Saturday, 28 September 2013 13:28

ዴንጌሣት

ዴንጌሣት - የልጅ እሳት
ዴንጌሣት - የልጅ መብራት…
የባህል ችቦ መቀነት
ከዘመን ዘመን ማብሰሪያ፣የመስቀል ብርሃን “ኬር” በሥራት፡፡
“በእሳት አትጫወት” ይላል አበሻ ልጁን ሲያሳድግ
ዴንጌሣትን ባያውቀው ነው፤ የጉራጌን ባህልና ወግ
ገና በጥንስስ በጭሱ፣ መስቀልን እንደሚታደግ
በችቦ ማህል ተወልዶ፣ ንግዱን እንደሚያንቦገቡግ
በእሳት አልፎ እሳት ሲሆን
አላየውም ጉራጌውን
ዴንጌሣት ነው የዚህ እርከን!
ጉራጌ የላቡን ሠርቶ
ዓመቱን በንግዱ ገፍቶ
በፍቅሩ ልጆቹን አይቶ
የለማው በፊናው ለፍቶ
የተገፋውም ተገፍቶ፤
ላንደኛው አዱኛ በርቶ
ያንዱ መክሊቱ ከስቶ
ያም ሆኖ በቀኑ ተግቶ
መስቀሉን በዕድሜው አብርቶ
የልጅ - እሳት፣ የዴንጋ - እሳት፤ ለምለም ጨረር ይዞ መጥቶ
ይሄው በመስቀል ወር ጥቢ፣ ኬር! ይላል የዓመቱን ንጋት
ኬር! ይላል የዓመቱን ብሥራት
ፍሬው በስሎ፣ ቅርሱ ሲያብብ፤ ማየት ነው ያገሬው ኩራት
ዴንጌሣት የልጆች ምትሃት
ጐርፍ ላይ የሚሄድ እሳት
ዓመቱን እንደብጤቱ፣ ሰው መቼም አቅሙን ለክቶ
እንደየርምጃው ነውና፣ የሚሄድ ብርሃን አይቶ
እንደዘመን እንደ ዓመሉ…ነግዶም አርሶም አምርቶ
ወይ ጀግኖ አሊያም ፈርቶ
ወይ ሸሽቶ ወይ ዝቶ ኮርቶ
ወይ ተኮራርፎ ወይ ታርቆ
ወይ ከስሮ ወይ አንሰራርቶ
አትርፎ ወይ “ፓሪ” ወጥቶ
በጋን እንደበጋ ፀሐይ፣ ክረምትን እንደዶፍ ዝናብ
ሁሉን ችሎ ሁሉን አዝሎ፣ ሁሉን የንግድ አጀብ ወጀብ
ተቀብሎ ታግሎ፣ ጥሎ፤
አቀርቅሮ ቀና ብሎ
የተስፋ ጐሁን በችቦ፣ ቀዶ በዴንጌሣት ፍካት
በዝናብ ውጋገን እሳት
የመስቀል ደመራ ዜማ
ያውዳመት ሆታ ዋዜማ
የልጆች ርችት ማማ
አገር ሲታጠር በአበባ
የኮከቦች ሳቅ ሲተባ
የማይሞት የማይነቀል
ኗሪ የጉራጌ ባህል፤
እንደህፃን ፍልቅልቅ ፊት፣ እነደመስክ ብርሃን ወለል፤
መስከረም ወር ፍንትው ሲል፣
ገጠር ከተማውን ዳብሶ፣ ዴንጌሣት ዙሪያ ይሞላል!
ዴንጌሣት የፍቅር እሳት
የልጅ መቅሰስ ያዋቂ እራት
ነግ እንዲያበራ ይህ ልማድ፣ መስቀል - ወፍ እንድትዘምረው
ምራቅ የዋጥን፣ ልማድ ያቀፍን፤
አሻግረን እንለኩሰው
ለአገር ልጅ እናስረክበው
ጐዶሏችንን እንሰብስብ፣ ሙሉማ አለ በጃችን
ዘለዓለምን ለማሸነፍ፣ ብርሃን ነው መሣሪያዎችን !
ሁሌም ዴንጌሣት ለማየት፣ አሁን ያለን እንበቃለን፡፡
ይህን የልጆች ህብር እሳት፣ እጅ በእጅ እንለኩሰው
ወትሮም በእፍኝ ጭራሮ ነው፣ አገር - ምድሩ የሚበራው
ባህል የሚኖር እንዲህ ነው፣ ትውልድ የሚጫር በዚህ ነው!
አገር ማለት ዴንጌሣት ነው!
ኬር እንሁን ኬር እናርገው!
የጉራጌ ብርሃን ህልም፣ እዚህ ጋ ነው ትርጉም ያለው፡፡
ዴንጌሣት የልጅ አገር ነው፤
አገር ማለት ዴንጌሣት ነው፡፡
መስከረም 14/2006
(ለዴንጌሣት በዓልና ባህሉን ለሚያከብሩ)

 

Published in የግጥም ጥግ
Saturday, 28 September 2013 13:25

ኢዮሃ

ኢዮሃ
አበባ ፈነዳ!
ፀሐይ ወጣ ጮራ
ዝናም ዘንቦ አባራ
ዛፍ አብቦ አፈራ፤
ክረምት መጣ ሄደ
ዘመን ተወለደ

አለም ሞቆ
ደምቆ
ብርሃን ሲያሸበርቅ
ጤዛው ሲብረቀረቅ
ህይወት ሲያንሰራራ
ፍጥረት ሲንጠራራ
ዘመን ተለወጠ መስከረም አበራ፡፡
“ኢዮሃ አበባዬ፡፡”
(1955)

Published in የግጥም ጥግ
Saturday, 28 September 2013 13:22

ለፈውስ ያልነው ለሞት!

እነፓራሲታሞል ለሞት ሊዳርጉ ይችላሉ

እንደ አለም ጤና ድርጅት ትርጓሜ፤ መድሃኒቶች በርካታ ንጥረ ነገሮችን የያዙ በሽታን ለማከም የሚረዱና ለህመምተኞች በሚስማማ መልኩ ተዘጋጅተው በፋብሪካ ደረጃ እየተመረቱ ገበያ ላይ የሚውሉና በጤና አገልግሎት ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላቸው ኬሚካሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች በተገቢው ጊዜና ሁኔታ፣ በትክክለኛው መጠንና በባለሙያ ትዕዛዝ ሲወሰዱ የታለመላቸውን ግብ በመምታት በሽታን ለመከላከል፣ለማከምና ህመምተኛውን ወደ ጤናማ ሁኔታ ለመመለስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው መድሃኒቶች በዘፈቀደና ያለባለሙያ ትዕዛዝ አሊያም ከታዘዘው መጠን በላይ ወይም በታች ሲወሰዱ ፈውስነታቸው ቀርቶ ህይወትን አደጋ ላይ የሚጥሉ መርዞች ሊሆኑብን ይችላሉ፡፡ መድሃኒቶች ነፍስን የመታደጋቸውን ያህል ህይወትን ሊቀጥፉ ይችላሉ፡፡ ለህመም ማከሚያና ማዳኛ የሚወሰዱ መድሃኒቶች ፈዋሽ ናቸው የሚባሉት የታለመላቸውን ግብ በአግባቡ መምታት ሲችሉ ነው፡፡

ይህንን ተግባር በሚያከናውኑበት ወቅት አላስፈላጊ ውጤቶችን (የጎንዮሽ ጉዳቶችን) ሲያስከትሉ ይችላሉ፡፡ መድሃኒቶች በጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚደረጉት የጎንዮሽ ጉዳታቸው ከጠቀሜታቸው አንፃር ተመዝኖ ጉዳቱ ያነሰ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ በመሰረቱ ሁሉም ዓይነት መድሃኒቶች የየራሳቸው የሆነ የጎንዮሽ ጉዳቶች (side effects) አሏቸው፡፡ ይህም መድሃኒቶቹ በሚይዟቸው ንጥረ ነገሮችና በሚሰሩባቸው ኬሚካሎች መነሻነት የሚከሰት ነው፡፡ አብዛኛዎቹ መድሃኒቶች በሃኪም ትዕዛዝ መሰረት የሚወሰዱና ከሀኪም ትዕዛዝ ውጪ ቢወሰዱ አደጋ ላይ የሚጥሉ ዓይነቶች ናቸው፡፡ ከህክምና ባለሙያ ትዕዛዝ ውጪ (prescription) ውጪ የማይሸጥና ቢሸጡ የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ የመድሃኒት ዓይነቶችም አሉ፡፡ የዚህ አይነት መድሃኒቶች የሚታዘዙትም በመደበኛ የህክምና ባለሙያ ሳይሆን የስፔሻላይዜሽን ዕውቀት ባላቸው የህክምና ባለሙያዎች ነው፡፡

