Saturday, 13 September 2014 13:42

አገኘሁ አዳነ - ጣምራ ጠቢብ

         ተወልዶ ያደገው ጎንደር ነው፡፡ በአባቱ የሥራ ጸባይ ምክንት በልጅነቱ አሥመራን፣ አቆርዳትን፣ ተሰኔን ጨምሮ ወደተለያዩ አካባቢዎች ተጉዟል፡፡ እናቱ በልጅ አስተዳደግ በጣም ጥብቅ በመሆናቸው ከቤት እንዲወጣ የሚፈቀድለት ወይ ወደ ትምህርት ቤት፣ ወይ ወደ ቤተክርስቲያን ብቻ ነበር፡፡ ያንን ዘመን ሲያስታውስ በኪነ ቅብ ሥራዎች ያሸበረቀችውን ሎዛ ማርያም ቤተክርስቲያንን ያነሳል፡፡ ዓይኑም ልቡም፣ ቀልቡም በሥዕል ሕብረ ቀለም የተወጋው ያኔ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከዚያ ሕፃናት አምባ ገባ፡፡ አምባ የፈለግከውን ለመሆን ነገሮች የተመቻቹበት፣ ነፃነት ያለበት አካባቢ እንደነበር ይናገራል፡፡ አጥር ተበጅቶለት ላደገው አገኘሁ ሕፃናት አምባ የተመቸ ሥፍራ ሆነለት፡፡ አንድ ቦታ ላይ በትኩረት መቆየትን፣ ማንበብን፣ ማስተዋልን ቀድሞ ስለሚያውቃቸው በመጣበት መንገድ ቀጠለ፡፡ ለዛሬ ማንነቱ ያ ዘመን እርሾ እንደሆነውም አይጠራጠርም፡፡
ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አንስቶ ሥዕልን ይሞክር ነበር፡፡ ዕድለኛም ስለነበር ከልጅነቱ ምርጥ ምርጥ የሚባሉ መምህራን ገጥመውታል፡፡
አገኘሁ ከልጅነቱ ጀምሮ ጠያቂ ባህሪይ እንደነበረው ያስታውሳል፡፡ አራተኛ ክፍል እያለ የሥዕል መምህሩ በውሃ ቀለም ይሥላል፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ አገኘሁ ያየውን ማመን አልቻለም፡፡ እጅጉን ተደነቀ፡፡
“የሚገርም ዓይነት፣ ዓይኑ እሳት የሚተፉ ጥቁር ሰውዬ ሳለ፡፡ ‘እንዴት ውሃ ሰው ይሆናል?’ ‘እንዴት ከሰው ዓይን እንደዚህ ዓይነት ኃይል የበዛበት ብርሃን ይረጫል?’ ስል በመደነቅ የጠየኩትን መቼም አልረሳውም፡፡”
የአገኘሁ ውስጣዊ ፍላጎት፣ ተሰጥዖውና ችሎታው እንዳለ ሆኖ ህፃናት አምባ ያንን የሚያለመልም ውሃ፣ አፈር እና ብርሃን እንደሆነው ይጠቅሳል፡፡ አገኘሁ ራሱን ወደ መንፈሳዊ ሰው አስጠግቶ ያስባል፡፡ ከአራት ማዕዘን ግድግዳ ውጪ ያለን ነገር የሚናፍቅ፣ በገሃድ የሚታይ፣ የሚጨበጠው የሚሰለቸው ዓይነት ሰውም ይመስላል፡፡
ሠዓሊነቱን ሳይቀር ወደዚ ቢወስደው ይወዳል፡፡ “ከሚዳሰስ እውነት ነገረ-ተረትን፤ ከዕለት ዜና ተረትን ልወድ እችላለሁ፡፡ ያለቀና የሚያልቅ ነገር ይሰለቸኛል፡፡ አገኘሁ ሠዓሊ ብቻ አይደለም፡፡ ገጣሚም ነው፡፡ “ጨለማን ሰበራ” እና “ለምን?” የተሰኙ ሁለት መድበሎች አሳትሟል፡፡ በባህርይው ማዳመጥ ደስ እንደሚለው የሚናገረው አገኘሁ አለማዊ ሰው ባይሆንም ይመስላል፡፡
“ሰውን ብደግፍ፤ ክርስቶሳዊ ስብዕና ቢሮረኝ እወዳለሁ፡፡ ማለም፣ ከሃሳብ ጋር መጫወት ደስ ይለኛል፡፡” ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ ስፔይንን፣ ሆላንድን፣ ፈረንሳይን፣ ጀርመንን ፖርቹጋልን እና ቤልጂየምን ገብኝቷል፡፡ በነበረው ቆይታም ብዙ ነገሮችን ስለመማሩ ይናገራል፡፡
“በራሴ ፍጹምነት ታስሬ እንደነበር ተገንዝቤአለሁ፡፡ ለምለሚቷ ሀገሬ የሚለውን ሳይቀር ቀንሼአለሁ፡፡ ምክንያቱም በሌላው ሀገር ሃሪፍ ነገር ስላለ፡፡” ሠዓሊ አገኘሁ ባለትዳር እና የሦስት ልጆች አባት ነው፡፡ ቤተሰቦቹ ለሁለመናው ብርታቱ እንደሆኑም ይጠቅሳል፡፡
አገኘሁ ከልጅነቱ መምህርነትን ይመኝ ነበር፡፡ እንደፈለገው ግን ፈጥኖ አላገኘውም፡፡ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ሲሰራ ቆይቶ ቢዘገይም ከመምህርነት ጋር ተገናኝቷል፡፡ ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ ፈለገ ሰላም የሥነ-ጥበብ እና ዲዛይን ት/ቤት መምህር ነው፡፡ ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ ወደፊት ወደ መፈውሰ ጥበብ ወይም ‘Art Therapy’፣ ‘Physical Therapy’፣ ‘Spritual Therapy’ ቢገባ ደስ እንደሚለው፣ ሥዕሉንም ቢሆን ከሰው ልጅ ጋር በቀጥታ እንዲገናኝ ማድረግ ቢችል ደስ ይለዋል፡፡
ምንጭ፡- ነቢይ ግርማ፣ “ጋለሪያ ቶሞካ አገኘሁ አዳነን ያቀርባል” (2007 ዓ.ም) በሚለው መጽሄት ላይ ያሰፈረው፡፡

Published in ጥበብ

  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት፤ “ፊውቸር ሜሞሪስ” በሚል ርዕስ ከመስከረም 6 እስከ 8 2007 ዓ.ም ዓለም አቀፍ ጉባኤ እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አሻግሬ ጉባኤውን ከጀርመኑ “ifa-institute for International Cultural Relation” ጋር በመተባበር ማዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፣ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገላቸው ደግሞ የጀርመን ፌደራል የውጭ ጉዳይ ጽ/ቤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሦስት ቀኑ ጉባኤ፣ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በሥነ-ጥበብ ላይ የሚሰሩ 23 የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የሥነ-ጥበብ ለባህላዊ ትውስታና ለእድገት በሚያበረክተው አስተዋፅኦና በወደፊት የከተሞች ገጽታ ላይ በሚኖረው እውነታ ላይ እንደሚወያዩ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ከውጭ አገራት የሚመጡትና የአገር ውስጥ የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎች እንዲሁም፣ ጉዳዩ ያገባናል የሚሉ የህዝብ ተቋማት፣ “በተለያዩ የሥነ-ጥበብ ውበቶች ወይም ባህላዊ መለያዎች (ቅርፆች) ላይ በምን ነጥቦች ነው መወያየትና መደራደር የሚቻለው? የሥነ-ጥበብ ልምዶች አዲስ ቅርፅ፣ ህዝባዊ ባህል ወይም የወደፊት ትውስታ መፍጠር ይችላሉ? ከቻሉስ እንዴት?” በሚሉና ከተለያዩ አመለላከቶች በሚነሱ ነጥቦች ላይ ይወያያሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ፈጣን የአቀማመጥ ለውጥ፣ ከሥነ-ሕንፃ፣ ከማኅበራዊና ከከተማ ለውጥ አንፃር እንዴት ይታያል? ለሚሉ የሥነ-ጥበብ መሰረታዊ ቅሬታዎች (ያለመግባባቶች) ምላሽ እንደሚሰጡም ይጠበቃል፡፡
ጉባኤተኞቹ በመዲናዋ ውስጥ ያሉ የሥነ-ጥበብ ሥፍራዎችን እንደሚጎበኙ፣ተለያዩ ምሁራን ንግግር እንደሚያደርጉና፣የሥነ-ጥበብ፣የቅርስና የሙዚየም ባለሙያዎች ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚያቀርቡም ለማወቅ ተችሏል፡፡

እናት ማስታወቂያ እና አጋ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ከጀርመን የባህል ማእከል፣ ከሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያና ከካፒታል ሆቴልና ስፓ ጋር በመተባበር “የክረምት ፊደላት” የተሰኘ የኪነ-ጥበብ ዝግጅት ለ3ኛ ጊዜ ባለፈው ማክሰኞ ማቅረባቸው ተገለፀ፡፡
በካፒታል ሆቴልና ስፓ በተካሄደው የኪነ-ጥበብ ምሽት ፕሮግራም ላይ ገጣሚ ሰለሞን ሳህለ፣ ምህረት ከበደ፣ ይታገሱ ጌትነት፣ ዮሐንስ ኃ/ማርያም፣ መስፍን ወ/ትንሳይ እና ፍሬዘር አድማሱ የግጥም ስራቸውን አቅርበዋል፡፡
ገጣምያኑ በጋራ በመሆንም ከነባሩ የቡሄና እና የአበባየሆሽ ጨዋታ ስንኞችን በመምዘዝ ለየት ያሉ የፈጠራ ግጥሞችን በቅብብሎሽ አቅርበዋል፡፡
“የክረምት ፊደላት” የኪነ-ጥበብ ዝግጅት በየአመቱ በክረምት ወቅት የሚካሄድ ሲሆን የሰሞኑ ለ3ኛ ጊዜ የተዘጋጀ መሆኑን የጠቆሙት የፕሮግራሙ አዘጋጆች፤ ከዚህም በተጨማሪ “የበጋ ፊደላት”፣ “የፀደይ ፊደላት”፣ እና “የመኸር ፊደላት” በሚል ስያሜ ወቅቱን ጠብቀው የጥበብ ዝግጅቶችን እንደሚያሰናዱ አስታውቀዋል፡፡

