Saturday, 07 September 2013 10:57

ካልዲስ ኮፊ

በ30ሚ ብር የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ከፈተ
በ200ሺ ብር ጀምሮ 11 ሚሊዮን ብር ደርሷል
አንድም ካፌ ፍራንቻይዝ አልተደረገም
በቅርቡ የታሸገ ወተት ለገበያ ያቀርባል
17 ቅርንጫፎችና 1,200 ሠራተኞች አሉት
ቦሌና ዙሪያውን አራት ቦታ፣ 22 አካባቢ ትራፊክ ጽ/ቤትን ተሻግሮና ሳይሻገሩ፤ መገናኛ፣ በቅሎ ቤት (ላንቻ)፣ ሳር ቤት፣ ሜክሲኮ፣ ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ፣ ፊላሚንጐ፣ ጉርድ ሾላ፣ ጥቁር አንበሳ ት/ቤት አካባቢ ኢ.ኢ ኤ፣ ብትሄዱ፣ አንድ የሚያጋጥማችሁ ካፌ አለ - ካልዲስ ኮፊ፡፡
አቤት! ጊዜው እንዴት ይሮጣል! ካልዲስ ኮፊ “ሀ” ብሎ ሥራ የጀመረው የዛሬ 10 ዓመት ነው -በ1995 ዓ.ም፡፡ የመጀመሪያው ካፌ ከኤድናሞል ፊት ለፊት ባለው አደባባይ አጠገብ የተከፈተው ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ በወ/ሮ ፀደይ አሥራትና በካፒቴን ዳንኤል ከተማ ካልዲስ ኮፊ ኃ.የተ.የግማ (ፒ ኤል ሲ) ሆኖ የተቋቋመው በ1998 ዓ.ም ነበር፡፡
አንዳንድ የንግድ ድርጅቶች ለ10 ዓመት ወይም ከዚያም በላይ ባሉበት ይቆያሉ። አንዳንዶቹ ሁለትና ሦስት ሊያደርሱት ይችላሉ፡፡ ጥቂቶች ደግሞ ከዚያም በላይ ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ የካልዲስ ግን የሚገርም ሆነብኝ፡፡ በብዙዎቹ የመዲናዋ አካባቢዎች ካልዲስ ካፌን መመልከት የተለመደ ሆኗል።
የስኬቱ ምክንያት ምንድነው በማለት ባለቤቴን ማነጋገር ፈለግሁና ወደ ካልዲስ ካፌ ጽ/ቤት ሄጄ ለምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ ለአቶ ተስፋዬ ደገፉ የመጣሁበትን ምክንያት ነገርኳቸው፡፡
እሳቸውም ምክንያቴን ካዳመጡ በኋላ፣ ባለቤቶቹን ማግኘት እንደማልችል፣ የምፈልገውን መረጃ ከእሳቸው ማግኘት እንደምችል ነግረውኝ አጭር ቀጠሮ ሰጡኝ። በቀጠሮዬ ቀን ስንገናኝ አቶ ተስፋዬን ካልዲስ ስንት ቅርንጫፎች አሉት በማለት ቃለምልልሴን ጀመርኩ፡፡

 

አሁን 17 ቅርንጫፎች አሉን፡፡ በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ወር 18ኛውን ቅርንጫፋችንን እንከፍታለን፡፡
የት?
ቦሌ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን አካባቢ፣ በአትሌት ብርሃኔ አደሬ ሕንፃ ላይ ይከፈታል፡፡
የካልዲስ ካፌ የስኬት ምስጢር ምንድነው?
ድርጅታችን በከተማችን ውስጥ በተመሳሳይ ዘርፍ ከተሰማሩ ድርጅቶች በተለየ ሁኔታ እያደገ ያለ ኩባንያ ነው፡፡ ለዕድገቱ ዋናው መሠረት፣ ሠራተኛው ለሥራ ያለው ጠንካራ ዲሲፕሊን፣ የሥራ አመራር አካሉ በወጣቶች የተገነባ መሆን፣ ሁልጊዜ ለለውጥና ለጥራት በጋራ የሚሠራ የሥራ አመራር ጥረትና ውጤት ነው ለዚህ ያበቃን፡፡
ድርጅታችን ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ በፈጣን ዕድገት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለድርጅታችን ግብዓት የሚሆኑትን ወተትና ዕንቁላል የመሳሰሉትን ምርቶችን ለማምረት አንዳንድ ጥረቶች ጀምሯል፡፡ ለዚህም በቅርቡ በሱልልታ ከተማ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንት አድርጐ የወተትና የወተት ተዋጽኦ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አቋቁሞ፣ ለራሱ የሚያስፈልገውን የወተትና የእርጐ ምርት ከተጠቀመ በኋላ፣ የተረፈውን ገበያ ውስጥ በማስገባት ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ፋብሪካ ለጊዜው ከ35 በላይ ለሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ወደፊት የወተት ማቀነባበሪያውን ሥራ ከጨረስን በኋላ፣ ለድርጅቱ ግብአት የሚሆኑ ምርቶችን የማምረት ዕቅድ አለው። ያኔ የሠራተኛው ቁጥር ይጨምራል፡፡
በማቀነባበሪያው ምን ምን ታመርታላችሁ?
እስካሁን ድረስ ቅቤ፣ አይብና ፓስቸራይዝድ ወተት ለራሳችን ነው የምናቀርበው፡፡ አሁን ግን ፍላጐቱ (ዲማንዱ) ከፍተኛ ስለሆነ ገበያ ውስጥ በስፋት ለመግባት እቅድ አለን፡፡
ወተቱን ከየት ነው የምታገኙት? የራሳችሁ ላሞች አሏችሁ እንዴ?
እኛ ላሞች የሉንም፡፡ ወተቱን የምናገኘው ከአካባቢው ገበሬ አሰባስበን ነው፡፡
ለካፌዎቻችሁ በቀን ምን ያህል ወተት እንቁላል፣ ስኳር… ትጠቀማላችሁ?
ለትኩስ መጠጦችና ለኬክ ሥራ በቀን በአማካይ ከ1,200 ሊትር በላይ ወተት እንጠቀማለን፡፡ እንቁላል ለፋስት ፉድና ለኬክም ግብአት ስለሆነ በቀን በአማካይ ከ15 ሺህ በላይ እንጠቀማለን። አሁን እንቁላል የምናገኘው ከኤልፎራ ነው፡፡ ወደፊት የወተት ማቀነባበሪያው ሥራ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ፣ የራሳችንን የእንቁላል ምርት ለማቅረብ አቅደናል፡፡ ቦታውም ተዘጋጅቷል፤ የሚቀረን ወደ ሥራ መግባቱ ነው፡፡ ስኳር በቀን ከሦስት ኩንታል በላይ እንጠቀማለን፡፡ ወደፊት የካፌዎቹ ቁጥር ሲጨምር የምንጠቀማቸው ግብአቶችም ይጨምራል፡፡
ካልዲስ ፍራንቻይዝ አድርጐ (ስሙን ሽጦ) ሸጧል፡፡ አንዳንድ ካፌዎች የእሱ አይደሉም ይባላል። ይኼ ምን ያህል እውነት ነው?
ውሸት ነው፡፡ ካልዲስ ኮፊ በአሁኑ ወቅት አንድም ቅርንጫፍ ፍራንቻይዝ አላደረገም፡፡ ማኔጅመንቱም፣ ሀብቱም በራሱ ነው፡፡ ፍራንቻይዝ እንድናደርግ ከአገር ውስጥም ከውጪም ለምሳሌ፣ ከቻይና ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን በተደጋጋሚ ጥያቄ ቀርቦልናል፡፡ ድርጅታችን አሁን ባለበት ሁኔታ ራሱን ለማስተዳደር፣ በፋይናንስም ሆነ በማኔጅመንት በቂ አቅም አለው፡፡ ስለዚህ ፍራንቻይዝ የምናደርግበት ምክንያት የለም፡፡
እቅዳችሁ ስንት ካፌ መድረስ ነው? ካልዲስ ዋጋው ውድ ነው የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ ምን ይላሉ?
የእኛ ዋጋ ውድ አይደለም፡፡ አንዳንድ ማቴሪያሎች ለምሳሌ አይስክሬም ከውጭ ነው የምናስመጣው፡፡ በከተማችን ያሉ አንዳንድ ካፌዎች ማኪያቶና ቡና በ10 ብር ነው የሚሸጡት፡፡ እኛም በ10 ብር ነው የምንሸጠው፡፡ ስለዚህ ውድ ነው የሚባል አይደለም፡፡ ከምንሰጠው አቅርቦት ጋር ሲተያይ ሚዛናዊ (ፌየር) ነው፡፡
ዕቅዳችን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 40 ካልዲስ ካፌዎች መክፈት ነው፡፡ ዕቅዳችንን ካሳካን በኋላ ከአዲስ አበባ ከተማ መውጣት ነው ሃሳባችን፡፡ ይህንንም የምናደርገው ወደ ክልል ከተሞች ወጥተን ቅርንጫፍ ካፌዎች ለመክፈትና ለመምራት ጠንካራ የፋይናንሻልና የማኔጅመንት አቅም አለን ወይ? ብለን ጠይቀን ስናምንበት ነው፡፡
ካልዲስ ሲመሠረት ካፒታሉ ምን ያህል ነበር? አሁንስ?
ካልዲስ ሲመሠረት ካፒታሉ 200ሺህ ብር ነበር። አሁን ከ10 ዓመት በኋላ፣ ለእህት ኩባንያዎች (ሱሉልታ ላይ የተገነባው የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካና ለእንቁላል ማምረቻ) የወጣውን ሳይጨምር ካፒታላችን በአሁኑ ወቅት 11 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡
በቀረጥና በታክስ በዓመት ምን ያህል ብር ለመንግሥት ታስገባላችሁ?
በታክስ፤ በቀረጥና በመሳሰሉት በዓመት ወደ መንግሥት ካዝና 12 ሚሊዮን ብር ፈሰስ በማድረግ ኢኮኖሚውን እንደግፋለን፡፡
አንድ ካልዲስ ካፌ ለመክፈት ስንት ብር ያስፈጋል?
በከተማው ውስጥ የቤት ኪራይ በጣም ውድ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ቢያንስ የ6 ወር ኪራይ መክፈል ግዴታ ነው፡፡ ይህንን ሳይጨምር የካፌዎቻችን ዕቃዎች (ጠረጴዛና ወንበር) ከፍተኛ ጥራት ያላቸውና ከውጭ የሚመጡ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የውስጥ ዕቃዎችን ለማሟላትና አስውቦ (ዲኮር አድርጐ) አንድ ካፌ ለመክፈት ቢያንስ 200ሺህ ብር ይጠይቃል፡፡
ካልዲስ ስንት ሠራተኞች አሉት?
በሁሉም ካፌዎች የሚሠሩ 1,200 ሠራተኞች አሉን፡፡
ሁሉም ካፌዎች አንድ ዓይነት ዕቃ በመግዛት ተመሳሳይ መልክ እንዲኖራቸው ማድረግ ይቻላል። የሰው ልጅ ግን አንድ ዓይነት ባህርይ አይኖረውም። እንዴት ነው ታዲያ ሠራተኞቻችሁ በሁሉም ካፌ ተመሳሳይ መስተንግዶ እንዲሰጡ የምታደርጉት?
በሥልጠና ነው፡፡ የራሳችን የሆነ የሥልጠና ማዕከል አለን፡፡ ሠራተኞቻችንን ቀጥረን ወደ ሥራ ከማሰማራታችን በፊት ወደማሠልጠኛው ገብተው የንድፈ ሐሳብ (የቲዎሪ) ትምህርት እንዲቀስሙና የተግባር ልምምድ እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ ከዚያ በኋላ፣ ድርጅቱ የራሱ መመዘኛ ስላለው፣ ያንን መለክያ ያለፉትን ብቻ ቀጥሮ ወደሥራ ያስገባቸዋል። ከዚህም በተማሪ በሁሉም ዘርፍ ለተሰማሩ ሠራተኞች በመስተንግዶ፣ በቁጥጥር፣ በምርት ሥራ ላይ የተሰማሩትን በየጊዜው የሥራ ላይ ሥልጠና በመስጠት ክህሎታቸውን እናዳብራለን፡፡ ቁጥጥር በማድረግ፣ ጉድለት ለሚታይባቸው ሠራተኞች ሥልጠና እንሰጣቸዋለን፡፡ ሠራተኞቻችን ተመሳሳይ መስተንግዶ የሚሰጡት ከአንድ የሥልጠና ማዕከል ስለሚወጡ ነው፡፡
ሥልጠናውን የሚሰጠው ማነው?
ሥልጠናው የሚሰጠው በተለያዩ የኦፕሬሽን ክፍሎች ነው፡፡ ከኦፕሬሽን ክፍሉ ሥራዎች አንዱ በየቅርንጫፉ እየተዘዋወረ ቁጥጥር ማድረግ ነው። ቁጥጥር አድርጐ ጉድለት ሲገኝ ወዲያውኑ እንዲታረም ያደርጋል፤ የሠራተኞችንም የሥራ አፈጻጸም ይገመግማል፡፡ ዕድገት የሚያስፈልጋቸው ሠራተኞች ካሉ ዕድገት እንዲያገኙ ያደርጋል፤ ድክመት ያለባቸው ሠራተኞችም ካሉ ሥልጠና አግኝተው ከሌሎች ጋር የተስተካከለ መስተንግዶ እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡
ታታሪ ሠራተኛ ያድጋል ብለዋል፡፡ እንዴት ነው የሚያድገው?
በካልዲስ የዕድገት በሩ ክፍት ነው፡፡ ነገር ግን ማንም ዘው ብሎ የሚገባበት አይደለም፡፡ አንድ ሠራተኛ በተመደበበት ስፍራ ብቃት ካለው፣ ድርጅቱ በሚፈልገው መንገድ ኃላፊነቱን የሚወጣ ከሆነ ዕድገት ያኛል፡፡ ለምሳሌ ከመስተንግዶ ላይ ተነስተው የአመራር አባል በመሆን ከፍተኛ ዲፓርትመንቶችን የሚመሩ ሠራተኞች አሉ። እነዚያን ሠራተኞች፣ ምንም ሙያ ሳይኖራቸው ተቀብለን አሠልጥነን በየጊዜው ክትትል በማድረግ ነው ለዚህ ያበቃናቸው፡፡ በሩ ክፍት ነው ስል፣ ብቃት ያለው፣ የድርጅቱ አሠራር ሲስተም የገባቸውና ጥረት የሚያደርጉትን ማለቴ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ በትላልቅ ድርጅቶች (በባለ 5 ኮከብ ሆቴሎች ሁሉ) ሠራተኛውና ማኔጅመንቱ አይስማሙም፡፡ ያለመግባባት እየተፈጠረ ፍ/ቤት የሚቆሙበት ጊዜም አለ፡፡ እናንተስ? በማኔጅመንቱና በሠራተኛው መካከል ያለው ግንኙነት (መግባባት) ምን ይመስላል?
እንደሚታወቀው ለአንድ ድርጅት ትልቁና ዋነኛው ሀብት ሠራተኛው ነው፡፡ ቤቱን የቱንም ያህል በውበት ብናንቆጠቁጠው፣ ሠራተኞቹ ጥሩ ካልሆኑ ያ ሁሉ ድካም ሜዳ ላይ ነው የሚቀረው። ይህን ግምት ውስጥ ስለምናስገባ፣ ሠራተኞቻችንን እናሠለጥናለን፣ እናሳድጋቸዋለን፣ ለመሪነት ደረጃም እናበቃቸዋለን፤ ይህም ሠራተኞቹን ያተጋቸዋል። በተጨማሪም ድርጅቱ በዓመት ለሠራተኛው 6 በመቶ የደሞዝ ጭማሪ ያደርጋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ የተገኘው ውጤት ይገመገምና ድርጅቱ በማንኛውም ጊዜ የደሞዝ ጭማሪ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በዓመቱ መጨረሻም ገቢና ወጪው ተሰልቶ የተገኘው ውጤት ይመዘንና ለሠራተኞች ቦነስ እንሰጣለን፡፡ ድርጅቱ የተገኘውን ትርፍ ብቻውን አይበላም፡፡ ትርፉን ካስገኙለት ሠራተኞች ጋር ይካፈላል፡፡
ሌላው መተማመኛችን በማንኛውም ሰዓት አንድ ሠራተኛ ኃላፊዎች በድለውኛል ካለ ለበላይ አካል ቅሬታውን ለማቅረብ በሩ ክፍት ነው፡፡ ይኼ የምንኮራበት ሲስተማችን ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሠራተኛ ምክትል ሥራ አስኪያጁ አቶ ተስፋዬ በደለኝ ካለ፣ ከእኔ በላይ ላለ ኃላፊ (አለቃ) ለዋና ሥራ አስኪያጇና ባለቤቷ ድረስ ቀርቦ ቅሬታውን የማቅረብ መብት አለው፡፡ ይኼ ነገር ሠራተኞቻችንን የሚያስደስታቸው ይመስለኛል፡፡
የሆቴልና ቱሪዝም (የካፌዎች) ኢንዱስትሪ እያደገ ነው ያለው፡፡
ካልዲስ ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ወደ ሌላ ቦታ ሄደው ለመሥራት ብቁ መሆናቸውን ስለሚያውቁ፣ እኛ ጋ መሥራቱን እንደማሠልጠኛ ተቋም ነው የሚቆጥሩት፡፡ እነዚህ ነገሮች ናቸው እንግዲህ በእኛና በሠራተኞቻችን መካከል ሰላም እንዲኖር የሚያደርጉት፡፡
40 ካፌዎች በአዲስ አበባ ከከፈታችሁ በኋላ ዕቅዳችሁ ምንድነው?
በአዲስ አበባ ከተማ 40 ካፌዎች ከከፈትን በኋላ ወደ አጐራባች ከተሞች እንወጣለን፡፡ ወደ ክልሎች የምንወጣው እዚህ 40 ካፌዎች ስለሞላን ብቻ ሳይሆን ለሥራችን ግብአት የሚሆኑ ነገሮችን 50 በመቶ ራሳችን ማምረት ስንችል ነው፡፡ ከወተት የሚገኝ ብዙ ተዋጽኦ አለ፡፡ ቺዝ፣ ቅቤ፣ ክሬም፣… እነዚህ ለኬክ አስፈላጊ ግብአት ናቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ ወደ እንቁላል ምርት (ፖልተሪ) እንገባለን፡፡
በመቀጠል ደግሞ አትክልቶችን ማቅረብ እንፈልጋለን፡፡ እነዚህ ሁሉ ከተሟሉና በአዲስ አበባ 40 ካፌ ከሞላን በኋላ ወደ ክልል ለመውጣት ነው ዕቅዳችን፡፡ ፍራንቻይዝ የሚለውንም 40 ከሞላን በኋላ ቆሞ ብለን የምናየው ይሆናል፡፡ በመጨረሻም፤ አንባቢዎች ሥራ አስኪያጁን እንዲተዋወቁ አቶ ተስፋዬ ማናቸው? ትምህርትና የሥራ ልምዳቸውስ በማለት ጠየቅሁ፡፡
አቶ ተስፋዬ ከንግድ ሥራ ኮሌጅ በአካውንቲንግ ዲፕሎማ፣ ከአልፋ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በአካውንቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፡፡ ለ10 ዓመታት በተለያዩ የመንግሥት ድርጅቶች በኦዲተርነትና በሂሳብ ኃላፊነት ሠርተዋል፡፡
በበደሌ ቢራ ፋብሪካ ለ8 ዓመታት ከአካውንታንት እስከ ፋይናንስ ሥራ አስኪያጅነት፣ በካልዲስ ለሁለት ዓመት በፋይናንስ ኃላፊነትና ለአራት ዓመት ድርጅቱን በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅነት እየመሩ ነው፡፡
አቶ ተስፋዬ በካልዲስ ካፌ ኃ.የተ.የግል ማህበር ውስጥ ለ6 ዓመት ስለሰሩ በደንብ ያውቁታል፤ በአድናቆት የሚናገሩለትም ነገር አለ፡፡ “አንዱ፣ በትንሽ ካፒታል ጀምሮ ለ1,200 ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ባለቤቶቹ በቅንነት የሚፈጽሟቸው ተግባራት ናቸው፡፡ አካለ ስንኩላንን፣ በሽተኞችን፤ ካንሰር ሶሳይቲን በገንዘብ ይረዳሉ፡፡
ጐበዝ ተማሪ ሆነው ችሎታው እያላቸው የሚረዳቸው በማጣት መማር የማይችሉትንም ይረዳሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ልጅ ከአምቦ አምጥተው እያስተማሩ ነው፡፡ ልጁ ከ1ኛ ክፍል እስከ 11ኛ ክፍል 1ኛ ነው የሚወጣው፡፡ እነዚህን ነገሮች አደንቅላቸዋለሁ፡፡” ብለዋል፡፡

Saturday, 07 September 2013 10:41

የግል ሐኪምዎ የሆነው ሙዝ!

