የኤች አይቪ ቫይረስ በአለም አቀፍ ደረጃ በገዳይነታቸው ከሚታወቁ የማህበረሰብ ጤና ችግሮች መካከል ቀዳሚውን ስፍራ እንደያዘ ይገኛል፡፡ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ 2014/ ብቻ 1.2/ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በዚሁ በሽታ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
አፍሪካ በተለይም ደግሞ ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት የችግሩ ከፍተኛ ተጠቂዎች ሲሆኑ 25.8 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ይገኛል፡፡ ይህም ከአለም 70%
የሚሆነውን ቁጥር ይሸፍናል፡፡ በተመሳሳይ በእነዚህ ከሰራ በታች ባሉት የአፍሪከ ሀገራት በየአመቱ 300.000/ አዳዲስ ህፃናት በቫይረሱ እንደሚያዙ የአለም የጤና ድርጅት ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡
መንግስት በጤናው ዘርፍ የምእተ አመቱ ግብ ብሎ ካስቀመጣቸው ጉዳዮች መካከል በፈረንጆቹ 2020 ከኤች አይቪ ነፃ የሆነ ትውልድ ማፍራት የሚለው አንዱ ነው፤ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው በተግባር ላይ ውለዋል ከእነዚህም መካከል፡-
በጤናው ዘርፍ ከሚሰሩ ፖሊሲ አውጪዎች ጋር በጋራ መስራት
የህክምና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ኤች አይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የPMTCT አገልግሎትን እንዲሰጡ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ
አገልግሎቱን በሚመለከት ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ
ዋናዋናዎቹ ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅትም የኤች አይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችለውን የህክምና ክትትል PMTCT(Prevention of mother-to-child transmission) አገልግሎት በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ የግል እንዲሁም የመንግስት የህክምና ተቋማት እንዲሰጥ አድርጓል፡፡
በፈረንጆቹ 2007 አመተ ምህረት የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው 977.397 የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 75.402 የሚሆኑት ነብሰጡር እናቶች ናቸው፡፡
የኤች አይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ በዋናነት የሚተላለፈው በወሊድ ግዜ እንዲሁም ጡት በማጥባት ሲሆን ይህንን ለመከላከል የሚሰራው ስራም Prevention Mother to Child Trans mission (PMTCT) ወይም ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ መከላከል በሚል በስራ ላይ ከዋለ ጥቂት የማይባሉ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በእኛም ሀገር ይህ አይነቱ አገልግሎቱ በፈረንጆቹ 2001 የተጀመረ ሲሆን አገልግሎቱ ከተጀመረበት ግዜ አንስቶ 79.4% የሚሆኑ እናቶችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ የፅንስ እና የማህፀን ሀኪሞች ማህበር (ኢሶግ) በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የክልል ከተሞች ለሚገኙ የግል የህክምና ተቋማት ይህን አገልግሎት ለህብረተሰቡ በተገቢው መንገድ ይሰጡ ዘንድ የስልጠና፣ የቁሳቁስ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረግ ይገኛል፡፡
በዛሬው ፅሁፋችንም በአዲስ አበባ ከተማ አገልግሎቱን እየሰጡ ከሚገኙ የግል የህክምና ተቋማት መካከል የሶስቱን ተሞክሮ ልናስነብባችሁ ወደናል፡-
በቅድሚያ የተገኘነው በሴማህ የእናቶች እና የህፃናት የህክምና ማእከል ነበር፡፡ ማእከሉ አገልግሎቱን በተደራጀ መልኩ ለመስጠት እንዲቻል እራሱን የቻለ ክፍል ተቋቁሞ እየሰራ እንደሆነ በክፍሉ ውስጥ በስራ ላይ ያገኘናት ሲስተር ጎንደሪት ነጋሽ ትናገራለች፡፡
“...አሁን በእኛ ማእከል ያለው ነገር በጣም ጥሩ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በዚህ ሶስት ወር ግዜ ውስጥ ያለውን እንኳን ብንመለከት የኤችአይቪ ምርመራ አድርገው ክትትላቸውን እያደረጉ ያሉ ሁለት እናቶች አሉን፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ውጤታቸውን አውቀው ለእርግዝና ክትትል እኛ ጋር የመጡ ሶስት እናቶች አሉን። ስለዚህ መጀመሪያ አንዲት እናት ለእርግዝና ክትትል እኛ ጋር ስትመጣ በቅድሚያ ኤች አይቪን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ ምርመራዎችን እንድታደርግ ይደረጋል፡፡ ባጠቃላይ አሁን ላይ ያለው ነገር አበረታች ነው፡፡ ሰዉም ከድሮው የተሻለ ግንዛቤ አለው፡፡...”
ሁሉም እናቶች የኤች አይቪ ምርመራውን ከማድረጋቸው አስቀድሞም በቂ ገለፃ እና የምክር አገልግሎት እንደሚደረግላቸው ትገልፃለች፡፡
“...ምርመራውን ከማድረጋቸው በፊት ለሁሉም እናቶች የምክር አገልግሎት እንሰጣቸዋለን፡፡ ጤናማ የሆነ ልጅ እንዲወልዱ ተመርምረው እራሳቸውን ማወቅ እንዳለባቸው እንነግራቸዋለን፡፡ ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ አብዛኞቹ እናቶች ፈቃደኛ ሆነው ምርመራውን ደርጋሉ፡፡ ውጤታቸውን ካወቁ በኋላም ያለማቋረጥ ክትትላቸውን ያደርጋሉ፡፡...”
ሲስተር ሄለን በበፀጋ የእናቶች እና የህፃናት ሆስፒታል በPMTCT ክፍል ውስጥ በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይም ሆነ በተጠቃሚዎች ቁጥር ላይ ብዙ መሻሻሎች አሉ ትላለች፡፡
“...ድሮ ከነበረው ጋር ስናነፃፅረው በእኔ አመለካከት አሁን ላይ ብዙ ለውጥ ያለ ይመስለኛል፡፡ ለእርግዝና ክትትል ወደ ሆስፒታላችን የሚመጡ ሁልም እናቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ አንዲት እናት ለክትትል ስትመጣ መጀመሪያ የሚያስፈልጉ ምርመራዎችን ሁሉ ጨርሳ ወደ እኛ ጋር ትላካለች የምክር አገልግሎት ከሰጠናት በኋላም ምርመራውን ታደርጋለች ማለትነው፡፡ ስለዚህ ከምናየው የተገልጋዩ ብዛት በመነሳት ለውጥ አለ ማለት እንችላለን፡፡...”
ሁለቱም ባለሙያዎች አብዛኞቹ እናቶች ምርመራውን ለማድረግ ያላቸው ተነሳሽነት ጥሩ የሚባል እና በዚህ ዙሪያ ምንም አይነት ችግር እንዳልገጠማቸውም ይናገራሉ፡፡    
“...በእኛ ተቋም በPMTCT በኩል እናቶች ማግኘት የሚገባቸውን አገልግሎት ሁሉ እንሰጣለን። ነገርግን ብዙ ግዜ ምርመራውን አድርገው ውጤቱ ፖዘቲቭ ከሆነ በጣም ይደነግጣሉ፡፡ በቀጣይ ያለውን ህክምና ለመጀመርም ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ አንዳንዴ እንደውም ክትትላቸውን አቋርጠው የሚጠፉብንም አሉ። ይህ ሲሆን በአድራሻቸው ፈልገን ጠርተን የምክር አገልግሎት ሰጥተን መድሀኒት እንዲጀምሩ እናደርገለን፡፡ ስለዚህ አገልግሎቱን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ እኛም የቻልነውን እያደረግን ነው በተጠቃሚዎችም በኩል ጥሩ ተነሳሽነት አለ፡፡...”
ያለችን ደግሞ በማሪስቶፕስ እስፔሻላይዝድ የማህፀን እና ፅንስ ህክምና ማእከል የነጋገርናት ሲስተር ሰናይት ብርቄ ነች፡፡
በአለም የጤና ድርጅት በተደረገ ጥናት ተገቢው ህክምና ካልተደረገ የኤችአይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ እድሉ ከ15-45 ፐርሰንት ይደርሳል፡፡ ይህም፡-
በእርግዝና ወቅት 5-10%
በወሊድ ግዜ 10-15% እንዲሁም
ጡት በማጥባት 5-20% ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ እድል ይኖረዋል፡፡
አገልግሎቱ በማይሰጥበት ሁኔታም ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ የሚኖረው መተላለፍ እንደየ ሀገራቱ ሁኔታ ሊለያይ የሚችል ሲሆን የመከላከሉ ስራ ውጤታማ ከሆነ ግን ስርጭቱ እስከ 5% ይወርዳል ተብሎ ይታሰባል፡፡
ቀደም ሲል በነበረው አሰራር አንዲት እናት ቫይረሱ በደሟ ሲገኝ መድሀኒት ከመጀመሯ በፊት የሲዲፎር መጠኗ እንዲታይ ይደረግ የነበረ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ ግን የትኛዋም እናት ፖዘቲቪ መሆንዋ ከታወቀ ግዜ አንስቶ መድሀኒት እንድትጀምር እንደሚደረግ ሲስተር ብርቄ ትገልፃለች፡፡
“...አንዲት እናት ኤችአይቪ ፖዘቲቭ መሆኗ ከታወቀ ወዲያውኑ መድሀኒት እንድትጀምር እናደርጋለን፡፡ እንደ ድሮ ቅድሚያ ሲዲፎር ይሰራ አንልም፡፡ በፊት ሲዲፎር አይተን ነበር መድሀኒት የምናስጀምረው አሁን ግን ፖዘቲቭ መሆኗን ካወቀች እና የምክር አገልግሎት ከወሰደች በኋላ በማንኛውም ሰአት መድሀኒቱን እናስጀምራታለን...”    
ይህም መንግስት የኤችአይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ለሚደረገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንዳለ አመላካች ነው፡፡       
ዩኒሴፍ በ2012 ያወጣው መረጃ በሀገራችን የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ከሚገኝ እናቶች መካከል 24 ፐርሰንት የሚሆኑት ብቻ ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ የሚሰጠውን ህክምና እንደሚያገኙ ጠቁሟል፡፡
ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ የትዳር አጋሮች የሚኖራቸው አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ሶስቱም ባለሙያዎች ይስማማሉ። ነገርግን በስራቸው ላይ ካስተዋሉት በመነሳት የትዳር አጋሮች ተሳትፎ ዝቅተኛ የሚባል እንደሆነ እና በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ ውጤታማ እንዳይሆን ተግዳሮት እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡
ሲስተር ሄለን ከብዙ ገጠመኞቿ መካከል አንዱን እንዲህ አጫውታናለች፡-
“...እናቶች መጀመሪያ ለእርግዝና ለክትትል ሲመጡ በቀጣይ ቀጠሮ የትዳር አጋሮቻቸውን ይዘው እንዲመጡ እና እነሱም እንዲመረመሩ እንነግራቸዋለን፡፡ ነገርግን ብዙዎቹ ይህን ለማድረግ ፈቃደኞች ስለማይሆኑ የቻልነውን ያህል ግፊት እናደርጋለን፡፡ አንድ ግዜ አንዲት እናት ለክትትል መጥታ በቀጣይ ቀጠሮ ስትመጣ ባሏን ይዛ እንድትመጣ እና እሱም እንዲመረመር ነገርኳት ...አንድግዜ ስራ ይበዛበታል... አድ ግዜ ሀገር ውስጥ የለም ስትለኝ ቆየች... እኔም ጥያቄን አላቆምኩም በመጨረሻ ይዛው መጥታ ሲመረመር ውጤቱ ፖዘቲቪ ሆነ... እንዲህ አይነት ሁኔታዎች በየግዜው ይገጥሙናል፡፡...”

