- ፖሊስ በህገ ወጥነት የተጠረጠሩ 66 ሺህ ያህል ድረ ገጾችን እየመረመረ ነው
       - ቻይናውያን በአሜሪካ ላይ 700 ያህል የኢንተርኔት ጥቃቶችን ፈጽመዋል


     የቻይና ፖሊስ የአገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥሉ አገር አቀፍና አለማቀፍ የኢንተርኔት ወንጀል ተግባራት ላይ ተሰማርተው ተገኝተዋል ያላቸውን 15 ሺህ ያህል ዜጎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ባለፈው ማክሰኞ ማስታወቁን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
የቻይና የደህንነት ሚኒስቴርን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የአገሪቱ ፖሊስ ከኢንተርኔት ጋር የተያያዙ 7 ሺህ 400 የወንጀል ክሶችን ሲመረምር ቢቆይም የተጠቀሱት 15 ሺህ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት በምን ያህል ጊዜ ውስጥ እንደሆነ አልገለጸም፡፡
የቻይና መንግስት ባለፈው ወር ኢንተርኔትን ማጽዳት የተሰኘ መሰል ወንጀሎችን መከላከል የሚያስችል የስድስት ወራት ብሄራዊ ዘመቻ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን የጠቆመው ዘገባው፤ ተጠርጣሪዎችን በማሰር የተጀመረው እርምጃ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአገሪቱ የደህንነት ሚኒስቴር ማስታወቁን ገልጿል፡፡
ዘመቻው በኢንተርኔት የሚሰሩ ወንጀሎችን ከመከታተልና ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ ከማቅረብ በተጨማሪ ተደራጅተው በኢንተርኔት ወንጀል የሚሰሩ ቡድኖችን የማጥፋት ተልዕኮ እንዳለውም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የቻይና ፖሊስ ህገወጥና ጉዳት የሚያስከትሉ መረጃዎችን በሚያስተላልፉ እንዲሁም የወሲብ፣ የጦር መሳሪያዎችና የቁማር ማስታወቂያዎችን በሚያሰራጩ 66 ሺህ ያህል የአገሪቱ ድረገጾች ላይ ምርመራ ሲያደርግ መቆየቱንም አስረድቷል፡፡
ኤንቢሲ ኒውስ በበኩሉ፤ የተደራጁ ቻይናውያን የኢንተርኔት ዘራፊዎች የአሜሪካን ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣናት የኢሜይል ቁልፍ ሰብረው በመግባት የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን እንደፈጸሙ መረጋገጡን ዘግቧል፡፡
ቻይናውያን የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች ባለፉት አምስት አመታት በአሜሪካ ላይ ለ700 ጊዜያት ያህል ጥቃት ፈጽመዋል ያለው ዘገባው፤ ከ600 በላይ የሚሆኑት ስኬታማ ጥቃቶች የተፈጸሙትም በአሜሪካ የመንግስት፣ የግልና የኩባንያ ድረገጾችና የኢሜል አድራሻዎች ላይ መሆኑንም ገልጿል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

20 ኪሎ ሜትር ቁመት ይኖረዋል፣ “የጠፈር አሳንሰር” ይገጠምለታል
   ቶዝ ቴክኖሎጂ የተሰኘው የካናዳ የጠፈር ምርምር ቴክኖሎጂ ኩባንያ በዓለማችን ትልቁ እንደሚሆን የተነገረለትንና 20 ኪሎ ሜትር ቁመት ያለውን ሰማይ ጠቀስ ማማ በመገንባት፣ ረጅሙን የጠፈር አሳንሰር ሊዘረጋ መሆኑን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
የጠፈር ተመራማሪዎችን ያለ መንኮራኩር በቀጥታ ወደ ጠፈር ማጓጓዝ የሚችለው  አሳንሰር፤ ጠፈርተኞችን በመንኮራኩር ወደ ጠፈር ለመውሰድ ከሚያስፈልገው ነዳጅ 30 በመቶ ያህል ያነሰ ነዳጅ እንደሚጠቀምና ወጪ ቆጣቢ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የጠፈር አሳንሰሩ ዲዛይነር የሆኑት ዶ/ር ብሬንዳን ኩይኔ እንዳሉት፣ ጠፈርተኞች በአሳንሰሩ ተሳፍረው ከመሬት በ20 ኪሎሜትሮች ርቆ ከሚገኘው የማማው አናት ላይ ከወጡ በኋላ፣ በቀላሉ በጠፈር አውሮፕላኖች እየተሳፈሩ ወደ ጠፈር ጠልቀው የሚገቡበትና ስራቸውን የሚያከናውኑበት ዕድል ይፈጠርላቸዋል፡፡
አሳንሰሩ የሚገጠምበት ሰማይ ጠቀስ ማማ፣ በአሁኑ ወቅት የአለማችን ረጅሙ ህንጻ በመሆን ክብረ ወሰን ይዞ ከሚገኘውና 830 ሜትር ርዝማኔ ካለው የዱባዩ ቡርጂ ከሊፋ ህንጻ በ20 እጥፍ ያህል ቁመቱ እንደሚረዝም የጠቆመው ዘገባው፤ ማማው  ከዚህ በተጨማሪም ለነፋስ ሃይል ማመንጫነት፣ ለኮሙኑኬሽንና ለቱሪዝም አገልግሎት እንደሚውልም ገልጿል፡፡
ማማው ቁመተ ረጅም ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በንፋስ የመገንደስ አደጋ ሊገጥመው አይችልም ወይ ለሚለው የብዙዎች አስተያየት ምላሽ የሰጡት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ካሮሊን ሮበርትስ፤ ስጋት አይግባችሁ፣ መሰል አደጋዎችን መቋቋም እንዲችል አድርገን ነው ንድፉን የሰራነው ብለዋል፡፡
የአሜሪካ የፈጠራ መብቶች ቢሮ፤ የካናዳው ኩባንያ ላቀረበው ልዩ የሆነ የጠፈር ማማና አሳንሰር ፈጠራ እውቅና መስጠቱንና ፕሮጀክቱም ተቀባይነት ማግኘቱን ዘገባው አክሎ ጠቁሟል፡፡ 

Published in ከአለም ዙሪያ

 ሌላ የልጅ ልጃቸውም በድብደባ ወንጀል ተከስሶ ነበር
   የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንትና የጸረ አፓርታይድ ታጋይ የኔልሰን ማንዴላ የልጅ ልጅ የሆነው ማንዴላ፣ አንዲትን ደቡብ አፍሪካዊት የ15 አመት ልጃገረድ አስገድዶ በመድፈር ወንጀል ተከስሶ ባለፈው ሰኞ ፍርድ ቤት መቅረቡን ዘ ጋርዲያን ዘገበ።
ልጃገረዷን ጆሃንስበርግ ውስጥ በሚገኝ አንድ መጠጥ ቤት ውስጥ አስገድዶ ደፍሯል በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው የ24 አመቱ ቡሶ ማንዴላ፤ ባለፈው ሰኞ  ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን በሳምንቱ መጨረሻ በጆሃንስበርግ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጉዳዩ እንደሚታይ ይጠበቃል፡፡
ቡሶ ማንዴላ ከሁለት ሳምንታት በፊት ልጃገረዷ በመጠጥ ቤቱ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ሳለች ተከታትሏት ሄዶ አስገድዶ ደፍሯታል መባሉን የጠቆመው ዘገባው፣ ጥቃቱ የደረሰባት ልጃገረድ ክስ መመስረቷን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉንም አስታውሷል፡፡
ተጠርጣሪው የማንዴላ የልጅ ልጅ ስለሆነ ብቻ ከሌሎች ወንጀለኞች ተለይቶ የሚታይበት ምክንያት የለም ያለው የጆሃንስበርግ ፖሊስ፤ እንደማንኛውም ተጠርጣሪ እንደሚያዝና ጉዳዩ በፍርድ ቤት ተጣርቶ የአገሪቱ ህግ ባስቀመጠው መሰረት ተገቢው ውሳኔ እንደሚሰጠው አስታውቋል፡፡
ተከሳሹ ማንዴላ ከሶስቱ ሚስቶቻቸው የመጀመሪያዋ ከሆነችው ኤቭሊን ማሴ ከወለዷቸው ልጆች ከአንዷ እንደተወለደና አያቱ ማንዴላ በህይወት ሳሉ በተናዘዙለት መሰረት 300 ሺህ ዶላር እንደወረሰ ያስታወሰው ዘገባው፤ ማንድላ ማንዴላ የተባለው ሌላ የኔልሰን ማንዴላ የልጅ ልጅም ከወራት በፊት አንድን የ40 አመት ደቡብ አፍሪካዊ ደብድቧል በሚል ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንደነበርም አክሎ ገልጿል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

