“The 48 Laws of power” የተሰኘው የሮበርት ግሪን መፅሃፍ “48ቱ የአሸናፊነት ሚስጥራት” በሚል በእስክንድር ስዩም ተተርጉሞ ለንባብ በቅቷል፡፡
በ48 ምስጢሮች የተከፋፈለው መፅሃፉ፤ “ከአለቃይ በልጠህ ለመታየት አትሞክር”፣ “በሌሎች ዘንድ ተፈላጊ መሆንን እወቅበት”፣ “ፍላጐትህን ላገኘኸው ሁሉ በግልፅ አትናገር”፣ “ሁሌም ከደሙ ንፁህ ለመሆን ጥረት አድርግ” የሚሉና ሌሎች ርዕሶችን ይዟል፡፡ በ161 ገፆች ተቀንብቦ የተዘጋጀው መፅሃፍ፤ በታዋቂ ሰዎች አባባልና ጥቅሶች የታጀበ ሲሆን በ39 ብር ከ45 ለገበያ ቀርቧል፡፡ ተርጓሚው ከዚህ ቀደም “ስኬታማ የጊዜ አጠቃቀም”፣ “የፍቅር መፍትሄ” እና “ወርቃማ የፍቅር ጥቅሶችና አባባሎች” የተሰኙ መፅሃፍትን ለንባብ ማብቃቱ ይታወቃል፡፡

.....ስንታየሁ መልካ እባላለሁ፡፡ የመጣሁት በሲዳማ ዞን ከሸበዲኖ ወረዳ ነው፡፡ ሙያዬም ክሊኒካል ነርስ ነኝ፡፡ በስራዬ አንድ የማልረሳው አጋጣሚ አለኝ፡፡ ሴትየዋ ለሕክምና ስትመጣ እንግዴ ልጅ ከማህጸንዋ ጋር ተጣብቆ ነበር፡፡ ጊዜ ወስደን ብንጠብቅም ከማህጸን ለመላቀቅ አልቻለም፡፡ ስለዚህ ሴትየዋ እንዳትጎዳ በመፍራት ወደከፍተኛ ሐኪም ላክናት፡፡ ነገር ግን አሁን በስልጠና ላይ እንዳየሁት ከሆነ ለካስ ሴትየዋን በቀላሉ ማዳን ይቻል ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ደም እየፈሰሳቸው የሚመጡ እናቶች ቢያጋጥሙን ጤና ጣብያ ላይ ምንም እርዳታ ለመስጠት ሳንሞክር እናስተላልፋለን፡፡ ነገር ግን ይህ ስልጠና ብዙ ነገር አስተምሮናል፡፡ ማከም የሚቻለውን ማከም...ማከም የማይቻል ከሆነ ግን በፍጥነት አላስፈላጊ መዘግየትን በማስወገድ ወደ ከፍተኛ ሕክምና ማስተላለፍ እንዳለብን በሚገባ ተረድተናል.....
                                                 -----///-----.
...ትእግስት ተሸመ እባላለሁ፡፡ ከጎርጂ ወረዳ ከጎርጂ ጤና ጣብያ ነው ለስልጠናው የመጣሁት፡፡ እኔ በሙያዬ ጤና መኮንን ነኝ፡፡ በሕክምናው ዘርፍ ከተሰ ማራሁ ወዲህ የማልረሳው አንድ አጋጣሚ አለኝ፡፡ እርጉዝዋ ሴት ለሕክምና ስትመጣ እትብቱ ከልጁ ቀድሞ ወጥቶ ነበር፡፡ እንደዚህ ያለ አጋጣሚ ተከስቶ አይቼ ስለማላውቅ በጣም ነበር የደነገጥኩት፡፡ አብረውኝ የነበሩትም ለነገሩ እንግዳ በመሆናቸው አማራጭ አልነበረንም። ወደከፍተኛ ሕክምና ላክናት፡፡ ነገር ግን እስከዛሬ የሚቆጨኝ ...እኛጋ በነ በረችበት ሰአት የልጁዋ የልብ ትርታ ይደመጥ የነበረ ሲሆን ወደተላለፈችበት ጤና ተቋም እስክትደርስ ግን ትርታው አልቀጠለም፡፡ በመሀከል ልጁዋን አጥታለች፡፡ ልጁን ያጣ ችው ይህች ሴት ብቻ ሳትሆን እንደዜጋ እንዲሁም እንደባለሙያ እኛም ነን ያጣነው፡፡ እናም እስከዛሬ ድረስ ይቆጨኛል፡፡ አሁን ግን ይህንን ስልጠና በማግኘታችን የምንች ለውን በፍጥነት መርዳት የማንችለውም ከሆነ አላስፈላጊ መዘግየትን በማስወገድ በፍጥነት ሌላ እርዳታ እንዲ ያገኙ ማድረግ እንዳለብን በሚገባ አውቄአለሁ፡፡ ቀደም ሲል በትምህርት ላይ እያለሁ የተወሰነ እውቀት ቢኖረኝም ተግባራዊ ሁኔታውን ግን በደንብ አላውቀውም ነበር፡፡ አሁን ግን በሚገባ ለመስራት ዝግጁ ነኝ፡፡
                                                 ----////----
ከላይ ያነበባችሁት WATCH (women ande their children health) ማለትም የሴቶችና ሕጻናትን ጤንነት መጠበቅ በሚል ትርጉዋሜ የተሰየመው በጎ አድራጊ ድርጅት ከኢሶግ እና ከፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ከሚሰራባቸው አካባቢዎች በሲዳማ ዞን ሐዋሳ ከተማ በመሰጠት ያለውን ስልጠና በተከታተልንበት ወቅት ያነጋገርናቸው ሰልጣኞችን ምላሽ ነው፡፡ በማስከተል የምናስነብባችሁ የዞኑን የጤና መምሪያ ኃላፊ የአቶ በድሉ ባዴጎን ማብራሪያ ነው፡፡
አቶ በድሉ ባዴጎ የሲዳማ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ እንዳብራሩት ከምእተ አመቱ የልማት ግቦች ከስምንቱ ውስጥ ሶስቱ በጤናው ዘርፍ ያተኮሩ ናቸው፡፡
1. የእናቶችን ሞት በ3/4ኛ መቀነስ ፣
2. የህጻናትን ሞት በ2/3ኛ መቀነስ፣
3. ዋና ዋና ተላላፊ በሽታዎችን...ወባ ኤችአይቪ ኤይድስ ቲቪ...መከላከል ናቸው፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ የሲዳማ ዞን ከ WATCH እና ከፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ እንዲሁም ከኢሶግ ጋር እየሰራ ያለው የእናቶችና ሕጻናትን ሞት መቀነስ በሚያስችለው ዙሪያ ነው፡፡
የእናቶችንና የህጻናቱን ጤና ለመጠበቅ ከሚያስችሉት መንገዶች ዋነኛው እናቶች በጤና ተቋም መውለድ መቻላቸው ነው፡፡ እናቶች ወደ ጤና ተቋም ለመውለድ ሲመጡ በሰለጠነና ብቃት ባለው የጤና ባለሙያ እንዲወልዱ እና መድሀኒትና የህክምና አገልግሎት መስጫው በተቋሙ በተሟላ ሁኔታ እንዲገኝ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህም በሁሉም የጤና ተቋማት ለተሰማሩ ባለሙያዎች መሰረታዊ ድንገተኛ የእናቶችና የጨቅላ ሕጻናትን እርዳታና እንክብካቤ በሚመለከት ስልጠና ሲሰጣቸው በዛ ረገድ እናቶችም ጨቅላ ሕጻናቱም ተጠቃሚ ይሆናሉ የሚል እምነት አለ፡፡ በእርግጥ ከምእተ አመቱ የልማት ግብ ጋር በተያያዘ ከዚህም በተጨማሪ የጨቅላ ሕጻናቱ ክትባት የሚያገኙበት እንዲሁም እናቶች የቤተሰብ እቅድ ዘዴ፣ በእርግዝና ወቅት ቢያንስ እስከ አራተኛ ዙር የሐኪም ክትትል ማድረግ፣ በምጥ ሰአት በጤና ተቋም በመቅረብ እንዲወ ልዱ የማድረግ ስራ በስፋት እየተሰራ ይገኛል፡፡ በሲዳማ ዞን በተለይም በ2005 ዓ/ም እናቶች በቤታቸው የመውለድ እርምጃ እንዳይወስዱ ለማድረግ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶ እርጉዝ የሆኑ እናቶችን በየቀበሌው በመመዝገብ እና መድረክ በመፍጠር ውይይት እንዲያደርጉ ሁኔታ ዎች ተመቻችተወ ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ በጤና ባለሙያ ምርመራ በማድረግም የሚወል ዱበ ትን ጊዜ እንዲያውቁት የማድረግ ስራ በመሰራት ላይ ስለሆነ በዚህም መነሻነት ምጥ ሲጀምራ ቸው ጊዜ ሳይፈጁ በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው ጤና ተቋም በመሄድ መውለድ የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቶአል፡፡ በዚህም ብዙ እናቶች ወደጤና ተቋም በመቅረብ በመውለድ ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሎአል፡፡
አቶ በድሉ የባለሙያዎችን የሙያ ብቃት በሚመለከት የአሰራር ለውጥ መኖሩን ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ማስረጃ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ከ2003/ ዓ/ም ወዲህ በመሰጠት ላይ ስለሆነ ብቃቱን በማረጋገጥ ወደሚቀጥለው ትምህርት እንዲገቡ በመደረግ ላይ ናቸው። በተለይም በጤና ሙያው ዘርፍ ለመቀጠርም ይህንን ፈተና ተፈትነው ሲያልፉ ብቻ ወደ ዘርፉ ይገባሉ፡፡ ወደህክምናው ዘርፍ የተሰማሩትን ባለሙያዎች በስልጠና ማገዝ ተገቢ በመሆኑም የተለያዩ ድርጅቶች ስልጠና ሲሰጡ ዞኑም ተገቢውን ባለሙያ በመምረጥ ለተሻለ እውቀት ስልጠና እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ በዚህም አሰራር የእናቶችንና የጨቅላ ሕጻናቶቻቸውን ሞት እንቀንሳለን የሚል እምነት አለን ብለዋል፡፡
በ WATCH ድጋፍ በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ማህበር አማካኝነት በዞኑ ሶስት ወረዳዎች ላይ ለተወሰኑ ባለሙያዎች የሚሰጠውን ስልጠና በሚ መለከትም እንዳብራሩት ስልጠናዎች የሚካሄዱት በመንግስት ፕሮግራም እየታገዙ ነው፡፡ መንግስት በራሱም ፕሮግራም ይሁን በተባባሪ አካላት አማካኝት ስልጠናው በሁሉም የዞኑ የህክምና ተቋማት ላሉ ባለሙያዎች እንዲሰጡ የበኩሉን ያደርጋል፡፡ በመሆኑም በየጤና ጣብያው አፋጣኝ የእናቶችንና የጨቅላ ሕጻናቶችን ጤንነት በመንከባከብ ረገድ ለሁሉም ባለሙያ ስልጠናው እንዲደርስ ለማድረግ መንግስት የራሱን አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል፡፡ መንግስት የሚችለውን እያሰለጠነ ሲሆን መንግስት የማይደርስበትን ደግሞ ከተባባሪ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ይሰራል፡፡
አቶ በድሉ ባዴጎ እንደገለጹት በ WATCH ድጋፍ በፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ እና በኢሶግ ትብብር በዞኑ በመሰጠት ላይ ያለው ስልጠና ወሳኝነት አለው፡፡ መሰረታዊ ድንገተኛ የእናቶችና የጨቅላ ሕጻናቶች እንክብካቤ ስልጠና በየጤና ጣቢያው እንዲሰጥ እና የሰለጠኑ ሰዎች ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ማድረግ ዞኑ በእቅድ የያዘው አሰራር ነው፡፡ ስለዚህም ይህንን አቅጣጫ በመከተል በዞኑ በሶስት ወረዳዎች ላይ ስልጠናን ለመስጠት የተደረገውን ስምምነት ከግብ ለማድረስ ዞኑ አብሮ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት በሸበዲኖ፣ ቦና እና ጉርቺ ወረዳዎች ላይ በሁለት ዙር ለአስራ ስምንት ቀን ስልጠናው ተሰጥቶአል፡፡ ሰልጣኞች ከስልጠ ናው ያገኙትን እውቀት በሶስት ሆስፒታሎች በቀንና በማታው ክፍለ ጊዜ በመመደብ በተግባር እንዲተረጉሙ በመደረጉ ይበልጡኑ እውቀታቸውን የሚያዳብሩበት አጋጣሚ ተከስቶአል፡፡ እያንዳንዱ ሰልጣኝ ቢያንስ ቢያንስ እስከ አምስት እናት የማዋለድ ስራ እንዲሰሩና ምናልባትም የማዋለድ ተግባሩ አስቸጋሪ ሁኔታዎችንም ጭምር እንዲመለከቱ ስለሚያስችላቸው ወደመጡበት የህክምና ተቋም ሲመለሱ ችግር አገልግሎቱን በብቃት ለመስጠት ያስችላል፡፡ ስልጠናው የሚሰጠው በብሄራዊ ደረጃ በተነደፈው ጋይድ ላይን መሰረት ስለሆነ ባለሙያዎችን ብቁ እንደሚያደርጋቸው እሙን ነው፡፡
በስልጠናው ላይ የተሳተፉት ባለሙያዎች ወደስራ መስካቸው ሲመለሱ በህክምና መገልገያ እና በመድሀኒት አቅርቦት በኩል የአሰራር ችግር እንዳይገጥማቸው ማድረግን በተመለከተ አቶ በደሉ ባዴጎ የሲዳማ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ እንደገለጹት በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስ..ር በኩል በየጤና ጣቢያው እናቶችንና ጨቅላ ሕጻናቶችን በማከም ረገድ ምን መሳሪያዎች እና መድሀኒቶች አስፈላጊ እንደሆኑ አስቀድሞ ይታወቃል፡፡ በእርግጥ ግዢው በውጭ ምንዛሪ በመሆኑና ዋጋውም በጣም ውድ ስለሆነ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን በአንድ ጊዜ ማሟላት እንደማይቻል እሙን ነው፡፡ ቢሆንም ግን የህክምና መሳሪያዎቹን ደረጃ በደረጃ ለወረዳዎች እያቀረበ ሲሆን በሂደት ይሟላል የሚል ተስፋ አለ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከ WATCH ጋር ተባባሮ ለስድስት ጤና ጣቢያዎች የህክምና መገልገያ እቃዎችን ገዝቶ ያቀረበ ሲሆን ይህ ድጋፍ በዚህ ይቆማል የሚል ግምት የለም። በቀጣይም ሌሎች ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ለተቀሩት ጤና ጣቢያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ በመነጋገር ላይ እንገኛለን፡፡ ነገር ግን ሁኔታውን መንግስት በፕሮራም ይዞ አስፈላጊውን እያደረገ ስለሆነ በወደፊት አሰራሩ ጤና ተቋማቱ በቂ በሆነ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ ስራቸውን መስራት የሚችሉበት ሁኔታ ይኖራል የሚል እምነት አለ ብለዋል አቶ በደሉ ማዴጎ በማጠቃለያ ሀሳባቸው፡፡

