በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ አርክቴክቸር ህንፃ ግንባታ እና ከተማ ልማት ኢንስቲትዩት ተማሪዎች፣ የጀርመኑ ዊመር ዩኒቨርስቲና በደቡብ ሱዳን ጁባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ትብብር በአስር ቀን ውስጥ የተገጣጠመ ባለ አንድ ፎቅ ህንፃ ዛሬ ለእይታ ይቀርባል፡፡ የህንፃው የመጀመሪያው ወለል የኮንክሪት ምሰሶና የብሎኬት ግድግዳ ያለው ሲሆን ሁለተኛው ወለል (ፎቁ) ከእንጨት እንደተሰራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአርክቴክቸር፣ ህንፃ ግንባታና ከተማ ልማት ኢንስቲትዩት የዲዛይን ክፍል ዳይሬክተር አቶ ብሩክ ተ/ሀይማኖት ገልፀዋል፡፡ ከሶስቱ አገር ዩኒቨርስቲዎች በተውጣጡ 30 ተማሪዎች በ10 ቀን ውስጥ የተገጣጠመው ህንፃ፤ በልደታ ክ/ከተማ ባልቻ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኝ ሲሆን ህንፃውን በዋናነት 20 ተማሪዎች እንደሰሩትና አስሩ ተማሪዎች በረዳትነት እንደተሳተፉበት የዲዛይን ክፍሉ ዳይሬክተር አብራርተዋል፡፡

የጁባና የጀርመኑ ዊመር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለልምድ ልውውጥ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ገልፀው፤ ባለፈው አመት የኢትዮጵያ ተማሪዎች ጀርመን ዊመር ዩኒቨርሲቲ ሄደው የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸውንና የጁባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ዛሬ ረፋድ አምስት ሰዓት ላይ ለእይታ በሚቀርበው ባለ አንድ ፎቅ ህንፃ ምርቃት ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ አምባሳደሮችና የዩኒቨርስቲው ሀላፊዎች እንደሚገኙ ተጠቁሟል። እንደ አቶ ብሩክ ገለፃ፤ አንድን ህንፃ በአጠቃላይ ለመገጣጠም በአማካይ 14 ቀን የሚወስድ ሲሆን የመገጣጠሚያ ቁሳቁስ ተዘጋጅቶ ካለቀ ለመገጣጠም ብቻ ዘጠኝ ቀናት በቂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

Published in ዜና

በኢትዮጵያ መንግስት አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁት ድርጅቶች አንዱ የሆነው የ“ግንቦት ሰባት” አመራሮች ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ እና አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፤ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ መንግስት ከስልጣን ለማውረድ ለሚያደርጉት ሁለገብ ትግል ከኤርትራ መንግስት የጦር መሣሪያ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ሰሞኑን ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ በሰጡት መግለጫ አስታወቁ፡፡ ባለፈው ሰኞ ከሶስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ቨርጂንያ ግዛት የድርጅታቸውን አቋም የገለፁት የድርጅቱ አመራር አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፤ ከኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቅ ጋር በአካል ተገናኝተው እንደተነጋገሩና ከኤርትራ መንግስት ጥሩ ምላሽ ማግኘታቸውን ጠቁመው የመሳሪያ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ ወደ ትጥቅ ትግል እንገባለን ያሉት አቶ አንዳርጎቸው ፅጌ፤ በስብሰባው ተሳታፊ ከነበሩ ሰዎች፤ ለምን ኤርትራን እንደመረጡና ሌላ አማራጭ ሀገር እንዳልፈለጉ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “በአሁኑ ሰአት ባለው ሁኔታ ከኤርትራ የተሻለ ድጋፍ የሚሰጠን የለም” ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ዘግቧል፡፡ “ግንቦት ሰባት” ከአልቃይዳ፣ አልሸባብ፣ ኦነግና ኦብነግ ጋር አሸባሪ ተብሎ በፓርላማ መፈረጁ የሚታወስ ሲሆን የድርጅቱ መሪዎች በሌሉበት የሞትና የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡

Published in ዜና

የ600 ሺህ ብር ቴሌቪዥን ለገበያ አቅርቧል

         አለምአቀፉ የደቡብ ኮሪያ የኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ኤልጂ፣ ከሜትሮ ፒኤልሲ ጋር በመተባበር በመኪና ባትሪ የሚሰራ ቴሌቪዥን ለኢትዮጵያ ገበያ አስተዋወቀ፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት ለገበያ በስፋት እንደሚያቀርብም ተገልጿል፡፡ በከተማችን ሁለትና ሶስት ቀን እየጠፋ ለሚመጣው የመብራት ችግር መፍትሔ ይሰጣል፣ መብራት የሌለባቸውን አካባቢዎችም ታሳቢ አድርጓል የተባለው ባለ 22 ኢንች LED ቴሌቪዥን፤ ከፍተኛ ጥራትና ማራኪ ቀለም ያለው ሲሆን በባትሪም በኤሌክትሪክ ሀይልም መስራት ይችላል ተብሏል፡፡ የኩባንያው የሆም ኢንተርቴይንመንት ረዳት ፕሮዳክት ማናጀር ሚስተር ቢዮጃንግ እንዳብራሩት፤ የቴሌቪዥኑ መጠን 22 ኢንች የሆነው ከመኪናው ባትሪ ጋር ወደተለያዩ ቦታዎች ይዞ ለመንቀሳቀስ ቀላል እንዲሆን ታስቦ ነው፡፡

በ7500 ብር ለገበያ የሚቀርበው ይህ ቴሌቪዥን ከዚህ በፊት ያልተሞከረ የመጀመሪያው ቴክኖሎጂ እንደሆነም ሚስተር ጃንግ አብራርተዋል፡፡ “ማንኛውም የመኪና ባትሪ ሙሉ ቻርጅ ከተደረገ ቴሌቪዥኑ ለ13 ሰዓታት በጥራት መስራት ይችላል” ያሉት ረዳት ፕሮጀክት ማናጀሩ፤ በተለይ የሃይል እጥረትና መቆራረጥ በሚከሰት ጊዜ የቴሌቪዥን ሥርጭት እንዳይስተጓጐል ይታደጋል ብለዋል፡፡ የትኛውም 70 አምፒር ያለው የመኪና ባትሪ፤ ቴሌቪዥኑን እንደሚያሰራውና አጠቃቀሙም ቀላል እንደሆነ ተብራርቷል፡፡ ኤልጂ ከአንድ ወር በፊት በዓለም የመጀመሪያ የተባለውን ባለ 84 ኢንች 3D ቴሌቪዥን ለአገራችን ገበያ አቅርቧል፡፡ በ600ሺህ ብር የሚሸጠው ቴሌቪዥኑ፤ በምስል ጥራቱ እና በአጠቃላይ ይዘቱ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ፈጠራን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡

ከኮምፒዩተሮች ጋር ማገናኘትና የፈለጉትን ዳታዎች ማስተላለፍም እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ በተያያዘ ዜና ኤልጂ “G2 ፍላግሺፕ” ስማርት ስልክ በያዝነው ወር መጨረሻ ወደ አገራችን ሊያስገባ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ስልኩ ሙሉ በሙሉ 3D የሆነ ባለ አምስት ኢንች ስክሪን እንዳለው ታውቋል። ለረጅም ሰዓት የሚዘልቅ ባትሪ በውስጡ በያዘው የፕሮሰሰር አይነት ከአለም ቀዳሚ ስማርት ስልክ እንዲሆን አድርጐታል ሲሉ የኤልጂ ኤሌክትሮኒክስ ሞባይል ክፍል ሃላፊ ዶ/ር ጆንግ ሲኦክ ገልፀዋል፡፡ ባለ 13 ሜጋፒክስል ካሜራ የተገጠመላት ስማርት ስልክ፤ በየትኛውም ሁኔታ ጥርት ያለ ምስል ያስቀራል ተብሏል፡፡ ስልኩ በተጨማሪም የስልክ ጥሪ ለማስተናገድ ወደ ጆሮአችን ስናስጠጋው ራሱ የሚያነሳ ሲሆን እንደ ሪሞት ኮንትሮል (የርቀት መቆጣጠሪያ) መሳሪያም ያገለግላል ተብሏል፡፡