Published in ላንተና ላንቺ

 ክፍል አንድ
15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሳምንት በኋላ በቻይና ዋና ከተማ ቤጂንግ ይጀመራል፡፡ 29ኛው ኦሎምፒያድን ከ7 ዓመት በፊት በድምቀት ባስተናገደው  ታላቁ የወፍ ጎጆ ስታድዬም ለሁለት ሳምንታት የሚካሄድ ነው፡፡ የወፍ ጎጆ የተባለው ዘመናዊ ስታድዬም ኦሎምፒክን  ያስተናገደው እስከ 80ሺ ተመልካች በመያዝ ነበር፡፡ ለዓለም ሻምፒዮናው ተስማሚ የአየር ንብረት እንዲኖር ሲባል  54000 ተመልካች ብቻ እንዲያስተናግድ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ተወስኗል። ብዙዎቹ ውድድሮች በምሽት መካሄዳቸው የውድድሩን ድምቀት ይጨምረዋል ተብሏል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናው በአጭር ርቀት አሜሪካና ጃማይካ፤ በረጅም ርቀት ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሚያደርጉት ትንቅንቅ ይደምቃል፡፡
በተለያዩ የውድድር መደቦችን ሚኒማዎችን ያሟሉ፤ ከ2 ዓመት በፊት ሞስኮ ባስተናገደችው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ የወሰዱ፤ የ2014 የዳይመንድ ሊግ አሸናፊዎች፤ የየአህጉሩ ሻምፒዮኖች መሳተፋቸው ሻምፒዮናው ያለበትን ከፍተኛ ደረጃ ያመለክታል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው የሚገኝ ስኬት ከዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለሚካሄደው 31ኛው ኦሎምፒያድ ውጤታማነት አመልካች ሲሆን በየውድድር መደቡ ሻምፒዮን ሆነው የወርቅ ሜዳልያ የሚያገኙት የሪዮዲጄኔሮ ትኬታቸውን በቀጥታ የሚቆርጡበት ይሆናል፡፡
ከ200 አገራት በላይ እንደሚሳተፉበት በሚጠበቀው የዓለም ሻምፒዮናው በ47 የውድድር መደቦች (24 በወንድ እና 23 በሴት)  ከ2000 በላይ አትሌቶች ይወዳደራሉ። በየሻምፒዮናው አጠቃላይ የሜዳልያ ሰንጠረዡን በመሪነት የመቆጣጠር ልምድ ያላቸው አሜሪካ፤ ጃማይካና ራሽያ ሙሉ ቡድናቸውን ሰሞኑን አሳውቀዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ሞስኮ ባስተናገደችው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ አሜሪካ 6፤ ጃማይካ 6፤ ኬንያ 5፤ ጀርመን 4 እንዲሁም ኢትዮጵያ 3 የወርቅ ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ ከ1 እስከ 6 ያለውን ደረጃ ይዘው መጨረሳቸው ይታወሳል፡፡በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ከ1 እስከ 8ኛ ደረጃ ለሚያገኙት እንዲሁም ለሌሎች የቡድን ውድድሮች የገንዘብ ሽልማት የሚበረከት ሲሆን የዓለም ሪከርድ ለሚያስመዘግብ አትሌቶች የ100ሺ ብር ቦነስ ተዘጋጅቷል፡፡ ለወርቅ ሜዳልያ 60 ሺ ዶላር፤ ለብር ሜዳልያ 30ሺ ዶላር፤ ለነሐስ ሜዳልያ 20ሺ ዶላር ሲበረከት፤ ከ4 እስከ 8 ደረጃ ለሚያገኙት 15ሺህ፤ 10ሺህ ፤6ሺህ፤ 5ሺ እና 4ሺ ዶላር እንደቅደመተከተላቸው ይሸለማል፡፡
የኢትዮጵያ ቡድን ኬንያ እና ሌሎች
ከመካከለኛ ርቀት እስከ ማራቶን 33 አትሌቶች ያሉበትን ቡድን የምታሰልፈው ኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታዎች ከአራት በላይ የወርቅ እንዲሁም በድምሩ እስከ 12 ሜዳልያዎች እንደምትሰበስብ ተገምቷል።  የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ካለፈው የዓለም ሻምፒዮና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚቻል ተስፋ ማድረጉን የገለፀ ሲሆን፤ ብሔራዊ ቡድኑን  ላለፈው 1 ወር በአራራት ሆቴል አስቀምጦ ከፍተኛ ዝግጅት እንዲያደርግ አስችሏል፡፡ አትሌቶች የቤጅንግ አየር ንብረትን ለመቋቋም እንዲያስላቸው ተግባራዊ በሆነው የልምምድ መርሃ ግብር ሰርተዋል፡፡ ከቃሊቲ እስከ ሶደሬ በሚገኙ የአገሪቱ ሞቃታማ አካባቢዎች በመዘዋወር ዝግጅታቸውን ሲያከናውኑ ከርመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በሁለቱም ፆታዎች በ6 የውድድር መደቦች ተካፋይ ትሆናለች፡፡ በ800፤ በ1500፤በ5ሺ በ10ሺ፤ በ3ሺ መሰናክል እና በማራቶን ማለት ነው፡፡ ባለፈው የዓለም ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳልያ ካስመዘገቡት በ10ሺ  የወርቅ ሜዳልያ የወሰደችው ጥሩነሽ ዲባባ በወሊድ እረፍት  እንዲሁም በ5ሺ የወርቅ ሜዳልያ ያገኘችው መሰረት ደፋር ባልታወቀ ምክንያት አለመሳተፋቸው ታውቋል፡፡ ከእነሱ ባሻገር የኢትዮጵያ ቡድን የዓለም ሻምፒዮና ፤ የዳይመንድ ሊግ እንዲሁም የትልልቅ የማራቶን ውድድሮች ልምድ ባካበቱ አትሌቶች፤ በወጣት እና ተተኪ አትሌቶች የተሞላ ነው፡፡ ከቡድኑ አባላት መካከል በ800 ሜትር ለኢትዮጵያ በታሪክ የመጀመርያውን የወርቅ ሜዳልያ ከ2 ዓመት በፊት ያገኘው መሃመድ አማን ግንባር ቀደም ተጠቃሹ ነው። በሴቶች ደግሞ የዓለም ሻምፒዮና ኮከብ አትሌት ሆኗ ተሳትፎዋ በጉጉት የሚጠበቀው ገንዘቤ ዲባባ ትነሳለች። በ1500 ሜትር ዘንድሮ የዓለም ሪከርድ ያስመዘገበችው ገንዘቤ ዲባባ በ5ሺ ሜትር እንድትወዳደር ፌደሬሽኑ ቢመርጣትም ገንዘቤ በ1500 ሜትር እና በ5000 ሜትር ደርባ መወዳደር ብትችል የብዙዎች ፍላጎት ነበር፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት በ3 የዓለም ሻምፒዮናዎች የመሳተፍ እድል የነበራት ገንዘቤ የወርቅ ሆነ የሜዳልያ ውጤት ለማስመዝገብ  ብዙም አልሆነላትም ነበር።  በ5000 ሜትር በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ስትሳተፍ በ2009 ላይ 9ኛ እንዲሁም በ2011 8ኛ ደረጃ አግኝታ የነበረ ሲሆን  በ2013 እኤአ ደግሞ በ1500 በመካፈል ስምንተኛ ነበረች፡፡ በተጨማሪም ከ2 ዓመት በፊት በሞስኮው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5ሺ የብር ሜዳልያ ያገኘችው አልማዝ አያና፤ በ10ሺ የነሐስ ሜዳልያ የወሰደችው በላይነሽ ኦልጅራ፤ በ5ሺ የብር ሜዳልያ ያገኘው ሐጎስ ገብረህይወት፤ በ3ሺ መሰናክል የነሐስ ሜዳልያ የወሰደችው ሶፍያ አህመድ ልምዳቸውን በመጠቀም ውጤታማ እንደሚሆኑ ተስፋ የተጣለባቸው ናቸው፡፡ በ10ሺ ለወርቅ ሜዳልያ የሚጠበቁት በሆላንድ በተደረገው የማጣርያ ውድድር አስደናቂ ውጤት ያስመዘገቡት ሙክታር ኢድሪስ እና ገለቴ ቡርቃ ይሆናሉ። ከወጣት ተተኪ አትሌቶች ውጤታማ እንደሚሆን ተስፋ የተደረገው በ5000 ሜትር ወንዶች የሚጠበቀው ወጣቱ ዮሚፍ ቀጀልቻ ነው፡፡  በኦሎምፒክ በ5ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ ያለው ደጀን ገብረመስቀል ደግሞ በ10ሺ ሜትር በሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች ከኢትዮጵያ የራቀውን የወርቅ ሜዳልያ ድል እንደሚመልስ ተገምቷል፡፡
የኢትዮጵያ የቅርብ ተቀናቃኝ የሆነችው ኬንያ 47 አትሌቶችን በማስመዝገብ ትሳትፋለች፡፡ ለኢትዮጵያ እና ለኬንያ ከመካከለኛ ርቀት እስከ ማራቶን ባሉ ውድድሮች የአሜሪካ፤ የእንግሊዝ፤ እና የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች እየተጠቀሱ ናቸው፡፡ በረጅም ርቀት በተለይ በወንዶች ለእንግሊዙ ሞፋራህ  ከፍተኛ ግምት ሲሰጥ፤ በ800 ሜትር የቦትስዋናው ኒጄል አሞስ፤ የአሜሪካዎቹ ጋለን ሩፕና ራያን ሂል በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ለምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የሜዳልያ ተስፋ ፉክክር እንደሚፈጥሩ ተነግሮላቸዋል፡፡ ኬንያ በ200 በወንዶች፤ በ400ሜ በሁለቱም ፆታዎች እና በ400 መሰናክል በወንዶች፤ በጦር ውርወራ በወንዶች በ5 የውድድር መደቦች ከኢትዮጵያ የተሻለ ተሳትፎ ይኖራታል፡፡ ከሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ባሻገር የደቡብ አፍሪካው ዋይዴ ቫን በ200 ሜትር፤ ናይጄርያ በ400 ሜትር  ሌሎች የአጭር ርቀት ውድድሮች ኡጋንዳ እና ኤርትራ ደግሞ በረጅም ርቀት የአፍሪካን ተሳትፎ ያጠናክሩታል ተብሏል፡፡

Saturday, 15 August 2015 16:05

የሜዳልያ ትንበያ

 በአሜሪካው የትራክ ኤንድ ፊልድ አትሌቲክስ መፅሄት ድረገፅ ለ15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከመካከለኛ ርቀት እስከ ማራቶን ባሉ የውድድር መደቦች በወቅታዊ ብቃት ላይ ተመስርቶ የሜዳልያ ትንበያ ተሰርቷል። በዚሁ የትራክ ኤንድ ፊልድ ድረገፅ ኤክስፐርቶች ትንበያ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ስኬት እንደሚኖራት የተገመተው ከወንዶች ይልቅ በሴቶች አትሌቶች ነው፡፡ በሴቶች ሶስት የወርቅ ፤ 3 የብር እና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች ኢትዮጵያ እንድመታስተመዘግብ በትራክ ኤንድ ፊልድ ሲተነበይ በወንዶች ደግሞ በ5ሺ ሜትር ዮሚፍ ቀጀልቻ ብቻ የነሐስ ሜዳልያ እንደሚወስድ ተገልጿል፡፡ በሴቶች ለኢትዮጵያ ከተመዘገቡት 3 የወርቅ ሜዳልያዎች ሁለቱን በ1500 እና በ5000 ሜትር ታስመዘግባለች የተባለው ገንዘቤ ዲባባ ስትሆን 3ኛውን የወርቅ ሜዳልያ በማራቶን ትእግስት ቱፋ ትወስዳለች ተብሏል። ከሶስቱ የብር ሜዳልያ ግምቶች ደግሞ ገለቴ ቡርቃ በ10ሺ ሜትር፤ አልማዝ አያና በ5ሺ ሜትር እንዲሁም ማሬ ዲባባ በማራቶን ሲጠቆሙ፤ ቀሪዎቹን ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎች በ3ሺ መሰናክል ህይወት አያሌው እንዲሁም በ10ሺ ሜትር አለሚቱ ሃሮዬ እንደሚያገኙ ተተንብዮላቸዋል፡፡
ከዓለም ሻምፒዮና 1 ወር በፊት የትራክ ኤንድ ፊልድ የወርቅ፤ የብርና የነሐስ ሜዳልያዎች ትንበያ ከመካከለኛ ርቀት እስከ ማራቶን
በወንዶች
በ800 ሜትር
ኒጀል አሞስ ቦትስዋና፤ ዴቪድ ሩዲሻ ከኬንያ፤ አቤል ቱካ ከሰርቢያ
በ1500 ሜትር
አዝቤል ኪፕሮፕ ከኬንያ፤ ሲላስ ኪፕላጋት ከኬንያ፤ አያልነህ ሱሌማን ከጅቡቲ
በ3ሺ መሰናክል
ጃሩስ ቢርዬች ከኬንያ፤ ኢቫን ጃገር ከአሜሪካ ፤ ኮንሴሌስ ኪፕሮቶ ከኬንያ
በ5ሺሜትር
ሞ ፋራህ ከታላቋ ብሪታኒያ፤ ካሌብ ኒዱኩ ኬንያ፤ ዮሚፍ ቀጀልቻ ከኢትዮጵያ
በ10ሺሜትር
ሞ ፋራህ ከብሪታኒያ፤ ጄይሪር ኪፕውሁር ከኬንያ፤ ጋሌን ሩፕ ከአሜሪካ
በማራቶን
ዊልሰን ኪፕሳንግ ከኬንያ፤ ስቴፈን ኪፕሮቺች ከኬንያ፤ ዴኒስ ኪሜቶ ከኬንያ
በሴቶች
በ800 ሜትር
ኢዪንሴ ሰም ከኬንያ፤ አጄል ዊልሰን ከአሜሪካ፤ ጃኔት ኪፕሶጌ ከኬንያ
በ1500 ሜትር
ገንዘቤ ዲባባ ከኬንያ፤ ሰይፋን ሃሰን ከሆላንደ፤ ጄኒ ሲምፕሰን ከአሜሪካ
በ3ሺ መሰናክል
ሃቢባ ጋሪቢ ከቱኒዝያ፤ ቨርጂና ናያምቡራ ከኬንያ፤ ሂይወት አያሌው ከኢትዮጵያከኢትዮጵያ
በ5ሺ ሜትር
ገንዘቤ ዲባባ፤ አልማዝ አያና ከኢትዮጵያ፤ሜርሲ ቼሮኖ ከኬንያ
በ10ሺ ሜትር
ቪቪያን ቼሮይት ከኬንያ፤ ገለቴ ቡርቃ  ከኢትዮጵያ፤ አለሚቱ ሃሮዬ ከኬንያ
በማራቶን
ትግስት ቱፋ ከኢትዮጵያ፤ ማሬ ዲባባ ከኢትዮጵያ፤ ኤድና ኪፕላጋት ከኬንያ

