Monday, 22 September 2014 14:05

“የሆቴል ሀሁ” ይመረቃል

በአቶ ደረጀ መኮንን የተዘጋጀውና በሆቴል ዙሪያ መሰረታዊ እውቀት ያስጨብጣል የተባለው “የሆቴል ሀሁ” የተሰኘ መጽሐፍ ሰሞኑን ለንባብ የበቃ ሲሆን ዛሬ ካዛንቺስ በሚገኘው ጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ እንደሚመረቅ አዘጋጁ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡ በሆቴል ሙያ ዙሪያ በአማርኛ የተዘጋጀ የመጀመሪያው መጽሐፍ እንደሆነ የተነገረለት “የሆቴል ሀሁ”፤ 200 ገፆች ያሉት ሲሆን በ40 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

       በዶ/ር አቡሽ አያሌው የተዘጋጁት “አልፋና ኦሜጋ” ቁጥር 2 እና ቁጥር 3 መጽሐፎች ሰሞኑን ለንባብ በቁ፡፡ አዘጋጁ በ“አልፋና ኦሜጋ ቁጥር 1” መጽሐፍ፤ ስለ ሰዎችና ዩኒቨርስ የመጀመሪያና የመጨረሻ ምስጢራት ሰፊ ትንታኔ በመስጠት የጀመሩትን ሃሳብ በቁጥር ሁለትና በቁጥር ሶስት መጽሐፋቸው በስፋት እንዲቃኙት ለማወቅ ተችሏል፡፡ “አልፋና ኦሜጋ” ቁጥር ሁለት፤ ስለ እኛና ስለ ዩኒቨርስ የመጀመሪያና መጨረሻ ምስጢራት አልበርት አንስታይንና ስቴፈን ሐውኪንግ ደርሰውበታል ስለተባለው እውነት፣ ስለ 666 አስገራሚ የዩኒቨርስ ቁጥርነት፣ በድንገት ፈነዳ ስለተባለው መንፈሳዊ እሳት፣ በመንፈሳዊ ሃይል ስለተሞላው ጨለማ፣ በአስገምጋሚው እሳት ውስጥ ተፈጠረ ስለተባለው ሰማይና ምድር እንዲሁም የአልበርት አንስታይንን መሳጭ የህይወት ታሪክ ያካተተ ሲሆን በ125 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ “አልፋና ኦሜጋ” ቁጥር ሶስት መጽሐፍ ደግሞ በተለይ ከሞት በኋላ ህይወትና የፈጣሪ መኖር በኳንተም ፊዚክስ ስለመረጋገጡ፣ በነፍስ ላይ ስለተካሄዱ ልዩ ልዩ ሳይንሳዊ ጥናቶች፣ የፈጣሪን ህልውና በማያዳግም መልኩ ስላረጋገጡ 15 ትልልቅ ፍልስፍናዎች፣ በፈጣሪ መኖር ስለሚያምኑ የዓለማችን 13 ምርጥ ሳይንቲስቶች እንዲሁም ስለ ገነት፣ ገሃነም፣ መላዕክት፣ ዲያቢሎስና ፈጣሪ፤ ሳይንስ የደረሰበትን እውነታ ያስቃኛል ተብሏል፡፡ በ224 ገፆች የተቀነበበው መፅሃፉ፤ በ100 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

የቀድሞው የ“አውራምባ ታይምስ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረውና በሽብርተኝነት ተከሶ 14 ዓመት የተፈረደበት የጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ “የነፃነት ድምፆች፤ ከማዕከላዊ እስከ ዝዋይ ግዞት” የተሰኘ መጽሐፍ ሰሞኑን ገበያ ላይ ውሏል፡፡ ጋዜጠኛው በዝዋይ ማረሚያ ቤት ጨለማ ክፍል ውስጥ እንዳሰናዳው በተገለፀው መጽሐፉ፤ ክስ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የገጠመውን ከትቦበታል፡፡ መጽሐፉ ስለእስረኞች አያያዝ፣ ከፖሊሶች ጋር ስላለው መስተጋብር፣ ስለሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የአገሪቱ ትልልቅ ባለስልጣናት ከነበሩ እስረኞች ጋር ስላደረገው ቃለ ምልልስና ስለታሰረባቸው ወህኒ ቤቶች ገጽታ ያስቃኛል ተብሏል፡፡ በአራት ምዕራፎች የተከፋፈለውና 200 ገፆች ያሉት “የነፃነት ድምፆች” በ50 ብር ከ60 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡

Monday, 22 September 2014 13:50

ሁለተኛዉ

ለምን ትጽፋለህ ? የሚሉኝ አሉ
ስለሚያመኝ ነዉ።
የምጽፈዉም ሲያመኝ ነዉ።
ሲያመኝ ነጩ ወረቀት ላይ ራሴን አክማለሁ
ነጭ ወረቀት ጤና-አዳም ነዉ
ነጭ ወረቀት ዳማ-ከሴ ነዉ።
ነቢይ መኮንን
(ቁጥር ሁለት ስዉር-ስፌት)

በነቢይ ግጥሞች የሚመሰጥ አንባቢ ለኅላዌ ህመም ፈዉሱ፥ ምሱ ቅኔ መበተን መሆኑ ያስደምመዋል። ባህላዊ
ሀገራዊ ጤና-አዳም በወተት በቡና መነከሩ ቀርቶ በግጥም ሲጨመቅና ዳማ-ከሴ ቅጠሉን ሲያሹት ቀይ የመሰለዉ
ፈሳሽ ቅኔ ሆኖ ሲጠል የቃሉ ዜማ ጭምር ጣዕም አግቷል። የገጣሚዉ ህመም አካላዊ ሳይሆን ሥነዉበታዊና
ህይወታዊ መብሰክሰክ ነዉ። ግለሰብ ብቸኝነት፥ እጦት ሆነ ጥጋብ ሲያዋክበዉ፥ ወንድ ለእንስት ሲስገበገብ፥ ሴት
የኑሮ መዳፍ ሲቆረፍዳት ... ሰዉ ሲፈካ ሲጠወልግም “ጊዜም ቀን ይጐድልበታል” ብሎም “አንዱ ያንዱን ጫፍ
ሲጐመጅ” እየተጤነ እንዴት አለመታመም ይቻላል ? በየዕለቱ እየኖርነዉ ለምደነዉ የፈዘዘብን ክስተት ሆነ
ትዕይንት ነቢይን ይኮሰኩሰዋል። ግጥሞቹ አንዳንዴ ጠብታ ቃል፥ ኮሽታ እንቅስቃሴ እየቆሰቆሳቸዉ፣
ከአስተዉሎት ከኑሮ ብዙ ብዙ ይቀጣጠላል። ለመግለጥ ቢያዳግትም አንድ ረጅም ግጥሙን ያሟሸበት ሁለት
ስንኝ ዘግነን አብረን ስዉር-ስፌቱን እንበርብረዉ።

አገር የሌለዉ ህዝብ፥ ህዝብ የሌለዉ አገር
ዕንቅቡም አይሞላ፥ ወንዝም አያሻግር

ነቢይ የሆነ ትዕይንት ካደናቀፈዉ፥ የሰዉ ሁኔታ ከጓጐጠዉ፥ ጊዜ እየተንቀረፈፈ ችክ ሲልበት በአንድ ነጠላ ጉዳይ
ሣይሆን የኖረዉ፥ ያነበበዉ፥ <የታመመበት> እየደፈረሰበት እሚዋከብ ይመስለኛል። ይህ ዉስጣዊ ግርግር ሰበቡ
የአያሌ ስብጥሮች ወረራ ነዉ። አገር-ህዝብ ሲል እንደ ዜና ሳይሆን ለተለየ ህሊናዉ ለሚነዝር ትስስር እንጂ።
ምናልባት “ዕንቅብ” ሲያፈተልክበት ከግራምጣ የተበጀ ጐድጓዳና ሰፊ የእህል መስፈሪያ ተረቱንም ይጠራል።
“በዕንቅብ ያሰጣ፥ በሰፌድም ያሰጣ /እኩል ቀን ወጣ” አሻሚነቱ ያዉካል። ወንዝስ ? የሚፈስ ወራጅ ዉሃ ወይስ
ሌላ ያባብሳል ? አለማየሁ ገላጋይ በአንድ ልቦለዱ ከግንፊሌና ቀበና ወንዝ እየቀዘፈ እየዋኘ ያደገን ህፃን እሞጆ
ያሸሸዋል። ኒኮላ የተባለ ጣሊያን የዉሃ ወፍጮ የተከለበት ሥፍራ “ኒኮላ ወንዝ” ተባለ። ህፃኑ በዚህ ወንዝ
ለመንጨቧረቀ ይጓጓል። ቅኔ በሚመጥን ዘይቤ ደራሲዉ “ኒኮላ ወንዝ ዉሃዉን ከየቤቱ በጣሳ የተበደረዉ
ይመስላል” ሲል ወንዝ-አልባዉ ወንዝ ይነካካል። ህዝባዊ ተረትና ምሳሌ ለደራሽ ወንዝ ካደፈጠበት ያፈተልካል።
“ጌታዋን የምታምን ዉሻ ፍሪዳ ሲታረድ ወንዝ ወረደች” ይህ የሰባ የእርድ ከብት ከእምነት አይበልጥም። ወንዝ
እማያሻግር አገር፥ ወንዝ እማያሻግር ህዝብ፥ ዉሻ የታማኝ ሰዉ አለኝታ ሳይነፈግ ጀማዉ ጉድ ሊሆን ? እንግዲህ
ነቢይ ሽራፊ ክስተት ከቧጨረዉ በእንደነዚህ ብዙ ጨረሮች ይወረራል። ብሎም በግሪኮች ሥነተረት ሰዎች
እንደሞቱ የሚነከሩበት ወንዝ አለ፤ ምድራዊ ትዉስታቸዉን እንዲዘነጉ እንደ ጠበል ዉሃዉን ይጠጣሉ።
የሚሰቅቀዉ፥ ነፍስ ሌጣዋን ብትላላጥም የቀዬዋን ትዝታ ለመርሳት በጀ ሳትል በሆነ ልክፍት ትነዝራለች። የነቢይ
በዕዉነታ የተጣደ ሆነ ገሐድ-ዘለል ግጥሞቹን የሚያነብ “የምፅፈዉ...ስለሚያመኝ ነዉ” ሲል ካነበበዉ፥ ከኑሮዉ፥
ከአጤነዉ... በተናደ እሳቦትና ምስሎች መወረሩ ያስጨንቃል። “አገር የሌለዉ ህዝብ”በሌላ ግጥም መች ያለ አገር
ተወሰነ ?