  ፌስቡክ  በግማሽ ደቂቃ 5 ሺ 483 ዶላር ገቢ ያገኛል

   በድረ-ገጾች አማካይነት በአለማቀፍ ደረጃ የሚከናወነው “የኤሌክትሮኒክ ንግድ” በየግማሽ ደቂቃው በድምሩ የ1.2 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እያስገኘ መሆኑ በጥናት መረጋገጡን ዘ ሂንዱ ታይምስ ረቡዕ ዕለት ዘገበ፡፡
አሶቻም ዲሎይት የተባለው አለማቀፍ የጥናት ተቋም ሰሞኑን ይፋ ያደረገውን የጥናት ውጤት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋፋት ላይ በሚገኘውና ትርፋማነቱ እየጨመረ በመጣው የኤሌክትሮኒክ ንግድ ከፍተኛ ገቢ እያገኙ ካሉት የአለማችን ታላላቅ ኩባንያዎች መካከል ቀዳሚነቱን የያዘው ታዋቂው የማህበራዊ ድረ-ገጽ ፌስቡክ ነው።
ፌስቡክ በኤሌክትሮኒክ ንግድ በየሰላሳ ሰከንዱ 5 ሺህ 483 ዶላር ገቢ ያገኛል ያለው ጥናቱ፤ ፒንተረስት እና ትዊተር የተባሉት የማህበራዊ ድረ ገጾችም በ4 ሺህ 504 እና በ4 ሺህ 308 ዶላር የግማሽ ደቂቃ ገቢ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃዎችን የያዙ የአለማችን የኤሌክትሮኒክ ንግድ ገቢ ቀዳሚ ኩባንያዎች ናቸው ብሏል፡፡
ማህበራዊ ድረገጾች መስፋፋታቸው በአለማቀፍ ደረጃ በኤሌክትሮኒክ ንግድ ገቢና ትርፍ ረገድ ከፍተኛ እድገት እንዲመዘገብ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል ያለው ዘገባው፤ ማህበራዊ ድረ ገጾቹ የኩባንያዎችን ምርቶችና አገልግሎቶች በተመለከተ ፈጣን መረጃዎችን በማሰራጨትና ንግዱን በስፋት በማቀላጠፍ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ዘገባው ገልጿል፡፡
ኤሌክትሮኒክ የክፍያ ስርአቶች በስፋት መዘርጋታቸውም ንግድ በአለማቀፍ ደረጃ የተቀላጠፈ እንዲሆንና ገዢና ሻጮችን ለአደጋ ከሚያጋልጠው የካሽ ግብይት ወደ ኤሌክትሮኒክ ክፍያ ፊታቸውን እንዲያዞሩ ያደረገ ሲሆን የኤሌክትሮኒክ ንግድ እንዲስፋፋም የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል ተብሏል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