በስትሮክ የመሞት አደጋን ከ50-60 በመቶ ለመቀነስ ያስችላል
ለስኳር ህመምና ለደም ማነስ ሙዝን መመገብ ይመከራል

በኢትዮጵያ እንደተገኘ የሚነገርለትና በዓለማችን በስፋት እየተመረተ ለምግብነት የሚውለው ሙዝ እጅግ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ሙዝ ከምግብ ይዘቱ በተጨማሪ ለተለያዩ በሽታዎች ፈውስ ሊያስገኙ የሚችሉ ንጥረ ነገሮችንም አካቶ ይዟል። እነዚህ ንጥረነገሮች ለበርካታ በሽታዎች ፈውስ ከመሆናቸውም በላይ፣ በሽታው ከመከሰቱም በፊት ለመከላከል የሚያስችለንን አቅም ያጐናጽፉናል፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በጠቅላላ ህክምና ክፍል ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ታዬ አለማየሁ እንደሚናገሩት፤ ሙዝ በስትሮክ ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን ሞት በግማሽ መቀነስ ይችላል፡፡
ሙዝ በውስጡ የካርቦሃይድሬት ንጥረነገሮችን የያዘ በመሆኑ ከፍተኛ ሃይል እንድናገኝ ይረዳናል። ሁለት ሙዝ በልተን በምናገኘው ሃይል ለዘጠና ደቂቃ አድካሚ የጉልበት ሥራዎችን መሥራት እንደምንችል ዶ/ር ታዬ ይናገራሉ፡፡
ብዙዎቻችን ሙዝን ለምግብነት በማዋል ለሰውነታችን ሃይልና ሙቀት ለማግኘት እንደምንችል ከማወቅ የዘለለ ነገር አስበን አናውቅም፡፡ ነገር ግን ሙዝ በውስጡ የያዛቸው ተፈጥሮአዊ የስኳር ወይም የጣፋጭ ምንጭ የሆኑት ግሉኮስ፣ ስክሮስ፣ እና ፍሩክቶስ የተባሉት ንጥረነገራት ከሙዝ የፋይበር (የቃጫነት) ተፈጥሮ ጋር ተዳምረው መጠነሰፊ ጠቀሜታዎችን ይሰጣሉ። ከበርካታ የሙዝ ጠቀሜታዎች መካከል ጥቂቶቹን ከዚህ እንደሚከተለው ለማየት እንሞክራለን፡፡
1. ለአእምሮ እድገት
ሙዝ በውስጡ ከፍተኛ የፖታሺየም ንጥረነገርን ይዟል፡፡ ይህም ንጥረ ነገር የአንጐልን የሥራ ብቃት ለማሻሻል እና ለማሳደግ እንዲሁም ንቁና ጤናማ አዕምሮ እንዲኖረን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
2. ለስትሮክ
በሙዝ ውስጥ ያለው ፖታሺየም፣ የደም ሥርዓትን በማስተካከል ባልታሰበ ሁኔታና በድንገት የሚከሰተውን የስትሮክ ችግር ለመከላከል ያግዛል። ሙዝ በሰው ልጆች የአመጋገብ ሥርዓት ውስጥ ተካቶ ዘወትር ለምግብነት የሚውል ከሆነ፣ በስትሮክ ምክንያት የሚመጣውን ድንገተኛ ሞትና የአካል ጉዳት ከ50-60 በመቶ ለመቀነስ ያስችላል፡፡
3. ለደም ግፊት
ሙዝ በተፈጥሮው በውስጡ የሚይዘው ዝቅተኛ የጨው መጠን በመሆኑ የደም ግፊትን ለማረጋጋት ይረዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በውስጡ ያለው ፖታሺየም የደም ግፊትን ለማስተካከልና በግፊት ሳቢያ የሚከሰቱ ከባድ የጤና ችግሮችን ለመከላከል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
4. ለጨጓራ ህመም
አብዛኛዎቻችን ሙዝ ከበድ ያለ ምግብ እንደሆነ በማሰብ፣ ሙዝ የጨጓራ ህመማችንን እንደሚያባብስብን ስንናገር እንደመጣለን፡፡ ይሁን እንጂ ሙዝ ለጨጓራ ችግሮች ሁነኛ መፍትሔ ነው። ሙዝ በባህርይው በጣም ለስላሳ በመሆኑ በጨጓራ ላይ መጨናነቅን የማይፈጥር ሲሆን የጨጓራ አካባቢን በመሸፈን፣ የጨጓራ ውስጥ አሲድን በማስተካከልና በማመጣጠን የጨጓራ ቁስለት እንዳይፈጠር ለማድረግ ያስችላል፡፡
5. ለድብርት
ሙዝ በውስጡ የሚይዘውና ትራይፕቶፋን የተባለው ንጥረ ነገር በሰውነታችን ውስጥ ሴሮቶኒን የባለ ሆርሞን እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
ይህ ሆርሞን አይነተኛ ተግባሩ ሰውነታችንን ከድካምና ከድብርት በማላቀቅ ወደተሻለ ስሜት ውስጥ እንድንገባ ማድረግ ነው፡፡
6. ለሆድ ድርቀት
በሙዝ ውስጥ የሚገኘው ፋይበር ለምግብ መፍጨት ሥርዓታችን ከፍተኛ ጠቀሜታን ይሰጣል፡፡ የምግብ መፍጨት ሥርዓትን የሚያከናውኑት የሰውነታችን ክፍሎች በቂ የውሃ መጠን እንዲኖራቸው በማድረግ ሆድ ድርቀትን ይከላከላል፡፡ አንጀት የተለሳለሰ እንዲሆን በማድረግ ከሰውነታችን መውጣት የሚገባቸው አላስፈላጊ ነገሮች (ቆሻሻዎች) እንዲወገዱ ለማድረግ ይረዳል፡፡
7. ለስኳር ህመም
ሙዝ በውስጡ ከፍተኛ ቫይታሚን B6 የያዘ ነው። ይህም በደም ውስጥ የሚኖረውን ከፍተኛ የስኳር መጠን እንዲቀንስ በማድረግ፣ በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘውን የስኳር መጠን ለመቆጣጠር ያስችለናል፡፡ ከስኳር መብዛት ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የጠዋት ህመምንም ያስቀራል፡፡
8. ሙዝና ደም ማነስ
በሙዝ ውስጥ የሚገኘው የብረት ማዕድን ጠቀሜታው በደማችን ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የሔሞግሎቢን ምርት እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ ይህም በሔሞግሎቢን እጥረት ሳቢያ የሚከሰተውን የደም ማነስ እንዳይከሰት ያደርጋል፡፡
9. ሙዝ ለስካር
ሙዝ ከወተትና ከማር ጋር ተደባልቆ ለምግብነት ሲውል በከፍተኛ መጠጥ ወይም በስካር ሳቢያ የሚከሰትን ሃንግኦቨር (ያደረ ድምር) በቀላሉ ያስወግዳል፡፡ በመጠጥ ሳቢያ የተጐዳን ሰውነት እንዲነቃቃና ብርታት እንዲያገኝ በማድረግ ረገድም ሙዝ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል፡፡ የሲጋራ እና መሰል ሱሶች ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ሱሱን ለማቆም እንዲችሉ ሙዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡
10. ለሞቃታማ አየር
በሞቃታማ የአየር ንብረት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሙዝን ቢመገቡ ሰውነታቸው ሙቀቱን እንዲቋቋም በማድረግ፣ የተረጋጋና የተስተካከለ የሰውነት ሙቀት እንዲኖረን ያደርገናል፡፡
11. የሙዝ ተጨማሪ ጠቀሜታዎች
በወባ ትንኝ የተነደፈ ሰው ወይንም በማንኛውም ተናካሽ ወይም ተናዳፊ ነፍሳት የተነደፈ (የተነከሰ) ሰው በሙዝ ልጣጭ የውስጠኛው ክፍል የተነደፈበትን (የተነከሰበትን) ቦታ በደንብ በማሸት እብጠቱን መቀነስ ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ንድፍያው (ንክሻው) የፈጠረበትን የማቃጠልና የመለብለብ ስሜት ለማስወገድ ይችላል፡፡ ጫማዎን ከጠረጉና ቆሻሻውን ካስወገዱ በኋላ በሙዝ ልጣጭ ቢወለውሉት ጫማዎ እንደመስታወት ያበራልዎታል።
ፍሪጅዎ መጥፎ ጠረን (ሽታ) ካመጣብዎ አንድ ሁለት ሙዞችን ያስቀምጡበት፡፡ የፍሪጅዎ ጠረን በቅጽበት ይቀየራል፡፡
ሰውነትዎ በድካም ወይም በህመም ከተጐዳና የምግብ ፍላጐት ከሌለዎ አንድ ሙዝ እንደምንም ይመገቡ፡፡ ሰውነትዎ ሲበረታና የምግብ ፍላጐትዎ ሲጨምር ይታወቅዎታል፡፡
በአጠቃላይ ሁላችንም እንደቀላል የምናየውና ብዙም ትኩረት የማንሰጠው ሙዝ ለከፍተኛ የጤና ችግር የሚዳርጉንን በሽታዎች ለመከላከልና ለማስወገድ ይረዳናል፡፡
ታዲያ ይህን የግል ሐኪምዎ የሆነ ፈዋሽ ፍሬ በፍሪጅ ውስጥ ከተው አያበላሹት፡፡ ንፋስ ያለበት ያልታመቀ አየር ለሙዝ የሚስማማ ነውና - በዚያ ያኑሩት፡፡

Published in ዋናው ጤና

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከመቋቋሙ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የሎተሪ ጨዋታ በተለያየ መልኩ ይካሄድ ነበር፡፡ ህግ ከመውጣቱ በፊት የሚካሄዱት ቁማር መሰል ጨዋታዎች በህብረተሠቡ ዘንድ “ኪሳራ” በመባል ነበር የሚታወቁት፡፡ በ1938 ዓ.ም ህገወጥ ሎተሪዎችን የሚያግድ አዋጅ ከወጣ በኋላ፣ “ኪሳራ” የሚባሉት የቁማር ጨዋታዎች ቀሩ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ አንዳንድ ግለሠቦች ፈቃድ እያወጡ ሎተሪ ማጫወት ጀመሩ፡፡ አንዳንዴ ገንዘቡን እየሰበሰቡ የሚጠፉ ሁሉ ነበሩ፡፡ በ1945 ዓ.ም ነው መንግስት ሎተሪ እንዲያካሂድ የሚፈቅድ አዋጅ የወጣው፡፡ በመጨረሻ በ1954 ዓ.ም የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ማቋቋሚያ አዋጅ ታወጀ፡፡ ብሔራዊ ሎተሪ ሲመሰረት የሠራተኞቹ ቁጥር አምስት ብቻ ነበር አሁንስ? የአዲስ ዓመት ዋዜማ እንግዳችን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ ነዋይ፤ መ/ቤታቸው ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ያለውን ሂደት እንዲሁም ከሎተሪ ዕድለኞች ጋር በተያያዘ አስገራሚ ታሪኮችንና ገጠመኞችን ለአዲስ አድማስ አዘጋጅ ኤልሳቤት ዕቁባይ በስፋት አውግተዋታል፡፡ እነሆ፡-

የመጀመርያዎቹ እድለኞች አምስት ኤርትራውያን ነበሩ…
የጐንደሩ ነዋሪ “መሐመድ ሎተሪ” 15 ጊዜ ሎተሪ ደርሷቸዋል…
አፄ ኃይለስላሴ የደረሳቸውን መኪና መልሰው ሸልመዋል…
የመጀመርያው እጣ 50ሺ ብር ነበር… አሁን 4ሚ. ብር ደርሷል…