አገሬን አገሬ እምላት
“በል በሩን መለስ አድርገዉ
አባትህ አልገባም አደል ?
ዉሃዉ አልተዘጋም እየዉ፤
ወንድምክን አንዳፍታ እቀፈዉ”፤
ያለች ዕለት ... ልክ እንደ እናት [ገፅ 64 ]
በኑሮ ወከባ እንደ የለሆሳስ ድምፅ የሰለለ የእናት ጭንቀት አገርን ወጥሮ ለመሞገት ጉልበት አለዉ - የገጣሚዉ
ምናብ አደንድኖታል።
ስዉር-ስፌት ቁ.2 የተመረቀዉ ገና ትናንት ስለሆነ በጥሞና ተላልጦ ቢነበብ የተደራሲን ጣዕመ-ፍሰት አንድም
መበረዝ፥ አንድም መገደብ እንዳይሆን አቅማማሁ፤ ከተብላላ ከተዳረሰ በኋላ እመለስበታለሁ። እንደገና የአዲሱ
ስብስብ ርዕስ ስዉር-ስፌት መባሉ በተለይም የሽፋኑ ምስልና ቀለም ለሰባት አመታት ረግቶ መክሰሙ ከነከነኝ።
ጀርባዉ ግን የራስ ምስል በሚመጥን ስዕል እና ለገብረክርስቶስ ደስታ በተበረከተ ግጥም በመወሳሰቡ አንባቢን
ክሶታል፤ ጀርባዉ ፊት በሆነና የስብስቡ ለጋ ርዕስ እምቁ ሀረግ <ሰዉ እያለ አጠገባችን> በወረሰዉና በወረሰን
ያስመኛል። ነቢይ “ጊዜም እኮ እንደ ሰዉ ፊት / ሲያረጅ ይጨማደድና /ገፁን ማድያት ይወረዋል”እያለን ለሰባት
አመት ያረጀዉን የሽፋኑን ርዕስና ምስል ማድያቱን ለምን ቸል አለዉ ? ምናልባት ቁጥር አንድ ድጋሜ ሳይታተም
ተጋርዶ ስለተሰወረ፣ አሁንም ሽፋኑ ገና አልፈዘዘ ይሆናል ከሚል ሲሜት ሊመጣ ይችላል። ቢሆንም ቁ.2
እዉስጡ የሚርመሰመሱት ሰማንያ ያክል ግጥሞች ያዉኩናል፤ እያነበብናቸዉ እንመሰጣለን። በስብስቡ ከሞት
ጋር ግብግብ ገጥሞ “ክብር ስምን” እነሎሬት ፀጋዬን፥ እነጥላሁን ገሠሠን ... ከመንደራችን የተመለሱ
እስኪመስለን ስሲሜቱ እና ዕይታዉ -የገጣሚዉ- ያባንኑናል። የአገር፥ የህይወት፥ የጥበብ ጉዳይ፥ እንደ በኩር
ዉበት በግጥሞቹ አቧራቸዉን አራግፈዉ ሲመጡብን፣ በፍቅርም በፍርሃትም በጥርጣሬም እንሞላለን።
ለየትዉልዳችን መብሰክሰክ ብሎም ዘመን ሲለወጥ፥ በአል ከተፍ ሲል እንደ አዘቦት ቀን ሳይደበዝዝ፣ ከልባችን
ከጭንቀታችን በቋንቋ ቅኝት በሚነዝር ሀቅ ይሁን ሀሰት እንሰወራለን፤ ትዉልድንና እራሳችንን እንታዘባለን።
“የኖርኩት፥ ያየሁት፥ የሰማሁት ነገር፥ የቧጠጥኩት አድማስ / ዉቅያኖስ ነዉ ህይወት፥ ተቀድቶ አይጨረስ”
ቢለንም ነቢይ የነፃነቱን አድማስ ሳይገድብ ከገሐድ ከዕዉነታ እያፈተለከ surrealistic (ዲበዕዉነታ) (ለምሳሌ
<መጻሕፍት ቤት ተዘግቶብኝ> )ግጥሞች ብቻ ሳይሆን እየረቀቀ ወደ አስማታዊ እዉነታዊነት -magical
realism- (ለምሳሌ <ለካ ሞት ግጥም አይችልም>) ዘልቆ ይፈካል። ፀደይ ወንድሙ የስብሐት ገብረ
እግዚአብሔርን <ስምንተኛዉ ጋጋታ> ስታነብ እሷ ሕልማለማዊነት የምትለዉን በsurrealism እና በአስማታዊ
እዉነታዊነት መካከል ያለዉን “ቀጭን ልዩነት” ታብራራለች። የነቢይን ግጥሞች“... ወጣ-ያለ አስተሳሰብ ያጨቁ፥
እብደቴ በፈቀደልኝና መንፈሴ እሺ ባለኝ ጊዜ የከተብኳቸዉ ...” ያላቸዉን በጥሞና ለመረዳት የፀደይን ድንቅ
ትንታኔ ማንበብ የግድ ነዉ:: [መልክአ ስብሐት፥ ገፅ 264-278]።
ዛሬ ብዙም ልነካካዉ አልደፈርኩም እንጂ በጃዝ ግጥም ምሽቶች ለመነበብ፥ በሙዚቃ ለመታጀብ፥ በመጠኑ
ግጥም መለጠጥ ስለአለበት በነቢይ ብዕር አንዳንድ ስንኙን የመበረዝ የማላላት አዝማሚያ ተጋብቶበታል። አስር
ገፅ የፈጀዉ <እነንትና ደሞ>ሳይሰለች ሁለት-ሶስት ገፅ የወጣዉ ግጥም መወጠርን፥ ትርፍ ስንኞችን ማራገፍን
ይጠይቃሉ። እንደ <ከአሮጌ ልደታ እስከ አዲስ ልደታ>የመሰለ ግጥም። የነቢይን ችሎታ የማይመጥኑ በጣም ጥቂት
ግጥሞች አምልጠዉ ተሸሽገዋል። “ነብሰ-ጡር ጊዜ እጅግ ወሩ ገብቷል / እጅግ ሆዱ ገፍቷል”የመሰለ ምስልና
እሳቦት ከግጥሙ በመትረፉ በጀ እንጂ። በደምሳሳዉ ግን የነቢይ ግጥሞች ከሀገር ቤት ጓዳኛ እምነት በታሹ
ቅላትና ሀረጐች፥ ጣዕማቸዉ በማይቸክ ረቂቅነት ከዕዉነታም ከዲበገሐድም በተወሳሰቡና በሚያባንኑ እሳቦትና
ኪነዉበት ሰርክ ይነዝራሉ።
በጥሞና እና በዝርዝር በማንበብ -እኔም ህመሜን በሂስ ልፈወስበት- የምርበተበትላቸዉ ድንቅ ግጥሞች አሉ።
<ለካ ሞት ግጥም አይችልም>፥ <ማቲን አዉቀዋለሁ>፥ <ጫፍ ወራጅ አለ>፥ <አይሳሳም ለሬሳዉ>፥
<ዜማ-አዉራጅ... >፥ <የራስክን እሳት ሙቅ>፥ <እነንትና ደሞ>፥ <ነብሰ ጡሩ ገና>፥ <አንዲት ቢራቢሮ ሆዴ
ዉስጥ ገብታ>፥ እና <ቅቤ የተቀባችዉን ልጅ ለምን ወደድኳት ?> ። እንደ ሞቆያ -ለጊዜዉ- አንድ አጭር አሳሳቢ
ግጥሙን <ያለ እኩያ መቅረት>ን በመጠኑ አብረን እናንበብለት።
ያለ እኩያ መቅረት
ከነገሬ ሁሉ እኔን ደስ የሚለኝ -ከእኩያ መጫወት።
ይሄ ሳይሆን ቢቀር -ሌላዉ ደስ የሚለኝ፥
ከእኩያ መጣላት።
አሁን ያለዉ ግና፥ አለመታደል ነዉ -የመርገምት መርገምት፥
ሁለቱን ፈልጐ፥ ሶስት ነገር ማጣት።
የሚያፈቅሩት ሲያጡ
የሚጣሉት ሲያጡ
ራስን ቢለምኑት፥
<እኩያህን ፈልግ !> ብሎ ራስም ጥፍት !
አያድርስ እንጂ ነዉ፥
እንዲያ ያለ ረሀብ፥ የኑሮ ዉድነት
እኩያን ጨርሶ፥ ያለእኩያ መቅረት !!
[በገዛ እጃቸዉ እኩያ ላጡ] ገፅ 94
ግለሰብ አልያም ግራ የተጋባ ነፍስ ለፍቅርም ለፀብም <እኩያ> ተነፈጐ በአባዜ ተቦረቦረ፤ ባዶነት፥ ለብቻ
መቅረት፥ከጀማዉ መሸሽ ይለመዳል እንዴ? ለኛ የመጨረሻ መጠለያ፥ የክፉ ቀን ምሽግ እራሳችን ነን። በቋጠርነው
ትዝታ፥ በአስተሳሰብ፥ በእድሜ ... ከሚመጥነን (እንደ ብልህ እንደ ጅል) ጊዜን ለማባበል <እኩያ> ያስፈልገናል።
ለብቻ ከመንገዳገድ፥ ለብቻ ከመሳቅ፥ ከራስ ላለመላተም ካባሰበት ሳይሆን ከአቻ ባልንጀራ መጫወትም
መጣላትም ያምረናል። ይህ ንፍገት ባለቅኔዉን እምብዛም አልቆረቆረዉም፤ የተፈታተነዉ ከራስ ጋር ለማዉጋት
ለማበድ ህሊናችን ዉስጠታችን ፊት ነስቶን <እኩያህን ፈልግ!> ተብለን መገፍተራችን ነዉ። ባይተዋርነት እራስን
መጥላት፥ ከራስ ጋር እኩያ የአለመሆን ሥነልቦናዊ ቀዉስ ግለሰብን ያሳድደዋል። በሌላ ግጥሙ ነቢይ እንደ
ተቀኘዉ “ምን ጫፍ አለ? ምንስ ወራጅ / አንዱ ያንዱ ጫፍ ሲጐመጅ // ጫፍ ወራጁን ሲጠብቁ / የራስ
መዉረድ ጣር ነዉ ጭንቁ”ከሌላዉም ከራስም መንገዳችን ላይ “እንደ ጨፈቃ ተሳስረን” ያለ እኩያ እየተጋፋን
መኖር ሰቆቃነቱ በቀልድም በምርም ይመዘምዛል። ሰባ አመቷን የዘለለች ፖላንዳዊት ባለቅኔ - ሽምቦሪስካ -
<ቁጥር ፍለጋ ተራ ከሚጠብቁ ዜሮዎች ይልቅ ብቻቸዉን የቀሩ ነፃ ዜሮዎች እመርጣለሁ:: > ትላለች:: ዜሮና ዜሮ
መደርደር:: ነቢይ ግን ለዜሮ በተመስጦ <እኩያ>ቁጥር እያፈላለገ ነዉ::
ስዉር-ስፌትን (ቁ2.) ስናነብ ልብ ለማንለዉ ክስተት ሆነ ትዕይንት እንነቃቃለን። ስሙን የዘነጋሁት ደራሲ
እንዳለዉ፤ “Each person carries within him the soul of a poet who died young” እንደ አንባቢ
የአንድ ሟች ግጥም መንፈስ እዉስጣችን የሚፀድቀዉና ለዉበት የምንደመመዉ ነቢይ መኮንንን ለመሰሉ
ባለቅኔዎች መመሰጥ ስንችል ነዉ።

