ተቋሙ ከኢትዮጵያ ጋር መስራቴን  ሙሉ ለሙሉ አቋርጫለሁ ብሏል

አለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዎች ለኢትዮጵያ የመረጃ ጠለፋ ቴክኖሎጂዎችን ሸጧል፤ ለደህንነት ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት የዜጎች መብቶች እንዲጣሱ እገዛ አድርጓል ያለውን “ሃኪንግ ቲም” የተባለ የጣሊያን ተቋም በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ምላሽ አልሰጠም፣ የመብቶች ጥሰቶችን ለማስቆምም እርምጃ አልወሰደም ሲል ከሰሰ፡፡
ሃኪንግ ቲም ለተለያዩ አገራት መንግስታት የመረጃ መጥለፊያ ቴክኖሎጂዎችን በመሸጥና ለባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት፣ መንግስታት የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች እንዲጥሱ እገዛ ያደርጋል ያለው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ በኢትዮጵያ ሲከናወን የቆየውን የመረጃ ጠለፋና የመብቶች ጥሰት በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጠው ቢጠይቅም በቂ ምላሽ ሊሰጠው እንዳልቻለ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ተቋሙ ጉዳዩን በተመለከተ ምርመራ ለማድረግም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በዜጎቹ ላይ የሚያደርሰውን የመብቶች ጥሰት ለማስቆም ምንም አይነት ተጨባጭ እርምጃ አልወሰደም ሲል የከሰሰው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ሃኪንግ ቲም ለኢትዮጵያ የደህንነት ባለሙያዎች የግለሰቦችን ኮምፒውተሮች ሰብረው መግባት የሚችሉበትን ስልጠና መስጠቱን እንደቀጠለና ቀጣይ ስምምነቶችን ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምሮ እንደነበር የሚያረጋግጡ መረጃዎችን በሃምሌ ወር እንዳገኘ አስታውቋል፡፡
ሃኪንግ ቲም ለኢትዮጵያ መንግስት የሸጣቸው የመረጃ መጥለፊያ ቴክኖሎጂዎች ከቫይረስ መከላከያ ፕሮግራሞች አቅም በላይ እንደሆኑና በቀላሉ ወደ ግለሰቦች ኮምፒውተሮች በመግባት መረጃዎችን እንደሚወስዱ የጠቆመው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ከተቋሙ ኢሜይል አፈትልከው የወጡ መረጃዎችም ተቋሙ በሚያዝያ ወር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ከ700 ሺህ ዶላር በላይ የሚገመት አዲስ የቴክኖሎጂና የስልጠና ስምምነት ለመፈጸም ሲያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ ሳይሳካ መቅረቱን ያመለክታሉ ብሏል፡፡
ሃኪንግ ቲም ጉዳዩን በተመለከተ ምላሹን እንዲሰጥ ባለፈው ሃምሌ ወር ላይ ከሂውማን ራይትስ ዎች ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽም፣ የሚያመርታቸው ሶፍትዌሮች የሚንቀሳቀሱት በእሱ ሳይሆን በገዙት ደንበኞቹ መሆኑን ጠቁሞ፣ ቴክኖሎጂው ለስለላ ተግባር ስለመዋሉ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገልጾልኛል ያለው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ከተቋሙ አፈትልከው የወጡ መረጃዎች ግን የኢትዮጵያ መንግስት የስለላ ተግባራት የሰብአዊ መብቶችን የሚጥሱ መሆን አለመሆናቸውን ለማጣራት በርካታ አጋጣሚዎች እንደነበሩት የሚያመለክቱ ናቸው ብሏል፡፡
ተቋሙ በዚሁ ምላሹ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት በ2015 የመጀመሪያዎቹ ወራት ሙሉ ለሙሉ አቋርጫለሁ ማለቱንም ሂውማን ራይትስ ዎች ጠቁሟል፡፡

Published in ዜና

በሰኔና ሐምሌ ዝናብ ባልዘነበባቸውና ለድርቅ አደጋ በተጋለጡ አፋርና ወሎ እንዲሁም ሃረርና ድሬደዋ አካባቢ ሰሞኑን ዝናብ መዝነብ እንደጀመረ ምንጮቻችን ገልፀዋል፡፡
በድርቅ አደጋ በቀን እስከ 100 የቤት እንስሳት እየሞቱ በነበረበት የአፋር ክልል በአሁን ወቅት አስቸኳይ እርዳታና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮቹ፤ በተለይ ከሎጊያ እስከ ክልሉ ዋና መቀመጫ ሠመራና አካባቢው ተደጋጋሚ ዝናብ እንደዘነበ ተናግረዋል፡፡
ድርቅ ተከስቶባቸው ከነበሩ ቦታዎች አንዱ የድሬደዋና ሀረር ቆላማ አካባቢ ከባለፈው ሠኞ ጀምሮ መጠነኛ ዝናብ እየዘነበ ሲሆን በድሬደዋ ከተማ ጠንከር ያለ ዝናብ መዝነቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በድሬደዋ ገጠራማ አካባቢዎች ግን አሁንም የዝናቡ ሁኔታ የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዱ በሆነውና ከፍተኛ የድርቅ ስጋት አንዣቦበት የነበረው ከሸዋሮቢት እስከ ወሎ ባለው መስመር በሣምንቱ ተደጋጋሚ ዝናብ መዝነቡን በአካባቢው የሚገኙ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በምስራቅ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ተብሎ በሚታወቀው ከአዳማ እስከ መተሃራ ባለው አካባቢም በሳምንቱ የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም ዝናብ መዝነብ መቻሉን በአካባቢው የሚመላለሱ ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
የብሄራዊ ሜትሪዎሎጂ አገልግሎት ማክሰኞ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በሰኔና በሐምሌ ወር በሰሜን ምስራቅ፣ በመካከለኛው እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ ስምጥ ሸለቆ አካባቢዎችና በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍሎች ከመደበኛ በታች ዝናብ መዝነቡን ጠቅሶ በነሐሴ ወር በነዚህ አካባቢዎች የዝናቡ መጠን ሊጨምር እንደሚችል ተንብይዋል፡፡
በዘንድሮ ክረምት የተፈጠረው የዝናብ እጥረት የኤሊኒኖ ክስተት ውጤት መሆኑን የአየር ትንበያ ባለሙያው ዶ/ር ድሪባ ቆሪቻ ጠቅሰው፣ በፓስፊክ ውቅያኖስ አካባቢ የተፈጠረውን ሙቀት መጨመር ተከትሎ የዝናብ እጥረቱ መፈጠሩን ገልፀዋል። በነሐሴ ወር የዝናቡ ሁኔታ በሚፈለገው መጠን እንደሚዘንብና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ብሄራዊ ሜትሪዎሎጂ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

Published in ዜና

    ያለፈውን የትግል ሂደቱን ሲገመግም የሰነበተው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፤ አዲስ የትግል ስልት መቀየሱን ጠቁሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከግንባር ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ ለመሸጋገር ማቀዱን አስታወቀ፡፡
የአራት ብሄር ተኮር ፓርቲዎች ግንባር የሆነው መድረክ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እያንዳንዱን የፓርቲ አባላት በማሳመን በውህደት አንድ ፓርቲ እንደሚፈጥር የጠቆሙት አቶ ጥላሁን፤ በቀጣዩ ምርጫም አንድ ፓርቲ ሆኖ ለውድድር ይቀርባል ብለዋል፡፡
መድረኩ በሁለት ቀን ጉባኤው፣ አባል ድርጅቶች በውህደት ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው በመወያየት የውህደቱን ሂደት እንዲያፋጥኑ ከስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን በየ6 ወሩ በሚካሄደው ስብሰባም የውህደቱ አጀንዳ እንደሚገመገም ኃላፊው ገልፀዋል።
ግንባሩ ባለፈው የግንቦት ወር ምርጫ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን መገምገሙን የጠቆሙት አቶ ጥላሁን፤ ገዥው ፓርቲ ምርጫውን ለማሸነፍ ማስፈራራትን፣ ጉልበትንና የገንዘብ አቅምን መጠቀሙን፣ እንዲሁም ምርጫው ህግና ስርዓትን በተከተለ መንገድ አለመከናወኑን ገምግሟል ብለዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜና እሁድ መድረኩ ባካሄደው ጉባኤ፣ እስካሁን ያከናወናቸው ፖለቲካዊ ትግሎች ያስገኙትን ውጤትና በቀጣይ ሊወሠዱ የሚገቡ አዋጭ የትግል ስልቶችን መገምገሙን የጠቆሙት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ጥላሁን እንደሻው፤ ግንባሩ የነበሩበትን ድክመቶች ለይቶ ማስመቀጡንና ከአሁን በኋላ የመንግሥትን ጫና ተጋፍጦ ወደ ህዝቡ በመውረድ፣ የተለያዩ አደረጃጀቶች ፈጥሮ ለመታገል መወሰኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ምርጫዎች መድረኩ ጫናዎችን ተቋቁሞ ህዝቡን ለትግል በማደራጀትና በማንቀሳቀስ ረገድ የራሱ ድክመቶች እንደነበሩበት የገመገመ ሲሆን፤ ግንባሩ በምርጫው ሙሉ ኢትዮጵያን መወከል አለመቻሉም ተጠቅሷል፡፡ በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ የመድረኩ እንቅስቃሴ በደካማነት ተገምግሟል ያሉት አቶ ጥላሁን፤ በትግራይና በኦሮሚያ በአንፃራዊነት ተሳትፎው እንደጨመረ ገልፀዋል። በጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ አፋርና ሌሎች ክልሎች የመድረክ መዋቅር እንዳልተዘረጋ ሃላፊው ጠቁመው በቀጣይ በነዚህ ክልሎች መዋቅር ለማበጀት ግንባሩ እንደሚተጋ አስታውቀዋል፡፡
በሁለቱ ቀናት ጉባኤው ግንባሩ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ሊኖረው ስለሚገባ ግንኙነት መምከሩ የተገለፀ  ሲሆን ከመድረኩ አላማና ፕሮግራም ጋር የሚቀራረቡ ፓርቲዎችን ለመሳብ በሩን ከፍቶ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የተወሰነ ርቀት ሄዶ ለመጋበዝም እንዳቀደ ታውቋል፡፡

Published in ዜና

    ግሪን ኮፊ አግሮ ኢንዱስትሪ፤ የመንግሥት ይዞታ የነበረውን የቴፒ ቡና ተክል ልማት ድርጅት በ1 ቢ. ብር  ጠቅልሎ መግዛቱን አስታወቀ፡፡
ትናንት ረፋድ ላይ በሂልተን ሆቴል በተደረገው የሽ    ያጭ ውል ስምምነት፣ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገ/መስቀልና የግሪን ኮፊ አግሮ ኢንዱስትሪ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደለ አብርሃ ውሉን ተፈራርመዋል፡፡
አቶ ታደለ በተለይ ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፣ ግሪን ኮፊ ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት የቴፒ ቡና ተክል ልማት ድርጅትን ድርሻ 51 በመቶ በመያዝ፣ መንግሥት ደግሞ ቀሪውን 49 በመቶ ይዞ በሽርክና ለመሥራት ተስማምተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ 12 ሺህ ሄክታር ስፋት ያለውን የእርሻ ልማት፣ በ1 ቢሊዮን ብር እንደገለፁት አቶ ታደለ፤ የፊርማ ሥነ - ሥርዓቱ የተፈፀመው የዋጋውን 35 በመቶ፣ 265 ሚሊዮን ብር ባንክ አስገብተው ሲሆን ቀሪውን 65 በመቶ በ5 ዓመት ውስጥ ከፍለው ለማጠናቀቅ መስማማታቸውንም አስረድተዋል፡፡
12ቱ ሺህ ሄክታር መሬት ባረጁ የቡና ዛፎች የተሸፈነ ስለሆነ፣ ከ8-9 ሄክታሩን የተሻለ ምርት በሚሰጡ አዳዲስ ዝርያዎች መተካቱን ጠቁመው፣ ቀሪውም በየዓመቱ 1000 ያህል ሄክታር በአዲስ ምርታማ ዝርያ ይተካል ብለዋል፡፡ ከእርሻ ልማቱ አጠገብ የጋምቤላ ክልል ይዞታ የሆነውን 3ሺህ ሄክታር መሬት ክልሉን ጠይቀው ስለፈቀደላቸው አዲስ ፕሮጀክት ቀርፀው እንደሚያለሙትም አቶ ታደለ አክለው ገልፀዋል፡፡
ከእርሻው የሚገኘውን የቡና ምርት ኤክስፖርት በማድረግ 20 ሚሊዮን ዶላር እንደሚገኝ የጠቀሱት ባለሀብቱ፤ እርሻው ለማር ምርት አመቺ በመሆኑ በዓለም ተወዳጅ የሆነውን ኮፊ ሀኒ የተባለ የማር ዓይነት በአነስተኛ መሳሪያ እያዘጋጁ ወደ ውጭ ሲልኩ ቆይተዋል፡፡ አሁን በብዛት (50 እና 60 ኮንቴይነር ኮፊ ሀኒ) ወደ ውጭ በመላክ ከ4-5 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ፋብሪካ እየገነቡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የቴፒ ቡና እርሻ ልማት በረከት ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች እያመረቱ ለመላክ አቅደዋል፡፡ ብዙም ባይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ፓልም ኦይል የሚገኘው በቴፒ እርሻ ልማት ብቻ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ታደለ፤ ለሙከራ ከማሌዢያና ኢንዶኔዢያ የተለያየ ዝርያ አምጥተው በ120 ሄክታር መሬት ላይ በመትከል ምርቱ ደርሶ አይተውታል፡፡ በአነስተኛ መሳሪያ እያዘጋጁ በየወሩ አንድ መኪና ዘይት ለተለያዩ ድርጅቶች የሚያቀርቡ ሲሆን፤ ወደ ዘይት ከመለወጡ በፊት ያለውን ድፍድፍ፣ የሳሙና ፋብሪካዎች በጥሩ ዋጋ በሰልፍ እንደሚገዙና በየወሩ አንድ መኪና ድፍድፍ እንደሚሸጡ ተናግረዋል፡፡ የፓልም እርሻውን ወደ 10,000 ሄክታር ለማሳደግ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ኩባንያ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፣ የእርሻ መሬት ለማግኘት ከክልሉ ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም አቶ ታደለ ገልፀዋል፡፡
በቴፒ እርሻ ልማት ውስጥ ባሉ 6 እርሻዎች፣ 16ሺ ሰራተኞች ተቀጥረው እንደሚሰሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Published in ዜና