ቢሮው የት ነበር? ዕጣው የሚወጣበትስ?
የመጀመሪያ ቢሮው በአሁኑ የመብራት ሀይል አዳራሽ ህንፃ ሲሆን በናዝሬት፣ በድሬዳዋና በአስመራ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ነበሩት፡፡ በአዲስ አበባ ሶስት ማከፋፈያዎች ነበሩት፡፡ በመስከረም 1954 ዓ.ም ነው የመጀመሪያው ሎተሪ ገበያ ላይ የዋለው፡፡ ዕጣው ሀምሳ ሺህ የሚያሸልም መደበኛ ሎተሪ ነበር፡፡ አምስት ክፍልፋዮች አሉት፤ እያንዳንዳቸው አስር ሺህ ብር የሚያሸልሙ፡፡ የመጀመርያው ሎተሪ የወጣው ታህሳስ 29 ቀን 1954 ዓ.ም የገና ዕለት በአሁኑ ጃንሜዳ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተሠበሰቡበት ነው፡፡ ከዚያም ትንሿ ስታዲየም በምትባለው ቦታ በታጠረ ቆርቆሮ የሎተሪ እጣ ሲወጣ ቆየ፡፡ በመጨረሻም አሁን ባለው የመስሪያ ቤቱ አዳራሽ ውስጥ የሎተሪ ዕጣ መውጣት ቀጠለ፡፡ ቢሮው ከመብራት ሀይል ህንፃ በመቀጠል የድሮው ፖስታ ቤት ሙኒ የሚባል አካባቢ ነበር፡፡ ከዛም ወደ አሁኑ ቢሮ የተዛወረ ሲሆን፡፡ የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ኤቦን ሚሞሪ የሚባሉ ግሪካዊ ነበሩ፡፡
የመጀመሪያዎቹ ዕድለኞች እነማን ነበሩ?
የመጀመሪያዎቹ ዕድለኞች አምስት የቀድሞው የኤርትራ ክፍለ ሀገር ነዋሪዎች ናቸው፡፡ አምስቱም የሚኖሩት በሀማሴን አውራጃ ነበር፡፡ እያንዳንዳቸው አስር አስር ሺህ ብር አግኝተዋል፡፡ አንድ ትኬት ገዝተው ነው የተከፋፈሉት፡፡ የመጀመሪያው አሸናፊ ቁጥር 07260 ነበር፡፡
ሎተሪ ሲደርስ በግለሰቦች መካከል የሚፈጠሩ ውዝግቦች እንዳሉ ይሰማል …
ትክክል ነው፡፡ ጊዜው ቆየት ብሏል፡፡ ሽሮሜዳ አካባቢ ነው፡፡ አንድ ሠው ሎተሪ ይቆርጥና ለሁለት የቅርብ ጓደኞቹ ይሠጣል፡፡ ሎተሪው ሎንቺና የሚያሸልም ነበርና አንዷ ይደርሳታል፡፡ በጣም ተደስታ ግብዣ ያደረገች እለት ሎተሪውን ለጓደኛዋ ያዥልኝ ብላ ትሠጣታለች፡፡ ጓደኛዋ ሎተሪውን ከራሷ ሎተሪ ጋር ቀያይራ አስተዳደሩ ጋ በመምጣት መኪናውን ለመውሰድ በሂደት ላይ ሳለች፣ “እውነተኛዋ” ባለዕድል ተጠራጥራ ትመጣና ሂደቱን በፍርድ ቤት ታስቆማለች፡፡ አራት አመት በክርክር ከቆየ በኋላ ፍርድ ቤቱ ለሁለት አካፍሏቸዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ሰኔ ሀያ ስምንት በወጣው የቶምቦላ ሎተሪ አምስተኛው ባለዕጣ የመቀሌ ነዋሪ ነው፡፡ አቶ ሰለሞን ይባላል፡፡ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር ሁልጊዜ ሎተሪ በጋራ ይቆርጣሉ። ስማቸውንም ሎተሪው ላይ ይፅፋሉ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ የቶምቦላው ሎተሪ ላይ አንደኛው እኔ ገንዘብ የለኝም ይልና አንደኛው አንዷን ሎተሪ ለጋራ ይቆርጣትና ስማቸውን ይፅፋል፡፡ ሎተሪው በሚወጣበት ጊዜ አቶ ሰለሞን እንደደረሠው ሲያውቅ፣ ሌላ ሎተሪ ያወጣና “እስቲ ይሄን ቁጥር እይ” ይለዋል፡፡ ጓደኝየው እንዳልወጣ ያይና ይጥለዋል፡፡ በኋላ አቶ ሠለሞን በሚዲያ መሸለሙን ጓደኛው ሲያይ፣ የሽልማት መኪናውን በፍርድ ቤት ያሳግደዋል፡፡ ብሩን ግን ሰለሞን ቀድሞ ወስዷል፡፡ አሁን ጉዳያቸውን በቤተሠብ ዳኝነት ይዘው ለመካፈል ተስማምተዋል፡፡
ከግለሰቦች መተማመን ጋር በተያያዘስ የሚያወጉን ገጠመኞች ይኖራሉ?
በጣም የሚገርም ዕምነትም ይታያል፡፡ በ2003 ወንዶ ገነት አቅራቢያ ቡሳ የምትባል ቦታ ላይ አቶ መዝገበ ገ/ህይወት የተባለ ጠጅ ነጋዴ፣ ሎተሪ እንደደረሠኝ እይልኝ ብሎ ጠጅ ቀጂውን ይልካል። ጠጅ ቀጂው የእድለኞችን ዝርዝር አይቶ አንድ ሚሊዮን ብር ደርሶሃል ብሎ አምጥቶ ሰጥቶታል። ከሁለት ዓመት በፊት እሸቱ ሀሠን የተባለ የደሴ ነዋሪ የሚስቱ ወንድም ታመው መቀሌ ሊጠይቃቸው ይሄዳል፡፡ ሰውየውም ለራሳቸውና ሊጠይቃቸው ለመጣው የእህታቸው ባል ቶምቦላ ሎተሪ ገዝተው፣ ስም ይፅፉና ”ከደረሰህ አሳውቅሃለሁ” ይሉታል። እንዳጋጣሚ ቶምቦላው የተገዛለት ግለሰብ መኪና ይደርሰዋል፡፡ ሰውየው ደውለው “መኪናው በአንተ ስም ደርሷል፤ ና ውሰድ” ብለው ሰጥተውታል። በቅርቡ ፈጠነ ዋቅጅራ እና ግርማቸው ሳህሉ የሚባሉ ጓደኛሞች ድራፍት እየጠጡ የቢንጎ ሎተሪ ይገዛሉ፡፡ አንደኛው ቢፍቀውም ሌላኛው ግን ወሬ ይዞ ሳይፍቀው ይቀራል፡፡ በኋላም አንተ ጋ ይሁን ብሎ ለጓደኛው ይሰጠዋል፡፡ እየተጫወቱ ከቆዩ በኋላ ይለያያሉ፡፡ ጓደኛው፤ ቤት ሄዶ ቢንጐውን ሲፍቀው 150ሺ ብር ደርሶታል፡፡ ደውሎ 150ሺ ብር እንደደረሰው ነገረው፡፡
መቼም አስገራሚ ታሪክ ያላቸው ባለዕድለኞችም አይጠፉም …
በ2003 ተስፋዬ ዋዴዬ የተባለ ግለሰብ ሚስቱ ወተት እንዲገዛላት 10 ብር ትሰጠዋለች፡፡ ወተቱን ሊገዛ ሲወጣ ግን ሎተሪ ሻጭ ያገኝና ከብዙ ማቅማማት በኋላ በገንዘቡ ቶምቦላ ይገዛበታል፡፡ ቤት ሲመለስ ከሚስቱ ጋር ቀውጢ ሆነ፡፡ ተጣሉ፡፡ ሎተሪው ግን የጭነት መኪናና የመቶ ሰማኒያ ሺህ ብር እድለኛ አደረጋቸው፡፡ አንዲት ሴት ደግሞ በቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በኩል ወደ ገበያ ሲሄዱ፣ አንዲት ሎተሪ ሻጭ “መደበኛ ሎተሪ፤ መደበኛ ሎተሪ” እያለች ትወተውታቸዋለች። እሳቸው ግን ብር የለኝም ብለው ሳይገዟት ያልፋሉ። ከገበያ ሲመለሱ አንድ ብር ተርፋቸው ነበር፡፡ አዟሪዋ አሁንም “መደበኛ ሎተሪ” ትላለች። በብሯ ሎተሪውን ገዟትና የመቶ ሀምሳ ሺህ ብር ባለ ዕድል ሊሆኑ ቻሉ፡፡
አንድ የመቀሌ ከተማ ነዋሪና ነጋዴ ደግሞ በ1986 ለጦር ጉዳተኞች ተብሎ የተዘጋጀ ሎተሪ ይቆርጣሉ፡፡ ነገር ግን ዕጣው መድረስ አለመድረሱን ሳያዩ ይዘነጉታል፡፡ ትዝ ያላቸው አንድ ቀን ለግል ጉዳያቸው አዲስ አበባ በመጡ ጊዜ ነበር፡፡ አንድ ምግብ ቤት ምሳ በልተው ሂሳብ ሲከፍሉ፣ ሎተሪ ሻጭ ያዩና ማውጫ ይጠይቃሉ፡፡ የሁለት መቶ ሺህ ብር እና የአምስት መቶ ካሬ ሜትር ቦታ ዕድለኛ ነበሩ፡፡ የሚገርመው ደግሞ ዕጣው የስድስት ወር ጊዜው ሊጠናቀቅ የቀረው ግማሽ ቀን ብቻ ነበር። መስሪያ ቤታችን የዛኑ ቀን ሚዲያውን ጠርቶ ተራሩጦ ነው ሽልማታቸውን የሰጣቸው፡፡
በቅርቡም ስምኦን ስዩም የሚባል ባሌ ጊኒር ውስጥ የሚሰራ ግለሰብ ከስራው ጋር በተያያዘ በሰራው ወንጀል ይታሰራል፡፡ ሁለት አመት ይታሰርና በተፈታ በሁለተኛው ቀን የዕንቁጣጣሽ ሎተሪ ይገዛል፡፡ እሱም ይረሳዋል፡፡ የስድስት ወሩ ገደብ ሊጠናቀቅ አስራ አምስት ቀን ሲቀረው ትዝ ብሎት ማውጫ በማየቱ፣ የዘጠኝ መቶ ሺ ብር ዕድለኛ ሆኖ ገንዘቡን ወስዷል፡፡ ወጣት አየነው አሰፋ ደግሞ የአስራ ዘጠኝ አመት ወጣት ሲሆን ሰሜን ሆቴል አካባቢ ብርጭቆ አጣቢ ነው፡፡ ሰባት መቶ ሀምሳ ሺህ ብር ደርሶት ሊወስድ እኛ ጋ ይመጣል፡፡ እጣውን ማሸነፉን በተመለከተ ቃለ መጠይቅ ሲደረግለት ግን 750ሺ ብር ማለት አልቻለም፡፡ በተደጋጋሚ ሰባት ሺህ ብር ነበር የሚለው፡፡ ወንድሙ ወዳጄ የሰበታ ነዋሪ ሲሆን ገቢው አርባ ብር ነበር፡፡ በገዛው የገና ስጦታ ሎተሪ 1ሚ. ብር ይደርሰዋል፡፡ ገንዘቡን ሊቀበል የመጣው ከአሰሪው ጋር ነበር፡፡ ባለ ዕድሉ መናገር ሁሉ አቅቶት ነበር፡፡ ሊሸለም ሲሄድ የተነፈሰውን አተነፋፈስ ዕድሜ ልኬን አልረሳውም፡፡ ሁለት የባንክ ሠራተኞች በጋራ አንድ ትኬት ይገዙና አንዱ ቁጥሩን ፅፎ ይይዛል፡፡ ሌላው ትኬቱን ያስቀራል። ቁጥሩን ይዞ የሄደው የገልባጭ መኪና አሸናፊ መሆናቸውን አረጋገጠ፡፡ ሰኞ ስራ ሲገናኙ ሎተሪ እንደደረሳቸው ሲነግረው፣ ትኬቱን ቅዳሜ ዕለት የጠጣበት ቤት ቀዳዶ እንደጣለው ይነግረዋል፡፡ ተያይዘው ወደ ቡና ቤቱ ሲሄዱ ቤቱን ጠርገው ቆሻሻውን ወንዝ ዳር እንደጣሉት ይነግሯቸዋል። ቆሻሻው የተጣለበት ወንዝ ሲሄዱ የሎተሪ ቁርጥራጮች ተንሳፈዋል፡፡ እንደምንም አውጥተው ሲያዩት አንዷ ቅዳጅ ሙሉውን ቁጥር በፊደል ይዛለች፤ በአሀዝ ግን አንድ ቁጥር ይጎድላል፡፡ ነገር ግን ተሸልመዋል፡፡
አሸናፊ ዕጣ ደርሷቸው ያልወሰዱ ግለሰቦችስ? ቁጥራቸው ይታወቃል?
ለሀምሳኛ አመት በዓል ባዘጋጀነው የአምስት ሚሊዮን ብር ሽልማት ሁለቱ ዕድለኞች አልመጡም። ከአራቱ ትኬቶች አንዱ ባለ ዕድል ጎዳና ላይና ሰው በር ላይ እያደረ በሊስትሮነትና በታክሲ ረዳትነት የሚሰራ ልጅ ነበር፡፡ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ነው የደረሠው፡፡ እሱ በአስራ አምስት ቀኑ መጥቶ ሲወስድ፣ በአራተኛው ወር ደግሞ አቶ አማኑኤል ስብሀቱ የተባሉ ዕድለኛ መጡ፡፡ እሳቸው አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር ባለ ዕድል ነበሩ። እኚህን ባለ ዕድል “ፎቶ እናንሳዎት” ስንላቸው “አይሆንም ሀኪም ከልክሎኛል” አሉ፡፡ ልብሳቸውን ገለጥ አድርገው ሲያሳዩን የልብ ትርታ መቆጣጠሪያ መሳሪያ ተደግኗል። ያልመጡት ባለ ዕድሎች ግን ቀልጦ ቀረ ማለት ነው። በ1999 ቶምቦላ ሎተሪ ገዝታ የሶስት መቶ ካሬ ሜትር ቦታና የሁለት መቶ ሺህ ብር እድለኛ የነበረችው የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚ/ር ሰራተኛ፣ ዕጣው ሰባት ወር ካለፈው በኋላ በመምጣቷ እጣው ከስሮ ቀርቷል። እንደዚህ አይነት አጋጣሚ አልፎ አልፎ አለ፡፡ አንዳንዶች መቁረጥ ይወዳሉ፤ ዕጣውን ግን አያዩትም፡፡
ከባለ ዕድለኞቹ በሀብት የሚታወቁ ወይም ዝነኛ ሠዎች አሉ?
አፄ ሀይለስላሴ የመኪና ባለዕድል ነበሩ፡፡ እሉን መልሰው ሸልመዋል፡፡ በ2003 ዓ.ም የአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ዕድለኛ የነበሩት የፋብሪካ ባለቤት ናቸው፡፡ አርቲስት ሀረገወይን አሠፋም የአምስት መቶ ሺህ ብር ባለዕድል ናት፡፡
በተደጋጋሚ ሎተሪ የሚደርሳቸውስ…
ትልቁ ተደጋጋሚ እድለኛ የጎንደር ነዋሪ ናቸው፡፡ መሀመድ አብደላ ይባላሉ፡፡ አስራ አምስት ጊዜ ዕድለኛ ሆነዋል፡፡ ጉራጌ አካባቢ የሚኖሩት አቶ በላይነህ ሸዋንግዛው ደግሞ ስድስት ጊዜ ባለዕድል ሆነዋል። ሁለት ጊዜ ሀምሳ ሺህ ብር፣ ሶስት መቶ ሺህ ብርና ሁለት መቶ ካሬ ሜትር ቦታ፣ መቶ ሺህ ብር፣ አምስት መቶ ብርና፣ ሬዲዮ ደርሷቸዋል፡፡ ወጣት ዳንኤል መሀሪ ወልዲያ ፒያሳ አካባቢ ነዋሪ ሲሆን መስከረም 5 ቀን 2001 በቢንጎ ሎተሪ 20ሺህ ብር ደረሠው፡፡ ጥቅምት ላይ በመደበኛ ሎተሪ ሰባ አምስት ሺህ ብር ወሰደ፡፡ በደርግ ዘመን አቶ ዘውዱ አስፋው የጎንደር ከተማ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ነበሩ፡፡ በዝሆን ሎተሪ መቶ ሺህ ብር ደርሷቸው በአስራ አምስተኛው ቀን በመደበኛ ሎተሪ የሀምሳ ሺህ ብር ዕድለኛ ሆነዋል፡፡
የአዲስ አበባ ነዋሪው አቶ ንጋቱ ተክለ ዮሀንስ፤ በ902 መደበኛ ሎተሪ ሀያ አምስት ሺህ ብር ከደረሳቸው በኋላ፣ በሚቀጥለው ሎተሪ በድጋሚ የሀያ አምስት ሺህ ብር ዕድለኛ ሆነዋል፡፡ አቶ ወርቅነህ ጥላሁን የቀጨኔ አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ በ1971 በመደበኛ ዕጣ አስራ ሁለት ሺህ ብር፣ በድጋሚ በዚሁ መደበኛ ዕጣ ሰባ ሰባት ሺህ ብር አግኝተዋል፡፡ አቶ አሠፋ ቁጥሶ፤ አመዴ ገበያ ጫማ ቤት አላቸው፡፡ ከሎተሪ ተነስተው ነው እዛ የደረሱት። በ279 መደበኛ ሎተሪ ሀያ አምስት ሺህ ብር፣ በ1974 በሶስት ትኬት ስድስት ሺህ ብር አሸናፊ ሆነዋል፡፡ አቶ ካሳ ያደቴ የተባሉ ዕድለኛ ደግሞ በሚሊኒየም ሎተሪ ከአራት ትኬት አርባ ሺህ ብር ዕድለኛ ሲሆኑ ከሀያ አመት በፊት የሀምሳ ሺህ ብር ባለ ዕድል ነበሩ፡፡ አቶ ዘውዱ ተሰማ የፒያሳ አካባቢ ነዋሪና ጠበቃ ናቸው። በመደበኛ ሎተሪ የሀያ ሺ፣ ስምንት ሺ፣ አንድ ሺ፣ ስምንት ሺ እና ከዝሆን ሎተሪ የሶስት ሺ ብር ዕድለኛ ናቸው፡፡ የጎንደር ቆላድባ ወረዳ ነዋሪ በቅርቡ ደግሞ አቶ እርዚቅ ፍሬው የካቲት ውስጥ በዝሆን ሎተሪ የሁለት ሚሊዮን ብር አሸናፊ ሆነው፣ በሚያዝያ ወር ላይ የስምንት መቶ ሺህ ብር ባለእድል ሆነዋል፡፡
አሁን የድርጅቱ የሠራተኛ ብዛት ስንት ነው? ቅርንጫፎቹስ?
አሁን ስምንት መቶ ሠራተኞች እና ሀምሳ ቅርንጫፎች አሉ፡፡ የወኪሎች ብዛት ከሰማኒያ በላይ ደርሷል፡፡
ዕጣውስ?
ሲጀመር ሀምሳ ሺህ የነበረው የመደበኛ ዕጣ ሽልማት አራት ሚሊዮን ደርሷል፡፡ በፊት መደበኛ ሎተሪ ብቻ ነበር የሚዘጋጀው፡፡ አሁን አስራ ስድስት የሎተሪ አይነቶች አሉ፡፡
የአስተዳደሩ ሰራተኞች ሎተሪ አሸንፈው ያውቃሉ?
አሁን ጡረታ የወጣ ሠራተኛ አስራ ሁለት ሺህ ብር ደርሶት ነበር፡፡ ደብረብርሀን ቅርንጫፍ ደግሞ የድርጅቱ ዘብ ስልሳ ሺህ ብር ደርሶታል፡፡ በጣም ትንንሽ ብር የሚያስገኙ ዕጣዎችም የደረሳቸው አሉ። በመቁረጥ ካየሽው ግን ሠራተኛው የሎተሪ ቆራጭ ነው፡፡ ምክንያቱም ማስታወቂያ በየጊዜው ስለሚሰማና ዕድለኞችን ስለሚያይ ነው፡፡
የትኛው የህብረተሰብ ክፍል ሎተሪ የመቁረጥ ልምድ እንዳለው ጥናት አድርጋችኋል?
ሁሉም የህብረተሠብ ክፍሎች የሎተሪ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ምክንያቱም የዕድለኞቹ ስብጥር ያንን ያሳያል። በአኗኗር ካየነው አርብቶ አደር አካባቢዎች የሎተሪ መጫወት ባህል ዝቅተኛ ነው፡፡
እስቲ ስለ አስተዳደሩ ማህበራዊ ተሳትፎ ይንገሩኝ … ምን ምን ጉዳዮች ላይ ተሳትፏል?
ብሄራዊ ሎተሪ ላለፉት ሀምሳ ሁለት አመታት በአገሪቱ በተከናወኑ አበይት ጉዳዮች ላይ ተሳትፏል። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የፊደል ሠራዊት በሚል መሀይምነትን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት በተካሄደው ዘመቻ አስተማሪዎችን በማስተማር አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ወወክማና ቼሻየር ሲቋቋሙ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ከህንፃው ማሰሪያ ሩቡ የተሸፈነው በብሄራዊ ሎተሪ ድርጅት ነው። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲቋቋምም ብሄራዊ ሎተሪ ዋና የገንዘብ አስተዋፅኦ ካደረጉት አንዱ ነበር፡፡ በአገሪቷ የመኪና መሪ ከቀኝ ወደ ግራ ሲለወጥ የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ለድርቅና ለጎርፍ ተጐጂዎች ድጋፍ አድርጓል፡፡ በ1968 ዓ.ም ለአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ድጋፍ ሰጥቷል፡፡ ከሜክሲኮ ኦሎምፒክ ጀምሮ እስከ ባርሴሎና ድረስ ከአትሌቲክስ ጐን አልተለየም፡፡ ሯጮች ወደ ኦሎምፒክ ሲሄዱ ሙሉ ሱፍ ልብስ በማልበስና ወጪያቸውን በመቻል ድጋፍ ያደርግ ነበር፡፡ የአክሱም ሀውልት በልዩ ሎተሪ ገንዘብ አሰባስቧል፡፡ የልብ የህክምና ማዕከል ሲሰራ ሎተሪ አዘጋጅቶ ግንባታውን አግዟል፡፡ በባርሴሎና እነ ደራርቱ አሸንፈው ሲመጡ ያጌጡ መኪኖችን በማዘጋጀት ተቀብሏል፡፡ ከአገሪቱ ታሪክ ጋር ተያይዞ ብዙ ሠርቷል፡፡ የአዲስ አበባ ሙዚየም ሲከፈትም አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
በዓለም ላይ የሎተሪ አጀማመር ታሪክ ምን ይመስላል?
አንዳንድ ሠዎች ሎተሪ የተጀመረው በቻይና ነው ሲሉ፤ ሌሎች ጣሊያን ይላሉ፡፡ ሎተሪ የሚለው ቃል ሎቶ ከሚለው የጣልያን ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም ሠውና መልካም አጋጣሚ ማለት ነው። የተለያዩ የሎተሪ ጨዋታዎች በጥንታዊት ቻይና እንደነበር ቢታወቅም የመጀመሪያው ሎተሪ በጣሊያን የሮም ግዛት በሆነችው ፍሎረንስ ከተማ መጀመሩ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
በመላው አለም ሎተሪ የህብረተሰቡን መሠረታዊ ጉዳዮች በመደገፍ የህብረተሰቡን ድንገተኛ አደጋዎች በመከላከል ላይ ሲሳተፍ ነው የኖረው፡፡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ ለመደገፍ ይሠራል፡፡ የረሀብ፣ የእሳት አደጋና ጎርፍ ችግሮችን ለማቃለል እንዲሁም የተለያዩ በሽታዎች ሲከሰቱ ለመከላከል፣ መድሀኒት በመግዛት ማህበራዊ ድጋፍ በማድረግ ይታወቃል። ክሊኒክ፣ ትምህርት ቤት፣ ዩኒቨርሲቲ፣ ፍርድ ቤት ግንባታ፣ ለህፃናት ማሳደጊያዎች አስተዋፅኦ አድርጓል። በአዲስ አበባ የንፁህ ውሀ ችግር ለማቃለል የመጀመሪያ ፕሮጀክት የተሠራው በሎተሪ በተገኘ ገንዘብ ነው፡፡
የውጭ አገር ዜጐች ሎተሪ ቆርጠው ቢደርሳቸው ይሰጣቸዋል? ህጉ ምን ይላል?
የሎተሪ እድል ከኢትዮጵያውያን ውጪ ሲሆን የተለየ ነገር አለው፡፡ የአስተዳደሩ የማቋቋሚያ አዋጅ ሎተሪ የሚሸጠው በአገሪቷ ግዛት እንደሆነ ይደነግጋል። ስለዚህ ከዛ ግዛት ውጪ የብሄራዊ ሎተሪ ስራ የለም፡፡ በዛ ግዛት ስር ተጫውተው አሸናፊ የሆኑ ግለሰቦች በሙሉ የአሸናፊነት ቁጥራቸውን ይዘው ከመጡ ሽልማታቸው ይሠጣቸዋል፡፡ ከመጀመሪያዎቹ አምስት ዕድሎች መካከል ሁለቱ በኤርትራ ነዋሪ ለነበሩ ጣሊያኖች ደርሷል፡፡ አንድ ፈረንሳዊም የሚፋቀውን ሎተሪ ተጫውቶ አምስት ሺህ ብር ደርሶት ተቀብሏል። የብሄራዊ ሎተሪ ከድንበር ከወጣ ምንዛሬ ይዞ እንደወጣ ይቆጠራል፡፡ ብሩን ቢቀበልም ይዞ መውጣቱ በሌላ ህግ ይታገዳል፡፡

