Monday, 16 September 2013 07:49

ኮራጁ ማርክስ!

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር በአዕምሮዬ እየተመላለሰ የሚበጠብጠኝ ነገር ቢኖር የማርክስ መንፈስ ነው፡፡ ከ60ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ እስከዛሬ ድረስ በሀገራችን ፖለቲካ ውሰጥ ወሳኝ እና ገናና ሆኖ የዘለቀ ፖለቲካዊ አስተምህሮ እና ርዕዮተ ዓለም ነው ማርክሳዊነት፡፡
በልጅነት የማስታውሰው ደርግ እንዲሁም ነፍስ ካወቅሁ የመጣውና እስከዛሬም ያለው ኢህአዴግ እንደ ኮሶ አንጀታቸውን የተጣባው የአመራር መርህ ማርክሳዊነት ነው፡፡ በእኔ ግምት በዚህ ዓለም ላይ ከኢየሱስ ክርስቶስ ቀጥሎ ስሙ በሰዎች ዘንድ ተደጋግሞ የተነሳ ቢኖር ካርል ማርክስ ይመስለኛል። ከፍተኛ የሆነ የህዝብ መነቃቃትን በመፍጠር፤ የፖለቲካ ነውጦችን በማውጠንጠን፤ የተበዳይነት ስሜትን በማጦዝ ሰፊውን የአለም ክፍል ያዳረሰ ተጽእኖ ፈጣሪ ነበር፤ ካርል ማርክስ፡፡ ከዘመኑ በፊት በነበሩ አሳቢዎችና ፈላስፋዎች፤ እንዲሁም በራሱ ዘመንም በነበሩ አሳቢዎች እና ፈላስፋዎች ከፍተኛ ተጽእኖ የተደረገበትና ተጽእኖ ማድረግም የቻለ ሰው ነው፡፡
ጊዜያዊ ወታደራዊ ደርጉ ይመራበት የነበረው አብዮታዊት ኢትዮጵያና አሁን እያበበ ነው የምንባለው አብዮታዊ ዲሞክራሲ አፍአዊ ካልሆነ በስተቀር ብዙም ለውጥ ያላቸው አይመስለኝም፡፡
ያኛው ወጣቶችን በጉልበት እያፈሰ ያዘምታል፣ አባልም ያደርጋል፡፡ ይሄኛው ደግሞ በድህነትና ውጥረት በመፍጠር አማራጮችን እያመነመነ ወጣቱን ወደ እራሱ ያግዛል፡፡ ያኛው ስለ ሀገር አንድነትና ወንበዴን ስለ መደምሰስ ሲያወሩለት ቃታ ከመሳብ ጣቶቹን ይሰበስባል፡፡ ይሄኛው ደግሞ ስለብሔሮች እኩልነትና አሸባሪዎችን ስለመዋጋት ሲዘምሩለት የገንዘብ ካዝናውን ይከፍታል፡፡ ሁለቱም የኔ መንገድ የጽድቅ ናት፤ ሌላው መንገድ ግን ፍጻሜው ሲዖል ነው የሚል ጽኑ እምነት አላቸው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሁለቱም መንግስታት በአባታቸው ማርክስ በመሆናቸው ነው፡፡
ካርል ፖፐር የተባለው የሳይንስ ፈላስፋ የ20ኛው ክፍለ ዘመን የሳይንስ ምርምር ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ በማሳደር ይታወቃል፡፡ ሳይንስን እና አስመሳይ ሳይንስን ለመመርመር በሰራው መጽሐፉ The logic of Scientific Discoveries ውስጥ የካርል ማርክስን ሃልዮት እልም ያለ አስመሳይ ሳይንስ ነው ይለናል፡፡ ምክንያቱም ትችትንና ሌሎች አማራጮችን ከመቀጠልና ከመመርመር ይልቅ ማውገዝና ማስወገድን ይመርጣልና ነው፡፡ በፓፐር ትንታኔ አንድ ሃልዮት የሳይንስነት ማዕረግ የሚጐናፀፈው እንዴት ሊሻሻል እንደሚችል ራሱን እየተቸ አማራጮችን ያሳየ እንደሆነ ነው፡፡ ያለዚያ አስመሳይ ሳይንስ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከጥንቆላ የማይሻል አይነት ማለት ነው፡፡ ማርክሳዊያን ርዕዮት ዓለማቸው ሲተችባቸው በምክንያት ከመወያየት ይልቅ አስቀድመው አፍቃሬ ቡርዥዋ የሚል ስያሜ ይሰጡና አፈሙዛቸውን ያመቻቻሉ፡፡ ልክ በኛ ዘመን “የድሮ ስርአት ናፋቂዎች” እንደሚባለው ማለት ነው፡፡
ካርል ማርክስ የተለያዩ ሰዎች፣ በተለያየ ዘመንና አውድ ውስጥ ሆነው የጻፏቸውን ቅቡልና ወርቃማ ሃሳቦችን ለቃቅሞ ልክ እንደራሱ ወጥ ሥራ አስመስሎ ማቅረብ ችሏል፡፡ በጣም ምርጥ ኮራጅ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ሃሳቦችን መልክ መልክ አላሲያዛቸውም ብዬ ለመሞገት ሳይሆን በዚህ ጽሑፌ ውስጥ የማቀርባቸው ማስረጃዎች ካርል ማርክስን የምንረዳበት ዋናዎቹ የማርክሲስት ርዕዮት ዓለም ፍሬ ጉዳዮች ማርክስ አንጡራ እሳቤ የተገኙ አለመሆናቸውን ለመጠቆም ብቻ ነው፡፡
ኩረጃ አንድ - surplus value (የተትረፈረፈ የሰው ጉልበት):- አዳም ስሚዝ እና ዴቪድ ሪካርዶ የተባሉ በእንግሊዝና በስኮትላንድ ታዋቂ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ናቸው የሃሳቡ አመንጭዎች። እነዚህ ምሁራን ከሚታወቁባቸው ሃሳቦች መካከል የጉልበት ሃይል እሴት (labor value) አንዱ ነው፡፡ በምርት አጠቃላይ ወጪ ውስጥ የሰው ጉልበት ምን ያህሉን ገንዘብ እንደሚፈጀው ለማስላት የሚረዳ ዘዴ የቀመሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ከነዚህ ሰዎች ሃሳብ በመነሳት ማርክስ “አላግባብ የተትረፈረፈ የሰራተኛ ጉልበት ቡርዡዋው እያግበሰበሰ ነው” የሚል ሃሳብ ይዞ ብቅ አለ፡፡ ሠራተኛው ለቀን ከሚከፈለው በላይ ጉልበቱ በቡርዡዋ እየተበዘበዘ፣ ቡርዡዋው አላግባብ ትርፍ ያግበሰብሳል ይለናል፡፡ ቡርዡዋው ለወዛደሩ በቀን የሚከፍለውን ገንዘብ የሚያገኘው በወዛደሩ የጥቂት ሰዓታት ምርት ነው፤ ቀሪው የወዛደሩ ድካም ለቡርዡዋው የተትረፈረፈ ትርፍ እንዲያጋብስ የሚያስችለው ነው ብሎ ያምናል ካርል፤ ማርክስ። ስለዚህም በቀን ውስጥ የሚከፈለውን ያህል ብቻ ማምረት ለወዛደሩ ፍትሃዊ አሰራር ይሆናል፡፡
ኩረጃ ሁለት፡- utopian community:- በፈረንሳዊው ቻርልስ ፊዮረር ፍልስፍና መሠረት፤ የሰው ልጅ ሁሉ እኩል የሆነባት፣ የሃብት ልዩነት የሌለባት፤ ማህበራዊ መደብ አልባ የሆነች አለም ማምጣት ይቻላል ብዬ ያስባል፡፡ ይህ በፈረንሳዮች አብዮት ዘመን ሲቀነቀን የነበረ ሃሳብ፣ ለማርክሳዊ መንግስት ሰማያት ግንባታ ታላቅ መሰረት ሆኖታል። እንደ ማርክስ አስተምህሮ ከሆነ ወዛደሮች ቡርዡዋውን ገልብጠው የሚፈጥሩቱ የወዛደሮች አምባገነንነት የተከማቸ የግል ሃብትን በማጥፋት፣ ቀስ በቀስ ወደ መደብ አልባ የእኩልነት ማህበረሰብ ይለወጣሉ ብሎ ያምናል፡፡ እናም አምሳለ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም የመሰለች ሃገር ገንብተው ሰዎች በእኩልነት ያለ ጭቆና ይኖራሉ፡፡
