በአብርሃም ግዛው ኢንተርቴይመንትና የፕሬስ ስራዎች እና በሰለሞን ማርያ ፊልም ፕሮዳክሽን ትብብር የተጠነሰሰው “ኪነጥበብ የሰላም እርግብ ናት” የተሰኘ በዘጠኙም ክልሎች በየተራ የሚዘጋጅ ፕሮግራም ሊካሄድ እንደሆነ ተገለፀ፡፡ አዘጋጆቹ እንዳሉት፤ የዝግጅቱ ዓላማ የኢትዮጵያን ሰላም ወዳድነት፣ ስላሉን የቱሪስት መስህቦች፣ ስለመቻቻል ባህላችንና ስለተፈጥሮ እሴቶቻችን ለትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ለመላው ዓለም ማስተዋወቅ ነው፡፡
በመስቀል ዋዜማ የዳመራ እለት በአዲስ አበባ የሚጀመረው ይሄው ፕሮግራም፤ በብሄር ብሄረሰቦች ሙዚቃ፣ በስዕል አውደርዕይ፣ በመድረክ ተውኔትና በተለያዩ ባህላዊ ትዕይንቶች፣ የሰላም አምባሳደር ምትሆን ቆንጆ የምትመረጥበት የቁንጅና ውድድር እንዲሁም በአስጐብኚዎች አውደርዕይ ይታጀባል ተብሏል፡፡ ዝግጅቱ ከአዲስ አበባ በመቀጠል  አዳማ፣ ሃዋሳ፣ ድሬደዋ,ኧ ባህርዳርና መቀሌ የሚካሄድ ሲሆን በቀጣይ በሌሎችም ክፍሎች እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሽልማት ስነ-ስርዓቱ መስከረም 24 ይካሄዳል

            በሸገር ኤፍኤም 102.1 የሚተላለፈው የለዛ ፕሮግራም የአድማጮች ምርጫ የሆኑ የመጨረሻዎቹ እጩዎች ተለይተው መታወቃቸውን አዘጋጆቹ ገለፁ፡፡ ለሁለት ወራት ያህል በwww.shegerFM.com እና yahoonoo.com ላይ አድማጮች ለአርቲስቶች ድምፅ ሲሰጡ መቆየታቸውን የገለፁት አዘጋጆቹ፤ 60 በመቶ በአድማጮች፣ 40 በመቶው በባለሙያዎች በሚሰጥ ውጤት አሸናፊዎች ታውቀዋል ብለዋል፡፡
በ “ምርጥ ወንድ ተዋናይ” ዘርፍ ግሩም ኤርሚያስ በ “ጭስ ተደብቄ” ፊልም፣ ይስሃቅ ዘለቀ በ “ቀሚስ የለበስኩ’ለት”፣ መሳይ ተፈራ በ“ትመጣለህ ብዬ”፣ ሚካኤል ሚሊዮን በ“አይራቅ”፣ ታሪኩ ብርሃኑ በ“ህይወትና ሳቅ” እና ሰለሞን ቦጋለ በ“ሶስት ማዕዘን” ፊልሞች የመጨረሻዎቹ እጩዎች ሆነዋል፡፡
በ “ምርጥ ሴት ተዋናይ” ዘርፍ፣ ድምፃዊት ዘሪቱ ከበደ በ“ቀሚስ የለበስኩ’ለት”፣ ሰላማዊት ተስፋዬ በ “በጭስ ተደብቄ”፣ ማህደር አሰፋ በ“አይራቅ”፣ ሩታ መንግስተአብ በ“ረቡኒ”፣ ማህደር አሰፋ በ“ህይወትና ሳቅ” እንዲሁም ማህደር አሰፋ በ “ዘውድና ጎፈር” የመጨረሻዎቹ እጩዎች ሊሆኑ ችለዋል፡፡
ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ የአድማጮች ምርጫ ላይ አምስት ፊልሞች በአድማጮች የተሻለ ነጥብ ያገኙ ሲሆን ፊልሞቹም “በጭስ ተደብቄ”፣ “ትመጣለህ ብዬ”፣ “ህይወትና ሳቅ”፣ “ቀሚስ የለበስሉ’ለት”፣ “አይራቅ” እና “ረቡኒ” መሆናቸው ታውቋል፡፡ በምርጫው ላይ ምርጥ አልበሞች የተካተቱ ሲሆን የብዙአየሁ ደምሴ “ሳላይሽ”፣ የስለሺ ደምሴ “ያምራል ሀገሬ”፣ የአስቴር አወቀ “እወድሃለሁ”፣ የሚካኤል ለማ “ደስ ብላኛለች”፣ የአብርሃም ገ/መድህን “ማቻ ይሰማኒሎ” እና የተመስገን ገ/እግዚአብሔር “ኮራሁብሽ” ተመርጠዋል፡፡ በምርጥ ነጠላ ዜማም የሙዚቃ ቪዲዮ ዘርፍ ደግሞ መካከል የጃኪ ጎሲ “ፊያሜታ፣ አስቴር አወቀ የተሳፈችበትና በ“የኛ” የተሰራው “ጣይቱ”፣ የበሃይሉ አጎናፍር “አዩ እሹሩሩ”፣ የናቲ ማን “ጭፈራዬ” እና የተመስገን ገ/እግኢዘብሔር “ኮራሁብሽ” በመራጮች ልቀው መገኘታቸውን አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡
በምርጥ ነጠላ ዜማ ዘርፍ የግርማ ተፈራ “መቼ ትመጫለሽ”፣ የበሃይሉ አጎናፍር “አዩ እሹሩሩ”፣ የጃኪ ጎሲ “ፊያሜታ”፣ የዘሪቱ ከበደ “የወንድ ቆንጆ”፣ የአቤል ሙሉጌታ “ልብ አርማ አመት” እና የ “እኛ” እና የአስቴር አወቀ ስራ “ጣይቱ” በአድማጮች ከፍተኛ ነጥብ አግኝተዋል ተብሏል፡፡ በሽልማት ዘርፍ ውስጥ አዳዲስ ድምፃዊያን በእጩነት የቀረቡ ሲሆን ሚካኤል ለማ፣ ተመስገን ገ/እግዚአብሔር፣ እመቤት ነጋሲ፣ አዩ አሳዬኝ አለሙና ዳንኤል ፍስሃዬ የመጨረሻ እጩ ሆነው ተመርጠዋል፡፡
የድምፅ መስጠት ሂደቱ በቀረቡት የመጨረሻ ዙር እጩዎች ላይ ለቀጣዩ 30 ቀናት ከተካሄደ በኋላ አሸናፊዎች መስከረም 24 ቀን 2007 ዓ.ም በጣሊያን ካልቸራል ኢንስቲትዩት በሚካሄድ የቀይ ምንጣፍ የሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ ይሸለማሉ ተብሏል፡፡
 በሽልማት ስነ-ስርዓቱ ላይ የፒያኖ ባለሙያው ግርማ ይፍራሸዋን ጨምሮ በርካታ ሙዚቀኞች ስራዎቻቸውን በማቅረብ የሽልማት ስነ-ስርዓቱን ያደምቃሉ ተብሏል፡፡          

Published in ጥበብ

የባህል ሙዚቃ ተወዛዋዥና ድምፃዊ  መኳንንት መሰለ፤ በሰቆጣ በተከበረው የሻደይ በዓል  ላይ የተለያዩ ስራዎቹን አቅርቧል፡፡ ከአሜሪካ የሶስት ወራት ቆይታው የተመለሰውም በቅርቡ ነው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው፤ አዲስ አበባና ባህርዳር እየተመላለሰ ከሚኖረው ከድምጻዊውና ተወዛዋዡ መኳንንት መሰለ  ጋር በህይወቱና በሙያው ዙርያ ያደረገችው ቃለ-መጠይቅ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡     