  የክርስቶስን ትምህርት በአንድ አረፍተ ነገር ግልፅ ስለተባለው ቄስ እያወራሁለት ነበር፤ ኤስን፡፡
“አንድ የካቶሊክ ቄስ በአንድ እግሩ ቆሞ በአንድ አረፍተ ነገር የክርስቶስን አስተምሮት እንዴት እንደገለፀው ታውቃለህ ኤስ?”
“እንዲደረግብህ የማትፈልገውን በሌሎች አታድርግ የሚለው ነው አይደል” አለኝ እርግጠኛ ሆኖ፡፡ ተሳስተሃል ለማለት ከት ብዬ ሳቅሁበት፡፡ ሲሳቅበት እንደማይወድ አውቃለሁ፡፡ ያወኩት እኔ ሲሳቅብኝ አለመውደዴን ተመርኩዤ ነው፡፡
“አይደለም…ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ ነው ያለው” አልኩት፤ ለስላሳዬን አንስቼ እየተጐነጨሁ፡፡ ጉሮሮዬ አልደረቀም፤ ግዜ ለመግዛት ያደረግሁት ነው። የሰነዘርኩትን ሀሳብ ተቀብሎ አፀፋውን እስኪሰጠኝ፡፡
አሰበበት፡፡ ግን እያሰበ ያለው በ “ኤስኛ” ነው። በጠማምኛ፡፡ ፍልስፍና፤ ጠማማ ጥያቄን ቀጥ ካለ አስተሳሰብ ውስጥ የማመንጫ መንገድ ነው ብዬ ስለማሰብ፤ ጓደኛዬ ኤስ ለእኔ ፈላስፋዬ ነው፡፡ አጣሞ ማሰብ ይችላል፡፡
“የክርስቶስን ትምህርት በቀላሉ መተግበር የሚችሉት እጽዋት ብቻ ናቸው” አለኝ በጣም ሲጨነቅ ቆይቶ፡፡
ምን ለማለት ገደማ እንደሆነ እስክረዳው ድረስ አይኔን አፍጥጬ፣ በአፌና በጠርሙሱ መሀል ያለውን ርቀት ባለበት ገትቼ አደመጥኩት፡፡
“ለምሳሌ የሙሴ ህግን እንመልከት፤ ቤተሰቦችህን አክብር ይላል፤ ታላቆቹንም ሆነ ቤተሰቡን የሚያከብር ትውልድ አይቼ አላውቅም፡፡ ‹ከታላቆቼ እሻላለሁ› ባልል ምን ወደፊት ያራምደኛል? የሰው ልጅ ወደፊት የሚራመድ ፍጡር ነው አይደል? ወደፊት ለመራመድ ከኋለኛው ጋር መነጣጠል ወይ ከኋለኛው መቀጠል ያስፈልጋል፤ አይመስልህም?” አይኑ ፈጧል፤ እየተናገረ ባለው ነገር ላይ ያለውን እምነት የምመዝነው በአይኑ አከፋፈት መጠን ነው፡፡ ምክንያታዊነቱን በአይኑ አበለጣጠጥ ነው የማረጋግጠው፡፡
ይህንን መሰል በሎጂክ ላይ መሰረት ያላደረጉ ድምዳሜዎች አሉኝ፡፡ ለምሳሌ፤ በአንድ ወቅት እንደዚሁ የሆነ አስተያየት አምጥቼ ነበር፡፡ የሰው የአስተሳሰብ ልቀት በአፍንጫው ርዝመት መጠን ይለካል ብዬ አምኜ፣ እምነቴን ተናገርኩ፡፡ ሰበክሁ፡፡
ኤስ እና ሌሎቹ እኩዮቼ ሁሉ ተቃወሙኝ፡፡ ተቃወሙኝ እንጂ፣ ያመጣሁትን አስተሳሰብ ማፍረሻ እርግጠኛ ነገር ማቅረብ አልቻሉም፡፡ እንደ ውሻ ቁርጭምጭሚቴን እየተገተጉ ሃሳቤን ለማስተው ተጉ፡፡ ይሄንን ያደረጉበት ምክንያቱ ደግሞ ለኔ ግልጽ ነበር፡፡ ከእኔ በስተቀር ሌሎቹ ጐራዳ አፍንጫ ነው ያላቸው፡፡ በጐራዳ አፍንጫ ማሰብ እንደማይቻል ከእኔ ሲሰሙ ተደናገጡ። በተፈጥሮ የተሰጣቸው አቅም እንደ አፍንጫቸው የማያድግ (የማይለወጥ) ከሆነ ምን ማድረግ ይችላሉ?
ብቻ ለጊዜው ለማጭበርበር ያ እይታ ጠቅሞኛል። ከዛ ትንሽ ሲቆይ እይታው ሰለቸኝ፡፡ የሰለቸኝ እነሱ በአፍንጫቸው እጥረት ሳይገቱ ማሰብ በመቀጠላቸው ምክንያት ነው፡፡ አሁን ዛሬ ደግሞ ጊዜው የኤስ ነው፤ በጐራዳ አፍንጫው ተጠቅሞ አዲስ እይታ አበቀለ። ያሸነፈ እንዳይመስለው ግን ያመጣውን ሃሳብ በደንብ አድምጬ ተከራክርኩት፡፡
“የሙሴ ህግ የተፈጥሮን ህግ ይመስላል፤ ግን የሰዎች ህግ ነው፡፡ ጥርስህን ያወለቀን ጥርሱን አርግፍለት ነው የሚለው” እያለኝ ቀጠለ፡፡ “ሰንበትን አክብር፣ አትመቀኝ… ከትርፍህ ለቤተክርስቲያን ቀንሰህ ስጥ አይደል የሚለው?”
ተስማማሁኝ፡፡ ግን እየተስማማሁኝ ፉክክር መሆኑ ታውቆኛል፡፡ አፍንጫዬን እያሳጠረ መሆኑ ገብቶኛል፡፡ የእኔን አሳጥሮ የራሱን ሊያሳድግ ነው፡፡ የምንከራከርበት ነገር ከእኛ ሰብዕና ውጭ ነው፡፡ እኔና ኤስ ቤተሰቦቻችንን አክብረን ስለማወቃችን ወይንም ስላለማወቃችን አይደለም ነገሩ፡፡ ለእኔና ለኤስ ጉዳዩ ፉክክር ነው፤ ሃሳብን አጠማዘን ጐል ማግባት እንድንችል ነው የምንከራከረው። ጐል የምናገባው ደሞ በተቃራኒ አቅጣጫ ነው፡፡ ባለመስማማት፡፡ እሱ እኔ ላይ፣ እኔ ደግሞ በእሱ ላይ፡፡ ክርክር የፉክክር መንፈስ መገለጫ አይደል?
ተስማማሁኝ፡፡ ተስማምቼ የማደምጠው ግን የምፈልገውን አንድ ክፍተት እስካገኝ ብቻ ነው …. ክፍተቷን ካገኘሁ የእሱን የ “ፒኖኪዮ” አፍንጫ … (በአሳማኝ የሀሳብ ውሸት የሚረዝም አፍንጫ) ሰብሬ እጥልለታለሁ፡፡ እንደዛ ማድረግ እንድችል ግን በደንብ አደብ ገዝቼ ወሬውን ማድመጥ አለብኝ፡፡ አደመጥኩት፡፡
“ስለዚህ የሙሴ ህግ ግማሽ የእንስሳት ዓለም ግማሽ ደግሞ የሰው ግዛት ነው፡፡ ጥርስ ያወለቀውን በአፀፋው ጥርሱን ማውለቅና ህግን ማስተካከል፡፡ አጸፋ መመለስ የሚቻለው በሰው ግዛት ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም እንስሳ ቂም ይዞ፣ ወቅት ጠብቆ የተደረገበትን ድርጊት መመለስ አይችልም፡፡ እንስሳ… በጉልበት ህግ ነው የሚሰራው፤ ጉልበት ያለው የሌላውን ጥርስ ያወልቃል፡፡ ጉልበት የሌለው ጥርሱን ለቅሞ ይሄዳል፡፡
እንደ አንበሳና ሚዳቋ ማለቴ ነው፤ በቀለላልኛ፡፡ …አንበሳ አሳድዷት ያመለጠች ሚዳቋ … ቀን ጠብቃ በተራዋ አንበሳውን አታሳድደውም፡፡ አንበሳው ሁሌ ለማሳደድ ሚዳቅዋ ሁሌ ለመሸሽ  ነው የተፈጠሩት … ትስማማለህ?” አለኝ ምራቁን እየዋጠ፡፡ የእኔን ምራቅ የዋጠብኝ ለምን እንደመሰለኝ አላውቅም፡፡ አፍንጫው እየረዘመ ነው፡፡
“አፍንጮ” ተብሎ በልጅነታችን እናነበው የነበረው የህፃናት ታሪክ … ለካ ለፈላስፎች የተሰጠ ምሳሌያዊ ተለዋዋጭ ዘይቤ ኖሯል? ዛሬ ነው የደረስኩበት፡፡ በጣም መዋሸትና ዋሽቶም ማሳመን የቻለው አሳቢ አፍንጫው ይረዝማል፡፡ ምናልባት ባለ አጭርና የማያድግ አፍንጫ እውነተኛው፣ ሀቀኛው ሊሆን ይችላል፡፡ መቼም፤ ራሴን ውሸታም ብዬ መወንጀል አልችልም፡፡ ውሸታም ቢሆንም እንኳን!