ኩረጃ ሦስት፡- “ከእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለእያንዳንዱ እንደ ፍላጎቱ” የተባለውን የማርክስን ዝነኛ ጥቅስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሃሳቡን ያፈለቀውና የተነተነው ሉዊስ ብላክ የተባለ ጸሃፊ ነው፡፡ ሉዊስ ብላክ ማህበራዊ መርሆዎችን ሲተነትን ገቢን እና የሥራ ክብደት /መጠን/ እንዴት መሰራጨት እንዳለባቸው የጠቆመበት ጥቅስ ነበር፡፡ በካርል ማርክስ ስሌት መሰረት፣ በአንድ ፋብሪካ ውስጥ የሚሰሩ መሃንዲስና ወዛደሩ ቢኖሩ፣ ገቢያቸውን የሚወስነው ፍላጎታቸው ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህም መሃንዲሱ ሁለት ቤተሰብ ቢኖረውና የወዛደሩ ቤተሰብ ቁጥር ደግሞ ስድስት ቢሆን የወዛደሩ ገቢ ከመሃንዲሱ ገቢ ሦስት እጥፍ ሊበልጥ ነው ማለት ነው፡፡ ይሰውረን! ነው መቸም፡፡
ኩረጃ አራት፡- (abolishing private property) የግል ንብረት ክልከላን በተመለከተ የፈረንሳይ ሶሻሊስት አንቀሳቃሽ ከነበሩት መካከል ዥን ጃኩስ ሩሶ እና ዮሴፍ ፑርዶኧ፤ የምጣኔ ሃብት ክምችት ከካፒታሊስቶች ወደ ሠራተኛው መዘዋወር እንዳለበትና የሃይል ዝውውሩን የተሳካ ለማድረግ ደግሞ የግል ንብረት ማፍራት ላይ ቁጥጥር እንዲኖር ይጠይቃሉ፡፡ ሰውን ክፉ ያደረገው ነገር የግል ንብረት የሚባለው ጉዳይ ነው ብለው ያስባሉ፤ እነዚህ ፈላስፎች፡፡ የግል ንብረት ለማፍራት በሚደረግ ግርግር ውስጥ ነው የሰዎች ጭቆና ስር የሚሰደው የሚል እምነት ይከተላሉ፡፡ ለካርል ማርክስ ታዲያ እንዲህ አይነት አስተምህሮ የተመቻቸና ከእራሱ ሃልዮት ጋር በቀላሉ የሚዋሃድ ሆኖለታል፡፡ በእኛም ሃገር አምስት መቶ ሺህ ብር የሃብት ጣሪያ ነበር። ዛሬ ዛሬ የአንዳንድ ልማታዊ ድርጅቶች ሥራ አስኪያጆች ደሞዝ ሆኖ ሊያርፈው፡፡
ኩረጃ አምስት፡- (dialectical materialism) የጀርመኑ ፈላስፋ ሔግል ታሪክ ዲያሌክቲካል ነው ይላል፡፡ ዲያሌክቲካል የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ግጭት የሞላበት ተቃርኖ የሚያዋክበው ሁኔታን የሚገልጽ ነው በተለምዶ፡፡ አንድ የሆነ ቀዳማዊ ሃሳብ/ታሪክ ቢኖር ቀጣዩ የሚፈጸመው ነገር የቀዳማዊው ተቃራኒ የሆነ ሃሳብ/ታሪክ ነው ብሎ እንደማሰብ ነው (በግርድፉ)፡፡ የቁስ አካል ፍልስፍናን በመውሰድ ማህበራዊ ህይወትን ተነተነበት፡፡ በማህበራዊ ህይወታችን ስናመጣው የቡርዡዋ ስርአትን ለመገርሰስ መገዳደል ትክክለኛው መንገድ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ማመጽ እና መደምሰስ ጤናማና ዋነኞቹ መለወጫ መንገዶች ይሆናሉ፡፡
ኩረጃ ስድስት፡- ሰው የአካባቢው ውጤት ነው፤ አስተሳሰቡ በአካባቢው ካለው ቁስ አካል በሚኖረው መስተጋብር ይወሰናል/ይቃኛል/፡፡ ሉድዊንግ ፊዮርባኧ የተባለው የጀርመን ፈላስፋ፤ የማህበራዊና ፖለቲካዊ እሳቤዎችን መሠረት ሲተነትን፣ በቁስ አካላት ላይ ያለን ፍላጎት ቁልፍ መለኪያ መሆኑን ያስረግጣል፡፡ ሃሳብ የሚባል ነገር የለም ይለናል ካርል ማርክስ፤ ከፊዮርባኧ በተኮረጀ ሃሳቡ፡፡ ያለ እውነታ ቢኖር ቁስ አካል ነው፡፡ የቁሳቁስ እንጂ የሃሳብ አለም የለም፡፡ አካባቢያችን በሙሉ በቁስ አካላት የተሞላ ስለሆነ እኛም የቁስ አካላት ውጤን ነን እንጂ መንፈስ ምናምን… ሃሳብ የሚባል ጉዳይ የለም፤ አይኖርምም ነው የሚለን ካርል ማርክስ፡፡
ሉድዊንግ ፊዮርባ “አምላክ የሰዎች ፈጠራ እንጂ አምላክ የሚባል ነገር የለም፡፡ ሰዎች ለፈጣሪ የሰጡት ባህሪያት የራሳቸውን አምሳያ ነው፡፡” ካርል ማርክስ ይህንን ሃሳብ በመውሰድ ሰዎች የቁስ አለም ውስጥ ስለሚኖሩ ሃሳቦቻቸውም የቁስ አካላት ውጤቶች እንጂ፤ ሰው በሃሳቡ ብቻ ያለ ቁስ አካላት አጋዥነት ያመጣው አንዳች ነገር የለም ይላል፡፡ ይሄን የፊዮርባኧ ፍልስፍና በቀጥታ በመኮረጅ ካርል ማርክስ፤ ሰዎች በራሳቸው ዛቢያ ላይ መሽከርከር ሲሳናቸው የሚጠለሉበት አምላክ የሚባል ነገር ፈጠሩ ይለናል፡፡
“ሃይማኖት የድሆች መጽናኛ ነው፡፡ ሃይማኖት ማለት የሰዎች ማደንዘዣ ነው፤ መንፈስ አልባ ለሆነው ማህበረሰብ መንፈስ ነው፤ ልብ አልባ ለሆነው ዓለም ልብ ነው” ሲል ያብራራል፡፡ በታሪክ ሂደት እንዳየነው ግን እራሱ ካርል ማርክስ ነው ለወዛደሮች መጽናኛ የሚሆን ርዕዮት አለም የፈለሰፈ። ማርክሳዊነት ለብዙ ስራ ፈቶችም ማደንዘዣ ሆኖ አገልግሏል፤ እያገለገለም ነው፡፡ ማርክስ ሃይማኖትን አጠፋለሁ በሚለው ርእዮት አለሙ፤ ሌላ አዲስ ማህበረሰባዊነት የተባለ የጭቁኖች/የወዛደሮች ሃይማኖት የፈጠረ ሲሆን ይሄው እስከዛሬም ካህናተ ማርክስ ካልተጠመቃችሁ እያሉ ይበጠብጡናል፡፡
አዲሱ ዓመት፤ በማርክሳዊነት የተኮረጀ ርእዮት አለም ውስጥ ሆነው መንፈሳቸውን አውከው የኛንም መንፈስ ከሚያመሳቅሉ የአልባኒያ ደብተራዎች በኢትዮጵያ መንፈስ ሰውሮን፤ ፍቅር አንድነት፣ መቻቻል፣ መተሳሰብና ሰው የመሆን ማእረግ እንድንጎናጸፍ እመኛለሁ፡፡ እኛን እኛን የሚሸት ፍልስፍና እና መንግስታዊ ስርአት የኢትዮጵያ አምላክ ያድለን! “ፊውዳሎች ይውደሙ!” ሲሉ የነበሩትን “ማርክሲስቶች ይውደሙ!” አንላቸውም። ይልቁንም “ኢትዮጵያዊያን እንደአደይ አበባ ይለምልሙ!!!”