    ትላንት ምሽት በጋለሪያ ቶሞካ የተከፈተው የሰዓሊ አገኘሁ አዳነ “ቃልና ምስል” የተሰኘ የሥዕል ትርኢት ለሁለት ወር ለተመልካች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ተገለፀ፡፡ በቶሞካ ቤተ ሥዕል ማሳያ የቀረበው “ቃልና ምስል”፤ በድብልቅ ቁስ ጥበባት የተሰሩ የኪነ - ህትመትና የኪነ ቅብ ሥራዎች እንደሆኑ ትርኢቱን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው አነስተኛ መጽሔት ይጠቁማል፡፡
በመጽሔቱ ላይ “ቃልና ምስል፤ ምስልና ቃል” በሚል ስለ ሰዓሊው ስራዎች ማብራሪያ የፃፈው ሰዓሊ ጥሩነህ እሸቱ፤ “ለሰዓሊና ገጣሚ አገኘሁ አዳነ ሥነግጥማዊ ቃልና ሥዕላዊ ምስል ‹ነፍስና አካል፤ ቃልና ሥጋ› ናቸው፤ አይለያዩም፤ አይነጣጠሉም” ብሏል - ጣምራ ጠቢብነቱን ሲገልፅ፡፡
ሰዓሊው የስዕል ትርኢት በግሉ ሲያቀርብ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አንዱን በስፔን ማቅረቡ ተፀቁሟል፡፡ ሰዓሊ አገኘሁ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ ፈለገ ሰላም የሥነ ጥበብ እና ዲዛይን ት/ቤት መምህር ሲሆን፣ “ጨለማ ሲበራ” እና “ለምን?” የተሰኙ የግጥም መጻሕፍት ማሳተሙ ይታወሳል፡፡

በደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ በተፃፈው “የብርሃን ፈለጎች” የተሰኘ ረዥም ልብወለድ መፅሃፍ ላይ ነገ ከ8 ሰዓት ጀምሮ ውይይት እንደሚካሄድ ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ አስታወቀ፡፡
ለውይይቱ መነሻ የሚሆን ሃሳብ የሚያቀርቡት ሃያሲ አብደላ እዝራ እንደሆኑ ታውቋል፡፡
የውይይቱ ሥፍራ የኢትዮጵያ ቤተመዘክርና ቤተመፃህፍት አዳራሽ ሲሆን የሥነፅሁፍ ቤተሰቦች በሙሉ በዝግጅቱ እንዲሳተፉ ሚዩዚክ ሜይዴይ ጥሪ አቅርቧል፡፡

 

Saturday, 13 September 2014 13:36

የእኔና የአደይ ነገር

         የካቻምናውን የክረምት ወራት ያሳለፍኩት ለመጀመሪያ ጊዜ ከገጠር መንደራችን ርቄ በመውጣት ነበር፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በዘመድ ዘመድ በተገኘልኝ ቤት ውስጥ በሰራተኝነት ተቀጥሬ ለሶስት ወራት ያህል ቆየሁ፡፡ የቀጣሪዎቼ መኖሪያ ወደ ፈረንሳይ ኤምባሲ አካባቢ ነበር፡፡ ሁሉም ያሰሪዎቼ ቤተሰብ አባላት በመልካም ባህርይ የታነጹ ሲሆኑ በእኔ ዕድሜ ያለች አንዲት ወጣት ሴት ልጅ ነበረቻቸው፤ አደይአበባ ትባላለች፡፡
አደይ የኮሌጅ መግቢያ ፈተና በግንቦት ወር በመውሰዷ፣ የክረምቱ ወቅት ሙሉ በሙሉ የእረፍትና የመዝናኛ ጊዜዋ ነበር፡፡ እዚያው ቤት ውስጥ ፊልም በማየት፣ ታላቅ ወንድሟ የሚያመጣላትን የተለያዩ መጽሐፍት በማንበብና የወላጆቿ ምርጫ የሆኑ ምግቦችን በእኔ ረዳትነት በማዘጋጀት ጊዜዋን ታሳልፋለች፡፡ እንደ እረፍት ማሳለፊያ የያዘችው ግብሯ፤ ከመደበኛ ስራ ባላነሰ ወጥሮ ይዟት ስመለከት ይገርመኝ ነበር፡፡ እጅግ ለስላሳ ፀባይ የታደለች፣ ቁመናና መልኳ በጣም የሚያምር፣ ቤተሰቦቿንና በአጠቃላይ ሰው የተባለ ፍጡር የምትወድ፣ በግብረገብ ያደገች ሸግዬ ነበረች፡፡ በእኔና በእሷ መካከል የነበረውን ያስተዳደግ፣ ያኗኗርና፣ የአስተሳሰብ ልዩነት የሚያትት ትልቅ ድርሳን ማዘጋጀት የምችል ይመስለኛል፡፡
ከከተማ ኑሮ ጋር በትረካ እና በተግባር ያስተዋወቀችኝ፣ ያልተገራ አንዳንድ ልማዴን አለዝባ እንዳዲስ የቀረፀችኝ፣ ስለራሴና ስለሰው ልጅ የነበረኝን ያልጠራ እይታ ያረመችልኝ፣ የዕድሜ ዘመን መምህርቴ የእኔዋ እኩያ አደይ ነበረች፡፡ ሴት እንደመሆኔ የግል ንጽህና አጠባበቄን እየተከታተለች፣ ወጣት እንደመሆኔ የስሜት ለውጤን እየታገሰች፣ ባላገር እንደመሆኔ ምስጢረኛነቴን እየሸረሸረች፣ እንደ ዱር እንስሳ አላምዳና ገርታ እሰው መሃል የለቀቀችኝ አደይ ነበረች፡፡ ከምትወዳቸው መጽሐፍ መካከል ቆንጥራ ታነብልኝ ነበር፡፡ የሚያስቋትን የፊልም ትዕይንቶች እንባዋ እስኪፈስ እየተንከተከተች ትተርክልኝ ነበር፡፡ ከእኩዮቿ የትምህርት ቤት እና የሰፈር ወንድ ልጆች የሚደርሷትን የፍቅር ተማጽኖ ያዘሉ ደብዳቤዎች በግልጽ ታነብልኛለች፡፡ የእኔንም ልምድ ትጠይቀኛለች፡፡ ኮሌጅ ስትገባ ለመማር ስላቀደችው ትምህርት እና የወደፊት ዕቅዷ በሰፊው ታወራኛለች፡፡ ከእርሷ ጋር ቁጭ ብዬ ወሬዋን ለመስማት እንኳን ይከብደኝ የነበርኩ እኔ፣ በጥቂት ሳምንታት እጄን አንስቼ ከእርሷ ጋር እስከመላፋት ባደረሰኝ አስማተኛ የለውጥ ዋሻ ውስጥ መራችኝ፡፡ በውስጤ በራስ መተማመንን ገነባችልኝ፡፡
የህይወት ታሪኬን አንድም ሳይቀር አውርቼላታለሁ፡፡ የቤተሰቦቼን አኗኗር፣ የግብርና ህይወትን ገጽታ፣ የአካባቢያችንን ባህልና ልማድ፣ የአገራችንን መልክአምድር፣ የቀዬአችንን የሰርግና የልቅሶ ስነ - ስርዓት ሁሉ ፈልፍላ እየጠየቀችኝ በገባኝ መጠን ተርኬላታለሁ፡፡
በዚህ መልኩ ለሶስት ወራት ያህል አብረን እንደቆየን ነበር ከቤተሰቦቼ ዘንድ “ነይ” የሚል መልዕክት የደረሰኝ፡፡ የምፈልገውን ያህል ገንዘብ አጠራቅሜአለሁ፣ የሚበቃኝን ያህል የአዲስ አበባ ህይወት ቃኝቼአለሁ፡፡ የሚጠቅመኝን ያህል ገንዘብ አጠራቅሜአለሁ፣ የሚበቃኝን ያህል የአዲስ አበባ ህይወት ቃኝቼአለሁ፣ የሚጠቅመኝን ያህል የከተማ ልምድ አግኝቼአለሁ፣ ለሰራሁበት ቤተሰብ በግልጽ አልተናገርኩም እንጂ ቀድሞም የመጣሁት ለእኒሁ ወራት ያህል ነበር፡፡ በቋሚነት ሰራተኛ ለሚፈልጉት ቤተሰቦች፣ ከመነሻው ይህንኑ ሀቅ መናገር የስራውን ዕድል የሚያሳጣኝ ስለመሰለኝ ትንፍሽም አላልኩም ነበር፡፡ ላገለግላቸው ቤታቸው ገብቼ፣ በብዙ መልኩ ህይወቴን ያሻሻሉልኝን እኒህን ቅን የቤተሰብ አባላት ለወራት አታልዬ መኖሬ እንደ ዕዳ የቆረቆረኝ መሄጃዬ የደረሰ ሰሞን ነበር፡፡ ከቶም ውሸት በማይወራበት ቤት ውስጥ፣ መልካምነታቸውን ቀደም ብዬ ተረድቼ እንኳ፣ እውነቱን በውስጤ ደብቄ መቆየቴ በእርግጥ አሻሽያለሁ ያልኩት ጠባዬ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርብኝ አደረገኝ፡፡ ጥርጣሬዬን የቀረፈልኝ ግን አሁንም ቢሆን ከጉዞዬ በፊት እቅጩን ለመንገር መወሰኔ ነበር፡፡
