ወታደራዊው ሃይል ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ባካሄደው መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የወረዱትና በግዞት የቆዩት የቡርኪና ፋሶው የሽግግር መንግስት ፕሬዚዳንት ሚሼል ካፋንዶ ረቡዕ ዕለት ወደ ስልጣናቸው መመለሳቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንት ሚሼል ካፋንዶ ወደስልጣናቸው መመለሳቸውን ይፋ ያደረጉት፣ የመፈንቅለ መንግስቱ መሪና ለአንድ ሳምንት በስልጣን ላይ የቆዩት የአገሪቱ መሪ  ጄኔራል ጊልበርት ዴንድሬ የስልጣን ሽግግሩን ለመታዘብ ወደ አገሪቱ በመግባት ላይ የነበሩ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎችን ለመቀበል ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ባመሩበት ወቅት ነው ብሏል ዘገባው፡፡
የምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ኢኮአስ በሽግግር መንግስቱና በወታደራዊው ሃይል መካከል የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ ድርድር ለመፍታት ያስችላል በሚል ባቀረበው የድርድር ሃሳብ መሰረት፣ አገሪቱ ወደ ብጥብጥ እንዳትገባ የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች ከቤተ መንግስቱ እንዲርቁ መደረጋቸውን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ኮፋንዶ ወደ ስልጣናቸው እንደተመለሱ ማወጃቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡በወታደራዊው ሃይልና መፈንቅለ መንግስቱን በተቃወሙ የአገሪቱ ዜጎች መካከል በተነሳው ግጭት ከ10 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከ100 በላይ የሚሆኑ የአገሪቱ ዜጎችም መቁሰላቸው ተነግሯል፡፡
ባለፈው አመት ጥቅምት ወር ላይ በተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመጽ ከስልጣናቸው የወረዱትን የቀድሞውን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬን ተክቶ መንበረ መንግስቱን የተረከበው የቡርኪና ፋሶ የሽግግር መንግስት፣ በመጪው ጥቅምት ወር በሚደረግ ምርጫ ስልጣኑን ለማስረከብ እቅድ እንደነበረውም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

    13.50 ዶላር የነበረው መድሃኒት፣ 750 ዶላር ገብቷል
    
   ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ዜጎች በሚወስዱት መድሃኒት ላይ የ5,000% የዋጋ ጭማሪ ያደረገው የአሜሪካ መድሃኒት አምራች ኩባንያ፣ ከታማሚዎች፣ ከመብት ተሟጋች ቡድኖች፣ ከህክምና ማህበራት፣ ከፖለቲከኞችና ከማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመውና ዋጋውን ለመቀነስ ማሰቡን እንደገለፀው ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ቱሪንግ ፋርማሲዩቲካልስ የተባለው የመድሃኒት አምራች ኩባንያ፤ ዳራፕሪም በመባል የሚታወቀውን የመድሃኒት ምርቱን የመሸጫ ዋጋ ከ13.50 ዶላር ወደ 750 ዶላር ማሳደጉን ማስታወቁን ተከትሎ ከታማሚዎችና ከተለያዩ አካላት ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመው የጠቆመው ዘገባው፣ የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚም የተወሰነ የዋጋ ቅናሽ ለማድረግ ማሰባቸውን እንደተናገሩ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የዋጋ ጭማሪው ያስነሳውን ተቃውሞ ለማጣጣል የሞከሩት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርቲን ሸክሬሊ፣ ተቃውሞውን የሚሰነዝሩት ስለ መድሃኒት አምራች ኢንዱስትሪው አካሄድ በቂ ግንዛቤ የሌላቸው ሰዎች ናቸው፤ የዋጋ ጭማሪውን አድርገን የምናገኘውን ተጨማሪ ገንዘብ ሌሎች መድሃኒቶችን ለመፍጠር ለምናደርገው ምርምር ለማዋል ነበር ያሰብነው ብለዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው ማርቲን ሸክሬሊ በትዊተር ገጻቸው ላይ የተሰነዘረባቸውን ከፍተኛ ተቃውሞ ተከትሎ፣ ቱሪንግ ፋርማሲዩቲካልስ የተባለው ኩባንያቸው በቅርቡ ከህብረተሰቡ የመግዛት አቅም ጋር የሚመጣጠን የዋጋ ቅናሽ እንደሚደርግ ቢናገሩም፣ ምን ያህል የዋጋ ቅናሽ ለማድረግ እንደታሰበ በግልጽ አላሳወቁም፡፡
ኩባንያው ዳራፕሪም የተባለውንና የቶክሶፕላዝሞሲስ የፓራሳይት ኢንፌክሽንን በማከም ረገድ ፍቱን የሆነውን መድሃኒት አምርቶ የመሸጥ ፍቃድ ያገኘው በቅርቡ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ኤችአይቪ ኤድስን በመሳሰሉ በሽታዎች የተጠቁና በሽታን የመከላከል ተፈጥሯዊ አቅማቸው ደካማ የሆኑ ታማሚዎች መድሃኒቱን በስፋት እንደሚወስዱ ገልጧል፡፡
በተያያዘ ዜናም በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የሚሰነዘሩ ሃሳቦችን መነሻ በማድረግ ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ፣ በአሁኑ ወቅት በአገረ አሜሪካ አይንህን ለአፈር በመባልና በመጠላት ረገድ፣ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ያደረገውን ኩባንያ የሚመሩት የ32 አመቱ ማርቲን ሸክሬሊ ቱሪንግ፣ ቀዳሚውን ስፍራ ሊይዙ እንደሚችሉ ጠቁሟል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

 ካንሰር ማለት ጤነኛ የነበረ የሰው ልጅ ሴል ጤነኛ ወዳልሆነ ሁኔታ ሲለወጥ ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት አንድ ሴል ስራውን በትክክል የማይሰራ፣ በትክክል የማያድግ ወደመሆን ሲለወጥ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ጤነኛ የነበረው ሴል የሚኖረው ስራ ሲቋረጥ ወይንም  ከቁጥጥር ውጪ ሲራባ አለዚያም ሲያድግ እና ከጎረቤቱ ያለውን ሴል ስራና ጤንነት ሲበጠብጥ የሚፈጠረው በሽታ ነው ካንሰር ማለት፡፡ ካንሰር አንድ ቦታ ሲፈጠር እዛው በነበረበት ቦታ አይቆይም፡፡ ወደ ሳንባ ወደጉበት እና ወደሌሎችም የሰውነት ክፍሎች ይሄዳል፡፡ ወደተለያዩ የሰውነት አካሎች ከሄደ በሁዋላም እድገቱን በመቀጠል የሰውነት ክፍሎችን ይበጠብጣል፡፡ ባጠቃላይም ካንሰር እንደእብድ ሰው የሚቆጠር ሕመም ነው፡፡ አንድ ሰው እብድ ነው ሲባል የተፈጥሮ ሕግ በትክክለኛው መንገድ እንዲመራ ስለማያዙትና ሁሉንም ነገር እንደፈቀደው ከተፈጥሮ ስርአት ውጪ የሚከውን ሲሆን ሴልም ወደ ካንሰርነት ሲለወጥ በዚህ መልክ ሊገለጽ ይችላል፡፡ የካንሰር ሴሎች ቁጥራቸው መጠናቸው በተፈጥሮ ሕግ መሰረት ሳይሆን እንደተመቸው ይጨምራል፡፡ መስራት የሌለባቸውን ስራ ይሰራሉ፡፡ ከራሳቸው አልፈው ከጎረቤት ያለውን ሴል ይበጠብጣሉ፡፡ ይህ በእንግሊዝኛው Carcinogenesis በመባል ይታወቃል፡    
ዶ/ር አበበ ፈለቀ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል
የቀዶ ሕክምና    ባለሙያና አሲስታንት ፕሮፌሰር
ካንሰር የተባለው በሽታ ባህርይ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህንን ሕመም በአመጋገብ መከላከል ይቻላል የሚለውን መረጃ ከተለያዩ ጽሁፎች ማመሳከር የሚቻል ሲሆን ለዚህ እትም ግን ምንጭ ያደረግነው ዌብ ሜድ (WEB MED) የተሰኘውን ድረ ገጽ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ጽሁፍ ለካንሰር መከላከል ምቹ ናቸው የተባሉ ምግቦችን በሙሉ የሚጠቅስ ሳይሆን በመጠኑ እና በእለት ተእለት አኑዋኑዋራችን የምንጠቀምባቸውን የሚመለከት ነው፡፡
አንድ አይነት ምግቦችን አዘውትሮ በመመገብ ካንሰርን መከላከል አይቻልም፡፡ ይልቁንም የተለያዩ ምግቦችን በይዘትም ሆነ በአይነት አመጣጥኖ በመመገብ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ የገበታዎ ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው ቅጠላቅጠል ቢሆን ይመረጣል፡፡ ከእንስሳት ተዋፅኦ የሚገኘው ፕሮቲንም ከገበታዎ አንድ ሶስተኛ በላይ መሆን የለበትም፡፡
እንደ አሜሪካ የካንሰር መከላከያ ተቋም ከሆነ የተመጣጠነ ምግብ ካንሰርን ለመከላከል አይነተኛ መሳሪያ ነው፡፡
አትክልትና ፍራፍሬን አዘውትሮ መመገብ፡-
አትክልት እና ፍራፍሬዎች  ካንሰርን ለመከላከል በሚያስችሉ ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ሲሆኑ ቀለመ ደማቅ የሆኑ አትክልት እና ፍራፍሬዎች ለዚህ አይነተኛ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምግቦች ሌላም ተጨማሪ ጥቅም አላቸው፡፡ አዘውትሮ አትክልት እና ፍራፍሬን መመገብ ጤናማ የሰውነት ክብደት እንዲኖረን ያደርጋል በዚህም ከልክ በላይ በሆነ የሰውነት ክብደት ሳቢያ የሚከሰቱ የካንሰር በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከል ይቻላል፡፡
በፎሌት የበለፀጉ ምግቦች፡-  
እንቁላል፣ ሱፍ፣ ባቄላ፣ አባባ ጎመን እና ሌሎች አረንጓዴ ቀለም ያላቸው አትክልቶች በውስጣቸው ከፍተኛ የሆነ የብረት ንጥረ ነገር አላቸው፡፡ በምግብ ሰአት የብርቱካን ጭማቂ ሎሚ እና እንጆሪ የመሳሰሉትን መጠቀም በትልቁ አንጀት እና በአንጀቱ የታችኛው አካባቢ እንዲሁም በጡት ላይ የሚከሰተውን ካንሰር ሕመም ሊከላከል ይችላል፡፡ በመድሀኒት መልክ
ውሀ እንዲሁም ሌሎች ፈሳሾችን መውሰድ፡-
አብዝተን ውሀ በመጠጣት ጥማችንን ብቻ ሳይሆን የምናረካው እራሳችንን በሽንት ፊኛ ላይ ሊከሰት ከሚችል ካንሰርም መከላከል እንችላለን፡፡ ሌሎች ፈሳሾችንም አብዝተን በወሰድን ቁጥር ብዙ ቆሻሻ በሽንት መልክ ከሰውነታችን ስለሚወገድ ለሽንት ፊኛ ካንሰር የሚኖረን ተጋላጭነት በእጅጉ ይቀንሳል፡፡
ስኳርን መቀነስ፡-
ስኳር በቀጥታ የካንሰር በሽታን አያመጣም፡፡ ነገርግን በሰውነታችን ያለው የስኳር መጠን ሲጨምር ካንሰር ተከላካይ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን መጠን ይቀንሳል፡፡ በተመሳሳይ በሰውነታችን ያለው የካሎሪ መጠን እንዲጨምር እና ከልክ በላይ የሆነ የሰውነት ክብደት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ይህም ለተለያዩ የካንሰር በሽታዎች ያለንን ተጋላጭነት ይጨምራል፡፡ ስለዚህም ከስኳር ይልቅ በተፈጥሮ ጣፋጭ የሆኑ ፍራፍሬዎችን መመገብ ተመራጭ ነው፡፡
ጥቁር አረንጉዋዴ መልክ ያላቸው ቅጠላቅጠሎች፡-
እንደ ጎመን እስፒናች የመሳሰሉት ቅጠላቅጠሎች የአፍ፣ የሳንባ፣ የጣፊያ፣ የቆዳ እና የሆድ ካንሰር ሕመሞችን ሊከላከሉ እንደሚችሉ ጠበብት መስክረዋል፡፡
አልኮሆሎን መቀነስ፡-
በጉሮሮ፣ በአፍ፣ በድምጽ መተላለፊያ መስመር፣ በጉበት፣ በጡት ላይ ሊከሰቱ የሚችሉትን የካንሰር ሕመሞች ለመከላከል የአልኮሆል መጠጥን መጠን መቀነስ ይገባል፡፡ አልኮሆል በአንጀት አንባቢም ለሚከሰተው ሕመም መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡
ባጠቃላይም የተጠቀሱትንና ሌሎችን ተመሳሳይ ምግቦችን በመመገብ ሕመሙን በመከላከል ረገድ ውጤታማ መሆን ይቻላል፡፡  
ካንሰር የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን የሚያጠቃ ሲሆን በተለይም ከሴቶች ጋር በተያያዘ ጡትና ማህጸን አካባቢ ይበልጡኑ ጎጂ ሆኖ ይስተዋላል፡፡ የጡት እና ማህጸን ካንሰርን በተመለከተ አንዳንድ ነጥቦችን ለትውስታ ታነቡ ዘንድ ለህትመት አብቅተነዋል፡፡  
የጡት ካንሰር  
የጡት ካንሰርን ስንመለከት በእርግጥ ይበልጡኑ ተጎጂዎቹ ሴቶች ቢሆኑም ወንዶችም እንደሚታመሙ መረጃዎች ያመለክታ፡፡ ከ/100/ የጡት ካንሰር ታማሚዎች ውስጥ /90/ ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ ወንዶች /10/ ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህ የጡት ካንሰር በብዛት የሚታየው ሴቶች ላይ ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱም የጡት መጠኑ ሴቶች ላይ ትልቅ ሲሆን የወንዶች ጡት ግን ትንሽ እና በአይን የማይታይና በእጅ የማይዳሰስ በመሆኑ በካንሰር የመያዝ እድሉም ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በጥቅሉ ትልቅ ጡት ያላቸው በካንሰር ሲያዙ ትንሽ ጡት ያላቸው ግን አይያዙም ለማለት አይደለም፡፡ ሴቶች በተፈጥሮአቸው ጡታቸው ላይ ብዙ ሴሎች የሚገኙ ሲሆን ወንዶች ግን እንደጡታቸው ማነስ ሴሎቹም ትንሽ ናቸው፡፡ የጡት ካንሰር ሲጀምር በጡት እና አካባቢው ቀድሞ ያልነበረ እብጠት ይታያል፡፡
የጡት ካንሰር ደረጃ አለው፡፡ ደረጃውም ከአንድ እስከ አራት ይከፈላል፡፡
1ኛ/ መጠኑ እጅግ ያነሰና በጡት ላይ ብቻ ያበጠ እጢ ነው፡፡ 2ኛ/ጡት ላይ ያለው እጢም አደግ ይላል፡፡ እንደገናም ብብት ስር እብጠቶቹ ሊዳሰሱ ይችላሉ፡፡ 3ኛ/ ጡት ላይ ያለው እጢም ትልቅ ሲሆን ብብት ስር እና ዙሪያውን ያሉት እጢዎችም በጣም ጠንካራ እና ያደጉ ሆነው ይዳሰሳሉ፡፡ 4ኛ/ ደረጃ የሚባለው የጡት ካንሰር ከጡትም ከብብት ስርም አልፎ ወደሌሎች የሰውነት ክፍሎች የተሰራጩ ሲሆን ነው፡፡  
ዶ/ር አበበ ፈለቀ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና                     ባለሙያና አሲስታንት ፕሮፌሰር
የማህጸን ካንሰር
የማህጸን ካንሰር አይነቱ እንደመብዛቱ መንስኤውም አንዳንዴ የሚታወቅና አንዳዴ  የማይታወቅ ነው፡፡ በአገራችን ሴቶችን በብዛት የሚያጠቃውና ገዳይ የሆነው የማህጸን በር ካንሰር መንስኤው ቫይረስ መሆኑ በሳይንስ የተረጋገጠ ነው፡፡ መንስኤያቸው በውል ካልታወቀው የማህጸን ካንሰር አይነቶች መካከል ከዘር ፍሬ (ኦቫሪ) ማፍለቂያ ከማህጸን ግድግዳና በአርግዝና የሚነሱ የካንሰር አይነቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጋር በተያያዘም እንደመንስኤ የሚጠቀሱት እንደ ውፍረት ደም ግፊት እና ስኩዋር ሕመም ያላቸው ሴቶች የማህጸን ግድግዳ ካንሰር  ያጠቃቸዋል፡፡ ብዙ ያልወለዱ እና በዘር አማካኝነት ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ደግሞ በዘር ፍሬ ማፍለቂያ ካንሰር ይጠቃሉ፡፡
በአጠቃላይ በከፍተኛ ሁኔታ ሴቶችን ይጎዳሉ ተብለው የሚታወቁት የካንሰር አይነቶች፡-
የማህጸን በር ካንሰር (Cervical Cancer) 80% ያህል በታዳጊ አገሮች ይከሰታል፡፡
የሴት ዘር ፍሬ ማፍለቂያ ካንሰር (Ovarian Cancer) ባደጉና ባላደጉ አገሮች ብዙ ልዩነት ሰያሳይ በተመሳሳይ ሁኔታ     ይከሰታል፡፡
ከማህጸን ግድግዳ የሚነሳ ካንሰር (Endometrial Cancer) በእድሜያቸው ገፋ ያሉትን ሴቶችን ያጠቃል፡፡
ዶ/ር ካሳሁን ኪሮስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
የማህፀንና ፅንስ ህክምና ስፔሺያሊስት