 

Published in ጥበብ
Monday, 22 September 2014 13:48

እንቁጣጣሽ

ጀማል ከዕንቅልፉ ማልዶ ተነሳ፡፡ በእንቁጣጣሽ ቀን አርፍዶ መዋል አልፈለገም፡፡ ለወትሮው እንቅልፍም ቢሆንም
ዛሬ ግን ስራ አለሙ፡፡ ትላንት በዋዜዋማው ቸበርቻቻ ከተመነዘረው ብር የቀሪውን ለማየት ኪሱን ዳበስ፡፡ አስር
ብር ብቻ ነበር የቀረው፡፡
ገንዘብ ሊያገኝ የሚችልበት ምንም ጭላንጭል አልታይህ ስላለው ተስፋ ቆርጧል፡፡ የሚተዳደረው ከሴት አያቱ
ከወረሰው ሶስት ክፍል ቤት ሁለቱን በማከራየት ሲሆን እሱንም ቢሆን ኪራዩን ለበቅድምያ ተቀብሎ ስለጨረሰው
ተከራዮቹን ገንዘብ መጠየቅ የማይሞከር እንደሆነ ያውቃል፡፡ ከቤት ኪራዩ ውጭ ሌላው የገንዘብ ምንጩ
ተማሪዎችን እንግሊዝኛ በማስጠናት የሚያገኘው ገቢ ነበር፡፡ እሱም ባለፉት ሶስት የክረምት ወራት ትምህርት
ቤቶች ዝግ ስለነበሩ ደርቋል፡፡ ሶስተኛውና አልፎ አልፎ የሚሰራው የገንዘብ ማግኛ ዘዴው “ወዲህ በሉ” ማለት
ሲሆን ይሄም ዛሬ እንደማይሰራ ግልፅ ሆኖ ታይቶታል፡፡ ምክንያቱም በሱ አነጋገር ሰው ሁሉ ተፈልጦ አልቋል፡፡
አዲሱን ዓመት እንደሰው በልቶ ጠጥቶ፣ ተደስቶና ተዝናንቶ እንደማያሳልፍ ሲያስብ ከዓለም ተገልሎ ብቻውን
የቀረ መስሎ ተሰማው፡፡ ጀማል ታጣፊ አልጋው ላይ እንደተቀመጠ ቤቱን ቃኘ፡፡ የሚሸጠው እቃ እንዳለ
ማጣራቱ ነበር፡፡ አንድ እግሩ የወለቀም ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠ አሮጌ ፊሊፕስ ሬዲዮና አያቱ ቡና ሲያፈሉበት
የነበረው ትልቅ ጀበና ብቻ ነበር አይኑ ውስጥ የገባው፡፡
ነፍሳቸውን ይማርና አያቱ የእንቁጣጣሽ ዕለት ጠዋት በማለዳ ተነስተው ነበር ጉድ ጉድ የሚሉት ብዙ ጊዜ፡፡ ቡና
ሲቆሉ ከእንቅልፍ ይነቃል፡፡ እየተነጫነጨ ነው፡፡ ከአልጋው የሚነሳው የሚነጫነጨው አንድም በማንከሻከሽ
በሚቆላው ቡና ድምፅ እንቅልፉን ሳይጠግብ ስለሚነሳ ሲሆን ሌላው አያቱ በባዶ ሆዱ ሆዱ እስኪገላበጥ ደረስ
የሚጎመዝዘውን የፌጦ ፍትፍት በግድ ስለሚያጎርሱት ነበር፡፡ ቡናቸውን ሲያፈሉ ታዲያ በስርአት ነበር፡፡
ከረከቦቱ ጎን ካለ ሰፌድ ላይ የማሽላ ፈንዲሻ፣ ኑግና ከረሜላ አይጠፋም፡፡ ማጨሻው ላይ ቀበርቾና የባህር ዕጣን
ቤቱ የተቃጠለ እስኪመስል ድረስ ይጨሳል፡፡ የህንን ሲያደርጉ ታዲያ ነጭ የሐበሻ ቀሚሳቸውን ለብሰው ከላይ
ቀይ ድርያ ጣል አድርገው ነው፡፡ ቡናውን ሲቀዱ ጀማል እንደተገረፈ ህፃን ልጅ አፏን ለጉሞና እጁን አጣምሮ
ይቀመጣል፡፡ ይህንን ካላደረገ ምን እንደሚከተለው ያውቃል፡፡
“ምን ይንከወከዋል ይሄ ቀልበ ቢስ” ካሉ በኋላ የእርግማን መዓት ያወርዱበታል፡፡ እሳቸውን የሚያመለኩትንና
“ደምና ፈርስ ሳይነካህ ሆድ ውስጥ ገብተህ የምትወጣ ያባት የናቴ አምላክ” እያሉ የሚለማመኑት አውልያቸውን
እየፈራ ነበር ያደገው፡፡
በእድሜ ሲጎለምስ በእውቀት ሲበስልና ቅዱሱን መጽሐፍ ቃል በቃል እስኪያስታውስ ካጠና በኋላ ነበር “እኔ
አንድ አምላክ ነኝ፡፡ ከኔ ሌላ አታምልክ” የሚለው ፈጣሪ ቃል ውስጥ የገባው፡፡ ያኔ ነበር አያቱ በባዕድ አምልኮ
የተተበተቡ መሆናቸውን የተረዳው፡፡
“ይሄ ጀበና ነው የኔ ጠላት” ሲል አልጎመጎመ ለብቻው፡፡ የአያቱ ባዕድ አምልኮ መንፈስ በዚህ ጀበና ላይ አርፎ
ህይወቱን እንዳጨለመው አሰበ፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጨለማ መንፈስ ተላቆ የፈጣሪውን በረከት ለማግኘት ጀበናውን
ከዚህ ቤት አርቆ መወርወር እንዳለበት ወሰነ፡፡
ትላንት በዋዜማው ከጓደኞቹ ጋር አሸሼ ገዳሜ ሲልና የነበረችውን ገንዘብ ሲያጠፋ ወ/ሮ ፀሐይን ተስፋ አድርጎ
ነው፡፡ ወ/ሮ ፀሐይን የእንቁጣጣሽ ቀን ቢጎበኛቸው እንዴት ደስተኛ እንደሚሆኑ ተሰምቶት ነበር፡፡ ታዲያ እግረ
መንገዱን ሁለት መቶ ብር ቢበደራቸው በዓሉን በደስታ አሳለፈ ማለት ነው፡፡
ወ/ሮ ፀሐይን የሚያውቃቸው ሁለቱ ልጆቻቸውን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ሲያስጠና እቤታቸው ሲሄድ ነበር፡፡
ከደሞወዙ ውጭ ለታክሲ እያሉ የሚሰጡት ጉርሻ ሶስት ቀናት የሚያውል ነበር፡፡ ወ/ሮ ፀሐይ ሞልቶ የተረፋቸው
ሴት ስለሆኑ ሁለት መቶ ብር ለሳቸው ሁለት ብር ማለት ነው፡፡
ለመጨረሻ ግዜ ያያቸው የዛሬ ሁለት ዓመት ሲሆን ድሮ ከነበሩበት ሰፈር ወደ ፍልውሐ አካባ ቤት እንደቀየሩ
ሰምቷል፡፡ አዲሱን ቤታቸውን ባያውቀውም ስልካቸው ስላለው ደውሎላቸው ይሄዳል፡፡ ከሁሉም በፊት ግን
ይሄን አጋንንታም ጀበና ድራሹ ማጥፋት አለበት፡፡
ጀበናውን አንስቶ ከቤት ወጣና ወደ ፍልውሃ የሚወስደውን ታክሲ ያዘ፡፡ ታክሲ ውስጥ እንዳለ ለወይዘሮ ፀሐይ
ደውሎ እንደሚመጣ ነገራቸው፡፡ ቤታቸውን በምልክት ከነገሩት በኋላ በመምጣቱ ደስ እንደሚላቸው በሰለለ
ድምፅ ነገሩት፡፡ ስልኩን ሲዘጋ ድምጻቸው እንደወትሮው እንዳልነበረ አስተዋለ፡፡
ፍልውሃ ፖስታ ቤቱ ጋ እንደወረደ መደዳውን የባህል እቃ መሸጫ ሱቆች ባሉበት ቀጭን መንገድ ወደ አምባሳደር
