የአዲስ ዓመትን በዓል ምክንያት በማድረግ ዜቲኢ ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለከተሞች ለሚገኙ 70 ችግረኛ ቤተሰቦች የአዲስ ዓመት ድጋፍ አበረከተ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ዜድቲኤ ባደረገው ድጋፍ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ አንድ እሽግ ደብተርና አምስት ኪሎ ስጋ የሰጠ ሲሆን በዕለቱ ህፃናትና ቤተሰቦች በኮርፖሬሽኑ ድጋፍ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
የዜቲኢ ሥራ አስኪያጅ ሚ/ር ሃን ኤችአር ድጋፉን አስመልክተው ሲናገሩ፤ “ዜቲኢ በመሰረተ ልማት አቅርቦት ስራ ላይ የተሰማራ ኩባንያ ብቻ ሳይሆን፤ ከማህበረሰቡ ጋር በጥብቅ የተቆራኘና የህዝቦችን አቅም በማጐልበት የሚያምን ነው” በማለት ኩባንያው ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ በደስታና በብልጽግና የተሞላ አዲስ ዓመት እንደሚመኝ ገልፀዋል ያሉት የጉለሌ ክፍለከተማ የሰራተኛ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ መሰረት መንገሻ በበኩላቸው፤ “የዜቲኢን ድጋፍ በደስታ የምንቀበለው ነው፡፡” “ድጋፉ ኮርፖሬሽኑ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያለውን ቅርርብና የህዝቡን አቅም በማጐልበት ረገድ የድርሻውን ለማበርከት ያለውን በጐ ፈቃድ ያሳያል።” ብለዋል - የዜቲኢ ድጋፍ ወደፊትም እንደሚቀጥል ያላቸውን ምኞት በመግለጽ፡፡

Published in ዜና
Friday, 13 September 2013 13:10

አርቲስቶች ለአዲስ ዓመት

“እወድሃለሁ” የአስቴር አዲስ አልበም ወጣ
የታዋቂዋ ድምፃዊ አስቴር አወቀ “እወድሃለሁ” የተሰኘ አዲስ አልበም ሰኞ ዕለት ለገበያ ቀረበ፡፡ አስራ ሁለት ዘፈኖች የያዘው አልበም፤ የድምፃዊቷ ድርጅት በሆነው ካቡ ሪከርድስ ኤክስኩዩቲቭ ፕሮዲዩሰር የተሰራ ሲሆን የሚያከፋፍለው ኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ነው፡፡የአብዛኛዎቹ ዘፈኖች ግጥም እና ዜማ ደራሲ ራሷ ድምፃዊቷ ስትሆን ቅንብሩን የሰሩት አበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ፣ሄኖክ ነጋሽ እና ካሙዙ ካሳ ናቸው፡፡

===============

የአርቲስት ስለሺ የአዲስ ዓመት ስጦታ

“ኢትዮጵያዊነት ጥበብ ነው”

ባለፈው አርብ አርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) “ያምራል ሀገሬ” የተሰኘውን የሙዚቃ አልበም በሂልተን ሆቴል አስመርቋል፡፡ የምረቃ ስነስርዓቱን ያዘጋጀው የማስተርስ ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ቢኒያም ከበደ፤ አልበሙ ከሁለት ዓመት በላይ የተለፋበት መሆኑን ጠቁሟል፡፡ አርቲስት ስለሺ ለአንድ ሰዓት ያህል ስለ አዲሱ ሥራውና ስለ ኢትዮጵያዊነት ሠፊ ማብራሪያ የሰጠ ሲሆን በዕለቱ ካቀረበው ንግግር ኢትዮጵያዊነት ላይ ያተኮረውን እንደሚከተለው ቀንጭበን አቅርበነዋል፡፡
“ሜታዎች ሙዚቃህን ሊያዳምጡ የሚችሉት እነማን ናቸው አሉኝ፡፡ እኔም ‘ለየት ያሉ ናቸው፤ ቤታቸው ያሉ፣ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በደንብ ያላገኙ ናቸው፡፡ አድማጮቼ የራሳቸው ምስጢር ያላቸው ናቸው ስላቸው’ ያለንን ገንዘብ ሁሉ ውሰድ ብለውኛል፡፡
“የዛሬ አስራ አምስት ዓመት ለዐይን ይቀፍ የነበረ ከተማ ብዙ ባይሆንም የፀዳው በእናንተ ጭምር ነው፡፡ ንፁሕ አመለካከት ቢኖረን ኢትዮጵያዊነት የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር አይደለም፡፡ እኛ ግን የማንነት ቀውስ ውስጥ ገብተናል፡፡ ሰው ራሱን ያጣ ጊዜ የመጨረሻ ውድቀት ነው፡፡ እስቲ ፈረንጅ ነኝ ብዬ ልቅረብ፤ ለእናንተ እንደ ፈረንጅ ላወራ እችላለሁ፡፡ ሰውነቴን መለወጥ እችላለሁ፡፡ ግን ፈረንጅ ነኝ? አይደለሁም፡፡ መሆንም የለብኝም፡፡ እያመራን ያለንበት አቅጣጫ ያሳፍራል፡፡ እንግሊዝኛ የምንጠቀመው የእናት የአባታችን ቋንቋ ጠፍቶን ነው? እንግሊዝኛ ማጣፈጫ የእውቀት ምልክት ስለሚመስለን ነው?
“የዛሬው የሙዚቃ ሥራ የኢትዮጵያን የባሕል መሳሪያዎች ይዞ የተሰራ ነው፡፡ ተረቶቻችንን፣ ፍልስፍናችንን፣ ጥበብን … ይዞ ማንነታችንን ይበልጥ የምናወጣበት ነው፡፡ ብዙ የውጭ ሰዎች ተስፋ ቆርጠውብናል፡፡ ኢትዮጵያ የራሷ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ቅኝ ያልተገዛች ሀገር ናት ብለን ስንመጣ ጣራው፣ ግድግዳው፣ ምግቡ … ውስጥ ኢትዮጵያዊነት የለም። እንግሊዝኛ ሳይችሉ አማርኛ የጠፋባቸው ብዙዎች አሉ ተባብለናል፡፡
“ፈረንሳዊቷ እዚህ መጥታ ካፌ ስትገባ ወንዶቻችን ነይ እዚህ ጋ ተቀመጭ አሏት፤ በእንግሊዝኛ፡፡
እርሷ ግን በአማርኛ “አይ እዚህ ጋ ነው መቀመጥ የምፈልገው” አለቻቸው፡፡
“አማርኛ ትችያለሽ እንዴ?”
“አዎ”
“የት ተማርሺው?”
“ፈረንሳይ ሀገር ሶርቦር ዩኒቨርሲቲ” አለች፡፡
ጀርመኖች፣ ፈረንሳዮችና ሌሎች እኛን ግእዝ፣ የግእዝ ቅኔ፣ አማርኛ … ያስተምራሉ፡፡ እኛን አማርኛ፤ እኛን ኦሮምኛ፤ እኛን ወላይትኛ የሚያስተምሩ ገና ይመጣሉ፡፡ እንኳን ደስ አለን …
ኢትዮጵያዊነት ጥበብ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና ነው፡፡ ሥልጣኔ ነው … አንድ ቦታ ከራሳችን ጋር መጋጨታችን መቆም አለበት፡፡ የልጆቻችንን ሥም የኢትዮጵያዊነት ሥም እንስጥ፤ ቆንጆ ቆንጆ ስሞች አሉን፡፡ ለምሣሌ የአንድ ሰው ስም ቶሚ እና ምናምን ከሚባል ደንድር ቢባል ራሱን የቻለ ሙዚቃ ነው፡፡ ኒውዮርክ ካፌ ከሚባል ቀበሪቾ ወይም ጤና አዳም ቢባልስ? ስንት ሥም አለን፤ አፀደ፣ ምንትዋብ፣ ሳልሳዊት፣ ዳግማዊት … እነዚህ ሁሉ ታላላቅ ሥሞች ናቸው፡፡ ይኼ እንቅልፍ ይነሳችኋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የራሳቸው ማንነትና ሐይማኖት አላቸው፡፡ ማንነታችንን ግን አሳልፈን እየሰጠን ነው። አስራ ሦስቱ ሙዚቃዎቼ ሥዕላዊ ናቸው፡፡ ለምሳሌ “አይ ምንትዋብ” በሚለው ምንትዋብን ታያላችሁ…”


=========================

“ጥረቴን ወደ ስኬት የቀየርኩበት ዓመት ነው”
በ2005 መጀመሪያ ላይ ከፍተኛ ፈተናዎች ነበሩብኝ፡፡ ሁለተኛ አልበሜን ለማጠናቀቅ ደፋ ቀና የምልበት ወቅት ነበር፡፡ 

እጅግ ውጥረት ነበረብኝ፡፡ በአመቱ መጨረሻ ላይ ግን ድካሜ፣ ውጥረቴና ጥረቴ ፍሬ ያፈራበት በመሆኑ ለእኔ የስኬት ዘመን ሆኗል፡፡ ስለሆነም ፈተናውን ስኬቱ ሸፍኖታል፡፡ በጤናም በማህበራዊ ግንኙነቴም በጣም ጥሩ ነበርኩኝ፡፡ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡
በ2006 አዲስ አመት ብዙ እቅዶች አሉኝ። በእቅድ የመመራት ልምድ አለኝ፡፡ አልበሜን በመስከርም ወር መጨረሻ ማለትም መስከረም 23 ቀን በሸራተን ጋዝ ላይት አስመርቃለሁ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ በአዲስ አበባና በክልሎች ኮንሰርቶችን ለመስራት እቅድ አለኝ፡፡ የውጭ አገር ጉዞዎችም ይኖሩኛል፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይሳካል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አዲስ አመት የደስታ፣ የጤናና የስኬት እንዲሆን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እመኛለሁ፡፡ መልካም አዲስ አመት ይሁንልን፡፡

=============

እውቋ ድምፃዊ ሐመልማል አባተ “ያደላል” በሚል መጠሪያ ለአዲስ አመት አዲስ አልበም ሰርታ ያሳተመች ሲሆን አልበሟ ከዛሬ ጀምሮ እንደሚሸጥ ብቸኛው የአልበሙ አከፋፋይ ሮማሪዮ ሪከርድስ ገለፀ፡፡
አልበሙ ጎጃምኛ፣ ጉራግኛ፣ ሙዚቃው ትግርኛ የሆነ እና የአማርኛ ዘፈን ኦሮምኛና ባህላዊ ዜማዎች የተካተቱበት ሲሆን በዛ ያሉ የፍቅር ዘፈኖችን እንደያዘም ታውቋል፡፡ ድምፃዊቷ ለአዲሱ አመት ዋዜማ በሚሌኒየም አዳራሽ በሚቀርበው የሙዚቃ ድግስ ላይ ከአዲሱ ሥራዋ የተወሰኑትን እንደምታቀነቅን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ድምፃዊ ሀመልማል አባተን ስፖንሰር በማድረግ አልበሟን ያሳተመው ሞሃ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ ሲሆን ለአልበሙ ከ500ሺ ብር በላይ እንዳወጣ ተገልጿል፡፡
ሮማሪዮ ሪከርድስ በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣በደብረ ማርቆስና በባህርዳር በከፈታቸው ቅርንጫፎቹ በርካታ የሙዚቃ ስራዎችን እያሳተመ በማከፋፈል ላይ ሲሆን ለአዲስ አመትም የሐመልማልን ስራ ጨምሮ አራት ስራዎችን ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የድርጅቱ ባለቤት አቶ ቴዎድሮስ በቀለ ገልፀዋል፡፡

 

Published in ጥበብ

ወደ 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለመብቃት ለጥሎ ማለፍ ምእራፍ ከደረሱ 10 የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በእግር ኳስ ደረጃው፤ በፕሮፌሽናል ተጨዋቾቹ ብዛትና በዝውውር ገያው የዋጋ ተመኑ ዝቅተኛው መሆኑን ከትራንስፈርማርኬት ድረገፅ ያገኛናቸው አሃዛዊ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ኢትዮጵያ
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 102 በአፍሪካ 27
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 5
የዝውውር ገበያ ተመን -775ሺ ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 25.20
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 321
አልጄርያ
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 34 በአፍሪካ
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 19
የዝውውር ገበያ ተመን -51.5 ሚሊዮን ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 26.8
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 300
አይቬሪኮስት
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 18 በአፍሪካ 1
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 25
የዝውውር ገበያ ተመን -135 ሚሊዮን ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 26.9
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 772
ናይጄርያ
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 35 በአፍሪካ 5
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 18
የዝውውር ገበያ ተመን -56 ሚሊዮን ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 24.10
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 362
ጋና
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 24 በአፍሪካ 2
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 34
የዝውውር ገበያ ተመን -77 ሚሊዮን ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 25.20
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 725
ኬፕቨርዴ
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 36 በአፍሪካ 6
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 25
የዝውውር ገበያ ተመን -16.5 ሚሊዮን ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 26.5
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 244
ግብፅ
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 61 በአፍሪካ 11
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 11
የዝውውር ገበያ ተመን -29 ሚሊዮን ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 26.5
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 880
ቡርኪናፋሶ
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 48 በአፍሪካ 7
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 26
የዝውውር ገበያ ተመን -235 ሚሊዮን ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 26.7
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 535
ሴኔጋል
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 78 በአፍሪካ 17
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 26
የዝውውር ገበያ ተመን -97.5 ሚሊዮን ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 25.5
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 247
ካሜሮን
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 51 በአፍሪካ 8
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 28
የዝውውር ገበያ ተመን -125 ሚሊዮን ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 26
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 498