Published in ላንተና ላንቺ

     ከእርሻና እና ደን  ተመራማሪው  አቶ ደቻሳ ጅሩ ጋር በኢትዮዽያ አትሌቲክስ ዙርያ  ያደረግነውን ቃለምልልስ ሰፊ ነበር፡፡ የመጀመርያውን ክፍል ባለፈው ሳምንት ማስነበባችን የሚታወስ ነው፡፡ አቶ ደቻሳን ተዋውቀናቸዋል፡፡ ስለሙያቸው  ገለፃ አድርገው፤ ከአትሌቲክስ ስፖርት እንዴት እንዳዛመዱት አብራርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሳይንስን በመቅረብ መንቀሳቀስ እንዳለበት የሚመክሩት ተመራማሪው፤  አትሌቲክሱን የሚመራው አካል ስፖርቱን በሚያጠናክሩ እና በሚያሳድጉ አቅጣጫዎች የሚሠራበትን ሁኔታን አነቃቅተዋል፡፡ በየዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ከስፖርቱ ጐን በመራመድ እንደ አማካሪ አካል ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም  አስገንዝበዋል፡፡
የአትሌቶችን ውጤት በመፈታተን ለከፍተኛ ውጣውረድ የሚዳርጉ በርካታ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ የጤና መጓደል፤ በስነልቦና ያለመረጋጋትን ጨምሮ፤የግል ብቃት፤ ከአሰለጣጠንና አቀባብል ጉድለትና ከመሳሰሉት የሚመነጩ ክፍተቶች ጉልህ ተፅእኖ በመፍጠር ከውድድር ውጭ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህን በተመለከተ አቶ ደቻሳ ጅሩ በቃለምልልሱ ሁለተኛ ክፍል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ትኩረት ሊሰጣቸው  በሚያስፈልጉ አቅጣጫዎች ባደረጓቸው  አስደናቂ ምርምሮች ዙርያ ያተኩራሉ፡፡ መልካም ንባብ
ወደ ዋናው ጉዳያችን  ሳንገባ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ አስተዋፅኦ ለማድረግ የተነሳሱባቸው ተጨማሪ ሁኔታዎች ካሉ?
ለአትሌቶቻችን እንደፈለግኩት አስተዋፅኦ የማደርገው ምን አቅም ኖሮኝ ነው፡፡ አንድ የማስበው ጉዳይ ግን አለ፡፡ እንደኔው እድሜያቸው ለገፋና ለተዳከሙት አሰልጣኞች በሁሉም ዘርፍ ያለን ባለሙያዎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ነው፡፡ ከ1990 እስከ1994 እ.አ.ኤ በፈረስ ግልቢያ በምትታወቀው አውስትራሊያ የእርሻና ደን ጥምር ጥናት ላይ እንደነበርኩ ነግሬሃለሁ፡፡ ያኔ መላው ዓለም በረሃብተኛነት  መሳለቂያ ሲያደርገን  ክቡራን አርማዎቻችን የነበሩት አትሌቶቻችን ናቸው፡፡ ባንድ ወቅት በተካሄደ ውድድር ኢትዮጵያዊ አትሌት ካሸነፈ በኋላ እንደማስመለስ ሲያደርገው ሁኔታውን የተቀበለው አልነበረም፡፡  በወቅቱ እነከበደ ባልቻ ለውድድር ወደ አውስትራሊያ ሲመጡ እንደ ነገ ሊሮጡ በዋዜማው ነበር የሰማነው፡፡  በአውስትራሊያዋ ሜልቦርን ከተማ ንፋሱ ሃይለኛ ከመሆኑ ባሻገር ከቅዝቃዜ ጋር ተዳምሮ መሰናክልነቱ ከበድ ይል ነበር፡፡ ምን ማድረግ እችላለሁ ብዬ በማሰብ  በለሊት ሩጫው በሚካሄድበት መንገድ በእግሬ ቀድሜ ደረስኩ፡፡ በውድድሩ ጎን ለጎን ተሩዋሩጬ ንፋሱን የሚከላከሉበትና ፋይዳቸውን የሚያጎሉበትን ዘዴ ለማቀበል  አቅጄ ነበረ፡፡ ተግባራዊ ላደርገው አልቻልኩም፡፡ እኔ ንፋስ እነሱ አውሎንፋስ ሆኑብኝ፡፡ ምናልባት ብስክሌት ቢኖረኝ ኖሮ መልእክቴ በትክክል ይተላለፍ ነበር፡፡ ግን ነጭ ልብስና ባርኔጣ አድርጌ በየአቁዋረጩ እየቀደምኩ ከረጅምና ወፍራም አትሌት ስር ገብታችሁ በጋሻነት እንደንፋስ መከላከያ ተጠቀሙባቸው እያልኩ የነበረ ቢሆንም አድናቂያቸውና ለማበረታታት የምጮህ ወገናቸው እንጂ የባለሙያ ድጋፍ ነው ብለው በፀጋ መልእክቴን መገንዘብ አልቻሉም፡፡ በመግቢያ አካባቢ ራሱን እየጠበቀ የሚሮጥ ለንፋስ ያልተጋለጠው  አሸነፋቸው፡፡ የኛ ከሁለት እከ 4 ተከታትለው ወጡ፡፡ እርስ በራስ ተፋጭተው ለውጪው እንደመሪ ወፍ ሃይላቸውን ጨረሱ፡፡ ከዚህ አጋጣሚ በኋላ በአትሌቲክሱ ሳይንሳዊና ጥበባዊ ግንዛቤን የማስፋፋት ቁጭት አደረብኝ፡፡ ይገርመሃል ያኔ የእኛ አትሌቶች ጫማቸው የተበጣጠሰና አሮጌ  ከመሆኑም በላይ ሰውነታቸውም የተጎሳቆለ ነበር፡፡  እኔ ማነኝ ተራ ሰው፡ አትሌቶቻችን አስደስተውናል ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ህይወት የሚሰዋላቸው ጀግኖች ናቸው፡፡ ያኮሩን  አንገት እንዳንደፋ ነፍስ የዘሩብን  ናቸው፡፡ ለእነሱ ምርምር በማድረግ ውሳኔዬ እጅግ ረካሁ፡፡ በቤቴም ሆነ በስራዬ ምርጥ ነገር መጠቀም እድሉ ቢኖርም ጨርሶ አልመኝም፡፡ በተሰለፍኩበት ውጤታማ ስሆን ብቻ ነው ውስጤ የሚቀበለው፡፡ ከአትሌቶቻችን ሁሉ በተለይ ጥሩዬን በጣም አደንቃታለሁ፡፡ ሎተሪ ቢደርሰኝ በቀድሞ ካራማራ ሆቴል ላይ ተጀምሮ ያዘገመውን ቤት ማስጨረሻ አዋጣላታለሁ፡፡ ገንዘብ ካላገኘሁ የምድረ ግቢ ውበት ላይ የሞያ እገዛ ላደርግላት እቅዱ አለኝ፡፡ ምክንያቱም ከምትሰራው ሆቴል ፊት ለፊት ያለውን የወርልድ ባንክ ምድረግቢ ዛፍና የውስጥ ገነተ ድንጋይ መሬት (ሮክ ጋርደኑን) የሰራውት እኔ ነኝ፡፡ ለአትሌቶቻችን ያለኝ ፍቅር በዚህ የሚገለፅ ይመስለኛል፡፡ የአውስትራሊያ የትምህርት ቆይታዬ እንደጣሊያኑ ቆይታ የእውቀትና ልምድ ግብይት ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም፡፡ ተሰደው ከአገር የወጡት በመንገዱ የሚደርስባቸው በየጊዜው ሲያገጥመኝ ናለዬን ያዞረው ነበር፡፡ ባጭሩ እራሴን ከተሰቃዩት ጋር አሰቃየሁ፡፡ በስፖርቱ ባለኝ ፍቅር ብቻ ሳልወሰን በትምህርትም በማህበራዊ ችግርም ቀንደኛ ተሳታፊ ሆኜ በባህርማዶ የነበረኝን ህይወት አልፌበታለሁ፡፡  ጺሜን አሳድጌ የምትመለከተው ይህ አይነቱ ብሄራዊ ፍቅር ለመግለፅ ነው፡፡ ሌላው ያለእድሜው እየሸበተ  ጥቁር ቀለም ሲቀባ የኔ ራስ ገባ ከማለት ውጭ ፀጉሬ አልሸብት አለኝ፡፡ ጺሜን ነጭ ቀለም ለመቀባት ሁሉ ሞክሬ ነበር፡፡  የተፈጥሮ አልመስል ሲለኝ መልሼ አጠቆርኩትና ተንዠርጎ ቀረ፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤት መዳከም ከሚጠቀሱ ችግሮች አንዱ የቡድን ስራ መጥፋት ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ለሚበላሹ ውጤቶችም እንደ ዋና ምክንያት ይጠቀሳል፡፡ እርሶም ደግሞ የቡድን ስራ ከአዕዋፍ ስለመማር ይናገራሉ?
እንደ አዕዋፍ የቡድን ስራ ቢኖረን ብዙ ውጤት በተቀየረ፤ በጨመረ ነበር፡፡ ወደ ሰማይ አንጋጣችሁ ብትመለከቱ እጅብ ብለው ከሚበሩት ወፎች የሚገርም ተመክሮ ትገነዘባላችሁ፡፡ በረራቸውን ሁሌም ስናስተውል አንዲት መሪ ወፍ ቀድማ ትበራለች፡፡ ከፍተኛ የግፊት ችግርን ተቁዋቁማ ነው ሙሉ ሃይልዋን ተጠቅማ አየሩን እየሰነጠቀች ትበራለች፡፡ ክንፍዋም ዕረፍት የለውም፡፡ የቀሩት ግን ስራቸው ተከታዮች መሆን ነው፡፡ ተከታዮች በግምት የከ20-3ዐ ዲግሪ የሚሆን ማዕዘን  ሰርተው ቀጥ ባለ የመስመር ጉዞ ይከተላሉ፡፡ ክንፋቸውን ብዙ አያወዛውዙም፡፡ መሪዋ በቀደደችላቸዉና ባመቻቸችላቸዉ የአየር መንገድ እየተዝናኑ ይበራሉ፡፡ የመሪነቱ ቦታ በጣም አድካሚ በመሆኑ በአንድ ፈር ቀዳጅ በሆነ በተወሰነ ወፍ የሚደረገው በረራ አስቸጋሪ በመሆኑ ቶሎ ቶሎ ይፈራረቃሉ፡፡ በአትሌቲክሱ ልንተረጉመው የምንችል ተመክሮ ነው፡፡ በሰው በኩል ይህ አይነት ዘዴ በቀጥታ የሚጠቅመን ንፋሱ ሃይለኛ ሆኖ ሲያሰናክለን ብቻ ነው፡፡ ንፋሱ ሲከፋ እጅግ ለጥቃት የሚጋለጡት ረጃጅም አትሌቶች ናቸው፡፡ ፊትም ቀደሙ መሃል ወይም ከሁዋላ ቢከተሉ ወሳኝ የሆነው ራሳቸው በኩል ልክ እንደ ረጅም ማሽላ ..አንድም ለወፍ አሊያም ለወንጭፍ.. እንደሚባለው ተጠቂ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በማራቶን ያለው አማራጭ በቁመት የሚመጥነውን ፈልጎ ወደንፋስ አቅጣጫ አድርጎ እንደጋሻ መከለከያ ማድረግ የሚቻልበትን ታክቲክ መቀመር ያስፈልጋል፡፡ ወደ አዕዋፍቱ ስንመለስ የምንገነዘበውም ይህንኑ ነው፡፡ በመሪ በመሆን የሚደረገው መስዋዕትነት አቀጣጣይና ተቃጣይ በሚባሉት የሯጮቻችን የቡድን ሥራ ድርሻ ጋር የሚዛመድ ይሆናል፡፡ በሕብረት ስራነቱ ግን መጠቀም ይቻላል፡፡   ይህንን የቴክኒክ እድል እስከዛሬ በትክክል መገንዘባችንን አልፎም መጠቀማችንን ወይም ያለመጠቀማችን ለኔ ግልጽ አይደለም፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ብቸኛው አማራጭ ግን አይደለም፡፡ በቁመቱ ረዘም ካለ ተፎካካሪ የውጪ ሯጭ ኋላ መከተልና ቀዳሚውን በንፋስ መከላከያነት መጠቀሚያ አድርጎ ለራስ የምቾት እድልን በማስፋት የመስራት ታክቲክን እንደምረዳው የሚጠቅም ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ዝርዝር የቴክኒክ ዘዴ በሜትሮሎጂ ከአየር ሃይል የኤሮኖቲክስ ባለሞያ ጋር በመገናኘት የየበኩላችንን ብሄራዊ አስተዋጽኦ በማድረግ በምርምሩና በትግበራው መስራት አለብን፡፡ እዚህ ጋር የንፋስን መሰናክልነት፤ የመከላከል ሳይንሳዊ ቴክኒክ ከተቀበልንና ከተገበርን ነው፡፡ ይሁንና በረራው ውጤቱን ቀኝ ኋላ እንዳይዞርብን አበክሬ ለማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡
ሌላው በአትሌቲክሱ ውጤት መዳከም የሚቀርብ ማመካኛ የ“አየሩ ከበደኝ” ሁኔታ ነው፡፡  የአየር ተስማሚነት በአትሌቲክሱ ላይ የሚፈጥረው ጫናን እንዴት ያብራሩታል?
የአየር ተስማሚነት መረጃ እንኳንስ ገና በእድገት ላይ ለምትገኘው ኢትዮዽያ ቀርቶ በሳይንሱ መጥቀዋል የተባሉትንም አገራት ያን ያህል አልጠቀመም፡፡ መረጃዎችን ሰብስቦ፤ አቀናጅቶ እና አገናዝቦ  ወደ መሬት በማውረድ ለመስራት ቢያስፈልግም ያሉት ክፍተቶች በተመጣጠነ መልኩ አልጠበቡም፡፡ በዓለም አቀፍም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ በአየር ትንበያ ዙርያ በመገናኛ ብዙሐናት የሚሰራጩት የሙቀት፣ ንፋስና ርጥበት፣ መረጃዎች ከመለኪያ መሳሪያዎች በቀጥታ የሚነበቡ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በቢቢሲ ትንበያ መሰረት የአዲስ አበባ የአየር ሁኔታ ሲገለፅ ከፍተኛው ሙቀት 19 ዲግሪ ሴቲግሬድ ነው ተባለ፡፡ በመንገድ ላይ የሙቀት መለኪያ መሳሪያውን በክፍት መኪና ላይ ይዘን ብንሄድ ተመሳሳይ  መጠን ያሳየናል፡፡ አብሮን ያለ ተሳፋሪ ሰው ግን ብርድ ይመታኛል በማለት መስኮት ይዘጋል፡፡ ብርድ በሚበረታበት የግጦሽ ቦታ፤ ከብቶችን ከንፋስ ለመከለል፣ መከላከያ ዛፍ በመጠቀም ተስማሚ የሙቀት ሁኔታን በመፍጠር የአውስትራሊያ ሳይንቲስቶች የተገናዘበ መረጃን አመንጭተዋል፡፡ ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡ በአንድ ወቅት የኢኮኖሚያቸው ዋና ምንጭ በሆኑት የሱፍ በጐች ላይ የደረሰው እልቂት መነሻቸው ነበር፡፡ 40ሺ የሱፍ በጐቻቸው ጸጉራቸውን በተሸለቱበት ዕለት በአንድ ሌለት የንፋስ አቅጣጫ ተለውጦ በሙሉ አልቀዋል፡፡ የሳይንቲስቶቹ የፈጠራ ግኝት ይህን አይነት አደጋ ለመከላከል ያገዘ ነው፡፡
ንፋስ  20 ኪ.ሜ. በሰአት ከነፈሰ ለሰውም ሆነ ለእንስሳ 8 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የቀነሰ የሙቀት ስሜትን ያስከትላል፡፡  ለምሳሌ የአዲስ አበባ አየር ጸጥ ያለ እንቅስቃሴ 0.0 ቢሆንና ገንዘቤ በ20 ኪ. ሜ በሰአት ፍጥነት ብትሮጥ ወደ ራስዋ ተመሳሳይ ፍጥነት ያለውን ነፋስ አነፈሰች ወይም ፈጠረች ማለት ይሆናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ግን ቴርሞሜትር የሚያነበው በተለምዶ የምናየውና የምንሰማውን 19 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነው፡፡ ገንዘቤን የሚሰማት ግን ወደ ታች የወረደውን 11 ወይም የ12 ዲግሪ ሴንትሬድ ነው፡፡ በመሆኑም ንፋስ በቀዝቃዛ ቦታ ጫና ሲሆን በሙቀት ቦታ ፋታ ይሆናል የሚለው ድምዳሜ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡ በተቃራኒው ርጥበት (Humidity) በሙቀት ቦታ አስጨናቂና መሰናክል ሲሆን በቀዝቃዛ ቦታ ደግሞ አያሰናክልም ፡፡ ለምሳሌ በአገራችን የሜትሮሎጂ ሰዎች ከአሜሪካ ሳይንቲስት የሳይንስ ጆርናል በመውሰድ ለጤና ጥበቃ በተለይ ለወባና ለሌሎችም ጫናን በመገመት መፍትሔ በመፈለግ ላይ እንደሆኑ አውቃለሁ፡፡ በዚህ ዙሪያ በእንስሳ ላይ የተሰሩ ዋናው ነገር መሠረታዊ መረጃዎችን ተንትኖ አቀናጅቶና አጠናቅሮ የአየር ተስማሚነትን በመተንበይ መስራት ነው፡፡ በአትሌቲክስ ሲተረጎም ለአትሌት ወደፊት የሚሮጥበት ቦታ መሰናክሉንና ፋይዳ እድሉን ማወቅ ነው፡፡ የትኛው አትሌት ይፈይድበታል፤ የትኛውስ ይጠቃል፤ በምንስ ያህል፤ የሚለውን የአገራችን ብቻ ሳይሆን አስጊ ተፎካካሪን ለይቶና አውቆ በማስቀመጥና በመስራት ስልት መተለም ይቻላል፡፡
የዛሬ 11 ዓመት በግሪክ ኦሎምፒክ ወቅት የኢትዮጵያ አትሌቶች አሰልጣኝ የአየር ጫና ለሁሉም ተወዳዳሪ እኩል ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡ ሌላ ታዋቂ አትሌትም ይህንኑ አባባል መድገሙን አስታውሳለሁ፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ዛሬም ሳይንሳዊ መረጃ አያስፈልግም የሚል አመለካከት እንደሰፈነ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች  በሳይንስ እውቀት የገዘፉትን  አገራት አሸንፈናል የሚለው አመለካከት ሊቀየር አለመቻሉ ከፍተኛው መሰናክል እንደሆነ ማመልከት እፈልጋለሁ፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ይወክለናል ፤ ያገባናል የምንል ሰዎች ደግሞ ይህ አይነቱን ኋላ ቀር አስተሳሰብ ለማስቀረት ጫና መፍጠር ይጠበቅብናል፡፡ የአየር ሁኔታ፤ የምግብ፤ የጤና፤ የስነልቦና፤ የዘረመል፤ እንዲሁም የስነ ምዳር ባለሙያዎችና የመሳሰሉት በጥናት ላይ የተመሰረቱ መረጃዎችን የማቀበል ድርሻቸው መጠናከር አለበት፡፡ ሁላችንም ሃላፊነትና ግዴታም አለብን፡፡ ማንኛውንም ተግባር በጥራትና ለማከናወንና ፉክክር ባለበት ሰብሮ ለመውጣት የተፎካካሪን የብቃት ደረጃና ደካማ ጐኑን ማወቅ ግድ ይላል፡፡ በዚህ ሰላማዊ ፍልሚያ ሳይንሱን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ከመገንዘብ አልፎ ማገነዛዘብም ይጠይቃል፡፡ የተቀናጀ የመረጃ አሃዝ እንደአየሩ ሁኔታ ስለሚለዋወጥ የሚወጣው ተለዋዋጭ ስልት በተዋኙ/ተዋኝዋ አትሌት ግንዛቤው መጨበጥ የግድና የግድ ይላል፡፡ ካልሆነማ ምኑን ተፋለሙ ማለት ይችላል፡፡
የአገራችን ስነምህዳር በፍጥነት ለሚሮጥ ወይም ለሚከንፍ ሰውም ሆነ እንስሳ እጅግ በጣም ግርድፍ ነው፡፡ የአውስትራሊያ ሳይንቲስቶች የአገራቸውን አየር ሲከፋፍሉ የቀረውንም አለም ከራሳቸው አከፋፈል አኳያ አገናዝበውታል፡፡ ለአገራቸው ተስማሚ የሆነውን እንስሳ፤ ለምሳሌ ፈረስ ከየት ብናመጣ የተሻለ ተመችቶት ይሮጣል ብሎ ለመወሰን ስለሚያስችላቸው የቀረውን ዓለም ሁኔታዎች በማጥናት ምርምር አድርገዋል፡፡ ከሜልቦርንና ታዝማንያ የመጣው ነጭ ባህርዛፍ በአዲስ አበባ ላይ ውጤት ማሳየቱን ከዛፍ ዘረመል ሳይንቲስቶች ጋር በአንድ አጋጣሚ አብረን በሰራንበት ወቅት የተረዳሁት ነው፡፡ ከበቆጂ 10 ኪ.ሜ ርቃ በስተሰሜን ከምትገኘው ሊሙ የተባለች የተስማማውን ዘረመል አግኝተናል፡፡ በአየር ንብረት ምስስል የአገራችን ከፍተኛ ተራራ ደጋው አካባቢ ማለት ነው፤ ከነሱ አከፋፈልና ግንዛቤ በላይ መሆኑን በዚህ መገንዘብ ይቻላል፡፡
ከአየር ተስማሚነቱ በተገናኘ የቦታ ስምምነትም ለአትሌቲክስ ውጤት ፋይዳ አለው ማለት ነው?
እሱን ለመረዳት በ2000 እ.ኤ.አ በሲድኒ ኦሎምፒክ የተመዘገበውን ውጤት ማስታወስ ይበቃል፡፡  በ5ሺ ሜትር ወንዶች ሚሊዬን ወልዴ በሲድኒ ኦሎምፒክ ላይ በወጣትነት የወሰደውን የወርቅ ሜዳልያ ለምን አልደገመም? የደራርቱ ብቃት ምንም እንኳን ጥያቄ ውስጥ ባይገባም፤ በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ የተጐናፀፈችው ከአራስነት ተነስታ መሆኑስ፤ እነዚህን ሁኔታዎች በማስተዋል የቀረበ ምርምር የለም፡፡ ለእነዚያ አስደናቂ ውጤቶች የአየሩ እጅግ ተስማሚ መሆን አስተዋጽኦ እንደነበረው በርግጠኝነት መመስከር ይችላል፡፡ በሲድኒ ኦሎምፒክ 2000 እ.ኤ.አ ላይ አራት ወርቅ የተገኘው በአራት የተለያዩ አትሌቶች ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ በኦሎምፒክና ዓለም ሻምፒዮና ሁለት ታዋቂ አትሌቶች በልዩ ብቃት የወርቅ ሜዳልያዎችን እያስመዘገቡ ቆይተዋል፡፡ የተለየ ለውጥ ማየት እና የስኬታማ አትሌቶች ብዛት ማየት ግን አልተቻለም፡፡ በእኔ አስተያየት በሲዲኒ ኦሎምፒክ በአራት የተለያዩ አትሌቶች 4 የወርቅ ሜዳሊያዎች መሰብሰብ የተቻለው በዋናነት የቦታውን ተስማሚነት የፈጠረው እድል ነው፡፡  በ2004 እ.ኤ.አ ግሪክ ባስተናገደችው ኦሎምፒክ የነበረው አየር በጣም በመሞቁና ወበቅ ስላለው ቀነኒሳን በአንድ ወርቅ አስቀረው፡፡ በአንፃሩ የሞሮኮው ኢል ጋሩዥ ከተመሳሳይ ቦታ ተነስቶ የተወዳደረ ስለነበር የወርቅ ሜዳልያውን ነጥቆታል፡፡ የግሪኳ ከተማ አቴንስ በክረምት ፀሐይ ሰሜን ንፍቀ ክበብ ላይ ስለሆነች ሙቀቱም ሆነ እርጥበቱ ተዳምሮ መሰናክሉ ይከፋል፡፡ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ አትሌቶች ጫና ነው፡፡ በአውስትራሊያዋ በሲድኒ ግን በተቃራኒው ተመሳሳይ አየርና ቦታ ላይ ስለሆነ ፋይዳ በፋይዳ ሆናልናለች፡፡ አየር ሙቀትና እርጥበት ለሁሉም እኩል ነው ተብሎ የሚሰጠው አስተያየት  የስህተት ድግግሞሽ ነው፡፡ በስንት ሳይንቲስት የሚታገዙትን የውጭ አትሌቶችን በራሳችን መንገድ አሸነፍን እየተባለም ነበር፡፡ እስቲ በሳይንስ የሚታገዙትን እንይ አሜሪካ ቅርብ ጊዜ ማራቶን እያሸነፈች አይደለም ወይ?  ….. ይቀጥላል

