በወጣት ገጣምያን የተጠነሰሰው “ግጥምን በጃዝ” ባለፈው ረቡዕ ምሽት የ3ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን  በብሄራዊ ቴአትር አዳራሽ በተለያዩ የጥበብ ዝግጅቶች አከበረ፡፡ በክብረ በዓሉ ምሽት ግጥሞች፣ ሙዚቃዊ ተውኔት፣ዲስኩሮችና የእውቅና የሽልማት ስነስርአቶች ተካሂደዋል፡፡
በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ተጀምሮ ወደ ራስ ሆቴል የተዛወረው “ግጥምን በጃዝ”፤ በኪነ-ጥበብ አፍቃሪያን ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈ ፕሮግራም ነው፡፡ በምሽቱ የጥበብ ዝግጅት ላይ ጸሀፌ ተውኔትና ገጣሚ ጌትነት እንየው፣ ገጣሚ ነቢይ መኮንን፣ አርቲስት ግሩም ዘነበ፣ ገጣሚ አበባው መላኩ፣ ምህረት ደበበ፣ በረከት በላይነህ፣ ምስራቅ ተረፈና ሌሎችም የጥበብ ስራዎቻቸውን ለታዳሚው ያቀረቡ ሲሆን አዳራሹ ገና በጊዜ ጢም ብሎ ሞልቶ ነበር፡፡

በጋዜጠኛ ደረጀ ትዕዛዙ የተጻፈው የዕውቁ ጋዜጠኛ፣ ደራሲና የታሪክ ጸሐፊ ጳውሎስ ኞኞ የህይወት ታሪክን የያዘው “ጳውሎስ ኞኞ ከ1926-1984” የተሰኘ መፅሐፍ ዛሬ ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ አራት ኪሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲሱ ህንጻ፣ 6ኛ ፎቅ ላይ ይመረቃል፡፡ በስነ-ስርዓቱ ላይ የጳውሎስ ኞኞ ቤተሰቦች፣ አድናቂዎች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

የእውቁ ድምፃዊ ታምራት ደስታ አራተኛ አልበም የሆነው “ከዛ ሰፈር” የተሰኘ አዲስ የሙዚቃ ሥራ በመጪው ሳምንት  ለአድማጭ ጆሮ ይደርሳል ተባለ። “ሃኪሜ ነሽ መድሃኒቴ” በሚል ነጠላ ዜማ ከህዝብ የተዋወቀውና በኋላም “አንለያይም” እንዲሁም “ካንቺ አይበልጥም” በተሰኙት አልበሞቹ አድናቆትን ያተረፈው ድምፃዊው፤በአዲስ አልበሙ አስራ አራት ስራዎችን አካትቷል፡፡
 “ከዛ ሰፈር” በተሰኘው አልበም ውስጥ በቅንብር ሚካኤል ሃይሉ፣ ካሙዙ ካሳ፣ ኪሩቤል ተስፋዬና ሚካኤል መለስ የተሳተፉበት ሲሆን በግጥምና በዜማ ደግሞ ጌትሽ ማሞ፣ አማኑኤል ይልማ፣ መሰለ ጌታሁንና ኢዩኤል ብርሀኑ መሳተፋቸው ታውቋል፡፡ የአልበሙ አሳታሚና አከፋፋይ ናሆም ሪከርድስ ነው፡፡

በአውሮራ ኤቨንትስ ኦርጋናይዘርስ የተዘጋጀው “ሬጌ ዳንሶል ኢን ኢትዮጵያ ቁጥር 1” የሙዚቃ ድግስ ዛሬ  ምሽት ከ12 ሰዓት ጀምሮ በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል፡፡ በሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ድምፃዊ ቢዚ ሲግናል፤ የምሽቱ ኮከብ ሆኖ እንደሚነግስ የአውሮራ ኤቨንትስ ኦርጋናይዘር ሸዊት ቢተው ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ የአሁኑ ኮንሰርት ከወራት በፊት ሊካሄድ ዝግጅቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ከቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ኮንሰርት ጋር በመገጣጠሙ አዘጋጆቹ ፕሮግራሙን መሰረዛቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
“ቀደም ሲል ከሰረዝነው የሙዚቃ ድግስ በላቀ ሁኔታ፣ በድምፅና በላይት ጥሩ አደራጅተነዋል” ያለው ሸዊት ቢተው፤ ናቲ ማን ወጥቶ ሃይሌ ሩትስና ጆኒ ራጋ መካተታቸው ከበፊቱ የሚለይበት አንዱ ጉዳይ ነው” ብሏል፡፡  በዛሬው የሙዚቃ ድግስ ቢዚ ሲግናልን ጨምሮ ሲድኒ ሳልመን፣ ራስ ጃኒ፣ ጃሉድ አወል እና ሃይሌ ሩትስ የሙዚቃ አፍቃሪውን ያዝናናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የመግቢያ ዋጋ 500 ብር ሲሆን ለVIP 1500 ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡ ትኬቶች በኤድናሞል፣ በሸራተን፣ በሚሊኒየም አዳራሽ፣ በሁሉም የቤሉስ ኬክ ቤቶች፣ በማማስ ኪችን፣ በሮሚና በርገርና በክለብ H2O በመሸጥ ላይ ናቸው ተብሏል፡፡

Saturday, 23 August 2014 11:55

“ኑዛዜው”