 

Published in ባህል
Saturday, 07 September 2013 10:35

የተሻለ አዲስ ዓመት…

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁማ!
ምን መሰላችሁ…ደግነቱ እንደ ድሮ “በአዲሱ ዓመት ዕቅድህ ምንድነው?” ምናምን ብሎ የሚጠይቅ ሰው ቁጥሩ በጣም ቀንሷል፡፡፡ ልክ ነዋ…ለሳምንት እንኳን ማቀድ ባልተቻለበት…“ለከርሞ ገንዘብ አጠራቅሜ ሶፋ እለውጥና…” ምናምን ብሎ ነገር ያስቸግራላ!
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ዘንድሮ እኮ፣ አይደለም ‘ሶፋ ተለውጦ’ የተቀደደ ብረት ድስት ሲበየድ ከታየ አንዳንዱ አከራይ (አሁን፣ አሁን… “አብዛኛው አከራይ…” ልንል እየቀረብን ነው) “እነኚህ ደልቷቸዋል ማለት ነው…” ብሎ ኪራይ ይጨምራል፡፡
አዲሱ ዓመት… ለቤት ኪራይም ይሁን ለሌሎች አገልግሎቶች ተገቢ ክፍያ ከመጠየቅ ይልቅ …አለ አይደል… ከተገልጋዮች የወር ገቢ በ‘ፐርሰንት መካፈል’ አይነት ተመን የሚያወጡትን ልብ ይስጥልንማ!
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይቺን የመልካም ምኞት መግለጫ ስሙልኝማ…“አዲሱን ዓመት ይቺን ወሬኛ ምላስህን የምትሰበስበበት እንዲያደርግልህ እመኛለሁ፡፡” አሪፍ አይደለች! የእውነት እኮ ግን…ዘንድሮ ‘ጦር ከፈታን፣ ወሬ የፈታን’ ቁጥራችን የበዛንበት ዘመን ነበር፡፡ አንዱ ወሬ ገና እውነትነቱንና ውሸትነቱን ለማረጋገጥ እየሞከርን ሌላ አንድ መቶ ወሬ ይፈለፈላል። እናላችሁ…“ታማኝ ከሆኑ የወሬ ምንጮች እንዳገኘነው…” ለመባባል እያቃተን ነው፡፡ ‘ኦፊሻል’ በሉት ‘አንኦፊሻል’ በሉት…አለ አይደል…እያንዳንዱ ወሬ በ‘ሀምሳ ምናምን አይነት’ እየቀረበ…የግል አመለካከትና ‘ጠጣር እውነት’ የሚሉት ነገር እየተደበላለቀ...በአንድ ቋንቋ እንኳን እየተነጋገርን መግባባት አቅቶናል፡፡
አዲሱ ዓመት እረፍት ያጣ እንደሚመስለው ‘መናገሪያ አንደበታችን’ ሁሉ ‘ማዳመጫ ጆሯችንም’ የሚከፈትበት ዓመት ይሁንልንማ! ከ‘ምላሳችን ጫፍ’ ሳይሆን ከ‘ልባችን ጥልቀት’ መልካም ምኞት የምንለወዋወጥበት አዲስ ዓመት ይሁንልንማ!
ስሙኝማ…እንግዲህ እኛ ዘንድ በዓል ማለት… አለ አይደል…ምግብ፣ ምግብና ምግብ ብቻ እየሆነ በእንቁጣጣሽ ለየጎረቤቱ የአበባ ስዕል መሰጣጣት እንኳን ‘ጊዜ እያለፈበት’ ነው፡፡
የሚሰጡ ቢኖሩ እንኳን በመልካም ምኞት መግለጫነት ሳይሆን በቤት ለቤት የሽያጭ ሥራ አይነት ነው፡፡ እግረ መንገዴን… አንዳንድ አገሮች አዲስ ዓመትን እንዴት እንደሚቀበሉ የሆነ ቦታ ያነበብኩትን ስሙኝማ…ኢኳዶር በምትባል የደቡብ አሜሪካ አገር ያለ የአዲስ ዓመት አከባበር እንዴት መሰላችሁ… የፖለቲካ መሪዎችና ሌሎች በህዝብ የሚጠሉ ሰዎችን ምስሎች በአሻንጉሊት መልክ ይሠሯቸዋል፡፡ እነኚህ አሻንጉሊቶች በአሮጌ ጋዜጦች፣ በጭድና በአሮጌ ልብሶች የሚሠሩ ሲሆን ተቀጣጣይ ርችቶች ይውሸቁባቸዋል፡፡ የየአካባቢው ነዋሪዎች እነኚህኑ አሻንጉሊቶች ይዘው ሌሊት ላይ ይሰበሰባሉ፡፡ ከዛ ምን ቢያደርጉ ጥሩ ነው… አሻንጉሊቶቹን ዶጋ አመድ ያደርጓቸዋላ! ይህ ልማድ እንዲሁ የሚደረግ ሳይሆን ትርጉም አለው። ይኸውም የመጪውን ዓመት መጥፎ መናፍስት መቃጠልና የአዲሱን ዓመት መቀበል ተምሳሌት ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እኛ አገር እንዲህ አይነት ባህል ቢኖር ኖሮ ለአሻንጉሊቶች መሥሪያ የሚበቃ አሮጌ ልብስ ይኖራል! ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…እዛው ደቡብ አሜሪካ ፑዌርቶ ሪኮ በምትባለው አገር ደግሞ ምን ይደረጋል መሰላችሁ… አሮጌውን ዓመት አጥቦ ለማባረር ነዋሪዎቹ መስኮቶቻቸው ላይ በባድሊ ውሀ ይደፋሉ፡ ቤቶቻቸውንም አጽድተው በጌጣ ጌጥ ያንቆጠቁጧቸዋል፡፡
እዚህ እኛ ዘንድ፣ አይደለም መስኮቶቻችን ላይ ውሀ ልንደፋ…ብዙ ቦታ ውሀ እንደ ማግኘት…አለ አይደል… የደሞዝ እድገት ከማግኘት የበለጠ ‘አንገብጋቢ ጉዳይ’ ሆኗል፡፡ በተለይ ይሄ እየወጣ ያለው ዓመት በውሀና በመብራት ማዳረስ በኩል አሪፍ አልነበረም፡፡ ውሀ ተርፎን በመስኮት ላይ እንድንደፋ የምንበቃበት ዘመን መምጫው ይፍጠልንማ!
የአየርላንድ ተወላጆች የአገራቸውን የወደፊት ፖለቲካዊ አካሄድ ለማወቅ በአዲስ ዓመት ዋዜማ እኩለ ሌሊት የነፋሱን አቅጣጫ ያያሉ፡፡ እናም በነፈሰበት አቅጣጫ መሠረት በአዲሱ ዓመት የአገራቸው ፖለቲካ ‘እኩይ’ ይሁን ‘እርጉም’ ይተነብዩበታል፡፡ (እኔ የምለው… ባለፉት ብዙ ዓመታት የእኛው ደመራ በአንድ አቅጣጫ ብቻ ነበር እንዴ የሚወድቀው! አሀ… ዘመንም አንዱ ሄዶ ሌላው በተተካ ቁጥር…አለ አይደል… ‘ከት ኤንድ ፔስት’ ሲመስል አሪፍ አይደለማ!)
በአሜሪካ ደግሞ ምን አይነት ባህል አለ መሰላችሁ… በአዲስ ዓመት እኩለ ሌሊት ላይ ከፍቅረኛ ወይም ደግሞ ከማንኛውም ሌላ ሰው ጋር የመሳሳም ልማድ አለ፡፡ ይህ መጪውን ዓመት እጅግ ውብ ያደርገዋል ተበሎ ይታሰባል። እውነተኛ ፍቅር ያመጣል ተብሎ ይታመናል፡፡ ያለፉትን መጥፎ ትውስታዎችና ዕጣ ፈንታዎች አስወግዶ አዲሱን ዓመት በአዲስ ፍቅርና በአዲስ ህይወት ለመጀመር ያስችላል ይባላል፡፡ እናላችሁ… እንደውም ይህንን የአዲስ ዓመት ልማድ ተከትሎም ‘ኢን ሰርች ኦፍ ኤ ሚድናይትስ ኪስ’ የሚል ታዋቂ ፊልም ተሠርቷል፡፡
እዚች ላይ እንኳን እኛ ባንወዳደራቸው ነው። አዲስ ዓመት የለ…ምን የለ ይኸው ‘ወጣት የነብር ጣት’ በሉት፣ ‘ጎልማሳ’ በሉት…በጠራራ ፀሀይ በየአደባባዩ ‘ኪሶሎጂ’ እያጦፈላችሁ አይደል! ‘አማሪካኖቹ’ ይቺን እንኳን ‘ከእኛ ቢማሩ’! አሀ…365 የ‘ኪሶሎጂ’ ቀናት እያሉላቸው ምን ዓመት ያስጠብቃቸዋል! ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ…እንቁጣጣሽ አንዱ በጣም ደስ የሚለው ሰዎች ከልባቸው ለአዲሱ ዓመት መልካም ምኞታቸውን ሲገልጹላችሁ ነው፡፡ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤናና የደስታ ይሁንልህ መባል በጣም ትልቅ ነገር ነው፡፡
ብቻ መጪውን ዓመት በሁሉም በኩል ‘የወሬ’ ሳይሆን ‘የእውነት’ አዲስ ዓመት ያድርግልንማ!
“ከብረው ይቆዩ ከብረው
በዓመት ወንድ ልጅ ወልደው
ሠላሳ ጥጆች አስረው
ከብረው የቆዩ ከብረው”
እያሉ ወጣት ሴቶች ከልብ የመነጨ ምኞት የሚያሰሙበትን ዘመን ያምጣልንማ!
“የእማምዬን ቤት
ወርቅ ይዝነብበት
የአባብዬን ቤት
ወርቅ ይዝነብበት”
እያሉ ወጣት ወንዶች ከልብ የመነጨ ምኞት የሚያሰሙበትን ዘመን ያምጣልንማ!
ከዓመት ዓመት “ሊነጋ ሲል ይጨልማል…” እያልን ራሳችንን የምንሸነግልበት ዘመን አልቆ የእውነትም ለሁላችንም ‘እኩል የሚነጋበትን’ ዘመን ያምጣልንማ!
እናላችሁ…ከአንጀታችን፣ ከልባችን ሎሬት ጸጋዬ ከዘመናት በፊት እንደጻፈው…
“ነጋ የአዲስ ዘመን ችቦ
ፈካ፣ ፀደይ አረብቦ
ሌሊቱ እንደ ጎሕ ቀደደ፣ ጨለማው እንደ ቀን ጠራ
እንደ ውቅያኖስ ዕፅዋት፣ እንደ ጠፈር ኮከብ ደራ
ምድር ስጋጃ ለበሰ፣ የጌጥ አልባሳት ተቀባ
ሰማይ በዕልልታ ተቀባ
እዮሀ መስከረም ጠባ፡፡”
እንድንል የምንበቃበት… በኑሯችንም፣ በእርስ ለእርስ ግንኙነታችንም፣ ለዚች መከረኛ አገር ባለን ራዕይም ፅንፍ ለጽንፍ ከመሆን ይልቅ ይበልጡኑ የምንቀራረብበትን ዘመን ያምጣልንማ!
“ከሳሽን ጠቆርሽን ይለኛል ባላገር
የሆዴን አውጥቼ ለስንቱ ልናገር”
ከሚሏት እንጉርጉሮ ነጻ የሚያወጣን ዘመን ይምጣልንማ!
“መሄዴ ነው መልቀቄ ነው ከአገር
እንቅቡም ሰፌዱም ነካካኝ በነገር”
እያልን በር ዘግተን የምንቆዝምበት እስከዘላለሙ በማይመጣ መልኩ ይጥፋልንማ! (‘ሰባኪ’ ነገር መሰልኩ እንዴ!)
መልካም የዋዜማ ቀናት ይሁኑልን፡፡
መልካምና የተሻለ አዲስ ዓመትም ይሁንልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