ባለፈው ሳምንት በአቢጃታና ሻላ ሀይቅ መካከል በሚገኘው የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ የተካሄደው 2ኛው የተራራ ላይ ሩጫ ኢትዮ ትሬል   ፈጣን እድገት እያሳየ ነው፡፡ የተራራ ላይ ሩጫው በክልሉ ያለውን የስፖርት እንቅስቃሴ በማነቃቃት፤ የቱሪስት መሳቢያ መንገዶችን በማጠናከር እና የተፈጥሮ ሃብትን በመጠበቅ ትኩረት እንዲፈጠር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ በአራት የውድድር መደቦች የተካሄደው 2ኛው የተራራ ላይ ሩጫው ከ500 በላይ የሚሆኑ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ሯጮችን ያሳተፈ ነበር፡፡  የተራራ ላይ ሩጫ ለአዳዲስ አትሌቶች የውድድር  ዕድል መፍጠሩም እንደትልቅ ውጤት የሚጠቀስ ይሆናል፡፡ በተለይ 50 አትሌቶችን ሙሉ ወጪ ተሸፍኖላቸው መሳተፋቸው ውድድሩ ስፖርቱን ለማስፋፋት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ያመለከተ ነው፡፡ የተራራ ላይ ሩጫው የውድድር እድል በመፍጠር ፤ተተኪ አትሌቶች ለማውጣት የሚያግዝ እንደሆነም ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
በአትሌት ገብረ እግዚአብሄር ገብረ ማርያም የተመሰረተው እና በሪያ ኢትዮጵያ ቱር እና ትራቭል ድርጅት አስተባባሪነት በተካሄደው 2ኛው የተራራ ላይ ሩጫ በታዳጊዎች 1ሺ 500 ሜትር  እንዲሁም በሁለቱም ጾታዎች 12 ኪሎ ሜትር ፣21 ኪሎ ሜትር እና 42 ኪሎ ሜትር በሸፈነ ፈታኝ የሩጫ ውድድሮች ልዩ ድምቀት ነበረው፡፡ ከ80 በላይ የሚሆኑት ተወዳዳሪዎች ከ9 የተለያየ ሀገራት በመምጣት የተሳተፉበት የተራራ ላይ ሩጫው እና በተለይ የስፔን ኤምባሲአጋር ሆኖ በየተጫወተው ሚና በርካታ ስፓንያርዶችን ያሳተፈ ነበር፡፡ በአራት የውድድር መደቦች አሸናፊ ለነበሩ ተሳታፊዎች የውድድሩ አዘጋጆች ከ70ሺ ብር በላይ የሽልማት ገንዘብ ያበረከቱ ሲሆን፤ አሸናፊዎች ከሽልማት ገንዘብ ባሻገር፤ የአካባቢውን ባህል የሚያሳይ ኩርሲ የተባለ መቀመጫ  ተበርክቶላቸዋል። ለአሸናፊዎቹ ሽልማት ካበረከቱት መካከል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኢታ አቶ እውነቱ ብላታ ፣የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሰልጣን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳውድ ኡመር የሚገኙበት ሲሆን የኢትዮጵያ ታላላቅ አትሌቶች፣ አትሌት ወርቅነሽ ኪዳኔ፣ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ አትሌት እልፍነሽ አለሙ፤ አትሌት ድሪባ መርጋ ፣ አትሌት ብርሃኔ አደሬ እና የውድድሩ ባለቤት አትሌት ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም ሽልማቶችን በመስጠት አሸናፊዎችን በከፍተኛ ደረጃ አበረታትዋል፡፡  
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ድጋፍ ለውድድሩ ከፍተኛ እገዛ እንዳበረከተ ለመገንዘብ የተቻለ ሲሆን በሚቀጥሉት ዓመታት ውድድሩ በከፍተኛ ደረጃ እድገት አሳይቶ የሚቀጥል እንደሚሆን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

 በወርቅአፈራሁ አሰፋ የተዘጋጀው “ISIS ከሶሪያ እስከ አቢሲኒያ” የተሰኘ አዲስ መጽሃፍ ለንባብ መብቃቱን ደራሲው አስታወቀ፡፡ በመጽሃፉ ውስጥ ከተካተቱት አበይት ጉዳዮች መካከል  አይሲስና አርማጌዶን ፣የአይሲስ አፈጣጠርና የሲአይኤ አሻጥር፣ ኢትዮጵያ የአይሲስ ቀጣይ ዒላማ ትሆን?----የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የመጽሃፉ ማስታወሻነት በሊቢያ ትሪፖሊ፣ በስጋት ህይወት ውስጥ ለምትገኘው ታናሽ እህቱ መሠረት አሰፋና ያለሃጢያታቸው ለታረዱትና በእሳት ለተቃጠሉት የሰይጣናዊ ቡድኑ ሰለባዎች በሙሉ ይሁንልኝ ብሏል - ደራሲው፡፡
በ160 ገጾች የተቀነበበው መጽሃፉ፤በዴርቶጋዳ ማተሚያ ድርጅት ታትሞ በሊትማን መጻህፍት እየተከፋፈለ ሲሆን ዋጋው 46 ብር ከ65 ነው፡፡

  የስዊድን ፍርድ ቤት አቃቤ ህጎች ዊኪሊክስ የተባለው አለማቀፍ ሚስጥር ጎልጓይ ድረገጽ መስራች በሆነው ጁሊያን አሳንጄ ላይ ከቀረቡት የተለያዩ የወንጀል ድርጊት ክሶች መካከል ሶስቱን ውድቅ ማድረጋቸውን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
የስዊድን ፍርድ ቤት አቃቤ ህጎች ሃሙስ እለት እንዳስታወቁት፤ በአሳንጄ ላይ ከቀረቡት ውንጀላዎች ሶስቱ ክስ መመስረት ከሚገባው ጊዜ አልፎ የቀረቡ በመሆናቸው ውድቅ የተደረጉ ሲሆን፣ በ2010 የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈጽሟል በሚል የቀረበበት ክስ ግን መታየቱን ይቀጥላል፡፡ አሳንጄ በስዊድን ከተላለፈበት የእስራት ትዕዛዝ በማምለጥ ከሰኔ ወር 2012 ጀምሮ ለንደን ውስጥ በሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ ውስጥ ጥገኝነት አግኝቶ እየኖረ እንደሆነ ያስታወሰው ዘገባው፤ውድቅ የተደረጉለት ወንጀሎች ክስ መመስረት ከሚገባቸው የአምስት አመት የጊዜ ገደብ አልፈዋል መባሉን ጠቁሟል፡
የ44 አመቱ አውስትራሊዊ አሳንጄ የቀረቡበትን የወንጀል ክሶች በሙሉ መካዱን  ያስታወሰው ዘገባው፣ በሺህ ዎች የሚቆጠሩ አሜሪካን የሚመለከቱ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ይፋ በማውጣቱ ሳቢያ እየተደረገበት ካለው ምርመራ ጋር በተያያዘ ለአሜሪካ ተላልፎ እንዳይሰጥ በመስጋት ወደ ስዊድን እንደማይመለስ መናገሩንም አክሎ ገልጧል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