አቀና፡፡ ወደ ወይዘሮ ጸሐይ ቤት ከመሄዱ በፊት ጀበናውን ሲኒማ ቤቱ ፊት ለፊት ያለው ወንዝ ውስጥ ለመጣል
አስቧል፡፡ አንዲት ወርቃማ ፀጉር ያላት የሐበሻ ቀሚስ የለበሰች ፈረንጅ ከአንዲት ዘመናዊ አለባስ ከለበሰች
ወጣት ሴት ጋር በመንገዱ እያለፉ ነበር፡፡ ጀማል የሐበሻ ቀሚስ የለበሰች ፈረንጅ አይቶ ስለማያውቅ በመገረም
ሲያት እስዋም በፈገግታ አተኩራ እያየችው ተላለፉ፡፡ ጥቂት እርምጃዎችን እንደተራመደ ነበር “ወንድም” የሚል
የጥሪ ድምፅ የሰማው፡፡ የጠራችው ከፈረንጇ ጋር የነበረችው ወጣት ሴት ነበረች፡፡
ዝግ ባለ እርምጃ ወደነሱ ተጠጋ፡፡ ሁለቱም ሞቅ ባለ ፈገግታ እያዩት በአክብሮት እጃቸውን ለሰላምታ ዘረጉ፡፡
“ሊንዳ ትባላለች፡፡ ከአውስትራልያ የመጣች ጓደኛዬ ነች፡፡ ሜልቦርን ውስጥ የአፍሪካን ባህል የሚያሳይ
ሬስቶራንት ከፍታለች፡፡ የዚህ አይነት ትልቅ ጀበና አይታ አታውቅም፡፡ የት እንደሚገኝ ልትነግረን ትችላለህ?”
ስትል ጠየቀችው ፈገግ እያለች፡፡
“አዲስ አበባ ውስጥ እንኳን ያለ አይመስለኝም፡፡ ድሮ አያቴ ከትግራይ ይዘውት የመጡት ነው፡፡ ስልክ
ከሰጣችሁኝ አጠያይቁ ላስመጣላችሁ እችላለሁ፡፡” አለ፤ አዲስ የቢዝነስ ሐሳብ ጭንቅላቱ ውስጥ እየታው፡፡ በጣም
የሚገርምህ ነገር ዛሬ ማታ ነው ወደ አገርዋ የምትመለሰው፡፡ ተመልሳ የምትመጣው ደግሞ ከሁለት ኣመት በኋላ
ነው አለችው አይኖችዋ አይኖቹን እየተሰማመጡ፡፡
“አይ ታዲያ ምን ይሻላል?” አለ በማስተዛዘን፡፡ በልቡ ግን “ልጥለው አልነበር?” ብሰጣቸውስ!” የሚል ሐሳብ
መጥቶበታል፡፡
“ደፈርሽኝ አትበልና ትሸጠዋለህ?” የፈለግከውን እንከፍላለን”
ጀማል አሁን ባነነ፡፡ ሴቶቹ ጀበናውን በጣም ይፈልጋሉ፡፡ እሱ ደግሞ ገንዘብ ስፈልገዋል፡፡ እዚህ ላይ ጭንቅላቱን
መጠቀም አለበት፡፡
“እንደዚያ እንኳን አልችልም፤ የአደራ እቃ ነው”
“ገዝተህ ልትተካላቸው ትችላለህ”
“እንደዚ ከባድ ነው I am sorry – I cant” አለ በእንግሊዝኛ
ፈረንጅዋን እያየ፡፡
“I will give you one hundred” አለች ፈረንጅዋ ቦርሳዋን እየከፈተች፡፡ ጀማል ልቡ መታ፡፡ ሴትየዋም
ጀበናውን ፈልጋለች፡፡ እሱ ደግሞ ሁለት መቶ ብር ለዓመት በዓል ያስፈልገዋል፡፡
“Two hundred” አለ የመጣ ይምጣ ብሎ፡፡ ፈረንጇ ትኩር ብላ ካየቸው በኋላ ፈገግ አለችና ቦርሳዋን መበርበር
ጀመረች፡፡ ገንዘቡን አውጥታ ስትሰጠው ያየውን ማመን አልቻለም፡፡ ሁለት መቶ የአሜሪካን ዶላር!
ጀበናውን ሰጥቷቸው፣ ሃሳባቸውን ቀይረው ፖሊስ ጠርተው እንዳያስይዙት እየፈራ ልቡ እየመታ መንገዱን
ተያያዘው፡፡
“Thank you God bless you” የሚለው የፈረንጅዋ ድምፅ ይሰማዋል፡፡ በፍጥነት ወደ አምባሳደር ሲቆለቁል
እንደ ዕድብ ብቻውን እየሳቀ ነበር፡፡
በወንዙ በኩል ሲልፍ ጀበናውን እዚያ ሊጥለው አስቦ እንደነነበር አስታወሰና ሁለት መቶ ዶላር ከመጣል
ያዳነውን አምላኩን አመሰገነ፡፡ ፈጣሪው እያስተማረው እንደሆነ የገባው ዶላሩን ሲመነዝር ነበር፡፡ ባዕድ አምልኮ
አስወግዶ ፈጣሪውን ብቻ በማየቱ የተሰጠው ሽልማት እንደሆነ አውቆዋል፤ ሶስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ብር ኪሱ
ሲከት፡፡
ወይዘሮ ፀሐይ ቤት የመሄዱን ነገር አልተወውም፡፡ አሁነ በያዘው ገንዘብ ላይ ሌላ ሁለት መቶ ብር ቢጨመርበት
ምን ይጎዳዋል? ሴትየዋንም በእንቁጣጣሽ ቀን መጠየቁ ደግ ተግባር ነው፡፡
የሰጡትን ምልክት እስታወሰ መስጊዱን አልፎ በስጋ ቤቶቹ አቋርጦ ፀጉር አስተካካይ ቤቱን አልፎ የቦይ ውሃ
ያለበት አጠገብ ሲደርስ ቆም አለ፡፡
እንደተሳሳተ ገምቶዋል፡፡ እንዴት ወ/ሮ ጸሐይን የመሰሉ ሴት እዚህ ቤት ውስጥ ይኖራሉ? የሚል ጥያቄ
መጥቶበታል፡፡
ፈራ ተባ እያለ አንዱን ጎረምሳ ያውቃቸው እንደሆን ጠየቀው፡፡ ሰማያዊ የእንጨት በር ያለው ቤት እንደሆነ
ነገረው፡፡
“ይሄ ቤት?” ሲል ጠየቀ በመገረም፡፡
ጎረምሳው በእርግጠኝነት ጭንቅላቱን ነቀነቀ፡፡
በሩን አንኳኩቶ ገባ፡፡ ሴትዮዋ አሮጌ ብርድልብስ ተከናንበው አልጋ ላይ ተኝተዋል፡፡ ፊታቸው ገርጥቶዋል፡፡
ከተኙበት አልጋና ከአንድ አሮጌ የዕቃ መደርደር በስተቀር ሌላ ዕቃ ክፍሉ ውስጥ የለም፡፡ ሰላምታ ሰጥቶዋቸው
ተቀመጠና ምን እንዳገኛቸውና ለምን እንደዚህ እንደሆኑ በሐዘንና መገረም በተቀላቀለበት ድምፅ ጠቃቸው፡፡
ምኑን ልንገርህ ልጄ! ሰውየው በሐሰት ማስረጃ ከስሶ ቤቴን ወሰደው፡፡ ልጆቼንም አልሰጥሽ አለኝ፡፡ ገንዘቤ
የጠበቃ ሲሳይ ሆነ፡፡ እስሩም እንደዚህ ጨረሰኝ፡፡
መድሐኒት መግዣ እንኳን አጣሁ፡፡ ፈጣሪን የፈራ ሰው በሚጥልልኝ ምፅዋት ህይወቴን እየገፋሁ ነው ልጄ አሉት
እንባ እያደናቀፋቸው፡፡ እጁን ወደ ኪሱ ላከና ሁለት መቶ ብር አውጥቶ ሰጣቸው ከሳቸው ቤት ወጥቶ ወደ
ታክሲው መያዣው ሲያመራ “የሚመካ በእግዚአብሄር ይመካ” የሚል ጠቅስ የፀጉር አስተካከይ ቤት መስተዋት
ላይ ተለጥፎ አይቷል፡፡