Published in ላንተና ላንቺ

            ዛሬ የኢትዮጵያውያን አዲሱ የ2006 ዓ.ም ከገባ የመጀመሪያው ቅዳሜ ነው፡፡ ይህን የአዲሱን ዘመን መልካምና አስደሳች ስሜት እያጣጣሙ ያሉት በሀገራቸው ውስጥ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደሉም። በመላው አለም ተበትነው የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንም ይህንን አይነቱን ጣፋጭ ስሜትና ደስታ ይጋራሉ፡፡
በምድረ እስራኤል ለሚኖሩትም ሆነ በመላው አለም ተበትነው ለሚገኙት አይሁዶች የዛሬው ቅዳሜ አዲሱን አመት ከተቀበሉ ለሁለተኛ ጊዜ የሚያከብሩት የሻባት (ሰንበት) ቀን ነው፡፡ መላ አይሁዳውያን “ሮሽ ሐሻና” እያሉ የሚጠሩትን የአዲስ አመት ክብረበአላቸውን ከዛሬ አስራ አንድ ቀን በፊት ነሐሴ 29 ቀን በታላቅ ስነስርዓት አክብረዋል፡፡ አይሁዳውያን ይህን የሮሽ ሃሻና ክብረበአል ካከበሩት እነሆ ዛሬ ስምንተኛ ቀናቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ልክ እንደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የበአል ስሜታቸው ገና አልበረደም፡፡ እናም እርስ በርስ ሲገናኙ “ሻና ቶቫ” (እንኳን አደረሰህ) እየተባባሉ መልካም ምኞታቸውን ይገላለጣሉ፡፡
እንደተቀሩት አይሁዳውያን ሁሉ ቤተእስራኤል በመባል ተለይተው የሚታወቁት ኢትዮጵያውያን አይሁዶችም የሮሽ ሀሻናን ክብረበአል ያከበሩት በሞቀ ስሜትና በአዲስ ተስፋ ተሞልተው ነው፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች የሚለው አገላለጽ የሚያመለክተው ከኢትዮጵያ የሄዱ መሆናቸውን ብቻ ነው፡፡
እንደ እስራኤል መንግስት ይፋ መግለጫ ዛሬ ከአንድ መቶ አርባ ሺ በላይ ቤተእስራኤል ይሁዲዎች በመላ እስራኤል ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ይህ ቁጥራቸው ከጠቅላላው የእስራኤል ህዝብ ጋር ሲነፃፀር ሁለት በመቶ ያክላል፡፡
ከጠቅላላው የእስራኤል ከተሞች ውስጥ በርካታ ቤተ እስራኤሎች (ወደ 12ሺ የሚጠጉት) የሚኖሩት በናታንያ ከተማ ሲሆን ሪሾን ላዚወንና አሽዶድ ከተሞች ከስድስት ሺ በላይ የሚሆኑትን ቤተእስራኤሎች በመያዝ በሁለተኛና በሶስተኛነት ይከተላሉ፡፡ ጥቂት ቤተእስራኤሎች የሚኖሩባት ደግሞ የባትያም ከተማ ብቻ ናት፡፡ በዚች ከተማ የሚኖሩት ቤተእስራኤሎች ቁጥራቸው ሁለት ሺ አንድ መቶ ሰባ ሰባት ብቻ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን የአዲሱን አመት መቀበያ ክብረበአላቸውን ያከበሩት መስከረም 1 ቀን ረቡዕ እለት ነበር፡፡ አይሁዳውያንም የአዲሱን አመት መቀበያ የሮሽ ሀሻና በአላቸውን ያከበሩት አንድ ሳምንት ቀደም ብለው ነሐሴ 29 ቀን ረቡዕ እለት ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ከአስር ቀን በኋላ በታላቅ ስነስርአት የሚያከብሩት “መስቀል” የተሰኘ ክብረበአል አላቸው፡፡
አይሁዶችም ዬምኪፑር (አስተሰርዬ) የተሰኘውን ታላቅ ክብረ በአላቸውን አዲሱ አመት በገባ ወይም በቲሸሪ አስረኛው ቀን ላይ በታላቅ ሃይማኖታዊ ስነ ስርአት ያከብራሉ፡፡
እነዚህ ሁለት ጉዳዮች የቀረቡት የዚህን አመት ግጥምጥሞጽ ለማመልከት ብቻ ነው፡፡ የእስራኤል የቀን አቆጣጠር በጨረቃ ኡደት ላይ የተመረኮዘ ስለሆነ የሮሽ ሀሻና በአል አንዳንዴ ጳጉሜ ላይ፣ አንዳንዴ መስከረም መጀመሪያ ላይ ወይም መስከረም አጋማሽ ላይ፣ በጣም ሲረዝም ደግሞ መስከረም መጨረሻ ላይ ይውላል እንጂ እንደ ኢትዮጵያውያን አሊያም እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠሮች የተወሰነ አይደለም፡፡
የሆነ ሆኖ ምንም እንኳን ኢትዮጵያውያንና አይሁዳውያን በአንድ ሳምንት ልዩነት አዲስ አመት ቢቀበሉም የአቀባበል ስርአታቸውን የሚያከብሩት እንደየራሳቸው ባህል፣ ወግና ሃይማኖታዊ ስርአት መሠረት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ቤተእስራኤሎችን ጨምሮ አይሁዳውያን የአዲሱን አመት መቀበያ የሮሽ ሀሻና በአላቸውን ያከበሩት ወይም የሚያከብሩት በሚከተለው አኳኋን ነው፡፡
ሮሽ ሀሻና ፈጣሪ አምላክ መላ አይሁዳውያንን በታላቅ ስነስርአትና፣ ሀይማኖታዊ መገዛት እንዲያከብሩት የአይሁዶች ቅዱስ መጽሀፍ በሆነው በቶራህ (ኦሪት) ካዘዛቸው አምስት ዋና ዋና በአላቶች (ዬምኪፑር፣ ሱከት፣ ፔሳህና፣ ሻሾች) አንዱ ነው፡፡
ሮሽ ሀሻና የሚለው የእብራይስጥ ቃል ተራ ትርጉሙ ሲተነተን እንዲህ ነው፡፡ ሮሽ ማለት ራስ ማለት ነው፡፡ ሀሻና ማለት ደግሞ አመት፣ ዘመን ማለት ነው፡፡ ጠቅለል ባለ አነጋገር ሲተረጐም ደግሞ “የአመቱ ራስ” ማለት ነው፡፡ የዚህ ቃል ጥልቅ ትርጉምና ትንታኔ ደግሞ “አኑመዲ” ወይም በኦሪት ዘፍጥረት 1÷5 “ብርሀን ይሁን አለ፡፡ ብርሀንም ሆነ” በሚል የተጠቀሰውን የአለምን መፈጠር ያመላክታል፡፡
ሮሽ ሀሻና በምድረ እስራኤል የሚኖሩ አይሁዶች ለአንድ ቀን፣ በመላው አለም ተበትነው የሚኖሩት አይሁዶች ደግሞ ለሁለት ቀናት ያከብሩታል፡፡ በዚህም መሠረት የዚህን አመት ሮሽ ሀሻና ክብረ በአል እስራኤል ውስጥ የሚኖሩ አይሁዶች ረቡዕ ነሀሴ ሀያ ዘጠኝ ቀን ሲያከብሩ ከእስራኤል ውጪ ያሉት ደግሞ ከነሀሴ 29 ፀሀይ ግባት ጀምረው እስከ አርብ ጳጉሜ አንድ ውድቅት ድረስ በሞቀ ስሜትና በአዲስ መንፈስ አክብረዋል፡፡
በመላው አለም የሚኖሩ ህዝቦች እንደየባህልና ወጋቸው አዲስ አመትን ሲያከብሩ ያለፈውን አመት ስኬትና ውድቀታቸውን በትዝታ እየቃኙ በመገምገም፣ በአዲሱ አመት አዲስ ነገር ለመፈፀም በአዲስ መንፈስ ሲነሳሱ ማየትና መስማት የሰው ልጅ ሰው ሆኖ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የነበረ ክስተት ነው፡፡ አይሁዳውያንም ከተቀረው የአለማችን ህዝቦች የተለዩ አይደለምና በሮሽ ሀሻና በአላቸው ላይ ያለፈውን አመት ስኬት በአዲሱ አመትም ለመድገም ወይም ያለፈውን አመት ውድቀታቸውን በአዲሱ አመት ሲሆን በስኬት ለመለወጥ አሊያም ላለመድገም በሞቀ ስሜትና በአዲስ መንፈስ ይነሳሳሉ፡፡
በሮሽ ሀሻና ቀን ወይም ከዋዜማው ምሽት ጀምሮ የሚቀርበውና የሚበላውም የምግብ አይነቶች የአሳ ራስ (ጭንቅላት) ማር በዳቦና በማር የተነከረ አፕል ናቸው፡፡
እነዚህ ሶስት የምግብ አይነቶች ራሳቸውን የቻሉ ልዩ ትርጉም አላቸው፡፡ የአሳው ራስ የሚቀርበው በአዲሱ አመት አምላካችን ለመልካም ነገር ሁሉ ራስ ያድርገን ለማለት ሲሆን ዳቦ በማር የሚቀርበው ደግሞ በአዲሱ አመት አምላካችን ህይወታችንን እንደ ማር የጣፈጠ ያድርግልን፣ በቶራህ ልባችንን ደስ ይበለው ወይም አምላካችን ልባችንን ደስ ያሰኘው ለማለት ነው፡፡ በማር የተነከረ አፕል የሚበላውም ፈጣሪ አምላክ መጭውን ህይወታችን እንደ ማር የጣፈጠ፣ እንደ አፕል አስደሳችና ረጅም ወይም ያልተቋረጠ (አፕል ክብ ስለሆነ) ያድርግልን ለማለት ነው፡፡
ከምግቡ ስነ ስርአት ቀጥሎ በእለቱ የሚከናወነው ሌላኛው ሀይማኖታዊ ስርአት የ “ሾፋር” ወይም ቀንደ መለከት የመንፋት ስርአት ነው፡፡ በዚህ የሮሽ ሀሻና በአል ላይ የሚነፋው ሾፋር የሚሠራው ቢያንስ አንድ ዙር ከተጠመዘዘ የራም ወይም የከነአን አካባቢ ሙክት በግ ወይም ፍየል ቀንድ ነው፡፡
የቀንዱ መጠማዘዝ ታላቁ የእስራኤላውያን አባት አብርሀም ልጁን ይስሀቅን ፈጣሪ አምላክ እንዳዘዘው ሊሰዋው ባለ ጊዜ አምላክ ያደረገውን ለማስታወስ ነው፡፡
ሾፋርን የመንፋት ስነ ስርአቱ የሚከናወነው በሶስት የአነፋፍ ስልት ነው፡፡ “ሐዘኑ” ወይም ፀሎቱን የሚመራው ራባይ ወይም በቤተእስራኤሎች ዘንድ ቄሱ፣ አሊያም እንደሚገባ አድርጐ መንፋት የሚችል ሌላ ማንኛውም ሰው አጠገቡ ቆሞ ቶራህን የሚያነበውን ሰው የአነባበብ ስልት በመከተል ይነፋል፡፡
በሮሽ በአል ወቅት ከሞላ ጐደል ሾፋር እየተነፋ ዘወትር የሚነበበው የቶራህ ክፍል፣ ፈጣሪ አምላክን በፍፁም ልብና ታማኝነት የመታዘዝን አስፈላጊነትና በእምነት የመጽናትን ፀጋ ለማስረዳት በኦሪት ዘፍጥረት 22÷2-15 የቀረበው የአብርሀምና የልጁ የይስሀቅ ታሪክ ነው፡፡
ሮሽ ሀሻና በሚከበርበት እለት “ሴፈር ቶራህ” ወይም “የኦሪቱ ጥቅል” እንዲወጣ ከተፈለገ “ማኒያን” ወይም ኮረም መሙላት የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ አንድ ማኒያን እንዲሞላ የሚያስፈልጉት አስርና ከአስር በላይ ሰዎች ናቸው፡፡ ሰዎቹ ዘጠኝ ቢሆኑ እንኳ ሴፌር ቶራህ በፍፁም መውጣት አይችልም፡፡
ሮሽ ሀሻና በሚከበርበት እለት ማንኛውም አይሁዳዊ ምንም አይነት ስራ መስራት አይችልም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ከስራ ቁሳቁሶችና ከስራ ቦታ አካባቢም ዝር እንዲል ፈጽሞ አልተፈቀደለትም፡፡
በዚህ ቀን ማድረግ የሚችለው መልካም ምኞታቸውን ለመግለጽ ወደ መኖሪያ ቤቱ የመጡትን በመልካም ሁኔታ ተቀብሎ ማስተናገድ አሊያም ወደ ምኩራብ ጐራ ብሎ በዚያ ለፈጣሪ አምላክ ምስጋና ማቅረብና መፀለይ ብቻ ነው፡፡
በዚህ በሮሽ ሀሻና ክብረበአል ይሁዲዎች እርስ በርስ ሲገናኙ “ሻና ቶቫ” መልካም አዲስ ዓመት ወይም “ሻና ቶቫ ቭሚቡራሸት!” መልካም አዲስ አመት ከአምላክ በረከት ጋር! ወይም ደግሞ በረጅሙ “ሻና ቶቫ ቴካቴቭ ቭትሀቲሙ!፡- ለመልካሙ ዘመን በህይወት መጽሀፍ ታተሙ! ይባባላሉ፡፡
ቀደም ብዬ እንደ ገለጽኩት፤ ኢትዮጵያውያን በተለይም የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑት እንቁጣጣሽ ወይም ቅዱስ ዮሀንስ የተሰኘውን የአዲስ አመት ክብረ በአላቸውን ካከበሩ በኋላ ቀጥለው ለሚያከብሩት የመስቀል በአል መዘጋጀት ይጀምራሉ፡፡ አይሁዳውያን ደግሞ የሮሽ ሀሻናን ክብረ በአል ካከበሩ ከጥቂት ቀናት በኋላ የሚከተለውን የዮምኪፑር (የመስተሰርየት) በአልን በታላቅ ስነስርአት ለማክበር በሚገባ መዘጋጀት ይጀምራሉ፡፡
የሮሽ ሀሻና በአል አከባበር ግን ይህንን ይመስላል፡፡ በመጨረሻ ሁላችሁንም “ሻና ቶቫ ቭሚቡራሸት!” እላችኋለሁ፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ
  • በአዲስ አበባና በአዳማ 20 ቅርንጫፎችና 52 ማከፋፊያዎች 
  • በቃሊቲ ትልቅ የዳቦ ማምረቻ ኢንዱስትሪ 
  • በአዳማ የዱቄት ፋብሪካ 
  • ሴንትራል ማተሚያ ቤት - እህት ኩባንያ

              በአዲስ አበባ ሆነ በክልል ከተሞች እያወቅን የማናውቃቸው (ስማቸውን እያወቅን አመሠራረትና ታሪካቸውን የማናውቅ) ብዙ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች አንዱ ሸዋ ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ ነው፡፡ በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ቢጓዙ፣ ሸዋ ዳቦን ወይም ማከፋፈያውን አያጡም ማለት ይቻላል፡፡ አባ ኮራን፣ ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ፣ ቃሊቲ፣ ወይራ ሰፈር፣ አየር ጤና፣ ቦሌ፣ ገርጂ፣ ጀሞ፣ ቄራ፣ … ሸዋ ዳቦን ወይም ማከፋፈያውን ያገኛሉ፡፡
ሸዋ ዳቦን ከ54 ዓመት በፊት በ1951 ዓ.ም (ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ማለት ነው) በተለምዶ አባኮራን በመባል በሚጠራው ሰፈር፣ የመጀመሪያዋን ዳቦ ቤት በመክፈት ሥራ የጀመሩት፤ የዛሬው የ83 ዓመቱ አረጋዊ አቶ ዘሙይ ተክሉ ናቸው፡፡ ሸዋ ዳቦ የግል ቢዝነስ ቢሆንም መሥራቹ በጡረታ ተገልለው፣ በእግራቸው ልጆቻቸው ተተክተዋል፡፡ አሁን ድርጅቱን የሚመሩት ልጆቻቸው ናቸው፡፡ አቶ ዘሙይ እንደቀድሞው ተሯሩጠው ባይሰሩም፣ በረዥም ዘመን ያካበቱትን ልምድ ልጆቻቸውን በማማከር እውቀታቸውን እያካፈሉ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ሸዋ ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ ኃ.የተ.የግ.ማኅበርን፣ በዋና ሥራ አስኪያጅነት የሚመሩት የአቶ ዘሙይ የበኩር ልጅ አቶ ፀሐይ ዘሙይ ናቸው፡፡ አቶ ፀሐይን ሸዋ ዳቦ እንዴት እንደተመሠረተ፣ በስንት ብር ካፒታልና ሠራተኛ ሥራ እንደጀመረ፣ አሁን ካፒታሉ ስንት እንደደረሰ፣ እንዴት እየሠራ እንደሆነና የወደፊት ዕቅዱን ማወቅ ፈልገን፣ ሸዋ ዳቦ እንዴት ተመሠረተ? አልናቸው፡፡
አሁን በተለምዶ ጎጃም በረንዳ እየተባለ ከሚጠራው ሰፈር ዝቅ ብሎ፣ አባ ኮራን እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ካለው ቤንዚን ማደያ አጠገብ፣ የአንድ ኢጣሊያዊ ትንሽ ዳቦ ቤት ነበረች፡፡ አባቴ ከአሥመራ እንደመጡ፣ እዚያች ዳቦ ቤት በኃላፊነት ተቀጥረው ይሠሩ ነበር፡፡ ጣሊያኑ አርጅቶ መሥራት ሲያቅተው፣ አቶ ዘሙይ ያቺን ዳቦ ቤት ከጣሊያኑ ገዝተው ማምረት ጀመሩ፡፡

