ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት የአዕምሮ ህመምተኞች የእንቁጣጣሽ ምግብ ሊበሉ በገበታ ዙሪያ ሆነው ይጨዋወታሉ፡፡
አንደኛው - አንድ ዕንቁላል ነው ያለው ማን ይብላት?
ሁለተኛው - ሁለት ላይ ማካፈል ነዋ በቃ
አንደኛው - ማን ይከፍለዋል?
ሁለተኛው - ወይ እኔ ወይ አንተ ነና
አንደኛው - እኔ አልገባበትም
ሁለተኛው - ለምን?
አንደኛው - በትክክል ዕንቁላሏን ሁለት እኩል ቦታ ለመክፈል አልችልም
ሁለተኛው - እንግዲያው እኔው ራሴ እከፍለዋለሁ
አንደኛው - ብትሳሳት ግን መልሰህ ትገጥመዋለህ - ዕወቅ
ሁለተኛው - እንደሱ ከሆነማ እኔም አልገባበትም!
አንደኛው - ታዲያ ምን እናድርግ?
ሁለተኛው - ዕጣ እንጣል
አንደኛው - ዕጣውን ማን ይፅፋል?
ሁለተኛው - ወይ እኔ ወይ አንተ ነሃ!
አንደኛው - እኔ አልገባበትም
ሁለተኛው - ለምን?
አንደኛው - ምልከት ብታረግበትስ?
ሁለተኛው - በደምብ ጠጋ ብለህ እየኛ!
ይህን ሲባባሉ አንድ መንገደኛ ያይ ኖሮ፣
“እንግዲህ ዕጣ እስክትጣጣሉ ድረስ‘ኮ ዕንቁላሉ ቀዘቀዘ” አላቸው፡፡
አንደኛው ብድግ አለና፤
“ዕጣ እማንጣጣለው በአንድ ጉዳይ ብቻ ነው”
መንገደኛው፤
“በምን?”
አንደኛው፤
“ያንተን መንጋጭሌ በማውለቅ!”
አለና መንገደኛውን አገጩን በቡጢ አነገለው!
*  *   *
ያለጉዳያችን ጣልቃ ስንገባ የሚገጥመን ነገር አይታወቅም፡፡ ራስን ችሎ በራስ ተማምኖ መጓዝ መልካም ነው፡፡ በአዲስ ዓመት የማያጠራጥር በምግብ ራስን መቻልን ይስጠን፡፡
በአዲሱ ዓመት ለትንሽ ለትልቁ ዕጣ የማንጣጣልበት እንዲሆንልን እንፀልይ፡፡
አዲሱ ዓመት የተሻለ ሹምና መልካም አስተዳደርን የሚሰጠን እንዲሆንልን እንመኝ፡፡
አዲሱ ዓመት ተስፋችን የሚለመልምበት፣ ከድርቅ የምንርቅበት ያድርግልን፡፡
አዲሱ ዓመት ፍትህ ርትዕ የሚሰፍንበት፣ የተዛባ የሚቃናበት ይሁንልን፡፡
አዲሱ ዓመት ከአምና የምንማርበት፣ የዘራነውን የምንለቅምበት፣ የወለድነውን የምንስምበት፣ ትምህርታችንን ይግለጥልን የምንልበት ይሁንልን፡፡ ከመጠምጠም መማር የሚቀድምበት፡፡ የተማረ የሚከበርበት ይሁንልን፡፡
አዲሱ ዓመት የማንወሻሽበት፣ ግልፅነትን የምናዳብርበት፣ ተንኮልን የምናስወግድበት ያድርግልን!
አዲሱ ዓመት ደግመን ደጋግመን ራሳችንን የምንመረምርበት፣ አንድነታችንን የምናይበት፣ ባህላችንን የምናከብርበት፣ በማንነታችን የምንኮራበት ያድርግልን፡፡
አዲሱ ዓመት አዲስ ትውልድ የምንኮተኩትበት፣ አበባ የምናሰባስብበት፣ ፍሬ የምንለቅምበት ይሁንልን፡፡
አዲሱ ዓመት ምሬት ወደ ምርት የሚለወጥበት እንዲሆን ያድርግልን!
ከሁሉም በላይ አዲሱ ዓመት የጊዜን አጠቃቀም የምናውቅበት፣ አርፍደን የማንፀፀትበትና “በጊዜ የመጣ እንግዳ እንደረዳህ ይቆጠራል” የሚለውን ተረት በቅጡ የምናጤንበት እንዲሆንልን፣ ትጋቱን ይስጠን!


           መልካም አዲስ ዓመት!