አፍንጮ የተባለው ያ የተረት ተረት ገፀ ባህርይ የታነፀው ከጉማጅ እንጨት እንደነበር ትዝ ይለኛል። “ጨቡዴ” የሚባል አናጢ ከእንጨትነት ወደ ሰው መሳይ ቅርፅነት በጥበብ ለወጠው፡፡ “የአፍንጮ” ህልም እውነተኛ ሰው የመሆን ነበር፡፡ እውነተኛው የእንጨት ፍጡር እውነተኛ ስጋ ደም ለባሽ ሰው ለመሆን ተመኘ፡፡ ምናልባት ክርስቶስ “ሰው ባልንጀራውን እንደራሱ አድርጎ እንዲወድ” እንዳስተማረው … እና የተማረው ሰውም የተስተማረውን ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሚመኘው። የፈለገ ይሞክራታል እንጂ ሰው ልዕለ ሰው አይሆንም። ግማሽ እንስሳና ግማሽ ሰው እንጂ ሙሉ አምላክ አይሆንም፡፡ ምናልባት አፍንጮ መቼም ከእንጨት ቅርፅነት ወደ እውነተኛ ሰውነት ሊቀየር እንደማይችለው ማለቴ ነው፡፡ ግን ምኞት ብቻ አለው። ምኞቱ ወደፊት ቀድሞ እውነተኛ ማንነቱ ወደ ኋላ ቀርቷል፡፡ ወደ ኋላ የቀረውን ማንነቱን ወደፊት ለመጎተት በሚያደርገው ሙከራና ስቃይ …. ነው ክህደት ውስጥ የሚወድቀው፡፡ ማንነቱ እንዳይቀየር ላለማመን ሲፈልግ ይዋሻል፡፡ አፍንጮ እውነተኛ የሰው ልጅ ለመሆን በሚያደርገው ትግል ምክኒያት እንደሚዋሸው፡፡ ሲዋሽ ደግሞ አፍንጫው ይረዝማል፡፡ ሰውም እውነተኛ አምላክ ለመሆን ወይንም ለመምሰል በሚያደርገው ሙከራ ይፈላሰፋል፡፡ …. እንዲህ እያልኩ በአንድ ጎን እያሰላሰልኩ በሌላ ጎን ደግሞ ፈላስፋውን ኤስ እያደመጥኩት ነው፡፡ አፍንጫውን አስረዝሞ ሲጨርስ ልቆርጥለት እንድችል፡፡
“…. እና እያልኩህ ያለሁት ገብቶሃል አይደል? …. በተለይ የክርስቶስን ትምህርቶች ምንም ሳያዛንፉ መወጣት የሚችሉት …. ሰውም እንስሳም ሳይሆኑ እፅዋት ናቸው፡፡ ይኼ ነው የደረስኩበት ድምዳሜ፡፡ እፅዋት… አይዘሩም… አያጭዱም …ባልንጀራ የላቸውም፡፡”
“… ታዲያ … ታዲያ” አልኩት ቸኩዬ፡፡ ያስረዘመውን የውሸት አፍንጫ የቱ ጋር ልቆርጠው እንደምችል እየታየኝ፡፡ “ታዲያ እፅዋት ባልንጀራ ሳይኖራቸው እንዴት ነው ባልንጀራቸውን እንደራሳቸው የሚወዱት? … ዝም ብለህ የማይመስል ሀሳብ አታስብ… ተንሳፋፊ ውሸትህን ልጓም አበጅለት … ህፃን አደረግኸኝ ልበል?” አልኩኝ … የውሸት ግልፍ ብሎኝ፡፡
“እኮ … ተመልከት! ባልንጀራውን እንደራሱ ሊወድ የሚችለው ባልንጀራ የሌለው ብቻ ነው፡፡ እንስሳት ከራሳቸው ዝርያ ባልንጀርነት አላቸው፡፡ ሚዳቋ ከሚዳቋ ጋር በአንድ ላይ ተሰብስቦ ሣር ይግጣል…። ግን በስተመጨረሻ አንበሳ ሲመጣ ሁሉም ለራሱ ነፍስ ወይንም እናት ሚዳቋ ለልጇ ነው አስቀድማ የምትቆረቆረው፡፡ ሰውም ትንሽ ከፍ ያለ ንቃተ ህሊና ያለው ቢመስልም ከሚዳቋዋ ብዙም የተለየ አይሆንም … ቁርጥ የሆነ የአደጋ ሲመጣ … ለራሱ ወይ ልጆቹ ያደላል … ከጥቅሉ የሰውነት መንፈስ ጋር ያለው ባልንጀርነት ፈተና ሲገጥመው … ይከዳዋል፡፡
ወደ ራስ ወዳድነቱ ያዘነብላል። ራስ ወዳድነት ደግሞ የእንስሳት ግዛት ነው፡፡ እፅዋት ግን መጀመሪያውንም ባልንጀራ ስለሌላቸው ባሉበት ፀንተው ይቆማሉ፡፡ … ገባህ?” በጣም ጓጉቷል እንዲገባኝ። የእንጨት አፍንጫውን አስረዝሞ እኔ እስኪገባኝ የሃሳብ ውሸቱን እየዋሸ ነው፡፡ “ገብቶኛል” ብለው የእንጨቱ ጉማጅ ስጋ ለብሶ “ሰው ነኝ ከእንግዲህ” ሊለኝ ስለሆነ፣ ይኼንን ፍላጐቱን ደግሞ እኔ አላረካለትም፡፡ ውሸት እግር አውጥቶ የሚሄደው እንደዚህ ነው ማለት ነው እንዴ?
“አልስማማም” አልኩኝ፤ አፍንጫዬን ነፍቼ፡፡ “እሺ ባልንጀራን እንደራስ መውደድ የሚለውን ተወው፡፡…ሌሎቹን የክርስቶስ ትምህርቶችስ? ለምሳሌ ‘ግራህን በጥፊ ሲመታህ ቀኙን ስጠው’ የሚለውን? እ? እሱስ እስቲ ትምህርቱ በእጽዋት ላይ ብቻ እንዴት እውነት ይሆናል?” አልኩት፡፡
“እቺ እንኳን ቀላል ናት፡፡ እንዲያውም ቀላልና ግልጽ። ማንኛውም እንስሳም ሆነ ሰው በነርቭስ ሲስተም የተዋቀረ ነው፡፡ ስትመታው መልሶ ይማታል ወይንም ይሸሽ ይሆናል እንጂ ተገላብጦ ለሌላ ምት ሊዘጋጅልህ አይችልም፡፡ ግን እጽዋት በተቃራኒው ለምሳሌ በዛፉ ላይ መጥረቢያ ብታሳርፍ ሌላውን ጐን ይሰጥሃል፡፡ መከላከል አይችልም፡፡ አልከላከልም ማለት ደግሞ ለመጠቃት መፍቀድ ማለትም ነው፡፡ አይሸሽም ወይንም መልሶ አይማታም… ማለት እጽዋት ሆኗል የሚለው ነው ለእኔ የሚገባኝ፡፡
“አንድ ሰው ልብስህን ቢወስድብህ መጐናፀፊያህንም ጨምረህ ተውለት፤ ይላል ክርስቶስ፡፡ ተክል ብቻ ነው ቅርንጫፉን ስትቆርጠው ግንድንም እንድትቆርጥ ጨምሮ የሚተውልህ”
“እንዴት እንደተወ ታውቃለህ?”
“እንቢኝ ባለማለቱ! ነዋ”
“በጣም ልክ ያልሆነ አስተሳሰብ ነው የያዝከው፤ ሌላ ሰው ፊት ግን እንደዚህ ብለህ እንዳታወራ፡፡ ቢያንስ ባልንጀሮችህን እንደራስህ የምትወድድ ከሆነ፣ ይኼንን ፍልስፍናህን ተናግረህ የሰው አእምሮ አትበርዝ”…  ያህል ብቻ ነው ልመልስለት የቻልኩት፡፡
“ባልንጀሮቼን እንደራሴ ስለምወድ እኮ ነው እውነቱን የምነግራቸው” አለኝ፤ መከራከሪያ ነጥብ እንዳጣሁ አውቋል፡፡
“ግን ያንተ እውነት እነሱን እንደ ጥፊ ይጐዳቸዋል፡፡ ወይንም ወደ ጽድቅ ያደርሰናል፣ እንደ አምላክ ፀጋ ያሞቀናል ብለው የሚያምኑበትን ካባ ነው የምትነፍጋቸው። ይኼንን ካባ ከገፈፋካቸው ደግሞ ሌላ ተጨማሪ መጐናፀፊያ አይኖራቸውም” አልኩት፡፡ ፍልስፍናውን (የውሸት አፍንጫውን) ማሳጠር ስላልቻልኩ ወደ ልምምጥ ሄድኩ፡፡ ከተለማመጥኩት ቢያንስ ከእኔ ለመፎካከር ሲል የፈጠረውን ጠማማ መንገድ ይተው ይሆናል ብዬ በመገመቴ ነው የተሸነፍኩለት፡፡
ግን ንግግሩን አላቆመውም፤ ማሰቡን ገፋበት፡፡
 “ሰው ከእንስሳነት ወደ እጽዋትነት ከተቀየረ ብቻ ነው ልዕለ ሰው የሚሆነው፣ እንዲያውም ሰው ሌሎች ሰዎችን አይደለም እንደ ባልንጀራው መቁጠር ያለበት፤ እጽዋትን እንጂ፡፡
ሰው ድሮ ራሱን እንደ እንስሳ ቆጥሮ በአራዊት ያመልክ ነበር ይባልለታል፤ ወደፊት ግን እጽዋትን ነው ማምለክ የሚጠበቅበት፤ ዛፍ ለመሆን ነው መጣር ያለበት፡፡ ዛፍ እስኪሆን ድረስ ግን የክርስቶስን ትምህርት ተግብረው የሚገኙት እጽዋት ብቻ መሆናቸውን መቀበል ይገደዳል” አለኝ፡፡
አስጠላኝ፡፡ አታውራብኝ አልኩት፡፡ ዝም ተባባልን፡፡ “አፍንጮ” ከእንጨት ልጅነት በውሸት አቅም አፍንጫውን አስረዝሞ አሸነፈኝ፤ እኔም ተናድጄ ዝም አልኩት፡፡
ሁለታችንም እንደ እጽዋት ከራሳችን ሃሳብ በፈጠርነው ነፋስ እየተወዛወዝን ቀሪውን ቀን በዝምታ አሳለፍን፡፡ 