እነዚህ ዓይነት መድሃኒቶች ሱሰኝነት ወይንም የመድሃኒት ጥገኝነትን የሚያበረታቱ ናቸው፡፡ እነዚህን መድሃኒቶች ያለሃኪም ትዕዛዝ ወይንም ያለመድሃኒት መሸጫ ወረቀት (prescription) ሲሸጥ የተገኘ የመድሃኒት ዕደላ ባለሙያ (pharmacist) በሙያ ሥነምግባር ጉድለት የሚጠየቅ ሲሆን ከህግ ተጠያቂነትም አያመልጥም፡፡ በአደጉት አገራት መድሃኒቶችን ያለሃኪም ማዘዣ ወረቀት መሸጥ የሚያስከትለው ቅጣት ቀላል ባለመሆኑ የመድሃኒት እደላ ባለሙያዎች (pharmacist) በእጅጉ ጥንቁቅ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ያለሃኪም ትዕዛዝ የመድሃኒት እደላ ባለሙያው ከህመምተኛው በሚያገኘው መረጃ መሰረት ሊሰጣቸው የሚችላቸው የመድሃኒት አይነቶችም አሉ፡፡ እነዚህ መድሃኒቶችም ቢሆኑ ለህመምተኛው ጊዜያዊ መፍትሄ የሚሰጡና የህመም ስሜትን ለማስታገስ የሚረዱ ከመሆን በዘለለ የሚሰጡት ጠቀሜታ እምብዛም መሆኑን ህመምተኛው በግልፅ ሊያውቅ ይገባል፡፡

የመድሃኒት እደላ ባለሙያው፤ ህመምተኛው መድሃኒቶቹን ለተወሰኑ ጥቂት ቀናት ወስዶ ለህመሙ መፍትሄ ካላገኘ ወደ ህክምና ባለሙያ ዘንድ ሄዶ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባው በግልፅ ሊነግሩ እንደሚገባ ህጉ ይደነግጋል፡፡ ለራስ ምታት፣ ለጉንፋን፣ ለሆድ ቁርጠትና መሰል ቀለል ያሉ በሽታዎች በፋርማሲ ባለሙያዎች ታዘው የሚወሰዱ መድሃኒቶች በራሳቸው እጅግ የከፋ ጉዳትና እስከሞት ሊያደርስ የሚችል የሚደርስ አደጋ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ እንደ አስፕሪን፣ፓራሲታሞል፣ፓናዶልና አድቪል ያሉ ያለ ሃኪም ትዕዛዝና ያለመድሃኒት ማዘዣ ወረቀት በቀላሉ እየተገዙ ጥቅም ላይ የሚውሉ መድሃኒቶች አለአግባብ ከተወሰዱ በጤና ላይ ከባድ ጉዳት ከማስከተላቸውም በላይ ህመምተኛውን ለሞት ሊዳርጉትም ይችላሉ፡፡ እንደ ጤና ድርጅቱ መረጃ፤ በዓለም ዙሪያ ፓራሲታሚል ያለአግባብ የሚወስዱ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች በየዓመቱ ይሞታሉ፡፡

እነዚህ ለቀላል የህመም ስሜት ማስታገሻነት ጥቅም ላይ የሚውሉ መድሃኒቶች ይህን መሰል እጅግ የከፋ አደጋ ማድረሳቸው አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡ ራስ ምታት፣የሆድ ቁርጠት፣ቀለል ያሉ ሳል፣አለርጂና መሰል የጤና ችግሮች በአብዛኛው እንደ ቀላል ችግር የሚታሰቡና እምብዛም ትኩረት የማይሰጣቸው የበሽታ ዓይነቶች ቢሆኑም የማጅራት ገትር፣የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽኖች ፣የልብ በሽታ፣የጉሮሮ ቫይረስ፣የኩላሊት፣ የጨጓራና የአንጀት በሽታዎች ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ህመምተኛው ከመድሃኒት መደብሮች በቀላሉ እየገዛ የሚጠቀማቸው መድሃኒቶች ለህመም ስሜቱ ማስታገሻና ጊዜያዊ መፍትሄ ሰጪ በመሆናቸው ከህመም ስሜቱ በመታገሱ ዋነኛውን ትልቁን ችግር ችላ ይለዋል፡፡ በዚህ ሳቢያም ችግሩ መፍትሄ ሳያገኝ ቀርቶ ስር እየሠደደ በመሄድ በቀላሉ ሊድን ለማይችል የጤና ችግር አሊያም ለሞት ሊያበቃው ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለቀላል ራስ ምታት፣ ለመጫጫንና ለተለያዩ የህመም ስሜቶች ማስታገሻ እየተባሉ በዓለማችን ዙሪያ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉት እንደ ፓራሲታሞልና ፓናዶል መሰል የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን በተደጋጋሚ የሚወስዱ ሰዎች ለመድሃኒቶቹ ጥገኛ ይሆናሉ፡፡ እነዚህን መድሃኒቶች ካልወሰዱ በስተቀር ጤናማ ስሜት አይሰማቸውም፡፡ ቀስ በቀስም የህመም ስሜታቸው በተቀሰቀሰ ቁጥር መድሃኒቶችን መውሰዳቸው በመድሃኒቶቹ ላይ እንዲጣበቁና ጥገኝነታቸውም እየጨመረ እንዲሄድ ያደርገዋል፡፡ ጥገኝነታቸው በጨመረ ቁጥርም የሚወስዱትን መድሃኒት መጠን እንዲጨምሩ ያስገድዳቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታም ህመምተኛውን ለሌላ እጅግ የከፋ ጉዳት ለሚያስከትልበት የጤና ችግር የሚያጋልጠው ይሆናል፡፡

የፋርማሲ ባለሙያው ከህመምተኛው በሚያገኘው መረጃ መሰረት የሚሰጣቸውና ለቀላል ህመም ማስታገሻ እየተባሉ የሚወሰዱት መድሃኒቶች ትላልቅ የጤና ችግሮችን በመደበቅ በወቅቱ ታይተው ምርመራና ህክም እንዳያገኙ በማድረግ ህመምተኛውን ከባድ ለሆነ የጤና ችግር ይዳርጋሉ፡፡ የመድሃኒት ዕደላ ባለሙያዎች እነዚህን መድሃኒቶች ለህመምተኛው በሚሸጡበት ወቅት ህመምተኛው በመድሃኒቶቹ ተጠቅሞ መፍትሄ ካላገኘ ወይም ህመሙ እየተባባሰ የሚከሰትበት ከሆነ ወደ ጤና ተቋም መሄድ እንዳለበት የመንገር ሙያዊ ግዴታ እንዳለባቸውና ህመምተኞችም በቀላል ገንዘብ ተገዝተው የሚወሰዱት እነዚህ መድሃኒቶች የከፋ ችግሮችን ሊያስከትሉ የሚችሉ መሆናቸውን ተገንዝበው ጥንቃቄ ሊያደርጉና ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ መረጃው አሳስቧል፡፡ ነፍሳችንን እንዲታደግ የወሰድነው መድሃኒት መጥፊያችን እንዳይሆን ትኩረትና ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል፡፡

Published in ዋናው ጤና
Saturday, 28 September 2013 13:20

ስልጣን - የነብር ጅራት!

                       በየአራት አመቱ አንዴ የሚደረገው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመጨረሻ ቀናቶች ሲቃረቡ በሪፐብሊካንና በዲሞክራቲክ ፓርቲ እጩዎች መካከል አንዱ ያንዱን ዋጋ ለማሳጣት የግል ምስጢር መውጣቱ፣ እርስ በርስ መዘላለፉ ወዘተ በእጅጉ ያይላል፡፡ ይህንን ሁኔታ ለመታዘብ የቻለ ማንም ቢሆን ስነስርአትና የሰለጠነ ግብረገብ የጐደለው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚካሄድበት እንደ አሜሪካ ያለ ሀገር ጨርሶ አይቶ አላውቅም ቢል ቂል ወይም ገሪባ ብሎ የሚያላግጥበት ብዙ ሰው አይኖር ይሆናል፡፡ ይህንን አስተሳሰቡን ለአንድ የአውስትራሊያ ዜጋ ቢያካፍለው ግን ኢትዮጵያውያን “አባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል” እንደሚሉት “የአውስትራሊያን ብሔራዊ ምርጫ ሳታይ እንዲህ የመሰለውን አቋም አትያዝ” ብሎ እንደሚመክረው ምንም አያጠራጥርም፡፡ በቅርቡ በሌበር ፓርቲው ጠቅላይ ሚኒስትር ኬቪን ሩድና በወግ አጥባቂ ፓርቲ ተቀናቃኛቸው ቶኒ አቦት መካከል በተደረገው ጠቅላላ ምርጫ የታየውን ቦክስ ቀረሽ የእርስ በርስ መሰዳደብ አይተውና ሰምተው አጀብ ያላሉ ቢኖሩ ራሳቸው አውስትራሊያውን ብቻ ነበሩ፡፡

ለእነሱ እንዲህ ያለው የምርጫ ወቅት የተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ከገደብ ያለፈ የእርስ በርስ ስድብና ዘለፋ ቢሊ ሂውዝ የአውስትራሊያ ሰባተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ከነበሩት ከ1920ዎቹ ጀምሮ ሲያዩትና ሲሰሙት የነበረ የአንድ ሰሞን ተራ ግርግር ነው፡፡ በዚህ ጠቅላላ ምርጫ የወግ አጥባቂው ፓርቲ እጩ ቶኒ አቦት የተዋጣላቸው ፖለቲከኛ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን አለብላቢት ምላስ፣ እሳት የላሱ ተሳዳቢ እንደሆኑም በተግባር አስመስክረዋል፡፡ ላለፉት ስድስት አመታት በስልጣን ላይ የቆየው ሌበር ፓርቲ የሰራቸውን ስህተቶች አንድ ባንድ ልቅም አድርገው በማውጣት፣ ፓርቲውንና መሪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኬቪን ሩድን ተሸጠውም ሆነ ተለውጠው አሊያም ለምነው እንኳ እንዳይበሉ አድርገው አበሻቅጠው በመስደብና በመዝለፍ የመራጩን ህዝብ የምርጫ ድምጽ ለእርሳቸው እንዲሆን ማድረግ ችለዋል፡፡