Published in ልብ-ወለድ

በአለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ ወደ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ሲፈጸም ይህም
ከ10/እርግዝናዎች አንድ ደህንነቱ ያልተጠበቀ እርግዝና እንደሚከወን ያሳያል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚያጋጥሙት ጽንስ ማቋረጦች 1/3ኛ የሚሆኑት ደህንነቱ ያልተጠበቀ ነው፡፡
90 % የሚሆነው ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ የሚፈጸመው በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ነው፡፡
ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ በአለም አቀፍ ደረጃ ከ70-200 ሺህ ለሚሆኑ እናቶች ሞት
ምክንያት ነው፡፡
..ምንጭ (WHO, Alan Guttmacher Institute, and Family Health International)
ከላይ የጠጠቀሱት ምንጮች ጨምረው እንደገለጹት ለበርካታ ዘመናት ማለትም እስከ 1800ዎቹ ድረስ ጽንስን
ማቋረጥ በአለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ መንገዶች ይካሄድ ነበር፡፡ ነገር ግን በሁሉም ቦታዎች የሚካሄደው
በህገወጥ መንገድ ነበር፡፡ የባህል ሕክምና የሚያደርጉ ሰዎች እራሳቸው ድርጊቱን ከመፈጸማቸው ባሻገር ሌሎች
ሰዎችንም እያሰለጠኑ እርስ በእርሳቸው እንዲረዳዱ ያደርጉ ነበር፡፡ ነገር ግን በህገ ወጥ ጽንስ ማቋረጥ ምክንያት
ለህልፈት የሚዳረጉት ሴቶች ቁጥር እያደገ በመምጣቱ አለምአቀፉ ህብረተሰብ ድርጊቱ በህግ የታገዘ እንዲሆንና
በዚያም መሰረት ሆስፒታሎች እና የጤና ተቋማት የሴቶቹን ደህንነት በጠበቀ መልኩ ጥንቃቄ የተሞላበት እና
ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስን ማቋረጥ እንዲፈጽሙ ህግ እንዲወጣ ምክንያት ሆኖአል፡፡ ስለሆነም ብሪ..ይን በ1803
ዓ/ም ለመጀመሪያ ጊዜ ህጉን አወጣች፡፡ ከዚያ በሀዋላ በአለም ላይ የተለያዩ ሐገራት በየደረጃው ጥንቃቄ የጎደለው
ጽንስን ማቋረጥ ተግባር እንዲወገድ ህግ አውጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉን ሲያሻሽል ከሰኔ 1/97 ጀምሮ በስራ ላይ የሚውል
የወንጀል ሕግ በአዋጅ ቁጥር 414/96 አውጥቶአል፡፡ ተሸሽሎ የወጣው ሕግ ካካተታ ቸው ጉዳዮች መካከል
ጽንስ ማቋረጥን የሚመለከት ይገኝበታል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስ..ርም በዚህ ሕግ መሰረት የአሰራር መመሪያውን
ቀርጾ ከሰኔ 1998 ዓ/ም ጀምሮ በተግባር ላይ እንዲውል አድርጎአል፡፡
ቁ.3. የወንጀል ሕጉ ድንጋጌ ፣
በአንቀጽ 551 መሰረት .. ፅንስን ማቋረጥ በህግ የተፈቀደባቸው ሁኔታዎች..
1. በሕክምና ሙያ በተፈቀደ የጊዜ ገደብ ውስጥ በህክምና ተቋም ጽንስ ሲቋረጥ በወንጀል
የማያስቀጣው፣
ሀ. በመደፈር ወይንም በዘመድ መካከል በተደረገ የግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት ጽንሱ የተገኘ ሲሆን፣
ለ. የእርግዝናው መቀጠል በእናቲቱም ሆነ በፅንሱ ሕይወት ወይንም በእናቲቱም ጤንነት ላይ አደጋ
የሚያስከትል ሲሆን ወይንም የልጁ መወለድ በእናቲቱ ጤንነት ወይንም ሕይወት ላይ አደጋ የሚያመጣ ሲሆን፣
ሐ. ጽንሱ ሊድን የማይችል ከባድ የአካል ጉድለት ያለው (ዲፎርምድ) ሲሆን ወይም
መ. አንዲት እርጉዝ ሲት የአካል ወይንም የአእምሮ ጉድለት ያለባት በመሆንዋ ወይም ለአካለ መጠን ያልደረሰች
በመሆንዋ የሚወለደውን ህጻን ለማሳደግ የህሊናም ሆነ የአካል ዝግጅት የሌላት ሲሆን ነው፡፡
የኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሰኔ 1998 አዲስ አበባ
እንደውጭው አቆጣጠር በ2003 ዓ/ም ጤና ጥበቃ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ አንድ
ሶስተኛው የእናቶች ሞት ምክንያት በህገወጥ መንገድ ጽንስን ማቋረጥ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በአመት ወደ 22 ሺህ
እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የሚሞቱ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ እድሜያቸው ከአስራ አምስት አመት እስከ
አርባ ዘጠኝ አመት የሚገመቱ ስምንት ሺሕ ያህል እናቶች በህገወጥ ውርጃ ምክንያት ለህልፈት እንደሚዳረጉ
ተረጋግጦአል፡፡ በእርግጥ በትክክል ተጠቃሽ ሊሆኑ የሚችሉ ጥናቶች ባይኖሩም ከየሆስፒታሉ ከሚሰሙ ሪፖርቶች
እንዲሁም አልጋ ከያዙ ህመምተኞች ሁኔታ ከሚገኙ መረጃዎች በመነሳት ህገወጥ ውርጃ ድርጊቱ በመጠኑ እየቀነሰ
ሄዶአል ማለት ያስችላል፡፡ ለህገወጥ ውርጃው መቀነስ እንደ አንድ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሰው ህጉ ላይ መሻሻል
መደረጉ ነው፡፡
ዶ/ር ሰሎሞን ቁምቢ /በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር/
በዚህ እትም ለንባብ ያቀረብነው ጽንስን በማቋረጥ ተግባር ላይ የሚያተኩረው ሕግም ሆነ መመሪያው ከወጣ
ጀምሮ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው አጠቃቀም እና በሕክምና ተቋማቱ ዘንድ ያለው አሰራር ምን ይመስላል?
የሚለውን በሚመለከት ይሆናል፡፡ በምንጭነት የምናቀርባቸው ባለሙያዎች ዶ/ር ደመቀ ደስታ በአይፓስ
ኢትዮጵያ ሲኒየር አድቫይዘር ፣ዶ/ር ጌትነት በቀለ በርጌስ ክሊኒክ ባለቤትና የህክምና ባለሙያ ከተክለሀይማኖት
ጠቅላላ ሆስፒታል ሲ/ር ነጻነት አባተ እና ከበርጌስ ክሊኒክ ሲ/ር አበባ ስለሺ ናቸው፡፡
እንደ ዶ/ር ደመቀ አገላለጽ ኢትዮጵያ በአለም በተለይም ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ብዙ እናቶች
ይሞቱባታል ተብለው ከሚጠቀሱት አገራት መካከል ናት፡፡ 100.000/ አንድ መቶ ሺህ/ ከሚሆኑ በህይወት
ከሚወለዱ ሕጻናት ወደ 673/ የሚሆኑ እናቶች ባጠቃላይ ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን ያጡ የነበረ
ሲሆን ለሞት ምክንያት ከሚሆኑት ውስጥ አንዱ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስን ማቋረጥ ነበር፡፡ ደህንነቱን
ያልጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ 32 ኀ ለሚሆነው የእናቶች ሞት ምክንያት ነበር፡፡
ዶ/ር ጌትነት በቀለ የበርጌስ ክሊኒክ ባለቤትና የህክምና ባለሙያ እንደሚሉት
‹‹....በአብዛኛው ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስን ማቋረጥ የህክምና አገልግሎት የምንሰጠው እስከ 12/ ሳምንት ወይንም
ሶስት ወር ድረስ ያለውን እርግዝና ነው፡፡ ይህንንም ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት ሕጉ
በሚፈቅደው መሰረት ልምድ ባላቸው የህክምና ባለሙያዎች አማካኝነት በተሟላ መልኩ እንሰጣለን፡፡
ይህንን አገልግሎት በሚመለከት ካለፉት ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር ብዙ ልዩነቶች ይታዩበታል፡፡ አይፓስ እና
ሜሪስቶፕስ ለህክምና ባለሙያዎቹ ከሚሰጡት ስልጠና ባሻገርም አገልግሎቱን የምን ሰጥበትን ቁሳቁስ የሚረዱን
በመሆኑ ብዙ የተሻሻለ ነገር አለ፡፡ዛሬ ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥን በሚመለከት ከየትኛው ሆስፒታል
ወይንም ክሊኒክ ልሂድ ብሎ መጨነቅ አይገባም፡፡ ስልጠናው በሁሉም ቦታ እየተሰጠ ስለሆነ በተለይም በአዲስ
አበባ ውስጥ ከ56/ ክሊኒኮች በላይ ተጠቃሚዎችን በማስተናገድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም አገልግሎቱን
ተጠቃሚዎችም አውቀውታል የሚል ግምት አለኝ፡፡››
ሲ/ር ነጻነት አባተ ከተክለሀይማኖት ጠቅላላ ሆስፒታል ያነጋገርናት አዋላጅ ነርስ ናት፡፡
‹‹ ...በሆስፒታላችን ውስጥ በወር ውስጥ ከ30-50/ የሚሆኑ ሴቶች ጽንስን የማቋረጥ አገልግሎት ሊያገኙ
ይመጣሉ፡፡ለሕክምና የሚመጡት ሴቶች አብዛኞቹ ውርጃው በተለያየ ምክንያት ጀምሮአቸው ደም እየፈሰሳቸው
የሚመጡ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ተገዶ ከመደፈር ወይንም ከተለያዩ በህግ ላይ ከሰፈሩ ምክንያቶች ፣ከተፈጥሮ
ሁኔታ ጋር በተያያዘ እርግዝናው እክል ገጥሞት ጽንሱ እንዲቋረጥላቸው የሚመጡ ናቸው፡፡ ይህንን አገልግሎት
የሚፈልጉት ሴቶች በእድሜ ሲለዩ ከ19-20 አመት የሚሆኑ ወጣቶች ይበዛሉ፡፡ ይህም የሚያመለክተው ብዙዎቹ
ወጣቶች እርግዝናውን ያልፈለጉ ሲሆኑ ምክንያታቸውም መከላከያውን አለመውሰድ ወይንም ተገደው
በመደፈራቸው እና ሌሎችም ልጁን ወልደው ሊያሳድጉ የማይችሉበት ሁኔታ ላይ ያሉ ናቸው፡፡ አንዲት ሴት
ጽንስ ማቋረጥ ስለፈለገች ብቻም ጽንስ አይቋረጥም፡፡ አንዲት ሴት ጽንስ እንዲቋረጥ ጥያቄ ስታቀርብ በተደነገገው
ህግ እና በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስ..ር አማካኝነት ህጉን ተንተርሶ በወጣው መመሪያ መሰረት ይሆናል
የምትስተናገደው፡፡››
ቁ.3. የወንጀል ሕጉ ድንጋጌ
በአንቀጽ 551 መሰረት ‹‹ፅንስን ማቋረጥ በህግ የተፈቀደባቸው ሁኔታዎች››
2. በአንቀጽ 551 ንዑስ ቁጥር 2 ስር በፍጥነት በሚደረግ የህክምና ስራ ካልሆነ በስተቀር ሊወገድ
የማይችል ከባድና ጊዜ የማይሰጥ አደጋ ሲያጋጥም የሚፈጸም የጽንስ ማቋረጥ አያስቀጣም፡፡
በአንቀጽ 552..2.. ስር ደግሞ የሚከተለው ተደንግጎአል፡፡
..በአንቀጽ 551..1..ሀ በተገለጹት ምክንያቶች ሴትየዋ መደፈሯን ወይም ከቤተዘመድ መፀነሷን መግለጽዋ ብቻ
ፅንስ ለማቋረጥ በቂ ይሆናል..
ሕብረተሰቡ ጽንስን በማቋረጥ ሂደት ላይ ምን ተገንዝቦአል? በመንግስት የጤና ተቋማት እና በግል የህክምና
ተቋማት መካከል ያለው የሪፈራል አተገባበር ምን ይመስላል? የእናቶች መጎዳት ምን ያህል ቀንሶአል ?
ይቀጥላል