    በስኳር በሽታ ሳቢያ የተጐዱ የልብ የደም ቱቦዎችና የሰውነታችን ውስጣዊ አካላቶች የአበባ ጐመን በመመገብ በፍጥነት እንዲጠገኑ ማድረግ እንደሚቻል በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ገለፁ፡፡
 በአሜሪካ ዋርዊክ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ባሉ ምሁራን የተደረገና በቅርቡ ይፋ የሆነ አንድ ጥናት እንዳመለከተው፤ በአበባ ጐመን ውስጥ የሚገኘውና ሰልፎራፔን የተሰኘው ንጥረ ነገር የደም ቱቦዎችን የሚጠብቁ ኢንዛይሞች በብዛት እንዲመረቱ ያደርጋል፡፡ ይህም በሴሎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሞሎኪውሎች ቁጥር እንዲቀነስ እንደሚያደርግ ባለሙያዎቹ ገልፀዋል፡፡ ከስኳር በሽታ ጋር ግንኙነት ያለውና Hyperglycemia በመባል የሚጠራው ከፍተኛ የጉሉኮስ መጠን በደም ስሮች ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በአበባ ጐመን ውስጥ የሚገኘው ሰልፎራፔን የተባለው ኢንዛይም እንደሚጠግነው መረጋገጡንም ምሁራኑ ተናግረዋል፡፡ የስኳር ህሙማን ከጤናማዎቹ በአምስት እጥፍ ለልብ በሽታዎች የተጋለጡ ናቸው፡፡ የስኳር ህመም በልብ ደም ስሮች ላይ በሚያስከትለው ጉዳት ሳቢያ ስትሮክና የልብ ድካም ይከሰታል፡፡

ለጤናዎ 10 ጠቃሚ ምግቦች
ፈረሰኛ ለስኳር ህሙማን ይመከራል
የምንመገባቸውን ምግቦች በማስተካከል ጤናችን የተጠበቀ ማድረግ እንደሚቻል የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ ቀጥሎ የተዘረዘሩት 10 የምግብ ዓይነቶች ሰውነታችን የበሽታ መከላከል አቅሙን እንዲጨምር በማድረግ፣ ጤናማና ደስተኛ ህይወት ለመምራት እንደሚያስችለን Changeone.com ከተሰኘው ድረ ገፅ ያገኘነው መረጀ ያመለክታል፡፡ እነዚህ ለጤናዎ ጠቃሚ የሆኑ አስር የምግብ አይነቶች የሚከተሉት ናቸው፡-
አሣ - ከእንስሳት የሚገኘውን ሥጋ የሚተካውና ጥሩ የፕሮቲን ምንጭ የሆነው አሣ Omega 3 ለተባለው ፋቲአሲድ ዋንኛ ምንጭ በመሆንም ይታወቃል፡፡ እነዚህ ፋቲአሲዶች የደም ቅዳዎቻችን ንፁህ እንዲሆኑ ያደርጋሉ፡፡ አሣ በተለይ ለስኳር ህሙማን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው የምግብ አይነት ነው፡፡ የስኳር በሽተኞች አብዛኛውን ጊዜ (HDL) የተሰኘው ጠቃሚ ኮሌስትሮል እጥረት ይታይባቸዋል፡፡ Omega 3 ይህንን የኮሌስትሮል እጥረት በማስተካከል ይታወቃል፡፡
በሣምንት ቢያንስ ሁለት ቀን አሣን መመገብ ለጤና እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ሳልመን፣ ማካፌል እና ቱና የተባሉት የአሣ ዓይነቶች የፋቲ አሲዱ ዋንኛ መገኛዎች ናቸው፡፡
የዶሮ ስጋ
ፈረሰኛ የምንለው የዶሮ ብልት፤ ለስኳር ህሙማን እጅግ በጣም ተመራጭና ጠቃሚ የምግብ አይነት ነው፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች ፈረሰኛን “ተአምረኛው ምግብ” ሲሉ ይጠሩታል፡፡ ፈረሰኛ የሥጋ ምግቦች ከያዙት የስብና የኮሌስትሮል መጠን በእጅጉ ያነሰ ነው የያዘው፡፡ በ85 ግራም ፈረሰኛ ውስጥ 142 ካሎሪና 3 ግራም ስብ ብቻ ይገኛል፡፡
እርጐ
እርጐ በፕሮቲንና ክብደትን ለመቀነስ በሚረዳው ካልሲየም በተባለው ንጥረ ነገር የዳበረ ነው፡፡ በርካታ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ በካልሲየም የዳበሩ ምግቦችን የሚመገቡ ሰዎች በቀላሉ ክብደታቸውን ለመቀነስ ይችላሉ፡፡ ደስተኛና ጤናማ ህይወት እንዲኖርዎ የእርጐ ወዳጅ ይሁኑ፡፡ ቁርስዎን ቅባት የሌለው እርጐ በመውሰድ ይጀምሩ፡፡
አትክልቶች
አትክልቶች በተፈጥሮአቸው ዝቅተኛ ካሎሪ ነው ያላቸው፡፡ በፋይበር (አስር) የበለፀጉም ናቸው፡፡ የምግብ ገበታዎን ለጤና ከፍተኛ ጠቀሜታ ባላቸው ንጥረ ነገሮች በዳበሩት አትክልቶች ሞሉት ማለት የደም ስኳር መጠንዎን ተቆጣጠሩ ማለት ነው፡፡
ፍራፍሬ
ፍራፍሬዎች የከፍተኛ ፋይበር ምንጭ ሲሆኑ ዝቅተኛ ስብና ዝቅተኛ ካሎሪን በመያዝም ይታወቃሉ፡፡ ፍራፍሬዎች ልባችንን፣ ዓይናችንንና ጥርሶቻችንን ከበሽታ በሚከላከሉ አንቲኦክሲደንቶች የበለፀጉ ናቸው፡፡ ፍራፍሬዎችን ከጭማቂው ይልቅ እንዳለ መመገብን ይምረጡ፡፡ በርካታ ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች በፍሬው ላይ ስለሚገኙና እነዚህ ጠቃሚ ነገሮች በሚጨመቅበት ወቅት ስለሚጠፉ ፍሬውን እንዳለ መመገቡ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ ፍራፍሬዎች በተፈጥሮ ስኳርና ካሎሪ የበለፀጉ በመሆኑ በብዛት ከመመገብ መታቀብ ይኖርብናል፡፡
ለውዝ
ለውዝ የቫይታሚን E ዋንኛው ምንጭ ነው፡፡ ይህ ቫይታሚን በውስጡ የያዘው አንቲኦክሲደንት ሴሎችን በመጠበቅ የነርቭና የአይን ጉዳት እንዳይከሰት ያደርጋል፡፡ ለውዝ በበርካታ ጠቃሚ የስብ አይነቶች የተሞላ የምግብ አይነት ነው፡፡ እነዚህ ስቦች የልብ በሽታን በመከላከልና ኢንሱሊን ያለመቀበል ሂደትን በመቀነስም ይታወቃሉ፡፡ የደም ውስጥ የስኳር መጠንንም ለመቆጣጠር ያስችላሉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ለውዝን አዘውትሮ መመገብ ክብደትን ለመቀነስ ይረዳል፡፡ የስኳር ህመምተኛ ከሆኑ ግን ለውዝን አዘውትረው አይመገቡ፡፡
ቀረፋ
በምግብዎ ውስጥ ቀረፋን ጣል የሚያደርጉ ከሆነ፣ አስገራሚ በሆነ ሁኔታ የደምዎ የስኳር መጠን ቀንሶ ያገኙታል፡፡ በቀረፋ ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች ሰውነታችን ኢንሱሊንን በአግባቡ እንዲጠቀም ያደርጉታል፡፡ በስኳር ህሙማን ላይ የተደረገ ጥናት፤ ግማሽ ማንኪያ ቀረፋ በየዕለቱ የሚወስዱ ሰዎች የደም የስኳር መጠናቸው በአስገራሚ ሁኔታ ቀንሶ ተገኝቷል፡፡ የቀረፋን ዱቄት በዳቦ ወይንም በሌሎች ምግቦችዎ ውስጥ በመጨመር ይመገቡ፡፡ እንጨቱንም በሻይ መልክ እያፈሉ በመጠጣት ጤናዎን ይጠብቁ፡፡
ጥራጥሬ
የጥራጥሬ ምግቦች በፋይበር የበለፀጉ ናቸው፡፡ አዘውትረው ቢመገቧቸው ጤናዎን ለመጠበቅ በእጅጉ ይጠቅምዎታል፡፡
የወይራ ዘይት
የወይራ ዘይት በልብ በሽታ የመያዝ ዕድልን ይቀንሳል፡፡ የደም የስኳር መጠንን ያረጋጋል፡፡ ምግብዎን በወይራ ዘይት አብስሎ ሲመገቡ ራስዎን ከተለያዩ በሽታዎች ይታደጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ የስኳር ታማሚ ከሆኑ፣ የወይራ ዘይትን አዘውትረው ከመመገብ ይቆጠቡ፡፡  