  ========

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ ስኬት በማግኘት በአገሪቱ እግር ኳስ ላይ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ ዋልያዎቹ በሚል ስሙ የታወቀው ይህ የእግር ኳስ ትውልድ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ 180 ደቂቃዎች ቀርተውታል፡፡ ዋልያዎቹ ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፍ በ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በቅተዋል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ በደቡብ አፍሪካ በሚስተናገደው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ “ቻን” ተሳታፊ ናቸው፡፡ በዋልያዎቹ አስደናቂ ጥረት 2005 ዓ.ም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ትልቁ ስኬት እንዲመዘገብ ሆኗል፡፡ የዚህ ትውልድ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች የአገሪቱን የእግር ኳስ ደረጃ ብቻ አላሻሻሉም፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የፕሮፌሽናሊዝም ጉዞ ፈር ቀዳጅ ለውጦችን እየፈጠሩ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ የዋልያዎቹ አባላት ባገኙት ውጤት ልክ በገንዘብ ሽልማት ከ300 እስከ 450ሺ ብር በመሰብሰብ የላባቸውን ዋጋ እያገኙ ነው፡፡ በፕሮፌሽናል ተጫዋችነት ወደ 6 የተለያዩ አገራት ወደ የሚገኙ ክለቦች በመሰማራት ከፍ ያለ ደሞዝና ጥቅም በማግኘትም በዝውውር ገበያው ተፈላጊነታቸው እየጨመረ የመጣ ነው፡፡ ለመሆኑ ዋልያዎቹ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያሳለፉት የእግር ኳስ ገድል ምን መልክ ነበረው? በአፍሪካ ዋንጫ እና የማጣርያ ውድድሮች ምን ታሪክ ሠሩ? በዓለም ዋንጫ በሁለት ዙር ማጣርያዎች 8 ብሔራዊ ቡድኖችን ጥለው ያለፉበት ጉዞ ምን ይመስላል?
ከ31 ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ
ዋልያዎቹ ከ31 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን ወደመሠረተችው አህጉራዊ ውድድር በመመለስ ደቡብ አፍሪካ ላስተናገደችው ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ያለፉት በቀላሉ አልነበረም፡፡ በመጀመርያ የማጣሪያ ምዕራፍ ከቤኒን ጋር በጥሎ ማለፍ ተደልድለው በሜዳቸው 0ለ0 ሲለያዩ፣ በአበበ ቢቂላ ስታድየም የተደረገው ጨዋታ ጐል ማግባት ያልተቻለበት መሆኑ በወቅቱ የነበሩትን ቤልጅማዊ ዋና አሰልጣኝ ቆም ሴንትፌንት እና ምክትላቸውን ሰውነት ቢሻው ያስተቸ ነው፡፡ በመልሱ ቤኒን ላይ ሲጫወቱ 1ለ1 አቻ ሆኑ፡፡ ጐሏን ያስቆጠረው አዳነ ግርማ ነበር፡፡ ስለሆነም ከሜዳ ውጭ ባገባ በሚለው የአሸናፊ መለያ ህግ ወደቀጣዩ ምእራፍ ተሸጋገሩ፡፡ወደ አፍሪካ ዋንጫ ወደየሚያሳልፈው የመጨረሻው ምእራፍ ማጣርያ የተገናኙት ከጐረቤት አገር ሱዳን ጋር ነበር፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ ዋልያዎቹ በሜዳቸው ሱዳንን 2ለ0 ነበር ያሸነፉት፡፡ በመልሱ ጨዋታ ካርቱም ላይ ሲገናኙ እጅግ አስጨናቂ በነበረበት ጨዋታ 5ለ3 ተሸነፉ፡፡ በአጠቃላይ የደርሶ መልስ ጨዋታዎቹ ውጤት 5ለ5 እኩል ሆነ፡፡ ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚያልፈው ብሔራዊ ቡድን ከሜዳው ውጭ ብዙ ባገባ በሚለው ተለየ፡፡ በሁለቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያዎች በዋልያዎቹ የተሰበረ መጥፎ ሪከርድ ነበር፡፡ ከሜዳ ውጭ ወሳኝ ጐሎችን በማግባት ውጤታማ መሆን ስለተቻለ ነው፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በቃ፡፡ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 3 ከናይጀሪያ ከቡርኪናፋሶ እና ዛምቢያ ጋር ተመደበ፡፡ በመጀመርያ ጨዋታ ከዛምቢያ ጋር 1ለ1 አቻ ወጣ ከዚያም በሁለተኛ ጨዋታው በቡርኪናፋሶ 4ለ0 እንዲሁም በመጨረሻው የምድቡ ጨዋታ በናይጀሪያ 2ለ0 ተሸነፈ፡፡ በዚህ ውጤቱ መሰረትም በምድብ 3 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባስመዘገበው 1 ነጥብና 6 የግብ እዳ የመጨረሻ ደረጃ ይዞ ከአፍሪካ ዋንጫው በግዜ ተሰናበተ፡፡ ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፋቸው ትልቅ ውጤት ነበረው፡፡ የመጀመርያው በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ለውድድሩ ከፍተኛ ድምቀት በማላበስ ለዋልያዎቹ ያስገኙት ትኩረት ነው፡፡ በሌላ በኩል ብሔራዊ ቡድኑ በምድቡ የመክፈቻ ጨዋታ ከዛምቢያ 1ለ1 አቻ ሲለያይ ለኢትዮጵያ የተመዘገበችው የአዳነ ግርማ ብቸኛ ጐል በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከ33 ዓመት በኋላ የተመዘገበች ነበረች፡፡ የዋልያዎቹ አባላት በደቡብ አፍሪካ፣ በሰሜን አፍሪካ፣ በምስራቅ አውሮፓ ክለቦች በመፈለግ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ጉዟቸው የተሟሟቀው በአፍሪካ ዋንጫ በነበራቸው ተሳትፎ ነው፡፡
በሁለት ዙር የዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች
ለ20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ ማጣርያ ሲገባ በመጀመሪያ ዙር ለጥሎ ማለፍ ጨዋታ የተደለደለው ከጐረቤት አገር ሶማሊያ ጋር ነበር፡፡ የመጀመሪያው ጨዋታ በጅቡቲ ሲደረግ ውጤቱ 0ለ0 ነበር፡፡ ይህ ውጤት ስፖርት አፍቃሪውን ተስፋ ለማስቆረጥ የተፈታተነ ነበር፡፡ በመልሱ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ 5ለ0 ሶማሊያን ያሸነፉን ዋልያዎች ወደ ሁለተኛው ዙር የምድብ ማጣርያ ምዕራፍ ተሸጋገሩ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 1 ከደቡብ አፍሪካ፣ ከቦትስዋና እና ከመካከለኛው አፍሪካ ነበር የተደለደለው፡፡ በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ በሩስተንበርግ ሮያል በፎኬንግ ስታድዬም ከደቡብ አፍሪካ ጋር 1ለ1 አቻ በመለያየት ጥሩ ጅማሬ አደረጉ፡፡ ከሜዳ ውጭ ደቡብ አፍሪካ ላይ ጐሉን ያስቆጠረው ሳላዲን ሰኢድ ነበር፡፡ በ2ኛው የምድብ ጨዋታ ዋልያዎቹ በአዲስ አበባ ስታድዬም መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊካን በማስተናገድ 2ለ0 አሸንፈው ምድቡን በአንደኛነት መምራት ጀመሩ፡፡ በዚህ ጨዋታ ላይም ሁለቱንም ጐሎች ከመረብ ያዋሃደው ሳላዲን ሰኢድ ነው፡፡ ከዚያም በ3ኛው የምድብ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ቦትስዋናን ገጠሙ፡፡ በጌታነህ ከበደ ጐል 1ለ0 በማሸነፍ መሪነታቸውን አጠናክረው ቀጠሉ፡፡ ከዚያ በኋላ በ4ኛው የምድብ ጨዋታ ከቦትስዋና ጋር ዋልያዎቹ በዋና ከተማዋ ጋብሮኒ ሎባታሴ ስታድዬም ተገናኝተው 2ለ1 ከሜዳ ውጭ አሸንፈው ነበር፡፡ አንዱን ጐል ሳላዲን፣ ሌላኛው ጌታነህ አስቆጥረዋል፡፡ በዚሁ ጨዋታ በሁለት ቢጫ ካርድ ቅጣቱ መሰለፍ ያልነበረበት ምን ያህል ተሾመ ተሰልፎ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በፊፋ ህገ ደንብ ተቀጪ ሆና 3 ነጥብ 3 ነጥብ ተቀነሰባትና ሙሉ ሶስት ነጥብ እና የ3ለ0 ውጤት ለቦትስዋና እንዲሰጥ ተወስኗል፡፡ ከዚያ አሳዛኝ ጥፋትና ቅጣት በፊት የምድቡ 4ኛ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የተደረገው ነበር፡፡ ዋልያዎቹ በሜዳቸው ደቡብ አፍሪካን 2ለ1 አሸነፉ፡፡ 1 ጐል ጌታነህ ከበደ ሲያስቆጥር የማሸነፊያውን ጐል ደግሞ የደቡብ አፍሪካው ተጫዋች መረብ ላይ ያገባው ነበር፡፡ ይሁንና ከምድቡ በመሪነት ማለፉን ለማረጋገጥ የምድቡ የመጨረሻ ዙር ጨዋታዎች መጠበቅ ነበረባቸው፡፡ ባለፈው ቅዳሜ በኮንጎ ብራዛቪል የምድብ 1 የመጨረሻ ጨዋታቸውን ከሴንተራል አፍሪካ ሪፖብሊክ ጋር ተደረገ፡፡ በሳላዲን ሰኢድ እና በምንያህል ተሾመ ጐሎች 2ለ1 በማሸነፍ ምድብ 1 ላይ በመሪነት ጨረሱ፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 1 የደረጃ ሰንጠረዥ በ6 ጨዋታዎች ምንም ሳይሸነፍ በ1 ጨዋታ በቅጣት 3 ነጥብ ተቀንሶበት በ13 ነጥብና በ2 የግብ ክፍያ መሪ በመሆን ለቀጣዩ ምእራፍ በቅቷል፡፡ ዋልያዎቹ በምድብ ማጣርያውን ያለፉበት ሂደት አስደናቂ ልዩ የሚሆነው በተመሳሳይ የተሳትፎ ታሪክ ትልቁ ውጤት በመሆኑ ነው፡፡ ከቅድመ ማጣሪያው ከተነሱ ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው 24 ብሔራዊ ቡድኖች ለመጨረሻው የጥሎ ማለፍ ምዕራፍ የደረሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ብቻ መሆኑ ደግሞ ሌላው ስኬት ነው፡፡ እስከ ምድብ ማጣርያው በአጠቃላይ 8 ጨዋታዎችን አድርገዋል፡፡ 5 ጨዋታዎችን ድል አደረጉ፡፡ አራቱን በሜዳ አንዱን ከሜዳው ውጭ ነው፡፡ በ2 ጨዋታዎች አቻ ወጡ፡፡ ሁለቱንም ከሜዳ ውጭ ነበር፡፡ እንደ ሽንፈት የተቆጠረው ግጥሚያ ሁለት ቢጫ ካርድ ያየ ተጨዋች በመሰለፉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጀመርያ 2ለ0 አሸንፎ ለቦትስዋና በቅጣት በፎርፌ 3ለ0 እንዲሸነፍ የተደረገበት ነው፡፡ በስምንቱ ጨዋታዎች በተጋጣሚዎቹ ላይ 13 ጎሎች ያስመዘገበው ብሄራዊ ቡድኑ የተቆጠረበት ግብ 6 ሲሆን በእያንዳንዱ ጨዋታ በአማካይ 1.63 ጎሎች እንደሚያገባ እና 0.75 ጎል ሊገባበት እንደሚችል የፊፋ ስታስቲካዊ ስሌት ያመለክታል፡፡ ከስምንቱ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ግጥሚያዎች ሁሉንም በመሰለፍ ለ709 ደቂቃዎች የተጫወተው አበባው ቡጣቆ ነው፡፡ ስዩም ተስፋዬ በ7 ጨዋታዎች ለ575 ደቂቃዎች በመሰለፍ ከፍተኛውን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ሳላሃዲን ሰኢድ በ6 ጨዋታዎች ለ540 ደቂቃዎች በመሰለፍ አራት ጎሎች ያገባ ሲሆን ሌሎቹ በ6 ጨዋታዎች ያገለገሉት 446 ደቂቃዎች ተሰልፎ ሁለት ያገባው ሽመልስ በቀለ እና ለ540 ደቂቃዎች የተጫወተው አምበሉ ደጉ ደበበ ናቸው፡፡ አይናለም ሃይሉ፤ አስራት መገርሳ፤ አዲስ ህንፃ እና ምንያህል ተሾመ እያንዳንዳቸው በ5 ጨዋታዎች ለብሄራዊ ቡድኑ በመሰለፍ ከ425 እስከ 450 ደቂቃዎች ግልጋሎት የሰጡ የዋልያዎቹ አባላት ናቸው፡፡
ለዓለም ዋንጫ 180 ደቂቃዎች ጉዳይ
ኢትዮጵያ ለዓለም ዋንጫ የመጨረሻ የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ በመብቃቷ በውድድሩ የተሳትፎ ታሪክ ትልቅ ውጤት ሆኖ ተዘመግቧል፡፡ በታሪካዊው የጥሎ ማለፍ ምዕራፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ 10 ብሔራዊ ቡድኖች አንዱ ሆኗል፡፡ የ3ኛው ዙር ወደ ዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ድልድል ለ10ሩ ብሔራዊ ቡድኖች የሚወጣው ከሳምንት በኋላ በካይሮ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከምዕራብና ከሰሜን አፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች የሚገናኝበት እድል ያመዝናል፡፡ ብራዚል በ2014 እኤአ በምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ በዓለም ዙርያ ከሚገኙ 6 ኮንፌደሬሽኖች የተውጣጡ 203 አገራት መካከል በተለያዩ የማጣርያ ምእራፎች ሲደረግ የቆየው ፉክክር 34 ወራትን አስቆጥሯል፡፡ ይሄው የማጣርያ ሂደት ሊጠናቀቅ 2 ወራት ቀርቶታል፡፡ በአዘጋጅነት ያለፈችውን ብራዚል ጨምሮ ጃፓን፤ አውስትራሊያ፤ ኢራንና ደቡብ ኮርያ ለ20ኛው ዓለም ዋንጫ ማለፋቸውን ያረጋገጡ ናቸው፡፡ በቀረው የ27 ብሄራዊ ቡድኖች የዓለም ዋንጫ የተሳትፎ ኮታ በስድስቱ ኮንፌደሬሽኖች 67 አገራት የማለፍ እድል እንደያዙ ናቸው፡፡ በዓለም ዋንጫ የተሳትፎ ኮታ መሰረት ለአፍሪካ ዞን የተሰጠው እድል ለ5 ብሄራዊ ቡድኖች ነው፡፡ እነዚህን 5 ብሄራዊ ቡድኖች ለመለየት በአፍሪካ ዞን የሚደረገው የመጨረሻ ጥሎ ማለፍ ምእራፍ ከ5 ሳምንት በኋላ በመጀመርያ ጨዋታዎች ይጀመራል፡፡
በአፍሪካ ዞን የምድብ ማጣርያ ከ10 ምድቦች በመሪነት ያለፉት 10 ቡድኖች ታውቀዋል፡፡ እነሱም ግብፅ፤ አልጄርያ፤ አይቬሪኮስት፤ ጋና፤ ኢትዮጵያ ፤ ኬፕቨርዴ፤ ጋና፤ ቡርኪናፋሶ፤ናይጄርያ፤ ሴኔጋል እና ካሜሮን ናቸው።
ከሳምንት በኋላ ለአስሩ ብሔራዊ ቡድኖች ወደ የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ድልድል በካይሮ ከተማ ሲመጣ ከቀናት በኋላ በሚታወቀው የፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ መሠረት ነው፡፡ በደረጃ ሰንጠረዥ ከፍተኛ እርከን ላይ የሚገኙ 5 ብሄራዊ ቡድኖች በአንድ የእጣ ማሰሮ ሌሎች ዝቅተኛ እርከን ላይ የሚገኙ ብሄራዊ ቡድኖች በሁለተኛ ማሰሮ እንዲቀመጡ ይደረጋል፡፡ በማሰሮ 1 አይቬሪኮስት፤ ጋና፤ አልጄርያ፤ ናይጄርያና ኬፕቨርዴ አይስላንድ እንዲሁም በማሰሮ 2 ቡርኪናፋሶ፤ ካሜሮን፤ ግብፅ፤ ሴኔጋል እና ኢትዮጵያ ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ የዓለም ዋንጫ በሚያሳልፈው ጥሎ ማለፍ ከአይቬሪኮስት፤ ከጋና፤ ከአልጄርያ፤ ከናይጄርያ ውይም ከኬፕቨርዴ አይስላንድ ጋር የሚገናኝበት ሁኔታ የሚፈጠር ይመስላል፡፡ በደርሶ መልስ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ላይ የማሸነፍ እድል ቡድኖች እኩል 50 በመቶ ይሆናል፡፡ በዓለም አቀፉ ‹አርኢቺ ስፖርት ሶከር ስታትስቲክስ ፋውንዴሽን› የመረጃ መዝገብ መሰረት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ባለው ታሪክ መነሻነት የሚያገኘውን ውጤት ለመገመትም ይቻላል፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጥሎ ማለፍ ሊገናኛቸው ከሚችላቸው 9 ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ያለው የማሸነፍ ስኬት በመቶኛ ሲሰላ የሚከተለውን ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በግምታዊ የጥሎ ማለፍ የጨዋታ ድልድል ላይ በማሰሮ 1 ሲደለደል ከአልጄርያ ጋር 50 በመቶ፤ ከአይቬሪኮስት ጋር 33.33 በመቶ፤ ከናይጄርያ ጋር 16.67 በመቶ፤ ከጋና ጋር 50 በመቶ የማሸነፍ እድል ሲኖረው ከኬፕቨርዴ ጋር በታሪክ ተገናኝቶ ስለማያውቅ ለመገመት ያስቸግራል፡፡ በተቀረ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አብሮ በማሰሮ 2 ለድልድል ከተመደበባቸው ቡድኖች ጋር የሚገናኙበት ሁኔታ ከተፈጠረ ከቡርኪናፋሶ ጋር 50 በመቶ፤ ከሴኔጋል ጋር 0 በመቶ፤ ከግብፅ ጋር 16.6 በመቶ እንዲሁም ከካሜሮን ጋር 16.67 በመቶ የማሸነፍ እድል ይኖረዋል፡፡