• ከ120 በላይ ሰዎች ተሸልመዋል
• የSMS ሎተሪ እስከ ጳጉሜ 2 ተራዝሟል

 የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (ኢሴማቅ)፤ ለእንቁጣጣሽ የ375ሺ ብር የመኪና ብር ስጦታ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ ነሐሴ 10 ይጠናቀቅ የነበረው 8400 የአጭር ጽሑፍ መልዕክት (SMS) የሎተሪ ዕጣ እስከ ጳጉሜ 2 ቀን 2007 ዓ.ም ተራዝሟል፡፡
ለኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ማዕከል የህንፃ ማስገንቢያ ታስቦ ሃምሌ 25 ቀን 2006 ዓ.ም ተጀምሮ የነበረው የ8400 የአጭር መልዕክት ጽሑፍ ሎተሪ፣ ከህዳሴው ግድብ የገንዘብ ማሰባሰቢያ 8100 የአጭር መልዕክት ጽሑፍ ሎተሪ ጋር በመገጣጠሙ፣ ከ6 ወር እንቅስቃሴ በኋላ መቋረጡን ኢሴማቅ አስታውሷል፡፡
በድጋሚ ከግንቦት 8 ቀን 2007 ጀምሮ የአጭር መልዕክት ጽሑፍ ሎተሪው ሲካሄድ መቆየቱን ጠቁሞ፣ ቀኑ በማጠሩ ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ድርጅት በተገኘ ፈቃድ እስከ ጳጉሜ 2 እንደተራዘመ ተገልጿል፡፡
የሎተሪ ጨዋታው ጊዜ በመራዘሙ በአዲስ መልክ የእንቁጣጣሽ ገጸ በረከት ይዘን ቀርበናል ያሉት የኢሴማቅ ዳይሬክተር፤ የሽልማቶችን ብዛትም ጨምረናል ብለዋል፡፡ አሸናፊዎች የልብስ ማጠቢያ ማሽን፣ ላፕቶፕ፣ ቴሌቪዥን፣ ሞተር ሳይክል፣ ፍሪጅና ሳምሰንግ ሞባይል እየተሸለሙ መሆናቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፤ በመጨረሻም የመኪና ሽልማቱ ዕጣ ይወጣል ብለዋል፡፡
የሎተሪ ዕጣ 8400 እንደገና ከተጀመረ ወዲህ ጥሩ ውጤት እያሳየና ዕድለኞችም እየተሸለሙ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፣ በየቀኑ ከሚበረከቱ ሳምሰንግ ሞባይሎች 85 ሰዎች፣ በየሳምንቱ ከሚሰጡ ቶሺባ ላፕቶፖች 7 ሰዎች፣ በየሳምንቱ ከሚሸለሙ 21 ኢንች ቴሌቭዥኖች 13 ሰዎች፣ በየ15 ቀኑ ከሚበረከቱ ዌስት ፖይንት ልብስ ማጠቢያ ማሽኖች 7 ሰዎች፣ በየሁለት ሳምንቱ ከሚሰጡ ሞተር ሳይክሎች 8 ሰዎች፣ በየ15 ቀኑ ከሚበረከቱ ፍሪጆች 9 ሰዎች መሸለማቸውን ገልፀው በሎተሪው አጋማሽ የሚወጣውን የቤት መኪና ዕጣም በሆሳዕና መምህራን ኮሌጅ አስተማሪ የሆኑት አቶ መሃሪ ዋኬሮ እንደተሸለሙ ተናግረዋል፡፡
ሎተሪው ብዙ ጥቅሞች እንዳለው ጠቅሰው ለሕንፃው ግንባታ የሚያስፈልገው 47 ሚሊዮን ብር ባይሞላም የኢሴማቅን ማንነት በኅብረተሰቡ ዘንድ ለማስተዋወቅ በእጅጉ እንዳገዘና ስለማህበሩ የበለጠ ግንዛቤ ለመፍጠር እንዳስቻለ ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡

Published in ዜና

...የእኔ ደም አይነት O-RH ነው፡፡ ስለሆነም የእኔ ደም በሌላ የደም አይነት ሊተካ የማይችል ነው። በመውለድም ሆነ በተለያየ ምክንያት እንደዚህ ያለ የደም አይነት ያላቸው ሰዎች ደም ሊሰጣቸው  ቢፈለግ የግድ O-RH መሆን አለበት፡፡ ስለሆነም እኔ     ምንግዜም ችግር ለሚገጥማቸው ሰዎች ደም በመለገስ መድረስ ስለምፈልግ የደም ባንክ ደንበኛ ነኝ፡፡ ደም መስጠት የጀመርኩት በ2001/ዓ/ም ሲሆን እስከአሁን ድረስ ወደ ሰባት ጊዜ ሰጥቻለሁ፡፡ አሁን አቋርጫለሁ። ያቋረጥኩት ግን በመውለድ ምክንያት ነው፡፡ ሁኔታዬ ሲደላደል ደግሞ እንደገና እቀጥላለሁ፡፡
ሕይወት ታደለ
እናቶች ሕይወት ሲሰጡ ሕይወታቸውን ማጣት የለባቸውም፡፡
ማንኛዋም እናት በሰለጠነ ሰው የሙያ ድጋፍ ልጅዋን መውለድ ይገባታል፡፡
ደም ሲሰጡ በቀላሉ የሚተኩት ሲሆን ለተቀባዩ ግን መተኪያ የሌለውን ሕይወት ማትረፊያ ነው፡፡
ደም በፈቃደኝነት መስጠት ማህበራዊ ግዴታ ነው፡፡
ደም መስጠትን በሚመለከት ከአሁን ቀደም የታዘቡትን ያጫወቱን አቶ እሸቱ ኃይሌ ከፒያሳ ናቸው፡፡
“...ባለቤቴ በሕመም ምክንያት ወደ ሆስፒታል ገብታ የቀዶ ሕክምና እንደሚያስፈልጋት ተነገረኝ፡፡ ለዚህም አገልግሎት ከሚያስፈልጉት ነገሮች አንዱ ደም ማቅረብ ነበር፡፡ እኔ በተደረገልኝ ምርመራ ደም መስጠት የማልችል ሆንኩ፡፡ አንዳንድ ቤተሰቦች ደግሞ በተለያየ ምክንያት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ስለዚህ ምን ይሻለኛል ብዬ ስጨነቅ... እንደኔው ደም ለመስጠት የቆመ ሰው ከምትቆም  ...ወጣ በልና አንድ ጎረምሳ ፈልግ አለኝ፡፡ እንዴት? የእኔ ጥያቄ ነበር፡፡ ትንሽ ገንዘብ ከሰጠሀቸው መጥተው ደም ይሰጡልሀል ነበር ያለኝ፡፡  ከዚያም አንዱን ይዤ ስሄድ... አንተማ በቅርብ ቀን ስለሰጠህ መስጠት አትችልም የሚል መልስ ተሰጠ፡፡ ከዚያም የተመለሰው ልጅ እራሱ አንዲት ሴት ልጅ ይዞልኝ መጣ፡፡ በዚህ መልክ የጠየቁኝን ገንዘብ ተደራድሬ ከፍዬ... የሁለት ሰው ደም ባንኩ ተክቶልኝ ለሆስፒታሉ አቀረብኩ፡፡ ይሄንን ገጠመኝ በፍጹም አልረሳውም። አሁን ግን እግዚአብሄር ይመስገን ሂዱና አምጡ የሚባለው ነገር ቀርቶአል አሉኝ...”
ከላይ ያነበባችሁት የሁለት ሰዎች አስተያየት የሚያሳየን ደምን በፈቃደኝነት መስጠት ለታማሚዎችም ይሁን ለአስታማሚዎች እንዲሁም ለሆስፒታሎቹ አሰራር በጣም ምቹ የሚሆን ከመሆንም በላይ ዜጎች ደም መስጠታቸው ደግሞ እንደ አንድ የውዴታ ግዴታ መወሰድ ያለበት ነገር መሆኑን ነው፡፡
እናቶች ከእርግዝና ጊዜ ጀምሮ እስከመውለድ ድረስ በሚኖራቸው ቆይታ በተለያየ ምክንያት የደም መፍሰስ ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ በተለይም በወሊድ ወቅት እስከ አስራ ሁለት ሰአት ድረስ ባለው ጊዜ በሚገጥም የደም መፍሰስ ምክንያት ህይወታቸው የሚያልፍ ብዙዎች ናቸው፡፡  ቀስ ብሎ ይደርሳል የማይባል... ጊዜ የማይሰጥ አጋጣሚ በምን ሊዳኝ ይችላል ቢባል የተዘጋጀ ደም መኖሩ የሚል መልስ የሚሰጠው ነው፡፡
የህክምና ባለሙያዎች ደም የሚያስፈልጋት ታካሚ ስትገጥማቸው ቤተሰቦቿን ደም አምጡ የሚል ትእዛዝ ከማስተላለፍ ባሻገር በተለይም ዛሬ ዛሬ እራሳቸው ተሳታፊ የሚሆኑበት ወይንም ደም የሚሰጡ መሆናቸው አበረታች ጅምር ነው ፡፡ ይህንን በሚመለከት የተወሰኑ ሐኪሞችን ለዚህ እትም አነጋግረናል፡፡
ዶ/ር ባልካቸው ንጋቱ በጳውሎስ ሆስፒታል ወይንም ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰርና መምህር እንዲሁም የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡
 “...የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያ እንደመሆኔ መጠን የደም ችግር ምን ያህል እንደሆነ በትክክል እረዳለሁ፡፡ ሁልጊዜም ደም ሲያስፈልግ አምጡ ብሎ ከማዘዝ ይልቅ የሚሻለው ደም እየሰጡ ምሳሌ በመሆን ሌሎችም በዝግጅት እራሳቸው ፕሮግራማቸው አድርገው ወገናቸውን ለማትረፍ ደም እንዲሰጡ ማድረግ ይገባል፡፡ ስለዚህም ይህ የማንኛውም ሰው ግዴታ ተደርጎ ቢወሰድ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ የህክምና ባለሙያው ከሌላው ሰው የሚለይበት ምክንያት በስራው ላይ ስላለና ችግሩን ስለሚያየው ሲሆን ሌላው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ የሚነግረው የሚያስ ተምረው ሰው ያስፈልጋል፡፡ በእኔ በኩል የሞራል ግዴታዬ ወይንም ማህበራዊ ግዴታዬ ነው ብዬ ስለማምን ለስድስተኛ ጊዜ ደም ለግሻለሁ፡፡”
ሌላው ያናገርናቸው ዶ/ር ሙስጠፋ ነጋሽ በእለቱ ደም ሰጥተው ወደ ቢሮአቸው ሲመለሱ ነበር ያገኘናቸው፡፡ ዶ/ር ሙስጠፋ በጳውሎስ ሆስፒታል ወይንም ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰርና መምህር እንዲሁም የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡ እሳቸውም እንደሚሉት፡-
“...እኛ ስራችን ከደም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ደም ከሌለ ስራችን ይቆማል ማለት ይቻላል፡፡ ስለሆነም እኛ ደም ሰጥተን ምሳሌ መሆን አለብን፡፡ ሐኪሙ እራሱ አምኖበት ደሙን ሲሰጥ የሚያይ ሰው ደም መስጠት ምንም ጉዳት እንደሌለው እና አስፈላጊ መሆኑን ይረዳል፡፡ ብሔራዊው የደም ባንክ ሰዎችን እያስተማረና እየቀሰቀሰ ደምን ከፈቃደኞች እና ከጤነኞች ሰዎች እየወሰደ ቢያከማች በችግር ጊዜ ያለምንም ችግር መውሰድ እና ታካሚዎችን ማዳን ይቻላል ማለት ነው። በችግር ጊዜ ደም ስጡ ሲባል ደም የሚሰጥ ከሆነ ሁሉም አገልግሎት ላይ ይውላል ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም በጤና እና በተለያዩ ምክንያቶች የተሰጠው ደም ከጥቅም ላይ ሳይውል ሊወገድ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ለእጥረት ይዳርጋል፡፡ ስለዚህ በጎ ፈቃደኞች ይህንን ማህራዊ ግዴታ አውቀውት ተግባራዊ ቢያደርጉት ጥሩ ነው፡፡
ዶ/ር ብርሀኑ ከበደ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ከአሁን ቀደም በነበረው አሰራር ሐኪሞች ባለባቸው የስራ መደራረብና ሌሎች ምክንያቶች እራሳቸው ደም እየሰጡ ምሳሌ የመሆናቸው ነገር ብዙም የሚታይ አልነበረም ይላሉ፡፡ ስለሆነም ሐኪሙ በአብዛኛው ደም አምጡ ይል ነበር፡፡ ነገር ግን በተለይም እናቶች በአጣዳፊ ሁኔታ በደም እጦት ሕይወታቸው ልታልፍ የምትችል በመሆኑ ከማንም በላይ ሐኪሙ ጉዳቱን ስለሚረዳ አሁን አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረው የሐኪሞች የደም መስጠት ልምድ እየዳበረ መጥቶአል፡፡ ስለዚህም እኛ ለተማሪዎቻችንም ይሁን ለህብረተሰቡ ምሳሌ ለመሆን የተቻለንን ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ የእናቶችን ሕይወት ለማትረፍ ደም እየሰጠን እንገኛለን፡፡ ማንኛውም ሰውም በደም እጦት ሕይወቱ ማለፍ ስለሌለበት የምንሰጠው ደም ለመላው ተገልጋይ ይጠቅማል የሚል እምነት አለን፡፡
ደም የመለገስ ደንበኛ የሆነችው ሕይወት ታደለ እንደምትለው
“...በእርግጥ ለእኔ የደም መስጠት ምክንያት የሆኑኝ የሁለት ወላድ ሴቶች በደም መፍሰስ ምክንያት ሕይወታቸውን ማጣታቸው ነው፡፡ ነገር ግን እኔ ደም የምሰጠው ለእናቴ ወይንም ለአባቴ ለእህት ወንድሞቼ ወይንም ለእከሌ በማለት አይደለም፡፡ ደም የምሰጠው ለማንኛውም ሰው ነው፡፡ እኔ በምሰጠው ደም እናቶች ወይንም በመኪና አደጋ     የተጎዱ ወይንም ሌሎች ሰዎች ድነውበታል የሚል እምነት አለኝ። ልክ ደም ሰጥቼ ስወጣ አንድ ሕይወት እንዳዳንኩ ስለሚሰማኝ እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡”  
በኢትዮጵያ ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ ወደ 85% የሚሆን የእናቶች ሞት ሲኖር ምክንያቶቹም ጽንስ በማቋረጥ ምክንያት 32% የተራዘመ ምጥ 22% ደም መፍሰስ 10% እና የደም ግፊት 9% ኢንፌክሽን 12% ናቸው፡፡ ይህንን ችግር ለመከላከልም በኢትዮጵያ የጤና ሽፋኑን ለማዳረስ ብዙ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው። 3.500 /የሚሆኑ የጤና ጣቢያዎች 130/ የሚደርሱ ሆስፒታሎች ወደ 90/ ሚሊዮን የሚሆን የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማዳን ተገቢውን ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ህ/ሰቡ ካለበት ድረስ ዘልቀው የጤና አገልግሎቱን የሚያደርሱ (38‚000) የሚሆኑ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች በስራ ላይ ናቸው፡፡
ሕይወት ታደለ እንደምትለው፡-
“...የደም ባንክ ደንበኛ በመሆኔ እስከአሁን በግሌ ለአባቴ እና ለእህቴ ደም ባስፈለገ ጊዜ ባንክ እንደአስቀመጥኩት ገንዘብ መዘዝ እያደረግሁ ተጠቅሜበታለሁ፡፡ በእርግጥ ልክ ገንዘብ ሲጎድል እንደሚሞላው ሁሉ እኔም ወደ ደም ባንክ ያወጣሁዋቸውን መልሼ ተክቼአለሁ፡፡ ማንኛውም ሰው ደም መስጠት ከባድ ነው ብሎ ማሰብ የለበትም። አንድ ሰው ደም ሲሰጥ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ በትክክል ወደነበረበት ቦታ የሚመለስ እና የሚጎድል አለመሆኑን መረዳት ይገባዋል፡፡
ደም መስጠት ባህል ሊሆን ይገባል። ምክንያቱም የሰዎችን ሕይወት ማትረፍ ነውና። የእናቶችን ሕይወት ቀላል ስጦታ በማድረግ ከማትረፍ በላይ የሚያስደስት ነገር የለም። ደም ለሰጪው በቀላሉ ሊተካው የሚችለው ነገር ሲሆን ለተቀባዩ ደግሞ ከባዱን እና መተኪያ የሌለውን ሕይወት ማትረፊያ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡”