ብቻውን ነው፡፡ በመንፈስም በአካልም፡፡ አባቱ ክዶታል፡፡ ፍቅረኛው ክዳዋለች፡፡ ጓደኞቹ ርቀውታል። አዱኛና ሲሳይ ከሱ ህይወት ዳግመኛ ላይመለሱ ተሰናብተውታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ፈጣሪ ራሱ ጠልቶታል፡፡
አራት በአራት በሚሆነው የግንብ ቤት ውስጥ ወንበር ላይ ተቀምጧል፡፡ ፊት ለፊቱ አንድ ጠረጴዛ፤ ጠረጴዛው ላይ ደግሞ ወረቀት አለ፡፡ ጠረጴዛው ላይ በተቀመጠው የታሸገ ውሃ መያዣ ላስቲክ ውስጥ የሐበሻ አረቄ፣ አጠገቡ ደግሞ አራት ሲጋራዎችና አንድ ክብሪት ይታያሉ፡፡
 በግራ በኩል አንድ ታጣፊ አልጋ ሲኖር በክፍሉ ውስጥ ሌላ ምንም የቤት ዕቃ የለም፡፡
ወረቀቱ ላይ ሲያፈጥ ቆየና ቀና አለ፡፡ የክፍሉ ኮርኒስ ላይ የተንጠለጠለ ገመድ አለ፡፡ ይህንን ገመድ ያንጠለጠለው እሱ አይደለም፡፡ ከዘመናት በፊት አባቱ ለሱ ያዘጋጀው ነበር፡፡ ወደዚህ ክፍል ላለመምጣት የቻለውን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ምክንያቱም እዚህ ክፍል ውስጥ ወደ ሞት የሚወስደው መታነቅያ ገመድ እንጂ ሌላ ምንም ነገር እንደሌለ ያውቃል፡፡
“እንዴት ጨካኝ ነው” ሲል አሰበ፤ አባቱን ሲያስታውስ፡፡
አባቱ ቀጭን ረጅም፣ የሚያምር ሪዝ የነበረው የተዋጣለት ነጋዴ ነበር፡፡ ሐብቱን ያካበተው ከምንም ተነስቶ ሲሆን ገንዘብ ላይ በጣም ጠንቃቃ፣ ብዙ የማይናገር፣ ከስራ በኋላ ሲጋራውን እያጨሰ ማንበብ የሚያዘወትር፣ ፊቱ ፈገግታ የማይለየው ሰው ነበር፡፡
በልጅነቱ ከሚጠጣው የብርጭቆ ወተት ግማሹን አስተርፎ ለሱ ከሰጠው በኋላ ፀጉሩን ይዳብሰው እንደነበረ አስታወሰ፡፡
አይኖቹ እንባ እያቀረሩ ላስቲኩ ላይ ያለውን አረቄ ተጐነጨ፡፡ ከሰአታት በፊት ኑዛዜውን ፅፎ ጨርሷል፡፡ ለሱ አሟሟት ተጠያቂው እራሱ እንጂ ሌላ ማንም ሰው እንዳልሆነ በግልፅ አስቀምጧል፡፡ ወረቀቱ ላይ ይህንን ይፃፍ እንጂ ለዚህ ያበቃው ሌላ ማንም ሰው ሳይሆን አባቱ እንደሆነ ግን ልቡ ያውቃል፡፡
ከሁለት አመታት በፊት የአባቱ አርባ እንዳለፈ እሱ፣ ሁለት እህቶቹና ወንድሙ ውርስ ሲከፋፈሉ ነበር የአባቱ ክህደት የጀመረው፡፡ ለሁሉም አንዳንድ ሚሊዮን ብር፣ ህንፃዎችና ቪላዎች ሲደርሳቸው፤ ለሱ ግን አንድ ሚሊዮን ብርና ይህን ከከተማ ውጭ ያለ ቢሸጥ ቢለወጥ ዋጋ የማያወጣ አሮጌ አንድ ክፍል ቤት ተናዘዘለት፡፡ እሱ የበኩር ልጅ ሆኖ ሳለ፣ ይህ አይን ያወጣ አድልዎ ለምን እንደተፈፀመበት እስካሁንም ሰአት ድረስ አልገባውም፡፡
ከውርሱ ክፍፍል በኋላ የአባቱ ጓደኛ የነበሩ አዛውንት፤ አባቱ ህይወቱ ልታልፍ ስትል ለሱ የፃፈውን ማስታወሻ ሰጡት፡፡
“ልጄ ሆይ፤ ገንዘብህን ጠብቅ፤ ይህ ካልሆነና ድህነት ካገኘህ ሌላ የትም ቦታ ሳትሄድ ወደ ግንቡ ቤት ሂድ፡፡ ከስቃይና ከውርደት ትድናለህ” ይላል፡፡
ወንበሩ ላይ እንደተቀመጠ አረቄውን ተጐነጨና ሲጋራ ለኮሰ፡፡ ይህ ሲጋራ በዚህ አለም ላይ የሚያጨሰው የመጨረሻ ሲጋራ መሆኑን ያውቃል፡፡ ኮርኒሱ ላይ የተንጠለጠለውን ገመድ ተመለከተ፡፡ ይህ ገመድ ከዘመናት በፊት ሸምቀቆውን አስፍቶ እሱን ይጠብቅ እንደነበረና እሱም አንገቱን ሸምቀቆው ውስጥ ለማስገባት ዕጣ ፈንታው እየጐተተው እዚህ መገኘቱ አስገረመው፡፡
ነገሩ የሆነው ቆም ብሎ ለማሰብ እንኳን ጊዜ ሳይሰጠው፣ እያሳሳቀው በዝግታ ነበር፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ የተጠናወተው የቁማር ሱስ ነበር ዋናው የሐብቱ ቀበኛ። የከተማውን ታላላቅ ቁማር ቤቶች እየጐበኘ በቀን እስከ አስር ሺህ ብር ድረስ ያጠፋ ነበር፡፡ ከስንት አንዴ ብቻ ሲበላ ብዙ ጊዜ ግን ይበላ ነበር፡፡ ሃብታም እንደሆነ ሁሉም ሰው ስለሚያውቅ የ”ፈላጩ” ቁጥር መንገድ ቀይሮ እስኪሄድ ድረስ አሰለቸው፡፡ እሱ የሚጠጣበት ጠረጴዛ ሁልጊዜ ከደርዘን በማያንሱ ሰዎች የተከበበ ሲሆን የሁሉንም ሂሳብ የሚዘጋው እሱ ነው፡፡ ሁሉም በፈገግታ እያየው በቁልምጫ ይጠራዋል፡፡ ይህንን ሲያደርግ ሰዎች ለሱ የሚሰጡት ክብር እየጣፈጠው መጣ፡፡ ያልገባው ነገር ግን ይህ ክብር የሚኖረው ገንዘቡ እስካለ ድረስ ብቻ መሆኑን ነበር፡፡
እሱ ሲመጣ ጠረጴዛው በጥንቃቄ ይወለወላል። ሴቶች እየሰረቁ ያዩታል፡፡ ደህና ገንዘብ ከያዘ ዊስኪ፣ ካልያዘ ደግሞ ቢራ የዘወትር ምርጫው ነው፡፡ አይፎን ስሪ ጂ ስልኩን እየነካካ የወሲብ ሳይቶችን ሲጐረጉር ያመሻል፡፡ አረብያን መጅሊስ፣ ዲኤስቲቪ፣ ውድ ጫት፣ ሺሻ፣ ድሪያ የለበሱ ቀያይ ሴት ካዳሚዎች ያለባቸው ውድ ጫት ቤቶች… መዋያዎቹ ነበሩ፡፡ ሐረግንም የተዋወቃት እዚያ ነበር፡፡
ውሸት ምን ያደርጋል ተወዳዳሪ የሌላት ቆንጆ ነበረች፡፡ ከዋክብት የመሳሰሉ አይኖችዋን እያስለመለመች በቁልምጫ ስትጠራው ልቡ እንደ ነጋሪት ይጐሰማል፡፡ ገላዋ ለስላሳ፣ ጠረንዋ ጣፋጭ፣ ድምፅዋ ሙዚቃ የሆነች የአልጋ ላይ ንግስት ነበረች፡፡ አንድ ችግር ግን ነበር። ሐረግ ያለገንዘብ ህዋሳቷ አይሰሩም፡፡ ገንዘብ ከሌለ ህይወት አልባ በድን ትሆናለች፡፡ ሰውነትዋ ይቀዘቅዛል፡፡ ንግግርዋ ይዘጋል፡፡ የአልጋ ላይ ዛርዋ ምሱ ወርቅ ወይም ውድ ገጸ በረከት አልያም በርካታ አረንጓዴ የብር ኖቶች ነበሩ፡፡
አረቄውን ደህና አድርጎ ተጎነጨና ሲጋራውን ለኮሰ። የተንጠለጠለውን ገመድ እያየ የሲጋራውን ጭስ ወደ ላይ ለቀቀው፡፡ ሰዓት ስለሌለው ስንት ሰዓት መሆኑን በትክክል ባያውቅም፣ እኩለ ሌሊት እንዳለፈ ግን እርግጠኛ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ከሚሰማው የውሾች ድምፅ በስተቀር ሌሊቱ ፀጥ እረጭ ብሏል፡፡ ሐረግን ለመጨረሻ ጊዜ ሲለያት አስታወሰ፡፡
አውሮፕላን ማረፍያ ውስጥ ነበር ለመጨረሻ ጊዜ ያያት፡፡ “ጠብቀኝ፣ የኔ ማር… ካንተ ተለይቼ መኖር አልችልም” ብላው ነበር ስትሰናበተው፡፡ የመኖርያ ፈቃዴን ላድስ በሚል ሰበብ፣ ዱባይ ስትሄድ የአውሮፕላን ቲኬትዋንና ሙሉ ወጪዋን የሸፈነው እሱ ነበር፡፡ ነገር ግን ተመልሳ አልመጣችም፡፡ ስልክም አልደወለችም። ደብዳቤም አልፃፈችም፡፡ የእስዋ ነገር በዚህ ሁኔታ ተጠናቀቀ፡፡
የባንክ ደብተሩ ላይ የቀረው ገንዘብ ሃምሳ ሺህ ብር ብቻ መሆኑን ያየ ዕለት ከያዘው አፍዝ አደንግዝ ባነነ፡፡ ያኔ ነው ገንዘብ ምንም ቢከማች ካልተሰራበትና በላዩ ላይ ካልተጨመረበት አላቂ መሆኑን የተረዳው፡፡
መጀመሪያ የወሰደው እርምጃ ወጪውን መቀነስና የቀረውን ገንዘብ ስራ ላይ ማዋል ነበር፡፡ ነገር ግን ሁለቱም አልተሳኩም፡፡ ገንዘቡ በየትና እንዴት እንደሚወጣ አይታወቅም፡፡ ንፋስ እንደበተነው አቧራ ተበተነ፡፡ አዋጪ መስሎት የገዛውም አክሲዮን ምንም የረባ ጥቅም አላስገኘለትም፡፡
ይባስ ብሎ የድርጅቱ ፕሬዚዳንት የባለ ድርሻዎችን ገንዘብ በሙሉ ጠራርጎ ከአገር መኮብለሉንና በፖሊስ እየተፈለገ መሆኑን ሰማ፡፡ የመጨረሻውን አንድ ሺህ ብር ከባንክ አውጥቶ ፊቱን አዙሮ ከባንኩ ሲወጣ፣ ገንዘብ ከፋይዋም በሀዘኔታ ከንፈርዋን ስትመጥ ሰማት፡፡ ያን ቀን ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡፡
አንድ ሺህ ብሩ ሶስት ቀን አልቆየም፡፡ ከዚያ በኋላ የነበረው ዕድል ከዚህ በፊት ውለታ የሰራላቸውን ሰዎች እየዞረ ብድር መጠየቅ ነበር፡፡ ሁሉም ሰው መክፈል እንደማይችል ስላወቀ የሚያበድረው ጠፋ፡፡ ከሚክስድ ግሪልና ከላዛኛ ወደ ምስርና ሽሮ፣ ከቢራና ዊስኪ ወደ ሐበሻ አረቄ ወረደ፡፡ ከበውት ሲስቁ የነበሩት ሰዎች ሁሉ የት እንደገቡ እስኪገርመው ድረስ አንዳቸውንም ማየት አልቻለም፡፡ ሁለቱ እህቶቹ ነዋሪነታቸው አውሮፓ ነው፡፡ አስተሳሰባቸውም እንደፈረንጅ ስለሆነ ችግሩን የሚረዱለት አልነበሩም፡፡
“ችግርህን እራስህን ችለህ መወጣት አለብህ፣ እኛ ከዜሮ በታች በሆነ ብርድ ነው በቀን 18 ሰዓት እየሰራን ቤተሰብ የምናስተዳድረው፡፡ ይሄ የምልክልህ የመጨረሻ ገንዘብ ነው” ብላ ነበር ትልቋ እህቱ መቶ ዶላር የላከችለት። ከዚያ በኋላ ድምፅዋ ጠፋ፡፡
ታናሽ ወንድሙ በመኪና ስራ ነው የሚተዳደረው፡፡ ችግሩን የነገረው ቀን በጣም ያዘነ መስሎ ሁለት መቶ ብር ሰጠው፡፡ በሁለተኛው ቀን መቶ ብር ብቻ፡፡ በሶስተኛው “የለም” አስባለ፡፡ ከዚያ በኋላ የእሱን ስልክ ማንሳት አቆመ፡፡
የቤት አከራዩ ኪራይ አልከፈልክም በሚል ሰበብ አንድ ቀን ማታ ዕቃውን በር ላይ አስቀምጠው ጠበቁት። ምርጫ ስላልነበረው በትኋንና በቁንጫ እየተሰቃየ፣ አንሶላው ታጥቦ የማያውቅ ርካሽ አልጋ ላይ በየቀኑ እየከፈለ ማደር ጀመረ፡፡ ስልኩ፣ ሰአቱ፣ ልብሶቹ… ተሸጠው አልቀዋል፡፡ ማንኛውንም ስራ ለመስራት ቢሞክርም ተያዥና ዘመድ ስለሌለው የሚቀጥረው ጠፋ። መራብ ጀመረ፡፡ ወደማይታወቅበት ሩቅ ሰፈር እየሄደ መለመን ጀመረ፡፡ ሁኔታውን ያዩ እያዘኑ ይሰጡታል፡፡ አንዳንዶቹ ያመናጭቁታል፡፡
አንድ ቀን መንገድ ዳር ቆሞ ሽንቱን ሲሸና፣ አንድ ከዚህ በፊት በአይን የሚያውቀው ሰውም አጠገቡ ቆሞ ይሸናል፡፡ እሱ ግን እየሸና እንባው ጉንጩ ላይ ይፈሳል። ሰውየው ምን እንደሚያስለቅሰው ጠየቀው፡፡ ምሳ እንዳልበላ ነገረው፡፡ ሰውየው ትከሻውን ያዘና አይኑን ትኩር ብሎ እያየው “ወንድ ልጅ እንደወርቅ በእሳት ይፈተናል፤ ፈጣሪህን እመን፤ ድቅድቁን ጨለማ ብርሃን ማድረግ ይችላል፤ ስለሌለኝ ገንዘብ አልሰጥህም፤ ይህን ቃል ግን እሰጥሃለሁ” አለውና ሄደ፡፡
እሱ ግን ያን ቀን ወሰነ፡፡ የእሱ ነገር ያከተመና ምንም ሊለወጥ እንደማይችል ስለደመደመ ሲሸሸው ወደነበረው ግንቡ ቤት መጣ፡፡ ገመዱም ተንጠልጥሎ እሱን እየጠበቀ ነበር፡፡ እሱም አሳምሮ ያውቃል፡፡ ስለዚህ ኑዛዜውን ጻፈ።
ሲጋራውን ረግጦ ካጠፋ በኋላ ከተቀመጠበት ተነሳ። አሁን ሰአቱ ደርሷል፡፡ ወንበሩን አንስቶ ከተንጠለጠለው ገመድ ስር አስቀመጠው፡፡ ወንበሩ ላይ ወጣና የገመዱን ሸምቀቆ አንገቱ ላይ አጠለቀ፡፡ “ፈጣሪዬ በምህረትህ ታረቀኝ” አለና በእግሩ ወንበሩን ገፍትሮ ጣለው፡፡ ገመዱ አንገቱ ላይ ሲጠብቅና የቤቱ አምፖል ሲፈነዳ አንድ ሆነ። አንዳች ናዳ እላዩ ላይ ወረደና በጀርባው መሬት ላይ ተዘረረ፡፡ ጨለማ ስለሆነ አይታየውም፡፡ ግን እንዳልሞተ እርግጠኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ይተነፍሳል፡፡
በጀርባው እንደተዘረረ ወደ አቅሉ ተመለሰ፡፡ ድንገት ትዝ አለው፡፡ ኪሱ ውስጥ ጋዙ ያለቀ ግን ባትሪ ያለው ላይተር ነበረው፡፡ ላይተሩን አወጣና ባትሪውን አበራ። ያየውን ማመን አልቻለም፡፡ ገመዱ ተንጠልጥሎበት የነበረው ኮርኒስ ተገንጥሏል፡፡ መሬቱ ላይ ረብጣ ብር ተከምሯል፡፡ በግምት ሶስት ሚሊዮን ይሆናል፡፡ ቁና ቁና እየተነፈሰ ከክምሩ ብር መሃል ያለች አንዲት ወረቀት አነሳ። የአባቱ እጅ ፅሁፍ ነው፡፡
“ልጄ ሆይ፤ ያለህን ጨርሰህ ወደዚህ እንደምትመጣ አውቅ ነበር፡፡ አሁን ሰው፣ ገንዘብ፣ ህይወት ምን መሆኑን አውቀሃል፡፡ ከሞት በላይ ምንም ስለሌለ ከአሁን በኋላ አትታለልም፡፡ ስለዚህ ይህ ሃብት ያንተ ነው፤ ጸልይልኝ” ይላል፤ እውነተኛውና ዋናው ኑዛዜ፡፡  