በጥንት ጊዜ አንድ ሰው ወደ ጐረቤቱ ማሳዎች ተደብቆ በመዝለቅ እህል አጭዶ ሊሰርቅና ሊወስድ ወሰነ፡፡ “ከሦስቱም ማሳዎች ትንሽ…ትንሽ አጭጄ ብወስድ አይታወቅም፡፡” በማለት ራሱን አሳመነ፡፡ “ለእኔ ግን ከሁሉም ማሳዎች የምሰበስበው ብዙ ይሆንልኛል፤” በማለት አሰበ፡፡
ስለዚህ ሰውየው ቀኑ ሲጨላልምና ደመናው ሲከብድ ያሰበውን ስርቆት ተግባራዊ ለማድረግ ተነሳ፡፡ ደመናው ጨረቃዋን ሲሸፍናትና አካባቢው ሲልም ሴት ልጁን ይዞ፣ ከቤቱ ወጣና ተሹለክልኮ ከማሳዎቹ ዘንድ ደረሰ፡፡
“ትሰሚያለሽ…ልጄ…የሆነ ሰው ካየኝ ንገሪኝ፡፡ እዚህ ጋ በትጋት ቁሚና ጠብቂ” በማለት ትንሿን ልጁን አዘዛትና እርሱ ወደ አንዱ ማሳ እየተንሿከከ ገባ፡፡
ሰውየው በመጀመሪያው ማሳ ገብቶ እያጨደ ስርቆቱን ተያያዘው፡፡ ብዙም ሳይቆይ ልጅቷ “አባቴ ኧረ እየታየህ ነው!” አለችው፡፡
ቆም ብሎ ዙሪያውን ሲመለከት ምንም ነገር የለም፡፡ የቻለውን ያህል አጭዶና ተሸክሞ ወደ ሁለኛው ማሳ ገባና ያጭድ ጀመር፡፡
“አባቴ አሁን ታይተሃል” በማለት ልጁ ተናገረች፡፡ ማጨዱን አቁሞ፣ አሁንም አካባቢውን ማተረ። ምንም ነገር ስላልታየው አጭዶ የሠረቀውን ሰበሰበና ወደ ሦስተኛው ማሳ ገባ፡፡ እዚያም ማጨድ እንደጀመረ፣ “አባቴ ኧረ እያዩህ ነው ታይተሃል!” እያለች ልጅቷ ጮኸች፡፡
ሌባው ሰውዬ አካባቢውን ቢቃኝም የሚታየው ነገር ስለሌለ ስርቆቱን ጨርሶ የሰበሰበውን አስሮ ተሸከመ፡፡ ወደ ልጅቷ ተጠግቶ “ማንም ሰው ሳያየኝ “አዩህ” እያልሽ ለምን ታስጨንቂኛለሽ?!” በማለት እየተናደደ ተቆጣት፡፡
“አባቴ፤ አንተ ግራና ቀኝ፣ ፊትና ኋላ እያየህ፣ ማንም የለም ትላለህ፡፡ የታየኸው ወይም ያየህ ከላይ ነበር፡፡ አንተ እኮ ወደ ሰማይ ቀና አላልክም” አለችው፡፡
* * *
አንታይም ብለን ያደረግነው ሁሉ የማታ ማታ የሚያየውን እጅ ላይ እንደሚጥለን አንርሳ፡፡ በዚያኛው ዘን ያደረግነው ወደዚህኛው ዘመን፣ በዚህኛው ዘመን ተደብቀን ሳይነቃብን ያለፍነው፤ በመጪው ዘመን ሊከሰትብንና ከላይ የሚያይ እንደሚያየን ልብ እንበል፡፡ የምናደርገው ክፉ ሥራ ሁሉ እንደጥቁር ጥላ ይከተለናል፡፡ ህሊናችንን ያመናል፡፡ እንቅልፍ እንደነሳን ይኖራል፡፡ “ሞት ላይቀር ማንቋረር” እንደሚባለው ነው፡፡ ከዚህም ከዚያም በዘረፍነው ገንዘብ ፎቅ ስንገነባ፣ ውድ ውድ መኪና ስንገነባ፣ ሰፋፊ ቢዝነስ ስንከፍት ወዘተ፤ ሌሎች ኑሯቸው እየቆረቆዘ፣ ሀገሪቱ ከነግ ሠርክ ቁልቁል እየወረደች መሄዷን የሚያይ ዐይን አለ፡፡
ከላይ ጂ ቤኔት “የማታየው ያይሃል” ብሎ የፃፈውና ደራሲ ገ/ክርስቶስ “ደወል” በሚለው መጽሐፉ ተርጉሞ ያስቀመጠው ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው፡፡ እንደ ሌባው አባት ሴት ልጅ “ኧረ እየታየህ ነው” የሚል የማስጠንቀቂያ ደወል የሚያንቃጭል አመራር ያስፈልገናል፡፡
ጤናችን በታወከበት፣ ትምህርታችን እየተዳቀቀ በሄደበት፣ ኪነጥበባችን ከእጅ ወደ አፍ በሆነበት፣ መቻቻላችን አጠያያቂ በሆነበት፣ ዲሞክራሲያችን አገም ጠቀም እየሆነ በሄደበት፣ መልካም አስተዳደራችን የብልጭ ድርግም ባህሪ በሚያሳይበት፣ ሰው ከዕለት ወደዕለት ራስ ወዳድነቱ ከሀገሩ ጥቅም እያየለ በተጓዘበት፣ ግብረ ገብነት የክፉ ቀን እርግማን በመሰለበት፤ የችግሮቻችን መፍትሔዎች “ጡቷን ስትሸፍን ታፋዋ ታየ፤ ታፋዋን ስትሸፍን ጡቷ ታየ” እየሆኑ ባሉበት፤ ሁኔታ ውስጥ የጉዳያችንን ጥልቀት አስተውለን የበለጠ ጥንቃቄ፣ የበለጠ ትጋት፣ የበለጠ ትግል እናደርግ ዘንድ የማስጠንቀቂያ ደወል ያሻናል፡፡ ይህን እንደበለጠ የጥረት መቀስቀሻ እንጂ እንደመርዶ ወይም እንደሟርት አንየው፡፡ እልህ ኖሮን እንነሳሳ!!
በእርግጥ ፒተር ዳያማንዲስ እንደሚለን፤ “የሚደማ ጉዳይ መሪ ዜና ይሆናል” የሚለው ጥንት ስለጋዜጦች የተነገረ ዕውነት ቢሆንም፤ ዛሬም ይሰራል፡፡
(If it bleeds, it leads እንዲሉ ፈረንጆቹ፡፡) “ዋሽንግተን ፖስት” ጋዜጣን አንሱና አሉታዊና አዎንታዊ፣ ደግና ክፉ፣ ዜናዎችን አወዳድሩ፡፡
ከዘጠና በመቶ በላይ ሐተታዎቹ ክፉ ወሬን የሚተርኩ ናቸው፡፡ በአጭሩ ደግ ደጉ ዜና ትኩረታችንን አይስብም፡፡ ምክንያቱም “አሚግዳላ” የተባለው የአንጐላችን ክፍል ሁሌም የሚያስፈራ’ንን ነገር ለመፈለግ ይገፋፋናል፡፡ ባጭሩ አንጐላችን አንዴ ክፉ ወሬን ፍለጋ ከተሰማራ፤ ክፉ ወሬ ያገኛል” ይኸው ፀሐፊ አጠንክሮና አበክሮ እንዲህ ይለናል፡፡ “የዛሬ ጊዜ አደጋዎች ከሞላ ጐደል የምናልባቴ ጉዳዮች ናቸው (Probabilistic)፡፡ ኢኮኖሚ ባፍንጫው ወይም ባፍጢሙ ሊደፋ ይችላል (nose-dive)፡፡ በማናቸውም ሰዓት የአሸባሪዎች ጥቃት ሊከሰት ይችላል፡፡ የሚገርመው ፍርሃትንና ቁጣን የሚቆጣጠረው የአንጐላችን ክፍል (አሚግደላ) በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት ላያውቅ ይችላል፡፡”
አዎንታዊ እንዳንሆን ሦስት ቅጣቶች አሉብን 1ኛ/ የአዕምሮአችን የማጣሪያ ነገረ-ሥራ ክፉ ክፉውን የሚመኝ ሆነ 2ኛ/ ሚዲያ ተነባቢ ለመሆን ክፉ ክፉውን ዜና መረጠ፡፡ 3ኛ/ ሳይንቲስቶችም የማንወጣበት ገደል ውስጥ ነን ማለታቸው ብቻ ሳይሆን ለመውጣት ፈቃደ ልቦናው የለንም ማለታቸው ነው፡፡
ዓለም፤ የሚያስፈራ አደጋ እያሸተተና የማያስተማምን መሆኑን፤ ፀሐፍት እየነገሩን ነው፡፡ ይህንን እንግዲህ ወደ ሀገራችን ሁኔታ መመንዘር ነው፡፡ እንደ ነጋዴ ስንጥቅ እያተረፍን “ባመጣሁበት ውሰደው” ባንልም፤ አደጋውን በሙስናው፣ በኢፍትሐዊነቱ፣ በአስተዳደር ጉድለቱ፣ በኢኮኖሚ ዝቅጠቱና በመቻቻል መመናመኑ ወዘተ ውስጥ አስተውሎ ሁሌ ንቁ ሆኖ ማየት ነው፡፡
ምዕራቦቹ የሚጠጣ ንፁህ ውሃና የሚተነፈስ ንፁህ አየር እየጠፋ ነው እያሉ ሥጋቱ ሊገላቸው ነው። እኛ ጥያቄው ከነመኖሩንም አናውቅም፡፡
እነሱ እየተቆጣጠሩትም ፍርሃቱ ሊገላቸው ደርሷል፡፡ እኛ እርምጃቸውንም ከጉዳይ አልጣፍነውም። እነሱ “ዓለም ወዴት እየሄደች ነው” ብለው ተጨናንቀው ሊሞቱ ነው፡፡ እኛ የዘረፍነውን ዘርፈን “እቺ አገር ወዴት እየሄደች ነው” እያልን በማላገጥ ላይ ነን! በዚህ ዓመት ምህረቱን ያምጣልን (If it bleeds it leads እንዳንል ይጠብቀን፡፡) ክፉ ወሬ ቀዳሚ ርዕሰ-ጉዳይ እንዳይሆን እንፀልይ፡፡
“በድህነቷ ላይ አገውኛ ጨመረችበት” የሚለው የትግሪኛ ተረት ያሳስባል፡፡ የሀገራችን አንዱ ችግር የጉዳዮች የአንድ ሰሞን ዘመቻ
መሆን ነው፡፡ ጨበጥነው፤ ተቆጣጠርነው ስንል፤ ተመልሶ እዛው ይዘፈቃል፡፡
ቢያንስ ለዘንድሮው ዓመት፤
“ጅግራ ያዝ፣ ሩጫ ከፈለክ ልቀቃት፤
ሥጋ ከፈለክ እረዳት” የሚለውን ተረት ልብ እንድንል ልብና ልቦና ይስጠን!!.