Published in ላንተና ላንቺ
Saturday, 20 September 2014 11:58

አያ ታሪኩ

የጐንደሩ “በለአም”

      በለአም በምድረ እስራኤል የኖረ ኦሪታዊ ነቢይ ነው፡፡ አያ ታሪኩ ደግሞ ከጣሊያን ወረራ ጀምረው ጐንደር ከተማ
በተለይ “ፒያሳ” ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ነዋሪ ናቸው፡፡ በለአም በረከተ መርገም የተሰጠው ነቢይ ነበረ፡፡ አያ
ታሪኩም በረከተ ዘለፋ ወእርግማን የተሰጣቸው ይመስላሉ፡፡ በለአም እየዞረ የሚረግምባት አንዲት አህያ
ነበረችው፡፡ አያ ታሪኩም ከፋኖ ዘመን ጀምረው ቁጭ የሚሉባት አንዲት ስሞተኛ ወንበርና አሮጌ ሲንጀር የልብስ
ስፌት መኪና አሏቸው፡፡
በለአም በያገሩ እየዞረ ይራገም ነበር፡፡ አያ ታሪኩም ፒያሳ ቁጭ ብለው አላፊ አግዳሚውን፣ ወጭ ወራጁን
እድሜና ጾታ ሳይለዩ ይራገማሉ፡፡ ልዩነት ቢኖር በለአም የረገመው ይረገማል፤ የመረቀውም ይመረቃል፡፡ አያ
ታሪኩ ግን እርግማን እንጅ ምረቃ ከአፋቸው ወጥቶ እንደማያውቅ አብረዋቸው የኖሩ ጐንደሬዎች ይመሰክራሉ፡፡
አያ ታሪኩን በተለይ አዛውንት እጅግ ይፈሩዋቸዋል፡፡ ደብር ደርሰው ሲመለሱ ወይም ወደ ሌላ ቦታ ሲሄዱም ሆነ
ሲመጡ ድንገት አያ ታሪኩን ካዩ መንገድ አሳብረው መሄድ ይመርጣሉ፡፡ በአካል ኮሰስ ብለው የሚታዩት አያ
ታሪኩ ግን ምናቸውም አያስፈራም - ያው አምሳ አንድ አመት ሙሉ የማይደክመው ምላሳቸው ብቻ እንጂ!
የጐንደሩ በለአም እርግማን ከጀመሩ ገላጋይ ቢገባ እንኳ የእርግማኑ በረከት ይደርሰው እንደሆነ እንጅ እሳቸውን
መክሮ መመለስ የማይታለም ነው፡፡ ልክ የማያባራ የሃምሌ ዝናብ ይመስል የስድቡን ዶፍ በአይነት
ያዥጐደጉዱታል፡፡
ያን ጊዜ ታዲያ በእድሜ ገፋ ያሉትና ለስማቸው የሚጨነቁት ቶሎ ብለው ጥግ ይይዛሉ፡፡ ወጣቶች ብቻ ያያ
ታሪኩን እርግማን እንደ ምረቃ፣ ዱላውን እንደ መዝናኛ ቆጥረውት ከበለአሙ ዙሪያ አይጠፉም፡፡ በለአሙ ደሞ
ወርዶባቸው ወጣት አይወዱም፡፡ “እራት” ይሉታል ወጣቱን “ራ”ን ጠበቅ አርገው “የቤት አይጥ ማለት ነው
ይላሉ በለዓሙ፡፡
ያን የፈረደበት ወጣትማ ምን የማይሉት አለ?! “ካንሰር፣ የሶማሌ አሞራ፣ የኢህአፓ ጭማቂ፣ ባርጤዛ፣ ወዘተ”ም
ይሉታል፡፡ “የዛሬ ዘመን ወላድ ጋራንት የሌለው ልጅ ከሚወልድ ዶሮ ቢያረባ ይሻለው ነበር ባይሆን እንቁላሉ
እየተሸጠ ለቤት ኪራይ ያግዝ ነበር፡፡ እንቅፋት ሁሉ!” ሲሉም ያክሉበታል፡፡ በለአሙ ለዚህ ሁሉ እርግማናቸው
የሚሰጡት ምክንያት “የዛሬ ዘመን ልጅ ዲግሪ ጭኖ እንኳ አይመራመርም፡፡ ለምሳሌ ጐንደር ከተማ የሚገኙ ቤተ
መንግስቶች የማን የማን ናቸው ተብሎ ቢጠየቅ እንዲያው በነሲቡ “የፋሲለደስ ናቸው” የሚል መልስ ነው
የሚሰጥ፤ እኔ ግን ተመራምሬ ደርሸበታለሁ፡፡” ባይ ናቸው፡፡
አያ ታሪኩ ስድቡንም ሆነ እርግማኑን “በምርምር ነው የደረስሁበት” ይላሉ፡፡ “ከመማር መመራመር፣
ከመጠምጠም መማር ይቅደም” የምትለዋን ነገር እንደ ተረት ይደጋግሟታል፡፡ (ይህንም በምርምር እንደደረሱበት
ይናገራሉ) “በመጀመሪያ አክሱም፣ ቀጥሎ ላሊበላ፣ ከዚያ ጐንደር ላይ ነው የኢትዮጵያ ታሪክ ያለ፡፡ ዛዲያ
ፈረንጆች ይህን ለማወቅ ሲመጡ፣ ይህ ባርጤዛ ሁሉ “ዩ!ዩ!...ዩ” እያለ አላስቆም አላስቀምጣቸው አለ፤ ከዩ
በሁዋላ እኮ የሚያውቀው እሰቬልንግ የለውም፡፡ እነሱ ደሞ ጥንታዊ ቦታዎችን ለማየት እንጅ የነራስ መስፍንን
ፎቅ ለመመራመርና እስቬልንግ ለመቁጠር አዲስ አበባ አልሄዱም፡፡” ሲሉም “በምርምር” የደረሱበትን ለወጣቱ
ያስተምራሉ፡፡
የጐንደሩ በለአም “ተመራምረው” የደረሱበትን እንግሊዝኛም ነግረውናል፡፡ ለምሳሌ “ካም ጐንደር/ጐንደርን
ጐብኝ/፣ ሃብዘፑር/ድሀን እርዳ/፣ ሉክ ገርል/ልጃገረድን ውደድ/፣ ኦቨር ዘኪንግ/ንጉስህን አክብር/፣ ዘ
አናርኪስት/እንዋጋቸዋለን እንጅ አንለቃቸውም/” የሚባሉት ቃላትና ፍቻቸው በአያ ታሪኩ “ምርምር”
የተደረሰባቸው ናቸው፡፡ በለአሙ ለዚህ ሁሉ “ምርምራቸው” ዋቢ መስከረም መጽሔት ቁጥር ሁለት መሆኑን
ይጠቅሱና “በስቬልንግ ነው የደረስሁበት” ባይ ናቸው፡፡
መቸም “ምርመራቸው” አያልቅም፤ የጐንደሩ በለአም ሌላ “በምርምር” የደረሱበት ነገር እንዳለ አባ ጃሌዎች
ያወሳሉ፡፡ ጊዜው “ቀሽ ሽብር” የተባለው ወጀቦ ጐንደርን ያንገላታት የነበረበት ወቅት ነው አሉ፡፡ አያ ታሪኩን
ማናደድ የፈለገ አንድ ጉብል በጨለማ ሄዶ፣ በለአሙ ልብስ ከሚሰፉባት ቦታ ላይ አንድ ነገር አስቀምጦ ዘወር
ይላል፡፡ የጐንደሩ በለአም ጠዋት መደበኛ ስራቸውን ለመስራት ወደ በረንዳቸው ሲመጡ ያን ጉድ ይመለከቱና
“ምርምር” ይጀምራሉ፡፡ ከራሳቸው ላይ አደፍ ያለች ጨርቅ ወይም ቆብ ቢጤ የማይለዩት አያ ታሪኩ፣ ቆባቸውን
አውልቀው ያን ያጋጠማቸውን ጉድ ይሸፍኑታል፡፡ ወዲያው ወደ ሻለቃ መላኩ ቢሮ ሲሮጡ ይሄዱና “ልብፋ
ከምሰፋበት ቦታ ላይ ኢህአፓ ቦምብ አጠመደችብኝ” ብለው ያመለክታሉ፡፡
ጥቆማውን የሰሙት ሻለቃ በንዴት ይጦፉና፣ አዘዞ ከነበረው ሰራዊትም በዙሪያቸው ከነበሩት ጠባቂዎቻቸውም
የምህንድስና ችሎታ ያላቸው ባስቸኳይ ሄደው ቦምቡን እንዲያከሽፉ ትዕዛዝ ይሰጣሉ፡፡ ፒያሳ በቅጽበት