“ይቅርታ አድርጉልኝ፤ እኔ ተማሪ ነኝ፤ በክረምቷ ትንሽ ሰራርቼ ቤተሰቦቼን ለማገዝ ነበር ወደከተማ የመጣሁት፡፡ ቀድሞ ያልተናገርኩት ስራውን ላለማጣት ነበር፡፡ ዘግይቼ ደሞ በጐ ጠባያችሁ ውሸቴን አጋኖብኝ ክፉኛ ፈራሁ፡፡ አሁን ግን ጊዜው ደረሰ፡፡ ይቅርታ አድርጋችሁ ሸኙኝ፤ ከናንተ ስለይ የምጐዳው እኔው ነኝ፡፡” ብዬ ሁሉም ለእራት በተሰበሰበበት አንድ ምሽት ተነፈስኩ፡፡
“ዋናው ተማሪ መሆንሽ ነው፤ በርቺ ብቻ አንቺ እኛ ሰው አናጣም፡፡” ብለው አበረታተው፣ ከሰራሁበት በላይ ገንዘብ ሰጥተው፣ በቅንነታቸው ቀጥተው፣ መናኸሪያ ድረስ ሸኝተው አሰናበቱኝ፡፡
ከአደይ ጋር ተቃቅፈን ተላቀስን፡፡
የዘነጥኩት በእሷ ልብስና ጫማ፣ የደመቅሁት በእሷ ጌጣጌጥ፣ የተቀባሁት የእሷን ቅባትና ሎሽን ነበር፡፡ በመንገዴ ላይ ሳለሁ ከሁሉ በላይ የከነከነኝ የአደይ ነገር ነበር፡፡ በእዚያ ሰላም እና ምቾት የተከበበች ፍልቅልቅ ወጣት፣ ከማንም ደብቃ ለእኔ ብቻ ያወራችኝ የህይወት ዘመኗ አሳዛኝ ምስጢር ለዘላለም በውስጤ ተዳፍኖ እንደሚቀር አውቃለሁ፡፡ ከእዚያ ባልተናነሰ ነፍሴን ያብሰከሰካት፣ ተማሪ መሆኔን በደፈናው ከመንገሬ ውጪ ባልገባኝ ምክንያት የደበቅኋት የእኔው እውነት ነበር፡፡
አንዳንድ የእውነት አጋጣሚዎች እውነት አይመስሉም፡፡
እኔና አደይ በፀደዩ ወራት አጋማሽ በአንድ ዩኒቨርሲቲ ተመድበን፣ የማመልከቻችን ዕለት እዚያው እምዝገባው ቦታ ተገናኘን፡፡ ይሄን እውነቴን ነበር የደበቅኋት፡፡ ራቅ ካለ ቦታ ነበር የተያየ ነው፡፡ መጀመሪያ አፏን ከፍታ አተኮረችብኝ፣ ቀጥሎ እምባዎቿ በጉንጮቿ ሲፈሱ አየኋቸው፡፡ ከዚያ ወደ እኔ ተንደረደረች፡፡ ደንዝዤ፣ ባለሁበት በዝምታ ነበር የምከታተላት፡፡ መጥታ ስትጠመጠምብኝ፣ ዶክመንቶቼ መሬት ላይ ሲበታተኑ፣ አላፊ አግዳሚው ሲያተኩርብን፣ ይታወቀኛል፡፡ ጨርሼ እንደበድን ሆኜ ነበር፡፡
አንድ ዲፓርትመንት ገባን፡፡ አንድ ዶርም ተመደብን፡፡ የመጀመሪያውን መንፈቅ ያሳለፍንበት ፍቅር፣ እምላለሁ፣ እህትማቾች ዘንድ አይኖርም፡፡ በመጀመሪያው መንፈቅ ከቁብ ያልቆጠርናቸው እንቅፋቶቻችን፣ ከመቼው በእረፍቱ እንደፋፋ እንጃ፣ በሁለተኛው ግማሽ ዓመት ልዩነቶች ይፈትኑን ጀመር፡፡ ተማሪው ሁሉ በመጠነኛ ትውውቁ ወደ መቧደን ያዘነበለው በነዚያ ወራት ነበር፡፡ መቧደኑ ሳይከፋ የጐሪጥ መታያየቱ ባሰ፡፡
በቅድሚያ፣ የከተማና የገጠር ልጅ የሚባል ፈሊጥ መጣ፡፡ በመቀጠል የኃይማኖት ልዩነቶች ተነሱ፡፡ እኔና አደይ ተነቀነቅን፡፡ እንደምንም አመቱ አልቆ ለእረፍት በየፊናችን ተበተንን፡፡ ለከርሞ፣ መንፈሳችን ታድሶ እንገናኝ ዘንድ በሰፊው ስፀልይ ከረምኩ፡፡ ከአደይ ጋርም አልፎ አልፎ ተደዋውለን ነበር፡፡ እኔ’ንጃ…የድሮው ፍቅራችን የሚመለስ አልመስል እያለኝ ስብሰከሰክ ሰነበትኩ፡፡
በሁለተኛው ዓመት እኔና አደይ እንደ አምናው አንድ መኝታ ቤት አልያዝንም፡፡ አመቱን የጀመርን ሰሞን፣ ከዩኒቨርሲቲው ራቅ ብሎ የሚገኝ ሻይ ቤት ተቀጣጥረን ተገናኘን፡፡ የምናውቃቸው ልጆች እንዳይመጡና እንዳየዩን በማጠነቀቅ ስሜት፣ የቻልነውን ያህል የፍቅር መንፈሳችንን ለመጠበቅ እየሞከርን ተጨዋወትን፡፡
በወሬአችን መሃል በክረምቱ የሆነችውን አጫወተችኝ፡፡ ከእናቷ ጋር በግል በማያወጉበት ሰዓት አደይ እናቷን “ብሔራችን ምንድንነው?” ብላ ትጠይቃቸዋለች፡፡ እናቷ መልሱን በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ “ይሄንን ተምረሽልኝ መጣሽ?!” እያሉ ብዙ ደቂቃ ወስደው አለቀሱ፡፡ አደይ ግን የዘመድ አዝማድ ወሬ አነፍንፋ በአስራ ዘጠኝ አመቷ ብሔሯን ደረሰችበት፡፡ አደይ እዚያ፤ እኔ እዚህ፡፡
ይሄም ዋና ልዩነት ሆኖ፣ እኔ እና አደይን ሳንፈልገው በተለያየ ጐራ አቆመን፡፡ ግንኙነታችን እየደበዘዘ፣ መራራቃችን እየሰፋ፣ ጓደኝነታችን ጨርሶ እየጠፋ ሄደ፡፡
በጊዜ ሂደት ሰላምታ መቀያየርም ተውን፡፡ እኔና አደይ ገዢ እና ተገዢ፣ እኔና አደይ በዝባዥ እና ተበዝባዥ፣ እኔና አደይ ጨቋኝ እና ተጨቋኝ ብሔሮች ሆነን ተሰለፍን፡፡ አይገርምም?!እኔም ሌሎች ወዳጆች አፈራሁ፡፡ አደይም ሌሎች ጓደኞች ኖሯት፡፡ በአዲሱ ጓደኝነት ውስጥ ነባር ስነምግባራችንን በወረት አራግፈን፣ መጤ ባህሪዎችን በጥራዝ ነጠቅነት ተላበስን፡፡ ሁለተኛ ዓመት ተጀምሮ ምን ያህል እንደቆየን እንጃ፡፡ አንድ ምሽት፣ እከተማው መሃል ካለ “ባር” እኔና ጓደኞቼ ተሰባስበናል፡፡ ወይን እየጠጣን፣ ሲጋራ እየተቀባበልን እናጤሳለን፡፡ መርዶዬን የሰማሁት ያኔ ነበር፡፡ አደይ የካቻምናውን ክረምቴን ለቅርቦቿ አውርታለች፡፡ ወሬው በምላስ ንፋስ ሃይል ግቢውን አጥልቅልቆታል፡፡ ጓደኞቼ ጆሮ ደርሶ፣ እኔው ብቻ ኖሬአለሁ የገዛ ታሪኬን ሳልሰማ የሰነበትኩ፡፡ በሞቅታ መሃል አንዷ አንስታ ተረተረችልኝ፡፡ አናቴ ነበር የተተረተረው፡፡ በብስጭት እንደቆምኩ፣ ሲጋራዬን በጣቶቼ እንዳንጠለጠልኩ፣ በመጠጥ እና በነገር እንደናወዝኩ፣ በግሌ ምዬ የተገዝትኩለትን፣ የእኔው አድርጌ የኖርኩትን፣ ያንን ዘግናኝ የአደይ ምስጢር እንደዋዛ ዘረገፍኩት፡፡ ጨርሶ ባልነበርንበት፣ ሰምተን ብቻ ባመንነው፣ የወሬ ቅጥልጥል ተጠላልፈን ተጠማመድን፡፡ አንዳንድ የውሸት ታሪኮች ውሸት አይመስሉም፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት መላው የግቢው አየር በዚያ ቀፋፊ ወሬ ታፈነ፡፡ ጓደኞቼ ደህና የመልስ ምት አግኝተዋል፡፡ በሌላኛው ሳምንት አደይ ትምህርቷን እስከወዲያኛው አቋርጣ ግቢውን ለቀቀች፡፡ ያው ወሬው እየነጣጠረ ይመጣል፡፡ ለወላጆቿ አየሩ እንዳልተስማማት አሳምና፣ ትምህርቷን በግል ዩኒቨርሲቲ እንደቀጠለችም ሰማሁ፡፡