Published in ርዕሰ አንቀፅ

                   በአቃቂ ቃሊቲ፣ በቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ፣ ባለፈው ነሐሴ 23 ቀን በቀስተ ደመና፣ በመብረቅና በነጐድጓድ ታጅቦ ከሠማይ እንደወረደ የተነገረለት መስቀል፣ በጳጳሳት የተጐበኘ ሲሆን፣ ከሁለት ሳምንት በኋላ ለህዝብ እይታ እንደሚቀርብ ተገለፀ፡፡
መስቀሉን ከወደቀበት ለማንሳት የሞከረ ወጣት ተስፈንጥሮ በወደቀበት ለ4 ቀን ራሱን እንደሳተ የሚናገሩ የቤተክርስትያኑ አገልጋይ፣ ከምሽቱ 9 ሰዓት ከፍንዳታ ጋር አካባቢው በብርሃን ተሞልቶ ስናይ የእሳት ቃጠሎ መስሎን ነበር ብለዋል፡፡ እያንፀባረቀ በሃይለኛ ግለት ያቃጥል ነበር የተባለው መስቀል፤ በማህበረ ቅዱሳን መሪዎችና በጳጳሳት የተጐበኘ ሲሆን የኢየሱስን ስቅለት የሚያሳይ ወርቃማ ቅርጽ ያለው ነው፡፡
ወደ አቃቂ ከተማ ከሚያስገባው ዋና የአስፓልት መንገድ በስተግራ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ገላን ጉራ በሚባለው ስፍራ የዛሬ 5 አመት የተቋቋመው የገብርኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ ነሐሴ 23 ቀን የክርስቶስ ሰምራ በአለ ንግስ እየተከበረ እያለ ከሌሊቱ 9 ሰዓት የተከሰተው ግርግር ነው የዚህ ሁሉ መነሻ፡፡ ከባድ የፍንዳታ ድምጽ የሰሙ እና የቀስተ ደመና ቀለማትን የተላበሰ ብርሃን የተመለከቱ ነገሩን ከዝናባማው የአየሩ ሁኔታ ጋር በማያያዝ ብዙም ትኩረት አልሰጡትም ነበር የሚሉት የቤ/ክርስትያኑ መጋቢ፤ በነጎድጓድና በኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለማት የታጀበ መስቀል ከሠማይ ሲወርድ አይቻለሁ ብለዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ባሉት ቀናት መስቀሉን ለማየት ወደ ቤተክርስትያኗ የሚጐርፉ ምዕመናን በርክተዋል፡፡
ባለፈው ሃሙስ ከአቃቂ ከተማ በማለዳ ተነስተን ከ2 ሠአታት የእግር ጉዞ በኋላ ከቤተ ክርስቲያኑ ስንደርስ፣ በጥቂት ምዕመናን ተሣታፊነት የእለቱ ቅዳሴ እየተከናወነ ነበረ፡፡ ከቆይታ በኋላ ግቢው ከየአቅጣጫው የመስቀሉን ታሪክ ሠምተው በመጡ ምዕመናን ተሞላ፤ መስቀሉ ከሰማይ ሲወርድ አይቻለሁ የሚሉት መጋቢ ሃዲስ ፍስሃ፣ ስለ መስቀሉ አወራረድ ገለፃ ማድረግ የጀመሩት ከቅዳሴው በኋላ ነው፡፡
ግቢው ውስጥ ከቤተ ክርስቲያኑ ህንፃ አጠገብ መስቀሉ የወደቀበትን ስፍራ እያመለከቱ ይናገራሉ -ቦታው በቆርቆሮ ታጥሮ ድንኳን ተተክሎበታል። መስቀሉ አርፎበታል ከተባለው ስፍራ አፈር እየቆነጠረ የሚቀርብላቸው ምዕመናን አፈር እየተመለከቱ የመጋቢ ሃዲስን ገለፃ ያዳምጣሉ፡፡
ለቅድስት ክርስቶስ ሠምራ በአል ነሐሴ 23 ቀን የፀሎት ስርአት ከምሽቱ አምስት ሠአት አካባቢ እንደተጀመረ የሚያስታውሱት መጋቢ ሃዲስ፣ ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ አካባቢው በቀስተደመና ብርሃን ደምቆ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና ምዕመናን ለዚህ ልዩ ክስተት ብዙም ትኩረት አልሰጡትም፤ ከዝናባማው የአየር ፀባይ ጋር በማዛመድ አቅልለው ነው የተመለከቱት ብለዋል መጋቢ ሃዲስ፡፡ የቀስተ ደመናው ብርሃን አንዴ ሲደምቅ፣ አንዴ ሲደበዝዝ መቆየቱን መጋቢ ሃዲስ ጠቅሰው፣ ከሌሊቱ 9 ሠአት ንፋስ ለማግኘት በካህናት መውጫ በር በኩል ስወጣ ግን ደብዛዛ የነበረው ብርሃን የበለጠ ደምቆ፣ እንደቀን ብርሃን ወገግ ብሎ ታየኝ ብለዋል፡፡
“አሻቅቤ ስመለከት ሠማዩ በነጭ ደመና ተከቦ ተመለከትኩ፡፡ አፍታም አልቆምየ፤ በኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለማት የተጠቀለለ አንዳች ነገር በዝግታ ከሠማይ እየተገለባበጠ ሲወርድ አየሁ” ይላሉ መጋቢ ሃዲስ፡፡