Published in ርዕሰ አንቀፅ

       አሮጌ ብለን የምንሸኘው የ2007 ዓ.ም በርካታ አነጋጋሪ፣ አሳዛኝና አስደሳች ክስተቶችን አስተናግዷል፡፡ ጥቂቶቹን እንቃኛቸው፡፡
“ሃና ላላንጐ…”
በአመቱ ብዙ ኢትዮጵያውንን ካሳዘኑ አነጋጋሪ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የ16 ዓመቱ ወጣት ሃና ላላንጎ ላይ የተፈፀመው ዘግናኝ ጥቃት ነው፡፡ የ10ኛ ክፍል ተማሪ የነበረችው ሃና፣ በአምስት ወጣቶች ተደፍራ ህይወቷ አልፏል፡፡ ደፋሪዎቹም፣ ከ17 አመት እስከ እድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡ ድርጊቱ በጥቅምትና በህዳር ወር አዲስ አድማስ ጋዜጣን ጨምሮ በበርካታ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በስፋት ተዘግቧል፡፡
እልቂትና የስደተኞች መከራ
በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በያሉበት፤ በሀገር ቤት ያሉትም በሃዘንና በቁጭት የተንገበገቡበት መርዶ የተሰማው በሚያዚያ ወር ነው፡፡ 30 ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ አሰቃቂ ግድያና ጭፍጨፋ የተፈፀመው፣ ‹አይኤስ› በተሰኘው አሸባሪ ቡድን ነው፤ በሊቢያ፡፡
የሰቆቃ ጊዜ ነበር፡፡ የስደት መከራ ሳያንስ በሰው ልጅ ዘንድ ለማመን የሚከብድ ጭካኔ ተፈፀመባቸው፡፡ በዚያው  ሰሞን 900 ገደማ አፍሪካውያን ስደተኞችን ጭና፣ ከሊቢያ ወደ ጣሊያን የምትጓዝ ጀልባ ሰጥማ፣ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ህይወት አልፏል፡፡ አዲስ አድማስ ይህንን አሳዛኝ ክስተት በመከታተልና የሟች ቤተሰቦችንና ወዳጆችን በማነጋገር ተገቢውን የዘገባ ሽፋን ሰጥታለች፡፡ 17 ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ህይወታቸውን በዚህ አደጋ አጥተዋል፡፡
በወርሃ ሚያዚያ፣ በሃይማኖት አክራሪነት የሚፈፀም ዘግናኝ ድርጊትንና በስደት ሳቢያ የሚከሰት አሳዛኝ አደጋን ብቻ ያየንበት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን የዘረኝነት ሰለባ የሆኑበትም ወር ነበር፡፡ በደቡብ አፍሪካ፣ የውጭ ዜጐችን አላማ ያደረገ ዘረኝነትን (ዜኖፎቢያን) የሚያራግቡ ቡድኖች በኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያን ላይ የጥቃት ዘመቻ አካሂደዋል፡፡ 3 ኢትዮጵያውያን በዚሁ ጥቃት በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውና የበርካቶች ንብረት ወድሞ ከኑሮ መፈናቀላቸው ተዘግቧል፡፡
በአመቱ የኢትዮጵያውያን የስደት ህይወት በአሠቃቂ ክስተቶች የተሞላ ሆኖ አልፏል፡፡
የድርቅ አደጋ
እያሰለሰለ በሚከሰተውና ኤልኒኖ በተሰኘው አለማቀፍ አየር ፀባይ መዛባት ሳቢያ በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተከሰተው የዝናብ እጥረት የሚሊየኖችን ኑሮ አናግቷል፡፡ የተዘሩት እህል በቡቃያነቱ የጠወለገባቸው፣ በመኖ እጦት የቤት እንስሳት የሞቱባቸው 4.5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል፡፡ የተጎጂዎች ቁጥር እስከ 6 ሚሊዮን ይደርሳል የሚሉ የእርዳታ ድርጅቶችም አሉ፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጉብኝት
ባራክ ኦባማ፣ በኢትዮጵያና በአሜሪካ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያን የጎበኙ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ድጋፍና ተቃውሞንም ያስተናገደ ነበር፡፡ ከአመት በፊት ከታሰሩ ጦማሪያንና ጋዜጠኞች መካከል 5ቱ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር የተለቀቁት በፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ዋዜማ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ፣ ከእስር የተፈታችውም በዚሁ ጊዜ ነበር፡፡ ትችትና ድጋፍ ባስተናገደው ጉብኝት ላይ፣ ባራክ ኦባማ ያስተላለፉት መልእክት አንድ ወጥ አልነበረም፡፡ የፓርላማ ምርጫ በሰላም መካሄዱን ደግፈው፣ ነገር ግን የተቃዋሚ ፓርቲዎችና የጋዜጠኞች እስርን ወይም ወከባን ማስቀረት፣ የፖለቲካ ነፃነትን ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ዋና ትኩረታቸው ግን፣ የኢትዮጵያ ጦር አሸባሪነትን የመዋጋት ብቃት አለው በሚለው ነጥብ ላይ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የአባታቸው ሃገር ኬንያንም ጐብኝተዋል፡፡
የግንቦቱ ምርጫ
በአመቱ አነጋጋሪ የነበረው ምርጫ፣ ከዝግጅቱ እስከ ውጤቱ ድረስ አከራካሪ ሆኖ ዘልቋል፡፡ ገዥው ፓርቲና አጋሮቹ የፓርላማና የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን መቶ በመቶ፣ ማሸነፋቸው አንዱ አከራካሪ ጉዳይ ነው፡፡ ከምርጫው ቀደም ብሎ በተለይ በአንድነት ፓርቲ መሪዎች መካከል እንዲሁም የመኢአድ ፓርቲ ውስጥ የተፈጠሩ አለመግባባቶች ላይ፣ ምርጫ ቦርድ ያሳለፋቸው ውሣኔዎችም በርካታ ትችቶችን ያስከተሉና በማህበራዊ የሚዲያ መድረኮች ያከራከሩ ጉዳዮች እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡
የመቀሌው የኢህአዴግ ጉባኤ
ከመቀሌው የኢህአዴግ ጉባኤ ቀደም ብሎ፣ አራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች የየራሳቸውን ጉባኤ አድርገው በኃላፊነት ላይ የነበሩ መሪዎችን በዚያው እንዲቀጥሉ ወስነዋል፡፡ በኢኮኖሚ መስክ ኢንዱስትሪና ኤክስፖርት አለማደጋቸው አሳሳቢ ነው፤ በፖለቲካው መስክ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች አሳሳቢ ናቸው፡፡ የሚሉ ሃሳቦች ተደጋግመው በተነሱበት የመቀሌው የኢህአዴግ ጉባኤ፣ የዘረኝነትና የሃይማኖት አክራሪነት አደጋዎችም አስጊ እንደሆነ መክረንበታል ብለዋል የድርጅቱ ቃል አቀባይ፡፡  ጉባኤው የተወሰኑ ነባር አመራሮቹን ከስራ አስፈፃሚነት አሰናብቷል፡፡
ተመርቆ የቀረው የባቡር ፕሮጀክት
የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ችግር ያቃልላል ተብሎ ከ3 አመት በፊት የተጀመረው የቀላል ባቡር ፕሮጀክት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በተገኙበት ተመርቆ ወደ ሙከራ ስራ መግባቱን ያበሰረው በየካቲት ወር ነው፡፡ ከ3 ወር ሙከራ በኋላ የህዝብ አገልግሎት ይጀምራል ቢባልም፣ በኤሌክትሪክ ሃይል እጦት ሳቢያ፣ ሙከራውን ማጠናቀቅ ተስኖታል፡፡ ምናልባት በአዲሱ አመት ስራ ይጀምራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የበርበሬና የምስር ዋጋ
መፍትሄ ከናፈቃቸው የዘይት፣ የስንዴ ዱቄት፣ የስኳርና የመሳሰሉ እጥረቶች በተጨማሪ፣ የመረጋጋት አዝማሚያ የነበረው የዋጋ ንረት፤ ከዓመቱ አጋማሽ ወዲህ ከ10% በላይ እያሻቀበ መምጣቱ፣ አነጋጋሪ ሆኖ ከርሟል፡፡ የበርበሬና የምስር ዋጋ በእጅጉ መናሩን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በርበሬ ኪሎ እስከ 180 ብር የተሸጠበትና ምስር በኪሎ እስከ 70 ብር የደረሰበት ዓመት ነው፡፡ መንግስት ኋላ ላይ በርበሬ በድብቅ ወደ ውጪ እየተላከ መሆኑን አረጋግጫለሁ፤ እርምጃም እወስዳለሁ ሲል ቢደመጥም፤ የበርበሬ ዋጋ ከተሰቀለበት ሳይወርድ አይቀመሴ ሆኖ ወደ አዲሱ አመት ተሻግሯል፡፡
የቢራ አብዮት
በ2007 መግቢያ ላይ፣ ሄኒከን ኩባንያ “ዋሊያ ቢራ መልካም አዲስ አመት” በሚል፣ አዲስ የቢራ ምርቱን ሲያስተዋውቅ፤ አቃቂ አካባቢ የተገነባው ፋብሪካውም በጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ተመርቆ በይፋ ስራ ጀምሯል፡፡ በአመቱ የቢራ ገበያውን የተቀላቀሉት ራያ ቢራ እና ሐበሻ ቢራ የአብዮቱ አካል ሆነዋል፡፡ አመቱንም ከቀደሙት አመታት በተለየ የቢራ አብዮት የተቀጣጠለበት ዓመት ያደርገዋል፡፡ የሜታ ቢራ ባለቤት የፈረንሳዩ ኩባንያ ዲያጆ፣ ‹ዘመን› የተሰኘ ቢራ ያስተዋወቀ ሲሆን፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ አምራች ቢጂአይ እንዲሁም ዳሽን ቢራ በማስፋፊያና በማስተዋወቁ ፕሮጀክት የተጠመዱበት ዓመት ሆኗል፡፡