Published in ላንተና ላንቺ

11 የኬንያ 8 የኢትዮጵያ ነው
                    
   ከሁለት ሳምንት በኋላ የሚጀመረው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዶፒንግ ዙርያ በተፈጠሩ አወዛጋቢ አጀንዳዎች መጥፎ ድባብ እያጠላበት ነው፡፡
በጀርመን ብሮድካስት ኩባንያ (ARD/WDR) እና በእንግሊዙ ሰንደይ ታይምስ ከሳምንት በፊት በዶፒንግ ማጭበርበር ዙሪያ የወጡ መረጃዎች ከመቶ በላይ አትሌቶችን በዶፒንግ ማጭበርበር ከስሰዋል፡፡ ሁኔታው የዓለም ሻምፒዮናውን የፉክክር ድምቀት ሊያደበዝዘው እንደሚችል ተሰግቷል፡፡ የዓለም አትሌቲክስን በሚመሩ ተቋማት በዶፒንግ ውንጀላው ዙሪያ የሚከተሉት አቅጣጫ ምን ሊሆን እንደሚችል በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ክሱ ከ2001-2012  እኤአ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናና በኦሎምፒክ የተሸለሙ አንድ መቶ ሃያ ሜዳልያዎች ትክክለኛነት በዶፒንግ ማጭበርበር ጥያቄ እንደሚነሳቸው የሚዲያ ተቋማቱ ቢገልፁም የስፖርቱን ዓለም ያሳሰበው የአትሌቲክስ ተወዳጅነት አደጋ ላይ መውደቁ ነው፡፡ በተጨማሪም 144 የዓለም ሻምፒዮንና የኦሎምፒክ አሸናፊዎች በዶፒንግ ማጭበርበር መከሰሳቸው እና ከእነዚህ የሜዳልያ አሸናፊዎች 55 የወርቅ ሜዳልያ የተሸለሙ መሆናቸውን የሚዲያ ተቋማቱ ገልፀዋል፡፡ ይህ ሁሉ አወዛጋቢ አጀንዳ በ2016 እ.ኤ.አ በብራዚሏ ከተማ ሪዮ ዲጂኔሮ የሚካሄደው 31ኛው ኦሎምፒያድ አንድ ዓመት ሲቀረው መነሳቱ ደግሞ ለመላው ዓለም መደናገርን ፈጥሯል፡፡
በጀርመኑ የብሮድካስት ኩባንያና በእንግሊዙ ሰንደይ ታይምስ ጋዜጣ የዶፒንግ ማጭበርበር ፈጽመዋል በሚል የተከሰሱት የ57 አገራት አትሌቶች ናቸው፤ በተለይ ከራሽያ ሜዳልያ አሸናፊ አትሌቶች 80 በመቶ በዶፒንግ ማጭበርበሩ ተጠያቂ መደረጋቸው እና የኬንያ 18 ሜዳልያ አሸናፊ አትሌቶችም በጥፋተኛነት መነሳታቸው የሚዲያዎችን ትኩረት የሳበ ነገር ነው፡፡  በ30ኛው የለንደን ኦሎምፒክ እንኳን 10 የወርቅ ሜዳልያ ድሎች የዶፒንግ ችግር አለባቸው በሚል መፈረጁ አስደንጋጭ ነው፡፡ የጀርመኑ የብሮድካስት ኩባንያ እና የእንግሊዙ ሰንደይ ታይምስ ይፋ ባደረጉት ዝርዝር መሰረት 30 የራሺያ፤ 28 የዩክሬን፤ 27 የቱርክ፤ 26 የግሪክ፤ 24 የሞሮኮ፤ 22 የቡልጋሪያ፤ 20 የባሕሬን፤ 19 የቤለሩስ ፤16 የስሎቬኒያ፤ 13 የሮማንያና የኡጋንዳ ፤ 12 የብራዚል፤  11 የስፔን፣ የኬንያ፣ የሆላንድና የኮሎምቢያ፤ 9 የጃማይካ፤ 8 የፖርቱጋል፣ ስሎቫኪያ፣ ኳታር፣ የኢትዮጵያና የኩባ፤ 7 የስዊድን፣ የቼክ፣ የኤርትራ፣ የባህማስና የደቡብ ኮሪያ፤ 6 የላቲቪያ፣ የጀርመን፣ የቤልጄም፣ የጣሊያንና የሜክሲኮ፤ 5 የቻይና፣ የአሜሪካ፣ የሀንጋሪ፣ የኖርዌይ፣ የፈረንሳይ፣ የፖላንድ፣ የጃፓን፣ የአልጄሪያና ህንድ፤ 4 የሉታንያ፣ ሂስቶንያ፣ ስዊዘርላንድ፣ የኦስትሪያ፣ የፊላንድ፣ የብሪታንያና የደቡብ አፍሪካ፤ 3 የአውስትራሊያ፣ የካዛኪስታን፣ የትሪንዳንድና የቶቤጐ፣ የአየርላንድ የካናዳና የሰርቢያ እንዲሁም 2 የኒውዝላንድ አትሌቶች በዶፒንግ ማጭበርበር ተከሰዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ  ከሳምንታት በኋላ በሚካሄደው የዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ በዶፒንግ ዙርያ የተፈጠሩ የውዝግብ አጀንዳዎች እየተወሳሰቡ መሄዳቸው ውጥረት እንደፈጠረ ነው፡፡
የእንግሊዙ ሰንደይ ታይምስ እና የጀርመኑ የብሮድካስት ኩባንያ ኤአርዲ ደብሊው ዲአር ከ2001 እስከ 2012 እኤአ 5ሺ አትሌቶች ያደረጓቸው 12ሺ የደም ምርመራዎች ዝርዝር መረጃ እንደደረሳቸው ካሳወቁ በኋላ ዓለም አቀፉ የዶፒንግ ተቋም ዋዳ ሁኔታውን በጣም እንዳስጨነቀው ገልፆ፤ መረጃዎች ትክክለኛ መሆናቸው ከተረጋገጠ የዓለም አትሌቲክስ ከስር መሰረቱ ሊናጋ እንደሚችልም እያሳሰበ ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ግዙፍ የአትሌቲክስ የውድድር መድረኮች የዶፒንግ ማጭበርበር በከፋ ሁኔታ መቀጠሉን አረጋግጠናል የሚሉት የጀርመኑ የብሮድካስት ኩባንያ እና የእንግሊዙ ሰንደይ ታይምስ እንዳስገነዘቡት በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና የውድድር መድረኮች ከተገኙ ሜዳልያዎች ሲሶው የተከለከለ መድሃኒት እና አበረታች ንጥረ ነገር በተጠቀሙ አትሌቶች የተመዘገቡ ናቸው በሚል ብጥበጣውን ቆስቁሰውታል፡፡ በሁለቱ የአውሮፓ ሚዲያዎች መረጃዎች መሰረት  በዶፒንግ ማጭበርበር የተጠቀሱት 800 አትሌቶች ያደረጓቸው የደም ምርመራዎች አጠራጣሪ እና የሚያደናግሩ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ የጀርመኑ ብሮድካካስት ተቋም ‹‹ታላቅ ምስጥር ጥላ የበዛበት የዓለም አትሌቲክስ›› በሚል የ55 ደቂቃዎች  ልዩ ዘጋቢ ፊልም የሰራ ሲሆን ዋዳ ይህን ፊልም በገለልተኛ ኮሚሽን ለማጣራት በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በወጣው መረጃ ዙርያ ይፋ ባደረገው መግለጫ አንዳችም ማረጋገጫ እንዳላገኘበት አመልክቶ፤ ተከታይ ርምጃዎችን ከመውሰድ በፊት ማጣራት እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በየዓመቱ ከዶፒንግ ጋር በተያያዘ  በአትሌቶች ላይ 35000 የደም ምርመራዎችን ያደርጋል፡፡ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በዶፒንግ ዙርያ የተሰሙ ክሶች ትክክለኛነታቸው ከተረጋገጠ የማያዳግም እርምጃ መውሰዳችን አይቀርም ብሏል፡፡
የኬንያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የዶፒንግ ክሱ ለዓለም ሻምፒዮና አትሌቶቻችን በመረጥን ማግስት ይፋ መሆኑ የቡድን መንፈሳችን የረበሸ ብሎ አውግዞ፤ ክሶቹ ይፋ ከመሆን በፊት በዶፒንግ ችግር ዙርያ ለአትሌቶች በቂ ግንዛቤ በመፍጠር መሰራት ነበረበት በሚል ሁኔታውን አጣጥሎታል፡፡ ለዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፕሬዝዳንትነት የሚወዳደረው አሁን ምክትል ፕሬዝዳንት የሆነው እንግሊዛዊው ሴባስቲያን ኮው በበኩሉ የዶፒንግ ክሱን በአትሌቲክስ ስፖርት ላይ የተከፈተ የጦርነት አዋጅ ብሎታል፡፡ የስፖርቱን ክብር እና ዝና ለመጠበቅ ሁላችንም በሃላፊነት የምንሰራበት ወቅት ብሎ ኮው ሲናገር፤ ለፕሬዝዳንትነት የሚፎካከረው ሰርጄይ ቡብካም የዶፒንግ ችግር በ21ኛው ክፍለዘመን በአትሌቲክስ ስፖርት ላይ የተጋረጠ አደጋ መሆኑን ገልፆ፤ የምርመራ እና የክትትሉን መንገድ ማጠናከር ቢሻል እንጂ አትሌቶችን መወንጀል ተገቢ አይደለም ብሏል፡፡
የወቅቱ የአይኤኤኤፍፕሬዝዳንት የሆኑት ሴኔጋላዊው ላሚን ዲያክ በበኩላቸው የአትሌቲክስ ስፖርትን በአስከፊ ቀውስ የከተተ ብለው ብዙ ሁኔታዎች በቂ ማረጋገጫ ሳይኖራቸው አትሌቶችን ለማዋረድ መሞከሩ የሚያሳፍር ብለውታል፡፡
የዶፒንግ ማጭበርበሩ በተለይ ፅናት በሚፈልጉ የአትሌቲክስ ውድድሮች ስፖርተኞች በደማቸው በቂ የኦክሲጅን ክምችት እንዲኖራቸው የሚያስችሉ መድሃኒቶችን ከመጠቀም ጋር ተያይዞ የተነሳ ነው፡፡ አይኤኤኤፍ ባለፉት 15 ዓመታት በዶፒንግ ዙርያ ከ19ሺ በላይ የደም ምርመራዎች በአትሌቶች ላይ ማድረጉን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን እስከ 2.3 ሚሊዮን ዶላር በጀት በማንቀሳቀስ የሚያካሂደው ክትትል ነው፡፡
በተያያዘ 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በቻይናዋ ከተማ ቤጂንግ ከ2 ሳምንት በኋላ የሚጀመር ሲሆን ኢትዮጵያ እና ኬንያ የውድድሩ ድምቀት ከሚሆኑ ተሳታፊዎች ግንባር ቀደም ናቸው፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ሞስኮ አስተናግዳ በነበረችው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ 46 አትሌቶችን ያሳተፈችው ኢትዮጵያ 3 የወርቅ፤3 የብር እና 4 የነሐስ  በድምሩ 10 ሜዳልያዎችን በማግኘት ከዓለም 6ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቅቃለች፡፡ 3 የወርቅ ሜዳልያዎች በ800 ሜትር መሃመድ አማን፤ በ5000ሜትር መሰረት ደፋር እንዲሁም በ10ሺ ሜትር ጥሩነሽ ዲባባ የተመዘገቡ ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የኮምኒኬሽን ክፍል እንደገለፀው 33 አትሌቶች የሚገኙበት ቡድን የዝግጅት ሂደት  እንደቀጠለ ነው፡፡ አትሌቶቹን  በወቅታዊ ብቃት፣ በሚኒማና በበርካታ የመምረጫ መስፈርቶች ተለይተው ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው ያለው አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ፤ ከመካከለኛ እስከ ማራቶን ድረስ ባሉት ኢቨንቶች የሚካፈሉት እነዚህ አትሌቶች በአራራት ሆቴል ካምፕ አድርገው የቤጂንግን የአየር ንብረት መቋቋም ይችሉ ዘንድ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረጉ ናቸው፡፡ ከቃሊቲ እስከ ሶደሬ ድረስ በሚገኙ ሞቃት አካባቢዎች ልምምዳቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ መደረጉን ያመለከተው መግለጫው ቤጂንግ ላይ  ከአትሌቶቻችን  አስደናቂ ውጤት እንደሚጠበቅም ተስፋ አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የቅርብ ተቀናቃኝ የሆነችው ኬንያ በቤጂንግ 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 40 አትሌቶችን እንደምታሳትፍ ታውቋል፡፡ በዚሁ የኬንያ ቡድን የቀድሞና የአሁን የዓለም ሻምፒዮንና የኦሎምፒክ አሸናፊዎች የተካተቱበት ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በሞስኮ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኬንያ አሥራ ሁለት ሜዳልያ በማግኘት ከራሽያ፣ ከአሜሪካና ከጃማይካ ቀጥላ በዓለም በአራተኛ ደረጃ ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡          