Published in ዋናው ጤና

በአገራችን ከአምስት ህሙማን አንዱ መድሃኒቶችን በስህተት ይወስዳል
የሃኪሙን የእጅ ፅሁፍ ማንበብ የሚያዳግታቸው ፋርማሲስቶች በዝተዋል

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በተደረገለት ሙሉ ምርመራ የጉበት ህመምተኛ መሆኑ ሲነገረው ድንጋጤው ልክ አልነበረውም፡፡ ህመሙ ዕለት ከዕለት እየተባባሰበት በመሄዱ ምክንያት ወደ ሆስፒታል ሄዶ ምርመራ ለማድረግ ሲወስን፣ ሃኪሙ ህመሙን አውቆለት ፈዋሽ መድሃኒት እንደሚያዝለት፣ ከበሽታውም እንደሚያገግም ጽኑ እምነት ነበረው፡፡
ከሃኪሙ የተፃፈለትን የመድሃኒት ማዘዣ ይዞ መድሃኒቱን ፍለጋ ወጣ፡፡ በከተማው ውስጥ ያሉ በርካታ መድሃኒት ቤቶችን ቢያስስም መድሃኒቱን ማግኘት አልቻለም፡፡ ቆይቶ ግን መድሃኒቱ በአንድ ፋርማሲ ውስጥ እንደሚገኝ ሰማ፡፡ ለመድሃኒቱ የተጠየቀውን ዋጋ ከፍሎ ገዛ፡፡ ችግሩ ግን ስለመድሃኒቱ አወሳሰድ ፋርማሲስቱ የነገረው ነገር አልነበረም፡፡ የገዛውን መድሃኒት ይዞ ወዳዘዘለት ሃኪም ሄደ፡፡ ሃኪሙ ዘንድ ቀርቦ መድሃኒቱን በብዙ ፍለጋ ማግኘቱን በመግለጽ፣ ስለአወሳሰዱ እንዲነግረው ጠየቀው፡፡ ሃኪሙ በጣም ተገርሞ፤
“ለመሆኑ መድሃኒቱ የተገዛው ከፋርማሲ ውስጥ ነው?” ጠየቀው
“አዎ” አለ ታካሚው፡፡
“ታዲያ እንዴት ፋርሚሲስቱ ስለአወሳሰዱ ሳይነግርህ ቀረ?” በማለት መድሃኒቱን ከነማዘዣው ከህመምተኛው ላይ ተቀብሎ አየው፡፡ ታካሚው በሃኪሙ ፊት ላይ ያየው ከፍተኛ ድንጋጤ እሱኑ ይበልጥ አስደነገጠው፡፡
“ችግር አለ?” ሲል ጠየቀው ሃኪሙን
“እርግጠኛ ነህ እኔ ላዘዝኩልህ የተሰጠህ መድሃኒት ይሄ ነው?” ሲል ጠየቀው ታማሚውን፡፡
“ጌታዬ 486 ብር የከፈልኩበት መድሃኒት እኮ ነው እንዴት ብዬ ከሌላ መድሃኒት ጋር እቀላቅለዋለሁ”
ለዚህ መድሃኒት መግዣ ያወጣውን 486 ብር ለማግኘት የተጋፈጠውን ውጣ ውረድ የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው፡፡ ሃኪሙ በጣም አዘነ፡፡
ታካሚው ከፋርማሲ ገዝቶ ያመጣው መድሃኒት፤ ለማህፀን ህክምና የሚያገለግልና ለሴቶች ብቻ የሚታዘዝ ነበር፡፡ ሁኔታው እጅግ ቢያስደነግጠውም ለመድሃኒቱ ያወጣው ገንዘብ ኪሣራ ላይ ሊወድቅ መሆኑ ይበልጥ አበሳጨው፡፡ ወደ ፋርማሲው ሄዶ ስለጉዳዩ በመንገር፣ ገንዘቡን እንዲመልሱለት ለማድረግ መድሃኒቱን ተቀብሎ ወደዚያው አመራ፡፡ ፋርማሲው ውስጥ ላገኘው ሰውም ሁኔታውን አስረዳ፡፡ በወቅቱ የተገኘው ባለሙያ፤ ከሰውየው ላይ መድሃኒቱን ተቀብሎ አየው፡፡ ምናልባት የፋርማሲ ባለሙያው በስህተት ሰጥቶት ሊሆን እንደሚችል ነግሮ፣ በማዘዣው ላይ የተፃፈውን መድሃኒት ሊሰጠው እንደሚችል አግባባው፡፡ ይሁን እንጂ ይህኛውም ሰው በመድሃኒት ማዘዣው ላይ የተፃፈውን ጽሑፍ በአግባቡ በማንበብ ተገቢውን መድሃኒት ሊሰጠው አልቻለም፡፡ ይልቁንም “መድሃኒቱ እኛ ጋ የለም ሲል” ማዘዣውንና ታማሚው ቀደም ሲል የከፈለውን 486 ብር መልሶ በመስጠት አሰናበተው፡፡
ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝን ይህንን መረጃ ያገኘሁት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለህክምና መጥቶ ካገኘሁት አንድ ታካሚ ነው፡፡ ታካሚው ከሃኪሙ የተፃፈለትን መድሃኒት በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ከሚገኘው የመድሃኒት መሸጫ ፋርማሲ ለማግኘት ባለመቻሉ ነበር መድሃኒቱን ፍለጋ ከተማውን ሲያስስ የከረመው፤ ይሁን እንጂ በአብዛኛው መድሃኒት ቤቶች ውስጥ መድሃኒቱን ለማግኘት አልቻለም፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ ከበሽታው ጋር ፈጽሞ የማይገናኝና ምናልባትም ለከፋ ችግር ሊያጋልጠው የሚችል መድሃኒት ባለሙያ ነኝ ብሎ ከተቀመጠ የመድሃኒት ቤት ሰራተኛ መሰጠቱ ነው፡
ወደ ሆስፒታሉ ተመልሶ የመጣው ሃኪሙ መድሃኒቱን በሌላ መድሃኒት ቀይሮ እንዲፅፍለት ለመጠየቅ መሆኑን አጫውቶኛል፡፡ ለፍለጋው በተዘዋወረባቸው በርካታ መድሃኒት ቤቶች ውስጥ ያገኛቸው የፋርማሲ ባለሙያዎች፤ በማዘዣው ላይ የተፃፈው የሃኪሙ የእጅ ጽሑፍ ፈጽሞ የማይነበብ መሆኑንም ነግረውታል፡፡ ስለዚህም ሃኪሙ ሊነበብ በሚችል መልኩ ማዘዣውን እንዲፅፍለት እንደሚጠይቀውም ገልፆልኛል፡፡
አለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) ለፋርማሲ ሙያ በሰጠው ትርጓሜ፤ የፋርማሲ ባለሙያ ማለት፣ ከሃኪም በሚሰጠው ትዕዛዝና መመሪያ መሠረት፣ መድሃኒቶችን ለህሙማን ማደል፣ ስለመድሃኒቱ አወሳሰድ፣ መድሃኒቱ ስለሚኖረው የጐንዮሽ ጉዳትና ከመድሃኒቱ ጋር ሊወሰዱና ላይወሰዱ ስለሚችሉ ምግብና መጠጦች በግልጽ ለህመምተኛው የሚያሳውቅ ሰው ነው፡፡ የፋርማሲ ባለሙያው መድሃኒቶችን ለህሙማን ከማደል በዘለለ ከህሙማኑ ጋር ጥብቅ መግባባትን ማድረግ የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡ ባለሙያው ሁልጊዜም ከህመምተኛው ጀርባ ሆኖ ስለህመምተኛው የሚጨነቅና የሚያስብ ሰው ነው፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ት/ቤት መምህር ዶክተር ተስፋዬ ታረቀኝ እንደሚናገሩት፤ “የፋርማሲ ሙያ እንደ ህክምና ሙያ ሁሉ ትልቅ ከበሬታ ሊሰጠው የሚገባና በአግባቡ የሰለጠነ የሰው ሃይልን የሚጠይቅ ነው፡፡ የፋርማሲ ባለሙያዎች ከህክምና ባለሙያዎች ጋር ጥብቅ ትስስር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የፋርማሲ ባለሙያ ማለት ከሃኪሙ በሚሰጠው ማዘዣ መሠረት ታማሚው መድሃኒቱን በአግባቡ መውሰድ እንዲችል ተገቢውን መመሪያ የሚያስተላልፍ ሙያተኛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን የሚታየው ነገር ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ታካሚው መድሃኒት ፍለጋ በሚሄድባቸው ፋርማሲዎች ውስጥ ያሉ ሰዎች ሙያውን በሚገባ ያውቁታል ለማለት ፈፅሞ አያስደፍርም፡፡ አንዳንድ ፋርማሲስቶች፤ የመድሃኒት ማዘዣዎች አልነበብ ሲላቸው፣ በደንበኞች ፊት ሃኪሞችን ከፍ ዝቅ አድርገው ሲሳደቡና ሲያዋርዱ ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ ለሙያው የሚሰጠውን ግምት በእጅጉ የሚያወርድና በሃኪሙና በህመምተኛው መካከል መተማመን እንዳይኖር የሚያደርግ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የመድሃኒት ማዘዣዎችን በሚገባ አንብቦና ተረድቶ መድሃኒቶችን ለህሙማን የሚያድል የፋርማሲ ባለሙያ ማግኘቱ እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው”
በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሃኪም መድሃኒት ከታዘዘላቸው ታካሚዎች ከአምስቱ አንዱ መድሃኒቶችን በስህተት ይወስዳል፡፡ ሃኪሞችን የፋርማሲ ባለሙያዎችን፣ ነርሶችንና ህሙማንን ያካተተው ጥናቱ፤ በመድሃኒት አስተዛዘዝ ዙሪያ ከባድ ችግር እየተከሰተ መሆኑን ይጠቁማል፡፡
አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች የሚጽፉት የመድሃኒት ማዘዣ የማይነበብና የተሟላ መረጃ የሌለው ሲሆን የሃኪሙን የእጅ ጽሑፍ በሚገባ አንብቦና ተረድቶ ተገቢውን መድሃኒት ለህመመተኛው የሚሰጥ የፋርማሲ ባለሙያ ማግኘትም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡
ህሙማኑም ስለታዘዘላቸው መድሃኒት አወሳሰድ ሃኪማቸውን አይጠይቁም፡፡ የፋርማሲ ባለሙያዎቹም፤ ለህሙማኑ መድሃኒቱን ሲሰጡ ስለአወሳሰዱ፣ ስለመድሃኒቱ ባህሪያትና ስለጐንዮሽ ጉዳቱ አይናገሩም፡፡
ይህ የሚያሳየው ደግሞ ህመምተኛው ስለሚወስደው መድሃኒት ምንነትና አወሳሰድ ሳያውቅ በስህተት መድሃኒቶችን ለመውሰድ መገደዱን ነው፡፡
በጥናቱ እንደተመለከተው፤ ብዙውን ጊዜ ህሙማን መድሃኒት ፍለጋ ከፋርማሲ ፋርማሲ የሚንከራተቱት መድሃኒቱ በፋርማሲው ሳይገኝ ቀርቶ ሳይሆን የፋርማሲ ባለሙያው ማዘዣውን አንብቦ መረዳት ባለመቻሉ ምክንያት መሆኑን አመላክቷል፡፡ ይህ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና ሁሉም ሙያተኞች የሙያውን ሥነምግባር አክብረው፣ ተገቢውን ህክምናና መድሃኒት ለህመምተኛው መስጠት እንዳለባቸው ይኸው ጥናት ይገልፃል፡፡
በሰለጠነው ዓለም የመድሃኒት ማዘዣዎች በዲጂታል ማሽኖች እየተተኩ ነው፡፡
ልክ እንደ ባንክ ኤቲኤም ማሽን፣ በደንበኞቹ በቀረበለት የመድሃኒት ማዘዣ መሠረት ትክክለኛውን መድሃኒት አውጥቶ ከነአወሳሰድ መመሪያው ለህሙማኑ መስጠት የሚችል መሣሪያ አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡
መድሃኒቶች ከበሽታ በመፈወስ ነፍስን የመታደጋቸውን ያህል በአግባቡ ካልተያዙና አገልግሎት ላይ ካልዋሉ አጥፊ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ስለዚህ ለህይወት ደህንነት የተሰራልን መድሃኒት አጥፊያችን እንዳይሆን፣ እራሳችንን ጨምሮ የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡       

Published in ዋናው ጤና

• ኢቢሲ፣ ይሄን ዘገባ ሰሞኑን ያሰራጨው የት ከርሞ ነው?