በወታደሮች ትጥለቀለቃለች፡፡ ወደ ጃን ተከል የሚወርደውም ወደ አስመራ መንገድ የሚያቀናውም ወደ ፔፕሲ
ፋብሪካ የሚያመራውም ብቻ ሁሉም እንዳይንቀሳቀስ ሆኖ መንገዶች በታጠቁ ኮማንዶዎች ዝግ ይሆኑና
መሃንዲሶች ስራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ወሬውን የሰማ ጐንደሬም በየቤቱ ሆኖ ካሁን አሁን ቦንቡ ፈንድቶ ኢትዮጵያ
ሆቴልና ሌሎች ባካባቢው ያሉት ሱቆች ብትንትናቸው ወጣ እያለ ሲጨነቅ፣ በፍንዳታው የሚያልቀውን ህዝብ
ቁጥር በህሊናው ሲያሰላ፣ ከመሃል ለራሱ ጨንቆት ጐንደርን አስጨንቋት የነበረ ያ ሁሉ ወታደር ከዳር ዳር በሳቅ
ይፈነዳል፡፡ “ቦንብ ነው” ተብሎ በአያ ታሪኩ ቆብ አጊጦ የተቀመጠው ነገር ለካ የዚያ ተንኮለኛ ጉብል አይነ
ምድር ኖሯል፡፡
በጉብል መደፈራቸው ያንገበገባቸው አያ ታሪኩ፤ ለሰራዊቱ የሰጡት መልስ ምን መሰላችሁ? “ይኸ እንቅፋት ሁሉ
ዛሬ እንትኑን ሲጥል ዝም ከተባለ፣ ነገ ቦምብ ከማጥመድ ወደ ሁዋላ አይልም” የሚል ነበር፡፡ እናም
“በምርመራቸው” የሻለቃውንም የሰራዊቱንም አንጀት ቅጥል አርገዋል፡፡
የጐንደሩ በለአም “በጣሊያን ጊዜ ሶስት መቶ ብር ገዛሁዋት” የሚሏት አንዲት አሮጌ የልብስ ስፌት መኪና
ብትኖራቸውም ከሚሰሩበት ቁጭ ብለው የሚራገሙበት ቀን ይበልጣል፡፡ አንዳንድ ቀንም ርግማኑ ወደ ዱላ
ተቀይሮ ወይ ፈንክተው አለዚያም ያችን ጥምጣም የማይለያትን አናታቸውን ተበጥርቀው ደማቸውን እያዘሩ ያንኑ
እርግማናቸውን ያንጐደጉዱታል፡፡ አያ ታሪኩ ለምን እንደተሸነፉ ሲጠየቁ “በምርምር” የደረሱበትን እንዲህ ሲሉ
ይመልሳሉ፤ “እንኳን እኔ አንዳንድ ቀንማ ማራዶናም ይጠቃል‘ኮ፤ መጠቃት እራሱ ስፖርት ነው፤ አንድ እሁድ
ብጠቃ በሚቀጥለው በለሱ ለእኔ ይሆናል፡፡ እና ዱላ ለወንድ ልጅ ጥሩ ነው፤ ወኔውን ያጐለብትለታል፤ እኔም
ቀስ በቀስ ነው ኑስ በኑስ ሙያውን እያዳበርሁት የመጣሁ፡፡”
በለአሙ ከእጃቸው ዱላ ከአንደበታቸው እርግማን ተለይቷቸው እንደማያውቅ ሁሉ ከመጠጥ ደሞ ጠጅ በጣም
ይወዳሉ፡፡ “የባላባት ዘር ነኝ፤ የጐጃም ባላባት - ሞጣን የመሰረቱት አያቴ ወለተ እስራኤል ናቸው፡፡ እሳቸው ደሞ
እቴጌ ምንትዋብ ናቸው፡፡ ዛዲያ አባቴ ግራ/ች በላይ ይባሉ ነበር፡፡ በብር ማርዳ አንቆጥቁጠው፣ በጐሽ ዋንጫ
ጠጅ እያጠጡ፣ ሎሌ ሞግዚት ተበጅቶልኝ በቅምጥልነት ነው ያደግሁ፡፡ ምን ያረጋል፤ ዛሬ የጋለሞታ ልጅ ሁሉ
ሲሰድበኝ ይውላል” ይላሉ ጠጅ የወደዱበትን ምክንያት “በምርምራቸው” ሲገልጹ፡፡
አንዳንድ ቀን ለእርሳቸው እንግዳ የሆነ ሰው ሊያናግራቸው ሲሄድ እንኳ የሚሰጡት መልስ “መጀመሪያ ጠጅ
አጠጣኝ፤ ከዚያ በሁዋላ የምትፈልገውን ጠይቀኝ፡፡ እኔ የነጻ ካድሬ አይደለሁም፡፡ ዝም ብዬ ቦንባ አልከፍትም፡፡
የዘጌ ወፍጮ እንኳ ካልተወቀረ አይፈጭም፡፡” የሚሉት አያ ታሪኩ፤ ጠጅ ካልቀመሱ እንግዳውን ነገሬ ሳይሉት
እርግማቸውን ይቀጥላሉ፡፡
በለአሙ እርግማናቸው የያዘበት ወቅት እንደነበር እራሳቸው ይናገራሉ - የቀይ ሽብር ወቅት፡፡ “የመላኩ ጥፋቱ”
ይላሉ አያ ታሪኩ “የሻለቃ መላኩ ጥፋት ልጅ ልጁን ብቻ ገድሎ እናቲቱን መተው ነው፡፡ ያኔ በነካ እጁ እናት
እናቱንም አብሮ ቢጠርግልኝ ኖሮ ዛሬ በጤና እኖር ነበር፡፡ ችግሩ እኮ ከእናቲቱ ላይ ነው፡፡ ከቀይ ሽብር በሁዋላ
የተወለደው እንደ ደጋ ባህር ዛፍ ተዥሞልሙሉ ያድግና የል ሸፕ ኤልሸፕ (ጠላ መንደር ነው) ወርዶ ቅጅ
እንደንስ ማለት ነው የሚችለው፡፡ ከዚያ መልስ ደሞ በትፋቱ እኔን ሲያስቀይም ይኖራል፡፡ ዛዲያ ይኸ የእናቲቱ
አለመሞት ያስከተለብኝ መዘዝ አይደለም? ካንሰር ሁሉ” በማለት በእርግማን የጀመሩትን በዘለፋ
ይደመድሙታል፡፡
አያ ታሪኩ የጐንደርን ወጣት እንደ ቤት ጥራጊ አውጥቶ የሚደፋላቸው ታላቅ ባለውለታቸው ነው፡፡ በዚህ የተነሳ
ሻለቃ መላኩን ይወዳሉ፡፡ “የጐንደርን ባለጌ በተመለከተ መስቀል አደባባይ በስብሰባ ለመላኩ ነግሬው ሃሳቤን
አሟልቷል፡፡ የጋሪን (የጋሪ ፈረስ) ዲስብሊን አስመልክቶም ቀበሌ ስድስት ላይ በተካሄደ ስብሰባ፤ ለኢህአዴግ
ምክር ሰጥቼ የፒያሳ አስፋልት ከፈረስ ፋንዲያ ነጻ ወጥቷል፤ ባለ ጋሪዎችም ዲስብሊን ይዘው ሲያልፉ ሲያገድሙ
አይሰድቡኝም፤ አሁን ያልቻልሁት ይህን ባርጤዛ የፒያሳን ውሪ ነው፡፡ ምናለ እግዚአብሔርም ስብሰባ ቢጠራና
እውነቷን ነግሬው ከጐንደር ውርጋጥ ቢገላግለኝ” ይላሉ፡፡ ሞጣ ከተማ ተወልደው ያደጉት አያ ታሪኩ፤ በጣሊያን
ወረራ ወቅት “የአያታቸው የእቴጌ ምንትዋብን ቤተመንግስት ለመጐብኘት ወደ ጐንደር ከሄዱበት” ጊዜ ጀምረው
ለአምሳ አንድ አመታት ከሲንጀር የልብስ ስፌት መኪናቸው ጋር ተጣብቀው እንዳሉ አሉ፡፡ ውጭ አገር የሚኖሩና
ድሮ የሚያውቋቸው የጐንደር ወጣቶች ዘመድ ለመጠየቅ ሲመጡ፣ አያ ታሪኩንም ይደጉሟቸዋል፡፡ በተረፈ
በለአሙ እርግማናቸውን አምርተው እሱኑ በልተው ነው የሚኖሩት፡፡
ከጐንደሩ በለዓለም ጋር ይህንን ቃለምልልስ ያደረግሁበት ጊዜ ትንሽ ቆየት ብሏል፤ በቅርቡ ወደ ጐንደር
ለእረፍት ሄጄ ነበርና ልጠይቃቸው ስሄድ በህይወት አለመኖራቸውን ሰማሁ፤ ነፍሳቸውን ይማር!