  በ15 ዓመት 30 ት/ቤቶች አሠርቶ፣ ከ225 ሺህ ዜጐች በላይ አስተምሯል
              አያት አካባቢ ሪል እስቴት እየሠራ ሲሆን ሌሎች ቢዝነሶችም አሉት
                 4ኛው አዲስ አልበሙ ለዲያስፖራ በዓል ይለቀቃል
              ከ30 ጋንግስተሮች ከፍተኛ አደጋ ማምለጥ ችሏል
                          
   በቺካጐ - አሜሪካ 1000 ሰዎች የሚያስተናግድ ትልቅ ክለብ ነበረው፡፡ እነሱ በሳምንት ሁለት ቀን ይዘፍናሉ። ሌላውን ቀን ባንዱ ይጫወታል፡፡ በ2008 (እ.ኤ.አ) የአሜሪካ ኢኮኖሚ ቀዝቀዝ ብሎ ስለነበር የባንዱ ገቢ እየቀነሰ መጣ። ከዚያ በፊት ወደ ኢትዮጵያ ይመላለስ ስለነበር የአገሪቷን ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ ሰላሟን ጭምር ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ልመለስ? አልመለስ? እያለ ሲያመነታ ነበር፡፡
በምርጫ 97 ወቅት ከፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅና ከፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ጋር ሆነው በመንግሥትና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል እርቅ ለመፍጠር ሞክረዋል። በዚህ አጋጣሚ ከመንግሥትና ከጠቅላይ ሚ/ር መለስ ጋር ብዙ ጊዜ ተነጋግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚ/ሩን በተደጋጋሚ በግል የማነጋገር ዕድልም አግኝቷል፡፡ እሳቸው ለምን ወደ አገርህ ገብተህ ኢንቨስት አታደርግም? እያሉ ያነሳሱት ነበር፡፡ ስለዚህ ማመንታቱን ትቶ ወደ አገሩ ለመመለስ ወሰነ፡፡
ቺካጐ ያለውን ቢዝነሴን ዘግቼ ወደ አገሬ ልመለስ ነው ሲል አሜሪካ ያሉ ታዋቂ የጋዜጣ፣ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጋዜጠኞች፡- “ቺካጐ ትሪቡን” “ሲቢኤስ”፣ “ኤንቢኤስ”፣ “ሲኤንኤን፣…የዓለም ታዋቂ ሚዲያዎች ካሜራቸውን በከባድ መኪና ደግነው ቤቱ ድረስ በመሄድ በጥያቄ እንዳጣደፉት ይናገራል፡፡
ለምንድነው ይህን የዓለም ሕዝቦች መገናኛ የሆነውን የቺካጐ የባህል ማዕከል (መልቲንግ ፖት) ዘግተህ የምትሄደው? ለደንበኞችህስ ምንድነው ያሰብከው?... እያሉ ጥያቄያቸውን አዥጐደጐዱለት፡፡ በዚህ ጊዜ አንድ ሐሳብ መጣለት - አገሩን ማስተዋወቅ፡፡ የዓለም ጋዜጠኞች እቤቱ መጥተውለት እንዴት ይህን ዕድል ይለፈው?! አሁን ኢትዮጵያ እያደገች ነው፡፡ 60 በመቶ የሥራ ኃይሏ ከ25 ዓመት በታች የሆነ ወጣት ነው፡፡ በዚህ ላይ የጉልበት ዋጋ ርካሽ ነው፣ ለኤሌክትሪክ የሚከፈለው ኪራይ እጅግ ዝቅተኛ ነው፣ ተዝቆ የማያልቅ ጥሬ ሀብት ሞልቷል… በማለት ነገራቸው፡፡
 በማግስቱ ታዲያ የአገሬው ትልቁ ጋዜጣ “ቺካጐ ትሪቡን” የእግር ኳስ ጨዋታ ይመስል “አዲስ አበባ ዎን፤ ቺካጐ ሎስት” (አዲስ አበባ አሸነፈች፤ ቺካጐ ተሸነፈች) በማለት በፊት ገጹ ዘገበው፡፡
ወደ ክበቡ የሚመጡት ሰዎች ቺካጐ ውስጥ አሉ የተባሉ ፕሮፌሰሮች፣ ዶክተሮች፣ ሀብታም ነጋዴዎች፣ የኮርፖሬሽንና የኩባንያ ማናጀሮች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣… ብቻ የማይመጣ ሰው አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ለ27 ዓመታት እዚያ እየመጣ ፣ እየተዋወቀ፣ እየተጋባ፣ ልጆቹ ሲመረቁ እዚያ እየሄደ ተዝናንቷል፤ ተደስቷል፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ ሴኔተር ሆነው በክለቡ ተዝናንተዋል። በቅርቡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ኢትዮጵያን ሲጐበኙ አብረዋቸው የመጡት የንግድ ሚኒስትሯ ፔኒ ፕሪትስከር፣ ዴቪድ ፕሪትስከር የተባለው ልጃቸው ከኮሌጅ ሲመረቅ ከቤተሰባቸው ጋር በዚያ ነበር የተዝናኑት፡፡
ለአንድ ሳምንት የቆየ ፕሮግራም አዘጋጅተው ነው ሕዝቡን የተሰናበቱት፡፡ በዚያን ወቅት በርካታ ፈረንጆች አልቅሰዋል፡፡ የሕዝቡና የጋዜጠኞቹ ሁኔታ ለአገር የሚበጅ ነገር እንዲያስብ አመቺ ሁኔታ ፈጠረለት፡፡ እነዚህን ሁሉ የከበሩ ሀብታም ሰዎች ዝም ብዬ ከምበትን ለምን ቱሪስት አድርጌ ወደ አገሬ እንዲመጡ አላደርግም? በማለት አሰበ። አገሬ ገብቼ ቢዝነስ እሠራለሁ  እንጂ የቺካጐውን ክለብ በአዲስ አበባ እከፍታለሁ የሚል ሐሳብ በጭራሽ አልነበረውም፡፡ ሆኖም የለመደው ሕዝብ በቱሪስትነት መጥቶ ኢትዮጵያን እንዲጐበኝ ለማነሳሳት “በእርግጥ ክለቡን ጭራሽ ልዘጋው ሳይሆን አዲስ አበባ ልወስደው ነው” አለ፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ጓዙን ጠቅልሎ የመጣው የዛሬ 4 ዓመት ነው፡፡ አሁን  በአያት አካባቢ ቤት (ሪል እስቴት) እየሠራ ነው። በሽርክና የገዙትን የኮንስትራክሽን ማሽነሪም ያከራያሉ፡፡ ሁለት ዶክሜንተሪ ፊልሞችን ሠርቷል፡፡ አንዱ ባስገነባቸው 30 ት/ቤቶች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በውጭ ያለው 2 ሚሊዮን ያህል ኢትዮጵያዊ ትንሽም ቢሆን የበኩሉን ጥረት ቢያደርግ አገሪቷን ሊለውጥ እንደሚችል ለማሳየት የሠራው ነው፡፡ ይህ ፊልም የዛሬ ዓመት ተኩል ገደማ በሲኤንኤን ኢንሳይድ አፍሪካ ፕሮግራም በጥቂቱ ቀርቧል፡፡ ሌላው ከአቢሲኒያ ፓይለት ማሠልጠኛ ት/ቤት ባለቤት  ከካፒቴን ሰለሞን ጋር በመሆን የማሻን ደን የሚያሳይ ትምህርታዊ ዶክሜንተሪ ፊልም ነው፡፡
በዘፋኝነቱ ደግሞ ለዲያስፖራዎች በዓል የሚለቀቅ “አይዞኝ” የተባለ አዲስ አልበም ሠርቷል፡፡  አልበሙ ኤልያስ መልካ፣ ሄኖክ መሐሪ፣ አየለ ማሞ፣ ታደለ ገመቹ ሁንአንተ ሙሉ የተሳተፉበት ሲሆን ሁለት ኦሮምኛ፤ የተቀሩት አማርኛና ሬጌ (እንግሊዝኛ) የሚበዛባቸው 12 ዘፈኖችን ያቀነቀነው እስካሁን ታሪኩን የተረኩላችሁ አርቲስት ዘለቀ ገሠሠ ነው፡፡
ዘለቀ ገሠሠ የተወለደው በአንድ ወቅት የኢትዮጵያና የኢሊባቡር (ኢሉአባቦራ) ዋና ከተማ በነበረችው ጐሬ ነው። እስከ 13 ዓመቱ ድረስ በትውልድ መንደሩ ሲማር ቆይቶ፣ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ አዲስ አበባ መጣ። ሕይወቱን እየመራበት ያለው የሙዚቃ ፍቅር የተጠነሰሰው እዚያው ጐሬ ሳለ ነው፡፡ ጐረቤቱ ሚሽነሪዎች ስለነበሩ ወደ ሙዚቃ ዓለም ያስገቡት እነሱ ናቸው፡፡ እቤታቸው እየሄደ ፒያኖ ይጫወት ነበር፡፡ በሙዚቃ እንዲገፋ ምክንያት የሆኑት ደግሞ እናቱ ናቸው። አዲስ አበባ እንደመጣ ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው ያኔ ፕሪንስ ዘነበወርቅ፣ አሁን ሚስፎርድ በሚባለው ት/ቤት 9ኛ ክፍል ገባ፡፡ ሚስ ፎርድ አሜሪካዊ ስለሆኑ እናቱ  “አንተ ከእነሱ ጋር ተለማምደሃልና እሳቸው ጋ ገብተህ ተማር” አሉት፡፡ እዚያ ት/ቤት ሁለት ዓመት እንደተማረ፣ ወደ ያኔው ልዑል መኮንን፣ አሁን አዲስ ከተማ መሰናዶ ት/ቤት ተዛወረ፡፡
ወቅቱ ተማሪዎች “መሬት ለአራሹ” እያሉ የሚጮሁበት ጊዜ ስለነበር በትምህርቱ አልገፋም፡፡ ዘለቀ ሙዚቃ መጫወት የጀመረው 9ኛ ክፍል ሳለ ነው፡፡ ያኔ ጀነራል ዊንጌት ይማር የነበረው ታላቅ ወንድሙ ሙሉጌታ ገሠሠ፣ ድራመሩና ኪ ቦርድ ተጫዋቹ ከሳንጆሴፍ፣ ዘለቀ ከሚስ ፎርድ ት/ቤት ሆነው፣ አራት ወጣት ሙዚቀኞች ናይጄሪያ ኤምባሲ አካባቢ በ1964 ዓ.ም ዳሎል ባንድን መሠረቱ፡፡ ዳሎል ባንድ በዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምረቃ፣ በ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የወላጆች በዓል ቀን እየተጋበዘ ሙዚቃ ያቀርብ ነበር፡፡
ምኒሊክ ወሰናቸውና አያሌው መስፍን ወጣቶቹ በነበራቸው የሙዚቃ ችሎታ በጣም ይወዷቸው ነበር። ስለዚህ ት/ቤት ሲዘጋ ምኒሊክና አያሌው አማርኛ፣ ዘለቀ እንግሊዝኛ እየዘፈኑ የትያትርና ድራማ ክበቦችን ይዘው በየክፍለሀገሩ እየተዘዋወሩ ሙዚቃ ያቀርቡ ነበር፡፡ ይህን የትያትርና ሙዚቃ ትርዒት ከ66ቱ አብዮት በፊት ለአንድ ዓመት፣ ከአብዮቱ በኋላ ለሁለት ዓመት ቀይ ሽብር እስኪጀመር ድረስ በየክፍለ ሀገሩ ቀርቧል፡፡
የዳሎል መበተን
ወጣቶቹ ሙዚቀኞች የሚጫወቱት የምዕራቦቹን ዘፋኞች የጀምስ ብራውን፣ ስቲቪ ዎንደር፣ አሪታ ፍራንክሊን፣… ዘፈኖች ስለነበር ሶሻሊስቱ ደርግ ደስ አላለውም፡፡ ወቅቱ የወሎ ድርቅ የተከሰተበት ጊዜ ነበር። በየ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ያሉ 10 የወጣት ባንዶች በድርቅ ለተጐዱ ረሃብተኞች ገቢ ማሰባሰቢያ በስታዲየም ትልቅ የሙዚቃ ድግስ (ኮንሰርት) አዘጋጁ፡፡ 10ሺህ ቲኬቶች ከሸጡ በኋላ ደርግ ሙዚቃዎቹን ሳንሱር አድርጐ፣ ዝግጅቱ በሚቀርብበት ዕለት ይህን የኢምፔሪያሊስት ሙዚቃ ማቅረብ አትችሉም ብሎ ከለከላቸው፤ ካልቾ የቀመሱም ነበሩ፡፡