  ፕሬዚዳንቱ ያስገደሏቸው ባለስልጣናት 70 ደርሰዋል ተብሏል
   አምና በሰኔ ወር ስልጣን ላይ የወጡት የሰሜን ኮርያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቾ ዮንግ ጎን በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኪም ጁንግ ኡን ትዕዛዝ ባለፈው ግንቦት ላይ እንደተገደሉ መነገሩንና ደቡብ ኮርያም ጉዳዩን እያጣራች እንደሆነ መግለጧን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ዮንሃፕ ኒውስ የተባለ የዜና ምንጭ የስለላ ተቋማትን መረጃ ዋቢ በማድረግ ባወጣው ዘገባ፣ የ63 አመቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሰሜን ኮርያው ፕሬዝዳንት ኪም ጁንግ ኡን የምከተለውን የደን ልማት ፖሊሲ ተችተዋል በሚል አስገድለዋቸዋል፡፡
የግንባታና የግንባታ መሳሪያ ኢንዱስትሪዎች ምክትል ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉትና ወደ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርነት ያደጉት ቾ ዮንግ ጎን ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ከህዝብ እይታም ተሰውረው መቆየታቸውና እሳቸውን በተመለከተ ምንም አይነት የዜና ሽፋን ተሰጥቶ አያውቅም ብሏል ዘገባው፡፡
ፕሬዝዳንት ኪም ጁንግ ኡን ስልጣን ከያዙ በኋላ በእሳቸው ትዕዛዝ የተገደሉና የገቡበት ጠፍቶ የቀሩ የሰሜን ኮርያ ባለስልጣናት ቁጥር 70 ያህል ደርሷል ያለው ዘገባው፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቾ ዮንግ ጎንም የፕሬዚዳንቱን አስተዳደር በመተቸታቸው እንዲገደሉ ተደርገዋል የሚል ዘገባ መውጣቱን ገልጧል፡፡
የደቡብ ኮርያ ብሄራዊ አንድነት ኢንስቲቲዩት ባለፈው ወር ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በሰሜን ኮርያ በ2012 ብቻ 21 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ኪም ጁንግ ኡን በ2013 የገዛ አጎታቸውን ማስገደላቸውንና በዚህ አመትም የመከላከያ ሚኒስትሩን ዮን ያንግ ቾልን በአሰቃቂ ሁኔታ በሞርታር ማስረሸናቸውን አስታውሷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንድ ሰው ብዙ ከብቶች ወዳሉበት አንድ በረት ገብቶ አንድ ላም ሰርቆ ሲወጣ፤ አንድ መንገደኛ ሰው ያየዋል፡፡ ያም ሌባ ጣቱን አፉ ላይ አድርጐ “ዝም በል አትንገርብኝ ባክህ!” ይለዋል፡፡
ያም መንገደኛ ለማንም እንደማይናገርበት ራሱን በአዎንታ ነቀነቀለት፡፡
ሌላ ጊዜ ሌባውና መንገደኛው አንድ ሆቴል ቤት ተገናኙ፡፡ መንገደኛው ምግቡን በልቶ ሌባውን ክፈልልኝ አለው፡፡
“ለምንድነው የምከፍለው?” አለው ሌባው፡፡
መንገደኛው፤
“ዋ! የላሟን ነገር ለመንደሩ አለቃ እነግርልሃለሁ!” አለው፡፡
ሌባው ተሽቆጥቁጦ ከፈለ፡፡
ሌላ ቀን አንድ የገበያ አዳራሽ ውስጥ ይገናኛሉ፡፡ መንገደኛው የሚችለውን ዕቃ ወስዶ ሲያበቃ ለባለሱቁ፤
“ያ ሰውዬ ይከፍላል” ብሎ ወደ ሌባው ጠቆመ፡፡
ሌባው አሁንም፤
“ለምንድነው የምከፍለው?” አለ፡፡
መንገደኛውም፤
“ዋ! የላሟን ነገር!” አለው፡፡
ሌባው የግዱን ከፈለ፡፡
በሌላ ቦታ መንገደኛው ሌባውን አገኘውና፤
“ገንዘብ ቸግሮኛልና ስጠኝ?” አለው፡፡
ሌባው፤ “ለምንድን ነው የምሰጥህ?” አለ፡፡
“ዋ! የላሟን ነገር!” ሲል ገና፤ ገንዘብ አውጥቶ ሰጠው፡፡
ሆኖም አሁን ቆም ብሎ ማሰብ ጀመረ፡፡
“ለምን ሄጄ ለመንደሩ አለቃ ላም መስረቄን ነግሬ፣ ይቀጣኝም እንደሆን አልቀጣም?” ብሎ አሰበ፡፡ ወሰነ፡፡
ቀጥ ብሎ ወደ መንደሩ አለቃ ሄደና፤
“ጌታዬ፤ ቸግሮኝ ከመንደሩ በረት አንድ ላም ሰርቄያለሁ፡፡ በህጉ መሠረት የምትቀጣኝን ቅጣኝ” ሲል ጠየቀው፡፡ (“የምታፋፍምብኝን አፋፍምብኝና ልሂድ!” እንዳለው ሰው በቀይ ሽብር ዘመን)
አለቅየውም፤ አውጥቶ አውርዶ፤ “ዋናው ይቅርታ መጠየቅህ ነው” ብሎ በምህረት ሸኘው፡፡
ሌባው በደስታ እየፈነጠዘ ሄደ፡፡
ሌላ ቀን መንገደኛው እንደልማዱ “ገንዘብ አምጣ” አለው፤ ሌባውን፡፡ “አልሰጥም” አለ ሌባው።
“ዋ! የላሟን ነገር!” ሲለው፤
“የፈለከው ቦታ ድረስ!” ብሎት ሄደ፡፡
መንገደኛው ተናዶ፤ ወደ መንደሩ አለቃ እየበረረ ሄደና፤ “እገሌ ላም ሰርቋል” ሲል ተናገረ፡፡
አለቃውም “እሱስ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ አንተ ነህ ሌባ!”
“ለምን?” አለ መንገደኛው፡፡
“እስካሁን በልብህ ላሟን ይዘህ የምትዞር አንተ ነህ!” አለው፡፡
*   *   *
በአካል የሠረቀው ሌባ ሲባንን ይኖራል፡፡ በልቡ ስርቆቱን የያዘው የባሰ ሌባ፣ ከሌባ እየተሻረከ ሳይነቃበት ይኖራል፡፡ ይህ የሚሆንበት አገር ለከፍተኛ ጥፋት የተጋለጠ ነው፡፡ ቀና የሚመስለው መንገድ ሁሉ ዕውን ቀና ነወይ? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ የምንገለገልባቸውን ቃላት እንመርምር።
እንደ “ነፃነት”፣ “አማራጭ” እና “ዕድሎች” ያሉ ቃላት ከሚሰጡት ዕሙናዊ ጥቅም የበለጠ ቀስቃሽ ኃይል አላቸው፡፡ በተግባር ግን ገበያ ቦታ፣ በምርጫ ጊዜ እና በሥራ ቦታ አማራጭ ያለን የሚመስሉን “ሀ” እና “ለ”፤ ሌሎቹን ሆህያት ተትተው የተሰጡን ናቸው፤” ይላል ሮበርት ግሪን፡፡
አንድ መሠረታዊ የገዢዎች መርህ አለ፡-
“የመጨረሻው ምርጥ የማጭበርበሪያ ዘዴ፤ ለባላንጣህ አማራጭ የሰጠኸው ማስመሰል ነው። ያኔ ያንተ ሰለባዎች ጉዳዩን የተቆጣጠሩ እየመሰላቸው አሻንጉሊትህ ይሆናሉ፡፡ ከሁለት እኩይ ነገሮች አንዱን እንዲመርጡ አድርጋቸው፡፡ (Choosing between two evils) ሆኖም ሁለቱም አንተን የሚጠቅሙ እንዲሆኑ ማድረግ ነው ዋናው ጥበብ፡፡” (ሮበርት ግሪን)
አማራጮችን አስፍቶ ያለማየት ድህነት፣ አንዱ የድህነታችን ምንጭ ነው፡፡ ይሄ አንድም ከዕውቀትና አቅም ማነስ፣ አንድም አርቆ የማስተዋል ባህል ከማጣት፣ አንድም ደግሞ በአፍንጫ ሥር ዕይታ ከመወጠር ሊከሰት ይችላል፡፡ ከታጠርንበት አጥር ባሻገር ማየት መልካም ነገር ነው። “ይቺን ያቀድኳትን በስኬት ከተወጣሁ” አመቱን እሰየው ብዬ ጨረስኩ፤” ማለት ሌላ እንዳናይ ሊገድበን የሚችል አካሄድ መሆኑን ልብ እንበል፡፡ በአጭር ርዕይ ታቅበን ጊዜ ያመልጣል፡፡ በጀማ ጉዞ ከጀማው ጋር ከማዝገም በላቀ ንቃተ ህሊና መፈትለክ የሚያሻበት ጊዜ ነው፡፡
አንድ ህፃን ልጅ፤ “ወደፊት ምን ለመሆን ታስባለህ?” ተባለ አሉ ዘንድሮ፡፡
ልጁም፤ “ዲያስፖራ!” አለ፡፡ (ስለዲያስፖራ ስንናገር ትውልድን እናስብ!)
ዳያስፖራ ማለት፤ አንድ ተሰብስቦ፣ በአንድ ቦታ ተቀምጦ የነበረ ህዝብ ወይም ቋንቋ አሊያም ባህል፤ ሲበተን ወይም ወደሌላ ሲሰራጭ የሚሰጠው መጠሪያ ነው፡፡ አይሁዳውያን ከእሥራኤል ውጪ የተበተኑበትንም ሁኔታ የሚያመላክት ነውም ይላሉ፡፡ እንግዲህ ለኢትዮጵያውያንም እንደዚያው ነው፡፡
ኢትዮጵያ የውጪውን ዓለም ኢትዮጵያውያን መሰብሰቧ ደግ ነገር ነው፡፡ አያያዟ ምን ያህል ከኢኮኖሚዋ፣ ከፖለቲካዋ፣ ከዲፕሎማሲዋና ከባህሏ ጋር መስተጋብር ይኖረዋል? ዳያስፖራውያኑስ ምን ያህል ከልባቸው መጥተዋል? ተስፋቸው፣ ምኞታቸው፣ የሀገር ፍቅር ስሜታቸው ምን ያህል የጠለቀ፣ ምን ያህልስ ከጥቅም ባሻገር አገርና ህዝብን ያግዛል? የሚለው የነገ ጥያቄ ነው፡፡ እግረ መንገዳችንን፤ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤ “ሰው ሆኖ ካሹት (ከፈተጉት) ጥቅም የማይሰጥ የለም” ያለውን ልብ ማለት ይጠቅማል፡፡
እንግዲህ መንገዱ ረጅም ነው፡፡ ከካሬ ሜትር እስከ ልብ ሜትር የሚያለካካ ነው! ማናቸውም ነገር አልጋ በአልጋ አለመሆኑን መገንዘብ ደግ ነው፡፡ ህጋዊውን፣ ቢሮክራሲያዊውንና ሰዋዊውን መንገድ በቀቢፀ - ተስፋ ለማያይ ሰው፣ ሁነኛና ቀና ብርሃን ሊያስተውልበት የሚችል ሁኔታ አለ። በተወሰነ ደረጃ ግን ሂደቱን ሊያሰናክሉ፣ ሊያቀጭጩና ሊያሟሽሹ የሚችሉ እንከኖች ይኖራሉ? ብሎ አለመጠበቅ ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ “ብላ ያለው ተጋግሮ ይጠብቀዋል፤ ተሸከም ያለው ታሥሮ ይጠብቀዋል” የሚለው ተረት መሠረታዊ፣ አገራዊ ፋይዳ የሚኖረው እዚህ ላይ ነው!  

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Saturday, 15 August 2015 15:57

የ3007 ዓ.ም ትውልድ ትርክት

(ደባኪ -ጋፋት - ጉባ)