Published in ዜና

በአገራችን እያደገ የመጣውን የእንግዳ አቀባበል (ሆስፒታሊቲ) ኢንዱስትሪ በባለሙያ የታገዘ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የተነገረለት “ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ 2013”፤ ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 2 ቀን 2006 ዓ.ም አዳራሽ ሊካሄድ ነው፡፡ በሶስቱ ቀን የንግድ ትርኢት ከ10ሺህ በላይ ጐብኚዎች እንደሚጠበቁ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡

በንግድ ትርኢቱ ላይ ከ65 በላይ በሆቴል፣ በአስጐብኚ፣ በሆቴል እቃ አቅርቦትና በዘርፉ ተያያዥነት ያላቸው ድርጅቶች እንደሚሳተፉ የአዘጋጁ የኦዚ ትሬዲንግ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቁምነገር ተከተል ተናግረዋል፡፡ የንግድ ትርኢቱ ሆቴሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሆቴል ተጠቃሚ ከሆኑ ድርጅቶችና ተቋማት፣ ኤምባሲዎች፣ አስጐብኚ ድርጅቶች እና የዲፕሎማት ማህበረሰብ ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠር መልካም አጋጣሚ ይሆናል ተብሏል፡፡

ከንግድ ትርኢቱ ጐን ለጐን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስብሰባዎችና ውይይቶች የሚካሄዱ ሲሆን ስብሰባዎቹ በሆቴል ልማት፣ በሰው ሀብት አስተዳደርና በውድድሮች ዙሪያ ከአረብ ኤምሬትስ በመጡ ባለሙያዎች እንደሚካሄዱ ታውቋል፡፡ በአካባቢ ተቆርቋሪነት ዙሪያ ለሚካሄደው ውድድርም እስካሁን ከስምንት በላይ ሆቴሎች መመዝገባቸው ተጠቁሟል፡፡ በሌላ በኩል በሆስፒታሊቲ ዙሪያ አዲስ አስተሳሰብ ያመጡና ሀሳብ ያላቸው ወጣቶች ይሸለማሉ ተብሏል፡፡ የንግድ ትርኢቱ በአመት ሁለት ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ የሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪ መድረክ ለማድረግ መታቀዱን አቶ ቁምነገር ተናግረዋል።

የሆቴል ደረጃን በተመለከተም እስካሁን ያለውን የደረጃ አሰጣጥ ዘመናዊና አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ፣ በተባበሩት መንግስታት የአለም የቱሪዝም ድርጅትና ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ፣ አዲስ መስፈርት በማዘጋጀት፣ በአዲስ አበባና በክልል ባህልና ቱሪዝም፣ እስከ 600 ለሚሆኑ ሆቴሎች ከአንድ እስከ አምስት ኮከብ ደረጃ ይሰጣል ሲሉ የኢፌድሪ ባህልና ቱሪዝም ተወካይ አቶ ሲሳይ ተክሉ ተናግረዋል፡፡ የንግድ ትርኢቱ በነፃ የሚጐበኝ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

Published in ዜና

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ብራዚል ለምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከናይጀሪያ ጋር ወሳኙን የመጀመርያው ጨዋታ ጥቅምት 3 በአዲስ አበባ ስታድዬም ያደርጋል፡፡ ይሁንና መስከረም 28 እና 29 ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን አዲስ አመራሮች በጠቅላላ ጉባዔ ለመሾም እቅድ በመያዙ ለብሄራዊ ቡድኑ የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ትኩረት እንዳያሳጣ ያሰጋል፡፡ ተተኪውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ለማስመረጥ ግልፅ ያልሆነ ዘመቻ በየአቅጣጫው በሚደግ ላይ ነው፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት የሚሆኑ እጩ ተወዳዳሪዎች ማሳወቂያ ጊዜው እስከ መስከረም 15 ቀን 2006 ዓ.ም. ድረስ እንደተራዘመም ታውቋል። ጎን ለጎን በተጧጧፈው የምረጡኝ ዘመቻ የጠቅላላ ጉባዔው ባለድርሻ አካላት መጠመዳቸው አላስፈላጊ መጨናነቅ እየፈጠረ ነው፡፡ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሚቀጥለው ወር ለሚያደርጋቸው የዓለም ዋንጫ የደርሶ መልስ የማጣሪያ ግጥሚያዎች ከፌደሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ አዲስ አመራሮች ምርጫ የቅድመ ትኩረት ያስፈልገዋል።

ስለዚህም በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ፤ የስራ አስፈፃሚዎች እና ፕሬዝዳንት ምርጫ ከብሄራዊ ቡድኑ ወሳኝ ፍልሚያዎች በኋላ መደረግ እንዳለበት እየመከሩ ናቸው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በጥቅምት 3 ለሚጠብቀው ወሳኝ የመጀመርያ ጨዋታ ከትናንት በስቲያ ዝግጅቱን ጀምሯል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ከዝግጅቱ ጎን ለጎን እጅግ የሚያስፈልገውን የአቋም መለኪያ ጨዋታ ከጋናና ካሜሮን ጋር ለማድረግ ጥረት ላይ እንደሆነም እየተገለፀ ነው። ሁለቱም ብሄራዊ ቡድኖች ከኢትዮጵያ ጋር ለመጫወት ፍላጎት ማሳየታቸውም ተዘግቧል፡፡ ከዛምቢያ ጋር ተጨማሪ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ሊኖር ይችላልም ተብሏል፡፡ የወዳጅነት ጨዋታዎቹ በእቅድ ደረጃ መኖራቸው በሰፊው እየተወራ ቢሆንም ግጥሚያዎቹ በእርግጠኝነት ስለመደረጋቸው የተገኘ ማረጋገጫ የለም። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት ከድልድሉ በኋላ ናይጀሪያን በማሸነፍ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ መነሳሳታቸውን ሰሞኑን ሲገልፁ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ደግሞ ከጥሎ ማለፍ ድልድሉ በኋላ በሰጡት አስተያየት በአፍሪካ ዋንጫ ተገናኝተው ከነበረው የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን ስለደረሳቸው ደስተኛ መሆናቸውን በመግለጽ ያለአንዳች ፍራቻ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ጥሩ ፉክክር እናደርጋለን ብለዋል፡፡ የናይጀሪያ ብሔራዊ ቡድን አባላት በበኩላቸው ኢትዮጵያን በቀላሉ በማሸነፍ ለ5ኛ ጊዜ አገራቸውን በዓለም ዋንጫ ለማሳተፍ እንደሚችሉ እየፎከሩ ናቸው፡፡ ናይጄሪያውያን ከዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ድልድሉ በፊት ለጎል ስፖርት ድረገፅ ከኢትዮጵያ ጋር እንደሚደርሳቸው የተነበዩት በአንደኛ ደረጃ 42.2 በመቶ ድምፅ በመስጠት ነበር፡፡