Published in ልብ-ወለድ

         የመጽሐፍ ገበያው ዐይን ያጥበረብራል። በተለይ እንደ በቆሎ እሸት ክረምቱን ጠብቆ የሚዘንበው የመጽሐፍ ዶፍ ከመብዛቱ የተነሳ ፍሬን ከገለባ ለይቶ ለማጨድ ጊዜም ችሎታም የሚሻ እየሆነ ነው፡፡ ለገበያ ብቻ ተብለው የሚቀመሙ መጻሕፍት፣ ለነፍስ ከተጻፉቱ ጋር ሰርገው እየገቡ ክረምት በመጣ ቁጥር እንደበረዶ አንባቢ ላይ ይዘንባሉ፡፡ እንደኔ ታዲያ ክረምቱን ብቻ ጠብቆ የሚያነብ ፍዝ አንባቢ ለምን አይጭበረበር!
በእርግጥ ተኮናኝ እና ጻድቅ ጸሐፍት በየፊናቸው ያበጃጁትን፣ የአቅሜ ያሉትን የጥበብ ሥራ እንካቹህ መባል ምንም ይሁን ምን ደስ ያሰኛል፡፡ በበኩሌ መጻሕፍት እንዴትም ሆነው ይብዙልን ከሚሉት ወገን ነኝ፡፡ ለምን ቢሉ መጻሕፍት እንደ ጨቅላ በአንቀልባ ታዝለው በሚሸጡባት መዲናችን የአንባቢም የተነባቢም ቁጥር እየበዛ ሲሄድ የተሻለ ማስተዋል፣ የተሻለ መስከን፣ የተሻለ መብሰል፣ የተሻለ መግባባት ቀስ በቀስ እየተዋሀደን ይሄዳል ብዬ ስለማምን ነው፡፡
በእግረኛ መንገድ መጻሕፍት እንደ ጌሾ ሜዳ ላይ ተሰጥተው አንባቢን ሽቅብ እየተቁለጨለጩ ሲለማመጡ ያሳዝናሉ፡፡ ይሄኔ አዱኛን መዥረጥ አድርጎ መሸመት ይፈታተነናል፡፡ ኾኖም ብስሉን ከጥሬ ለመለየት አንዳንዴ እድልም ያስፈልጋል ልበል? በቅርብ ጊዜ በሳሳ የንዋይ አቅም መቀነቴን የፈታሁላቸው የጥበብ ሥራዎች መናኛ ሆነው ክፉኛ አስኮርፈውኝ ያውቃሉ፤ ከአንዴም ሁለት ሦስቴ፡፡ በዚያ ላይ ትክክለኛ ዋጋቸው ተፍቆ እጥፍ ዋጋ ከፍዬባቸው እንደነበረ የኋላ ኋላ ስረዳ ኩርፊያዬ ሰነበተብኝ፡፡ ከዚህ ልምዴ ተነስቼ መፃሕፍትን ከመግዛቴ በፊት የወዳጅ ዘመድ ጥቆማንና የሕትመት ሚዲያ ሂስን ‹‹እህ!›› ብዬ እሰማለሁ፡፡ እንዳለመታደል መጻሕፍትን የሚሰብኩን ጥቂት እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። በግሌ ከጋዜጣ አዲስ አድማስን፣ ከሬዲዮ ሸገርን በዚህ ረገድ አደንቃለሁ፡፡
እስኪ ዛሬ ከረዥም ጊዜ በኋላ ብዕር እንዳነሳ ምክንያት የኾነኝን አንድ ታሪካዊ ልቦለድ መጽሐፍ ላስቃኛችሁ፡፡ “አውሮራ” ይሰኛል፡፡ ደም የመሰለ የሽፋን ልባስ የተጎናጸፈ፣ ታንክ ላይ የቆሙ ታጋዮች ጥላ በስሱ የሚታይበት፣ ጦርነት ጦርነት፣ ባሩድ ባሩድ የሚሸት፣ በክብደቱም “ድልብ” የሚባል ዓይነት መጽሐፍ ነው፡፡ የገጹ ብዛት ከ350 በጥቂት ያነሰ፣ ለገበያ ከቀረበ ሁለት ወርም ያልሞላው የታሪክ ልቦለድ መጽሐፍ፡፡
ቅኝቴን ከሽፋኑ ብጀምርስ! በመጽሐፉ ጀርባ ላይ የተጻፈው ነገር፣ ይህን በይዘቱና ባነሳው ጭብጥ በደምሳሳው ግሩም ኾኖ ያገኘሁትን መጽሐፍ እንዳልገዛው አድርጎኝ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ አንድ ስማቸው ያልተጠቀሱ ዲፕሎማት ስለመጽሐፉ ተናገሩ ተብሎ የተቀመጠ አንቀጽ ነው ለዚህ አፍራሽ ስሜት የዳረገኝ። እንዲህ ይላሉ፡-“ …የተኖረን ሕይወት እየጻፉ ልቦለድ ብሎ ነገር የለም…በእውነቱ (ይህ መጽሐፍ) ከኦሮማይ በኋላ የመጣ ድንቅ የጥበብ ሥራ ነው ብዬ አፌን ሞልቼ እናገራለሁ…”
ይህ የጀርባ ጽሑፍ ብሽቅ አድርጐኛል፤ በሁለት ምክንያት፡፡ አንደኛ ይህንን መጽሐፍ ለማድነቅ አንድን ዘመን ተሻጋሪ ቱባ መጽሐፍ ስም አንስቶ ማወዳደር መልካም ዘዴ ኾኖ አልተሰማኝም፡፡ “ኦሮማይ” በሚሊዮን አንባቢዎች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በሁለት አገር ሕዝቦች ዘንድ እንደ የጋራ አድባር የሚታይ ታላቅ የጥበብ ዉጤት ነው፡፡ አንድን አዲስ ሥራ ከዚህ ዘመን ተሸጋሪ የሥነ-ጽሑፍ ሥራ ጋር (ያውም ደራሲው ሕይወቱን ከፍሎበታል) ማነጻጸር ለኔ ቀሽምነት ብቻ ሳይሆን የ‹‹አውሮራ›› መጽሐፍ ደራሲን በሥራው እንዳይመዘንና ለጥቃት እንዲጋለጥ ያደረገ ነው። በቦክስ ስፖርት ቋንቋ ከመነዘርነው፣ የከባድ ሚዛን ሻምፒዮን የሆነን ቡጢኛ ከቀላል ሚዛን ተወዳዳሪ ጋር እንደማቧቀስ ያለ ነው፡፡
ሁለተኛው ምክንያቴ ይህንን የመሰከሩት ሰው (ዲፕሎማት) ስማቸው አለመገለጹ ነው፡፡ እንዲህ አፋቸውን ሞልተው ስለ መጽሐፍ የሚናገሩ ዲፕሎማት ስለማንነታቸው ያልገለፁት ለምንድነው? ስል ጠየቅሁ። ምናልባት የመጽሐፉ ማጠንጠኛ በአመዛኙ የኤርትራና የኢትዮጵያን ስስ ብልቶች የሚነካ በመሆኑ ፍርሃት ገብቷቸው ይሆን? ከፈሩ የሰው መጽሐፍ ሽፋን ላይ ምን ድቅን አደረጋቸው? መልስ ያላገኘሁለት ጥያቄ ነው፡፡
ለማንኛውም ወደ ውስጥ ገጾች ይዣችሁ ልዝለቅ፡፡
የመጽሐፉን የመጀመሪያ ገጾች ገልጬ ከሰዓታት በኋላ ራሴን የአንደኛው ምዕራፍ የመጨረሻው ገጽ ላይ ሳገኘው፣ ጊዜ ቆሞብኝ እንደነበር ተረዳሁ። እንደ ፊልም ከጅምር እስከ ምዕራፉ መቋጫ ዝም ብዬ ተወጣሁት ብል ይቀለኛል። ስሟ “ፍልይቲ” የምትባል ኤርትራዊት የኢሳያስ ልዩ ሰላይ ስታዲየም አካባቢ ከሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ወጥታ ሒልተን ሆቴል ውስኪ እየጠጣ ከነበረ አንድ ጎልማሳ መልከመልካም ኢትዮጵያዊ ሚኒስትር ጋር ስተቀብጥ በምልሰት የሚተርክ ንዑስ ክፍል ነው እንዲህ ፉት ያልኩት፡፡ ወቅቱ (መቼቱ) ደግሞ ሁለቱ አገራት ነፍጥ ለማንሳት ጥቂት ወራት ሲቀራቸው ነው፡፡ ደራሲው የሁለቱን አገራት እፍ ያለ ፍቅር የመጨረሻ ቀናትን ነው እንግዲህ በዚህች ፍልይቲ በተባለች ኤርትራዊትና በዚህ ስሙ ባልተጠቀሰ መልከመልካም ኢትዮጵያዊ ሚኒስትር ዉሉ ያለየለት ግንኙነት ሊያሳየን የሞከረው፡፡ ተሳክቶለታል፡፡
አጠቃላይ የመጽሐፉ ጭብጥ በድንበር ውዝግብ የተነሳ ከኤርትራ ጋር ያካሄድነውን መሪር ጦርነት ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ አመክንዮዎችን በተጨባጭ መረጃ እያዋዛ የሚተርክ ዘጋቢ ፊልም ይመስላል። እኛ እንደ ሕዝብ ከሚነገሩንና ከተነገሩን የጦርነቱ ምክንያቶች ጀርባ በምስጢር ይካሄዱ የነበሩ ጉዶችን ነው ልቦለዱ የሚተርክልን፡፡ አንዳንዶቹን በተባራሪ ሰምተናቸዋል፣ አንዳንዶቹ ደግሞ እንዲሁ 6ኛ ህዋሳችን ነግሮን እንጠረጥራቸው የነበሩ ጉዳዮች ናቸው። ባድመ ጦርነቱን ለመጫር ህዝብን ለማነሳሳት ያገለገለች ክብሪት ከተማ እንጂ አንድም ጊዜ እውነተኛ የጦርነት ምክንያት እንዳልነበረች በመረጃና በማስረጃ ይነገረናል። የናቅፋ መታተም፣ ኤርትራዊያን ከኢትዮጵያ ያገኙት የነበረው ልዩ ጥቅማጥቅም መቋረጥ (ቡናን ወደ ዉጭ ገበያ መላክን ይጨምራል)፣ የኢሳያስ ኢትዮጵያን ጥሬ እቃ አቅራቢ፣ ኤርትራን አምራች አድርጎ የመገንባት ህልም ተግዳሮት ማጋጠሙ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኤርትራዊያን ጭንቅላት ውስጥ ስለራሳቸው የሚሰጡት የተጋነነ ምስል… እንደ ካንሰር እየፈራረሰ መሄድ ወዘተ… እንዴት ጦርነቱን አይቀሬ እንዳደረጉት ከ “አውሮራ” መጽሐፍ ትርክት እንረዳለን፡፡ የመጽሐፉን እንዲህ ከኮብልስቶን የጠጠረ ጭብጥ፣ ፖለቲካ ጭራሽ ለማይስማማው አንባቢ ማቅረብ ደረቅ ጂን ያለ አምቦ ዉኃ እንዲጋት ከማስገደድ አይተናነስም፡፡ ኾኖም ደራሲው በዚህ ረገድ መለኛ መሆኑን ተገንዝቤአለሁ፡፡ “ፍልይቲ” የምትባል በቁመና የኦሮማይዋን “ፊያሜታ” የምትስተካከል፣ ሳህል በረሀ የተወለደች፣ ሃይላይ ከሚባሉ በሳልና አመዛዛኝ ኤርትራዊ ሚኒስትር የተገኘች፣ በድርጊቷም በአስተሳሰቧም ፍቅር የምታሲዝ ገጸባህሪን ቅልብጭ ቁልጭ አድርጎ ስሎልናል። ምናልባት በልቦለድ ዓለም መንታ መፍጠር የሚያስችል ዘረመል ካለ ፍልይቲ የኦሮማይዋ ፊያሜታ መንታ ገጸባህሪ ሆና የተወለደች ትመስለኛለች፡፡ ፍልይቲ መጽሐፉን አገባድጄውም ቢሆን ከአእምሮዬ ተሰንቅራ የቀረች፣ የሆነ ቦታ የማውቃት የማውቃት የምትመስለኝ ድንቅ ገጸባህሪ ናት፡፡ ደራሲው ይቺን ከሳሕል በረሀ ውጭ ዓለም ያለ የማይመስላት፣ በኤርትራ ስም ምላ፣ በወዲ አፈወርቂ ስም የምትስል የተቃጠለች ኤርትራዊት ብሔርተኛን፣ አስገደ ከሚባል አንድ ሚስኪን ኢትዮጵያዊ የቴሌኮሚኒኬሽን ኢንጂነር ጋር በፍቅር አስተሳስሮ የነገር መላ ቅጡን ያስጠፋታል፡፡ በዚህ የጦፈ የፍቅር ታሪክ ውስጥ ነው እንግዲህ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የሚተነተንልን፡፡