አመቱ የምርጫ አመት ነበር፡፡ ምርጫው በአፍሪካም እንኳን ቢሆን ከደረጃ በታች የሆነ፣ በዲሞክራሲ ስም ትልቅ ቀልድ የተቀለበት ውድድር ነበር፡፡ ይሄ በዓመቱ ውስጥ በመጥፎነቱ የተመዘገበ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአብዛኞቹ የኦሮሚያ አካባቢዎች ወጣቱ ለመብቱና ለነፃነቱ ለመታገል የነበረው ቁርጠኝነት እንዲሁም አምባገነኖችን ለመሸከም ትከሻ እንደሌለው ያሳየበት ስለነበር በዚያ ምርጫ ውስጥ መግባቴ ልዩ ደስታን ሰጥቶኛል፡፡
በነዚህ በሁለቱ መሃል ነው እንግዲህ አመቱን ያሳለፍነው፡፡ አሁንም ለዴሞክራሲ የምናደርገው ትግል ይቀጥላል፡፡ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር የለውም፡፡ ህዝቡ ተቃዋሚን ለመምረጥ ችግር አልነበረበትም፡፡ የድምፅ ሌባን ለመጠበቅ ግን አልቻለም፡፡ ትልቁ ክፍተታች እሱ ነው፡፡ እንግዲህ ድምፁንም ለማስጠበቅ የሚችል ህዝብ ማደራጀት ይገባል ማለት ነው፡፡
ተቃዋሚው ግን የታሪክ ፈተናውን አሁንም አላለፈም፡፡ የትብብር ጥያቄ ላለፉት 40 ዓመታት ምላሽ አላገኘም፡፡ ይሄ ተቃዋሚው መስራት ያለበት ትልቁ የቤት ሥራ ነው፡፡ ያንን ካላደረገ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ይሄ በቅጡ ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ የተቃዋሚው ትልቁ ፈተና እሱ ነው፡፡
በመጪው አዲስ ዓመት ተቃዋሚው ራሱን እንደገና ያደራጃል፣ ወደተባበረ ትግልም ይገባል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ተቃዋሚዎች ተባብሮ መታገልን መርጠው እንዲንቀሳቀሱ አደራዬ የጠበቀ ነው፡፡

“የበግና የበሬ ዋጋ ብዙ ጭማሪ አላሳየም”