 

Published in ልብ-ወለድ
Saturday, 13 September 2014 13:25

የመይሳው ግጥሞች!

      “መይሳው” የአጤ ቴዎድሮ የፉከራ ስም ነው፡፡ ጠላታቸውን ጥለው ሲፎክሩ “መይሳው ካሳ’! አንድ ለእናቱ! ሺ ለጠላቱ!” ብለው ይፎክሩ ነበር ይባላል፡፡ ቴዎድሮስ በመሳፍንት እንደ አክርማ ተሰነጣጥቃ የነበረችውን ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ መሰረቱን በመጣላቸውና እንደ ክርስቶስ ሞትን በሞታቸው ድል በማድረጋቸው ከቀዳሚያን መሪዎች የተለዩ ናቸው፡፡ ከጥቃት ይልቅ ሞትን የመረጡ ልበ ሙሉ ነበሩ!

የጽሑፌ ዓላማ ስለጀግንነታቸው ማውሳት አይደለም፡፡ እሱ እጅግ ብዙ ጊዜ ተብሏል፤ ገናም በትውልድ ቅብብሎሽ ሲወሳ ይኖራል፡፡ ዛሬ የፈለግሁት ስለአጤ ቴዎድሮስ በተለያዩ ሰዎች “ተገጠሙ” ከሚባሉ በርካታ ግጥሞች ጥቂቱን እያነሳሁ መጠነኛ ማብራሪያ መስጠት ነው፡፡ የግጥሞቹን ባለቤትነት ለእርሳቸው ያደረግሁትም ለእሳቸው ወይም በእርሳቸው ምክንያት ስለተገጠሙ ነው፡፡
ቴዎድሮስ “አጤ” ከመባላቸው በፊት ካሣ ሃይሉ ነበር ስማቸው፡፡ አጤ ቴዎድሮስ የተባሉት የሰሜኑን ገዥ ደጃዝማች ውቤን ደረስጌ ላይ ድል አድርገው ዘውድ ከጫኑ በኋላ ነው፡፡ ደጃዝማች ውቤ የመጨረሻው ተድል ተነሺ መስፍን ነበሩ፡፡
አጤ ቴዎድሮስ ገና በሽፍትነት ዘመናቸው “ጋረድ” የተባለ የአጎታቸው ልጅ ለራስ ዓሊና ዘውድ ጠባቂ ለነበሩት ወይዘሮ ምንትዋብ አድሮ፣ በጦርነት ሊያንበረክካቸው ዘመተ፤ ከእሱ ጋር የነበረ አዝማሪም የጋረድን ሰራዊት ለማበረታታት ሲል የሚከተለውን ገጠመ፡-
“አያችሁልኝ ወይ ይህን ታላቅ እብድ፣
ሁለት ጋሞች (ጋሜዎች) ይዞ ጉርአንባ ሲወርድ፡፡
ያንጓብባል እንጂ መች ይዋጋል ካሣ፤
ወርደህ ጥመድበት በሽንብራው ማሳ”
ጦርነቱ ጉራንምባ ላይ ተካሄደና የሰራዊቱ መሪ የነበረው ጋረድም፣ ይህንን ግጥም የገጠመው አዝማሪም ተማርከው ከካሣ ፊት ቀረቡ፡፡ ካሣ “ያንን የኮሶ ሻጭ ልጅ አንገቱን ይዤ ባላመጣው ወንድ አይደለሁም” ብሎ ፎክሮ የነበረውን ጋረድን ዋርማ (ትልቅ ቅል) ሙሉ የተበጠበጠ ኮሶ ግተው እንዲሞት ሲያደርጉ፣ አዝማሪውን ግን ለምን እንደሰደባቸው ጠየቁት፡፡ እሱም በፍርሃት እየራደ እንዲህ አለ፡-
“አቤት የአምላክ ቁጣ፣ አቤት የእግዜር ቁጣ!
አፍ ወዳጁን ያማል የሚያረገው ሲያጣ፤
ዱላ ይገባዋል ለአዝማሪ ቀልባጣ”
አዝማሪው ይህንን ሲገጥም የካሳን አንጀት ለመብላት ሲል መቀላመዱ ነበር፤ ካሳ ግን “ትክክለኛ ውሳኔህን በራስህ ላይ ወስነሃልና ተግባራዊ ይሆንብሃል” በማለት በዱላ ተቀጥቅጦ እንዲሞት ተደረገ፡፡
ካሳ በጉልበትም በአመራር ጥበብም እየፈረጠሙ ሲሄዱ፣ ከጎንደር አልፈው ሌሎችን መሳፍንት መውጋትና ግዛታቸውን ማስፋፋት ያዙ፡፡ በወቅቱ ጎጃምን ይገዙ የነበሩት ደጃዝማች ጎሹ የጎንደር ቤተመንግስት እንደራሴ ለነበሩት ራስ ዓሊ አግዘው ካሳን ለመውጋት ሄዱ፡፡ ሆኖም በለስ አልቀናቸውም ነበርና ከጦር ሜዳ ላይ ሞቱ፡፡ ጉዳዩን ሲከታተል የነበረ (ምንአልባትም የቤተ ክህነት ሊቅ ሊሆን ይችላል) አዝማሪ፣ ኦሪታዊው ንጉስ ዳዊት በቤርሳቤህ ፍቀር ተነድፎ በሏን ኦርዮንን ወደ ጦር ሜዳ ልኮ በግፍ እንዳስገደለው ሁሉ፣ ራስ ዓሊም ደጃዝማች ጎሹን ልከው አስገደሉት ለማለት የሚከተለውን ገጥመዋል፡-
“ጎሹ እንደ ኦርዮ ዓሊ እንደ ዳዊት፣
ከጥንት አይደለም ወይ ተልኮ መሞት”
“ሲያስፈራ የነበር መኳንንቱን ሁሉ፣
ላሞች ተሰብስበው ጎሹን ወጉት አሉ”
“ገበጣ ተጫውተው ጅሙ ሳይነሳ፣
ኧረ በጎሹ ሞት ተጫወቱ ካሳ!”
ካሳ አንድ ባንድ እያናጠሉ መሳፍንቱን ሁሉ አምበርክከው ደረስጌ ላይ ደጃዝማች ውቤን ከማረኩ በኋላ እዚያው ደረስጌ ማርያም (ሰሜን ጎንደር ዳሽን ተራራ አካባቢ የሚገኝ ቦታ ነው) ላይ ዘውድ ጫኑ ስመ መንግስታቸውንም “ቴዎድሮስ” አሰኙ፡፡ አጤ ቴዎድሮስ ዘውድ ከጫኑ በኋላም የመኳንንትና መሳፍንት ርዝራዦችን ማሳደዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ከጎጃም በኩል አምልጠው ወደ አፋር ሀረሃ የተደበቁት ራስ ዓሊም ዘመን እንደ ከፋባቸው ሲረዱ እንዲህ የሚል ግጥም ለአጤ ቴዎድሮስ ላኩ፡-
“የጣቴን ቀለበት አንተ አድርገው ካሳ!
በእኔማ ጣት ገብቶ አስቸገረኝሳ!”
ቁም ነገሩ “ህብር” በሚባለው የቅኔ መንገድ የተገለጠበት ቅኔ ነው፤ “ካሳ አንተን ጊዜ አንስቶሃል፤ በስልጣነ መንበሬ ላይ ተዝናንተህ ተቀመጥበት፣ እኔን ግን ማጣት እያሰቃየኝ ነው” ማለታቸው ነው፡፡ “በእኔማ ጣት ገብቶ አስቸገረኝሳ!” የሚል መልእክት ይዟል ግጥሙ፡፡
በሌላ ጊዜ ደግሞ በካህናት የተደገፈ አመፅ ጎጃም ላይ ተካሄደባቸው፤ አጤ ቴዎድሮስም የአገሪቱን አንድነትና ሰላም ለማስጠበቅ ላይ ታች ሲዋትቱ ነበርና ፊታቸውን ወደ ጎጃም አቀኑ፤ ሞጣና ቀራንዮ አካባቢም ከፍተኛ ቅጣት ፈፀሙ፡፡ በዚህ የተነሳ ህዝቡ እንዲህ ሲል ገጠመ፡-
“የቤተስኪያን ንብረት አትንኩ እያላችሁ፣
ምነዋ ደብተሮች ስለት የበላችሁ?”
“ሞጣ ቀራንዮ ምነው አይታረስ?
በሬ ሳላይ መጣሁ ተዚያ እስተዚህ ድረስ”
ሬሳ እየተራመድሁ መጣሁ፤ ማለቱ ነው፡፡ ወይም አገሩ በሙሉ (ሞጣና ቀራንዮ) በአስከሬን ተሞልቷል በማለት የአለቀውን ሰው ብዛት አመልክቷል፡፡ ከዚያም ጎጃሞች ቴዎድሮስን እንደ እብድ ያዩአቸው ጀመር፡፡
“አትሂድ ጎጃሜ! አትመላለስ!
አበደ ይሉናል አዲሱ ንጉሥ” ሲሉም ሰውየው ጤና የራቃቸው ስለሆኑ መጠንቀቅ እንደሚያዋጣ በግጥም መመካከር ያዙ፡፡
ፊታውራሪ ቸኮል አለነ የሚባሉ ባላባት ከልጃቸው ጋር በመሆን በአጤ ቴዎድሮስ ላይ አምፀው ስለነበር ተያዙና ባሶ ገበያ ላይ (ጎጃም ውስጥ የሚገኝ ቦታ ነው) በስቅላት ተቀጡ፡፡ የሟቾቹ ቤተሰቦችም አንጀታቸው እያረረ የሚከተለውን የሃዘን እንጉርጉሮ ገጠሙ፡-
“የጎጃም ባለቤት፤ ዓባይን ከልካይ፣
ገበያ ጠባቂ አደረጉህ ወይ?”
“ወይ አልተባረከ ይኸ ሁሉ ሰው፣
ንጉሥ መስቀልዎን ቢተዉት ምነው?”
“የጎጃም መኳንንት እንዴት ከረማችሁ?
ለመስቀል ንጉሱ ጎንደር ግቡ አሏችሁ”
“እኛስ እንሞቃለን ትንሽ ትንሽ ጣይ፣
የእናንተ ደመና መቅረቱ ነወይ?”
ግጥሞቹ ህብር ቅኔ በሚባለው መንገድ የተነገሩ ናቸው፡፡ “ለመስቀል ንጉሡ ጎንደር ግቡ አሏቸው” ሲል “ሊሰቅሏችሁ ነው ጎንደር ድረስ ኑ ያሏችሁ” ማለቱ ሲሆን፤“ንጉሥ መስቀልዎን ቢተዉት ምነው?” ሲል ደግሞ “ንጉስ ሆይ ሰው እንደሆነ አልተባረክልዎትም ወይም እሽ ብሎ አልተገዛልዎትም፤ ታዲያ በየቦታው በስቅላት መቅጣትዎን ቢተዉት ምን አለበት?” የሚል ነው ኃይለ ቃሉ፡፡
“የእናንተ ደመና መቅረቱ ነወይ?” የሚለው ሃረግም “የእናንተ ደም በከንቱ ፈስሶ መቅረቱ ነውን?” ሲል የቁጭት ጥያቄ ያቀርባል፡፡ ፊታውራሪ ቸኮልን “ገበያ ጠባቂ አደረጉህ ወይ?” በማለት የሚጠይቀውም “የጎጃሙ ባላባት፣ የታላቁ ዓባይ ወንዝ ጌታ ወይም አዛዥ የሆንኸውን ታላቁን መኳንንት እንዴት ገበያ ላይ ይሰቅሉሃል?” ሲል በቁጭትም በሃዘንም መጠየቁ ነው፡፡
አጤ ቴዎድሮስ ከጎጃሞች ቀጥለው ፊታቸውን ወደ ሸዋ በመመለስ “አልገዛም” ያሏቸውን ሁሉ ያለምህረት ቀጡ፤ የብዙ መኳንንቶችን እጅ በመቁረጥም የመረረ ቁጣቸውን በሸዋ ላይ አዘነቡ፡፡ ይህን የተመለከተ አዝማሪም፤
“ኧረ ዛሬስ ንጉሥ በጣም ተዋረዱ!
የሸዋን መኳንንት እጅ ነስተው ሄዱ”አለ፤ ቴዎድሮስ በትህትና ሰጥ ለጥ ብለው ለመኳንንቱ ሁሉ የሰገዱ በማስመሰል፡፡ “እጅ ነስተው ሄዱ” ሲል መኳንንቱን ሁሉ እጀ ቆራጣ ማድረጋቸውን ገለጠ፡፡ ንጉሥ ይሰገድለታል እንጂ አይሰግድማ!
“አንጥረኛው ብዙ ከንጉሱ ቤት
ባለ አልቦ አደረጉት ይህን ሁሉ ሴት” የሚል ግጥም የተገጠመውም በዚያን ዘመን ነው፡፡ በርካታ ሴቶች በተለያዩ የጦር ሜዳዎች በተደረጉ ውጊዎች ባሎቻቸው ተገድለውባቸው ነበርና ገጣሚው የእግር ጌጥ (አልቦ) ያደረጉ አስመስሎ “ባለ አልቦ አደረጉት” ሲል ትዝብቱን ገልጧል፡፡