ከቤተክርስቲያኑ ቤተልሄም አጠገብ ያለውን የአገር አቋራጭ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ ማማ እያመለከቱ፣ “ከሠማይ እየተጠቀለለ የሚወርደው ነገር ከማማው አካባቢ ሲደርስ ነጐድጓዳማ ድምፅ ማሠማት ጀመረ” የሚሉት መጋቢ ሀዲስ፤ “መሬት ላይ ሲያርፍ በከፍተኛ የፍንዳታ ድምፅ አካባቢውን የእሣት ንዳድ በመሰሉ ብርሃን ሞላው” ይላሉ፡፡ “ቤተልሄሙ ተቃጠለ እያልኩ ብጮህም ድምፄን የሰማ ሰው አልነበረም፤ ለደቂቃዎች ያህል ለሠዎች እንዳይሠማ ሆኖ ታፍኖ ነበር” የሚሉት መጋቢ ሀዲስ፤ “ድምፄ መሰማት ሲችል ግን ፣ ካህናቱ ጩኸቱን ሰምተው ተደናግጠው ወደ ውጭ መጡ” ብለዋል፡፡ አንዳች አደጋ ደርሶ እሳት ተቀጣጥሎ ሊሆን ይችላል በሚል ድንጋጤ ሁሉም እሣቱን ለማጥፋት እንደተሯሯጠ ጠቅሰው፣ ነገር ግን በአካባቢው ከብርሃን በቀር የእሣት ቃጠሎ ማግኘት አልተቻለም ብለዋል - መጋቢው፡፡
“አንድ የቤተክርስቲያናችን ወጣት አገልጋይ ወደ ደመቀው ብርሃን ተጠግቶ ለማየት ሞከረ፡፡ አንዳች ነገር ወደ ላይ አስፈጥንሮ መሬት ላይ ጣለው፡፡ ምዕመናን ተደናገጡ፡፡ የኤሌትሪክ መስመር ተበጥሶ ኮንታክት ፈጥሮ ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ነበር ያደረብን” ሲሉም ተርከዋል፡፡ “የወደቀው ወጣት ምላሱ ተጐልጉሎ በወደቀበት ራሱን ስቶ ተዘርግቷል” የሚሉት መጋቢ ፍሰሃ፤ ከወደቀበት በጥንቃቄ አንስተን ፀበልና ቅባ ቅዱስ ብናደርግበትም አልተሻለውም ብለዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ካህናቱ እንደምንም ወደ ብርሃኑ አካባቢ ተጠግተው የተመለከቱት፡፡ እናም በብርሃን የታጀበ መስቀል መሬት ላይ ወድቆ አዩ ብለዋል መጋቢው፡፡ ካህናቱና ምዕመናኑ በአግራሞት ሲመለከቱ ቢቆዩም የእሣቱ ወላፈን ይፋጃል ያሉት መጋቢ ፍሰሃ፤ በርቀት መጐናፀፊያ ተወርውሮበት እንዲለብስ እንደተደረገ ይገልፃሉ፡፡ የተቋረጠው ስርዓተ ማህሌት ከ10 ሰዓት በኋላ እንደቀጠለ የተናገሩት መጋቢ ፍሰሃ፣ በካህናቱ ትዕዛዝ ጠዋት 12፡30 ላይ መስቀል በወረደበት ቦታ ላይ ድንኳን ተተከለ፤ ብፁዐን አባቶችም በስልክ እንዲያውቁ ተደረገ ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በማግስቱ የአቡነ ተክለሃይማኖት ክብረ በል ስለነበረ ብዙዎቹ ጻጳሳት ወደ ደብረሊባኖስ፣ ቀሪዎቹም ወደየአድባራቱ ሄደው ስለነበረ መምጣት አልቻሉም ብለዋል - መጋቢው፡፡ ከበላይ አካላት በተነገረን መሠረት ለወረዳው ፖሊስ ካሳወቅን በኋላ፣ የፖሊስ ሃይል አካባቢውን ተቆጣጠረ” የሚሉት መጋቢ ሃዲስ፤ ቅዳሜ እለት የማህበረ ቅዱሳን አባላት መጥተው መመልከታቸውን ገልፀዋል፡፡ በዚያው እለት ከሰአት በኋላ ለመምጣት ቀጠሮ የሰጡ ጳጳሳት ግን ከአንድ ሰአት በላይ በረዶ የቀላቀለ ዝናብ በመጣሉና ጭቃው የማያስገባ በመሆኑ ከመንገድ ተመልሰዋል። በማግስቱ እሁድም አክራሪነትን በመቃወም ሰልፍ የሚካሄድበት ቀን በመሆኑ መምጣት አልቻሉም፡፡ ሰኞ እለት ነሐሴ 27 ቀን ግን በርካታ ጳጳሳት በቦታው ተገኝተው በበርካታ ምዕመናን ታጅቦ መስቀሉ ከወደቀበት መሬት ተነስቶ፣ ወደ መቅደሱ እንዲገባ መደረጉን መጋቢ ፍሰሃ ተናግረዋል፡፡ በደረሰበት አደጋ ራሱን ስቶ የቆየው ወጣት፤ በ4ኛው ቀን መንቃቱንና በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ መጋቢ ሃዲስ ጠቅሰዋል፡፡
ወጣቱ ሲጠየቅም፣ መስቀሉን ተመልክቶ ሊያነሳው እጁን ሲሰነዝር ከኋላው አንዳች ህፃን ልጅ የመሰለ ነገር ጐትቶ መሬት ላይ እንደጣለውና ከዚያ በኋላ የሆነውን እንደማያውቅ መግለፁን እኚሁ መጋቢ ተናግረዋል፡፡
መስቀሉ ከወደቀበት መሬት ተነስቶ ሲገባ ከፍተኛ ግለት እንደነበረውና የተሸከሙት አባት “እያቃጠለኝ ነው” ሲሉ እንደነበር መጋቢ ፍሰሃ ገልፀዋል፡፡ መስቀሉ የሰው ስራ እንዳይሆን የተጠራጠሩ ካህናት መኖራቸውን ያመኑት መጋቢ ፍሰሃ፣ መስቀሉ ከምን እንደመጣ የሚያውቀው ፈጣሪ ነው ብለዋል፡፡
አቶ እንግዳው የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ፣ መስቀሉ ከሠማይ ሲወርድ እንዳልተመለከቱ ጠቅሰው፤ በጳጳሣቱ ተነስቶ ወደ መቅደሡ ሲገባ ወርቃማ ብርሃን ነበረው ብለዋል፡፡ አንዳንድ የአካባቢው ሠዎችም ሌሊቱን ነጐድጓዳማ ድምፅ መስማታቸውንና በማግስቱም ይህን ክስተት በቤተክርስቲያኑ ከነበሩ ሰዎች ታሪኩ እንደተነገራቸው ገልፀዋል፡፡ ለአካባቢው ፀጥታ በማሰብ መስቀሉ በየእለቱ ለምዕመናን እንዳይታይ ከቤተክህነት ትዕዛዝ እንደተላለፈ ጠቅሰው፤ መስከረም 19ቀን 2006 ዓ.ም በቤተክርስቲያኑ ቅፅር ግቢ መስቀሉን በይፋ ለእይታ ለማብቃት ቀጠሮ መያዙን መጋቢ ሃዲስ ተናግረዋል፡፡