1. ወጪው ከ1 ቢ. ብር በታች ነው የተባለው ግንባታ፣ ከ5 ቢ. ብር በላይ ፈጅቶም አላለቀም።  
2. ቢበዛ በ3 ዓመት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል የተባለው ግድብ፣ 10 ዓመት አልበቃውም።
3. ግድቡ እየተጓተተ ወጪው እንደናረ፣ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አድማስ ሲዘገብ ቆይቷል።
4. በ2006 ዓ.ም፣ የፌደራል ዋና ኦዲተር፣ ግንባታው መዝረክረኩን ገልጿል - (አዲስ አድማስ)።
5. ነገሩ ሲባባስም፣ አምና፣ የገንዘብ ሚ.ር፣ ለግድብ በጀት አልመድብም ብሏል። (አዲስ አድማስ)።
6. የመንግስት ሚዲያ (ኢቢሲ) እና የመሳሰሉ፣ እነዚህን ዘገባዎች፣ “ጨለምተኛ” ሲሏቸው ነበር።

    ከአንድ ቢሊዮን ብር በታች ይፈጃል ተብሎ በ1997 ዓ.ም የተጀመረው የተንዳሆ ግድብ ፕሮጀክት፣ በሁለት ወይም በሦስት ዓመት እንዲጠናቀቅ ነበር የታሰበው። ምን ዋጋ አለው? ወጪው ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል። አስር አመትም ሞላው። ግን ግንባታው አላለቀም። የሚያሳዝንና የሚያስቆጭ ትልቅ ኪሳራ ነው።
በዚህ መሃል…ኢቢሲ፣ ድንገት ተነስቶ፣ ይህንን የኪሳራ መረጃ ዘንድሮ የሚነግረን፣ የት ከርሞ ነው? ላለፉት ስድስት አመታት የት ነበር? “የግድቡ ግንባታ፣ በተያዘለት እቅድ፣ እየተከናወነ ነው” የሚል... ከእውነት የራቀ፣ ‘የሌለ’ ዜና ለመስራት ሲተጋ ነበር፡፡ ለዚያውም ለበርካታ አመታት።
እና፣ አሁን ምን አዲስ ነገር ተፈጠረና ነው፣ ‘ግንባታው ተጓተተ፤ ወጪው ሸመጠጠ’ የሚል ዜና የሚያቀርብልን? ምናልባት፣ በአዲስ መንፈስ፣ ‘ከእንግዲህ ትክክለኛ ዜና እሰራለሁ’ የሚል፣ የአዲስ አመት እቅድ አውጥቶ ይሆን? ቢሆንማ፣ ጥሩ ነበር።
ግን አይደለም። “ትክክለኛ ዜና የመስራት እቅዱ፣ ለተንዳሆ ግድብ ብቻ ነው” ካልተባለ በቀር ማለቴ ነው። እንዴት ካላችሁ፣... ኢቢሲ፣ ከተንዳሆ ዜና ጎን ለጎን፣ ስለ ህዳሴ ግድብ ያቀረበውን ዜና መመልከት ትችላላችሁ።   
ኢቢሲን ስትከፍቱ፣ “የሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ በተያዘለት እቅድ በጊዜው እየተከናወነ ነው” የሚል ዜና መስማታችሁ አይቀርም። ለሕዳሴ ግድብ፣ ከፍተኛ ክብር ያላቸው ብዙ ኢትዮጵያዊያን፣ ዜናውን በትኩረት አዳምጠውት ይሆናል። በእርግጥ፣ በየጊዜው የሚደጋገም ዜና ስለሆነ፣ ‘ሳልሰማው አመለጠኝ’ የምንለው አይነት ዜና አይደለም። ባለፈው ሳምንት ቢያመልጣችሁ፣ ከዚያ በፊት በወዲያኛው ሳምንት፣ ተመሳሳይ ዜና ሰምታችሁ ሊሆን ይችላል። ካልሆነም፣ በያዝነው ሳምንት ትሰሙታላችሁ፤... ወይም በሚቀጥለው ሳምንት።
የሕዳሴ ግድብን የሚመለከት፣ የግንባታ ዜና እየተደጋገመ መምጣቱ አይደለም ችግሩ። የሕዳሴ ግድብ፣ እንደ ትልቅነቱ፣ በየጊዜው ከግንባታው ሂደት ጋር ብዙ አዳዲስ መረጃዎች ይኖራሉ። በዚህም ምክንያት፣ የሕዳሴ ግድብ፣ በተደጋጋሚ የዜና ርዕስ ሲሆን ብንሰማ፣ ችግር የለውም። ችግሩ ሌላ ነው። የተሳሳተ መረጃና የውሸት ዜና፣ (ለዚያውም እየተደጋገመ) መምጣቱ ነው ችግሩ።
ኢቢሲ፣ እንደተለመደው፣ “የሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ በተያዘለት እቅድ፣ በጊዜው እየተከናወነ ነው” ካለ በኋላ፤ የግድቡ ግንባታ፣ 47% ላይ መድረሱን ገልጿል። ከምር ለመናገር፣ በትልቅነቱ የሚጠቀስ ግድብ፣ የዚህን ያህል ተገንብቶ ማየት፣ ቀላል ነገር አይደለም። ብዙ ተሰርቷል። ኢቢሲ፣ ይህችን እውነተኛ ዜና ብቻ መግለፅ እየቻለ፣ “በተያዘለት እቅድ፣ በጊዜ እየተከናወነ ነው” የሚል ውሸት ለምን ይጨምርበታል? ግራ ያጋባል።
‘ከተያዘለት እቅድ ዘግይቷል።  ግንባታው ግን 47% ደርሷል’ ብሎ እንዲዘግብ መጠበቅ ያስቸግራል። ቢያደርገውማ፣ “the truth, the whole truth, nothing but the truth” እንደሚባለው፣ እውነተኛ መረጃ... የተሟላ እውነተኛ መረጃ፣... ሌላ ነገር (ውሸት) ያልተቀላቀለበት እውነተኛ መረጃ… ይሆን ነበር።
ግን፣ እሺ... ይቅር። እውነተኛ መረጃን አሟልቶ ለመናገር ፈቃደኛ አይሁን። ግንባታው መዘግየቱን ሳይገልፅ ይተወው። ጎደሎ መረጃ መናገር ይችል ነበር - ግንባታው፣ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ብቻ መግለፅ! ያው፣ ‘የተሟላ እውነት’ አይደለም። ግን፣ ቢያንስ ቢያንስ... ውሸት አልተቀላቀለበትም። አይደለም?
ለነገሩ ይህንን እንተወው። ኢቢሲ፣ ‘እንዲህ ቢያደርግ’፣ ‘እንዲያ ቢያደርግ’ እያልን ለምን በከንቱ እንደክማለን። ኢቢሲ፣ ለዚህ ሁሉ ደንታ ያለው አይመስልም። ደንታ ቢኖረው ኖሮ፣ በየጊዜው እየደጋገመ በድፍረት፣ የሃሰት መረጃ ይናገር ነበር? አገር ምድሩ የሚያውቀው የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ፣ የሃሰት መረጃ መናገር... ሌላ ምን ትርጉም ይኖረዋል? በጣም ቀላል ጉዳይ ነዋ።       
የግድቡ ግንባታ፣ “በአምስት አመት ውስጥ ይጠናቀቃል” ተብሎ እንደነበር ማስታወስ ያቅተናል? አሁን፣ አራት አመት ተኩል ሆኖታል። ግንባታው ግን፣ ወደ ማጠናቀቂያው ሳይሆን፣ ወደ ግማሽ ነው እየተጠጋ ያለው። ቢያንስ፣ ተጨማሪ አራት አመታት ያስፈልጉታል ማለት ነው። ኢቢሲ፣ ይህንን ሳይገነዘብ ቀርቶ ይሆን፣ ቀን ከሌት የተሳሳተ መረጃ የሚያሰራጨው? እንዴት ሊሆን ይችላል?
አሁን አይደለም፣... ከአመት ከሁለት አመት በፊትም፣ የግንባታ ሂደቱንና አዝማሚያውን ለመገንዘብ ከባድ አልነበረም። ከሦስት ዓመት በፊት፣ መስከረም 12 ቀን 2005 ዓ.ም፣ በአዲስ አድማስ የወጣውን ዘገባ ማየት ይቻላል።
የመንግስት ፕሮጀክቶችን በሚዳስሰው በዚሁ ዘገባ ላይ፣ የሕዳሴ ግድብ ተጠቅሷል። የሕዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት፣ የታቀደለትን ያህል እየፈጠነ እንዳልሆነ ዘገባው ገልፆ፤ በዚያ አያያዙ፣ ግንባታው ከስምንት እስከ አስር አመት ሊፈጅ እንደሚችል ይጠቁማል። ይሄ ከሦስት ዓመት በፊት የወጣ ዘገባ ነው። በእርግጥም፣ አሁን እንደሚታየው፣ ግድቡ በተያዘለት ጊዜ (ማለትም ዘንድሮ) ሊያልቅ አይችልም። ግማሽ ያህል ይቀራል።
 ይሄ፣ መንግስትን የመተቸት ወይም የማወደስ፣ የመደገፍ ወይም የመቃወም ጉዳይ አይደለም። ጥሬ መረጃ ነው። ችግሩ፣ ኢቢሲ፣ ለእንዲህ አይነት መረጃ፣ “ፊት የሚሰጥ” አልሆነም። ግን፣ አስቡት። ችግሮችን በመደበቅ፣ ማስተካከል አይቻልም። “ችግር አለ” ብለን ካልተናገርን፣ “ችግር ብን ብሎ የሚጠፋ” ይመስል! “በተያዘላቸው እቅድ እየተከናወኑ ነው” ብሎ መናገር ብቻውን፤ “የእቅድ ክንውን” ሆኖ ይመዘገባል ካልተባለ በቀር።
ለእውነተኛ መረጃ፣ “ፊት የማንሰጥ” ከሆነ፣ የመጓተትና የመዘግየት ችግሮች ሲያጋጥሙ፣ ተገቢውን ያህል ትኩረት የሚያገኙበትም ሆነ የሚስተካከሉበት እድል እንዴት ይፈጠራል?
 በተንዳሆ እና በሌሎች የስኳር ፕሮጀክት ላይ ያየነው ኪሳራ፣ ሳይስተካከልና መፍትሄ ሳያገኝ ለአመታት እየተባባሰ የመጣውም በዚሁ ምክንያት ነው። ስለ ተንዳሆ ግድብም ሆነ ስለሌሎቹ ፕሮጀክቶች፣ ኢቢሲ መረጃ ሳያገኝ ወይም ችግሩን ሳይገነዘብ ቀርቶ ነው?
እሺ፣ አላወቀም፤ አልተገነዘበም እንበል። ግን፣ ለማወቅና ለመገንዘብ ፈቃደኛ እስከሆነ ድረስ፣ ቀላል ዘዴዎችን አያጣም ነበር። በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የወጡ ዘገባዎችን ማንበብ፣ ያን ያህል ከባድ ስራ አይደለም።
ሌሎች የስኳር ፕሮጀክቶች፣ የተንዳሆ ስኳር ፕሮጀክትም ጭምር፣ በ1997 ዓ.ም በወጣላቸው እቅድ እየሄዱ እንዳልሆነ፣ በ2001 ዓ.ም በአዲስ አድማስ ሲዘገብ አስታውሳለሁ።
የተንዳሆ ግድብ፣ በ98 ዓ.ም፣ ከዚያም በ99 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር በጀት ተመድቦለት በፓርላማ ከፀደቀ በኋላ፣ ምን እንደተከሰተ የሚዘረዝር ሌላ ሰፊ ዘገባም በዚሁ ጋዜጣ ቀርቧል። በሰፊው መቅረቡ አለምክንያት አይደለም። በየአመቱ የሚመደበው ገንዘብ ቀላል አይደለም። ከመቶ ሚሊዮን ብሮች እስከ ቢሊዮን ብር ይደርሳል። ግን፣ ግድቡ ተገንብቶ አላለቀም። እንደገና፣ የ2000 ዓም. በጀት ሲዘጋጅም፣ ገንዘብ ተመደበለት - የግድብ ግንባታውን ዘንድሮ ለማጠናቀቅ በሚል። ግን አልተጠናቀቀም።
በቀጣዮቹ አመታትም... በ2003፣ ከዚያም በ2004... ምንም የተቀየረ ነገር የለም። የበጀት ሰነዶቹ ላይ፣ አረፍተ ነገሮቹ እንኳ አይቀየሩም። “የተንዳሆ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቀ...” የሚለው ፅሁፍ “ኮፒ ፔስት” እየተደረገ በየአመቱ ይደጋገማል - ዓመተ ምህረቱ ብቻ እየተቀየረ።
የመንግስት ቴሌቪዢን ግን፣ እውነታውን ከመዘገብ ይልቅ (እናም መፍትሄ እንዲበጅለት ከማሳሰብ ይልቅ)፣ የአዲስ አድማስ አይነት ዘገባዎችን ለማስተባበል ነበር የሚተጋው - ፕሮጀክቶቹ፣ በተያዘላቸው እቅድ በጊዜ እየተገነቡ ነው’ እያለ።
ለዚህ ምላሽ እንዲሆንም ይመስላል፣ “እንደ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የመሳሰሉ ትልልቆቹ እቅዶች’ኮ ለአመታት እየተጓተቱ እስከ ዛሬ መዝለቃቸውን ራሱ መንግስት አይክደውም” የሚል ፅሁፍ በአዲስ አድማስ የታተመው (ሰኔ 2 ቀን 2004 ዓ.ም)። “መቼ ነው መንግስት፣ የማይሳኩትን እቅዶች በግልፅ የሚነግረን” በሚል ርዕስ የቀረበ ትንታኔ ላይ ከተጠቀሱት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ፣ የተንዳሆው ፕሮጀክት ነው። አዲስ አድማስ እንዲህ፣ እውነተኛ መረጃዎችን በመስከረም 2005 ዓ.ም ሲዘግብ፣ የመንግስት ሚዲያ በዚያ ሰሞን ምን ዘገበ?
መስከረም 3 ቀን 2005 ዓ.ም የኢዜአ ርዕስ እንዲህ ይላል - “የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በቀጣዩ ጥር ወር በከፊል ወደ ሥራ ይገባል”።
ለነገሩ፣ የመንግስት ሚዲያ፣ በቀላሉ ለእውነተኛ መረጃ “ፊት ይሰጣሉ” ብሎ መጠበቅ አስቸጋሪ እንደሆነ ለመረዳት ከፈለጋችሁ፣ የፌደራል ዋና ኦዲተርን ሪፖርት መመልከት ትችላላችሁ። የተንዳሆ ፕሮጀክት፣ እጅጉን እንደተጓተተና በከፍተኛ የሃብት ብክነት እንደተዝረከረከ፣ ዋናው ኦዲተር ሰፊ ዝርዝር ሪፖርት ያቀረበው በ2006 ዓ.ም ነው። አዲስ አድማስ ይህንን ዘግቧል። በመንግስት ሚዲያ ግን አልተዘገበም።
ሰሞኑን ድንገት ተነስቶ ግን ፕሮጀክቱ ለዓመታት መጓተቱን የሚገልጽ ዘገባ አሰራጨ፡፡ ለዓመታት ለተጓተተ ፕሮጀክት ለዓመታት የተጓተተ ዘገባ !!