ድምጻዊና ተወዛዋዥ መኳንንት መሰለ

አሜሪካ ቆይተህ በቅርቡ ነው የተመለስከው ---አሜሪካን እንዴት አገኘሃት?
ው ው.. ደግሞ አሜሪካ!  አየራቸው እኮ አርቴፊሻል ነው፤ ከሞቀሽ የሚያቀዘቅዝ፤ ከቀዘቀዘሽ የሚያሞቅ አየር (IC) ይከፍቱልሻል እንጂ የተፈጥሮ ነገር እኮ የላቸውም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የሚያስደንቅ አይገኝም፡፡ እኔ ሶስት ወር ቆይቼ ነው የተመለስኩት፡፡ አሜሪካና ኢትዮጵያ የሚለያዩት ታዲያ በስልጣኔ እንጂ ለመኖር ኢትዮጵያን የሚያህል የለም፡፡
ብዙ ኢትዮጵያውያን የአገራቸው ወግና ባህል ትዝ የሚላቸው ወደ ውጭ ሲሄዱ ነው ይባላል…በዚህ ትስማማለህ?
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ወጣ ሲል ለባህል አለባበሱ፣ ለባህል ሙዚቃው፣ ለኢትዮጵያዊ ማንነቱ እጅግ የሚጨነቅ ነው፡፡ የአገር ናፍቆት አለባቸው፡፡
 እንደምታይኝ የባህል ልብሴን ለብሼ በየግዛቱ ስዘዋወር፣ በአገር ፍቅር ስሜት የሚያለቅሱ ኢትዮጵያውያን ገጥመውኛል፡፡ ብዙዎቹ ለአገራቸው ባህል፣  ለኢትዮጵያዊነታቸው እጅግ የሚጨነቁ ናቸው፡፡
አሜሪካ ሁሉ ነገር አለ …ጥሬ ስጋ አልበላህም፤ ጠጅስ?
ይቅርታ እኔ አይጥመኝም፡፡ እንጀራው ያልሽ እንደሆነ ለንቆጥ ለንቆጥ የሚል ነው፡፡ የእውነተኛውን የሀበሻ ምግብ እንኳን ፈልገን ፈልገን አላገኘንም፡፡ ከኢትዮጵያ በአውሮፕላን ነው የሚመጣው አሉ፤ ያችን ፈልገን ነበር፡፡ እንጀራቸው የሚያያዝ ነው… ቢቸግረኝ ሶስቱን እንጀራ ደርቤ በላሁ፤ ኧረ እሱም አልጠቀመኝ፡፡ እንግሊዝኛውም ችግር ነበር፡፡
እንግሊዝኛ ቋንቋ ምንም አችልም …?
ለአስተርጓሚ ብዙ ብር ስከፍል ከርሜ ነው የመጣሁ ባክሽ፡፡ ወይ ነጮቹ አማርኛ አይችሉ፤ ወይ እኔ እንግሊዝኛ አልችል… በምን እንግባባ?!
አስተርጓሚ ቀጥረህ ነበር እንዴ?
መቅጠር በይው--- በጉቦ፡፡ ፋሲል ደሞወዝ በጣም ጓደኛዬ ነው፡፡ እንግሊዝኛ “እችላለሁ” ስለሚልና  ሰዎች ሲናገሩ በደንብ ስለሚያዳምጥ መኮረጅ ይችላል፡፡ ሁሏንም ወዲያው ነው የሚይዛት፡፡ ሰዎች ሊጋብዙ ወስደውት ‹No. 6 Chicken› ሲሉ ሰምቷል፡፡ ያችን ይዞ ‹No. 6 Chicken› እያለ ሲቀልድብኝ ሰነበተ፡፡ ብዙ ጊዜ ይችኑ ምግብ ነበር የሚያዘው፡፡ እኔ ትንሽ ቀደም ቀደም ካልኩ “ዝም በል አዝዤያለሁ… ባላገር” ይለኛል፡፡ … ስወጣ ስገባ እሱን መጋበዝ፣ ጉቦው ሊገለኝ ሲሆን እሱ የሚያደርገውን ነገር በደንብ አጠናሁና … አንድ ቀን ፋሲል እንደተኛ ሳልቀሰቅሰው በጠዋት ተነስቼ ቁርስ የምንበላበት ስፍራ ሄድኩ፡፡ ገባሁና እርሱ እንደሚያዘው፣ ‹No 6 Chicken› ብዬ አዘዝኩና ግጥም አድርጌ በልቼ ወደ ክፍሌ ተመለስኩ፡፡ ፋሲል ከእንቅልፉ የሚነሳው ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ ነው፡፡ እንደሌላው ቀን እሱን ቁጭ ብዬ የምጠብቀው መስሎታል፡፡
“አንተ ባላገር! ተነስ ቁርስ እንብላ” አለኝ፡፡
“እኔን ነው!! እኔማ ሽር ብትን ብዬ ራሴ አዝዤ፤ እንግሊዝኛ ተነጋግሬ፣ ገንዘቤን ከፍዬ ቁርሴን ግጥም አድርጌ በልቼ መጣሁ” አልኩት፡፡
“…ው…በል ተነስ! ለአንተ ደግሞ ማን  አስተርጉሞልህ” ብሎ አላገጠብኝ፡፡
“ሂድና ጠይቅ በልቼ መጥቻለሁ” ስለው፤
“በቃ ይህቺ ባላገር ሰለጠነች” ብሎ ሳቀብኝ፡፡ ከዚያ ቀን ጀምሮ ‹No 6 Chicken› ስል ከርሜ መጣሁልሽ፡፡
ትምህርት እንዴት ነው…ፊደል አልቆጠርክም እንዴ?
እስከ አስረኛማ ተምሬያለሁ፡፡ ግን ቋንቋ የለም፡፡
አሜሪካ ለመቅረት አላሰብክም ነበር ?
በበጋም ብትይ በክረምት አገሩን አልወደድኩትም፡፡ ጉድ ያሰኘኝ በረዶው ነው፤ በረዶ ተጋግሮ ቁጭ ሲል በጣም ነው የገረመኝ፡፡ ምን አገር ነው ብያለሁ፡፡
የአንድ ዓመት ቪዛ ነበር የተሰጠኝ፤ ግን እኔ አልፈልግም አገሬ ልግባ ነው ያልኳቸው፡፡ ቢለምኑኝ፤ ሽማግሌ ቢልኩ በፍፁም አልኩ፡፡ ኢትዮጵያ አገሬን የሚመስል የለም ብዬ ነው የመጣሁት፡፡ ኧረ አገሬ ይግደለኝ፡፡
ግን እኮ አሜሪካ ብዙ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች አሉ?
እህ ታዲያ እነሱ በሙያቸው አይሰሩ.. ታክሲ ነው የሚሠሩት፡፡ በታክሲያቸው ሄጃለሁ፡፡ ምን እንደሚሠሩ አውቄአለሁ፡፡
 አሁን ቋሚ መኖሪያህ ሰቆጣ ነው?
አገሬ ሰቆጣ ነው፡፡ የምኖረው ግን ባህርዳር፤ አዲስ አበባ እያልኩ ነው፡፡ ባህርዳር ከተማ “ጨጨሆ የባህል ምሽት ቤት” የሚባል አለ፤ እዚያ ነው የምሰራው፡፡ ሁለተኛው “ጨጨሆ የባህል ምሽት ቤት”  አዲስ አበባ ተከፍቷል፡፡ ባህርዳር አዲስ አበባ እያልኩ እሰራለሁ፤ እኖራለሁ፡፡
አሜሪካ የጋብቻ ጥያቄ ቀርቦልህ እንደነበር ሰምቻለሁ…?
ብዙ!…ግን እኔ አሜሪካዊት ማግባት አልፈልግም፡
የሰቆጣ ቆንጆ መሆን አለባት አይደል?
ማንም ኢትዮጵያዊት ትሁን፤ ማግባት እፈልጋለሁ፡፡
የሰቆጣ የባህል አምባሳደር የሚል ማዕረግ ያገኘኸው እንዴት ነው
በአማራ ክልልም “የባህል አምባሳደር” ተብዬ ተሸልሜያለሁ፡፡ የከተማ አለባበስ ጠፍቶኝ አይደለም፤ ገጠር ውስጥ ገብተሽ ስትወጪ ያልተነገረ፣ ያልተፃፈ፣ ገና ያልታየ የተደበቀ፣ እጅግ ረቂቅ መንፈሳዊም በይው ባህላዊ ትርጉም ሰጪ የሆኑ ማንነቶች፣ ታሪኮች አሉን፡፡ ባህሌ ኩራቴ ነው፡፡ የባህል ልብስ ስለብስ የሚሰማኝን መግለጥ ያቅተኛል፡፡ ከተማ ስዘዋወር ደስታዬ ነው፡፡ ከዛ በተረፈ የባህልና ዘመናዊ ልብሶችን በራሴ ዲዛይን አሰርቼ እለብሳለሁ፡፡
ፀጉርህ ላይ ያለው ሚዶ አይነሳም አይደል?
ይሄ ከተነሳማ አገር ከቦታዋ ለቀቀች ማለት ነው፡፡ ይህን የማደርገው ከልጅነቴ ጀምሮ ነው፡፡ አሜሪካም፣ እስራኤልም፣ ግብጽ አገርም በሄድኩ ጊዜ ከራሴ ላይ አልወረደም፡፡
እዚህ ሰቆጣ የገጠመኝን ልንገርሽ፡፡ ሽማግሌ ናቸው፤ ጐንበስ ጐንበስ እያሉ ሲሄዱ፤ ዝናሬን ታጥቄ  አዩኝና  ጠሩኝ፡፡
“ልጄ ና እስኪ፤ይሄን ቁምጣ፣ ዝናሩን የት አገኘኸው? ከየት አመጣኸው?” አሉኝ፡፡
የድሮ አባቶች እንደዚህ አድርገው ስለሚንቀሳቀሱ ታሪኩን ስለማውቀው…ባህሌን ላስተዋውቅ ብዬ ነው አልኳቸው፡፡ እንባው እንቅ እንቅ አደረጋቸውና አምስት ብር እንካ ብለው ሰጡኝ፡፡ …”ምርቃትዎ ይበልጥብኛል” ስላቸው “ትንሽ ናት ብለህ ነው፤ ያዝ” ሲሉኝ ተቀበልኳቸው፡፡
ነብር ገድለሃል የሚባለው እውነት ነው?
ሰቆጣ ገብተሽ ዘመዶቼን በጥያቄ ጠምደሻቸው ነበር ማለት ነው…ደሞ ማን ነገረሽ? በ1994 ዓ.ም ነው፡፡ በአካባቢያችን የሚዘከር በዓል ነበር፤ ከአንድ አማቼ ጋር ከቆላ ወደ ደጋ እየተጓዝኩ ነው፤ በቀኝ በግራ ጭው ያለ በረሃና ገደል ነው፡፡ የነብሩን ኮቴ አየሁትና ለአማቼ ከፊታችን ያለውን አደጋ ነገርኩት፡፡ ሰላሳ ጥይት የሚጎርስ ጠመንጃዬን አቀባብዬ መጓዝ ቀጠልን፡፡ ካየኸው ወደ ኋላ እንዳትል፤ በዱላው ቀርድደህ ጣለው አልኩት፡፡ ወደ አንደኛው መንገድ እጥፍ ስንል፣ ስጋ በልቶ አድሮ እንደመንጎማለል አደረገው፡፡ በያዝኩት ጠመንጃ ግራ እግሩን መታሁት፡፡ ነገር ግን በሶስት እግሩ እየዘለለ ወደ እኔ ተጠጋ፡፡ ለአንድ ሰዓት ያህል ተጋጠምን፤ ተያያዝን ይጥለኛል፣ እጥለዋለሁ፡፡ በጣም ተዳክሚያለሁ..ሸሽቶኝ ቆም ብሎ ፊት ለፊት ተፋጠጥን..ቁመቱ ከእኔ ስለሚበልጥ ተንደርድሮ መጥቶ እንደሚይዘኝ ገባኝ..መሳሪያዩን እንደምንም አንስቼ ተኮስኩበትና ወደ ገደል ከተትኩት፡፡ እኔም ከገደሉ አፋፍ ተንጠልጥዬ ስለነበረ.. አማቼን ፈርቶ ከሸሸበት “ድረስልኝ” ብዬ ጮህኩኝ፡፡ ሲያየኝ ሰውነቴ ሁሉ ተተልትሏል..እጅግ ተጎድቻለሁ፡፡ ወደ ህክምና ተወሰድኩ፡፡ የተጎዳው አካሌ ሁሉ እየታወቀኝ ተሰፋሁ፡፡ የዚያ ነብር ቆዳው እንደ ታሪክ አበርጌሌ ወረዳ ባህል ማዕከል ይገኛል፡፡   
ትዳር እንዴት ነው --አልያዝክም
አሁን አገባለሁ፡፡ እንደውም ሻደይ ለመጨፈር ከመጡት የአገሬ ልጆች ለማጨት እየመረጥኩ ነው፡፡ ቆንጆ ከአገኘሁ አገባለሁ፡፡ እኛ አገር የምትገኘው የምትታጨው በሻደይ፣ በጥምቀት ነው፡፡ ለከርሞ ሻደይ የሚቀናኝ ይመስለኛል፡፡ ባለቤት ነበረችኝ፤ ገጠር እያለሁ ያገባኋት፤ ከእርሷ የወለድኳት የ13 ዓመት ልጅ አለችኝ፡፡ ልጄ ተወልዳ እኔ ወደ ሙዚቃ ገባሁ፡፡ ሚስቴም ሌላ ባል አግብታ፣ በወሊድ ምክንያት ሞተች፡፡ ልጄ ግን አሁን ከቤተሰቤ ጋር ነው የምትኖር፡፡
ወደ ሙዚቃ አገባብህ እንዴት ነው
የሰቆጣ ባህል ዞን ማዕከል መልምለው አመጡኝ፡፡ 150 ብር ይከፈለኝ ነበር፡፡ በወቅቱ አንድ ሺ አምስት መቶ ብር ማለት ነው፡፡ ሰቆጣ ተከራይቼ መኖር ጀመርኩ፡፡ ስድስት ዓመት ሰቆጣ እንደሠራሁ፤ ወደ ባህርዳር ሄድኩ፤ ሙሉዓለም የባህል ቡድን ውስጥ ስድስት ዓመት አገለገልኩ፡፡ ከዚያ ወጥቼ በግሌ መስራት ጀመርኩ፡፡ “ሶራ” ባህላዊ ዘፈን ላይ ተወዛዋዥ ነበርኩ፡፡ የድምፃዊ ካሣሁን ዘፈን ነው፡፡ ክሊፑን ሰቆጣ፣ ላሊበላ ከተማ መጥተን ሰራነው፡፡
ከዚያ ራስህም ዘፋኝ ሆንክ?
አዎ፡፡ በአገውኛ “አገሬ ናፈቀኝ” በሚል ዘፈኔ ነው የታወቅሁኝ፡፡ የሰቆጣ ባህል ገና አልተነካም እህቴ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የባህል ዘፈኖች ገና አልተነኩም፡፡ አሁን ገና እየተሰሩ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ወደው መሰለሽ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን፣ ባህላቸውን እሚናፍቁት፡፡ ባህል ማለት እኮ ሃውልት ነው፤ የማንነት አሻራ ነው፡፡ አሁን ደግሞ አዲስ ስራ ሰርቻለሁ፤ ሰሞኑን ይለቀቃል፡፡
ከውጭ አገራት የኮንሰርት ሥራ ግብዣዎች አልመጡልህም
እየመጡ ነው፡፡ አውስትራሊያም፣ እስራኤልም እያነጋገሩኝ ነው፡፡ ዋጋውን አልተስማማሁም፤ ነገር ግን ከተሳካ ሰርቼ ተመልሼ እመጣለሁ፡፡
እስካሁን ቤትና መኪና ለመግዛት የሚበቃ ገንዘብ አላገኘህም
ገቢው ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን አርቲስት ገንዘብ አይዝም፤ ገንዘቡ ህዝብ ነው፡፡ ሀብት፣ ብሩ፣ ባንኩ ሁሉ ሰው ነው… እንጂ ቆጥሬ የማልዘልቀው ሽልማት አግኝቻለሁ፡፡ የአዲስ አበባ ከንቲባ፣ የአማራ ክልል፣ ከአገር ውስጥ እስከ ውጪ ድረስ  በርካታ ዓይነት ሽልማቶች አግኝቻለሁ፡፡
ምን ያህል ሥራዎች አበረከትክ?
በሰቆጣ ዘፈን በርካታ የውዝዋዜ ክሊፖች ላይ አለሁ፡፡ በድምፃዊነት ወደ ሰባት ነጠላ ዜማዎችን ሰርቻለሁ፡፡ አዲሱ ስራዬ ያልኩሽ ጐጃምኛም፣ ጐንደርኛም አለው፤ በቅርብ ይለቀቃል፡፡
መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልህ..
ለመላው ኢትዮጵያውያን እንቁጣጣሽ በይልኝ!!!