   በዘንድሮ የአዲስ አመት የበዓል ገበያ፣ የዶሮ ዋጋ ከበፊቱ በእጥፍ የጨመረ ሲሆን የበግና የበሬ ዋጋ ካለፉት በአላት የተሻለ እንደሆነ ነጋዴዎችና ሸማቾች ተናገሩ፡፡
በአቃቂና በሳሪስ አካባቢ ዶሮ ከ200 ብር እስከ 400 ብር የሚሸጥ ሲሆን፤ በግ ከ1100 እስከ 3500 ብር፣ በሬ ከ4500 እስከ 25ሺ ብር፣ ፍየል ከ750 እስከ 4ሺ ብር እየተሸጡ ነው፡፡ በሾላ ገበያ በግ ከ900 ብር እስከ 4500 ብር፣ በሬ ከ5 ሺህ እስከ 22 ሺህ ብር ሲሸጥ፤ የዶሮ ዋጋ ከ180 እስከ 350 ብር  እንደሚደርስ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በካዛንቺስ አካባቢ ደግሞ በግ ከ800 ብር እስከ 3 ሺህ ብር የሚገኝ ሲሆን የዶሮ ዋጋ ከፍተኛው 400 ብር ነው፡፡ በዘንድሮ የበዓል ገበያ ለእርድ ከሚውሉ እንስሳት መካከል የዶሮ ዋጋ ከአምናው በዓል በእጥፍ የጨመረ ሲሆን የበግና የበሬ ዋጋ ግን የተረጋጋ ነው ተብሏል፡፡
አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የበግና የበሬ ነጋዴዎች በሰጡት አስተያየት፤ ዘንድሮ በቁም እንስሳት አቅርቦት በኩል ችግር እንደሌለ ጠቁመው፣ ከብት አርቢው ዋጋ ለቀቅ በማድረጉ ብዙም ጭማሪ አላደረግንም ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል በበአሉ ወሳኝ ከሆኑት መካከል በአብዛኞቹ የአዲስ አበባ የገበያ ስፍራዎች ቅቤ በኪሎ እንደየአገሩ ከ140 ጀምሮ እስከ 250 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ የቅቤ ገበያም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር እንደየደረጃው በኪሎ ከ30 ብር ጀምሮ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ቀይ ሽንኩረት በአትክልት ተራ ገበያ በችርቻሮ ከ14.50 እስከ 16 ብር በጅምላ ደግሞ ከ13-50 እስከ 14 ብር እንደየአይነቱ እየተሸጠ የሚገኝ ሲሆነ በሾላ ገበያም ከ13 ብር እስከ 14 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡  
ነጭ ሽንኩረት በተለያዩ የገበያ ቦታዎች በኪሎ ከ60 ብር ጀምሮ እስከ 70 ብር እየተሸጠ ሲሆን፡፡ አይብ በኪሎ ከ40-50 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
የአበሻ እንቁላል በአብዛኛው የመዲናችን ገበያዎች 3.30 እስከ 3.75 እየተሸጠ ሲሆን የፈረንጁ ከ3.50 እስከ 3.75 በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡

Published in ዜና

       ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግም ሆነ ዋነኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባለፈው ዓመት ቀላል የማይባሉ ችግሮችና ፈተናዎችን ቢጋፈጡም ስኬታቸው ላይ ማተኮርን የመረጡ ይመስላል፡፡ ሁለቱም ጐራዎች ዓመቱ በስኬት ማለፉን ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ፤ የዓመቱ ዋነኛ እቅዱ በምርጫው መሳተፍ እንደነበር የጠቆሙት ሊቀመንበሩ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ ፓርቲያቸው በተወዳደረባቸው የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባዎች በ100ሺ ከሚቆጠሩ ሰዎች ጋር መገናኘት መቻላቸውን እንደ ከፍተኛ ስኬት እንደሚቆጥሩት ተናግረዋል፡፡ ለምርጫው ወደ 1ሺ ገደማ እጩዎች ማቅረባችንም ሌላው ስኬታችን ነው ይላሉ - ሊቀመንበሩ፡፡ የምርጫው ውጤት ግን በፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ስኬታማ አልነበረም - ብለዋል፡፡ መድረክ ከምርጫው በፊት ከገዢው ፓርቲ ጋር ለመደራደር አቅዶ እንደነበር የጠቆሙት ሊቀመንበሩ፤ ከገዥው ፓርቲ በኩል ፍላጎት ባለመኖሩ ግን ጥረቱ ሣይሳካ መቅረቱን ጠቁመዋል፡፡ “በዓመቱ ከያዝናቸው እቅዶች አብዛኛውን አሳክተናል፤ አመቱም የተሳካ ነበር ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ ናቸው፡፡ በ5ኛው አገራዊ ምርጫ እጩ ለማስመዝገብ ያደረግነው ጥረት በእጅጉ የተሳካ ነበር የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ “በገዥው ፓርቲ ተፅዕኖ ምክንያት በምርጫው ውጤት ማጣታችን ግን አሳዝኖናል” ብለዋል፡፡ በአዲስ ዓመት ፓርቲው አደረጃጀቱን በማስፋትና በንቃት በመንቀሳቀስ ለቀጣይ ምርጫ ዝግጅት እንደሚያደርግ ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው፤ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በህብረት ለመስራት  እንደሚጥሩም ገልፀዋል፡፡
ባለፈው የግንቦት ምርጫ በአዲስ አበባ ከኢህአዴግ ቀጥሎ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ መዋቅሩን በመዘርጋት ረገድ ስኬታማ እንደነበር ጠቁሟል፡፡ የፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት ሰብሳቢ አቶ ይድነቃቸው ከበደ፤ በምርጫው የስርአት ለውጥ ለማምጣት ቢያቅዱም እንዳልተሳካላቸው ተናግረዋል፡፡ “እቅዳችን የስርአት ለውጥ ማምጣት በመሆኑ ባለፈው ምርጫ ያገኘነው ውጤት ለቀጣይ ጉዞአችን ያግዘዋል” ብለዋል ሰብሳቢው፡፡ ኢህአዴግ በበኩሉ፤ ዓመቱ የ1ኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በስኬት የተጠናቀቀበትና ሃገሪቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሸጋግራታል ተብሎ የታሰበው ሁለተኛው እቅድ ይፋ የሆነበት አመት በመሆኑ እንዲሁም 5ኛው አገራዊ ምርጫን በውጤታማነት በማጠናቀቁ 2007 ስኬታማ አመት ነበር ብሏል፡፡
ፓርቲው የመጀመሪያውን እቅድ አፈፃፀም ገምግሞ፣ ሁለተኛውን በተጠና መልኩ አዘጋጅቶ ለህዝብ ውይይት ማቅረቡን የጠቀሙት የኢህአዴግ ፅ/ቤት የህዝብና የውጪ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደስታ ተስፋው፤ በዓመቱ የተከናወነው ምርጫም በሰፊ የህዝብ ተሳትፎ በስኬት ተጠናቋል  ብለዋል፡፡በህዝብ ውይይት ወቅትም ሆነ በ10ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ የመልካም አስተዳደርና የልማት ተደራሽነት ጉድለቶች እንዳሉ መገለፁን የተናገሩት ኃላፊው፤ በቀጣይ በነዚህ ጉዳዮች ላይ በተለየ ትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡ የድርጅቱ ቀጣይ እቅድ በጉባኤው የተላለፉትን የለውጥ ሃሳቦችና የእድገት እቅዱን ማሳካት ነው ያሉት ኃላፊው፤ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች እንሰራለን ብለዋል፡፡ ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች፤ አዲሱ ዓመት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የለውጥና የብልፅግና እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡  