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 26 September 2015 09:04

የ‘ምስኪን ሀበሻ’ ነገር…

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለብርሀነ መስቀሉ አደረሳችሁማ!
ምስኪን ሀበሻ በቀጠሮው መሠረት ዛሬም ለአንድዬ አቤቱታውን እያቀረበ ነው፡፡
አንድዬ፡— አጅሬ፣ መጣህ! እኔ ረሳኸው ብዬ ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እንዴት እረሳለሁ፣ ይህን ያህል ዝንጉ አልሆንኩም እኮ!
አንድዬ፡— እሱን እንኳን ተወው፡፡ ሌላው ህዝብ የተቀበረ ታሪኩን እንዳይረሳ ከየትም እየፈለገ ያወጣል እናንተ ያላችሁን ታሪክ እንኳን ሆነ ብላችሁ እየረሳችሁ ይህን ያህል ዝንጉ አልሆንኩም ትለኛለህ!… ተወው፣ እኔ እኮ ዝም ብዬ ነው ለማይሆን ነገር የምለፈልፈው፡፡ እና አሁንስ ምን ሁን ልትለኝ ነው…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ሳምንት እንደነገርኩህ ዘንድሮ ብዙ ነገሮች እያሳሰቡን፣ እያስጨነቁን፣ እያሰጉን ስለሆነ እንደ ሌላው ጊዜ እንዳትረሳን ከአሁኑ ለመለመን ነው፡፡
አንድዬ፡— እኔ እኮ ግራ የገባኝ ምን ሁን እንደምትሉኝ ነው! ሥሩበት፣ ዘርታችሁ እጨዱበት ብዬ ለም መሬት ብሰጣችሁ እናንተ ትዘፍኑልኛላችሁ፡፡ ‘ወተቱ ከጓዳ እሸቱ ከጓሮ’ ስትሉ ያው አሁንም በሬ እንደጠመዳችሁ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ አተቆጣ እንጂ!
አንድዬ፡— ለምን አልቆጣ! ለምን አልቆጣ! የወንዝ መአት ሰጠኋችሁ፡፡ ያንን እንደመጠቀም አንዴ ‘ግንድ ይዞ ይዞራል፣ አንዴ ‘ቢሞላ መሻገሪያው ሌላ’ እያላችሁ ስትዘፍኑለት ግብጽ ደግሞ እየጠለፈ በረሀውን አለማ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱን እንኳን አሁን እያስተካከልን ነው፡፡
አንድዬ፡— አይ ማስተካከል…ሌሎቹንስ ወንዞች ለጌጥ ነው የሰጠኋችሁ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ያው እንደምታውቀው እኛ ብዙ ዘመን እርስ በእርሳችን…
አንድዬ፡— ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ዕድል አግኝቼ ነው አንድዬ!
አንድዬ፡— በየዘመናቱ ዓለም እርስ በእርስ ተላልቋል፡፡ እናንተም ስትተላለቁ ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ትክክል አንድዬ፣ ትክክል….
አንድዬ፡— ይኸው አሜሪካን ጃፓንን ዶጋ አመድ አድርጋ ስንት መቶ ሺህ ህዝብ ገድላ አልነበረም…
ምስኪን ሀበሻ፡— አዎ አንድዬ…
አንድዬ፡— ታዲያ አሁን ጃፓን አሜሪካንን ‘ያኔ ዜጎቼን በቦምብ ፈጅተሽ የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም’ ስትል ሰምታችሁ ታውቃላችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ኧረ ጌታዬ እንደውም በጣም ወዳጆች ናቸው፡፡
አንድዬ፡— ጀርመን እነኛን ስንት ሚሊዮን አይሁዶች — ያውም የእኔን ህዝቦች — ፈጅታ ስንት ዘመን ሲንከራተቱ ኖሩ፡፡ ‘አሁን ያኔ የፈጃችሁንን ብንረሳ ብረሳ ሞት ይርሳን’ ምናምን ሲሉ ሰምታችሁ ታውቃላችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ኧረ እንደውም ወዳጆች ናቸው!
አንድዬ፡— ታዲያ እናንተ ዘላለም ዓለም ትንሹንም ትልቁንም እያነሳችሁ፣ ‘ያኔ እንዲህ አድረግኸኝ’ ‘እንደዛ ስታደርጊኝ የነበረው’ ..እያላችሁ እናንተስ አይሰለቻችሁም፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን እናድርግ፣ አንድዬ…ቂም በቀል ተጣባን! ትንሹም ትልቁ በሆነ ባልሆነው ቂም መቋጠር፣ መበቀል ነው የያዝነው፡፡
አንድዬ፡— እኮ፣ ዘላለማችሁን ጠብ ያለሽ በዳቦ የት አደረሳችሁ!
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱማ…
አንድዬ፡— ታዲያ ለራሳችሁ ሳታውቁ እኔን ምን አድርግ ነው የምትሉኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ልቦና ስጠና፣ ዲያብሎስን አባርልና!
አንድዬ፡— አሁንማ ነገረ ሥራችሁን ሳያችሁ፣ በክፋታችሁ ራሱ ዲያብሎስ የሚፈራችሁ ነው የሚመስለኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እዚህ ደረጃማ አልደረስንም፡፡
አንድዬ፡— ያኔ አባቶቻችሁ ድሀ ቢሆኑም ለፈረንጅ አልተንበረከኩም፡፡ አሁን እናንተ ነጭ ባያችሁ ቁጥር የምትሆኑትን ሳይ እኔም አዘንኩባችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ከዚህ በፊት ነግሬህ የለ…እንግዳ አክባሪዎች ስለሆንን እኮ ነው፡፡
አንድዬ፡— የራሳችሁን ሰው እየናቃችሁ፣ ራሳችሁ ሰው ላይ እንደ አንበሳ እየተጎማለላችሁ፣ ለራሳችሁ ሰው ግንባራችሁን እየቋጠራችሁ ፈረንጅ ስታዩ እንደዛ ስድሳ ስድስት ጥርስ የሚያደርጋችሁ፣ ግንባራችሁ መሬት የሚነካው… እንኳንም እነኛ እኔን ከልባቸው የሚወዱ አያቶቻችሁ አላዩ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንተ ጋ ሆነው ማየታቸው ይቀራል!
አንድዬ፡— አያዩም፣ እሱ የሚታይበትን ቻነል ጃም አድርጌዋለሁ፡፡ (ከት ብሎ ይስቃል፡፡) አሁንስ ደጋግሜ እናንተን ሳናግር፣ እናንተን ሆኜ ቁጭ ልል ነው፡፡ ይልቅ ዓለምን በወሬ ሳይሆን በሥራ ድረሱበት፡፡ ትናንትና ከእናንተ እኩል የነበሩት አገሮች የትና የት ደርሰዋል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እሱን ነገር ካነሳኸው አይቀር… ለምሳሌ ከሀምሳ ዓመት በፊት ከእነኮሪያ ጋር እኩል ነበርን ይባላል፡፡ አሁን እነሱ ያሉበትና እኛ ያለንበት ፍትሀዊ ነው? አንድዬ፣ እንደ ልጅና እንደ እንጀራ ልጅ ትለየናለህ!
አንድዬ፡— እነሱ እዚህ የደረሱት ሠርተው ነዋ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እኛም እኮ እንለፋለን፡፡
አንድዬ፡— እውነት! አሁንማ አንደኛችሁን ከማለዳ ጀምሮ መጠጥ ላይ ተቀምጣችሁ መዋል ጀምራችኋል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ችግራችንን ማስረሻ ነዋ አንድዬ፡፡ ስንስቅ ደልቶን መስሎህ ነው እንዴ!
አንድዬ፡— ደልቷችኋል እንጂ፣ በጣም ነው የደላችሁ፡ በቀደም ቁልቁል ሳይ በየቦታው ተሰልፋችኋል፡፡ አንዱን መልአኬን ጠራሁና እነኚህ ሰዎች እንዲህ የተሰለፉት አሁንም ስንዴና ጤፍ ላክልን ሊሉ ነው ወይ አልኩና አጣርቶ እንዲመጣ ላክሁት፡ መጥቶ የነገረኝ ነገር አሳዘነኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን አለህ አንድዬ?
አንድዬ፡— ለፍልሰታ ጾም ሊቀበሉ ሥጋ ለመግዛትና ለመብላት ተሰልፈው ነው አለኝ፡፡ እንደው ምን ባደርጋችሁ ይሻላል!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ምን አለበት ዞሮ፣ ዞሮ አንተን ለማስታወስ ስንዘጋጅ ነው፡፡
አንድዬ፡— ሥጋ በሰልፍ እየገዛችሁና እየበላችሁ ነው እኔን የምታስቡት…
ምስኪን ሀበሻ፡— እንምሰል ብለን ነዋ! ኪሳችን ሞልቶ መሰለህ! ይኸው ያኔ የተሰለፍነው እስከዛሬ ድረስ መሶባችንን የተለቀቀ ቤት አስመስሎታል፡፡ ከዚች ከዛች እያልን ነው እኮ ከወር ወር የምንደርሰው፡፡
አንድዬ፡— ከዚች ከዛች ማለት…
ምስኪን ሀበሻ፡— በቃ ከሥራ ማስኬጃዋም ከምኗም እየቆነጠጣርን…
አንድዬ፡— እየሰረቃችሁ…
ምስኪን ሀበሻ፡— መስረቅ አይደለም አንድዬ፡፡ እንደውም አንድ ነገር አስታወስከኝ፡፡ አንድዬ በቀደም የጀመርኩልህን የአሥርቱ ትዕዛዛት ነገር… አንድዬ፣ አትስረቅ የሚለው ህግ ሲወጣ እኮ ያኔ ካዝና ምናምን የሚባል ነገር አልነበረም፡፡
አንድዬ፡— እና…
ምስኪን ሀበሻ፡— እናማ መለወጥ አለበት፡፡ በቃ ሲቸግረን ከካዝናው ወጣ አድርገን እናሯርጠውና ቦታው እንመልሳለን፡፡ ማንም ኪስ አልገባን!
አንድዬ፡— ቢሆንስ…የእናንተ ያልሆነውን ነዋ የምትወስዱት፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ማንም ሳያውቅ እኮ ነው፡፡ ብሩ ዝም ብሎ ካዝና ከሚያሞቅ የእኛን ኑሮ ሞቅ ያድርግልን ብለን ነው፡፡
አንድዬ፡— ሞቅ ያድርግልን ነው ያልከው፡ አሁን ገና ሸጋ አማርኛ ተናገርክ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ደግሞ ምን አድርገንህ ነው ዝናቡን እንዲህ ያጠፋህብን?
አንድዬ፡— አሁንም ዝናብ ላይ ናችሁ? ስንቱ የዓለም ህዝብ በረሀውን አረንጓዴ እያደረገ ተትረፍርፎታል! እኔ ግን እናንተን ሁሉ ጊዜ እንደ አራስ እየፈተፈትኩ ማጉረስ አለብኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እኛም እኮ እንለፋለን፡
አንድዬ፡— በአፋችሁማ ትለፋላችሁ… በመፈክርማ ትለፋላችሁ… ያኛው ይውደም፣ ይሄኛው አፈር ይብላ በማለትማ ትለፋላችሁ…ምናለ ትንሽ ምላሳችሁን አሳርፋችሁ አእምሯችሁን ብታሠሩት!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ ቢሆንስ እንደገና ዝናብ ያጠፋህብን የዓለም መዘባበቻ ልታደርገን ነው! በስንቱ ነገር ከዓለም ምናምነኛ… ከአፍሪካ አንደኛ እያልን… ዓለም በስንቱ ነገር እያደነቀን ነው እያልን…ጤፍ የዓለም አንደኛ ሆነች ብለን እየፎከርን…እንደገና መዘባበቻ ልታደርገን ነው!
አንድዬ፡— መጀመሪያ ያላችሁትን ሁሉ ዓለም ሲያምናችሁ አይደል!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንዲህማ አትለንም፡፡ በቀደም ኦባማ እኮ እስክስታ ሞከሩ፡
አንድዬ፡— እና…
ምስኪን ሀበሻ፡— እናማ በዓለም ተቀባይነታችን ለመጨመሩ ማሳያ ነዋ፡
አንድዬ፡— (በሀዘኔታ ራሱን ወዘወዘ) ይሄን ያህል ራሳችሁን ዝቅ ታደርጋላችሁ ብዬ ጠርጥሬም አላውቅ፡፡ ሰውየው እስክስታ ስለወረደ ነው ተቀባይነታችሁ የጨመረው! በል፣ በል አንተን መስማቱ እኔኑ ወደእናንተ እየጎተተኝ ስለሆነ ይብቃን፡፡ ወይ እስክስታ ሞከረ ብሎ ነገር!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ምን መሰለህ…
አንድዬ፡— በቃ፣ በቃ…ሌላ ጊዜ፡፡ ደህና ክረም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አሜን አንድዬ፣ አሜን!  
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

“ልጃገረዶች አግብተው እስኪያልቁ ድረስ እንኖራለን”