ስም ምሩፅ ገ/እግዚአብሔር ይባላል፡፡ በራሽያዋ ከተማ ሴንቲ ፒተርስበርግ የባቡር ዝርጋታ ምህንድስና (ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ) ተማሪ ነው፡፡ በሃሮማያ ዩኒቨርስቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ዲፓርትመንት መምህር ሆኖ በማገልገል ላይ ሳለ በመጣ የነፃ ትምህርት ዕድል አሸንፎ ራሽያ የገባ ኢትዮጵያዊ ነው። ከጋዜጠኛ ግሩም ሰይፉ ጋር በሞስኮ ከተማ ተገናኝተው ያደረጉት ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

ትውልድህ የት ነው? የተማሪ ቤት ቆይታህስ?
የተወለድኩት በትግራይ ክልል ግሎማህደር በተባለ ስፍራ ነው፡፡ በአዲግራት ውስጥ የምትገኝ የገጠር መንደር ናት፡፡ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት እዚያው አዲግራት በሚገኘው አጋዚ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ጥሩ የማትሪክ ውጤት ስለነበረኝ ጥሩ ትምህርት ለመማር እድል አገኘሁ፡፡ ኢንጂነሪንግ የመማር ፍላጐት ነበረኝ፡፡ እናም ሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ገብቼ ሲቪል ኢንጂሪነግ ለ4 ዓመት ተምሬ በጥሩ ውጤት ተመረቅሁ፡፡ የምረቃ ውጤቴ ለዩኒቨርስቲ አስተማሪነት የሚያበቃ ነበር፡፡ ሃሮማያ ዩኒቨርስቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ዲፓርትመንት በአስተማሪነት ተመደብኩ፡፡ እዚያ ለሁለት ዓመት ካስተማርኩ በኋላ፣ የነፃ ትምህርት ዕድል ከሁለት አቅጣጫዎች መጣልኝ፡፡ አንደኛው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሃይዌይ ኢንጂነሪንግ ሲሆን ሁለተኛው ከራሽያ በሬልዌይ ኢንጂነሪንግ የምማርበት እድል ነው፡፡ የሬልዌይ ኢንጂነሪንግ ትምህርት በኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት እንቅስቃሴ አዲስና ተፈላጊ ሆኖ የመጣ ዘርፍ ቢሆንም በዘርፉ ብዙ የተማረ ሃይል የለም፡፡ በአገራችን ከባቡር ትራንስፖርት ፕሮጀክቶች መጀመር ጋር በተያያዘ በሬልዌይ ኢንጂነሪንግ በራሽያ የተማሩ የመጀመሪያ ተመራቂዎች አገራቸው ተመልሰው መስራት የጀመሩት ባለፈው ዓመት ነበር፡፡ እኔ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችም በዚሁ ዘርፍ በራሽያ ለመማር እድል አገኘ፡፡
የነፃ ትምህርት ዕድሉን ያገኘኸው እንዴት ነው?
የራሽያ የነፃ ትምህርት ዕድል እንደሌሎች የአውሮፓና ያደጉ አገራት በግልህ በመፃፃፍ አይደለም የምታገኘው፡፡ የራሽያ እና የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስትር መ/ቤቶች በሚያደርጉት ስምምነት የሚገኝ ዕድል ነው፡፡ እኔ በሃሮማያ ዩኒቨርስቲ እያስተማርኩ ከትምህርት ሚኒስቴር ለራሽያ የነፃ ትምህርት ዕድል ተወዳደሩ የሚል ማስታወቂያ መጣ፡፡ መስፈርቶቹን ለማሟላት በመቻሌ፣ የነፃ ትምህርት ዕድሉን ካገኙት ኢትዮጵያውያን አንዱ ሆንኩኝ። ዕድሉ የመጣልኝ ራሽያዋ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ሴንት ፒተርስበርግ ከሚገኘው ስቴት ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ ነው፡፡ ዩኒቨርስቲው በዓለም ላይ ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ ከሚያስተምሩ ዩኒቨርስቲዎች ታዋቂና በጥራቱ የሚጠቀስ ነው። በዩኒቨርስቲው ውስጥ ብዙ ኢትዮጵያዊ የለም። ከእኔ ጋር ከሚማሩት ኢትዮጵያውያን አንዱ፣ ከሌላ ዩኒቨርስቲ በተመሳሳይ መንገድ የመጣ ሲሆን፤ ሌሎቹ ደግሞ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የላካቸው ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በዩኒቨርስቲው ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ እየተማርን ያለነው ኢትዮጵያውያን አስር ነን፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት አንድም ተማሪ የለም፡፡
ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ ምን አይነት የትምህርት ዘርፍ ነው? ትምህርቱ እንዴት ነው? ከባድ ነው እንዴ?
መማር የጀመርኩት በራሽያኛ ቋንቋ ነው። በመጀመሪያ ቋንቋውን ማጥናት ነበረብኝ፡፡ በኢትዮጵያ በሬልዌይ ኢንጂነሪንግ የሚያስተምር አንድም ተቋም አለመኖሩም የትምህርቱን አጀማመር ከባድ ያደርገዋል፡፡ ቋንቋውንና የሬልዌይ ኢንጂሪነግ የጀማሪ ኮርሶች ለማጥናት አንድ ዓመት ያስፈልግ ነበር፡፡ በኋላ በቀጥታ ወደ ዋናው የሬልዌይ ኢንጂሪነሪግ ትምህርት ገብተናል፡፡ ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ የባቡር ትራንስፖርት እና መሰረተ ልማት የሚያጠና ዘርፍ ነው፡፡ እኛ የምንማረው “ዲዛይን ኤንድ ኮንስትራክሽን ኦፍ ሬልዌይ” ይባላል። የባቡር መስመር ግንባታና ቅየሳን የሚመለከት ነው፡፡ ጥሩ እና ደስ የሚል አጀማመር ነው፡፡ ትምህርቱን ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ጨርሼ ወደ አገሬ እገባለሁ ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ እየተማርን ያለነው በቀጥታ ወደ አገር ቤት ተመልሶ ለመስራት ነው፡፡ ትምህርቱን ስንጀምር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ውል ፈፅመን ነው፡፡ ሆኖም የሚያዝህ የውል ወረቀት ሳይሆን ህሊናህ ነው፡፡ ተምረህ ስትጨርስ አገርህ ላይ ነው የምትሠራው፡፡ በራሽያ በዘርፉ የምናገኘውን የላቀ ትምህርትና ክህሎት ምንም ባልተሠራባት ኢትዮጵያ፣ መጠቀም መቻል በራሱ የሚያጓጓ ነው፡፡
እስቲ ስለሞስኮ ሜትሮ ንገረን…
አስደናቂው የሞስኮ ባቡር ትራንስፖርት ሜትሮ እ.ኤ.አ በ1935 ሲመሰረት፣ በሁለት ሃዲዶችና በ13 ጣቢያዎች 11 ኪሎ ሜትር ብቻ የሚሸፍን ነበር፡፡ ዛሬ የሞስኮ ሜትሮ 185 ጣቢያዎች፤ ከ12 በላይ ሀዲዶች ያሉት ሲሆን በአጠቃላይ 305.5ሺ ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡ የሜትሮ ሲስተሙ የሞስኮን ከተማ ከአጓራባቾቿ ትንንሽ ከተሞች ክራስኖጎርስክ እና ሬውቶቭ ጋር ያገናኛል፡፡ የሞስኮ ሜትሮ በሰዓት ከ45 በላይ ባቡሮች ይመላለሱበታል፡፡ የጉዞ ፍጥነታቸው በአማካይ 41 ኪሎ ሜትር በሰዓት ነው፡፡ የባቡር አገልግሎቱ በቀን ተሳፋሪዎች ብዛት ከቶኪዮ እና ከሴኦል ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ የሚጠቀስ ሲሆን በቀን እስከ 8 ሚሊዮን ህዝብ ይገለገልበታል። በየ90 ሰከንዱ በየጣቢያው ባቡሮች ማግኘት ይቻላል፡፡ በ28 ሩብል ወይም 1.5 ዶላር በመክፈል፣ የሜትሮውን ባቡሮች በየትኛውም ጣቢያ መሳፈርና ሞስኮን ምድር ለምድር መሽሎክሎክ ይቻላል፡፡
ከመሬት ስር የሚገኙ የባቡር መስመሩ መናሐሪያና መሳፈሪያ ጣቢያዎች በአስተማማኝ የግንባታ ግብዓት በተለያዩ የስነህንፃ ጥበቦች አምረው የተገነቡና እንደሙዚየም ሊታዩ የሚችሉ ናቸው፡፡ እዚህ ሞስኮ ያለው የባቡር ትራንስፖርት መስመር ከተማ ውስጥ አንደር ግራውንድ (በመሬት ስር) የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ የባቡር ጣቢያዎች ከምድር 100 ሜትር ጥልቀት ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ይህ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ የቦታ ርቀትን ቀንሶ በፍጥነት ያደርሳል፡፡ በየቦታውም አይቆምም፡፡ በተለይ በክረምት ወራት በበረዶ የተነሳ ከጉዞ ከመስተጓጐል ያድናቸዋል፡፡ በፀጥታና ደህንነት በኩልም አስተማማኝ ነው፡፡ ከመሬት በላይ ባለው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚፈጠረውን የትራፊክ መጨናነቅም ይቀንሳል፡፡ አጠቃቀሙ በጣም ቀላል ነው፡፡ ሜትሮ በከተማ ውስጥ በመሬት ስር በተዘረጉ መስመሮች የሚያገለግል ይሁን እንጂ ከከተማ ሲወጣ ከመሬት በላይ ነው፡፡
አሁን አንተ ከሴንት ፒተርስበርግ የመጣኸው በባቡር ነው?
በሞስኮ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጓደኞቼን ለመጠየቅ እና በተለያየ ጉዳይ ወደ ከተማዋ ስመጣ ሜትሮን ነው የምጠቀመው፡፡ ከሴንት ፒተርስበርግ ወደ ሞስኮ የመጣሁት በምቹ አገር አቋራጭ ባቡር ተሳፍሬ ነው፡፡ ከሴንት ፒተርስበርግ ሞስኮ የሚያመጡ የተለያዩ አማራጭ የባቡር ትራንስፖርቶች አሉ፡፡ በፍጥነታቸውና በክፍያቸው ይለያያሉ፡፡ 350 ኪ.ሜ በሰዓት በሚከንፈው ፈጣኑ የኤክስፕረስ ባቡር ከሴንት ፒተርስበርግ ሞስኮ ለመድረስ 3 ሰዓት ተኩል የሚፈጅ ሲሆን ክፍያው 7ሺ ሩብል (4ሺ ብር ገደማ) ነው፡፡ ከቸኮልክ ፈጣኑን ባቡር መያዝ ትችላለህ፡፡ ለመዝናናት እና ለሽርሽር ከሆነ ግን በ6 ሰዓት የሚደርሱትን ባቡሮች መጠቀም ይቻላል፡፡ ርካሽ ናቸው፤ 2ሺ ሩብል ቢሆን ነው፡፡
በኢትዮጵያ የባቡር ትራንስፖርት በምኒልክ ዘመን ቢጀመርም አላደገም፡፡ እድገቱ በጣም የዘገየ አይመስልህም?
ይህን ጥያቄ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ብመልስልህ፣ በእርግጠኝነት በጣም ዘግይቷል ነው የምለው፡፡ ለምን ዘገየ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ብዙ ተጽእኖዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ያለፍንባቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚያ ችግሮች በመደራረባቸው የባቡር ትራንስፖርት እድገት በጣም ዘግይቷል፡፡ የባቡር ትራንስፖርት ከአንድ አገር ዕድገት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። በአንድ አገር ውስጥ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች የሲሚንቶ፣ የብረታብረት ፋብሪካዎች የሚንቀሳቀሱ ከሆነ፣ የባቡር ትራንስፖርት ያስፈልጋል፡፡ የእነዚያን ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ዕቃዎች በቀላሉ ለማመላለስ ያግዛል፡፡ በከተማ ውስጥ ያለውን የትራንስፖርት ችግር እና የትራፊክ መጨናነቅም በባቡር ትራንስፖርት መቅረፍ ይቻላል፡፡ ከአዲስ አበባ አዳማ፣ መቀሌ፣ ጅማ፣ አሶሳ ወዘተ … በቀላሉ ለመጓዝ ባቡር የተሻለ ነው፡፡ የባቡር ትራንስፖርት ከተሞችን ከከተሞች በቀላሉ ለማገናኘት ወሳኝ ነው፡፡ የባቡር ትራንስፖርት በዓለም ላይ ካሉት መጓጓዣዎች ሁሉ ተመራጭ ነው፡፡ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዛት ያለው ተሳፋሪ የሚያገለግል ሲሆን ለአደጋ ተጋላጭነቱ በጣም አነስተኛ ነው። ባቡር በተለይ ባደጉት አገራት ሰፊ አገልግሎት እና ጥቅም ይሰጣል፡፡ እንግዲህ በሞስኮ ከተማ የባቡር ትራንስፖርትን ጠቀሜታ እንዳየኸው ነው። የባቡር ትራንስፖርት እንደአየር ትራንስፖርት ብዙ የምትጉላላበትና የምትጨናነቅበት አይደለም። በጣም ቀላል ነው፡፡ ማንም የህብረተሰብ ክፍል በርካሽ ዋጋ ይጠቀምበታል፡፡ ከአደጋ የራቀ መጓጓዣ በመሆኑም አስተማማኝ ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ አንድ ስፍራ ለመሄድ ስትፈልግ ዛሬውኑ ወደ አንዱ ጣቢያ በመሄድ የምትሳፈርበትን ትኬት መቁረጥ ትችላለህ፡፡ የአየር ትኬት ግን ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ በእኛ አገር እንግዲህ ገና የ5ሺ ኪሎ ሜትር የባቡር ትራንስፖርት ለመዘርጋት እቅድ ተይዟል፡፡ ግንባታው በተግባር የተጀመረው በ2ሺ ኪሎ ሜትር ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለባቡር ትራንስፖርት አመቺ ናት ማለት ይቻላል?
የባቡር ትራንስፖርት ሜዳማ እና አስቸጋሪ ያልሆነ መልክዓ ምድር ይጠይቃል፡፡ የኢትዮጵያ መልክአዓ ምድር የባቡር ትራንስፖርት ለማስፋፋት አመቺ አይደለም፤ ፈታኝ ነው፡፡
የሬልዌይ ኢንጂነሪንግ መማር፣ ይህን አስቸጋሪ የመልክዓ ምድር ፈተናዎች ለመለወጥና በዘዴ ለመጠቀም የሚያስችል ዕውቀትን ያስጨብጣል። በእኛ አገር ተራሮች ስትወጣ፣ በውስጥ ለውስጥ ዋሻ ወይንም በድልድይ መሸጋገር ያስፈልግ ይሆናል። እነዚህ የመልክዓ ምድር ሁኔታዎች ከፍተኛ ወጭ ይጠይቃሉ እንጂ ለመስራት ይቻላል፡፡ ተራሮች፣ አስቸጋሪ ስፍራዎች እና ወንዞች ሲያጋጥሙ ዋሻዎች መስራትና ድልድዮችን መገንባት ያስፈልጋል፡፡
በሬልዌይ ኢንጂነሪንግ ዘርፍ አስቀድመው ተምረው እየሰሩ ያሉትና አሁን በመማር ላይ የምንገኘው ኢትዮጵያውያን፣ በአገራችን የባቡር ትራንስፖርትን ለማስፋፋትና ለመገንባት የሚያስችሉ ዕውቀቶችና ክህሎቶችን እየሰበሰብን ነው፡፡ ሁላችንም ተቀናጅተን ብዙም ወጭ የማይጠይቁ የባቡር ትራንስፖርት መሰረተልማቶችን በማቀድ እና በመገንባት ብዙ እንሰራለን ብዬ አስባለሁ፡፡
እስቲ አሁን ደግሞ ስለምትኖርባት ከተማ ፒተርስበርግ ንገረኝ…
ሴንት ፒተርስበርግ ለኑሮ ተመችታኛለች፡፡ ከተማዋ ልዩ ውበት ያላት ፀጥታ የሰፈነባት፣ የራሽያ የባህል መዲና ናት ማለት ይቻላል፡፡ ከተማዋ በታሪካዊ ስነ ህንፃዎች የተከበበች ናት፡፡ በታላቁ የራሽያ ንጉስ ፒተር ዘ ግሬት፣ በኔቫ ወንዝ ላይ ነው የተገነባችው፡፡ ጥንት የተመሠረቱ ትልልቅ ዩኒቨርስቲዎች አሏት፡፡
አሁን እኔ የምማርበት ዩኒቨርስቲ ከተመሠረተ ከ200 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ የከተማዋ ልዩ መገለጫ ከምላቸው ነገሮች በቀዳሚነት የምጠቅሰው “ኤር ሚታዤ” የሚባለውን ዓለም አቀፍ ሙዚየም ነው፡፡
በዓለም ትልቁ ሙዚየም ነው፡፡ ሁሉንም የሙዚየሙን ክፍሎች በደንብ ተዘዋውሬ ልጐበኝ ካልክ 10 ዓመት ይፈጅብሃል፡፡ የኪነጥበብ፣ ቅርፃቅርጽ፣ ታሪካዊ ቁሳቁሶች፣ የየአገሩ… የየራሱ ክፍል ያለው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ክፍል አለ፡፡ በዚህ ክፍል የብራና መጽሐፍት፣ የታሪክ መዛግብት፣ ታሪካዊ ቅርሶችና ቁሳቁሶች፣ የታሪካዊ ቦታዎች ምስሎች ይታያሉ፡፡ ሌላው የሴንት ፒተርስበርግ መገለጫ ወንዞቿ ናቸው፡፡ ራሽያውያን ከተሞቻቸውን በወንዞች ዙሪያ የሚያደርጉት ያለምክንያት አይደለም፡፡ አሁን ለምሳሌ በራሽያ ወንዝ ለትራንስፖርት አገልግሎት ያገለግላል፡፡ በሞቅታ መሬት የአየር ንብረቱን ለማቀዝቀዝ ይጠቅማል፡፡
ከወጣቱ ትውልድ ምን ይጠበቃል ትላለህ?
በግሌ የማስበው ምን መሰለህ? በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ጥሩ የሚባሉ ነገሮች እየታዩ ናቸው፡፡ በአንፃሩ ትውልዱን ወደ መጥፎ አዝማሚያ የሚወስዱ ነገሮችን እየተመለከትኩ ነው፡፡ አሁን ያለው ትውልድ በብዙ ነገሮች አንድ ሆኖ፣ በብዙ ነገሮች ደግሞ የሚለያይበት ሁኔታ ይታያል፡፡ እኔ በበኩሌ ሰዎች በመረጃ ላይ የተመረኮዘ እውቀት እንዲያዳብሩ ነው የምመርጠው፡፡ አሁን ጊዜው በምትፈልገው መስክ በርካታ መረጃዎችን በቀላሉ የምታገኝበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የምታገኛቸውን ሁሉንም መረጃዎች በተገቢው መልኩ ተርጉመህና አውቀህ በራስህ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ላይ መድረስና መጠቀም አለብህ፡፡ ትውልዱ ከአሉባልታ፣ እና በዕውቀት ባልዳበረ መረጃ መነሳት የለበትም፡፡ ስራ ሲሰራ፣ ማነው የሚሰራው ሳይሆን ምንድነው እየተሰራ ያለው ብሎ መደገፍና የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል፡፡ ያንድ ትውልድ ድርሻ የራሱን ታሪክ ሰርቶ ማለፍ ነው፡፡ ለአገሪቷ የሚጠቅማት የሚሰራውን እያየህ መደገፍ፤ የማይሰራውን ደግሞ ያለውን ክፍተት በችሎታህና በእውቀትህ እየሰራህ መሙላት ነው፡፡ በአጠቃላይ ይህ ትውልድ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት መጣር አለበት፡፡ በዕውቀት እና በግንዛቤ ላይ የተመሰረተ ስራ ለአገሩ የሚያከናውን መሆን ይገባዋል፡፡