በምን ያህል ነበር የገዙት?
ከ5ሺህ ብር ጥቂት ከፍ ባለ ትንሽ ካፒታል ነበር የገዙት፡፡ እሳቸው ሥራ በጀመሩበት ጊዜ፣ ዳቦ ቤቷን ከገዙበት በተጨማሪ ገንዘብ አልነበራቸውም፡፡ ሥራ ማካሄጃው፣ ከዘመድ ከወዳጅ፣ በብድር የተገኘ ነበር፡፡ ሥራ ለመጀመር፣ ለዱቄት መግዣ የሚሆን ገንዘብ ስለቸገራቸው፣ አቶ ሰይድ አህመድ የተባሉ ወዳጃቸው ነበር ያበደሯቸው፡፡ ከዚያም ያለ ዕረፍት ሌት ተቀን ጥርሳቸውን ነክሰው በመሥራት ዕዳቸውን ከፈሏቸው፡፡
አባቴና እናቴ ወ/ሮ ውቧ ሀብተየስ፣ ከወዳጅና ከዘመድ የወሰዱትን ገንዘብ ከከፈሉ በኋላ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ጠንክረው በመሥራት ፒያሳ፣ ከማዘጋጃ ቤት የኋለኛ በር በታች አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት አካባቢ፣ 2ኛውን የሸዋ ዳቦ ቅርንጫፍ ከፈቱ፡፡ ከዚያም አምስት ኪሎ ከቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት 3ኛውን ቅርንጫፍ፣ 4ኛውን ደግሞ በደጃዝማች በላይ መንገድ ወደ አዲሱ መንገድ አካባቢ እያሉ ቀጠሉ፡፡ እንደዚያ እያደረጉ፣ የቅርንጫፎቻቸውን ቁጥር 7 አደረሱ፡፡
ሥራ ሲጀምሩ ምን ያህል ሠራተኛ ነበራቸው? አሁንስ ስንት አሉ?
እርግጠኛ ባልሆንም ከ20 የሚበልጡ አይመስለኝም፡፡ ዳቦ ሥራ ላይ ብዙ ጊዜ ሰው ይቀያየራል፡፡ ምርት ላይ፣ በማከፋፈል፣ በጉልበት ሥራ፣ … የተሰማሩ ሠራተኞች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ይለዋወጣሉ፡፡ ይህ የዳቦ ቤት ባህርይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በየጊዜው የሠራተኛ መቀያየር ዛሬም አለ፡፡
በዚያን ጊዜ ከሸዋ ዳቦ ቤት ሌላ አልነበረም እንዴ?
በወቅቱ የተከፈቱ ሌሎች ዳቦ ቤቶችም ነበሩ፡፡ ግን በውድድሩ እየተሸነፉ ወጡ፡፡ እውነት ለመናገር በዚያን ጊዜ ከተጀመሩ ዳቦ ቤቶች በአሁኑ ወቅት ያሉት አንድ ወይም ሁለት ናቸው፡፡ እነሱም ቢሆኑ ውጤታማ የሆኑ አይመስለኝም፡፡
ከዚያስ የአቶ ዘሙይ ጥረት ምን ደረሰ?
ቀጠለ፡፡ እንደዚያ እየሠሩ ሀብት፣ የሠራተኞች ቁጥርና የቅርንጫፎች ብዛትም እየጨመረ ሄደ፡፡ እስካሁን ያወራነው በንጉሡ ዘመን የነበረውን ነው፡፡ ከዚያም ደርግ ሥልጣን ሲይዝ በ47/67 አዋጅ ብዙ ንብረታቸው ተወረሰ፡፡
ምን ምን ተወረሰባቸው?
ያው፣ እንደማንኛውም ዜጋ ነበር የተወረሰው፡፡ በዚያን ጊዜ አዳማ ላይ የዱቄት ፋብሪካ አቋቁመው ነበር፡፡ በቀላጤ ነው የተወረሰባቸው፡፡
ቀላጤ ምንድነው?
በትንሽ ደብዳቤ ማለት ነው፡፡ በቦሌ መንገድ ከኦሎምፒያ ፊት ለፊት አሁን ጌቱ ኮሜርሻል ሕንፃ ካለበት ፊት ለፊት ያለው ዳቦ ቤትና ሕንፃው የእሳቸው ነበር፤ ተወረሰ፡፡ እዚያ ያለው ዳቦ ቤት ሲመለስላቸው ሕንፃው ግን እንደተወረሰ ቀረ፡፡ አባ ኮራን ያለውም ሕንፃ ተወረሰ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም። ሌሎች በርካታ ንብረቶችም ተወርሰውባቸዋል፡፡ በዚህ ዓይነት ብዙ ፈተናዎች ተደቀነባቸው፡፡ የባንክ ዕዳ ነበረባቸው፤ ብዙ ችግር ወደቀባቸው፡፡
ታዲያ ምን አደረጉ? ተስፋ ቆርጠው ተቀመጡ?
እንዲያውም! ያ ሁሉ ችግር አልበገራቸውም፡፡ በዚያ ሁሉ በደል ሞራላቸው ሳይወድቅና ሳይጨናነቁ ሥራውን ቀጠሉ፡፡ ከአንድ እናትና ከአንድ አባት የተወለድነው 13 ልጆች በሙሉ የምንኖረው ውጭ አገር ነበር፡፡ ዕድሜአችን እየጨመረ ለሥራ ስንደርስ ወደ አገር ቤት ተመለስን፡፡ በዚያን ጊዜ የአባታችን ዕድሜ እየገፋ ነበር፡፡ ስለዚህ እሳቸውን አሳርፈን እኛ በእግራቸው ተተክተን መሥራት ቀጠልን። እሳቸውም በረዥም ዘመን ባካበቱት ልምድ እየመከሩንና እየመሩን እስካሁን ዘልቀናል፡፡
የአዳማው የዱቄት ፋብሪካ እንደተወረሰ ቀረ?
አይ! ተከራክረን አስመልሰናል፡፡ አሁን ለራሳችን የሚያስፈልገንን ዱቄት የምናስፈጨው እዚያ ነው። ፋብሪካው የሚፈጨው ዱቄት ብቻ ስለማይበቃን መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ከውጭ እየገዛ የሚያመጣውን ስንዴ ገዝተን እያስፈጨን እንጠቀማለን፡፡
የውጭ ስንዴ የምትጠቀሙ ከሆነ ዋጋችሁ ውድ ነው ማለት ነው?
አይደለም፡፡ መንግሥት፣ ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ኑሮው እንዳይከብደው ለመደጐም ብሎ ያመጣው ስለሆነ በስንዴዉም በዱቄቱም በዳቦውም ላይ የዋጋ ጣሪያ (Price Cap) ተቀምጧል፡፡ ከዚያ አስበልጠን መሸጥ አንችልም፡፡ በዚያ ነው እየተሠራ ያለው፡፡
አከፋፋይ የተባሉት ፍራንቻይዝ ያደረጋችሁት ነው?
እንደሱ አይደለም፡፡ ከእኛ ጋር በኮሚሽን የሚሠሩ ማለት ነው፡፡ እነዚህ በኮሚሽን የሚሠሩ ሰዎች የራሳቸውን የዳቦ መሸጫ ያዘጋጃሉ፡፡ ቤቱ የግዴታ ሰፊና የእኛን ቅርንጫፎች መስፈርት ማሟላት የለበትም፡፡ ዓላማው ምንድነው? ብትል፣ ኅብረተሰቡ በየአቅራቢያው ትኩስ ዳቦ ማግኘት አለበት ከሚል የመጣ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ እኛ ያደረ ዳቦ አንሸጥም፣ አያድርምም፡፡ ምናልባት መሽቶ ካደረም፣ እናደርቀውና ለኮተሌት መሥሪያ እንጠቀምበታለን፡፡)
አንድ ሰው አከፋፋይ መሆን ከፈለገ፣ ቤት ይከራያል፣ ሠራተኛ ይቀጥራል፣ ካውንተሮች ያዘጋጃል፡፡ ከዚያም ለእኛ ያሳየናል፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ከሆነ ከእኛ ዳቦ ወስዶ ይሸጣል፤ እኛ 10 በመቶ ኮሚሽን እናስብለታለን፡፡ ይህ አሠራር ብዙ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ አንድ ሰው በሁለትና በሦስት ሺህ ብር ተቀጥሮ ከሚሠራ፣ ከእኛ ዳቦ እየወሰደ ቢሸጥ የበለጠ ይጠቀማል፡፡ በአገራችን የቤት አስተዳዳሪው ይሠራል፣ ሌሎች የእሱን እጅ ይጠብቃሉ፡፡
የቤት እመቤት የሆኑት ሴቶች ግቢያቸው ወይም በአቅራቢያቸው ፅድት ያለ ቤት ሠርተው ወይም ተከራይተው ከእኛ ዳቦ ወስደው ይሸጣሉ። በዚህ ዓይነት ገቢ ይፈጥራሉ፡፡ ከአባወራው ጋር ተደጋግፈው ቤተሰብ ያስተዳድራሉ፡፡ ብዙዎች በዚህ ዓይነት ይተዳዳራሉ፤ እኛም ከችርቻሮ ንግድ መውጣት እንፈልጋለን፡፡ እነዚህ አከፋፋዮች እስካሁን ችግር ስላላገኘንባቸው ቀጣይ ዕቅዳችን ከችርቻሮ ንግድ ወጥተን ወደ ዳቦ ኢንዱስትሪ መግባት ነው፡፡
አከፋፋዮች የሚሸጡበት ዳቦ የእናንተን የጥራት ደረጃ ማሟላቱን እንዴት ነው የምትቆጣጠሩት?
እንደገለጽኩት እነሱ ዳቦ አይጋግሩም - ከእኛ ወስደው ነው የሚሸጡት፡፡ እየተዘዋወሩ የሚቆጣጠሩ ሱፐርቫይዘሮች አሉን፡፡ የሌላ ዳቦ ቤት ዳቦ እንዳያስገቡና ከዳቦ ጋር የማይስማማ ነገርም ጨምረው እንዳይሸጡ ይቆጣጠራሉ፡፡ ለምሳሌ ከእኛ ዳቦ ጋር ወተት እንዲሸጡ አንፈቅድላቸውም። ምክንያቱም በፆም ጊዜ ወተት መኖሩን ከሃይማኖት ጋር የሚያያይዙ ሰዎች ስላሉ ደስ ላይላቸው ይችላል። ሌላው ደግሞ ወተት ዝንብ የመሳብ ባህርይ አለው። በዚህ ረገድ ወተት ታሽጐ ስለሚቀርብ ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ ዳቦ ግን እንዲሁ ነው የሚሸጠው፡፡
ለምን እናንተ ዳቦ አሽጋችሁ አታቀርቡም?
ልክ ነው፡፡ በውጭ አገር ዳቦ ታሽጐ ነው የሚቀርበው፡፡ እኛም ሞክረን ነበር፡፡ ሰው ግን የታሸገ ዳቦ የቆየ ስለሚመስለው እሺ አይልም፡፡ እኛማ የሚቀለን እሱ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሰዓት የተጋገረ ዳቦ አሸግንና እንዲሁ አቅርበን የታሸገውን ስንሰጠው አይገዛም፡፡ “ከዚያኛው ከትኩሱ ስጠኝ” ይላል። ዳቦ ሲታሸግ ከዝንብና ላዩ ላይ ከሚያርፍ ቆሻሻ ነገር ይጠበቃል፡፡ ሕዝቡ እንቢ አለ እንጂ ሞክረን ነበር፡፡ ወደፊት ኅብረተሰቡ የአመለካከት ለውጥ ያደርግና ሁሉም ዳቦ ቤቶች ዳቦ አሽገው ያቀርባሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኛ ግን አሁንም ቢሆን አሽገን የምናቀርባቸው ምርቶች አሉን፡፡
ቁጥጥር ስናደርግ ከሌላ ቦታ ረከስ ባለ ዋጋ ጥራቱ አነሰ ዳቦ አስገብተው ሲሸጡ ያገኘናቸው አከፋፋዮች አሉ፡፡ እነሱን ዘግተናቸዋል፡፡ የዳቦ ጥራት የሚታወቀው በግብአቱ ነው፡፡ የማይሆን ርካሽ ዘይት ይጠቀሙና ጣዕሙን ያበላሹታል፡፡ የተሻለ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ደግሞ እርሾ፣ ዘይት፣ … የሚቀንሱ አሉ፡፡ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ዱቄት ሳይቀር የሚጠቀሙ አሉ፡፡ እኛ ግን ትርፋችን የፈለገውን ያህል ይቀንስ እንጂ እንደዚህ አናደርግም።
ሸዋ ዳቦ ምን ያህል ሠራተኛ አለው?
ሲጀመር ከ20 እና ከ30 አይበልጡም ነበረ፡፡ አሁን ግን ከአንድ ሺህ በላይ ቋሚ ሠራተኞች አሉን - በዳቦና በዱቄቱ ማለት ነው፡፡
የሸዋ ዳቦ የስኬት ምስጢር ምንድነው?
ማንኛውም ሥራ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ በተለይ ምግብ ነክ ሲሆን የበለጠ ትኩረት ይፈልጋል፡፡ እኛ የምናመርተው ዳቦ የት ይሄዳል? ማን እጅ ይገባል? ብሎ ማሰብ ይፈልጋል፡፡ ሸዋ ዳቦ፣ በጥራት ጉዳይ ላይ በፍፁም ድርድር አያውቅም፡፡ ዱቄት ስንገዛ ተጠንቅቀን ነው፡፡ ስንዴም ከገዛን መጀመሪያ ሞክረን ነው፡፡ ትርፍ ለማብዛት ብለን ያገኘነውን አንገዛም፡፡ እርሾም ስናስመጣ ጥራቱ የተጠበቀና መጨመር ያለበት መጠንም መቀነስ የለበትም። ጨውም ሆነ ዘይት እንዲሁም ሌሎች ግብአቶች ጥራታቸው የተጠበቀ ነው የምንጠቀመው፡፡ ለምሳሌ የምንጠቀመው ዘይት 1ኛ ደረጃ ነው፡፡ ጥራቱን ያልጠበቀ ዘይት በፍፁም አንጠቀምም፡፡
ዘይት ለባትራው (ለመጋገሪያው) ነው?
አዎ! ለባትራው ብቻ ሳይሆን በተወሰነ መጠን ላይ ይጨመራል፡፡ እህሉን እያየን ነው የምንጨምራቸውን ነገሮች ፐርሰንቴጅ የምንወስነው። ለምሳሌ ውሃ የማያነሳና የሚያነሳ እህል አለ፡፡ የሚያነሳው ላይ ጨው ስንጨምር ተጠንቅቀን ነው፡፡ ዝም ብለን ጥሬውን ጨው አንጨምርም፡፡ በውሃ አሟሙተንና አጣርተን ነው፡፡ ምክንያቱም ዝቃጩ አሸዋና ሌላም ነገር ስለማያጣ ተጠንቀቀን ነው፡፡
የዳቦ ዋጋ ከጫማ ማስጠረጊያ ዋጋ በታች ነው። ከእንጀራ ጋር ካየነው ደግሞ አንድ እንጀራ ከዳቦ ዋጋ ከሦስት እጥፍ በላይ ይበልጣል። ሁለቱን ስናስተያይ ግን ምንም የጥራት ለውጥ የለም፡፡ እንዲያውም ዳቦ የሚበልጥበት ጊዜ አለ፡፡ ስለዚህ የእኛ የስኬት ምስጢር ታማኝነት፣ ጥራትና አቅርቦት ነው፡፡ አቅርቦት ካልተሟላ ገንዘብ እያለህ መግዛት አትችልም፡፡ የአባቴ የዳቦ ባለሙያነት፣ ሥራ ወዳድነት፣ ጥንካሬና ታታሪነት ሳይዘነጋ ማለቴ ነው፡፡ አቶ ዘሙይ ዳቦውን በማየት ብቻ ይኼ ነገር ጐድሎታል የሚሉ ባለሙያ ናቸው፡፡ እኛም ከእሳቸው ተምረን የማንኛውንም ዳቦን ጥራትና ደረጃ በማየት ብቻ እንለያለን፡፡ በዓመት 365 ቀናት እየሠራን ነው፡፡ ሱቆቻችን ከንጋቱ 11 ሰዓት እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ለሸማቾች ክፍት ናቸው-በዓል ሆነ አልሆነ ሸዋ ዳቦ ከተከፈተበት ዕለት ጀምሮ በር ዘግተን አናውቅም፡፡
ሠራተኞቻችሁ በአስተዳደሩ ምን ያህል ደስተኞች ናቸው?
ሠራተኞቻችን ዋነኞቹ የስኬታችን ምንጮች ናቸው፡፡ ሠራተኞቻችን ደከመን ሰለቸን ብለው አያውቁም፡፡ ሌሊትም ቀንም እንሠራለን፡፡ ሌሊት ሽያጭ የለም እንጂ ከተለያዩ ድርጅቶች (ከሆስፒታሎች፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከጦር ካምፖች…) ትዕዛዝ እንቀበላለን፡፡ እኛም ሠራተኞቻችን ምስጋና ይግባቸውና አናሳፍርም፤ በትዕዛዙ መሠረትና በተጠየቅነው ጊዜ እናቀርባለን-የቱንም ያህል ትዕዛዙ ብዙ ቢሆን፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ከ30 ዓመት በላይ የሠሩ ሠራተኞች አሉ፡፡ ይህን ያህል ጊዜ አብረውን የቆዩት በአስተዳደራችን ደስተኛ ስለሆኑ ይመስለኛል።
የአንድ ሠራተኛ ትንሹና ትልቁ ደሞዝ ምን ያህል ነው?
የተለያየ ደረጃ አለ፡፡ ገና ምንም የማያውቅ ሰው ሲቀጠር (Starting Salary) ከ700 ብር በላይ ነው። ትልቁ ደግሞ ከ8ሺህ በላይ ነው፡፡ ከሙከራ ጊዜ በኋላ ደግሞ ይጨመርለታል፡፡ በዋጋ ግሽበቱ የተነሳ ኑሮ ስለተወደደ ሁለት ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ከ200 ፐርሰንት በላይ የደሞዝ ማስተካከያና ጭማሪ አድርገናል፡፡ ከትርፍ ጋር የተያያዘ ሳይሆን በኅብረት ስምምነታችን መሠረት በዓመቱ መጨረሻ ቦነስ እንሰጣለን፡፡
የወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድነው?
አሁን በጀመርነው የዳቦ ኢንዱስትሪ መቀጠል ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ወደ ኩኪስ መግባት እንፈልጋለን። ፓስታና ማካሮኒም ለማምረት ዕቅድ አለን፡፡ የስንዴ እርሻም ለመጀመር ሐሳቡ አለ፡፡ አረማመድን በጥንቃቄ ካልመሩ በስተቀር እንደፈለጉ መንቀሳቀስ ጥሩ ስለማይሆን ከአቅማችን በላይ አንሄድም፡፡ ሁሉንም ባይሆን ከ95 በመቶ በላይ ሠራተኞቻችንንና ደንበኞቻችንን ያስደስት ይመስለናል፡፡ ስለዚህ እስካሁን አብረውን የተጓዙትን እናመሰግናለን፤ እናከብራለን፡፡
ለዱቄት የምንጠቀምባቸው ሁለት የጭነት መኪኖች፣ ውስጣቸው በሞላ በአሉሚኒየምና በደረቅ ስፖንጅ የተሸፈነ ዳቦ በየቦታው የምናመላልስባቸው 8 መኪኖች አሉን፡፡ እነዚህን ረዥም ጊዜ አንጠቀምባቸውም፡፡ በሁለትና በሦስት ዓመት እንቀያይራቸዋለን፡፡ ሸዋ ዳቦ የራሱ ሪል እስቴትም ብዙ አለው፡፡ በአዳማም ብዙ ንብረቶች አሉን፡፡
በአሁን ሰዓት ሸዋ ዳቦ ካፒታሉ ምን ያህል ነው?
ቁጥሩ በእጄ የለም፡፡ ግን እጅግ ብዙ ነው ብዬ ብደመድም ጥሩ ነው፡፡ የተሳሳተ ቁጥር ባልናገር ይሻላል፡፡

አቶ ተፈራ የኋላወርቅ በባህርዳር አካባቢ በሚገኝና “መሸንቲ” በተባለ የገጠር መንደር የተወለዱ የገበሬ ልጅ ናቸው፡፡ በቴክስታይል እና በማይኒንግ ኢንጅነሪንግ ሁለት ዲግሪ ያላቸው አቶ ተፈራ፤ በሞስኮ ከተማ “አቬኑ አፍሪካ” በተባለ የራሳቸው ባርና ሬስቶራንት ማናጀር ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ግሩም ሠይፉ 14ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመዘገብ ወደ ሞስኮ በሄደበት ጊዜ አግኝቶ አነጋግሯቸዋል፡፡ ቃለምልልሱን እነሆ:-

