍና ግብዐት ሣትሆን ልሂቃን ልብ ውስጥ መቅረቷ ገርሞኛል፡፡ ጥቂት የተጠቀመበትና ወደ ቀጣዩ ትውልድ ልብ ያሻገራት ሟቹ ብርሃኑ ገበየሁ ብቻ ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ የሥነ - ግጥምን ጥበብ የሚመለከት “ወፌ ቆመችን እንደ ዘሪሁን አስፋው (የሥነ ፅሁፍ መሰረታዊያን በሚለው መጽሐፍ) “ውበት እና ህይወት”ንና “ወፌ ቆመች” ን አዳብሎ በመተንተን እንደ ብርሃኑ ገበየሁ ያሉ ምሁራን አላገጠሙኝም፡፡
“ፎክር ፎክር አለኝ”
ፎክር!
ፎክር!
    አለኝ፣
ነዘረኝ
ነሸጠኝ
ፎክር - ፎክር አለኝ፣
    ሽለላ - ሽለላ፣
አለ ይሆን ዛሬ
    ግብር የሚበላ!? …
ፎክር
ፎክር
አለኝ፡፡
እንዴ …. !
በነ አባጃሎ አገር
በጀግኖቹ ጎራ፣
ገዳይ በጎራዴ
ገዳይ በጠገራ፡፡
በሾተለ አንደበት
    ገዳይ በአፈር ሳታ፣
በነገር ነጎድጓድ
            ገዳይ በቱማታ፤ …
በነዘራፍ ስንቁ
    ባለ ብር ሎቲ፣
በተሞላች አገር ፡-
ጅረት ባበጀባት
ዘንቦ የደም ዕምባ፤
ተራህ ነው ይለኛል፣
ተሠራ ሹርባ፡፡
በአማርኛ ሥነ ግጥም ምን ይታይሃል?
በተስፋና በፅልመት መካከል ያለ ግራጫ ነገር ሆኖ ይታየኛል፡፡
(ይቀጥላል)

Published in ጥበብ
Saturday, 05 September 2015 09:55

የግጥም ጥግ

 የዕንቁጣጣሽ አበባ!

           -ነ.መ.
አንዳንድ ህፃን ዕድሏ፣
ያስታውቃል ከብቅሏ
አበቅቴዋ አይስትም ውሉን
ለእንቁጣጣሽ ልትወለድ፣ ተፅፏል ቃሉ
  ቀድሞውን!
በአበባ ወር የመጣች፣ የዕንቁጣጣሽ አበባ
ትስቃለች ታለቅሳለች - ፣
      የዕድሏን ያህል ለዕማማ!
    የዕድሏን ያህል ለአባባ!!
እንኳን መጣሽ አንች አበባ፣
እንኳን መጣሽ አንች ወለባ!
የጎመንም፣ የገንፎሽም፤ ምንቸቱ
       አንቺው ቤት ይግባ!!
(ለኪዳኔና ለጤና አዲሷን
የዕንቁጣጣሽ
አበባይቱን ለሚቀበሉ፣
ልጆቻቸው ሁሉ)
                 - ነሐሴ 29 2007 ዓ.ም.

Published in የግጥም ጥግ
Saturday, 05 September 2015 09:54

የኪነት ጥግ

ዝነኛ ስትሆን ድክመትህ ሁሉ የሚጋነን ይመስለኛል፡፡
ማሪሊን ሞንሮ
ዝነኛ መሆን ሳይሆን ስኬታማ መሆን ነበር የምፈልገው፡፡
ጆርጅ ሃሪሰን
ዝነኞች ዕድሜ ልካቸውን ታዋቂ ለመሆን ሲለፉ ኖረው በኋላ ላይ እንዳይታወቁ ፊታቸውን በጥቁር መነፅር የሚሸፍኑ ሰዎች ናቸው፡፡
ፍሬድ አለን
የዝነኛ አማካይ የህይወት ዘመን በከሰል ማዕድን ማውጪያ ውስጥ ከሚሰራ ሰው በ20 ዓመት ያንሳል፡፡
ሞቢ
ምን መስራት እንደምፈልግ ብትጠይቁኝ - ዝነኛ መሆን አልፈልግም፤ እኔ የምሻው ትርጉም ያለው ለውጥ መፍጠር ነው፡፡
ሌዲ ጋጋ
የእኔ የስኬት መለኪያ ገንዘብ ወይም ዝነኝነት አይደለም፡፡ የስኬት መለኪያዬ ደስተኛነት ነው፡፡
ሉፔ ፊያስኮ
ዝነኛ ስትሆን ዓለም አንተንና መልካም ስምህን የራሱ ንብረት ያደርገዋል፡፡
ሜጋን ፎክስ
በመጀመሪያ የእግዜአብሔር ልጅ ነኝ፡፡ ዝነኛ ከመሆኔ በፊት የተጠመቅኩ ክርስትያን ነኝ፡፡
Mr.t
ወደፊት ሁሉም ሰው ለ15 ደቂቃ ዝነኛ ይሆናል
አንዲ ዋርሆል
ዝነኛ የመሆን አስከፊው ነገር የግል ህይወትህ መጣሱ ነው፡፡
ጀስቲን ቲምበርሌክ
ብዙ ባጨበጨቡ ቁጥር ደሞዝህ ያድጋል
አና ኸልድ

Published in ጥበብ
Page 13 of 16