በዚህ የተነሳም ሌበር ፓርቲንና ጠቅላይ ሚኒስትር ኬቪን ሩድን በዝረራ ለማሸነፍ የመሪነት ስልጣኑን ለመጨበጥ በቅተዋል፡፡ ምርጫውን ከ ሀ እስከ ፐ ነገሬ ብለው የተከታተሉ ባለሙያዎች፤ በዚህ ምርጫ ተሸናፊው ጠቅላይ ሚኒስትር ኬቪን ሩድ ጥይት ጨርሰው እንደነበር በጥሞና ያስረዳሉ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ የባለሙያዎቹ አስተያየት አሳማኝነት አለው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬቪን ሩድ፤ መላ ሀይላቸውንና የምርጫ ቅስቀሳ ችሎታቸውን አሟጠው የተቀመጡት ለዚህኛው ምርጫ ሳይሆን ባለፈው ሰኔ ላይ ለሌበር ፓርቲው መሪነት በወቅቱ የሌበር ፓርቲው መሪና የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከነበሩት ወይዘሮ ጁሊያ ጂላርድ ጋር ላደረጉት ምርጫ ነበር፡፡ በዚህ ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሊያ ጂላርድን አይሰየሙ ስያሜ በመስጠት፣ አያወጡ ስም በማውጣት አሸንፈው የሌበር ፓርቲውን መሪነትና የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስልጣን መልሰው ለመቆጣጠር ችለዋል፡፡ የዚህ ምርጫ ድል ለኬቪን ሩድ ቀዝቅዞ የቀረበ ጣፋጭ በቀል ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቆናጠጡትን የሌበር ፓርቲ መሪነትና የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣናቸውን በ2010 ዓ.ም በተደረገው የፓርቲ መሪነት ምርጫ አሸንፈው የነጠቋቸው እኒሁ ወይዘሮ ጂሊያን ጂላርድ ነበሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኬቪን ሩድ፤ ጠቅላላው ምርጫ ደርሶ የወግ አጥባቂ ፓርቲውን መሪ ቶኒ አቦትን የተጋፈጧቸው የፓርቲ መሪነት ድላቸው የፈጠረባቸውን ደስታ ገና በወጉ እንኳ አጣጥመው ሳይጨርሱና ለጠቅላላ ምርጫው በቂ ዝግጅት ሳያደርጉ ነበር፡፡ ከተገመተውና ራሳቸውም ካሰቡት ሳይሆን ከተመኙትም በላይ የሆነ ታላቅ ድል የተቀዳጁት ቶኒ አቦት፤ በምርጫው በለስ እንደቀናቸው እንዳወቁ “እነማን ናቸው እኔን የሚንቁ፣ ደረስኩባቸው ሳይታጠቁ!” የሚለውን ዘፈን በመዝፈን፣ በተሸናፊው ጠቅላይ ሚኒስትር ኬቪን ሩድ ላይ በአደባባይ አላግጠውባቸዋል፡፡ ኬቪን ሩድም ምርጫው ከተጠናቀቀና አይሆኑ አሸናነፍ መሸነፋቸው ከተረጋገጠ በኋላ፣ ከሌበር ፓርቲ መሪነታቸው በፈቃዳቸው አይነት ምርጫ ስወዳደር ብታዩኝ ሰው ብላችሁ አትጥሩኝ በማለት ራሳቸውን በራሳቸው የፖለቲካ ጡረታ አውጥተዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ድል ባለ ድግስ ስልጣቸውን ለአዲሱ ተመራጭ ቶኒ አቦት ሲያስረክቡም ያሳዩት ስሜት በምርጫ ተሸንፎ ስልጣን የሚለቅ መሪ አይነት ሳይሆን ስልጣኑን በገዛ ፈቃዱ ለተተኪው የሚያስረክብ መሪ አይነት ነበር፡፡ ባለፈው ሰኔ ወር ባሁኑ ተሸናፊ ኬቪን ሩድ የሌበር ፓርቲ መሪነታቸውን በምርጫ ተሸንፈው በመነጠቃቸው የተነሳ፣ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጠናቸውንም ላጡት ጁሊያ ጂላርድ ግን እስከአሁንም ድረስ ነገሮች ሁሉ በእጅጉ የተለዩ ናቸው፡፡

ሳይወዱ በግድ በምርጫ ያጡት ስልጣን እጅግ ከፍተኛ ለሆነ የስነልቦና ቀውስ ዳርጓቸዋል። በአውስትራሊያ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት የሌበር ፓርቲ መሪና ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ እስካለፈው ሰኔ ወር ድረስ በስልጣን ላይ ለቆዩት ጁሊያ ጂላርድ ስልጣን ማለት የነብር ጅራት ማለት ነው፡፡ አስቀድመው የማይዙት፣ አንዴ ከያዙት ግን ጨርሰው የማይለቁት፡፡ ተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ አቦት፤ ቃለ መሀላ ፈጽመው ስልጣን ሲረከቡ የነበረውን ስነስርአት ጁሊያ ጂላርድ በቴሌቪዥን የተከታተሉት ብቻቸውን ሀይለኛ የምሬት ለቅሶአቸውን እያነቡ ነበር፡፡ እናም ይህንን ስሜታቸውን ዘ ጋርድያን ለተሰኘው ጋዜጣ የገለፁት “ስልጣንህን ማጣት ማለት ልክ ሳታስበው አፍንጫህን በቦክስ እንደ መመታት ማለት ነው” በማለት ነው፡፡ ይህንን የተናገሩት የቀድሞዋ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሊያን ጅላርድ፤ አፍሪካዊ ፖለቲከኛ ሆነው ቢሆን ኖሮ ማንም ይህን ያህል ነገሬ ባላላቸው ነበር፡፡ ነገሩ እንዲህ ከሆነ ዘንዳ መጠየቅ የሚገባን ጉዳይ እንዲህ የሚል ነው፡፡ “ለመሆኑ እኒህን ሴትዮ ስልጣንን የነብር ጅራት ነው እንዲሉ ያበቃቸው ምን ነገር ቢያገኛቸው ነው? ሳምንት በቀረው ጉዳይ እንገናኛለን፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

        “የኢህአዴግን የሥልጣን ዘመን አጭበርብረሃል” የሚል ወቀሳ ደርሶብኛል “ሥልጣን ለኢህአዴግ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው!” ውዲቷን ኢትዮጵያ ላለፉት 12 ዓመታት በርዕሰብሔርነት የመሯት (ወይስ መራቻቸው?) የ90 ዓመቱ አዛውንት ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፤ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሥልጣናቸውን በአደራ ለሰጣቸው ኢህአዴግ አስረክበው ከቤተመንግስት በመውጣት ኢህአዴግ ወዳዘጋጀላቸው መኖርያ ቤት ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። “ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ይደረጋል” ሲባል ሰማሁ ልበል? ወይስ ጆሮዬ ነው? (ጆሮዬ በሆነ!) ለምን መሰላችሁ? መቼም እሳቸው ከሥልጣን አልወርድም ብለው ከኢህአዴግ ጋር ሙግት ሊገጥሙ አይችሉም። ይሄማ ውለታ ቢስ መሆን ነው። እናላችሁ ---- “ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር” ከሚለው ይልቅ “ሰላማዊ የሥልጣን እርክክብ” ቢባል የተሻለ ሳይሆን አይቀርም የሚሉ ወገኖች አሉ። በነገራችሁ ላይ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በሥልጣን ዘመናቸው ከህመማቸው በቀር በሌላ በሌላው እድለኛ ናቸው ማለት ይቻላል። እንዴት ብትሉ---- ስንቱ ቱባ ቱባ የኢህአዴግ ሹማምንት በጋዜጠኞች ሲሞለጩና ሲተቹ፣ በፓርቲያቸው ሲገመገሙና “ሂሳችሁን ዋጡ” ሲባሉ፤ እሳቸው ግን ለ12 ዓመት እንደተከበሩ ኖረዋል። (ከተሳሳትኩ እታረማለሁ!) የፕሬዚዳንቱ አማካሪ አቶ አሰፋ ከሲቶ፤ “ውጤታማና እድለኛ ናቸው” ያሉት ለዚህ ይሆን እንዴ? በእርግጥ አልተሳሳቱም፤ሰውየው እድለኛ ናቸው። ባለቀ ሰዓት ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባልሾመ አንጀታቸው የትችት መዓት አወሩዱባቸው እንጂ።

ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ ላይ ስለፕሬዚዳንቱ የ12 ዓመት የሥልጣን ዘመን አስተያየት የሰጡ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና ምሁራን በአንድ ድምፅ “ውጤታማ አልነበሩም” ብለዋቸዋል። እኔ ፕሬዚዳንቱን ብሆን (ምኞት እኮ ነው!) ምን እንደምል ታውቃላችሁ? “የእኔን እድል ይስጣችሁ” (እርግማን እኮ አይደለም!) “እንደእኔ ፕሬዚዳንት ሆናችሁ እዩት” ለማለት ነው። ልክ ነዋ! ኢህአዴግ በፕሬዚዳንትነት የሾመው ሰው ያለው ሥልጣንና ሃላፊነት የቱ ድረስ እንደሆነ ሳያውቁ እኮ ነው ተመቸን ብለው የሚናገሩት። ኢህአዴግ የሾመው ከኢህአዴግ ፍላጎት ውጭ ተዓምር እንዲሰራ መጠበቅ “ፌር” አይደለም። (በኢህአዴግ ደግሞ ትግል እንጂ “ተዓምር” መስራት አይፈቀድም!) ከፓርቲው አፈንግጦ ተዓምር ለመስራት የሚወራጭ ካለም የቀድሞው ፕሬዚዳንት የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ዓይነት እጣ ፈንታ ይገጥመዋል። ከቤተመንግስት ወጥቶ ጣራው የሚያፈስ የኪራይ ቤቶች ቤት ውስጥ ይገባል።

ይሄም ታዲያ እጁን ከፖለቲካ ሰብስቦ ከተቀመጠ ብቻ ነው። ነጋሶ ግን እጃቸውን ሰብስበው አልተቀመጡም። በግላቸው በምርጫ ተወዳድረው በማሸነፍ ፓርላማ ገቡ። ራሴ ባረቀቅሁት ህገመንግስት ውስጥ የሰፈረውን ፖለቲካዊ መብቴን ከማስወስድ የሚያፈስ ቤታችሁን ውሰዱልኝ አሉ። (“የነጋሶ መንገድ” በሚለው መፅሃፋቸው እንደነገሩን) በነገራችሁ ላይ ፕሬዚዳንት ግርማ “ውጤታማ አልነበሩም” የሚለውን የተቃዋሚዎች ትችት እየተቃወምኩም ሆነ እየደገፍኩኝ አይደለም። (“አይቻልም ወይ መኖር የማንም ሳይሆኑ” ያለችው ድምፃዊት ማን ነበረች?) እኔ ግን ጥያቄ አለኝ - በፕሬዚዳንቱ ላይ በተሰነዘሩት አስተያየቶች ዙሪያ። ፕሬዚዳንቱ ይሄን ሁሉ ዘመን ኖረው ኖረው ከቤተመንግስት ሊወጡ አንድ ሐሙስ ሲቀራቸው “ውጤታማ ነበሩ? አልነበሩም?” የሚለውን የጦፈ ሙግት ምን አመጣው? ምናልባት ኢህአዴግ አዲስ ለሚሾመው ፕሬዚዳንት ይጠቅም እንደሆነ እንጂ ለተሰናባቹ እኮ የሚተርፋቸው ፀፀት ብቻ ነው። (The damage is already done! አለ ፈረንጅ) እውነቱን ለመናገር--- ተቃዋሚዎች ስለፕሬዚዳንቱ የሰጡት አስተያየት የድሮ ተረት ከማስታወስ ያለፈ ፋይዳ አለው ብዬ አላስብም (“ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” አሉ) የሚገርመው ደግሞ ከአስተያየት ሰጪዎቹ መሃል ጠንካራና ደካማ ጎኖቻቸው ወይም ስኬትና ውድቀታቸው ብሎ ከፋፍሎ ለማየት አንድ እንኳን የሞከረ የለም። ተቃዋሚዎቹ “የማርያም ጠላት” ያደረጓቸውን ያህል በፓርላማ የኢህአዴግ ደጋፊና ብቸኛው የግል ተመራጭ ዶ/ር አሸብርም እንከን የሌለባቸው ፍፁም ፕሬዚዳንት አድርገው ነው ያቀረቧቸው። (“ወልደህ ሳትጨርስ---”የሚለው ተረት ትዝ ብሏቸው ይሆን?) የፕሬዚዳንት ግርማ አማካሪ አቶ አሰፋ ከሲቶ እንኳን የቱንም ያህል መላዕክ ቢያደርጓቸው አይፈረድባቸውም (ሥራቸው ነዋ!) እኔ ተቃዋሚዎችን ብሆን ግን ትችቴን አንድም ኢህአዴግ ላይ አሊያም የፕሬዚዳንቱን ሥልጣን በገደበው ህገመንግስቱ ላይ ነበር የማነጣጥረው።

(“አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” አሉ!) እኔ የምለው ግን--- ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ በፕሬዚዳንት ግርማ ላይ የወረደውን የትችት ውርጅብኝ ሰምቶ ይሆን? ከሩጫ በኋላ ፕሬዚዳንት የመሆን ፍላጎት አለኝ ስላለ እኮ ነው! (ፍላጎት ነው ምኞት?) በኋላ ከሚቆጨኝ ለአትሌታችን ምክር ቢጤ ጣል ባደርግለት ደስ ይለኛል። ለፖለቲካ ዲሲፕሊንና ልምምድ ብቻ በቂ አይደሉም። (ሩጫና ፖለቲካ ለየቅል ናቸው!) እንግዲህ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ባለፉት 12 ዓመታት ሰሩም ተባለ አልሰሩ በቅርቡ ከሥልጣናቸው ይሰናበታሉ። ከወር በፊት ይመስለኛል--- ፕሬዚዳንቱ ከ“ሚት ኢቲቪ” አዘጋጅ ተፈራ ገዳሙ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ሲመረጡ የፍርሃት ስሜት አድሮባቸው እንደሆነ ጠይቋቸው፣ በመጀመርያው ጊዜ እንጂ በሁለተኛው ምንም ዓይነት ፍርሃት እንዳልተሰማቸው ገልፀው፣ለሦስተኛ ዙር በፕሬዚዳንትነት መቀጠል አለመቻሉ ትንሽ እንደሚያናድድ ተናግረዋል - በቀልድ መልክ። (ከአንጀታቸውም ሊሆን ይችላል!) ግን አያችሁልኝ--- የኢህአዴግን ምስጢር ወዳድነት። እስካሁን እኮ ቀጣዩ ፕሬዚዳንት ማን እንደሚሆን ፍንጭ እንኳ አልሰጠንም። (ኢህአዴግ “ሰርፕራይዝ” ማድረግም ነፍሱ ነው አሉ!) እናላችሁ--- ችግር የለም፤ ቀኑ ሲደርስ አዲሱን ፕሬዚዳንት በፓርላማ አቅርቦ ሰርፕራይዝ ይለናል - እንደ ልደት ስጦታ (ስጦታውስ ለኛ ሳይሆን ለተሿሚው ነው!) ባለፈው ሳምንት “ታጋይ ደከመኝ አይልም እንጂ ኢህአዴግ ድክም ብሎታል” በሚል ርዕስ ያቀረብኩትን ፅሁፍ ያነበቡ አንድ ደንበኛ ስልክ ደውለው እንዴት እንደወቀሱኝ አልነግራችሁም። ወቀሳው ምን መሰላችሁ? “የኢህአዴግን የሥልጣን ዘመን አጭበርብረሃል” የሚል ነው። በመቆርቆር ግን አይመስልም፤ “23 ዓመት አንቀጥቅጦ ገዝቶን እንዴት 21 ዓመት ብቻ ትላለህ? ሁለቱን የት ደብቀህለት ነው?” ነበር ያሉኝ።

እኔ እንኳን መደበቄ አልነበረም። ሁለቷ ዓመት የልምምድ ጊዜ ናት ብዬ ነበር የተውኳት (ለካስ ሂሳብ ማወራረድ ተጀምሯል!) እኔ ግን 30 እና 40 ዓመት የመግዛት ራዕይ ላለው ፓርቲ ገና ወገቡ ላይ ሆነን ሂሳብ መተሳሰብ ፋይዳው አልታየኝም። ባይሆን 30ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ሲገባ የሥልጣን ዘመኑን መቆጣጠር እንጀምራለን፤ አሁንማ ምን ተነካና። በነገራችሁ ላይ --- ኢህአዴግ የሥራ ብዛትና ጫና ስላደከመው ከመውደቁ በፊት የአንድ ዓመት እረፍት ይውሰድ በሚል ያቀረብኩትን ሃሳብ አብዛኞቹ የኢህአዴግ አባላት ክፉኛ እንደተቃወሙትና እንዳወገዙት ሰምቻለሁ - “ታጋይ አይደክመውም” በማለት። ከዚህ ሃሳቤ የማልታቀብ ከሆነም በቅርቡ የተቃውሞ ሰልፍ ለመውጣት እንደዛቱብኝ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ሹክ ብለውኛል። ከሁሉም የገረመኝ ግን ምን መሰላችሁ? አንዳንድ የኢህአዴግ ካድሬዎች በእኔ ላይ ለሚደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ገና ካሁኑ መፈክሮች ማዘጋጀት መጀመራቸው ነው። (የሰልፍ ፈቃድ ሳያገኙ?) እስቲ ከመፈክሮቹ ጥቂቶቹን እንያቸው - “ኢህአዴግ ደክሞታል በሚል ማደናገርያ ሥልጣን በአቋራጭ መያዝ የህልም እንጀራ ነው!” “ሥልጣን ለኢህአዴግ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው!” “ኢህአዴግ አረፍ እንዲል የሚፈልጉት የኒዮሊበራል ተላላኪዎች ናቸው!” እኔ ግን እንደነሱ አይደለሁም።

ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ቀንደኛ አቀንቃኝ ስለሆንኩ በዛቻውም ሆነ በመፈክሮቻቸው ቅያሜ አላደረብኝም። እንደውም ያለውዝግብ የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ ካገኙ ከእነሱ ጋር ሰልፍ ለመውጣት ሁሉ አስቤአለሁ - ተቃውሞው በእኔ ላይ ቢሆንም። ከገዢ ፓርቲ ጋር ተቃውሞ ሰልፍ ማድረግ ምን ዓይነት ስሜት እንደሚፈጥር ማወቅ እፈልጋለሁ (ለጠቅላላ እውቀት እኮ ነው!) በዚያ ላይ ተቃዋሚዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚጠሩት በእያንዳንዱ ሰልፍ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ፈቃድ ክፍልና ከፖሊስ ጋር የሚጋቡትን እልህና ውዝግብ ሰበብ ለማወቅ እፈልጋለሁ። ኢህአዴግስ ተመሳሳይ ውዝግብና እልህ ውስጥ ይገባል ወይስ ነገሩ አልጋ በአልጋ ይሆንለታል? (የባለቤቱ ልጅ መሆኑ እኮ አልጠፋኝም!) ይሄን ሁሉ የመፈተሽና የማጥናት ፍላጎት አለኝ። ስፖንሰር ተደርጌ እኮ አይደለም። (የሃገሬ ጉዳይ አያገባኝም እንዴ?) ባለፈው እሁድ ሰማያዊ ፓርቲ በመስቀል አደባባይ ሰልፍ ለማድረግ ጠይቆ፤ ቦታው በኮንስትራክሽን ሥራ ላይ እንደሆነና “ለልማት ነው ቅድምያ የምንሰጠው” የሚል ምላሽ እንደተሰጠው ገልጿል።

በዚሁ ሰበብ ፖሊስ ከቢሮው ንብረቶች እንደወሰደበት እንዲሁም እሁድ እለት ሰልፉን ሊያካሂዱ ሲሉ መንገድ በመዝጋት ሰልፉን እንዳቋረጠባቸው ፓርቲው በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። አንድነት ፓርቲም በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ጠይቆ፤ ሌላ አማራጭ ቦታዎች አቅርብ ከተባለ በኋላ ያቀረበው ሁሉ ውድቅ ሆኖ ሰልፉን ጃንሜዳ አድርግ እንደተባለ አስታውቋል። በዚሁ ሰሞን ሰላማዊ ሰልፍን የሚገድብ አዲስ መመሪያ ከአዲስ አበባ መስተዳድር መውጣቱን የሚናገሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ የተቃውሞ ሰልፉ የሚደረግበትን ቦታና ጊዜ የሚወስነው መስተዳድሩ እንደሆነ ጠቁመው፤ “አሁን የቀራቸው የምትቃወሙትንም የምንሰጣችሁ እኛ ነን” ማለት ብቻ ነው ሲሉ ክፉኛ አሽሟጠዋል። አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊ አዲስ ወጣ በተባለው መመሪያ ተናዶ ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ? “እንደዚያ ከሆነማ ለምን ሰልፍ የሚወጣውንም ህዝብ እነሱ አይመድቡልንም?” በአሁኑ ጊዜ ኢህአዴግ የተቃዋሚዎች ሰልፍ በጣም አስፈርቶታል የሚለው ይሄው የተቃዋሚ ደጋፊ፤ “በመኪና ለመቀስቀስ፣ ፖስተር ለመለጠፍ፣ በራሪ ወረቀት ለመበተን፣ ወዘተ--- ለሁሉ ነገር አስፈቅዱኝ እያለ ነው፣ ለምን መፈክሮቹንም እሱ አያዘጋጅልንም” በማለት አዲስ የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ለገዢው ፓርቲ አበርክቶለታል። “እናም ኢህአዴግ በቅርቡ “ሰላማዊ ሰልፍ እናዘጋጃለን፣ የተቃውሞ አጀንዳዎችን እንቀርፃለን፣ ለሰልፍ የሚወጣ ህዝብ እንመለምላለን፣ በራሪ ወረቀቶችን እናዘጋጃለን፣ የተቃውሞ ሰልፍ ቅስቀሳ እናደርጋለን ወዘተ-- የሚል ልዩ ማስታወቂያ በኢቴቪ ሲያስተላልፍ ልንሰማ እንችላለን” ብሏል - የተቃዋሚ ደጋፊው። (ግን ወዴት እየሄድን ይሆን? ለሁሉም የቀረበ ወቅታዊ ጥያቄ ነው!)

በደራሲ አዳም ረታ ተፅፎ ለንባብ የበቃው “ግራጫ ቃጭሎች” የረጅም ልቦለድ መፅሐፍ ከስምንት አመታት በኋላ በድጋሚ ታትሞ በዚህ ሳምንት ለገበያ ቀረበ፡፡
ከደራሲው ተወዳጅ ስራዎች አንዱ የሆነው፣ ለአመታት ከገበያ ጠፍቶ የነበረውና ተፈላጊነቱ የጨመረው ይህ መፅሐፍ በ75 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
ደራሲው የተለየ የአፃፃፍ ስልትን እንዳሳየበት የሚነገረው “ግራጫ ቃጭሎች”፣ በኦላንድ አሳታሚዎች ታትሞ ነው ለገበያ የበቃው፡፡ ደራሲ አዳም ረታ በቅርቡም “የስንብት ቀለማት” የተሰኘ በአይነቱ ለየት ያለና ከአንድ ሺህ ገፆች በላይ ያሉት ረጅም ልቦለድ መፅሐፍ ለንባብ ያበቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

ላለፉት 12 ዓመታት ኢትዮጵያን በርዕሰ ብሔርነት የመሩትና በሚቀጥለው ሳምንት ስልጣን የሚያሥረክቡት ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን የሚዘክር የፎቶግራፍ አውደርእይ ባለፈው ረቡዕ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ቀረበ፡፡ አውደርዕዩ ፕሬዚዳንቱ በስልጣን ላይ ሳሉ ያከናወኗቸውን ተግባራት እንደሚያስቃኝ “ታሪኳ ኤቨንት ኦርጋናይዘር” አስታውቋል፡፡

Saturday, 28 September 2013 11:38

የጀግና አሟሟት

              “ይኸውልሽ እህትሽ ሁሌ እንደምታስቸግረኝ ታውቂያለሽ፡፡ እንድታሳርፊልኝ ደጋግሜ ነግሬሻለሁ፤ የምሬን ነበር፤ አንቺን እንዳይደብርሽ ብዬ ነው ግን፤ ለሌላ አይደለም፤ ግድ እንደሌለኝ ታውቂያለሽ፤ እንኳን ነገር ፈልገውኝ እንዲሁም እንዲያው ነኝ፡፡” “ግን እህቴን;! አልጋዬ ላይ;!” “ምን ሆነሻል;! ሌሎች ሴቶች እንደማወጣ ታውቂያለሽ! እህትሽ መሆኗ ምን ለውጥ ያመጣል;! አንቺ እንዳይደብርሽ እንድታሳርፊልኝ ነግሬሻለሁ፤ … እህቴን ብሎ ነገር! በጣም ብዙ እህትማማቾች ተኝቻለሁ፤ እያወቁም በድብቅም፡፡” “እሺ አልጋዬ ላይ;!” “ቦታው ምን ለውጥ ያመጣል; አልጋሽ ላይ ሆነ፣ ሆቴል ሆነ፣ ጫካ ውስጥ ሆነ፣ ቢሮ ውስጥ ሆነ፣ ምን ለውጥ ያመጣል;” እነዚህ ቦታዎች ሁሉ ላይ እህቷን ተኝቷታል፡፡ ያስታውቃል፤ አውቆ ነው ቦታዎቹን የቆጠረላት፡፡ ትወደዋለች፡፡ እንደማታሸንፈው ታውቃለች፡፡ እሱ ሌላ ሲጋራ ለኮሰ፡፡ እሷ በተቆጡ አይኖቿ አሻግራ ታይ ጀመር፡፡ ቅድም ከኔ ጋር ወንበር ሲናጠቅ የነበረው ሰው ሲወራጭ አየችው፡፡ ለሷ ነው የሚወራጨው፡፡ በእጁ ምልክት “እሱን ተይው…” “ወድጄሻለሁ…” “ነይ ወደኔ…” አይነት ምልክቶች አሳያት፡፡ ዝም አለችው፡፡ ምልክቶቹን ደጋገማቸው፡፡