ራሺያ ከመግባትዎ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ሰርተዋል?
ራሺያ ከመጣሁ እነሆ 27 ዓመታት አልፈዋል፡፡ በ1986 እ.ኤ.አ በደርግ ስርዓት የመጣሁት፡፡ በግሌ ባገኘሁት የነፃ ትምህርት ዕድል ከባህርዳር ፖሊቴክኒክ በቴክስታይል ኢንጂነሪንግ ተመርቄያለሁ፡፡ ይህን ትምህርት ከጨረስኩ በኋላ በአዲስ አበባ ለስድስት ወራት ያህል እንደሰራሁ ለኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ተከላ ከተመረጡ ሠራተኞች አንዱ ነበርኩ፡፡ የባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ፣ የተግባረዕድና የዊንጌት ተማሪዎችም ለተመሳሳይ ተግባር ተመድበው ነበር፡፡ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካው መሣሪያዎች ከውጭ የገቡ ሲሆን በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችን በመትከል ልምድ ካላቸው አፍሪካውያን ጋር ሆነን ሰርተናል፡፡ የደርግ ባሰስልጣናት የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካን ለ10ኛው አብዮት በዓል አድርሱ የሚል ትዕዛዝ ሰጥተውን ነበር፡፡ በአስቸኳይ ትዛዝ ውስጥ ሆነን ሙሉ ፈረቃ ስንሰራ ሽንት ቤት ለመሄድ እንኳን በተራ ነበር፡፡
የፋብሪካውን ተከላ ለመጨረስ የተሰጠን ጊዜ አራት ዓመት ነበር፡፡ በዚያን ሰዓት በዲፕሎም ከቴክኒክ ትምህርት ቤት የተመረቀ ለመንግስት አገልግሎት ለሁለት ዓመት የመስራት ግዳጅ ነበረበት፡፡ እኔ ደግሞ ትምህርቴን በውጭ አገር ለመቀጠል ፍላጐት ነበረኝ፡፡ ግዳጁን ባለመጨረሴ ግን አልቻልኩም፡፡ ነፃ የትምህርት ዕድል ለማግኘት የግዴታ የአኢወማ አባል መሆን እንዳለብኝም ተነገረኝ፡፡ በዚያን ጊዜ የዩኒቨርስቲ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና ምሩቃን የአኢወማ አባል መሆን አለባቸው የሚል ግዳጅና ብዙ ጭቅጭቅ ነበረ፡፡
ለኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ተብለን የተመደብነው 56 የፖሊ ቴክኒክ ምሩቃን ነበርን። ምደባው እንደአገራዊ ግዴታ ይታይ ነበር፡፡ ያኔ ደሞዙ 357 ብር ነበር፡፡ ከወጭ ቀሪ ተጣርቶ ወደ 290 ብር ይደርሰናል፡፡ በካምፕ ውስጥ ነበር የምንሰራው፡፡ በኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ተከላ ስሰራ ለመጀመርያ ጊዜ ከቤተሰብ ተለያይቶ መኖር እና የብቸኝነት ህይወት ያየሁበት ጊዜ ነው፡፡ ወቅቱ የረሃብ ነው፡፡ አይኔ እያየ ሰው የሚሞትበት ወቅት ነበር፡፡ ጠዋት ቁርስ ሰጥተናቸው ማታ ስንመለስ ሞተው የምናገኛቸው ሰዎች ነበሩ፡፡
የኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ተከላ በቶሎ እንዲደርስ የተፈለገው ለምንድነው?
የአብዮቱ ፍንዳታ 10ኛ ዓመቱ ስለሆነ፣ ታላላቅ ፋብሪካዎች ግንባታቸው አልቆ ለበዓሉ ጊዜ ስራ እንዲጀምሩ በመፈለጉ ነው፡፡ ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ብቻ አልነበረም፡፡ ሙገር ሲሚንቶ፣ የናዝሬት ትራክተር ፋብሪካ፣ በአጠቃላይ አስር ትልልቅ ፕሮጀክቶች በዚያን ጊዜ ስራ መጀመር ነበረባቸው፡፡ የኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ጣቃዎችን የሚያመርት ነበር፡፡ ፋብሪካው ለምርት ሙሉ ለሙሉ ሳይዘጋጅ ነበር ከአገሬ የመጣሁት፡፡
ከአገር ሊወጡ የሚችሉበት ምን አይነት አጋጣሚ ተፈጠረ?
ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ተከላ ላይ ለአንድ ዓመት እንደሰራሁ የነፃ ትምህርት ዕድል መጥቶ ስለነበር መውጣት ፈልጌ ነበር፡፡ ለወሎ ክፍለሀገር በመጣው ኮታ መስፈርቱን የሚያሟላ ተወዳድሮ ዕድሉን ማግኘት ይችላል ተባለ፡፡ ለመወዳደር ስንመዘገብ ማሟላት የሚገባን ብዙ ቅድመ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ከቀበሌ፣ ከወረዳ፣ ከአውራጃና ከክፍለሀገር ከሚመጡ ዕጩዎች ጋር ነበር ውድድሩ። ሆኖም በወረዳና በክፍለሀገር ደረጃ የነበሩት የአኢወማ መሪዎች የፓርቲ አባል ስለነበሩ ቅድሚያ ይሰጣቸው ነበር፡፡ ስለዚህ እኛ በትምህርት ደረጃ ከፍተኛ ነጥብ ቢኖረንም ዕድሉን ዘጉብን፡፡ እናም በመጀመሪያው ዓመት የመጣ ዕድላችን ተበላሸ። በሚቀጥለው ዓመት የነጻ ትምህርት የምትፈልጉ ሠራተኞች የአኢወማ አባል ካልሆናችሁ መሄድ አትችሉም ተባለ፡፡ ይህንኑ መስፈርት ለማሟላት በአኢወማ አባልነት ተመዘገብንና እኛው ራሳችን ምርጫ አካሄድን፤ በዲፕሎማ የነበረን 2.6 ነጥብ ውጤትና የምንሰራበት መ/ቤት የአገልግሎት ምስክር ወረቀትም ነበረን፡፡ በመጨረሻም የነፃ ትምህርት ዕድሉ ተሳካ፡፡ በመጀመሪያ ጀርመን የመሄድ እቅድ ነበረኝ፡፡ ያኔ ግን ብዙ የነፃ ትምህርት ዕድል የነበረው በሶቭየት ኅብረት ነው፡፡
የነፃ ትምህርት ዕድሉ በሶቪየት ኅብረት ግዛት የት ዩኒቨርሲቲ/ኮሌጅ ነው የተገኘው?
ተወዳድሬ ባሸነፍኩት የነፃ ትምህርት ዕድል መሠረት፣ ከሌሎች ዕድሉን ካገኙ 3ሺ ተማሪዎች ጋር ራሽያ ገባሁ፡፡ ተቋሙም በትልቅነቱ በ2ኛ ደረጃ የሚታወቀው ድሮ “ፓትሪስ ሉቡምባ” ዩኒቨርሲቲ ይባል የነበረው ነው፡፡ ፓትሪስ ሉቡምባ የመጀመሪያውን የኮንጐ ኮምኒስት ፓርቲ ያቋቋመ መሪ ስለነበር ነው የዩኒቨርሲቲው ስያሜ ለእሱ መታሰቢያ ተደርጐ የነበረው፡፡ እኛ በዩኒቨርሲቲው መማር ስንጀምር፣ ከተለያዩ አገሮች በተለይ ሶሻሊስት ከነበሩት የሚመጡ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ እነ ደቡብ አፍሪካ፣ ኩባ፣ ምስራቅ ጀርመን የመሳሰሉት አገራት ተማሪዎችን ይልኩ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲው የሶሻሊዝም ስርዓትን ከሚከተሉ አገራት የሚመጡ ተማሪዎችን የማስተናገድ ትኩረት ነበረው፡፡ ዛሬ ግን ዩኒቨርሲቲው ያኔ የነበረው ኮሚኒስታዊ ትኩረት ተቀይሮ ከመላው ዓለም በርካታ ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያስተምር ሆኗል፡፡ እዚያ ዩኒቨርሲቲ ያለምንም ችግር ገባሁ፡፡ ለመማር የመረጥኩት ትምህርት ማይኒንግ ኢንጂነሪንግ ነበር፡፡
ለመሆኑ ራሽያ ስትገቡ የአገሪቱ አጠቃላይ ገጽታ ምን ይመስል ነበር?
ራሽያ እንደገባሁ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋጨሁት ከአየር ፀባዩ አስቸጋሪ ሁኔታ ጋር ነው፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረው የኮምኒስት ስርዓት ስለነበር፣ የአገሬው ሰው የውጭ ዜጋ ሲያይ ብርቁ ነበር፡፡ አቀራረባቸው እና እንክብካቤያቸው የተለየ ነበር፡፡ የፀጥታ ኃይሎች እኛን የሚተናኮል ሰው ካለ መብታችንን በማስከበር ይደግፉን ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ዘረኝነትም ብዙ አልነበረም፡፡ ግን አንዲት ራሽያዊት ሴት ከጥቁር ሰው ወይንም ከሌላ አገር ዜጋ ጋር ግንኙነት ቢኖራት ያባርሯት ነበር፡፡ የራሽያ ሴቶች ከእኛ ጋር ጓደኛ የሚሆኑት ተደብቀው ነበር፡፡
ከቴክስታይል ኢንጂነሪንግ ሙያ ወደ ማይኒንግ ኢንጂነሪንግ ትምህርት ለመቀየር ለምን ወሰኑ?
ይገርምሃል ያን ጊዜ የቴክስታይል ኢንጂነሪንግ ተምሬ ከተመረቅሁና ከዚያም በኋላ ስራ ስጀምር በዚህ የሙያ ዘርፍ በብዛት የተሰማሩት ሴቶች ነበሩ፡፡ እናም የሴቶች ሙያ እየመሰለኝ ለምን ይሄን የትምህርት መስክ አጠናሁኝ እያልኩ እቆጭ ነበር፡፡ ስለዚህ የኮንስትራክሽንና ሌላ ዓይነት መሠረተ ልማት ላይ የሚያሰማራ ሙያ እፈልግ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የሰው ኃይል የሌለበትና አዲስ የሆነ የትምህርት መስክ ባገኝ እያልኩ አስብ ነበረ፡፡ እናም በማይኒንግ ኢንጅነሪንግ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የተማረ ሰው እንደሌለ በመገንዘቤ፣ በራሽያ ያገኘሁትን የነፃ ትምህርት ዕድል በዚህ የሙያ መስክ አድርጊያለሁ፡፡
ትምህርቴን የጨረስኩት ከ5 ዓመታት በኋላ ነው፡፡ አንድ ዓመት የራሽያ ቋንቋ መማር ግድ ነበር፡፡ የተመረቅኩት በማስተር ኦፍ ሳይንስ¸ኤንድ ኢንጅነሪንግ የዲግሪ መርሐግብር ነው፡፡ ትምህርቱን እንደጨረስኩ ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩ፡፡
ያን ጊዜ በአገር ቤት ያለው ሁኔታ ምቹ ነበር?
ኢትዮጵያ እንደመጣሁ በጠቅላላው የአገሪቱ ሁኔታ እየተቀያየረ ነበር፡፡ የኑሮው ሁኔታ ደስ አይልም፡፡ በዚህ ምክንያት ወደ ራሽያ ተመልሼ ለመስራት ወይም ለመኖር ወሰንኩ፡፡ ተመልሼ ወደ ራሽያ ስገባ ምንም ነገር አልነበረኝም፡፡ በኪሴ የነበረው ይገርምሃል 20 ዶላር ብቻ ነበር፡፡ ዋናው የተማመንኩበት ነገር ትምህርቱን እንደጨረስኩ ሚስት ማግባቴ ነው፡፡ ባለቤቴ ራሽያዊት ናት። እሷን ከማግባቴ በፊት እንግሊዝ አገር ለመሄድ የምችልበትን ዕድል አግኝቼ ቪዛ ሁሉ አስመትቼ ነበር፡፡ ራሽያዊቷን ባለቤቴን ትቼ ወደ እንግሊዝ መሄዱን ስላልፈለግሁት በራሽያ ኑሮዬን ለመቀጠል ወሰንኩ፡፡ በርግጥ በዚያን ወቅት በራሽያ የነበረው አጠቃላይ ሁኔታና አስተሳሰብ ተቀይሯል፡፡
የራሽያና የኢትዮጵያ ግንኙነት የቀዘቀዘበት ጊዜ ስለነበር ያ ሰአት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ትምህርቴን ብጨርስም በራሽያ ለመኖር የመኖሪያ ፈቃድ የለኝም፡፡ በሌላ በኩል የዘር ልዩነት ከፍተኛ ተጽእኖ ያስከትል ጀምሮ ነበር፡፡ የሚገርምህ በዚህ አስጨናቂ ጊዜ የምበላው ነገር እንኳን አልነበረኝም፡፡ ምን ማድረግ አለብኝ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡
የመጀመርያው አማራጭ ያደረግነው በመንገድ ላይ ዕቃዎችን የመቸርቸር ንግድ ውስጥ መግባት ነበር፡፡ በወቅቱ ሚክሲድ ኢኮኖሚ ተጀምሮ ነበርና እንደሩስያዎቹ መንገድ ላይ መነገድ መስራት ጀመርኩ፡፡ የሽግግር ጊዜ ስለነበር ከቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ እና ከሌሎች አገራት የሚገቡ ዕቃዎች ነበሩ፡፡ የራሽያዊቷ ሚስቴ ጓደኞች ነጋዴዎች ነበሩና ከእነሱ ዕቃዎችን እያመጣሁ በመንገድ ላይ መቸርቸር ጀመርኩ፡፡ የማልሸጠውና የማልቸረችረው የዕቃ አይነት አልነበረም፡፡ ሱሪ፣ ካልሲ፣ ካኔታራ፣ የሴቶች ልብሶች በቃ በያይነቱ ዕቃዎችን እቸረችር ነበር። ገበያው ልክ እንደመርካቶ ነበር፡፡ መንገድ ላይ በመለስተኛ ጠረጴዛ ዕቃዎችን ደርድሬ በችርቻሮ ስነግድ ቆይቼ፣ መጨረሻ ላይ የራሴን የችርቻሮ መደብር ከፈትሁ፡፡ በጐዳና ላይ የችርቻሮ ንግድ ለ4 ዓመታት ሠርቻለሁ፡፡ በእነዚያ ጊዜያት ከ20 በላይ ኢትዮጵያውያን ቀጥሬ ማሰራትም ችያለሁ፡፡ ይህን የችርቻሮ ንግድ የምሰራው ፓታሮቭባ በተባለ አካባቢ ነበር፡፡ አሁን ይህ የገበያ ቦታ ተዘግቷል፡፡
ሩስኪዎች ቮድካና ኮኛክ እየጠጡ ሲሰሩ፣ እኔ ምንም ሳልጠጣ በበረዶ ላይ ቆሜ በረዶ ፊቴ ላይ እየደረቀና እየተሰበረ፣ ከብርድ የሚከለክል “ቫሌንኮ” የተባለ ቦቲ ጫማ አድርጌ እሰራ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ መስዋዕትነት እከፍል የነበረው ለራሺያዊቷ ባለቤቴ ፍቅርና ለትዳራችን አክብሮት ስል ነው፡፡ እሷን ትቼ መሄድ አልፈለግሁም፡፡ ያንንም በተግባር አስመሰከርኩኝ፡፡ ለ4 ዓመታት በጐዳና ንግድ ስሰራ ቆይቼ የራሴን ኩባንያ አቋቋምኩ፡፡ በእርግጥ በወቅቱ የኢኮኖሚ ለውጥ ስለነበር ኩባንያውን ያቋቋምኩት ብዙም ገንዘብ ሳይኖረኝ ነበር፡፡ ግን ምንም ተስፋ የቆረጥኩበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ መጀመሪያ የከፈትነው የኢትዮጵያ ሬስቶራንትን ነበር፡፡
የስራ መስክዎን ወደ ሬስቶራንት የለወጡት በምን ምክንያት ነው?
ዋናው ምክንያት የንግድ ስራው መቀዝቀዝ ነው፤ ብዙም አማራጭ አልነበረኝም፡፡ በጐዳና ላይ ንግድ እሠራ በነበረበት ጊዜ በከፍተኛ ብርድ እና አስቸጋሪ አየር ሁኔታ ያሳለፍኩት ህይወት ለጤንነቴም አሳሳቢ ሆኖ ስለነበር ሃኪሞች ይህ ዓይነቱ ስራ አይበጅህም ብለው ከመከሩኝ በኋላ ነው ሬስቶራንት የመክፈት ሃሳቡን ያኘሁት፡፡ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ተመካክሬ በመጀመሪያ የተለያዩ ምግቦችን የሚሸጥ መለስተኛ ሬስቶራንት ከፈትኩ፡፡ በምሠራበት ሬስቶራንት አካባቢ ደግሞ አንድ የውጭ ሬስቶራንት ነበር፤ እሱንም ተከራየሁኝ፡፡ ቦታው ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ብዙም አይርቅም ነበር፡፡ ሬስቶራንት ስጀምር ስለራሽያ ምግቦች አሰራር ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ስለዚህም ራሽያውያን ምግብ አብሳዮችን ቀጠርኩ፡፡ እነሱን ቀጥሬ በማሰራት ምግቦቹን እንዴት እንደሚሠሩና እንደሚያዘጋጁ ማጥናትና መማሬን ቀጠልኩ፡፡
ከተፈጥሮም፣ ከቤተሰቦቼም ሊሆን ይችላል፤ ተስፋ መቁረጥ እና መሸነፍ አልወድም፡፡ ወላጆቼ ሲያሳድጉኝ ደጅ ቆይቼ በሆነ ነገር ተሸንፌ ወደ ቤቴ ብመጣ እንደ ልጅ አይቆጥሩኝም፡፡ ስለዚህ የዚህ ዓይነት አስተዳደጌ በእልህ እንድሰራ አድርጐኛል። የምግብ አሰራሩን በደንብ ከተማርኩ እና ካወቅሁ በኋላ ተከራይቼ እሠራ የነበረውን ቤት በመተው በሌላ ስፍራ ሰፋ ያለ ቦታ አፈላለግሁ፡፡ ፓትሪስ ሉቡምባ ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ ሄጄ ቦታ ጠየቅሁ፡፡ ያንን ያደረግሁት ለተማሪዎች የሚያገለግል ምግብ ቤት በዩኒቨርሲቲው አካባቢ መክፈት ያስፈልግ እንደነበር ስለማውቅ ነው፡፡ በተለይ ለአፍሪካውያን የተለየ ሬስቶራንት አልነበረም፡፡ እናም ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ተመካክረን አብረን መስራት ጀመርን፡፡ ዶ/ር የዝናወርቅ ይባል ነበር፡፡ ከእሱ ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ ውላችን ፈረሰ፡፡ መጨረሻ ላይ ፓትሪስ ሉቡምባ ዩኒቨርሲቲ ደጃፍ የተከፈተውን ትልቅ ሬስቶራንት ሙሉ ለሙሉ ጠቅልዬ ያዝኩት፡፡ አሁን ይህ ሬስቶራንት “አቬኑ አፍሪካ” ይባላል፡፡ የአፍሪካ ጐዳና እንደማለት ነው፡፡
ባርና ሬስቶራንቱ በቀን ቢያንስ 50 ቢበዛ እስከ 100 ሰው ያስተናግዳል፡፡ የመላው ዓለም ምግብ አለ፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ምግቦች፤ የብዙ አፍሪካ አገራት ምግቦችም በሬስቶራንቱ ይገኛሉ፡፡ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ምግቦችም ይሠራሉ፡፡ ለአፍሪካዊያን ተማሪዎችና ዲፕሎማቶች ዋነኛ መመገቢያ ሬስቶራንት ሆኗል፡፡ የአፍሪካ ዲፕሎማቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ሞስኮ ሲገቡ በቅድሚያ የሚጎበኙት የእኛን ሬስቶራንት ነው፡፡ “አቬኑ አፍሪካ ሬስቶራንት” በአሁኑ ጊዜ 15 ሠራተኞች አሉት፡፡ ሶስት አፍሪካዊ፣ ሁለት ራሽያዊና አንድ ኢትዮጵያዊ ምግብ አብሳዮች አለ፡፡ የእኔ ስራ ማኔጅመንት ነው፡፡ ባርና ሬስቶራንቱ በእኔና ሚስቴ ባለቤትነት የተያዘ ነው፡፡
ከአቬኑ አፍሪካ ባርና ሬስቶራንት በተለየ ኢንቨስትመንት ሊንቀሳቀሱ አቅደዋል? ብዙውን ጊዜ በውጭ አገር የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች ወደ አገራቸው ተመልሰው በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት ያደርጋሉ፡፡ በእርስዎ በኩልስ?
በአገሬ ኢንቨስት ለማድረግ የመጀመሪያ ሙከራ አድርጌ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ተወልጄ ያደግሁት ባህርዳር ነው፡፡ በአንድ ወቅት በትውልድ ቦታዬ ኢንቨስት ለማድረግ መጥቼ ለከተማው ባለስልጣናት የኢንቨስትመንት ዕቅዴን ሰጥቼ ነበር። የት እንዳስገቡት አላውቅም፡፡ በተወለድኩበት፣ ባደግኩባትና በተማርኩባት ከተማ ላይ በተለይ ትራንስፖርትን በተመለከተና የከተማዋን ንጽህና መጠበቅ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይዤ ነበር የሄድሁት። የከተማ ቆሻሻዎችን ለማጥፋት የሚችል ልዩ ቴክኖሎጂ ነበር፡፡ ይህን እቅድ ወደፊትም የምተወው አይደለም። ሌላ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ በቱሪዝም መስክ ለመንቀሳቀስ በነበረኝ እቅድ የጀመርሁትም ስራ ነበር፡፡
ከአንድ ሰው ጋር ለመስራት የቱሪዝም መኪና ሁሉ አስገብቼ ባለመግባባት እና እምነት በማጉደል ልሠራበትና ውጤት ላመጣበት አልቻልኩም። በክስ የተያዘ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ግን በአገሬ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ያለኝን እቅድ አይቀይሩትም፡፡ ተስፋም አላስቆረጡኝም፤ እናም ወደ ኢትዮጵያ እመለሳለሁ፡፡ ስመለስ ግን ባዶ እጄን አይደለም፡፡ ያስተማረኝን ህብረተሰብ በጭራሽ ልረሳው አልፈልግም፡፡ በሞስኮ ነዋሪ ሆኜ በተለያዩ የንግድ መስኮች ስንቀሳቀስ ጊዜ ፈተናዎች አልነበሩም ማለት አይደለም፡፡ በአንድ አገር የውጭ ዜጋ ሆኖ በሚሰራ ማንኛውም ሰው ላይ ፈተናዎች መኖራቸው በየትኛውም የዓለም ክፍል የተለመደ ነው፡፡ በሞስኮ ስሰራ የእኔና የባለቤቴን መኪና፣ የምንሰራበትን ቦታ፣ ልጆቼ ምን እንደሚለብሱና የት እንደሚማሩ እየተከታተሉ የሚበሳጩ አሉ፡፡ ይህ አንዱ ፈተና ነው፡፡ ይሄ ጥቁር ሰው እንዴት አገራችን ገብቶ ሃብት አካበተ ብለው ሊናደዱ ይችላሉ፡፡ እኔና ባለቤቴ ሃቀኛ እና ቁርጠኛ ሰዎች ነን፡፡ የሰው አንነካም፤ የራሳችንንም አናስነካም፡፡
እስቲ ስለራሽያዊቷ ባለቤትዎ ይንገሩ…?
ባለቤቴ ማርቼንኮ ትባላለች፡፡ የ3 ልጆች እናት ናት፡፡ ለሦስቱም ልጆቼ ኢትዮጵያዊ ስም አውጥቼላቸዋለሁ፡፡ የመጀመሪያ ልጄ 20 ዓመቷ ሲሆን ማርያ ትባላለች፡፡ በማይኒንግ ኢንጂነሪንግ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ናት፡፡ ሌሎቹ የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው አስቴር እና የ5ኛ ክፍል ተማሪዋ ኤልሳ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ወገኖቼ ራሽያዊ ሚስቴን ጐጃሜ ይሏታል፡፡
ያለምክንያት አይደለም። የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦችን መስራት ትችላለች፡፡ የሬስቶራንቱን የምግብ አሰራር የምትቆጣጠረው እሷ ነች። የምግብ ባለሙያነቷ ጐጃሜ ያስመስላታል፡፡ ልጆቼን በኢትዮጵያዊ ባህልና ወግ ነው አስተዳደግ የማሳድጋቸው፡፡ አማርኛ መናገር ብዙ አይችሉም። ቋንቋውን መማር አለባቸው፡፡ ለመግባቢያ እንግሊዝኛ እና ራሽያኛ ብንጠቀምም አማርኛ ማወቅ አለብን እያልኩ እየመከርኳቸው ነው፡፡