Published in ጥበብ

የኒውዮርክ ታይምስ መጽሔት “From Chopin to Ethiopia and Part way Back Again (“ከቾፐን እስከ ኢትዮጵያ እና ደርሶ መልስ”) በሚል ባስነበበው የሙዚቃ ቅኝት ስቲቭ ስሚዝ ስለግርማ ይፍራሸዋ ያሰፈረው በከፊል ይሄን ይመስላል፡-
 “…በተነፃፃሪ ሲታይ፤ ስለክላሲካል ሙዚቃ በአፍሪካ፤ የሚያመላክቱ ጥቂት ማረጋገጫዎች ብቻ ይኑሩ እንጂ የምዕራቡ ክላሲካል ባህል በሌላው ዓለም ማለትም ከቬኔዝዌላ እስከ ቻይና እንደተንሰራፋው ሁሉ የአፍሪካንም ዙሪያ መለስ ማዳረሱ ገሀድ ነው፡፡ ለዚህ አስረጅ የሚሆነን የ45 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ፒያኒስትና ቀማሪ ግርማ ይፍራሸዋ በብሩክሉን “ኢሹ ፕሮጀክት ሩም” ቅዳሜ ምሽት ያቀረበው ምርጥ የፒያኖ ሥራ፤ እጅግ ብርቅ፣ ሥነ ውበታዊና ተምሳሌታዊ የክላሲካል ሙዚቃ መናኸሪያ መሆኑን የሚያሳይ ነው!
…. ግርማ “የኢትዮጵያዊያን በገና” ሊባል በሚችለው በክራር ነው የሙዚቃ ልጅነቱን የጀመረው፡፡ አዲስ አበባ ሙዚቃ ት/ቤት ሲገባ ከፒያኖ ጋር ተገናኘ፡፡ ከዚያ ነው በነቃ አዕምሮው በቡልጋሪያ የሶፊያ ስቴት ኮንሰርቫቶሪ መደበኛ ትምህርቱን ገፍቶ የተካነው…
“… ወደ ኢትዮጵያ በ1995 እ.ኤ.አ ከተመለሰ በኋላ ግርማ ደረጃውን የጠበቀ ክላሲካል ትርዒት ምን እንደሚመስል ደርዝ ያለው ግንዛቤ ማስጨበጥን ሥራዬ ብሎ ከመያያዙ ሌላ፤ አዳዲስ የሙዚቃ ስራዎችን ፅፏል፡፡ ለነዚህ አዳዲስ የጥበብ ስራዎች መቀመሪያ ይሆነው ዘንድ የአውሮፓን የጥበብ መላ ከኢትዮጵያ ሙዚቃና ሥነ-ትውፊታዊ ዕሴት ጋር በማጋባት ተጠቅሟል፡፡....››


ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገበው አዲሱ አልበሙ በአሜሪካ በቢልቦርድ ሰንጠረዥ 23ኛ ደረጃ አግኝቷል ታዋቂው ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ በቅርቡ በአሜሪካ ያስመረቀው “Love and peace” የተሰኘ አዲስ አልበሙ፤ በቢልቦርድ ሰንጠረዥ 23ኛ ደረጃ ላይ እንደተቀመጠለት ይናገራል፡፡ በአሜሪካ ያቀረበው ኮንሰርት እንደተወደደለት የገለፀው ፒያኒስቱ፤ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በአድናቆት የተሞላ ጽሑፍ እንዳወጣለት ጠቁሟል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት ዕቁባይ ከግርማ ይፍራሸዋ ጋር ያደረገችው ቃለምልልስ እንዲህ ቀርቧል፡፡ ወደ ሙዚቃ እንዴት እንደገባ በመናገር ይጀምራል፡-  


ሙዚቃ የጀመርኩት በልጅነቴ ክራር በመጫወት ነው፡፡ ክራር ስጫወት ነው ያደግሁት፡፡ ፡፡ሙዚቃን በሳይንሳዊ መንገድ ለማጥናት ደግሞ  ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በመግባት፤ ከባህል ክራር፣ ከዘመናዊ ደግሞ ፒያኖን ለአራት አመት ተማርኩ፡፡ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ትምህርቴን እንዳጠናቀቅሁ፣  በ1980 ስኮላርሺፕ አግኝቼ ወደ ቡልጋሪያ  አቀናሁ፡፡
እዚያ ከሄድክ በኋላ ግን ችግር ገጠመህ…
ፒያኖ ለመማር አልሜ ቡልጋሪያ በሚገኝ የሙዚቃ አካዳሚ ለሁለት አመት ከተማርኩ በኋላ በወቅቱ  በተፈጠረው የሶሻሊስት ካምፕ መፍረክረክና መፍረስ   ሳቢያ  የእኔና  በሙዚቃ ትምህርት ቤቱ የነበሩ ሌሎች ተማሪዎቸ እጣ ፈንታ ስደት ሆነ፡፡ ሁሉም በየፊናው ሲበተን እኔ  ጣሊያን ስደተኞች ካምፕ ውስጥ ገባሁ፡፡ ለስድስት ወራት ያህል  “ክርስቲያን ብራዘርስ” የተባሉ በጎ አድራጊዎች እየረዱኝ በካምፑ ተቀመጥኩ፡፡ ካምፑ ውስጥ ያሉ የተለያዩ አገር ስደተኞች በሞሉት ፎርም ላይ አሜሪካ ወይም ካናዳ መሄድ እንደሚፈልጉ ሲያሰፍሩ፣ እኔ  ግን ትምህርቴ  ለምን እንደተቋረጠ በመግለፅ የፒያኖ ትምህርቴን ቡልጋሪያ ሄጄ መቀጠል እንደምፈልግ ገለፅኩ፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቱም የኔን ጥያቄ ከሌሎች በመለየት ነገሮች ሲረጋጉ የትምህርት ክፍያውን እየከፈሉ ትምህርቴን እንድጨርስ ቡልጋሪያ  መልሰው ላኩኝ፡፡ በአጠቃላይ ሰባት አመት የፈጀውን የፒያኖ ትምህርቴን አጠናቅቄ ማስተርሴን ካገኘሁ በኋላ ተመልሼ ጣሊያን ሄድኩ፡፡
ትምህርቴን እንድጨርስ የረዳኝ ድርጅት አሮጌ ፒያኖ ቢሰጠኝ እያልኩ እመኝ ነበር፡፡ ጣሊያን አገር በቆየሁበት ጊዜ ኮንሰርት ሰርቼ ስለነበር እሱን ተከትሎ ድርጅቱ አዲስ ፒያኖ በሽልማት ሰጠኝ፡፡ አሮጌ ቢሰጡኝ እያልኩ ስመኝ ፋብሪካ ድረስ ሄጄ መርጬ ባለፒያኖ ሆንኩ፡፡ ያ ለኔ ትልቅ ደስታ ነበር የፈጠረልኝ፡፡
ፒያኖዋ ግን ሌላ ስጋት ይዛ መጣች…
አዎ ፒያኖዋ በአውሮፕላን ከኔ ቀደም ብላ ነበር አዲስ አበባ የገባችው፡፡ እኔ ከመጣሁ በኋላ ፒያኖዋን ለመውሰድ ስጠይቅ፣ የቅንጦት እቃ ስለሆነ ታክስ መክፈል አለብህ በሚል ሁለት ወር ተያዘች፡፡ ሁለት ወር ሙሉ በየቀኑ አየር መንገድ እመላለስ ነበር፤ ምክንያቱም ፒያኖዋ የተቀመጠችው ደጅ ላይ ስለሆነ ፀሀይና ዝናብ እንዳያበላሻት በየቀኑ እየሄድኩ የምትሸፈንበትን ላስቲክ አስተካክላለሁ፣ እቀይራለሁ፡፡ እዚያ አካባቢ ያሉ ሰዎች እንዲንከባከቡልኝም አደራ እላለሁ፡፡ በመጨረሻ የጣሊያንና የቫቲካን ኤምባሲዎች ጣልቃ ገብተው በስጦታ እንደተሰጠኝ ለኢትዮጵያ መንግስት በደብዳቤ አሳውቀውልኝ እጄ ገባች፡፡ ፒያኖዋን ስረከብ ገልጬ ሳያት ከወገቧ በታች ዝናብ ገብቶባታል፡፡ በጣም አዘንኩና አለቀስኩ፡፡ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ለምን እንደማለቅስ ግራ ገባቸው፤ አንዳንዶች ደግሞ ለእንጨት ያለቅሳል እንዴ ብለውኛል፡፡ በነገርሽ ላይ ይህ ታሪክ የእንግሊዝ መንግስትና አዲስ አበባ የሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ፣ ለኢትዮጵያ ሚሊኒዬም  በጋራ ባወጡት ትልቅ መፅሀፍ ውስጥ ከተካተቱ ታሪኮች አንዱ ነው፡፡
ክላሲካል ሙዚቃ ምን አይነት ሙዚቃ ነው? እኛ አገር በመሳሪያ ብቻ ከተቀነባበረ ሙዚቃ ጋር የመቀላቀል ነገር ይስተዋላል…
የክላሲካል ሙዚቃ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረ የሙዚቃ ስልት ሲሆን በረጅም ጊዜ የትምህርት ሂደት የሚገኝ የሙዚቃ ክህሎት ነው፡፡ ክላሲካል ሙዚቃን በልምድ መጫወት አይቻልም፡፡ የክላሲካል ሙዚቃ ተብሎ ሲነሳ  እነ ሞዛርት፣ ሀይደን፣ ቤትሆቨን የመሳሰሉት የሰሯቸው ስራዎች ይጠቀሳሉ፡፡
እኛ አገር ያለው የክላሲካል ሙዚቃ ተቀባይነት ምን ይመስላል?
አድማጭ አለው፤ አቅርቦት ግን የለም፡፡ ፒያኖ ማግኘት እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡ በዚህ የሙዚቃ ዘርፍ መውጣት የሚፈልጉ ብዙ ልጆች አሉ፤ ግን የክትትል ችግር አለ፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ የረጅም ጊዜ ስልጠና ይፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ተሰጥኦ ያላቸው ልጆች አሉ፡፡ እነሱን የሚፈልጉበት ለማድረስ ግን ብዙ ክትትል እና ድጋፍ ይፈልጋል፡፡
ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ማስተማሩን ለምን ተውከው?
እንዳልኩሽ ማስተማሩ በጣም ጊዜ ይጠይቃል፡፡ እኔ ደግሞ አጫጭር ኮርሶችን ስከታተልና ኮንሰርቶች ማሳየት ስጀምር፣ ቁጭ ብሎ የማስተማሩን ስራ እንዳያስተጓጉል በማለት ነው የተውኩት፡፡
 ቡልጋሪያ አስተማሪህ የነበሩትን ፕሮፌሰር አንተ በምታስተምርበት ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ኮንሰርት እንዲያሳዩ አድርገህ ነበር፡፡ እስቲ ስለሱ ንገረኝ…
ለእኔ እዚህ መድረስ የቡልጋሪያ አስተማሪዬ ፕሮፌሰር ኢታናስ ኮርቴሽ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ እንደመምህሬ ሳይሆን እንደ ወላጄ ነው የማየው፡፡ እሱን ኢትዮጵያ አምጥቶ ኮንሰርት እንዲያሳይ ማድረግ ደግሞ የረጅም ጊዜ ህልሜ ነበር፡፡ በ2011 የሀንጋሪያዊው አቀናባሪ የፍራንስ ሊስታ 200ኛ አመት በአለም አቀፍ ፌስቲቫሎች ይከበር ስለነበር፣ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ፣ እዚህ አገር ያሉትን የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አግባብቼ ፕሮፌሰሩ አዲስ አበባ መጥቶ ኮንሰርት እንዲያቀርብ ጠየቅሁና ተሳካ፡፡ ኮንሰርቱም ተሰራ፡
አንተም ባለፈው ጥር ቡልጋሪያ በተማርክበት አካዳሚ ኮንሰርት አቅርበሃል…
አዎ፡፡ ከዚያም በተጨማሪ በቫዮሊን፣ በቼሎ እና በሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎች አዲስ ስራ ሰርቻለሁ፡፡ ቡልጋሪያ የሄደኩት እሱን ለማስቀረፅ ነበር፡፡ የተማርኩበት አካዳሚ ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ተቀረፀ፡፡ ከዚያ እዚህ ያደረሰችኝን ቡልጋሪያን ኮንሰርት ሰርቼ ላመስግናት አልኳቸው፡፡ በጣም ደስ አላቸውና ኮንሰርቱን ሰራሁ፡፡ እነሱ የኔን የሙዚቃ እድገት እያንዳንዷን ደረጃ ይከታተሉ ነበር፡፡ ከኮንሰርቱ በኋላ “ቡልጋሪያን በተለያዩ የአለም መድረኮች እያስጠራህ ነው” ብለው  ትልቅ ሙያተኛና አስተዋፅኦ ላደረጉ ሰዎች የሚሰጠውን ከፍተኛ ሜዳሊያ ሸለሙኝ፡፡ በአሜሪካን በ2010 ዓ.ም ላይ  ትልቅ ኮንሰርት ተደርጎ ተሳትፌ ነበር፡፡ ሁለት የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች በሙዚቃ ዲፕሎማሲ የክብር እውቅና ሰጥተውኛል፡፡
የአሜሪካኑ የአልበም ማስመረቅ ፕሮግራም እንዴት ነበር?
የአሜሪካኑ ፕሮግራም  በጣም ውጤታማ ነበር፤ እንደምታይው ደስታው እስከአሁን ከፊቴ ላይ አልጠፋም፡፡ ሂደቱ ከተጀመረ ቆይቷል፡፡ “ኤምሲል ዎርልድ ሪከርድስ ሌብል”  በሚል የተባለ ኩባንያ ነው፡፡ ጥሩ ስራ የሰሩ ታዋቂ ሰዎችን ማስተዋወቅ ሲሆን ትልቁ ስራቸው ግን ያልታወቁ ሰዎችን መፈለግና ማስተዋወቅ ነው፡፡ “ስራህን በኢንተርኔት ላይ አይተነዋል፤ ጥሩ ነው እናስተዋውቅህ” ቢሉኝም ብዙዎች እንደዚያ እያሉ ተግባራዊ ስለማያደርጉት  አላመንኳቸውም ነበር፡፡ በኋላ ግን ስራዎቼን በአዲስ እንድቀርፅና ኮንሰርት እንዳደርግ የሚያስችል የስራ ፈቃድ እና ቪዛ ላኩልኝ፡፡ በ2013 ሄጄ ኮንሰርት አቀረብኩ፤ ስራዬንም ቀረፅኩ፡፡ በወቅቱ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በአድናቆት የተሞላ ፅሁፍ አወጣ፡፡ ሞራሌን በጣም ከፍ አደረገው፡፡ ከአንድ አመት በኋላ፣ ሰሞኑን ማለት ነው ሲዲዬን ለቀቅኩ፡፡ የአልበሙ መጠሪያ “ላቭ ኤንድ ፒስ” ነው፡፡ አልበሙ  ከፍተኛ ሽያጭ ነው ያስመዘገበው፡፡ በአሜሪካ የሙዚቃ ደረጃ በሚያወጣው የቢልቦርድ ሰንጠረዥም 23 ደረጃ ላይ ነበር፡፡ ከዚህ በፊት ከአርቲስት ሚካኤል በላይነህ ጋር የሰራሁት “መለያ ቀለሜ” የሚለው አልበምም በቢልቦርድ ሰንጠረዥ የገባ ሲሆን ለብቻዬ ከሰራኋቸው ውስጥ ግን የአሁኑ የመጀመሪያዬ ነው፡፡
የአሜሪካው ኮንሰርት ብዙ ኢትዮጵያውያን ታድመውት ነበር?
ብዙ ባይሆኑም ነበሩ፡፡ እንዲያውም ከኮንሰርቱ በኋላ እራት ጋብዘውኝ እንዴት አናውቅህም አሉኝ፡፡ ከጋባዦቼ አንዱ ደግሞ “አንተን የሙዚቃ ግርማ ሞገስ ብዬሀለሁ” አሉኝ፡፡ ይህ አባባል ለኔ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ አባቴ አስራ ሁለተኛ ክፍል ጨርሼ ዩኒቨርሲቲ ከተማርኩ በኋላ ወደ ስራ እንድገባ ነበር የሚፈልገው፡፡ የሙዚቃ ጉዞውን እንዳታደናቅፉት ብለው ብዙ እገዛ አድርገው ለዛሬ እኔነቴ የለፉት አጎቴ ናቸው፤ ስማቸው ደግሞ ሞገስ ነው፡፡ ግርማ ሞገስ ሲሉኝ በጣም ደስ አለኝ፡፡
ልጆችህን ፒያኖ እያስተማርክ ነው?
አዎ! የትምህርት ጊዜያቸውን ሳልሻማ በትርፍ ሰአት አስተምራቸዋለሁ፡፡
በሚቀጥለው ሐሙስ አዲስ አመት ነው፡፡ መጪውን  አመት እንዴት ትቀበለዋለህ?
እንግዲህ እድሜ አግኝቶ  አዲስ አመትን መቀበል  ትልቅ ነገር ነው፡፡ በተቻለ መጠን አዳዲስ ስራዎቼን እንዲሁም ተሰርተው የተቀመጡትን የማስተዋውቅበት አመት ይሆናል፣ ሌሎች ብዙ በሮችም ይከፈታሉ ብዬ በተስፋ እቀበለዋለሁ፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 06 September 2014 11:30