ለእኔ 2005 ዓ.ም በአጠቃላይ ሲታይ መጥፎ አመት አልነበረም፡፡ ያሰብኩትን ያህል ባልሄድም ያቀድኳቸውን ነገሮች ከሞላ ጐደል ሳላሳካቸው አልቀረሁም፡፡ በቴፒና በሚዛን መካከል በሚገኝ ማሻ በተባለ ቦታ ላይ የቡና እርሻ ለመጀመርና ሁለት መቶ ሄክታር ቡና ለመትከል አቅደን ነበር፤ እሱን አሳክተናል፡፡ ሁለተኛው ስኬት የሻሸመኔው ሆቴሌ መጠናቀቅ ነው፡፡ ሆቴሉ “ኢ-ላይት” ይባላል፡፡ በ“ማራቶን ሞተር” ድርጅታችን በኩልም ውጤታማ ነበርን፡፡ “በሀይሌ አለም ሪል ስቴት” አማካኝነት ባለፈው አመት ያቀድነውን በርካታ ቤቶች ገንብተናል፡፡ ቤቶቹ ሀያት አካባቢ የሚገኙ ናቸው፡፡ በሀይሌ አለም ኢንተርናሽናል ቢሯችን በኩል ግን እንሰራለን ብለን ያልሰራናቸው ነገሮች አሉ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ያልተሳኩ ማለት ነው፡፡ ለስራው አለመሳካት እንደ እንቅፋት የሆነብን የውጭ ምንዛሬ ችግሮች ነበሩ፡፡ ያው ነጋዴ ስትሆኚ አንዴ ከፍ፣ አንዴ ዝቅ ማለት ያጋጥማል፡፡ አንድ ሚሊዮን አተርፋለሁ ብለሽ ግማሽ ሚሊዮን የምታተርፊ ከሆነ ከእቅድ በታች ነው ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ሀይሌ አለም ኢንተርናሽናል በ2005 ዓ.ም ከ2004 ዓ.ም ብዙ የተለየ እንቅስቃሴ አላሳየም ማለት ይቻላል፡፡
በ2006 ብዙ ነገሮች አቅጃለሁ፡፡ ዋናው ግን በማዕድን ፍለጋ ዘርፍ ልሰማራ ነው፡፡ ትልቁ እቅዴም እርሱ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የጀመርኳቸው ሂደቶችም አሉ፡፡ በቡና እርሻው በኩል በዚህ አዲስ አመት ሶስት መቶ ሄክታር ቡና ለመትከል እቅድ አለን፡፡ ይሄ ሁለተኛው እቅድ ነው። ሶስተኛው እቅድ በ2005 ከገነባናቸው ሪል እስቴቶች በተጨማሪ በአዲሱ ዓመት ከ55-60 አፓርትመንቶችን ለመገንባት አቅደናል፡፡ በሪል እስቴቱ በኩል አጠቃላይ ልንገነባ ያቀድነው ወደ 220 አፓርትመንቶችን ነው፤ አብዛኞቹ በ2005 ዓ.ም ተገንብተዋል፡፡ እንግዲህ እነዚህ ዋና ዋናዎቹ እቅዶች ናቸው፡፡ ሌሎቹ ጥቃቅኖቹ ደግሞ ይቀጥላሉ፡፡ በተረፈ በቤተሰብ፣ በጤናና በመሳሰሉት አመቱ ጥሩ ነበር፡፡
2006 ዓ.ም የምናቅድበት ብቻ ሳይሆን ያቀድነውን የምንከውንበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ ምክንያቱም አንድ አመት ጥሩ ነው የሚባለው የምንፈልገውንና የምናቅደውን ስናሳካበት ነው፡፡ አመቱ የጤና፣ የሰላምና የብልፅግና እንዲሆን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እመኛለሁ፡፡ መልካም አዲስ አመት፡፡