Published in ጥበብ

  ባለፈው ሳምንት ለገበያ የቀረበው ሌላው መፅሐፍ በደራሲ ተስፋዬ ገብረሥላሴ የተደረሰው “ጣፊናስ” የተሰኘ ልብወለድ ነው፡፡ አሁን በህይወት የሌለው ደራሲና ሃያሲ መስፍን ኃብተማርያም በመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን ላይ በሰጠው አስተያየት፤ “…በታሪኩ ሂደት ለጥቅም የቆሙና ከአገርና ከህዝብ እንቅደም ያሉ ኢትዮጵያውያን የመኖራቸውን ያህል ለአገራቸው የሚሟገቱና መስዋዕትነት ለመክፈል የቆረጡ ውድ የኢትዮጵያ ልጆችም ስሜትን ወጥረው ይይዛሉ…” ብሏል፡፡ የቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ያሳተመው “ጣፊናስ”፤ 308 ገፆች ያሉት ሲሆን ዋጋው 68 ብር ነው፡፡

Monday, 24 August 2015 10:10

አምባና ትዝታ

    ለሎሬት ጸጋዬ የልደት ቀን መርበትበት
                       
   ነቢይ መኮንን ለሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ህልፈት የተቀኘው ለልደቱም ትዝ ይለኛል፤ “ሞተ ቢሉኝ እንኳን በአካል /በነብሱ ነብሴን የሚያከር/ አለው የውበት መዘውር /መሸብህ ይበሉኝ አንተን?/ ፀሐይና ከዋክብቱን፥ ሰማይ ላይ የዘራኸውን?” የጸጋዬ አካል እድሜው ቢያበቃም ብዕሩ በየወቅቱ የሌላን አእምሮና ምናብ እየገራ ይቀጥላል። “የባለቅኔ ቀለሙ // ሰከነ እንጂ ከሰለ አንበል፥ ቢከሰከስ እንኳን አፅሙ” ብሎ ነበር ሎሬት ጸጋዬ የካሳ ተሰማ ህልፈት የቆጨው እለት። ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 11 የልደት ቀኑ እንደ ነገሩ በዝምታ ደበዘዘ። ይቅርታ ይደረግልኝና የጸጋዬ ባለቤትና ልጆቹ ምነው ጀርባቸውን አዞሩበት? አንጋፋ ደራሲና ባለቅኔ አበራ ለማ በስደት ላይ - ኖርወይ - እያለ ለጸጋዬ እጅጉን ተብሰክስኮ አኩሪ ተግባር ፈፅሟል። የኖርወይ ደራሲያን ማኅበር ለሎሬት ጸጋዬ ጥበብና አእምሮ እውቅና ለግሶ ሸልሞታል። ባለቅኔው ሞት ቢቀድመውም፥ ቤተሰቡ ሽልማትና ገንዘቡን ተረክበዋል፤ ለምን ከሽልማቱ ቆረሰው “እሳት ወይ አበባ”፥ “የከርሞ ሰው” ፥ “የእማማ ዘጠኝ መልክ” ... ለማሳተም አልተጣደፉም? ሚካኤል ሽፈራው የጸጋዬን ሰላሳ አምስት ዋና ዋና ተውኔቶች ጠቅሷል። [ምሥጢረኛው ባለቅኔ፥ ገፅ 357-361]።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ የጸጋዬን ታሪካዊ ተውኔቶች አሳትሟል። ማንኩሳ አሳታሚ - ዓይናለም መጻሕፍት - የበዐሉ ግርማን ልቦለዶች ዳግም በማተሙ ተደራሲ ፈንድቋል። የሎሬት ጸጋዬ ቤተሰብ፣ አቶ ዓይናለምን የመሰለ ግለሰብ ቢያማክሩ የባለቅኔው ግጥሞች፥ ተውኔቶች፥ ትርጉሞች እና የጥናት ወረቀቶች ታትመው ለአንባቢያን ሊዳረሱ ይችላሉ። ነገሩ ከልብ ካለቀሱ ... ነው። ሞት ሎሬት ጸጋዬን ከቀማን እኮ ከመንፈቅ በኋላ አስር አመት ሊሞላው ነው። ሎሬት ጸጋዬ ለሌላው የተቀኘው፥ ለብዕሩም እንደ ትንቢት መደመጡ ይከነክናል፤ “የብዕር አሟሟት ሌላ፥ /ሲፈስ የብሌኑ ኬላ/ የፊደል መቅረዝ አሟሟት /ከውስጥ ነው እንደጋን መብራት”። የሎሬት ጸጋዬ የፈጠራና የምርምር ውጤት መጋረዱ ተገቢ አይደለም፤ ለኔ በአማርኛ ሥነግጥም ተወዳዳሪ የሌለው ብርቅና ዕንቁ ባለቅኔ ነው።
ይህን የቁጭት ድባብ ለማርገብ ባለቅኔው በተባዕትና እንስት አንደበት - personna – ስለፍቅር፥ ስለማይሰክነው የወንድና የሴት ፍትግያ የተመሰጠባቸውን ሁለት ባለ አንድ አንጓ ግጥሞች ገረፍ አድርገን ዜማውን እናጣጥምለት።
መሸ ደሞ አምባ ልውጣ
አምባ ወጥቼ እኩለ-ሌት፥ ስለት ገብቼ በስሟ
ከርሞ ሰይጣን በሷ አስቶኝ፥ ልገላገል
 ከሕመሟ
ጠበሏ አፋፍ በጨረቃ፥ ደጋግሜ፥ ማሕሌት
ቆሜ
ሆዴ ቃትቶ ባር ባር ብሎ፥ እርቃኔን ከሷ
 ታድሜ
ደጀ ሰላሟን በአራት እግር፥ ተንበርክኬ
ተሳልሜ
በሥጋዬ እሚነደውን፥ በጸሎት ላቤ አጣጥሜ
እፎይ ብዬ አመስግኜ፥ ውዳሴዋን ደጋግሜ ....
ገና ከደጅዋ እልፍ ሳልል፥ ደሞ ይምጣ የቁም
 ሕልሜ ?
ሌት በጥምቀቷ የነጣው፥ ነጋ፥ ደፈረሰ ደሜ።
ለሷ እንጂ ለኔ አልያዘልኝ፥ አዬ የስለት
 አታምጣ !
በውጣ ውረድ በጠበል፥ ባሣር ወዜ ቢገረጣ
ልክፍቷ እንደሁ አልለቀቀኝ፥ መሸ ደሞ አምባ
 ልውጣ !
[እሳት ወይ አበባ ፥ 1951፥ ገፅ63]
ጸጋዬ በዚህ ጥልቀት ሲቀኝ፥ ዕድሜው ገና ሃያ አንድ ነበር፤ የቋንቋ ምጥቀቱና የአስተሳሰብ አድማሱ ከመነሻው የረቀቀ ነበር። አምባ በከፊልም ቢሆን ሜዳነት የተለገሰ ኮረብታ ነው። እንዲሁም ብዙ ቤቶች የተሰባሰቡበት መንደርም ይሆናል። እኩለ ሌሊት ተናጋሪው እየተቅበዘበዘ ሰው ዝር ከማይልበት አምባ -ቤተ ክርስትያን የመሰለ መቼት- በጨረቃ ብርሃን ልቡን ፈልቅቆ ፍቅሩን ያስታምማል። ከመንፈሳዊ ስብከት ያቀረረውን የሄዋንና የሰይጣን መመሳጠር እያባነነው ይሳላል፤ “ከርሞ ሰይጣን በሷ አስቶኝ፥ ልገላገል ከሕመሟ” ብሎ ቢመኝም ለአካሏ የሚነደውን ፍትወት ማፈን አይችልም። ይህ በየዕለቱ የሚኖረው ትግል የማያበቃ ነው። ግጥሙን በጥሞና ብናነበው ተናጋሪው መንፈቀ ሌሊት ከክፍሉ ሳይወጣ፥ በምናቡ እንደ ቀናዊ ህልም የተቧጠጠበት ትምኔታዊ ጉዞ ነው።
የስጋና የመንፈስ ፍልሚያ ሰምና ወርቁ ነው፤ ፍቅር እንቅልፍ እየነሳን ዳር ላይወጣ እንደ ልክፍት ይመዘምዘናል። ግጥሙ ይተንተን ከተባለ ከስሜት ባሻገር የግለሰብ ማቅማማት፥ በጐ እንደ እኩይ እየተመነዘረ ስንላተም፥ ሥነልቦናዊ መገጣጠብ አንድምታዎቹ ጨረር ቋጥረዋል። እንስት፥የወንድ ልብ ከተተረተረላት ራመድ ራመድ ብሎ አፈፍ ሲያደርጋት እንጂ ግራ ቀኝ እየገላመጠ ሲያመነታ መች ትደፋፈራለች? ፍቅር እኮ የወደድናትን ላለመነፈግ፥ እንዳናወላውል ብርታት ይለግሰናል፤ ልብ ደግሞ ሌላው ሲያቅማማ ካጤነ ለድንገት ቅብጠት ሰለባ ሊሆንም ይችላል። “ገና ከደጅዋ እልፍ ሳልል፥ ደሞ ይምጣ የቁም ሕልሜ?/ ሌት በጥምቀቷ የነጣው፥ ነጋ፥ ደፈረሰ ደሜ።” የምናፈቅራት ሴት ከናፈቀችን፣ የጊዜ መንቀራፈፍ ያስበረግጋል።
ሎሬት ጸጋዬ ከአያሌ አማርኛ ገጣሚያን የተነጠለው በግጥሞቹ የተለበለበች እንስት ድምጿ እንዲደመጥ መፍቀዱ ነው፤ በአንደበቷ ይቀኛል። “ማን ነው ‘ምንትስ’?”፥ “ተወኝ” እና “ትዝታ” ግጥሞቹ ተጠቃሽ ናቸው።
             ትዝታ
ዓይንህን በዓይኔ ፀንሼ፥ የቀስቱን ጮራ
 እንደቋጠርኩ
ሌሊት በሕልሜ አማምጨህ፥ ሕመምህን
 እየፈጠርኩ
ቀን ጥላህን እንደለበስኩ
የፍቅራችንን ነበልባል፥ በቁም ሰመመን
 እንዳቀፍኩ
ልብ ውስጥ እንዳዜሙት ሙሾ፥ የሲቃ ስልት
 እንዳቃጨልኩ
የነፍሴን የእሳት ዘለላ፥ ጐዳናህ ላይ
እንዳነጠብኩ
እንደገደል ዳር ቄጠማ ፥ የሥጋት እንባ
እንደቃተትኩ
ሕይወቴን ላንተ እንዳሸለብኩ
ሕልምህን በጄ እንደዳሰስኩ
ያን የመጀመሪያ ሞቴን፥ በመሸ ቁጥር
እንደሞትኩ
አለሁ፥ እንደብኩን መረብ፥ ትዝታህን
እንዳጠመድኩ።
[እሳት ወይ አበባ፥ 1959፥ ገፅ199]
ይህ ግጥም ከላይ እስከ ታች ቁልቅል ይነባባል፤ ባልተለመደ ሁኔታ ከታች --- “አለሁ፥ እንደብኩን መረብ፥ ትዝታህን እንዳጠመድኩ።” --- ተነስተን ወደ ላይ እያነበብን ብንወጣ የትርጉም መዛባት ሳያስከትል በመንታ አቅጣጫ ያስደምማል። ከእያንዳንዱ ሀረግና ስንኝ የሚነዝሩት ዘይቤና ምስል ገለልተኛ አይደሉም፤ ምናብን ይናደፋሉ። ሙሉ ግጥሙ “ ኩ ኩ ኩ” በሚለው ፊደል ቤት መምታቱ፥ የተናጋሪዋ ልብና ህሊና ላይ ያልሰነፈው ቅጥቀጣ ይስተጋባል፤ ሰቆቃዋ ፈታኝ ነው። በዚህ ጥበባዊ ውበት ስለ ፍቅርና የአንዲት ሴት በስሜት የመለብለብ ርቀትና ቅርበት እስኪላተም የተቀኘበት ግጥም በአማርኛ አላነበብኩም።
“እንደገደል ዳር ቄጠማ ፥ የሥጋት እንባ እንደቃተትኩ” የመሰለ ስንኝ እንደ ድፍን ግጥም ሌጣውን አቅም አለው። መጠበቅ ጐዳት፤መዘንጋት ተሳናት፤ ያለ ማቅማማት ኅላዌዋን የለገሰችው ተባዕት ችላ ያላት ይመስላል። አሜሪካዊ ደራሲ ሄሚንግዌይ፤ “ሽማግሌውና ባህሩ” (መስፍን ዓለማየሁ ተርግሞታል) በተባለ ድንቅ ልቦለዱ ይታወቃል። ሎሬት ጸጋዬ በ“ትዝታ” ግጥሙ ስለቀረፃት ሴት የታዘበው አለ። “The most painful thing is losing yourself in the process of loving someone too much, and forgetting that you are special too.” ሌላውን በማፍቀር ማንነትሽን እስከ መነፈግ መብቃት ያማል፤ አንቺም ልዩ ሴት መሆንሽን መርሳት የለብሽም ባይ ነው። የጸጋዬ ሴት ይህ ሰቆቃዋ የተባዕቱን እሺነት ለማፍረጥ ከተጠናወታት እልህ የፈለቀ በመሆኑ፥ ስቃይ ትኮተኩታለች። የተሰወረ ቁስል ነው፤ ለማከም የሚያዳግት። ከሰመረ ፍቅር ይልቅ የወንዱ ትንፋሽ ያጠረበት ብኩን ትዝታ አከለ። ይህች አፍቃሪ የተለየ ጥንካሬ ይኖራት ይሆን ? ቁስሉም አልጠገገ፥ ልክፍቱም አልቀዘዘ፤ ግን ኅላዌ እየተፈረካከሰ ለፍቅር ያላትን ሥጋና መንፈስ መገበር እንዴት ወንዝ ያሻግራል? ወንድ በወንድ ለምን አይተካም?
ሎሬት ጸጋዬ በአካል ቢለየንም፥ መንፈሳችን የተሰለበው የብዕሩ ውጤት ለብርሃን ሳይበቃ በመጋረዱ ነው፤ በቤተሰቡም ችላ መባሉ ይሰቅቃል። ለሀገራችን ሥነጽሑፍ የሚቆረቆር ማንም አቅም ያለው ግለሰብ፥ ለድንቁ ባለቅኔ ብዕር ዘብ መቆም ይኖርበታል። የጸጋዬ የፈጠራ ውጤት አለመታተም እንደ ተደፈጠጠ በረሮ ቁብ ሳይሰጠው፥ ለምዕራቡ እግር ኳስ ከጐህ እስከ ዕንቁጣጣሽ ላንቃውን እየወለወለ የሚያገሳ ግለሰብ በዕውነት የረባ ሰው ነው ወይ? ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን “ተስፋ ባጣ ምድረ በዳ / ያንድ እውነት ይሆናል ዕዳ” ብሎ የተቀኘው ለራሱም ጭምር ይመስላል።