“ይድረስ ለእግዚአብሔር…”

    እሁድ ረፋዱ ላይ በአካባቢዬ ከሚገኝ አንድ ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ ቁጭ ብያለሁ፡፡ ወቅቱ ክረምት ቢሆንም፣ ዕለቱ ፀሐያማና ሰማዩም ጥርት ያለ ነው፡፡ በዚህ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለው ፀጥታ ደስ የሚያሰኝ ስሜትን ለልብ ይለግሳል፡፡
ወገባቸው ላይ አዳፋ ነጠላ ያሰሩ እናቶች፣ የቤተክርስቲያኑን ቅፅር ግቢ ይጠርጋሉ፡፡ አልፎ አልፎ ለመሳለም ወጣ ገባ ከሚሉ ሰዎች በስተቀር ግቢው ጭር ያለ ነው፡፡
የተቀመጥኩበትን የግንብ አጥር እየታከከ ከተዘረጋው ጣውላ የለበሰ ረጅም የግንብ መቀመጫ ላይ ራቅ ራቅ ብለው የተቀመጡ ወንድ ወጣቶች፣ አዛውንትና ጎልማሶች ይታያሉ፡፡ አንዳንዱ የፀሎት፣ ሌላው ደሞ ሌላ ዓይነት መጽሐፍ ያነባል፡፡ ዓይኖቻቸውን ከድነው ወደ ኋላ ግንቡ ላይ የተደገፉም አሉ፡፡ አካባቢው የወንዶች ስለሆነ፣ ሴቶች አይታዩም፡፡
 ድንገት በዛ ያሉ ሰዎች ፊት ለፊት ከሚታየው የቤተክርስቲያኑ የውጭ በር አጠገብ በደራሽ ውሃ ዓይነት ግር ብለው ሲሳለሙ ተመለከትኩ፡፡ ከአፍታ በኋላም በቀጥታ የግቢውን ሰፊ የአስፋልት ሜዳ በማቋረጥ ወደ ውስጥ ዘለቁ፡፡ ሁሉም በዕድሜ ከፍ ከፍ ያሉ እናቶች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ የውሃ ጄሪካንና ባልዲ አንጠልጥለዋል፡፡ እንስራ ያዘሉ፤ ጣሳ፣ ሸንኬሎ፣ ጠርሙስ፣ ማንቆርቆሪያ፣ ሳፋና ቅል የያዙም ይታያሉ፡፡ የለበሱትን አዳፋ ነጠላ አዘቅዝቀው መልበሳቸው አስከሬን ለመሸኘት የወጡ አስመስሏቸዋል፡፡ ከመሃከላቸው ጉልህና ጥቃቅን ጽሁፎች የሰፈሩባቸውን ትላልቅ ክርታሶች ከፍ ከፍ አድርገው የተሸከሙ እናቶችም አሉ፡፡ አካሄዳቸው የቀዘቀዘ ስሜት የሚነበብበት፣ የሰላማዊ ሰልፍ ዓይነትና ፍፁም ፀጥታ የተሞላበት ነው፡፡
እነዚህ ልዩ ሰላማዊ ሰልፈኞች፤ የቤተክርስቲያኑ መሳለሚያ በር አጠገብ ሲደርሱ፣ የያዟቸውን የውሃ መቅጃ ዕቃዎች መሬት ላይ በማኖር፣ ትላልቅ የክርታስ ጽሁፎች የተሸከሙት ደሞ በጥንቃቄ ግድግዳው ላይ በማስደገፍ፣ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ፡፡ ከሩቅ ለሚያያቸው፣ መሬት ላይ የተርከፈከፉ አዳፋ ቡትቶዎች ይመስላሉ፡፡ በየጥጋጥጉ ያለ ታዛቢ ከየተወሸቀበት እየወጣ ግርምታ በተቀየጠበት ዕይታ ያስተውላቸዋል፡፡ እኔም ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ወደ ሰዎቹ ተጠጋሁ፡፡ የቤተክርስቲያኑን ግድግዳ ተደግፈው ከተኮለኮሉት ትላልቅ ጽሁፎች መካከል አንደኛው ገዘፍ ያለና ከሁሉም ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡ አንዲት ሸበቶ፣ ፀጉራቸው ካሰሩት ሻሽ አፈትልኮ የወጣ፣ እናት መሬት ላይ እንደተደፉ የዚህን ትልቅ ጽሁፍ መቆሚያ እንጨት በአንድ እጃቸው አቅፈው ይዘዋል፡፡ ጽሁፉ ረዘም ያለ፣ ጎላ ጎላ ተደርጎ በጥቁር ቀለምና በሚያምር የእጅ ጽሁፍ የተጻፈ ነው፡፡ ቀልቤን  ስለሳበው ቀረብ ብዬ ለማንበብ ሞከርኩ፡፡
‹‹ይድረስ ለእግዚአብሔር፣›› የሚለው ርዕስ በእርግጥም ሁለመናን ይስባል፡፡ ርዕሱ በቀይ ነው የተጻፈው፡፡“…ውድ ታላቁና የሁሉ የበላይ የሆንከው ፈጣሪያችን፣ ያንተን ደህንነት መጠየቅ ስለማያስፈልግ እንዴት ነህ በማለት ጊዜህን ላባክንብህ አልፈልግም፡፡ የእኔን ደህንነት አንተም ስለምታውቀው፣ ለጊዜው ክብርህ ይስፋ፣ መንግስትህ ባስቸኳይ ወደ’ኛ ትምጣ ከማለት ሌላ ምንም የምለው የለኝም፡፡ ይልቁንም የዛሬውን ደብዳቤ ለመፃፍ የተገደድኩበትን ምክንያት አስቀድሜ በመግለጽ ወደ ጉዳዬ እገባለሁ፡
“ውድ እግዚአብሔር፡- የደብዳቤዬ ይዘት ልመናና አቤቱታ ነው፡፡ ወዳንተ የፃፍኩበት ምክንያት ደሞ አንተ እንደምድራችን ንጉሦች፣ ለአቤቱታና ለሰላማዊ ሰልፍ ፍቃድ የማትጠይቅ፣ ቅድመ-ሁኔታ የማታስቀምጥ፣ በቀጠሮ የማታጉላላ፣ አማላጅ አምጡ የማትል፣ የፖሊስ አጀብ የማትሻ፣ ሌላው ቢቀር ለደብዳቤ መስደጃ የሚሆን ቴምብር፣ ቀረጥና ሌሎችንም አምጡ የማትል ሃያል፣ የሁሉ ፈጣሪና በሁሉም ቦታ የምትገኝ በመሆንህ ነው፡፡ እንደምታየው በበሶ የታሸ የመሰለ ነጠላ ለብሼ ተደጅህ መምጣቴ፣ ንፅህናን ሳልፈልግ ቀርቼ እንዳልሆነ አንተም አትስተው፡፡ ጨርቄን የምጨፈጭፍበት አንድ ጣሳ ውሃ ባጣ ነው፡፡ እግሬ እንደመጅ ሻክሮ፣ ገጤም ዱቄት የተነፋበት ብረት ምጣድ መስሎ ፊትህ ለመቅረብ የተገደድኩበት ምክንያትም ይሄው ብቻ ነው፡፡
“የኔ መድሐኒአለም፣ኧረ ለመሆኑ ውሃና መብራት የምትከለክለን ምክንያቱ ምን አጥፍተን ነው? ኑሮው እንዲሁም አምሮበታል እንኳንስ የውሃና የኮረንቲው ችግር ተጨምሮበት! … ይቅርታ የኔ መድሐኒአለም ፣ እኔ የማውቀው እዚህ አለሁበት ሃገሬ ላይ የሚጠጣ ውሃና የምግብ ማብሰያ መብራት ማጣቴን እንጂ፣ በማንና በምን ምክንያት ይጥፋ አልተመራመርኩም፡፡ ለዚህ ነው ስለችግሩ አንተን ለመጠየቅና ለመውቀስ የተገደድኩት፡፡ ምናልባት፣ ልብ አድርግ ፈጣሪ፣ ምናልባት ነው ያልኩት፣ ምናልባት ችግሩ ወደ’ዚህ ወደ’ኛም አካባቢ ከሆነ፣ አሁንም ቢሆን እኔ ምስኪን ያንተዪቱ ከርታታ ባልቴት የምወቅሰውና አቤት ብዬ የማስቸግረው አንተኑ ነው፡፡ ምነው ሸዋ!…ደሞ ‹ይህን ስትይ፣ያንን ለማለት አስበሽ ነው፣…ምንትሴ ቅብርጥሴ፣› ተብዬ ዘብጥያ መወርወር አልፈልግም፡፡ ከምድራዊ መፍትሄ አፈላላጊ ተብዬዎች ሁሉ የበላይ የሆንከውን፣ በሰበብና በምኽኝያት መንገድ መዝጋት የማታውቀውንና ሁሉንም እንደየስራው አደብ የምታስይዘውን ሁሉን ቻይ ፈጣሪ አንተን ማስቸገር ይሻለኛል፡፡ ከአንተ ሌላ የምሮጥበት ሜዳ፣ የምገባበት ቀዳዳ የሌለኝ ፍጡርህ እንደሆንኩ ታውቀዋለህ፡፡