ግምታቸው በመሳካቱም ተደስተዋል፡፡ የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ድልድሉ በይፋ ከተነገረ በኋላም ደስታው ቀጥሏል፡፡ በናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽንና ሌሎች የሙያ ማህበራት የሚሰሩ የተለያዩ ባለስልጣናት ኢትዮጵያን መቶ በመቶ አሸንፈን ዓለም ዋንጫ እንሄዳለን በሚል አስተያየት የአገራቸውን ሚዲያዎች አጨናንቀዋል። ተቀማጭነታቸውን በናይጄርያዋ መዲና ያደረጉ በርካታ የስፖርተ ተንታኞች እና ባለሙያዎች ኢትዮጵያን ጥሎ ማለፍ እንደሚቻል በሙሉ ድምፅ ተንበየዋል፡፡ ኪክኦፍ ናይጄርያ ለተባለ ሚዲያ ‹‹ጥሩ ድልድል አግኝተናል›› ሲሉ የተናገሩት የናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዋና ፀሃፊ ለኢትዮጵያ በደንብ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግና ቀላል ተጋጣሚ ተገኝቷል በሚል መዘናጋት እንዳይፈጠር ሲመክሩ ከፍተኛ አልቲትዩድ ባላት አዲስ አበባ በኢትዮጵያ ደጋፊዎች ፊት የሚደረገው የመጀመርያው ጨዋታ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችልም ገልፀዋል፡፡ የፌደሬሽኑ ፀሃፊ የመልሱ ጨዋታ ከአቡጃ ስታድዬም ይልቅ በካላባር ከተማ በሚገኘው ኢስዋኔ ስታድዬም ቢደረግ ይጠቅማል የሚል ሃሳብም አቅርበዋል። ምክንያታቸውም በአቡጃ ካሉት ደጋፊዎች በካላባር ከተማ ያሉት የተሻሉ ናቸው የሚል ነው፡፡ የአቡጃ ስታድዬም ባለፉት ሁለት ዓመታት ጥገና ላይ በነበረበት ወቅት የብሄራዊ ቡድኑ ጨዋታዎች በካላባር በሚገኘው ዩጄ ኤስዋኔ ስታድዬም ነበር፡፡ ለዚህም ነው ሌሎች የፌደሬሽኑ አንዳንድ ባለስልጣናት ቡድኑ በካላባር እንዲጫወት የፈለጉት፡፡ የፌደሬሽኑ ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረገው ወሳኝ የመልስ ጨዋታ በአቡጃ ወይም በካላባር መደረጉን የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ እና ተጨዋቾች እንደሚወስኑ ይጠበቅ ነበር፡፡

የናይጄርያ ወሳኝ እና ውዱ ተጨዋች የሆነው ጆን ኦቢ ሚኬል እና አንጋፋው ተጨዋች ጄጄ ኦካቻ ከኢትዮጵያ ጋር በመደልደላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ በመድረስ ጥንካሬውን አሳይቷል ያለው ኦካቻ አሁን ያለው የናይጄርያ ቡድን ግን ሙሉ ለሙሉ የማሸነፍ ብቃት እንዳለው ተናግሯል፡፡ ጆን ኦቢ ሚኬል በበኩሉ በአንድነት እና በትኩረት ከሰራን ኢትዮጵያን በሰፊ ውጤት አሸንፎ ለማለፍ እንደማንቸገር ተስፋ አደርጋለሁ ብሎ ተናግሯል፡፡ እስከወሩ መጨረሻ እረፍት ለማድረግ ከቤተሰባቸው ጋር አሜሪካ የገቡት ዋና አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ ግን ናይጄርያውን በዓለም ዋንጫው የጥሎ ማለፍ ድልድል ከኢትዮጵያ ጋር በደረሳቸው ድልድል ከልክ ባለፈ የራስ መተማመን ውስጥ መግባታቸውን አልወደዱትም፡፡ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በማቅለል ወደ ሜዳ አንገባም፣ እነርሱ እዚህ የደረሱት ጠንክረው በመስራታቸው እንጅ በስህተት አይደለም“ በማለት ለቢቢሲ አስተያየት ሰጥተዋል። የናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ቴክኒካል ኮሚቴ ሊቀመንበር ሙሳ ታሌ በበኩላቸው ለዓለም ዋንጫ ጥሎማለፍ ምእራፍ የደረሱት 10 ብሄራዊ ቡድኖች ጠንካሮች መሆናቸውን ሲናገሩ ንስሮቹ ኢትዮጵያን ሽንፈት የማከናነብ አቅም እንዳላቸው ገልፀው በናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን ዝግጅት የወዳጅነት ጨዋታዎች ከአፍሪካ እና ከአፍሪካ ውጭ ከተገኙ ቡድኖች ጋር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በመምከር በተጨማሪም መላው ናይጄርያውያንና በአገሪቱ ያሉት የሃይማኖት ተቋማት ፀሎት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሌሎማላላም ቦላጂ አብዱላሂ የተባሉት የናይጄርያ ስፖርት ሚኒስትር በበኩላቸው ንስሮቹ ኢትዮጵያን እንደቀላል ተጋጣሚ በመመልከት ለዓለም ዋንጫ በታሪካቸው ለአምስተኛ ጊዜ የሚያልፉበትን አጓጊ እድል እንዳያበላሹ አስጠንቀቀዋል፡፡ ናይጄርያው የፊፋ ቴክኒካል ኢንስትራክተር ኦጊቦንዴ ለሱፕር ስፖርት በሰጠው አስተያየት ‹‹እግር ኳስ ዲሞክራት ነው፡፡ በየትኛውም ጊዜ እና ጨዋታ ቡድኖች የሚፋለሙት 11ለ11 ነው። በ1998 ሴኔጋል ፈረንሳይን እንደምታሸንፍ የገመተ አልነበረም። ስለዚህ ኢትዮጵያ ለመቋቋም በትኩረት እና በጥንቃቄ መዘጋጀት ይገባል። የትናንቷ ኢትዮጵያ ከዛሬዋ ጋር በፍፁም አትመሳሰልም። ሰላዮች አሰማርተን እንኳን አቋማቸውን ብናጠና አይበጀንም። ኢትዮጵያውያኑ ኳስ ይዘው ይጫወታሉ፡፡ እኛ ደግሞ በፍጥነት እና በጉልበት እንጠነክራለን፡፡ ይህን ልዩነት በመጠቀም ኢትዮጵያን ጥሎ ማለፍ እንችላለን፡፡›› ብሏል፡፡ የሁለቱ አገራት የቅርብ ዓመታት የእግር ኳስ ታሪክ እንደሚያሳየው ናይጄርያ ኢትዮጵያን በቀላሉ ለማሸነፍ ችግር የለባትም፡፡ ከዓለም ዋንጫው የደርሶ መልስ ትንቅንቆች በፊት ሁለቱ ቡድኖች በአጠቃላይ በሰባት ጨዋታዎች ተገናኝተው ናይጄርያ 4ቱን ስታሸንፍ፤ ኢትዮጵያ አንዱን ብቻ አሸንፋ ሁለቴ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ከወር በኋላ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ በሚደረጉ የመልስ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ እና ናይጄርያ ለስምንተኛ እና ዘጠነኛ ጊዜ ይፋጠጣሉ ማለት ነው፡፡ ጎል ስፖርት በድረገፁ በሰራው ትንተና ናይጄርያ እና ኢትዮጵያ የተገናኙበትን ጨዋታ ከጎልያድ እና ከዴቪድ ፍጥጫ ጋር አመሳስሎታል፡፡