Published in ጥበብ

በተስፋዬ በላይነህ የተፃፈው የታሪክ መጽሐፍ፤ “ትንሣኤ ናፋቂዎች - መልዕክት ወደ ኢትዮጵያ ሰዎች” ይላል፡፡ ባለፈው ሳምንት ለገበያ የቀረበው ይሄ መፅሐፍ፤ በ302 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን በሁለት ክፍሎችና በሰባት ምዕራፎች የተዘጋጀ ነው፡፡ ከምዕራፎቹም መካከል “የኢትዮጵያ ታሪክ ሥልጣኔ - እድገት ወይስ ውድቀት?”፣ “የኢትዮጵያ ህዝቦች ታሪክ በአጭር ምልከታ”፣ “ታሪክ በየ33 ዓመት” ፣ “የኢትዮጵያ ታሪክ የውድቀት ምክንያቶች” የሚሉ ርዕሶች ይገኙበታል፡፡
መጽሐፉ ለአገር ውስጥ በ69 ብር፣ ለውጭ በ20 ዶላር እንደሚሸጥ ታውቋል፡፡
ደራሲው ከዚህ ቀደም “የሚንከራተቱ ክዋክብት” የተሰኘ መጽሐፍ አሳትሟል፡፡

 በሰዓሊ ይድነቃቸው ሙሉጌታና በሰዓሊ ሰብለ ወ/አማኑኤል እገዛ የተዘጋጀው የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ህሙማን የስዕል አውደ ርዕይ ትላንት በሂልተን ሆቴል ተከፈተ፡፡
ለቀናት ለዕይታ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ በተነገረለት በዚህ የስዕል አውደ ርዕይ ላይ በህሙማኑ የተሰሩ በርካታ ስዕሎች ቀርበዋል፡፡