Published in ህብረተሰብ

“ለግብረሰዶማውያን ግን ቅጣታቸው ሰይፍ ነው!”
“ልጃገረዷን በግድ ቢይዛት አፍንጫውን ይፎንኑት፡፡ ለእርሷም ከገንዘቡ ሲሶውን ይስጧት። አስራ ሶስት ዓመት ሳይሆናት አስቀድሞ ልጃገረዲቱን የያዛትን ሰው አፍንጫውን ይፎንኑት፡፡ ከገንዘቡም እኩሌታውን ለእርሷ ይስጧት፡፡”
ይህ ሕግ ነው፤ ሴቶችን ከእንስሳዊ ጥቃት ለመታደግ ከ570 ዓመት በፊት የተደነገገ፡፡ ዘመኑ የአገራችን ሥነ ጽሑፍ አብቦበት እንደነበረ የሚነገርለት ነው - የአፄ ዘርዓ ያዕቆብ (1434-1468) ዘመነ መንግስት፡፡ ለሥነ ጽሑፉ መዳበር ትልቁን ድርሻ የሚይዙት ከጉንዳንጉዶ ገዳም የተነሱት የአባ እስጢፋኖስና ደቀመዛሙርታቸው አዲስ ሃሳብ ማቀንቀን ነው፡፡ መነኮሳቱ ለሚያነሱት አዲስ ነገረ መለኮት መልስ ለመስጠት ሲባል በርካታ መጻሕፍት በንጉሱ እና በተቃራኒው ወይም በነባሩ አስተሳሰብ መመራትን በሚሹ መነኮሳት ይጻፉ ነበር፡፡
“ፍትሐ ነገሥት” የተባለው የሕግ መጽሐፍ ሥራ ላይ የዋለውም ከዚያ የፍትጊያ ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ በ1923 ዓ.ም በወጣው ሕገ መንግሥት እስከተተካ ድረስም ለአራት መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ዓመታት መንግሥትና ሃይማኖት/በተለይ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት/ በተግባር ሲያውሉት ቆይተዋል፡፡
ዛሬ “የሕግ ትምህርት ቤት” እንደሚባለው ድሮ ፍትሐ ነገሥት ራሱን ችሎ ወይም ከትርጓሜ መጻሕፍት ጋር በአንድ ጉባኤ ትምህርቱ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ፍትሐ ነገሥት የተማሩት ሊቃውንትም ከነገሥታቱ የፍርድ አደባባይ ላይ በመገኘት ነገሥታቱ በፍትሐ ነገሥቱ ህግጋት መሠረት የፍርድ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ያግዙ ነበር፡፡
የፍትሐ ነገሥቱ ድንጋጌዎች የተመሠረቱት በብሉይና አዲስ ኪዳን መጻሕፍት ላይ ሲሆን በተለይ አስገድዶ መድፈርንና ግብረ ሰዶማዊነትን በተመለከተ የሚያስገርሙና ጠንከር ያሉ ድንጋጌዎችን ይዞ ይገኛል፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ የሕግ ቅርስ ካላቸው ጥቂት የዓለማችን አገሮች አንዷ እንድትሆንም አስችሏታል፡፡ ህጉ (ፍትሐ ነገሥት) በተለይ ጥቃት ለሚደርስባቸው ሴቶች ተገቢ መፍትሔ እንደነበረው ከተደነገጉት አናቅጽ መረዳት ይቻላል፡፡
“ያልተነካ ግልግል ያውቃል” እንደሚባለው ምን አልባት “ሕጉ የሚጥለው ቅጣት ጠንካራ ነው፤ ኋላቀር ነው” ሊባል ይችላል፡፡ ግን በወቅቱ ልጃገረድ ደፋሪዎች አፍንጫቸው ይፎነን (ይቆረጥ) ነበር። ቅጣቱ የሚያሳየው ጭካኔን ሳይሆን ወንጀሉ ምን ያህል ትኩረት እንደተሰጠው ነው። እናም በወቅቱ አፍንጫ ፎናና (ቆራጣ) ሰው ከታየ ለምን እንደተቆረጠ ምክንያቱ ግልጽ ነበር፡፡ ወንጀል አድራጊውም ከደረሰበት የአካል ጉዳት ይልቅ የማህበረሰቡ መጠቋቆሚያ መሆኑ እያሳፈረው ዕድሜውን በሰቀቀን መግፋት ግድ ይሆንበታል። አካሉን ከማጣቱ ሌላ ግማሽ ሃብቱ በተደፋሪዋ ስለሚወረስበት የሰራው ወንጀል የአካል ብቻ ሳይሆን የምጣኔ ሃብት ጣጣ ስለሚያስከትልበት ውርደቱና የሞራል ስብራቱ ከተደፋሪዋ በላይ ይሆናል፡፡ ቅድመ 1923 የነበሩ ነገሥታት ይህን ህግ በተገቢው መንገድ ስለሚተረጉሙ ከመሰል ድርጊት ሁለመናን መሰብሰብ ግዴታ ነበር፡፡
በፍትሐ ነገሠቱ አንቀጽ 48 ላይ የተደነገገው ይህ ጠንካራ ሕግ፣ ዛሬ ተግባራዊ ቢሆን ስንቱ አፍንጫ ፎናና ይሆን ነበር? ምክንያቱም በ1949 ዓ.ም ወጥቶ ከ48 ዓመታት በኋላ በ1997 ዓ.ም የተሻሻለው የወንጀል ህጋችን አንቀጽ 620 (1) ለተመሳሳይ ጥፋት የሚጥለው ቅጣት ከአምስት እስከ አስራ አምስት ዓመት የሚደርስ እስራት ነው፡፡
የተጠቂዋ ዕድሜ ከ18 ዓመት በታች ከሆነ፣ በተከሳሹ ጥበቃ ወይም ቁጥጥር ሥር የምትገኝ ወይም የእሱ ጥገኛ ከሆነች፤ ወይም በዕድሜ መግፋት፣ በህመም፣ ወይም በሌላ ምክንያት የድርጊቱን ምንነት በውል ለይታ በማታውቅ ሴት ላይ ሲሆን፤ የተደፈረችው ከአንድ በላይ በሆኑ ወንዶች ሲሆን፣ ቅጣቱ ከአምስት እስከ 20 ዓመት በሚደርስ እሥራት እንዲሆን ይደነግጋል (620፡2) እድሜዋ ከ13 ዓመት በታች በሆነ ሕጻን ላይ ለሚፈፀም ጥቃትም ህጉ ከ15-25 ዓመት እስራት ቅጣት ይደነግጋል፡፡
አስገድዶ መድፈሩ ከባድ የአካል ወይም የአዕምሮ ጉዳትን ወይም ሞትን ያስከተለ ከሆነ ግን “ቅጣቱ የዕድሜ ልክ እሥራት ይሆናል (620፡3)” ይላል፡፡ ግን እድሜ ልክ እስራት 25 ዓመት ሲሆን ጥፋተኛው 20 ዓመት ከታሰረ አምስቱን ዓመት ሳይቀጣ በአመክሮ ይለቀቃል፡፡
ይህ ታላቁ የዘመናችን ቅጣት ነው፡፡ ቅጣቱ ከባድ ይመስላል፤ ግን ከፍትሐ ነገሥቱ ድንጋጌ አንቀጽ 48 ጋር ሲገናዘብ ደካማ ነው፡፡ ምክንያቱም ደፋሪው የህጻናትን ህይወት በዘላቂነት የተጐዳ ስለሚያደርገው፣ የፈፀመው ድርጊትም እንስሳዊ ስለሆነ ጠንከር ያለ ቅጣት ይገባው ይመስለኛል፡፡
በመገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ የምንሰማውና የምንናበው ድርጊት በእጅጉ ይሰቀጥጣል፡፡ የ60 ዓመት አዛውንት የሶስት ዓመት ሕፃን መድፈሩ፣ ወይም የ20 ዓመት ወጣት የ70 ዓመት ባልቴት ማዋረዱ፤ ሶስት ወይም አራት ወሮበሎች አንዲትን ደካማ ሴት በህብረት ማጥቃታቸው ወዘተ እጅግ በጣም አሳፋሪም ነውረኛም ድርጊት ነው፡፡ ታዲያ ለእንዲህ ዓይነቱ ነውረኛና አደገኛ ድርጊት ቆንጠጥ የሚያደርግ ቅጣት ካልተጣለ እንዴት ነው “የጾታ ዕኩልነት ተከብሯል” የሚባለው?
አፍንጫ የመፎነኑ ቅጣት የሚያሳየን ትልቅ ቁምነገር በቀልን አይደለም፤ ይልቁንም በተጠቂዋ ሥነልቡና እና ዘላቂ ህይወት ላይ ምን ያህል ከባድ ጉዳት እንደደረሰ ነው፡፡ ለዚህም ነው በአጥቂው ላይ ቋሚ ምልክትና የገንዘብ ቅጣት ይወሰን የነበረው፡፡ የአሁኑ የወንጀል ህጋችን አጥፊውን ይቀጣል እንጂ ተበዳዩ እንዲካስ አያደርግም፡፡ ፍትሐ ነገሥት ግን አጥፊው ከባድ ቅጣት ተቀጥቶም ተበዳዩን ይክሳል፡፡
ሕጉ የወንጀል ብቻ ሳይሆን የፍትሐ ብሔርን ድርሻም ጨምሮ ይሰራ ነበር፡፡ ዛሬም ጥቃት የደረሰባት ሴት የሞራል ካሣ ልትጠይቅ ትችላለች። ግን ከሚጠብቃት ውጣ ውረድ ሌላ ገንዘቡም ደካማ ነው፡፡ ፍትሐ ነገሥቱ የደፋሪዎችን አፍንጫ ከመፎነን የሚያስጥል ሌላ ድንጋጌም አለው። እንዲህ ይላል “በፈቃድዋ ወይም ያለፈቃድዋ ወላጆቿ ሳያውቁ ከልጃገረድ ጋር የተገናኘ ሊያገባት የሚወድ ቢሆን ለወላጆቿ ፈቃዱን ይፈጽሙለት ዘንድ ምርጫ ይገባቸዋል፡፡ ከወላጆቿ አንዱ እንቢ ቢል የገሰሳት ሰው ቢቻለው ባለፀጋም ቢሆን ምዝን ወርቅ ይስጣት፤ በሁሉም ችግረኛ ቢሆን ገርፈው ራሱን ላጭተው ይስደዱት” (ገፅ 419) ይላል፡፡
ይህን ድርጊት በፈፀመው ሰው ላይ ህጉ ጥብቅ እርምጃ እንዳይወሰድበት የሚያደርገው ዓላማውን በመደገፍ ነው፡፡ ጋብቻ ትልቅ ማህበራዊ ተቋም ነው፡፡ እንደተቋምነቱም ህጉ ጥበቃ ያደርግለታል። ለዚህም ነው ክብረ ንጽህናዋን የገሰሰ ወንድ መጀመሪያ ድርጊቱን ለምን ዓላማ እንደፈፀመው መታወቅ የሚገባው፡፡ ጉልበት ስላለው ብቻ ከደፈረ ቅጣቱ ያው የአፍንጫ መፎነን ነው፤ ለጋብቻ ዓላማ ግን ቅጣቱ ቀላል እንዲሆን የታሰበበት ይመስላል፡፡ በተለይ ከወላጆቿ አንዱ ካልተስማማ እና አጥፊው ድሃ ከሆነ ቅጣቱም ቀለል እንዲል ተደርጓል፡፡ ሃብታም ከሆነ ግን ጋብቻውም የማይፈቀድለት ከሆነ ምዝን ወርቅ የመክፈል ግዴታ ተጥሎበታል፡፡
ምዝን ወርቅ አሁን በምናውቀው ሚዛንና መመዘኛ የሚታሰብ አልነበረም፤ የክብደቱ መለኪያ ድቡልቡል ድንጋይ ነበር፡፡ እናም ከድንጋዩ ክብደት ጋር የሚመዝን ወርቅ መክፈል ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻለ የገንዘቡን (የሃብቱን) ዕኩሌታ እንዲሰጣት ይገደዳል፡፡
ከዚህ አንፃር ሲታሰብም ፍትሐ ነገሥት የሴቶችን መብት በማስከበር ረገድ ትልቅ ትኩረት ይሰጥ እንደነበር እንገነዘባለን፡፡ ዛሬ በትዳር አጋራቸው ወይም በፍቅረኛቸው ገላ ላይ አሲድ እየረጩ፣ በጩቤ ዓይናቸውን እየጐለጐሉ፤ ወይም በአደባባይ በጥይት እየደበደቡ፣ ወይም በልጆቿ ፊት የእናታቸውን አንገት በቢላዋ እንደ ዶሮ የሚቀነጥሱ፣ ወዘተ ጨካኞችና ነውረኞች እንደ አሸን ሲፈሉ “ምናለ በፍትሐ ነገሥት ዘመን ተፈጥረን ቢሆን ኖሮ” ያሰኛል፡፡
ሌላውና ጠንካራው የፍትሐ ነገሥት ድንጋጌ በግብረሰዶማውያን ላይ ይጥል የነበረው ቅጣት ነው፡፡ “ግብረሰዶም የሚሰሩ ሰዎች ለአድራጊውና ለተደራጊው ቅጣታቸው ሰይፍ ነው፡፡ ተደራጊው 12 ዓመት ያልሞላው ቢሆን የዘመኑ ማነስ ከቅጣት ያድነዋል” (ገፅ 421) ይላል፡፡ ዛሬ ላይ ይህ ሕግ በአገራችን እየተሰራበት ቢሆን ኖሮ የስንቱ ብላሽ አንገት ለሰይፍ ይዳረግ እንደነበር ሳስበው “ምን አለ መንግሥት ይህን የፍርድ መጽሐፍ ቢያነብበውና የአገሪቱ የወንጀል ሕግ አካል ቢያደርገው” የሚል ብርቱ ምኞት ያድርብኛል፡፡ ይህ ደግሞ ያለምክንያት አይደለም፤ ጨካኝ ባህርይ ኖሮኝም አይደለም፡፡ ምንም በማያውቁ ህጻናት ላይ የሚፈፀመውን ዘግናኝ ድርጊት ስለምሰማ ነው፡፡ በቅርቡ እንኳ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ያለ የስድስት መምህራን ድርጊት ይህን አይነት ቅጣት እንድመኝ ገፋፍቶኛል። ልጅን ያህል ታላቅ አደራ ተሰጥቷቸው በትክክልና በስርዓት አስተምረው መላክ ሲገባቸው አንድን ህፃን ለስድስት መድፈር በእርግጥስ በሰይፍ ሊያስቀጣ የሚችል እጅግ ከባድ ወንጀል አይደለም?
ለእንዲህ ዓይነቶቹ ነውረኛ ግለሰቦች የልብ ልብ የሰጣቸው የወንጀል ህጋችን መላላት ይመስለኛል፤ ጉዳዩን በተመለከተ የወጣው ድንጋጌ አንቀጽ 631 (1) እንዲህ ይላል፡፡
“ማንም ሰው ከእርሱ ጋር አንድ አይነት ጾታ ባለውና ለአካለ መጠን ባልደረሰ ልጅ ላይ የግብረ ሰዶም ጥቃት የፈፀመ እንደሆነ ሀ) የተበዳዩ ዕድሜ አስራ ሶስት ዓመት ሆኖ አስራ ስምንት ዓመት ያልሞላው ሲሆን ከሶስት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑዕ እሥራት፤ ለ) የተበዳዩ ዕድሜ ከ13 ዓመት በታች ሲሆን ከ15-25 ዓመት በሚደርስ ጽኑዕ እሥራት ይቀጣል፡፡”
ሴት ለሴት የሚደረግ ግብረሰዶማዊነትንም ህጉ እንደወንዶች ባይሆንም በወንጀል ፈጻሚዎች ላይ የተለያየ የቅጣት ዕርከን ደንግጓል፡፡ ግን እንደ ፍትሐ ነገሥቱ አስተማሪ አይደለም፡፡ በ1977 ዓ.ም ወሎ ክፍለ ሃገር በደረሰው ከባድ ድርቅ ምክንያት ወላጆቻቸውን በረሃብ የተነጠቁ ህፃናትን ለመርዳት “ጃሪ የህፃናት መንደር” በውጭ አገር ሰዎች ቢመሰረትም ምንም በማያውቁ ምስኪን ህጻናት ላይ ከፍተኛ የሆነ ግብረሰዶማዊ ጥቃት ሲደርስባቸው ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ጥቃቱን ራሳቸው ተጐጂዎቹ ቢያጋልጡም ከፊሉ ወንጀለኞች አገር ጥለው ሲወጡ የተያዘው አንድ ግለሰብ ግን በስምንት ዓመት እስር ብቻ እንደተቀጣ አስታውሳለሁ፡፡
በርካታ ህፃናት (ያውም ወላጆቻቸውን በጠኔ የተነጠቁ) ላይ አስነዋሪ ድርጊት የፈፀመ ወንጀለኛ ሰይፍ አይገባውም ነበር? እርግጥ ነው ዳኞች ህጉ ከሚደነግገው በላይ አልፈው ሊቀጡ ስልጣን የላቸውም፡፡ የሴቶችንና የህፃናትን ጥቃት ለመከላከል ግን ዛሬም ፍትሐ ነገሥት ያሻን ይመስለኛል፤ እንወያይ!