የሁለቱ ቡድኖች ግጥሚያ በወረቀት ላይ ሲታይ ማን የአሸናፊነት ግምት እንደሚኖረው ለመገመት የሮኬት ሳይንቲስት መሆን አይስፈልግም ያለው የጎል ስፖርት ዘገባ ፤ ይሁንና ናይጄርያ ቀላል ግምት የምትሰጣቸውን ቡድኖች ለማሸነፍ ሁሌም ስትቸገር መስተዋሉን ጠቅሶ ፤ ምናልባትም ይህን ሁኔታ በመጠቀም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአፍሪካ ሻምፒዮኗን ናይጄርያ ጥለው በማለፍ እግር ኳስ አፍቃሪ ህዝባቸውን ለዓለም ዋንጫ የሚያስተዋውቁበት ታሪክ ሊሰሩ ይችላሉ ብሏል፡፡ የጥሎ ማለፍ ድልድሉ ይፋ ከሆነ በኋላ ጎል ስፖርት በድረገፁ አንባቢዎችን አሳትፎ በሰራው የውጤት ትንበያ ኢትዮጵያ እና ናይጄርያ በመጀመርያ ጨዋታቸው አዲስ አበባ ላይ ሲፋለሙ 22.2 በመቶ 2ለ0 እንዲሁም 22 በመቶ 1ለ0 በሆነ ውጤት ኢትዮጵያ እንደምታሸንፍ ሲገምቱ ሌሎች 22 በመቶ ደግሞ ናይጄርያ 2ለ1 ከሜዳ ውጭ ታሸንፋለች ተብሏል። በእርግጥም የኢትዮጵያ እና የናይጄርያ የዓለም ዋንጫ ትንቅንቅ የዳዊት እና የጎልያድ ፍጥጫ መሆኑን በተለያዩ ንፅፅሮች ማመልከት ይቻላል፡፡ 5 በከፊል የፕሮፌሽናል ደረጃ ላይ የሚገኙ ተጨዋቾችን በሙሉ ቡድኑ ያካተተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዝውውር ገበያ ተመኑ 775ሺ ፓውንድ ሲሆን ፤ ከ18 በላይ ምርጥ ፕሮፌሽናሎችን በአውሮፓ ታላቅ ሊጎች ያሰማራው የናይጄርያ ቡድን ግምቱ 19.5 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡

የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን በ17 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች በመሳተፍ ሶስት ጊዜ ሻምፒዮን ከመሆኑም በላይ በዓለም ዋንጫ ለአራት ጊዜያት በ1994፤ በ1998፤ በ2002 እና በ2010 እኤአ ላይ በመሳተፍ ከፍተኛ ልምድ ያካበተ ነው። በአፍሪካ ዋንጫ 10 ጊዜ በመሳተፍ 1 ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአንፃሩ በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች ከቅድመ ማጣርያ ምእራፍ ማለፍ ተስኖት የቆየ ነው፡፡ በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ ናይጄርያ ከዓለም 36ኛ ከአፍሪካ 4ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ ኢትዮጵያ ግን ከዓለም 93ኛ ከአፍሪካ 25ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ ቅድመ ትንበያዎችን ፉርሽ ማድረግ ይቻላል? በተለያዩ የስፖርት ዘጋቢ ድረገፆች በ20ኛው የዓለም ዋንጫ አፍሪካን በመወከል ለማለፍ የሚችሉ 5 ብሄራዊ ቡድኖች እነማን እንደሚሆኑ ለመገመት በተሰሩ ቅድመ ትንበያዎች ለመጨረሻው ጥሎ ማለፍ ምእራፍ ከደረሱት 10 ብሄራዊ ቡድኖች ዝቅተኛው የማለፍ ግምት የተሰጠው በተለይ ለኢትዮጵያ ነው ፡፡ በዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ድልድሉ ከኢትዮጵያ እና ከናይጄርያ ፍልሚያ ባሻገር ጋና ከግብፅ ፤አይቬሪኮስት ከሴኔጋል ፤አልጄርያ ከቡርኪናፋሶ እና ካሜሮን ከቱኒዚያ ይገናኛሉ፡፡ በማላዊ የሚሰራ አንድ የዓለም ዋንጫ ብሎግ የሚሰራበት ድረገፅ የአስሩ ብሄራዊ ቡድኖችን የማለፍ እድል ለማስላት አንባቢዎቹን የሰጡትን ድምፅ በመመርኮዝ በሰራው ግምት 19 በመቶ ድምፅ በማግኘት አይቬሪኮስት ግንባር ቀደም ነች፡፡ ጋና 18 በመቶ፤ ናይጄርያ 14 በመቶ ፤ግብፅ 13 በመቶ ፤ ካሜሮን 11 በመቶ ፤ አልጄርያ 7 በመቶ፤ ቱኒዚያ እና ኢትዮጵያ እያንዳንዳቸው 5 በመቶ እንዲሁም ሴኔጋል እና ቡርኪናፋሶ እያንዳንዳቸው 4 በመቶ ለማለፍ እድላቸው ተገምቷል፡፡

ላቲኖስ ስፖርት የተባለው ድረገፅ በበኩሉ በሰፊ ትንተና ባቀረበው ግምታዊ ስሌት ለምእራብ አፍሪካ ቡድኖች ያደላ ትንበያን ይፋ አድርጓል፡፡ እንደላቲኖስ ስፖርት ትንበያ በአምስቱ የጥሎማለፍ ድልድሎች በደርሶ መልስ የሚደረጉትን ጨዋታዎች በማሸነፍ ብራዚል ለምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ አፍሪካን በመወከል የሚያልፉ 5 ቡድኖች ናይጄርያ፤ ጋና፤ አይቬሪኮስት፤ ቡርኪናፋሶ እና ካሜሮን ናቸው ፡፡ ጊቪሚስፖርት በድረገፁ የሰራው ትንበያ ደግሞ ለሰሜን አፍሪካ ቡድኖች ሙሉ የማለፍ እድል በመስጠት አይቬሪኮስት፤ ናይጄርያ፤ ቱኒዚያ፤ ግብፅ እና አልጄርያ ለ20ኛው ዓለም ዋንጫ ይበቃሉ ብሏል፡፡ ታዋቂው ዓለም አቀፍ የስፖርት ዘጋቢ የሆነው ብሊቸር ስፖርት ለዓለም ዋንጫ ጥሎማለፍ ምእራፍ የደረሱትን የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ልምድና ውጤት ያላቸው እና ብዙም ግምት የሌላቸው ቡድኖች እንደተሰባሰቡበት በመግለፅ፤ 10ሩ ብሄራዊ ቡድኖች ያላቸውን ወቅታዊ አቋም እና የፊፋ እግር ኳስ ደረጃ በማገናዘብ ለዓለም ዋንጫ የሚያልፉት አይቬሪኮስት፤ ናይጄርያ፤ ጋና፤ አልጄርያ እና ቡርኪናፋሶ ናቸው በሚል ገምቷል፡፡ ዋልያዎቹ ለዓለም ዋንጫ ቢያልፉ… የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ አፍሪካን በመወከል የሚያልፉ 5 አገራትን ለመለየት ለሚደረግ የጥሎ ማለፍ ትንቅንቅ ከደረሱ አስር ምርጥ ብሄራዊ ቡድኖች ተርታ መሰለፉ ፈርቀዳጅ ውጤት እና ድንቅ ስኬት ነው፡፡ እጅግ የሚያጓጓው ትልቅ ታሪክ ግን በዓለም ዋንጫ መድረክ ለመጀመርያ ጊዜ መሳተፍ ነው፡፡