ዘመን መቁጠር የተጀመረው “በዚህ” ወይም “በዚያ ጊዜ ነው” ማለት ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም የተለያዩ አገሮች እንደየእምነታቸውና የሥልጣኔ ደረጃቸው ልዩ ልዩ የዘመን ቀመር ሊኖራቸው ይችላል፤ አላቸውም፡፡ ብዙውን ጊዜ ግን የዘመን አቆጣጠር ከሃይማኖቶች አነሳስና ዕድገት ጋር ይያያዛል፡፡
ባቢሎናውያን፣ ግሪካውያን፣ ህንዳውያን፣ ግብፃውያን፣ ቻይናውያን፣ ሮማውያን፣ ኢትዮጵያውያን፣ የአረብ አገሮች ወዘተ የተለያዩ የዘመን ቀመሮችን የሚከተሉ ሲሆን የአብዛኞቹ ቀመሮች መነሻ ሃይማኖት ነው፡፡ አገራችንን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ አገሮች የዘመን አቆጣጠራቸው መነሻ አዳም ነው፡፡ የሥነ ፍጥረት ተመራማሪዎች “የሰው ልጅ በምድር ላይ ኖረ” የሚሉት በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ጀምሮ ቢሆንም የክርስትና እምነት ተከታዮች ግን ዘመንን ከአዳም መፈጠር ጋር ያያይዙታል፡፡
ይህ ማለት ሰው በዚች ዓለም ላይ መኖር ከጀመረ በእኛ አቆጣጠር 7505 ዓመት ሞላው ማለት ነው፡፡ በአውሮፓውያኑ ቀመር ደግሞ 7513 ዓመት ይሆናል፡፡ የሁለቱም መነሻ ፍጥረተ አዳም ነው፡፡ ግን በመሀላቸው የሰባት ዓመት ከስምንት ወራት ልዩነት አለ፡፡ ለምን? የዛሬ ጽሑፌ ዓላማም ይህን ጥያቄ ማጉላትና ለልዩነቱ ሰበብ የሆነውን ሰውና ጊዜውን ማሳወቅ ነው፡፡
አውሮፓውያንም ሆኑ ኢትዮጵያውያን ለዘመን ቆጠራቸው መነሻ የሚያደርጉት አዳምን ነው ብያለሁ፡፡ ለዚህ ማስረጃ ይሆናቸው ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚከተለው ይጠቅሳሉ
ከአዳም እስከ ኖህ 2256 ዓመት፤
ከኖህ እስከ ግንብ ሥራ (ባቢሎናውያን ዘመን) 531 ዓመት፣
ከግንብ ሥራ አብርሃም እስከ ተወለደበት 551 ዓመት
ከአብርሃም እስከ ሙሴ ልደት 425 ዓመት፤
ከሙሴ እስከ ዳዊት ልደት 684 ዓመት፤
ከዳዊት እስከ ናቡከደነጾር ምርኮ 469 ዓመት፣
ከናቡከደነጾር እስከ ታላቁ እስክንድር 265 ዓመት
ከታላቁ እስክንድር እስከ ኢየሱስ ልደት 319 ዓመት፤
ድምር 5500 ዓመት በማምጣት ከኢየሱስ ልደት በኋላ እና በፊት እያሉ ዘመኖቻቸውን ያሰላሉ፡፡
በመስኩ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያስረዱት፤ የመጀመሪያውን የዘመን መቁጠሪያ ቀመር ያወጡት “ሱሜሪያውያን” በመባል የሚታወቁት ጥንታውያኑ የባቢሎን ዜጐች ናቸው፡፡ የሱሜራዊውያኑ የቀን አቆጣጠር ዋና መነሻ የጨረቃ እንቅስቃሴ (ዑደት) ነው፡፡ የጨረቃን ዑደት በማጤን አሥራ ሁለት ወራትን ሰይመው ነበር፡፡ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ የሚጨመር 13ኛ ወርም ነበራቸው። ይህን ያደረጉበት ምክንያት ዓመቶቹን ለመለየት እንዲረዳቸው ነበር፡፡
ግሪኮች፣ ግብጾችና የሴም ዝርያ ያላቸው ሌሎች ህዝቦችም በሱሜሪያውያን የቀን መቁጠሪያ ይጠቀሙ ነበር፡፡ ሆኖም ቀስ እያሉ የራሳቸውን ምርምር ማድረግ ቀጥለዋል፡፡ ከጊዜ በኋላ ግብጾች ምንም እንኳ የቅመራ መሠረታቸውን ጨረቃ ላይ ቢጥሉም የራሳቸውን የቀን መቁጠሪያ ለማዘጋጀት ቻሉ፡፡ ቅመራቸው በዓመት ውስጥ የሚውሉ ባህላዊ የእምነት በዓላትንና ወቅቶችን ግምት ውስጥ ያስገባ ስለነበር ከሱሜራውያኑ ቀመር የተሻለ ጥቅም አስገኝቷል፡፡
የቀን መቁጠሪያው ከባቢሎናውያኑ የሱሜራውያን የተሻለ ነበር የሚባለው ከዓባይ ወንዝ መሙላትና መጉደል ጋር የተያያዘ ስለነበር፣ የሀገሪቱን መንግሥት ስሜት መግዛት በመቻሉ ነው፡፡
በዚህ መሠረት የግብጽ መንግሥት ከሥራውና ከመንግሥታዊ አደረጃጀቱ ጋር የሚስማማ የቀን መቁጠሪያ እንዲዘጋጅ አደረገ፡፡ አይሁዳውያንና ሙስሊሞች ደግሞ የጨረቃን ዑደት የተከተለ የቀን መቁጠሪያ ሥርዓት አዘጋጁ፡፡ ሮማውያንም ልክ እንደ አይሁዶችና ሙስሊሞች የዘመን ቆጠራ ስርዓታቸውን ያዘጋጁት በጨረቃ እንቅስቃሴ ላይ ተመሥርተው ሆኖ፣ ቀመራቸው በዓመት ውስጥ 355 ቀናትን እንዲይዝ ተደርጐ ተቀረፀ፡፡ ሮማውያን የዘመን አቆጣጠራቸውን የወሰኑት ልክ እንደሱሜራውያኑ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ 13ኛ ወር እንዲያካትት በማድረግ ነው፡፡
ጥቅምት፣ መጋቢት፣ ግንቦትና ሐምሌ እያንዳንዳቸው 31 ቀናት እንዲኖራቸው ሆኖ የተቀረፀው የሮማውያን ቀመር፤ ለየካቲትም 28 ቀናት መድቦ ነበር፡፡ ለቀሩት ወሮች ግን ለእያንዳንዳቸው 29 ቀናት ተወስኖላቸው እንደነበር ሻለቃ አባይነህ አበራ “ካዘና” በሚለው መጽሐፋቸው ያስረዳሉ፡፡
ይሁን እንጂ በወቅቱ የሮማ ሊቃውንት የቀመሩት ያ ቀመር፣ መሬት በፀሐይ ዙሪያ የምታደርገውን ኡደት (መሽከርከር) ግምት ውስጥ ያስገባ ስላልነበር ውሎ አድሮ ችግር ማስከተሉ አልቀረም፡፡
ችግሩም በተቀመረው የዘመን ስሌት መሠረት ከመግባትና ከመውጣት ይልቅ ወቅቶች በተቃራኒው የሚከሰቱበትና የሚጠፉበት አጋጣሚ እየበዛ መሄዱ ነበር፡፡
ለምሳሌ በቀን መቁጠሪያው ላይ “በጋ ነው” ተብሎ በተመለከተው ወር ክረምት ይገባል፤ ወይም በፀደይ ወራት በልግ ይከሰታል፡፡ ችግሩን በአግባቡ የተገነዘበው የወቅቱ የሮማ ንጉሠ ነገሥት ቄሳር ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለጉን ተያያዘው፡፡ እናም በ46 ዓመተ ዓለም የተሻለ የቀን መቁጠሪያ አዘጋጀና ችግሩን በመጠኑም ቢሆን ማቃለል ቻለ፡፡ የዓመቱ ቀናትም 366 ከስድስት ሰዓታት እንዲሆኑ ደነገገ፡፡
በዚህ የተነሳ ቀድሞ “ኩዊንቲሊስ” ይባል የነበረው ወር ለጁሊየስ ቄሳር መታሰቢያነት ሲባል “ጁላይ” እንዲባል ተወሰነ፤ ቀመሩም “የጁሊያን ቀመር” እየተባለ መጠራት ጀምሮ ነበር፡፡ በጁሊየስ ቄሳር የተቀመረው የዘመን መቁጠሪያም የበዓላትንና የወቅቶችን መፈራረቅ በማስከተሉ የመስኩን ሊቃውንት ማሳሰቡ አልቀረም ነበር፡፡ የዚህ ችግር ዋናው ምክንያት በየአራት ዓመት አንድ ጊዜ የካቲት ላይ የሚጨመረው አንድ ቀን ለበዓላት፣ ዕለታትና ለወቅቶች መለዋወጥ (መግቢያና መውጫ ጊዜያቸው መለዋወጥ) ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጉ ነበር፡፡
ከብዙ ጊዜ በኋላ ችግሩን ያጤኑት “አባ ጐርጐርዮስ 13ኛ” የተባሉ ሊቀ ጳጳስ፤ ሌላ ቀመር አወጡና በነበረው የጊዜ መቁጠሪያ ላይ 10 ቀናት (ሻለቃ ዓባይነህ አበራ 11 ቀናት ተጨመሩ ይላሉ) በመደመር እ.ኤ.አ ጥቅምት 5 ቀን 1575 ዓ.ም “ነገ ጥቅምት 15 ቀን ነው” ብለው አወጁ፡፡ የአባ ጐርጐርዮስን ሃሳብ ብዙ የካቶሊክ እምነት ተከታይ አገሮች ቢቀበሉትም የኦርቶዶክስና የፕሮቴስታንት እምነትን የሚከተሉ አገሮች ግን በሃሳቡ ሊስማሙ አልፈለጉም ነበር፡፡
አባ ጐርጐርዮስ ይህን የ10 ቀን ልዩነት ያገኙት ከ375 ዓመተ ምህረት ጀምረው በማስላት መሆኑን ጥናታቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ተናግረዋል፡፡ በጥናታቸው መሠረት፤ አንድ ዓመት 365 ቀናት፣ ከስድስት ሰዓት የነበረው የዩሊየስ ቄሳር ቀመር፤ በደቂቃ፣ በሰዓትና በዕለት ሊከፋፈል ይገባል፡፡ እናም አንድ ዓመት ማለት 365 ቀናት፣ ከአምስት ሰዓት፣ ከአርባ ስምንት ደቂቃዎችና ከአርባ ስድስት ሰኮንዶች ይሆናል፡፡ በመሆኑም “11 ደቂቃዎችና 14 ሰኮንዶች ሳይኖሩ እየተኖረባቸው አልፈዋል” በማለት አባ ጐርጐርዮስ ከሰባት እስከ አስር ቀናትን በመጨመር ነው ከላይ የተገለፀውን ቀመር ይፋ ያደረጉት፡፡
ኢትዮጵያውያኑ የሐሳብ ዘመን ሊቃውንትም ጥቃቅን የሰከንድና የደቂቃ ሽርፍራፊዎች መኖራቸውን ያምናሉ፡፡ የሁለት ሺህ በዓልን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ባወጣችው ልዩ እትም ላይም፣ ይኸ አስተሳሰብ እውነት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
“የዓመቱ አንድ ሳልሲት ሶስት መቶ ስልሳ አምስት ነው፤ አምስቱን ድቁቅ ደቃዲቅ ብለህ ተወው፡፡ ሶስት መቶ ስልሳ ሳልሲት ስድስት ካልኢት ይሆናል፤ ስድስት ካልኢትን እስከ 10 ዓመት ቢወስዱት ስሳ ካልኢት ይሆናል፡፡
ስሳ ካልኢት አንድ ኬክሮስ ይሆናል፤ እስከ መቶ ዓመት ቢወስዱት አስር ኬክሮስ ይሆናል፡፡ እስከ ሁለት መቶ ዓመት ቢወስዱት ሃያ ኬክሮስ ይሆናል፤ እስከ ሶስት መቶ ዓመት ቢወስዱት ሰላሳ ይሆናል። እስከ አራት መቶ ዓመት ቢወስዱት አርባ፣ እስከ አምስት መቶ ዓመት ቢወስዱት ሃምሳ፣ እስከ ስድስት መቶ ዓመት ቢወስዱት ስሳ ኬክሮስ ይሆናል፤ ስሳ ኬክሮስ አንድ ዕለት ይሆናል፡፡ እነዚህ በጣም አነስተኛ የሆኑ የጊዜ ትርፍራፊዎች በስድስት መቶ ዓመት አንድ ዕለት ይሆናሉ፡፡ በዚህም ጊዜ ዐቀድ የሚባል ኮከብ ይወጣና ፀሐይን ይጋርዳል” በማለት ይቀምራሉ፤ የፀሐይ ግርዶሽ ምክንያቱንና ጊዜውንም ያብራራሉ፡፡
ከላይ ማየት እንደሚቻለው ኢትዮጵያውያኑ የሐሳብ ዘመን ሊቃውንት የጊዜ ሽርፍራፊዎችን “ድቁቅ” እና “ደቃደቅ” በማለት ጀምረው በእነዚህ ሽርፍራፊዎች ምክንያት ከስድስት መቶ ዓመት በኋላ ሊከሰት ስለሚችለው ኮከብና ስለ ፀሐይ ግርዶሽም የተለያዩ የቅመራ ዘዴዎችን በመጠቀም ይነግሩናል፡፡ እነዚህ “ጥቃቅን” የተባሉ የጊዜ ሽርፍራፊዎች የዕለታት ልዩነትን እንደሚያመጡም ያስረዳሉ፡፡
አባ ጐርጐርዮስ በቀመሩት የጊዜ መቁጠሪያ ላይ የዓመታትና የዕለታት ልዩነት የመታየቱ ምስጢርም ይኸው ይመስላል፡፡ ሆኖም አባ ጐርጐርዮስ የተነሱበት ሐሳበ ዘመን፣ ነባሩን አቆጣጠር ማፋለሱ አልቀረም፡፡ ለዚህም ነው ከጥቅምት 5 ቀን 1575 ዓ.ም ጀምሮ በእኛና በአውሮፓውያን ቀመር ላይ አሁን የሚታየው የቀን ልዩነት የመጣው፡፡
የዕለታቱ ልዩነት የአባ ጐርጐርዮስ ቀመር ከሆነ የሰባት ዓመት ከስምንት ወራት ልዩነቱን ምን አመጣው?
የእኛም ሆነ የምዕራባውያን የዘመን አቆጣጠር መነሻው የኢየሱስ ልደት ነው፡፡ የኢየሱስ ልደት መነሻቸው ከሆነ ለምን ተለያዩ? የሚለው ጥያቄ መነሳት ያለበት ነው፡፡ ኢየሱስ አንድ ነው፤ የተወለደውም “ቤተልሄም” በተባለ አንድ ቦታ ነው፡፡ በዚህ ምዕራቡም ሆነ ምስራቁና የቀረው ዓለም ሁሉ ይስማማበታል፡፡ ከዚህ እውነት በመነሳትም እስከ 532 ዓ.ም ድረስ የምዕራባውያንና የእኛ ዘመን አቆጣጠር አንድ ነበር፡፡
በ532 ዓ.ም ግን “ዲዮናስዮስ” የተባሉ ሮማዊ መነኩሴ፣ አዲስ ቀመር በማውጣት ነባሩን የዘመን አቆጣጠር ከመሠረቱ አናጉት፡፡ ይህም በእኛና በአውሮፓውያን አቆጣጠር መሃል የሰባት ዓመት ከስምንት ወር ልዩነትን አመጣ፡፡ በአባ ዲዮናስዮስ ቀመር መሠረት፤ ኢየሱስ የተወለደው በ5492 ዓመተ ዓለም ላይ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመስርተው ቀመራቸውን ላወጡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች የሚዋጥ አልሆነም፡፡
ምክንያቱም እግዚአብሔር ለአዳም “በ5500 ዓመት ተወልጄ…” ብሎ የገባለትን ቃል በማሰብ “የእግዚብሔር ቃል አይለወጥም፤ እግዚአብሔርም አይዋሽም፡፡ የተወለደውም በገባው ቃል መሠረት ልክ በ5500 ዓመተ ዓለም ላይ ነው” በማለት የአባ ዲዮናስዮስን ሐሳበ ዘመን ውድቅ ያደርጉታል፡፡ ይህ ዐቢይ ጉዳይም ነው የልዩነቱ መነሻ፡፡
ስለሆነም ለሰባት ዓመት ከስምንት ወራት ልዩነት የተፈጠረው በ532 ዓ.ም አባ ዲዮናስዮስ በቀመሩት ሂሳብ ምክንያት ሲሆን የዕለታቱ ልዩነት የተከሰተው ደግሞ በ1575 ዓ.ም አባ ጐርጐርዮስ ባወጡት ቀመር መሠረት ነው፡፡
የዓመት መጀመሪያችን ለምን መስከረም እንደሆነ የተለያዩ ማስረጃዎች አሉ፡፡ መምህር አፈወርቅ ተክሌ በ2005 ዓ.ም “መጽሐፈ ታሪክ ወግስ” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው፤ “እግዚአብሔር ለእስራኤል ከግብጽ የወጣችሁበት ወር የዓመት መጀመሪያ ይሁናችሁ (ዘፀዓት 12፡1) እንዳላቸው ሁሉ፣ የካም ልጆችም ወደ ኢትዮጵያ የገቡበትን ይህንን ወር የዓመት መጀመሪያ ይሁነን ብለው ርዕሰ አውደ ዓመት አድርገው ሰይመውታል” ይላሉ፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት የሌሎች አገሮች ሁሉ የዘመን መለወጫ ወር መስከረም እንደነበረም እኒሁ መምህር ያስረዳሉ፡፡ መልካም አዲስ ዓመት!

Published in ህብረተሰብ

                        ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ባለፈው ሳምንት በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ “ኅብረተሰብ” አምድ ላይ ካሌብ ንጉሤ የተባሉ ፀሃፊ “ሴቶች ለምን አይቀድሱም?” በማለት ራሳቸው ጠይቀው ራሳቸው የ”መለሱበት” ፅሁፍ ነው፡፡ ፀሐፊው ለሴቶች መቆርቆራቸው ያስመሰግናቸዋል፡፡
መፅሐፍ ቅዱስን አንብበው ከሆነ የፃፉት፣ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 2 ቁጥር 18 “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት” ይለናል እንጂ እርሳቸው “ይመስለኛል” በማለት እንደገለፁት የመጀመርያው ሰው ብቻውን መኖር ስላቃተው “ኧረ ረዳት ፍጠርልኝ” አላለውም፡፡ የፈጣሪ ቅዱስ ፈቃድ ሆኖ ነው አዳም እና ሔዋን የተፈጠሩት፡፡
ነገር ግን ሄዋን የአምላክ ትእዛዝ እንዲጣስ በር ከፈተች፡፡ በከፈተችው በር አዳምም ገብቶ አታድርጉ የተባሉትን ስላደረጉና አትብሉ የተባሉትን ስለበሉ በሰዎች ላይ ሞት መጣ፡፡ ፍጥረቱን የማይረሳ እግዚአብሔር በሄዋን ስህተት የመጣውን ይህን ሞት ዳግማዊት ሄዋን ከሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ከ5500 ዓመታት በኋላ ተወልዶ አድኖናል፡፡ ሰለዚህ ሴቶች ምንም እንኳ በመስቀል ምእመናን ባርከው፣ በጥና ፀሎት አሳርገው ባይቀድሱም ቅድስናን ግን አልተነፈጉም፡፡

ድንግል ማርያም ወላዲት አምላክ ለሴቶች ቅድስና አቻ የሌላት መገለጫ ብትሆንም ሌሎችም ቅዱሳት እንስት አሉ፡፡ ቅዱሳት ስለሆኑ፣ ሴቶች መቅደስ ገብተው መቀደስ አለባቸው ብሎ መሟገት መፅሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት የለውም፡፡ ስለዚህ አቶ ካሌብ ፅሁፋቸው ነገረ ሃይማኖት ላይ አተኮረ ይበሉን እንጂ ከነገረ ሐይማኖት መነሻዎች አንዱ የሆነውን መፅሐፍ ቅዱስን አለያም ሌላኛውን መነሻ ተፈጥሮን በቅጡ አልዳሰሱም፡፡ ቢዳስሱማ ኖሮ መፅሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ እሳቤ ባላመጡ፣ ተፈጥሮን ከማስተዋልም ባልወጡ ነበር፡፡ ተፈጥሮን የተመለከተ ሰው፣ ተፈጥሮ የራሷ የሥራ ክፍፍል እንዳደላደለች ይረዳል፡፡ ከነዚህ ኃላፊነቶች አንዱ “መቅደስ ገብቶ መቀደስ ነው” ልክ የመውለድ ፀጋ ለሴቶች የተሰጠውን ያህል ቀድሶ መባረክም ለወንደች ከአምላክ የተሰጠ ኃላፊነት ነው፡፡

ዛሬ ሴቶች መቀደስ አለባቸው ያሉን ፀሐፊ፤ ነገ ደግሞ ወንዶች አርግዘው መውለድ ይችላሉ ላለማለታቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ይህ በራሳቸው ቃል ልጠቀምና “የፈጣሪን ትእዛዝ በአግባቡ አለመተግበር ወይም ያላዘዘውን የእሱ ቃል አስመስሎ የመተርጐም አባዜ ያለ ስለሚመስለኝ ነው” እንዳሉት ፀሐፊው ራሳቸው በይመስለኛል እየተረጐሙ ሌሎችን አጣመው ተረጐሙ ለማለት ይችላሉን? የራሳቸውን ዝሆን ሲያጠሩ የሌላውን ትንኝ ውጠዋልና አይችሉም፡፡
“ሴቶች ለምን አይቀድሱም?” በሚለው ፅሁፍ ውስጥ እስራኤላውያንን ከግብፅ ለማውጣት ከሰው ወገን ትልቁን ሚና ስለተወጣው ሙሴ ከመፅሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ የማይገኝ የተሳሳተ መረጃ ተቀምጧል፡፡ ለእስራኤላውያኑ ሕግ ያወጣው አምላከ እስራኤል እግዚአብሔር እንጂ ሙሴ አይደለም፡፡ የሙሴ ሚና ከሲና ሕጉን ለሕዝብ ማድረስ ነበር፡፡ ታዲያ እግዚአብሔር ሙሴን ሲያስነሳ ታላቅ እህቱ ማርያም እና ወንድሙ አሮን ነበሩ፡፡ ቢፈልግ ኖሮ ልክ እነ አስቴር፣ ዮዲት… እንደተጠሩት ማርያምንም “ሕዝቤን ከግብፅ አውጭልኝ” በማለት ለሙሴ የተናገራቸውን ህግጋት በሙሉ በነገራት ነበር፡፡ ፀሐፊው ሙሴ ሕጉን ሴቶችን ለማርከስ እንደተጠቀመበት አስመስለው ፅፈዋል፡፡ እውነታው ግን እሳቸው እንደሚሉት አይደለም፡፡
እዚያው በኦሪት መፃህፍት ወዳለው እውነታ ከማምራቴ በፊት አለቃ ገብረሐና አደረጉ የተባለውን መጥቀስ ፈለግሁ፡፡
አለቃ ከሴቶች ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት እየፈፀሙ በቅዳሴ ሰዓት ሳይነፁ ቤተክርስትያን ገቡ፡፡ ይህን ከጊዜ በኋላ የተረዱት ካህናት በመቋሚያ ደብድበው አባረሯቸው፡፡ በዚህ ቂም የያዙት አለቃም በሌላ የቅዳሴ ቀን ማልደው ወደ ቤተክርስትያን በመሄድ በሴቶች መግቢያ በኩል ቆሙና ሴቶቹን “ዛሬ ቅዳሴ የለም” እያሉ መመለስ ያዙ፡፡ ቅዳሴ ሲጀመር አንዲትም ሴት ዝር አላለችም። ይህ ያደናገጣቸው ቀሳውስት ጉዳዩን ሲመረምሩ፣ የአለቃ ተንኮል መሆኑን ደረሱበት፡፡ አለቃንም በማፋጠጥ “ምነው?” ብለው ሲጠይቋቸው “ከምንጩ የቀመሰ ከረከሰ፣ ምንጩ ራሱ ርኩስ፤ ነው ከሴት ጋር ተኛህ ብላችሁ መቅደስ አረከስክ ካላችሁኝ፣ ራሳቸው ሴቶቹ ረከሱ ማለታችሁ ነው” አሉዋቸው፡፡
ሙሴ አርባ ቀን በሲና ተራራ ከፆመ በኋላ ነው ሕገ ኦሪት ከእግዚአብሔር የተሰጠው፡፡ በእነዚህ ሕጐች ክህነት ለተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻ የተሰጠ ፀጋ ነው፡፡