Published in ዜና

   የፍቅር አዲስ - “ምስክር”

ታዋቂዋ ድምፃዊት ፍቅር አዲስ ነቃጥበብ፤እንደ ብዙዎቹ ድምጻውያን ሁሉ ለብዙ ዓመታት ድምጽዋን ሳንሰማ ቆይተናል፡፡ 2007 ዓ.ም ሊሰናበት ጥቂት ቀናት ሲቀሩትና አዲሱ ዓመት ለመጥባት እየተሽኮረመመ ሲጠባበቅ እሷ በመሃል 8ኛ የዘፈን አልበሟን ይዛ ከተፍ አለች፡፡  ቢያንስ ፍቅር አዲስ በዚያው አልቀረችም ወይም ተስፋ ቆርጣ የሙያ ዘርፏን አለወጠችም፡፡ በዚህም ትደነቃለች፡፡ የፍቅር አዲስ የዘመን መለወጫ ስጦታዋ - “ምስክር; ይሰኛል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ታዋቂዋ ድምፃዊት ፍቅር አዲስ ነቃጥበብ፤እንደ ብዙዎቹ ድምጻውያን ሁሉ ለብዙ ዓመታት ድምጽዋን ሳንሰማ ቆይተናል፡፡ 2007 ዓ.ም ሊሰናበት ጥቂት ቀናት ሲቀሩትና አዲሱ ዓመት ለመጥባት እየተሽኮረመመ ሲጠባበቅ እሷ በመሃል 8ኛ የዘፈን አልበሟን ይዛ ከተፍ አለች፡፡  ቢያንስ ፍቅር አዲስ በዚያው አልቀረችም ወይም ተስፋ ቆርጣ የሙያ ዘርፏን አለወጠችም፡፡ በዚህም ትደነቃለች፡፡ የፍቅር አዲስ የዘመን መለወጫ ስጦታዋ - “ምስክር; ይሰኛል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ድምጻዊቷን የእንቁጣጣሽ እንግዳ አድርጓታል፡፡