እውነት ለመናገር በህወሓት እና ሻእቢያ የጫጉላ ሽርሽር መገባደድ ያልተስጓጎለውን ይህን ድንበር ዘለል የጦፈ የፍቅር ታሪክ ስለተከለሰበት ብቻ አይደለም “አውሮራ” መጽሐፍን ለመክደን የምንቸገረው። ህወሓት መቀሌ ላይ በምስጢር ያካሄዳቸው ስብሰባዎች፣ በስብሰባዎቹ ላይ የሚታየው የመለስ ዜናዊ ግትርነት፣ የገብሩ አስራት እልኸኝነት፣ የስዬ አብረሃ ጦረኝነት ወዘተ… ‹‹ልቦለድ›› በሚል የይለፍ ቃል መጽሐፉ ላይ ስለተዘከዘኩልን ጭምር ነው፡፡ በግሌ እነዚህ ስብሰባዎች ያለ በቂ ጥናት እንዲሁ በፈጠራ ተጽፈዋል ብዬ አላምንም፡፡ ምናልባት በኋላ ላይ በማኅበራዊ ድረገጾች እንደሰማሁት፤ ደራሲው ቀደም ሲል በኢህአዴግ መዋቅር ውስጥ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሆነው ለአጭር ጊዜ አገልግለዋል የሚለው ተባራሪ ወሬ እውነት ከሆነ፣ መጽሐፉ ላይ ይፋ የተደረጉልንን ምስጢራዊ ስብሰባዎች ቢያንስ ቃለ ጉባኤዎቹን የማግኘት እድል ገጥሟቸው፣ የኋላ ኋላ ደራሲው ከኢህአዴግ ቤት ወጥተው ለጻፉት ልቦለድ እንደ ግብአት ተጠቅመውበት እንደሚሆን እገምታለሁ። ተስፋዬ ገብረአብ ዛሬም ድረስ በኢህአዴግ ቤት ሳለ የሰበሰባቸውን ሀሜቶች እየመዘዘ እንደሚያስግተን አይነት መሆኑ ነው፡፡
አተራረክ
“አውሮራ” በበዓሉ ግርማ ኦሮማይ ከምናውቃት አስመራ ጋር ዳግም ለአይነስጋ የምንበቃበት የጥበብ ስራ ነው፡፡ ኾኖም አስመራን የናፈቀ ሰው መፅሀፉን ሲያነብ ናፍቆቱ ቢበረታበት እንጂ አይበርድለትም፡፡ አስመራ ከነጻነት በኋላ የኢሳያስ ሳሎን ሆናለች፡፡ ሕዝብ ኢሳያስን ያመልካል፤ ኢሳያስ ኤርትራን ያመልካል፤ ሁለቱም ሀሳቦች ግራ ለሆኑባቸው የአዲሱ ትውልድ አባላት ሁለት ምርጫ ተቀምጧል፤ ወይ ወደ ሳዋ ወይ ወደ ስደት ማዝገም፡፡ ለአዲሱ ትውልድ አባላት ኢትዮጵያ ቀኝ ገዢ ተደርጋ ትሰበካለች፣ ከአንድ ፕሬዝዳንት ውጭ ለማየት አልታደሉም፣ ሳዋ ዩኒቨርስቲ እንጂ የጦር አካዳሚ እንደሆነ አይነገራቸውም፡፡ በዚህች ምድር ላይ ለመቆየት ከሳዋ መመረቅ ወይም ቀይ ባሕርን ማቋረጥ ብቻ እጣቸው እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ ያሳዝኑናል፡፡ እኛን እንደ ቅኝ ገዢ ከሚያስቡ የኤርትራ አዲስ ትውልድ ጋር መታረቅ እንዴት ፈታኝ እንደሚሆን ደራሲው ጠቆም አድርጎን ትረካውን ይቀጥላል፡፡
የአስመራ ሕዝብ ኢትዮጵያ ልትወረን ነው ብሎ ከልቡ አምኖ በሰላም አገር ክተት ያውጃል፡፡ አሁንም ድረስ በተጠንቀቅ ላይ እንደሆነ የምንረዳው “አውሮራን” ስናነብ ነው፡፡ “…አጋሜን እኛው ሹካ አያያዝ አስተምረናት፣ እኛው ለስልጣን አብቅተናት ዛሬ ጠግባ በኛው ተነሳች….!” እያለ ቁጭቱን በአደባባይ ይናገራል፤ የአስመራ ሕዝብ፡፡ በጥቅሉ ኤርትራዊያን አጋሜ ብለው ለሚጠሩት የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተወላጆች ብሎም ለኢትዮጵያዊያን ያላቸውን ዝቅ ያለ ግምት የምንረዳው የመፅሃፉን ገጾች በገለጥን ቁጥር ነው፡፡
የኤርትራ የፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ሀይላይና የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ቁርሾ ፣ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ጄነራል ባህታ እና የነጻነት ድብቅ ግንኙነት፣ ‘የፍልይቲ እና የአስገደ እውነተኛ ፍቅር’፣ የአጋሜና የአስመራዊያን የስነልቦና ጦርነት በታሪኩ ውስጥ የተሰደሩ ጡዘትን የሚጨምሩ የስሜት እቶኖች ናቸው። ይህ ሁሉ ታሪክ ከገጽ ገጽ ሲንደረደር በድንቅ የአተራረክ ስልት በመታጀብ አንባቢው ሊገምተው በማይችለው መልኩ እየተቋጨ ስለሚሄድ የስሜት ገዢነቱ ደረጃ ከፍተኛ ነው።ምናልባት ትርክቱን አልፎ አልፎም ቢሆን የሚያናጥቡት የመልከዓ ምድር ገለጻዎች እዚህም እዚያም መሰንቀር ሊሆን ይችላል፡፡ ገጸ ባህርያት ቃለምልልስ ሲያደርጉ “…አለው” “…አላት” የሚሉ ማሳረጊያ አንቀጾች ቢቻል መገደፍ ካልሆነም መቀነስ ነበረባቸው፡፡ ኾኖም በብዙ ጸሐፊዎቻችን ላይ የማናስተውለው ስለሚጽፉት ነገር ግልብ ሳይሆን ጥልቅ መረጃን ይዞ መነሳት እንዲሁም አንድ ርዕሰ ጉዳይን ጥንቅቅ አድርጎ መገንዘብ፣ የ “አውሮራ” ጥንካሬ ሆኖ ጎልቶ ስለወጣ የመጽሐፉን ድክመቶች አንሰው እንዲታዩ ያደረገው ይመስለኛል፡፡  ደራሲው ከየት እንዳመጣው ባላውቅም የውትድርናውን ዓለም ቋንቋና ሳይንስ ከበቂ በላይ በሆነ ሁኔታ የተረዳ፤ የሁለቱን ሕዝቦች ባህልና የጦርነት ስነልቦና ከፍ ባለ ደረጃ መተንተን የቻለ፣ ጠንቅቆ የሚያውቀውን ጉዳይ ብቻ በጥንቃቄ ለመጻፍ የተነሳ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
ይህንንም በበርካታ ማሳያዎች መመልከት ይቻላል። በጦር ሜዳ ውሎ አሸናፊው የሚሆነው ወገን ማሟላት ስለሚገባው የሞራል እና የብቃት ስንቅ፣ ወታደራዊ ስትራቴጂክ ቦታዎችን ለመቆጣጠር የኃይል አሰላለፍ ምን ሊሆን እንደሚገባው፣ የዉጊያ መልክአምድርና ስነልቦና እንዴት እንደሚገነባ፣ የጦርነት ፕሮፓጋንዳ ሕዝብን እንዴት እንደሚያውር በወከላቸው ገጸ ባህሪያት አማካኝነት በአንባቢያን አእምሮ ውስጥ ምስል እየከሰተ፣ ከምዕራፍ ምዕራፍ ይዞን ይነጉዳል። ይህም የመረጃ አቀራረብ የታሪኩን ልብወለድነት መቀበል እስኪያዳግትን ድረስ ለእውነታው ዓለም ቅቡል የሆነ ስሜት ሲፈጠርብን መልሰን እንገረማለን። መጽሐፉን አጋምሰንም ልቦለድ መሆኑን በመዘንጋት ቱግ እንላለን፡፡ ደረቅ ሀቆችን ሳይታሹ እንደወረደ በማቅረብ አንባቢያንን ገጽ በሚያስቆጥሩ አሰልቺ መፃህፍት ላይ የሚታይ የአተራረክ ረሃብ እዚህ ጋ አይስተዋልም። ገጸ ባህሪያቱ የሚያደርጉት ምልልስ የተመጠነ፣ደረጃውን የጠበቀ የቋንቋ አጠቃቀም ያለው፣ የደራሲው ጣልቃ ገብነት በጣም ኢምንት የሆነ ድንቅ የጥበብ ስራ ነው ብዬ ለመመስከር እገደዳለሁ።
በቋንቋ አጠቃቀም ረገድ ምናልባት ደራሲው ሊተችበት የሚገባ ነጥብ ቢኖር፣ የትግርኛ ገለጻዎችን አቻ ትርጉም ሳይሰጥ የማለፉ ጉዳይ ነው፡፡ ምናልባት የታሪኩን ግስጋሴ ላለመግታት ሊሆን ይችላል፡፡ ኾኖም አልፎ አልፎ ወሳኝ ለሆኑ ቃላት በግርጌ ማስታወሻም ቢሆን ትርጉም መስጠት ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ፍቅር እና ጦርነት
ፍልይቲ የመጻሐፉ ታሪክ ሃዲዱን ሳይስት ሚዛኑን ጠብቆ እስከ ፍጻሜው ድረስ በአማረ መልኩ እንዲዘልቅ የፊትአውራሪነቱን መንበር ተቆናጣ የሾፈረች ገጸ ባህሪ ናት። ፍልይቲ አንዳንዴ የምትሄድበት የመሰጠት ደረጃ ከደራሲው ምናብ ውጪ በእውኑ ዓለም የማትገኝ የፍቅር ሰማእት አድርገን እንድንቆጥራት ታስገድደናለች። ከኢትዮጵያዊው አስገደ  ሙሉጌታ ጋር እፍ ክንፍ የምትልበት ፍቅር፣ የታሪኩ አስኳል ሆኖ የተቀመጠ ሲሆን ይህንን ኢትዮጵያዊ በማፍቀሯ  የተነሳ የምታየው ውጣ ውረድ አንባቢን በስሜት አብሮ ከፍ ዝቅ የሚያደርግ ትእይንት ነው። የጦርነት ታሪክ ውስጥ ፍቅር መነስነስ የተለመደ ነው፡፡ የፍልይቲና የአስገደ ፍቅር ግን ይለያል፡፡ በሁለቱ ገጸ ባህርያት ፍቅር በኩል የሚነገረን ታሪክ የአገር ታሪክ ነው፡፡ የሁለት አንድ ነን የሚሉ ሕዝቦች ታሪክ፡፡ የሁለት በነፍስ የሚፈላለጉ ወንድማማች ህዝቦች ታሪክ፡፡
ሁለቱ አገሮች ወደለየለት ጦርነት ለመግባት አፋፍ ላይ በነበሩበት በዚያ ቀውጢ ወቅት የአስገደ እና የፍልይቲ ፍቅር በሀገሬውም ሆነ ስልጣን ላይ በነበረው የፖለቲካ አመራር ዘንድ ጥርስ የሚያስገባ ተግባር ቢሆንም ጥንዶቹ በጀብደኝነት የሚነጉዱበት ወሰን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ የሚዘልቅ ነው። በተለይ ኤርትራያውያን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደጸጉረ ልውጥ በሚታዩበት በድንበር ግጭት ዋዜማ፣ ለፍልይቲ የሀገሯ መንግስት የሰጣትን ከፍተኛ ሃላፊነት ገሸሽ በማድረግ ከአስመራ እስከ ደብረሲና ድረሰ የምታደርገው በውጥረት የተሞላ ጉዞ፣ የታሪኩን የልብ አንጠልጣይነት ደረጃ ከጫፍ ላይ ያደርሰዋል። ደራሲው የፍልይቲን ለፍቅር የሚከፈል ፈተና ልብ ሰቃይ በሆነ አተራረክ እስከ ታሪኩ መገባደጃ ድረስ እያዋዛ አብረነው እንድንዘልቅ ስለሚጋብዘን፣ መፅሐፉን ሳንከድን በአንድ ትንፋሽ ለመጨረስ ዳገት አይሆንብንም። በአጠቃላይ ደራሲው በልብ ሰቀላው ረገድ እጅግ በጣም እንደተዋጣለት ዋቢ የሚሆኑ ታሪኮችን ለማግኘት ብዙ መድከም አይጠበቅብንም። ጥንዶችን በጦርነት ውስጥ አፋቅሮ ልብን መስቀል በፊልምም በመጽሐፍም ብዙ የተሰራበት በመሆኑ አሰልቺ ሊመስል ቢችልም ደራሲው በአዲስ አካሄድ ሞክሮት ተሳክቶለታል፡፡
የስነልቦና ጦርነት- በ“አጋሜ” በአስመራዊያን መሐል