Friday, 13 September 2013 12:51

አጭር ልብወለድ

       ዛክሃር ኩዝሚች ድያድችኪን በመኖሪያ ቤቱ ድግስ አዘጋጀ። የአዲሱን ዓመት መግቢያ ለመቀበልና... የውድ ባለቤቱን የወ/ሮ ማላንያ ቲኮኖቭናን የልደት ቀን ለማዘከር፡፡
የደጋሹን ክብር የሚመጥኑና የተከበሩ የከተማይቱ ታዋቂ ሰዎች በእንግድነት ተሰብስበዋል። የሁሉም ፊት ብሩህ ገጽታ ይነበብበታል፡፡ ለመደሰት ያቆበቆቡ እንግዶች በተለያየ የአለባበስ ስልትና በማራኪ ፈገግታ አዲሱን ዓመት ለመቀበል አሰፍስፈዋል ማለት ይቀላል፡፡ ከነዚህ ሁሉ መሃል አዳፋ ጨርቅ በለበሰው አግዳሚ ላይ ፈንጠር ብለው የመሬት ከበርቴው ጉሴቭና የሱቅ ጠባቂው ራዝማካሎቭ ተቀምጠዋል፡፡ ድግሱን ያዘጋጀው ቤተሰብ፤ አስፈላጊዎቹን ነገሮች የተበደረው ከነዚህ ሰዎች መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ሆኗል፡፡ ሁለቱ አበዳሪዎች ስለደጋሾቹ ልጆችና (ልጃገረዶች)፣ ስለለበሱት ቀሚስና ስለመሣሠሉት ወግ ይዘዋል፡፡
“በአሁኑ ጊዜ የማይጠጣና ጠንካራ ሠራተኛ የሆነ ሰው ማግኘት እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው... ቢገኝም ከስንት አንድ!” አለኝ፤ የመሬት ከበርቴው ጉሴቭ፡፡
“ቤቱ ይቁጠረው እንጂ ክቡር ሆይ ይኸ በምን ሊታወቅ ይችላል? በየቤቱ ያለው የሥርዓት አጠባበቅና የትዕዛዝ አሰጣጥ... ይወስነዋል” አለ ሱቅ ጠባቂው፡፡ “በእያንዳንዱ ቤት የሥነ ሥርዓት መጓደል ተዳምሮ በሁሉም ቤት ከተከናወነ ዓለማችን የሥርዓት አልበኞች መተራመሻ መሆኗ እሙን ነው። ” መልስ ሰጠ፤ የመሬት ከበርቴው
ከፊት ለፊት ሦስት በዕድሜያቸው ጠና ያሉ ሴቶች፣ የሁለቱን ሰዎች የአንደበት እንቅስቃሴ በአድናቆት እያዩ መሆኑን ሁኔታቸው ይናገራል። የደጋሾቹ አጎት አቶ ጉሪ ማርኮቪች፣ ግድግዳ ላይ የሚሰቀሉትን የቅዱሳን ሥዕሎች ያስተካክላሉ። ውስጥ ባሉት ክፍሎች ልጃገረዶችና ሌሎች እንግዶች በእያንዳንዱ ኮፔክ ውርርድ ልዩ ልዩ ጨዋታ እያደረጉ ሲያውካኩ ደምፃቸው ይሰማል፡፡ ከመወራረጃው ጠረጴዛ አጠገብ የሰባት ዓመቱ ህፃን ኮልያ ካላጫወታችሁኝ በማለት ያለቅሳል፡፡ ከጉዳይ የጣፈው አልነበረም፡፡ ወይ ሣንቲም የለው? ወይንም ትልቅ ሰው አይደለም!
“ውጣ ከዚህ! አትነጫነጭብን... ዋ! እናትህ የሰማች እንደሆን” ያም ያቺም አመናጨቁት፡፡
“ማነው የሚያለቅሰው!?... ኮልያ የት ነህ?” የእናቱ ድምፅ ከወደ ማድቤት በኩል ተሰማ፡፡ “ማነሽ ባርባራ!... ዛሬ ሥራ በዝቶብኝ ስላላቀመስኩት ነው... ጆሮውን ለምዝጊልኝ” አለች፡፡
ከማረፊያ ክፍሉ የእንግዶች መኝታ ላይ ውሃ አረንጓዴ ቀሚስ የለበሱ ሁለት ልጃገረዶች ተቀምጠዋል፡፡ የተቀቡት ሽቶ መዓዛ አካባቢውን አውዶታል፡፡ ከፊት ለፊታቸው የኢንሹራንስ ኩባንያ ሠራተኛውና የ23 ዓመቱ ወጣት ኮፓይስኪ ‘እዩኝ እዩኝ’ የማለት አዝማሚያ ይታይበታል፡፡
“ሴቶች በወንዶች አዕምሮ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ቢሆኑም፣ የሰውን ማንነት ዝቅ በማድረግ በኩል የሰይጣን ድርሻ አላቸው፡፡ ስለዚህም ትዳር ለመያዝ አስቤም አላውቅ...” ልጆቹን እያወናጨፈና እየተውረገረገ ጉራውን ነፋ፡፡
“ሰፍሳፋና ያልታረመ ምላስ ያለው ወንድ፣ ምንም ቢል የሚያፈቅረው አያገኝም፡፡” መልስ ተሰጠው በአንዷ ሴት፡፡
“የምለው አልገባችሁም ማለት ነው፡፡ ሁሉንም ሴቶች ማለቴ አይደለም’ኮ... “ጉረኛው፡፡
የሰማው አልነበረም፡፡ ሰዎች ይወጣሉ ይገባሉ፡፡ የቤቱ ባለቤትና የድግሱ አዘጋጅ ዛክሃር ኩዝሚችና የበኩር ልጁ ግሪሻ ካንዱ ጥግ ወደ አንዱ ጥግ እየተወናጨፉ ሥነ ሥርዓቱን ለማድመቅ መጣጣራቸው ይታያል፡፡
አባትዬው ወደ ማድቤት ሲሮጥ፤ ልጁ በበኩሉ ወደ ሳሎን በመጣደፍ የበዓል ስሜት እንዲፈጠር በማለት ግርግሩን ያጋግሙታል፡፡ እናቲቱ የማድ ቤቱን ትርምስ እያጋፈረች መሆኑን ከወገብ በላይ በሚታየው እንቅስቃሴዋ መገመት ይቻላል፡፡
“ሜሊና” በማለት ተጣራ ባል፤ የልጁን እናት። “እንግዶቻችን በንቃት እየጠበቁሽ ነው... ፈጠን ፈጠን በይ... በምግብ ጉምጅት ምራቃቸውን እየዋጡ ነው”
“ኡፍ! አታጣድፈኝ... እኔ ስንቱን እሆናለሁ?... አይዟችሁ እየደረሰ ነው በልልኝ፤ ትንሽ ነው የሚቀረኝ... ካሁኑ መብላት የተጀመረ እንደሆነ የአዲሱ ዓመት መግቢያ - እኩለ ሌሊት ሲደርስ ምን ላቀርብ ነው? እስከዚያ ሰዓት ብትታገሱ ምናለ... ሂድ ውጣልኝ...”
“ሜሊና ለመክሰስ ያህል ጥቂት ነገር ነው’ኮ ያልኩሽ... እንጂ ያለው ሁሉ ይቅረብ አላልኩም’ኮ...”
“ውጣ ባክህ... ሂድ እንግዶቹን አይዟችሁ እየደረሰ ነው እያልክ አባብልልኝ... ውጣ! ኩሽናው የሴት ነው”
በፀጥታ አትኩሮ ሲያያት ከቆየ በኋላ ምንም ሳይናገር ወደ እልፍኝ ተመለሰና መሃል ላይ ቆሞ፣ የግድግዳውን ሰዓት ተመለከተ፡፡ አምስት ሰዓት ከዜሮ ስምንት ደቂቃ ይላል፡፡ ሚስቱ እንደምትለው ከሆነ፣ ምግብና መጠጡን ለመጀመር ሃምሣ ሁለት ደቂቃዎች ይቀራሉ፡፡ ሰው ለመብላትና ለመጠጣት ህዋሳቶቹ ከተነሳሱ በኋላ፣ ይህን ያህል ደቂቃ መጠበቅ ምን ማለት እንደሆነ የደረሰበት ብቻ ያውቃል፡፡ ለመጠጣት አዕምሮ ተነሳስቶ አምስት ደቂቃ ከመጠበቅ ይልቅ እየበረደህ በባቡር ላይ 5 ሰዓት መቆየት ይመረጣል፡፡
ደጋሻችን ሰዓቱን መልሶ መላልሶ አትኩሮ ካየው በኋላ ራመድ ራመድ አለና የሰዓቱን መዘውር ከነካ በኋላ ደቂቃ ቆጣሪውን አምስት ደቂቃ ወደፊት ጨመረለት፡፡ ትልቁ ልጃቸው ግሪሻ ተራውን በእንግዶች መሰልቸት ስሜቱ ስለተነካ፣ ባይሆን መጠጥ እንኳን ላምጣላቸው በማለት ኩሽና ደረሰ፡፡
“እማዬ ኧረ በማምላክ እንግዶቹ በሙሉ እያፋሸጉ ነው፡፡ በረሃብ ጨረስናቸው’ኮ... ባይሆን ለቅምሻ ያህል... አፋቸው እንዲያረጥቡ እንኳን...”
“አንተ ደግሞ እያወቅኸው ግሪሻዬ... በቃ እያደረስኩ ነው... ሂድ ሣሎን... ኩሽናውን ለኔ ተውልኝ” አለች እናቱ፡፡
ግሪሻም ሣሎን ደረሰና ለመቶኛ ጊዜ ሰዓቱን አተኩሮ ማየት ጀመረ፡፡ ንቅንቅ ያለም አልመሰለው። የደቂቃ ቆጣሪው ጭካኔ ያለቅጥ ገረመው፡፡
“ይኸ ቀርፋፋ!” አለ ለራሱ ደቂቃ ቆጣሪውን ነጥሎ እየተመለከተ... ራመድ! ራመድ! አለና አጠገቡ ደረሰ፡፡ ሰባት ደቂቃ በመጨመር ጊዜውን አፈጠነው። በዘለዓለማዊነት ላይ ፈረደ ማለት ይቀላል፡፡
ህፃኑ ኮልያ ሲሮጥ መጣና ከሰዓቱ ፊት ለፊት ቆሞ በማንጋጠጥ ሰኮንዶቹን አ-ን-ድ ሁለት... ሦ...ስ..ት እያለ መቁጠር ጀመረ፡፡ በጭራሽ ጊዜው የሚነቃነቅ አልመስለው አለ፡፡
በሁካታው መሃል እየተሽሎከሎከ ግድግዳው ጥግ ወንበር ላይ ቆመና እሱም ከጊዜ ህግ ውጪ አምስት ደቂቃ በመስረቅ የፍላጎቱን ያህል አፈጠነ፡፡
ጉረኛው የኢንሹራንስ ሠራተኛ “በአዲስ ዓመት ዋዜማ ደስታን ማግኘት ሲገባን በረሃብ ሊጨርሱን ነው’ንዴ?” በማለት ድምፁን ከፍ አድርጎ ደጋሾቹን አሣለቃና ‘ይቅርታ’ ‘ይቅርታ’ እያለ ሰዓቱ አጠገብ ደረሰና እሱም የድርሻውን ለደቂቃ ቆጣሪው ዘንግ አምስት ደቂቃ ጨመረለት፡፡
ደጋሹ አባወራ ሁለት ብርጭቆ የግዜር ውሃ ጠጥቶ ምላሱን ካራሰ በኋላ፤ ሁለት እጆቹን ወደ ኋላ አቆላልፎ ከጥግ ወደ ጥግ ሲንጎራደድ ቆየ፡፡ ሚስቲቱም መንጎራደዱን ትቶ ወደ ሣሎን ወጥቶ እንግዶችን እንዲያግባባ በግሣፄ መልክ ነገረችው። በዚህን ሰዓት የምግቡ ሽታና የቮድካው ሥዕለ ገፅታ ዓይኑ ሥር እየደነሱ ተስፋ አስቆረጡት፡፡ ወደ ሣሎን ደረሰና ሰዓቱን ሲመለከት የዓለም መጨረሻ የደረሰ መሠለው፡፡ ተንደረደረና የደቂቃ ቆጣሪውን ዘንግ የበላ የጠጣውን ያህል አሽከርክሮ፣ አዲሱ ዓመት ሊጀመር አሥራ አንድ ደቂቃ ቀሪ መሆኑን እንዲያውጅለት አደረገ፡፡
አባትና የበኩር ልጁ ግሪሻ፣ ጠረጴዛዎቹ ላይ በልባቸው የተደፉትን ሣህኖች እየገለበጡ፣ ብርጭቆዎችንም በፍጥነት ለመቅዳት ምቹ እንዲሆኑ በማደራጀትና... እየተሯሯጡ በማዘገጃጀት የዕድምተኛውን ስሜት አነቃቁት፡፡ እና ፊቱን ወደኩሽና መልሶ፤
“ሜሊና!” በማለት በከፍተኛ ድምፅ ተጣራ፡፡ አባወራው “ሜሊና እነሆ አዲሱ ዓመት ደረሰ - ሰዓቱ ሊደውል ነው” አለ፡፡
የባሏን ማንባረቅ የሰማችው ሜሊና፤ ከኩሽና ተወርውራ በመውጣት የታወጀውን ለማረጋገጥ የግድግድውን ሰዓት ብትመለከት እውነትም ሰዓቱ ደርሷል፡፡
“ምን አባቴ ይሻለኛል? ሾርባው አልተዋኻደልኝም፡፡ ጥራጥሬዎቹም ቢሆኑ አንድ ሃያ ደቂቃ እሳት ካልመታቸው አይታኘኩም፡፡ ምን አባቴን ላድርግ? - እንዴት ጥሬ ነገር ዝም ብዬ ላቅርብላቸው?” በማለት ለራሷ ስታጉተመትም ከቆየች በኋላ፤ በግርግሩ መሃል ተሽሎኩልካ ወደ ሰዓቱ ተጠጋችና፣ የደቂቃውን ዘንግ በፍጥነት ሃያ ደቂቃ ወደ ኋላ በመጠምዘዝ ጊዜውን ወደ አሮጌው ዓመት መልሳ ወደ ኩሽና ተመለሰች፡፡ “ሃያ ደቂቃ መጠበቅ አያቅታቸው” እያንሾካሾከች ፈገግ አለች፡፡

Published in ልብ-ወለድ

ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን (የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ፕሬዚዳንት)

በ2005 ዓ.ም በግል ህይወቴ ትልቁ ፈተና የነበረው የእናቴ መታመም ነው፡፡ ህመሟ ከባድ ነበር፤ አሁን ግን ተሽሏታል፡፡ በስራ ቦታ ባሉ እንቅስቃሴዎች እንቅፋት የሚሆንብሽ ብዙ ነገር አለ፡፡ የአገር ስራ ስትሰሪ ለግልሽ የምትሰሪ ይመስል በተሳሳተ ግንዛቤ እንቅፋት የሚፈጥሩብሽ ሰዎች ያጋጥሙሻል፡፡ ደግነቱ ጉዳዩን ሲረዱ መመለሳቸው ነው፡፡ እንዲህ አይነት ፈተናዎች የተለመዱ ናቸው፤ ግን በጥሩ ሁኔታ ተወጥቶ መፍታቱ ጥሩ ነው፡፡ በንግድ ምክር ቤቱ ከገጠሙኝ ፈተናዎች ውስጥ እኔ ፕሬዚዳንት ሆኜ ስመጣ ብዙ ማህበራት ተጣልተው ስለነበረ እነሱን ማስማማት አንዱ ነበር፤ ምክንያቱም በሰላማዊ የስራ ድባብ ውስጥ ካልተሰራ የትም አይደረስምና፡፡ በኋላ ግን ሁሉንም በማስታረቅ ተወጥቼዋለሁ፡፡ ይህ እንደስኬት የምቆጥረው ነው፡፡
ሌላው ስነ-ምግባር ያለው የንግድ ማህበረሰብ እንዲፈጠር እዚህም ሆነ በክልል በብዛት እየተንቀሳቀስን ስለሆነ ይህም ስኬት ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ስነ-ምግባር ያለው የንግድ ማህበረሰብ ለማፍራት የተጀመረው ጥረት በራሱ ጥሩ ነው፡፡
በግሌ ብዙ ያቀድኳቸው ነገሮች አሉ፤ የተጀመሩና መጠናቀቅ ያለባቸው፡፡ ከንግድ ም/ቤቱ እቅድ ደግሞ የመጪውን የአምስት አመት ስትራቴጂ እቅድ በዚህ ሳምንት አፅድቀናል፡፡ በመጭው አምስት አመት እኛም ብንቀጥል ሌሎችም ቢተኩ የሚሰራው ሰው አቅጣጫ ይዞ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችል ነው፡፡ ሌሎችንም የንግድ ምክር ቤት አደረጃጀትና ቻምበር ሲስተሙን አስመልክቶ እንደዚሁ ያፀደቅናቸው ነገሮች አሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ትልቁ ስኬታችን ቻምበር አካዳሚ ማቋቋማችን ነው፡፡ በየጊዜው በድንገት ተመርጠው ስልጣን ላይ የሚቀመጡ የም/ቤቱ ሀላፊዎችም ሆኑ ማህበራት ስለ አስተዳደር እና ስለ ጉዳዩ ሳያውቁ ስራው ላይ ይጋፈጣሉ፡፡ የቻሉትን ያህል ሲሰሩ ስህተት ነው ተብለው ይተቻሉ። ጥሩም ቢሰሩ ጥሩ ስራቸው በአንዳንድ ስህተት ይሸፈንባቸዋል፡፡ ይህንን ለመቅረፍ ቻምበር አካዳሚ ወይም “ኢንተርፕረነርሺፕ፣ ሊደርሺፕ ኤንድ ማኔጅመንት” ማዕከል አቋቁመናል፡፡ ይህ ማዕከል ወደፊት በአለም አቀፍ ደረጃ ነው የሚሰራው። ለጊዜው ግን “ቻምበር አካዳሚ” ብለነዋል፡፡ በአጠቃላይ ይህን ይመስላል፤ ችግሮችም ስኬቶችም አሉ፡፡ አብዛኛውን ፈተና ግን በድል ተወጥተናል፡፡
በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያም ሆነ ለአለም ህዝብ የምመኘው ከስስት ተላቀን ሁሉንም ሰው በፍቅር እንድናገለግል ነው፡፡ በራሳችን ሊደረግ የማንፈልገውን በሌሎች ላይ ባለማድረግ፣ ለራሳችን የምንፈልገውን መልካም ነገር ለሌሎችም በማድረግ፣ ይህች አለም በሰላምና በፍቅር የተሞላች ትሆን ዘንድ እንድንጥር እመኛለሁ፡፡ አለምን ለመቀየር ስናስብ ራሳችንን ለመቀየር እንሞክር እላለሁ፡፡ ከፈለግን ደግሞ እንችላለን፡፡ አዲሱ አመት የጤና፣ የሰላም፣ የፀጋና ያሰብነውን የምናሳካበት እንዲሆን ምኞቴ ነው፡፡