“ግድየለሽም እሱን ተይው…” “በጣም እወድሻለሁ…” “ነይ ወደኔ…” እሷም በምልክት እና በንዴት “ከሠው ጋር ነኝ እኮ” አይነት አለችው፡፡ በምልክት እንዲህ ማውራት የሚቻል አይመስለኝም ነበር፡፡ ተችሎ እያየሁ ነው፡፡ ቋንቋው በግልፅ እየተሰማኝ፡፡ ወዲያ ማዶ የተቀመጠው ሠው፡- የሰማውን ሰምቷል፡፡ “ድንቄም ከሠው ጋር!” አይነት ምልክት አሳያት፡፡ የሰማውን ሰምቷላ፡፡ እሷንም አብሯት ያለውንም ሠው የሚያጣጥል ምልክት አሳያት፡- “ደግሞ እንዲህ እያደረገሽ!” የሚል አይነት፡፡ አይኗን ከሰውየው ላይ አነሳች፡፡ አብሯት ያለው ሠው እያጨሰ ነው፡፡ አያያትም። ጭሱ ውስጥ እህቷን እያየ ይመስላል፡፡ አሁን ወዲያ ማዶ ስላለው ሠውዬ እናውራ፡፡ ጨዋ ወልዶ ጨዋ ያሳደገው ነው፡፡ አባቱ ኮሎኔል ናቸው፡፡ ልጃቸውን ያሳደጉት እሳቸው ከኖሩበት ሙያ በጠነከረ ዲሲፕሊን ነው፡፡ የስኬት ሶስቱ ስላሴዎች የታደሉት ሠው ነበር፡፡ ለተሳካ ህይወት የሚያስፈልጉት ሶስት ነገሮች ናቸው magic, method, reason, (የአእምሮ ጥሬ ብቃት፣ ትጋት እና በምክንያት መመራት ልንላቸው እንችላልን) እሱ ሶሰቱንም ተጎናጽፏል፡፡ ሶስቱም ነገሮች ብዙ ጊዜ አብረው አይከሰቱም፤ የአእምሮ ምርጥ ጥሬ ብቃት እያለህ ሰነፍ ልትሆን ወይም በምክንያት የማታምን ልትሆን ትችላለህ፡፡) ልጅ እያለ ጎበዝ ተማሪ ብቻ አልነበረም፡፡ በሁሉም ጨዋታዎች አንደኛ ነበር፡፡

ፈጣን ሯጭ፣ አብዶ የሚችል ኳስ ተጫዋች፣ በአንድ ጠጠር አራት በልቶ ባንዴ የሚነግስ ዳማ ተጫዋች፣ በአምስት ስድስት እርምጃዎች check mate ላይ የሚደርስ ቼስ ተጫዋች ነበር፤ ገና በልጅነቱ፡፡ ዩኒቨርሲቲ በማዕረግ ገብቶ፣ በማዕረግ ተመርቆ ወጣ፡፡ ስራ ያዘ፡፡ መኪና ገዛ፡፡ ቤት ገዛ፡፡ ለወላጆቹ ብቻ ልጅ ነው፡፡ እናት እና አባቱ እሱን ሲያዩ ሁሌ እንባ ይተናነቃቸዋል፤ የደስታ እንባ፡፡ ሁሌ እሱን ሲያዩት የደስታ እንባ በአይናቸው ግምጥ ይላል፡፡ ገና ፍቅር ምን እንደሆነ ሳያውቅ የፍቅር ደብዳቤዎች ይደርሱት ነበር፤ ገና የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ የተጻፈለትን የፍቅር ደብዳቤ ለአባቱ ወስዶ አሳያቸው፤ ሳቁ አባቱ፡፡ “መጥፎ ነገር አይደለም፤ ግን ጊዜው ገና አልደረሰም፡፡” አሉት፡፡ “እሺ አባባ፡፡” አለ፡፡ ጊዜው መቼ እንደሚደርስ ግን አልነገሩትም፡፡ “ሌሎች እንዲህ አይነት ደብዳቤዎች ሲደርሱህ አሳየኝ፡፡” “እሺ አበባ፡፡” የተጻፉለትን ሁሉ ለአባቱ አቀበለ፡፡ ኋላ ላይ አባቱ ማንበብ ታክቷቸው፣ እየተቀበሉት ጣሏቸው።… ዘንድሮ ስራ ከያዘ አምስተኛ አመቱ ነው፡፡ ከሴት ጋር ታይቶ አይታወቅም፡፡ የተደላደለ ኑሮ እና ምርጥ ዘር የሚፈልጉ ሴቶች ሁሉ በግልፅም በስውርም ለትዳር ወይ ገፋፍተውታል ወይ ጠይቀውታል፡፡

አባት እና እናት አሁን መፍራት ጀመሩ፡፡ አሁን ልጃቸው ትዳር ይዞ ማየት ይፈልጋሉ፡፡ ቤተሰቦቹ የሚወዱትን ያህል ልጃቸውን ይፈሩታል፡፡ እንከን የለሽ ነው፡፡ አባቱ አንድ ቀን እየፈሩ፡- “የሚመችህ ከሆነ እራት ልጋብዝህ ዛሬ፡፡” አሉት፡፡ “እሺ አባባ፤ ይመቸኛል፡፡” እራት ጋበዙት፡፡ “አባባ የሆነ ያሳሰበህ ነገር ያለ ይመስላል!” “አዎ ልጄ፡፡” “ምንድነው;” “አንተ ነህ ዳግም፡፡” ስሙ ዳግማዊ ነው፡፡ “እንዴ አባባ;! እኔ;!” “አዎ ዳግሜ፡፡” “ምን አጠፋሁ;” “ኸረ ምንም፤ ትዳር፣ ትዳር ነው፤ ለምን ትዳር አትይዝም;” ቅልል አለው፤ አባትም እንዲሁ፡፡ “የሚገርምህ አባባ እኔም እያሰብኩበት ነበር፤ ግን አዋይሀለሁ እያልኩ ትንሽ አፍሬ ነው የተውኩት፤ እንጂ ሰሞኑን እቤት ስመላለስ የነበረው ይህንኑ ላዋይህ ነበር፤ እንዴት እንደማወራህ ግራ ገብቶኝ ነው የተውኩት፡፡” አባት የደስታ እንባ በአይናቸው ግጥም አለ፡፡ “ምኑ ነው ግራ የገባህ;” “ምን አይነት ሴት ነው ማግባት ያለብኝ የሚለው ነዋ!” “ይኸማ በጣም ቀላል ነው፤ ማግባት ያለብህ የምታፈቅራትን ሴት ነው፤ እና የምታፈቅርህን፡፡ እኔ እና እናትህ አርባ አምስት አመት በፍቅር እና ያለ አንዳች ኮሽታ የኖርነው ስለምንፋቀር ነው፤ እናትህን ያገባኋት አፍቅሬያት፣ እንደምታፈቅረኝ ካረጋገጥኩ በኋላ ነው፡፡ ፍቅር ካለ ሌላው እዳው ገብስ ነው፡፡” አባት እና ልጅ በደስታ እና በፍቅር ተያዩ፡፡ ተጨባበጡ፡፡ ልጅ ሲያስጨንቀው የነበረው ጥያቄ ተመለሰለት፡፡ አባትም ሲያስጨንቃቸው የነበረው ነገር እንዲህ በቀላሉ ሲፈታ እንደ ልጅ ሆኑ፡፡ የደስታ እንባ በአይናቸው ግጥም አለ፡፡ ሲለያዩ ዳግም አባቱን አቅፎ እንዲህ አላቸው፡- “እማማን በቅርቡ ለሰርግ ተዘጋጂ በላት፡፡” አባት መኪናቸው ውስጥ የደስታ ለቅሶ አለቀሱ። ዳግማዊም አለወትሮው እየደነሰ ነበር የመኪናውን በር የከፈተው፡፡ ማግባት ያለብህ የምታፈቅራትን ነው! አለቀ፡፡ ለካ እንዲህ ቀላል ነበር፡፡  

                                                 * * *

አሁን ወደ ቴሌ ባር እንምጣ፡፡ ዳግማዊ ልጅቷን እንዳየ አፍቅሯታል፡፡ ደግሞም አብሯት ያለዉ ሰዉ ያላትን ሰምቷል፡፡ አድርጎት የማያውቀውን እያደረገ ያለው ልጅቷን ስላፈቀራት ነው፡፡ አፍቅሮ አያውቅም፤ እና ምን እና እንዴት ማድረግ እንዳለበት አያውቅም፡፡ ግን ስህተት እያደረገ እንዳይደለ ታውቆታል፡፡ ልጅቷን አፍቅሯታል፡፡ ይሄ 1 + 1 ነው፤ እውነት። ልጅቷ ደግሞ እህቷን እራሷ አልጋ ላይ ከሚተኛ ሰውዬ ጋር ናት፤ ይሄ እድል ነው፡፡ እውነት + እድል, ስኬት ልጅቷ እህቷን የተኛባትን ሰውዬ፡- “ልጃችንስ;” አለችው በሚያሳዝን እና በሚለማመጥ ድምጽ፡፡ “ልጃችንስ; የምን ልጃችን ነው;! ልጃችን የሚባል ነገር የለም፤ ልጁ ያንቺ ነው፤ እኔ ልጅ የለኝም፡፡ በመጀመሪያም ነግሬሻለሁ፤ እኔ ልጅ አልፈልግም። በምድር ላይ ልጅ እንደመውለድ ወይም ለዚያ ተባባሪ እንደመሆን ያለ ቀፋፊ ሀጢያት እንደሌለ ነግሬሻለሁ፤ አትስሚም ግን፤ ወይም አላመንሽኝም፤ እኔ አልዋሽም፡፡ በሀጢአቴ አታስሪኝም፡፡ እኔ ፤ልጅ መውለድ ሀጢአት መሆኑን ነግሬሽ እየተጠነቀቅኩ ነበር፤ አንቺ ተሳሳትሽ፡፡ ሀጢአቱ ያንቺ ነው፤ ልጁ ያንቺ ነው፡፡ ነግሬሻለሁ፡፡” ነግbታል፡፡ ተስፋ በመቁረጥ አይኗን ወደ ማዶ አማተረች፤ ዳግማዊ ይወራጫል፡፡ “ግድ የለሽም እሱን ተይው…” “በጣም እወድሻለሁ…” “ነይልኝ እና አብረን እንኑር..” ተናደደች፡፡ “እንዴት ማየት ይሳነዋል;! ምንም ይሁን ከሰው ጋር ነኝ! ምን ሆኗል ልጁ;! እንዲህ አይነት ሰዎች ናቸው ሰው በሰላም አብሮ እንዳይኖር የሚያደርጉት! እህቷን ወደተኛባት ፍቅረኛዋ አየች፡፡