የህወሓት እና ሻእቢያ አፍላ ፍቅር እስከ ድንበር ግጭቱ ድረስ ንፋስ አልገባውም ነበር። ሁለቱ ግንባሮች ምንም እንኳን ለተመልካች የሚያስቀና የእርስ በእርስ ግንኙነት ያላቸው ቢመስሉም በስነልቦናው ረገድ የነበራቸው መቃቃር ግን አስደንጋጭ የሚባል ነው፡፡ ደራሲው ሳያስበውም ይሁን አስቦት የነገረን አንድ ትልቅ ጭብጥ ቢኖር ይህንኑ ነው፡፡ ሻዕቢያ በተለይም ቆለኛው ኤርትራዊ ለአጋሜዎች ያለው ንቀት ስር የሰደደ ነው፡፡ ጦርነቱ የመነጨውም ከሻዕቢያ የባድመ ይገባኛል ጥያቄ ሳይሆን ለህወሃት ካለው ፍጹም የዘቀጠ ንቀት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ከመጽሐፉ ልብወለድነት የተነሳ ይህን መሰሉ ደረቅ የታሪክ እውነታ ተደፍጥጦ ቢታለፍ የደራሲውን ገለልተኛነት በተጠራጠርን ነበር። ይህ ግን አልሆነም። ከዚህ በተቃራኒው ደራሲው ከታሪክ የሚቀዳ እውነታን ለዚህ ዓላማ በተፈጠሩ ገጸ ባህሪያት አማካኝነት መጠነኛ ግንዛቤ ያስጨብጠናል። ሻእቢያ ህወሓትን እንደ ሎሌ የሚመለከትበትን ስነልቦና ከድህረ ደርግ በኋላም እንዳልተወው በተለያዩ ገጾች ላይ በሰፈሩ ኃይለ ቃላት እንረዳለን። በገጽ 78 ላይ የኤርትራ መከላከያ ሚኒስትር የሆኑት ሰው (ጄኔራል ስብሐት እንደሆኑ ይገመታል) አዲስ አበባ በሄዱ ጊዜ በህወሓት ሊቀመንበር ሞቅ ያለ መስተንግዶ እንዳልቀረበላቸው በማመካኘት ውስጣቸው የተዳፈነውን የንቀት አመለካከት እንዴት እንደሚያፈነዱት ያሳያናል…
“…ትናንት እሽኮኮ ብለን ለስልጣን ያበቃነው የወያኔ አለቃ ከኤታማዦር ሹሙ ጋር ተነጋገር ብሎ ሆቴል ውስጥ ጎልቶኝ የአውሮፓ መሪ ለመቀበል ቦሌ ይሄዳል እንዴ?....(እስከዚህ ድረስ ንቀውናል)….”
ይህ ራስን ማማ ላይ ሰቅሎ የማየት አመለካከት በፖለቲካ አመራር ላይ በተቀመጡት ሰዎች ዘንድ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። ተራው የሀገሬው ህዝብ ሳይቀር የሚጋራው ነው።
..በገጽ 131 ላይ አስመራ ውስጥ ፍልይቲን የጫነው አካል ጉዳተኛ ባለታክሲ እንዲህ ይናገራል…………
“..ሰላሳ ዓመት ሙሉ ተዋግተን አማራን ስንጥል አሁን ደግሞ አጋሜ በተራዋ ልትቀልድብን ተነሳች።ይህንን በዐይኔ ከማይ በቃ……የቀረውን አካሌን ብገብር ይሻለኛል ብዬ ከማንም በፊት (ለመዝመት) ተመዘገብኩ …” ይላል፡፡
ሁለቱም ግለሰቦች ስለ ህወሓት እና ስለትግራይ ሕዝብ ያላቸውን አመለካከት በምልልሳቸው ሹክ ይሉናል። ይህ ከአስመራዊያን አንጻር ብቻ አይደለም የተብራራልን፡፡ የህወሓት ጎበዝ አለቆች የኤርትራ አቻዎቻቸውን እንዴት እንደሚመለከቱም በጥልቀት ተብራርቶልናል፡፡ በተለይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ በኤርትራዊያን ላይ የሚጨክን አንጀት እንዳልነበራቸውና ይህም የኋላ ኋላ ለህወሓት መሰንጠቅ እንደዳረጋቸው አቶ ስዬ አብረሃን በሚወክሉ ገጸ ባህሪ በኩል ተነግሮናል፡፡ በወቅቱ የትግራይ ክልል ገዢ የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት ስማቸው አይጠቀስ እንጂ ግብራቸውና ገጽታቸው እዚህም እዚያም ተጠቅሷል፡፡
ለምሳሌ ገጽ 97-98 ላይ  እኔ በግሌ እሳቸውን ይወክላሉ ያልኳቸው ገጸ ባህሪ እንዲህ ተገልጸዋል፡-
“…ከዐይኖቻቸው ተለይቶ የማያውቀውንና ከኮካ ጠርሙስ ቂጥ የተሰራ የሚመስለውን ነጭ የዕይታ መነጽር በእጃቸው አስር ጊዜ ከፍ ከፍ እያደረጉ፣ አንዴ የቀኝ ወዲያው ደግሞ የግራ ጆሯቸውን በእጆቻቸው ሌባ ጣቶች እየጎረጎሩ....ዝቅ ባለ ድምጽ መናገር ጀመሩ፣ “…አዲስ አበባ ያለው የ’ኛ አመራር በጣም ዝቅ ሲል ሀሳባዊ ነው፣ በጣም ከፍ ሲል ግን እንዝህላል ሆኖ አግኝቼዋለሁ:: እኛ ‘ፍቀዱልን፣ ከጎረቤት መንግሥት ጋር ጦርነት እንግጠም...’ ብለን አልጠየቅናችሁም እኮ:: እኛ የጠየቅናችሁ ‘እንደማንኛውም ዘመናዊ መንግሥት ዝግጅት ጀምሩ ነው:: የኤርትራ መንግሥት የወረራ ዝግጅት እያለ ይቅርና እንዲሁም ቢሆን ያበደ ነው:: ምን ለማለት ፈልጌ ነው….ፈረንጆች እንደሚሉት ‹ጦርነትን ማስቀረት የሚቻለው ለጦርነት በመዘጋጀት ነው›::’’
‘…የኤርትራ መሪዎች ኢትዮጵያን ለመውረር የሚጋብዛቸው አንዳችም መዋቅራዊ ምክንያት የለም::’ ነው የምትሉን:: ከዚህ ያለፈ መራመድ አልቻልንም:: ስለዚህ ያው ታሪክ ራሱን ይደግማል እንደሚባለው፣ ያልታደለው የትግራይ ሕዝብ በጂኦግራፊ እውነታና አዲስ አበባ ባላችሁ መሪዎች ስህተት ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከሚደርስለት ድረስ እንደተለመደው ንጹህ ደሙን የሚገብርበት ጊዜ ቀናት ብቻ ቀርተውታል::’’
በታሪክ የምናወቀው ደረቅ እውነታ በዚህ መሰሉ የፈጠራ ስራ ላይ መካተቱ የአንባቢን የንቃት እና የግንዛቤ ደረጃ ከፍ በማድረግ የሚጫወተው ሚና አሌ የሚባል አይደለም።
የታሪክ አረዳድ ድክመት
የ“አውሮራ” ደራሲ ብዙ ጉዳዮች ላይ አንጀትን ቢያርስም በአንዳንድ ጥቃቅን ጉዳዮች ግን ጨጓራ መላጥም ያውቅበታል። ይኸውም የታሪክ አረዳድ ላይ እንደቀላል የተዋቸው ቁምነገሮች ኋላ ላይ ምን ያህል ክፍተት እንደሚፈጥሩ ማየት ይቻላል። ይህንንም የኤርትራ የፍትህ ሚኒስትር ተደርገው በተሳሉት አቶ ሀይላይና ሊጽፉት አስበውት በነበረው ረቂቅ መጽሐፍ ላይ እናስተውላለን። በመሰረቱ የአቶ ሃይላይ ረቂቅ መጵሐፍ የኤርትራ ታሪክ ላይ ያጠነጥናል። በመጽሐፉ መግቢያ ላይ የኢትዮጵያ መሪዎች ኤርትራ የምትባለው ሀገር እንድትፈጠር የተጨዋቱትን ሚና ያትታል።
ለምሳሌ ገጽ --61 …
“….ኤርትራዊነት ተጸንሶ የተወለደው በኢትዮጵያ ገዢዎች ስህተት ነው። እነዚህ ገዢዎች ኤርትራን በሚመለከት ምንጊዜም እርስበእርሱ የሚቃረን ፖሊሲ በመከተል ሂደቱን አፋጥነውታል። በጊዜው ስሜት ባይፈጥርም አሁን ግን ትዝታ ትቶ ካለፈው የአጼ ምኒልክ ድርጊት እንጀምር። አጼው በአንድ በኩል ኤርትራ የግዛቴ አካል አይደለችም ብለው በውጫሌ ስምምነት ለኢጣሊያ አሳልፈው ሰጡ። ነገር ግን ከአድዋ ድል በኋላ ለኢጣሊያ ተቀጥረው ሲዋጉ የማረኳቸውን 400 ኤርትራውያን አገራቸውን በመክዳት ወንጀል ከስሰው እግርና እጃቸው እንዲቆረጥ አደረጉ።…”
ይህ አይነት የታሪክ አረዳድ በእርግጥ በሻእቢያ እና በህወሓት ቤት ውስጥ እንግዳ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ሁለቱም ዘውጌ ተኮር ግንባሮች ኤርትራን በተመለከተ የጊዜ ችካል የሚቸክሉት ከምኒልክ ዘመን መንግስት ጀምሮ ነው። ከምኒልክ ይነሱ እና ለጥቀው ኢትዮጵያን በመሩት መንግስታት ላይ የወቀሳውን ዶፍ ያወርዳሉ። ደራሲው በአቶ ሃይላይ በኩል አድርጎ ይህንን ሊደግምልን መነሳቱ እንድታዘበው አድርጎኛል፡፡ የፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ሀይላይ በደራሲው የተሳሉት ሚዛናዊ፣ ከስሜት የጸዱ እና ባለስል አእምሮ ተደርገው ነው፡፡ ይህም በመሆኑ እንደ ገጸባህሪ የሚናገሩትንና የሚጽፉትን ነገር ሁሉ በታላቅ አክብሮት ስንቀበል እንቆያለን።
ደራሲው ይህን ባለ ስል አእምሮ ገጸባህሪ የፈጠረልን ታሪክ አንሸዋሮ ለማቅረብ ይሆን እንዴ ብለን እስከመጠራጠር የምንደርሰውም ግን በኋላ ነው፡፡ በአቶ ሀይላይ በኩል ደራሲው እንደ መሰል የትግል አጋሮቹ የኤርትራ ታሪክን በተመለከተ አጼ ዮሐንስን ከጨዋታ ወጪ አድርጓቸዋል። ወደድንም ጠላንም አጼ ዮሐንስ ኤርትራ የምትባል ሀገር እንድትፈጠር የበኩላቸውን ጡብ አቀብለዋል። አጼው ከእንግሊዝ ጋር በገቡት የ “ሂወት ስምምነት” ምክንያት በተፈጠረባቸው ተላላነት ኢጣሊያ ምጽዋና ቀይ ባህር ላይ በእንግሊዝ አማካኝነት ተደላድላ እንድትቀመጥ ሳያውቁት ትልቅ እገዛ አድርገዋል።
እንደ ማስረጃ “መክሸፍ ኦንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” በፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም ገጽ 110 ላይ የተጠቀሰውን ማየት ይቻላል፡፡    
“…ብሪታኒያ ሂወት የሚባል የባሕር ሀይል አዛዥ ልካ ከአጼ ዮሐንስ ጋር አንድ ውል እንዲፈጽም አደረገች። በምስራቅ በኩል ኢትዮጵያን በምጽዋ ወደብ የመጠቀም መብት ለማጎናጸፍ በምእራብ በኩል ቦጎስን ለኢትዮጵያ ለመመለስ ውል ተፈራረሙ…”
እዚሁ መጽሐፍ ላይ እልፍ ብሎ በገጽ 114 የሚከተለው ነጥብ ሰፍሯል:-
“…ብሪታኒያ ምንም ሳታወጣ በኢትዮጵያ ኪሳራ በሱዳን ላይ ተጠናክራ ተደላደለች። ኢጣሊያም በሰሜን-ምስራቅ ኢትዮጵያ ተተከለች። አጼ ዮሐንስ ለብሪታኒያ ስለተንበረከኩ ኢጣልያ በቀይ ባሕር ላይ ተተከለች፡፡”
እንግዲህ ከላይ የምንረዳው የ“ሂወት ስምምነት ጦስ የባህር በር እንዲዘጋብን ኋላም ለአጼ ዮሐንስ ሞት ምክንያት መሆኑን ነው። ደራሲው አቶ ሀይላይን በኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ፍጹም ሚዛናዊ አድርጎ ከሳላቸው አይቀር በነካ እጃቸው ሁሉንም የታሪክ ዳራዎችን በበቂ ሁኔታ እንዲሸፍኑ አለመድረጉ እንደ ከባድ ድክመት የሚተች ነው፡፡ ይህም በ “አውሮራ” ደራሲ ላይ ጥያቄ ፈጥሮብኛል። ከዚህ በተረፈ አንባቢያን መጽሐፉን አንብበው የራሳቸውን ፍርድ እንዲሰጡ ትቼዋለሁ፡፡ እኔ ግን ቅኝቴን በዚሁ ቋጨሁ።