Friday, 13 September 2013 12:49

እንቁጣጣሽ

ልጅ እያለሁ እንቁጣጣሽን የሚያህል ደስ የሚለኝ በዓል አልነበረም፡፡ የአበባ ስዕል መሳል አልወድም። የማልወደው ግን ስዕል መሳል ስለማልችል ብቻ ነው፡፡ እቤታችን ሌሎች ልጆች የሚያመጡአቸውን ስዕሎች ወስጄ እንድሸጥ ስለሚፈቀድልኝ ባለመሳሌ ብዙም አልቆጭም፡፡ በዚህ በልጅነት ህይወት ውስጥ ከሌሎች ጐልተው ትዝ የሚሉኝ፣ አክስቴ እና ክርስትና አባቴ ናቸው፡፡
አክስቴ ስዕል ማማረጥ ትወዳለች፡፡ እኔ ባልሳልኩት ስዕል ሁልጊዜ ማብራሪያ ስለምትጠይቀኝ በጣም እናደድ ነበር፡፡
“አክስቴ እንኳን አደረሰሽ!”
“እንኳን አደረሰህ! ጐሽ አምጣው እስቲ”
እሰጣታለሁ፤ ትኩር ብላ ታየዋለች፡፡
“ሰይጣኑን ስለህ ቅዱስ መልዓኩን ያልሳልከው ለምንድነው?”
“እሱ እኮ ሰይጣን አይደለም ብሩስሊ ነው፡፡”
“ማነው ብሩስሊ?”
“ካራቲስት ነው፤ ካራቴ የሚችል፡፡”
“እግሩን እዚህና እዚያ የከፈተው ታዲያ ምን ሆኖ ነው?”
“ወደ ላይ ዘሎ ሌቦቹን ሲማታ ለማሳየት ነዋ። አይታዩሽም እንዴ ሌቦቹ ተመተው ሲወድቁ?” በጣም እየተናደደች፣ “ይሄን ወደዛ ውሰድልኝ! የመልዓክ ስዕል ካለህ አምጣ!” ትለኛለች
“እሺ እንቺ” ሌላ ስዕል እሰጣታለሁ፡፡
“ይሄ ነው መልዓክ? አንተ እርኩስ! ይሄ ነው? ግራና ቀኝ ወገቡ ላይ የኮባ ቅጠል የበቀለበት አስመስለህ ሰርተህ መልዓክ ትለኛለህ?... ዓይኖቹንስ እንዲህ አድበልብለህ ያፈጠጥከው ምን አድርጐህ ነው አንተ?”
አክስቴ እንቁጣጣሽ በመጣ ቁጥር እንደተጨቃጨቀች ነው፡፡ ደስ የምትለኝ ግን እንዲህ ተጨቃጭቃም እንኳን አንዱን ስዕል ከወሰደች በኋላ የምትሰጠኝ ድፍን አንድ ብር ነው፡፡
ክርስትና አባቴ ደግሞ እንደ አክስቴ ስዕል የሚያማርጥ ሰው አይደለም፡፡ ቢሆንም ግን ገንዘብ የማይወጣው ቆጥቋጣ አይነት ስለሆነ፤ ከእርሱ ሳንቲም ተቀብሎ ለመሄድ የሚገጥመኝ ፈተና ቀላል አልነበረም፡፡
“ጌታሁን!”
“አቤት”
“እንኳን ለቅዱስ ዮሐንስ በዓል አደረሰህ፤ ና እስኪ ሳመኝ”
“እሺ” አበባውን ይዤ ወደ እርሱ እቀርባለሁ፡፡
ቀረብ ስል ጉንጬን በሁለት እጆቹ ይዞ አገላብጦ ይስመኛል፡፡ ልቤ “ስንት ሳንቲም ይሰጠኝ ይሆን?” በሚል ጥያቄ ስለሚያዝ የሚስመኝን ጉንጬን እንኳ አስተካክዬ አልሰጠውም፡፡
“ማነሽ ጌጤ …” ስሞኝ ሲጨርስ ትልቋን ልጅ ይጣራል፡፡
“አቤት”
“ለጌታሁን እስቲ ዳቦ ስጪው”
“እሺ”
ዳቦ በሰሀን ይዛ መጥታ ትሰጠኛለች፡፡ ቶሎ ሣንቲሜን ተቀብዬ ለመሄድ ትንሷን ዳቦ መርጬ ሳነሳ “እንዴ! ምነው አንተ! ያባትህ ቤት እኮ ነው፤ ጌጤ፤ ተለቅ ያለውን ዳቦ ጨምሪለት” ይላል፡፡ ጌጤ ትመጣና ትልቁን ዳቦ ያለአቅሜ ታሸክመኛለች፡፡ በቃ መከራዬ የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡ ዳቦውን ካልጨረስኩ ሳንቲሙ አይሰጠኝም፡፡ ሳንቲሙ ካልተሰጠኝ ደግሞ አልሄድም፡፡ ቶሎ ካልሄድኩ ደግሞ ሌሎች ዘመዶቼ ቤት ለመሄድ ይረፍድብኛል።
ዳቦውን ቶሎ ለመጨረስ ስጣደፍ ካየ፣ “ጌጤ ርቦታል መሰል ጨምሪለት!” ይላል፡፡ በጣም እናደድና፣ “በቃኝ! ኧረ በቃኝ!” እላለሁ፤ አፌ ላይ ያለውን ዳቦ በቅጡ ሳልጨርስ፡፡ ጌጤ እግዜር ይስጣትና ፍላጐቴ ገብቷት ምልስ ትላለች፡፡
ዳቦውን ጨርሼ፣ ላመጣሁት ስዕል ሳንቲም ሰጥቶኝ ምናለ ቶሎ በሄድኩ እያልኩ ስቁነጠነጥ፣
“አባትህ ደህና ነው?” ይለኛል፡፡
“ደህና ነው፡፡” እየተናደድኩ እመልሳለሁ፡፡
“እናትህስ ተሻላት?”
“አዎ! ተሽሏታል፡፡ መድኃኒት እየዋጠች ነው፡፡” ሌሎች ዘመዶቼ ጋር መሄድ አለብኛና ስናገር ፈጠን ብዬ ነው፡፡
“ወንድምህ ትምህርቱን ጨርሶ መጣ?”
“አዎ! መጥቶ ነገ ተመልሶ ይሄዳል፡፡ የሚቀጥለው ዓመት ትምህርቱን ይጨርሳል” ስመልስ ለጠየቀኝ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ለሚጠይቀኝም ጭምር ነው፡፡
ጥያቄውን ምነው በጨረሰ እያልኩ በሆዴ ስፀልይ፣
“ለመሆኑ ስንተኛ ክፍል ደረስክ?” ይለኛል፡፡
“አምስት” ድምፄ መቸኮሌን ይናገር ነበር፡፡ እርሱ ግን ግድ የለውም፡፡
“ጐብዘሃልና ለመሆኑ ለምንድነው እየመጣህ የማትጠይቀኝ?”
“እ?”
“እኔ አባትህ አይደለሁም? ዘመድ አይጠየቅም?”
ዝም፤ ዳቦዬን በፍጥነት እያላመጥኩ፡፡
“እኔ አንተን ከጌጤ ከትንሷ ልጄ ነጥዬ አያለሁ ወይ? ከወንዱ ልጄስ አሳንሼ የማይህ ይመስልሃል?”
ዝም፤ መጨረሻውን በመናፈቅ፡፡
“‘አባቴ አምስተኛ ክፍል ደርሻለሁ፤ ደብተር መግዣ ቸገረኝ፣ እስኪብርቶ ግዛልኝ’ ብትለኝ እንቢ እላለሁ”
በሆዴ እያጉረመረምኩ ፀጥ፡፡
“ሰማህ ወይ?”
“አቤት”
“ላንተ ለልጄ የሚሆን ሳንቲም የማጣ ይመስልሃል?”
የተሰጠኝን ዳቦ ጨርሼ፣ እጁን ወደ ኪሱ የሚከትበትን ሰዓት በመናፈቅ ዓይኔን እያቁለጨለጭኩ ነው፡፡
“እኔ አባትህ ቀላል ሰው አታድርገኝ! እ! ይመስገነው፤ ላንተ ለልጄ የሚሆን ገንዘብ የማጣ አይደለሁም፡፡”
በመከራ እጁን ወደ ኪሱ ከተተ፡፡ ሳንቲም ሰጥቶ ሊሸኘኝ ነውና ደስ አለኝ፡፡ ድንገት እጁን ሰብሰብ አድርጐ፤
“ኧረ ለመሆኑ ያቺ እህትህ ከቤት እንደወጣች ቀረች ወይስ ተመለሰች?”
“መጥታለች፡፡ አጐቴ ነው ይዟት የመጣው፡፡”
“ጐሽ!”
“እሰይ! ጥያቄውን ጨረሰ” ብዬ በረጅሙ ስተነፍስ፣
“እንዴ! እንዴ! ያ አጐትህ እንዲህ የጠፋው በደህና ነው?”
“እ?”
“ያ አጐትህ እንዲህ የጠፋው በሰላም ነወይ?”
ማን ይሙት ያጐቴን አጠፋፍ እኔ በምን አውቃለሁ? አጐቴ ትልቅ፤ ያውም ያባቴ ታላቅ፡፡ እኔ ደግሞ...
“ሁልጊዜ እየመጣ ይጠይቃችኋል?”
“አልፎ አልፎ”
“ይገርማል! ምናለ እኔንስ ብቅ እያለ ቢጠይቀኝ እ...”
“የመጣሁበትን እረሳው እንዴ?” እያልኩ በሆዴ ሳጉተመትም፣ እጁን በድጋሚ ኪሱ ከተተ፡፡ አሁንም ደስ አለኝ፡፡ ሳንቲሞች ተቃጨሉ፡፡ እንዴ ይሄን ያህል አስለፍልፎ ዝርዝር ሳንቲም ብቻ ሊሰጠኝ ነው እንዴ? ተነጫነጭኩ፡፡ ሳንቲሞቹን አወጣቸው፡፡ አይኔ ከእጆቹ ጋር አብረው ተንከራተቱ፡፡
አዎ! እጁ ላይ ድፍን ስሙኒና ድፍን ሃምሳ ሳንቲም ይታዩኛል፡፡
“ማነሽ ጌጤ!”
ደግሞ ምን ሊል ነው፡፡ “እንዴ ዳቦ በቃኝ! አሁንስ ዳቦ በቃኝ! ወሬም በቃኝ! እንዴ ሌላ ቦታ የማልሄድ አደረገኝ እንዴ? ዘመዴ እሱ ብቻ የሆነ መሰለው እንዴ?” ንጭንጩ ለሌላ ሰው ባይሰማም ለሚመለከተኝ ሰው ያስታውቅብኝ ነበር፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው? ክርስትና አባቴ እንደሆነ ምንም ሊገባው አልቻለም፡፡
“ጌጤ!”
“አቤት”
“ያንን ኮፖርት አቀብ’ኝ”
እፎይ አልኩ፡፡ የጌጤ መጠራት ለዳቦ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ለኔ ብር ለመስጠት ታስቦ ጭምር በመሆኑ ተደሰትኩ፡፡ ጌጤ ካፖርት አምጥታ ሰጠችው፡፡ ወዲያው የክርስትና አባቴ እጆች በየካፖርቱ ኪሶች ውስጥ መንከራተታቸውን ተያያዙት፡፡
“እዚህ ውስጥ ዝርዝር ሳንቲም አልነበረኝም እንዴ ጌጤ?”
“እኔ እንጃ ፈልገዋ”
እንደተባለው ፈለገ፡፡ የሆኑ ሳንቲሞች አገኘ፡፡ ያሰብኩት ድፍን ብር ባይሰጠኝም፣ ከሱሪው ኪስ ውስጥ ከተገኘው ሰባ አምስት ሳንቲም ጋር አብሮ ከሰጠኝ ያው ነው ብዬ ተዝናናሁ፡፡
የሆነው ግን ይህ አልነበረም፡፡
“ና ጌታሁን” አለኝ በኩራት ብዙ ብር እንደሚያሸክመኝ ሁሉ፤ ሄድኩ፡፡
“ዝርዝር ሳንቲም አጥቼ አቆየሁህ አይደል!?”
“ኧረ ችግር የለም”
“በል ይቺን ያዝ ይኸውልህ፡፡ ስዕሉን ሌላ ቦታ ወስደህ ስትሸጠው ብዙ ሳንቲም ይሆንልሃል እሺ ያዝ!” አዘንኩ፡፡ በጣም አዘንኩ፡፡ ክርስትና አባቴ የሰጠኝ አስራ አምስት ሳንቲም ብቻ ነበር፡፡ ሃምሳ ሳንቲም ላለመስጠት፤ ሃምሳው ይቅርብኝ፤ ስሙኒ ላለመስጠት ካፖርታ አስመጥቶ እንደዛ መልፋቱ አበሳጨኝ፡፡ ከእጁ ላይ የመመንጨቅ ያህል ተቀብዬው ልወጣ ስል፣
“ጌታሁን” ጠራኝ፡፡
“አቤት” ተመለስኩ ወደ ኋላ፣ ድንገት ተፀፅቶ ሳንቲም ቢጨምርልኝ ብዬ፡፡
“ሰማኸኝ፤ እናትህን እንደምትላት ‘እንዴት ነሽ? ተሻለሽ ወይ? መጥቼ እጠይቅሻለሁ ስል ሳይመቸኝ ቀረ’ በልልኝ፡፡”
“እሺ” እያልኩ ወደ ውጪ ወጣሁ፡፡
እሱ ግን አልጨረሰም፡፡
“አባትህንም፣ ‘እንኳን ለቅዱስ ዮሐንስ አደረሰህ’ በለው፡፡ ያ ተማሪ ወንድምህንም ሰላም በልልኝ፤ ‘አንተ ወመኔ ምን ሆነህ ነው መጥተህ የማትጠይቀኝ’ በለው...”
ክርስትና አባቴ እንቁጣጣሽ በመጣ ቁጥር ይኸው ነበር ባህሪው፤ ሲያናድድ!