Monday, 24 August 2015 10:08

የህይወት አዙሪት

 ማናችንም ህይወት ወዴት እንደምትመራን አናውቅም፡፡
ማናችንም!
እሷ የደሀ ልጅ ነበረች፡፡ ትምህርት አልሆናትም። ስለዚህ ተሰደደች፡፡ የተሰደደችው የራስዋን ኑሮ ልታሸንፍና ቤተሰቦችዋንም ለመርዳት አስባ ነው፡፡ ተሰደደች ወደ ጅዳ!፡፡
ህይወትዋ ኩሽና ውስጥ ሆነ፡፡ ኑሮዋ የሚያብበው የሰው አፓርታማ ከነባኞ ቤቱ፣ ከነሽንት ቤቱ ስታፀዳ ሆነ። ዕጣ ፈንታ እንዲህ ነው! አንዱን ለተሽከርካሪ ወንበር፣ አንዱን ለሰው ጓዳ፣ አንዱን ለክብር፣ ሌላውን ለውርደት፤ አንዱን ለሳቅ፣ አንዱን ለለቅሶ፣ አንዱን ለደስታ፣ አንዱን ለሀዘን፣ አንዱን ለቁንጣን (ከጥጋብ አልፎ)፣ አንዱን ለጠኔ (ከረሀብም አልፎ)፣ አንዱን ለድህነት … ዕጣ ፈንታ እንዲህ ነው! …..
የመጀመሪያ ሰሞን ከብዷት ነበር፡፡ ብቸኝነቱም፤ ዕድሏም፣ እያማረርዋት እረፍት ነስተዋት ነበር፡፡ በኋላ ግን በመጠኑም ቢሆን ለመደች፡፡ የግድ ሲሆን የማይለመድ ነገር የለም አይደል!
ቀኑን ሙሉ ከፎቅ ፎቅ ስትሮጥ፣ አፓርታማውን ስታካልል ትውላለች፡፡ ሌሊቱን ስለ ቤተሰቦችዋና ስለ ወደፊት ህይወትዋ ስታልም ታድራለች። የመጀመሪያዎቹ ዓመታት እየነጎዱ ሄዱ፡፡ እንደ ቀልድ አስር ዓመት ሆናት። አንድ ቀን እንደ ልብዋ ስቃ ሳትጫወት፣ አንድ ቀን እንደ ፍላጎትዋ ለብሳ ሳትታይ፤ እንደ ሴትነትዋ ሳትጋጌጥና ሳትዋብ፡፡ ሳትዋብና ወንድ ሳትስብ፡፡
ከጊዜያት በኋላ ህይወትዋ ያሳስባት ጀመር፡፡ ወንድ ስማ አታውቅም! በወንድ ተስማ አታውቅም!
ሴትነትዋ ከወንድነት ጋር አልገጠመም፡፡ ተፈጥሮን የተቃወመችው ይመስላት ጀመር፡፡ ወንድ ያለ ሴት፣ ሴትም ያለ ወንድ መኖር እንደማይችል ሲነገር፣ ሲባል ሲወራ ሰምታለች፡፡ እሷ ግን ….
ልክ ነው፤ “አዳም ብቻውን ቢሆን መልካም አይደለም፤ አጋር ያስፈልገዋል” ብሎ አይደል እግዜርስ ከጎድን አጥንቱ ሄዋንን የፈጠረለት?! ስለዚህ …
በዚህ ሀሳብ መብሰልሰል ከጀመረች በኋላ ምንም ነገር ሳይለወጥ አምስት ዓመት እንዲሁ እንደዋዛ ጨመረች፡፡ በአረብ ሀገር ለአስራ አምስት ዓመታት ኖረች፡፡ ያሳሰባት ዕድሜዋ ገባ፡፡ ሰላሳዎቹን አጋመሰች፡፡ እንደ ሸረሪት ድር፣ ሀሳብና ጭንቀት አናትዋ ላይ ጎጆውን ሰራ፡፡
በእረፍት ቀንዋ ከሀገርዋ ልጆች ጋር ወደተከራዩት ቤት እየሄደች ታሳልፋለች፡፡ ወደዚያ ስትሄድ እንደቀድሞው በግድየለሽ አለባበስ ላለመሄድ ወሰነች፡፡ ቢያንስ በሰው ዓይን ውስጥ ለመግባት፣ ቢበዛ ወንድ ለመማረክና የግልዋ ለማድረግ መሽቀርቀር ጀመረች፤ ሴት ጓደኞችዋ እስኪገረሙባትና ተገርመው እስኪያሟት ድረስ!
“ምን ተገኘ ባካችሁ?”
“አዲስ ነገር አለ እንዴ?”
“ቤዛ ምን አገኘች እንዲህ የተለወጠችው?”
ወዘተ ወዘተ ተባለ፡፡ ….
በስልክዋ ላይ ካስጫነቻቸው ዘፈኖች አንዱ የኃይሌ ሩትስ ዘፈን ነው፡፡
“እርጅና መጣና ድቅን አለ ፊቴ
እባክህ ተመለስ ልጅነት በሞቴ!”
ደግማ፣ ደጋግማ ትሰማዋለች፡፡ የራስዋ ጩኸት የሆነ ያህል ይሰማታል፡፡ ግጥሙን ራስዋ የፃፈችው ሁሉ ይመስላታል፡፡
“እርጅና መጣና ድቅን አለ ፊቴ
እባክህ ተመለስ ልጅነት በሞቴ!”
የአዲስ አበባ ልጆችና ጥቂት የክፍለ ሀገር ልጆች ሆነው ነው የእረፍት ቀናቸውን የሚያሳልፉበትን ቤት የተከራዩት፡፡ ታዲያ “ዘር ከልጓም …” እንዲሉ በኢትዮጵያዊነታቸው በጣም ነው የሚዋደዱት። የአንድ ሀገር ልጆች ሳይሆን የአንድ እናት ልጆች ነው የሚመስሉት፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን መዘማል መጣ፡፡
የመጣው ጓደኛቸው አዜብ ጋ ነበር፡፡ መዘማልና አዜብ የሐዋሳ ልጆች ናቸው፡፡
ቤዛ የአዲስ አበባ ልጅ ብትሆንም ከአዲስ አበባዎቹ ጋርም ሆነ ከክፍለ ሀገር ልጆች ጋር በደንብ ትግባባለች፡፡ መዘማል ቤዛን ሲያይ፤ “የማን ቆንጆ ናት ባካችሁ እቺ!!” አለ፤ ተደንቆ፡፡
እነ አዜብ አስተዋወቁዋቸው፡፡
“ቤዛ ትባላለች፤ የአዲስ አበባ ልጅ ናት፤ እዚህ ከመጣች አስራ አምስት ዓመት አልፏታል” ለሷም ነገርዋት፡፡
“መዘማል ይባላል፤ የሀዋሳ ልጅ ነው፡፡ እዚህ ከመጣ ሁለት ዓመቱ ነው፡፡” ቤዛና መዘማል ተዋወቁ፡፡
መዘማል በእረፍት ቀን መምጣቱንና ከቤዛ ጋር ጥግ ይዞ ማውራቱን አዘወተረ፡፡
ከብዙ ………. ብዙ ግንኙነት
ከብዙ ………. ብዙ ትውውቅ
ከብዙ ………. ብዙ ጭውውት
ከብዙ ……….. ብዙ ጊዜ በኋላ፤ መዘማልና ቤዛ ፍቅረኛሞች ሆኑ፡፡
ቤዛ “ያሰብኩት ተሳካ፤ ያለምኩት ደረሰ ብላ” አንጎራጎረች፡፡
ስለ ወደፊት ህይወታቸው ሲነጋገሩ፣ ቤዛ አገርዋ መግባት እንደምትፈልግ ገለፀችለት፡፡
“እዚያ ተኪዶስ ምን ይሰራል? ኢትዮጵያ እኮ ለኑሮ በጣም አስቸጋሪ አገር ሆናለች” አላት
“ታዲያ በግርድና ልቀር ነው፤ እስቲ ልሂድና አንድ ቀን እንኳን የሀገሬን ንፁህ አየር ልተንፍስ!” አለችው፡፡
“አይ አባባሌ እዚህ ቅሪ ለማለት ሳይሆን ትንሽ ጊዜ ሰርተን .. ገንዘብ ካጠረቃቀምን በኋላ ብንሄድ ብዬ ነው።” አላት
“ለማንኛውም አስብበት! አብረን ነው ወደ ሀገራችን የምንገባው፤ ገብተን ቶሎ መጋባት አለብን እሺ!?”
“አታስብ የሆነ ነገር ላይ የምናውለው ገንዘብ እኔ አላጣም … አንተ ከመጣህም ቅርብ ስለሆነ ምንም ላይኖርህ ይችላል፡፡ እኔ ግን ያጠራቀምኩት የሆነ ያህል ገንዘብ ስላለኝ፣ እሱን አንድ ነገር ላይ እናውለውና መተዳደሪያችን እናደርገዋለን፡፡”
ቀና ብላ ፊቱን አየችው፡፡ ምንም ዓይነት የስሜት ለውጥ ፊቱ ላይ አላየችም፡፡ እናም ቀጠለች፡፡ “እኔ የምልህ”
“አንቺ የምትይኝ?”
“የትራንስፖርት ዘርፍ እንዴት ነው? በኢትዮጵያ ማለቴ ነው …”
“ደህና ይመስለኛል …”
“ባንድ ልቤ የሆነ የጭነት መኪና ገዝተን አንተ ብትሾፍረው … እያልኩ አስባለሁ … በሌላ ልቤ ደግሞ ደህና ቦታ ላይ ሱቅ ነገር… ቡቲክ ምናምን ብንከፍት ብዬ አስባለሁ፡፡ የቱ የሚሻል ይመስልሃል?”
“ስለ ሱቁ ብዙ የማውቀው ነገር የለም፡፡ የመኪናው ሀሳብ ግን ጥሩ ይመስለኛል” አላት፡፡