Published in ዜና

“ታዋቂ አርቲስቶች አንሳተፍም ማለታቸው አሳዛኝ ነው” ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
የመንግስት ሲኒማ ቤቶች ትያትሩን ለማሳየት ፈቃደኛ አልሆኑም
ሰማያዊ ፓርቲ ባለፈው እሁድ ያስመረቀውን “የነፃነት ፈለግ” የተሰኘ ቲያትር በቪሲዲ ለህዝብ ሊያቀርብ እንደሆነ የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ገለፁ፡፡
እሁድ እለት በጣሊያን የባህል ተቋም የተመረቀው ትያትሩ፤ በፕሮፌሽናል ካሜራ መቀረፁንና በቅርቡ ኤዲቲንጉ አልቆ በቪሲዲ ለህዝብ እንደሚደርስ የጠቆሙት ኢ/ር ይልቃል፤ ትያትሩን በመንግስት ሲኒማ ቤት ለማሳየት ሲኒማ ቤቶች ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በቪሲዲ ለማውጣት ተገደናል ብለዋል፡፡
የ70 ደቂቃ ርዝመት ያለው ትያትሩ በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካና ማህበራዊ ችግሮች ላይ የሚያተኩር መሆኑንና የፓርቲው አባል በሆነው ወጣት ዳዊት ፀጋዬ እንደተፃፈ የተናገሩት ኢ/ር ይልቃል፤ ታዋቂ አርቲስቶች በትያትሩ ላይ ለመሳተፍ ለሶስት ወራት ሲለማመዱ መቆየታቸውን ጠቁመው፤ በኋላ ግን መንግስትን በመፍራት ጥለው እንደወጡና በዚህም እርሳቸውና ሌሎች የፓርቲው አባላት እንዳዘኑ ገልፀዋል፡፡ “ታዋቂ አርቲስቶች ሙያቸውን በመጠቀምና ለእውነት በመቆም ህዝቡን ማገልገል አለባቸው” ያሉት ኢ/ር ይልቃል፤ ታዋቂ የትያትር አዘጋጅና አስተማሪ የሆነው ግለሰብ “ሀላፊነት አልወስድም” ብሎ ዝግጅቱን አቋርጦ ከአገር መውጣቱንም ገልፀዋል። “አዘጋጁ ሀላፊነት አልወስድም” ያለው በተለይ ግንቦት ላይ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረጋችንና ጉዳዩ መነጋገሪያ በመሆኑ ነው” ብለዋል፡፡
“ተዋንያኑም አዘጋጁን አምነን ነው ስራውን የጀመርነው፤ እርሱ ሀላፊነቱን ካልወሰደ እኛም አንፈልግም” በማለት ከሶስት ወር በኋላ ጥለው መበተናቸውንና እንደ አዲስ ሌሎች ወጣት ተዋንያንና አዘጋጅ ተፈልገው ልምምዱ መጀመሩን የገለፁት የፓርቲው ሊቀመንበር፤ በዚህ ምክንያት ቴያትሩን ለእይታ ለማብቃት ከስድስት ወር በላይ መፍጀቱን ገልፀዋል። ትያትሩ ትርፍን ማዕከል ባላደረገ መልኩ የተዋንያን እና የደራሲውን ወጪ ለመሸፈን በመጠነኛ ዋጋ ለህዝብ ይደርሳል ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ፓርቲዎች ለአጭር ጊዜ ገቢ ማስገኛ ስራዎችን የመስራትና ለገበያ የማቅረብ መብት እንዳላቸው አዋጁ እንደሚደነግግ ገልፀው፤ ቪሲዲውን በቅርቡ ለማከፋፈል ዝግጅት እየተጠናቀቀ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ትያትሩ በተመረቀ እለት ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያምን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ተገኝተው አድናቆታቸውን መግለፃቸውን የተናገሩት ኢ/ር ይልቃል፤ ሥራው በተቃዋሚ ፓርቲ ደረጃ የመጀመሪያና አስተማሪ መሆኑን ፕሮፌሰሩ መናገራቸውን አውስተዋል፡፡
ፓርቲው ትያትሩን በመንግስት ሲኒማ ቤት ለማሳየት ፈልጎ ይሁንታ በማጣቱ በጣሊያን የባህል ተቋም ካስመረቀ በኋላ ተቋሙ ለትያትሩ ደራሲ “አገባባችሁ ትክክል አይደለም፣አታላችሁናል፣ አዳራሹም ለፖለቲካ ስራ ውሏል” የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ መፃፉን የተናገሩት ኢ/ር ይልቃል፤ በዚህም ማዘናቸውን ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና

አንድነት ለዲሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ በነገው ዕለት በአዲስ አበባ ለማካሄድ አቅዶት የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ ለመስከረም 19 ማዛወሩን የፓርቲው ዋና ፀሃፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ ገለፁ፡፡
ፓርቲው “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በሚል መሪ ቃል ለሶስት ወራት ሲያደርግ የቆየውን የተቃውሞ ሰልፍ ማጠናቀቂያ በነገው ዕለት በአዲስ አበባ ለማድረግ አቅዶ የነበረ ሲሆን ከመስተዳደሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ሰላማዊ ሰልፉን ለመስከረም 19 ለማዛወር ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቋል፡፡ ፓርቲው እስካሁን በተለያዩ ክልሎች ባካሄዳቸው ሰላማዊ ሰልፎች ላይ በራሪ ወረቀቶችና ፖስተሮች እንዳይበትኑና እንዳይለጠፉ እንዲሁም ቅስቀሳ እንዳያካሂዱ ጫና ይደረግባቸው እንደነበር የጠቆሙት የፓርቲው ዋና ፀሃፊ፤ እንዲህ ያሉ ችግሮች እንደማይደርስባቸው ከመስተዳደሩ ጋር ባደረጉት ውይይት እንደተገለፀላቸው ተናግረዋል፡፡
መስተዳደሩ እስከ መስከረም 16 ድረስ ምንም ዓይነት ሰልፍ ማድረግ እንደማይቻል የገለፀላቸው መሆኑን የተናገሩት አቶ ዳንኤል፤ ለዚህ ምክንያቱም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱበት፣ የበዓል ወቅት በመሆኑና ለባቡር ዝርጋታ ተብሎ የተከለለው አጥር መነሳት ስላለበት እንደሆነ መስተዳደሩ ገልፆልናል ብለዋል፡፡ ፓርቲው ምክንያቱን ተቀብሎ የሰላማዊ ሰልፉን ቀን እንደለወጠና ከመስተዳደሩ ሰላማዊ ሰልፉ መፈቀዱን የሚገልፅ ደብዳቤ መቀበሉን ዋና ፀሃፊው ገልፀዋል፡፡
ቀኑ መቀየሩ ለእኛም ጥቅም አለው ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ፖስተር ለመለጠፍ እና ፍላየር ለመበተን ጊዜ ያስፈልገን ነበር፤ ጊዜው መራዘሙ ይህንን በስፋት እንድናከናውን ያግዘናል ብለዋል። መስከረም 19 ቀን የሚደረገውን ሰላማዊ ሰልፍ የፓርቲው ሊ/መንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እንደሚመሩትም አክለው ገልፀዋል - አቶ ዳንኤል።

Published in ዜና

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩትና የምርመራ ሂደታቸው ባለመጠናቀቁ ጉዳያቸው ወደ ምርመራ መዝገብ የተመለሰው እነ አቶ ምህረትአብ አብርሃ፣ በእግዚአብሔር አለበል፣ ተክለአብ ዘርአብሩክ እና ፍፁም ገ/መድህን ላይ በትናንትናው እለት በዋለው ችሎት ለመጨረሻ ጊዜ ተብሎ የ7 ቀን የምርመራ ጊዜ ለ3ኛ ጊዜ ተፈቀደ፡፡
የፌደራሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ቀደም ሲል በነበረው ችሎት በተሰጠው የ8 ቀን የምርመራ ጊዜ በአብዛኛው የኦዲት ስራ መጠናቀቁን በመግለጽ፣ ቀሪ የአንድ ኩባንያ የኦዲት ስራ ባለመጠናቀቁ ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው፤ በምርመራ ሰበብ ያለ አግባብ እየተጉላሉ መሆኑንና ሌሎች የየግል ምክንያታቸውን በማቅረብ የምርመራ ጊዜ የሚፈቀድ ከሆነ ጉዳያቸውን በዋስ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡ የግራ ቀኙን የቃል ክርክር ሲያዳምጥ የቆየው ፍ/ቤቱም፤ መርማሪ ቡድኑ ከጠየቀው የ14 ቀን ውስጥ 7 ቀን ብቻ በመፍቀድ ለመጨረሻ ጊዜ በሚል መዝገቡን ለመስከረም 10 ቀጥሯል፡፡

Published in ዜና

የ1ሺ 500 ብር ሱፍ ወደ 500 ብር ዩኒፎርም ዝቅ ተደርጓል
ጫት የሚቅም ፣ሲጋራ የሚያጨስና ፀጉሩ የተንጨባረረ ሹፌር መግባት አይፈቀድለትም

ኤርፖርት ውስጥ ገብተው የሚጭኑ የሚኒባስ ታክሲ ሾፌሮችና ረዳቶች ዩኒፎርም እንዲለብሱ የታዘዘ ሲሆን ከሚቀጥለው ረቡዕ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንም ተገለፀ፡፡
ቀደም ሲል ሹፌሮቹ የ1ሺ 500 ብር ሱፍ እንዲለብሱ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም አቅማቸውን ያላገናዘበ በመሆኑ በ500 ብር ዩኒፎርም መተካቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በቦሌ ዞን የንስር ታክሲ ባለንብረቶች ማህበር የስምሪት እና የቁጥጥር ሃላፊ አቶ አያሌው ሲሳይ እንደገለፁት፤ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ቅጥር ግቢ ገብተው እንዲሰሩ የተፈቀደላቸው የሚኒባስ ታክሲ ሾፌሮችና ረዳቶች ለአየር መንገዱ ስርዓትና ክብር ሲባል አንድ አይነት ዩኒፎርም እንዲለብሱ ተወስኗል፡፡
የኤርፖርቱን ደረጃ ለመጠበቅና “ታክሲ አሽከርካሪዎች ነን፣ ረዳቶች ነን” በሚል ማጭበርበር እንዳይፈፀም ታስቦ ዩኒፎርሙን ማስለበስ እንዳስፈለገ የሚናገሩት አቶ አያሌው፤ ቀደም ሲል ሹፌሮቹም ረዳቶቹም ሱፍ እንዲለብሱ ታስቦ እንደነበረ ገልፀው ነገር ግን ዋጋው 1ሺህ 500 ብር በመሆኑና የሹፌሩንና የረዳቱን አቅም ያገናዘበ አይደለም በመባሉ ከተወካዮቻቸው ጋር ተወያይተን ሹፌሮቹ 500 ብር የሚያወጣ ጥራቱን የጠበቀ እንደጋውን ያለ ሸሚዝ እንዲለብሱ፣ ረዳቶች ደግሞ በ300 ብር ወጪ ዩኒፎርም እንደሚያሰፉ ገልፀው፤ ዩኒፎርሙ የሚያገለግለው ታክሲዎቹ በኤርፖርቱ ለሚመደቡበት የሶስት ወር ጊዜ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ዩኒፎርሙን ያልለበሱ የታክሲ ሹፌሮችና ረዳቶች ወደ ተርሚናሉ እንደማይገቡ የገለፁት አቶ አያሌው፤ ፀጉራቸውን ያንጨባረሩ፣ ጫት የሚቅሙና ሲጋራ የሚያጨሱም ወደ ኤርፖርቱ መግባት አይፈቀድላቸውም ብለዋል፡፡ ዩኒፎርም መልበሳቸው ብቻ ሳይሆን ንፅህናቸውንም መጠበቅ እንዳለባቸው የተናገሩት አቶ አያሌው፤ ይህንን ማሟላት የማይችሉ ሹፌሮች ውስጥ መግባት ባይችሉም ከቦሌ ድልድይ ጀምረው መስራት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡በኤርፖርት ውስጥ ገብተው የሚሰሩ ታክሲዎች ሲወጡና ሲገቡ ሰዓት ከመመዝገብ አንስቶ ከፍተኛ ቁጥጥር እንሚደረግባቸው የገለፁት አቶ አያሌው፤ ይህም አገልግሎቱ በስርዓት እንዲሰጥ ከማድረጉም በተጨማሪ የተሳፋሪዎች ንብረቶች እንዳይጠፉ ለመከላከል ያስችላል ብለዋል፡፡