 አዲሱ አልበምሽ ምን አይነት ይዘት አለው? ዘመናዊ ነው ባህላዊ?
ዘመናዊ፣ ባህል ዘመናዊ እና ባህላዊ ዘፈኖች ናቸው የተከታቱበት፡፡
 በግጥምና ዜማ እነማንን አሳተፍሽ?
ይልማ ገብረአብ፣ ተስፋ ብርሃን፣ አበበ መለሰ፣ ፀጋዬ ደቦጭ፣ ቢኒያሚር አህመድ፣ ጋዜጠኛ ዮናስ አብርሃም (በተለይ “እናት” የሚለውን ከአቤ ጋር በመተባበር የገጠመው ዮናስ ነው) የሙዚቃ አቀናባሪው ወንድሜነህ አሠፋ ራሱ አንድ ዜማ ሠርቶልኛል፡፡
ባለፈው ጊዜ ቴዲ ማክ ብቻውን ይመስለኛል አልበምሽን ያቀናበረው፡፡ አሁን ደግሞ የተለያዩ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል ------
አዎ ወንድሜነህ አሠፋ ከወንድሞቹ ጋር ሆኖ ነው ያቀናበረው፡፡ ሃብታሙ የሻምበልና ብርሃኑ ሞላ ማሲንቆ ተጫውተዋል፣ ክራር ደግሞ አበበ መለሰ አለ፡፡ ሌላው አቀናባሪ ካሙዙ ካሣ ነው፡፡ ሣክስ ሚካኤል መላኩ አለ፤ሊድ ጊታር ግሩም መዝሙር ነው የተጫወተው፡፡ ማስተሪንግና ሚክሲንግ----በአጠቃላይ በዋናነት የሠራው ወንድሜነህ አሠፋ ነው፡፡
በአዲሱ አልበምሽ በተለየ የድምጽ አወጣጥና ቅላጼ እንደመጣሽ የሚናገሩ አድማጮች አሉ፡፡ በእርግጥ አልበሙን የተለየ ለማድረግ ሞክረሻል? የተቀየረው ነገር ምንድን ነው?
አዎ---- ስንሰራውም ጥሩ እንደሆነ አውቀነዋል፡፡ የሠራው ሰው ደስ ካለው፣ ሌላውም እንደሚደሰት ጥርጥር የለውም፡፡ በፊት ቅኝቶች ብዙም ሠርቼ አላውቅም፡፡ አሁን ትዝታ ማይነር አለ፣ ትዝታ ማይነሩ “ባሻ ወልዴ” ነው መጠሪያው፡፡ ግጥሙን ይልማ ገ/አብ ነው የፃፈው፡፡ የድሮን ትዝታ የሚቀሰቅስና የሚያስታውስ ነው፡፡ አራዳ አካባቢ ፈርሶ፣ የምፈልገውን ልጅ አጣሁት የሚል አይነት ነው፡፡ ለሱ መጥፋት ምክንያት የሆነው የከተማው መስፋት ነው፣ የሚል ይዘት ያለው ቆንጆ ግጥምና ዜማ ነው፡፡ ግጥሙን ይልማ በደንብ ነው ያስጠናኝ፤ ተጨንቀንበት የሠራነው ስራ ነው፡፡ እንግዲህ በአጠቃላይ ዜማዎቹን ጥሩ አድርጌ እንድሠራ የተለመደ ድጋፉን ያደረገልኝ ባለቤቴ አቤ ነው፡፡
የአሁኑ አልበምሽ ከቀድሞዎቹ በምን ይለያል?
እንግዲህ ስለ ፍቅር ብዙ ጊዜ አዚመን እናውቃለን፡፡ ይሄኛው አልበም ላይ ያለው የፍቅር አገላለፅ ግን ትንሽ ይለያል፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያው “በለው በለው” የሚለው ዘፈን፣ ዜማውን ለይልማ ስንሰጠው እንዴት አድርጎ አሳምሮ እንደሰራው ለኔም ይገርመኛል፡፡ ሌላው ቢኒያሚር የሰጠኝ “ባንተ ላይ” የሚለው፣ የትም ቦታ ሆኜ ጥፋት ባጠፋም ፍቅር አይናማ ነው፤የትም ቦታ ያየኛል የሚል ይዘት አለው፡፡ የሁሉም ግጥሞች ሀሳብ ደስ ይላል፡፡ “ምስክር” የሚለው ዘፈን እንዲሁ ጠንካራ መልዕክት ያለው ነው፡፡
 ስለ “እናት” የዘፈንኩት ደግሞ የኔን ታሪክ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ይሄን ዘፈን እናቴ ሳትሰማው እንዳትሞትብኝ እያልኩ ነው ያለፈችው፡፡ አሁን ታዲያ ውስጤ ይረበሻል፡፡ እኔና አቤ ይሄን ዘፈን ስንሰራ ሁሌ እናለቅስ ነበር፡፡ በአጋጣሚ ደግሞ ከ6 ወር በፊት የእኔና የአቤ እናቶቻችን የሞቱብን በአንድ ቀን ልዩነት ነበር፡፡ በአንድ ጊዜ ሄደን ቀብረናቸው ነው የተመለስነው፡፡ እናቶች ለልጆቻቸው የከፈሉት መስዋዕትነት አለ፣ ትልቅ ሆነንም ቀልባቸው ከኛ ጋር ነው፡፡ ዘፈኑ ውስጥም ያለው ሀሳብ፣ #እንኳን እናት በህይወት እያለች ብታልፍም ምርቃቷ ይዞህ ይኖራል” የሚል ነው፡፡ አቤ በመጨረሻ የጨመረበት ስንኝ፣“በመጨረሻዋ ደቂቃ ስለ እናት ለማውጋት ምንም ጊዜ አይበቃም” ይላል፡፡ ዘፈኑም 5 ደቂቃ ነው፡፡ የእናትንም ውለታ ዘርዝሮ በ5 ደቂቃ ውስጥ መጨረስ አይቻልምና ይሄ የዘፈኑ ባህሪ ደስ ይላል፡፡ እኔ እውነቱን ልንገርህ እስካሁን ለእናቴ ሳልዘፍን መቅረቴ ይገርመኝ ነበር፡፡ በዚህኛው አልበሜ ባሳካውም እናቴ ሳትሰማልኝ በማለፏ ግን ይቆጨኛል፡፡
 በአጠቃላይ አልበሙን ወድጄው የሰራሁት አስደሳች ስራ ነው፡፡ ይወደድልኛል ብዬም አምናለሁ፡፡ ዘመናዊና ባህላዊ ቅልቅል  አልበም ነው፡፡ አንድ ዳንሶል ዘፈንም አለው፡፡ አቤ ነው የሰራልኝ፡፡ ርዕሱ “ስፈልግህ መጣህ” የሚል ነው፡፡
ከአልበም በኋላ ኮንሰርት ማቅረብ የተለመደ ነው፡፡ እንዴት ነው ዕቅድሽ?
አዎ! መጀመሪያ ሲዲ ሪሊዝ አደርጋለሁ፡፡ መቼም ይሄን አልበም ፕሮዱዩስ ያደረግነውም የምናከፋፍለውም እኔና ባለቤቴ ነን፡፡ ግን በዚህ የአልበም ስራ ላይ ከኪነጥበብ ጎን ሁሌም የሚቆሙት ሞሃና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ አግዘውኛል፡፡ ስፖንሰር አድርገውኛል፡፡ እነሱ ባይደገፉት፣ ይሄ አልበም ለህዝብ መቅረብ አይችልም ነበርና ምስጋናዬ ወደር የለውም፡፡ በዚህ ጊዜ እነዚህ ድርጅቶች ባያግዙን፣ ሙዚቃን የመስራት ነገር የማይታሰብ ነበር፡፡
አልበሙ በህዝብ ዘንድ ያለው አቀባበል እንዴት ነው?
በእውነቱ በዚህች በሁለት ቀን ውስጥ ብቻ የነበረው አቀባበል አስደሳች ነው፡፡ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ አመሰግናለሁ፡፡ በሁለት ቀን ውስጥ ባልጠበቅሁት መጠን ህዝቡ አልበሜን ገዝቷል፡፡ አመሠግናለሁ፡፡ በእውነቱ ህዝቡ አሁንም ከኪነጥበቡ ጐን እንደቆመ ያረጋጥኩበት አስደሳች አጋጣሚ ነውና አቀባበሉ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
በአዲሱ አመት ዋዜማና የበአሉ እለት አድናቂዎችሽ የት ሊያገኙሽ ይችላሉ?
ለዋዜማው ቀድሜ የያዝኩት ቤላቬርዲ ሆቴል ነው፡፡ እዚያ እገኛለሁ፡፡
ብዙ ጊዜ ለኮንሰርት ወደ ውጩ ስትሄጂ አትታይም፡፡ አሁንስ እቅዱ አለሽ?
እሱ እንግዲህ ስራው ነው የሚመራው፡፡ ስራ ከተሠራ----ስራው ራሱ እያንኳኳ ይመጣል፡፡
አልበሙን ለመስራት ምን ያህል ጊዜ ፈጀብሽ?
አራት አመት ነው፡፡ ይሄም የሆነው ከጐኔ የነበሩት ሰዎች ሁሉ ያልተቆጠበ ድጋፍ ስላደረጉልኝ ነው፡፡ በተለይ አቀናባሪው ወንድሜነህ አሠፋ፣ በትልቁ የማመሰግነው ሰው ነው፡፡ እስከ ሲዲ ህትመቱ ድረስ ያልተለየኝ፣ በጣም እውቀት ያለው፣ ሰው አክባሪ፣ ስራውን አፍቃሪ ሰው ነው፡፡ በጣም አመሰግነዋለሁ፡፡