“ጌታዬ፣ ምነው ጨከንክብኝ! ምነው የልጆቼን ጉሮሮ የማረጥብበትን፣ ዱቄት በጥብጬ አብሽ የምግትበትን፣ ለማቲዎቼ ቂጣ እጠፈጥፍበት ዘንድ የጤፍ ዱቄት የማቦካበትን ውሃ የምታሳጣኝ! አሁን ያለሁበት ቦታ ከተማ ቢሆንም፣ ከየስርቻው ኩበትና እንጨት ለቃቅሜና ደጃፌ ላይ ጉልቻ ጎልቼም ቢሆን ጥርስ ላወጡት፣ ለትልልቆቹ ጥሬ ቆልቼ ማብላት አያቅተኝም፡፡ የቸገረኝ የትንንሾቹ ነው፡፡ …አይ የኔ ነገር…እንጨት ብል አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ መቼም ማብሰያ መብራቱ ቢጠፋም… ይሄ የእታጉ ልጅ፣ አቡሽ፣ ውሎ ይግባና የእንጨቱን ችግር ገላግሎኛል፡፡ ከየሄደበት በመኪናው ለእናቱ እየጫነ ሲመጣ፣ እኔንም አልረሳኝ፡፡ እባክህ፣ ለሰራው ደግነት በረከትህን አዝንብለት! ተዝቆ ከማያልቀው የዕድሜ ጎተራህ አፈስ አርገህ መርቅለት!
“መቼም ያልታደልሽ እንዴት አደርሽ ይባላል! …የማብሰያ መብራቱ ነገር በአያሌው የቸገረን ጉዳይ ሆኗል፡፡ የሰለጠንን መስሎን የሸክላውን ሰታቴና ምጣድ ወዲያ ብለን ስናበቃ፣ አሁን መብራት የሚሉት ነገር ጉድ ቢሰራን፣ ቅጥ አምባሩ ጥፍት ብሎብናል፡፡ በእንጨት ማብሰሉና መጋገሩ መቸ እንደ ጥንቱ ሆነና! በብረት ድስትና በእንጨት እሳት የሚበስለው ወጥና አጥሚት አሁን አሁን መላም የለው! … ሌላው ቢቀር፣ ምሽት ላይ የመንደሩ ሰው በየማደሪያው ገብቶ አልጋው ላይ እስኪሰፍር፣ ከጨለማ ይሻላል በሚል፣ተየደጃፉ ተጎልቶ ሲያንጎላጅ ነው የሚያመሸው፡፡ ይኸውልህ፣ አዳሜ ጀንበር በጠለቀ ቁጥር ሥራው ይሄ ሆኗል፡፡
“አሁን ለታ የተቦካ ሊጥ በፍራንክ የሚያስጋግሩ ሰዎች አሉ ቢሉኝ፣ ቡኻቃዬን ተሸክሜ ወደተባለው ስፍራ ሄድኩ፡፡ አላፊ አግዳሚው የለመደው በመሆኑ፣ የቾምቤ እናት ሊጧን ይዛ ባቡር መንገድ ላይ ትዞራለች ያለኝ አንድም ሰው አልነበረ፡፡ መቼም የወረፋው ነገር አይጣል ነው፡፡ ተራ ደርሶኝ አንድ-አምስት እንጀራ እንዳወጣሁ፣ አንድ ልጅ እግር ቢጤ መጥታ፣ ‹‹እማማ ፈጠን ፈጠን ይበሉ እንጂ! ብዙ ሰው ተራ እየጠበቀ እኮ ነው›› አለችኝ፡፡ እኔም፣ ‹‹ምነው፣ ልጄዋ! መቼም ሊጡን ተምጣድ ላይ አላወጣው›› ብላት፣ ‹‹ካልፈጠኑ መሄድ ይችላሉ፡፡ እንደውም ብዙ ለሚጋግሩት ነው ቅድሚያውን የምንሰጠው›› አለችኝ፡፡ ለካ ያችን ጎስቋላና ሽንቁሯ በጨርቅ የተወታተፈ ቡኻቃዬን አይታት ኖሯል ይሄን ማለቷ! አይ መጨካከን! ለአንድ እንጀራ ሁለት ብር እየተከፈለ ለሚጋገረው ይሄ ሁሉ ጥድፊያ የት ለመድረስ ነው!… ልጅቱ ብታጣድፈኝ አስፍቸው የነበረውን እንጀራ ገና ሳይበስል ተምጣዱ ላውጣው ብል፣ እንኩሮ ሆነና አረፈው፡፡ የተረፈች ሊጤን ሸክፌና አምስት እንጀራዬን በዳንቴል ሸፍኜ ወደ ቤቴ ተመለስኩ፡፡ መቼም ያን ለታ የገባኝን ብስጭት እኔና አንተ ብቻ ነን የምናውቀው፡፡ … ሆድ ብሶኝ ነው’ኮ! … ምናባቱንስና! አንዴ ለመድነውና ነውዪ ስለኮረንቲው ማውራቴ፣ የሱስ ነገር ላንተ ተሚወራ ቢቀር ነው የሚሻለው፡፡ እንደው ተውሃና ተኮረንቲውስ ያው ውሃው ቢኖር ይሻለናል፡፡ ጌታዬ፣ መቼም… ሁለቱም ቢኖሩ ደግ ነው፡፡ ግና ተሁለቱ ምረጭ ብትለኝ፣ እኔ’ቴ! የምን ኮረንቲ…ውሃው አስር እጅ ይበልጥብኛል፡፡ ያለውሃ ምን ዓይነት ኑሮ ይኖራል ብለህ ነው! … ኤዳልኝ ኤዳ!!
“የኔ መድሐኒአለም፣ ድሮ በንጉሡ ጊዜ አምስት እንስራ ውሃ በሁለት ፍራንክ (አምስት ሳንቲም) እንዳልገዛን፣ አሁን ለአንዲት ጄሪካን ውሃ አንድ ባውንድ ክፈሉ ይሉናል፡፡ አቤት ጭካኔ! አስከሬን ለሚታጠብበት! ምነው፣ የኔ ጌታ፣ ፍዳችንን አበዛህብን! … አንተ ሆነህ ነውዪ እንደምድሩ የዘመኑ ጭቃ ሹሞችና መኳንንት ቢሆንማ ኖሮ፣ ስለንጉሡ ትንፍሽ ማለት መዘዙ የከበደ በሆነ ነበር! ደሞ በዚህ በአሮጌ ዕድሜዬ ‹የቀድሞ ሥራት ናፋቂ› ብለው የልኬን ያስገቡኝ! … የሆነስ ሆነና፣ ጌታዬ፣ምነው እንዲህ ጨከንክብን! አንዱን ስታጠጣ ሌላውን በጥም መግደልህ፣ ምነው!
“አሁን ለታ ባለቤቴ ባሻ፣ ቢቸግረው እንደጥንቱ እንደጠዋቱ ተግቢያችን ውስጥ የውሃ ጉድጓድ ታልቆፈርኩ ብሎ ቢነሳ፣ የቤቴ ማቲ ሁላ አይሆንም በማለት አገረገረ፡፡ ‹‹ምነው፣ ለምን አይሆንም? ፊት የጉድጔድ ውሃም አይደል ጠጥተን የኖርነው፣›› ብሎ ቢጠይቅ፣ ‹‹አሁን ከተማይቱ ስላደገችና የጉድጓድ ውሃ በየምኽኛቱ ስለሚበከል ለጤናችን ደግም አይደል… ምንትሴ ቅብርጥሴ›› አሉና ነገሩን አጣጣሉት እልሃለሁ፡፡ ድንቄም…! ኧረ እናንተው፣ ታዲያ በውሃ ጥም መሞት ይሻላል ነው የሚሉት! ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረ ጉዳይ ነው’ኮ እናንተው! ተንግዲህ ወዲያማ፣ አንተ ፈጣሪ ብቻ ነህ ሚሆነውን ምታውቀው!
በያ ሰሞን የጦሙ ለት ቤተክርስቲያን ለብሼ የምሄደውን ነጠላዬን የምለቀልቅበት ውሃ ባጣ፣ ይኸውልህ አሻሮ የተሰጣበት የመሰለውን ጨርቅ ተከናንቤ ግቢህን ስጠቀጥቅ ሰነበትኩ፡፡ አበስኩ ገበርኩ! …አይ የኔ ነገር… የምጠጣው የለ ስለሸማ መጨፍጨፊያው መቀባጠሬ!…ዘንድሮ የጤናዬን ነው ብለህ ነው! የተመቸው ገንፎ ያላምጣል፣አሉ! …
“ጌታዬ መድሐኒአለም ሆይ፣ አንተንም አስጨነቅሁህ፡፡ የት ልግባ ታዲያ! የምሮጥበት ሜዳ፣ የምገባበት ቀዳዳ ያጣሁ ያንተው ከርታታ አይደለሁ! … ምን ላድርግ! ያላንተ ማን አለኝና ብሶቴን ልተንፍሰው! አንተ ብቻ ነህ የድሃን ብሶት የምታደምጠው፡፡ የምድሩ ጌቶቻችንማ ታንጀት ጠብ በማይል እሰጥ አገባ ነው ሥራ ሲያስፈቱን የሚውሉት! …የኔ አባት፣ እውር አሞራን የምትመግብ የሰራዊት ጌታ፣ ምነው ረሳኸን! ጉሮሯችንን የምናርስበት፣ አብስለን የምንጎርስበት፣ አጥድተን የምንከናነብበት፣ ጭቅቅታችንን የምናራግፍበት ትንሽ ውሃ እንኳን የነፈግኸን በየትኛው ኃጢያታችን ነው!
“መድሐኒአለም ሆይ፣ በል እንግዲህ ችግሩ ቢጠናብኝ ነው ነገር መደረቴ… አሁንም ተራ ውሃ ብቻ ሳይሆን ተውሳኩን ሁሉ የሚከላ ጠበል የሆነውን ዝናብህን ትሰጠን ዘንድ ተደጅህ ተደፍቼ እለምንሃለሁ፡፡ እኔም ሆንኩ መሰሎቼ፣ የቻለ ጄሪካንና እንስራ፣ ያልቻለ ባልዲ፣ ሳፋ፣ ሸንኬሎ፣ ገረወይና፣ ቅል፣ ጠርሙስ፣ መዘፍዘፊያ… ባጠቃላይ ውሃ መያዣ የሆነውን ሁሉ ተሸክሞ በናፍቆት ይጠብቅሃል፡፡ ዝናብህ ለጥማችን መቁረጫ ብቻ ሳይሆን፣ ለክፋታችን ማንጫ እንደሚሆነን ፍፁም እምነቴ የፀና ነው፡፡ መቼም ለልመናዬ አንጀት አርስ ምላሽህን በመስጠት እንደምታስደስተኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ያንተው…”