   በጎፋ ብሄረሰብ መስቀል የበአላት ሁሉ አውራ ነው፡፡ ለ7 ተከታታይ ቀናት የሚያከብሩት ልዩ በዓላቸው ነው፡፡ አሁን የሥራ ጊዜን እንዳይሻማ በሚል ተቀንሶ ነው እንጂ ድሮ ለ15 ቀናት ነበር የመስቀል በዓል የሚከበረው፡፡
የዘንድሮ አከባበር ግን የተለየ ነው፡፡ ጐፋዎች የመስቀል በአልን ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ ተሰባስበው በተለያዩ ባህላዊ ስርአቶች በመናገሻቸው በሳውላ ከተማ እያከበሩ ይገኛሉ፡፡ “ማስቃላ ዮ!” (እንኳን ለመስቀል በአል አደረሰን) ሰሞነኛ የሠላምታና የመመራረቂያ ቋንቋቸው ነው፡
ብሄረሰቡ በአሉን መቼ ማክበር እንደጀመረ የሚጠቁም አረጋጋጭ ማስረጃዎች ባይኖሩም በአካባቢው ከ100 ዓመታት ቀደም ብሎ (ክርስትና ከመስፋፋቱ በፊት) ከአሁኑ አከባበር ጋር ተመሳሳይነት ባለው መልኩ በመስከረም ወር ይከናወን እንደነበር የሀገር ሽማግሌዎችና የመስቀል በአል አከባበርን ያጠኑ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ክርስትና ከመጣ በኋላ ይበልጥ የሀይማኖት ይዘቱንም የባህል ትውፊቱንም አስማምቶ ማክበር እንደተጀመረም ይገለፃል፡፡
ወርሃ መስከረም ወይም በብሄረሰቡ አጠራር ጉስታማ፤ የጭፈራና የደስታ ወር ነው - ለጎፋዎች፡፡ የእድሜ ባለፀጋዎች ልጆቻቸውን የሚመርቁበት፣ ወጣቶች እጮኛ የሚመርጡበት፣ በብሄረሰቡ ተወዳጅ የሆኑት “ግሶሌ”፣ “ሄራሶ”፣ “ጋዜ”፣ “ባራንቼ”፣ “ሆሴ” … የመሳሰሉት ባህላዊ ዜማዎች ጐልተውና ደምቀው የሚዜሙበት የፌሽታ ወቅት ነው - መስከረም፡፡
በአሉን ለመታደም ከአዲስ አበባ በ516 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ሳውላ ባቀናንበት ወቅትም እነዚህ የወርሃ መስከረም የደስታ ዜማዎች የበአሉ ማድመቂያ ሆነው ሰንብተዋል፡፡
ጎፋዎች የመስቀል በአልን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት የሚያደርጉት ከመስከረም 1 ጀምሮ ነው፡፡ ለተከታታይ 15 ቀናት እያንዳንዱ አባወራ የቤት እንስሳቱ እንዳይራቡበት ለ7 ተከታታይ ቀናት የሚበቃ መኖ ያዘጋጃል፡፡ ሴቶች ለበአሉ ባህላዊ ምግብና መጠጥ በማዘጋጀት ሥራ ይጠመዳሉ፡፡ የደመራው እለት እየተቃረበ ሲመጣም ወንዶች ለደመራ የሚሆነውን የተመረጠ “ግን ግና” የተባለ እንጨት መርጠው ያዘጋጃሉ፡፡ ህፃናት ልጆች ከብቶቻቸውን እያገዱ “መስቀል እንኳን መጣህልን፣ የኛ ደስታ፣ የኛ መዝናኛ መስቀል እንኳን መጣህልን፡
ሎያ ባይ ሎያ ባይ
ሎያ ባይ ማስቃላ ባይ
ማስቃላ ኡፋይስ ባይ
ሙሰ ሀሹ ባይ”… እያሉ በደስታ ያዜማሉ፡፡
አባወራዎች የደረሰ አዝመራ በደቦ ይሰበስባሉ፣ ያልደረሰውን ያርማሉ፣ ለእርድ የሚሆን በሬ ይገዛሉ፡፡ የመስከረም ወር ለጎፋዎች ሀብታም ከድሃ እኩል የሚሆኑበት ነው፡፡ “ጉስታ ጉስቴስ ጊታ ጊቴኤስ” ይባላል፤ ወሩ ላለው ይጨምራል፣ ለድሃውም ይሞላለታል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በዚህም ሁሉም ለበአሉ የሚያደርጉት ዝግጅት እኩልነትን መርህ ያደረገ ይሆናል፡፡
የጎፋዎች ደመራ
መስከረም 16 የደመራ ቀን ነው፡፡ ለደመራ የሚተከለው ለቤት መስሪያ የሚውል ረጅም ቀጥ ያለ እንጨት ነው፡፡ በደመራው ጫፍ አደይ አበባ ይታሰራል፤ ይህም ተስፋን አመላካች ነው፡፡ የችቦ አስተሳሰርና የደመራው አቆራረጥ፣ የቤተሰቡን ቁጥርና እድሜ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡ በረጅሙ ደመራ ዙሪያ የሚቀመጡት ጨፈቃዎች (ሶልዜ ይሉታል) በቤተሰቡ አባላት የእድሜ ደረጃ ቁመታቸው ተመጥኖ ይዘጋጃል፡፡ ረጅሙ ለአባወራው፣ ቀጥሎ ያሉት ከታላቅ እስከ ታናሽ ወንድ ልጆች እንዲይዙት ይደረጋል፡፡ የደመራ እንጨት በማስቀመጡ ስነስርአት ላይ ሴቶች ፈፅሞ አይሳተፉም፡፡ ሴቶች ከደመራው በኋላ የሚበላ ገንፎና የሚጠጣ ነገር ያሰናዳሉ፡፡
ወንዶቹ በእድሜ ደረጃቸው የያዙትን ጨፈቃ፣ በረጅሙ ምሰሶ ዙሪያ ለማስቀመጥ ሶስት ጊዜ “መስቀላ ዮ! ዮ! ዮ!…” እያሉ ይዞራሉ፡፡ ይህም ሁሉ ነገር የሚፀናው በ3 ነው ከሚል የብሄረሰቡ እምነት የመነጨ ነው ይላሉ አቶ በላይ፡፡ ሽማግሌ እንኳ ሲመረጥ ወይ ሶስት ወይ 5 አሊያም 7 ነው የሚሆነው፤ ምክንያቱም በውሳኔዎች የድምፅ ብልጫ እንዲፈጠር ነው፡፡
ለደመራው ረጅምና ዝንፍ ያላለ ቀጥ ያለ እንጨት የሚመረጥበት ምክንያትም ልጆች በአስተሳሰብና በአመለካከት ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ፣ ዘመኑ የሰላምና የስኬት እንዲሆን በመመኘት ነው፡፡ በመስቀል በአል በምንም አይነት መንገድ ጠማማ እንጨት ከደመራው ጋ አይቀላቀልም፡፡
ለዓይን ያዝ ሲያደርግ የቤቱ አባወራ (አባወራው በህይወት ከሌለ) የቤቱ ታላቅ ልጅ፣ ሁሉንም ችቦዎች ይዞ ለገንፎ ማብሰያ ከሚነደው እሳት ስር በመለኮስ፣ የቤቱን ምሰሶ በመዞር፣ የከብቶች ጋጣና በሩን በተለኮሰው እሳት እየነካካ፣ “መስቀላ ዩ! ዮ! ዮ!” እየተባለ ወደ ደጅ ይወጣል፡፡ አባት መጀመሪያ ችቦውን ከደመራው ካቀጣጠለ በኋላ ልጆች እንደየቅደም ተከተላቸው ባህላዊ ጨዋታዎችን እየተጫወቱ ችቧቸውን ያለኳኩሳሉ፡፡
በሚነደው ደመራ ዙሪያም “መስቀላ ዮ! ዳናው ዳና አልባ ዙማዳን ዳና” (መስቀል እንኳን መጣህልን … በአካባቢው እንደሚገኘው አልባ ዙማ ተራራ ገና ረጅም ዘመን እንኖራለን) “ከንቲ ሻላዳን ዳና” (በአካባቢው እንደሚገኘው ክንቲ ሻላዳ አለት ገና እንኖራለን) እያሉ ያዜማሉ፡፡ ዜማው በዚህ አያበቃም፤ “ሀረይ ካጨ ከሳናዳን፣ ገላኦ ገል ውራናስ ዳና” (አህያ ቀንድ እስኪያበቅል…. ልጃገረዶች አግብተው እስኪያልቁ ድረስ እንኖራለን) እያሉ እርስ በእርስ ይሸካከማሉ፡፡ ተቃቅፈው በመጨፈርም የእርስ በርስ ፍቅራቸውን ይገልፃሉ፡፡
በደመራ ሀዘን (ለቅሶ) የለም
የደመራ እለት የሞተ ሰው ካለ አይለቀስም፡፡ ከደመራ በኋላ የሀዘን ማስረሻ ጭፈራ እየተጨፈረ፣ ለቀስተኛው በራፍ ላይ ይዞራል፡፡ ከእንግዲህ ሀዘን የለም ይባላል፡፡ ሟች በመስቀል እሳት ተበልቷል (ማስቃላ ታማን ሜቴትስ) ይባላል፡፡ ለቀስተኞች ለቅሶውን አቁመው፣ “መስቀላ ዮ! ዮ” እያሉ ወደ ተጀመረው የመስቀል በአል ይመለሳሉ፡፡ ለበአሉ የተዘጋጀው ሰንጋም በ17 በዋናው በአል እለት ይታረዳል፡፡ ለ7 ቀናት ያህልም መከበሩን ይቀጥላል፡፡ (ድሮ ለ15 ቀናት ነበር የሚከበረው)
ሳምንቱን ሙሉም ስጋና በቅቤ የተዘጋጀ ገንፎ ብቻ እየተበላ፣ ቦርዴና ሌሎች መጠጦች እየተጠጡ ይሰነበታል፡፡ ከብቶችም የተዘጋጀላቸውን መኖ ይመገባሉ፡፡ አባወራዎች በበአሉ መዳረሻም ሆነ እስከ በአሉ ፍጻሜ ድረስ ከቀዬው መራቅ የለባቸውም፡፡
በመጨረሻም ደማቅ የመስቀል አሸኛኘት ስነ ስርአት “ሆሴ” እና “ጋዜ” በተባሉ ጭፈራዎች ደምቆ ይከናወናል፤ “ሰሮ ያራደሳ ሰሮ ረባ” (መስቀል በደህና መጥተህልናል በደህና ሂድ) ተብሎም ይመረቃል፡፡ “ሆሴ ማስቃላ ላይታን ሳሮያ!” (መስቀል ደህና ሁን! በዓመቱ ደህና ተመለስ) እየተባለ በአሉ ይሸኛል፡፡ ከዚያን ቀን በኋላ ስለመስቀል አይወራም፡፡
በአሉን ምክንያት አድርገው ከሚከናወኑ ተግባራት አንዱ ጎረምሶች የወደፊት ውሃ አጣጫቸውን የሚመርጡበት ሥነ ስርአት ነው፡፡ ልክ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ለጥምቀት በአል እንደሚደረገው መተጫጨቱ የሚፈፀመው በሎሚ ነው፡፡ በጭፈራ ወቅት ወንዱ የበሰለ ባለቢጫ ቀለም ሎሚ ልቡ ለከጀላት ልጃገረድ ይሰጣል፡፡ ሴቶችም መልስ የሚሰጡት በሎሚ ነው፡፡ ሶስት አይነት ሎሚ ያዘጋጃሉ፡፡ እንስቷ፤ የጠየቃትን ወንድ የማትፈልገው ከሆነ ያልበሰለውን ትሰጠዋለች፣ ልቧ ከጅሎት ትንሽ ጊዜ እንዲጠብቃት ከፈለገች እንደ መብሰል ያለውን ሎሚ ትሰጣለች፤ ሙሉ በሙሉ የምትፈልገው ከሆነ ደግሞ የበሰለውን ሎሚ ከጡቶቿ መሃል አውጥታ ትሰጠዋለች፡፡ የበሰለ ሎሚ ያገኘ ወንድ፣ ከዚያን ቀን ጀምሮ የሰርግ ዝግጅት ማድረግ ይጀምራል፡፡ ጥንዶቹ እንደ ምርጫቸው በጥቅምት ወይም በጥር ይጋባሉ፡፡
ጥቂት ስለጎፋዎች
የጎፋ ብሄረሰብ በደቡብ ክልል ከአዲስ አበባ 516 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በጋሞ ጎፋ ዞን በደንባ ጎፋ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙ 5 ነባር ብሄረሰቦች አንዱ መሆኑን በብሄረሰቡ ላይ የቀረቡ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ብሄረሰቡ ከሚኒልክ ዘመን ጀምሮ ከነባሩ የማዕከላዊ መንግስት አስተዳደር ጋር የነበረው ግንኙነት ጥብቅ እንደነበርም ይነገራል፡፡ በተለይ በአድዋ ጦርነት ጊዜ ጎፋዎች የፈፀሙት ጀግንነት በአፄ ምኒልክ ዘንድ ሞገስን አግኝቶ ነበር፡፡ የጣሊያንን ቅኝ ገዢ ኃይል አድዋ ላይ ለማስቆም በተደረገው የሞት ሽረት ተጋድሎ፣ ጎፋዎች ስንቅና የጦር መሳሪያ በማቀበል ለመላው ጥቁር ህዝብ ኩራት ለሆነው የአድዋ ድል ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡
ለዚህም ተጋድሏቸው መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በአዲስ አበባ በስማቸው ቦታ ተሰይሞላቸዋል፡፡ የጎፋ ሰፈር፡፡
ወደ ሻሸመኔ አካባቢ የሚገኘው የጎፋ በር እየተባለ የሚጠራ ስፍራም በጦርነቱ ወቅት የብሄረሰቡ ተወላጆች ሰፍረውባቸው የነበረ ሲሆን ስያሜውን ያገኙት በዳግማዊ ምኒልክ በጎፈቃድ እንደሆነ ታሪክ ይጠቁማል፡፡
ጎፋዎች ቀደምት አባቶቻቸው ቅኝ ገዢውን የጣሊያን ጦር በመስዋዕትነት ለመመከታቸው ማስታወሻ ይሆን ዘንድም በሚለብሱት ባህላዊ ልብስ ላይ (2020 ይሉታል) ባለቀይ ቀለም ጥለትን ይጠቀማሉ፡፡
ባህላዊ አልባሳቶቻቸው ሲዘጋጅም ምንም ይሁን ምን ቀይ ቀለም ከላይ ተደርጎ ነጭና አረንጓዴ እንዲከተሉት ይደረጋል፡፡ ነጩ ሠላምን፣ አረንጓዴው የብሄረሰቡን አምራችነትና የአካባቢውን አረንጓዴ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ እንደሚወክል የብሔረሰቡ ተወላጆች ይናገራሉ፡
“መስቀላ ዮ! መልካም የመስቀል በዓል!”
“አህያ ቀንድ እስኪያበቅል ድረስ እንኖራለን!”
“ልጃገረዶች አግብተው እስኪያልቁ ድረስ እንኖራለን!”

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 26 September 2015 09:02

Voilà!