የጎጃም መኳንንት ከነበሩት እና በአጤ ቴዎድሮስ ከተገደሉት የአንዱ (ምን አልባት የፊታውራሪ ቸኮል አለነ) ልጅ ሳትሆን አትቀርም፤ “ምንትዋብ” የተባለች ሴት ደግሞ ከአጤ ቴዎድሮስ ሰራዊት ጋር ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሰች በቴዎድሮስ ላይ መግጠም መደበኛ ባህሪዋ ሆነ፡-
“ሽ ብረት በኋላው፣ ሽ ብረት ከፊቱ፣
ሺ ፈረስ ከኋላው ሺ ፈረስ ከፊቱ
ይህን ሳታይ ሞተች ኮሶ ሳጭ እናቱ”
* * * *
“አንድ እግር በርበሬ መንቀል አቅቷችሁ፣
አንድዶ፣ ለብልቦ አቃጥሎ ይፍጃችሁ?”
* * * *
ይህንን ሲሰማ ያጓራል ላመሉ፣
“ማንናት’ም ቢላችሁ ‹ምንትዋብ ናት› በሉ!”
እና ሌሎችንም ግጥሞች እየደረደረች መሳደብና ሰራዊቱንም ሆነ ህዝቡን በግጥሟ መቀስቀስ የማይገታ ግዴታዋ አድርጋ ያዘችው፡፡ አንድ ቀን በጥፋቷ ተያዘችና ከንጉሡ ፊት ቀረበች፣ ለምን እንደምትሰድባቸው ሲጠይቋትም በመደንገጥ፣ በመፍራትና በማፈር ፈንታ የሚከተለውን ገጠመች፡-
“ጠጅም እንዳያምረኝ ድሮ ጠጥቻለሁ፣
ሥጋም እንዳያምረኝ ቋንጣ ሰቅያለሁ፣
ቢሻኝ ከወንድሜ ካባቴ እበላለሁ” አለች፡፡
ሴትየዋ በስቅላት ከተቀጡት የጎጃም መኳንንት የአንዱ ልጅ መሆኗን ሲረዱም አጤ ቴዎድሮስ በብስጭት ከመቅጣት ይልቅ በሃዘን ምህረት አደረጉላትና ከሰራዊቱ ጋር እስከ መጨረሻው የንጉሡ ውድቀት ድረስ ስትከተል ኖረች፡፡
አጤ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያን መኳንንት ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በቱርኮች እጅ ወድቃ ስትሰቃይ የነበረችውን እስራኤልንም ነፃ የማውጣት ህልም ነበራቸው ይባላል፤ በዚህ የተነሳ ሲፎክሩ እንኳ “መይሳው ካሳ! የኢትዮጵያ ባል፣ የኢየሩሳለም እጮኛ!” ይሉ ነበር አሉ፤ ይህንን እውነት የሚያረጋግጡ ግጥሞችም በተለያዩ ሰነዶች ተገኝተዋል፡-
“ታጠቅ ብሎ ፈረስ ካሣ ብሎ ስም፤
አርብ አርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም”
የዚህን ግጥም ይዘት ትንሽ ዘርዘር አድርጎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ “ታጠቅ ብሎ ፈረስ ካሳ ብሎ ስም…” ቱርኮች ሙስሊሞች ናቸው፡፡ አርብ ደግሞ የጁምአ (የስግደት፣ የዕረፍት) ቀን ነው፤ ስለሆነም ስግደት ወይም ዕረፍት ላይ እያሉ “ካሣ” የሚባል አበሻ ንጉሥ ድንገት ደርሶ ያጠፋቸዋል የሚባል ወሬ ኢየሩሳሌምን ይንጣት ነበርና ሁል ጊዜ አርብ በከተማዋ ሽብርና ጭንቀት ነበር ይባላል፡፡ ለዚያ ነው “አርብ አርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም!” የተባለው፡፡
“የኢየሩሳሌም ሰው ካልጫነ በርሙሌ፣
አንተም ጌታ አይደለህ፤ እኔም አልሆን ሎሌ”
ይህኛው ግጥም ደግሞ አጤው ኢየሩሳሌምን ከሙስሊሞች ነፃ የማድረግ ሃሳባቸውን እውን እንዲያደርጉት የሚገፋፋ ነው፡፡
የኢየሬሳሌም ሰው በርሙሌ (ግብር) ካልጫነ በቀር ኃይልህን፣ ታላቅ መሪነትህን አላውቅልህም፣ ስለዚህ እኔ ለማዳ አሽከር (ሎሌ)፣ አንተም የእኔ ጌታ ልትሆን አትችልም እያለ ወደፊት የሚገፈትር ነው፡፡
በአጤ ቴዎድሮስ ድል ከተነሱት መኳንንት አንዱ የጎጃሙ መስፍን የደጃዝማች ጎሹ ልጅ ደጃዝማች ብሩ ናቸው፤ የአጤ ቴዎድሮስ የፖለቲካ እስረኛ በመሆን ለብዙ ዘመን ተሰቃይተው ነበርና የሚከተለውን ገጥመዋል፡-
“መከራን በሰው ላይ እንዲያ ሳቀለው፣
ምንኛ ከበደ በእጄ ስይዘው”
“መከራ ሲመጣ አይነግርም አዋጅ፣
ሲገሰግስ አድሮ ቀን ይጥላል እንጂ!”
“ዘሃው ስለሰላ ሸማኔው ተቆጣ፣
እስከ ወዲያው ድረስ መጠቅለያው ታጣ” ከእነዚህ ስንኞች ውስጥ “ቀን ይጥላል እንጂ” የሚለውና “መጠቅለያው ታጣ” የሚሉት የግጥሞቹ ዋና ኃይለቃላት ናቸው፡፡
ለማንም ሰው ጉልበቱ ጊዜ ነው፤ ጊዜ ከከዳው ማንም ከጐኑ ሊቆም አይችልም፤ እናም ደጃች ብሩ ቀን እንጂ ማንም እንዳልጣላቸው፤ ቀን ፊቱን ነስቷቸው የታላቁ መስፍን የደጃዥማች ጐሹ ልጅ ከቋራ በተነሳ “ተራ ድሃ” እጅ በምርኮኛነት ወድቀው መማቀቃቸውን ለመግለጥ ይመስላል ይህንን ግጥም ያንጐራጐሩት - ጊዜው ከመኳንንቱና መሳፍንቱ ኮብልሎ ሄዶ የቴዎድሮስ ጥገኛ መሆኑን ለማሳየት፡፡
“መጠቅለያው ታጣ” ያሉትም የዚያ ክፉ ቀን መጨረሻ፣ ከአሰቃቂው የእስር ቤት ህይወት ሊያወጣቸው የሚችል አንዳች ተአምር ሊፈጠር የሚችለው መቼ እንደሆነ ምን አልባት አምላካቸውን የጠየቁበት ሊሆን ይችላል፡፡
ቴዎድሮስ በተለይ ከካህናት ጋር ስለማይስማሙ ብዙ ጊዜ መረር ያለ ቅጣት ይፈጽሙ ነበር፡፡ ይህን የታዘበ አንዱ የዘመኑ ገጣሚ (አዝማሪ ሊሆን ይችላል) እንዲህ ብሏል፡-
“እኔስ ፍረድ ቢሉኝ ሞት በደለኛ ነው፤
አንድ ቄስ ባገሩ ቆሞስ ቢገኝ ምነው”
በደንብ መታየት ያለበት ህብር ቅኔ ነው፡፡ የቅኔው ምስጢር ያለው “ቆሞስ” ከሚለው ቃል ላይ ነው፡፡ ቆሞስ ከቅስና በላይ የሚገኝ ሃይማኖታዊ ማዕረግ ሲሆን ብዙ ጊዜ ለመነኮሳት የሚሰጥ ነው፡፡ ትልቁ የግጥሙ መልእክት ግን ቄስና ቆሞስን ለመመኘት አይደለም፡፡
“ካህናቱ ሁሉ አለቁ ፤ምን አለበት አንድ ቄስ እንኳ ከቴዎድሮስ ቅጣት ተርፎ ቆሞ (በህይወት) ቢገኝ” የሚል ነው መልክቱ፡፡
ቴዎድሮስ ራሳቸውም ገጣሚ ነበሩ ይባላል፤ ባለቤታቸው እቴጌ ተዋበች ሞተው ሃዘናቸውን የገለጡባቸው ግጥሞች ለአስረጅነት ይቀርባሉ፡-
“እስኪ ጠይቁልኝ ርቃ ሳትሄድ፣
እቴጌ ተዋበች ሚስት ናት? ወይ ገረድ?” የሚለው ቀዳሚው ግጥም ነው፡፡
እቴጌ ተዋበች “ሚስት፣ እናት፣ ገረድ ነበረች” በማለት ነው የባለቤታቸውን ሁሉን አቀፍ ባህርይ የገለጡት፡፡
“መድሃኒቱን ምሳ ታበላኝ ነበረች፣
ሌባዬ ተይዛ ባልጋ ትሄዳለች” ሲሉም ተዋበች የህይወታቸው ዋልታና ማገር እንደነበሩ፤ ያኔ ግን አስከሬናቸውን በአልጋ አጋድመው ከቦታ ቦታ መንከራተት መራር ዕጣቸው መሆኑን ገልጠዋል ቴዎድሮስ፡፡
በየጐጡ በነበሩ መሳፍንትና መኳንንት ለሰባ አምስት ዓመታት ፍዳውን ሲበላ የኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ቴዎድሮስን አቅፎና ደግፎ ለሥልጣን እንዳላበቃ ሁሉ እየዋለ ሲያድር ግን በካህናት ስብከትና በርዝራዥ መሳፍንት እየተታለለ መክዳቱ አልቀረም፡፡ እናም ረጅሙ የቴዎድሮስ ህልም በአጭሩ ተቀጨ፡፡
እንግሊዞች ከምጽዋ እስከ መቅደላ ያለአንዳች መሰናክል እንዲገቡም በሩ ወለል ብሎ ተከፈተላቸው፡፡ እንደ ደጃዝማች ካሣ ምርጫ (በኋላ አጤ ዮሐንስ) ያሉት መኳንንት እንዲያውም ለወራሪው የናፒር ሠራዊት ስንቅ እያቀበሉና፣ መንገድ እየመሩ ወረሪው በቴዎድሮስ ላይ እንዲዘምት ቀላል የማይባል ዕገዛ አደረጉ፡፡
መኳንንቱ ሁሉ ከድተው፣ ሠራዊታቸው ተመናምኖ ብቻቸውን መቅረታቸውን የተረዱት አጤ ቴዎድሮስም ከውርደት ይልቅ ሞትን መርጠው፣ ራሳቸውን በራሳቸው አጠፉና ወራሪውን በሞታቸው ድል ነሱት፡፡ ይህን የተገነዘቡ ገጣሚዎችም የሚከተሉትን የአድናቆትም የቁጭትም ግጥሞች ገጠሙ፡-
“መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ፤
የሴቱን አናውቅም፤ ወንድ አንድ ሰው ሞተ፡፡
የትግሬንም ንጉሥ ሲንቁ፣ ሲንቁ፣
የጐጃምን ንጉሥ ሲንቁ፣ ሲንቁ፣
የሸዋውን ንጉሥ ሲንቁ ሲንቁ፣
ወንድ ያለራስዎ ገድለውም አያውቁ”
“እንደዚህ ስሱ (ስስታም) ነው ያበሻው ንጉሥ
እህል ባገር ሞልቶ ጠመንጃ እሚጐርስ?”
ገደልን እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው
ማረክን እንዳይሉ ሰው የለ በእጃቸው፣
ምን ይሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው?
ለወሬ አይመቹም ተንኮለኛ ናቸው!
“ቴዎድሮስ ጠፍቶ የምትጠይቁኝ
ፊትም አላለፈ ከኋላም አይገኝ”
እርግጥ ነው ከቴዎድሮስ በፊት እሳቸውን የመሰለ ልበ ሙሉ ጀግና አልነበረም፡፡
ከእሳቸው ህልፈት በኋላም ቴዎድሮስን ያህል ለኢትዮጵያ ልዕልና ቀን ከሌሊት የሚተጋ፣ ሩቅ ራዕይ ያለውና ሰውን በዘሩ፣ በቋንቋውና በሃይማኖቱ ሳይሆን በሰውነቱ ብቻ የሚያከብር መሪ አገራችን እስካሁን ያገኘች አይመስለኝም፡፡
ቸር ይግጠመን!!