Published in ጥበብ

           በአለማችን የስነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ከተነሱ ታላላቅ ደራሲያን መካከል “ፖለቲካ ምኔ ነው!” ብለው ጥግ የያዙ በርካታ ደራሲያን የመኖራቸውን ያህል በዘመናቸው የነበረውን የፖለቲካ ትኩሳት የድርሰቶቻቸውን ጭብጥ(theme) ያደረጉ፤ በዚህም ስለ ነጻነት፣ እኩልነት፣ የሰው ልጆች መብትና ሰብዕና… በብርቱ ያቀነቀኑ ደራሲያንም በየዘመኑ ተነስተዋል፡፡ እነዚህ ፀሐፍት አይበጅም ያሉትን ስርዓት በድርሰቶቻቸው በፅኑ ታግለዋል፡፡ ይጠቅማል ያሉትን ስርዓትም ብዕሮቻቸውን ቀስረው አገልግለዋል፡፡ በድርሰቶቻቸው የዘውዱን ስርዓት ከተቃወሙና የሶሻሊዝም ስርዓት እንዲመሰረትና እንዲያብብ በብርቱ ከታገሉ የአለማችን ታላላቅ ደራሲያን መካከል ለዛሬ የረጅምና አጫጭር ልቦለዶች ደራሲና  ፀሐፌ ተውኔት ስለነበረው ሩሲያዊው የብዕር ሰው ማክሲም ጎርኪይ (1868-1936) በጥቂቱ ለማለት ወደድኩ፡፡
ታላቁ የሩሲያ የሳይንስና የታሪካዊ ልቦለድ ደራሲ የነበረው አሌክሴይ ቶልስቶይ (1883-1945) ማክሲም ጎርኪይን “የክላሲካል እና የሶቭየት ስነ ፅሑፎችን የሚያገናኝ ሕያው ድልድይ” ይለዋል፡፡ ደራሲና ፖለቲከኛ የነበረው ጎርኪይ በሀገረ ሩሲያ ዛሬ ጎርኪይ ተብላ በምትጠራው የቀድሞዋ ኒዥኒኖብጎርድ ከተማ በ1968 ነው የተወለደው፡፡ እውነተኛ ስሙ “አሌክሴይ ማክሲሞቪች ፔሽኮቭ” ቢሆንም በመላው ዓለም የሚታወቀው ግን ማክሲም ጎርኪይ በሚለው የብዕር ስሙ ነው፡፡
ከዝቅተኛው ማህበረሰብ የተገኘውና ከልጅነት እስከ ጉልምስና ዘመኑ በከፍተኛ ችግር የተንገላታው ጎርኪይ እንደ አንዳንድ የአለማችን ታላላቅ ደራሲያን ቻርለስ ዲከንስ፣ ማርክ ትዌይን፣ አልቤርቶ ሞራሺያ እና ኤሜሊ ዞላ… መደበኛ ትምህርቱን እንኳን ማጠናቀቅ ያልቻለ ደራሲ ነው፡፡

ጐርኪይ ገና በአፍላ ዕድሜው በሀገሩ ህዝቦች ላይ ይመለከት የነበረው ድህነት እና ስቃይ እጅጉን ያሳስበው ነበር፡፡ የዚህም ተፅእኖ በወጣትነትና ጉልምስና ዘመኑ በጻፋቸው ድርሰቶቹ ላይ በጉልህ ይታያል፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ወደ ስነ ጽሑፉ አለም ብቅ ያለው ጎርኪይ ተቀባይነትና ዝናን ለማትረፍ ብዙም ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ ስሙ በመላው ዓለም በአጭር ጊዜ ውስጥ ናኘ፡፡ ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ ጎርኪይ ይህን የሚያህል ዝና እና አድናቆትን የተጎናጸፈው ሊዮ ቶልስቶይንና አንቶን ቼኮቭን የመሳሰሉ ታላላቅ ደራሲያን በነበሩበት ጊዜ መሆኑ ነው፡፡
ጎርኪይ ገና ወደ ስነ ጽሑፉ መድረክ ብቅ ከማለቱ በድርሰቶቹ የዘውዱን አገዛዝ በይፋ መቃወምና ስለ ድሆች መታገል ጀመረ፡፡ በዚህም በቄሳራዊው መንግስት ጥርስ ውስጥ በመግባቱ በ1905 ተካሂዶ በነበረው የመጀመሪያው ህዝባዊ አመፅ ሙከራ ወቅት ተይዞ ታሰረ። ጎርኪይ ግን በዚህ አልተበገረም፡፡ ከእስር ከተለቀቀም በኋላ የዘውዱን አገዛዝ የሚቃወሙና “ሰፊውን ህዝብ” ለፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያነሳሱ ረጅምና አጭር ልቦለዶችን፣ እንዳሁም ተውኔቶችን ለህዝብ አቀረበ። በፖለቲካዊ ተግባሮቹና የዛሩ መንግስት ተቃዋሚ ከነበረው የቦልሸቪክ ፓርቲ ጋር በነበረው ግንኙነት ምክንያት በተደጋጋሚ ከመታሰሩም በላይ እስከ መጋዝም ደርሶ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ መንገላታት ግን የዘውዱን ስርዓት ከመቃወምና ሶሻሊዝምን ከማቀንቀን አላስቆመውም፡፡
ማክሲም ጎርኪይ ክላሲካል ለሆነው ለሩስያ “የስነ ጽሑፍ ማህበራዊ ወግ” ከፍተኛ ዋጋ ይሰጥ ነበር፡፡ እንደውም የአንጋፋዎቹ ደራሲያን የሊዮ ቶሊስቶይና አንቶን ቼኮቭ ውለታ እንዳለበት ይናገር ነበር፡፡ “በእነርሱ ስራዎች የስነ ጽሑፍን ጥበብ ብቻ ሳይሆን ሀገሬን ሩሲያንና ሩሲያውያንን እንዲሁም የሩሲያውያንን መንፈሳዊ አኗኗርና ስነ ልቡናዊ ምኞት ተገንዝቤአለሁ” ይላል፡፡
ማክሲም ጎርኪይ ታላቁ የሩሲያ የጥቅምት አብዮት ከመፈንዳቱ በፊት በድርሰቶቹ ለወዛደሩ ትግል መሳካትና ለድሆች ነጻነት ከፍተኛ ትግል ሲያደርግ የቆየውን ያህል ከአብዮቱም በኋላ አዲስና ተራማጅ ስነ ጽሑፍ ለመመስረት በፅኑ ታግሎአል፡፡ በዚህም በ1903 በዓለም እጅግ አድናቆትን ያተረፈለትን ልቦለዱን “Mother’s ጽፎአል፡፡ ጎርኪይ ይህን ልቦለድ የጻፈው በ1902 ሶርሞቮ ላይ በ“የወዝ አደሮች ቀን (May Day)” የተካሄደውን ሰልፍን መነሻ አድርጎ ነው፡፡ (ይህ መጽሐፍ በዘመነ ደርግ “እናት” በሚል ርዕስ በአማርኛ ቋንቋ ታትሞአል።) “Mother” በመጀመሪያ የታተመው በ1907 ሲሆን ወዲያውኑ በአለም ከፍተኛ ተቀባይነትን አገኘ። ይህንን የጎርኪይን ድርሰት የወቅቱ የሩሲያ አብዮት መሪ ሌኒን ሳይቀር “የጊዜው አስፈለጊ መጽሐፍ” በማለት አወድሶታል፡፡ ሩሲያዊው የስነ ጽሑፍ ፕሮፌሰር ቦሪስ ቡርሶቭም “የሩሲያ የኢንዱስትሪ ወዝ አደሮችን ቅድመ አብዮት እንግልት የሚያሳይ መስታወትና የዓለም ሰርቶ አደሮችን ለአመፅ፣ ለአርነት ትግል፣ ለሶሻሊዝም ምስረታ የሚቀሰቅስ ብርቱ ጥሪ ነው፡፡” ብሎታል፡፡
የጎርኪይ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ በዚህ ልቦለዱ በጉልህ እንደተንጸባረቀ ይነገራል፡፡ የልቦለዱ ዋና ዋና ገፀባህሪያት የሆኑት “እናት”፣ ልጅዋ ፓቬልና ጓደኛው ኒሎቨና ታሪክ፣ ድርጊትና ምልልሶችም ይህንኑ የጎርኪይን ሶሻሊስታዊ አስተሳሰብና ምኞት በቅጡ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ብዙዎች “የሶቪየት ስነ ጽሑፍ መስራች ነው፡፡” የሚሉት ማክሲም ጎርኪይ፤ ቀዳሚውን የሩሲያን የስነ ጽሑፍ ስልት ይከተል የነበረ ቢሆንም አዳዲስ ነገሮችን ካመጡ የሩሲያ ታላላቅ ደራሲያንም አንዱ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በብዙ ደራሲያን ስራ የበለጸገውን የሩሲያን ክላሲክ የስነ ጽሑፍ ባህል እንዲቀጥል በማድረግ አድሶና አሻሽሎ ለተተኪው አዲስ “ሶሻሊስት” ትውልድ ለማስተላለፍ ከፍተኛ ጥረት አድርጎአል፡፡ ተሳክቶለታልም፡፡
የ1905ቱ የሩሲያ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ከከሸፈ በኋላ በሀገሪቱ የነበረው ሁኔታ አመቺና አስተማማኝ ባለመሆኑ ጎርኪይ ሀገሩን ለቅቆ ለመሄድ ተገደደ፡፡ መኖሪያውንም ካፕሪ በተባለችው የኢጣሊያ ደሴት አድርጎ በስደት ከቆየ በኋላ፣ በ1913 በተደረገው የምህረት አዋጅ  ወደ ሀገሩ ተመልሶ ለቮልሼክ ፕሬስ ጽሑፎችን ይልክ ጀመር፡፡ ቆይቶም የራሱን መጽሔት ለማቋቋም በቃ፡፡
የጥቅምቱ ሶሻሊስት አብዮት በድል ከተጠናቀቀና የመጀመሪያው “የሠራተኛው መደብ” መንግስት ከተመሰረተ በኋላ ጎርኪይ በጤንነቱ መታወክ የተነሳ እምብዛም በሩሲያ ለመቀመጥ ባይችልም በርከት ያሉ ልቦለዶችን፣ አጫጭር ታሪኮችን፣ ሂሳዊ መጣጥፎችንና ተውኔቶችን በመጻፍ ለአዲሱ “የሶሻሊስት ስነ ጽሑፍ” መዳበር ታላቅ አስተዋጽኦ አበርክቶአል፡፡ የሶቪየት ህብረትን ተራማጅ የደራሲያን ማህበር በመመስረትም ግንባር ቀደሙን ሚና ተጫውቶአል፡፡
ይህ ሶሻሊዝምን የድርሰቶቹ ጭብጥ አድርጎ የድሆችን ጎስቋላ ሕይወት በስራዎቹ በጉልህ በመሳል፣ የዘውዱን መንግስት ሲቃወምና የሶሻሊዝምን ስርዓት ለመመስረት ሲታገል የኖረው “ሶሻሊስቱ ብዕረኛ” ማክሲም ጎርኪይ፤ ከዕድሜው አርባ አራቱን አመታት ለስነ ጽሑፍ ስራና ለሶሻሊዝም ማበብ መስዋዕት አድርጎአል፡፡ በእነዚህም ዓመታት Mother ጨምሮ The Lower Depths፣ Danko’s Burning Heart፣ Tales of Italy፣ Summer Folk፣ Children of the Sun፣ Twenty-six Men and a Girl እና ሌሎች በርካታ ረጅምና አጭር ልቦለዶችንና ተውኔቶችን ጽፎአል፡፡ ማክሲም ጎርኪይ ይህቺን ሲታገልባት የቆየባትን ዓለም የተሰናበተው በ1936 ዓ.ም በ68 ዓመቱ ሲሆን ህይወቱም ያለፈችው የፖለቲካ ተቀናቃኞቹ በሰጡት መርዝ ነበር፡፡ ማክሲም ጎርኪይ እጅጉን “ሶሻሊስቱ ብዕረኛ” የሚያሰኘውን ድርሰቱን “Mother’s በተመለከተ የተናገረውን ጠቅሼ የዛሬው ጽሑፌን ላብቃ፡፡ “Only mothers can think of the future - because they give birth to it in their children.” (ስለመጪው ዘመን ማሰብ የሚችሉት እናቶች ብቻ ናቸው፤ ምክንያቱም በልጆቻቸው ውስጥ አምጠው ወልደውታልና” እንደማለት ነው - በግርድፉ ሲተረጐም፡፡)
መልካም ሰንበት!!