   አንድ ሰው ‹‹የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ›› ሲል፤ ለመግለፅ የፈለገው የኢትዮጵያን የቅርብ ዘመን ታሪክ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ትኩረቱ ከአፄ ቴዎድሮስ ወዲህ ባለው የሐገሪቱ ታሪክ መሆኑ ይገባናል፡፡ ከዚህ ያለፈ ትርጉም ሊኖረው አይችልም። ግን ‹‹ዘመናዊ ታሪክ›› (Modern History) የሚል ነገር በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በጣም የተሳሳተ መልዕክት የሚሰጥ ሐረግ ነው፡፡ ይሁንና ቃሉ ከአገልግሎት አልተሻረም፡፡
ለምሣሌ፤ ከአንድ ሺህ ዓመት በኋላ የሚመጡ የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪዎች፤ እንኳን በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን የተፈፀመን ጉዳይ በ2007 ዓ.ም የተከሰተውን ድርጊትም በዘመናዊ ታሪክ ክፍል ሊያካትቱት አይችሉም፡፡ በ3007 ዓ.ም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ ገና ታሪክ ለመሆን ያልበቁትን የ2007 ሐገራዊ ምርጫ እና የኦባማን ጉብኝት፤ ‹‹እጅግ ጥንታዊ ታሪክ›› በሚል ይጠቅሱት ይሆናል እንጂ - ለመጠቀስ የሚያበቃ ፋይዳ ይዞ ከታያቸው- ዘመናዊ ታሪክ አይሉትም፡፡ ዛሬ ገና የታሪክ ማዕረግ ያላገኙትን (ከፖለቲካ መዝገብ ያልተፋቁትን) እነዚህን የ2007 ክንውኖች፤ እንኳን በዘመናዊ ታሪክ በጥንታዊ ምዕራፍም ሊያካትቷቸው አይችሉም፡፡ ‹‹ዘመናዊ ታሪክ›› (Modern History) የሚለው ገለፃ አስቸጋሪ የሚሆነው በዚህ የተነሳ ነው፡፡
እንዲያውም በ3007 ዓ.ም፤ ምናልባት ራሱ ታሪክ የሚባል ፅንሰ ሐሳብ ሊጠፋ ይችላል፡፡ የታሪክ ፀሐፊ የሚል የሙያ ዘርፍም ሊከስም ይችላል፡፡ ዛሬ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ግስጋሴ፤ የቦታን ገዳቢነት እንዳጠፋው፤ የጥንቱን እጅግ ሰፊ ዓለም አንድ መንደር እንዳደረገው ሁሉ፤ በተመሳሳይ የጊዜን ገዳቢነት አፍርሶ፤ ዛሬ፣ ትናንት እና ነገ የሚባሉ የጊዜ አውታሮች ሊያጠፋቸው ይችላል። ስለዚህ፤ የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን፤ ‹‹ቢጫ›› ቀለም በተቀቡ የጊዜ ታክሲዎች ተሳፍረው፤ በጊዜ ጎዳና እየከነፉ ወደፊት እና ወደ ኋላ ለመሄድ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ‹‹ደመና›› ጠቅሰው፤ ከዛሬ ወደ ነገ ወይም ወደ ትናንት ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን፤ ሰባት (?) የቅዱስነት ማዕረጋት ውስጥ በአንዱ ቅዱሳን የቦታንና የጊዜን አጥር በማፍረስ፣ እንደ እግረ ፀሐይ በአንድ ጊዜ ብዙ ቦታዎች የመገኘትና ደመና ጠቅሶ የመጓዝ ብቃት የሚያገኙ ቅዱሳን እንዳሉ ይተረካል፡፡ በ3007 ዓ.ም ቴክኖሎጂ ይህን ችሎታ ሊፈጥር ይችል ይሆናል፡፡
የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን፤ ‹‹ለጉብኝት ወደ 2007 ዓ.ም እንሂድ›› ለማለት የሚችሉ ስልጡኖች ይሆኑ ይሆናል። ምናልባት፤ ታሪክን ከዲጂታል ገፆች ወይም ከወረቀት በማንብብ ሳይሆን፤ ‹‹መሚፋይድ›› የሆኑ (በሬሳ ማድረቂያ የደረቁ) የታሪክ ክስተቶችን በዓይን ማየት የሚቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ምናልባትም ‹‹ሃሎ ሲኦል፣ ሃሎ ገነት ወይም ሃሎ ሰማይ ቤት›› እያሉ መደወል የሚችሉ ይሆናል፡፡ ይህ የስብሃትን ሀተታ- ኮምቡጡር ይመስል ይሆናል፡፡ ግን በዚህ ትውልድ ዕድሜ ስንት ነገር አየን፡፡
ሆኖም፤ የነገሮች መሠረታዊ ይዘት ብዙ ሳይቀየር በአሁኑ መልክ ከቀጠለ፤ በ3007 ዓ.ም የሚኖር አንድ ጋዜጠኛ፤ የኛን ዘመን ኢትዮጵያውያን ከቀደሙትና ከእኛ በኋላ ከሚመጡት በርካታ ትውልዶች ለይቶ መጥቀስ ከፈለገ፤ በእነሱ ዓይን ወይም ሚዛን እርባና ያለው ሥራ ካለን፣ የኛን ዘመን ታሪክ ሲጠቅስ - ‹‹በጥንታዊ ታሪክ›› እያለ ነው፡፡
የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ፤ ‹‹በምርጫ 97 ቅንጅትና ኢህአዴግ ባካሄዱት ክርክር የተሻለ ነጥብ ያስመዘገበው ማነው? ምርጫው ተጭበርብሯል አልተጭበረበረም?›› የሚል ነገር በፍፁም አጀንዳ አድርጎ አያነሳም፡፡ ሌላው ቀርቶ፤ ደርግን ከስልጣን ያባረረው ኢህአዴግ ይሁን ቅንጅት ለመለየት ይቸገራል። ዛሬ ሰይፍ የሚያማዝዙ የፖለቲካ ጉዳዮች በመጭው ዘመን እይታ የጅሎች ንትርክ መስለው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን (ኢትዮጵያዊ፣ አሜሪካዊ ወዘተ የሚባል ነገር ትርጉም የሚሰጥ ከሆነ) ውሎ አድሮ ታሪክ የሚሆነውን የዛሬውን ዘመን ድርጊት በዝርዝር ሊያስታውሱት አይችሉም። እኛ የአንደኛውን ሺ ዓመት (ሚሊኒየም) ‹‹ከታላቅነት ማማ ወርድን በድህነትና ኋላቀርነት መርመጠመጥ የጀመርንበት ዘመን›› ብለን በጥቅል እንደ ጠቀስነው፤ በጥቅል ይጠቅሱን ይሆናል፡፡
እናም፤ በእነሱ ዓይን ወይም ሚዛን፣የእኛ ትውልድ እርባና ያለው ሥራ ሊጠቀስ የሚችለው #ከረጅም ዘመናት ውድቀት በኋላ የተስፋ ዘር መዝራት የቻለ ትውልድ” በሚል ይመስለኛል፡፡ ነገሩ ይመስለኛል ነው። በእርግጠኝነት ለመናገር የማይቻል ጉዳይ መሆኑ ሳይዘነጋ፤ ጋዜጠኛው ‹‹ለረጅም ዘመናት ቁልቁል ስንወርድ ከቆየን በኋላ፤ እንደገና መነሳት የጀመርነው፤ በሦስተኛው ሚሊኒየም መጀመሪያ በነበረው ትውልድ ነው›› በሚል ያስታውሰን ይሆናል፡፡ መቼም፤ የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን የእኛን ትውልድ በዚህ ዓይነት ጥቅል ነገር ካስታወሱን ዕድለኞች ነን፡፡ በተረፈ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ወይም በኃይለማርያም ደሳለኝና በመንግስቱ ኃይለማርያም መካከል ልዩነት አይመለከቱም ብቻ ሣይሆን ልዩነት የማየት ፍላጎትም ጨርሶ አይኖራቸውም ማለት ይቻላል፡፡
በ3007 ዓ.ም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ታሪክ ፀሐፊ የሚኖር ከሆነ፤ ይህ ታሪክ ፀሐፊ፤ ‹‹ለበርካታ ዓመታት የአባይን ወንዝ ለማልማት የሚያስችሉ የተለያዩ ጥናቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም፤ ብዙዎቹ ከሸልፍ ላይ ተጥለው አቧራ ሲጠጡ ከርመዋል፡፡ የአባይን ወንዝ የማልማት ዕቅድ ሁሌም ከውጭ ዕርዳታ ጋር ተያይዞ የሚታሰብ በመሆኑ፤ ዕርዳታ ፍለጋ ስንወጣ፤ ዘወትር ሐሳባችንን በእንጭጩ የሚጨፈለቅና የሚቀጭ ምላሽ እየገጠመን፤ ከኛው ሐገር መንጭቶ በበራችን ከሚፈሰው የአባይ ወንዝ አንዲት ጠብታ ውሃ መንካት ሳንችል ቆይተናል፡፡ ግብፅ፤ ‹ከአባይ ውሃ አንዲት ጠብታ ውሃ መንካት አትችሉም› በሚል እያስፈራራችን፤ እንዲህ ዓይነት መራራ በደል ተሸክመን በመኖራችን ከፍተኛ የመንፈስ ስብራት ደርሶብን ነበር፡፡ ሰፊ ለም መሬትና የውሃ ሐብት ይዘን፤ በተደጋጋሚ በረሃብ ማለቃችንና በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች እየተራቡ በዓለም ህዝብ ፊት ለልመና መቆማችን ከፍተኛ የመንፈስ ስብራት ፈጥሮብን ነበር፡፡ ስለዚህ የ‹መቻል› ሳይሆን ‹ያለመቻል› መንፈስ ነግሶብን ቆየን፤ ድህነት እንደ በሬ ቀንበር ጭኖ፣ እንደ ባሪያ ቋንጃችንን ሰብሮ ሲገዛን ኖሯል›› ብሎ ሊጽፍ ይችላል፡፡  
ጠፈርተኞች፤በህዋ ሆነው ምድርን ሲመለከቱ፤ረጅሙ የቻይና ግንብ ይታያቸዋል ይላሉ፡፡ እናም፤ በ3007 ዓ.ም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ኋላ ሲመለከቱ ጎልቶ ሊታያቸው ከሚችሉ ነገሮች አንዱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ ላይ ቆሜ ስመለከተው፤ እንደኛ ያለ ታሪክ ላለው ህዝብ፤ እንደ ታላቁ የህዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ ያለ ግዙፍ ፕሮጀክት በራስ አቅም ለመስራት መነሳት ትልቅ ሥራ ነው፡፡
እኛ ታላቁ የህዳሴን ግድብ ለመገንባት መነሳታችን፤ የበራ ሻማን እፍ ብሎ ማጥፋት ይሳነው የነበረ ሰው፤ተራራን ገፍቶ ለመጣል ሲነሳ ከማየት ጋር ሊነፃፀር የሚችል የለውጥ ኃይል ያጀበው ድርጊት ነው፡፡ ለብዙ ዘመናት እንደ በሬው በዝማም ሸብቦ ከያዘን ‹‹የአይቻልም መንፈስ›› መፈታት ነው፡፡ ስለዚህ፤ የህዳሴውን ግድብ ያለ ውጭ ዕርዳታ ሰርቶ ማጠናቀቅ ሳይሆን ‹‹ግድቡን ራሳችን እንገነባዋለን›› ብሎ ከመነሳት የሚልቅ ተዓምራዊ ተግባር ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ከሞት መነሳት እንጂ፤ከተነሱ በኋላ መራመድ ተአምር ሊሆን አይችልም፡፡
የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን፤ የህዳሴው ግድብ የፈጠረው የመንፈስ ብርሃን ጎልቶ ይታያቸው ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ እንዲያውም፤ ከኢትዮጵያ ድንበርና ከዚህ ዘመን አጥር ተሻግሮ፤ በተከታታይ ብዙ ትውልዶች ልብ ውስጥ ደምቆ ሊያበራ የሚችል ብርሃን ነው፡፡ የአፍሪካ ህዳሴ ፋና ለመሆን የሚችል አህጉራዊ ክስተት ነው፡፡    
የህዳሴው ግድብ፤ አፍሪካን በበታችነት መንፈስ ቀይዶ ለማኖር፣ ቀፍድዶ ለመያዝ ሲባል በመሰሪ ጥበብ ከተሸረበው ሰንሰለት በማውጣት እግረ-መንፈሳችንን፤ ከቅኝ ግዛት እግረ ሙቅ የሚያላቅቅና ካቴናን አውልቆ የሚጥል የአርነት መንፈስ ነው፡፡ የህዳሴው ግድብ ለአፍሪካውያን የሚሰጣቸው ትርጉም ምን እንደሆነ ለመረዳት፤ ጉባ በመሄድ ግድቡን የጎብኙ አፍሪካውያንን ቃል ልብ ብሎ ማድመጥ ብቻ በቂ ነው፡፡
ሰምታችኋቸው ከሆነ፤ የዛሬ ሁለት ዓመት ለጉብኝት ወደ ጉባ የሄዱ የአፍሪካ ሐገራት ወታደራዊ መኮንኖች፤ እንደ ማንኛውም ጎብኚ ያለውን ሁኔታ ከተመለከቱ በኋላ፤ ‹‹በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ጥሩ ሥራ ሠርታችኋል። ከገመትኩት በላይ ነው›› በማለት ነገር አዳንቆ ከመመለስ አለፍ ብለው፤ ለፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ለኢንጅነር ስመኘው ሽልማት ሲያበረክቱ አይተናል፡፡ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ወታደራዊ መኮንኖች መካከል፤ የዛምቢያው መኮንን፤ ‹‹ታላቁ የህዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ፤አፍሪካ ያለ ውጭ ዕርዳታ በራሳቸው አቅም ምን መስራት እንደሚችሉ አሳይቶናል›› ሲሉ የተናገሩት ቃል፤ግድቡ ለአፍሪካውያን የሚሰጣቸውን ትርጉም በትክክል የሚያመለክት ይመስለኛል፡፡
አፍሪካውያን ከምዕራብ የዕርዳታ አንቀልባ ወርደው በራሳቸው እግር ለመቆም ሲሞክሩ የታየበት፤የቅኝ ግዛት ኮተትና ግሳንግስ ተሽቀንጥሮ ሲጣል ያየንበት፣ኢ-ፍትሃዊ ሰንኮፍ በይቻላል መንፈስ የተነቀለበት፣ክፍለ - አህጉራዊ የትብብር ማዕከል ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ግድብ መሆኑን እያየን ነው፡፡ የሱዳኑ አምባሳደር ግድቡን ከጎበኙ በኋላ፤ ‹‹ይህ ግድብ የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤የአፍሪካ አህጉር ግድብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ፤ ለዓለም ጭምር የሚጠቅም ሥራ እየሰራች ነው›› ሲሉ መናገራቸው ለዚህ አብነት ነው፡፡ ስለዚህ የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ይህን ትውልድ በዚህ ያስታውሱት ይሆናል የሚል ግምት አለኝ፡፡