ለምን ቢባል ለዓለም ዋንጫ ማለፍ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ስለሚኖሩት ነው። የመጀመርያው ጥቅም ኢትዮጵያን በዓለም የእግር ኳስ ካርታ ላይ በወርቃማ ቀለም እንድትሰፍር ማስቻሉ ነው። ይህም የአገሪቱን የስፖርት እንቅስቃሴ በከፍተኛ እድገት ማቀላጠፍ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን የቱሪዝም፤ የዲፕሎማሲ፤ የባህልና የኢኮኖሚ ገፅታ በመገንባት ከፍተኛ ውጤት ይገኝበታል፡፡ ለ20ኛው ዓለም ዋንጫ ከሚሳተፉ 32 አገራት ኢትዮጵያ አንዷ ከሆነች ብሄራዊ ቡድኑ በተሳትፎው ብቻ እስከ 14 ሚሊዮን ዶላር ከፊፋ በኩል የሚከፈለው ይሆናል፡፡ ይሄው የገንዘብ ድርሻ በተለያዩ የስፖንሰርሺፕ ድጋፎች፤ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር የተያያዙ ቁሳቁሶች ሽያጭ እና ንግዶች እስከ 24 ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ አልፎ ከ32 ብሄራዊ ቡድኖች አንዱ ከሆነ በኋላ በምድብ ድልድል ከየትኛውም አገር ጋር መገናኘቱም ሌላው ትልቅ እና የሚያጓጓ ታሪክ ይሆናል፡፡

ለምሳሌ ኢትዮጵያ በምድብ 1 ከብራዚል፤ ከስፔን፤ ከጃፓን ጋር ትመደብ ይሆናል፤ ወይም በሌላ ምድብ ከአሜሪካ፤ ከሆላንድ፤ ከኢራን እና ከጀርመን ልትገናኝ ትችላለች። በአጠቃላይ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ አልፎ ከየትኛውም አገር ተገናኝቶ የሚደለደልበት ምድብ እና የሚያደርጋቸው ሶስት ጨዋታዎች የሚኖራቸው የታሪክ አሻራ ከፍተኛ ትኩረት የሚያስገኝ ይሆናል። የዋልያዎቹ ለዓለም ዋንጫ መብቃት 2006ን በሁሉም ዘርፍ ልዩ የዓለም ዋንጫ ዓመት ያደርገዋል፡፡ ለመጪው እና ተተኪው ትውልድ የሚፈጥረው የአገር ፍቅር መንፈስ እና መነቃቃት በገንዘብ ሊለካ የማይችል ይሆናል፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች በታላቁ የዓለም አቀፍ ውድድር ለመሳተፍ በመብቃታቸው ኢትዮጵያዊ ተጨዋች በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ኢንዱስትሪው ተፈላጊነት ምክንያት ይሆናሉ፡፡ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ በአገር አቀፍ ደረጃ በእግር ኳስ እና በሌሎች ስፖርቶች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ አቅም የሚያድጉበት እድል ከመፈጠሩም በላይ በጅምር እና በእቅድ ያሉ የስፖርት መሰረተ ልማቶች በቶሎ ተገንበተው ስራ እንዲጀምሩ እና እንዲስፋፉ ተፅእኖ ይፈጥራል።

                  በ10ኛው ኮንፌደሬሽን ካፕ የምድብ ፉክክር ውስጥ የከረመው ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጨረሻ ጨዋታውን ከቱኒዚያው ኤትዋል ደሳህል ጋር በአዲስ አበባ ስታድዬም ሲያደርግ የሚያወራርደው ሂሳብ ይኖራል፡፡ በኮንፌደሬሽን ካፑ የምድብ ፉክክር በሚገኝ የደረጃ ውጤት መሰረት ለተወዳዳሪ ክለቦች ብቻ እና ለሚወከሉት የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የገንዘብ ድርሻቸውን እንደሚያከፋፍል ይታወቃል፡፡ በዚህ መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገ ኤትዋል ደሳህልን በ4 የግብ ልዩነት ማሸነፍ ችሎ በምድቡ ሶስተኛ ደረጃ አግኝቶ ከጨረሰ 239ሺ ዶላር በመውሰድ ለወከለው ፌዴሬሽን ደግሞ እስከ 20ሺ ዶላር ሊያስገኝ ይችላል፡፡ ምድቡን በአራተኛ ደረጃ ካጠናቀቀ ደግሞ 150ሺ ዶላር አግኝቶ ለፌዴሬሽን 15ሺ ዶላር ያስገባል፡፡

በአጠቃላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች ታሪክ ወደ ኮንፌደሬሽን ካፕ የምድብ ፉክክር በመግባት የመጀመርያ ክለብ ሆኖ ታሪክ መስራቱ እና ከገንዘብ ሽልማት ተጠቃሚ በመሆን ለፌደሬሽኑም ገቢ ማስገኘቱ የዘንድሮ ስኬቱን ልዩ ያደርገዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ከምድብ ማጣርያው በፊት በነበረው የመጨረሻው የማጣርያ ምዕራፍ በግብፁ ዛማሌክ ተሸንፎ ከተሰናበተ በኋላ በኮንፌዴሬሽን ካፕ ጥሎ ማለፍ የሚሳተፍበትን እድል በማግኘት የኮንፌደሬሽን ካፑን ጉዞ የጀመረው ከሌላው የግብፅ ክለብ ኤን.ፒ.ፒ.አይ ጋር በመገናኘት ነበር። በሜዳው ኢኤንፒፒአይን 2ለ0 አሸንፎ በመልስ ጨዋታው ወደ ካይሮ በመጓዝ 3ለ1 ቢረታም የደርሶ መልስ ውጤቱ 3ለ3 ሆኖ ከሜዳው ውጭ ባስቆጠረ በሚለው ደንብ ወደ ኮንፌደሬሽን ካፕ የምድብ ድልድል ገብቷል፡፡

የ2013 ኮንፌደሬሽን ካፕ የምድብ ፉክክሩን ቅዱስ ጊዮርጊስ የቀጠለው በምድብ1 ከሁለቱ የቱኒዚያ ክለቦች ኤትዋል ደሳህልና ሴፋክሲዬን እንዲሁም ከማሊው ስታድ ደማሌይን በመደልደል ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የምድብ ትንቅንቁን የጀመረው በሜዳው ስታድ ዴ ማሊዬን 2ለ0 በማሸነፍ ነበር፡፡ በሁለተኛው ጨዋታው ከሜዳው ውጭ 2ለ1 በሆነ ውጤት በኤትዋል ደሳህል ተሸነፈ፡፡ በ3ኛው ጨዋታ ደግሞ ባልተጠበቀ ሁኔታ አዲስ አበባ ላይ በሴፋክሲዬን 3ለ1 ተረታ፡፡ በ4ኛው ጨዋታ ሴፋክሲዬን በሜዳው ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግዶ 1ለ0 አሸነፈ፡፡ ከሳምንት በፊት ደግሞ በባማኮ ከማሊው ስታድ ዴ ማሊዬን ጋር በምድቡ አምስተኛ ጨዋታው የተገናኘው 1ለ0 ከተሸነፈ በኋላ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የማለፍ እድሉን በሜዳው የሚወሰንበትን እድል አጥቶታል፡፡