አያያትም፤ እያጨሰ ነው፡፡ “ስማ!” አለችው፡፡ አያት፡፡ “እግዜርን እንኳ አትፈራም;!” ከት ብሎ ሳቀ፡፡ ደስ የሚል ሳቅ፡፡ “እግዜር ! እግዜርን አትፈራም;! እግዜርን እኔን መፍራት አለበት፤ ደሞ እንደሚፈራኝ እርግጠኛ ነኝ። ይሄውልሽ እኔ እግዜርን ባገኘው፤ ሮበርት ዲኔሮ እንዳለው you have a lot of explaing to do ምናምን አይነት ቀሽም ነገር አይደለም የምለው!….” አቋረጠችው፡፤ ንዴቷ እና ንቀቷ በጣም፣ በጣም፣ በጣም ያስፈራል፡፡ አብሯት ያለው ሠውዬ እያያት ስለማያወራ አላያቸውም፡፡ “ምን ነበር የምለትለው;” አለችው በቁጣ፣ በንዴት እና በንቀት፡፡ “አናቱን ነበር የምለው፡፡” በርጋታ የምትጠጣውን ቢራ አነሳች፤ ተነስታ ቆመች፤ አናቱን አለችው፡፡ ጠርሙሱ አናቱ ላይ ተሰበረ፡፡ (እግዚአብሔር ሰውየው ያለውን ሠምቶ ተናዶ ይሆን እንዴ;) አሻግራ አየች፡፡ አሁን ዳግማዊ ክው ብሎ እያያት ነው፡፡ የተሰበረውን ጠርሙስ ይዛ በቀስታ ዳግማዊ ወዳለበት ወንበር መራመድ ያዘች፡፡

ምን ልታደርግ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ዳግማዊ በአባቱ ምክር የታጠቀውን ሽጉጥ አወጣ፡፡ “እዛው ሁኚ፤ እንዳትጠጊኝ፡፡” እንደማይተኩስ አውቃለች፤ ጆን ስቴንቤክ ፈረስ እና ሴቶች፣ ወንዶች (ጋላቢዎቻቸው) እርግጠኛ ሲሆኑ እና ሲያመነቱ በእርግጠኝነት ያውቃሉ ብሏል፡፡ “እተኩሳለሁ፤ እውነቴን ነው፡፡” በቀስታ እና በእርጋታ ተራመደች፡፡ “እ-ተ-ኩ-ሳ-ለ-ሁ፡፡” አሁን እውነቱን እንደሆነ ገብቷታል፡፡ የሽጉጡ አፈሙዝ ወዴት እንደዞረ አላየችም፡፡ መሞት ፈልጋለች፡፡ መሰንዘር የምትችልበት እርቅት ላይ ስትደርስ የተኩስ ድምጽ ተሰማ፡፡ ፊቷ በደም ተሸፈነ፡፡ ጠርሙስ ባልያዘው እጇ ደሙን ከፊቷ ላይ ጠረገች፡፡ ዳግማዊ ሽጉጡን በአንድ እጁ እንደያዘ ተጋድሟል፡፡ እራሱን አጥፍቷል፡፡ ጀግና፡፡ ማን በሴት እጅ ይሞታል;! እኔ አሁን እራሴን ማጥፋት አልፈልግም፡፡ ለመኖር ምክንያት አግኝቻለሁ፡፡ አንድ፡- ያቺን ልጅ እስር ቤት እየሄድኩ ሁሌ እጠይቃታለሁ፡፡ ሁለት፡- ልጇን አሳድጋለሁ፡፡

Published in ልብ-ወለድ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን የቅርስ ጥበቃና የቤተመጻሕፍት ወመዘክርና ቱሪዝም መምርያ፤ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሊወገዱ የነበሩ ሦስት ጥንታዊ የብራና መጻሕፍትን ተረከበ፡፡ እንደ መምሪያው ገለፃ፤ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጊዜ ጀምሮ በቬርባል ሲገላበጡ ቆይተው ለመወገድ በዝግጅት ላይ የነበሩት የብራና መፃሕፍት የተገኙት በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አባል ጥቆማ ነው፡፡ መጻሕፍቱ በፖሊስ ኮሚሽን ግምጃ ቤት እንደሚገኙ በጠቆሙን መሰረት ተጻጽፈን ባለፈው ሰኞ መጻሕፍቱን ተረክበናል ብለዋል - የመምርያው ሃላፊ መምህር ሰለሞን ቶልቻ፡፡ የተገኙት የብራና መጽሐፍት እያንዳንዳቸው ከ200 ገጽ በላይ ሲሆኑ፤ መፃሕፍቶቹም ድርሳነ ኡራኤል፣ ድርሳነ ማህየዊ እና ድርሳነ ሚካኤል ናቸው፡፡ መምርያቸው ተመሳሳይ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ሃላፊው ገልፀዋል፡፡

እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከኦክቶቨር 3-5/2013 ከመስከረም 22-24/2006 ዓ/ም FIGO የአለም የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ፌደሬሽንን አህጉራዊ ስብሰባ በኢትዮጵያ ያካሂዳል፡፡ FIGO በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን ጨምሮ 27/ሀገራት ያሉበት የአፍሪካ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በሚል አህጉራዊ የስራ አካል እንደ ኤ/አ ኦክቶቨር 2012/ዓ/ም ያቋቋመ ሲሆን የዚህ አካል የመጀመሪያው ስብሰብ በ FIGO አስተባባሪነት እና በኢት ዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር አስተናጋጅነት ይካሄዳል፡፡ የስብሰባውን ሙሉ መንፈስ በመጪው እትም ለንባብ እናቀርባለን፡፡ በዚህ እትም የምናስነብባችሁ የቤተሰብ እቅድ ወይንም Family Planning ማለት ልጅን ካለመውለድ ጋር ብቻ የሚያያዝ ሳይሆን ፕሮግራሙ ልጅን ለመውለድ የሚደ ረገውን ክትትል እንደሚጨምርም የሚያሳይ ነው። “… አንድ ገጠመኝ ላካፍላችሁ፡፡ ...እኔ የምኖረው በአዲስ አበባ ነው፡፡ ባለቤ ደግሞ በስራ ምክንያት አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው በባህርዳር ነው፡፡ ባለቤ ቤተሰቡን ለመጠየቅ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣው በአመት ሁለት ጊዜ ለዘመን መለወጫ እና ለት ንሳኤ በአል ብቻ ...ያውም ለአንድ ሳምንት ያህል ነው፡፡ በእንደዚህ ያለው አኑዋ ኑዋ ራችን...እኔ ሳረግዝ ...ስወልድ ልጆቻችን ስምንት ናቸው፡፡

እግዚሀር አልፈቀደለት ምና... ባለቤ ልጆቹን ሳያሳድግ ሞተ፡፡ እኔ በቤት ያሉት ልጆች ቁጥራቸው በዛ እያልኩ ስጨ ነቅ ...እሱ ለካንስ በሚሰራበት አካባቢ ሌላ ሴት አግብቶ ሶስት ልጆችን አፍርቶ አል፡፡ ለነገሩ...ንብረት የለንም...የምንጨቃጨቅበት ምንም ነገር አልገጠመንም፡፡ ይሁን እንጂ እኔም ሆንኩ ጉዋደኛው የቤተሰብ እቅድ ዘዴን ሳንጠቀም ልጆችን በመውለዳችን ለማሳ ደግ ተቸግረናል ... ከላይ ያነበባችሁት ገጠመኝ አስተያየት ሰጪዋ እንዳሉትም የቤተሰብ እቅድ ዘዴን አለመጠቀም በብዙዎች ዘንድ ውጤቱ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሚሆን ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ዶ/ር ዮናስ ጌታቸው የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ ጥ/ የቤተሰብ እቅድ Family Planning ሲባል ምን ማለት ነው? መ/ Family Planning ¨ይንም የቤተሰብ እቅድ ማለት ሴቶችና ወንዶች በፈለጉት ጊዜ የፈ ለጉትን ያህል ልጅ መውለድ እንዲችሉ የሚያቅዱበት ዘዴ ነው።