Published in ህብረተሰብ

2005 ሊገባ ሁለት ቀን ሲቀረው ነው፤ ጳጉሜ 3 ቀን 2004 ዓ.ም፡፡ ጊዜው ወደ አስር ሰዓት ገደማ ይሆናል፡፡ የቢሮ ስራዬን አጠናቅቄ ለበዓል ዝግጅት ወደ ቤቴ በመጓዝ ላይ ነበርኩ፡፡
ከ22 በታክሲ ተሳፍሬ ፒያሳ ደረስኩኝ፡፡ ወደ ሰፈሬ የሚወስደኝን ታክሲ ለመያዝ “መኮንን ባር” ፊት ለፊት ልደርስ ጥቂት ሲቀረኝ “የኔ እህት” የሚል የትልቅ ሰው ድምፅ ተሰማኝ፡፡ ዞር አልኩኝ። መጀመሪያ ሰውየውን የማውቃቸው መስሎኝ ነበር። ግን አላውቃቸውም፡፡ ሰላምታ ተለዋወጥን።
“ከየት ነው? ከስራ ነው ከትምህርት?” ጠየቁኝ። ከስራ እየተመለስኩ መሆኔን ገለፅኩ፡፡
ሰውየው እድሜያቸው በግምት በ60ዎቹ መጀመሪያ ይሆናል፡፡ አለባበሳቸውና ኮፍያቸው የወጣት አይነት ነው፡፡ ዘንጠዋል፡፡ “እባክሽ ሻይ ልጋብዝሽ” ጥያቄ አቀረቡ፡፡ እንደምቸኩል ገለፅኩላቸው፡፡ የእውነትም ቸኩዬ ነበር፡፡
“በዓልን እንዴት ልታሳልፊ አስበሻል?” ጥያቄው ቀጠለ፡፡
ሰውዬው ለምን ያደርቁኛል ስል ተበሳጨሁ። ሆኖም ትልቅ ሰው በመሆናቸው ታግሼ ጥያቄያቸውን ከመመለስ ያለፈ ምንም ላደርግ አልቻልኩም፡፡
“ቀለል አድርጌ ነው የማሳልፈው” አልኳቸው። መንገድ ላይ ቆመን ስናወራ አላፊ አግዳሚው በትኩረት ይመለከተን ነበር፡፡ “ሹገር ዳዲዋ ይሆናል” ብለው የገመቱ እንደነበሩ ቅንጣት አልተጠራጠርኩም፡፡
“ከቤተሰብ ጋር ነው ለብቻሽ የምትኖሪው?” ቃለ-ምልልሱ ቀጥሏል፡፡
“ይሄ ጥያቄ ይለፈኝ” አልኳቸው፡፡ ብቻዬን ነኝ ካልኩኝ መጥተው ተከርቸም የሚገቡ ስለመሰለኝ ነው፡፡
“ለምን መሰለሽ? እኔ በበዓል አንድ ልምድ አለኝ” አሉኝ፡፡
“ምንድነው ልስማዋ” አልኳቸው፡፡ ወደ ቤቴ የምገባበት ጊዜ በጣም ናፍቆኛል፡፡ እንዲህ መቆሜ ካልቀረ ምናለ የሻይ ግብዣውን ተቀብዬ ትንሽ አረፍ ባልኩኝ ስል ተቆጨሁ፡፡
“ላለፉት 20 ዓመታት ካናዳ ቶሮንቶ ነው የኖርኩት፤ የካናዳ ዜግነትም አለኝ፤ እዚህ መኖር ከጀመርኩኝ አራት አመታትን አስቆጥሬያለሁ” በማለት ጥቂት ስለራሳቸው ነገሩኝ፡፡ እኔ ደግሞ ልምድ አለኝ ያሉትን ነገር ቶሎ ነግረውኝ ወደ ቤቴ ብሄድና የበዓል ዝግጅቴን ባካሂድ ምኞቴ ነበር፡፡
“እስኪ ልምድዎትን ይንገሩኝ” አጣደፍኳቸው፡፡
“በዓመት ሁለት ጊዜ ለአዲስ አመትና ለፋሲካ ለሁለት ለሁለት ሰዎች የበግ ስጦታ አበረክታለሁ” አሉኝ፡፡
“በጣም ጥሩ ልምድ ነው፤ ግን በጉን ለመስጠት መስፈርትዎ ምንድነው?” ስል ጠየቅኋቸው፡፡
“በቃ እየሄድኩኝ ድንገት አጠገቤ ያገኘሁትን ሰው አናግሬ እሰጣለሁ፤ አንቺም የዚህ እድል ተጠቃሚ ሆነሻል” ብለውኝ አረፉት፡፡
“ሰውየው ይቀልዳሉ እንዴ?” አልኩኝ በሆዴ። እውነት ለመናገር አላመንኳቸውም፡፡ ሰውዬው አገባባቸውን አሳምረው ምን ሊጠይቁኝ ነው እያልኩ መብሰክሰክ ጀምሬአለሁ፡፡
“ምነው ቅር አለሽ እንዴ? ደስ አላለሽም?” ዝም አልኳቸው፡፡ “ለማንኛውም አንቺንም አላቆይሽ፤ እኔም አይምሽብኝ ስልክሽን ስጭኚና ነገ ዋዜማው ነው ከሰዓት በኋላ በጉን አመጣልሻለሁ” አሉ ኮስተር ብለው፡፡
“እንዴ የምርዎትን ነው እንዴ?” ስላቸው ከት ብለው ሳቁ፡፡ ነገሩ የባሰ ግራ አጋባኝ፡፡
“ስልኬን እንኳን አልሰጥም በጉ ይቅርብኝ እንጂ” አልኳቸው፡፡ “ግዴለሽም የእኔ ልጅ፤ ስልክሽን ስጪኝ ጥርጣሬሽና ፍራቻሽ ይገባኛል ግን በእኔ ይሁንብሽ” በማለት እንደምንም አግባብተው ስልክ ቁጥሬን ተቀበሉኝና የእሳቸውንም ሰጥተውኝ ተለያየን፡፡
የሰውየው ሁኔታ ሲያስገርመኝ አመሸ፡፡ በነጋታው የበዓል ስራዎቼን ስከውን ስለ ዋልኩ ጉዳዩን እረስቼው ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ 11 ሰዓት አካባቢ ሰውየው ደወሉ፡፡ እናም ሰፈሬን ፣የት ቦታ ቆመው እንደሚጠብቁኝ ጠየቁኝ፡፡ አሁን ፍርሃት ፍርሃት አለኝ፡፡ ሰውየው የሆነ ነገር አስበው ነው እንጂ እንዴት እንዲህ ሊያደርጉ ይችላሉ እያልኩ ከሰፈሬ ራቅ ያለ ቦታ እንዲጠብቁኝ ምልክት ሰጠኋቸው፡፡
ከዚያ በኋላ አንድ ፖሊስ ዘመዴ ጋ ደውዬ ቶሎ እንዲመጣልኝ ነገርኩት፡፡ ዘመዴም የሆነ ነገር ገጥሟት ነው በሚል ፈጥኖ መጣልኝ፡፡ የጓደኛዬ ወንድም በቅርቤ ስለነበረ ፖሊሱ ዘመዴና ይህ የጓደኛዬ ወንድም ከኋላ ከኋላዬ በቅርብ ርቀት እንዲከተሉኝ ነግሬያቸው፣ ሰውየውን ወደቀጠርኩበት ቦታ አመራሁ፡፡ ጥቁር ፒክ አፕ መኪና ይዘዋል፡፡
ጥቁር መነፅር አድርገዋል፡፡ ነገሩ ጥቁር በጥቁር ሲሆንብኝ የባሰ ፍርሃት ለቀቀብኝ፡፡ ሆኖም የኋላ ደጀኖቼን በመተማመን ወደ ሰውየው ቀረብኩ፡፡ ከመኪና ወርደው የሞቀ ሰላምታ ከሰጡኝ በኋላ “ስጦታዬን ትወጂዋለሽ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እስኪ እይው” በማለት መኪናው ላይ እግሩን ተጠፍሮ ታስሮ የተጋደመውን ነጭ በግ አሳዩኝ፡፡ በጣም ትልቅና ግርማ ሞገስ ያለው በግ ነው፡፡ በጣም ተገረምኩ፡፡ ምንም የምናገረው ነገር አጣሁ፤ አንደበቴ ተለጎመ፡፡ “ቤትሽ ቅርብ ከሆነ የሚሸከምልሽ ሰው ጥሪ፤ የተሸከመበትን እከፍልልሻለሁ” አሉ፡፡ ተሸካሚ ተጠራ፡፡ ተሸካሚው እስኪመጣ እንዲህ አጫወቱኝ፤
“ላለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ከጀመርኩ አንስቼ ይህን አደርጋለሁ፤ የዘንድሮው ባለዕጣዎች የፒያሳ አካባቢ ሰዎች ናቸው” አሉኝ፤ “በመጀመሪያው ዓመት መርካቶ እና አብነት አካባቢ፣ በሁለተኛው ዓመት ኮተቤና ጎተራ፣ሶስተኛው ዓመት ላይ ፈረንሳይና ጦር ሀይሎች፤ አራተኛው አመት አሁን ፒያሳ በአንቺ ጀምሬአለሁ፤ የፋሲካው ተረኛ የትኛው ሰፈር እንደሆነ ገና አልወሰንኩም” አሉኝና ሳቁ፡፡ እኔም ተገረምኩኝ፡፡ ከዚያም ባለ አንድ ሺህ ስድስት መቶ ብር የጠገበ በግ ሰጥተውኝና፣ መልካም በዓል እንዲሆንልኝ ተመኝተው መኪናቸውን አስነስተው ተፈተለኩ፡፡ እኔም ከኋላ ያስከተልኳቸው የ“ደህንነት” ሰራተኞቼን ራቅ ብለው ከቆሙበት ጠርቼ እየተሳሳቅንና እየተገረምን ወደ ቤታችን ሄድን፡፡
እውነት ለመናገር ከዚያ በኋላ ይደውላሉ ብዬ ጠብቄ ነበር፤ ነገር ግን ይሄው አንድ አመት ሞላቸው፤ ደውለውም ደውዬም አላውቅም፡፡ የዘንድሮው የሰውየው የበግ ስጦታ የት ሰፈር ገብቶ ይሆን? የሚታወቅ ነገር የለም፡፡
እኔ ግን በድጋሚ የበግ ስጦታው የሚደርሰኝ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ “ሰርፕራይዝ” የማድረግ ወይም የመደረግ ልምድ ያላችሁ እስቲ ገጠመኛችሁን አካፍሉን፡፡
መልካም አዲስ አመት!!

Published in ባህል
Monday, 16 September 2013 07:56

‘ልብ የመግዣ’ ዓመት…

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ከዘመን ዘመን በሰላም፣ በጤናና በደስታ አሸጋገራችሁማ!
(መባል ሰላለበት ነው እንጂ…አለ አይደል… “ሰላም ሲኖረን፣ ጤና ስንሆን፣ ደስ ሲለን የት ያየኸውን ነው!” ምናምን የሚል ጥያቄ ቢመጣ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡)
እናላችሁ…ይኸው ‘ተሸጋርናል’…ቢያንስ፣ ቢያንስ ግድግዳችን ላይ ያለውን ‘አሮጌ’ ቀን መቁጠሪያ በአዲስ እንለውጣለን፡፡ ማንም መጥቶ (ወይም በሰፈር ‘ፌርማቶሪ’) “ቤቱ ግድግዳ ላይ የለጠፈው በምስጢር ምን የሚሠራው ነገር ቢኖር ነው ይሉኝ ይሆን?” ብለን ሀሳብ ሳይገባን የምንለጥፈው ቢኖር የቀን መቁጠሪያ ካላንደር ነው፡፡
ግን’ኮ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እንደ ዘንድሮ ነገረ ሥራችን ከሆነ ካላንደሩ ላይ የተጻፈው የድርጅት ወይም ተቋም ስም ‘ሊያስመርዝ’ ይችላል፡፡ ልክ ነዋ…“ከመቼ ወዲህ ነው እሱ ሀይማኖተኛ የሆነው፣ ለሽፋን ንው እንጂ!” ምናምን ሊባል ይችል ሁሉ ይሆናል፡፡
የማንጫወትበትን ቡድን ማልያ የማልበስ እርግማችንን አዲሱ ዓመት ይዞት ጥርግ ይበልማ! ላለፉት ጥቂት ዓመታት…አለ አይደል… በአገር ልጅነት፣ በእምነት፣ በፖለቲካ አስተሳሰብ፣ በምንሠራባቸው ቦታዎች፣ በምናዘወትርባቸው ‘ፉት’ ቤቶች፣ አብረን በምንውላቸው ጓደኞች… ብቻ የምንፈረጅባቸው ነገሮች እየተባዙ ነው የመጡት፡፡
እናማ… መጪው ዓመት በሆነ ባልሆነው ‘የተመረጠልንን ማልያ’ እንድንለብስ የምንደረግበትን ‘እርግማን’ ያንሳልንማ!
ስሙኝማ…ያው እንደተለመደው በዓላችን ‘ምግብ ተኮር’ ነው፡፡ ቱርካውያን በአዲስ ዓመት በማህበራዊ አገልግሎቶች መሳተፍና የእርዳታ መሰብሰቢያ ዝግጀቶችን ማዘጋጀት ደስታ እንደሚያመጣላቸው ያስባሉ ይባላል፡፡ እኛ ዘንድ…አለ አይደል… በኤን.ጂ.ኦ. ምናምን ሳይሆን በዜግነታችን ብቻ በማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ የምንሳተፍበት ጊዜ አይናፍቃችሁም! ለነገሩ… እኛ ዘንድ አንዳንድ ጊዜ በተናጥል ወይም ሰብሰብ ብላችሁ በጎ ነገር ስታደርጉ…አለ አይደል… በዚህ ወይ በዚያ ወገን ‘ቦተሊካው’ ይጠልፈውና በህልማችሁ ያላለማችሁት ‘ስክሪፕት’ ይጻፍለታል፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ የበዓል ማግስት ጨዋታም አይደል…ስለ ምግብ ካወራን ይቺን ስሙኝማ…ጓደኛሞቹ ጥሬ ሥጋ ሊበሉ የሆነ ቤት ይገባሉ። እናላችሁ…‘ሻሽ’ የመሰለ ሥጋ አስቆርጠው ይቀመጣሉ፡፡ ታዲያላችሁ… ከእነሱ ፊት ለፊት የነበሩ ሰዎች ፍጥጥ ብለው ያዩዋቸዋል፡፡ እናማ…ጓደኛሞቹ “እኛ ቁርጥ ልንበላ ብንመጣ ሰዎቹ ቁርጥ ሊያደርጉን ነው እንዴ!” ምናምን ተባባሉና ከመሀላቸው አንዱ ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው… ወፈር ያለ ሥጋ ይቆርጥና መሬት ላይ ይጥለዋል፡፡ ጓደኞቹም ምን እያደረገ እንደሆነ ሲጠይቁት ምን ቢል ጥሩ ነው…“ግራውንድ ላደርግ ነው!” አሪፍ አይደል፡፡ ጦስ ጥብምቡሳሳችንን ይዞ ምድር ይግባ አይነት መከላከያ ነው፡፡ (እኔ የምለው…ከዚች በፊት ያነሳናትን ጥያቄ እንደገና እናንሳትማ…አፍጥጠው የሚያዩ ሰዎች በጣም፣ እጅግ በጣም አልበዙባችሁም! ትንሽ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡ ሰው አፍጥጦ ማየት ‘ጎጂ ኋላ ቀር ባህል’ ስለሆነ በመጪው ዓመት የአፍጣጮች ዒላማ ከመሆን ይሰውረንማ!
ስሙኝማ…የተለያዩ አገሮችን የአዲስ ዓመት መልካም ምኞቶች የፈረደበት ‘በይነ መረብ’ ላይ ሳይላችሁ…ያገኘኋቸውን ስሙኝማ፡፡ ይሄ ለወላጆች የሚጻፍ ነው…“ወደ ህልሞቼ የምበርባቸውን ክንፎች ሰጥታችሁኛል፣ የመጣሁበትን እንዳልረሳም ስረ መሰረቴን አሳይታችሁኛል፡፡ ምንም ያህል ወደላይ ብመጥቅም ስረ መሰረቴን እንዳልረሳና እንዳልለቅ አስተምራችሁኛል፡፡ ሁልጊዜ በአጠገቤ በመሆናችሁና ስለምታግዙኝም በዚህ በአዲሱ ዓመት ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡”
አሪፍ አይደል!…የዚሀ አገር አንዱ ትልቁ ችግር ምን መሰላችሁ…ስረ መሰረታችንን በራስ አነሳሽነት የምንረሳ መአት መሆናችን፡፡ የምር ግን…ከትንሽ ቦታ ተነስቶ ትልቅ ቦታ የመድረስን ያህል የሚያኮራ ነገር አለ!
እናላችሁ…ሲወለድ በ‘ወርቅ ማንኪያ’ ወተት ይጠጣ የነበረውማ…አለ አይደል… ‘ጣጣው ያለቀለት፣ ካርታው የወጣለት፣ ሊዙ ሙሉ የተከፈለለት’ ህይወት ውስጥ ነው የገባው፡፡ አንዳንድ ሰው ግን በአቅም ማነስ በሦስት ቀን አንዴ እንኳን በማይበላበት ቤተሰብ ተወልዶ በኋላ ላይ ስኬት ላይ ሲወጣ…“እኔ ስወለድ እኮ ድፍን ሰፈር ሠርግና ምላሽ ነበር…” አይነት ነገር ቀሺም ነው፡ መጪውን ዓመት ስረ መሠረታችንን ያልረሳን ይዘን እንድንቆይ፣ የረሳነውም መልስን የምንይዝበት ዓመት ያድርግልንማ! ‘ራስን ከማጣት’ የበለጠ ውድቀት የለም፡፡
ሩስያ ውስጥ የሚኖር አንድ አይሁዳዊ ወደ አሜሪካ ለመሄድ የቪዛ ማመልከቻ ያቀርባል። ወደ አሜሪካ ለመሄድ የፈለገበትን ምክንያትም ይጠይቃል፡፡
አሜሪካ ያለው ወንድሙ እንዳመመውና ሊያስታምመው እንደሆነ ይናገራል፡፡ የፓስፖርት ሰዎቹ እንግዲያው አንት እዛ ከምትሄድ ወንድምህ ለን እዚሀ አየመጣመ አሉት፡፡
አይሁዳዊው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…“አሞታል አልኩ እንጂ አብዷል አላልኩም!” መጪው ዓመት ከውጪ ለመምጣትም ውስጥ ሆኖ ለመክረምም “አሞታል አልኩ እንጂ አብዷል አላልኩም!” የማንልባት ዓመት ትሁንልንማ!
ስሙኝማ…ስለ መልካም ምኞት መግለጫ ስናወራ አልነበር…እናማ ለአዛውንቶች ደግሞ እንዲህ አይነት የመልካም ምኞት መግለጫ አለላችሁ…“እርሶ በብዙ ዘመናት ያጠራቀሙት እውቀትና ጥበብ እኔን ወደ ግቦቼ ለመድረስ በማደርጋቸው ጉዞዎች መንገድ መሪዎቼ ናቸው፡፡ እርሶ በህይወት ባገኟቸው ትምህርቶች ክፉ ጊዜን ለመሻገር ይርዱኝ፡፡ መልካም አዲስ ዓመት፡፡”
ስሙኝማ…እዚህ አገር አንድም የጎደለን ነገር በኑሮ ልምድ የሚመጣ ጥበብና ተሞክሮ ነው፡፡ አንድ ሰሞን ሁሉንም ዕድሜ ጠገብ ነገር የማውገዝና “ኋላ ቀር!” የማለት ነገር እንደ ወረርሽኝ በሚዲያው ጭምር ተባብሶ ነበር፡፡ አሁን፣ አሁን በትንሽ፣ ትንሽም የትናንቱ ነገር ሁሉም መጥፎ እንዳይደለ፣ የዛሬውም ነገር ሁሉም መጥፎ እንዳልሆነ…ሁሉም ዘመናት የየራሳቸው መጥፎና ጥሩ ነገሮች እንዳሏቸው ባይበዛም እየተቀበልን መሰለኝ፡፡ አዲሱ ዓመት ከወዲያኛው ዘመን ማድነቅና መውረስ ያለብንን እንድናደንቅና እንድንወርስ የመንፈስ ጥንካሬውንና በራስ መተማመኑን የምናገኝበት ይሁንልንማ!
የምር ግን…ለምሳሌ ብዙ የሬደዮ ፕሮግራሞች ላይ የምናየው ችግር…አለ አይደል… ለረጅም ዓመታት ከመኖርና፣ በብዙ ህይወት ተሞክሮ ከማለፍ የሚገኙ እስተምህሮቶች መሳሳታቸው ነው፡፡ በአዲስ ዓመት ከህይወት ልምዳቸው ትምህርት የምናገኝባቸውን የዕድሜ ባለጸጎች እንፈልጋለን፡፡ እናማ መጪውን ዓመት…“እናንተ በህይወት ባገኛችኋቸው ትምህርቶች ክፉ ጊዜን ለመሻገር እርዱን፣” የምንልበት ዓመት ያድርግልንማ! (በሬድዮ የምትሠሩ አቅራቢዎች…ፕሮግራሞቻችሁ ‘ሚዛን እንዲደፉ’ና ይበልጥ ተደማጭ እንዲሆኑ ከ‘ቁም ነገር ንባቡ’ ጨመርመር የምታደርጉበት ዓመት ያድርግላችሁማ!)
እናላችሁ… ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…በየትኛውም ስርአት ‘ቦተሊከኞች’ ያለፉ ትውልዶችን እንዳለ ጥምብርኩሳቸውን የሚያወጧቸው …..አንድም ከታሪክ መጽሐፍት ይልቅ የውስኪ ስም ማንበብ ስለሚቀላቸው (ቂ…ቂ…ቂ…) ወይም የራሳቸውን ቅሽምና ለመሸፈን መስዋእትነት የሚያቀርቡት ‘የአብረሀም በግ’ ስለሚፈልጉ ይመስለኛል፡፡ በቃ መሰለኝ…ደግሞም አበቃሁ፡፡ )
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በቀድሞዋ ሩስያ ነው አሉ…የመሥሪያ ቤቱ ካድሬ ሠራተኞቹን ሰብስቦ ስለወደፊቷ ሩስያ ብሩህ ጊዜ እየሰበካቸው ነው፡፡
አያችሁ ጓዶች፣ ይህ የአምስት ዓመት ፕላን ሲጠናቀቅ፣ እያንዳንዱ ቤተሰብ አፓርትመንት ይኖረዋል፣ የሚቀጥለው የአምስት ዓመት ፕላን ሲጠናቀቅ ደግሞ እያንዳንዱ ሠራተኛ የየራሱ መኪና ይኖረዋል! ሦስተኛው የአምስት ዓመት ፕላን ሲጠናቀቅ ደግሞ እያንዳንዱ ቤተሰብ የየራሱ አውሮፕላን ይኖረዋል!” ይላቸዋል፡፡
ከተሰብሳቢዎቹ አንዱ “አውሮፕላን ምን ያደርግልናል?” ሲል ይጠይቃል፡፡ ካድሬው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…“ጓዶች፣ አይታያችሁም እንዴ! በከተማችሁ የድንች እጥረት አለ፡፡ አታስቡ፣ ችግር የለም፡፡ አውሮፕላኖቻችሁን ታስነሱና ሞስኮ ሄዳችሁ ድንች ገዝታችሁ ትመጣላችሁ!” አንዳንዴ የዚቹ የእኛ አገር እንደ ወረደ የሚበተን ‘ብሮባጋንዳ’ በአውሮፕላን ሞስኮ ሄዶ ድንች እንደመግዛት አይመስላችሁም!
ብቻ መጪውን ዓመት ለሁላችንም ‘ልብ የመግዣ ዓመት ያድርልግንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