በወቅቱ ከነበሩት ነገደ እስራኤል የሌዊ ልጆች ብቻ አገልግሎቱን እንደሚሰጡ፣ ከነሱም አሮን ክህነቱን እንደሚመራ ተጠቅሷል፡፡ እግዚአብሔር ይህን ሕግ ሲሰጥ ሴቶች መኖራቸውን ዘንግቶት ወይንም ሴቶችን ለመበደል አይደለም፡፡ አገልግሎቱ የሚጠይቀውን ንፅህና ወንዶች ራሳቸው ካላሟሉ ቤተመቅደስ አይገቡም፡፡ መግባትም አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ቅዳሴ የመብትና የዲሞክራሲ ጉዳይ ሳይሆን የአገልግሎት ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ በዚያው በሙሴ ጊዜ የነበረውን ዳታን ከወንድሙ ከአቤሮን ጋር በመሆን ገብተን ካላጠንን ብለው በማመፃቸው መቀሰፋቸውን እንዴት ዘነጉት አቶ ካሌብ? ዳታንና አቤሮን ወንዶች ናቸው፡፡
ወንዶች ብቻ መቀደሳቸው የአገልግሎት እንጂ የፆታ ጉዳይ ባለመሆኑ ለዘመናት ዘልቋል። ይህንንም በየዘመኑ የነበሩ ወንዶች እና ሴቶች ምእመናን ሲተገብሩት ቆይተዋል፡፡ አሁንም እየተገበሩት ነው። ለወደፊትም ይህንኑ ይቀጥላሉ፡፡
በታሪክ የተነሱ እና የዘመናቸውን ሕግ ለመቀየር አቅም የነበራቸው ሴቶች ሳይቀሩ ቅዳሴ ለወንድ ብቻ የተተወ መሆኑን አምነው ተቀብለዋል፡፡ ይህ ግን ሴቶች በቅዳሴው የራሳቸው ሚና የላቸውም የሚያሰኝ አይደለም፡፡ የራሳቸው የሥራ ድርሻ አላቸው፡፡
ገዳማት ለሴቶች ክፍት የሚሆኑበትና የማይሆኑበት ሕግም አለ፡፡ ገዳማት የሴት፣ የወንዶች ወይም የአንድነት በመባል ይከፈላሉ፡፡ ከነዚህ ወንዶችንም ሴቶችንም የሚያስተናግደው የአንድነት ገዳም ነው፡፡ የወንድ ገዳም ሴት፣ የሴት ገዳም ወንድ አይገባበትም፡፡
በሴት ገዳም ወንድ ሊገባ የሚችለው በቀዳሽነት ብቻ ነው፡፡ ከወንድ ገዳማት አንዱ የሆነውን ሴቶች ፈፅሞ የማይገቡበትን የደብረዳሞ ገዳም የማየት ጉጉት ያደረባት አንዲት ፈረንጅ እንደወንድ ለብሳ ለመግባት ባደረገችው ጥረት ገመዱ ተበጥሶ መከስከሷ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡
መፅሐፍ ቅዱስን አንብቤአለሁ፤ ክርስትናን እቀበላለሁ ያሉት ፀሐፊ “ማረጥ… መጠውለግ…” የሚሉትን ቃላት ከየት እንዳመጡት ፈፅሞ አልገባኝም፡፡ ምክንያቱም እነ ሳራ ካረጁ በኋላ ሌሎችም በመካንነት ከቆዩ በኋላ ለመውለድ በቅተዋልና፡፡ እኔ የምለው የት ሀገር ይሆን ወላጅ (እመጫት) ሴት መቅደስ ገብታ የምትቀድሰው?
እርስዎ ያነሱት ጥያቄ ተገቢ ቢሆን ኖሮ ያነሱዋት ልጆች ከወለደች በኋላ ቅድስና ያገኘችው ቅድስት ክርስቶስ ሰምራም አምላኳን ጥያቄዎን በጠየቀች ነበር፡፡ እሷ ግን ሴቶች መቅደስ ገብተው ይቀድሱልኝ ብላ ሳይሆን ባህር ገብታ የፀለየችው እንደ እርስዎ እና እኔ አይነቶችን እንዳያስት ሰይጣንን ማርልኝ ነው ያለችው፡፡
እርሷም ሆነች ሌሎች እንስቶች እርስዎ እንዳሉት፤ ጀግና ወልደዋል፡- የጀግና እናት፣ የቄስ እናት፣ የጳጳስ እናት፣ የአምላክ እናት… ናቸው፡፡ ጉልበት ስለሌላት አይደለም ቄስ፣ ጳጳስ፣ ያልሆነችው፡፡ የእግዚብሔር ምርጫ ነው፡፡ ጉልበትም የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው፡፡ አላዩም እንዴ እቴጌ ጣይቱን? አላዩም እንዴ የቀድሞዋን የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሬት ታቸርን ከአጀንዳ እንዳልወጣ፡፡ አጀንዳዬ አሁንም ሴቶች መቅደስ አልተፈቀደላቸውም የሚል ነው፡፡ አልተፈቀደላቸውም ማለት ቅዱሳን አይደሉም ማለት ግን አይደለም፡፡
ስለዚህ ሴቶች የክርስቶስን ትንሣኤ ቀድመው ስላዩ መቅደስ ገብተው መቀደስ አለባቸው በሚል ያቀረቡት መከራከሪያ የሚያዋጣ አይደለም፡፡
ጌታችን፣ መድሃኒታችን፣ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስራሁለት ሐዋርያት ሲመርጥ ሁሉም ወንዶች ነበሩ (ሐዋርያነት የፆታ ጉዳይ ባይሆንም) ሰላሳ ስድስት ቅዱሳት እንስትም መርጧል ከሴቶች። ሰባ ሁለት ሌሎች አርድእትም ነበሩ ከሁለቱም ፆታ፡፡ በደብረታቦር ምስጢረ መለኮቱን ሲገልፅ ከሐዋርያት ሦስቱ ብቻ ናቸው ተራራው አናት ላይ አብረው የነበሩት፡፡ ዘጠኙ ሐዋርያትና ሰላሳ ስድስቱ ቅዱሳት ሴቶችም ሆኑ አርድእት አልነበሩም፡፡ ሞትን ድል ነስቶ ሲነሳ አቶ ካሌብ ንጉሤ እንዳሉት ቀድመው ያዩት ሴቶች ናቸው፡፡ ከሴቶችም የመጀመርያዋ መቅደላዊት ማርያም ነበረች፡፡ ነገር ግን “ረቡኒ (መምሕር)” ብላ ስትጠጋው ዳስሳው የተፈወሰችውን ሴት “አትንኪኝ” ብሏታል፡፡ በጥርጣሬ ተኮማትሮ በጌታ ምህረት ቢፈወስም ቶማስ ነበር የዳሰሰው፡፡ ምን ያህል ተረዱልኝ አቶ ካሌብ?

 

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 07 September 2013 10:27

የወር አበባ ርኩሰት አይደለም!

ለጽሁፉ መሰናዳት ምክንያት የሆነኝ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ያለፈው ሳምንት ዕትም “ሴቶች ለምን አይቀድሱም?” በሚል ርዕስ በካሌብ ንጉሴ የቀረበው ጽሁፍ ነው፡፡ በጽሁፉ የቀረቡት ጥያቄዎች መልስ የሚያሻቸው ሆነው ስላገኘኋቸው ለጥያቄዎቹ የሚመጥን መልስ አጠናክሬአለሁ፡፡ የጥያቄው መሰረቱ የሴቶች የወር አበባ እንደመሆኑ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ያስችለን ዘንድ በመጠኑ ስለ ሴቶች የወር አበባ ምንነት አጭር ገለጻ አደርግና ወደ መልሶቹ እገባለሁ፡፡
የወር አበባ በሴቶች ላይ በየወሩ የሚታይ የደም መፍሰስ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ “ደመ ጽጌ፣ አበባ ደም” በመባል ይጠራል፡፡ አሰያየሙም የወንድ ዘር ካላገኘ ከማህጸን ግድግዳ ፍራሽ ጋር በደም መልክ ስለሚፈስና የኋለኛው ማንነቱ ደምነት ስለሆነ ነው፡፡ ይህም ማለት አገልግሎቱን የጨረሰ፣ ያረጀ፣ ቆሻሻ ማለት ነው፡፡ ይህ በየወሩ ዑደትን ተከትሎ የሚሄደው የዘር ፍሳሽ በስነ ህይወት ትምህርት ኦቫሪ (ከዘር ከረጢት) የሚለቀቅ የወንድ ዘር ካላገኘ ኦቫ (ሴቴ ዘር) ጋር እየተቀላቀለ የሚወርድ ነው፡፡
በጽሁፉ ውስጥ ከተነሱት ጥያቄዎች መሃከል የመጀመሪያው ሙሴ “በወር አበባ ላይ ያለች ሴት የረከሰች ናት” ግን ለምን? የሚል ነው፡፡ በመሰረቱ የወር አበባ በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በሁለት ከፍለን ነው መመልከት ያለብን፤ በዘመነ ኦሪትና ዘመነ አዲስ ኪዳን በማለት፡፡ በርግጥ በዘመነ ኦሪት የወር አበባ የርኩሰትና የመርገም ምልክት ነበር፡፡ ለዚህም ማስረጃነት በመጽሃፍ ቅዱስ ዘሌ 18÷19፣ 20÷18 ያሉ ጥቅሶች “በመርገምዋ ርኩሰት ሳለች” እና “ባለ መርገም ሴት” በማለት ሲገልጸው፤ ባንጻሩ ደግሞ ከወር አበባዋ ነጻ የሆነችውን ሴት “ከርኩሰትዋ ነጽታ” በማለት የወር አበባ የርኩሰትና የመርገጥ ምልክት መሆኑን ይጠቁማል፡፡
በዘመነ አዲስ ደግሞ የወር አበባ የርኩሰትና የመርገም ምልክት መሆኑ ቀርቷል፡፡ ርኩሰት አይደለም፤ ርኩስም አያሰኝም፡፡ በብሉይ ኪዳን አዳምና ሄዋን በገነት በነበሩ ጊዜ ዕጸ በለስን በልተው እግዚአብሔርን በደሉ፤ እግዚአብሔርም ሄዋንን ደመ ዕጸ በለስን አፍስሰሻልና “ወበከመ አድመውኪያ ለእንትኩ ዕጽ ከማሁ ድምዊ ለለወርኁ፡፡” በማለት ደሟ በየወሩ እንዲፈስ ፈጣሪ ፈረደባት፡፡ ስለዚህ የሄዋን ደም መፍሰስ መነሻው መርገም ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሥቶስ በፈጸመው ቤዛነት መርገምነቱና ርኩስነቱ ተወግዷል፡፡
ነገር ግን የወር አበባ በዚህ ዘመን ርኩሰት ወይም መርገም ባይሆንም እድፍ (ቆሻሻ) ነው፡፡ እድፍና ርኩሰት ልዩነት አላቸው፡፡ ርኩሰት ውስጣዊ ነው፤ በንስሃ እንጂ በውሃ አይጠራም፡፡ እድፍ ደግሞ ግዘፍ አካል ያለው፣ የሚታይና ውሃ የሚያነጻው ነው፡፡ የወር አበባ በሴቶች ባህሪ ሳለ እንደ ቆሻሻ አይቆጠርም፣ ከሰውነት ሲወገድ ግን ይቆጠራል፡፡ ይህንን ለማስረዳት ምሳሌ መሆን ከሚችሉት ውስጥ ዛህል (ንፍጥ)፣ ሽንት፣ ምራቅ፣ ዓይነምድርና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡
የወር አበባ ርኩሰት ባለመሆኑ መስቀል ከመሳም፣ ከመጸለይ፣ ቅዱሳት መጻህፍትን ከማንበብና ከመድገም አያግድም፡፡ ነገር ግን ከሩካቤ፣ ከመጠመቅ፣ ከመቁረብና ቤተ መቅደስ ከመግባት ይከለክላል፡፡
እነዚህ ዋና ዋና በወር አበባ ጊዜ የተከለከሉ ነገሮችን መከልከላቸው ለምን እንደሆነ መጽሃፋዊ መረጃዎችን በአጭር በአጭሩ በማቅረብ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
ከሩካቤ
ሩካቤ በወር አበባ ጊዜ ከሚከለከሉ ነገሮች አንዱ ነው፡፡ በወር አበባ ጊዜ የሚደረግ ግንኙነት የህክምና ባለሙያዎች ሳይቀር ለአባላዘር፣ ለልዩ ልዩ በሽታዎችና ለልክፋት (infection) ሊያጋልጥ እንደሚችል በመናገር እንዲፈጸም ይመክራሉ፡፡ በመንፈሳዊው አስተምህሮ ስንመለከተው ደግሞ የሰው ልጅ ዘር ቅዱስ በሆነው በእግዚአብሔር አምሳል በመፈጠሩ፣ ይህንን የተከበረ ዘር፣ እዳሪ ወይም ቆሻሻ ከሆነ ደም ጋር ማዋሃድ ኃጢያት እንደሆነ ይቆጠራል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ሴት ልጅ በወር አበባዋ ጊዜ እንዳለች የሚፈጸምን ሩካቤ “እርሷም በመርገምዋ ርኩሰት ሳለች ኃፍረተ ሥጋዋን ትገልጥ ዘንድ ወደ እርሷ አትቅረብ” ዘሌ 18÷19፣ ዘሌ 20÷18።
በዚህም ምክንያት በወር አበባ ጊዜ የሚፈጸም ሩካቤ በኦሪትም ይሁን በአዲስ ኪዳን ክልክል ነው፡፡
ከመጠመቅ
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌ ሆኖ አሁን ያድነናል፤ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፡፡ ለእግዚአብሔር በጎ ህሊና ልመና ነው እንጂ” 1ኛ ጴጥ 3÷21 በማለት ተናግሯል፡፡ ስለዚህ ጥምቀት ስጋዊ እድፍን ማስወገጃ ስላልሆነ፣ ከመጠመቅ በፊት ተጣጥበው እንጂ ከእድፍ ጋር ለመጠመቅ መቅረብ ተገቢ አይደለም፡፡ የወር አበባም ከላይ እንደተመለከተው ከሰውነት ሲወጣ እድፍ (ቆሻሻ) በመሆኑ፣ ከዚህ የቤተ ክርስቲያን ስርዓት ውጪ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
ከመቁረብ
ሴቶች ከወር አበባ ሳይነጹ ሥጋ ወደሙ መቀበል አይችሉም፡፡ ይህንን ስርዓት ተላልፈው ወደ ሥጋ ወደሙ እንዲቀርቡ ያደረገ ዲያቆንም ይሁን ቄስ ከክህነቱ እንዲሻር ፍትሕ ነገስት ይደነግጋል፡፡ “ከግዳጅዋ ያልነጻችውን ሴት በደሟ ወራት ከቤተ ክርስቲያን አግብቶ ሥጋውን ደሙን ያቀበለ ከክህነቱ ይሻር፡፡” ፍትነገ 6፣ ዘሌ 7፡19
ቤተ መቅደስ ከመግባት
በወር አበባ ላይ ሳለች ሴት ወደ ቤተ ክርስቲያን አትግባ ማለት ቤተ ክርስቲያን አትሂድ ማለት ሳይሆን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዳ የመጀመሪያውን ቅጽር (አጥር) ከገባች በኋላ በመጠለያ ውስጥ በመሆን ትጸልይ፣ ትማር ወይም ማንኛውንም አይነት መንፈሳዊ ስራዎችን ሰርታ ትመለስ እንጂ ደፍራ ካለ ንጽህናዋ ወደ ቤተ መቅደስ አትግባ ማለት ነው፡፡
አቶ ካሌብ ንጉሴ፤ በጽሁፋቸው እንደማስረጃነት የጠቀሷት በአመንዝራነት ተይዛ ጌታ ፊት የቀረበችውን ሴት ነው፡፡ ቃሉን የምናገኘው በዮሐ 8÷1 ላይ ሲሆን ትርጓሜው ደግሞ በዮሐ 8÷3 እና ዮሐ 20 ላይ ቤተ ክርስቲያን ሶስት ቅጽሮች (አጥር) እንዳላት ተብራርቷል፡፡ ስለዚህ ድቀት ያገኘው ማለትም፡- በዝሙት የተሰነካከለ፣ ህልመ ለሊት ያየ ሰውና በወር አበባ የተያዘች ሴት የመጀመሪያውን ቅጽር ብቻ አልፈው ተሳልመው፣ መባቸውን ሰጥተው ሌሎችንም መንፈሳዊ ተግባራት ፈጽመው ይመለሳሉ፡፡
ወደ ቤተ መቅደስ ለምን አይገባም?
በወር አበባ ጊዜ ሴት እህቶቻችን የወገብ ህመም፣ ሆድ ቁርጠት፣ የአጥንት መፈልስፈስ (ድካም) ስለሚሰማቸው በቤተ መቅደስ የሚደረገውን የጸሎት ሥርዓት ጎንበስ ቀና በማለት የሌላውን ጸሎተኛ ልቡና እንዳያውኩና ራሳቸውም ምቾት እንዳያጡ በማሰብ እንዳይገቡ ተከልክለዋል፡፡
የወር አበባ ርኩሰትና መርገም ባይሆንም እዳሪ (ቆሻሻ) በመሆኑ ከወር አበባ ሳይነጹ ወደ ቤተ መቅደስ መግባት ነውርና ጸያፍ ነገር ይዞ እንደመግባት ይቆጠራል፡፡
ይህ ሥርዓት በሴቶች ላይ ብቻ ሳይሆን ወንዶችም ህልመ ለሊት በሚያጋጥማቸው ሰዓት እንዳይገቡ ይከለከላል፡፡
ቤተ ክርስቲያን የገነት ምሳሌ ናት፡፡ ሔዋን ከአዳም ጋር በገነት ለሰባት ዓመታት ስትኖር የወር አበባ አታይም ነበር፡፡
ቤተ መቅደስ የገነት ምሳሌ መሆኗ የተሟላ እንዲሆን የወር አበባ የምታይ ሴት ወደ ቤተ መቅደስ አትገባም፡፡
ከሞላ ጎደል የወር አበባ በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ምን እንደሚመስል ያሳያል ብዬ አምናለሁ፡፡ መልካም ሳምንት፤ መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን፡፡