ከምድብ 1 የመጨረሻ ጨዋታዎች በፊት ጊዮርጊስ ባደረገጋቸው 5 ጨዋታዎች 3 ነጥብ እና 3 የግብ እዳ በመያዝ የመጨረሻ ደረጃውን ይዞ ይገኛል፡፡ የቱኒዚያው ሲኤስ ሴፋክስዬን በ5 ጨዋታዎች 13 ነጥብ እና 5 የግብ ክፍያ በማስመዝገብ ምድቡን በመምራት ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፉን አረጋግጧል፡፡ በምድቡ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ የሚገኘው 7 ነጥብ እና 1 የግብ እዳ ያለበት የማሊው ስታድ ዴ ማሊዬን ሲሆን ኤትዋል ደሳህል በ5 ነጥብ እና በ1 የግብ እዳ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኤትዋል ደሳህል በአዲስ አበባ ሲገናኙ በተመሳሳይ ሰዓት ደግሞ በምድቡ ሌላ ጨዋታ ሴፋክሴዬን በሜዳው ስታድ ዴ ማሊዬንን ያስተናግዳል። ኤትዋል ደሳህል ጊዮርጊስን በአዲስ አበባ ካሸነፈ እና ሴፋክሴዬን የማሊውን ክለብ በሜዳው ከረታ ከምድብ 1 ሁለቱ የቱኒዚያ ክለቦች ተያይዘው ለግማሽ ፍፃሜ ያልፋሉ፡፡ በኮንፌደሬሽኑ ካፑ ሌላው ምድብ 2 ደግሞ ከመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች በፊት የዲሪ ኮንጎው ቲፒ ማዜምቤ በ10 ነጥብ እና በ5 የግብ ክፍያ ወደ ግማሽ ፍፃሜ መሸጋገሩን ሲያረጋግጥ በሁለተኛ ደረጃ የማለፍ ሰፊ እድል ይዞ የሚገኘው 8 ነጥብ እና 1 የግብ ክፍያ ያለው የአልጄርያው ሲኤ ቢዘርቴን ነው። የሞሮኮው ኤፍሲ ራባት በ5 ነጥብ እና በ3 የግብ እዳ በምድቡ ሶስተኛ ደረጃ በመያዝ በመጨረሻ ጨዋታው የቤዘርቲንን እድል ለመንጠቅ ተስፋ ያደርጋል፡፡

የክብር ዶ/ር ጥላሁን ገሰሰ መታሰቢያ ዝግጅት በመጪው አርብ ከቀኑ 8 ሰዓት እንደሚቀርብ የኢትዮጽያ ብሔራዊ ትያትር አስታወቀ፡፡ በትያትር ቤቱ በሚቀርበው የሙዚቃ ዝግጅት፣ ከኢትዮጵያውያን አርቲስቶች በተጨማሪ ከሱዳን የመጣ የሙዚቃ ቡድን ጣዕመ ዜማዎችን በነፃ ለታዳሚዎች ያቀርባሉ፡፡ ዝግጅቱ የሚቀርብበት ዕለት ዐርብ መስከረም 17 የከያኒው የልደት ቀን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በሌላም በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ባለፈው ዓመት ክረምት “በመሠረታዊ የቴአትር ጥበብ” ዘርፍ ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ ከጧቱ 3 ሰአት እንደሚያስመርቅ አስታወቀ። 60 ለሚሆኑ ተመራቂዎች ሥልጠናውን በትያትር ዝግጅት ጌትነት እንየው፣ በጽሑፈ-ተውኔት ተስፋዬ ገብረማርያም እንዲሁም በትወና ሳሙኤል ተስፋዬና መሠረት ሕይወት ሥልጠናውን እንደሠጡ ለማወቅ ተችሏል፡፡

“የፍቅር ኬምስትሪ” ተመረቀ፤ “የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገመና” ለንባብ በቃ

በቶሌራ ፍቅሩ ገምታ የተፃፈው “Raayyaa Dhugaa” የተሰኘ የኦሮምኛ ረዥም ልቦለድና የሙሉጌታ ጌቱ “ሰይጣን አሳስቶኝ” የአማርኛ የግጥም መድበል ዛሬ እና ሰኞ በፑሽኪን አዳራሽ እንደሚመረቁ ተገለፀ፡፡ ዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት በማዕከሉ ፑሽኪን አዳራሽ የሚመረቀው የቶሌራ ፍቅሩ ገምታ የኦሮምኛ ረዥም ልብወለድ፣ በኦሮሞ ሕዝብ ማህበራዊ እውነታ ላይ ተንተርሶ የተፃፈ ሲሆን የምረቃ ሥነስርዓቱን የሩስያ ሳይንስና ባህል ማእከል ከኢትዮጵያ ደራስያን ማሕበር እና ከኦሮሞ ደራስያን ማህበር ጋር እንዳዘጋጁት ለማወቅ ተችሏል፡፡

ደራሲው ካሁን ቀደም ‘Immimman Hadhaa’ የተሰኘ ሌላ መጽሐፍ አዘጋጅተው አሳትመዋል፡፡ “ሰይጣን አሳስቶኝ” የተሰኘው የግጥም መድበልም እንዲሁ የፊታችን ሰኞ ምሽት በ11፡30 በማዕከሉ የሚመረቅ ሲሆን የመፅሃፉ ገጣሚ አቶ ሙሉጌታ ጌቱ፣ የባሕል ማእከሉና የኢትዮጵያ ደራስያን ማሕበር አባል ናቸው፡፡ በሌላም በኩል በብርሃኔ ንጉሤ የተዘጋጀው “የፍቅር ኬምስትሪ ሴቶችን የመማረክ ጥበብ” የተሰኘው መጽሐፍ፣ከትላንት በስቲያ ምሽት ተመረቀ፡፡ የመፅሃፉ አዘጋጅ “ኢትዮፒካሊንክ” የተባለው የሬዲዮ ፕሮግራም መስራችና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ብርሐኔ ንጉሴ ሲሆን በ250 ገፆች የተቀነበበው መፅሃፉ፣ በ55 ብር እንደሚሸጥ ለማወቅ ተችሏል። በተማሪዎች አንደበት ተነገሩ የተባሉ እውነታዎችን ያካተተና በሄለን መልካሙ የተዘጋጀ “የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገመና” የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ 134 ገፆች ያሉት መጽሐፍ፣ ለገበያ የቀረበው በ35 ብር ነው፡፡

“የአማርኛ ፊደልን ስለማሻሻል” በሚል ርእስ ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ለሦስት ሰዓታት የሚዘልቅ ውይይት በብሔራዊ ቤተመፃሕፍት አዳራሽ እንደሚያካሂድ ሚዩዚክ ሜይዴይ አስታወቀ። ከአሁን ቀደም በርእስ ጉዳዩ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ የመነሻ ሀሳብ በማቅረብ ውይይቱን ይመሩታል ተብሏል፡፡

Saturday, 21 September 2013 11:19

ዝምተኛው ገዳይ! (Silent Killer)

  • የደም ግፊት መነሻዎች፣ ምልክቶችና ጥንቃቄዎች
  • ወንዶች ከሴቶች የበለጠ በደም ግፊት የመያዝ ዕድል አላቸው በአገራችን የደም ግፊት ህሙማን ቁጥር 30 ሚ. ይደርሳል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በሽታው እንዳለባቸው እንኳን አያውቁም