ባለፈው ዓመት ማተምያ ቤት የገባ ጋዜጣ ለአዲሱ ዓመት አልደረሰም!
አንድ ሚኒስትር ለተሰበሰበው ህዝብ ንግግር ሲያደርጉ ገለፃውን በጣም ያረዝሙትና ብዙ ሰዓት ይወስዳሉ፡፡ ታዳሚው እስኪታክተው ድረስም ያብራራሉ፡፡ ከፊሉ እያንቀላፋ ከፊሉ እየተንጠራራ ስብሰባውን እንደምንም ይካፈላል፡፡ ሚኒስትሩ ንግግራቸውን ሲጨርሱ በጣም ብዙ ሰዓት መፍጀታቸው ለራሳቸው ተሰማቸውና ይቅርታ ለመጠየቅ ፈልገው፣ ሰዓት አለማሰራቸውን እያሳዩ “ሳላውቅ ብዙ ጊዜያችሁን ወሰድኩባችሁ፣ ይቅርታ ሰዓቴን ስላልያዝኩኝ ነው” አሉ፡፡ ከተሰብሳቢዎቹ አንዱ እጁን ያወጣና “ክቡር ሚኒስትር፤ ከጀርባዎ ካላንደር ተለጥፎልዎ ነበር እኮ!” አላቸው፡፡
እንግዲህ ሚኒስትሩ ይቅርታ እስከመጠየቅ ድረስ ከሄዱ አነሰም በዛም የህዝቡን ሰዓት በእንቶ ፈንቶ አባክነዋል ማለት ነው አሊያም ጊዜውን አጭበርብረውታል፡፡ እቺን ቀልድ ለመሸጋገርያ ያህል ጣል ካደረግሁላችሁ አሁን ወደ ዋናው ቁምነገር እንለፍ - ወደ ዋናው የዓመቱ መጭበርበር!
አባቶቻችን ሲተርቱ እድሜ የሰጠው ብዙ ነገር ያያል ይላሉ (ይሄም ተጭበርብሯል እንዴ?) እኔ ግን የፈለገ እድሜ ቢሰጠኝ አዲስ ዓመት እንዲህ እንደ ዘንድሮ ሲጭበረበር አያለሁ ብዬ በህልሜም በእውኔም አልሜም አስቤም አላውቅም፡፡ እውነቴን እኮ ነው--- እስከዛሬ የማውቀው ምርጫ (ያውም የሥልጣን ) ሲጭበረበር እንጂ አዲስ ዓመት?----በፍፁም ሲጭበረበር አይቼም ሰምቼም አላውቅም፡፡ ዘንድሮ ግን አዲሱ ዓመት (2006 ማለቴ ነው!) ዓይኔ እያየ በግላጭ ተጭበረበረ! (አዲስ ዓመታችንን መልሱልን!) ክፋቱ ግን እማኝ የሚሆኑ ታዛቢዎች አላስቀመጥንም (እንደምርጫ) ለነገሩ እኮ ምርጫውስ ቢሆን መች ከመጭበርበር ዳነ! (የተቃዋሚዎችን “መሰረተቢስ ወሬ” ሰምቼ እኮ ነው) እናላችሁ---- አረረም መረረም ከአሁን በኋላ አዲስ ዓመትን እንደወትሮው ለብቻችን ማክበር አንችልም ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ምነው የተባለ እንደሆነ---- ተጭበርብረናላ! ስለዚህም በየዓመቱ የፈረደባቸውን የአውሮፓ ህብረት ታዛቢዎች ልናስቸግር ነው ማለት ነው (የግድ አና ጎሜዝ መሆን እኮ የለባትም !)
እውነቴን ነው የምላችሁ ---- የኛ ነገር እኮ በጣም ይገርማል፡፡ ያለውጭ ጣልቃ ገብነት ራሳችንን ችለን የምንፈፅመው አንድ ነገር ቢኖረን በዓል ማክበር ነበር፡፡ እሱም ግን ይኸው ዘንድሮ ተጭበርብሮ አረፈው፡፡ ከአሁን በኋላ እኮ አዲስ ዓመትንም ያለ ውጭ አገር ታዛቢዎች አናከብርም ማለት ነው (አያምኑንማ!) የሚገርመው ደግሞ የኛ ሳያንስ የፈረንጆቹንም አዲስ አመት ማጭበርበራችን ነው። ምናልባት እናንተ አላስተዋላችሁት ይሆናል ---- ኢቴቪ ባለፈው ረቡዕ የአዲስ ዓመት ልዩ ዝግጅት ሲያስተላልፍ “እንኳን ለ2006 በሰላም አደረሳችሁ” ከሚለው የአማርኛ ፅሁፍ ቀጥሎ ፈረንጆቹም ለምን ይቅርባቸው ብሎ ነው መሰለኝ “Happy New Year 2014 ” የሚል ፅሁፍ አቅርቧል (አዲስ ዓመት ወደ እንግሊዝኛ ይተረጎማል እንዴ ?) ይታያችሁ-----የፈረንጆች አዲስ አመት እኮ ገና አራት ወር ይቀረዋል! (ቀላል ተጭበረበሩ!)
በነገራችሁ ላይ አዲሱን ዓመት ያጭበረበረን እንደ ምርጫ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ እኮ አይደለም። ከተለያዩ አካላት ተውጣጥተው ነው፡፡ አዲስ ዓመታችንን በዋናነት ያጭበረበሩን ግን “ፒ ስኩዌር” የተባሉትን ታዋቂ የሙዚቃ ቡድን አባላት አስመጥተን በዋዜማው እናስቀውጣችኋለን በማለት ከ1ሺ ብር እስከ 2ሺ ብር የተቀበሉን ድርጅቶች ናቸው (የመሃሙድን “አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው ---” ጋብዘናቸዋል!) እኛማ ምን እናድርግ --- ሰው እናምን የለ! ሲቪያቸውን ሳናይ ዝም ብለን ብራችንን መዘዝን (ኢቴቪ እኮ ነው የሰራልን) እናማ የበዓሉ ዋዜማ አንድ ቀን ሲቀረው ኮንሰርቱ ተሰርዟል ተባልን (አዲስ አመት ተሰርዟል እኮ ነው ያሉን!) ምክንያታቸው ደግሞ ግርም ይላል ---- አንዴ በውጭ ምንዛሪ እጥረት (ብሔራዊ ባንክ እንዳይሰማ ብቻ!) ----- አንዴ ደግሞ በትራንስፖርት ችግር (መቼም አየር መንገድ አልሰማም!) ወዘተ--- መምጣት አልቻሉም አሉንና አዲስ ዓመታችንን አጭበረበሩብን፡፡ እውነቴን ልንገራችሁ አይደል---- ህዝቡን ያበገነው እኮ የሙዚቀኞቹ መቅረት አይደለም---- የአዲሱ ዓመት መጭበርበር እንጂ! (ለማየት ለማየትማ እነ ቢዮንሴንም አይተናል እኮ!)
የባሰው ደግሞ የማን መሰላችሁ? የኢቴቪ! በዋዜማው ሌሊት ያደረገንን አይታችኋል? (ከተኛችሁ ተገላግላችኋል) “አይዟችሁ እኔ እያለሁ አዲስ ዓመትን አትጭበረበሩም” አለና ዋዜማውን አንዴ ቬላ ቨርዲ፣ አንዴ አዝማሪ ቤት፣ ሲቸግረው ደግሞ ያለፈ የዋዜማ ዝግጅት እያቀረበልን ሲያንከራትተን አደረ (ትሻልን ትቼ ትብስን አገባሁ --- አሉ!) አንዳንዶች ደግሞ በሪችትም ተጭበርብረናል ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ (የመጭበርበር ዓመት ሆኖ አረፈው እኮ!) “ሪችት ይተኮሳል ተብለን እስከ ሌሊቱ 6 ሰዓት እንቅልፍ እያዳፋን ብንጠብቅም እንኳን ሪችት ጥይትም አልተተኮሰም” ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል - አዲሱን ዓመት ተጭበርብረናል ባዮች። እኔ እንኳን ሪችቱ መቅረቱ ብዙም አላስቆጨኝም። ለምን መሰላችሁ? የእኛ ባህልና ወግ አይደለማ! ዋናው ነገር ማለዳ ላይ 21 ጊዜ የሚተኮሰው መድፍ እኮ ነው፡፡ እሱም አልተተኮሰም እንዳትሉኝ ? (በፍፁም አይደረግም!)
የዘንድሮ የአዲስ ዓመት መጭበርበር በየዘርፉና በየአቅጣጫው ይመስላል፡፡ እስቲ በግሉ ፕሬሱ ላይ የተፈፀመውን የአዲስ ዓመት መጭበርበር ደግሞ እንመልከት፡፡ ለምሳሌ አዲስ አድማስ ጋዜጣ አዲስ አመትን ምክንያት በማድረግ ጳጉሜ 5 ቀን 2005 ዓ.ም የሚወጣ ልዩ እትም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ መቼ ቢወጣ ጥሩ ነው? መስከረም 3 ቀን 2006 ዓ.ም! ባለፈው ዓመት ማተምያ ቤት የገባ ጋዜጣ እኮ ለአዲሱ ዓመት አልደረሰም (ይሄስ--- ከመጭበርበርም ይብሳል!) የዚህ አስደናቂ ገድል ባለቤት ደግሞ ማን መሰላችሁ? በአገሪቱ የህትመት ታሪክ ብዙ ብዙ ድንቅ ገድሎችን የሰራውና በንጉሱ የተቋቋመው ብርሐንና ሰላም ማተምያ ቤት ነው። (“አልቻልኩምና አግዙኝ” ማንን ገደለ?) እስቲ ይታያችሁ---- “በኢኮኖሚ በፍጥነት እየተመነደጉ ካሉ አገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ---” እያሉ መዘገብ የጀመሩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች፣ ይሄን አሉታዊ መረጃ ቢሰሙ ምን ሊሉ ነው? (“አፋችንን በቆረጠው!”ማለታቸው እኮ አይቀርም!)
እኔ የምለው ግን --- ሰፊው ህዝብ ህገመንግስቱ ያጎናፀፈውን መረጃ በወቅቱ የማግኘት መብት ሲነፈግ ኢህአዴግ ዝም ብሎ ያያል ማለት ነው? (“መረጃ እየተጭበረበረ” እኮ ነው!) እውነት ግን ለዚህ ተጠያቂው ማነው? (ብቻ የኢኮኖሚ እድገታችን ያመጣው ጣጣ ነው እንዳትሉኝ!) እግረ መንገዴን ለመንግስት ወይም ለአውራው ፓርቲ አንድ ቀላል ግን ወሳኝ የሆነች ጥያቄ ጣል አድርጌ ልለፍ። ለምንድነው መንግስት ትላልቅ የግል ማተምያ ቤቶች እንዲቋቋሙ የማያበረታታው? ማተምያ ቤትም እንደ ቴሌ ገንዘብ ማተምያ ማሽን ከሆነ በግልፅ ይነገረንና አርፈን እንቀመጥ! (“ፖለቲካዊ ውሳኔ” ይሆን እንዴ ?) የሚገርማችሁ ግን በ93 ዓ.ም የታተመ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ እንዲህ የሚል ማስታወቂያ ወይም መግለጫ አንብቤአለሁ “በኢንተርኔት ግንኙነት መስተጓጎል ምክንያት የዚህ ሳምንት ሳምንቱ በታሪክ ውስጥ አልተዘጋጀም። ዕድሜ ለቴሌ!” ይኸው ከ13 ዓመት በኋላ ደግሞ ቴሌ ብቻ ሳይሆን ለሶስት- ማተምያ ቤት፣ መብራት ኃይልና ቴሌ ተባብረው የህዝቡን መረጃ የማግኘት ህገመንግስታዊ መብት እየነፈጉ ነው፡፡ (ድብቅ አጀንዳ ካላቸው ይንገሩን !)
በነገራችሁ ላይ በዛሬው የፖለቲካ ወግ ስለመጭበርበር በስፋት ያወጋነው “አዲስ ዓመት ተጭበረበረ” ብለን ነው እንጂ መጭበርበርማ ለሃበሻ ልጅና ለጦቢያ አዲስ ነገር ሆኖ እኮ አይደለም፡፡ ለመሆኑ ሳንጭበረበር ውለን አድረን እናውቃለን እንዴ!?
እስቲ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ስሟቸው ---- የዘወትር እሮሮአቸው ምንድነው? “ህገመንግስቱ ያጎናፀፈንን በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት ራሱን አውራ ፓርቲ እያለ የሚጠራው ኢህአዴግ አጭበረበረን” የሚል እኮ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲም እኮ በተቃዋሚዎች ተጭበረበርኩ እንዳለ ነው (መንግስትም ይጭበረበራል እንዴ?) አዎ ኢህአዴግም “ለሰፊው ህዝብ ለማስፈን ያቀድኩት ሰላምና ልማት በተቃዋሚዎች እየተጭበረበረብኝ ነው” ሳይል ቀርቶ አያውቅም፡፡ ይሄ ዓይነቱ የተጭበረበርኩ አቤቱታ እንግዲህ በአዘቦት ቀን ብቻ የሚሰማ ነው፡፡ ምርጫ በመጣ ቁጥር የምንሰማው የመጭበርበር ስሞታ ደግሞ ተዘርዝሮ የሚያልቅ ስላልሆነ ለሌላ ጊዜ ቀጠሮ ይዘንለት እንለፈው፡፡
ሰፊው ህዝብ (እኛ ማለት ነን!) ደግሞ የራሱ በርካታ የተጭበረበርኩ አቤቱታዎች አሉት (ጆሮ የሚሰጠው አጣ እንጂ!) ለምሳሌ በእያንዳንዷ ሻማ እያበራን ባደርንባት ምሽት ሁሉ መብራት ተጭበረበረናል፡፡ ብጫ ጀሪካን እየያዝን በምንዞርባትና ውሃን እስከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በምንጠብቅባት ውድቅት ሌሊት ሁሉ ደግሞ ውሃ ተጭበርብረናል፡፡
በሞባይል ስልካችን ደውለን የምንፈልገውን ሰው ማግኘት ሲያቅተንም በኔትዎርክ እየተጭበረበርን መሆኑን ካወቅንም ቆየት ብለናል፡፡ በታክሲ እጥረት ሳቢያ በወረፋ ስንገላታ ደግሞ በትራንስፖርት መጭበርበራችንን እናውቀዋለን፡፡ (እድሜ ለቀጣና ስምሪት!) እኒህ ሁሉ ጠቅለል ሲደረጉ አውራው ፓርቲ በምርጫ ሰሞን አሰፍነዋለሁ እያለ ምሎ በሚገዘትለት የመልካም አስተዳደር ጉዳይ በሚገባ መጭበርበራችንን እንገነዘባለን (ኢህአዴግም እኮ አልካደውም!) አሁን ትንሽ ያሳሰበን ለምን መሰላችሁ? ማጭበርበሩ የተጀመረው ገና በአዲሱ ዓመት መጀመርያ ላይ በመሆኑ ነው፡፡ (እስቲ አንድዬ ይሁነና!)
ሴትየዋ አንድ አዋቂ ዘንድ ትሄድና “እጣ ፈንታዬን ንገሩኝ!” ትለዋለች፡፡ አዋቂው የሥነፈለክ እውቀት ያለው ነውና ኮከቧን አየላት፡፡ መዳፏንም አነበበላት፡፡ ከዚያም “የእኔ እህት 30 ዓመት እስኪሞላሽ ድረስ መከራና ጉስቁልና እንደ ጉድ ይፈራረቁብሻል!!” አላት፡፡ ሴትዮይቱም በጣም በመጣደፍ “ከዚያስ--- ከ30 ዓመት በኋላስ እንዴት እሆናለሁ?”
አዋቂውም “ከዚያ በኋላ እንኳን ምንም ችግር የለም - ትለምጂዋለሽ!” (መጭበርበርን ከመልመድ ያውጣን!) መልካም አዲስ አመት ለሁላችንም!! (በተለይ ደግሞ ለብርሐንና ሰላም ማተምያ ቤት!)