ጉዞ ጀምረናል
‹‹ጀምረናል ጉዞ ጀምረናል፤ወደ ኋላ ማን ይመልሰናል›› የሚለው ህብረ - ዝማሬ፤ የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውንን ልብ ላያሞቅ ይችላል፡፡ ሆኖም፤የሕዳሴው ግድብ በአባይ ተፋሰስ ሊገነቡ ከሚችሉት ግድቦች ውስጥ ትልቁ ግድብ በመሆኑ፤መጭው ትውልድ ከታላቁ ህዳሴ የሚበልጥ ግድብ በዚህ ተፋሰስ ሊሰራ እንደማይችል እናውቃለን። ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፤ የህዳሴው ግድብ ለመጪዎቹ 400 ዓመታት ሊያገለግል የሚችል ግድብ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ የኛ ትውልድ፤ ወደፊት የሚመጡ ተከታታይ ትውልዶች በልዩ አድናቆት የሚመለከቱት ሥራ እየሰራ መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ ይህ ትውልድ፤ ሐገሪቱን ከአንድ ሺህ ለሚበልጥ ዓመታት ቁልቁል እያወረዳት፤ እንደ ሲዖል አዘቅት ያለ ማቋረጥ እየዋጣት፣ ከተስፋ መቁረጥ ጠርዝ ከጣላትና በተሸናፊነት መንፈስ ከከፈናት የውርደት ጉዞ እንድትወጣ የሚያግዝ ሥራ እየሰራ ያለ ጀግና ትውልድ ይመስለኛል፡፡ የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን፤ ‹‹ለራስ ሲቆርሱ…›› ብለው ሊቀልዱብኝ ይላሉ፡፡ ግን እንደዚህ ማሰቤን መደበቅ አልሻም፡፡  
ስለዚህ፤ ጉባ የምትገኘው የግድቡን ግንባታ ያበሰረችው የመሠረት ድንጋይ ብዙ ትውልዶች በአድናቆት የሚመለከቷት ድንጋይ ትሆናለች፡፡ በእርግጥ፤ የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ፤ ‹‹ለእኔ ይህች ድንጋይ የውርደት ካባን ማራገፍ የጀመርንባት ድንጋይ ነች›› ሲሉ መናገራቸውን የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ላያስታውሱ ይችላሉ፡፡ ሆኖም፤ ዛሬ ላይ ቆሞ ለሚያይ ሰው፤ጉባ በክብር የተቀመጠችው ያቺ ድንጋይ፤ ተራ የፕሮቶኮል ጌጥ ወይም የተለመደ የማስታወሻ ድንጋይ መስላ አትታየኝም። ለአንድ የታሪክ ምዕራፍ፤እልባት ሆና የተቀመጠች ልዩና ክቡር ድንጋይ ነች፡፡ ከዚያች ድንጋይ በይፋ መቀመጥ በፊትና በኋላ ነገሮች በእጅጉ ተቀያይረዋል። እኛ ስለ ራሳችን ያለን ግምት ብቻ ሣይሆን ዓለም ስለኛ ያለው ግምትም ተለውጧል፡፡   
በዚህ በእኔ ስሌት፤ ትልቅ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ታሪክ ሊሆን የሚችለው ታላቁ የህዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ እየተሰራ ያለው፤ የውርደትን መራራ ጽዋ ሲጨልጥ በቆየ፤ረሃብን፣ ድህነትን፣ ስደትን እስኪበቃው በተጋተ፤በመጥፎ የታሪክ ሸክም ጎብጦ፤ ቅስሙ ክፉኛ በተሰበረ የኛ ትውልድ ነው፡፡ ከመከራ አዘቅት ወጥቶ ይህን ገድል የሰራው፤ ኑሮ በሞላለት ወይም በልቶ በተረፈው ትውልድ ሳይሆን፤ገና በልቶ መጥገብ ባልጀመረ ትውልድ በመሆኑ፤ለ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ልዩ ትርጉም ይሰጣቸው ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ትውልድ፤ ከፊተኛው ትውልድ ድህነትን ተቀብሎ፤ከእርሱ በኋላ ለሚመጡ ትውልዶች ብልፅግናን አውርሶ የሚያልፍ  ከሆነ፤ በእርግጥ በመጭው ትውልድ በክብር ይታወሳል፡፡
ያለፉ አራት መቶ ዓመታት የኢትዮጵያ ታሪክን በወፍ በረር ቃኝተህ፤ ከቅኝትህ የተገነዘብከውን የታሪክ ሐቅ አስፍር ብባል፤ ኢትዮጵያን እጅ ከወርች አስረው ያሰቃይዋት፣ የግሪንግሪት ጥለው የረጋገጧት ሁለት ዋነኛ ችግሮችን ተናገር ቢሉኝ፤ ‹‹የሀገራችን ሁለት ሠይጣን ችግሮች፤ ሐይማኖትንና ‹ጠቅላይ ግዛትን› ሰበብ አድርገው የሚለኮሱ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ወይም ግጭቶች፤ እና የውጭ ወራሪ ኃይሎች ቀጥተኛ ጥቃትና ዘወርዋራ ሸፍጥ ናቸው›› እላለሁ፡፡ እነዚህ ሁለት ቀያይ ሰይጣኖች ወይም ችግሮች፤ ለድህነትና ለኋላ ቀርነት አሳልፈው ሰጡን፤ ድህነትና ኋላ ቀርነት መልሰው ለሌሎች በርካታ ችግሮች አቀባበሉን፡፡ ቅብብሎሹ ያለ ማቋረጥ ቀጥሎ እዚህ ደርሰናል፡፡ በዚህ ትውልድ ይገታል ወይስ….? የሚለው ለትንቢት የማይመች ጉዳይ ነው፡፡ ግን ተስፋ እንዳለን አምናለሁ፡፡
እርግጥ፤ያለፉ ተከታታይ ትውልዶች፤ ደምና አጥንታቸውን ገብረው፤ ውድ የሐገር ነፃነት ቅርስ አስረክበውናል፡፡ ድሃና ኋላ ቀር ብንሆንም፤ ነፃነቷ የተከበረ ሐገር አውርሰውን አልፈዋል፡፡ የአፍሪካ የነፃነት ፋና፣ የፀረ - ቅኝ አገዛዝ ትግል ቀንዲል የሆነች፤ ለጥቁር ህዝቦች ትግል የመንፈስ ኃይል በመሆን ታላቅ ከበሬታ የሚሰጣት ሐገር ሰጥተውናል፡፡
ኢትዮጵያ፤ኋላ ቀርነት የተጫናት፣ድህነት ያደቀቃት፣ የእርስ በእርስ ጦርነት ያደከማት፣ የተረጋጋ የመንግስት አስተዳደር መመስረት የተሳናት ሐገር ሆና፤ የቅኝ አገዛዝ ኃይሎች እንደ ተራበ አውሬ በዙሪያዋ ሲያንዣብቡ፤ እንደ ተኩላ መንጋ ዘለው ሊሰፍሩባት ሲያደቡ ቢቆዩም ነፃነቷን አስከብራ ኖራለች፡፡ ግን ኋላቀርነትና ድህነት እንደ ረግጠው ገዝተውናል፡፡በእኔ አስተያየት፤ሐገሪቱን ለጠላት ተጋላጭ የሚያደርጋት፤ኋላ ቀርነት መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነዘቡ ኢትዮጵያዊ መሪ አፄ ቴዎድሮስ ናቸው። አፄ ቴዎድሮስ፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የመቀጠሏ ጉዳይ አደጋ እንደተጋረጠበት ገብቷቸዋል፡፡ በየአካባቢው ሥልጣን በያዙና እርስ በእርስ በሚቀናቀኑ መሳፍንት የተከፋፈለችውን ሐገር በጦርነት አንድ ለማድረግ ሲሞክሩ፤ አደጋው ታይቷቸው ነበር፡፡
ቋራ በሚገኝ አንድ ገዳም ውስጥ ትምህርቱን ሲከታተል የነበረው ትንሹ ቴዎድሮስ (ካሣ ኃይሉ)፤ጥቂት ተከታዮችን ይዞ፤ የጎበዝ አለቃ ሆኖ የታሪክ ጉዞውን ጀመረ፡፡ ከሌሎች አቻ የአካባቢ መሳፍንት በተለየ አስተሳሰብ እየተመራ፤ ለተጠቁ አለኝታ የመሆንና ለፍትህ የመቆም ዝንባሌን እያሳየ፤ እያደርም ተከታዮቹን እያበዛ  የመጣው ካሣ ኃይሉ፤ የኢትዮጵያን ድንበር ገፍቶ፤ሱዳንን በኃይል በመያዝ በሐገሪቱ አገዛዙን ከመሠረተው የግብፁ ገዢ መሐመድ ዓሊ ጋር ‹‹ደባኪ›› በተባለች ሥፍራ ጦርነት ገጠመ፡፡ ‹‹ደባኪ›› ላይ አስቦትና ገምቶት የማያውቅ ሽንፈት ደረሰበት፡፡ አንዳንድ የታሪክ ፀሐፊዎች፤ ‹‹በአፄ ቴዎድሮስ ህሊና ለሥልጣኔ የመጓጓት ልዩ ስሜት እንዲፈጠር ያደረገው፤ የደባኪ ጦርነት ነው›› ይላሉ፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ልዩ የመሪነት ሰብዕና እና ብቃት የተገለጠው በዚሁ ጦርነት መሆኑንም ይመሰክራሉ። ካሣ ኃይሉ፤ ‹‹ድባኪ››  ላይ ከግብፁ መሐመድ ዓሊ ጋር ጦርነት ገጥሞ  ክፉ ሽንፈት ሲገጥመው፤ ሽንፈቱን ሳያቅማማ ተቀብሎ፤የሽንፈቱ ምንጭ ምን እንደሆነ ለመረዳት መቻሉን በማድነቅ፤የመሪነት ብቃቱ የተገለጠበት የመጀመሪያው አጋጣሚም ይኸው መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ የታላቅ መሪነት መገለጫ ጠባዩ፤ሽንፈቱን መቀበሉና የሽንፈቱን ምንጭ ለይቶ ችግሩን ለማስወገድ ጥረት ማድረጉ ነው፡፡
የታሪክ ፀሐፊዎች እንደሚሉት፤ ካሣ ኃይሉ በህይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ያየው፤ ደባኪ ላይ በተካሄደው ጦርነት ነበር፡፡ የቋራው ካሳ እንደ አንበሳ የሚያስፈሩ ጋሜዎቹን አሳልፎ፤ ከመሐመድ ዓሊ ጋር ደባኪ ጦርነት በገጠመ ጊዜ፤ ከዚያ ቀደም አይቶት የማያውቀው የመድፍ ቅምቡላ እያስገመገመና እየተምዘገዘገ መጥቶ መሬት - ሰማዩን ሲደበላልቀው ተመለከተ፡፡ ጦርነቱን፤ በልበ ሙሉ ወታደሮቹ ጀግንነት የሚዘልቀው መሆኑ ገባው። ደባኪ ላይ ጦርነት የገጠሙት፤ ጥበብና ድንቁርና ነበሩ፡፡
ሻምላቸውን አገንድረው፤ በጀግንነት ገድሎ መሞትን እንጂ፤ ንግድ የሚባል ነገር የማያውቀውት እኒያ የጃፓን የጦር አበጋዞች፤ ይህን ወግ አፍርሶ፤ ከጀርመኖች ጥበቡን ቀስሞ ቢራ ሲነግድ ያገኙትን አንድ ዘመዳቸውን ሲወቅሱ፤ ‹‹ልጄ የአባቶችህን ወግ ትተህ፤ ሻምላ አገንድሮ በጀግንነት መሰለፉን እንደ ከንቱ ነገር ወዲያ ጥለህ፤ ቢራ ጠማቂ ትሆን?›› በሚል ሲወቅሱት፤ ‹‹አጎቴ ተሳስተሃል፡፡ የዘንድሮ ሻምላ እንደ ድሮው፤ አየሩን ሲቀዝፍ ጆሮ የሚበጥሰውን የጃፓኖችን ዘመን ሻምላ ይዞ መገኘት አይደለም፡፡ የዚህ ዘመን ጀግንነት፤ ዶላር ይዞ መገኘት ነው›› እንዳለው፤ ካሣ ኃይሉ በደባኪ (Dabaki) አውድ ግንባር፤  ዋናው ነገር ጥበብ እንጂ ባዶ ጀግንነት እንዳልሆነ ተረዳ፡፡ የደባኪ ትምህርት ዕድሜ ዘመኑን ሁሉ  እረፍት ነስታ ጥበብን ፍለጋ እንዲባዝን አደረገችው፡፡ በመጨረሻ፤ ለሞት የሚያበቃ ስህተት አሰራችው፡፡
ያቺ ‹‹የአባቶቼ ሀገር›› እያለ ይጠራት የነበረችው ኢትዮጵያ፤ ዘመናዊ ዕውቀትን ወይም የጦር መሣሪያን ካልታጠቀች፤ በዙሪያዋ ከሚያገሱት የተራቡ አውሬዎች አንዱ መጥቶ እንደሚሰለቅጣት፤ የጦር መሣሪያ ‹‹ሀሁ›› የተማረባት ዳባኪ ነግራዋለች፡፡ ስለዚህ የጦር ኃይሉን ለማዘመን፣ የመንግስትን አስተዳደር ለማፅናት፣ ወሳኝ አድርጎ የሚመለከተውን ጥበብ ለመቅሰም ተጋ፡፡
በዚሁ ሰበብ ከታላቋ ብሪታንያ ጋር ለመቀያየም በቃ፡፡ ‹‹የእጅ ሙያ የሚያሰለጥን ሰው ላኩልኝ›› እያለ በወዳጅነት ሲጠይቅ ቆይቶ፤ አልሆን ሲለው፤ በግሉ ሙያተኞች አውሮፓውያን እንዲያመጡላት በወዳጆቹ በኩል (በግል) ሙከራ አድርጎ አልሳካ ሲለው፤ ለስብከት ከመጡት  አውሮፓውያን መካከል መርጦ፤ ጋፋት ላይ ጥበብን በኢትዮጵያ ሊያላምድ ሞከረ፡፡ በመንገድና  በብረታ ብረት ወዘተ ሥራ የሚያግዙትን እያከበረ፤ ሰባኪ ነኝ ባዮቹን ሰሜን ‹‹ያና›› እንዲቀመጡ አድርጎ የቻለውን አደረገ፡፡ በመጨረሻም፤ እየወሻከቱ፤ እንዳሰበው አልሆን ሲሉት እና እንግሊዝ ለላከው ደብዳቤ ምላሽ ስትነፍገው፤ ሰባኪ ነን ባዮቹን እና ቆንስላዎቹን ጠራርጎ እስር ቤት አስገባቸው፡፡
በዚህ ዘመን፤ ለእኛ ምሣሌ መሆን የሚችሉ ቦታዎችን እናገኛለን፡፡ ‹‹የና›› እና ‹‹ጋፋት››፡፡ ‹‹የና›› እና ‹‹ጋፋት›› የቴዎድሮስን ሁለት ፈተናዎች መወከል የሚችሉትን ያህል፤ ለዛሬው ዘመን ትውልድ ኑሮ ምሣሌ የመሆን ልዩ ትርጉም አላቸው፡፡ ‹‹ጋፋት›› የጥበብ መንደር ነች። ‹‹የና›› ደግሞ የሐይማኖት፡፡ ‹‹የና›› በአፄ ቴዎድሮስ ፈቃድ ያገኙ ሚሲዮናውያን፤ ለቤተ እስራኤሉ ሐይማኖት የሚሰበክባት (ክርስትና) ምድር ናት፡፡ ‹‹የና›› እና ‹‹ጋፋት›› በተምሳሌትነት፤ የዚህ የኛን ትውልድ ፈተናም ሊገልጡ ይችላሉ፡፡ ትንታኔ የሚያስፈልገው አልመሰለኝም፡፡ ሆኖም፤ የኛ ትውልድም በ‹‹የና›› እና ‹‹ጋፋት›› ሊጠቀስ የሚችል ፈተና እንደተጋረጠበት አምናለሁ፡፡
ሐገሪቱ ሳይወራረድ የዘለቀ የታሪክ ዕዳ ተሸክማ፣ የዜጎችን ነፃነት የሚያከብር አስተዳደር አጥታ፤ ከቴዎድሮስ ዘመን እየተጎተተ የመጣ ያልተመለሰ ጥያቄ እንደሰቀዘ ይዞ ከ1983 ዓ.ም አደረሳት፡፡ በ1983 እንደ ቴዎድሮስ ዘመን የመበታተን አደጋ ላይ ነበረች፡፡ ህገ መንግስታዊና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በመዘርጋት የእርስ በእርስ ጦርነት መነሻዎችን ማስታገስ ብትችልም፤ ኋላ ቀርነትና ድህነት አጉብጦ ሊገድላት አንድ ሐሙስ የቀራትን ሐገር የተረከበው ይህ ትውልድ፤ባለተስፋ ሐገር መፍጠር መቻሉን የሚያውቀው የ3007 ዓ.ም ትውልድ ብቻ ይሆናል፡፡ በመጨረሻ፤ የጀመርነው ጉዞ ከተሳካላን የ3007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን፤ ድንቅ የዕድገት ጉዟቸውን ሲተርኩ፤ ከደባኪ ተነስተው፤ በጋፋት በኩል አድርገው፤ ጉባን በማጣቀስ፤ አፍሪካን የሚጨምር ትርክት ሊሰሩ የሚችሉ ይመስለኛል፡፡