Published in ዜና

    “ዘ ዊኪንድ” በሚል ቅፅል ስሙ የሚታወቀው  ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ፣ ባለፈው ሳምንት በአለም ደረጃ በቢልቦርድ ምርጥ አልበሞች ሰንጠረዥ የ1ኛነትን ደረጃ በዚህ ሳምንትም አለምን እየመራ ይቀጥላል ተብሎ  እንደሚጠበቅ ተዘገበ፡፡“ቢዩቲ ቢሃይንድ ዘ ማድነስ” የተሰኘው አዲሱ የአቤል አልበም፣ ለገበያ በቀረበበት የመጀመሪያው ሳምንት በሽያጭ ብዛት መሪነቱን እንደሚይዝ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም፣ ከተገመተው በላይ እንደተሳካለት ፎርብስ ዘግቧል፡፡ በ350 ሺህ የአልበም ሽያጭ አንደኛ እንደሚሆን የተገመተው የአቤል አልበም፣ በ412 ሺህ ያህል ተቸብችቧል፡፡ በአዲሱ አልበሙ ውስጥ የተካተቱት 12 ሙዚቃዎችም በያዝነው ሳምንት የቢልቦርድ 50 ምርጥ ሙዚቃዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል፡፡ካለፉት ሰባት አመታት ወዲህ፣ በቢልቦርድ የምርጥ ዘፈኖች ሰንጠረዥ፣ በአንድ ሳምንት ሁለት ዘፈኖቹ፣
 ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ባለው ደረጃ ውስጥ የተካተቱለት የመጀመሪያው ወንድ ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ ብቻ መሆኑን ቢል ቦርድ ገልጿል የሰሞኑን የአቤል ስኬት ሲዘግብም፤ በ57 አመታት የቢልቦርድ ሰንጠረዥ ታሪክ፣ አቤል በአንድ ሳምንት ውስጥ ብዙ ዘፈኖቹ፣ በምርጥ 100 ዘፈኖች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱለት ስድስተኛው ድምጻዊ ነው ብሏል፡፡  ዘንድሮ፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ፣ ከአቤል የአልበም ሽያጭ የሚበልጥ ሪከርድ ያስመዘገበ ድምፃዊ የለም - ከድሬክ በስተቀር፡፡ አመቱ የአቤል ተስፋዬ ነው ያለው ፎርብስ መጽሄት፤ የድምጻዊው የሙዚቃ ስራዎች የካናዳንና የአሜሪካን ሬዲዮ ጣቢዎች በስፋት መቆጣጠራቸውንና ከፍተኛ ተወዳጅነት ማትረፋቸውን ዘግቧል፡፡ የአቤል ዘፈን በአሜሪካ ሬዲዮ ጣቢያዎች በብዛት በመሰራጨት አቻ አልተገኘላትም፡፡ “ስድ” ቃላትን በሙዚቃዎቹ ውስጥ ይደጋግማል በሚል ትችት የሚሰነዘርበት አቤል ተስፋዬ፤ በሙዚቃዎቹ ኢትዮጵያዊኛ ቃና  ይንፀባረቃል የሚለው አስተያየት ከሁሉም በላይ እንደሚያስደስተው ገልጿል፡፡ በዘፈን መሃልም አልፎ አልፎ አማርኛ ያስገባል፡፡