ከአዘጋጁ፡- ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍ ከዶ/ር መረራ ጉዲና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የህይወቴ ትዝታዎች መፅሃፍ አለፍ አለፍ ተብሎ የተወሰደ ሲሆን መፅሃፉን ያላገኙ አንባቢያን መጠነኛ ግንዛቤ እንዲያገኙ በሚል ያወጣነው ነው፡፡
ምዕራፍ 11፡ የ2002 ምርጫና አዳዲስ የኢህአዴግ ሴራዎች
በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም የብዙ ሰዎች ዓይን የተተከለው በ1997ቱ ምርጫ ላይ ነው። እስከ 1997ቱ ምርጫ ድረስ ደግሞ የብዙዎች የፖለቲካ እይታ የተሰራው በተጨናገፈው የ1966ቱ አብዮት ላይ ነበር፡፡ የ1997ቱ ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ የትውልድን ቀልብ ስቦ አልፎአል፡፡ ህዝቡን ከዛ አላቆ ወደፊት እንዲመለከት ለማድረግ ቀላል አልሆነም፡፡ በምርጫ ውጤት ተደናግጦ የነበረው ኢህአዴግም አስተማማኝ ምርኩዜ ነው በሚለው ጠመንጃ ስር መደበቁን መርጧል፡፡ ተቃዋሚውም ድርጅት ከመፈልፈልና ከመከፋፈል በሽታው አልዳነም። በተለይ አንባቢ ልብ እንዲልልኝ የምፈልገው፣ ተቃዋሚው በ1997ቱም ሆነ ዛሬ ሰፊ ህዝባዊ ድጋፍ (popular support) አለው። ዛሬም ከአንድ ወር ባነሰ እንቅስቃሴ ኢህአዴግን ኮርቶ ማሸነፍ ይችላል። የኢህአዴግ ባለስልጣናትም በህዝብ እውነተኛ ድጋፍ ሳይሆን የሀገሪቷን ፀጥታ ኃይል ምርኩዝ አድርገው እንደሚኖሩ ልቦናቸው ያውቃል፡፡ ተቃዋሚው በ1997ቱም ሆነ ዛሬም በቂ የተደራጀ ድጋፍ (organized support) የለውም፡፡ ደጋግሜ ለማሳየት እንደሞከርኩት ይህ ክፍተት ካልተደፈነ በስተቀር ሁሉም ነገሮች በጎ ፈቃድ እስከምን ድረስ ድረስ እንደሆነ በ2002ቱ ምርጫ በሚገባ አይተናል። ስለሆነም፣የተቃዋሚዎች አጣዳፊ ተግባር መሆን ያለበት ክፍተቱን በመድፈን አቅም ፈጥሮ መንቀሳቀስ ብቻ ነው፡፡
እስከሚገባኝ ድረስ የሀገራችን ፖለቲካ አንድ ወሳኝ እርምጃ ወደፊት ሊሄድ የሚችለው ሁሉም ከራሱ የህልም ዓለም በመውጣት፣ ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ዋነኛ አጀንዳ ላይ መረባረብ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ፣ በአንድ በኩል መገንጠልን እንደዋነኛ የፖለቲካ አጀንዳ ማራመድንና በሌላ በኩል ደግሞ “ኢትዮጵያ እምዬ ምኒሊክ በፈጠሯት መልኳ ትኑር” የሚሉትን ሁለቱን የሀገራችንን የፖለቲካ ጫፎች በማቀራረብ በመሃል መንገድ ላይ ወርቃማ አማካይ (the golden mean) መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ከታሪክ ጣጣችን የሚመነጩ ልዩነቶች በአንድ ጀንበር ካልተፈቱ ብሎ የሙጥኝ ማለት የዲሞክራቲክ ኢትዮጵያን መወለድ ማዘግየትና የገዢው ፓርቲ የከፋፍለህ ግዛ ሴራ ሰለባ ከመሆን ያለፈ ምንም ፋይዳ የለውም። የአንዳንዶች ህልም እስኪሟላ የጋራ ህልም እንዳይሳካ ማጨናገፍ፣ከራስ ህልም ጋር እየዋዠቁ ከመጓዝ ያለፈ የፖለቲካ ፋይዳ የለውም፡፡ ያለፉት የአርባ ዓመታት ታሪካችንም የሚያረጋግጥው ይህንኑ ሃቅ ነው፡፡
ምርጫ 97 እና 2002
በሁሉም መንገድ የ2002 ምርጫ የ1997ቱን አይመስልም፡፡ ኢህአዴግ የ1997ቱ ጎርፍ ተመልሶ እንዳይመጣበት በዓለም ሊኖሩ የሚችሉ ሁሉም ምርጫን የማዛባት ታክቲኮችን ቀምሞ ነበር የጠበቀን፡፡ ከሁሉም በላይ የ1997ቱን የሕዝብ ጎርፍ የቀሰቀሰውን የቀጥታ ስርጭት ክርክር እንዳይኖር አድርጓል፡፡ ጥቂት የተፈቀዱ ክርክሮችም የተደረጉት በተመልካች አልባ ስቱዲዮ በቀጥታ የማይሰራጩ ነበሩ፡፡ በቴሌቪዥንና ሬድዮ እንዲነበብ የሚደረጉ የሳንሱር መቀስን ማለፍ ነበረባቸው፡፡ ህዝባዊ ስብሰባዎችም በብዙ መንገዶች ተተብትበው እንዳይካሄዱ ተደርገዋል፡፡ የተካሄዱትም የ1997ቱን ጎርፍ የሚመስሉ በጥቂት ቦታዎች ብቻ ነበር፡፡ ለአብነት መኪናችንን እንዲሰብሩ የንብ ምክንቶች (ንብ ኢህአዴግ የምርጫ ምልክት ነው) የያዙ ወጣቶች በብዙ ቦታዎች ተሰማርተው መንገድ ይዘጉብን ነበር፡፡ አንዳንድ ቦታዎች እስታዲየሞች ተፈቅዶልን ቁልፍ የያዙ ዘበኞች እንዲሰወሩ ተደርገዋል፡፡ እዚህ ላይ አንባቢው የተሻለ ሥዕል እንዲኖረው ትንሽ ልዘርዝር፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ባልታዬ መንገድ በተደረገው የ1997ቱ ክርክር ውስጥ በተደጋጋሚ ተሳትፎ የነበረኝ ሰው፣በ2002ቱ ምርጫ የተሳተፍኩት አንድ ጊዜ ብቻ ነበር፡፡ እሷም በተደረገችው በጠባብ ስቱዲዮ ያለተመልካች ስትሆን፣ኢህአዴግ ጋዜጠኛ ጠያቂ ሆኖ፣አጠቃላይ ሁኔታውን በተቆጣጠረበት መንገድ ነው፡፡ የቀጥታ ስርጭቱን ስለከለከሉ ፕሮግራሞች ተቆራርጠው ይተላለፉ ነበር፡፡ ኢህአዴግ በፈለገበት ሰዓትና መንገድ ብቻ ነበር የሚቀርቡት፡፡ ንፅፅር ካስፈለገ ጣሊያን የአድዋን ሽንፈትዋን ለመቀበል የቻለችውን ሁሉ ተዘጋጅታ ከ40 ሰዓት በኋላ እንደመጣች ሁሉ ኢህአዴግም የ1997ቱን ሽንፈቱን ለመቀበል ሊያደርግ የሚችለውን ሁሉ አድርጎ ነበር ተዘጋጅቶ የመጣው፡፡ በእንግሊዝ ዲፕሎማቶች አቀናባሪነት (ሴራም ለማለት ይቻላል) አቶ ሃይሉ ሻውልም የፈረሙት ስነ-ምግባር ተብዬው ምን ያክል እንደጎዳን ያወቅሁት ለቅስቀሳ መስክ በወጣሁ ጊዜ ነበር፡፡ “እዚህ ቤተክርስቲያን አለ፣ቅስቀሳ ክልክል ነው፤ እዛ መስጊድ አለ መቀስቀስ አይቻልም፤ ዛሬ ገበያ ነው ቅስቀሳ አይፈቀድም፤ እዚህ ትምህርት ቤት አለ፤ መቀስቀስ ፈፅሞ የተከለከለ ነው” እየተባለ እንቅስቃሴዎቻችንን ገደቡ፡፡ ከሌሎቹ የመድረክ መሪዎች በተለየ መንገድ ለመንቀሳቀስ ስለሞከርኩ ኢህአዴግም እያንዳንዱን እንቅስቃሴዬን ለመቆጣጠር መንቀሳቀሱን ያወቅሁት ከውስጥ ከተገዙት አባሎቻችን፣ ሲፈን ጐንፋ የሚባል ወጣት በመጨረሻ ላይ ከያዘው ለየት ያለ የድምፅ መቅጃ መሣሪያ ጋር የተያዘ ጊዜ ነው፡፡ ይህን ልጅ ብጠረጥር በኦነግነት እንጅ በጭራሽ በመንግሥት ሰላይነት አልነበረም፡፡ ሲፈን እውነተኛ የኦሮሞ ልጅ ለመሆን ስሙን ወደ ኦሮሞ የቀየረና፣ አንድ ጊዜ ኦፒድኦ ብዙ የኦሮሞ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ጂማ ላይ ሰብስቦ የድርጅት አባል እንዲሆኑ የጠየቀ ጊዜ “ኦፒዲኦ ከመሆን እራሴን እሰቅላለሁ” ብሎ ገመድ ይዞ ሲሮጥ ተማሪዎች ተረባርበው እንዳስጣሉት መረጃው ስለነበረኝ፣ በፍጹም ለመንግስት ሰላይ ሆኖ ይሠራል ብዬ አልጠረጠርኩትም፡፡ ከነድምፅ መቅጃው እጅ ከፍንጅ ባይያዝ ኖሮ ሰው ሰላይ ነው ብሎ ቢነገረኝ አላምንም ነበር፡፡ ከመኢሶን ዘመን ጀምሮ በክህደት ባልደነግጥም፣ የዚህኛው ልጅ ትንሽ ገርሞኛል። ፖሊሶች ሊይዙት ሲሉ፣ የያዘውን ወረቀት አኝኮ ውጧል ተብሎ የሚወራለት አበራ የሚባል ዘመዱም እንዲሁ በቀላሉ ከድቶናል፡፡ የኦሮሞ ልጆች ለዓላማቸው ሳይሆን ለሆዳቸው ብለው ሕዝባቸውን ሲክዱ ከመናደድ ይልቅ በጣም ያሳዝነኛል፡፡ ሲፈን ጎንፋ የሚባለውን ልጅ ከኔ ጋር ለቅስቀሳ ወደ ወለጋ ስንሄድ፣ ቶኬ የምትባል የትውልድ አካባቢዬ ላይ ሆዱ እጅግ በጣም ገፍቶ እርጉዝ ሴት የመሰለ ሰው፣ “ኢህአዴግን ለልማት ምረጡ” የሚል መፈክር ይዞ ቆሞ አገኘነው፡፡ ሲፈን ቶሎ ብሎ የዚህን ሰው ያረገዘ ሆድ እያሳየ “የቶኬ ህዝብ በአንተ ሀብት የለማው አንተ ሳትሆን የእሱ ሆድ ነው” ማለቱንና የኢህአዴግ ካድሬዎች የሰበሰቡት ሕዝብ ጭምር ሲስቅበት፣ ሰውዬው አፍሮ ቦርጩንና የኢህአዴግን መፈክር ይዞ መሰወሩ ዛሬም ትዝ ይለኛል፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ሲፈንን ባላየውም ሆዱ እንደዛ ሰው ለምቶ ይሆናል። እሱም የከዳን ከዛ ለተሻለ ዓላማ አይመስለኝም፡፡
“የሐረርጌ ህዝብ ልብ ከናንተ ጋር ነው”
…ከ1997ቱ ምርጫ ይልቅ በሰሜን ሸዋ/ስላሴ በ2002ቱ ምርጫ ብዛት ባላቸው ወረዳዎች ውስጥ ብንወዳደርም፣ እንቅስቃሴያችን ብዙ የተሻለ አልነበረም፡፡ መለስተኛ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ያደረግነው በኩዩና ወረጀርሶ (ጐኃጽዮን) ከተማ ብቻ ነበር፡፡ በቀሩት ከተሞች፣ እንደቡ አቦቴ የነጄኔራል ታደሰ ብሩ ወረዳ ጨምሮ በብዙ ቦታዎች ያደረግነው በጎዳና ላይ ቅስቀሳ ብቻ ነበር፡፡ የመንገድ ላይ ቅስቀሳውን ግን ብዙ ሠርተንበታል፡፡
ከሰላሌ ቀጥሎ ጉዞአችን ወደ አንዱና ትልቁ መሥመራችን የሐረርጌ መሥመር ነበር፡፡ በዚህ መሥመር፣ በሁለት ፓርላማ አባላት የሚመሩ ሁለት ቡድኖችን አስቀድመን አስመርተን ነበር፡፡ እኔ ተከትያቸው ስደርስ፣ በምዕራቡም፣ በምሥራቁም የ1997ቱ ምርጫን የመሰለ የሕዝብ ጐርፍ አልነበርም። ተወዳዳሪዎቻችንም ከጫት ያለፈ ዓላማ የነበራቸው አይመስልም፡፡ ከ90ሺ በላይ ሕዝብ ወጥቶ፣ እኔንም ሰዎች ተሸክመው መድረክ ላይ ያወጡበት የሐረር ከተማ ጭር ብላ ነበር የጠበቀችን፡፡ ሐሮማያ/ዓለማያ ዩኒቨርሲቲ አጠገብ በጠራነው ስብሰባ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንኳ አልነበሩም፡፡ ስብሰባውን ለማዳመጥ ከመጡት ሰዎች የመንግሥት ቪዲዮ አንሺዎች ይበዙ ነበር፡፡ የነበረን ብቸኛ አማራጭ በጎዳና ላይ ሰፊ ቅሰቀሳ አድርገን ወደ ድሬዳዋ ማምራት ነው፡፡ የድሬዳዋ ከተማ የኦሮሚያ ክልልና የሱማሌ ክልል ካድሬዎች የሚራኮቱበት ቦታ ስለሆነችና በከተማው ላይ ስብሰባ የምናካሂድበት ቦታ ስለከለከሉን በሦስት ላንድክሩዘሮች የመንገድ ላይ ቅስቀሳችንን አድርገን ወደጨለንቆ ጉዞአችንን ቀጠልን፡፡ ጨለንቆ ላይ የነበረው አህመድ ነጃሽ የሚባለው ተወዳዳሪያችን የጃራ አባ ገዳ የቅርብ ዘመድ የሆነ ሰው ስለሆነ እራሱን ችሎ ለመንቀሳቀስ የሚችል ነበር፡፡ ከዛ ሁለት ቀን በፊት ደደር ላይ ከባድ ዝናብ ዘንቦ ስብሰባ እንደከለከለን፣ ጨለንቆ ላይም ከለከለን። ተፈጥሮም ከነዚህ ሰዎች ጋር ተባብሮብናል ብለን ወደ ጭሮ አመራን፡፡ ጭሮ ላይ ኦፒዲኦ መሆናቸውን ባይረሱም፣ ቢራ የጋበዙን የኦፒዲኦ ልጆችን አገኘን፡፡ ገለምሶና ጭሮ ላይ መለስተኛ ስብሰባዎችን አድርገን ወደ ሸገራችን ተመለስን፡፡ እንደ ሐረር ከተማው፣ ጭሮም ላይ የ1997ቱን ስብሰባ የመሰለ ነገር ማካሄዱ አልተሳካልንም፡፡ የ1997ቱ ምርጫ ላይ አግኝታኝ የነበረች ልጅ “የህዝብ ብዛቱን አይተህ አትዘን፤ የሀረርጌ ህዝብ ልብ ከእናንተ ጋር ነው” አለችኝ፡፡ በዚሁ ጥሩ ማፅናኛ የሐረርጌን ህዝብንና ምድር ተሰናብተን ጉዟችንን ወደ ሸዋ ቀጠልን፡፡

Page 8 of 16