    የዛሬ ጽሑፌን፤ ያለ ክፍያ ማስታወቂያ በመናገር እጀምራለሁ፡፡ ያቀረብኩትም ያፋልጉኝ ማስታወቂያ ነው፡፡ ይህን ማስታወቂያ ሳወጣ ክፍያ እንዳልተጠየቅኩ፤እንደ ሌሎች የአፋልጉኝ ማስታወቂያ አስነጋሪዎች፤ ‹‹……ለጠቆመኝ ወረታ ከፋይ ነኝ››  ማለት አልፈልግም፡፡ ማስታወቂያዬ፤ የ‹‹ታሪክ››ን ታሪክ የፃፈ ደራሲ የምታውቁ ሰዎች ካላችሁ፤ እባካችሁ ጠቁሙኝ የሚል ነው፡፡ መቼም እኔ ባይገጥመኝ እንጂ ‹‹ታሪክ›› የራሱን ታሪክ ሳይጽፍ ይቀራል ብዬ አላስብም፡፡ ካልፃፈ፤ ‹‹የራሷ አሮባት፤ የሰው ታማስላለች›› ብዬ አሽሟጥጠዋለሁ፡፡ አደራ ብያችኋላሁ፡፡ ጉዞ ወደ ደብረ ፍልስፍና፡፡
ዛሬ የታሪክን ታሪክ የማወቅ ፍላጎት ያሳደረችብኝ፤ ሃይፓትያ (Hypatia) ነች፡፡ ሃይፓትያ፤ ከ370 -415 የኖረች ግብፃዊት ፈላስፋ ነች፡፡ ሉካስ ሲዮርባነስ (Lucas Siorvanes) የተባለ ፀሐፊ፤ የሃይፓትያ የፍልስፍ መንደር፤ከኒዮ-ፕላቶኒስቶች ቀበሌ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ሃይፓትያ ህዝብ ከተሰበሰበበት አደባባይ በመቆም፤ በስነ-ፈለክ እና በፍልስፍና ላይ ያተኮረ ትምህርት በመስጠት ዝናን አትርፋለች፡፡ ከዚህ ሌላ፤ ወሲብን በተመለከተ ያላትን ሓሳብ ሳትሸማቀቅ በግልጽ በመናገርም ትታወቃለች፡፡
ሉካስ ሲዮርባነስ (Lucas Siorvanes) እንደሚለው፤ ፈላስፋ ወይም የሥነ ፈለክ እና የሒሳብ ሊቅ ብቻ አይደለችም፡፡ ሃይፓትያ፤ ‹‹ፖለቲካዊ እንስሳም ነች፡፡›› ሲዮርባነስ፤ በ‹‹Routledge Concise Encyclopedia of Philosophy›› እንደ ጻፈው፤ ሃይፓትያ በተግባር የተገለጠ ፖለቲካዊ ትሩፋት ያላት ሴት ነበረች፡፡ ገና በ45 ዓመቷ በጭካኔ ተገድላለች፡፡ ምናልባት፤የሞትዋ መንስዔ ከፖለቲካ ወይም ወሲብን ያለሽፍንን ከመናገር ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ፡፡ በአንድ ወቅት በተነሳ የክርስቲያኖች ‹‹እውር አመፅ›› (Mob) ለሞት እንደ ተዳረገች የሚገልፀው ሲዮርባነስ፤ ‹‹ሃይፓቲያ ስለ ፍልስፍና ሰማዕት የሆነች ሴት›› በሚል የምትታወስ መሆኗን ጠቅሷል፡፡
በታሪክ ፀሐፊዎች ብዙ ትኩረት ካላገኙ ሴት ፈላስፎች አንዷ ናት፡፡ ‹‹ለተወሰነ ጊዜ ታይተው ከጠፉ ሴት ፈላስፎች መካከል ከፍ ያለ ዝና ያላት›› በሚል ትጠቀሳለች፡፡ በዘመኗ ከነበሩ ኒዮ-ፕላቶኒክ ፈላስፎች ሁሉ ላቅ ያለች እና በእርሷ ጊዜ ከነበሩ የሒሳብ ሊቃውንት በግንባር ቀደምትነት ትነሳለች፡፡ ገና የ30 ዓመት ወጣት ሳለች፤ ከግብፅ ድንበር ተሻግሮ እስከ ሊቢያ እና ቱርክ ድረስ ዝናዋ የናኘ ጠቢብ ነበረች፡፡ ሃይፓቲያ፤ በግብፅ የእስክንድርያ ሙዚየም የሐሳብ እና ሥነ-ፈለክ ፕሮፌሰር የነበረው ቲዮን (Theon) የተባለ ምሁር ልጅ ስትሆን፤የአባቷን ብቃት የሚያስከነዳ ብሩህ አዕምሮን የታደለች በውበቷ ሁሉን የምታነሆልል ቆንጆ ሴት እንደ ነበረች ታሪክ ፀሐፊዎች ያወሳሉ፡፡ በአባቷ ዘንድ ጨርሶ የማይገኝ የትህትና ጠባይ እንደ ነበራትም ይገልፃሉ፡፡
በሃይፓቲያ ዘመነ መዋዕል፤ ግብፅ በሮማውያን ቁጥጥር ሥር ነበረች፡፡ የፈላስፋዋ ሃይፓቲያ ሞኖሪያ ከተማ የነበረችው እስክንድርያ፤ የዓለም የሥነ-ጽሑፍ እና የሳይንስ ማዕከል በመሆን የምታገለግል ከተማ ነበረች፡፡ የትላልቅ ውብ ቤተመንግስታት፣የቤተ መጻኅፍት እና የልዩ ልዩ ሙዚየሞች ባለቤት በመሆኗ ትኩራራ የነበረችው እስክንድርያ፤ በርካታ የፍልስፍና አስተምህሮትን ያቀነቅኑ የነበሩ ፈላስፎች፤ መናኸርያ በመሆንም ትታወቅ ነበር፡፡ በደንብ ያበበ ምሁራዊ ህይወት በነበረባት በዚህች ጥንታዊት ከተማ፤ የተለያየ እምነት እና አመለካከት የያዙ ሰዎች የሐሳብ ፍልሚያ ያደርጉ ነበር፡፡ ክርስቲያኖች፣ አይሁዶች እና ‹‹አረማውያን›› የሰላ የሐሳብ ጦርነት የሚያደርጉበት እና በዓይነተ-ብዙ የሐሳብ ብፌ የተዝበጠበጠ የጥበብ ገበታ የተዘረጋባት ውብ ከተማ ነበረች - እስክንድርያ፡፡
የሃይፓቲያ የእሳቤ አውራጃ ከፕላቶኒስቶች የሚያስመድብ በመሆኑ፤ በሐይማኖት ረገድ ሰልፏ ከአረማውያን ጎራ ነው፡፡ ምናልባት፤ በዘመናችን የአገላለፅ ዘይቤ፤የነፃ ሐሳብ አቀንቃኝ (freethinker) አሰር ተከታይ ትባል ይሆናል፡፡ በወቅቱ፤ ግብፅን የሚያስተዳድረው ክርስቲያናዊው የሮማ መንግስት ነበር፡፡ ስለዚህ፤ ያ ክርስቲያናዊ የሮማ መንግስት፤ አይሁዳዊ እና አረማዊ የሚባል እምነት ያላቸውን ሰዎች እያሳደደ ያድን - ይገድል ነበር፡፡ ሆኖም፤ የሮማ መንግስት ‹‹አረማዊ›› በሚል የሚፈርጃትን ሃይፓቲያን ባልተለመደ ትዕግስት አክብሮ ይዟት ነበር፡፡ ‹‹ፕሎቲነስ›› (Plotinus) እየተባለ በሚጠራ አንድ ባለ ዝና ትምህርት ቤት ውስጥ በርዕሰ መምህርነት መድቦ፤ ደመወዝ እየከፈለ አቀማጥሎ ይዟት ነበር፡፡
የሃይፓቲያ ዜና መዋዕል ፀሐፊው ኒሴፎር (Nicephore) እንደሚያስረዳው፤ የሮማ መንግስት ሃይፓቲያን አቀማጥሎ እና አክብሮ ሊይዛት የቻለው፤ በብዙ የጥበብ ዘርፎች የላቀ ብቃት የነበራት እና በእርሷ ዘመን ብቻ ሳይሆን ከእርሷ ቀድሞ በነበሩ ዘመናት ከሚያስተምሩ ሌሎች ፈላስፎች ሁሉ እጅግ የላቀ ብቃት የነበራት ፈላስፋ በመሆኗ ነበር፡፡
ሃይፓቲያ፤ በዘመኑ እጅግ ከፍተኛ ከበሬታን ያተረፈው የ‹‹ፕሎቲነስ›› ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ከመሆኗ ባሻገር፤ የረቀቀ የጂኦሜትሪ፣ የሒሳብ፣ የነገረ አፍላጦን፣ የነገረ አሪስጣጣሊስ፣ የሥነ - ፈለክ እና የመካኒክ ጥበባትን በማስተማር 15 ዓመታትን እንዳሳለፈች ታሪኳ ያስረዳል፡፡ ከእርሷ እግር ሥር ተቀምጠው ለመማር የሚሹ በርካታ ወንዶች እና ሴቶች ተማሪዎች ከሩቅ ሐገር ተጉዘው ወደ እስክንድርያ ይመጡ ነበር፡፡
ኒሴፎር (Nicephore) የተባለ አንድ የዜና የመዋዕል ፀሐፊ እንደ ገለጸው፤ ሃይፓቲያ ሥራዋን በእምነት እና በፍቅር፤ በሐቅ እና በላቀ ትኩረት የምትሰራ ሴት ስለነበረች፤ በብዙዎች ዘንድ ፍቅር እና ከበሬታን ለማትረፍ በቅታለች፡፡ የወንድ የበላይነት በሰፈነበት በዚያ ዘመን፤ መላ ህብረተሰቡ የሃይፓትያ አመራርን ተቀብሎ ለማደር መወሰኑ፤ በሥራዋ ከፍተኛ ብቃት የነበራት ሴት መሆኗን ያረጋግጣል፡፡
ሃይፓቲያ የአደባባይ ንግግር ስታደርግ ከሚያዳመጡ በርካታ ወንዶች መካከል፤ ብዙዎቹ ‹‹በፍቅር አበድኩልሽ›› ማለታቸው የተለመደ ነገር ሆኖ ሳለ፤ አንዱ ጎረምሳ ግን ‹‹እርሷን ካጣሁ ህይወቴን አጠፋለሁ›› ባይ ወጣት ሆነ፡፡ የዚህን ወጣት ነገር የሰማችው ሃይፓቲያ እጅጉን ተደነቀች፡፡ ለወጣቱ ‹‹Voilà!›› አለችው፡፡ ‹‹እየውልህ፤ ተመልከት!›› ማለቷ ነው፡፡ ሃይፓቲያ፤ የለበሰችውን ቀሚስ ቁልቁል ቀድዳ ውበቷን በማጋለጥ ‹‹ቮይላ! ወንድሜ፤ አንተ ያፈቀርከው ይሄንን ነው!›› አለችው፡፡እውነትም ቪዮላ! ሆኖም፤ ሃይፓቲያ አንድ ፈላስፋ የሆነ ባል አግብታ ነበር፡፡ ከዚህ ሌላ፤ አርቃዲየስ (Arcadius) የሚባል ንጉስ ወዳጁ አድርጓት ነበር፡፡
ሃይፓቲያ በምትሰጠው ትምህርት ብዙ የምታተኩረው በሎጂክ እና በሒሳብ ላይ ነው፡፡ ይሁንና፤ በጂኦሜትሪ እና በአርትሜቲክ ያተኮሩ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎችን ትደጉስ ነበር፡፡ እንዲሁም የ‹አስትሮላቤ› (astrolabe) አሰራር ዘዴን የሚያስረዳ ጥናታዊ ፅሑፍም ነበራት፡፡ ‹‹አስትሮላቤ›› የፕላኔቶችን አውዳዊ ዑደት እና የፀሐይን እንቅስቃሴ ለማስላት የሚያገለግል መሣሪያ ነው፡፡ ሆኖም፤ ከሃይፓቲያ ሥራዎች ውስጥ ከጥፋት ተጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻገረ አንድም የፅሑፍ ሥራ አለመገኘቱ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ስለ እርሷ ሥራዎች ለማወቅ የቻልነው፤ የተለያዩ ሊቃውንት ይለዋወጧቸው በነበሩ ደብዳቤዎች ውስጥ አንዳንድ ሥራዎቿ ተጠቅሰው በመገኘታቸው ነው፡፡ራሳችን የሃይፓቲያን ሥራዎች አንብበን ለመፍረድ ባንታደልም፤ከተለያዩ የዜና መዋዕል ፀሐፊዎች ገለፃ የሚያኮራ ድንቅ ሥራ መስራቷን መረዳት እንችላለን፡፡ ከእነዚህ የዜና መዋዕል ፀሐፊዎች አንዱ፤‹‹የሃይፓቲያ ሥራዎች ሰማይ የነኩ ናቸው›› ሲል ጽፏል፡፡ አክሎም፤‹‹ሃይፓቲያ ለጣዕመ-ንግግር አብነት የሚሆን የንግግር ችሎታ የነበራት እና በጥበብ ሰማያት ደምቃ የምታበራ ወደር-የለሽ ኮከብ ነበረች›› በማለት ጽፏል፡፡ ለሞት የዳረጋትም ይኸው ብቃቷ ነበር፡፡በዘመኑ የእስክንድርያ ጳጳስ በመሆን ያገለግሉ የነበሩት ቅዱስ ሲሪል (Saint Cyril) የተባሉ ሰው ነበሩ፡፡ ጳጳሱ የሃይፓቲያ ሥራ የሚያስደስታቸው ሰው አልነበሩም፡፡ እርሳቸው ባይወዷትም፤ ሐገር ምድሩ ሲያወድሳት ይሰማሉ፡፡ እናም ክፉ ሐሳብ አደረባቸው፡፡ ጳጳሱ፤ ሃይፓቲያ ትገደል ዘንድ፤ አክራሪ ክርስቲያናዊ ህብረት (Sect) ለመሠረቱት የኒትሪያን (Nitrian) መነኮሳት ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡
ከጳጳሱ ትዕዛዝ የተቀበሉት መነኮሳት፤ ሃይፓቲያን በሰረገላ ስትጓዝ አገኝዋት፡፡ ከሰረገላዋ ጎትተው በማውረድ በዚያው በአቅራቢያ ከሚገኝ ቤተክርስቲያን ወሰዷት፡፡ ዓይኗ እያየ በመጋዝ ሰነጠቋት፡፡ እንኳን የፍልስፍና ሐሳቧ፤ የአጥንቷ ፍላጭ እንዳይገኝ አድርገው በእሳት አቃጠሏት፡፡ በምድር መታወሻ የሚሆን ነገር ያጣችው ይህች ድንቅ ፈላስፋ፤ ብዙ ፈላስፎች ያላገኙትን አንድ ክብር አግኝታለች፡፡ ለአርባ አምስት ዓመታት በተመላለሰችባት እና ባስተማረችባት በዚህ በእኛዋ ምድር ለስሟ ማረፊያ የሚሆን መካነ መቃብር ያጣችው ውቢቷ ፈላስፋ፤ በጨረቃ ከሚገኙ ዋሻዎች አንዱ፤ በእርሷ ስም እንዲጠራ ተደርጓል፡፡
ውቢቷን ፈላስፋ ያስገደሉት ጳጳስ፤ ታሪክ የሚጠቅስባቸው ሌላ የግፍ ተግባርም አላቸው፡፡ የእስክንድርያ ጳጳስ ሲሪል (Cyril)፤በጥንታዊቷ የእስክንድርያ ከተማ ይኖሩ የነበሩ በርካታ አይሁዶችን በማስጨፍጨፍ ስማቸው ይነሳል፡፡ በተቃራኒ፤ እንዲህ ያለ የጭካኔ ተግባር የፈጸሙት ጳጳስ፤ በእስክንድርያ እጅግ የተከበረ የሥነ መለኮት ሊቅ ከመሆን የገታቸው ነገር አልነበረም፡፡
ዛሬ፤ የሃይፓቲያን ህይወት የሚዘክሩ የተለያዩ ሥራዎች በገበያ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም፤በሃይፓቲያን ህይወት ዙሪያ በ19 እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከተጻፉት መፃህፍት የሚበዙት ልቦለዳዊ ናቸው፡፡ ከእነኝህ የጥበብ ሥራዎች መካከል፤የህይወት ጉዞዋን እና የማስተማር ተግባሯን መሳጭ በሆነ መልክ ለመግለጽ የሞከረው ኧልበርት ሑባርድ (Elbert Hubbard) የተባለ ደራሲ ነው፡፡ ሑባርድ፤ በ1908 ዓ.ም ባሳተመውና ‹‹Little Journeys to the Homes of Great Teachers›› የሚል ርዕስ በሰጠው የድርሰት ሥራው፤ በሃይፓቲያን ህይወት ዙሪያ ያለውን የታሪክ ማስረጃ እጦት በምናብ ጸጋ አሟልቶ ድንቅ የሚባል ሥራ ሰርቷል፡፡
አንዳንድ ሰዎች፤ እውነተኛ የሃይፓቲያ ንግግር አድርገው የሚጠቅሷቸውን የተለያዩ አባባሎችን ከምናቡ አንቅቶ ፅፏል፡፡ የአንባቢን ምናብ ለማገዝ የስዕል መግለጫ ጨምሮበታል፡፡ ለባለታሪኳ እውነተኛ ባህርይ ተስማሚ የሆነ እና ጥንታዊ ገፅታን የሚያንፀባርቅ ሥዕልን አስሏል፡፡
ኧልቨርት ሑባርድ በምናብ ተደግፎ የተረከው የሃይፓቲያን ህይወት፤ ለህፃናት ታስቦ ተዘጋጀ ድርሰት ነበር፡፡ ይሁንና፤ዛሬ አዋቂዎች የሚያነቡት እና የዘመናችን ምሁራንም በጥናት ሥራዎቻቸው የሚጠቀስት ተረክ ሆኗል፡፡ ታሪክ እና ተረት መለያየት እየተቸገሩ በጣም መቀላቀል ይዘዋል፡፡ ይህም የታሪክን ነገር ደጋግመን ለማሰብ ያነሳሳናል፡፡ አሁን፤ ከመነሻ ያቀረብኩት ማስታወቂያ እና የገጠመኝ ችግር ምን እንደሆነ ትረዱኝ ይሆናል ብዬ ተስፋ አድርጊያለሁ፡፡ እግረ መንገዴንም፤ ከታሪክ ዘገባ ጋር የተያያዙ አንድ - ሁለት አሳሳቢ ነገሮችን ጠቀስ አድርጌ ጽሁፌን አሳርጋለሁ፡፡
የሃይፓቲያ ታሪክን የተመለከተ ሰው፤ በታሪክ አፃፃፍ ሂደት በተደጋጋሚ የሚስተዋል አንድ ችግርን በደንብ ይገነዘባል፡፡ በሃይፓቲያ ታሪክ እንደሚታየው፤ የብዙዎቹ ጥንታዊ ፈላስፎች አስተምህሮት፤ በአድማጮች አዕምሮ ወይም ትውስታ ተመዝግበው በቃል ቅብብሎሽ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገሩ ናቸው፡፡ ይህ ብዙ ችግር ይጎትታል፡፡ ጥቂቶቹ በዚያው በወቅቱ ተጽፈው ይሆናል፡፡
ግን የሚፃፉት በወረቀት አልነበረም፡፡ በጥንቱ ዘመን ፓፒረስ እንጂ ወረቀት አልነበረም፡፡ ፓፒረስ ደግሞ እርጥበት ሲያገኘው በቀላሉ ሊበላሽ ወይም ሊፈረካከስ የሚችል ነው፡፡ በዚህ የተነሳ፤ በወቅቱ በፅሁፍ መስፈር የቻሉት የጥንት ዘመን የፍልስፍና ሥራዎች፤ በአብዛኛው የቅጂ ቅጂ ቅጂ ይሆናሉ፡፡ የሚቀዳው መጽሐፍ ደጓሽ፤ ምንም ያህል ጠንቃቃ ሰው ቢሆን፤የሆኑ ስህተቶች ማምለጣቸው አይቀርም፡፡ በተጨማሪም፤ አብዛኞቹ የፍልስፍና ሥራዎች ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ ቋንቋ በትርጉም እየተቀዱ፤ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፉ የመጡ ናቸው፡፡
 በግሪክ ቋንቋ የተጻፈ አንድ የፍልስፍና ሥራ መጀመሪያ ወደ አረብኛ ተተርጉሞ ይሆናል፡፡ ከአረብኛ ደግሞ ወደላቲን ይመለሳል፡፡ ከላቲን እንደገናወደ ግሪክ ቋንቋ ተመልሶ ይቀዳል፡፡ ዛሬ በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉመው የምናነባቸው ሥራዎች እንዲህ ያለ ጠመዝማዛ መንገዶችን አቋርጠው ከኛ የደረሱ ናቸው፡፡ታዲያ፤ በዚህ ሁሉ ሂደት ስንት ነገር ተዛብቶ ይሆን? ብዙ የግሪክ ሊቃውንት ሥራዎች ከኛ የደረሱት፤ ቅጅአቸው በአረብኛ ቋንቋ ተገኝቶመሆኑ የሚዘነጋ አይደለም፡፡የወረቀት እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ በዚህ ረገድ ያለውን ችግር አስወግደውት ይሆን? አይመስለኝም፡

Published in ህብረተሰብ
Page 2 of 16