የዕድገት በሕብረት ዘመቻ ታውጆ ስለነበር፣ 10ኛ ክፍል የደረሱ ሁሉ የመዝመት ግዴታ ነበረበት፡፡ የዳሎል ባንድ አባላትም ለዘመቻ ተመዘገቡ፡፡ ወጣቶቹ ሙዚቀኞች አንድ ሐሳብ መጣላቸው፡፡ እኛ ተበታትነን ከምንዘምት አንድ ላይ ሆነን፣ በየዘመቻ ጣቢያ እየዞርን ዘማቾቹን እናነቃቃ በማለት ሐሳባቸውን ለዘመቻ መምሪያ ሄደው አቀረቡ፡፡ በቢሮው የነበሩት ኮሎኔል (አሁን በሕይወት የሉም ተገድለዋል) ዱላ ቀረሽ ስድብ አውርደውባቸው ተባረሩ፡፡
በዚያን ወቅት ት/ቤቶች ተዘግተዋል፤ ሙዚቃቸው የኢምፔሪያሊስት ነው ተብሎ ተከልክሏል፡፡ በዚህ ላይ ኪቦርድ ተጫዋቹ ጓደኛቸው ተገድሎና ሬሳው ፒያሳ ተጥሎ ሲያዩ በጣም አዘኑ፤ ተስፋ ቆረጡ፤ አገር ጥለው ለመሰደድ ቆረጡ፡፡
ለአንድ ሳምንት በእግራቸው ተጉዘው ጂቡቲ ደረሱ። በጂቡቲ መጥፎ ዕድል አጋጠማቸው፡፡ በስደተኝነት ለመመዝገብ የሄዱበት ጣቢያ አዛዥ የኢሳ ጐሳ አባል ነበር፡፡ ያ ሰው ኢትዮጵያና ሱማሌ ባደረጉት ጦርነት በመሸነፋቸው፣ ለኢትዮጵያውያን ጥሩ አመለካከት ስላልነበረው ደርግ እንዲያስራቸው በመኪና አሳፍሮ ወደ ኢትዮጵያ መለሳቸው። መኪናው እየተጓዘ ሳለ ሳይጠበቅ ከባድ ዶፍ ዝናብ ጣለና መኪናው ጐርፉን መሻገር ስላቃተው እዚያው አውርዷቸው ተመለሰ፡፡
ወጣቶቹ ስደተኞች ተስፋ ሳይቆርጡ ዞረው ወደ ጂቡቲ ተመለሱ፡፡ የጅቡቲ ድንበር አጥር ስላለው ሾልከው ገቡና በስደተኝነት ተመዝግበው ለአንድ ወር ታሰሩ፡፡ ከእነዘለቀ ቀድሞ ታላቅ ወንድሙ ሙሉጌታ ገሠሠ ጅቡቲ ገብቶ ነበር፡፡ ሙሉጌታ፣ በዚያን ወቅት ሥልጣን ላይ የነበረ የጅቡቲ ጠቅላይ ሚ/ር ዘመድ የሆነ የሚያውቀው ሙዚቀኛ ልጅ አግኝቶ ወደ ወህኒ ቤቱ አምጥቶ አስተዋወቃቸው። ልጁ የባለሥልጣን ወገን ስለሆነና ሰዎቹን ስለሚያውቅ አስፈትቷቸው ጅቡቲ ገቡ፡፡
የሙዚቃ ፍላጐታቸው ስላልበረደና ተመሳሳይ ስሜት ያላቸው ወጣቶች ስለተገናኙ፣ ያስፈታቸውን ልጅ ወኪላቸው አድርገው “ብራዘርስ ባንድ” የተባለ የሙዚቃ ክለብ አቋቋሙ፡፡ ታላቅ ወንድማቸው አዲስ ገሠሠ፤ በንጉሡ ጊዜ የአውሮፕላን አብራሪነት ትምህርት ለመማር አሜሪካ ተልኮ ነበር፡፡ ደርግ ሥልጣን ሲይዝ ሳይመለስ እዚያው ቀረ፡፡ በጂቡቲ ለ6 ወራት ሙዚቃ ሲጫወቱ ከቆዩ በኋላ የአዲስን አድራሻ እንደምንም አፈላልገው መጻጻፍ ጀመሩ፡፡ በጂቡቲ ቆይታቸው ዕድለኞች ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ጥሩ እየሠሩ ከመሆኑም በላይ፤ ልጁ ትልቅ ቤት ተከራይቶላቸው ስለነበር፣ ስደተኞቹ ሙዚቀኞች ለ20 ሌሎች ስደተኞች መጠለያ ሆነው ነበር፡፡
አሜሪካ መግባትና ውጣ ውረድ
አዲስ ገሠሠ አሜሪካ የሚገባበትን ዘዴ ያውቃል። የተማሪ ቪዛ አውጥቶላቸው የአውሮፕላን ቲኬት ልኮላቸው በ1971 ወንድማማቾቹ ሙሉጌታና ዘለቀ ገሠሠ አሜሪካ ገቡ። የያዙት የተማሪ ቪዛ ስለሆነ ኮሌጅ ገብቶ መማር እንጂ ሥራ መሥራት አይችሉም፡፡ አዲስ ገሠሠ ቺካጐ ስለሆነ እነዘለቀም ማረፊያቸው ቺካጐ፣ ትምህርታቸው ኤሊኖይ ሆነ፡፡ በአሜሪካ ኮሌጆች ስትማር ስኮላር ሺፕ (ነፃ የትምህርት ዕድል) ካላገኘህ በስተቀር የውጭ ዜጋ ለትምህርት የሚከፍለው ነዋሪዎቹ ከሚከፍሉት እጥፍ ነው፡፡
ለመኖር፣ ለቤት ኪራይ፣ ለት/ቤት ክፍያ፣… ከአንድ በላይ ሥራ ማግኘት ፍላጐት ሳይሆን ግዴታም ነው። “ከ24 ሰዓት ውስጥ 4 ሰዓት ነው የምንተኛው፡፡ 4ቱ ሰዓት የትምህርት ሲሆን ቀሪው ሥራ ላይ የምትቆይበት ነው፡፡ እኔ ግሮሰሪ ውስጥ ክለርክ ነበርኩ፡፡ ክለርክ ማለት ዕቃ ያወርዳል፣ ይደረድራል፣ ቤት ይጠርጋል… የዚህ ዓይነት ከባድ ሥራ እየሠራን ነው ለኮሌጅ የምንከፍለው፡፡ እየቆየን ስንሄድ መንጃ ፈቃድ አውጥተን ታክሲ መሥራት ጀመርን፡፡ እንዲህ እየሠራን፣ እየተማርን፣ ሙዚቃ እየተጫወትን ነው አሜሪካ የኖርነው” ይላል ዘለቀ፡፡
የዳሎል ዳግም ልደት
ያለ ዕረፍት ቀን ተሌት እየሠሩ፣ ጂቡቲ ለቀሩት የዳሎል ባንድ አባላት የአውሮፕላን ቲኬትና አስፈላጊ ዶክመንቶች ልከው እንዲቀላቀሏቸው አደረጉና ኤሊኖይ በገቡ በዓመታቸው ዳሎል ባንድ እንደገና በአሜሪካ ተመሠረተ፡፡ የመጀመሪያ ሙዚቃቸውን ያቀረቡት በሚማሩበት ኢሊኖይ ኮሌጅ ነበር፡፡ በአሜሪካ ለጥቁሮች የሚከበር (ፌብሩዋሪ ብላክ ሂስትሪ መንዝ) የሚባል ወር አለ፡፡
ለዚያ በዓል አከባበር ሙዚቃ እናቅርብ በማለት ጠየቁ። አሜሪካኖቹ አላመኑም፡፡ አንድ ጥሩ መምህር ነበሩ፡፡ እስቲ እንሞክራቸው ብለው ፈቀዱላቸው፡፡ ዳሎል ባንድ ሙዚቃውን አቀረበ፡፡ ተመልካቹ በጣም ተደስቶ አጨበጨበላቸው፡፡ ወጣቶቹ ያጨበጭቡልናል ብለው ስላልጠበቁ፣ ሞራላቸው ተበረታታና የተሻለ መጫወት ቀጠሉ፡፡
በዚያን ወቅት አሜሪካ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ባንድ አልነበረም፡፡ ሙዚቃቸውን ይዘው ዋሽንግተን ሄዱ። እዚያ፣ የመጀመሪያውን ኢትዮጵያዊ ሬኮርድ ካምፓኒ የጀመሩት አቶ አመሃ እሸቴ የተባሉ ሰው ብሉ ናይል የተባለ ሬስቶራንት ነበራቸው፡፡ ያኔ እዚያ የነበሩት አቶ አብነት ገ/መስቀልም በሙዚቃው ረድተዋቸዋል፡፡  በዚያ ሬስቶራንት ለዘመን መለወጫ ዝግጅታቸውን አቀረቡ። እዚያ የነበረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በጣም ወዶላቸው ተመለሱ፡፡ ለፋሲካ በዓልም በዋሽንግተን ደግመው ካቀረቡ በኋላ፣ ዳሎል ባንድ ካሊፎርኒያም ሄዶ ትልቅ ዝግጅት አቀረበ፤ በጣም ተወደደለት፡፡
ከቦብ ማርሌ ቤተሰብ ጋር ትውውቅ
ካሊፎርኒያ እያሉ እንደ ዕድል ሆኖ ስቲቪ ወንደርን አገኙ፡፡ ስቲቪ ኩባንያ ውስጥ የሬዲዮ ማናጀር ሆና የምትሠራ ኢትዮጵያዊት ዶክተር ነበረች፡፡ ሙዚቃቸውን ሲያቀርቡ አይታቸው ኖራ፣ ስቲቪ‘ኮ የኢትዮጵያ ወዳጅ ነው፡፡ የኢትዮጵያንና የጃማይካን ሙዚቃ በጣም ይወዳል።  ላስተዋውቃችሁ ብላ አስተዋወቀቻቸው። ስቲቪ በስቱዲዮው 5 ሙዚቃ ቀድቶላቸው እንዴት የአሜሪካ ሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ መግባት እንደሚቻል ነገራቸው። መጀመሪያ ዴሞቴፕ አንድ አምስት ዘፈን ቅዱ፤ ፎቶ ተነሱ። ከዚያ ታሪካችሁንና ስልካችሁን ጽፋችሁ እንደ ፓኬጅ አድርጋችሁ ለየኩባንያው ላኩ ብሎ መከራቸው፡፡
የባንዱ መሪ ዘለቀ ማናጀሩ ደግሞ አዲስ ገሠሠ ነበሩ፡፡ እንደተመከረው አድርጐ ፕሮፋይላቸውን ለ25 ኩባንያዎች ላከ፡፡ በአጋጣሚ ፓኬጁ የተላከለት አንደኛው ኩባንያ ለንደን የሚገኘው የቦብ ማርሌ አይላንድ ሬከርድስ ነበር። ያኔ ቦብ ማርሌ ካረፈ ዓመት እንኳ አልሞላውም። የኩባንያው ኃላፊ አስቸኳይ መልዕክት ለቦብ ማርሌ ሚስት ለሪታ ማርሌ ጃማይካ ላከላት፡፡ ሪታ ደስ ብሏት “ቦብም‘ኮ ሕልሙ ከኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ጋር መሥራት ነበር። እሱ አሁን በሕይወት ባይኖርም በቅርቡ ሙት ዓመቱን ስለምናከብር እዚያ ላይ ቢገኙ ጥሩ ነው” በማለት በዘለቀ ቁጥር ደወለችለት፡፡
ስልኩን አንስቶ ሄሎ ሲል “ሪታ ማርሌ ነኝ” ስትለው ያልጠበቀው ነገር ስለሆነበት ደንግጦ ስልኩን ሊጥለው ነበር። የቦብን ሕልም ነግራው በሙት ዓመቱ ላይ ቢገኙ ደስ እንደሚላት ገለፀችለት፡፡ ሐሳቡን ቢቀበልም አንድ ችግር እንዳለባቸው አጫወታት፡፡ ያን ጊዜ የነበራቸው የተማሪ ቪዛ ስለሆነ ከአሜሪካ ውጭ መጓዝ እንደማይችሉ ነገራት፡፡ ልዩ ደብዳቤ ጽፋ ለጃማይካ ቆንስላ ላከች፡፡ የጃማይካ ቆንስላ ደግሞ ለአሜሪካ ሚግሬሽን ጽፎ የዳሎል ባንድ አባላት ጃማይካ ገቡ፡፡
የቦብ ሙት ዓመት የተከበረው ተራራ ላይ ነበር፡፡ ዳሎሎች እዚያ ላይ ሙዚቃቸውን ሲያቀርቡ ያላያቸው የዓለም የሙዚቃ ኢንዱስትሪ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ተመልካቹም በጣም ተደሰተ፤ ሪታም እጅግ ፈነጠዘች፡፡ ያኔ እነ ዚጊ ማርሌ ልጆች ነበሩ፡፡ ቦብም ሆነ ልጆቹ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ባህል የቆረቡ ክርስቲያኖች ናቸው። ሪታ፤ “እናንተን ማግኘቴ የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆነ ነው፡፡ ከልጆቼ ጋር እንድትቀራረቡ እፈልጋለሁ” አለችው ዘለቀን፡፡ አዲስ ገሠሠን የልጆቹ ማናጀር አድርጋ እዚያው አስቀረችው። የክብር ዶክተሩን የመሐሙድ አህመድን “አሽቃሩና” የካሜራዊውን ዘፋኝ ማኑ ዲባንጐን “ሶል ማኮሳ”ን ዘለቀ “ሬጌ ማኮሳ” ብሎ ሲጫወት ሪታ በጣም ወደደችው፡፡ ስለዚህ በበአሉ ዕለት ካልቀዳህልኝ ብላ ወጥራ ያዘችው። የቦብ ስቱዲዮ የሚገኝበት ከበዓሉ ስፍራ 100 ኪ.ሜ ወደ ዋና ከተማዋ ኪንግስተን ሄደው ቀዳቻቸውና እነ ዘለቀ ከጃማይካ ሳይወጡ ነጠላ ዘፈኑ ተለቀቀ፡፡