 

 

Published in ጥበብ

(እስቲ እውነት እውነቱን እናውራ)

   ሰው መሬት መንገሻው ሰማይ መናፈሻው ተደርገው የታነፁለት ንጉስ ነው፡፡ ስለሆነም ልቡን ስሎ፣ አዕምሮውን አብስሎ ሲተጋና ጥበብን ሲሻ በመሬት የተተከሉ፣ በሰማይ የተሰቀሉ እንዲሁም መሀል ላይ የሚንቀዋለሉ ፍጥረታት ሁሉ ያለማመንታት ይገዙለታል፡፡ እሱም ለስጋው ድሎት፣ ለነፍሱ ችሎትና ለመንፈሱ አገልግሎት ያስገብራቸዋል፡፡ ይሄኔም ልኩ ታውቆ፣ ቦታው ተጠብቆ በፀጋ ስያሜው የፍጥረት ራስ ተብሎ ይጠራል፡፡ ሰው አስተሳሰቡን ማበጠር አካባቢውን መቆጣጠር ሲሳነው ግን የፍጥረት ራስ መሆኑ ቀርቶ ትራስ ይሆናል፡፡ ትራስ የሚሆን ራስ ደግሞ የመስመጥ እንጂ የማበጥ፣ የመልፋት እንጂ የመፋፋት፣ የማለቅ እንጂ የመዝለቅ ህልውና የለውም፡፡ ሰብዕናው መታሸት፣ እድሉ መበላሸት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ውስጡ ተንፍሶ፣ ውጪው ተበጣጥሶ እስከሚወረወር ድረስ የሌሎች መሞላቀቂያ፣ የእንቅልፋቸው ማድመቂያ፣ የድካማቸው ማስለቀቂያ ሆኖ ያገለግላል፡፡
ትራስ የሚሆን ራስ በልማዱ ከስር የመርመጥመጥ እንጂ ከላይ የመቀመጥ ጠባይ ስለሌለው አምላኩም ፈለኩም የተጫነበት ተራራ፣ የወደቀበት መከራ ነው፡፡ በመሆኑም ጭነቱን ገፎ፣ ሸክሙን አራግፎ ለመለወጥ አይባጅም፡፡ ይልቁንም ባለበት አምኖ፣ በኖረበት ተከድኖ ያለመገረም፣ ያለማጉረምረም ይቀጥላል፡፡ ትራስ የሚሆን ራስ ከታሰረበት ከተማ፣ ከተወረወረበት ጨለማ ለመውጣት ፀጋውን መርምሮ፣ ተሰጥኦውን በርብሮ ስለማይንቀሳቀስ ብርሃን ቤቱን ጥበብ ህይወቱን አያውቁትም፡፡
ይህ የእኔና የአንተ እውነት ነው፡፡ በቤታችን መሬት መታሻ፣ ሰማይ ማልቀሻ ሆነው ሰው ራስ በሆነ ማንነት ሳይሆን ትራስ በሆነ መናኛነት ይመላለሳል፡፡ የአዕምሮ ጥቅሙ፣ የጥበብ ቀለሙ አይታወቅም፡፡ የፍጥረት አቻዎቻችን በየወቅቱ እየተነሱ ምድርን በግኝት ብርሃናቸው ሲያጠምቋት፣ በፍላጐት ክንዳቸው ሲያመጥቋትና በአስተሳሰብ ሃይላቸው ሲያደምቋት እኔና አንተ በፍርሃት ተከበን፣ በጨለማ ተሸብበን እንገኛለን፡፡ ወደ ብርሃን መውጣት ለውጥ ማምጣት አይታየንም፡፡ ጥበብ መካፈል ግኝት መፈልፈል አይቃጣንም፡፡ ድካምን ማድከም እረፍትን ማከም አንሻም፡፡ ችግርን መርሳት ተድላን ማውሳት፣ ህሊናን ማደስ ኑሮን ማወደስ ወደ ሀሳባችን አይመጣም፡፡ ልዩነት በድህነት መዝለቅ፣ በዕጦት ወረርሽኝ ማለቅ ይመስለናል፡፡ ልዩ መሆን፣ ልዩ ነኝ እያሉ ማውራት፣ የዋሻና የሀውልት ስም መጥራት ሆኖብናል፡፡
ዛሬም ድረስ በአዳም በሬ፣ ጅራፍ በያዘ ገበሬ እናርሳለን፡፡ ውሃ እና መብራት፣ ቁርስና ራት ይርበናል፡፡ በልቶ ማደር ፀሎታችን፣ ለብሶ ማጌጥ ህልማችን ነው፡፡ የቤት ዕቃ መቀየር ብርቃችን፣ ጐጆ መቀለስ ድንቃችን ነው፡፡ ዘመናችን ሁሉ መሰረታዊ ፍላጐታችንን ለማሟላት ለማናውቀው አዚም የተከፈለ ቀብድ ነው፡፡ መኖር ፈጽሞ ሌላ አላማ የሌለው እስኪመስለን ድረስ ዕለት በዕለት፣ ከልጅነት እስከ እውቀት የሰቀቀን ተላላኪ፣ የግዞት ህላዌ አምላኪ፣ የሲኦል ፍዳ ተራኪ ሆነን፣ አካላችን ተበዝብዞ፣ ህሊናችን ተመርዞ መቆም ታክቶን፣ ሳቅ ተረስቶን ከምሬት ወደ መሬት፣ ከሞት ወደ ሞት እንሸጋገራለን፡፡ በጨለማ ውስጥ ተወልደን፣ በጨለማ ውስጥ አርፍደን ወደጨለማ እንመለሳለን፡፡ የዚህ ምድር አባል ለመሆን ቀደም ሲል መወለዳችን ሳይወሳ የቀብራችን ጡሩንባ ይነፋል፤ የዘመዶቻችን እንባ ይጐርፋል፡፡ አቶ ሀበሻ ወደዚህ ምድር ሳይመጡ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል ይባላል፡፡
ሰው ለመታከት ለምን ይፈጠራል! ህይወታችን ጉልበት እንጂ ሽበት፣ ክበብ እንጂ ጥበብ የለበትም፡፡ ጥጃ ከእናቷ ወተትን፣ እኛ ከእናታችን መዋተትን እንቀበላለን፡፡ አንበሳ ከአባቱ ጋማ፣ እኛ ከአባታችን የድህነት አርማ እንወርሳለን፡፡ ውጣ ውረድ የኛ ውርስ፣ የልጆቻችን ቅርስ ነው፡፡ ምኞታችን የኋሊት፣ መንገዳችን በሌሊት ነው፡፡ ለሚቀለው በር፣ ለሚከብደው ድንበር የለንም፡፡ ከለበስነው የተሻለ ማቅ፣ ከምናውቀው የበለጠ ሀቅ ያለ አይመስለንም፡፡ ከለመድነው ያለመድነው እንደሚበዛ፣ ከምናየው የማናየው እንደሚገዛ አናስተውልም፡፡ ጨረቃ ልጅ ሆና ትወለዳለች፡፡ ከዛም በአካል ጐርምሳ በብርሃን ጐልምሳ ትጠፋለች፡፡ እኛ ልጅ ሆነን እንወለዳለን፡፡ ሆኖም በአካል ዳጉሰን በብርሃን አንሰን እንጠፋለን፡፡ በአሰራርም በአኗኗርም አንጐለምስም፡፡