Published in ዜና

     የታዋቂው የጫማ አምራች ኩባንያ “ሶል ሪበልስ” መስራችና ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵዊቷ የቢዝነስ ሰው ቤተልሄም ጥላሁን፤ በታዋቂው የአሜሪካ የቢዝነስ መጽሄት “ኳርትዝ” የአመቱ የአፍሪካ 30 ፈርቀዳጅ፣ የድንቅ ፈጠራ ባለቤቶች ዝርዝር ውስጥ ተካተተች፡፡ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገው መጽሄቱ፤ ፈርቀዳጅ፣ አዲስ ሃሳብ አፍላቂና ለአካባቢያዊ ችግሮች ተስማሚ መፍትሄ የሚሰጡ ድንቅ ፈጠራዎችን አበርክተዋል ያላቸውንና ከ15 የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመረጣቸውን 30 ምርጦች ይፋ ባደረገበት ዝርዝር የ35 አመቷን ቤተልሄም አካትቷታል፡፡ከ10 አመት በፊት ቤተልሄም ያቋቋመችው “ሶል ሪበልስ”፣ በአሁኑ ወቅት አለማቀፍ ተፈላጊነትን ያተረፉ የጫማ ምርቶቹን ወደተለያዩ 30 የዓለማችን አገራት ኤክስፖርት እያደረገ መሆኑን የጠቆመው መጽሄቱ፤ ቤተልሄም ያመነጨችው የቢዝነስ ሃሳብ ብዙዎችን ተጠቃሚ ያደረገና ውጤታማ በመሆኑ በዝርዝሩ ውስጥ ልትካተት እንደቻለች ገልጿል፡፡

Published in ዜና

መኢአድ በምዕራብ ሸዋ ናኖ ወረዳ ነዋሪ በነበሩ 87 አባወራዎች ላይ በአካባቢው የመንግስት ባለስልጣናት ተፈፅሟል የተባለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የአቤቱታ ደብዳቤ ፃፈ፡፡ ፓርቲው በደብዳቤው እንደገለፀው፤ በወረዳው ከ87 በላይ ሠላማዊ ሰዎች ያለምክንያት ከታሰሩ በኋላ መኖሪያ ቤታቸው እንዲቃጠል ከመደረጉም በላይ አንድ ግለሰብ ተደብድቦ ሲሆን ድርጊቱን በዋናነት ፈፅመዋል ያላቸውን 3 የመንግስት ባለስልጣናትና አንድ ባለሀብት ስም ጠቅሷል፡፡
ጉዳዩን ገለልተኛ የሆነ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንዲያጣራ ወንጀሉን የፈጸሙት ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ ቤት ንብረታቸው ለተቃጠለባቸው ግለሰቦች አስቸኳይ መንግሥታዊ እርዳታ እንዲደረግና መንግስት ለተጎጂዎች ተገቢውን ካሣ እንዲከፍል ፓርቲው ጠይቋል፡፡ በቅርቡ ጉዳዩን በተመለከተ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) ሪፖርት ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

Published in ዜና

ዓመቱ ብዙ ሥራ የተሰራበት ነው፡፡ የንባብ ባህል በማሳደግ አቅጣጫ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ ሰኔ 30 የንባብ ቀን በመላው ኢትዮጵያ እንዲከበር አድርገናል፡፡ ቀኑም የንባብ ባህል ንቅናቄ ተምሳሌት ሆኖ ይታይ ዘንድ፣ በመንግስት በኩል ታስቦ እንዲውል ጥያቄ ያቀረብንበትም አመት ነው፡፡ የማህበሩ አባላት ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየሄዱ ልምድ እንዲያካብቱ የተደረገባቸው ጉዞዎች ነበሩ፡፡
ለምሳሌ “የጥበብ ጉዞ ወደ ፀሃይ መውጫ ሀገር” በሚል ወደ ድሬደዋና ወደ ሃረር ያደረግነው ጉዞ ተጠቃሽ ነው፡፡ ወደ ህዳሴው ግድብም የተደረገ ጉዞ አለ፡፡ ባለፈው አመት ከበርካታ ዩኒቨርስቲዎች ጋር ማህበሩን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ አብረን ስንሰራ ከርመናል፡፡ የተለያዩ የሥነ ፅሁፍና የኪነጥበብ ዝግጅቶችንም አከናውነናል፡፡
ሌላውና ዋነኛው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለዘመናት የዘለቀ የትውልድ ጥያቄ መልሷል፡፡ ይኸውም የመሬት ጥያቄ ነበር፡፡ ወደ 3ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቶናል፡፡ በቦታው ላይ የኢትዮጵያ ደራሲያን መቀመጫ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ደራሲያን መቀመጫ ፅ/ቤት እንዲሆን አስበን ለመገንባት እቅድ አለን፡፡
በቀጣይ አመት የምናስበው በየክልሉ ያሉ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶችን ማጠናከርና ማስፋፋት ነው፡፡ ከተማን መሰረት ያደረጉ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶችን ወደ ክልል ፅ/ቤትነት ለማሳደግ ነው ያቀድነው፡፡ የንባብ ባህልን በሚመለከት በየኮንደሚኒየሞቹ የማስፋፋት አዲስ አይነት እቅድ አለን፡፡ በተንቀሳቃሽ ቤተመፅሃፍት አማካይነት ወደ ህብረተሰቡ እንደርሳለን ብለን እናስባለን፡፡ የአዲስ አበባውን ተሞክሮ ወስደን በክልሎችም እንተገብራለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በየዓመቱ የምናደርጋቸውን የመፃህፍት ኤግዚቢሽኖች አጠናክረን በክልሎች ጭምር እናካሂዳለን፡፡ የህንፃውን ግንባታ ሂደትም ወደ አንድ ምዕራፍ እናሸጋግራለን የሚል እምነት ነው ያለን፡፡

Published in ዜና
Page 11 of 16