ከዚያማ የሪታና ዳሎል ባንድ ፍቅር በፍቅር ሆኑ። እነዘለቀም ጃይማካ ሲሄዱ በኢትዮጵያዊ ባህል መሠረት የሐበሻ ቀሚስ፣ የአገልግል ምግብ፣ የእንጨት መስቀል… ይዘውላት ስለሚሄዱ ቤተሰብነታቸው በጣም ጠነከረ። ሪታ ማርሌም ከመውደድ አልፋ  የዳሎል ባንድ ማናጀር ሆነች። በዚህ ዓይነት ፍቅራቸው ጠንቶ፣ ትላልቅ ፌስቲቫሎች በሚዘጋጁበት ጊዜ ሁሉ እንዲቀርቡ ስለምታደርግ ጃማይካን ብዙ ጊዜ ተመላለሱባት፤ ሦስት ወይም አራት ነጠላ ዘፈኖች አወጡባት፡፡
ስኬት በአሜሪካ
ቺካጐ ውስጥ የሚጫወቱበት ናይት ክለብ በመንግሥት ተዘግቶ ጨረታ ወጣ፡፡ ዘለቀ፣ የቢዝነስ ፕሮፌሰሩን አማክሮ በባንዱ ስም ለመጫረት ፈለገ፡፡ ጨረታውን ያወጣው ፌዴራል መንግሥት ስለሆነ ሪታ ማርሌ “ማናጀራቸው እኔ ነኝ” ብላ ነግራላቸው ጨረታውን አሸነፉ፡፡ ያን ጨረታ ማሸነፋቸው አሜሪካ ውስጥ መነጋገሪያ ሆነ፡፡ በዚያን ወቅት ፕሬዚዳንቱ ሬጋን ነበሩ፡፡ “የሬጋን የሬጌ ኮኔክሽን! ሪፐብሊካኖቹ ለኢትዮጵያውያኖቹ ክለብ ስጧቸው” በሚል ትልቅ ዜና ሆነ። ይህ ሁሉ ሲሆን አሜሪካና ጃማይካ እየተመላለሱ ነበር የሚሠሩት፡፡ በዚህ መሃል አልበም አስቀርፁ ተባሉና “ላንድ ኦፍ ዘ ጀነሲስ” የተባለውን “ሆያ ሆዬ”፣ “ሰላም ሰላም”፣… የሚሉትን ዘፈኖች የያዘው የመጀመሪያ አልበማቸው  ጃማይካ ውስጥ በቦብ ማርሌ ስቱዲዮ ተቀረፀ፡፡
የቦብ ልጆች እነ ዚጊ ማርሌ እያደጉ ነበር፡፡ የዳሎል ባንድ አባላት በየኮንሰርቶቹ ሲጫወቱ ሲያይ፣ ዚጊ ማርሌ ከእነሱ ጋር ለመጫወት ልቡ ተነሳሳና እናቱን፣ “የአባቴም ምኞት ይኼው ነበር፡፡ እኔ ‘ኮ ከእነሱ ጋር ነው መጫወት የምፈልገው” አላት፡፡
ሪታ፣ አዲስንና ዘለቀን፣ “ዚጊ እንዲህ ይላል፤ ምን ይመስላችኋል?” በማለት አማከረቻቸው፡፡ እነሱም ታዲያ ምን ችግር አለው? አብረን እንሠራለን አሏት፡፡ ከዚጊ ማርሌ ጋር እየሠሩ ሁለት አልበም አወጡ፡፡ እነዚያ አልበሞች እያንዳንዳቸው ሦስት ሦስት ሚሊዮን ኮፒ ስለተሸጡ ትሪፕለም ፕላቲንየም ተባሉ፡፡ (አዲስ አልበም ወጥቶ አንድ ሚሊዮን ኮፒ ከተሸጠ ፕላቲኒየም፣ ሁለት ሚሊዮን ከተሸጠ ደብል ፕላቲኒየም፣ ሦስት ሚሊዮን ከተሸጠ ትሪፕለም ይባላል)፡፡
የግራሚ አዋርድም አሸነፉ፡፡ ዚጊ ማርሌ መጣ ሲባል ሕዝቡ እንደ ጉድ ነው የሚያያቸው፡፡ ዓለምን ዘጠኝ ጊዜ ዞረዋል፡፡ አውሮፓ ውስጥ 40ሺህ፣ 80ሺህ 100ሺህ ሕዝብ እየወጣ ይታደማቸው ነበር፡፡ ከዚጊ ጋር አንድ አልበም ከሠሩ ለዘጠኝና ለአሥር ወር ዓለምን ይዞራሉ፡፡ እነዘለቀ ትምህርቱን መከታተል ስላልቻሉ አቋርጠው ከዚጊ ጋር ለ4 ዓመት ዓለምን ዞሩ፡፡ ከዚያ ሲመለሱ ደግሞ የቺካጐውን ክለብ ማጠናከር ያዙ፡፡
የዳሎል ባንድ አባላት ኤል ፒ የተባለች 8 ዘፈን የያዘች አልበም አውጥተው ነበር፡፡ ክለቡም ቺካጐ ውስጥ ትልቅ ስምና ዝና አገኘ፡፡ ከሰኞ እስከ እሁድ መቆሚያ ቦታ የለም። ዳሎሎች ሁለት ቀን ይጫወታሉ፤ በተቀሩት ቀናት ሌሎች የሬጌ ባንዶች ነበር የሚጫወቱት፡፡ በቃ የቺካጐ የባህል ማዕከል ሆነ፡፡
ከዚጊ ጋር መለያየትና የዳሎል መከፋፈል
ከዚጊ ጋር እየሠሩ ጥሩ ገቢ፤ ጥሩ ስምና ዝና እያተረፉ ነበር፡፡ ነገር ግን በዚሁ ከቀጠሉ ሕልማቸውን መርሳት ሆኖ ተሰማቸው፡፡ የዳሎል ባንድ ሕልም የኢትዮጵያን ሙዚቃ ማንሳትና ማሳደግ ስለሆነ ዚጊን የእኛንም እንሥራ አሉት፡፡ ከእሱ መለየታቸውን ባይወደውም ሊጫናቸው ስላልፈለገ ቅር እያለውም ቢሆን “ኦኬ! ዩ አር ፍሪ” አላቸው። የራሳቸውን ሙዚቃ መሥራት እንደጀመሩ በመሃከላቸው ልዩነት ተፈጠረ፡፡ የልዩነቱ ምክንያት በሬጌው እንቀጥል ወይስ ሌሎች የአማርኛ፣ ጉራጊኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግሪኛ… ዘፈኖች እንጨምርበት የሚል ነበር፡፡ አልተስማሙም። ዘለቀ፣ ሙሉጌታና መላከ ረታ ሆነው “ባሮ” የተሰኘ ክለብ አቋቁመው ተለዩ፡፡ ሴሎቹ  አንድ የዶሚኒካ ዘፋኝ ጨምረው “ጊዜ ባንድ”ን መሥርተው በሬጌ ቀጠሉ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ክለቡ አልፈረሰም፣ የጋራ ሀብታቸው ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ዘለቀ “ዶንት ሌትሚዳውን”፣ “ሺቨሪንግ ሚ” … የተሰኙ ዘፈኖች የያዘውን የራሱን አልበም አወጣና መላውን አሜሪካ እየዞረ አልበሙን አስተዋወቀ፡፡ የቺካጐው ክለብ ዕድገት
እየሰፋ ሲሄድ፣ ሁለቴ አፍርሰው ከላይም ከታችም አስፍተው ባለሁለት ፎቅ አደረጉት፡፡ ሙሉጌታ ገሠሠና መላከ ረታም የየራሳቸውን አልበም አወጡ፡፡ ስለዚህ፣ ዘለቀ፣ “ዳሎል ቅርንጫፍ አወጣ እንጂ አልፈረሰም” ይላል፡፡     
የዘረኝነትና ጣጣ
ዳሎል ባንድ በአሜሪካ ጥሩ እየራ ሳለ ብዙ ጊዜ ችግር ገጥሞታል፡፡ ችግርን ተቋቁሞ ማለፍ ነው እንጂ ህይወት ያለ ችግር መች ይጣፍጣል ይላል ዘለቀ፡፡ የባንዱ አባላት በሙሉ አፍሪካዊ  ጥቁሮች ናቸው፡፡ በመላ አሜሪካ እየዞሩ ኮንሰርት ሲያቀርቡ፣ በቴክሳስና በአለባማ ዘረኛ ነጮች አደጋ ሊያደርሱባቸው ሞክረው ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ኮንሰርት አቅርበው እንደጨረሱ ህዝቡ በሰጣቸው ሞራል ተደስተው ወደሚቀጥቀለው ከተማ እየጨፈሩ ሲጓዙ፣ 30 የሚሆኑ ጋንግስተሮች አደጋ ሊያደርሱባቸው በሞተር ሳይክል ተከተሏቸው፡፡
የባንዱ አባላት ባቀረቡት ኮንሰርት ተደስተው ያጀቧቸው ነበር የመሰሏቸው፡፡ ሊያስቆሟቸው ሲሞክሩ ግን ጋንግስተሮች መሆናቸውን ስለተረዱ እግሬ አውጪኝ ብለው ተፈተለኩ፡፡ መኪናቸውን የያዘው ዘለቀ ነበር፡፡ በከፍተኛ ፍጥነት እየነዳ ወደፊት ከነፈና የሆነ ቦታ ሲደርስ ቤንዚን ማደያ ስላየ ወደዚያ ታጠፈ፡፡ ጋንግስተሮቹም ታጠፉ፡፡ እንዳልለቀቋቸው ሲያውቁ ከመኪናዋ ወርደው ወደ ማደያው ኪችን ዘለው ገቡ፡፡ ምክንያቱም ኪችን የሚሰሩት ብዙ ጊዜ የተለያየ ቀለም ያላቸው ዜጎች ስለሆኑ አንለይም በማለት ነው፡፡ ትረፊ ያላት ነፍስ ሆኖ ጋንግስተሮቹም ከዚያ በላይ አላሳደዷቸውም፡፡ በኋላ ፖሊሶች ተጠርተው ከዚያ ጉድ አወጧቸው፡፡ ዘለቀ የዚያን ዕለት ሁኔታ ሲናገር፤ በረሃው ላይ አስቁመውን ቢሆን ኖሮ መጥፎ ይሆን ነበር ብሏል፡፡
የዘረኝነት በደል በዚህ ብቻ አላቆመም፡፡ በሚኖሩባት ቺካጎ ከተማም አልቀረላቸውም፡፡ ከሚሰሩበት ክበብ ጀርባ ሀብታም ዘረኛ ነጮች ቤት ገዝተው ገቡ፡፡ ከዚያ ሊያባርሯቸው ስለፈለጉ፣ “የክለቡ ድምፅ ይጮሃል፣ ረበሸን፣ ፀጥታ አጥተናል፣” … እያሉ ብዙ ጊዜ ሊያስወጧቸው ሞከሩ። “ጉዳዩ የድምፅ ብክለት ሳይሆን ዘረኝነት ነው” በማለት ለማዘጋጀት ቤት አመለከቱ፡፡ ማዘጋጃ ቤቱ በህጉ መሰረት “በመኖሪያ አካባቢ ድምፅ ማስጮህ አትችሉም አላቸው፡፡
ስደተኞች “አሜሪካን ድሪም” የሚባል ነገር አላቸው፡፡ ሁሉም ሰው በስደት አሜሪካ ሲገባ፣ እንዲህ አድርጌ፣ እንዲህ ሰርቼ፣ እንዲህ ሆኜ … የሚለው ህልም አለው፡፡ የባንዱ አባላትም ሕልም ነበራቸው፡፡ እናም ትልልቆቹ የጥቁሮች መብት ተከራካሪዎች እነ ጄሲ ጃክሰን ወዳሉበት ሄደው፣ “ሙዚቃ መጫወትና ታዋቂ መሆን የአሜሪካ ህልማችን ነው፡፡ እነዚህ ዘረኞች ህልማችንን እውን እንዳናደርግ ቤታችንን ሊያዘጉብን ነው” ብለው ነገሩ፡፡
የከተማዋ ገዥ የዴሞክራት ፓርቲ አባል ናቸው፡፡ እነ ጄሲ ጃክሰን ለምን የፑሽ (PUSH) ኮሚቴ ሆናችሁ አታገለግሉም? አሏቸው፡፡ ለምን? ሲሉ ጠየቁ፡፡ እናንተ ተማሪ ናችሁ፡፡ ለምን በዚህ አጋጣሚ ስለ አሜሪካ ፖለቲካ፣ ስለ ዴሞክራሲ አትማሩም? አሏቸውና የምርጫ አቀነባባሪ ሆነው አረፉት፡፡ በዚህ ሁኔታ ወደ ፖለቲካ ገቡና የአሜሪካ ፖለቲካ እንዴት እንደሚሰራ ጠንቅቀው አወቁ፡፡
አርቲስት ዘለቀ ገሠሠ፤ በአሜሪካ ከሚጫወተው ሙዚቃና በግሉ ከሚሰራው ቢዝነስ በተጨማሪ በበጎ አድራጎት ተግባርም የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ አገልግሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቺካጎ ውስጥ ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የያዘ ኢትዮጵያን ኮሙኒቲ አሶሴሽን አለ፡፡ ይህን ድርጅት ዶ/ር እርቁ ይመር ሲያቋቁሙ፣ ዘለቀና ዶ/ር አብርሃም ደሞዝ ከመስራቾቹ አንዱ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቺካጎ ሲደርሱ ስለ አገሩ ስለማያውቁ ብዙ ይቸገራሉ፣ ግራ ይገባቸዋል፡፡ ስለዚህ ማኅበሩ አገር ያሳውቃል፣ መታወቂያ ካርድ፣ መንጃ ፈቃድ እንዴት እንደሚወጣ፣ የት መ/ቤት ማመልከት እንዳለባቸው … ይረዳቸዋል፡፡
አርቲስቱ ከኢትዮጵያ ከወጣ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አገሩን የረገጠው ከ17 ዓመት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ በአድዋ 100ኛ ዓመት ክብረ በዓል ወቅት ነው፡፡ ያኔ ኢትዮጵያን ተዟዙሮ ጎበኛት፡፡ በወቅቱ እንዳሁኑ ትምህርት በየገጠር ከተማውና መንደሮች አልተዳረሰም ነበር፡፡ በደረሰበት ሁሉ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናትና ወጣቶች ጊዜያቸውን በአልባሌ ሁኔታ እንደሚያሳልፉ ተመለከተ፡፡