Published in ህብረተሰብ

   ቴሌ የኩኩ ሰብስቤን “ቻልኩበት ዘንድሮ ቻልኩበት የኑሮ አያያዙን እኔም አወቅሁበት” ጋብዞናል!
ሰሞኑን ከቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሙት ዓመት ጋር ተያይዞ ምስላቸው በተደጋጋሚ በኢቴቪ እየቀረበ ነው (ለምን ቀረበ አልወጣኝም!) አንድ የአራት ዓመት ህፃን ይሄን ዓይቶ በንፁህ የጨቅላ አንደበቱ ምን እንዳለ ታውቃላችሁ? “መለስ አሁንም አልተሻለውም? እንደሞተ ነው?” አንጀት የሚያንሰፈስፍ ንግግር ነው፡፡ (ህፃኑ የገባውን ያህል መጠየቁ እኮ ነው!) አሁን “ነፍስ ይማር” ብለን ወደ ዛሬው አጀንዳችን እንግባ፡፡ (እሳቸው የሚሰሩትን ሰርተው አልፈዋልና ኢህአዴግም ወደ ስራው ቢገባ ሸጋ ነው!)
አንዳንድ የኢህአዴግ በጐ ነገር ፈጽሞ የማይታያቸው (ፓርቲው ጨለምተኞች ይላቸዋል!) ሰዎች ምን ይላሉ መሰላችሁ? “ኢህአዴግ ከሁለት አስርት ዓመታት የስልጣን ዘመን በኋላም ምንም ለውጥ አላመጣም፤ አልተሻሻለም” (የእኔ ሃሳብ አለመሆኑ ይታወቅልኝ!) ከምሬ እኮ ነው … እኔ በዚህ ሃሳብ ፈጽሞ አልስማማም፡፡ ሌላው ሁሉ ቢቀር እንኳ “ተራ ፓርቲ” ሆኖ መጥቶ “አውራ ፓርቲ” ለመሆን መብቃቱን እንክዳለን? (በእርግጥ ራሱ ነው “አውራ ፓርቲ ሆኛለሁ” ያለን!) እናላችሁ…አውራው ፓርቲያችን ለውጥ አላመጣም የሚለው አሉታዊ አስተያየት “የምቀኞች ወሬ ነው” ባይ ነኝ፡፡ (“አውራ ፓርቲ ሳይሆን አውራ ዶሮ ነው” ያሉት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ማን ነበሩ?) እንደሚመስለኝ “ጉልቤ ነው” ሊሉ ፈልገው ነው፡፡
እንዴ ምን ነካቸው? የአገሪቱ ገዢው ፓርቲ መሆኑን እረሱት ልበል! መንግስት እኮ ሁሌም “ጉልቤ ነው” (የአፍሪካን መንግስት ማለቴ ነው!) እስቲ በጦቢያ ታሪክ መንግስት ሆኖ “ጉልቤ” ያልነበረ አንድ ገዢ እንኳን ጥቀሱልኝ፡፡ (ኢህአዴግ ዕድሉ ሆኖ ነገር ይከርበታል!)
ሰሞኑን በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ከአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ጋር ስናወጋ የኢህአዴግን “ጉልቤነት” ደጋግሞ ነገረኝ-በቁጣ እየተግተረተረ፡፡ (የተቃዋሚዎች “ፖለቲካዊ ውሳኔ” ይሆን እንዴ?)
“እስቲ ስሜትህን ትተህ ሃሳብህን ንገረኝ” አልኩት - ጭፍን ጥላቻ እያንፀባረቀ እንዳይሆን በሚል ስጋት (ከስጋት ነፃ የሆነ ዓለም ናፈቀኝ!)
“ጉልቤ እኮ ሌላ አይደለም፤ ከህግ በላይ ልሁን የሚል ነው” ብሎ አፈጠጠብኝ (ራሱ “ጉልቤ” የሆነ መሰለኝ!)
“መረጃና ማስረጃ ልትጠቅስልኝ ትችላለህ?” ስል ጠየቅሁት ስፈራ ስቸር (“ህጋዊነትና ህገወጥነትን ያጣቅሳሉ” የተባሉት ተቃዋሚዎች መስለውኝ!)
“ሺ ማስረጃዎች እጠቅስልሃለሁ … ሩቅ ሳንሄድ በእሁዱ ሰላማዊ ሰልፍ እንኳን ህገመንግስቱን ጥሷል…ለምን ያላወቃችሁ ትመስላላችሁ…ለነገሩ ብትፈሩ አይፈረድባችሁም…በአንድ የስልክ ጥሪ ከህትመት ውጭ ያደርጋችኋል!” (ኢህአዴግን ትቶ ወደ ግሉ ፕሬስ!)
“ነገሩን ብታብራራው አይሻልም?” ኮስተር ብዬ ጠየቅሁት፤ የተቃዋሚ ፓርቲውን መሪ፡፡
“በራሳችሁ ጋዜጣ የወጣውን ጉዳይ እኮ ነው የምነግርህ!… ‘ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማሳወቅ ብቻ አይበቃም፤ ማስፈቀድ ያስፈልጋል’ በማለት የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ ህገወጥ መሆኑን የተናገሩት በናንተ ጋዜጣ አይደለም እንዴ? እስቲ አሳየኝ የትኛው ህግ ላይ ነው እንዲህ የሚለው?” በቁጣ ድምፀት ጠየቀኝ (ተወንጃዩ እኔ ነኝ ኢህአዴግ?)
“ስማ …ራሱ ያረቀቀውን ህግ የሚጥስ ጉልበተኛ ያልተባለ…ማን ሊባል ነው? ልንገርህ አይደል…ኢህአዴግ የለየለት ጉልበተኛ ነው!” በንዴት እየተንተከተከ ነው የሚናገረው፡፡
ባለፈው ቅዳሜ ማታ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ ተከብቦ አመራሮቹ ታስረው ተደበደቡ የሚለው “ዜና” ትዝ አለኝና ሰቀጠጠኝ፡፡ መቼም ለዜጐች መብትና ነፃነት የታገለ ፓርቲ፤ ይሄንን ፈፀመ ሲባል ማመን ያዳግታል (ያልታወቁ ኃይሎች ቢሆኑስ? አልኩ-ለራሴ) ከክስተቱ በኋላ ተቃዋሚዎች ያወጡት መግለጫ ግን አስደስቶኛል፡፡ ጥሰቱን ማንም ይፈጽመው ለህገመንግስቱ መከበር በጋራ ማበራቸው ይበል ያሰኛል፡፡ (ኢህአዴግም እኮ ሳንሰማው አውግዞት ሊሆን ይችላል!) (ፓርቲ ቢኖረኝ ብዬ ተመኘሁ!) በእርግጥ መኢአድ እግረመንገዱን “ሰማያዊ ፓርቲ ከተቃዋሚዎች ጋር አልሰራም” ማለቱን በቅሬታ ጠቅሷል፡፡ (ያዝኩህ” እንደማለት እኮ ነው!) ግን እኮ ሰማያዊ ፓርቲም ወዶ አይደለም፡፡ አደረጃጀቱ ከሌሎች ተቃዋሚዎች ስለሚለይ ብቻ ነው (ቀለማዊ ፓርቲ እኮ ነው!) አንዳንዶች ግን “ፓርቲው ምድራዊ አይደለም፤ ሰማያዊ ነው” ሲሉ ሰምቻለሁ (“ዕጣ ክፍሉ ከሰማያዊው ዓለም ነው” ለማለት ነው!) በዚህ እንኳን አልስማማም (“የመላዕክት ስብስብ” ፓርቲ አይሆንማ!)
“እስቲ አሁን ደሞ ስለ አዲስ ዓመት ህልሞችና ተስፋዎች እንጨዋወት …እርግጠኛ ነኝ…2006 የተሻለ ዓመት ይሆናል! በጐ በጐውን መመኘት መቼም ጥሩ ነው…አይደል?” አልኩት ለተናደደው የተቃዋሚ መሪ፡፡
ሰውየው በአንድ ጊዜ ሁለመናው ተቀያየረ - አራስ ነብር መሰለ፡፡ ዓይኑ ተጐልጉሎ ሊወጣ ምንም አልቀረው፡፡
“በጐ መመኘት ነው ያልከው? ‘ያልተነካ ግልግል ያውቃል’ አሉ” ከተቀመጠበት ተስፈንጥሮ ተነሳ፡፡ በዚህች ቅጽበት አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ የአዲሱ ሚሊኒየም መጥቢያ ላይ ይመስለኛል፡፡ በአዲሱ ሚሊኒየም የኢህአዴግ ምኞት ምን እንደሆነ የተጠየቁ አንድ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር “ፓርቲያችን በምኞት አያምንም፤ በትግል እንጂ!” ብለው ነበር፡፡ ይሄም የተቃዋሚ መሪ ተመሳሳይ ነገር እንዳይል ሰጋሁኝ፡፡ (ዕድሜ ልክ መታገል እኮ “ፍርጃ” ነው!)
የጠረጠርኩትም አልቀረ፡፡ በሚያስፈራ ዓይኑ ቁልቁል እያጉረጠረጠብኝ “ትሰማኛለህ… ጉልበተኛ ፓርቲ በምኞት ተሸንፎ አያውቅም፤ ነፃነትና ዲሞክራሲ ቁጭ ብሎ በማለም አይመጣም…በትግልና በመስዋዕትነት ብቻ ነው!” አለና በንቀት ገርምሞኝ ፊቱን አዞረ - መንገድ ሊጀምር፡፡
“ምን ዓይነት ትግል? ማለቴ…” ሳያመልጠኝ ጠየቅሁት (ከአፌ ያመለጠችኝ ጥያቄ ናት!) የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ ቀጥ ብሎ ቆመና ወደ እኔ ዞር ብሎ በነገረኛ ዓይኖቹ ትክ ብሎ እያየኝ “ጐሽ! አንቺም የሆዳሞቹን ሊግ ተቀላቀልሽ ማለት ነው” አለኝ - የለበጣ ፈገግታ እያሳየኝ፡፡ (“የሆዳሞች ሊግ” ተቋቁሟል እንዴ?)
“ለማንኛውም የትግሉ ዓይነት ሰላማዊ ነው፤ መስዋዕትነቱም እንደዚያው! ኢህአዴግን የምንታገለው ራሱ በሰጠን መሳሪያ ነው፡፡ በህገመንግስቱ እንታገለዋለን! ይሄንንም በደንብ ንገራቸው እሺ… ሆዳም ትውልድ!” ብሎኝ በፍጥነት እየተራመደ ሄደ፡፡ (“ሰላማዊ ትግል በአዲስ መልክ ጀምረናል” ያለኝ መሰለኝ!)፡፡ በጣም ገረመኝ፡፡ ሰውየው ለምን እኔን በኢህአዴግነት እንደጠረጠረኝ ፈጽሞ አልገባኝም፡፡ (እሱም እኮ ከሚከሰው ኢህአዴግ የባሰ “ጉልቤ” ሆነብኝ) ከተቀመጥኩበት ከመነሳቴ በፊት አንድ ነገር ተመኘሁ - ጦቢያ የ“ጉልበተኞች” ሳይሆን የነፃነት ወዳዶችና የዲሞክራቶች አገር እንድትሆንልኝ! (እኔ በምኞት አምናለኋ!)
እኔ የምላችሁ … አዲሱ ዓመት ከተፍ አለ አይደል! ለመሆኑ የአዲሱ ዓመት ምኞታችሁ ምንድነው? (እንደ ኢህአዴግ በትግል የምታምኑትን አይመለከትም!) እኔ ምን ተመኘሁ መሰላችሁ? የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽንን በ “ልማት አደናቃፊነት” ለማስፈረጅ! (በፓርላማም ባይሆን በማህበር!) እስቲ አስቡት … ዓመቱን ሙሉ የአገሪቱን ልማት ሲያደናቅፍ እኮ ነው የከረመው፡፡ አንዳንዴ በመንግስት ተቋቁሞ ፀረ-መንግስት አጀንዳ የሚያራምድ ተቋም ይመስለኛል (ኧረ ጀርባው ይጠና!) እንዴ የስንቱን ድርጅት ሥራ እንዳስተጓጐለ … ያው የምታውቁት ነው፡፡ ስንቱን የውጭ ኢንቬስተር ሃሳብ እንዳሰረዘም አስቡት፡፡ (ወደ ኩራዝ ዘመን የምትጓዝ አገር ላይ ማን ኢንቨስት ያደርጋል!)
በነገራችሁ ላይ ኢትዮ ቴሌኮምን በ “ፍቅር አደናቃፊነት” ለማስፈረጅ የተዘጋጁ ዜጐች መኖራቸውንም ሰምቻለሁ፡፡ በኔትዎርክ መጥፋት የፍቅረኞች ህይወት ተቃውሷላ! (ፍቅርና ትዳር የማፍረስ ድብቅ አጀንዳ ያራምዳል እንዴ?) ስንት ቢዝነሶች በኔትዎርክ ችግር እንደሚዘገዩም እያየነው ነው፡፡ በቅርቡ ደግሞ የሃይማኖት መዝሙሮችን ለሞባይል ጥሪ አገልግሎት መስጠቱን አቁሞ የኩኩ ሰብስቤን “ቻልኩበት ዘንድሮ ቻልኩበት የኑሮ አያያዙን እኔም አወቅሁበት” የሚል ዘፈን ተክቷል መባሉን ሰማሁ (“ፖለቲካዊ ውሳኔ” ይሆን?) አንዳንዶች ግን የቴሌኮም የአዲስ ዓመት ገፀበረከት ነው ሲሉ ፎትተዋል፡፡
እኔ ግን ሌላ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ በኑሮ ውድነት የተማረረውን ዜጋ ለማፅናናት ወይም ምሬቱን ለማባባስ ታልሞ የተደረገ ይመስለኛል (ግምት እኮ ነው!) መጪው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ከተጠረጠሩ እንስቶች አንዷ የሆኑ ሴት ስለቴሌኮም ያሉትን ልንገራችሁ፡፡ “በሞባይሌ ሁሉ ስደውል ሴትየዋ … የደወለሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም ትለኛለች፡፡ አንድ ቀን ግን “ኧረ ደንበኛ አይደለም … ወንድሜ ነው” … አልኳት” አሉ፡፡(እሷጋ ሁሉም ደንበኛ ነው!)
በነገራችሁ ላይ በልማት አደናቃፊነት መፈረጅ ያለበት መብራት ሃይል ብቻ አይመስለኝም፡፡ ሌሎች የመንግስት ተቋማትም አሉ፡፡
ለምሳሌ ታክሲዎችን ወደ ቀጣና (ታፔላ) አሰራር የመለሰው መ/ቤት ተጠቃሽ ነው። (የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮን ማለቴ ነው!) እንዴ … ከዚያ በኋላ እኮ ነው ነዋሪዎች በደርግ ዘመን የቀረውን የትራንስፖርት ሰልፍ የጀመሩት! (እንደውም “ልማት አደናቃፊ” ብቻ አይበቃውም!) በአዲሱ ዓመት ከጨለማና ከታክሲ ወረፋ እንዲገላግለን ተመኘሁ! (ዕዳውን ለኢህአዴግ ጥያለሁ!)