Published in ጥበብ

          ባለፉት አስርት ዓመታት በልብ በሽታ ሳቢያ የሚጠፋው የሰዎች ህይወት በከፍተኛ መጠን እየቀነሰ መምጣቱ ተገለፀ፡፡ በከፊል አውሮፓ በቀዳሚ ገዳይነቱ ይታወቅ የነበረው የልብ በሽታ በሰዎች ህይወት ላይ ሲያደርስ የቆየው የሞት አደጋ በከፍተኛ ደረጃ እንደቀነሰ በቅርቡ የወጣ ጥናት ጠቆመ፡፡ በምስራቅ አውሮፓ አገራት ግን የልብ በሽታ በግንባር ቀደም ገዳይነቱ እንደቀጠለ ጥናቱ አመልክቷል፡፡
“European Heart Journal” ላይ የወጣ ሪፖርት እንደሚጠቁመው ደግሞ ዴንማርክን በመሳሰሉ አንዳንድ አገሮች በአሁኑ ሰዓት የልብ በሽታን ተክቶ ካንሰር ትልቁ ገዳይ በሽታ እየሆነ መጥቷል ተብሏል፡፡
በከፊል አውሮፓ የልብ ህመም ገዳይነት የቀነሰው ከአኗኗር ዘይቤ መሻሻል ጋር ተያይዞ ነው ያለው ጥናቱ፤ በዋናነት የሲጋራ ማጨስ መቀነስና የተሻሻሉ ህክምናዎች ተጠቅሰዋል፡፡
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ትንተና እንደሚያሳየው፤ በአስር አውሮፓ አገራት ወንዶችን በከፍተኛ ደረጃ ለሞት እየዳረገ ያለው ከልብ ህመም ይልቅ ካንሰር ነው፡፡ በዴንማርክ ደግሞ ካንሰር የልብ ህመምን ቦታ ተክቶ በከፍተኛ ደረጃ ህልፈት እያስከተለ የሚገኘው በሴቶች ህይወት ላይ ነው ይላል፤ የጥናት ውጤቱ፡፡
ምስራቅ አውሮፓውያን ግን ከአቻዎቻቸው በእጅጉ ወደ ኋላ እንደቀሩ የጠቆመው ጥናቱ፤ በአንዳንድ የምስራቅ አውሮፓ አገሮች የልብ በሽታ አሁንም ከፍተኛ የሞት አደጋ እያስከተለ ነው ብሏል።
ከተመራማሪዎቹ አንዱ የሆኑት ዶ/ር ማይክ ራይነር ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ “በልብ በሽታ የሚከሰተው አጠቃላይ የሞት መጠን እየቀነሰ ነው፤ በአንዳንድ አገራት ከሌሎች አገራት ፈጣን ነው፤ አሁንም ግን በአውሮፓ ትልቁ ገዳይ ነው” ብለዋል፡፡
የብሪቲሽ ኸርት ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሲመን ጊሌስፒ በበኩላቸው፤ “በልብ ህመም በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሞቱ የነበሩ በርካታ ሰዎች ቁጥር በመላው አውሮፓ መቀነሱ መልካም ዜና ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