ወደሚኖርበት አሜሪካ ሲመለስ፣ ያየውን ነገር ሁሉ ለዚጊ ማርሌ ነገረው፡፡ ኢትዮጵያን  እንዴት እንርዳ? በየዘፈኖቻችን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እንላለን፡፡ ኢትዮጵያን ለመርዳት ምን እናድርግ? በማለት አማከረው፡፡ ዚጊም ጥናት አድርግ አለው።
ዘለቀ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ትምህርት ያልተዳረሰባቸው አካባቢዎች የት የት ናቸው በማለት የአፍሪካ ህብረት (ያኔ የአፍሪካ አንድት ድርጅት) ዩኒሴፍና ዩኔስኮን አነጋገረ፡፡ ድርጅቶቹም ትክክለኛውን መረጃ ሰጡት፡፡ አብዛኞቹ ገጠር ናቸው - ሩቅ ገጠር፡፡ መረጃውን ይዞ ተመለሰና ዘለቀ ገሠሠ፣ ዚጊ ማርሌና አዲስ ገሠሠ ሆነው ዋን ላቭ አፍሪካ (One Love Africa) የተሰኘ ድርጅት በ1992 ዓ.ም በኢትዮጵያ አቋቋሙ፡፡ የቦርድ ኮሚቴ አባላትም መሠረቱ፡፡
ከቦርድ አባላት አንዱ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩን የመረጠው እንዲመሯቸው ነው፡፡ በነጆ - ወለጋ የተወለዱት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ እንደተመረቁ (በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመን) ወደ አገራቸው ተመልሰው “ፊደል ሰራዊት” መስርተው “የተማሩ ያስተምሩ” እያሉ በኩምቢ ቮክስዋገን እየዞሩ ይቀሰቅሱ እንደነበር ዘለቀ ያውቃል፡፡ ነገሮችን መንገድ ያስያዙላቸው በሂውስተን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ኤፍሬም መሆናቸውን ዘለቀ ይናገራል፡፡ አሜሪካ እያለ ከሙዚቃና ከግል ቢዝነሱ በተጨማሪ ዋን ላቭ አፍሪካን በኃላፊነት እየመራ ቆይቷል፡፡
በፈረንጆች ሚሊኒየም (ከዛሬ 15 ዓመት በፊት) በደቡብ ክልል በሲዳማ ዞንና በቦረና ዞን 10 ት/ቤቶች ከፈቱ። ት/ቤቶቹን የሚከፍቱት ከመንግሥት ጋር ተነጋግረውና ተፈራርመው ነው፡፡ ት/ቤቱ ከማኅበረሰቡ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ለት/ቤቱ መስሪያ መሬት ይሰጣል፣ እንጨት፣ ድንጋይ፣ ለክዳን ሳራ፣ … ያቀርባል። ከማኅበረሰቡ ውስጥ የተማሩና ሥራ የሌላቸው ተመርጠውና ሰልጥነው በመምህርነት ይቀጠራሉ፡፡ ዋን ላቭ አፍሪካ ለ4 ዓመት በሴቭ ዘ ችልድረን ዩኤስኤ በኩል አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ እነዘለቀ ገንዘቡን ከአሜሪካ ለጋሽ ድርጅቶች ለምነው ለሴቭ ዘ ችልድረን ዩኤስኤ ይሰጣሉ፡፡ ወጪ የሚያደርገውና ሂሳቡን የሚቆጣጠረው ዩኤስኤይድ ነው፡፡
ት/ቤቱቹ በየአካባቢያቸው ከፍተኛ ለውጥ አምጥተዋል። ዘለቀ፣ ከ4 ዓመት በኋላ በ2004 (እኤአ) ት/ቤቶቹ ያሉበትን ሁኔታ ለማየት ድጋፍ ያደረጉላቸውን ድርጅቶች ይዞ መጥቶ ነበር፡፡ እጅግ የሚገርም ነገር ነው ያዩት፡፡ በሲዳማ ዞን ከይርጋዓለም ከተማ 70 ኪ.ሜ ገባ ብሎ ያሉት የማደኖ ማኅበረሰቦች፣ ያደረጉትን ማመን ነው ያቃታቸው፡፡ “ልጆቻችን 4ኛ ክፍል ከጨረሱ በኋላ ለመቀጠል 2 ሰዓት የእግር ጉዞ ሊያደርጉ ነው፡፡ በተለይ ሴቶቹ ዕድሜያቸው ከፍ ስላለ ከቤተሰብ ርቆ መሄድ ችግር አለው፡፡ ስለዚህ እኛ ሁለት መማሪያ ክፍል ሰራን፡፡ እናንተ ደግሞ ቀሪውን አስፈላጊ ነገር አሟሉልንና እስከ 6ኛ እዚሁ ይማሩ” በማለት ጠየቁ፡፡ የፈለጉት ነገር ተሟላላቸው፡፡
በቀጣይ የታቀደው ፕሮግራም ሸዋ ውስጥ ነው። ፕሮፖዛል አዘጋጅቶ ለለጋሽ ድርጅቶች አቅርቦ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ፣ ከአዲስ አበባ ዙሪያ ወጣ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች በቦሌ ወረዳ፣ በውንጪ፣ በፍቼ፣ በአቃቂ … ሌሎች 10 ት/ቤቶች ሰርተዋል፡፡ እነዚህን ት/ቤቶች ሲጎበኙ ማኅበረሰቡ ክፍሎች እየሰራ የጎደለውን አሟሉልን እያለ ይጠይቃቸዋል፡፡ እነሱም ያሟላሉ፡፡ ሌሎች 10 ት/ቤቶች የተሰሩት ደግሞ ጎንደር ውስጥ በደንቢያ ወረዳ ነው፡፡ በአጠቃላይ 30 ት/ቤቶች ተሰርተው በመንግሥት ሲስተም ውሰጥ እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡
ዋን ላቭ አፍሪካ ያደረገው ት/ቤት መገንባት ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች ተግባራትም አሉ፡፡ አርቲስቱ ሸዋ ውስጥ ያሉ ት/ቤቶችን ሲጎበኝ አንድ ነገር ተገነዘበ፡፡ ት/ቤቶቹ የተሰሩበት አካባቢ ውሃ የለም፡፡ ሴት ተማሪዎች ወደ ት/ቤት የሚመጡት ዘግይተው ከመሆኑም በላይ ደክመው ስለሚደርሱ የትምህርት አቀባበላቸው ደካማ መሆኑን ዳይሬክተሮቹ ነገሩት፡፡ ፕሮፖዛል አዘጋጅቶ የገንዘብ ድጋፍ ለሚያደርጉለት ለጋሾች አቀረበ፡፡ ለጋሾች ም ፊት አልነሱትም። ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ከ10ሩ ት/ቤቶች 7ቱ የውሃ ጉድጓድና ፓምፕ አላቸው፡፡
ት/ቤቶቹ ያሉበትን ሁኔታ ፊልም ቀርፆ ተመለሰ፡፡ ከዚያም ትልቅ ዝግጅት አድርጎ ቺካጎ በሚገኘው ክለባቸው ያንን ፊልም አሳየ፡፡ ፊልሙን የተመለከተ አንድ ድርጅት “እኔ ለት/ቤቶቹ ኮምፒዩተር እችላለሁ” ማለቱን ዘለቀ ገልጿል፡፡ የኮምፒዩተሩ ጥያቄ መነሻ አለው፡፡ ሲዳማ ውስጥ ያሉትን ት/ቤቶች ሲጎበኝ፣ አንዲት ትንሽ ልጅ “ኮምፒዩተር እፈልጋሁ” አለችው፡፡ ያነሳውን ፊልም ለፈረንጆቹ ሲያሳይ ልባቸው በጣም ተነካ፡፡
ስለዚህ “ዋን ላፕቶፕ ፎር ኢች ቻይልድ” በሚለው ፕሮግራም መሰረት፣ ከ6 ዓመት በፊት ዋጋቸው ሩብ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ 1,000 ላፕ ቶፖች ገዝተው ለ16 ት/ቤቶች አከፋፈሉ፡፡ 30ዎቹ ት/ቤቶች በየዓመቱ 15,000 ተማሪዎች ያስተናግዳሉ፡፡ መጀመሪያ ትምህርት የጀመሩት በአሁኑ ወቅት ኮሌጅ መድረሳቸውን ዘለቀ ተናግሯል፡፡ አርቲስት ዘለቀ ከግራሚ ሽልማቱና ከወርቅ ሬከርዱ በላይ ትልቅ እርካታ የሚሰጠው፣ ወገኖቹ ከድንቁርና ጭለማ ወጥተው የእውቀት ብርሃን እንዲያዩ ማድረጉ ነው፡፡ ከ7 ወይም 8 ዓመት በፊት በወንጪ አካባቢ የተሰራውን ት/ቤት ሲጎበኙ ያየው ነገር ከምንም በላይ እጅግ የላቀ እርካታ እንዲሰማው አድርጎታል። ለካንስ ወጣቶቹ አባቶቻቸውንና አረጋዊያን አያቶቻቸውን ፊደል ለይተው እንዲያውቁና ገጣጥመው እንዲያነብቡ አስተምረዋቸዋል፡፡
አንድ የ80 ዓመት አዛውንት ተነስተው “በጠቅላላው እንኳን ሰው እግዜርም ረስቶናል ያልነውን ቦታ እናንተ ት/ቤት ከሰራችሁ በኋላ ልጆቻችን ተማሩ፤ እኔ ሽማግሌው እንኳ ማንበብ ቻልኩ” በማለት ከፍ - ዝቅ፣ ራቅ - ቀረብ እያደረጉ፣ በደከመ ዓይናቸው በግድ ሲያነብቡ፣ እሱና አብረውት የነበሩት የደስታ ሲቃ ከውስጣቸው ፈንቅሎ ማልቀሳቸውን መቼም እንደማይዘነጋው ተናግሯል፡፡
አርቲስቱ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ የተለያዩ ቢዝነሶች ጀምሯል፡፡ አጀማመሩ ታዲያ በችኮላ አይደለም። ቀስ እያለ በማጥናት ነው፡፡ በአያት አካባቢ እየተሠራ ያለው ባለ 2 ፎቅ መኖሪያ ቤት በ18 ወሮች እንደሚጠናቀቅ ተገምቷል፡፡ የአያቱ ሲጠናቀቅ ቦሌ አካባቢ የእንግዳ ማረፊያ ለመሥራት ዲዛይኑ አልቋል፡፡ በሽርክና የተገዙ ቢሆንም የሚከራዩ የግንባታ ማሽነሪዎች አሉት፡፡
ዘለቀ፣ ከቺካጐ ሲለቅ ክለቡን አዲስ አበባ ልወስደው ነው ያለው ከአንጀቱ ባይሆንም አሁን ግን አዲስ አበባ ከአምስትና ከሰባት ሺህ በላይ እንግዶች እያስተናገደች ስለሆነ ሰፊ መዝናኛ እንደሚያስፈልጋት አምኗል፡፡ ለመዝናኛው ግንባታ ሰፊ ቦታና ትልቅ ካፒታል የሚጠይቅ ስለሆነ ከመንግሥትና ከፋይናንሰሮች ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ገልጿል፡፡
አርቲስት ዘለቀ አሜሪካ የሚኖሩ ሦስት ልጆች አሉት። ትልቁ ልጅ ትምህርቱን ጨርሶ ሆሊዉድ ውስጥ ፊልም እየሠራ ነው፡፡ በቅርቡ ልጅ ወልዶ አባቱን አያት አድርጓል። ሴቷ ልጅ በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በሂዩማን ራይት ሎው ማስተርሷን እየተማረች ሲሆን በዚህ ዓመት (2015) ትመረቃለች። የመጨረሻው ልጅ በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፍሎሪዳ እየተማረ ሲሆን ከዓመት በኋላ ይመረቃል፡፡ ሎቢስት (ሕግ ሲወጣ የመንግሥትና የቢዝነስ ሰዎችን የሚያግባባ፣ የሚያቀራርብ) እሆናለሁ እያለ ስለሆነ ፖለቲከኛ የመሆን ፍላጐት ያለው ይመስላል ብሏል አባቱ - አርቲስት ዘለቀ ገሠሠ፡፡