Published in ህብረተሰብ

                        ከ1997 ዓ.ም መጨረሻ፣ ከ1998 ዓ.ም የዘመን መለወጫ ጀምሮ የኑሮ ውድነት ያለ ቅጥ እያሻቀበ ሲመጣ፣ የእነ ዶሮ፣ በግ፣ ፍየልና በሬም ዋጋ እንደዛው ማሻቀቡ አልቀረም፡፡ በተለይ ከሁለት ሺኛ ዓመታችን (ከሚሊኒየማችን) ዋዜማና መባቻ ጀምሮ፣ የኑሮ ውድነት እንዴት ለመለካት (ለመመዘን) አስቸጋሪ መሆኑን ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ የታሰበ እስኪመስል፣ ጣራ እየነካ ነው። ለነገሩ ከ2002 በኋላ ግን የኑሮ ውድነት ጣራ እንደሌለው በሚገባ ያረጋገጠ ይመስላል፡፡ ስለዚህ፣ የኑሮ ውድነት ጣራው በመበሳቱ፣ ኧረ እንደውም ጣራው በመቦደሱ “ውደነት” ብቻው ሽቅብ እንደ ሮኬት እየተተኮሰ ነው ቢባል፣ ተጋነነ የሚል ያለ አይመስለኝም፤ ካልሆነ ሽቅብ ከሚተኮሰው የኑሮ ውድነት ያለ ቅጥ የሚያተርፍ ባለ ጊዜ ሰው መሆን አለበት!
የዘንድሮው ማለቴ የ2005 ዓ.ም በዓላት ላይ የእርድ እንስሳት ዋጋ ከጣሪያ በላይ ስለመሆኑ የገበያ መረጃ እንዳጣቅስ መቼም አትጠይቁም፤ “አገር ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው” ሀቅ ነበረና፡፡ ታዲያ 2005 ዓ.ም መቋጫ ወይም የ2006 ዓ.ም አዲስ ዓመት መባቻ ላይ የእርድ ዋጋ እንደተለመደው ያለ ቅጥ ባያሻቅብ እንኳ ቢያንስ እንደማይቀንስ ግን ይታወቃል፤ እሺ “ይታወቃል” የምትለዋን ቅድመ ፍርጃ አገላለጽ፣ ለስለስ ባለ ትሁት ቋንቋ መግለጽ ካስፈለገ ወይም ከተገባ፣ “ቢያንስ እንደማይቀንስ ይገመታል” ልንል እንችላለን፡፡
እናም የአዲስ ዓመት መባቻው ዕለት ሳይቀርብ፣ በጳጉሜ የመጀመሪያ ቀናት ወደ ገበያ ወጣ ብዬ የዶሮና የበግ ዋጋ ስጠይቅ የማይቀመስ ነው። በነገራችን ላይ ይቺ ጳጉሜ የምትባል የወር ደመወዝተኛን የምታጐሣቁል ወር በሏት የማትቆጠር ቀናት አትመቸኝም! ሆድ፣ ለአምስት ቀናት፣ ከአራት ዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ ለስድሥት ቀናት እረፍት ያደርግ ይመሥል፣ እየሠሩ ክፍያ አለማግኘት ፍትሐዊ ነው!? ለአምሥት ወይም ለስድሥት ቀናት ወደ ሥራ ቦታ ለመጓዝ የታክሲ ወጪ ብቻ አሁን አሁን የማይቀመሥ እየሆነ ነው፡፡ ታዲያ ጳጉሜ በነፃ ልታሥፈጋን በየዓመቱ ሥትመጣ፣ “እንቁ”ን ትተን “ጣጣሽ” መጣች ብንላት የሚፈረድብን አይመሥለኝም፡፡
ታዲያ የጳጉሜ የወር ገቢያችንን የማፋለሷ ጣጣ እያለብን፣ የልጆች የትምህርት ወጪዎች እያፏጩብን፣ የአዲስ ዓመት በዓል እርድ ወጪ ሲታከልበት ኑሮ፣ “ንሮ፣ ንሮ…እሮሮ” ብቻ ሆነብን። በዚህ ጊዜ ከባለቤቴ ጋር ተመካከርንና “የዘንድሮ የአዲስ ዓመት እርድ ቢቀርስ?” ወደሚል አቅጣጫ አዘመምኩ፡፡ ባለቤቴም፣ “ለወትሮው ዶሮውም፣ በጉም አይቅር እያልሽ፣ ከመሥሪያ ቤት ብድር ሁሉ ታስጠይቂኝ ነበር፤ ዘንድሮ ደግሞ ሁሉም እርድ ይቅር ነው የምትይ? ልጆቹስ? ባይሆን በጉ ይቅርና ዶሮ እንገዛለን፤ በዓሉ ደግሞ እሮብ ላይ ስለሚውል ጥሩ ማሳበቢያ ይሆነናል…” በማለት መለሰልኝ፤ “ማሳበቢያ ይሆነናል…” የሚለው ገለፃው በርግጥም በጣም አስቆኛል፡፡
በሚቀጥለው ቀን በሾላ ገበያ፣ የዶሮዎችን ዋጋ ስጠይቅ ውዬ ሳልገዛ ተመለስኩ፡፡ ሰፈራችን፣ ፈረንሳይ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ጥግ ላይ ስለሆነ፣ መጠነኛ ጫካ ማየት ብርቅ አይደለም። ከገበያ መልስ ወደ ቤት ልገባ ስል ከቤታችን በላይ ያለው በባህር ዛፍና አልፎ አልፎ በጽድ የተሸፈነ ተራራ ታየኝ፡፡ በዚህ ተራራ ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ የጅብ ጩኸት መስማት የተለመደ የአካባቢው የተፈጥሮ ገፀበረከት ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በአንዳንድ ጉዳዮች ወይም በኑሮው ሁኔታ ስንጨናነቅ መፍትሔ ፍለጋ ለማሰላሰል፣ ለመጠሞን (ጥሞና ለማድረግ) ወይም ለመናፈስ በጫካው ውስጥ መንጐራደድ የተለመደ ነው፡፡
እኔም የቤታችንን አጥር አልፌ ወደ ተራራው ሳቀና ባለቤቴ፣ “ከገበያ መልስ ወደ ጫካ ምን ያስኬዳል?” በማለት በፈገግታ ጠየቀኝ፡፡ “በገበያው መናር ተስፋ ቆርጬ፣ ልታነቅ ነው አልልህም፡፡ ባይሆን የእርዱ ዋጋ ስላልቻልን ወደ አደን እየወጣሁ ነው…” ስለው በመልሴ እግሩን አንስቶ ሳቀ፡፡ እኔም ሳቅሁና ወደ ቤት ገባን፡፡
ጫካው ግፋ ቢል ጅብ ይገኝበት እንደሆነ እንጂ የእርድ እንስሳት አይታሰብም፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ዶሮ እንኳ በጫካው ትርው አይሉም፤ ያውም ዓመት ባዕል ሲደርስ፡፡ በርግጥ ዶሮ ባይኖር፣ ዶሮ አራጅ (ሙጭልጭላ) አይጠፋ ይሆናል፡፡ በእውነት ግን ዶሮን የሚተካ የሚበላ የአሞራ ዘር ባድን ምን ይለኛል? የሚል ሃሳብ መጣብኝ፡፡ አባታችን የቆቅና የዝግራ ሥጋ እንዴት እንደሚጣፍጥ ሲተርክልን የነበረው ትዝ አለኝ፡፡ ዛሬ ቆቅና ዝግራ ያውም በዚህ ጫካ ማደን ቀርቶ ማየት የሚከብድ ይመስለኛል። ሌሎች የወፍ ወይም የአሞራ ዘሮችም ሥጋቸው ስላልተቀመሰ እንጂ ከዶሮም ሊበልጡ ይችላሉ የሚል ሃሳብ መጣብኝ፤ ወዲያው የምግብ ምርጫ ማህበራዊ ህጋችን ወይም በአጠቃላይ አነጋገር የአመጋገብ ባህላችን ችግር እንዳለበት፣ ለችጋር የሚያጋልጥ እንደሆነ መጠየቅ፣ መመራመር ወይም መፈላሰፍ አሰኘኝ፡፡
ኧረ ለመሆኑ፣ የሚታደኑ እንስሳት ቢገኙ እንኳን እንዴትና በምን ማደን እንደሚቻል አላውቅም…መቼም የሽንኩርት ቢላዋ ወይም የድስት ማማሰያ ይዤ ለአደን አልወጣም፡፡ ባለቤቴንና ልጆቼን አስከትዬ ብሄድም፣ የሚሳካ አይመስለኝም ወዘተ…እያልኩ ከራሴ ጋር ማውጋት ጀመርኩ፡፡ መቼም፣ “ሳይጠሩት ዘማች” የሚል ምሣሌ የሚጠቅሱብኝ አይመስለኝም፡፡ እኔ ወደዚህ ሁሉ ጣጣ የገባሁት፣ የአዲስ ዓመት እርድ ገበያ፣ ከጳጉሜ የኪሣራ ቀናትና ከልጆች የትምህርት ወጪ ጋር አብሮ ስለ ኑሮ ሁኔታ ስላሳሰበኝ ነው፤ “ስላሳበደኝ ነው” እስከማለት ግን አልደፈርኩም፡፡
ምንም ሆነ ምን ግን “ለእርድ የሚሆኑ እንስሳትን ማደን” የሚል አማራጭ የኑሮ ዘዴ ፖሊሲ በመንደፌ ቢያንስ ባለቤቴን አስቄበታለሁ፡፡ ከፍ ሲልም፣ የሥራ ፈጠራ ጥረቴን ለማሳየት አስችሎኛል…ባለቤቴም በእቅዴ እየተገረመና እየሳቀ አንድ ወሳኝ ጥያቄ አነሳብኝ፤ “ለመሆኑ ለአዲስ ዓመት የሚሆኑ የእርድ እንስሳትንም ቢሆን ለማደን ፈቃድ አያስፈልግም? የምር ግን ማንም እንደፈለገው ማደን ይችላል? …ህግ፣ ፍቃድ ምናምን የሚባል ነገር ባይኖር እኮ ሰው ሁሉ የጐረቤቱን ዶሮና በግ ‘ያደንኩት ነው’ እያለ ያርድ ነበር…” አለ፡፡ እኔ ግን ንግግሩን ሳይጨርስ፣ ሼልፍ ላይ ወደተቀመጡ መጻሕፍት አመራሁ፡፡ አንድ ትልቅ ሀገርኛ መጽሐፍ አውጥቼ፣ ማገላበጥ ጀመርኩ፡፡
ባለቤቴም፣ ልጆቼም ወደ “እኔ ቀርበው አይናቸውን ከመጽሐፉ ገፆች ላይ ተከሉ፡፡ “ብራቮ! ‘ስለ ዱር አውሬ አደን’ የሚል ጽሑፍ” ስል፣ ባለቤቴ ፈጠን ብሎ፣ “ይነበብልና” አለኝ፡፡ ወዲያው፣ “የአውሬ አደን በኢትዮጵያ የጨዋ ልጆች ዋና ሞያ ሆኖ ክብርም ደረጃም ያስገኝ እንደነበረ እኔም ከደረስኩ ተመልክቼዋለሁ” የሚለውን የብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደመስቀል ጽሑፍ አነበብኩ። እንደቀልድ የተጀመረው የአደን ጉዳይ ብዙ እንድንጠይቅና እንድናነብ አነቃቃኝ፡፡
“በቀድሞ ዘመን ገና ጠመንዣ ባገራችን ሳይገባ፣ ጐበዞቹ አውሬ ያድኑ የነበሩት በጦርና በጐራዴ ስለነበረ፤ ይኸም ዐይነት አደን ከበሽታው ሌላ ለሕይወት የሚያሰጋ ነገር ያመጣባቸው እንደነበር ማንም ሊገምተው ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ዠግኖቹ ከክንዳቸው መጠንከርና ከልባቸው ሙሉነት የተነሳ የሚያስፈሩትንና የሚያሰጉትን አውሬዎች በድፍረት በጦር እየወጉ መግደላቸውን ያዩ ሽማግሌዎች ያረጋግጣሉ” የሚለውን በጋራ አነበብነው፡፡
አንዷ ልጄ፣ “የጨዋ ልጆች” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ላነሳችብን ድንገተኛ ጥያቄ፣ ወደ አባቷ “ሪፈር” በመላክ እኔ ንባቤን ቀጠልኩ፡፡ ጥያቄው ብዙ ታሪካዊና ባህላዊ ዳራዎችን እያወሱ ማስረዳትን እንደሚጠይቅ እኔም ባለቤቴም ጠንቅቀን እናውቃለን፤ ትንሹ ልጄ፣ “የባለጌ ልጅ ያልሆነ ማለት ነው?...” ብሎ በጥያቄ የመለሰውን ድፍረት አባቱን ቅር ያሰኘው መሰለኝ፤ ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፤ “የኢትዮጵያን ታሪክና ባህል በቀላል አቀራረብ” የሚል መጽሐፍ ለማዘጋጀት በሚያነቃ ደረጃ በወጉ ማስረዳቱን የተያያዘው፡፡
እኔ አሁንም፣ ዐይኔን ከመጽሐፉ አንቀፆች መንቀል አልተቻለኝም፡፡ ቀድሞ ከሚታወቁ ስመጥር አዳኞች መካከል፣ ዝሆን በጦር በመግደል ተደጋጋሚ ጀብዱ የፈፀሙትን “ፊታውራሪ ቡራዮ የሚባሉትን የወለጋ ሰው” የመጽሐፉ አዘጋጅ፣ ደራሲ ማኅተመሥላሴ እንደደረሱባቸውና በአካል እንዳዩዋቸው የገለፁበትን አንቀጽ እያነበብኩ ተደመምኩ፡፡ በአፄ ምኒሊክ የመካከለኛ ዘመን መንግሥታቸው ወዲህ የተለያዩ የአደን መሣሪያዎች እንደ ዛሬው ዘመን ባይበዙም ጥቅም ላይ ይውሉ እንደነበረ፣ እነዚህ የአደን መሣሪያዎቹም የጦር ወይም የውጊያ መሣሪያዎች እንደሆኑ እያነበብኩ፣ እኔ በሽንኩርት ቢላዋና በድስት ማማሰያ ለአደን መውጣት እንዳሰብኩ አድርጐ ባለቤቴ ያሳቀብኝ ወሬ ትዝ አለኝ - ሳቅሁ፡፡ ባለቤቴና ልጆቼ ውይይታቸውን አቁመው የሳቅሁበትን ምክንያት ለማወቅ ወደ እኔ ዞሩ፡፡ ትንሹ ልጄ የሳቅሁበትን እንድናገር በጥያቄ ወተወተኝ፡፡ “በሉ ሁላችሁም የሽንኩርት ቢላዋና ማማሰያ እየያዝን ወደ ጫካ እንውጣ፤ ለአደን ተዘጋጁ፤ የአመት ባዕል ሥጋ ቁጭ ብሎ አይገኝም!” ሥል ቤቱ ሁሉ ጥርስ በጥርስ ሆነ፡፡
ባጋጣሚ የተጀመረው የአደን ወሬና ንባብ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን አሳወቁን፡፡
በአገራችን በነበረው የአደን ባህል፣ አንበሳ ከገደለ ግስላ የገደለ የበለጠ ክብርና ሞገስ እንደሚያገኝ፣ በጀግንነቱም የበለጠ እንደሚደነቅ አነበብኩ፡፡ የአራዊቶች ሁሉ ንጉስ አንበሳ ነው እያለ በሚናገር ህብረተሰብ ውስጥ አድገን፣ ከአንበሳ የበለጠ ግስላ ወይም ቀጭኔ ያደነ ትልቅ ክብርና ሞገስ እንዳለው በማወቃችን እኔና ባለቤቴም ተገርመናል፤ ልጆቻችንም ከአንበሳ በላይ የሚያስከብሩ ሌሎች አራዊቶች መኖራቸውን ለመቀበል ሁሉ ተቸገሩ፡፡ ስለዚህ ስለ አደን ባህላችን ብዙ እያነበብን ብዙ ለመወያየት ተስማማን፡፡
እናም፣ ስለ አደን ህግ፣ አዋጅ፣ ስለሚታደኑ እንስሳትና ስለሚገኘው ክብርና ሞገስ…የማኅተመሥላሴን መጽሐፍ እያጣቀስን በቤታችን የምናደርገውን ውይይት “ለአዲስ አድማስ” አንባቢዎችም ለማካፈል እሞክራለሁ፡፡ እስከዚያው ግን፣ በእኔ ቤት የአዲስ ዓመት መዋያ እርድ ባይታረድ እንኳ፣ ብዙ አያስጨንቀንም፤ ቢያንስ ስለ አደን ባህላችን እያነበብንና እየተወያየን ቤት ባፈራው ምግብና መጠጥ በደስታ እንደምናሳልፍ ማረጋገጫ አግኝቻለሁ፡፡ በርግጠኝነት ግን የምነግራችሁ፣ አላስፈላጊ ብድር ውስጥ ገብተን እርድ ወደ ማረድ እንደማንገባም ይታወቅልን፡፡ እኔና ቤተሰቤ በአዲስ ዓመት ዋዜማም በሉ መባቻ በግና ዶሮ ባናርድ እንኳ፣ መጻሕፍትን እያነበብን አዳዲስ መረጃዎችንና እውቀቶችን በመበለት በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ ያረቀቅሁትን የኑሮ ዘዴ አያችሁልኝ? አያዋጣም? “የአዲስ ዓመት እርድ ቢሉ፣ አደን ትዝ አለኝ” ማለት እንዲህ ነው፡፡