“በቃ ከስድስት ወር በላይ መቆየት የለብንም … ወደ ሀገራችን ተመልሰን መኖር አለብን!”
* * *
ከስድስት ወር በኋላ …..
መዘማል ከእሷ ቀድሞ ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ የስራውን ሁኔታ ካጠና በኋላ መኪናውን ገዝቶና ቤት ተከራይቶ እንዲጠብቃት ነግራው፣ ብሩን ሰጥታው ወደ ኢትዮጵያ ሸኘችው፡፡ ከወር በኋላ እሷም ጓዜን ማቄን ሳትል፣ ለቤት ማሟያ የሚሆናትን አንዳንድ ነገር ሸምታ ወደ ኢትዮጵያ ተሳፈረች፡፡
አዲስ አበባ ስትደርስ ግን መዘማል ቤት አልተከራየም። ቤዛ ወላጆችዋ ቤት አረፈች፡፡
ለምን ሳይከራይ ቆየኝ ብላ ማዘኗ አልቀረም፡፡ ግን እሱን ትታ ሌላኛው አጀንዳቸው ላይ አተኮረች፡፡ ስለ ስራው አጥንቶ ምን ላይ እንደደረሰ ጠየቀችው፡፡
“ጥሩ ስራ ነው” አላት “ቆንጆ አይሱዙም ገዝቻለሁ … መንጃ ፍቃዴን አሳድሼ ስራውን እጀምራለሁ፡፡” አላት፡፡
ቤዛ ደስ አላት፡፡ ወደ ሀገርዋ በመመለሷ ፈንጥዛለች። መዘማል ስለ ስራው አጥንቶ ያገኘው መረጃና መኪናውንም መግዛቱ አስደስቷታል፡፡ አሁን ዋና ዓላማዋ ልጅ መውለድ ነው፡፡ የአብራክዋን ክፋይ ስታሳድግ በዓይነ ህሊናዋ እየሳለች ሀሴት አደረገች፡፡
ዕድሜዋ ሰላሳ ሰባት ደርሷል፡፡ ከዘጠኝ ወር በኋላ የመጀመሪያ ልጅዋን ለመውለድ ወስናለች። ቢሆንላት አንድ አራት ልጆች የመውለድ ዕቅድ አላት፡፡ ስለዚህ ተፈጥሮ ማዕቀብ ሳትጥልባት ልትቀድማት አሰበች፡፡ ቶሎ ቶሎ መውለድ አለብኝ ብላ ከራሷ ጋር ተማከረች፡፡
ነገሮች መስመር እየያዙላት ነው፡፡ አሁን የሚያሳስባት የጋብቻቸው ሁኔታ ነው፡፡ ሠርግ ይደገስ አይደገስ የሚለው ሀሳብ አወዛገባት፡፡ እንደ ማንኛዋም ዕድለኛ ሴት ቬሎ ብትለብስ ደስ ይላታል።
ሚዜው ፈዛዛ ነው
ሽቶው ውሃ ነው
የኛ ሙሽራ ዘመናይ
… ቢባልላት ትወዳለች፡፡ ግን ደግሞ ወጪው አስፈርቷታል፡፡ ታዲያ ምን ይሻላል? ቤዛ ብቻዋን ተጨነቀች፡፡
ከ17 ዓመት በኋላ ነበር ወደ አገሯ የተመለሰችው። የ17 ዓመት የቤተሰብ ናፍቆት ተሸክማ፡፡ ለቤተሰቦችዋ ብርቅ ሆናለች፡፡ የእናትና አባትነት፤ የእህትና ወንድምነት ፍቅር፡፡ የከረመ ናፍቆት ….
ዛሬ ግን ቤቱ ደስታ በደስታ ሆኗል፡፡ ያወራሉ …. ይጯጯሃሉ …፡፡ ምን ያክል ተበድላ እንደነበር የታያት አሁን ነው፡፡ የማይረሳ የለም፤ የቤተሰብ ፍቅር ረስታ ነበር፡፡ ቢናፍቋትም፤ ልታገኛቸው ብትፈልግም፤ እንዲህ ጣፋጭና ማራኪ ጊዜ እንደሚኖራቸው ተዘንግቷት ነበር፡፡ አሁን የፍቅር ጥልቀቱ ታያት፡፡ ይህን እውነት መገንዘብዋ ሆድ አስባሳት፤ አለቀሰች፡፡
ደስ ብሏት አለቀሰች! በቁጭት አለቀሰች! የደስታና ሀዘን፤ የሳቅና ለቅሶ ድንበር ጠፋባት፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላ የመዘማልን ስልክ ስትሞክር እምቢ አላት፡፡ ናፍቀዋለች! ………... ግን እንዴት ታግኘው? … ብቸኛው የግንኙነታቸው ድልድይ ስልክ ነበር፡፡ ቤተሰቦቹ ጋ እንዳታስልክ ወይ ራስዋ እንዳትሄድ እነሱ ያሉት አዋሳ ነው፡፡ የዚህ ሀገር ጓደኞቹን ደሞ አታውቃቸውም፡፡ ቤዛ ግራ  ገባት! ….
“ምን ሆኖ ይሆን?” ብላ ተጨነቀች፡፡ “አዲስ አበባ ውስጥ ድንብርብር ሲል ሌቦች አግኝተውት ያለውን ተቀብለው ደብድበውት ይሆን?” ብላ ሰጋች፡፡ ሳምንቱን ሙሉ ብትደውል ብትደውል ስልኩ እምቢ አላት፡፡
እንዳጋጣሚ አንድ ሌሊት እንቅልፍ እምቢ ብሏት ስትገላበጥ፣ እስቲ ለማንኛውም ብላ ስትሞክር ስልኩ ጠራላት፡፡ ከደስታዋ ብዛት ከአልጋዋ ላይ ዘላ መሬት ወረደች፡፡
“ሄሎ”
“ሄሎ መዘማልዬ …. ምን ሆነህ ነው? ምን ገጥሞህ ነው የኔ ማር… ስልክህን ዘግተህ እንዲህ የጠፋኸው?”
“ሞክረሽ ነበር?”
“ይሄን ሳምንት ያልደወልኩበት ቀን የለም፤ በየቀኑ ስሞክርልህ ነበር”
“ነው?”
“አዎ … እንዴት እንደናፈቅኸኝ ደግሞ!”
“ለመሆኑ … መቼ ለመሄድ ወሰንሽ?”
“ወዴት?”
“ወደ ጅዳ ነዋ!”
ፈፅሞ ያልጠበቀችው ዱብዕዳ ነበር፡፡ “እንዴ የምን ጅዳ ነው? ተነጋግረን አይደል እንዴ የመጣነው፤ በመኪናው እየሰራን ተጋብተን እዚሁ ልንኖር‘ኮ ነው ቃላችን!”
“እሱማ ልክ ነሽ …. ግን ….”
“ግን ምን?”
“የመኪናው ገቢ ለሁለት ሰው የሚበቃ አልመሰለኝም፤ ስለዚህ እሱን እኔ እዚሁ እንደሚሆን እንደሚሆን አደርገዋለሁ፡፡ አንቺም የራስሽን አማራጭ መውሰድ አለብሽ!”
“ምንድነው የራስሽን አማራጭ ማለት! ይሄ‘ኮ ተነጋግረንና ተመካክረን የጨረስነው ጉዳይ ነው፡፡”
“አዝናለሁ ቤዛ፤ መኪናው የኔና የኔ ብቻ ነው!” ብሎ ጆሮዋ ላይ ዘጋ፡፡
“ሄሎ …… ሄሎ…… ሄ……..ሎ”
ድጋሚ መልሳ ስትሞክር ስልኩ ዝግ ነው አላት፡፡ ቤዛ አለቀሰች፡፡ ደም እንባ አነባች፡፡
በወግ በማዕረግ አግብቼ እኖራለሁ ስትል፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የልጅ እናት እሆናለሁ ስትል፤ እንዲሁ ሜዳ ላይ መቅረትዋ ክፉኛ ስሜትዋን ጎዳት። ልብዋ ተሰበረ፡፡ በህይወት ተስፋ ቆረጠች፡፡
መዘማል ድምፁ ጠፋ፡፡ ተሰወረ፡፡ እንዳትከሰው ውል የላትም፡፡ ውሉስ ቢኖር እሱ የት ተገኝቶ?!
ብሩን የሰጠችው በእምነት ነው፡፡ እንኳን ገንዘብ ሁለመናዋን ሰጥታው የለ? የወደፊት ባሌ፣ የልጆቼ አባት ብላ … ነበር ያሰበችው፡፡
እሱ ግን መኪናውን በራሱ ስም ከገዛ በኋላ በጠራራ ፀሐይ ከዳት፡፡ … ብዙ አስባ … ብዙ አውጥታ አውርዳ … ሌላ ምርጫ እንደሌላት ተገነዘበች፡፡ ሁሉን ነገር ተዘርፋ መለመላዋን ቀርታለች፡፡ ገንዘቧን … ፍቅሯን … ያለመችውን ትዳርና ልጅ … ሥነ ልቦናዋን … የቀራት ምንም የለም፡፡
ቤዛ ጓዟን ሸክፋ ጨርሳለች፡፡ ዛሬ ማታ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ወደ ሳውዲ አረቢያ ጅዳ ትበራለች። የአገሯን አየር እየተነፈሰች፣ ከቤተሰቧ አጠገብ ለመኖር አልታደለችም፡፡ ዕጣፈንታ እንዲህ ናት!

Published in ልብ-ወለድ
Page 5 of 19