በማኑፋከቸሪንግ፣ በሪል ኢስቴት፣ በመጠጥ ኢንዱስትሪ፣
በሆቴልና ሪዞርት፣ …. ተሰማርተዋል

   በርካታ ጐስቋሎች ደረታቸውን እየደቁ እምዬ! እያሉ በሚያሞካሿት፣ ብዙዎች በአፍሪካ ትልቁ የገበያ ማዕከል እያሉ በሚጠሯት መርካቶ በ1956 ዓ.ም ተወልደው አድገውባታል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኒው ኤራ፣ ሁለተኛ ደረጃ በያኔው ተፈሪ መኮንን በዛሬው እንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ት/ቤት ተማሩ፡፡
ደርግ፤ “አድሃሪ ነጋዴ፣ ሸቀጥ ደብቀሃል”…. በማለት ገደላቸው እንጂ አባታቸውም መርካቶ ውስጥ ታዋቂ ነጋዴ ነበሩ፡፡ አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ በልጅነታቸው በንግድ ባይሰማሩም ከነጋዴ ቤተሰብ መወለዳቸው፣ በትልቁና በዋናው የንግድ ማዕከል ማደጋቸውና ዛሬ በንግድ (ቢዝነስ) የደረሱበት ደረጃ ሲታይ ንግድ ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉበት ነው ብንል የሚበዛባቸው አይመስለኝም፡፡
የአቶ ሙሉጌታ አባት አቶ ተስፋኪሮስ፤ የቤተሰቡ ኃላፊና አስተዳዳሪ ነበሩ፡፡ እሳቸው ከተገደሉ በኋላ የቤተሰቡ ሁኔታ ጥሩ አልነበረም፡፡ ወቅቱ በኢሕአፓ ሰበብ ወጣት ሁሉ የሚታፈስበት፣ የሚታሰርበት፣ የሚገረፍበት የሚሰቃይበትና የሚገደልበት…ስለነበር እዚህ ሆኖ ለአደጋ ከመጋለጥ ለመሰደድ ወሰኑ። አንድ ወር በእግር ተጉዘውና ድንበር አቋርጠው ሱዳን ደረሱና በ1975 ዓ.ም አሜሪካ ገቡ፡፡
በአሜሪካ የመጀመሪያ እቅዳቸው ትምህርት ነበር፡፡ ነገር ግን እዚያ፣ የሚረዳህ ከሌለህ  ለኮሌጅ የሚጠየቀው ክፍያ ነዋሪዎቹ ከሚከፍሉት እጥፍ ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ስደተኛ አሜሪካ ሲገባ ለቀለብ፣ ለቤት ኪራይ፣ ለትራንስፖርት፣ ለኮሌጅ ክፍያ… መሥራት አለበት፡፡ አንድ ብቻ ሳይሆን ቢያንስ ሁለት ቦታ መሥራት ግዴታ ነው፡፡ አቶ ሙሉጌታ የተለያዩ ሥራዎች እየሠሩ ቆይተው ነው በሁለተኛው ዓመት ኮሌጅ የገቡት፡፡
የተገኘው ሁሉ አሸሸ ገዳሜ ከተባለበትና ከባከነ በአሜሪካ ሰው አይኮንም፡፡ እየተቸገሩም ቢሆን መቆጠብ የግድ ነው፡፡ እየቆጠቡ ቆይተው ጥሪት ከቋጠሩ በኋላ አሁን የራሴን ቢዝነስ ብጀርምስ? አሉ። የሚሠሩትን ነገር ማጥናት ጀመሩና የግል ክሊኒንግ ሰርቪስ ቢዝነስ ጀመሩ፡፡ ትልልቅ ድርጅቶችን ኮንትራት ወስደው የጽዳት አገልግሎት ይሰጡ ጀመር፡፡ በአንድ ወቅት የዓመት 70 እና 80ሺህ ዶላር የፅዳት ኮንትራት ነበራቸው፡፡
አገራቸው ገብተው መሥራት የሚያስችላቸው ሀብት ከቋጠሩ በኋላ በአገራቸው ልማት ለመሳተፍ ፈለጉ፡፡ ለምን ያለችኝን ይዤ አገሬ ገብቼ እንደ አቅሜ ኢንቨስት አላደርግም? ጥቂትም ቢሆኑ ለአገሬ ዜጐች የሥራ ዕድል ፈጥሬ፣ አገሬን ከድህነት ማጥ ለማውጣት በሚደረገው ጥረት የበኩሌን ሚና መጫወት አለብኝ አሉ፡፡ አሜሪካን ከመልቀቃቸው በፊት ሦስት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ተመላልሰው አገሪቷ ያለችበትን ሁኔታ አይተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ሁሉም ነገር የተመቻቸና የተደላደለ ባይሆንም በአገሪቷ ሰላም ስለሰፈነ መሥራት ይቻላል ብለው አሰቡ፡፡
የአገራችንን ችግሮች እኛው ዜጐቿ ተጋፍጠን ካላሻሻልናቸው የውጭ ዜጋ መጥቶ አያሻሽልልንም። ሁላችንም በጋራ በችግሮቹ እየተፈተንን፣ እየተማማርንና እየተማከርን ካልሆነ ችግሮቹ ምን ጊዜ አይቀረፉም፣ አይወገዱም፡፡ ሁሉም ነገር ይሟላ ብለን ከጠበቅን የአገራችን ለውጥና ዕድገት ረዥም ጊዜ ይፈጃል በማለት ንብረታቸውን ሸከፉ፡፡ ጊዜ ሳያባክኑ 13 ዓመት ከኖሩባት አሜሪካ የዛሬ 18 ዓመት በ1989 ዓ.ም ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡
አቶ ሙሉጌታ ወደ አገራቸው እንደተመለሱ የጀመሩት ቢዝነስ ከአሜሪካ ወረቀት ማስመጣት ነበር፡፡ ነገር ግን አሰራሩን ስላላወቁ እንዳሰቡት አልሆነም - አከሰራቸው፡፡ እሱን ትተው ወደ ማኑፋክቸሪንግ መግባት ፈለጉ፡፡ መሳሪያውን ከቻይና በ2 ሚሊዮን ብር ያህል ገዝተው በአዲስ አበባ የዱቄት ፋብሪካ ተከሉ፡፡ ጥናት ሳያካሂዱ፣ መብራትና ገበያ በሌለበት አካባቢ ስለተከሉ ይኼኛውም እንደ በፊቱ አልተሳካም፤ አከሰራቸው፡፡
ኢንቨስተሩ ተስፋ ቆርጠው ወደ ለመድኳት አሜሪካ ልመለስ አላሉም፡፡ ይልቁንስ በቢዝነስ ዓለም ማግኘትና ማጣት፣ ማትረፍና መክሰር ያለ ነው፡፡ ዛሬ ባጣ ነጋ አገኛለሁ፡፡ እዚሁ በአገሬ ከወገኖቼ ጋር ወድቄ እየተነሳሁ፣ ብሠራ ይሻላል ብለው ትናንሽ ቢዝነሶች መሥራት ቀጠሉ። እንዳሰቡትም ትናንሾቹ ቢዝነሶች አላሳፈሯቸውም - ጥሩ ሆኑ፡፡
ትናንሾቹን ቢዝነሶች እየሠሩ ሳለ ሁለት ፕሮፌሽናል ሸሪኮች አግኝተው አካካሰ ሎጀስቲክስ ኃ.የተ.የግ.ማ መሠረቱ፡፡ ድርጅቱ ከጅቡቲ ወደብ ዕቃ ጭኖ በማጓጓዝ አዲስ አበባ ካደረሰ በኋላ አስፈላጊ የጉምሩክ ፎርሟሊቲዎችን አጠናቆ፣ ዕቃውን ለባለንብረቱ ያስረክባል፡፡ ሥራው ውጤታማ ሆኖ በፊት የከሰሩትን በዚህኛው መለሱ። ድርጅቱ አሁንም ጥሩ እየሠራ ነው፡፡ በመቀጠልም ሦስቱ ሸሪኮች በአፋር ክልል ጨው ማምረት ተሰማርተው በጋራ እየሠሩ ነው፡፡ ሸሪኮቻቸው በየግላቸው ኩባንያዎች ከፍተው ማሰራት ሲጀምሩ አቶ ሙሉጌታም የግል ኩባንያዎች አቋቁመው በማኑፋክቸሪንግ፤ በሪል እስቴት፤ እየሠሩ ነው፡፡
በለገጣፎ የተተከለው ሁለተኛው የዱቄት ፋብሪካ በቀን 850 ኩንታል ይፈጫል፡፡ ከዚያም በሽሬ፣ በአድዋ፣ በመቀጠልም 60 ዓመት ያስቆጠረ የዱቄት ፋብሪካ ኩሃ በአዳማ ከተማ ብዙ  ዓመት ያስቆጠረውን የረር ዱቄት ፋብሪካ ባንክ ጨረታ አውጥቶ ገዙ፡፡ በአጠቃላይ በዱቄት ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አምስት የዱቄት ፋብሪካ አላቸው፡፡ ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ በመግባት በአዳማ ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ብስኩትና የአልሚ ምግቦች ፋብሪካ ለማቋቋም አቅደዋል፡፡ የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ የሚያስተዳድራቸውን የመንግሥት ንብረቶች ወደ ግል ይዞታ ለማዞር ጨረታ ሲያወጣ በመጀመሪያ የዱቄት ፋብሪካዎቹን ተጫርተው ገዙ፡፡ ከዚያም የቤቶች ሥራ ድርጅትን (ሃውስ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ) በጨረታ በ51 ሚሊዮን ብር ገዙ፡፡ ኤጀንሲው የአዋሽ ወይን ጠጅ ፋብሪካንም ለመሸጥ ጨረታ አወጣ፡፡ መጀመሪያ የወጣው ጨረታ እርሻውን አያካትትም ነበር። ስለፋብሪካው ጥናት አካሄዱና ፕሮፖዛል አዘጋጅተው በ200 ሚሊዮን ልግዛው በማለት አስገቡ፡፡ ኤጀንሲው ያቀረቡትን ዋጋ ሳይቀበል ቀረ፡፡ ያቀረቡትን ጥናት መሠረት አድርጐ ከላይኛው አዋሽ 500 ሄክታር እርሻ ጨምሮ በድጋሚ ጨረታ አወጣ፡፡
እርሻውን ጨምሮ ለጨረታ የቀረበው ዋጋ አቶ ሙሉጌታ ብቻቸውን የሚሞክሩት አልነበረም። ስለዚህ አብሯቸው የሚሰራ የውጭ ኩባንያ ሲፈላልጉ፣ የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆነው ሰር ቦብ ጊልዶፍ በቦርድ ሊቀመንበርነት ከሚመራው “8 ማይልስ” ከተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ ጋር በሽርክና በ453 ሚሊዮን ብር አዋሽ ወይን ጠጅ ፋብሪካን ገዙ፡፡ በወቅቱ የአቶ ሙሉጌታ ድርሻ 49 በመቶ፣ የ“8 ማይልስ” 51 በመቶ ነበር፡፡