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቆ ሥራ ከጀመረ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የተደላደለ የሰውነት አቋም ነበረው፡፡ ጤናማና ንቁ የ26 ዓመት ወጣት በነበረበት ወቅት ምኞቱና ህልሙ ትምህርቱን መቀጠልና በተሰማራበት የሥራ መስክ ስሙን ሊያስጠራ የሚችል ተግባር ማከናወን ነበር፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ይህን ህልሙን ማሳካት እንደሚችልም እርግጠኛ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ራሱን ከተለያዩ ሱሶች ጠብቆ ትምህርቱን ለመቀጠል የሚያስችለውን ገንዘብም ማጠራቀም የጀመረው፡፡ ምንም ዓይነት የህመም ስሜት ስለማይሰማው ጤናማነቱን ተጠራጥሮት አያውቅም፡፡ “እንኳን እሱ እራሱ እኛም የከፋ በሽታ ቀርቶ ጉንፋን እንኳን ጠንከር ብሎ ይይዘዋል ብለን አናስብም ነበር” ይላል ታናሽ ወንድሙ ዳንኤል ታደሰ፡፡ ሆኖም የዚህን ወጣት የረጅም ጊዜ ህልምና ምኞት የሚያጨልምና ከህይወት ሩጫው የሚያስተጓጉል አጋጣሚ በአንዲት ክፉ ቀን ገጠመው፡፡

“የዛን ዕለት ቀኑን በሥራ አሳልፎ ወደቤቱ የተመለሰው በሠላም ነው፡፡ ወንደላጤ ስለሆነ ምሽቱን የሚያሳልፈው በላፕቶፑ ላይ በሥራ ተጠምዶ ነው። ብቻዬን ከምሆን ብሎ እኔን ከወላጆቼ ቤት እሱ ጋ ሲወስደኝ ሠላሙንና ፍላጐቱን መጠበቅና ማክበር እንዳለብኝ አስጠንቅቆኝ ስለነበር ሥራ ከጀመረ በኋላ በምንም አይነት ሁኔታ አልረብሽውም፡፡ የዛን ዕለት ምሽትም እራታችንን ከበላን በኋላ አጠገቡ ድርሽ አላልኩም፡፡ እስከሌሊቱ አጋማሽ ድረስ ላፕቶፑ ላይ ሲሰራ አምሽቶ ወደመኝታው ሲሄድ፣ በሰመመን ሰምቸዋለሁ፡፡ ንጋት ላይ ከወትሮው በተለየ ከአልጋው ላይ ሳይነሳ መቆየቱ እንግዳ ነገር ሆነብኝ። ብዙውን ጊዜ ምሽት ላይ የተረፈውን ሥራ ንጋት ላይ አጠናቆ፣ በማለዳ ወደ ሥራው ነው የሚሄደው፡፡ የዛን ዕለት ግን ከመኝታው ሳይነሳ ሰዓቱ ረፈደ፤ ሁኔታው ግራ አጋብቶኝ ልቀስቅሰው ወደ ክፍሉ ስገባ፣ ከአልጋው ወድቆ ወለሉ ላይ እጥፍጥፍ ብሎ አየሁት፡፡ በድንጋጤ እሪ ብዬ ጮህኩ፡፡ ሰዎች ደርሰው ስናየው ትንፋሹ አለች፤ ይዘነው ወደ ሆስፒታል በረርን፡፡” ሲል ታናሽ ወንድም በዕለቱ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል፡፡

ወጣቱ ቀደም ሲል መኖሩን እንኳን የማያውቀው የደም ግፊት በሽታ ባስከተለበት መዘዝ ሳቢያ፣ የደም ቧንቧዎች መዘጋት ችግር (ስትሮክ) ገጥሞት ሰውነቱን መቆጣጠር አቃተው፡፡ መነጋገርና ሽንትና ሠገራውን መቆጣጠር የማይችል ሰው ሆነ፡፡ የዚህ ወጣት አሣዛኝ ህይወት አሀዱ ብሎ የተጀመረው እንዲህ ነው፡፡ ገና ሮጦ ባልጠገበበት፣ የረዥም ጊዜ ህልሙን ሰንቆ ከህይወት ጋር ግብ ግብ በጀመረበት የአፍላነት ዕድሜው፣ ከአልጋው ላይ ያለሰው ድጋፍ መነሳት የማይችል ህመምተኛ ሆነ፡፡ በጥቁር አንበሣ ሆስፒታል በተደረገለት የህክምና እርዳታ ህይወቱ ሊተርፍ ቢችልም በህይወት ዘመኑ ሁሉ አብሮት የሚኖር የአካል ጉዳት ገጠመው፡፡ ቤተሰቦቹ ህይወቱን ለማትረፍና ወደ ቀድሞው እሱነቱን ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉለትም አልተሳካላቸውም፡፡ ረዘም ባለ የህክምና ክትትል በሰው ድጋፍ መንቀሣቀስ፣ ሽንትና ሠገራውን መቆጣጠር ቢችልም ዛሬም ወደ ሥራው መመለስና ሃሳቡን እንደልቡ በንግግር መግለፅ አልቻለም። ወጣቱን ለንግግር የሚረዳ ህክምና (Speech Therapy) በአገሪቱ በብቸኝነት በሚሰጥበት የካቲት 12 ሆስፒታል ውስጥ ሲሆን በሆስፒታሉ ህክምናውን ለማግኘት ተመዝግበው ረዥም ቀጠሮ ከሚጠባበቁት ህሙማን መካከል አንዱ ነው፡፡

ህክምናውን በአገራችን ውስጥ የምትሰጠው ባለሙያ አንዲት ብቻ ስትሆን ህክምናውን የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ ለረዥም ጊዜ ተራ መጠበቅ የግድ ሆኗል፡፡ ባላሰበውና ባልጠበቀው ሁኔታ የ26 ዓመቱን ወጣት አልጋ ላይ ያዋለው የደም ግፊት በሽታ፤ አሁን አሁን በአገራችን በስፋት የሚታይና የተለመደ በሽታ ለመሆን እንደቻለ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የአለም ጤና ድርጅት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአሜሪካ ብቻ ከ45 ሚሊዮን በላይ የደም ግፊት ህሙማን አሉ፡፡ ዘመኑ የተራቀቀ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን መጠቀም የሚያስገድድበት ጊዜ በመሆኑ፣ ሰዎች እንደልብ ተንቀሳቅሰው እንዳይሰሩ ማድረጉና የጣፋጭና ፈጣን ምግባች ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱ እንዲሁም የሰዎች የዕለት ተዕለት ህይወት በውጥረትና በጭንቀት የተሞላ እየሆነ መምጣቱ በደም ግፊት በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እንዲያሻቅብ አድርጐታል፡፡ በአገራችንም በአግባቡ የተደረገ ጥናትና ቆጠራ ባይኖርም የደም ግፊት ህሙማን ቁጥር ከሃያ አምስት እስከ ሰላሣ ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል የሚናገሩት የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ተስፋሁነኝ ታዴ፤ የኑሮ ውጥረቱ፣ ጭንቀትና የተዛባ የአመጋገብ ሥርዓት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር እንዲበራከት ምክንያት መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ በሰውነታችን ውስጥ ጤናማ የሚባለው የደም ግፊት መጠን የታችኛው ዲያስቶሊክ (Diastolic) 80፣ የላይኛው ሴስቶሊክ ደግሞ ከ120-130 ድረስ ሲሆን ነው የሚሉት ዶ/ር ተስፋሁነኝ፤ የታችኛው ከ90 በላይ፣ የላይኛው ደግሞ ከ140 በላይ ከሆነ ከፍተኛ የደም ግፊት መኖሩን ጠቋሚ እንደሆነና ሰውየው (ሴትየዋ) አደጋ ላይ መሆናቸውን እንደሚያመላክት ይገልፃሉ። ዝምተኛው ገዳይ (silent killer) እየተባለ የሚጠራው የደም ግፊት በሽታ፤ ይህንን ስያሜውን ያገኘው ያለአንዳች ማስጠንቀቂያና ምልክት ለህልፈተ ህይወት በመዳረጉ ነው፡፡ የደም ግፊት ህመም (hyper tension) በደም ቧንቧዎች መጥበብ ወይም በግድግዳዎቹ እንደልብ መለጠጥ አለመቻል ሳቢያ የሚከሰት ህመም ሲሆን ምልክቶቹ ከባድና ድንገተኛ ራስ ምታት፣ ትኩሳት፣ ማጅራትን ጨምድዶ መያዝ፣ ጭንቅላት ላይ የማቃጠል ስሜትና የልብ ድካም ናቸው፡፡