አዲስ አድማስ ባለፈው ሳምንት እትም ሁለት ሰላማዊ ሰልፎች በአንድ ቀን መጠራታቸውን አስመልክቶ ባቀረበው ዘገባ፣ የጠቀሳቸው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር “የሚጠበቅብን ማሳወቅ ነው፤ ይህንኑ በወቅቱ ፈጽመናል” ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል ደግሞ “ማሳወቅ ብቻ አይበቃም፣ ማስፈቀድ ያስፈልጋል” ማለታቸውን አስነብቦናል፡፡ ሁለቱም በአንድ ሀገር የሚኖሩ፣ በአንድ ህግ የሚተዳደሩ ናቸውና ለተናገሩት ዋቢ የሚያደርጉት የትኛውን አዋጅና የትኛውን አንቀጽ እንደሆነ መጠየቅ ቢቻል አንባቢያን በቂ ግንዛቤ በጨበጡ ነበር፡፡
አቶ ሽመልስ ዳኛም አቃቤ ህግም ሆነው የሰሩ እንደመሆናቸው ስለ ሕገ መንግሥቱም ሆነ ስለሌሎች አዋጆች ከሌላው ሰው በተሻለ ግንዛቤ ይኖራቸዋልና ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ ሕዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ ፈቃድ መጠየቅን የግድ የሚያደርጉትን ህጎች ቢገልጿቸው ሁሉም በቂ ግንዛቤ ይዞ በህጉ አግባብ በመሄድ አላስፈላጊ ንትርክ ውስጥ ባልተገባ፣ ፖሊስም መሀል ቤት ከመቸገር በዳነ ነበር፡፡
እስካሁን የምንሰማውም የምናውቀውም መሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን አስመልክቶ የሚጠቀሱት የህገ መንግሥቱ አንቀጽ 30/1 እና የሰላማዊ ሰልፍና የፖለቲካ ስብሰባ ሥነ ስርዓት አዋጅ ቁ.31/1983 ናቸው፡፡
“የመሰብሰብ፤ ሠላማዊ ሰልፍ የማድረግና አቤቱታ የማቅረብ መብት” በሚል ርዕስ በሁለት ንዑሳን አንቀጾች የተገለጸው የህገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 ንዑስ አንቀጽ 1 “ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሳሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሠላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡ ከቤት ውጪ የሚደረጉ ስብሠባዎችና ሰላማዊ ሠልፎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች በሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ለማድረግ ወይም በመካሄድ ላይ ያለ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሠልፍ ሰላምን፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥሱ ለማስጠበቅ አግባብ ያላቸው ሥርዓቶች ሊደነገጉ ይችላሉ” ይላል፡፡
በዚህ ንዑስ አንቀፅ ድንጋጌ ውስጥ ፍቃድ የመጠየቅ ግዴታም ሆነ የመከልከል መብት የለም። ሕግ ይወጣል የሚለውም ከቤት ውጪ ለሚካሄዱ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሰልፎች ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው በቤት ውስጥ የሚደረጉ ስብሰባዎች፣ ማንም ጣልቃ ሳይገባባቸው በአድራጊው አቅምና ፍላጎት ብቻ የሚከናወኑ መሆኑን ነው፡፡
ከቤት ውጪ የሚደረግን ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍን በሚመለከትም “አግባብ ያላቸው ሥርዓቶች ሊደነገጉ ይችላሉ” ተብሎ በሕገ መንግሥቱ ቢገለጽም የወጣ አዋጅ፣ ደንብም ይሁን መመሪያ የለም፡፡ ወይንም አላየሁም፡፡ በዚህ ንኡስ አንቀጽ የተገለጸውን የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ ለማስፈጸም ሥራ ላይ የዋለው ከህገ መንግሥቱ ቀድሞ በ1983 ዓ.ም የወጣው “የሰላማዊ ሠልፍና የፖለቲካ ስብሰባ ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 31/1983” ነው፡፡ ይህ አዋጅ በአንቀጽ 6/2 ስብሰባ ወይንም ሠላማዊ ሰልፍ የሚያደርገው አካል ከ48 ሰዓት በፊት አስቀድሞ ለአካባቢው የመስተዳድር አካል እንዲያሳውቅ ግዴታ ይጥላል፡፡ ማወቅ አለበት ለተባለው የአካባቢ መስተዳድር ደግሞ የጸጥታ ጥበቃ የመመደብን ኃላፊነት ይሰጣል፡፡ ስብሰባው አዘጋጆቹ ባሰቡት ቀን እንዲካሄድ የማያስችል በቂ ምክንያት ሲኖር ደግሞ ይህንኑ ገልጾ ለሌላ ቀን እንዲያስተላልፉ ሀሳብ ይሰጣል፡፡ ህጉ ከዚህ ውጪ በሰልፍ አዘጋጆች ላይ የሚጥለው ግዴታ ለመስተዳድሩም የሚፈቅደው መብት የለም፡፡
አቶ ሽመልስ ከማል በጣም ርግጠኛ ሆነው (ከጋዜጣው እንዳነበብነው) “ማስፈቀድ ያስፈልጋል” ሲሉ፣ እርሳቸው የሚያውቁት ከላይ ከተጠቀሱት ሌላ ስለ ሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ የተደነገገበት አዋጅ ደንብ ወይንም መመሪያ ይኖር ይሆን? ኖረም አልኖረ ሙግት ሳይነሳ ተቀባይነት የለውም። ለምን ቢባል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9/1 “ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይንም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም” ተብሎ ተደንግጓልና፡፡
አቶ ሽመልስ “ፈቃድ ያስፈልጋል” ለማለት ያበቃቸውን የህግ አንቀፅ እስካልነገሩን ድረስ ንግግራቸው ሕገ መንግሥቱን በግልጽ የጣሰ ነው። የመንግስት ቃል አቀባይ እንደመሆናቸውም ህገ መንግስት የመጣስ ክሱ መንግሥትንም ይመለከታል።
አቶ ይልቃል የተናገሩት ተብሎ እንደተጻፈው፤ የአዲስ አበባ መስተዳድር ኃላፊነቱን አልተወጣ ከሆነ እንዲሁም የአቶ ሽመልስ “ፈቃድ ያስፈልጋል” የሚል ንግግር፣ መሀል ቤት ለችግር የሚዳርገው ፖሊስን ነው፡፡ ፖሊስ በመንግስት መገናኛ ብዙሀን “የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ እውቅና ያላገኘ ነው” ለማለት የበቃውም በዚሁ ምክንያት ይመስለኛል፡፡ ግን ፖሊስ ለምን?
ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ በዚሁ ክፍል ኃላፊነት የምናውቃቸው (በፊት ፈቃድ በኋላ ማሳወቂያ የተባለው ክፍል) አቶ ማርቆስ፤ ለአዲስ አድማስ በግልጽ አይናገሩት እንጂ ሰላማዊ ሰልፍ ከጠሩት ሁለት ክፍሎች ደብዳቤ እንደቀረበላቸው በገደምዳሜም ቢሆን ተናግረዋል፡፡ ታዲያ ዘግይቶ ደብዳቤ ላመጣው አካል “እናንተ በጠየቃችሁን ቦታና ቀን፣ ከእናንተ ቀድሞ ሰልፍ ማዘጋጀቱን የገለጸልን አለ” በማለት ወዲያውኑ መልስ በመስጠት ጉዳዩን በአጭሩ መቅጨት ለምን ሳይቻል ቀረ? ዘግይቶ የመጣው ከቀደመው በተለየ ሁኔታ ጥያቄው መስተናገድ ያለበት ከሆነም፣ ይህንኑ ገልጾ ቀድሞ ያሳወቀው ለሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፍ በመንገር፣ የተፈጠረውን አላስፈላጊ ነገር ሁሉ ማስቀረትስ አይቻልም ነበር? ይህ ሁሉ ካልሆነም አንደኛው ፍቃድ ማግኘቱን ሌላኛው መከልከሉን ወይንም ፈቃድ ያልተሰጠው መሆኑን (ፈቃድ የምለው እነርሱ ስላሉ እንጂ ሕገ ወጥ ነው) መግለጽና ያልተፈቀደለት ያሉት ፓርቲ ሰልፉን ቢቀጥል ሕገ ወጥ መሆኑን ማሳወቅ የዚሁ ክፍል ኃላፊነት መሆንስ አልነበረበትም? ፖሊስን አጣብቂኝ ውስጥ መክተትና በዜጎች የመብት ጥያቄ ላይ አሉታዊ አመለካከት ያለው መስሎ እንዲገመት ወይም እንዲታይ ማድረግስ ተገቢ ነው? “ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ እንደሚያደርግ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ያልተገለጸልኝ በመሆኑ” እውቅና ያልተሰጠው በመሆኑ” የሚለው የፖሊስ ገለጻ፣ ጥንቃቄ የተሞላበት ነው፡፡ ይህም ጥንቃቄ ከላይ የገለጽኩት ስሜት በህብረተሰቡ ውስጥ እንዳያድር ለማድረግ ከማሰብ የተፈጸመ ነው ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ ለቃላት ሲጠነቀቅ የነበረው ፖሊስ፤ “የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችንና አባሎችን ከቢሮአቸው አፍሶ ወሰደ፤ ብዙዎቹንም ደበደበ” የተባለው በርግጥ ተፈጽሞ ከሆነ፣ የባለሥልጣናት ትዕዛዝ ከህገ መንግሥት በላይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡
የዛሬ 10 ዓመት የተፈጸመን ድርጊት ዛሬ ከሆነው ጋር በንጽጽር ማየት ምን አልባት ያስተምር ከሆነ በአጭሩ ላስታውስ፡፡ ኢዴፓ በመስቀል አደባባይ ያቀደው ሰላማዊ ሰልፍ በተለያየ ምክንያት ሲተላለፍ ቆይቶ፣ ለየካቲት 2/95 ዓ.ም ይወሰንና አቶ ማርቆስ ለሚመሩት ክፍል የማሳወቂያ ደብዳቤ ይጻፋል። በክፍሉ በኩል የታዩ ተደጋጋሚ ችግሮችን ግምት ውስጥ በማስገባትም ለፖሊስ በግልባጭ እንዲደርሰው ይደረጋል፡፡ አቶ ማርቆስ የሚመሩት ክፍልም “በአደባባይ ሳይሆን በአዳራሽ ብታደርጉት” የሚል ደብዳቤ ይጽፋል፡፡ በተባለው ቀን አደባባዩ ነፃ መሆኑ እየታወቀ፣ በአዳራሽ አድርጉ ማለቱ ህጋዊም አሳማኝም አልሆነምና ኢዴፓ የአደባባይ ዝግጅቱን ይቀጥላል፣ በዚህ መሀል ፖሊስ ግራ በመጋባቱ፣ ጥር 25/1995 ዓ.ም በወቅቱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ከነበሩት ሻለቃ በፍቃዱ ቶሌራ ቢሮ “ልናነጋግራችሁ ስለምንፈልግ ሶስት ሰዎች ከሰአት ብትመጡ” የሚል የስልክ መልእክት ደረሰን፡፡ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ፣ አቶ ክፍሌ ጥግነህና እኔ ሆነን ስንሄድ፣ ሻለቃ በፍቃዱ አሁን ስማቸውንና ማዕረጋቸውን ማስታወስ የቸገረኝ የወንጀል መከላከል ሀላፊ ከነበሩት ጋር ሆነው ጠበቁን፡፡ አቶ ማርቆስ ብቻቸውን መጡ፡፡ ሻለቃ በፍቃዱ “የአዲስ አበባ መስተዳድር በ23 በጻፈው ደብዳቤ በመስቀል አደባባይ ሳይሆን በአዳራሽ ማድረግ የምትችሉ መሆኑን ገልጾ ጽፏል፤ እናንተ በ25 የጻፋችሁትን ደብዳቤ ግልባጭ አድርጋችሁልናል፡፡ በዚህም ፖሊስን ግራ ስላጋባችሁት ተገናኝታችሁ ተነጋገሩ በማለት ነው አቶ ማርቆስ ባለበት የጠራናችሁ” አሉ።
አቶ ማርቆስም “ከዚህ በፊት ሰፊ ስብሰባ በአደባባይ አድርጋችኋል፣ በህዳር ወርም ተፈቅዶላችሁ የተዋችሁት እናንተ ናችሁ፣ ሕገ መንግሥታዊ መብትን ተጋፍተን አታድርጉ ማለት አይቻልም፤ ደብዳቤያችንም ይህን አይልም” አሉ። በእኛም በኩል በአዳራሽ አድርጉ ሲባል የቀረበው ምክንያት አሳማኝና ተገቢ ባለመሆኑ የአደባባይ ፕሮግራማችንን ለመሰረዝ የሚያበቃን ስላልሆነ ዝግጅታችን መቀጠሉን አስረዳን፡፡ የወንጀል መከላከል ኃላፊውም “ኢዴፓ ሕግ አክብሮ የሚሰራ ነው፤ ይህንንም መስቀል አደባባይ በተደጋጋሚ ባደረጋቸው ህዝባዊ ስብሰባዎች ከፖሊስ ጋር ተባብሮ በመስራት አሳይቷል፣ አሁን ችግሩ ያለው በእነ አቶ ማርቆስ በኩል ነው” አሉ፡፡ አቶ ማርቆስም ጉዳዩ በርሳቸው ክፍል የማያልቅ የበላይ አካልን ውሳኔ የሚጠይቅ እንደሆነና ለሚመለከተው አካል ቀርቦ ውሳኔ አለማግኘቱን ገለጹ፡፡ ከሶስታችንም በኩል ሀሳቦች እየተሰነዘሩ ከተነጋገርን በኋላ፣ ሻለቃ በፍቃዱ “ጥያቄዬን አንስቻለሁ፤ መስተዳድሩ በአደባባይ መሆን ይችላል ካለ ጥበቃ ለማሰማራት፣ የለም በአዳራሽ ያልኩትን አላነሳሁም ካለ ለጥበቃ ላለመዘጋጀት ነው፣ የእኔ የቤት ሥራ ይህ ነው” ብለው በዚሁ ተለያየን፡፡
ከላይ በተገለጸው ድርጊት ፖሊስ “ተፈቅዷል አልተፈቀደም” የሚል ሕግ መንግሥቱን የሚጋፋ ተግባር ውስጥ አልገባም፡፡ “ሕጋዊ ነው፤ ሕገ ወጥ ነው” የሚል ዳኝነትም አልሰጠም፡፡ አቶ ማርቆስም “ሕገ መንግሥታዊ መብትን ተጋፍተን አታድርጉ ማለት አንችልም” ነው ያሉት፡፡ ዛሬ ከ10 ዓመት በኋላ ከፖሊሲም ሆነ ከአቶ ማርቆስ አሊያም ከአቶ ሽመልስ የሰማነው እድገትና መሻሻል ነው ወይስ የኋሊት ጉዞ?
ለዚህ አስተያየት መጻፍ ምክንያቴ የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ መካሄድ አለመካሄዱ አይደለም፡፡ የህገ መንግስቱ ድንጋጌ መከበር አለመከበሩ ነው፡፡ አቶ ማርቆስ የዛሬ 10 አመት ያሉትን ዛሬም ማጽናት መቻል ነበረባቸው፡፡ የያኔው ፖሊስ አዛዥ የተናገሩትን የዛሬውም ሊደግሙት በተገባ ነበር፡፡ የህገ መንግስቱ ድንጋጌ አልተለወጠም አልተሻሻለምና፡፡ ከዛ ወዲህ ሰልፍና ስብሰባን የሚመለከት አዋጅ ስለመውጣቱ አይታወቅም፡፡
አቶ ሽመልስ እንደ ህግ ባለሙያነታቸውና እንደ መንግሥት ቃል አቀባይነታቸው “ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ፈቃድ መጠየቅ ግዴታ ነው” ሲሉ ይህ ሊሆን የሚችለው በርሳቸው አስተሳሰብ ወይንም ፍላጎት ሳይሆን በህግ ድንጋጌ ነውና ፈቃድ መጠየቅን ግዴታ የሚያደርገውን የህግ አንቀጽ ጠቅሰው ማስረዳት ነበረባቸው፡፡ አንድም የህግ አንቀጽ ሳይጠቅሱ፣ በህገ መንግስት ለተረጋገጠ መብት የባለሥልጣናት ፈቃድ ያስፈልጋል ብለው በጋዜጣ መናገራቸው፣ በሕገ መንግሥቱ ገዢነትና ተግባራዊነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን የሚያጠናክር ይሆናል፡፡
አቶ ሽመልስ የመንግሥት ቃል አቀባይ ናቸውና የሚናገሩት ሁሉ የመንግሥት አቋም፣ እምነትና ውሳኔ ተደርጎ ስለሚወሰድ ሲናገሩ ማስረጃ እያጣቀሱ፣ ማስረጃ ከሌለ ደግሞ ባይናገሩ ሳይበጅ አይቀርም፡፡
ሕገ መንግሥት የሚምሉ የሚገዘቱበትና ሌላውን የሚያስፈራሩበት ሳይሆን በአንቀጽ 9/2 እንደተገለጸው የሚገዙበት መሆኑ በተግባር መታየት አለበት፡፡ የሀገሪቱ የበላይ ህግ የሆነው ህገ መንግስት ካልተከበረ ወይንም ለድንጋጌዎቹ ከራስ ፍላጎትና ስሜት አንጻር የተለያየ ትርጉም እየተሰጠ የሚሸራረፍ ከሆነ የህግ የበላይነት አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ዜጎችም በህግ የማመናቸውና ለህግ የመታመናቸው ስሜት ይዳከማል፡፡ ይህ ደግሞ አጠቃላይ የሆነ ሀገራዊ ችግር ያስከትላል፡፡ ለዚህም ነው ባለፈው ሳምንት የሆነውን ነገር የሰማያዊ ፓርቲ፣ አቶ ማርቆስ የሚመሩት ክፍል እንዲሁም የአቶ ሽመልስና የፖሊስ ጉዳይ ብቻ አድርገን ልናየው የማይገባን፡፡ ይህን እንድናደርግ ደግሞ የህግ መንግሥቱ አንቀጽ 9.2 “ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማህበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለህገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው” በማለት ግዴታ ጥሎብናል፡፡

በ3 አመት ውስጥ 20ሺህ ቤቶች ለተጠቃሚ ይተላለፋሉ
በቀጣይ አመት የመጀመሪያዎቹ እድለኞች የቤት ባለቤት ይሆናሉ
በ5 አመት ውስጥ ሁሉም ተመዝጋቢዎች ቤት ያገኛሉ
ቀደም ብሎ በተዘጋጀው የ40/60 የቤቶች ፕሮግራም ስትራቴጂክ እቅድ መሠረት በሶስት አመት ውስጥ 20ሺ ቤቶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች እንደሚተላለፉ እንዲሁም ግንባታቸው አስቀድሞ የተጀመሩት በመጪው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ለመጀመሪያዎቹ እድለኞች ተጠናቀው እንደሚሠጡና ባለፈው ነሐሴ የተመዘገቡ 164ሺ ቤት ፈላጊዎች በአምስት አመት ውስጥ የቤት ባለቤት እንደሚሆኑ ተገለፀ፡፡
ይህንኑ ፕሮግራም ተከታትሎ እንዲያስፈፅም የተቋቋመው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ፅ/ቤት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የስራ ሂደት መሪ አቶ ዮሐንስ አባይነህ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ከ2005-2006 ዓ.ም ሊገነቡ ለታሠቡት የ40/60 መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በአጠቃላይ 1.25 ሚሊዬን ብር በጀት የተያዘ ሲሆን በአሁን ወቅት 10ሺ 820 ለሚሆኑ ቤቶች ግንባታ ወደ 50 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቷል፡፡
እነዚህ በአጠቃላይ በሶስት አመት ውስጥ ይጠናቀቃሉ የተባሉ ቤቶችም በሠንጋ ተራ ክራውን ሣይት፣ እህል ንግድ፣ ቦሌ፣ መሪ፣ አስኮ እንዲሁም ቦሌ ቡልቡላ አካባቢዎች ለመልሶ ማልማት በተመረጡ ቦታዎች ላይ ይገነባሉ የሚሉት ሃላፊው፤ ቀደም ብሎ በሠንጋ ተራ፣ ክራውን ሣይት እንዲሁም ቦሌ ቡልቡላ አካባቢዎች የቤቶቹ ግንባታ ተጀምሯል ብለዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ አክለውም፤ በሠንጋ ተራ አካባቢ ግንባታው 20 በመቶ የደረሠ መሆኑን በማመልከት፣ የሚገነቡት ቤቶች በአምስት ብሎኮች የተከፋፈሉ ሆነው ብዛታቸው 410 መሆኑን፤ በክራውን ሣይት ደግሞ በ14 ብሎኮች ተከፋፍለው 882 ቤቶች የሚገነቡ ሲሆን ግንባታው 10 በመቶ ደርሷል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በእነዚህ አካባቢዎች የሚገነቡት ቤቶች በግንቦት ወር 2006 ግንባታቸው 95 በመቶ ይደርሣል ተብሎ የሚገመት ሲሆን ቀሪውን የማጠናቀቂያ ስራ የቤቱ ባለቤቶች የሚፈፅሙት ይሆናል ብለዋል፤ ሃላፊው፡፡
በመስከረም አጋማሽ ግንባታቸው በሚጀመረው በኢምፔሪያል አካባቢ ወደ 650 ቤቶች፣ በእህል ንግድ አካባቢ 1476 ቤቶች፣ በመሪ አካባቢ 1148 ቤቶች፣ በአስኮ አካባቢ 1148 ቤቶች እንዲሁም በቦሌ ቡልቡላ 550 ቤቶች እንደሚገነቡ የተናገሩት አቶ ዮሐንስ፤ እቅዱ ምናልባት አዲስ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቀውን የከተማዋን ስትራቴጂክ እቅድ ታሣቢ ባደረገ መልኩ ሊቀየር እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
ግንባታቸው የተጀመሩት ቤቶች ሙሉ በሙሉ በሃገር ውስጥ ደረጃ 1 የህንፃ ተቋራጮች የሚገነቡ ሲሆን በአሁን ሠአት ከ1226 በላይ ለሚሆኑ ሠዎች የስራ እድል መፈጠሩን በቀጣይ ደግሞ ቁጥሩ ወደ 10ሺህ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የሥራ ሂደት መሪው ገልፀዋል፡፡
የሚገነቡት ህንፃዎች ቁመት እንደየአካባቢው የሚለያይ ሲሆን አሁን በተጀመሩት ሣይቶች ላይ የሚገነቡት በሠንጋ ተራ ባለ 12 ፎቅ፣ በቦሌ ቡልቡላ ባለ 7 ፎቅ እንዲሁም ክራውን ሣይት ባለ 9 ፎቅ ህንፃዎች ይገነባሉ፡፡
በምዝገባው ወቅት በርካቶች በባለ ሁለት እና ሶስት መኝታ ቤት የተመዘገቡ በመሆኑም ቀደም ብሎ የነበረው የቤቶቹ የውስጥ ዲዛይን ለውጥ እንደሚደረግም አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል ሁለት የ40/60 ቤት ግንባታዎች የሚከናወኑት በአዲስ አበባ በ10 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ሲሆን የሁሉም አካባቢ ቤቶች ዋጋ ተመሣሣይ መሆኑን ሃላፊው ገልፀዋል፡፡

Page 14 of 16