አዋሽ ወይን ጠጅ የ60 ዓመት አንጋፋ ፋብሪካ ነው። እድሳት ሳይደረግለት ቢቆይም፤ 600 ሠራተኞቹና የፋብሪካው ደንበኞች ለወይን ጠጁ ያላቸው ፍቅርና ታማኝነት ከፍተኛ ነው፡፡ በእርግጥም የገዛነው እሱን ነው ማለት ይቻላል ይላሉ አቶ ሙሉጌታ፡፡ ፋብሪካውን ከገዙት በኋላ ከሠራተኞቹ ጋር ብዙ ተወያይተው መሻሻል የሚገባቸውን ነገሮች ነቅሰው አውጥተው፣ የሚሰባበሩና በጊዜ የማይቀርቡ ዕቃዎችን ለማቅረብ፣ የተሰበሩ ወይም የሚለወጡ መሳሪያዎችን ለመለወጥ፣ እርሻው የተሻለ ምርት እንዲሰጥ በማድረግ 600 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት አድርገውበት፣ በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የተመረተው ወይን ጠጅ ሁሉ ይሸጣል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሁለተኛ ፋብሪካ ካስቴል ወይን ጠጅ ሥራ ጀምሯል፡፡ እኛም በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪ ሆነን ለመቆየት አራት የወይን ዓይነቶች “ገበታ” በማለት ሁለት ቀይና ሁለት ነጭ ወይን ጠጆች አቅርበናል፣ ደንበኞቻችንም ወደዋቸዋል፣ ገበያቸውም በጣም ጥሩ ነው፡፡ በአገራችን 2ኛ የወይን ጠጅ ፋብሪካ በመከፈቱ በጣም ደስ ይለናል እንጂ አይከፋንም፡፡ ምክንያቱም ካስቴል ወይን ጠጅ በዓለም በ2ኛ ደረጃ የሚገኝ ነው። የኢትዮጵያን ወይን በዓለም ባስተዋወቀ ቁጥር ለእኛ በጣም ጥሩ ዕድል ይፈጥርልናል፡፡ ገበያው እንደሆን ለሁለታችን ቀርቶ ሌላም ቢመጣ ያስተናግዳል። በፊት ወይን ጠጅ ወደ ውጭ አገር ይላክ ነበር፡፡ አሁን ወደ ውጭ መላኩን አቁመን የጥራት ደረጃውን ከፍተኛና አስተማማኝ ደረጃ ለማድረስ እየሠራን ነው ሲሉ አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡
አቶ ሙሉጌታ በ200 ሚሊዮን ብር ካፒታል የጀመሩት ሌላው ትልቅ ፕሮጀክት ሙለር ሪል እስቴት ነው፡፡ ከመንግሥት የተሰጣቸው ቦታ ቢኖርም በአንዳንድ ያልተሟሉ ነገሮች እስካሁን መሬቱን አልተረከቡም። በቅርቡ እንረከባለን ብለዋል፡፡ ሙለር ሪል እስቴት እስካሁን ቦታ እየገዛ ነው ቤቶች የሚገነባው፡፡
በለቡ ቀለበት መንገድ ዳር ፣ በሳህሊተማርያም፣ በአያት አካባቢ እንዲሁም ሮፓክ የተባለውን የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ ድርሻ በመግዛት፣ ለደንበኞቹ ቪላና አፓርትመንት እየሠራ ነው፡፡ ሪል እስቴት በኢትዮጵያ ረዥም ዕድሜ ስለሌለው ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ ግማሾቹ ከከተማ ወጣ ብለው ስለተሠሩ መሠረተ ልማት አልተሟላላቸውም፡፡ አንዳንዶቹ እስካሁንም መብራት፣ መንገድ፣ ውሃ የላቸውም፡፡ የግንባታ ማቴሪያሎች ዋጋ መናር፣ የሠራተኛ ጉልበት ዋጋ መጨመር፤ ሌሎች ችግሮችንም ተቋቁመው እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሪል እስቴት ሌላው ከፍተኛ ችግር ትልቅ ካፒታል መጠየቁ ነው፡፡ ይህን ችግር እየተወጡ ያለው ከቤት ገዢ ደንበኞች ቅድሚያ ክፍያ በመቀበልና ከራስ ኪስ በማውጣት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በጥቂት ሪል እስቴት አልሚ ድርጅቶችና በደንበኞቻቸው መካከል የሚፈጠር ያለመግባባት (ያለመተማመን) ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የቤት ሽያጭ ገበያ በጣም ተዳክሞ ቆይቷል፡፡
ሁሉንም ደንበኛ ማስደሰት ከባድ እንደሆነ አቶ ሙሉጌታ ያምናሉ፡፡ በሙለር ሪል እስቴት ወደ ፀብ ወይም ወደ አለመግባባት የደረሰ ደንበኛ እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ ያሉትን ችግሮች ከደንበኞቻቸውን ጋር ተወያይተን በመፍታት፣ የቤቶቹ ግንባታ እንደቀጠለ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከአቅም በላይ በሆኑ ችግሮች የተነሳ መዘግየት ይኖራል፡፡ የችግሮቹን ምክንያት ለደንበኞቻችን በማስረዳትና በመግባባት እየሠራን ነው ብለዋል አቶ ሙሉጌታ፡፡
ወደፊት በቤት ገዢና ሻጭ መካከል ችግር እንዳይፈጠር፣ ኩባንያዎች ቤት የሚሰሩበትን ቦታ ማሳየት፣ የተሰጣቸውን የቦታ ካርታ ማቅረብ፣ … ይኖርባቸዋል። ከገዡዎችም ብዙ ይጠበቃል፡፡ ቤት ሰሪ ነኝ ላለ ሁሉ ገንዘባቸውን አንስተው መስጠት የለባቸውም፡፡ ቤቴን የምትሰራበትን ቦታ አሳየኝ፤ ካርታው የት አለ? … በማለት መጠየቅና ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ የኩባንያውን ቀደም ያለ ታሪክ ማወቅም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ጥንቃቁ ከተደረገ በኋላ ችግር ከተፈጠረ መንግሥት በሚያወጣው ህገ ደንብና መመሪያ መጠየቅ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
ሪል ኢስቴት አትራፊ አይደለም፡፡ አትራፊ ያለመሆኑን ለማወቅ እኛ ቤት ሠርተን የምንሸጥበትን ዋጋና ሰዎች ባዶ ቦታ የሚጫወረቱበትን ዋጋ ማየት ነው፡፡ እኛ ሙሉ ለሙሉ ቤቱን ጨርሰን ከምናስረክብበት ዋጋ እጥፍ ነው ለባዶ ቦታ በጨረታ የሚቀርበው፡፡ ይህ እኛ በቤቱ ላይ ሲሚንቶ፣ ብረት፣ ፊኒሽንግ ማቴሪያል ከውጭ አገር አምጥተን ገጥመን… ሙሉ በሙሉ ጨርሰን የምንሸጥበት ዋጋ ከባዶ ቦታ ዋጋ ያነሰ ነው፡፡ የህም ትርፋችን በጣም አነስተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ መዘግየት ቢኖርም በመጨረሻ ግን ተጠቃሚዎች ገዢዎቹ ናቸው፡፡ ምክንያቱም እኛ ጨርሰን ካስረከብናቸው በኋላ ሦስት እና አራት እጥፍ ጨምረው ነው የሚሸጡት፡፡ አያት አካባቢ ለመኖሪያ አንድ ካሬ ሜትር ባዶ ቦታ በ20ሺህ ብር እየተሸጠ እኔ ተገንብቶ ሁለመናው ያለቀለትን ቤት አንድ ካሬ በ16ሺህ ብር ነው የምሸጠው፡፡ ስለዚህ ትርፋችን በጣም ትንሽ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
ሙለር ሪል ኢስቴት በ500 ካ.ሜ ላይ ያረፉ 12 ትላልቅ ጂ + 1 ቪላ ቤቶች አጠናቆ ለደንበኞቹ አስረክቧል። በ3 ሚሊዮን ብር የሸጡት ቤት ባለቤቶቹ 12 እና 13 ሚሊዮን ብር ለመሸጥ እያስማሙ ነው፡፡ ለቡ ቀለበት መንገድ ዳር የተሠሩ የነበሩ ቤቶች በ3 ሺህ በ4ሺህ ዶላር እየተከራዩ ስለሆነ ደንበኞችቻችን ደስተኞች ናቸው። ሳህልተማርያም አካባቢ 45 ቪላዎች ጀምረን 28ቱ አልቀው ደንበኞች ካርታቸውን እየተረከቡ ወደቤታቸው እየገቡ ነው። በአያት አካባቢ 24 ቪላዎች እየተሰሩ ሲሆን 50 በመቶ ተጠናቀዋል፡፡ በሌሎች ሳይቶች እየተሰሩ ያሉት ቤቶች በተለያየ ደረጃ ላይ ይገኛሉ በማለት አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡
በመኸል ከተማም ለሞል፣ ለገበያ ማዕከል ለቢሮ የሚሆኑ ህንፃዎች የመስራች እቅድ አላቸው፡፡ አንዱን ሕንፃ 22 የተባለ በሚጠራው አካባቢ እየሰሩ ነው። አቶ ሙሉጌታ በሆቴል ዘርፍም ተሰማርተዋል፡፡ ከበቀለ ሞላ መዝናኛዎች አንዱ የሆነውን የላንጋኖ ሐይቅ መዝናኛ ሆቴል በ80 ሚሊዮን ብር ከባንክ ገዝተውና በ20 ሚሊዮን ብር አድሰው እየሰሩበት ነው፡፡ ወደፊት ባለ 5 ኮከብ መዝናኛ ለማድረግ ዲዛይን አሰርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ካዛንቺስ አካባቢ ለሆቴል የሚሆን ቦታ ገዝተው ወደፊት ገንዘብ በተገኘ ጊዜ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ለመሥራት ዲዛይን እያሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ወደፊት የአገቲቷን ኢኮኖሚ ዕድገትና ፍላጎት እያዩ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የመሰማራት ራዕይ አላቸው። ሌላው ህልማቸው ደግሞ ለወገኖቻቸው የሥራ ዕድል መፍጠር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በግልና በሽርክና በሚሰሩባቸው ድርጅቶች 2000 ያህል ሰራተኞች አሉ። ይህን ቁጥር ወደ 10, 000 ማሳደግ ትልቁ ምኞታቸው ነው፡፡  

Page 10 of 19