ስልጣኔ ተመኝተን፣ ከተማ ሰርተን፣ ስርአት አበጅተን ያው ነን፡፡ በጣት ከመቁጠር ደን ከመመንጠር፣ ጌሾ ከመውቀጥ፣ ቲማቲም ከመቀጥቀጥ አልወጣንም፡፡ ምስር በሰፌድ ከመልቀም ሳፋን ለገላ መታጠቢያነት ከመጠቀም፣ ሌት ፖፖ ላይ፣ ቀንም መንገድ ላይ ከመሽናት አልተላቀቅንም፡፡ መኖሪያችን ጭቃ፣ መጥረጊያችን ጨፈቃ ነው፡፡ ወለላችን እበት፣ ማገዷችን ኩበት ነው፡፡ መኝታችን ኬሻ፣ ሸክማችንም በትከሻ ነው፡፡ በታሪክ እግር በዘመን ሽግግር የኖረ ልምዳችንን ለውጠን፣ ከነባር ድህነታችን አፈንግጠን አልተራመድንም፡፡ አሁንም ወተት በእንስራ፣ አቀበት በከዘራ እንገፋለን፡፡ በመጅ ፈጭተን፣ በእጅ አቡክተን እናድራለን፡፡ መቀመጫችን አጐዛ፣ አንቡላንሳችን ቃሬዛ፤ መፋቂያችን እንጨት፣ መኮፈሻችን ፉጨት ነው፡፡ በየጉዟችን ምዕራፍ ደም አፍሰን፣ አጥንት ከስክሰን ስለጠበቅነው በር፣ ስላፀናነው ድንበር ብናቅራራም ከአድዋ የገበየነው ቅዋ፣ ከመቅደላም የተጐናፀፍነው ተድላ የለም፡፡ ትርፋችን እንቶ ፈንቶ፣ ጡረታችን ቀረርቶ ነው፡፡
ኮንጐ ዘምተን፣ ኮንጐ ጫማ ሰፍተን እናደርጋለን፡፡ ኮሪያ ዘምተን፣ ኮሌታ አብክተን እንለብሳለን፡፡ ሁልጊዜ ዕቅድ ነድፈን፣ ህልም ጽፈን ብንነሳም ከዘፈን አልፈን፣ ቁርን አርግፈን፣ መረቅ ጨልፈን አናውቅም፡፡ የምንማረው ተመራምረን ሳይሆን ተማረን ለመኖር ነው፡፡ ዲግሪ ጭነን፣ ፈተና ተጭነን እንዞራለን፡፡ ሰብሮ ከመውጣት ታግሶ መቀጣት፣ ሃሳብ ከማመንጨት ፀጉር መንጨት ይቀለናል፡፡ በወረቀት እንጂ በዕውቀት፣ በዝናብ እንጂ በምናብ አንተማመንም፡፡ በዚህም ከንስሮቻችን ዶሮዎቻችን እየገዙን፣ ከአራዶቻችን ወራዶቻችን እያዘዙን እና ከመሪዎቻችን ፈሪዎቻችን እየገረዙን ወባ እና ሌባ የሚያምሱን ልሞች፣ ጨፌ እና እጥፌ የሚጐለስሱን ደካሞች ሆነናል፡፡ ሁኔታችን ልቦናውን እንደጣለ ሰው ነው፡፡ ግልፁ ድብቅ፣ ፍሬው እብቅ፣ ጥንቡ ዘረፋ፣ ኦናው ወረፋ፣ ቀኙ ግራ፣ ሰላምታውም አተካራ ይሆንብናል፡፡ ጐፈሬውን ከልጩ፣ ምንጩን ከፍንጩ አንለይም፡፡ ቀጂ ሆነን ጥም ያንቀናል፡፡ አራጅ ሆነን ቅልጥም ይናፍቀናል፡፡
ለመለወጥ ባለን መሻት ውስጣችን ያመነ፣ አቋማችን የሰከነ፣ እርምጃችን የተካነ አይደለም፡፡ ነፍሳችን በሃሳዊ ኩራት የረጋች፣ በግለኝነት የተዘጋች፣ በምንቸገረኝነት የተወጋች ቁስለኛ ናት፡፡ ስለ ሀገራችን ከከንፈር ያለፈ ትኩረት፣ ከልብ የገዘፈ ህብረት የለንም፡፡ አንድነታችን የዕድር፣ በጀታችን የብድር ነው፡፡ ይህም አብሮ ከመተለቅ አብሮ ማለቅን ስውር ግብ ባደረገው ህይወታችን ለሽሚያ እንጂ ለቅድሚያ፣ ለመኳተን እንጂ ለመተንተን ልግመኞች በመሆናችን ውስጥ ይሰበካል፡፡ እርስበርሳችን በጋራ የምንኖር ባለጋራዎች ነንና አቋራጫችን የረዘመ፣ መፍትሔያችን የቆዘመ ነው፡፡ ከመተላለፍ መቆላለፍ ያፈጥነናል፡፡ ከመደናነቅ መተናነቅ ያከባብረናል፡፡ በዘመናችን ተመሳስሎ ማደር እንጂ ተለያይቶ መደራደር ሲያሳጣ እንጂ ሲያዋጣ ተመልክተን ስለማናውቅ፣ የብሔር እንጂ የሀሳብ ልዩነት አይገባንም፡፡ በአንድ አቅጣጫ ፈጠን፣ በአንድ ሩጫ ተመስጠን ቀርተናል፡፡ ንግግራችን የፍራቻ ምግባራችን የዘመቻ ነው፡፡ ከመወያየት መተያየት፣ ከመኮረጅ መፈረጅ ይቀለናል፡፡ ለመውደድ አደብ፣ ለመጥላት ሰበብ የለንም፡፡ ውንጀላችን ያለቦታው፣ ውዳሴያችን ያለጌታው ነው፡፡
ቅድመ አያቶቻችን ሲያልፉ፣ ምንጅላቶቻችን ሲጠፉ የተረከብነው መሪነት፣ የከረከምነው ኋላቀርነትም ሆነ ያበለፀግነው ማንነት የለም፡፡ እንዲያውም ወኔያችንን ሰልበን፣ ጠኔያችንን አራግበንና ልቦናችንን አጥብበን ቀጥለናል፡፡ ከትችት ርችት፣ ከክርክር ዝክር፣ ከንባብ የመሸታ ቤት ድባብ ደስ ይለናል፡፡ ዝንባሌዎቻችን ችግርን መልመድ፣ እርስበርስ መጠማመድ፣ ዛር ማብላት፣ ባለጉዳይ ማጉላላት፣ ወሬ ማቃጠር፣ ፀጉር መቆጣጠር የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ለችርቻሮ የሚቀርበው መብታችንም ሆነ በቀጠሮ የሚቀረው ኑሯችን አያስጨንቀንም፡፡ መሬቶቻችን የአበባ፣ መስሪያ ቤቶቻችን የስብሰባ እርሻዎች ናቸው፡፡ የቢራ ፋብሪካ እንጂ የማንበቢያ ዋርካ የለንም፡፡ እስካሁን ካነበብነው ህልዮት፣ ከተከተልነው ርዕዮትም ሆነ ካፈነዳነው አብዮት የቀዳነው ትምህርት፤ ስንኖር እንባ፣ ስንሞት ሰካራም የሚነፋው ጡሩንባ ብቻ ነው፡፡ በወሬ ጠግበን በፍሬ ተርበን ግን እስከመቼ? እስከመቼ ማለትስ እስከመቼ ነው? ትራስ ከመሆን ራስ መሆን ይሻላል፡፡
እስኪ በአዲስ አመት አዲስ ማንነት እንቀምር፤ አዲስ ህይወት እንጀምር፡፡ ከአቧራ ምኞት ከአቧራ ህይወት እንውጣ፡፡ የቤታችን ሰላምታ፣ የስራ ቦታችንም እንቢልታ ይሁን፡፡ እስኪ ወደ ብርሃን እንውጣ. ፤ውጦች እናምጣ፡፡ ጥበብ እንካፈል፣ ግኝት እንፈልፍል፡፡ ህሊናን እናድስ፣ ኑሮን እናወድስ፡፡ እስኪ በአዲስ ዓመት ለመናቆር ሳይሆን ለመፋቀር ቦታ እንስጥ፡፡ እንደ ግለሰብ መቋሚያ የሚያሲዝ እምነት ብቻ ሳይሆን እንደ ማህበረሰብ መቋቋሚያ የሚሆን እውነት እንጨብጥ፡፡ ፓርላማ ውስጥ የሚያዛጉ ብቻ ሳይሆን የሚተጉም ይለመዱ፡፡ በርቀት መነቋቆር ሳይን በቅርበት መነጋገር ባህል ይሁን፡፡ አዲስ ዓመት ሲመጣ ከአሮጌ ማንነት እንውጣ!!