Published in ጥበብ

           የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሞሮኮ ወደ 30ኛው አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በምድብ 2 ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታው ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድዬም አልጄርያን ያስተናግዳል፡፡ በምድቡ ሌላ ጨዋታ ባማኮ ላይ ማሊ ካሙዙ በተባለው ስታድዬም ከማላዊ ትገናኛለች፡፡
በምድብ 2 ያሉት አራት ቡድኖች የምስራቅ፤ የሰሜን ፤ የደቡብ እና የምእራብ አፍሪካ ዞኖችን በመወከል ከፍተኛ ፉክክር የሚያደርጉ ሲሆን ማጣርያውን በመሪነት በማጠናቀቅ እንደምታልፍ ቅድሚያ ግምቱን የወሰደችው አልጄርያ ብትሆንም  ኢትዮጵያ እና  ማሊ  የማለፍ እድል እንደሚኖራቸው የተለያዩ ትንተናዎች አመልክተዋል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ 10 ጊዜ የተሳተፈችው ኢትዮጵያ በ1962 እኤአ ሻምፒዮን ስትሆን 14 ጊዜ የተሳተፈችው አልጄርያ ደግሞ በ1990 እኤአ ዋንጫውን ወስዳለች፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ሁለት ጊዜ የተሳተፈችው ማላዊ በሁለቱም ከመጀመርያው ዙር ስትሰናበት፤ በአፍሪካ ዋንጫ 8 ጊዜ የተሳተፈችው ማሊ ትልቁ ውጤቷ በ1972 እኤአ ላይ ሁለተኛ ደረጃ ያገኘችበት ነው፡፡
የምድቡ ሁለተኛ ዙር የማጣርያ ጨዋታዎች ከአራት ቀናት በኋላ ይቀጥላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ በመጓዝ በብላንታዬር ከተማ በሚገኘው  ስታዴ ዱ 26 ማርስ  ስታድዬም ማላዊን የሚገጥም ሲሆን አልጄርያ በዋና ከተማዋ አልጀርስ ላይ ማሊን ታስተናግዳለች፡፡
ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም ለሚካሄደው የኢትዮጵያና አልጄሪያ ጨዋታ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የህዝብ ግንኙነቱ መግለጫ ያመለክታል፡፡
የስታድዬም መግቢያ ትኬት ሽያጭ ስርዓቱን እንዲጠብቅ ፌዴሬሽኑ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን ገልፆ፤  ከጨዋታው በፊት የዋሊያዎቹ ብቸኛ ስፖንሰር ከሆነው በደሌ ስፔሻል ጋር በመተባበር የተለያዩ አዝናኝ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ አስታውቋል፡፡ በዚህ መሰረት ለኢትዮጵያና አልጄሪያ ጨዋታ የመግቢያ ዋጋ ከሚስማር ተራ እስከ ጥላ ፎቅ 10፣ 20፣ 30 ፣100 ፣500 ብር  እንዲሁም ክቡር ትሪቢዩን ብር 1000 እንዲሆን ተወስኗል፡፡  በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ስታድዬም የሚካሄደው የኢትዮጵያ እና አልጄርያ ጨዋታ በዲኤስቲቪ እና በስፖርት ፋይቭ ቻናሎች የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭት ይኖረዋል፡፡
በተለይ ስፖርትፋይቭ የተሰኘውና ሁሉንም የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያና የመጨረሻ ጨዋታዎች የማሰራጨት ሙሉ መብት ከካፍ የተሰጠው የማርኬቲንግና የሚዲያ ኩባንያ የመደባቸው ከ20 በላይ ከፍተኛ ሙያተኞች ይህንን ወሳኝ ጨዋታ በሳተላይት ስርጭት ለማስተላላፍ ሰሞኑን ከነሙሉ የማሳራጫ መሳሪያዎቻቸው አዲስ አበባ እንደገቡ ፌደሬሽኑ አስታውቋል፡፡
ከመቼውም ጊዜ በላቀ ደረጃ የተዘጋጁት ዋልያዎች በሜዳቸው አጀማመራቸውን ማሳመር ይፈልጋሉ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሞሮኮ ወደ 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው የምድብ ማጣርያ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ ከሁለት ወራት ከፍተኛ ዝግጅት አድርጓል፡፡ በፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ የሚመራው ቡድኑ ዝግጅቱን እንደጀመረ ከሜዳው ውጭ ከአንጎላ ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ 1ለ0 ተሸንፎ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ወደ ብራዚል በመጓዝ ጠንካራ ዝግጅት ነበረው፡፡ በብራዚል በነበረው ቆይታ ከመደበኛ ልምምዶች ጎን ለጎን በአገሪቱ አራተኛ ዲቭዝዮን ከሚወዳደሩ 5 ክለቦች ጋር  የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ ከአናፖሊ ጋር 2ለ2፤ ከክለብ ጋማ ጋር 1ለ1 አቻ ሲለያዩ፤ በክለብ ዶ ሮምዮ እና በሊውዚና በተመሳሳይ 1ለ0 እንዲሁም ብራዚሊኒሴ 2ለ0 ተሸንፏል፡፡
ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ብሄራዊ ቡድኑ ለሁለት ሳምንታት በብራዚል ያደረገው የዝግጅት ቆይታ ጠቀሜታው ያመዘነ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫው የምድብ ማጣርያ የመጀመርያ ሁለት ዙር ግጥሚያዎች ሊገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ነጥብ ለመሰብሰብ ዝግጁ ነን ያሉት ዋና አሰልጣኙ፤ ቡድኑ በብራዚል በነበረው ቆይታ በፕሮፌሽናል የግብ ጠባቂ እና የአካል ብቃት አሰልጣኞች በቀን ሁለቴ ልምምዶቹን በተሟላ የስፖርት መሰረተ ልማት መስራቱ እንዳረካቸው ተናግረዋል፡፡
በዛሬው ጨዋታ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ የታመነባቸው እና ከአገር ውጭ የሚጫወቱት የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች ከባለፈው ማክሰኞ ጀምሮ  አዲስ አበባ በመግባት ልምምድ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ጋር በብራዚል በነበረው ዝግጅት ባይሳተፉም ፤ በግብፆቹ ክለቦች አልሂላልና አልኢትሃድ አሌክሳንድርያ የሚጫወቱት ሳላዲን ሰኢድ እና  ኡመድ ኡክሪ እንዲሁም በሱዳኑ ክለብ አልሃሊ ሸንዲ የሚገኘው አዲስ ህንፃ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ለ1 ሳምንት ከቡድኑ ጋር ለመቀናጀት ሰርተዋል፡፡በደቡብ አፍሪካው ቢድቬስት ዊትስ የሚጫወተው ጌታነህ ከበደም ቡድኑን በመጨረሻ የተቀላቀለ ሌላኛው ወሳኝ ተጨዋች ነው፡፡
የዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎቹ ሳላዲን፤ ኡመድ እና ጌታነህ ከኢትዮጵያ ውጭ በሚጫወቱባቸው ክለቦች በከፍተኛ ብቃት ላይ መቆየታቸው ለምንፈልገው ውጤት አስደሳች ዜና ነው በማለት ለሱፕር ስፖርት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ባሬቶ በብራዚል በነበሩበት ጊዜ የቡድናቸውን አቅም ለማጠናከር በየትኛውም አገር እና  ክለብ ለሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች ጥሪ ሲያቀርቡ ሁሉም ተጨዋቾች ለቀረበላቸው ግብዣ በደስታ ምላሻቸውን ገልፀው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ከቀረበላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ተጨዋቾች መካከል  በስዊድኑ ክለብ ቢኬ ሃከን የሚገኘው ዩሱፍ ሳላህ ቡድኑን በመቀላቀል ብቸኛው ነው፡፡ በሌላው የስዊድን ክለብ ኢክ ሲሩስ የሚጫወተው ዋዲል አታ ጥሪውን ቢቀበልም ባለቀ ሰዓት በደረሰበት ጉዳት በብሄራዊ ቡድኑ ለመካተት ሳይሆንለት ቀርቷል፡፡ እንዲሁም በኖርዌይ ሊግ ለሚጫወት ክለብ የሚሰለፈው አሚን አስካር ብሄራዊ ቡድኑን በቀጣይ የማጣርያ ጨዋታዎች ለመቀላቀል ፍላጎቱን እንዳለው ተናግሯል፡፡
በአፍሪካ እግር ኳስ አንደኛ ደረጃ የያዘችው አልጄርያ፤ በፕሮፌሽናሎች ስብስብ ተጠናክራና በዓለም ዋንጫ ልምድ ገዝፋ ትቀርባለች
ጋዜጠኞችን ጨምሮ 70 ያህል ተጨዋቾች አሰልጣኞች ሃኪሞችና የቡድን መሪዎች የሚገኙበት የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ሙሉ ለሙሉ ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ ገብቷል፡፡  ፈረንሳዊው የአልጀሪያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ክርስቲያን ጉርኩፍ  በምድብ 2 ከኢትዮጵያ እና ከማሊ ጋር በአንድ ሳምንት ልዩነት የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች አጠቃላዩን የማጣርያ ጉዞ የሚወስን አጀማመር እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡ ዋና አሰልጣኙ ከሶስት ሳምንት በፊት  ከኢትዮጵያ እና ከማሊ ጋር በሚደረጉ ጨዋታዎች የሚያሰልፏቸውን የ27 ተጨዋቾች ስም ዝርዝር  አስታውቀዋል፡፡  
የተጨዋቾች ስብስቡ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ አልጄርያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጥሎ ማለፍ ምእራፍ ያበቋት በብዛት ሲገኙ፤ 23 ያህሉ በተለያዩ አገራት በፕሮፌሽናልነት የሚጫወቱ ናቸው፡፡ በፖርቱጋል፤ ስፔን እና እንግሊዝ ክለቦች የሚሰለፉ ምርጥ ተጨዋቾች የበዙበት የአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን እንደኢትዮጵያ አቻው በቂ የዝግጅት ጊዜ አልነበረውም፡፡ በአጠቃላይ ግን ቡድኑ ባለው የተደራጀ ፕሮፌሽናል አቅም እና የዓለም ዋንጫ ልምድ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆን ተጠብቋል፡፡ ከ3 ሳምንታት በፊት አልቤርቶ ኤቦሲ የተባለ ካሜሮናዊ ተጨዋች በስታድዬም ከነበሩ ደጋፊዎች በተወረወረ ቁስ ህይወቱ በማለፉ  የአልጄርያ እግር ኳስ ከማንኛውም እንቅስቃሴ እንዲታገድ ምክንያት ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ በብሄራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ላይ የሚፈጥረው ተፅእኖ እንደሌለ የአገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሽን ገልጿል፡፡  የአልጀሪያ ብሔራዊ ቡድን በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ  በአፍሪካ አንደኛ መሆኑና ከዓለም ዋንጫ ተሳትፎ በኋላ ወደ ትልልቅ የአውሮፓ ክለቦች ስኬታማ ዝውውር ያደረጉ ተጨዋቾች በስብስቡ መብዛታቸው የቡድኑን ወቅታዊ ጥንካሬ ያመለክታል፡፡

          የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት  ጊዜው የኢትዮጵያ እንደሆነ ሱፐር ስፖርት ዘገበ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሊቢያን በመተካት በ2017 እ.ኤ.አ ላይ 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ እንደሚፈልግ ያስታወቀው ከ2 ሳምንታት በፊት ሲሆን በኦፊሴላዊ ደረጃ ለካፍ ማመልከቻ ስለማስገባቱ ግን የታወቀ ነገር የለም፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን  ሊቢያን በመተካት  አዘጋጅነቱን ለሚያመለክቱ አገራት የሰጠው የግዜ ገደብ  3 ሳምንታት ይቀሩታል፡፡ ኢትዮጵያ አመልክታ ተቀባይነት ካገኘች ለ4ኛ ጊዜ የምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ይሆናል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በወጡ ዘገባዎች ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ መስራች እንደነበረች በማስታወስና ባለፉት 3 ዓመታት ለ31 ዓመታት ከውድድሩ የራቀችበትን ሁኔታ በቀየረ የእግር ኳስ ለውጥ ላይ እንደምትገኝ በመግለፅ አዘጋጅነቱን ብታገኝ ይገባታል ብለዋል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት በአፍሪካ የኢኮኖሚ፤ የፖለቲካ እና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ መናሀርያነት የምትጠቀሰው  ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ፍላጎት እንዳላት ገልፆ የዘገበው ቢቢሲ ነበር፡፡ በወቅቱ በአዲስ አበባና  በባህርዳር  ሁለት ዝግጁ ስታድዬሞች መኖራቸውን ለቢቢሲ የተናገሩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ሲሆኑ ፤ በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ደረጃቸውን የጠበቁ ስታድዬሞች ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑን በመጥቀስ ውድድሩን ለማስተናገድ ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የፊፋ እና የኦሎምፒክ ስታንዳርድን የሚያሟላ እና 60ሺ ተመልካች የሚያስተናግድ ብሄራዊ ስታድዬም በአዲስ አበባ ለመስራት እቅድ እንዳላት የገለፀው የሱፕር ስፖርት ዘገባ ሶስት አፍሪካ ዋንጫዎችን ያስተናገደው የአዲስ አበባው ብሄራዊ ስታድዬምም ከፍተኛ እድሳት ተደርጎለት ለመስተንግዶ ሊደርስ እንደሚችል ጠቅሷል፡፡
በ2017 እኤአ ላይ 31ኛውን አፍሪካ ዋንጫ እንድታዘጋጅ  ተመርጣ የነበረችው ሊቢያ  መስተንግዶውን የተወችው በአገሪቱ በቂ ሰላምና መረጋጋት አለመስፈኑ በፈጠረባት እክል እንደሆነ ያስታወቀችው ከሶስት ሳምንት በፊት ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ባወጣው መግለጫ  እንዳመለከተው ሊቢያ ለውድድሩ የሚያስፈልጉ ስታድዬሞችን በመገንባት እንደማይሳካላት እና በአስተማማኝ ፀጥታ ውድድሩን ለማካሄድ እንደማትችል አረጋግጫለሁ በማለት ለአባል ፌደሬሽኖቹ ምትክ አዘጋጅን ለማግኘት ጥሪ አቅርቧል፡፡
ሱፕር ስፖርት  ጊዜው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን የምታዘጋጅበት ነው በሚል ርእስ በሰራው ዘገባ በኢትዮጵያ ስፖርት ዙርያ ባሉ ባለድርሻ አካላት የተሰጡ አስተያየቶች የመስተንግዶውን ፍላጎት አድርገውታል፡፡ ለሱፕር ስፖርት በሰጡት አስተያየት አፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ያለንን ፍላጎት መላው ኢትዮጵያዊያንና እና የአፍሪካ አገራት ከደገፉት ይሳካል ያሉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ  ናቸው፡፡
‹‹የአፍሪካ ዋንጫን ማዘጋጀት፤ በአህጉሪቱ እግር ኳስ ያለንበትን ከፍታ ለማሳየት እድል ይፈጥራል›› ብሎ የተናገረው ደግሞ ኤልሻዳይ ነጋሽ የተባለው ታዋቂ ጋዜጠኛ ነው፡፡ አዲስ አበባ በአፍሪካ የባቡር ሜትሮ ኔትዎርክ ካላቸው ጥቂት ከተሞች አንዷ መሆኗን፤ በመሰረተ ልማት እየተጠናከረች መምጣቷን ለሱፕር ስፖርት የገለፀው ኤልሻዳይ  ፤ የፓን አፍሪካኒዝም መዲና በሆነች ከተማ ውድድሩ መዘጋጀቱ ተገቢ ነው በማለት ድጋፉን ገልጿል፡፡ ‹‹የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለውድድሩ አዘጋጅነት ፍላጎት ማሳየቱን ስሰማ በጣም ጉጉት ፈጥሮብኛል፡፡ ለእኛ ተጨዋቾች አፍሪካ ዋንጫን በሜዳችን በደጋፊችን ፊት መጫወት ከፍተኛ ሞራል እና መነቃቃትን የሚፈጥር ይሆናል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ፌደሬሽኑን እና መንግስትን በሙሉ አቅም መደገፍ አለባቸው፡፡  በዚህም አፍሪካ ዋንጫ የማዘጋጀት ህልምን ማሳካት ይቻላል፡፡›› በማለት ለሱፕር ስፖርት የድጋፍ አስተያየት ያቀበለው የብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋች አበባው ቡጣቆ ነው፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ ወሳኝ የአማካይ መስመር ተሰላፊ የሆነው ሽመልስ በቀለ በበኩሉ ‹‹አስደሳች  እና ታላቅ ዜና ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነት እንደሚሳካላት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡   አዘጋጅ ሆነች የሚለውን ዜና በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡›› በማለት ተናግሯል፡፡
ከ29 የአፍሪካ ዋንጫዎች በአስሩ ላይ መሳተፍ የቻለችው ኢትዮጵያ ለሶስት ጊዜያት የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ነበረች፡፡ በ1962 ውድድሩን በማዘጋጀት ሻምፒዮን ስትሆን እንዲሁም በሌሎች ባዘጋጀቻቸው ሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች በ1968 እኤአ ላይ አራተኛ ደረጃ እና በ1976  እኤአ ደግሞ ከመጀመርያው ዙር ከውድድሩ ተሰናብታለች፡፡ ከኢትዮጵያ ሌላ የውድድሩን አዘጋጅነት ለመረከብ ፍላጎታቸውን የገለፁት አገራት አምስት ደርሰዋል፡፡ የመጀመርያዋ ኬንያ ስትሆን የአፍሪካ ዋንጫውን ከጐረቤቶቿ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ እና ሩዋንዳ ጋር በጣምራ የማዘጋጀት ጥያቄ አቀርባለሁ እያለች ነው፡፡ የምእራብ አፍሪካዋ ጋና እና የደቡብ አፍሪካዋ ዛምቢያም አዘጋጅነቱን እንደሚፈልጉ ሲያስታውቁ በመጨረሻም ለመስተንግዶ ፍላጎቷን እያሳየች የመጣችው አልጄርያ ናት፡፡ 16 ብሄራዊ ቡድኖች የሚሳተፉበትን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ዓለም አቀፍ ደረጃን የሚያሟሉ ስታድዬሞች፤ የሆቴል እና የትራንስፖርት መሰረተልማቶች እጅግ ወሳኝ ሲሆኑ እስከ 55 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደሚያስፈልግም ይገመታል፡፡

       በኢትዮጵያ እናቶች በአማካይ በሕይወት ዘመናቸው የሚወልዱት ልጅ መጠን በ2005 /5.4/ በ2011 /4.8/ (DHS)› ሲሆን በ2015 ይህን ቁጥር ወደ /4.4/ ዝቅ የማድረግ እቅድ ተይዞአል ፡፡ በዚህ ዙሪያ በተለይም ቋሚና የረዥም ጊዜን የመከላከያ ዘዴዎች ጠቀሜታን እና የጎንዮሽ ጉዳታቸውን ዶ/ር ነጋ ተስፋው የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት አብራርተዋል፡፡ ዶ/ር ነጋ  በአሁኑ ወቅት በማሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የጥራትና የህክምና አገልግሎት ዳይሬክተር ሆነው ይሰራሉ፡፡
ጥ/ የረዥም ጊዜ የእርግዝና መከላከያዎች ሲባል ምን ማለት ነው?
መ/ የእርግዝና መከላከያዎች የተለያዩ ናቸው፡፡ በተወሰነ የጊዜ እርቀት ወይንም በየእለቱ ከሚወሰዱት በኪኒን መልክ እና በመርፌ ከተዘጋጁት ውጪ ለረዥም ጊዜ እንዲሁም በቋሚነት እርግዝናን ለመከላከል የሚያስችሉ ዘዴዎች አሉ፡፡ የረጅም ጊዜ የሚባሉት በማህጸን ውስጥ እስከ 12/ አመት ድረስ መቀመጥ የሚችል (IUD) ወይንም ሉፕ እና በክንድ ቆዳ ስር እስከ አምስት አመት ድረስ በመቆየት ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከል የሚችያስችል የህክምና ዘዴ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱም መከላከያዎች 99 % ያህል አስተማማኝ የእርግዝና መከላከያዎች ሲሆኑ ሕክምናው የሚሰጠውም ለሴቶች ነው፡፡
ጥ/ (IUD)  ሉፕ የተባለው የረዥም ጊዜ የእርግዝና መከላከያ በማህጸን ውስጥ ለ12/አመት ያህል ሲቆይ ችግር አያመጣም?
መ/ (IUD)  ሉፕ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ላይ የሚውል በመሆኑ እንደመርፌ ወይንም እንክብል በየጊዜው ውሰዱኝ የማይል እና ጊዜውን በትክክል ባለመጠበቅ ምክንያት ችግር የሚያስከትል አይደለም፡፡ ምናልባትም ሕክምናው በተሰጠ ለመጀመሪያዎቹ የሶስት ወራት የወር አበባ መዛባት ሊያስከትል ቢችልም ይህም ጊዜ ሳይፈጅ የሚስተካከል በመሆኑ ምንም አያሳስብም፡፡ በማህጸን ውስጥ ለረጅም ጊዜ ወይንም እስከ 12/አመት ድረስ በመቆየቱም የመመረዝ ወይንም የመቆሸሽ እድል የማይገጥመው ሲሆን በየመሀሉ ማውጣት የሚያስፈልገው አይደለም፡፡ ተጠቃሚዋ በፈለገችው ጊዜ እንዲወጣ ከማድረግ በስተቀር እስከ12/ አመት ድረስ ካለምንም ችግር ሊቆይ የሚችል አስተማማኝ የመከላከያ ዘዴ ነው፡፡ ..ህ.... ሉፕ ቀላል የሆነ የመከላከያ ዘዴ ሲሆን ለተጠቃሚዎችም ምቹ የሆነ እና ከባድ የጤና ችግር የማያስከትል ተስማሚ የሆነ የህክምና ዘዴ ነው፡፡
ጥ/ (IUD)   ሉፕ የተባለው የእርግዝና መከላከያ አንዳንዴ እርግዝናን ሳይከላከል ከልጅ ጋር አብሮ ይወለዳል?
መ/ በመጀመሪያ ደረጃ የረጅም ጊዜ የእርግዝና መከላያ (IUD)   ሉፕ 99 % ያህል እርግዝናን የመከላከል አቅም ያለው ስለሆነ እርግዝናው ይከሰታል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ከኑሮ ሁኔታ ወይንም የግብረስጋ ግንኙነቱ ባህርይ በሚፈጥረው ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ እርግዝናው ቢከሰት እርግዝናው ጊዜው ሳይገፋ ክሩ የሚታይ ከሆነ ሉፑን በቀላሉ ስቦ ማውጣት ይቻላል፡፡ምናልባት ትኩሳት ወይንም የደም መፍሰስ ቢያጋጥም ግን ወደሐኪም በመሔድ መታየት ያስፈልጋል፡፡  ሳይታወቅ እርግዝናው የገፋ እና (IUD)    ሉፑም ክሩ የማይታይ ከሆነ ግን ከልጁ ጋር አብሮ ቢወለድ ምንም ጉዳት አያስከትልም፡፡ በአጠቃላይ ግን (IUD)    ሉፕ በማህጸን ውስጥ በሚቀመጥበት ጊዜ የሚሰጥ የህክምና ባለሙያዎች ምክር ስለሚኖር ያንን በትክክል ተግባራዊ ማድረግ ከተጠቃሚዎች ይጠበቃል፡፡
ጥ/ ቋሚ የእርግዝና መከላከያዎች ምን አይነት ናቸው?
መ/ ቋሚ የሚባለው የእርግዝና መከላከያ  በቀዶ ሕክምና ለሴቷም ሆነ ለወንዱ የሚሰጥ የመከላከያ ዘዴ ነው፡፡  ቋሚ የሚባለው የእርግዝና መከላከያ ዘዴ በተለያየ የጋብቻ ሁኔታ ፣የስራ መስክ ፣የእድሜ ክልልና የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ተጨማሪ ልጅ ለመውለድ የማይፈልጉ ሴቶችና ወንዶች የሚመርጡት ዘመናዊ ዘዴ ነው፡፡ ይህ የቤተሰብ እቅድ ዘዴ ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች በቀላል የቀዶ ሕክምና የሚሰጥ ፣ ለሕይወት ዘመን በቋሚነት እርግዝናን የሚከላከል አስተማማኝና በጤና ላይ ምንም ጉዳት የማያስከትል ነው፡፡ ለሴቷ የሚደረገው ቋሚ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ የዘር መተላለፊያውን ቱቦ በመቋጠር ሲሆን የወንዱ ቋሚ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ የወንዱ የዘር ፈሳሽ መተላለፊያን በመቋጠር እርግዝናን በቋሚነት መከላከል የሚያስችል ዘዴ ነው፡፡
ጥ/ ከቀዶ ሕክምናው በሁዋላ ተጠቃሚዎች ምን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል?
መ/ ቀዶ ሕክምናው በጣም ቀላል በመሆኑ ምክንያት ከጥቂት ቆይታ በሁዋላ አገልግሎቱን ያገኙ ሁሉ ወደቤታቸው ይሄዳሉ፡፡ በተለይም ሴቶች ከሆኑ ለሁለት ቀናት ያህል በቤታቸው ከባድ ስራን ከመስራት እንዲቆጠቡ እና በቂ እረፍት እንዲያደርጉ ይመከራል፡፡ ሴቶች ለአንድ ሳምንት ወይንም ቁስሉ እስኪድን ድረስ ከግብረስጋ ግንኙነት መታቀብ ይኖርባቸዋል፡፡ ወንዶችን በሚመለከት ከቀዶ ሕክምናው በሁዋላ እንደሴቶቹ ለሁለት ቀናት ያህል በቂ እረፍት ማድረግ የሚገባቸው ሲሆን የግብረስጋ ግንኙነትን በሚመለከት ግን ከቀዶ ሕክምናው በሁዋላ ለሶስት ወራት ያህል የማስረገዝ እድል ስለሚኖር  መታ ቀብ፣ ሚስትየዋ ሌላ ዘዴ እንድትጠቀም ማድረግ ወይንም ኮንዶም ሁልጊዜና በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
ጥ/    አገልግሎቱን ያገኙ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ተመልሰው ወደጤና ድርጅት መሄድ ያስፈልጋቸዋልን?  
ሴቶች
* ከፍተኛ ትኩሳት፣
* በታችኛው የሆድ ክፍል ከባድ ሕመም፣
* የቁስሉ እብጠት ቅላትና መመርቀዝ.. መምገልና መድማት..  የሚያዩ ከሆነ በፍጥነት ወደሕክምናው ተቋም መሄድ ያስፈልጋቸዋል፡፡
ወንዶች
* ቀዶ ሕክምናውን ካደረጉ ከጥቂት ቀናት በሁዋላ በቀዶ ሕክምናው ቦታ ላይ እብጠት ከተፈጠረ፣
* ቁስሉ ከመድረቅ ይልቅ የማመርቀዝ ፣የመድማት ወይም የመምገል ምልክት ካሳየ ወደ ሕክምና ተቋም መሔድ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ጥ/ ቋሚ የእርግዝና መከላከያ ምን ያህል ተጠቃሚ አለው?
መ/በአለም አቀፍ ደረጃ ሁለቱም ማለትም ወንዶችም ይሁኑ ሴቶች በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ  ሆነው ይታያሉ፡፡ በአገራችን ግን እስከአሁን በአለው ልምድ ተጠቃሚው በአብዛኛው መርፌውን የሚመርጥ የነበረ ቢሆንም አሁን ግንቋሚ የእርግዝና መከላከያ ዘዴው ከውሳኔ በደረሱ ሰዎች ዘንድ በስፋት እየተለመደ እና በስራ ላይ እየዋለ ያለ ነው፡፡ ይህ ያልተፈለገ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ሁለቱ ጥንዶች ተስማምተው ወይንም በግልም ቢሆን በእርግጠኝነት በቂ ልጅ ስለአለኝ ወደፊት ልጅ መውለድ አልፈልግም ከሚል ውሳኔ ላይ እስከደረሱ ድረስ ደስተኛ የሆነ ሕይወትን ለመምራት የሚያስችል የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ነው፡፡
ጥ/ ቋሚ የእርግዝና መከላከያ ጉዳት አለውን?
 መ/ በሕክምናው ዘዴ የሚደርስ ምንም አይነት ጉዳት የለም፡፡ ወንድም ሆነ ሴት የቋሚ የእርግዝና መከላከያ እንዲወስዱ በሚወስኑበት ጊዜ ግን መጠንቀቅ ያለባቸው ነገር አለ፡፡
* በጊዜያዊ የኑሮ ሁኔታዎች ተገፋፍቶ፣
* በትዳር ጉዋደኛ አሳማኝነት ወይንም ግፊት ብቻ ተመርቶ፣
* ስሜትን ወይንም የእራስን ፍላጎት በደንብ ሳያዳምጡ፣
* ከሚመለከተው ቅርብ ከሆነው የትዳር ጉዋደኛ ጋር በትክክል ተወያይተው ሳይወስኑ፣
* በአጠቃላይም ሁኔታዎችን በትክክል ሳያመዛዝኑ ...ወዘተ
በዚህ መልክ እርምጃ በአካልዎ ላይ ከወሰዱ በእርግጥ ውጤቱ የሚጸጽት ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን በሁኔታው አምነው እርምጃ ከወሰዱ ሕክምናው ቀላል እና ከማንኛውም አይነት የኑሮ ሁኔታ ወይንም ከፍቅር ግንኙነት የማያግድ መሆኑን ባለሙያዎችም ሆኑ ተጠቃሚዎች የሚመሰክሩት ነው፡፡ ቋሚና የረዥም ጊዜ የእርግዝና መከላከያዎች አስተማማኝ እና ለተጠ ቃሚዎች ተስማሚ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ይህንን ተረድቶ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ  እንዲጠ ቀምበት ይመከራል፡፡