Published in ጥበብ

አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ

ባለፈው ዓመት የያዝናቸውን የስራ እቅዶች ከሞላ ጐደል ማከናወን ችለናል፡፡ ለአዲሱ አመት የተላለፉም አሉ፡፡
በአጠቃላይ 2006 መጥፎ አመት አልነበረም፤ ጥሩ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡
በአዲሱ ዓመት ሁሉም ሰው ሃላፊነት እንዲወስድ እጠይቃለሁ፡፡ ሃላፊነትን መውሰድና መወጣት ቀላል ነገር
ይመስላል እንጂ ከባድ ነው፡፡ ለምሣሌ ስለ መኪና አደጋ ችግር ሲነሳ ጥፋቱ ሁሌም በአንድ ወገን (ሹፌሩ) ላይ
ብቻ ነው የሚደመደመው፡፡ ሃላፊነቱ ለአንድ ወገን ብቻ እየተሰጠ ስለሆነ በዚህ ረገድ ውጤታማ መሆን
አልተቻለም፡፡ ነገር ግን መንገደኛው (እግረኛው)፣ የእንስሳት መንገድ አጠቃቀም፣ የመኪናው ቴክኒካዊ ብቃት
የመሳሰሉትን ሁሉ የሚመለከት ነው፡፡ መንግስትም ሃላፊነቱን እኔ ብቻ እወስዳለሁ ሣይል ወደ ህብረተሰቡም
ማውረድ አለበት፡፡ ያ ካልሆነ የምንመኘው ነገር ውጤታማ ላይሆን ይችላል፡፡
2006 ዓ.ም እውነቱን ለመናገር ለስፖርቱ ጥሩ አልነበረም፤ በአትሌቲክስም ሆነ በእግር ኳሱ፡፡ በዚህ ዘርፍም
ለውጥ እንዲመጣ ሁሉም የየራሱን ሃላፊነት ወስዶ ግዴታውን በሚገባ መወጣት አለበት፡፡ አዲሱ ዓመት
የእድገትና የብልፅግና እንዲሆን መልካም ምኞቴ ነው፡፡

Published in ጥበብ

አሜሪካ 300 ወታደሮች ወደ ላይቤሪያ ልትልክ ነው

እንግሊዛዊቷ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ሩት አትኪንስ ሰሞኑን በኦክስፎርድ ለ60 በጎ ፍቃደኞች ሊሰጥ የታቀደውን
የኢቦላ ቫይረስ የሙከራ ክትባት በመውሰድ የመጀመሪያዋ በጎ ፈቃደኛ እንደሆነች መሆኗን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የሙከራ ክትባቱን የሚወስዱ በጎ ፈቃደኞች እንደሚፈለጉ በቢቢሲ ሬዲዮ መስማቷን የገለፀችው አትኪንስ፣
በምዕራብ አፍሪካ ሁኔታው በጣም አሳዛኝ ስለሆነና የዚህ ክትባት ሂደት አካል መሆን ትልቅ ውጤት ለማምጣት
በሚደረገው ጥረት ማበርከት የምችለው ትንሹ ነገር እንደሆነ በማሰብ፣ ክትባቱን በበጎፈቃደኝነት ለመውሰድ
ወስኛለሁ” ብላለች፡፡
ክትባቱ ከኢቦላ ቫይረስ ትንሽ የዘረመል ንጥረ ነገር ብቻ የያዘ በመሆኑ ተከታቢው በበሽታው እንደማይያዝ
የተገለፀ ሲሆን በኦክስፎርድ የጄነር ኢኒስቲቲዩት ዳይሬክተርና የሙከራ ክትባቱ መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አድርያን
ሂልም፤ “ይሄ ክትባት ማንንም ኢቦላ ያስይዛል የሚል ቅንጣት ስጋት የለም” ብለዋል፡፡
ክትባቱን ለመወጋት ስታስብ የደህንነቷ ጉዳይ እንዳላስጨነቃት የተናገረችው ሚስ አትኪንስ፤ የ15 ዓመት ታዳጊ
ልጇ የኢቦላ ቫይረስ ተሰጥቷት የምትሞት መስሎት እንደነበርና እንዳረጋጋችውም ገልፃለች፡፡
ብዙ ጊዜ አዲስ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ ከማግኘቱ በፊት ለዓመታት በሰዎች ላይ ሙከራ ሲደረግ
ይቆይ ነበር ያለው ቢቢሲ፤ በምዕራብ አፍሪካ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ አጣዳፊነት ግን ይሄ የሙከራ ክትባት
በአስደናቂ ፍጥነት ጥቅም ላይ እንዲውል ጥረቱ እንዲጠናከር አድርጓል ብሏል፡፡
በሰዎች ላይ የሚደረገው ሙከራ ውጤታማ ሆኖ ከተገኘ፣ ክትባቱ በፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ላይ በቫይረሱ
በተጠቁ አካባቢዎች የሚገኙ የጤና ሰራተኞችን ከበሽታው ለመከላከል ጥቅም ላይ እንደሚውል ታውቋል፡፡
ያን ጊዜ ግን ለ10ሺ ሰዎች ያህል የሚሆን ክትባት እንደሚያስፈልግ የተገለፀ ሲሆን በምዕራብ አፍሪካ ክፉኛ
የተጠቁ አካባቢዎች ላይ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችን ከቫይረሱ ለመከላከል ጥቅም ላይ ይውላል ተብሏል፡፡
ክትባቱ እየተሰራ የሚገኘው ግላክሶስሚዝክላይን በተባለ ኩባንያና በአሜሪካ ብሔራዊ የጤና ተቋም ሲሆን፣
የእንግሊዝ ዓለምአቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ የምርምር ተቋማት ለሙከራ ክትባቱ የገንዘብ
ድጋፍ እንዳደረጉ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የኢቦላ ቫይረስን ለመከላከል እገዛ የሚያደርጉ 3ሺ ወታደሮችን
ወደ ላይቤሪያ የመላክ ዕቅድ እንዳላቸው ባለፈው ማክሰኞ አስታወቁ፡፡ ኦባማ ይሄን ያስታወቁት የላይቤሪያዋ
ፕሬዚዳንት አለን ጆንሰን ሰርሊፍ በሽታውን ለመከላከል እገዛ ያደርጉላቸው ዘንድ ለኦባማ በቀጥታ ያቀረቡትን
ጥያቄ ተከትሎ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የአሜሪካ ወታደራዊ ሃይል የህክምና ማዕከሎችን ግንባታ በመቆጣጠርና የጤና ሰራተኞችን በማሰልጠን
ለላይቤሪያ መንግስት እገዛ እንደሚያደርግ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በምዕራብ አፍሪካ ለተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ፈጣን ያልሆነ ምላሽ ትችት ሲሰነዘርበት
፣ቆየቱ ይታወቃል፡፡
በበሽታው ክፉኛ የተጠቁት የምዕራብ አፍሪካ አገራት ሴራሊዮን፣ ላይቤሪያና ጊኒ ሲሆኑ ወረርሽኙ ከ2400 በላይ
ሰዎችን ለህልፈት እንደዳረገ ተጠቁሟል፡፡ ከእዚህ የሞት አደጋ ውስጥ ግማሹ የተከሰተው በላይቤሪያ ነው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት፤ አገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎችን በቫይረሱ ልታጣ እንደምትችል በቅርቡ
አስጠንቅቋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኃላፊዎች፣ በጄኔቫ በሚያካሂዱት ስብሰባ ለወረርሽኙ
በተሰጠው ዓለም አቀፍ ምላሽ ላይ እንደሚወያዩ ቢቢሲ ጠቁሟል፡፡
የጋና ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ባለፈው ሰኞ ወረርሽኙን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤
“በምዕራብ አፍሪካ ለተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ከፍተኛና ፈጣን የውጭ እርዳታ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

Published in ዋናው ጤና

የኢቦላ ቫይረስ በተስፋፋባቸው የምዕራብ አፍሪካ አገራት በበሽታው ተይዘው የነበሩና ከህመማቸው ያገገሙ
ሰዎች ደም፣ ታማሚዎችን ለማከም በሚል በድብቅ እየተሸጠ መሆኑን ሲኤንኤን ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በበሽታው ተይዘው ያገገሙ ሰዎች ደም በውስጡ የኢቦላ
ቫይረስን የሚያጠፋ ንጥረ ነገር አለው በሚል እየተናፈሰ ባለው መረጃ የተነሳ፣ በአገራቱ የሚገኙ የኢቦላ
ታማሚዎች ደሙን በድብቅ ከሚሸጥበት ስውር ገበያ እየገዙ ይገኛሉ፡፡
የአለም የጤና ድርጅትን በሽታው በተስፋፋባቸው የምዕራብ አፍሪካ አገራት እየተከናወነ ያለውን ስውር የደም
ሽያጭ ለማስቆም ከአገራቱ መንግስታት ጋር በመተባበር እየሰራ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ ታማሚዎች
በአገራቱ ሆስፒታሎች በሚሰጠው ህክምና ተስፋ በመቁረጥ ፊታቸውን ወደዚህ ህገወጥ ገበያ ማዞራቸውን
ገልጿል፡፡ ዘ ቴሌግራፍ በበኩሉ፤ ምንም እንኳን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ደም ታማሚዎችን ቶሎ እንዲድኑ
በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ቢረጋገጥም፣ ደሙ ኤችአይቪ ኤድስን በመሳሰሉ ቫይረሶች የተበከለ
መሆን አለመሆኑ ሳይረጋገጥ በድብቅ የሚሸጥ መሆኑ ሌላ ቀውስ እንዳያስከትል ስጋት መፍጠሩን ዘግቧል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ማርጋሬት ሃሪስን ጠቅሶ፣ ድርጅቱ ከኢቦላ በሽታ ያገገሙ ሰዎችን ደም
በአግባቡ መርምሮ በመሰብሰብና በማጠራቀም ለተመሳሳይ ህክምና ለማዋል የሚያስችል ደህንነቱ የተጠበቀ
አሰራር እየቀየሰ እንደሚገኝ የዘገበው ዋሽንግተን ፖስት በበኩሉ፣ ድርጅቱ መሰል የደም ህክምናን እንደሚደግፍ
ቃል አቀባይዋ መናገራቸውን አስታውቋል፡፡

Published in ዋናው ጤና
Page 5 of 14