የደም ግፊት በሽታ ከያዛቸው ሰዎች መካከል 40 በመቶ የሚጠጉት በሽታው እንዳለባቸው እንኳን የማያውቁና ህክምና የማይከታተሉ ናቸው፡፡ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው የደም ግፊት መከሰቻው በውል የማይታወቅ ሲሆን በበቂ ምክንያቶች የሚከሰተው የደም ግፊት ከአስር በመቶ በታች ነው። ለደም ግፊት መከሰቻ ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የዘር ውርስ፣ የኩላሊት በሽታ፣ የነርቭና የልብ ሥርዓት መቃወስ፣ የሆርሞን መዛባት፣ በጣፋጭና በቅባት የተሞሉ ምግቦች፣ የማያንቀሳቀስ ስራ፣ የዕድሜ መግፋት፣ ጨው በብዛት መመገብ፣ ጭንቀትና ውጥረት ይገኙበታል፡፡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በህክምና እርዳታም ሆነ በሌሎች መንገዶች በቁጥጥር ስር ያልዋለ የደም ግፊት፣ ግፊቱ እየጨመረ ሄዶ በደም ስሮች ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር፣ ደም ስሮቹ እንዲደድሩና ደም እንደልብ እንዳይዘዋወሩባቸው ያደርጋል፡፡ ይህም ለከፋ የጤና ችግርና ለሞት ሊዳርግ እንደሚችል የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ከእነዚህ የጤና ችግሮች መካከል ደም በሚፈለገው መጠን ወደ ኩላሊት እንዳይገባ በማድረግ ኩላሊት የተለመደ ተግባሩን በአግባቡ እንዳያከናውን ማዳከም፣ ደም በአንጐል ውስጥ እንዲፈስ ማድረግ፣ የልብ የደም ቧንቧዎችን መዝጋትና ማጥበብ ዋንኞቹ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ማንኛውም የደም ግፊት ያለበት ሰው መድሃኒት መውሰድ እንደሚገባው የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ የአኗኗር ዘይቤን በመቀየር፣ ክብደትን በመቀነስና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማድረግ ብቻ ደም ግፊትን ማስቀረት ወይም ማጥፋት ይቻላል የሚለው ግምት የተሳሳተ መሆኑን የሚናገሩት ባለሙያዎች፤ ክትትል ያልተደረገለትና መድሃኒት ያላገኘ የደም ግፊት በድንገት ለከፍተኛ ችግርና ለአደጋ ሊያጋልጥ እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ፡፡

የደም ግፊት መድሃኒትን በመውሰድ በግፊቱ ሳቢያ የሚከሰተውን ሞት 13 በመቶ፣ ከደም ግፊቱ ጋር ተያይዞ የሚከሰት የስትሮክ (በአንጐል ውስጥ ደም የመፍሰስ ችግር) 42 በመቶ፣ የልብ ድካምን ደግሞ 28 በመቶ ማስቀረት እንደሚቻል ዶ/ር ተስፋሁነኝ ይናገራሉ፡፡ የደም ግፊት በሽታ ከሴቶች ይልቅ በወንዶች ላይ በስፋት እንደሚታይ በርካታ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ወንዶች በተፈጥሮአቸው ከሴቶች የበለጠ የቁጡነት ባህርይ ስላላቸውና በጭንቀት በቀላሉ ስለሚጠቁ ሲሆን የወንዳወንድነት ሆርሞን በደማቸው ውስጥ በብዛት መኖሩና ይህም ባህርይን የመለወጥ አቅም ስላለው ወንዶች ከሴቶች ይልቅ በከፍተኛ ደም ግፊት የመያዝ ዕድል እንዳላቸው ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ የደም ግፊት ችግሮችን ከሚያባብሱ ነገሮች መካከል ሲጋራን ማጨስ፣ አልኮል አብዝቶ መጠጣት፣ በዘር ወይም በቤተሰብ በደም ግፊት በሽታ የተጠቃ ሰው መኖር፣ የጣፊያ ወይም የስኳር በሽታ፣ ጨው በብዛት መመገብ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ጨውን አብዝቶ መመገብ የደም ግፊትን በከፍተኛ ደረጃ የሚያባብስ ከመሆኑም በላይ የደም ግፊት መድሃኒቶች በአግባቡ እንዳይሰሩም ያደርጋል፡፡ ቡና መጠጣት ለደም ግፊት ህሙማን የማይመከርና በሽታውን ለማባባስ አስተዋፅኦ እንዳለው በተደጋጋሚ ቢነገርም ይሄን እውነታ የሚያረጋግጥ መረጃ በቅርቡ አለመውጣቱን ጥናቶቹ ጠቁመዋል፡፡

የደም ግፊት በሽታ ከመከሰቱ በፊት ሊደረጉ ከሚገባቸው ጥንቃቄዎች መካከል የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ፣ የአመጋገብ ስርዓትን ማስተካከል፣ በየጊዜው የጤና ምርመራዎችን መከታተል፣ ራስን ከጭንቀትና ውጥረት ማላቀቅ፣ ክብደትን መቀነስና ጣፋጭና ቅባት ነክ ምግቦችን ማስወገድ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ችግሩ ከተከሰተ በኋላም ህመምተኛው ክብደቱን በመቀነስ፣ የእግር ጉዞ እንቅስቃሴዎችን በማድረግና ጨውና ቅባት አልባ ምግቦችን በመመገብ የደም ግፊትን ለማስወገድና በግፊቱ ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉትን አደጋዎች ለመቀነስ ይችላል፡፡ ፖታሺየም ለደም ግፊት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ንጥረ ነገር ሲሆን ፖታሺየም በአብዛኛው በሙዝ፣ በቲማቲምና ቅጠላቅጠሎች ውስጥ በስፋት ይገኛል፡፡ ስለዚህም የደም ግፊት ህሙማን ፖታሺየም ያላቸውን ምግቦች ቢመገቡ ግፊቱ እንዲወርድና ጉዳት እንዳይደርስ በማድረግ ሊከላከሉት ይችላሉ፡፡ ከልክ ያለፈ ፖታሺየም መመገብም ለከፍተኛ አደጋና ለጉዳት ሊዳርግ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ ዕድሜና ፆታ ሳይለይ ባልታሰበ ጊዜና ሰዓት ለአካል ጉዳተኝነትና ለሞት ሊዳርግ የሚችለው የደም ግፊት በሽታ፤ ዛሬ የዓለማችን ሁሉ ሥጋት ሆኗል፡፡ እናም ይህንን አስከፊ በሽታ ለመከላከል የጤና ምርመራ ማድረግና በሽታው እንዳለብን ባወቅን ጊዜም ተገቢውን ህክምና በመከታተል ልንቆጣጠረውና በእሱ ሳቢያ ሊመጡ የሚችሉ አደጋዎችን ልናስወግዳቸው ይገባል፡፡

Published in ዋናው ጤና
Page 4 of 16