Published in ባህል

(ደርግ፣ መስከረም 1967 ዓ.ም)
የ1967 ዓ.ም አዲስ ዘመን ሊብት የዋዜማው ዕለተ ምሽት ጀምሮ የጆናታን ዲንቢልቢን “ዘ ሂድን ፌሚን” በማሳየት፣ “ለአዲሱ ዘመን ለኢትዮጵያ ሕዝብ የምናቀርበው ስጦታ [ከዚህ ሌላ] የለንም” የሚል ዝግጅት፣ በጥቁርና ነጩ ቲቪ አቀረቡ፡፡ ሕዝብ አለቀሰ፡፡ ነገር አለ ማለት ነው፡፡
አዎን፣ አለ፡፡ መስከረም 1967 ዓ.ም ልክ እንደ ዘንድሮው ረቡዕ ዕለት ነበር ዘመን መለወጫው፡፡ ሐሙስ ዕለት መስከረም 2 ጧት የአፍሪካ አዳራሽ የሚባለው ኢሲኤ ፊት ለፊት ሕዝብ ግጥም ብሎ ወደ ኢዮቤልዮ ቤተመንግሥት አሻግሮ ይመለከታል። ታንክና ብረት ለበስ ጦር በዙሪያው ከብቧል፡፡ የዚያኑ ዕለትም ንጉሱ ከሥልጣን የመውረዳቸው ዓዋጅ ታውጇል፡፡ ጳጉሜ 5/1966 ማክሰኞ ዕለት ነበር ለማውረድ ሲያመነታቱ የነበሩትና የደርግ አባላትን የሚያሾሩት ኃይሎች ለመጨረሻ ጊዜ የገንዘብ ጥያቄ ለንጉሱ እንዲቀርብላቸው ያደረጉት፡፡
“በስዊዝ ባንክ ያስቀመጡትን ገንዘብ ይመልሱ” ተባሉ፡፡ የርሳቸው ምላሽ ከዚህ በፊት ሲመልሱላቸው ከነበረው የተለየ አልነበረም፡፡
“ገንዘብ የለንም፡፡ የነበረንንም ለልጆቻችን አውርሰናል፤” የሚለውን ቁርጥ ያለ መልሳቸውን አጥብቀው ገለጹ፡፡
በዚህ ወቅት ይሁን ወይም ከዚህ በፊት ባይለይም፣ ትልቂቱ ልጃቸው ልዕልት ተናኜ ወርቅም፣ “የምን ገንዘብ ነው፡፡ እኛም እኮ ልጆች ነን፡፡ ወራሾች ነን” ሲሉ በቁጣና በኃይለ ቃል እንደመለሱላቸው ይታወቃል፡፡
ምናልባትም፣ የደርጉ መሪ ተዋናይ የነበሩት ሻለቃ መንግሥቱ ኃ/ማርያም በፕሬዚዳንትነታቸው ዘመን፣ “እኔ እንዲያውም ርሳቸውን አከብራቸው ነበር፡፡ እንዲያ ያሉ አድርጌ አላስባቸውም ነበር፡፡ ነገር ግን የዚያን ጊዜ የተናገሩት ከርሳቸው የማልጠብቀውን ነበር፣” ሲሉ ስለ ልዕልቲቱ በይፋ የተናገሩትም እንዲህ ያለ ጥያቄም ሲያቀርቡላቸው የተናገሯቸውን ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል፡፡
ነገር ግን ሻለቃው ከንጉሱ ፊት ቀርበው እንደነበር የማይታሰብበት ታሪክን ስለምናገኝ፣ (እንደ ግብፁ ጋማል አብዱል ናስር ሌሎችን ፊት እያስቀደሙ የፈለጉትን ሲያስፈጽሙ የነበሩ ናቸውና) ምናልባት ንጉሱ ከወረዱ በኋላ፣ በተለይም ከ10 ወሮች በኋላ በኮ/ል ዳንኤል አስፋው የሚመራው የቅልቡ ነፍሰ ገዳዮቻቸው ቡድን ከደብረብርሃን አዲስ አበባ ገብቶ፣ እንዲገድሏቸው ከማዘዙ በፊት ይሆናል ከኝህ ጊዜ ጥሎአቸው እንኳ ይፈሯቸው ከነበሩት ግርማዊው አዛውንት ፊት የቀረቡት፡፡
ያ መቼም ይሁን፣ በጳጉሜ 5/67 ዓ.ም ለደርግ አስተባባሪ መልእክተኞች የመለሱት ምላሽ ግን ከወራት በፊት ጀምሮ በደርግ ሲብላላ የቆየው ንጉሱን የማውረዱን ሥራ ቁርጥ አደረገው፡፡ ወደዚያው፣ ሕዝቡንም ለማነሳሳትና ተገቢ ርምጃ እንደሆነ እንዲታሰብ፣ አዲስ አበባ ላይ ለነበሩ ባለቴሌቪዥኖች የጆናታን ዲንቢልቢ “ዘ ሂድን ፌሚን” የአዲስ አመት ስጦታ ሆኖ እንዲተላለፍ ተደረገ፡፡ “እኛ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመኑ መለወጫ የምናቀርብለት ስጦታ የለንም” በሚል ርዕስ ይህ የዲንቢልቢ ፊልም እና የንጉሠ ነገሥቱ የደግ ጊዜ ዓለም ጐን ለጐን እየተቀነባበረ፡፡ የዚያኑ ዕለት ምሽት (ለአዲስ አመት ዋዜማ ምሽት) ጀምሮ በጥቁር ነጩ ምስል ቀረበ፡፡
በዚህ ፊልም የሚታየው የረሃቡ ሰለባዎች ሁኔታ አሳዛኝና ሰው ሆኖ መፈጠርን ሁሉ የሚያስጠላ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ በየጣልቃ ከሚገቡት በንጉሡ አካባቢ የነበሩ አንዳንድ ድግሦችና ፌሽታዎች ጋር፣ በተለይም አሠርተውት ከነበረ ሐውልት ጋር ሲቀናጅ ብዙዎችን አስለቅሶ እንደነበር የገለጹ አሉ፡፡
የሚገርም ነው! ደርግ በወሎ የነበረውን ወደ 1 ሚሊየን ሰው የተጠቃበትን ረሃብ ከንጉሡ ሐውልት ግንባታ ጋር በማቅረብ ሰውየው ላይ ዘመተባቸው። በእርሱ ዘመን ደግሞ የረሃብተኛው ቁጥር በ3 እጥፍ አድጐ የዓለምን ልብ ባሳዘነበት ወቅት፣ እርሱም ትግላችን ሐውልትን ይገነባ ነበር፡፡ የርሱ ተከታዮችም የንጉሱንና ይህን የደርጉን ዘመን የረሃብ ሰቆቃ እና የሐውልት ግንባታዎች ታሪክ እየተረኩም ነበር የቀሰቀሱትም የገቡትም፡፡ በሚያስገርም ተመሳሳይነት የረሃብተኛው ብዛት ከንጉሱ ዘመን ከስምንት እጥፍ በላይ በሚሆን ቁጥር ጨምሮ በነበረበት ጊዜ ደግሞ እነሱ የሰማዕታት ሐውልትን ግንባታ ላይ ነበሩ፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ በቅርብ ካለው ሕዝብ ሊገጥም የሚችል ተቃውሞም እንዳይኖር፣ ይልቁንም ድርጊቱን እንዲደግፉላቸው እንዲህ ተደርጐ ሲቀርብ አድሮና ውሎ፣ በቀጣዩ ቀን፣ መስከረም 2 ቀን ላይ ንጉሱን ከሥልጣን የማውረዱ ሥራ ተከናወነ፡፡ የማውረጃው ዓዋጅም ታወጀ፡፡ ሐሙስ ዕለት ጧት ላይ ነበር፡፡ ሰውም አስቀድሞ አውቆታል፡፡ አዋጁ በማለዳው ጧት እንደተሰማ ይታወቃል፡፡ ያም ሆኖ ይሆናል የአፍሪካ አዳራሽ ፊት ለፊት (ኢሲኤ) ጧቱኑ በብዙ የአዲስ አበባ ነዋሪም የተሞላው፡፡
በኢዮቤልዩ ቤተመንግሥቱ ውስጥ የ83 ዓመቱ ንጉሠነገሥት ከሚታወቅላቸው የዕለት ተዕለት የጧት መደበኛ ውሎአቸው በተለየ ሁኔታ ከዙፋናቸው ተቀምጠዋል፡፡ ለርሳቸው ከሚቀርቡት ልዑል ራስ እምሩም በዚያች ጧት ላይ በታዛቢነት እንዲገኙ አዛዥ - ናዛዥ የሆነው ደርግ በጠራቸው መሠረት ተገኝተዋል፡፡
ከደርግ የተመረጡ 13 አባላት የያዘው ቡድን አባላት፣ ከአሁን አሁን ወገቤን ሊያነክቱኝ ነው ብላ ተሸማቅቃ ቁልጭልጭ እንደምትል ውሻ ከፊታቸው ወደ ቀኝ ጐን፣ ትከሻ ለትከሻ ከመተዛዘል ብዙም ባልራቀ ሁኔታ ተጠራቅመው ቆመዋል፡፡
እንደ አንድ ፖላንዳዊ አገላለጽ፣ ፍርሃታቸው ያ የሞት ሽረት ደብዳቤ ለነሱው ራሳቸው የሚገለጽ ይመስል ነበር፡፡
የቡድኑ መሪ የነበሩት ሻለቃ ደበላ ዲንሳ የያዙትን ወረቀት አነበቡ፡፡
“የጦር ኃይሎች የፖሊስ ሠራዊትና የብሔራዊ ጦር ደርግ ለግርማዊነትዎ ደህንነትና ጤንነት በሰፊው እሚያስብ እንደመሆኑ መጠን፣ ለዚሁ ለጤንነትዎም ሆነ ለደህንነትዎ የተዘጋጀ ሥፍራ ስለ አለ ወደዛ እንዲሄዱልን በትህትና እንለምናለን፡፡”
እንደምንም ጨረሷት አንብበው፡፡
ንጉሡ ዝም ብለው ቆዩ፡፡ ከዚያ ያላንዳች ድንጋጤና መረበሽ ይጠይቋቸው ጀመሩ፡፡
“እንዴት ነው የሚኬደው?”
“ወደተዘጋጀ ሥፍራ…ሥፍራ አለ፡፡ በተለይ ያዘጋጀነው፡፡ ከኛ ጋር እንሄዳለን”
“በጠቅላላው መቼም የተናገራችሁትን ሰምተናል፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ስንሆን ስም ብቻ አይደለም፤ ሕዝቡም አገሩም በሰላም ጊዜ የሚሰራለትን፣ ጠላትም ቢመጣ የሚመክትበትን በማሰናዳት ነው እንጅ፡፡ ይኸው ቢሆንም፤ በየጊዜው የሚለዋወጠው ነገር ደግሞ ላገር የሚጠቅም ነገር እስከአለበት ያገርን ጥቅም በሌላ ለመለወጥ አይቻልምና ይህ ያነበባችሁትን ሰምተናል፤ አሁንም እንደዚህ ነው፡፡ ማቆም ነው፡፡
“የኔ ታሪክ እዚህ ያበቃል፡፡ የናንተ ታሪክ እዚህ ይጀምራል፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት በመጠበቅ ዳር ድንበሯን ማስከበር ካቃታችሁ፣ ያን ጊዜ የናንተ ታሪክ ይሞታል፤ የኔ ታሪክ ደግሞ ያኔ ይጀምራል፡፡
አሁንም ዝም ብለው ቆዩና “መጻሕፍት ይዤ መሄድ ይፈቀድልኛል?” ሲሉ ጠየቁ፡፡
“አዎን” ለማለት አላመነታሁም ይላሉ፣ ደበላ ዲንሳ በምሥክርነት መጽሐፍ ላይ፡፡
“አሽከርስ ከእኔ ጋር መሄድ ይቻላል ወይ?” አሏቸው፡፡
“ግርማዊ ሆይ! ማንን ነው የሚፈልጉት?” - ደበላ ዲንሳ፡፡
“አሽከር ብዬኻለሁ! ምን አማረጠህ” ብለው ተቆጡ፡፡
በዚያን ጊዜ ከደበላ ዲንሳ ጀርባ “ወሰኔ ወሰኔ” የሚል ስም ተጠርቶም ነበር፡፡
ከደቂቃዎች ዝምታ በኋላ ደግሞ “ለመሆኑ ወዴት ነው የምንሄደው፣” ብለው ጠየቁ፡፡ ትክክለኛ የቦታውን ስም ሊገልፁላቸው ባይችሉም ከአዲስ አበባ ውጭ እንደማይሆን ደበላ ዲንሳ ገለጹ፡፡
አሁንም ረጅም ዝምታ፡፡ ይኼኔ ደበላ ወደ ልዑል ራስ እምሩ ተናገሩ፣ “ልዑል ሆይ፣ ለጃንሆይ ይንገሩልን፣ ወደተዘጋጀላቸው ቦታ…” እንዳሉዋቸው፣
“ተነሳና ሂድ መቸስ ምን ይደረግ፣” በማለት ልዑሉም ወደ ንጉሡ ተናገሩ፡፡
ይኼኔ ብድግ አሉ፡፡ ቀጥታ ወደ ደበላ ዲንሳ ተራመዱና ከፊታቸው ቆመው፣ የመሣሪያ አያያዛቸውን ተመለቱላቸው፡፡ እናም፣ “ለምንድነው መሣሪያውን እንዲህ የያዝከው” አሏቸው፡፡ “ለአያያዝ ይመቸኛል ብዬ”
”እኛን ለመያዝ?”
“የለም፣ ግርማዊ ሆይ ጠመንጃውን”

Published in ባህል
Page 10 of 16