Saturday, 08 August 2015 09:39

የዳንኤል ታዬ በርጠሜዎስ!

 የሰው ልጆች ከሚኖሩበት ዓለም ከምትባለው ድንኳን ሥር የሚወጡ የጋራ ስሜቶች፣ እምነቶችና አተያዮች አሉ፤ ነበሩም፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ መሣቁ፣ ደግሞ መልሶ ማልቀሱ፣ መውለዱና መሞቱ የጋራው ናቸው፡፡ ታዲያ ይህንን የጋራ ሕይወት የሚመዝዘውና የሚያበጥረው ኪነጥበብም የጋራ መልክ፣ የጋራ የአፃፃፍ ይትበሃልና የነፍስ ውዝዋዜ የሚኖረው ብዙ ጊዜ ነው። እንደሚታወቀው የጥበቡ መነሻ በአብዛኛው ግሪክ ትሁን እንጂ በየመንገዱ እያደገ፣ በየሀገሩ - ሌላም እየበቀለ፣ ተያይዘው እዚህ ለመድረሳቸው ድርሳናትን መፈተሽ ብቻ በቂ ነው፡፡
በዓለማችን የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ዘውጐች የየራሳቸውን ቅርፅ ይዘው ሲተምሙ፣ አንዳንዴ ሠልፋቸው እየተደናቀፈ፣ መልካቸው እየተፈገፈገ፣ እንደ እባብ ቆዳቸውን እየቀየሩ፣ እየከሱና እያማረባቸው እዚህ ደርሰዋል፡፡ ከነዚያ መንገደኛ ዘውጐች ወይም ዝርያዎች እንደየሀገሩ ባህልና እምነት መርገጫ አግኝተው ያረፉ፣ ወይም አጥተው ወደ ሌላ ያለፉ ይኖራሉ፡፡ ዛሬ በጥቂቱ ልቃኘው ያሰብኩት የሰዓሊና ደራሲ ዳንኤል ታየ፣ “ቅዠት” መጽሐፍም መርገጫ ካጡት ውስጥ አንዱ ይመስለኛል፡፡ በ108 ገፆች የተጠረዘችው መጽሐፍዋ፤ ከዚህ ቀደም ባነብባትም እንደ አሁኑ እትም ዘልቄ የገባሁ ወይም ዘልቃ ውስጤ የገባች አይመስለኝም፡፡ መረረኝ ጣፈጠኝ ሌላ ነው፡፡
በብዙዎቻችን ዘንድ እንደሚታወቀው ዳንኤል ታዬ ሰዓሊ ነው፡፡ እንዲያውም ብርቱ ሰዓሊ፡፡ እኔ ሥዕሉን የመበርበር አቅሙና ሙያው ባይኖረኝም፣ ከዚህ ቀደም ሰዓሊው በአሜሪካው ሲኤንኤን ቴሌቪዥን ላይ መቅረቡን አስታውሳለሁ፡፡ መቼም ይሄንን ከሜዳ ላይ አያፍሰወም፡፡ ጥሮ ግሮና በርትቶ በመትጋት እንጂ፡፡ ምናልባት ጽሑፎቹ ላይ የሚታየው የፍልስፍና ጭላንጭልም በግጥሞቹ ውስጥ በበረታ ሃይል እንደሚገኝ አምናለሁ፡፡
የዳንኤል ሃሳቦች ግርም የሚሉና ጥልቀት ያላቸው ቢሆኑም ለኔ ግን ሕይወትን በተሰባበረ ልብ የማየት ድምፀት አለው፡፡ አሁን ለጊዜው ባላነሳውም “ምስጦቹ” በሚል ርዕስ የፃፈው ያሠቅቃል፤ ያስፈራል፤ ግን ደግሞ ይደንቃል! ዛሬ ትኩረቴ “የጢሞቴዎስ ልጅ በርጠሜዎስ” የምትለው አጭር ታሪክ ናት፡፡ ይህቺ ታሪክ እኛ ሀገር መርገጫ አጥቷል ብዬ ከጠቀስኩበት ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የተቀነጨበች ናት፡፡ ይልቁንም ከአራቱ ወንጌላት ከአንዱ በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ አስር፡፡ በርጠሜዎስ፣ በርባን፤ ኮብላዩ ልጁ፣ አሥራ ሁለት ዓመት ደም የፈሰሳት ሴት፣ በአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ ጐላ ብለው የወጡ ገፀ ባህርያት ናቸው፡፡
 ይሁንና ኮብላዩ ልጅ ብዙ ጊዜ በውጭ ደራሲያን በተለያየ ዕይታ ተተርኳል፡፡ እዚህም ሀገር ተተርጉሞ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ የዳንኤልን ቀልብ የሳበው ደግሞ በርጠሜዎስ ነው፡፡ “በርጠለሜዎስ” የሚል ስም ግን በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም፡፡ ምናልባት በርተለሜዎስ ከሚባለውና ናትናኤል ሊሆን ይችላል ተብሎ ከሚገመተው፣ በተቃዋሚዎቹ በአሠቃቂ ሁኔታ ከሞተው ሃዋርያ ጋር ተመሳስሎበት እንደሆን አላውቅም፡፡ ብቻ ወደ በርጠሜዎስ ለመምጣት ድልዳል እንዲሆነን የማርቆስ ወንጌልን ዳራ ማየት ይኖርብናል፡፡ የሥነ - ጽሑፉስ ዘውግ የት የት ይረግጣል? የነገረ መለኮትና የሥነ ጽሑፍ ምሁራን ከሚሉት ተነስተን እንድንሄድ ትንሽ መረማመጃ ላንጥፍ፡፡
የማርቆስ ወንጌል ከአራቱ ወንጌላት መካከል በመጀመሪያ የተፃፈ ነው፡፡ ፀሐፊው ማርቆስ ቢሆንም ሀሳቡ የሃዋርያው ጴጥሮስ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ ለሚለው ደግሞ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ አሁን ወደዚያ ከገባን ግን ጀንበር እንዳትጠልቅ ወደ ዋናው ጉዳይ እንሂድ፡፡
የማርቆስ ወንጌል አፃፃፍ የግሪክ ትራጀዲን ይመስላል የሚሉት ተመራማሪዎች፤ በተለይ የታሪክ መዋቅሩ ከማቴዎስ ወንጌል ጋር ተቀራራቢነት እንዳለው ያብራራሉ፡፡ ከግሪክ ትራጀዲ ጋር የሚያመሳስለውም ትውውቅ፣ የግጭቶች ከፍታና መወሳሰብ እንዲሁም ጡዘት፣ ልቀት፣ ፍርሰት- ፍፃሜ ነው፡፡
ይህ ጥቅል የሆነውንና የበርጠሜዎስ ታሪክ የተመዘዘበትን የማርቆስ ወንጌል አፃፃፍ ያሳያል፡፡ ይሁንና ከዚህም ሌላ ማርቆስ የራሱ መልክ አለው፡፡ ሉቃስ በምሣሌያዊ ንግግር የተሞላ፣ ማቴዎስ ደግሞ ከብሉይ ኪዳን ጥቅሶች ጋር የተያያዙ የኋላ ንግርቶች ያሉት ሲሆን ማርቆስ እንደ ድራማ መጋረጃው የሚገለጥ ትዕይንት ዐይነት ነው፡፡ ይህን አይነቱን አፃፃፍ ተመራጭ ያደረገው በጊዜው ትኩረት የተደረገበት የተደራሲያኑ ሥነ ልቡናና እምነት ነው፡፡ ማቴዎስ ለአይሁድ ሲፅፍ፣ ስለ ኢየሱስ የተነገሩትን መስሃዊ ጥቅሶች እያስታወሰ ነበር፡፡ ማርቆስ ደግሞ የፃፈው በሮማውያን ላይ አተኩሮ ስለነበር መሲሁ አገልጋይና በሥራ ብርቱ እንደነበረ እንደ ሥዕል ማሳየት ነበረበት። እንግዲህ በርጠሜዎስም በዚያ ትዕይንት ብቅ ካሉ ሰዎች አንዱ ነው፡፡
ታዲያ ዳንኤል በርጠሜዎስን እንዴት አየው? መጽሐፍ ቅዱሱ በሦስተኛ መደብ የሚተርከው በርጠሜዎስ፤ ዳንኤል ጋ መጥቶ በአንደኛ መደብ ነው የሚያወራው፡፡ ለዚያውም ሲጀምር “ፈጽሞ መታወር እፈልጋለሁ፡፡” ነው የሚለው፡፡ ከዚያም “አሁን የት ባገኘሁት” ይላል፤ አይኑን ያበራለትን ኢየሱስን። ዝናውን ሰምቼ ነው እንጂ የጮኽኩት አልጮኽም ነበር ይላል፡፡ ምክንያቱም ዓይኑ እንዲበራ “የዳዊት ልጅ ማረኝ” ማለቱ ቆጭቶት ነበር፡፡
በርግጥ የሚተርክበት መንገድ ጥሩ ነው፡፡ ታሪኩ በጣም አይፈጥንም እንጂ፡፡ ለነገሩ የማርቆስ ወንጌልም ፈጣን ትረካ የሚባል ዐይነት ነው፡፡ ቶሎ ቶሎ ወደ ድርጊት ይጣደፋል፡፡ የዳንኤልን ግን ያን ያህል አይፈጥንም፡፡ እናም በርጠሜዎስ በጩኸቱ ሠፈሩን ቀውጦት እንደነበር በምልስት እያወራ፣ አሁን ግን ዐይኑን ማጥፋት ሁሉ ይመኛል፡፡ እንዳያጠፋ ደግሞ ሕግ መተላለፍ እንደሆነ ያስባል፡፡ መለስ ብሎም መንደሩን ምኩራቡን ሁሉ እንዳየው ያወራል። የቀደመ ሕይወቱ የታሸገ ስልቻ ውስጥ የመኖርን ያህል እንደነበር በማስታወስ ይደነቃል፡፡ ከዚያ መደነቅ በኋላ ግን እንዲህ ይላል፡- “ያው የጨለማ ቤቴ ይሻለኛል። ያው አለማየት ይሻላል፤ ምን ለማየት ዐይኖቼን አበራሁ? እኔ እውር ስለነበርኩ ነው ለማየት የጓጓሁት። አሁን እፈልገዋለሁ፡፡ ፊት የነበረኝን ልበ ብርሃን ይመልስልኝ፡፡ ምንም የሚታይ ነገር የለም፡፡”
 ታሪኩ ሲጀምር፣ ጀምሮ ሲጠናቀቅም ኢየሱስን እየፈለገ ነው፡፡ እየባተተ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ግን ጨለማን ፍለጋ ነው፡፡ ብርሃን የሚሰጠው መሲህና ጌታ ጨለማውን እንዲመልስለት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የማየውን ሁሉ ጠላሁት ነው፡፡ የሰው ልጅ፣ እንስሳት፣ እጽዋት… ሁሉም አያጓጉም፤ አያምሩም፤ ወደሚል ድምዳሜ ይወስዳል፡፡
ተራኪው ዳንኤል፤በርጠሜዎስ ውሰጥ ገብቶ ያያት ዓለም፤ እኛ ከምናያት ለምን ተለየች? የሚል ጥያቄ የለኝም፡፡ ዝም ብሎ ያገኘውን ሁሉ ሳይጠይቅ የሚያድበሰብስ ሰው ሕይወትም ፉንጋ ነው። መመርመር ዕድል ነው፣ መጠበብም የሰው ልጅ ውበት ነው፡፡ ግን ደግሞ የጠቢብ ዐይን፣ ውበት ብቻ ሳይሆን እውነት እንደ ሀረግ የተጠመጠመባት ናት ብዬ አምናለሁ፡፡
በርጠሜዎስ ዓለም አስጠላችው፡፡ የሚያየውን ነገር ተፀየፈው፡፡ እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል?...አንዳንዴ ሕይወት ስታስመርራቸው፣ ቀዳዳው ሲጠብባቸው ሰዎች የተፈጠሩበትን ቀን እንደሚረግሙ ይታወቃል። ተስፋ ሲቆርጡ ደግሞ ሕይወታቸውን በገዛ እጃቸው ይቀጥፋሉ፡፡ ሩቅ ሳንሄድ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትልቁ ነቢይ ኤርሚያስ እንኳ፣ ከእናቱ ማህፀን የወጣበትን ቀን ረግሟል፡፡ ያንን ስሜት የፈጠረበት የፈተናው ብዛትና የሕይወቱ ነውጥ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ሰው ዓይን ሲኖረው የሚያያቸው ነገሮች የሚዘገንኑና የሚያስጠሉ ብቻ አይደሉም፡፡ የአበቦች ቀለም፣ የኮረደች ውበት፣ የጐረምሳ ርምጃ----እንኳ ይማርካል፡፡ ታዲያ ተራኪው ዳንኤል እንዴት ቢያየው ነው ዳግም ይህችን ዓለም በዐይኔ በብረቱ አላይም... ያሰኘው? ለዚያውም ቀለም ለሚያጣጥም ለዚህ ሰው፣ ሸራ ለሚያጠልቅ ለዚህ የጥበብ ቀንድ፣ እንዴት ሆኖ ዓለም የጨለማ ግግር ሆነበት?
 በዚህ ዓለም ስንኖር እሾሆች ቢበዙ፣ ቢቧጭሩንና ደማችን ቢፈስስ፤ ቁስላችንን የሚያስረሱ፣ ብዙ ካሣዎች አሉን፡፡ እርግጥ ነው፡፡ ሕይወት ብዙ ጥያቄ ተሰግስጐባታል፣ ግን ደግሞ አጠገባቸው መልሶቹን እናገኛለን፡፡ ያላገኘንላቸውንም እያየን ወደሚቀጥለው ምዕራፍ እንጓዛለን፡፡
ግባችን የት ነው የሚለው … በየራሳችን እምነትና ፍልስፍና ይወስናል፡፡ ግን ሕይወት በእሾህ ትከበብ እንጂ በሕብረቀለማት የሰከሩ አበቦችን ታቅፋለች። ተስፋ አለን! ምናልባት ዳንኤል “ቅዠት” የሚል ርዕስ የሰጠው መርገጫ እግሮቹ ዶልዱመው ስለተንሳፈፉ ይሆን? እንዲህም ሆኖ ግን ዳንኤል ብዙ ያልተለመደውን የትረካ መንገድ መከተሉ የሚወደድ አካሄድ ነው፡፡ ከሆነ አይቀር ደግሞ አድምቶ መፃፍ፣ ፈልቅቆ መፍተል ይቻላል፡፡ ያውም እርሱን ለሚያህል የጥበብ ተመሳጭ ሰው!
ዳኒ፤ጨለማውን ብቻ ሳይሆን ብርሃኑን፣ እሾሁን ብቻ ሳይሆን አበባውንም አሳየን፡፡ ቀጣዩ መጽሐፍህ “የሌማሁስ መንገደኞች” የተስፋ መቁረጥ ጉዞም ቢሆን አብሯቸው ካለው ተስፋ ጋር ደምቆ እንደሚመጣ ተስፋ አለኝ፡፡  

Published in ጥበብ
Saturday, 08 August 2015 09:38

የዘላለም ጥግ

(ስለ ስኬት)
ውድቀት አማራጭ አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው ስኬትን መቀዳጀት አለበት፡፡
አርኖልድ ሽዋዚንገር
ያለ አንተ ይሁንታ ማንም ሰው የበታችነት ስሜት እንዲሰማህ ማድረግ አይችልም፡፡
ኢሊኖር ሩስቬልት
ስኬት የዕድል ጉዳይ ነው፡፡  ያልተሳካለትን ማንኛውንም ሰው ጠይቁ፡፡
ኢርል ዊልሰን
አሸናፊው ሽንፈትን ይፈራል፡፡ የተቀረው ደግሞ ማሸነፍን ይፈራል፡፡
ቢሊ ዣን ኪንግ
ውድቀት በራሱ ከተማርንበት ስኬት ነው፡፡
ማልኮም ፎርብስ
የስኬት ምስጢሩ ሃቀኝነት ነው፡፡
ዣን ጊራውዶክስ
ተፈጥሮአችን ነው፡- የሰው ልጆች ስንባል ስኬትን እንወዳለን፤ ስኬታማ ሰዎች ግን እንጠላለን፡፡
ካሮት ቶፕ
ስኬትን መቀዳጀቴ ብቻ በቂ አይደለም - ሌሎች መውደቅ አለባቸው፡፡
ዴቪድ ሜሪክ
ስኬት ሁሉንም ነገር አይደለም፤ ነገር ግን ሰውን ቀጥ ብሎ እንዲቆም ያደርገዋል፡፡
ሊሊያን ሄልማን
ስኬት ምንም ምስጢር የለውም፡፡ የዝግጅት፣ ተግቶ የመስራትና ከውድቀት የመማር ውጤት ነው፡፡
ኮሊን ፓውል
ህልሞችህን ገንባ፤ ያለበለዚያ ሌሎች ህልማቸውን እንድትገነባላቸው ይቀጥሩሃል፡፡
ፋራህ ግሬይ
ህይወት ራስህን የመፈለግ ጉዳይ አይደለም፤ ራስህን መፍጠር ነው፡፡
ጆርጅ በርናርድ ሾው
ደስታ ሁልጊዜ ክፍት እንደነበር ባላሰብከው በር ያጮልቃል፡፡
ያልታወቀ ሰው

Published in ጥበብ
Page 12 of 19