Published in ዜና

የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር በ100 ሚሊዮን ብር ለሚያስገነባው የዋና መ/ቤት ሕንፃ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ ዛሬ የመሠረት ድንጋይ ያኖራሉ፡፡
ቀበና ሼል በመባል በሚጠራው አካባቢ የሚሠራው ሕንፃ 2 ምድር ቤትና ሰባት ፎቅ ሲኖሩት ማኅበሩ በሊዝ በገዛው 885 ካ.ሜ ስፍራ እንደሚያርፍ ታውቋል፡፡
የሕንፃው ዲዛይን በኤም ኤች ኢንጂነሪንግ የተሠራ ሲሆን የሕንፃው ግንባታ ሲጠናቀቅ የማኀበሩ ዋና ጽ/ቤት ሆኖ ከማገልገሉም በላይ፣ ምርጥ የጤና አጠባበቅ ማስተማሪያ፣ ማሠልጠኛ፣ የምርምር ማዕከል፣ የኅትመት ክፍሎችና፣ ቋሚ የስብሰባ አዳራሽ እንደሚኖረው ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከክብር እንግዳው በተጨማሪ የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር የበላይ ጠባቂ፣ የዓለም አቀፍ ድርጅትና ኤጀንሲ ተወካዮች፣ የዲፕሎማቲክ አባላት፣ የልማት አጋሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

Published in ዜና

“ሁዋዌ ኢትዮጵያ” በአዲስ ዓመት ዕለት ለክብረ የአረጋውያን ግብረ ሠናይ ድርጅት የተለያዩ ቁሳቁስ ስጦታ ያበረከተ ሲሆን የምሳም ግብዣ አድርጓል፡፡
ሁዋዌ፣ ያበረከተው ቁሳቁስ ትልቅ የልብስ ማጠቢያ ማሽን፣ የውሃ ማጣሪያ፣ ፍራሾች፣ ብርድልብሶችና የምግብ እህሎች ሲሆኑ፣ ጠቅላላ 60ሺህ ብር ግምት እንዳላቸው ታውቋል፡፡
ስጦታውን ለማዕከሉ መሥራችና ዳይሬክተር ለወ/ሮ ወርቅነሽ ሙንኤ ያስረከቡት የ “ሁዋዌ ኢትዮጵያ” ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚ/ር ቶኒ ዱዋን ባደረጉት ንግግር፤ በዚህ ልዩ ዕለት ከአረጋውያን አባቶቻችንና እናቶቻችን እንዲሁም ከማዕከሉ ሠራተኞች ጋር ተጋርተን የተመገብነው ምሳ የበዓል ስሜት መፍጠሩን እርግጠኛ ነኝ ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ወርቅነሽ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፤ ክብረ የአረጋውያን ምግባረ ሰናይ ድርጅትን ከስድስት ዓመት በፊት በቤተሰባቸው በጀት መጀመራቸው ጠቅሰው በአሁኑ ሰዓት 14 ሴትና 24 ወንድ አረጋውያንን በቀን ሦስት ጊዜ እያበሉ፣ እያለበሱና ንጽህናቸውን እየጠበቁ በመንከባከብ ላይ መሆናቸውን እየተንከባከቡ መሆኑን ገልፀዋል።
በማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮግራማቸው ደግሞ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤቶች ማደሳቸውን፣ የመሥራት አቅም ላላቸው ሴቶች ከ100 እስከ 150 ብር የገንዘብ ድጐማ በመስጠት ገቢያቸውን ከፍ እንዲያደርጉ መርዳታቸውን ጠቅሰው፣ በዚህ ፕሮግራም እስከ አሁን ድረስ 716 አረጋውያንን መርዳታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ መስተዳድር ለአረጋውያን መርጃ መሬት በነፃ ስለሰጣቸው አመስግነው፣ በቦታው ላይ 200 አረጋውያንን መያዝ የሚችል መኖሪያ፣ ሆስፒታል፣ እንግዳ ማረፊያ፣ የስብሰባ አዳራሽና የገቢ መፍጠሪያ ማዕከል እየገነቡ መሆኑን ጠቅሰው፣ አቅሙ ያለው ሁሉ ለግንባታው ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡ “ሁዋዌ ኢትዮጵያ” በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ የተሰማራ የቻይና ኩባንያ መሆኑ ታውቋል፡፡

Published in ዜና

በሙዚቃው በመንቀሳቀስ የ11 ዓመታት ልምድ ያለው ዛዮን ሬብልሥ የሙዚቃ ባንድ የአዲስ አልበም “ፕሮቫ” ለአዲስ ዓመት ገበያ አቀረበ፡፡
ዛዮን ሬብልሥ የሙዚቃ ባንድ ለገበያ ያበቃው ፕሮቫ አልበም አራት ዘፈኖች ያሉት ሲሆን፤ ሚክሲንግና ማስተሩን ናቲ ሲምስ እንደሰራው ታውቋል፡፡ ከአራቱ ዘፈኖች የመጀመሪያው ‹‹አዲስ ዓመት›› የተባለው እና ጭብጡ አዲስ ተስፋ አዲስ ትውልድ በሚል የተሰራ ሲሆን ግጥምና ዜማ የሰሩት ዛዮን ሬብልሥ እና ናቲ ሲምስ ናቸው፡፡ ሁለተኛው ‹‹አፍሪካ›› በሚል ለአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዮ የተሠራ ዘፈን ሲሆን፤ ግጥምና ዜማውን በመሥራት ዛዮን ሬብልሥ፣ ናቲ ሲምስ እና ዶቭ ቤንጂ ተሳትፈዋል፡፡
ሦስተኛው፤ ‹‹ላቭ ዊዝ ዋት ዊ ኒድ›› የተባለው ዘፈን ሲሆን፤ በዩቲዩውብ ተጭኖ ከሁለት ሺ አምስት መቶ በላይ ተመልካች ያገኘ ነው፡፡ በዚሁ ዘፈን ግጥምና ዜማ ሥራ ላይ ዛዮን ሬብልሥ፣ ናቲ ሲምስ እና ዶ/ር ቢ (ብሩክ ቦካ) ተሳትፈዋል፡፡ አራተኛው ዘፈን ‹‹ሳባዊት›› በሚል የተዘጋጀ ሲሆን፤ ግጥምና ዜማውን የሰሩት ዛዮን ሬብልሥ እና ናቲ ሲምስ ናቸው፡፡
ዛዮን ሬብልሥ የሙዚቃ ቡድን ሁሉንም ዓይነት ሙዚቃ ይሰራሉ፡፡ ሬብልስ የተባሉት ለአገራቸው መልካም እና ጥሩ ነገሮች በማሰብ ያዳበሩት የታጋይነት መንፈስ ሲሆን በተለይ በሬጌ ሙዚቃቸው የተካኑና ጥሩ መልዕክት እና አህጉራዊ አጀንዳ ያላቸው ዘፈኖችን በመሥራት ከፍተኛ ልምድ ያዳበሩ ናቸው፡፡ በዛዮን ሬብልሥ የሙዚቃ ቡድን ያሉት ዘፋኞች ውቅያኖስ ፍቅሩ፣ ቴዎድሮስ ኃይሌ እና ይስሃቅ ኤልያስ ናቸው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በአዲስ አበባ፣ በድሬደዋ እና በሀዋሣ በርካታ ተመልካች ያገኙ የሙዚቃ ዝግጅቶችን የሠራው ዛዮን ሬብልሥ የሙዚቃ ቡድን ከተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር አርቲስቶች ጋር በመሥራትም ይታወቃል፡፡
አራት ዘፈኖች ያሉበት የዛዮን ሬብልሥ ፕሮቫ አልበም በ2006 ዓ.ም ለገበያ የሚበቃው ሙሉ ዓልበም ማስተዋወቂያ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

 

Published in ዜና