Published in ላንተና ላንቺ

*    ጋዛን መልሶ ለመገንባት 6 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል
*    እስራኤል ለጦርነቱ 2. 3 ቢሊዮን ዶላር አውጥታለች

ለሰባት ሳምንታት ያህል ከወደ እስራኤል ቀን ከሌት ሲሰነዘርባት በቆየው አሰቃቂ ድብደባ አሳር መከራዋን ስታይ የቆየችው የፍልስጤሟ ጋዛ፣ ከቀናት በፊት በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን እፎይ ብትልም፣ ድብደባው ያደረሰባት ጥፋት ግን እጅጉን የከፋና በቀላሉ የሚሽር አይደለም፡
በሁለቱ ሃይሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ለ70 እስራኤላውያን ሞት ምክንያት መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ ግጭቱ እጅግ የከፋ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ጥፋት ያስከተለው ግን፣ በፍልስቴም ላይ መሆኑን የኣለማችን መገናኛ ብዙሃን እየመሰከሩ ይገኛሉ፡፡
ግጭቱ ለህልፈተ ህይወት ከዳረጋቸው 2ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን መካከል አብዛኞቹ ጨቅላ ህጻናት ሰለመሆናቸው የዘገበው ሲኤንኤን፣ ለሳምንታት ስትደበደብ የቆየችው ጋዛ እንዳታገግም ሆና መፈራረሷንና የደረሰባት ኢኮኖሚያዊ ቀውስም እጅግ የከፋ እንደሆነ ገልጧል፡፡
በእስራኤል ጥቃት የፈራረሰችዋን ጋዛ መልሶ ለመገንባት ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚጠይቅ የጠቆመው ሲኤንኤን፣ መልሶ ግንባታውን በተገቢው መንገድ ለማከናወን እስከ 6 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የገንዘብ  እንደሚያስፈልግ ገልጧል፡፡የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና አጋሮቹ በጋዛ ለሚከናወኑ የሰብዓዊ መልሶ ማቋቋም ስራዎች ተጨማሪ 367 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግና፣ ከዚህ ገንዘብ ውስጥም ከግማሽ በላይ የሚሆነው የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ከ500ሺህ በላይ የጋዛ ነዋሪዎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ፤ የተቀረው ገንዘብም ለቤቶች ግንባታ፣ ለውሃና ንጽህናና ለትምህርት ተቋማት ግንባታ እንደሚውል ገልጠዋል፡፡
ኦክስፋም በበኩሉ በጋዛ ነዋሪዎች ላይ የደረሰው የመሰረተ ልማት አውታሮች ውድመት፣ በአለማችን ባለፉት 20 አመታት ከተከሰቱ መሰል ውድመቶች ሁሉ ባደረሰው ቀውስ ከፍተኛነት ወደር እንደማይገኝለት ገልጧል፡፡ ከ15 በላይ ሆስፒታሎች እና በጋዛ ብቸኛው የነበረው የሃይል ማመንጫ፣ ከእስራኤል በደረሰባቸው የድብደባ ጥቃት ሙሉ ለሙሉ መፈራረሳቸውንም ተናግሯል፡፡
በጋዛ እስካለፈው ነሃሴ 3 ቀን ድረስ ከ10    ሺህ 600 በላይ መኖሪያ ቤቶች መውደማቸውን የጠቆመው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም፣ የፈራረሱትን ቤቶች መልሶ የመገንባቱ ስራ እጅግ ፈታኝ እንደሚሆንና ምናልባትም አራት አመታትን ያህል ጊዜ ሊፈጅ እንደሚችል አስታውቋል፡፡
የእስራኤል የታክስ ባለስልጣን በበኩሉ፣ ከሃማስ በተሰነዘሩ ጥቃቶች የወደሙ የአገሪቱ ቤቶችን ቁጥር በተመለከተ ተጨባጭ መረጃ ባይኖርም፣ የመሰረተ ልማት አውታሮችን መልሶ ለመገንባት ግን 11 ሚሊዮን ዶላር ያህል ወጪ እንደሚጠይቅ አስታውቋል፡፡
የእስራኤል መንግስት የንብረት ውድመት ለደረሰባቸው ዜጎቹ ማካካሻ ገንዘብ እየሰጠ እንደሚገኝ የጠቆመው የሲኤንኤን ዘገባ፣ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት አውታሮች ውድመት በደረሰባት የሰሜን እስራኤሏ ከተማ የአሽዶድ ነዋሪዎችን ጨምሮ፣ 3ሺህ 700 ያህል የአገሪቱ ዜጎች ለመንግስት የማካካሻ ገንዘብ ጥያቄ ማመልከቻ ማቅረባቸውንና ከግማሽ በላይ የሚሆኑትም ለመኖሪያ ቤት ውድመት ያመለከቱ መሆናቸውን ገልጧል፡፡
ግጭቱ በእስራኤል የቱሪዝም ገቢ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠሩን፣ ምርታማነት ላይ ቅናሽ እንዲፈጠር ማድረጉንና ይህም የሆነው በርካታ የአገሪቱ ሰራተኞች የሮኬት ጥቃትን በመፍራት ስራ አቋርጠው በመኖሪያ ቤቶቻቸው በመደበቃቸው እንደሆነም አስረድቷል፡፡
እስራኤል ለሰባት ሳምንታት ያህል በጋዛ ላይ በሰነዘረችው ጥቃት ያወጣችውን አጠቃላይ ወታደራዊ ወጪ በተመለከተ ይፋዊ መረጃ ባትሰጥም፣ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ግን ወጪው እስከ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል እያሉ ነው፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

       በሳምንቱ መግቢያ ላይ በሮም ከተማ በሚገኘው ስታድዮ ኦሎምፒኮ በተዘጋጀው የዓለም ሃይማኖቶች ሁሉን አቀፍ የሰላም ግጥሚያ ላይ የዋልያዎቹ የቀድሞ ዋና አምበል ደጉ ደበበ ተሳተፈ፡፡ የእግር ኳስ ግጥሚያውን በክብር እንግድነት የታደሙት የቫቲካኑ ጳጳስ ፍራንሲስ ሲሆኑ፤ የሰው ልጆች በጭራሽ ሰይፍ የማይማዘዙበት ዘመን እንዲመጣ ሃይማኖት እና ስፖርት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በዓለም እግር ኳስ የታዩ ከ50 በላይ የአሁን ዘመንና የቀድሞ እግር ኳስ ተጨዋቾች በሰላም ግጥሚያው ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ለሁለቱ ቡድኖች ተሰላፊዎችን የመረጡት አዲሱ የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጌራርዶ ታታ ማርቲኖ እና የአርሰናሉ አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር ናቸው፡፡ በሁለቱ ቡድን የተመረጡ ተጨዋቾች በግጥሚያው የሁለት ግብረሰናይ ተቋማትን የሚወክሉ ማልያዎችን ለብሰው ተሳትፈዋል፡፡ በሃቪዬር ዛኔቲ አምበልነት የሚመራው ፑፒስ እና  በጂያንሉጂ ቡፎን የሚመራው ስኮላስ ናቸው፡፡
በጨዋታው ተሳታፊ ከሆኑት የጊዜያችን ምርጥ ተጨዋቾች መካከል ሊዮኔል ሜሲ፤ ኤቶና ፒርሎ እንዲሁም ከአንጋፋዎች ዲያጐ ማራዶና፣ ዴልፒዬሮና ሮበርቶ ባጂዮ ይገኙበታል፡፡
 የዓለም ህዝቦችን አንድነት ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንደሚኖርበት የታመነበት የሰላም ግጥሚያው በመላው ዓለም ሰላምን ለማስፋፋት ቅስቀሳ የተደረገበት ሲሆን በከፋ አደጋ ላይ ለሚገኙ የዓለም ህፃናት ድጋፍ የሚሆን ገቢም ተሰባስቦበታል፡፡  የሰላም ግጥሚያውን ስፖንሰር ካደረጉት መካከል ዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ፊፋ፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ፋኦ፤ የመኪና አምራቹ ኩባንያ ፊያት እና ሌሎች ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ይጠቀሳሉ፡ በመላው ዓለም በአምስት አህጉራት በቴሌቭዥን የቀጥታ ስርጭት የነበረው ዝግጅቱ በጣሊያን፤ በኦስትርያ፤ በፈረንሳይ እና በጀርመን ልዩ  ትኩረት እንዳገኘም ታውቋል፡፡
በዓለም ሰላም እንዲሰፍን ለመቀስቀስ የተዘጋጀውን የእግር ኳስ ልዩ  ግጥሚያ በማስተባበር በቦነስ አይረስ የሚገኘውን ፑፒ ፋውንዴሽን መስራች የቀድሞው አርጀንቲናዊ ተጨዋች ሃቪዬር ዛኔቲ ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡
  ሃቪዬር ዛኔቲ  በአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን አምበልነት ያገለገለ፤ በሚላን ከተማው ክለብ ኢንተር ሚላን ለ19 ዓመታት የተጫወተ እና አሁን የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኖ እየሰራ ነው፡፡

Page 12 of 14