Published in ዋናው ጤና

ጉዲፈቻ የሚለው ቃል ከኦሮምኛ ቋንቋ በቀጥታ ወደ አማርኛ የተወሰደ ሲሆን ፍቺውም ከሌላ አብራክ የተገኘን ልጅ ከሌላ ሰው የተወለደ መሆኑን አምኖና ተቀብሎ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መብቱን ጠብቆ እንደ ገዛ ልጅ አድርጎ ማሳደግ ማለት ነው፡፡
ጉዲፈቻ ለሚለው ቃል የእንግሊዝኛ አቻው “adoption” ሲሆን አመጣጡም ‘ad-optare’ ከሚል የላቲን ቃል ነው፡፡ ትርጉሙም “መምረጥ” የሚል ነው፡፡ ይህም ጉዲፈቻ በጉዲፈቻ አድራጊው ምርጫ ብቻ የሚከናወን መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ጉዲፈቻ አድራጊው በነጻ ፈቃዱ ከሌላ አብራክ የተገኘን ልጅ ለማሳደግና ለመጠበቅ እንዲሁም ለእድገቱ አስፈላጊ የሆኑትን ማናቸውም እንክብካቤዎች ለማድረግ ወስኖ የሚወስደው እርምጃ ሲሆን ይሄም ልጁ የጉዲፈቻ አድራጊውን ቤተሰብ ስም፣ ንብረትና ህይወት እንዲካፈል የሚያደርግ መብት ያጐናጽፈዋል፡፡ ከአብራኩ ክፋይ የተገኘው ልጅ ያለው ማንኛውም መብት ይኖረዋል፡፡
በአጠቃላይ ጉዲፈቻ አንድ ሰው ቀደም ሲል የነበረውን ቤተሰባዊ የደም ትስስር በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ በአዲስ ቤተሰባዊ ትስስር የሚተካ ወይም የሚለውጥ ማህበራዊ ተቋም ነው ሊባል ይችላል፡፡
ጉዲፈቻ ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ የዓለም ማህበረሰቦች ዘንድ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ሲከናወን የቆየ ሥርዓት ነው፡፡ ለዚህም በአይሁድና በክርስትና ሃይማኖቶች ታሪክ ውስጥ የሚጠቀሰው የነቢዩ ሙሴ ጉዲፈቻ እንደ አብነት ሊነሳ ይችላል፡፡ በህንድ፣ በግብፅና በሮማውያን ዘንድ የዘር ግንዳቸው መቀጠል ባልቻለበት ሁኔታ የቤተሰብ ስም እንዲቀጥል ጉዲፈቻን እንደመሳሪያ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ በእስልምና ህግ የሚተዳደሩ አገሮች የሚጠቀሙበት “የጉዲፈቻ” ሥርዓት ከዚህ በመጠኑ ለየት ይላል፡፡ ካፍላህ በመባል የሚታወቀው ይሄ የጉዲፈቻ ሥርዓት ከኢንዶኔዥያና ቱኒዚያ በስተቀር በእስልምና ሃይማኖት ተከታይ አገራት በሙሉ  በስፋት ይተገበራል፡፡ ካፍላህ የተፈጥሮ ወላጆቻቸው ወይም ቤተሰቦቻቸው ሊያሳድጓቸው ላልቻሉ ልጆች የተፈጠረ አማራጭ የእንክብካቤ መንገድ ሲሆን በህጉ መሰረት ካፍላህ አድራጊዎች ልጆቹን ለዘለቄታው ወስደው እንደራሳቸው ልጆች የማሳደግ ግዴታ አለባቸው፡፡ ሆኖም ልጆቹ ማንነታቸውን ይዘው ማደግ አለባቸው ተብሎ ስለሚታመን የካፍላህ አድራጊዎችን የቤተሰብ ስም እንዲጠቀሙ የማይፈቀድ ሲሆን ንብረት የመውረስ መብትም የላቸውም፡፡
በጥንቱ ዘመን ጉዲፈቻ የልጆችን ሳይሆን የጉዲፈቻ አድራጊዎችን ጥቅም መሰረት በማድረግ ነበር የሚከናወነው፡፡ ጉዲፈቻ የዘር ሀረግን በቀጣይነት ለማረጋገጥ፣ በወንድ ጉዲፈቻ ተደራጊ ልጅ አማካይነት ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ እንዲሁም በገበሬዎች አካባቢ ተጨማሪ አጋዥ ሐይል ለማግኘት ጭምር ሲተገበር ቆይቷል፡፡ የጉዲፈቻ ተደራጊዎች የእድሜ ክልልም በአብዛኛው ከ10 ዓመት በላይ ነበር፡፡
በአብዛኛው የዓለም ክፍል ሲተገበር የቆየው የጉዲፈቻ ሥርዓት በመካከለኛው ዘመን ላይ በተለይ በአውሮፓ አገራት ወደ መጥፋት ደረጃ ደርሶ ነበር፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ ከክርስትና ሃይማኖት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የቤተሰብ ተቋም የደም ትስስር መለያ ባህሪ ስለተሰጠው ነው፡፡
ጉዲፈቻ ዳግም እንደ ሥርዓት ያንሰራራው በፈረንሳይ ቡርዥዋ አብዮት ማግስት በነገሰው ነፃ አስተሳሰብና ዘመናዊ ፍልስፍና ተፅዕኖ ሲሆን እ.ኤ.አ በ1804 በወጣው የፈረንሳይ ፍትሀብሔር ህግ ላይ ጉዲፈቻ በተወሰኑ ሁኔታዎች እንዲደረግ ተፈቅዶ ነበር፡፡
ይህን የፈረንሳይ ተሞክሮ ተከትሎ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ ጉዲፈቻ በአውሮፓ አገራት እንደ አዲስ የህግ ማዕቀፍ እውቅና አግኝቷል፡፡ በእንግሊዝ ጉዲፈቻ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕጋዊ ማዕቀፍ ያገኘው እ.ኤ.አ በ1926 “Children Act of 1926” (የ1926 የህፃናት ድንጋጌ) በሚል ሕግ ሲሆን በአሜሪካ በማሳቹስቴት ግዛት ደግሞ “The Massachusetts Adoption of Children Act” (የማሳቹሴትስ የህፃናት ጉዲፈቻ ድንጋጌ) በሚል በወጣው የጉዲፈቻ ህግ ዕውቅና አግኝቷል፡፡ በወቅቱ ህግ ጉዲፈቻ ተደራጊው ከሁለቱም ቤተሰቡ ማለትም ከቀድሞ ቤተሰቡና ከጉዲፈቻ አድራጊዎቹ ዝምድናውን ይዞ የሚቆይ ሲሆን ከሁለቱም የመውረስ መብት ነበረው፡፡ እነዚህ በአሜሪካና በእንግሊዝ የወጡት የጉዲፈቻ ድንጋጌዎች የመጀመሪያዎቹ ዘመናዊ የጉዲፈቻ ህጎች ተብለው ይታወቃሉ፡፡
የአሜሪካው የማሳቹሴትስ የጉዲፈቻ ድንጋጌ፣ ለቀጣዩ የጉዲፈቻ ህግ መበልጸግ የማእዘን ድንጋይ የጣለ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ህጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የጉዲፈቻ ውል በፍርድ ቤት እንዲጸድቅ የደነገገ ሲሆን ፍ/ቤቱም ውሳኔውን ከማስተላለፉ በፊት የሚመለከታቸው አካላት ለጉዲፈቻው ፈቃድ መስጠታቸውንና ውሳኔው የልጁን ደህንነት የሚያስጠብቅ መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለበት ይገልፃል፡፡ ፍ/ቤቱ ጉዲፈቻ  አድራጊዎቹ ለህፃኑ ተስማሚ መሆናቸውን በቅድሚያ ማረጋገጥ እንዳለበትም ህጉ ያስቀምጣል፡፡
በሃያኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ ከአዳዲስ የጉዲፈቻ ህጐች መውጣት ጋር ተያይዞ የጉዲፈቻ አላማና ግብ ከጉዲፈቻ አድራጊው ጥቅሞች ተላቅቆ የህፃናትን ደህንነትና ጥቅም የሚያስጠብቅ እየሆነ መጣ፡፡ ጉዲፈቻ መንግስታት የተጣሉ፣ ቤተሰብ የሌላቸው/የማይንከባከባቸው ወይም ከጋብቻ ውጭ የተወለዱ ልጆችን የሚንከባከቡበትና ደህንነታቸውን የሚያስጠብቁበት ተቋም ለመሆንም በቃ። ይሄን ተከትሎም የጉዲፈቻ ተቋም የሚያስከትለው ህጋዊ ውጤትም ተቀይሯል፡፡ በፊት ጉዲፈቻ ተደራጊው ከቀድሞ ቤተሰቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ የማያቋርጥ ሲሆን ይህም ከፊል ጉዲፈቻ /weak or simple adoption/ በመባል ይታወቃል፡፡ አሁን በተሻሻለው የጉዲፈቻ ህጋዊ ሥርዓት ግን ጉዲፈቻ ተደራጊው ከቀድሞ ቤተሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ያቋርጣል፡፡ ይህም ሙሉ ጉዲፈቻ / ‘strong’ or ‘full’ adoption/ በሚል የሚታወቅ ሲሆን የህፃናትን ደህንነት ከማስጠበቅ አንፃር ተቀባይነቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡
በአውሮፓና በአሜሪካ የጉዲፈቻ መርህ “የህፃናትን ደህንነት ማስጠበቅ ነው” የሚለው አስተሳሰብ እየጠነከረ የመጣው ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በኋላ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ በርካታ ልጆች ያለቤተሰብና አሳዳጊ በመቅረታቸውና ከጋብቻ ውጪ የሚወለዱ ልጆች በመበራከታቸው ነበር፡፡ ጉዲፈቻ አድራጊዎች በአብዛኛው ባለትዳር ጥንዶች ቢሆኑም በርካታ ያላገቡ (ወንደላጤ ወይም ሴተላጤ) ግለሰቦችም ልጆችን በጉዲፈቻ ወስደው ያሳድጋሉ፡፡
ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች የጉዲፈቻ ልጅ ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ ብዙዎች የአብራካቸውን ክፋይ ማግኘት ባለመቻላቸው (የማይወልዱ በመሆናቸው) የጉዲፈቻ ልጅ ሲያሳድጉ፣ ሌሎች ደግሞ አዲስ አባል ቤተሰባቸው ውስጥ ለመጨመር ሲሉ የጉዲፈቻ ልጅ ይወስዳሉ፡፡ አሳዳጊ ለሌለው ልጅ መኖሪያ ቤት ለመስጠትና ቤተሰብ እንዲኖረው ለማድረግም የጉዲፈቻ ልጅ የሚወስዱ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡
ህፃናቱም በተለያዩ ምክንያቶች በጉዲፈቻ የሚያሳድጓቸው ቤተሰቦች የሚፈልጉበት ሁኔታ አለ። አንዳንዶቹ ወላጆቻቸውን በሞት በማጣታቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ወላጆች ቢኖሩም በህመም ወይም በሌላ የግል ችግር ማሳደግ አቅቷቸው በጉዲፈቻ የሚሰጡበት ሁኔታም አለ፡፡ ሌሎች ደግሞ ተፈጥሯዊ ወላጆቻቸው ጥለዋቸው በጉዲፈቻ የሚሳድጋቸው ቤተሰብ ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡
ፍላጐት ሳይኖራቸው የወለዱ ወላጆችን ማንነትን የሚያጋልጥ አለመሆኑ እንዲሁም የልጆችን ደህንነት የሚያስጠብቅ መሆኑ በህፃናት ሥነልቦናና ዕድገት ላይ በተደረጉ ጥናቶች መደገፉ ለጉዲፈቻ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘት ምክንያት ሆኗል፡፡
በአሜሪካ “የጉዲፈቻና አስተማማኝ ቤተሰቦች ድንጋጌ” (Adoption and Safe Families Act 1997) መውጣት ጋር ተያይዞ የህፃናትን ጥቅም ይበልጥ ሊያስጠብቅ የሚችለው ዘላቂ የሆነ አያያዝ ነው የሚለው ይበልጥ እየታመነበት መጥቷል፡፡ ቀደም ሲል ልጆችን በተቻለ መጠን “ከቤተሰብ ጋር መቀላቀል” የሚለው መርህ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት የቆየ ሲሆን በዚህም ሳቢያ ልጆች ለረዥም ጊዜ በማሳደጊያ (ፎስተር ኬር) ውስጥ እንዲቆዩ ይደረግ ነበር - አሳዳጊ ቤተሰብ እስኪመጣ፡፡ ይሄ ደግሞ መንግስትን ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ ከመሆኑም በላይ ልጆችን ከቤተሰብ ለመቀላቀል የሚደረገው ሙከራ በአብዛኛው እንደማይሳካ ተሞክሮዎች ያሳያሉ፡፡ አሁንም ቢሆን ልጆችን ከቤተሰብ ጋር መቀላቀል የሚለው መፍትሄ ቅድምያ የሚሰጠው ቢሆንም ህፃናት በማሳደጊያ ውስጥ ለረዥም ጊዜ መቆየታቸው በደህንነታቸው ላይ  አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ጥናቶች ይጠቆማሉ፡፡
የአሜሪካ የጉዲፈቻ ህግ ይሄን ለማስታረቅ የጊዜ ገደብ አስቀምጧል፡፡ ልጁ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ከቤተሰቡ ጋር መቀላቀል ካልቻለ የወላጅነት መብት እንዲቋረጥ በቤተሰብ ላይ ክስ ተመስርቶ፣ ልጁ በጉዲፈቻ ሊመደብ እንደሚችል ህጉ ይደነግጋል፡፡ አሁን በአሜሪካ ተመራጩ የህፃናት እንክብካቤ መንገድ ጉዲፈቻ ሲሆን ለልጆች ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥ አማራጭ የእንክብካቤ መንገድ መሆኑ ይበልጥ እየታመነበት መጥቷል፡፡    
በኢትዮጵያ ጉዲፈቻ በትክክል መቼ እንደተጀመረ የሚጠቁም ጥናት ባይገኝም ከ1800 ክፍለ ዘመን መጀመርያ አንስቶ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በባህላዊ መንገድ ይካሄድ እንደነበር ይገመታል፡፡ በተለይ በኦሮሞ ብሄረሰብ ዘንድ ይተገበር እንደነበርም ይነገራል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የህግ ማዕቀፍ የተበጀለት በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐብሄር ህግ ሲሆን በዚህ ህግ ስለ ድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻ በግልፅ የተቀመጠ ነገር ባለመኖሩ፣ በፍትሐብሄር ህግ ውስጥ ያለውን የቤተሰብ ህግ ክፍል ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት ጋር አጣጥሞ ማሻሻል አስፈልጓል፡፡ በዚህም መሰረት የተሻሻለ የቤተሰብ ህግ በአዋጅ ቁ፣ 213/92 ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ ፀንቶ በስራ ላይ ውሏል፡፡   
ምንጭ - የጉዲፈቻ አሠራር በኢትዮጵያ
በወ/ሮ ረሂላ አባስ

Published in ዋናው ጤና

የስዕል ተሰጥኦ ከዘረመል ጋር ግንኙነት አለው ተብሏል

ህጻናት በአራት አመት እድሜያቸው ላይ ሆነው የሚስሏቸው ስዕሎች አጠቃላይ ሁኔታና የስዕል ችሎታቸው፣ በቀጣይ የህይወት ዘመናቸው የሚኖራቸውን አእምሯዊ ብቃት በተወሰነ መልኩ የሚያመላክት እንደሆነ በጥናት መረጋገጡን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ለንደን ውስጥ በሚገኘው ኪንግስ ኮሌጅ የሥነ አዕምሮ ተቋም ተመራማሪዎች በጥናታቸው ያካተቷቸውን 7ሺህ 752 ጥንድ መንታ ህጻናት፣ የአንዲትን ህጻን ፎቶግራፍ በወረቀት ላይ እንዲስሉ በማድረግ የህጻናቱን የስዕል ችሎታ የገመገሙ ሲሆን የስዕሎቹ ውጤትም ህጻናቱ ከአስር አመታት በኋላ የሚኖራቸውን አእምሯዊ ብቃት እንደሚያመላክት ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡
በአይን የተመለከቱትን ነገር በወረቀት ላይ በስዕል መልክ ማስፈር መቻል ለሰው ልጆች የተሰጠ ልዩ ክህሎት ነው ያሉት የተመራማሪዎች ቡድኑ መሪ ዶ/ር ሮዚላንድ አርደን፤ የስዕል ችሎታ የሰዎችን መረጃን በአእምሮ የማቆርና በተፈለገው ጊዜ የማውጣትና የማሰብ ብቃት የሚያመለክት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የስዕል ችሎታ ህጻናት ሲያድጉ የሚኖራቸውን አእምሯዊ ብቃት የሚያመለክት ቢሆንም፣ ይህ ችሎታ አእምሯዊ ብቃትን የሚወስን አለመሆኑን የገለጹት ዶ/ር አርደን፤ አእምሯዊ ብቃትን የሚወስኑ ሌሎች ተፈጥሯዊና አካባቢያዊ ምክንያቶች እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡
“በስዕል ችሎታና በአእምሯዊ ብቃት መካከል ያለው ግንኙነት የተወሰነ በመሆኑ፣ ወላጆች የልጆቻቸው የስዕል ችሎታ አነስተኛ በመሆኑ ሊሰጉ አይገባም” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ተመራማሪዎቹ ከዚህ በተጨማሪም፣ ጥናት ያደረጉባቸው መንታ ህጻናት የሳሏቸውን ስዕሎች በመገምገም፣ የስዕል ችሎታ በዘር የሚተላለፍ መሆን አለመሆኑን ለማጥናት የሞከሩ ሲሆን፣ በዚህም የስዕል ችሎታ ከዘረመል ጋር ግንኙነት እንዳለው ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡

Published in ዋናው ጤና
Page 5 of 20