በዚህም ምን ያህል ልጅ በምን ያህል የጊዜ ልዩነት መውለድ እንደሚፈልጉ አስቀድሞውኑ በመወሰን የሚ ወለዱት ልጆች በቂ በሆነ አቅም ...ማለትም አቅም በፈቀደ መጠን የትምህርት የህክምና እንዲሁም የተመጣጠነ ኑሮ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው አሰራር ነው፡፡ በእርግጥ የቤተ ሰብ እቅድ ሲባል ሴቶችና ወንዶች መውለድ ባልፈለጉበት ጊዜ እንዳይወልዱ ማድረግ ብቻ ሳይሆን መውለድ ካልቻሉ እንዲወልዱ ለማድረግም የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው፡፡ ጥ/ ልጅ መውለድ ለሚፈልጉ የቤተሰብ እቅድ (Family Planning) እንዴት ያገለግላል? መ/ ከላይ እንደተገለጸው የቤተሰብ እቅድ ሲባል ልጅ መውለድ ለማይፈልጉ የእርግዝና መከ ላከያን በመጠቀም የልጅ ቁጥርንና ጊዜን ለመወሰን የመርዳቱን ያህል በዚህ ፕሮግ ራም ልጅ መውለድ ያልቻሉም መውለድ እንዲችሉ የሚያስችል አሰራር አለው፡፡ ሴቶ ችና ወንዶች ልጅ መውለድ ባልቻሉበት ወቅት ወደሐኪም በመቅረብ ባልና ሚስቱ መውለድ ያልቻሉባቸው ምክንያቶች በሕክምና በምርመራ ታውቆ ወደቀጣይ እርምጃ እንዲሄዱ ያስችላል፡፡

ጥ/ ልጅ መውለድ ለሚፈልጉ በFamily Planning ምን አይነት ሕክምና ይሰጣል? መ/ ልጅ መውለድ አለመቻል ሲባል ምናልባት በሴቷ ወይንም በወንዱ ምክንያት የተከሰተ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ በሴቷ በኩል ከሆነ ምክንያቶቹ፡- የተፈጥሮ ችግር እና የሆርሞን መዛባት፣ የዘር ፍሬ አለመኖር፣ የማህጸን በር ተስተንክሎ አለመፈጠር፣ የወንዱ ፈሳሽ በትክክል ከእንቁላል ጋር እንዳይገናኝ ምክንያት ይሆናል፡፡ የሴቷ እንቁላልና የወንዱ እስፐርም የሚገናኙበት (fallopian tube) የሚባለው መስርመር በተለያዩ ምክንያቶች መዘጋት፣ በዚህ መስመር ላይ የሚከሰት የተለያየ ቁስለት መመረዝ ወይንም ጠባሳ የሴቷ እንቁላል ከወንዱ ስፐርም ጋር እንዳይገናኝ ያውካል፡፡ ለሴቶች ልጅ ያለማግኘት ምክንያት ከሚሆኑት መካከል የሆርሞን መዛባት ይገኝበታል፡፡ሴቶች የወር አበባቸው ጊዜ ከመድረሱ በፊት ወደአጋማሽ በሚሆነው ቀን አንድ እንቁላል ለእርግዝና ዝግጁ የምትሆን ሲሆን ይህ እንቁላል በጊዜው እስፐርም ካላገኘ እርግዝና መሆኑ ቀርቶ በወር አበባ መልክ ይፈሳል፡፡ ይህ ለሴቶች ልጅ ያለመውለድ 25% ድርሻ ይይዛል፡፡

በወንዶች በኩል ልጅ ያለመውለድ ችግር፡- የአባላዘር በሽታ እንደ ጎኖሪያ...ጨብጥ...ወዘተ የዘር ፍሬ አለመኖር፣ የዘር ማስተላለፊያ ቱቦው በተለያየ ምክንያት ሲዘጋ፣ የወንድ የዘር ፍሬ እንቁላልን የመስበር አቅም ከሌለው፣ የእስፐርም መጠን ማነስና እንቅስቃሴው አዝጋሚ መሆን፣ የእስፐርም ጥራት መጉዋደል፣ በተለያዩ ምክንያቶች በብልት አካባቢ ጉዳት ደርሶበት ከነበረና ያም በጊዜው ሳታከም ቀርቶ ወደመመረዝ ወይንም ወደህመም ከተለወጠ ...ወዘተ፡፡ አንዳንድ ጊዜም ሴቶችና ወንዶች ያለመጣጣም ችግር ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ምክንያቶች ልጅ መውለድ ያልቻሉ ሴቶችና ወንዶች በቤተሰብ እቅድ አገልግሎት Family Planning ፕሮግራም መሰረት ወደሕክምና ባለሙያ ቀርበው አስፈላጊውን ሕክምና ቢያደርጉ ልጅ መውለድ የሚችሉበትን አጋጣሚ መፍጠር ይቻላል፡፡ ጥ/ ያለመጣጣም ሲባል ምን ማለት ነው? መ/ ያለመጣጣም ሲባል በተለያየ መንገድ የሚታይ ሲሆን በተለይም የወንድ የዘር ፍሬና የሴት የዘር ፍሬ ቢገናኙም ዘር ለመፍጠር ካልቻሉ እንዳልተጣጣሙ ይቆጠራል፡፡

ይህ አጋጣሚ በተለያየ ምክንያት ሊፈጠር የሚችል ነው፡፡ ለምሳሌም ...እንደ ጎኖሪያ ወይንም ጨብጥ የመሳሰሉት በሽታዎች ምክንያት ከሚፈጠሩት ሕመሞች መነሻነት የሚፈጠረው ኢንፌክሽን ከወንድየው ለሚወጣው ፈሳሽ ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡ በሌላም በኩል በማ ህጸን በር አካባቢ ያለው (mucus) ማለትም ማህጸንንና የማህጸን በርን ከተለያየ መመረዝ የሚከላከ ለው ወፈር ያለ ፈሳሽ ምናልባትም ለወንዱ ፈሳሽ የሚወፍርበት ከሆነና ፈሳሹ ያንን ማለፍ ካቃተው ወይንም ለወንዱ ፈሳሽ መርዝ የሚሆን ከሆነ እንደ አንድ አለመጣጣም ሊቆጠር ይችላል፡፡ ስለዚህ ከላይ በተገለጹትና ሌሎችም ተመሳሳይ ምክንያቶች ልጅን ማፍራት ያልቻሉ ሰዎች የስነተዋልዶ አካሎቻቸውን በተገቢው በመፈተሸ የህክምና ምርመራ ማድረግ እና ሴቶችም ሆኑ ወንዶች የሚሰጣቸውን መድሀኒትም ሆነ ሌላ የህክምና አገልግሎት በተገቢው መከታተል ይጠበቅባቸዋል፡፡ የወንዶች እስፐርም ጥራትና ብዛት ወይንም የሴቶችን ማህጸን አፈጣጠርና እንቁላል ማምረት አለማምረት የመሳሰሉት በተገቢው የህክምና ድጋፍ ካገኙ የነበሩበት ሁኔታ ሊሻሻል ይችላል፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በተለይም በሆርሞን መዛባት የሚከሰቱ ልጅ የመውለድ ችግሮች እስከ 75 ኀ ያህል በህክምና ፈውስን ያገኛሉ፡፡

ጥ/ አስፈላጊ የሆነው ሕክምና ሁሉ በኢትዮጵ ሊሰጥ ይችላልን? መ/ በእርግጥ ልጅ መውለድ ለተቸገሩት ለሁሉም አይነት ምክንያቶች ሕክምናውን በኢትዮጵያ መስጠት ይቻላል ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን በአገር ውስጥ የሚሰጡትን ሕክምናዎች በአግባቡ በመጠቀም ብዙዎች ውጤታም እንደሆኑ መመስከር ግን ይቻላል፡፡ ልዩነቱ በተለይም በሴትዋም ይሁን በወንዱ በኩል የሚፈጠሩትን የመውለድ ችግሮች እስከመጨረሻው ሕክምናው ተሞክሮ ነገር ግን ውጤታማ አልሆን ሲል በሳይንሳዊ ዘዴ በማዳቀል ልጅ እንዲያገኙ ለማድረግ በኢትዮጵም ሆነ ሌሎች ተመሳሳይ ሀገራት መሳሪያው ስለሌለ ብዙዎች ሕክምናው ወደሚሰጥበት ሀገር በመሄድ ልጅ ማግኘት ይሞክራሉ። ስለዚህ ሕክምናው ይሰጣል አይሰጥም ለሚለው በዚህ ሀገር ባለው የህክምና አሰጣጥ ደረጃ ታክመው መፍትሔ የሚያገኙ የመኖራቸውን ያህል ወደውጭም ሄደው መፍትሔ የሚያገኙ አሉ፡፡ ጥ/ የእርግዝና መከላከያ ኪኒን እርግዝና እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላልን? መ/ የእርግዝና መከላከያ ኪኒን የእርግዝና መከላከያ እንጂ ለመውለድ የሚረዳ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሴቶች የወር አበባ መዛባት ሲያጋጥማቸው ለተወሰኑ ጊዜያት እንዲወስዱት ይመከራል፡፡ የዚህም ምክንያቱ የወር አበባ መዛባት ባለበት ሁኔታ እርግዝናን ማሰብ ስለማይቻል ነው። ስለዚህ የወር አበባቸው እንዲስተካከል በሚደረገው ሕክምና ለሶስት ወር ያህል የእርግዝና መከላከያ ኪኒን እንዲወስዱ ይደረግና ከዚያ በሁዋላ እንዲያረግዙ ይደረጋል።

Published in ላንተና ላንቺ
Page 2 of 16