 

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 13 September 2014 13:20

የዛሬ 40 ዓመት፡፡

(መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም)
… መስከረም ሁለትን ሳስብ ብዙ ነገር ወደ አዕምሮዬ ይመጣል፡፡ ደርግ ከንጉሰ ላይ ሥልጣን ከተረከበ በኋላ በየዓመቱ መስከረም ሁለት ትልቅ ክብረበአል ነበር፡፡ ወጣቱ አብዮት የሚባለውን ሲያይ መጀመሪያ አካባቢ ጉጉና ደስተኛ ነበር፡፡ በአሉም በሠራዊቱ የተለያዩ ትርኢቶች ታጅቦ፣ በየአመቱ በአብዮት አደባባይ (መስቀል አደባባይ) በከፍተኛ ድምቀት ይከበር ነበር፡፡ ወታደሩ ከ4-5 ሰአት የሚዘልቅ ትርኢቶችን ያቀርባል፡፡ በታላቁ ቤተ-መንግስትና በብሔራዊ ቤተመንግስትም በእለቱ ጓድ መንግሥቱ ኃለማርያም እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ውብአንቺ ቢሻው በተገኙበት ለሁሉም የቤተመንግስቱ ጠባቂዎች ታላቅ ግብዣ ይደረግ ነበር፡፡
መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ደግሞ ሲታወስ ደርግ አዋጁን ከተናገረ በኋላ፣ ህዝቡ የእርስ በእርስ ግጭት ጠብቆ ነበር፡፡ ከፍተኛ እልቂት ይመጣል ተብሎ ተሠግቶ ነበር፡፡ ታንኮችና መትረየስ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ይርመሰመሱ ነበር፡፡ ሰው መተያየት ፈርቷል፣ መኪናዎቹንና ታንኮቹን ቀና ብሎ ማየት ፈርቷል፡፡ ሰው በአጠቃላይ እርስ በእርስ ተፈራርቷል፡፡ ምናልባት ሌሊት አሜሪካን በአውሮፕላን ወረራ ፈጽማ ወይም እስራኤል መጥታ ንጉሱን ይወስዳሉ የሚሉ ሃሳቦች በፍራቻ መሃል ይንሸራሸሩ ነበር፡፡
ክቡር ዘበኛ እና ወታደሩ ሊጋጭ ይችላል የሚል ስጋትም ነበር፡፡ ነገር ግን ክቡር ዘበኛ ምንም የወሰደው እርምጃ የለም፡፡ የመሣሪያ ድምጽ እንኳ በእለቱ ኮሽ አላለም፡፡ መውረዳቸውን አምኖ ተቀብሏል፡፡ ይህ ባይሆን እንኳ መፈንቅለ መንግስት አድራጊው ወገን፣ ክቡር ዘበኛ ካንገራገረ ማጥቃት የሚችል ሠራዊት በቤተ-መንግስቱ በድብቅ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡
ንጉሡ ከቤተ-መንግስታቸው በደርጉ ሃይሎች ተከበው፣ በተዘጋጀችለቸው ቮልስዋገን መኪና ውስጥ ገብተው ወደ 4ኛ ክ/ጦር ሲወሰዱ፣ ብዙ ህዝብ በመንገድ ላይ ወጥቶ ይመለከት ነበር፡፡ በእድሜ ጠና ባሉት ሰዎች ላይ የማዘን ስሜት ይስተዋል ነበር፡፡ ወጣቱ ደግሞ “ሌባው! ሌባው! ሌባው!” የሚል ስድብ በፉጨትና በጩኸት እያጀበ ይሰነዝራል፡፡ ወጣቱ በጣም ይሳደብ ነበር፡፡ በተለይ ቮልስዋገኗ መስቀል አደባባይ አካባቢ ስትደርስ የነበረው ፉጨትና ጭብጨባ ልዩ ነበር፡፡
ደርጉ ዋና ዋና የሚባሉትን የመንግስት ስልጣኖች በሚገባ በቁጥጥሩ ስር ከዋለ በኋላ ስለነበር እሣቸውን ከስልጣን ያወረደው መንገዱ ሁሉ የቀና ሆኖለታል፡፡ ጃንሆይም ይህን ስለሚያውቁ በአጋዦቻቸው አማካይነት ሌላ እርምጃ ለመውሰድ አላንገራገሩም፡፡ ዝም ነው ያሉት፡፡ ወደ ቮልስዋገኗ እንዲገቡ ሲጠየቁ አላንገራገሩም፡፡ ለምን በቮልስዋገን ተወሰዱ? ተብሎ ሲታሰብ ደርግ እሣቸው መሆናቸው ሳይታወቅ እንዲሄዱ የተጠቀመበት ቴክኒክ ነበር፡፡ ተራ ሰው እንዲመስሉና ግርግር እንዳይፈጠር ነው፡፡ ነገር ግን ሰው አውቆታል፡፡ በኋላ ዳርና ዳር መትረየስ የጫኑ ጂፖች አጅበዋቸው ሲሄዱ ሰው ከፉጨትና ጭብጨባ፣ ስድብ በቀር አንዲት ጠጠር እንኳ አንስቶ አልወረወረም፡፡ በዚያ ላይ ደህንነቱ በሰው መሃል ተሰግስጓል፡፡ ወታደሩም አንዳንዱ ሲቪል ለብሷል፡፡ ጃንሆይ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ በእውነቱ ምስኪናዊ ህይወት ነው ያሳለፉት፡፡ ማንም ጠያቂ የላቸውም ነበር፡፡ የሚቀርባቸውም ሰው አልነበረም፡፡ ብቻቸውን አንድ ቤት ውስጥ ነበር የሚኖሩት፡፡ ንጉሱ ዘወትር ፊታቸውን ወደ ቤተክርስቲያኑ አዙረው ፀሎት ሲፀልዩ ስታይ በጣም ያሳዝኑ ነበር፡፡ ማንም አያናግራቸውም፤ አይጠጋቸውም ነበር፡፡ አንዲት ምግብ የምታበስል ልጅ አለች፤ እሷም ብትሆን በተወሰነ ሰዓት መጥታ ስራዋን ሰርታ ነው የምትሄደው፡፡ አርብ እና አሮብን ጠንቅቀው ይፆሙ ነበር፡፡ ልጅቱም ዘግይታ ነው ምግብ የምትሰራላቸው፡፡ ልጅቱ ልብሱን አዘጋጅታላቸው ትሄዳለች፡፡ ራሳቸው ይለብሳሉ፡፡ በዚህ መልኩ በዚያው በቤተ መንግስቱ በቀን እስረኝነት ከሰው ተገልለው ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ ህይወታቸው ማለፉ ተነገረ…
(“ህይወት በመንግስቱ ቤተ-መንግስት” የተሰኙ ተከታታይ መፅሃፎች ደራሲና የቀድሞ ልዩ ሃይል አባል ወ/ር እሸቱ ወንድሙ ለአዲስ አድማስ ከፍተኛ ሪፖርተር አለማየሁ አንበሴ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም አስመልክቶ ከሰጡት ቃለ ምልልስ የተወሰደ፡፡)

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 13 September 2014 13:20

የዛሬ 40 ዓመት፡፡

(መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም)
… መስከረም ሁለትን ሳስብ ብዙ ነገር ወደ አዕምሮዬ ይመጣል፡፡ ደርግ ከንጉሰ ላይ ሥልጣን ከተረከበ በኋላ በየዓመቱ መስከረም ሁለት ትልቅ ክብረበአል ነበር፡፡ ወጣቱ አብዮት የሚባለውን ሲያይ መጀመሪያ አካባቢ ጉጉና ደስተኛ ነበር፡፡ በአሉም በሠራዊቱ የተለያዩ ትርኢቶች ታጅቦ፣ በየአመቱ በአብዮት አደባባይ (መስቀል አደባባይ) በከፍተኛ ድምቀት ይከበር ነበር፡፡ ወታደሩ ከ4-5 ሰአት የሚዘልቅ ትርኢቶችን ያቀርባል፡፡ በታላቁ ቤተ-መንግስትና በብሔራዊ ቤተመንግስትም በእለቱ ጓድ መንግሥቱ ኃለማርያም እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ውብአንቺ ቢሻው በተገኙበት ለሁሉም የቤተመንግስቱ ጠባቂዎች ታላቅ ግብዣ ይደረግ ነበር፡፡
መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ደግሞ ሲታወስ ደርግ አዋጁን ከተናገረ በኋላ፣ ህዝቡ የእርስ በእርስ ግጭት ጠብቆ ነበር፡፡ ከፍተኛ እልቂት ይመጣል ተብሎ ተሠግቶ ነበር፡፡ ታንኮችና መትረየስ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ይርመሰመሱ ነበር፡፡ ሰው መተያየት ፈርቷል፣ መኪናዎቹንና ታንኮቹን ቀና ብሎ ማየት ፈርቷል፡፡ ሰው በአጠቃላይ እርስ በእርስ ተፈራርቷል፡፡ ምናልባት ሌሊት አሜሪካን በአውሮፕላን ወረራ ፈጽማ ወይም እስራኤል መጥታ ንጉሱን ይወስዳሉ የሚሉ ሃሳቦች በፍራቻ መሃል ይንሸራሸሩ ነበር፡፡
ክቡር ዘበኛ እና ወታደሩ ሊጋጭ ይችላል የሚል ስጋትም ነበር፡፡ ነገር ግን ክቡር ዘበኛ ምንም የወሰደው እርምጃ የለም፡፡ የመሣሪያ ድምጽ እንኳ በእለቱ ኮሽ አላለም፡፡ መውረዳቸውን አምኖ ተቀብሏል፡፡ ይህ ባይሆን እንኳ መፈንቅለ መንግስት አድራጊው ወገን፣ ክቡር ዘበኛ ካንገራገረ ማጥቃት የሚችል ሠራዊት በቤተ-መንግስቱ በድብቅ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡
ንጉሡ ከቤተ-መንግስታቸው በደርጉ ሃይሎች ተከበው፣ በተዘጋጀችለቸው ቮልስዋገን መኪና ውስጥ ገብተው ወደ 4ኛ ክ/ጦር ሲወሰዱ፣ ብዙ ህዝብ በመንገድ ላይ ወጥቶ ይመለከት ነበር፡፡ በእድሜ ጠና ባሉት ሰዎች ላይ የማዘን ስሜት ይስተዋል ነበር፡፡ ወጣቱ ደግሞ “ሌባው! ሌባው! ሌባው!” የሚል ስድብ በፉጨትና በጩኸት እያጀበ ይሰነዝራል፡፡ ወጣቱ በጣም ይሳደብ ነበር፡፡ በተለይ ቮልስዋገኗ መስቀል አደባባይ አካባቢ ስትደርስ የነበረው ፉጨትና ጭብጨባ ልዩ ነበር፡፡
ደርጉ ዋና ዋና የሚባሉትን የመንግስት ስልጣኖች በሚገባ በቁጥጥሩ ስር ከዋለ በኋላ ስለነበር እሣቸውን ከስልጣን ያወረደው መንገዱ ሁሉ የቀና ሆኖለታል፡፡ ጃንሆይም ይህን ስለሚያውቁ በአጋዦቻቸው አማካይነት ሌላ እርምጃ ለመውሰድ አላንገራገሩም፡፡ ዝም ነው ያሉት፡፡ ወደ ቮልስዋገኗ እንዲገቡ ሲጠየቁ አላንገራገሩም፡፡ ለምን በቮልስዋገን ተወሰዱ? ተብሎ ሲታሰብ ደርግ እሣቸው መሆናቸው ሳይታወቅ እንዲሄዱ የተጠቀመበት ቴክኒክ ነበር፡፡ ተራ ሰው እንዲመስሉና ግርግር እንዳይፈጠር ነው፡፡ ነገር ግን ሰው አውቆታል፡፡ በኋላ ዳርና ዳር መትረየስ የጫኑ ጂፖች አጅበዋቸው ሲሄዱ ሰው ከፉጨትና ጭብጨባ፣ ስድብ በቀር አንዲት ጠጠር እንኳ አንስቶ አልወረወረም፡፡ በዚያ ላይ ደህንነቱ በሰው መሃል ተሰግስጓል፡፡ ወታደሩም አንዳንዱ ሲቪል ለብሷል፡፡ ጃንሆይ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ በእውነቱ ምስኪናዊ ህይወት ነው ያሳለፉት፡፡ ማንም ጠያቂ የላቸውም ነበር፡፡ የሚቀርባቸውም ሰው አልነበረም፡፡ ብቻቸውን አንድ ቤት ውስጥ ነበር የሚኖሩት፡፡ ንጉሱ ዘወትር ፊታቸውን ወደ ቤተክርስቲያኑ አዙረው ፀሎት ሲፀልዩ ስታይ በጣም ያሳዝኑ ነበር፡፡ ማንም አያናግራቸውም፤ አይጠጋቸውም ነበር፡፡ አንዲት ምግብ የምታበስል ልጅ አለች፤ እሷም ብትሆን በተወሰነ ሰዓት መጥታ ስራዋን ሰርታ ነው የምትሄደው፡፡ አርብ እና አሮብን ጠንቅቀው ይፆሙ ነበር፡፡ ልጅቱም ዘግይታ ነው ምግብ የምትሰራላቸው፡፡ ልጅቱ ልብሱን አዘጋጅታላቸው ትሄዳለች፡፡ ራሳቸው ይለብሳሉ፡፡ በዚህ መልኩ በዚያው በቤተ መንግስቱ በቀን እስረኝነት ከሰው ተገልለው ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ ህይወታቸው ማለፉ ተነገረ…
(“ህይወት በመንግስቱ ቤተ-መንግስት” የተሰኙ ተከታታይ መፅሃፎች ደራሲና የቀድሞ ልዩ ሃይል አባል ወ/ር እሸቱ ወንድሙ ለአዲስ አድማስ ከፍተኛ ሪፖርተር አለማየሁ አንበሴ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም አስመልክቶ ከሰጡት ቃለ ምልልስ የተወሰደ፡፡)

Published in ህብረተሰብ